Wednesday, September 16, 2015

የአመቱ ከፍተኛ ሐዘናችን! ጌታቸው ረዳ (Edior Ethiopian Semay) መስከረም 1/2008 ዓ/ም

የአመቱ ከፍተኛ ሐዘናችን!
ጌታቸው ረዳ (Edior Ethiopian Semay)
መስከረም 1/2008 ዓ/ም
የተወለድንባት ምድር ኢትዮጵያ በታሪኳ ውስጥ ታይቶ ተስምቶ በማይታወቅ ብሔራዊ ሐዘን ውስጥ ተወጥራ በምትገኝበት በዚህ “አዲስ አመት” የኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ ፤ እንደወትሮው እንኳን ለአዲሱ አመት አደረሳችሁ አንዳይል የአማራው ሕብረተሰብ በወያኔ ትግራይ መሪነትና ሥልጣኑን ለማቆየት በየቦታው ባሰማራቸው ተባባሪ “የሰው ጅቦች” በአማራው ላይ የዘር ማጽዳት/በጀነሳይድ ጥቃት ከመቸውም በተጠናከረ በስፋት በከፍተኛ ሂደት እየተስፋፋና እየተፈጸመ ነው። ስለሆነ አዲሱ አመት ብሔራዊ ሐዘን እንዲሆን “ይህ ጥቃት በቁጭት የሚሰማው” ዜጋ ሁሉ፤ በጥቃቱ የተጠቁትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአማራ ወጣት ገበሬዎች፤ እናቶች፤ህጻናትና አረጋዊያን አባቶች ነብስ ለመዘከር በየድግስ ቤቱ/ኮንሰርት የሚገኝ ወጣት ብሔራዊ ሰንደቃላማውን ዝቅ አድርጎ ሐዘኑን ለመግለጽ የደቂቃ ጸሎት በማድረግ አንዲያስባቸው ጥሪ አቀርባለሁ።

ፎቶወቹ ስትመለከትዋቸው ሊዘገንኗችሁ ይችላሉ፤ ሆኖም ጉሙዝ ጋምቤላ ውስጥ አማራው የደረሰበት የዘር ጥቃት በሰንድ የተመዘገበ ካላየን አናምንም እያሉ ክህደት ውስጥ ያሉ ዜጎች ስላሉ የግድ አቅርቤላችሓለሁ። ሐዘኔን ለተጠቁ ቤተሰቦቻቸው አስተላልፋለሁ። ይህንን ማስረጃ ለላኩልኝ ወዳጆቼም እጀግ አመሰግናለሁ።

ድረገፆችም ሆኑ የሆሆ ጋጋታ ቡድን ደጋፊዎች፤ የግለሰቦችን ተክለሰውነት ማሳመር “የአመቱ ሰው” እያሉ በተለይም ጸረ አማራና የሻዕቢያ አሞጋሾች የሆኑ የፖለቲካ ተቃዋሚ መሪዎችንና የግራኝ አህመድ ታሪክ አሞጋሾች የማሽሞንሞን ሱስ ይዟቸዋል። በእነዚህ ክፍሎች ብዙም አልተገረምኩም፡ እነ ጃዋር መሐመድን፤ ወደ ኤርትራ ሄደው ኢሳያስን ሲያሞካሹልን የነበሩትና ወደ ኤርትራ ሔደው “ሕዝባዊ ሓይል” ተብየው የተሰለፉ ኢትዮጵያዊያን ዜጎችን ሲያስገርፉ የነበሩትን እነ አንዳርጋቸው ጽጌን እና  እነ ተስፋዬ ገበረአብን የመሳሰሉት አማራን ሲዘልፉ ፤ በመጽሐፍቶቹ ላይ የመግቢያ መቅድም ቃላቸውን ሲያሰፍሩ እና ሲያሻሽጡለት የነበሩትን፤ እንዲሁም የኦነግን ወንጀለኞችና የስብሰባ ድግሳቸውን ሲያሟሙቁ  ከነበሩት ድረገፆች የሚጠበቅ ነውና አልገረመኝም። ዛሬም እንደወትሮው ትኩረቴ በነዚህ ክፍሎች ሳይሆን፤ አማራ ሆነው፤ አማራ ሲጠቃ ዝምታን በመረጡ ምሁራን ላይ ነው (አማርኛ ተናጋሪ አንጂ አማራ አይደለሁም በሚሉ እና ኢትዮጵያዊ አንጂ አማራ አይደለሁም ብለው ስለ አማራ ሰቆቃ ፍንክች የማይላቸውንም ጭምር አይደለም እየተናገርኩ ያለሁት፤ ወይንም አማራ ሆነው አማራን በማጥፋት ተልዕኮ የተሰማሩ የወያኔ ቡችሎችና ራሳቸውን የካዱና እራሳቸውን ሚሰድቡ “ትንንሽ ሰዎችን” አይደለም) ። ትኩረቴ አማራ ነኝ በሚሉት አማራው ሲገደል፤ሲባረር ጩሆታቸውን ለዓለም ሕዝብ ላለማሰማት የለገሙትን ምሁራን ላይ ነው።

ከፍተኛ ውርደትና ሐዘን የደረሰባቸው በሚሊዮኖች የሚጠቆጠሩ የአማራ ገበሬዎች በዚችው የመጀመሪያዋ ቀን በሐዘን ተኮማትረው ይገኛሉ።ልጆቻቸው ተበታትነዋል፤ተገድለዋል፤ ምስቶቻቸው ተነጥቀዋል፤ ገሚሶቹም ታስረው እየተደበደቡ “ሽንታም አማራ  ምን ታመጣለህ” ተብለዋል። በቆጨራ ፤በጥይት፤በቢላዋ ሰውነታቸው ተዘልዝሎ በየጫካው የተጣሉ አማራዎች ሬሳቸው የትም ወድቆ የቀባሪ ያለህ ይጮሃል። አማራው “ሽንታም አማራ” ተብሎ ተሰድቦ ተዋርዷል! ይህ ውርደት ያልተሰማው ምሁር ክፍል በተለይም የአማራው ምሁር፤ ውርደት ለምን አንዳልተሰማው ደግሜ ደጋግሜ ብጠይቅም፤ እስካሁን ድረስ መልስ ያልተገኘለት “ዝምታ” ሆኖ አግኝቼዋለሁ።

በየገጠሩ ያሉ ድሃ አማራ ገበሬዎች ይህንን ጥቃት ሲደርስባቸው፤ ከተማ ውስጥ ያሉ አማራዎችም ጥፋራቸው እየተነቀለ በወያኔ ጎስታፖ መርማሪዎች እየተሰቃዩ ነው። ሰቆቃ በማዕከላዊ July 16, 2015 ነገረ ኢትዮጵያ የዘገበውን  አንብቡት።  
ልጥቀስ ፦

“አበበ ካሴ እባላለሁ። ከወንዶች በተጨማሪ ሴቶችም ይመረምሩኛል፡፡ ሴቶቹ የሚመረምሩኝ ራቁቴን አርገው ነው፡፡ እነሱም ራቁታቸውን ሆነው ነው የሚመረምሩኝ፡፡ አሁን ለመናገር የማልደፈርው አፀያፊ ነገርም ፈፅመውብኛል፡፡ ይህን አፀያፊ ነገር የሚፈፅሙት አደንዛዥ እፅ እየተጠቀሙ ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉ በአይኔ አይቻቸዋለሁ፡፡ መርማሪዎቹ ሰውነቴን በኤሌክትሪክ አቃጥለውኛል፡፡ ኤሌክትሪኩን የሚሰኩት ደረቴና የውስጥ እግሬ ላይ ነው፡፡ በዚህም የውስጥ እግሬ ተገልብጦ ሌላ ሰውነት አምጥቶ ነበር፡፡ እጄን ወደ ላይ አስረው ብልቴ ላይ ሀይላንድ አንጠልጥለውበታል፡፡ ሴቶቹ ሀይላንዱን የሚበቃቸውን ያህል ያወዛውዙታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከጥቅም ውጭ ሆኗል፡፡ የዘር ፍሬየን ከጥቅም ውጭ አድርገው ዘሬን እንዳልተካ አድርገውኛል፡፡ ሽንቴንም መቆጣጠር አልችልም፡፡ ይህን ያህል አሰቃይተው ከጥቅም ውጭ ስሆን ቂሊንጦ አምጥተው ጣሉኝ፡፡ 11 ወር ያህል አልጋ ላይ ነበርኩ፡፡ በኤሌክትሪክ ግርፊያው ምክንያት ግራ ሰውነቴ ሽብ ሆኖ ነበር፡፡ ግራ እግሬ መንቀሳቀስ አይችልም ነበር፡፡ በምርኩዝ ነበር የምሄደው፡፡ አሁን እያነከስኩ ነው የምሄደው።” ይላል፤

ወያኔ ትግራይ ያሰማራቸው ጎስታፖ መርማሪዎች የጎንደሬውን የአበበ ካሴን የአማራውን ጥፍር እንዲህ ይነቀላል እያሉ ጥፍር በፒንሳ እየነቀሉ የተጨወቱበትን መረጃ ሰነድ ይኼው፡ ተመልከቱት፤

 ሽሽቱ ምንድነው? የትስ መሸሸግ ይቻላል?
ትግሬው አብሮን መጮህ ተስኖት ከዳር ቆሞ ይገኛል ስንል የነበርነው ሁሉ፤ ዛሬ አማራው ዘር ማንዘሩን ለማጥፋት ጥቃት ሲደርስበት እራሳችን ችለን ቆመን ድርጅት መስርተን አሰባስብን መድረክ አዘጋጅተን ለራሳችን ለምን መጮህ አልቻልንም ብየ ደጋግሜ በቃለ መጠይቄ ተከራክሬአለሁ። አሁንም ጥያቄዬ መልስ እስካላገኘ ድረስ ጩሆቴ ይቀጥላል።

ደቂቃ፤ ሰዓትን፤መአልትን፤ወራትን አመትን ወልዳ አዲስ ዘመን ተብላ በጥቅል ብትመጣም፤ ለአማራው ገበሬ፤ ከእያንዳንዷ ደቂቃ ጋር ላለመሞት ትግል ገጥሟል። አማራው ተከድቷል። ያውም በልጆቹ። ከአብራኩ የተገኙ ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ቁጭ ብለው “ልፋጭ አማራ/ትምክሕተኛ አማራ”  እያሉ የገዛ ጎሳቸውን የሚዘልፉ አማራዎች ተበራክተዋል። ባጭሩ እራሱን የጠላና ማንነቱን የካደ አማራ ተፈጥሯል። አማራው በልጆቹ የተከዳ ማሕበረሰብ ነው። አማራ የሚባል ውጭ አገር ተፈጥሮ ቀስ እያለ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ “አማራ ነኝ” የሚል ክፍል በመፈጠር ላይ ነው አንጂ አማራ የሚባል የለም ለሚሉ ምሁራንም በዚህ ዘመን አናስታውሳለን።

ፕሮፌሰር መስፍን አሌፍ መጽሔት ላይ “እርስዎ ግን አማራ አይደሉም?” ተብለው ሲጠየቁ፤ “አማርኛ ተናጋሪ ነኝ” ነበር ያሉት። “በአንድ ወቅት አማራ የለም ብለው ነበር ዛሬም ይህንኑ አባባል ያምኑበታል?” ብሎ ሲጠይቃቸው “በመሰረቱ አማናለሁ፤ ነገር ግን እየተፈጠረ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠለ እርግጠኛ ነኝ ይፈጠራል። ያን ጊዜም አማሪካ ውስጥ ተፈጥሯል። ኢትዮጵያም ውስጥ ሊፈጠር ይችላል ብዬ ነበር። አሁን በአንድ አመት ውስጥ ያ ስሜት እየተፈጠረ ስለሆነ አሁን ፈፅሞ የተለየ ሁኔታ ነው ያለው ባይ ነኝ።

“ተፈጥሯል ነው የሚሉኝ?”

 አዎ ተፈጥሯል። ግን ንዲህ በአንድ ጊዜ ጠንካራ ስሜት ያለው ሁኔታ ለመፍጠር አይቻልም።

ለምን ጠንካራ ስሜት ያለው አማራ እንዳይፈጠር ተደረገ ለሚል ጥያቄ የፕሮፌሰር መስፍን ግምት የተለየ ቢሆንም  የሌለች ሊቃውንት ጥናት ስንመረምር የአገር ወዳዶቹ የእነ ዶክተር አበባን እና የዶክተር አሰፋ ነጋሽን ቃለ መጠይቆች ሰፊ ጊዜ ወስዳችሁ ዩ ቱብ ላይ የተለጠፈውን ካደመጣችሗቸው መልሱ ዛው ታገኙታላችሁ በኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ፤ ሞረሽ እና ወልቃይት.ካም እና ኢትዮ- ፓትርዮትስ ድረገጽ በመሳሰሉት ገብታችሁ ልታደምጡዋቸው ትችላላችሁ።። እነዚህ ሁለት ምሁራን የሳይኮሎጂ እና የሳይኪያትሪሰት ሊቃውንት ናቸው።ለ24 አመት የቀጠለው የዘር ማጽዳት ዘመቻ፤  ሁለቱ ሊቃውንቶች  የአማራን ጎሳ መጠቃት በወያኔ የተመራ የዘር ማጽዳትወንጀል እንደሆነ በማስረጃ ለ24 አመት ሳይታክቱ  በአደባባይ ሲጮሁ የነበሩ እና አሁንም እየጮኹ ያሉ ምሁራን ናቸው። 

አማራ መሆኑን ያወቁት ፤አማራ ነው ተብሎ የጎሳ ጥቃት ሲፈጸሙበት፤ አማራ የሚባል የለም፤ ተብሎ የተነገረው ወጣት በህልቆ መሳፍርት እያለቀ ያለው የአማራ ገበሬ “አማራ አይደለም” ተብሎ ስለተነገረው፤ ወጣቱ የአማራን ጥቃት በዝምታ እየተቀበለ እንዲቀጥል አስተዋጽኦ አድርጓል ባይ ነኝ።

ልብ ማለት ያለባችሁ፤ የከበሮው ምት ሲቀየር የዳንኪራው ስልትም አብሮ መቀየር አለበት ብሏል፤ ሐሰን ዑመር አብደላ (ጦቢያ) ። አማራ የሚባል ካልነበረና ከሌለ “አማራ የሚል አጠራር ማን ፈጠረው? አማራ ሳይንት ምን ማለት ነው? አማራ ማለት ምን ማለት ነው? አማራው በተወለደበት የአካባቢ መጠሪያ ጎጃሜ፤ ጎንደሬ፤ዳሞቴ፤መንዜ፤ ወሎዬ ………..ወዘተ ሲል በነበረበት ወቅት ጥቃት አልደረሰበትም እና “አማራ ነኝ” የሚልበት ምክንያትና ግፊት ስላልነበረ የራሱ ግንዛቤ ይዞ ተጉዟል። ያ ግንዛቤ ለ24 አመት  አልቀጠለም። ጠላቶች ምቱን፤ዳንኪራውን ለውጠውታል። በጥቅሉ “አማራ ነህ” ተብሎ ተጨፍጭፏል፤ ለውርደት ተዳርጓል፤ በስሙ ወደ ኤርትራ ተጉዘው አማራ ነው የጨፈጨፈህና የአማራ ሕዝብ በስሙ ይቅርታ አንድንጠይቃችሁ ልኮናል እና “ይቅርታ እንጠይቃለን” ብለው ‘አማራው’ የኤርትራን ሕዝብ ይቅርታ እንዲጠይቅ በስሙ በሃሰት ነግደውበታል።  ስለሆነም፤ አማራ የሚባል አለ። ከበሮው ዳንኪራውን ቀይሮታል። ስለሆነም፤ እራሱን ለመከላከል፤ ጎጃሜ ነኝ ጎንደሬ ነኝ…….ወዘተ ወዘተ..በሚለው ስልቱ ለመቀጠል አማራ ነህ እና ትገደላለህ ሲባል፤ አልገደልም፤ ብሎ እራሱን ችሎ አደጋውን ማስቆም አንጂ፤ አማራ አይደለሁም ብሎ በሌላ ዳንኪራ ምት ግበቶ መዳከር ውርደትን መቀበል ከቶ መወገዝ አለበት።

ኢትዮጵያ ውስጥ በአራቱ መዓዝናት ዛሬ በአማራው ላይ፤ በሰንትራል አፍሪካ፤ በሩዋንዳ….የደረሰ እልቂት በማይተናናስ ሂደትና ግዝፈት እልቂት እየተፈፀመበት ነው። ጥያቄው ምን ታደርጊውያለሽ? ምን ማለት ይቻላል?፡ ብሎ ዝም ሳይሆን ፤ “ምን ማለት ይቻላል!” ብለህ ከምትጠይቀኝ  “ምን ማድረግ ይሻላል?” ብለህ ብትጠይቀኝ ይሻለኛል፡ ማለት የሚቻለው ተብሏል፡ ያልተባለ የለም፤ ምን ቢደረግ ይሻላል? የሚለው ጥያቄ ጠይቀኝ”  ብለው እንጂኔር ሃይሉ ሻውል መሳይ የተባለው “የግንቦት 7 የኢሳት ጋዜጠኛው ካድሬ” እንዳረሙት ሁሉ፤ “ምን ማለት ይቻላል?” ሳይሆን “ምን ቢደረግ ይሻላል?” የሚለው ጥያቄ አማራዎች እራሳችሁ መፍትሄው ካላፈላለጋችሁ፤ ሌላ ቀርቶ አማራን የሚዘልፉ ሕሊና ቢስ የወያኔ አማራዎች ተፈጥረዋልና አደጋው እንደ ዋዛ አትዩት።

ላንዳንዶቻችሁ ልነገራችሁ የምፈልገው፡ አሁን ጥቂት ቢመሰልም ፤በዝምታ ሂደት ቢጓዝም፤ ብታምኑም ባታምኑም፤ አማራ የሚባል ማሕበረሰብ የተቆጣ ማሕበረሰብ ተረግዟል። የተቆጣው ክፍል ጊዜ ጠብቆ በአጥቂዎቹ ላይ የመልሶ ማጥቃት ቂም ቢሰነዝር፤ በጣም አስከፊ እልቂት ብቻ ሳይሆን “ኢትዮጵያን የመበተን ሂደትን ያገባድደዋል”። ወያኔዎችም እየሰሩበት ያሉ ሴራ ይህንኑ እንዲከናወን ነው። ይህን አደጋ ካሁኑ ካልተገታ፤ ወንጀለኞቹ በዓለም ፍረድ ቤቶች ካልተከሰሱ፤( ይህንን አባባሌ እንደ ዋዛ የምታዩት ክፍሎች ብትሩ)፤ የሗላ ሗላ “አማራው” አጥቂዎቹን ያገኘ መስሎት ሰላማዊ ሰዎችን ቢጎዳ ያኔ አሁን የምለውን ማስጠንቀቂያ ታስታውሱታላችሁ። በተጠቀሱት አገሮች የሆነው ይህንኑ ነው።አንዱ ሲደክም በተራው ሌላው ጉልበተኛ ሆኖ የሚነሳበት ወቅት አለ፡፤ ወቅት የሰዎችን፤ የአገሮችን ጉልበት በተለያ  ጫናዎች የመለወጥ ባሕሪ አለው።

እኔ እንደ ትግሬነቴ ወያኔ ትግራይ በአማራው ላይ አርግዞት የነበረው አሁን እየቀጠለበት ያለው በአማራ ማሕበረስብ ላይ ያለው ጥላቻ ተቃውሜዋለሁ። ትግሬው መሸሺያውን በደምብ አጠናክሯል። አስፈላጊ የመከላከያ መሳሪያዎች፤ እና ዝግጅቶች ወደ ትግራይ አሽሾ ትግራይን አንዲከላከል ለመጪው ጊዜ ዕቅድ ነደፏል። ምን እንደሚከሰት በደምብ ይረዳዋል።  ስለሆነም ሁላችንም አጥፊና ጠፊ ሆነን ከምንጠፋና ከዚህ ጦስ ለመዳን በረጋ መንፈስ በአማራ ገበሬዎችና  አራሳቸውን ባወቁ በወጣት አማራዎች ላይ እየደረሰ ያለው የዘር ጥቃት ለማስቆም አሁኑኑ መፍትሄ ካልተፈለገለት ኢትዮጵያ ወደ “ነበር” ትለወጣለች። አማራው ገ ሲገቡ መሳሪያውን ትጥቁ አስፈትተውታል! ሆን ብለው! ብትር አንኳ እንዳይዝ ተቆጣጥረውታል።

 የወያኔ የኢንተርሃሙዌ መሪዎች አማራ የሚባል የተገደለ የለም፤ የሚል መልስ ንደሚሰጡት ሁሉ፤ በአማራነቱ እየተገደለና እየተሰደበ ያለው ማሕበረሰብ ከጥቃት ማዳን ሐላፊነት አለባችሁ።

አማራ ሲገደል፤ በየኢንተርኔቱ “ኢትዮጵያ ላይ ጸሐይ በርቷል” እያሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚጽፉ ምሁራን እያነበብን ነው። የበራው ፀሓይ የት እና ለማን አንደወጣችለት አልነገሩንም። እንዲህ የሚሉ ደግሞ “ተቃዋሚ’ ነን የሚሉ ናቸው (የግንቦት7 ደጋፊዎች)። እንዲህ ያለ ማጃጃያ ለኢትዮጵያዊነት የሚበጅ አይደለም። አማራን እየዘለፋችሁ ተቃዋሚ ነን ማለት አትችሉም። አማራ ይጥፋ የምትሉም አማራ ከሌለ ይዛችሁት የምትራመዱት ኢትዮጵያዊነት ጥሩ ስዕል አያሳይም። እርግጥ የወያኔ ፀሐይ በታለች፤ በርታ እስከመቸ ትቀጥላለች የሚለው ራሳችሁን መጠየቅ አለባችሁ።  የአማራ ሬሳ ሳይቀር በሰው ጅቦች ተበልቷል። አማራው የትም ሜዳ ፈስሶ ቀባሪ አጥቶ በፀሐይ እየተቃጠለ ነው። ሕዝቡም ጋዜጠኛውም ምታን መርጧል። ለምን? መልሱም ይኸው ቁልጭ ብሎ ከዚህ በታች ታገኙታላችሁ።

በኢትዮጵያን ሰማይ አዘጋጅ የመረጠላችሁ “የአማራን ጥቃት ቆርቁሮአቸው ግምባር ቀደም እየተጋፈጡ ከሚገኙ ሁለት ምርጥ ኢትዮጵያዊያን የሰጡት አስተያየት ለዚህ አዲስ አመት አቅጣጫ ቀያሽ እንዲሆን ይረዳን ዘንድ የመረጥኩላችሁ የአመቱ ምርጥ ትኩረት እነሆ ”፦

የግንቦት 7 የኢሳቱ ካድሬ ጋዜጠኛ ማሳይ መኮንን፤ ለመኢአድ ሊቀመንበር ለኢንጂኔር ሃይሉ ሻውል ከሁለት አመት በፊት የጠየቃቸው ጥያቄና የሰጡትን መልሰ በጥሞና እንድታነብቡት እጋብዛለሁ። ኢሳት ያን ጊዜ ይህንን ጥያቄ ሲያቀርብላቸው የአማራን ሕዝብ ሰቆቃ ዘግቡ እያልኩ ስወተውታቸውና ስወቅሳቸው በነበረበት ወቅት የቀረበ ዘገባ ነው። ከዚህ አያይዞ ሰሞኑን የሞረሽ ሊቀ መንበርም በኢሳት የሰብአዊ ነክ ጉዳዮች አዘጋጅ ተጠይቀው የሰጡት አጠር ያለ እጅግ ጠቃሚ አስተያያትና ቅሬታ ለታሪክ ዘጋቢዎች እንዲመች አውዲዮውን ወደ ጽሑፍ አቀነባብሬ አቅርቤላች አለሁ፤። አማራው ሲጠቃ “ሕዝቡም ጋዜጠኛውም ምታን መርጧል። ለምን?” ለሚለው  ያቄ  መልሱም ይኸው ቁልጭ ብሎ ታገኙታላችሁ።

ጋዜጠኛ መሳይ፤-
መጋቢት 20/2005 ዓ.ም፤ አርብ። ከቤንሻንጉል ጉምዝ የአማራ ብሔር ኢትዮጵያዊያንን ማፈናቀል ቀጥሏል። ሻግኒ እና ፍኖተ ሰላም በሺዎቹ ተፈናቃይ አማራዎች ተጨናንቋል። የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፕረዚዳንት ኢንጂኔር ሃይሉ ሻውል ይናገራሉ፡

ሃይሉ ሻውል
 “እዛው ያለው አንድ ሰው ከቤቴ አልወጣም ሲል ሚሊሺያ መጥቶ ደብድቦ አጎሳቁሎ ከቤቱ አስወጥቶ ሜዳ ላይ ይጥለዋል። ማን መጥቶ ይከላከልለት? መንግሥት የለ፤ የሌላ ብሔረሰብ መጥቶ አይረዳውም፤ ብቻውን አማራ የሚባለው “በሽታ ይመስል” ሁሉም ….ሌላ ቀርቶ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች አንኳ ሁሉም የአማራ ጉዳይ መስማት አይፈልጉም!” በቃ እውነቱን መር ነው፡ አይፈልጉም! በቃ መስማት አይፈልጉም! ከመጀመሪያ ቀን ይህ መንግሥት ከመጣ ቀን ጀምሮ  ይህንኑ ነው እየተደረገ ያለው። አላልቅ አለ እኮ ሕዝቡ፤ አላልቅ አላቸው! ማለቅ ከሆነ ሁላችን ይጨርሱን እንለቅ፤ አላልቅ አለ…….!

 በሚል የጥያቄው መክፈቻ ይጀምራል፡
መሳይ፤
ሰሞኑን በተከታታይ እየዘገብነው ያለው የአማራው መፈናቀል እየዘገብን ነው። ሰሞኑን በሺዎቹ ተፈናቃዮች በሻግኒ እና ፍኖተ ሰላም ገብተው ተጨናንቀዋል። የድረሱልን ጥሪ እያቀረቡ ነው። አሁንም የመንግሥት ምላሽ ለማግኘት ጥረታችን ያለ ስኬት እንደቀጠለ ነው። የአማራ ክልል ባለሥልጣኖች በጉባኤና ስብሰባ ተጠምደዋል ተብለን ሳናገኛቸው  ቀርተናል። ለአሁን ለማላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት ፕረዚዳንት ኢንጂኔር ሃይሉ ሻውልን በጉዳዩ ላይ አነጋግረናቸዋል።

ኢንጂነር ሃይሉ ሻውል በጣም ነው የማመሰግነው፤ እንግዲህ በዋናነት  በቤንሻንጉል ጉምዝ ይህንን በአማራ ላይ ጥቃት መሰንዘሩ በኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱ በአማራው ላይ  እየደረሰ ያለው ስቃይ ምን ማለት ነው?
ሃይሉ ሻውል

ይኼ ነገር ከዳር ሆነህ ስታየው ጥልቀቱ አይገባህም፤ ይኼ ግን ትልቅ፤ እጅግ ትልቅ ችግር አገርን ለወደፊት  ጉድ ውስጥ  የሚያስገባ ነው። ይኼ እኮ የመጀመሪያ አይደለም። በየቦታው ሲባረሩ፤ ምን አደረግን?  ምንም! በዙሪያ ኢትዮጵያ ድምበር ያሉት ቦታዎች አማራ አንዳይኖሩ እኮ እየተደረገ ነው። ምክንያቱም ይህች አገር የአንድነቷን ጠባቂ ለማሳጣት  ነው። ስለዚህ እየተለቀመ ከየቦታው  እየተባረረ ነው። እኔ ቤንሻንጉል ውስጥ የዚህ ዓይነት ጉድ ይመጣል ብየ አልጠበቅኩም። ሁሌም ቢሆን በሕዝብ መሃል አንዳንድ የግለሰቦች ንትርክ ይፈጠራል እና ያ ይሆን? ብዬ ነበረ፡  ግን ያ አይደለም። ይኼ መፈናቀል በመንግሥት የተዘጋጀ  በመንግሥት ሥራ ላይ የዋለ ነው። አማራው ሠርቶ ገቢ ያሚያገኝበት፤  ከሚሠራበትና ቤተሰቡን ከሚያበላበት ተነስቶ ወደ ረሃብ ሜዳ እየተሰደደ ነው።  ምንድነው ለመሆኑ በዚህ ዓለም  “ጀነሳይድ” የሚባል ከዚህ የባሰ ነገር አለ እንዴ?  ከዚህ ከማሰር ከማባረር፤በመኪና ከማጎሳቆል፤  ከመግደል፤ ኡኡ እያለ መሄድ ፤……አሁን ፍኖተ ሰላም ሜዳ ላይ ፈስሰው ያሉ ሰዎች ስንቶቹ ናቸው በበሽታ  ተጠቅተው ልጆቻቸው ተጠቅተው ለወደፊቱም ልጆቻቸውም እነሱም በሽተኞች የሚሆኑት?

ጉራ ፈርዳ ስንል ቆየን፤ ጅጅጋ ስንል ቆየን፤ አርሲ፤ሐረረጌ ስንል ቆየን፤ አሁን ደግሞ፤ ባዲስ መልክ በምዕራብ ድምበር እንደ አዲስ አማራው እየተፋነቀለ ነው። መጀመሪያውኑ እዛው ሲሄድ የሚታረስ መሬት አጥቶ ነው የኼደው፤ አሁን ተመልሶ እዛው ወደ አገርህ ሂድ፤ የገባህበት ግባ ፤ ብትፈልግ …እየተባለ ነው፤ ታዲያ እኛ ይህንን ሁሉ ሲሰራ ምን አደረግን? አማራ  ብቻውን ነው እንዴ ለአማራ የሚጨኸው?  ምነድ ነው ነገሩ?!

መሳይ፤
ምናልባት ኢንጂኔር ሃይሉ፤ ወደ ሗላ ልመልሰዎትና፤  ይኸ ጉዳይ ከመጀመሪያ ጀምሮ ይህ ነገር በተለያዩ አካባቢዎች ሲከሰት ነበር። አሁን ካለፉት ሁለት አመት ወዲህ ግን  በተጠናከረ ሁኔታ ነው፤  አንዱ ሳይቆም ፤ባንደኛው  ይከሰታል። በተለይ ባለፈው አመትና ዛሬም ተጠናክሮ እየቀጠለ ነው; ለምን ድነው አንደዚህ የከፋ ነገር? መጀመሪያውኑ ሰዎቹ ማለት የሕዝባዊ ሓርነት ትግራይ መሪዎች አማራን በጠላትንት መፈረጃቸውን አልካዱም። በቅርቡ አቶ ሰብሐት ነጋም ተናግረዋል። “አማራ እና ኦርቶዶክስን ሰብረናዋል” ብለዋልና፤ እንደዚህ ዓይነት ነገር በፊትም ዓለማ ነበራቸው፤ አሁን ለምን ተጠናከረ? ምነ ተገኝቶ ነው አሁን?

 ሃይሉ ሻውል    
የተጠናከረው ጠንካራ ረዚስታንስ  ቆሞ አምቢ የሚል ስለጠፋ ነው። አንድ ሰው ከቤቴ አልወጣም ሲል ሚሊሺያ መጥቶ ደብድቦ አጎሳቁሎ፤አቁስሎ፤ ከቤቱ አስወጥቶ ሜዳ ላይ ይጥለዋል። ማን መጥቶ ይከላከልለት? መንግሥት የለ፤ የሌላ ብሔረሰብ መጥቶ አይረዳውም፤ ብቻውን አማራ የሚባለው “በሽታ ይመስል” ሁሉም ….ሌላ ቀርቶ የአገር ውስጥ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች አንኳ ሁሉም የአማራ ጉዳይ መስማት አይፈልጉም!” በቃ እውነቱን  ነው፡ አይፈልጉም! በቃ መስማት አይፈልጉም! ከመጀመሪያ ቀን ይህ መንግሥት ከመጣ ቀን ጀምሮ  ይህንኑ ነው እየተደረገ ያለው። ለወር ትጮሃለህ፤ ነገሩ ተድበስብሶ አንደገና ተረስቶ ዝም ይባላል፤ ከወር በሗላ ሲከሰት እንደገና ተድበስብሶ ይታለፋል፤አንደዛ እያለ ኮንሲስታንት/ቀጣይ የሆነ፤ በሕብረት የሚሰራ በውጭም በውስጥም የለም።

 አሁን ለምሳሌ ሰልፍ ይደረጋል ይባላል። አማራ አለቀ ተብሎ ተከታታይ ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጎ ያውቃል?  የሰማሁት አለ? ዋሽንግተን ተደርጓል? ፍራንክፈርት ተደርጓል? ብርሊን ተደርጓል? የለም!  ለምንድነው ይህ ሕዝብ በራሱ ሕዝብ የተጠላው?  አማራው የሌላው ጉዳይ ሲመጣ አብሮ ይሰለፋል፡ አብሮ ያለቅሳል፡ የራሱን ጉዳይ ግን፤ ማንም፤ምንም፤ማንም አንድ ፋይዳ አድርጎለት አያውቅም። እራሱ ለአማራ ቆመናል የሚለው እንኳ ድምጻቸው ምነው ጠፋ ? ለምን ተደበቁ?  ለምን አይወጡም? ለምን ዛሬ  ወጥተው ጮክ ብለው አይናገሩም?  ለዓለም እኮ ማሳወቅ ማለት ፤ በዚህ በኢሳት ብቻ ሬዲዮ የሚጮኸው ብቻ በቂ አይሆንም፤  በሕብረት ተባብሮ  አንኳን ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያ ወዳጅ የሆኑ የሌላ አገር ዜጎችነም አንዲያግዟቸው ተባብረው  ለዓለም ማሰወቅ ይኖርባቸዋል።

ይህ ሁሉ “ሁማን ራይት ድርጅት” ምነው ዝም አለ? ሰው ሳይነግረው ቀርቶ ነው?  ወይንስ እምቢ አንተባበርም አንጮህላችሁም ብለውን ነው?  ይህነን ማወቅ ያስፈልገናል።  ይለቁ ተውዋቸው ተብሎ ዓለም ወስኖ ከሆነ እንለቅ ግድ የለም፤ አሁን ያለው የማስጨረስ ፕሮግራም ነው እየቀጠለ ያለው፤ ፍኖተሰላም ያለው ተፈናቃይ በሚያለቅሱ ሕጻናት ተጨናንቋል።  ሌላ ቀርቶ መንግሥት ለመጓጓዣቸው አልከፍልላችሁም ብሎአቸው  የመጡበትን ደረቅ የእቃ መጫኛ መኪና ተጭነው፤ ከኪሳቸው ገንዘብ በግድ እየተወሰደ ለሾፌር በግድ ከፍለው እንዲጓዙ ነው የተገደረገው። ባዶ እጁ ነው የደረሰው። ለማኝ ሆኖ እንዲቀር ነው የተደረገው።

መሳይ፤
እንጂነር ሃይሉ እኚህ ዜጎቻችን፤ እነኚህ ኢትዮጵያዊያን ችግር ላይ ናቸው ያሉት፤ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል፤ ሌላው እርስዎ ለገለጿቸው ድርጅቶች፤ተቋማት  የሚደረገው ጩኸት ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡ መፍትሄውም ትንሽ ቀናትም ወራትም ሊወስድ ይችላል፤ አሁን ግን እየሞቱ ያሉ ህፃናት አሉ፤ ሕዝቡ ችግር ላይ ነው ያለው፤። እንደው ሕዝቡ መተባበር የለበትም? በየቦታው የምንስማው ነገር አለ፤ ማለትም፤ በየቦታው ያለ ኢትዮጵያዊ ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቅ መረጃው እንኳን ያለው ምን ያህል ነው? እንዳው ለመርዳትም ለመረዳዳትም መረጃው የለም፤ ስለዚህ እንዴት አዩት?

ሃይሉ ሻውል 
 መረጃው እውነትክን ነው ብዙ የለም፡ ነገር ግን፤ እኛ የምንለው አሁንም ቢሆን ሕዝቡ ያው የገጠሩ ድሃ  ሕዝብ እየለመነ ነው ያለው። የገጠሩ ድሃ ሕዝብ ደግሞ ድርቅ  ገብቶበት ራሱ  ሰርቶ ምግብ መብላት አልቻለም። ስለዚህ ከየከተማው ሰውን የምናሰባስብበት መንገድ፤ እያደረግን ነው። እና ፤እንዲያም ሆኖ አንድ ቡድን ተደራጅቶ እቦታው እየሄደ እንዲረዳቸውና አንዲያስተባብር ነው የምናስበው። ይህ አንዳይደረግ ደግሞ መንግሥት እየዘጋ ነው። ሰውን እያስፈራራ ነው። ታዲያ አንድ መንግሥት የራሱን ሕዝብ  እስኪያልቅ ድረስ  ጠብቁ፤ቁጭ በሉ፤አትሂዱ፤ ሲል ምን ይደረጋል? ሠልፍ አይደረግም፤ ሠልፍ ቢደረግ ደግሞ ውጭ እንጂ እዚህ እኮ እከተማው ውስጥ “የተፈናቀለው ሕዝብ አጠገቡ ቁጭ ብሎ እያለ፤ “ሰው እኮ አለቀ” ብለህ ሰውን ስትነግረው “የት?” ብሎ ይጠይቅሃል። አያውቅም፤ ምንም! ያው ኢሳት ኖሮት የሚያዳምጥ ከሆነ እንጂ ምንም መረጃ የለውም። እኛ የምንለው፡ “እናንተ እንኳ ጥያቄ ስትጠይቁ ስለ አማራ  የምትጠይቁት አማራን ብቻ ነው። ስለ ኦሮሞ የምትጠይቁት ኦሮሞውን ብቻ ነው። አረ እባካችሁ ለምን የአማራ ጉዳይ የኦማራ ብቻ ነው? የኦሮሞ ጉዳይ የኦሮሞ ብቻ ነው?  የወላይታ ጉዳይ ..የአማራ..የኦሮሞ ጉዳይ በሙሉ የኢትዮጵያ ጉዳይ አይደለም? እንዴ የወደፊት ትውልድ እኮ እያለቀ ነው! ያ ለውጭ ዜጋ የሚሰጥ/የሚዘጋጅ መሬት፤ አለ፤ ሕዝቡ ግን የሚያርሰው መሬት እየተነጠቀ ፤እየተባረረ፤ የሚበላው አጥቶ ለረሃብ እየተዳረገ ነው።”

ይኼ እኮ ‘ሰልፍ ኢንክሪሚነትድ’ የሆነ በሕግ በግልፅ እየታዬ ያለ ሴራ ነው። እኛ ገደብ አለን። ይህንን ተናግረናል። እኛ ባንነግራችሁም፤ ይህንን ታውቁታላችሁ፤ ሰፊ ነፃነት የአለበት አገር ነው ያላችሁት፤ ብዙ ምሁራን ያሉበት፤ የኢትዮጵያ ምሁራን አገራቸው ለወደፊቱ የምትሄድበት መንገድና አቅጣቻ ያውቁ ፤ የተመራመሩ’፤ አንጎል ያለቸው ብዙ ምሁራን ያሉበት አገር ነው ያላችሁበት፤ ይኼ ባጭር ጊዜ ቁጭ ብሎ፤ በ24 ሰዓት ሥራ ላይ ማዋል ይቻላል፡ ብዙ መሰራት የሚቻል ጉዳይ ነው። ከዚህ የበለጠ ነገር የለም።

 መሳይ፤-
ኢንጂኔር ሃይሉ፤ እርስዎ የጠቀሱት ጉዳይ አለ። እኛም ይህንን በሚመለከት ጉዳይ የተለያዩ መድረኮች አናዘጋጃለን(ይህ የተለመደው የኢሳት ማታለያ ውሸት ነው! ሁለት አመት ሆኖታል ይህ ቃለ መጠይቅ ከተደረገ፤ ለነብርሃኑ፤ ለነ አንዳርጋቸው፤ ለነ….ሲጮሕ፤መድረክ ሲከፈትና በየአገሩ ተደጋጋሚ መድረክ ሲዘጋጅ፤ ስለ አማራ ጉዳይ የተደረገ ነገር የለም። ያውም እዚህ ሳንሆዘ ካሊፎረኒያ ውስጥ፤ ስለ አማራ ጉዳይ ሞረሽ ያዘጋጀውን መድረክ አማራዎቹ እነ ታማኝ በየነ እና የመሳሰሉ ታዋቂ የኢሳት ሰዎች የአማራውን መድረክ ለመነጋጋር የተዘጋጀውን አዳራሽ እየረገጡ፤ በጎሪጥ አዳራሹን እያዩ በማለፍ ኢሳት ስለ አንዳርጋቸው ጽጌ ወደ አዘጋጀው መድረክ እና አዳራሽ ነበር የሄዱት።ያውም፤ ሆን ብለው ኢሳቶች የአማራውን መድረክ ሰው አንዳይገባበት ሞረሽ ባዘጋጀው ሰዓት፤ቀን እና ቦታ አዘጋጅተው፤ ሕዝቡ ጎን ለጎን በሁለት አዳራሽ ተከፍሎ ነበር የተመለከትነው። በዚህ ላይ እኔ የሞረሽ ተናጋሪ አንግዳ ሆኜ ተጋብዤ ስለነበር፤ በጉዳዩ ልዩ ትችት ለኢሳት አዘጋጆች…በታማኝ፤ በአበበ ገላው (አበበ በላው ኢትዮጵያዊ እንጂ “አማራ” አይደለሁም ብሎ ኢመይል ቢያደርግልኝም ) እና በመሳሰሉት ላይ በማግስቱ ትችት ጽፌአለሁ።ስለዚህም “ እኛም የተለያዩ መድረኮች እናዘጋጃለን” እያለ መሳይ የሚዋሸው ለፕሮፓጋንዳ ጠቀሜታ ተብሎ የተናገረው መሆኑንን ይታወቅ። )

 እዛው ባላችሁበት ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ሰዎች ለማነጋጋር ሞክረን “የምናውቀው ነገር የለም ነው የሚሉት”፡ እናንተስ ለማነጋገር ሙከራ አድረጋችሗል ትኩረት አንዲሰጡት ጥረት አድርጋችሗል?

ሃይሉ ሻውል 
ባሕርዳር ድረስ ሰው ልኬ የሚያናግረው ባለሥልጣን አጥቶ ነው በየመንገዱ እየዞረ ችግረኞቹን ቁጭ ብሎ  እያነጋገረ መረጃ እየወሰደ፤ አብሮ እያለቀሰ የሚገኝ ሰው አለን። ስለዚህ እናንት ቃለ መጠይቅ ስታደርጉ  እንሰማለን፡ ስለ አማራ ጉዳይ አማራ ክልል ውስጥ የጠየቃችሁት ሰው “አማራ ያልሆነ ሰው ነው”። አጥፊዎቹ ውስጥ ተደብቀው፤ ባለሥልጣኖቹ መደበቅ ስለፈለጉ፤ ያንን ሰው “ፍሮንት” አድርገው እነሱ ቦሮአቸው ውስጥ ተደብቀው አገር ጤና አንደሆነ ሲናገሩ የሚያሳዝኑ ሰዎች ናቸው። እንዲሀ ዓይነቶቹ የተሸጡ ሰዎች አንዴት  የአማራ ክልል መሪዎች ይሆናሉ! እንዴት?! ስለዚህ ሁሉ ነገር “ሕዝቡን የሚፃረር/አገይንስት ዘ - ፖፑለሽን ነው” “ሕዝቡን ለማጥፋት የተነሱ ናቸው። የአገሩን አስተዳዳሪዎችም ሆኑ የሌሎቹ አስተዳዳሪዎች። ሕዝቡ ከማን ጋር ሄዶ አቤት ይበል? ስለዚህ ውጭ አገር ጠንከር ያለ ‘ረፕረዘንተሽን” መደረግ አለበት። እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሳ ተቃውሞ በጣም አስቸጋሪ ነው። በጣም፤በጣም አስቸጋሪ ነው! እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ተከታታይ/ ሰላይ አለው። ስለዚህ እንደ ቀላል ነገር አትዩት።

መሳይ፤
 ግፉ በዝቷል። ብዙ ሰዎች የሚስማሙበት ነገር አለ፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ የመብት ጥያቄ ለማንሳት ብዙ በቂ ምክንያቶች አሉ፤ ለምንድ ነው ሕዝቡ ወደ እዚያ ያልመጣ፤ የሚል ብዙ ሊያወያይ ይችላል።  በርግጥ አመፅ መጥራት አይደለም።መብት መጠየቅ አልተቻለም። ሁሉም  ነገር እንደው መንግሥትን መጠበቅ ብቻ አይደለም። መንግሥት መፍትሔ ካልሰጠ ሕዝቡ ጥያቄ ማንሳት  ያለበት አይደለም ወይ ይላሉ? እንደው ይህንን ጥያቄ ሳነሳለዎት “በአማራ ጉዳይ” ብቻ ኢይደለም፤ እንዳው  በጠቅላላ የሕዝብ ጥያቄ እየተነሳ አይደለም። ዝም እየተባለ ነው ያለው። በሃይማኖትም ነገር ቢኬድ’ እግዚአብሔር ያመጣው እሱ ያውቃል’፤ አግዚአብሔር ያመጣውን እራሱ ይመልሰው..” የሚል ነው የሚነገረውና እንደው፤  ምን ማለት ይቻላል ኢነጂነር ሃይሉ?

ሃይሉ ሻውል 
 ምን ማለት ይቻላል? የሚለው ሳይሆን ምን ማድረግ ይሻላል? የሚለው ጥያቄ ይሻለኛል። ምክንያቱም ማለት የሚባለው ሁሉ ተብሏል። እየተባረረ፤ ቤቱ እየፈረሰ አይደለም እንዴ ያለው፡ ሁሉም ተብሏል፤ያልተባለ የለም። ምን ተደረገ? ምንም? ምክንያቱም ያለው ሃይል እና የተበሳጨው ሕዝብ ቁጥር እኩል አይደለም። ትንሽ ቢኖሮው፤ ያችን ትንሽ ነገር ይዞ ለነገ ልኑር ብሎ የሚኖር ሕዝብ ነው።  ሕዝቡ እኮ ከ97 ወዲህ ‘ሞቲቬሽን’/ ተነሳሺነት አጥቷል። መንቀሳቀሻ አጥቷል;፤ታፍኗል ። ብዙ ዲክታተሮች በዚህ አይነት መንገድ አገር ገዝተዋል; ነገር ግን  አንዲህ ያለ አገር ሚያፈረስ አልታየም። አገር አይኖረንም፤ የተናደደ ሕዝብ ነው ያለው፡ ለጊዜው ግን ልጄን ት/ቤት እልካለሁ፤ ልጄን አበላለሁ በሚል ነው። ይህ የልጅ ጉዳይ አስቸጋሪ ነው። በደርግ ጊዜም የተደረገው ይሄው ነው። ግን አሁን ምን መደረግ አለበት ለሚለው ጥያቄ  ሕዝቡ፤ አሁን ባለው አቅም  ከውጭ ካልተጮኸለት፤ ከውጭ ካልተገፋ፤ ‘ሪሶርስ’ እየተላከለት ‘አይዞህ’ እስካልተባለ፤ ድረስ ‘ሃሞቱ’ ሞቷል፡ ነብሱም እየሞተ ነው። ይኼው ነው!

መሳይ፤
ኢጂኔር ሃይሉ፤ አመሰግናለሁ፤ በቀጣዩ ተከታታይ መድረክ ከፍተን ሕዝቡ አንዲወያይበት፤ ሃሳብ አንዲሰጥበት እናደርጋለን። ሲል መሳይ ጥያቄውን
በተለመደው የግንቦት 7 ጋዜጠኛ ካድሬነቱ በማሞኚያ ስልቱ ቃለ ምልልሱን ዘግቶታል።፡

ሆኖም እውነት ኢሳት “ቀጣይ እና ተከታታይ መድረክ ከፍቶ ስለ አማራ ጉዳይ ሕዝቡ እንዲወያይበት የማድረግ ፍላጎት አለው? የለውም። መልሱም ከሞረሽ ሊቀመንበር አቶ ተክሌ የሻው ባለፈው ሰሞን ከኢሳት ከሰብአዊ መብት ጉዳይ አዘጋጅ ተብዬው (ጠያቂውም ተብዬው እንድለው ያስገደደኝ ብዙ የካሁን በፊት ስራዎቹ ምክንያቶች ስላሉኝ ነው)። “ኢሳት በማስረጃ ብቻ ነው ዜናዎችን የሚያሰራጨው እያለ ሲዋሽ፤ ከተወሰንን ሰዎች ግፍት እና ትችት ሲደርስበት ፤ለማስመሰል ሲል አለፍ አልፍ ብሎ ካልሆነ ኢሳት ማስረጃ ተሰጥቶትም የአማራ ጉዳይ በማስረጃ ተካትቶ ሲሰጠው አይዘግብም።  የሞረሹ ሊቀመንበር አቶ ተክሌ የሻው ጉሙዝ ውስጥ አማራዎች ታርደው መበላታቸው በሚመለከት ጉዳይ ከኢሳት ጋር ባለፈው ሰሞን ያደረጉትን ቃለ መጠይቅ ለኢሳት ያቀረቡትን እሮሮ አጭር ማስረጃ ልጥቀስ እና ልደምድም፡
ቃለ መጠይቅ፤

የኢሳት ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ክ/ጊዜ አዘጋጅ
“በጉሙዝ  እና በሌሎቹ ክልሎች እንዲህ ያለ ነገር እንዳይከሰት ለአካባቢው ተወላጆችም ለሌሎች ኢትዮጵያዊያንም የሚሉት ነገር አለ?

የአቶ ተክሌ የሻው (ሞረሽ) መልስ፤
እንዳይከሰት እማ ምንም የምንለው ነገር የለም፤ “ኦልረዲ” እኮ ተከስቷል። የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ የክልል አስተዳዳሪዎች የተደራጁት እኮ አማራን ለማጥፋት ነው።  አማራ አገራችሁ ሌላ ቦታ ነው፤ “ውጡ!”  እየተባሉ እኮ ነው ከየቦታው እየተባረሩ እየተገደሉ ያሉት። ምሳሌ ውሰድ፤ ቤንሻንጉል፤ጋምቤላ ውስጥ ከሚኖረው ሕዝብ አብዛኛው አማራው ነው፤የነሱ ዞን ግን አልተፈጠረም። ። አማራ ክልል የሚሉት ስትመጣ ግን ለምሳሌ ጎጃም ውስጥ አዊ ዞን ብለው አጎቦቹ ለይተዋል፤ ወሎ ላይም አንዲሁ አሁን በቅርቡ ደግሞ “ቅማነት” ተብለው ተለይተዋል። አማራ ግን ሓረርም ሎችም ቦታዎች ብትሄድ ዞን የላቸውም። ሆን ተብሎ ለአደጋ እንዲጋለጥ በጥናት በመንግሥት ፖሊሲ የተቀረጸ ነው። የወያኔ ዓላማ ይኼው ስለሆነ፤ በጎሳ ላይ የተመሰረቱ ድርጅቶች የሚሰሩት ይህ ነው። አርባ ጉጉ የተፈጸመው ይኼው ነው፡ ጉራፈርዳ የተደረገው ይህ ነው። ከምስራቅ ወለጋ ተባርረው፤1993 ዓ/ም ቡሬ ላይ በረሃብ እና በበሽታ ያለቁት በዚህ ምከንያት ነው፡ (ጦቢያ መጽሔትን አንብበው)ምን ያለተጪኸበት ጊዜ አለ! ነገዱ እራሱን አደራጅቶ ከጥቃት ካልተከላለከ ለወያኔ ማመልከቻ በማስገባት ይቆማል ብለን አናምንም።

የኢሳት ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ክ/ጊዜ አዘጋጅ
አሁን ሰሞኑ 240 ሰዎች ሞትን ፈርተው በየጫካው ተደብቀው እስካሁን ድረስ ይገኛሉ እሚባሉትስ ሁኔታቸው እንዴት ነው? የት አካባቢስ ነው ያሉት?

የአቶ ተክሌ የሻው (ሞረሽ) መልስ፤
እዛው ጫካ ውስጥ ነው ያሉት። ተበታትነዋል። እያደኗቸው ነው ያሉት። በየበረሃው ላይ ነው ያሉት። በተናጠል አንዲገደሉ ስለሆነ ውሳኔው፤ በተናጠል ነው ከአደናው ለማምለጥ እየተደበቁ ተበታትነው ነብሳቸውን ለማዳን በየጫካው ነው እየተሯሯጡ ያሉት። አንዳንዶቹ እየተደበቁ እየተንጠባጠቡ ወደ አማራው ክልል እየተጠጉ እንዳሉ ነው እስካሁን የደረሰን መረጃ። የተወሰኑነት ደግሞ ወደ ዳንግላ/ጋንድላ (የስም ስሕተት ቢደረግ ቴፑ/ድምፁ ጥራት ስለማይሰማ ስሕተት ካለ የዚህ ጸሓፊ ነው)፤ ወደ ፍኖተ ሰላም የገቡም አሉ፤ አብዛኛው ግን አሁንም እጫካው ውስጥ ተደብቀው ነው ያሉት የሚል መረጃ ነው የደረሰን።

 የኢሳት ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ክ/ጊዜ አዘጋጅ፤-
በዚህ ጉዳይስ በመንግሥት በኩል  የአማራው ክልል ይህንን ለማስቆም ወይንም ፍትሕ ለማግኘት እንዲህ ያሉ የተደረጉ ሙከራዎች ወይንም ጥረት አለ?

የአቶ ተክሌ የሻው (ሞረሽ) መልስ፤
ቅድም እንዳልኩህ ነው። የአማራ ክልል ወያኔ ገና እንደገባ ክልሉን ሲከልል፤ የክልሉ  የማሕበራዊ ጉዳይ ሃላፊ የነበረው፤ “አምባቸው አባተ ሃዳስ” ይባላል። አማራ አለቀ ሲባል ‘አማራ  ከዓባይ ወዲያ ምን አሻገረው?” ነው ያለው። ስለዚህ አማራው ክልል ያሉት ሰዎች  እነ በረከት ስሞን ናቸው፤ እነ ሕላዌ ዮሴፍ ናቸው፤ እነ ታደሰ ጥንቅሹ ናቸው፤ ሆን ብለው ሊያጠፉት የተሰማሩ ናቸው። አማራ በኤርትራ ሕዝብ ጭፍጨፋ አካሂዷል እና ተጠያቂ ነው፤ ስለሆነም አማራው የኤርትራን ሕዝብ ይቅርታ ይጠይቅ ብለው ኤርትራ ድረስ ሄደው በይፋ ዓለም እየሰማ፤ እኛ አማራዎች ላደረስንባችሁ ጥቃትና ስቃይ ይቅርታ እንጠይቃችሗለን፤ ብለው አስመራ ድረስ ሄደው በአማራው ስም ይቅርታ ጠይቀዋል። ይህ እኮ ሆን ተብሎ አማራውን ሕብረተሰብ ወንጀለኛ አድርገው አንዲጠላ የወነጀሉት በወያኔ መንግሥት የተላኩ እና የተሰማሩ ሰዎች ናቸው። እኒህ ሰዎች እኮ አብዛኛዎቹ አመራር ላይ ያሉት አማራ አይደሉም!

ኢሕዴን/ብአዲን ሲመሰረትና ድርጀቱ ውስጥ ያሉት ሰዎችና መመሪያቸው እኮ “አማራ ጸረ ትግሬ ነው። አማራ የኢትዮጵያ ችግር ነው፤አማራ ለኤርትራ ሕዝብ ስቃይ ተጠያቂ ነው፡” ብለው የፈረሙ ሰዎች ናቸው። አስቀድመው ከመነሻቸው አማራውን በጠላትነት የፈረጁ ሰዎች፤ ለአማራው ደህንንት ይቆማሉ ብለን ስለማናስብ፤ እስካሁን ድረስ እኛ የምናውቀው የተወሰደ እርምጃ የለም። የናንተ ቴ/ቪዥን ጨምሮ “የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ነኝ” የሚለው ኢሳት ከ60 በላይ መግለጫ ሰጥተናቸው አንዱንም አላወጡትም! መረጃው የት ነው? እውነት ነው ወይ ብለው ሊጠየይቁን  አልፈለጉም። ይህንን የሚያሳየው ምንድ ነው፤ በአማራው ላይ ሁሉም ፊቱን  ዙሮበታል!

የኢሳት ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ክ/ጊዜ አዘጋጅ
የማስረጃ ጉዳይ አንገብጋቢ ነው፡ ኢሳት ውስጥ እንዲህ ያለ ጉዳይ የተለመደ ነው!

የአቶ ተክሌ የሻው (ሞረሽ) መልስ፤
አልኩህ እኮ፤ የናንተ ቴ/ቪዥን ጨምሮ “የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ነኝ” የሚለው ኢሳት ከ60 በላይ መግለጫ ሰጥተናቸው አንዱንም አላወጡትም! መረጃው የት ነው? እውነት ነው ወይ ብለው ሊጠየይቁን  አልፈለጉም። ይህንን የሚያሳየው ምንድ ነው፤ በአማራው ላይ ሁሉም ፊቱን  ዙሮበታል!

የኢሳት ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ክ/ጊዜ አዘጋጅ፤-
እስካሁን ድረስ የሰጣችሁን የሞቱ የ88 ሰዎች ስም ዝርዝር እና በርካታ ሰዎች ጫካ ውስጥ ተደብቀው እንዳሉ ነው። ድርጊቱ የተደረገው ከ4 ወር በፊት ነው። ከዚህ በሗላ በቀጣይ መደረግ ያለበት ምንድነው? ለሰብአዊ መብት የቆሙ አካላት ይህነን ጉዳይ ለማስቆም ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል?

የአቶ ተክሌ የሻው (ሞረሽ) መልስ፤
ስለ አማራው ሕዝብ የቆመ ድርጅት ስለሌለ እኛ ተቋቁመን፤ በኛ በኩል ወንጀል ፈጻሚው፤ አድራጊው ተደራጊው፤አጥቂና ተጠቂው ለይተን በስም ዝርዝር በባለ ሙያዎች እንዲጣራ በመረጃ አስደግፈን በግልም በቡድንም ወደ ፍርድ የሚቀረብበት ማሕደር እያዘጋጀን ነው። ባጠቃላይ ግን ከከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በአማራው፤ በተለያዩ ቦታዎች የደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል አንድ ባንድ የደረሰው ሁኔታ በዝርዝር ተጠንቶ ሥራው አልቋል; በሚቀጥለው አምስት ወይንም ስድስት ወር ውስጥ ለዓለም ይፋ እናደርገዋለን። በኛ በኩል የአማራ ጉዳይ ሕዝብ አንዲያውቀው እያደረግን ነው።

የኢሳት ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ክ/ጊዜ አዘጋጅ
የማስረጃ ጉዳይ አንገብጋቢ ነው፡ ኢሳት ውስጥ እንዲህ ያለ ጉዳይ “የተለመደ” ነው!

የአቶ ተክሌ የሻው (ሞረሽ) መልስ፤
ነገርኩህ እኮ!…….የናንተ ቴ/ቪዥን ጨምሮ “የሕዝብ ዓይንና ጆሮ ነኝ” የሚለው ኢሳት ከ60 በላይ መግለጫ ሰጥተናቸው አንዱንም አላወጡትም እኮ ነው የምልህ! መረጃው የት ነው? እውነት ነው ወይ ብለው ሊጠየይቁን  ያጣሩ አልፈለጉም። ይህንን የሚያሳየው ምንድ ነው፤ በአማራው ላይ ሁሉም ፊቱን  ዙሮበታል!
አመሰግናለሁ።
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay ኢትዮጵያን ሰማይ አዘጋጅ) getachre@aol.com