የሻማ መብራት ከነፈግናቸዉ አርበኞቻችን (ቃለ መጠይቅ) ጌታቸዉ ረዳ http://www.ethiopiansemay.blogspot.com/
አርበኛዉ የኤርትራ ክፍለሃገር ተወላጁ ኢትዬጵያዊዉ አበራ የማነአብ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ሲል በወቅቱ ኢድሃቅ ተብሎ ሲጠራ የነበረዉ የተቃዋሚዎች የሕብረት ግመባር የዉጭ ጉዳይ አስፈጻሚ እና ቃል አቀባይ በመሆን አሱን ጨምሮ ስድት ራሱ ግምባሩን ወክለዉ በስደት ከሚኖሩበት ከዉጭ አገር ወደ አገራቸዉ ኢትዬጵያ ምድር በመጓዝ በሽግግር መንግሥትነት ስልጣን ከተቆጣጠረዉ ከወያነ ሓርነት ሕዝቢ ትግራይ ጋር ለመደራደር 1986 ዓ.ም. (ኢት. አቆጣጠር) አዲስ አባባ ከገቡ በሗላ ምንም ችግር እንደማይገጥማቸዉ ቃል የተገባላቸዉ ተደራዳሪዎች በቀና መንፈስ ለመደራደር ከገቡ በሓላ ወድያዉኑ ቦሌ አይሮፕላን ማረፍያ እንደደረሱ ታፍነዉ ለእስር ተዳርገዉ አምስቱ በድርድር ፈርመዉ ሲለቀቁ አበራ የማነአብ ግን ሳይለቀቅ እስካሁን ድረስ አለም በቃኝ እስር ቤት ዉስጥ አላግባብ ለስቃይ ተዳርጎ ይገኛል፣፣
የሻማ መብራት የነፈግነዉን የአርበኛ አቶ አበራ የማነአብ ቃለ መጠይቅ የተደረገዉ በ991 ሲሆን ቃለ መጠይቁ ያደረጉት “የአንድ ኢትዬጵያ ራዲዬ” ጋዜጠኛ እና እንዲሁም በወያነ ትግራይ አመራሮች እና በሻዕብያ አመራሮች ሰበብ የተቀሰቀሰዉ የባድመ ጦርነት ለመጎብኘት እና ለጦርነቱ የሞራል እና የገንዘብ እገዛ ለማድረግ ወደ ኢትዬጵያ የተጓዙ ዉጭ አገር ከሚኖሩ ኢትዬጵያዊያን/ያት ጭምር ጋር ነበር፣፣ ቃለ መጠይቁ ስለ ጦርነት፣ ስለፍትሕ፣ስለፖለቲካ ፣ ስለ ሰላም፣ ለሕዝብ እና ለሃገር ተብሎ መከፈል ያለበት መስዋእትነት እንዲሁም ስለ ቆራጥ እርምጃ እና እሩቅ አሳቢነት በተለይም ስለ ሰላም ሲባል ከገዢዉ መንግሥት ሳይቀር መነጋገር ነዉር እንዳልሆነና ያላግባብ በእስር እየተሰቃየ ባለበትም ወቅት አነገበዉን የሰላም መልክቱ የሚቀጥልብት መሆኑን በአጽንኦት የጠቀሰዉን እና የተዘገበዉ እጅግ ጠቃሚ ትምህርት በጦብያ መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 4 1991 ዓ.ም. ታትሞ ነበር፣፣ ዛሬም በድጋሚ በዚህ “በኢትዬጵያ ሰማይ” ድረገጽ በማቅረብ አበራ የማነአብም ሆነ ሌላዉ የደቡብ ኢትዬጵያ (አልታ) ሰዉ የማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ እንግሊዝ አገር ምሁሩ ኢትዬጵያዊዉ አርበኛች “ፊታዉራሪ መኮንን ዶሪ” እና ቀደም ብለዉ ለፍትሕ ሲታገሉ በወያነ ትግራይ እጅ የወደቁ እና የታሰሩ ሌሎች ካህናት እና የፖለቲካ መሪዎች ሻማ አብርተን ያላስታወስናቸዉ የኢትዬጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በአሜሪካ እና በአዉሮጳ ሻማ እያበራን እንደ ሌሎቹ የቅርብ ታሳሪዎች “በሱፐር ኖቫ” ነት (Super Nova)ነት ገድላቸዉ እየተደጋገመ የመገናኛ ድረገጾቻቸዉ እስኪጣበቡ ድረስ እንዲዘግቡት ባይደረግም በእስር ተወርዉረዉ የተረሱት የቁርጥ ቀን ምሳሌዎች በእስር ዉስጥ ሆነዉ ለሕዝብ ያስተላለፏቸዉ መልክቶቻቸዉ ሕያዉ ቃሎች ስለሆኑ ዛሬም በመዘከር እናስታዉሳቸዋለን፣፣ ወደ ቃለ መጠይቁ ሳንገባ አቶ አበራ የማነአብ ከጠቀሳቸዉ ከብዙዎቹ አገራዊ ጉዳዬች/ቁም ነገሮች ለመግቢያችን ጥቂት ላስቀምጥ እና ወደ እዛዉ እንሸጋገር፣፣
1- “ፍርድ ቤት የለቀቀዉ ሰዉ መለቀቅ የለበትም እንዴ?”
2- “ምንም እንኳ እኔ እዚህ እስር ቤት ከገባሁ ወደ 5 ኣመት ሊሆነኝ ጥቂት ወራት ቢቀረኝም ያንኑ የመጣሁበትን ተልእኮ ነዉ የማራምደዉ፣፣ አሁንም የተላኩበትን መፈክር እንዳነገብኩ ነኝ፣፣ ብሔራዊ እርቅ የግድ ያስፈልጋል፣፣”
3-“መንግሥት የተጠየቀዉ ቅድመ ሁኔታ የለም፣፣ የፈጠራቸዉን መሰናክሎች በማንሳት በሩን ወለል አድርጎ ተቃዋሚዎችንም ሌላዉንም ማንኛዉም የሕብረተሰብ ክፍል በአገር ጉዳይ ማሳተፍ ያስፈልጋል፣፣ከነጋዴ ጋር ተጣልቶ ከሕዝባዊ ማሕበራት ጋር ተጣልቶ፣ከተማሪ ጋር ተናንቆና ተጣልቶ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለሁሉም ስም ሰጥቶ እስከመቸ ድረስ ይዘለቃል?”
4-“እናንተ ደግሞ በዚህ ባጭር ቆይታችሁ በኢትዬጵያ ዉስጥ ዲሞክራሲ ሰፍኗል ብላችሁ ከሆነ በዚህ አመለካከት እንለያያለን…..፣፣” “ ……በድርጅቱ መዋቅር መሠረት እዚህ አንድ ሰልፍ እዚያም አንድ ሰልፍ፣ እዚያም ታች የተወሰነ ጭብጫባ ለማድረግ ይቻላል፣፣በደረግ ጊዜም ቢሆን መዘንጋት የሌለበት ሰዉ እኮ ስንቁን እየሰነቀ፣ልጁን እየሰጠ ነበር፣፣ ሁሉንም አገር እየከፈለ ነበር እያደር ነዉ ነገሮች እየተለዋወጡ የሄዱበት፣ ወደ ግዳጅ የተሸጋገረዉ፣፣”
5--“በኤርትራና በኢትዬጵያ መካካል በተለይ በሻዕብያ እና በወያኔ መካከል በተፈጠረዉ ሁኔታ ምክንያት አንዳንድ በዜና ማሰራጫ የሚተላለፉት እዉነት ከሆኑ ለዘላለም የሚያሳፍሩ ነገሮች ናቸዉ በሁለቱም ወገኖች የተፈጸሙት፣፣……….ትናንትና እኮ ሁላችንም ኢትዬጵያዉያን ነበርን፣፣ በብዙዎቻችን ግምት ዛሬም ሁላችንም አንድ ነን፣፣ ኢትዮጵያዉያን ነን ብለን የምናምን አሁንም ብዙ ሰዎች አለን፣፣ እንዴት እነሱ በኢትዬጵያዉያን ላይ እንዴት ደግሞ እኛ እዚህ በኤርትራዉያን ላይ አሁን የሚባሉት ነገሮች ይፈፅማሉ? ይኸ በጣም ሚያሳዝን ነገር ይመስለኛል፣፣ በሁለቱም ወገን ቢሆን እንደዚህ ዓይነቱ ግብታዊና ስሜታዊ የሆኑ እርምጃዎች መቆጠብ አስፈላጊ መስሎ ይታየኛል፣፣” (አበራ የማነአብ) ከቃለመጠይቁ የተወሰደ፣፣
ሙሉዉን ቃለ መጠይቅ
አንድ ኢትዬጵያ፣- በአሁኑ ሰዓት በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ? አበራ የማነአብ፣- ይኸንን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት ከመነሻዉ አንድ ነገር ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ፣፣ ይኸዉም አሁን እንዳልነዉ እኔ ከመጣሁ አምስት ዓመት ሊሆነኝ ጥቂት ነዉ የቀረኝ፣፣ በዚህም ምክንያት ብዙ ነገሮች ዉጭ የሆነ ሰዉ እንደሚከታተለዉ መከታተል በማልችልበት ሁኔታ ላይ ነዉ ያለሁት፣፣ በመሆኑም ዛሬ ከእናንተ ጋር ይህነን ቃለ ምልልስ ለማካሄድ ስስማማ የግል አስተያየቴ ብቻ መሆኑን እንድታዉቁልኝ እፈልጋለሁ፣፣ ወክለዉ ስለላኩኝ ድርጅቶች አሁን ባለሁበት ከጊዜና ከሁኔታ ይህን ያህል ርቄ መናገር የምችልበት ሁኔታ ላይ አይደለሁም፣፣ የምናገረዉ ማንኛዉም ሃሳብ የግል አስተያየት መሆኑን እንድትገነዘቡልኝ እፈልጋለሁ፣፣ አንድ ኢትዬጵያ፣ - ከዚህ በፊት መታመምዎ ተነግሮ ነበር፣፣ አሁን ጤንነትዎ ያለበትን ሁኔታ ይነግሩናል? አበራ የማነአብ፣- አሁን ደህና ነኝ፣፣ከ4 ወር በፊት አንድ 2 ወር ያህል ከተቸገርኩ በሗላ ፖሊስ ሆስፒታል ገብቼ እንድታከም ተደርጎ ይኸዉ አንድ ሳምንት ሆኖኛል ታክሜ ከወጣሁ፣፣ አንድ ኢትዬጵያ፣- በአሁን ሰዓት ጤንነትዎ ደህናነዎት?
አበራ የማነአብ፣- ጤንነት ይሰማኛል ደህና ነኝ፣፣ አንድ ኢትዬጵያ፣- ሕመምዎ ምን እንደነበር ሊነግሩኝ ይፈቅዳሉ? አበራ የማነአብ፣- የጀመረኝ እንደ ጉንፋን አድርጎ ነዉ፣፣ በሗላ እየቆየ ሲሄድ ሳይሻለኝ ሲቀር ሆስፒታል ከሄድኩ በሗላ በምርመራ የደረሱበት የሳምባ በሽታ መሆኑን ነዉ፣፣ በዚህ መሰረት እዚያ ለሁለት ወር ከተኛሁ በሗላ ስለተሻለኝ አሁን ወጥቼ ተጨማሪ ህክምና እየተከታተለኩ ነኝ ያለሁት፣፣ አንድ ኢትዬጵያ፣- ልጅዎ ሊጠይቅዎት መጥቶ ነበር ተገናኛችሁ? አበራ የማነአብ፣- እንደመጣ እኔ ሆስፒታል እያለሁ ለአንድ ሦስት ጊዜ ያህለ በጣም ላጭር ጊዜ ምናልባት ካስር ደቂቃ ለማይበልጥ ጊዜ እንዲገባ እና እንዲያየኝ ፈቅደዉለት ነበር፣፣ ከዚያ ወዲያ ከልጄ ጋር ለመገናኘት አልቻልኩም፣፣ እዚያም እያለሁኝ ወድያዉኑ ግንኙነት እንዲቋረጥ ተደረገ፣፣ አሁን ከሆስፒታል ከወጣሁ እንድ ሳምንቴ ነዉ፣፣ ባለፈዉ ሳምንት ቤተሰብ መጠየቂያ ሰዓት ቅዳሜ እና እሁድ ላይ መጥቶ ነበረ፣፣ እንደተነገረኝ የዉጭ ዜጋ ፓስፖርት ነዉ የያዝከዉ በሚል ከዉጭ በራፍ ላይ አልፎ ሊገባ አልቻለም፣፣ በእዉነቱ እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም ቅር ብሎኛል፣፣ ምክንያቱም እስከዛሬ ድረስ የብዙ ሰዎች ልጆች፣ዘመዶች፣ ቤተሰቦች የዉጭ አገር ፓስፖርት እየያዙ እየመጡ፣እንደማንም ሌላ የቤተሰብ አባል ቅዳሜ እና እሁድ እየገቡ ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር ዓለም በቃኝም ሲገናኙ አይቻለሁ፣፣ የእኔ ልጅ እንዳይገባ የመከልከሉ ነገር በጣም አሳስቦኛል፣፣ የዜግነት ጥያቄ እንዴት ተደርጎ በአባትና ልጅ መካከል እንደሚነሳ አይገባኝም፣፣ ሕገ መነግሥቱ ራሱ እስረኛ ከቤተሰብ ጋር እንዲገናኙ ይፈቅዳል፣፣ማንም ቤተሰብ እንደሚገናኘዉ እኔም ከቅርብ ቤሰብ ጋር ለመገናኘት ይሄን ያህል አስቸጋሪ ሆኖ እንዴት እንደታያቸዉ አላዉቅም፣፣ በእዉነቱ ለማንኛዉም ልጄ ራሱና ሌሎች ከተማ ዉስጥ ያሉ ወዳጆቼ ሁኔታዉን ለሚመለከተዉ ክፍል እንዲያሳዉቁና መፍትሄ እንዲፈልጉ ነግሬአቸዋለሁ፣፣ እስካሁን ድረስ የሰማሁት ነገር የለም፣፣ አንድ ኢትዬጵያ፣- ባንድ ወቅት ፍረድ ቤት አንዲፈቱ አዝዞ ነበር፣፣እንደገና ታስረዋል፣፣ ስለሁኔታዉ አጭር ማብራርያ ቢሰጡን? አበራ የማነአብ፣- ፍርድ ቤቱ አንድፈታ የወሰነበት ሁኔታ አጠቃላይ አመጣጡ ባጭሩ እንደሚከተለዉ ነዉ፣፣ ከዉጭ እንደመጣን አብረን የመጣነዉ ሰዎች ሁላችንም ነበር የተከሰስነዉ፣፣ “በፀረ ሰላም እና ጦርነት በመቀስቀስ” በሚሉ ክሶች ነበር የተከሰስነዉ፣፣ በመንግሥትና በኛ መካካል ድርድር ከተደረገ በሗላ 5 ሰዎች ሲፈቱ እኔ ሳልፈታ ቀረሁ፣፣ መጀመርያ ሁላችንም አንድነት ተከስሰን በነበረበት ጉዳይ ላይ አቃቤ ሕግ ክሱን አሻሽሎ የእነሱን ስም አዉጥቶ የእኔን ስም ብቻ አስቀርቶ ያንኑ ክስ መልሶ በእኔ ላይ መሠረተ፣፣ በዚህ አኳሃን ክሱ ቀጠለ፣፣ በዚህ ዓይነት ክርክሩ በፍርድ ቤቱ በሚያዚያ 5 ቀን 1986 ዓ.ም.ሳልለቀቅ ቀረሁ፣፣ “እንዴት ይሆናል?” ተብሎ ሲጠየቅ ከጥቂት ጊዜ በሗላ የተሰጠን መልስ እኔ በሌላ ወንጀል ተጠርጣሪ ስለሆንኩኝ በእስር ቤት እንድቆይ ጥያቄ የቀረበ መሆኑ ተነገረኝ፣፣ እና በዚህ ዓይነት ከሚያዚያ 1986 ዓ.ም. ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል በሚል አዲስ ክስ ተመሥርቶብኝ ከነበርኩበት ከመደበኛ እስር ቤት ወደ ዓለም በቃኝ ተዛዉሬ አሁን ዓለም በቃኝ እገኛለሁ፣፣ ይህም የዘር ማጥፋት ወንጀል ተብሎ የተመሠረተዉ ክስ እኔን በተለይ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ሰዎች ጋር ደምረዉ 161 ሰዎች ጋር በአንድ መዝገብ ላይ በ155 ክሶች ተከሰስን፣፣ከ61 ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ከእኔ ጋር የተከሰሱት ሁለት ሰዎች ናቸዉ፣፣ እኛን ይመለከታችሗል የተባልነዉ 15 ክስ ነዉ፣፣ የሁላችንም ክስ በአንድነት ነዉ የሚታየዉ፣፣ ተነጣጥሎ ሊታይ አልተቻለም፣፣
አንድ ኢትዬጵያ፣- የወደፊት የኢትዬጵያ ሁኔታ በእርስዎ አመለካከት ምን ይመስለዎታል? በተለይ አሁን በሻዕቢያ የተቃጣብንን ወረራና እንደዚሁም አሁን የኢትዬጵያ ሕዝብ ወረራዉን ለመቋቋም ወይም ሻዕቢያን ለማስታገስ በሚደረገዉ ርብርብ ላይ አገራዊ ትብበርዎን እንዴት ያሳያሉ? አበራ የማነአብ፣- እንደማንኛዉም ኢትዬጵያዊ በሻዕቢያ በኩል በኢትዬጵያ ላይ የተፈጸመዉን ወረራ አወግዛለሁ፣፣ በእዉኑ ይኸ ነገር ግልጽ ይመስለኛል፣፣የሁላችንም አቋም ይኸዉ ነዉ፣፣ በሌላ በኩል ይህንን ክስተት አስመልክቶ ሊባሉ የሚችሉ በጣም ብዙ ነገሮች አሉ፣፣ በመጀመርያ ደረጃ በሻዕቢያ እና በወያኔ መካከል ያለዉን ግኙነት በአገሮች መካካል ሊኖር የሚገባዉ በጣም ያለፈና ስለግንኙነታቸዉ ለሕዝብ የሚታወቀዉ በጣም የተወሰነ ሆኖ ለምን ይኸ ግጭት ሊፈጠር እንደቻለና እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደቻለ አናዉቅም የሚል ቅሬታ በጽሑፍም ሆነ በሌላ ዘዴ ሲነገር ይሰማል፣፣ በመሠረቱ በሻዕቢያና በወያኔ መካካል የነበረዉ ግንኙነት እኔ እንደሚመስለኝ በጊዜዊ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንጂ በመርህ ላይ የቆመ ግንኙነት የነበረ አይመስለኝም፣፣አንዱ በሌላዉ ሊሰጠዉ የሚችል ጥቅም ነበረዉ፣፣ሰጥቷልም፣፣ ለምሳሌ ህወሓት እንደተመሰረተ ህወሓት እንዲጎለብት እንዲጠናከር የማድረግ ጉዳይ ከማንኛዉም በላይ የሻዕቢያ ፍላጎት ነበር፣፣ ስለሆነም ሻዕቢያ ብዙ ድጋፍ ሰጥቶ ወያኔ እንዲጠናከር እና እንዲጎለብት በትግሉ እንዲገፋ ብዙ አስተዋጽኦ አድረጓል፣፣ ይህን ነገር ሁሉም ወገን የሚያዉቀዉ ነዉ፣፣ ይህም በሌላ በምንም ምክንያት ሳይሆን ሻዕቢያ በኤርትራና በቀረዉ የኢትዬጵያ ክፍል መካካል አንድ ከለላ ሆኖ የሚያገለግል አጥር ይፈልግ ስለነበር ነዉ፣፣ በኢትዬጵያ መንግሥት ሊሰነዘርበት የሚችለዉን ጥቃት የሚከላከልበት አንድ አጥር ነገር መፍጠር ነበረበት፣፣ ለዚያዉ ዓላማ እንደ ወያኔ ዓይነት ድርጅት ፈጠረ፣ አደራጀ፣፣ ይህን ድጋፍ በሚሰጥበት ጊዜ እንዲሁ አይመስለኝም፣፣ ወደ ሗላ ተመልሰን ስንመለከት ወያኔ ይህንን ድጋፍ እንዲያገኝ የተወሰኑ ነገሮችን ማድረግ ነበረበት፣፣ ከእነዚህም ዉስጥ ዋናዉ የኤርትራን የቅኝ ግዛትነትና የኤርትራን የነፃነት ጥያቄ መቀበል ነበረበት፣፣ በዚህም አኳሃን ሁለቱም ድርጅቶች ተደጋግፈዉ ለረጅም ጊዜ ሲታገሉ ቆዩ፣፣ ብዙ የጋራ ጥቅሞችም ስለነቡሯቸዉ አንዱ ሌላዉን እየረዳ ሲታገል ቆየ፣፣በተለይ ከነፃነት በሗላ የዚህ የመደጋገፍ ጉዳይ ከማንም ይበልጥ የነበረዉ ኤርትራን ነዉ፣፣ይህንን ሁኔታ መቀጠል ከማይቻልበት ደረጃ ሲደረስ፣ በኢትዬጵያ በኩል በልዩ ልዩ ምክንያቶች በተለይም በራሱ በወያኔ ዉስጥ ባሉ ትግሎችና ቅራኔዎች ችግሩ ይፋ ወጣ፣፣ለኤርትራ ሲሰጥ የነበረዉ ገደብ የለሽ ድጋፍ ሲቋረጥ፣ ኤርትራን በሁለም መንገድ የመደገፉ ጉዳይ እየላላ ሲሄድ በሻዕቢያና በወያኔ መካከል ቅራኔዎች ተወልደዉ እያደጉና እየሰፉ መጥተዉ አሁን እዚህ ደረጃ ደረሰ፣፣
አንድ ኢትዬጵያ፣- የአገራችን ህልዉና ለማስጠበቅ ምን መደረግ አለበት ይላሉ? አበራ የማነአብ፣- አሁን ባለበት ሁኔታ ኢትዬጵያዉያን ባንድነት ተሰልፈዉ ከዉጭ የመጣዉን ጥቃት ለመከላለክ እንዲችሉ ለማገዝ አኔ እንደሚመስለኝ ዋናዉ ጉዳይ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ያነሳነዉን ጥያቄ መሠረታዊ መስሎ ይታየኛል፣፣ ይኸዉም በተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች በኢሕአዴግና በሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል አጠቃላይ የሆነ የመግበባት መንፈስ ፣ የመተማማን መንፈስና የመተማመን ዕርቅ መዉረድ ይኖርበታል የሚል እምነት አለኝ፣፣ ይህ እንዳይሆን ዋናዉ እንቅፋት ራሱ ሥልጣን ላይ ያለዉ መንግሥት ነዉ፣ ፣ እንደሌላዉ በሩን ከፍቶ ኑ በጋራ እንሳተፍ የአገራችንን ችግር በጋራ እንፍታ፣ ሁሉም እንደየችሎታዉ አስተዋጽኦ ያድርግ ብሎ መጠየቅ ሲገባዉ በማንኛዉም ለተሳትፎ አኳያ የሚቀርብለትን ጥያቄ ልዩ ልዩ ደንቃራዎችን በማስቀመጥ እያደናቀፈ እስከ ዛሬ ድረስ ሰባት ዓመት ሙሉ አልፏል፣፣ እንደ እዉነቱ ከሆነ እኔ የቀይ ሽብርም ሆነ የዘር ማጥፋት ወንጀለኛ አይደለሁም፣፣የመጣሁበት ምክንያት ማንም ሰዉ ያወቀዋል፣፣ እኛ ዓላማችን ከኢሕአዴግ ጋር ለመወያየት ነበር፣፣ በሩን ጥርቅም አድረጎ የሰላም ዉይይት ያከሸፈዉ ኢሕአዴግ ነዉ፣፣ ዋናዉ ጉዳይ የተለያየ አጋጣሚዎችን እየጠበቁ ከሁለት ከሦስት የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር የመታረቅ ጥያቄ አይደለም፣፣ የሕዝብን ፍላጎት ተከትሎ የተዘጋዉን ተሳትፎ በር የመክፈት ነገር ነዉ፣፣ባጠቃላይ ያለዉ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነዉ፣፣ ሥልጣን ቢባል፣ኢኮኖሚ ቢባል፣ፕሬስ ቢባል፣ ማናቸዉም የፍትሕ አካላት ቢባል፣ ኢሕአዴግ በመኖፖል ይዟቸዋል፣፣ይሄ ምን ማለት ነዉ? ሕዝብ በኢሕአዴግ ፍላጎት መሠረት በአንድ ድርጅት መመርያ መሠረት ካልሆነ በስተቀር ነፃ በሆኑ ድርጅቶቹ አማካኝነት ሃሳቡን እየገለጻ እየተከራከረ የማይስማማበትን ነገር እየተቃወመ ሊሳተፍ የሚችልብት ሁኔታ አይደለም ያለዉ፣፣ ይኸ ሁሉ ሃይል፣ ይኸ ሁሉ ወገን.ይኸ ሁሉ እጥረት ይኖራል፣፣የተማረ ሰዉ እኮ ያለ ምንም ሥራ ቁጭ ብሏል፣፣የቀረዉ ደግሞ አገር ዉስጥ ስላልተመቸዉ አገር ለቅቆ ሄዷል፣፣ ለዚህ ዋናዉ ምክንያት የመንግሥት ፖሊሲ ነዉ፣፣ ኢሕአዴግ በብቸኝነት ሁሉንም ነገር መቆጣጠር ይፈልጋል፣፣ ይኸ ፍላጎቱ እስከቀጠለ ድረስ ኢኮኖሚዉንም ፖለቲካዉንም የፍትህ መዋቅሩንም ሁሉንም ነገር እኔ ብቻ ተቆጣጥሬ፣ “እኔ በምለዉ መንገድ ብቻ ይሠራ” ብሎ እስካለ ድረስ ለረጂም ጊዜ ወደፊት ለመጓዝ አስቸጋሪ ይመስለኛል፣፣ እርግጥ በአጭር ጊዜ ሲታይ የፕሮፖጋንዳ የብልጠት ሥራዎችን መሥራትና በተሌቪዢን ማሳየት ይቻላል፣፣ የድርጅት ሥራ ምን እንደሆነ ማንም ያዉቀዋል፣፣ በድርጅቱ መዋቅር መሠረት እዚህ አንድ ሰልፍ እዚያም አንድ ሰልፍ፣ እዚያም ታች የተወሰነ ጭብጫባ ለማድረግ ይቻላል፣፣በደረግ ጊዜም ቢሆን መዘንጋት የሌለበት ሰዉ እኮ ስንቁን እየሰነቀ፣ልጁን እየሰጠ ነበር፣፣ ሁሉንም አገር እየከፈለ ነበር እያደር ነዉ ነገሮች እየተለዋወጡ የሄዱበት፣ ወደ ግዳጅ የተሸጋገረዉ፣፣ እና አሁንም እኔ ሚመስለኝና ሊሆን የሚገባዉ ባንዳንድ የፖለቲካ ሰዎች፣በስልታን ላይ ባሉት የፖለቲካ ሰዎች እንደሚነገረዉ ቅድመ ሁኔታ ማቅረብ ሳይሆን መንግሥት ራሱ የፈጠራቸዉን መሰናክሎች እንዲያነሳ ነዉ መደረግ ያለበት፣፣
መንግሥት የተጠየቀዉ ቅድመ ሁኔታ የለም፣፣ የፈጠራቸዉን መሰናክሎች በማንሳት በሩን ወለል አድርጎ ተቃዋሚዎችንም ሌላዉንም ማንኛዉም የሕብረተሰብ ክፍል በአገር ጉዳይ ማሳተፍ ያስፈልጋል፣፣ከነጋዴ ጋር ተጣልቶ ከሕዝባዊ ማህበራት ጋር ተጣልቶ፣ከተማሪ ጋር ተናንቆና ተጣልቶ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለሁሉም ስም ሰጥቶ እስከመቸ ድረስ ይዘለቃል? እነኚህ ሁሉ ላገራቸዉ ጉዳይ የመሳተፍ መብት እኮ ሊሰጣቸዉ ይገባል፣፣ ያን ጊዜ ሕብረተሰብም ባንድነት እጅ ለጅ ተያይዞ መራመድ ይችላል፣፣ እነኚህ ሁኔታዎች ካልተሟሉ በስተቀር ዘላቂ ችግሮችን ለመፍታት፣ዘላቂ በሆነ መንገድ ሰላም ለማስፈን፣የተፋጠነ ልማት ለማምጣት አይቻልም፣፣ ወይም በጣም አስቸጋሪ ነዉ፣፣ አንድ ኢትዬጵያ፣- ከዚህ ለየት ያለ ለመናገር ፈልገዉ ያሉት ካለ ቢነግሩን?
አበራ የማነአብ፣- ምናልባት ከዚህ ላይ ላነሳዉ የምፈልገዉ ጉዳይ በተለይ እኔንም ሆነ በአሁኑ ጊዜ ወደ 2ሺህ እና ከዚያም በላይ የሚገመተዉ በእስር ላይ በዓለም በቃኝና በቃሊቲም የምንገኝ ሰዎችን ሁኔታ ነዉ፣፣ ሰባት ዓመት ያለፍርድ መቀመጥ በጣም ረጅም ጊዜ ነዉ፣፣ በየትም አገር ያልታየ ነዉ፣፣ መንግሥት በበኩሉ ምን ነገር እንደሚያስብ አላዉቅም፣፣ የፈለገዉ ሰበብ ይስጥ ሰባት ዓመት እጅግ በጣም ረዢም ጊዜ ነዉ፣፣ ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነዉ ደግሞ ከሰባት ዓመት እስር በሗላም የፍርድ ሂደቱ እጅግ ዝግምተኛ ነዉ፣፣ ብዙ ምክንያቶች ናቸዉ የሚሰጡት ሰዉ ሰባት ዓመት ከታሰረ በሗላ፣ ባሁኑ ጊዜ የሦስት ወር አንዳንዴም የአራት ወር ቀጠሮ ይሰጠዋል፣፣ ይኸ የፍትሕ ስርዓት ነዉ አዲሲቷ “ኢትዬጵያ” የምንላትን እዉን ማድረግ የሚቻለዉ? ሁለተኛ ክሱ በዘር ማጥፋት ወንጀል ዙርያ የተመሠረተ ክስ ነዉ፣፣ዘር ማጥፋት በመሠረቱ ዓለም አቀፍ ወንጀል ነዉ፣፣ ሕጉም የሚሰጠዉ ትርጉም የመጀመርያዉ አገሮች በሙሉ የሚመሩበትን በ1948 በወጣዉ ኮንቬንሽን ላይ የሰፈረዉን ትርጉም ነዉ፣፣ በወንጀለኛ መቅጫ ላይ አሁን የተጠቀሰዉ 281 የሚባለዉና በዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን መሠረት ስለ ዘር ማጥፋት ወንጀል የተሰጠዉ ትርጉም አይጣጣምም፣፣ በዚህ ሁኔታ የቀረበ ክስ ፍትሕ ማግኘት ይቻላል ወይ? ዘር ማጥፋት ዓለም አቀፍ ወንጀል ነዉ ብለናል፣ እንደ ሩዋንዳ፣ ለምን እንደ ቦስኒያ በዓለም አቀፍ ፍረድ ቤት ለምን አይታይም? እዉነት ይኸ መንግሥት የሚያዋጣዉ ከሆነ፣በቂ ማስረጃ ካለዉ በኢትዬጵያ ዉስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል የተፈፀመ መሆኑን ለምን አደባባይ አያወጣዉም? በእዉነቱ በእነዚህ ጉዳዬች ላይ ብዙ ቅሬታ አለ፣፣ አንድ ኢትዬጵያ፣- ለቤተሰብዎም ሆነ ለዋሽንግቶን አካባቢ ኢትዬጵያዉያን የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ? አበራ የማነአብ፣- ወደ ቤተሰብ ጉዳይ ከመግባቴ በፊት አሁን ስላለንበት ሁኔታ አንድ አጠቃላይ ነገር እንድል ይፈቀድልኝ፣፣ በኤርትራና በኢትዬጵያ መካካል በተለይ በሻዕብያ እና በወያኔ መካከል በተፈጠረዉ ሁኔታ ምክንያት አንዳንድ በዜና ማሰራጫ የሚተላለፉት እዉነት ከሆኑ ለዘላለም የሚያሳፍሩ ነገሮች ናቸዉ በሁለቱም ወገኖች የተፈጸሙት፣፣ እኔ የምፈራዉ ቋሚ የሆነ ጠባሳ በሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል እንዳናስቀር ነዉ፣ ፣ ትናንትና እኮ ሁላችንም ኢትዬጵያዉያን ነበርን፣፣ በብዙዎቻችን ግምት ዛሬም ሁላችንም አንድ ነን፣፣ ኢትዮጵያዉያን ነን ብለን የምናምን አሁንም ብዙ ሰዎች አለን፣፣ እንዴት እነሱ በኢትዬጵያዉያን ላይ እንዴት ደግሞ እኛ እዚህ በኤርትራዉያን ላይ አሁን የሚባሉት ነገሮች ይፈፅማሉ? ይኸ በጣም ሚያሳዝን ነገር ይመስለኛል፣፣ በሁለቱም ወገን ቢሆን እንደዚህ ዓይነቱ ግብታዊና ስሜታዊ የሆኑ እርምጃዎች መቆጠብ አስፈላጊ መስሎ ይታየኛል፣፣
ሁለተኛ ነገር፣ በቤተሰብ ስላለዉ ጉዳይ፣ መላዉ ቤተሰቤ ባለቤቴም ጭምር እንድያዉቁት ባሁኑ ሰዓት ከነበረኝ ሕመም አገግሜ ተሽሎኝ ሕክምናም ጨርሼ በደህና ሁኔታ ላይ መሆን ነዉ፣፣ በእዉነቱ ባለቤቴ ልጆቼ እና የቅርብ ጋደኞቼ በጠቅላላዉ ላደረጉልኝ ድጋፍ በጣም፣በጣም አመሰግናለሁ፣፣ በተለይም ለረጂም ዓመታት እኔንም ሆነ ባለቤቴን በሞራልና በሌላም አኳሗን በመደገፍ ለተባበሩን ጓደኞቼ በሙሉ በዚያ በዋሺንግቶን እና አካባቢ ለሚኖሩ ኢትዬጵያዉያን ላደረጉልን ድጋፍ በድጋሚ በጣም አመሰግናለሁ፣፣ ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ አብረዉ በባድሜ ጦርነት ምክንያት ለጉብኝት ከዉጭ አገሮች ተወጣጥተዉ ወደ ኢትዬጵያ ሄደዉ የነበሩትም ጭምር አቶ አበራ የማነአብን ለመጎብኘት ዓለም በቃኝ እስር ቤት ድረስ በመገኘት እነሱም ያደረጉላቸዉ ቃለ መጠይቅ አብሮ ታትሟል እነሆ፣፣
ጎብኚ፣- የርስዎ የፍረድቤት ጉዳይ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል? አቶ አበራ የማነአብ፣- ነገሩ የመጓተት ባሕሪ አለዉ፣፣ይህ የሆነበት ምክንያት ሰዎች ክስ እንደየጥፋታቸዉ ለየብቻ ሳይሆን ሰዎቹ የተከሰሱት በድምር ነዉ፣፣ለምሳሌ እኔ የተከሰስኩት ከ61 ሰዎች ጋር ነዉ፣፣ እና ወደ 155 በሚሆን ክስ ዓይነቶች ተከስሰናል፣፣ በዚህ ሁሉ ሰዉ ላይ የቀረበዉ ክስ ተሰምቶና የዚህ ሁሉ ሰዉ መቃወሚያ ተሰምቶ እስኪያልቅ ድረስ ከዓቃቤ ሕግ የሚሰጥ መልስ የለም፣፣ ምክንያቱም መዝገቡ አንድ ነዉ፣፣ እንግዲህ ከተጠየቁት ጥያቄዎች አንዱ መዝገቡ ተነጥሎ ይታይልኝ፣፣ ምክንያቱም እኔ ከማላዉቃቸዉ አብሬአቸዉ ካልሰራሁ ሰዎች ጋር ነዉና የተከሰስኩት፣ ምናልባትም እኔ ለብቻየ ብከሰስ፣ወይንም ደግሞ አብረዉኝ ሠርተዋል ከሚባሉት ጋር ብከሰስ፣ አለበለዚያም ለብቻ ተነጥሎ ቢታይ ፈጠን ያለ ሂደት ይኖሮዋል የሚል እምነት አለኝ፣፣ ጎብኚ፣- ልጅዎ ሊጠይቀዎት መጥቶ ነበር፣ አግኝተዉታል? አቶ አበራ የማነአብ፣- በአለፈዉ ጊዜ ለአንድ ለ3 ጊዜ ያህል በጣም ለአጭር ጊዜ አግኝቼዋለሁ፣፣ ከሕክምና ከተመለስኩ ግን ወደ አራት ሣምንት ሊሆነኝ ነዉ እስካሁን ልጄን አላየሁትም፣፣ ጎብኚ፣- ምናልባት ልጁ አልመጣ እንደሆን?
አቶ አበራ የማነአብ፣- አይደለም፣ እኔ እዚህ ካሉት ቤተሰቦቼ ጋር ቅዳሜ እና እሁድ እገናኛለሁ፣፣ እና ልጄ እንዳለና በተለያዩ ቀኖች እየመጣ አይቻልም እየተባለ መመለሱን አዉቃለሁ፣፣ አንድ ነገር መኖር አለበት፣፣ በኔ በኩል እንዳልተፈቀደ ነዉ የማዉቀዉ፣፣ አሁን ከትናንት ወዲያ እንኳን ባለሥልጣኖቹን አነጋግሬ (የግቢዉን ባለሥልጣኖች) እስቲ አነጋግረን ይፈቀድልሃል የሚል መልስ ነዉ የተሰጠኝ፣፣ እስካሁን ድረስ ግን የደረሰኝ ነገር የለም፣፣ ጎብኚ፣- ወደ ኢትዬጵያ የመጣዉን ከመላዉ ዓለም የተዉጣጣ የልዑካን ቡድን ያደረገዉ ጉብኝትና ዉይይት እንዴት ያዩታል? አቶ አበራ የማነአብ፣- ለዚህ ነገር አፍን ሞልቶ ለመናገር በጣም አስቸጋሪ ነዉ፣፣ እኔ የምሰማቸዉ ነገሮች አብዛኛዉ በመገናኛ ብዙሃን በተለይ በመንግሥት መገናኛ የሚነገሩትን ያህል ብቻ ነዉ፣፣ የመንግሥት ብዙሃን መገናኛ ድጎሞ እናንተ የተናገራችሁት ሁሉ እንደማይነግረን ታዉቃላችሁ፣፣ ዞሮ ዞሮ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን በተለይ እዚህ አገር በጣም ወገናዊ ነዉ፣፣ ለምሳሌ በቴሌቪዥን በቀደም ለታ በቀረበዉ እንኳን እናንተ ስለሌሎች ጉዳዬች ያነሳችሗቸዉ ነገሮች በፍጹም እዚያ ላይ አይታይም ነበር፣፣ እና በዚህ ላይ ተመሥርቼ ብዙ ነገር መናገር ያስቸግረኛል፣፣ ተልእኮዉን በተመለከተ በእናንተ በኩል ድርሻችሁን ፣ አገራዊ ግዴታችሁን ለመወጣት የወሰዳችሁት የናንተ አቋም ነዉ፣፣ እኔ ምንም የምናገረዉ ነገር የለኝም፣፣ ጎብኚ፣- የኢትዬጵያ ዳር ድንበር በሻዕቢያ ሠራዊት መደፈሩን እንዴት ይመለከቱታል? አቶ አበራ የማነአብ፣- እንደ እኔ ከዚህ በፊትም እንደነበረኝ አመለካካት ከነበርኩበት ድርጅት አኳያ ስመለከተተዉ ነገሩ አስቸጋሪ ነዉ፣፣ ማለት የምችለዉ በምን ምክንያት ይሁን ብምን የኢትዬጵያ ግዛት መደፈሩን እንደማንም ኢትዬጵያዊ እቃወማለሁ፣፣ ከዚህ ለመዉጣት የኢትዬጵያ ሕዝብ በሞላ በአንድነት ቢሰለፍ በዚህ በድምበር አካባቢ ለተፈጠረዉ ግጭት ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ በኢትዬጵያ ሕለዉና ላይ ለተቃጣዉ ወይም ለተጋረጠዉ ግጭት ብቻ ሳይሆን በጠቅላላ በኢትዬጵያ ሕልዉና ላይ ለተቃጣ ወይም ለተጋረጠዉ አደጋ የተሻለ መፍትሔ መስጠት ይቻላል የሚል እምነት አለኝ፣፣ ምንም እንኳ እዚህ እስርቤት ከገባሁ ወደ 5 ዓመት ሊሆነኝ ጥቂት ወራት ቢቀሩኝም ያንኑ የመጣሁበትን ተልኮ ነዉ የማራምደዉ፣፣ አሁንም የተላኩበትን መፈክር እንዳነገብኩ ነኝ፣፣ ብሔራዊ እርቅ የግድ ያስፈልጋል፣፣የፖለቲካ እርቅ የግድ አስፈልጋል እላለሁ፣፣ የትም አገር ቢሆን በማናቸዉም አገሮች ታሪክ ብንመለከት ከፖለቲካ እርቅ በፊት ዲሞክራሲ የሰፈነበት ሀገር በዓለም ላይ የለም፣፣ እናንተ ደግሞ በዚህ ባጭር ቆይታችሁ በኢትዬጵያ ዉስጥ ዲሞክራሲ ሰፍኗል ብላችሁ ከሆነ በዚህ አመለካከት እንለያያለን፣፣ ኢትዬጵያ ዉስጥ ዲሞክራሲ አለ ማለት አይቻልም፣፣ ያንድ ፓርቲ አገዛዝ ነዉ ያለዉ፣፣ በፖለቲካ እና በርእዬተዓለም አንጻር ዛሬም እንደጥንቱ “እኛ ሶሻሊስት ነን” አይበሉ እንጂ ያለዉን መንግሥት የሚመራዉ ኢህአዴግ ነዉ፣፣ ከኤኮኖሚዉ እስከ ፖቲካዉ ከማህበራዊ ኑሮዉ እስከ መገናኛ ብዙሃኑ በሙሉ እንዲህ ወጥሮ ይዞና ተቆጣጥሮ በሚያስተዳድርበት ሁኔታ ዉስጥ ነዉ አሁን ያለነዉ፣፣ ታዲያ ይኸ መከፈት የለበትም እንዴ? የሕግ የበላይነት ኢትዬጵያ ዉስጥ መስፈን የለበትም እንዴ? ፍርድ ቤት የለቀቀዉ ሰዉ መለቀቅ የለበትም እንዴ? ላዳኝነት የሚቀረበዉ ሰዉስ ፋጣን ፍትህ ማግኘት መብት ሊኖረዉ አይገባም እንዴ? እኛ የምንመኘዉ ለኢትዬጵያ እንዲህ ያለ ነገር አይደለም እንዴ? ማንም ኢትዬጵያዊ ከየትኛዉም ዓይነት ብሔር ይሁን አድልዎ ሳይደረግበት የሚኖርባት ኢትዬጵያ አይደለም እንዴ የምንመኘዉ? ከዚያ በጣም ሩቅ ነን፣፣ ያንን ማድረግ የሚቻለዉ በመጀመርያ መተማመን ሲፈጠር ነዉ፣፣ ያ ሁኔታ እንዳልተፈጠረ ግልጽ ይመስለኛል፣፣
ሁሉም ነገር በአንድ ቀን ላይፈጠር ይችላል፣፣ ግን ወደዚያ ጎዳና ዪወስድ ጅማሮ እንኳን እስከ ዛሬ ኢትዬጵያ ዉስጥ አልተደረገም፣፣ ይኸ መዘንጋት ያለበት አይመስለኝም፣፣ የታል? ምን የተጀመረ ነገር አለ? ስለ ፕሬስ ሲወራ ፕሬሱን ማጥላላት ነዉ፣፣ስለተቃዋሚዎች ሲወራ ተቃዋሚዉን ማጥላላት ነዉ፣፣ ስለ ኢኮኖሚ ነጻ እና መሆን ሲወራ አብዛኛዉን የኢኮኖሚ መስክ አንድ ድርጅት ፡ጨምድዶ መያዝ አለ፣፣ ስለሕግ የበላይነት እዚህ አገር ፍርድ ቤት ዉሎ ማየት የስፈልጋል፣፣ በእዉነቱ በተለይ ፖቲካ ነክ የሆኑ ሰዎች በሚከሰሱበት ጊዜ፣፣ እኔ በበኩሌ መቼም ገና ብዙ ይቀረናል ነዉ የምለዉ፣፣ ጅማሮዉም አልተደረገም፣፣ ዛሬ ያልተጀመረ ደግሞ መቼ ይጀመራል? ይኸ ጥሩ አጋጣሚ ይመስለኛል፣፣ በእዉነቱ አይቻልም የሚል እምነት የለኝም፣፣ ይቻላል፣፣ አሁንም በመንግሥት በኩል ፍላጎቱ ካለ፣ ስላለፈዉ ሳይሆን ስለወደፊቱ ነዉና የምንነጋገረዉ፣በመሆናችን መግባባት ቢኖር በተሻለ ይህንን ዓላማ ግቡን እንዲመታ ማድረግ በተሻለ በአንድ አፍ በአንድ ቃል፣ በአንድነት ተነስተን ወረራዉን እንደምናወግዘዉ ሁሉ ስለሌላዉም ነገር ደግሞ በአንድ መንፈስ፣ እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ በእኩልነትና ጎን ለጎን ቆመን ሕግ ይከበር ብንል፣የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን አብረን ብንታገል በጣም ጥሩ ዉጤት ይገኝ ነበር የሚል እምነት አለኝ፣፣ ጎብኚ፣- ብሔራዊ ዕርቅ በምን ዓይነት መልክ ነዉ የሚያዩት?
አቶ አባራ የማነአብ፣- እኔ ብሔራዊ ዕርቅ ስል እንግዲህ ሰፊ ነገር ነዉ የማስበዉ፣፣ የፖቲካ ዕርቅ መለቴ ነዉ፣፣ ሰዎች የተለያዩ አመለካከት ስላላቸዉ በሕግ ፊት ማበላለጥ ሊኖር አይገባም፣ መንግሥታዊ አግልግሎትን ማበላለጥ አይገባም፣፣ እርቅ በሌለበት ሁኔታ የአጥፊ እና የጠፊ ግንኙነት ነዉ የሚኖረዉ፣፣ እርቅ በሌለበት ሁኔታ አሁን ተቃዋሚን በአስፈለገ መንገድ ሁሉ ወደ ታች የመያዝ፣ ምርጫ ቢደረግ በምርጫዉ ተሳትፎን በመዛባት ተግባር ይኖራል፣፣ አንዱ ተወዳዳዳሪ ወገን (ኢሕአዴግ) በጠቅላላዉ ምንድን ነበር ሲያደርግ የነበረዉ? በመንግሥት መሣርያ አይደለም እንዴ ሲጠቀም የነበረዉ? በመንግሥት ነዳጅ አይደለም እንዴ የተንቀሳቀሰዉ? የመገናኛ ብዙሃን ባብዛኛዉን ጊዜ ያን ሪፖርት ማድረግና ያን በማሰማት አልነበረም እንዴ የሚያልፈዉ? የት አሉ ሌሎቹ? እኔ በበኩሌ ይህ አካሄድ አይጠቅምም ነዉ የምለዉ፣ ከወደፊቱ አንፃር ሲታይ? ጎብኚ፣- በቀደም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊናገሩ ‘እኛም እርቅ እንፈልጋለን” የሚል አመለካከት አቅርበዉልናል፣፣ እርሱን በምን ዓይነት ይመከቱታል? እርሱን በምን ዓይነት ነገር ይመለከቱታል አርስዎ? ካለፈዉ ነዉ የሚመለከቱት? ከዛሬ ጀምሮ እንሂድ ነዉ የሚሉት? አቶ አበራ የማነአብ፣- እኔ ከመጨረሻዉ ነጥብ ብነሳ፣፣ ከእርሳቸዉ አንደበት ይኸ መዉጣቱ በጣም ጥሩ ነዉ እላለሁ፣፣፡በጣም ጠቃሚም ይመስለኛል፣፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደበት የሚነገረዉን ነግግር እንደመንግሥት ፖሊሲ አድርጌ ነዉና የምወስደዉ እሳቸዉ ይህንን ካሉ በአዎንታዊ ነገር አድርጌ ነዉና የምወስደዉ እሳቸዉ ይኸነን ካሉ አዎንታዊ ነገር አድርጌ ነዉ የምመለለኩ፣፣ መቸም የሁላችንም ተስፋ ነዉ፣፣በተግባር የተወሰኑ እርምጃዎች አንደምናይ ተስፋ አለኝ፣፣ መጀመሩ ነዉ ዋነዉ ነገር፣፣በሂደት የሚፈቱ ብዙ ነገሮች ይኖራሉ፣፣ ግን ጅማሮ ቢኖር እንደ መተማመን ከተፈጠረ፣መግባባት ከተፈጠረ ሁሉም ትንሽ እያለ አንን እያዳበረ ይሄዳል ማለት ነዉ፣፣ እንግዲህ ተባለዉ ነገር ወደ ተግባር የሚተረጎምበትን ጊዜ በናፍቆት ነዉ የምንጠብቀዉ፣፣
ጎብኚ፣- ዉጭ ያለን ኢትዬጵያዉያን የአገራችንን ሉዑላዊነት ለማስጠበቅ ብዙ ትብብር እያደረግን ነዉ፣፣ ከዚህ አንጻር ዉጭ ላሉ ኢትዬጵያዉያን የሚያስተላልፉት መልዕክት አለ? አቶ አበራ የማነአብ፣- በአጠቃላይ ጉዳዩን ስንመለከተዉ በአሁኑ ጊዜ እናንተ የምታደርጉት ዓይነት ነገር ማድረግ የሁላችንም ብሔራዊ ግዴታ ይመስለኛል፣፣ በዚህ ጥያቄ ላይ ማመንታት እኮ ሊኖር የሚችል አይመስለኝም፣፣ የኢትዬጵያን ሉዐላዊነትና የኢትዬጵያን አንድነት በሚመለከት በሚመጣ እና ለሚፈጠር ችግር በእኛ በኢትዬጵያዉያን መካከል ልዩነት የለም፣፣ ልዩነት የሚኖረዉ እኛ እርስ በርሳችን ዉስጥ አኗኗራችን ፣ በዲሞክራሲያዊ ሂደታችንና በመሳሰሉት ነገሮች በሚመለከተዉ ነዉ እንጂ የምንለያየዉ በዚህ ጥያቄ ላይ መለያየት ሊኖር አይችልም የሚል እምነት አለኝ፣፣ በመጨረሻም ምንም እንኳን አሁን በእስር ላይ ብሆንም፣ አሁንም ቢሆን ከመንግሥት ጋር በመነጋገር አምናለሁኝ፣፣ ከመንግሥት ጋር ካልተነጋገርን ከማን ጋር እንነጋገራለን? እና ወደድንም ጠላንም ያለዉ መንግሥት ሥልጣን ላይ ነዉ ያለዉ፣፣ ተከታይ ያለዉ ድርጅት ያለዉ የሃገሪቱ መሪ ነዉ፣፣ ከነሱ ጋር የመነጋገር ፍላጎት ከኛ በኩል ሁልጊዜም መኖር ይኖርበታል፣፣ በዚህ መሠረት ተወያይተን የት እንደርሳለን፣፣ በዚህ መሠረት ተወያይተን የት እንደርሳለን? ወደፊት በሂደት የሚታይ ነገር ነዉ፣፣ አለመነጋገር ግን ስህተት ይሆናል፣፣//-//ጌታቸዉ ረዳ http://www.ethiopiansemay.blogspot.com/