Monday, September 23, 2019

በእውኑ ኢትዮጵያ መንግሥት አላትን? ብሥራት ደረሰ (posted on Ethio Semay)


በእውኑ ኢትዮጵያ መንግሥት አላትን?
ብሥራት ደረሰ (posted on Ethio Semay)

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት መንግሥት አላት ብሎ ማሰብ አይቻልም፡፡ በተሳሳተና ወደ አንድ ወገን ባጋደለ የኦነግ/ኦህዲድ ቅኝ ግዛታዊ አገዛዝ ሥር ወድቀናል፡፡ ይህን ገሃድ የወጣ ሀገራዊ እውነት በምንም መንገድ ለመደበቅ ወይም ለማስተባበል መሻት የኦነግ/ኦህዲድን የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ ወዶና ፈቅዶ ለመቀበል እንደመዘጋጀት ይቆጠራል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ስም እየማላችሁና እየተገዘታችሁ በሥውርና በግልጽ ግን ኢትዮጵያን እያወደመ ከሚገኘው ኦነግ/ኦህዲድ ጋር የምትሞዳሞዱ ተቃዋሚ ተብዬዎች እጃችሁን ከዚህች ቅድስት ሀገር እንድታነሱ ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡  የብዙኃን ዕንባ የሚያስከትለውን የቅጣት ዶፍ በሚገባ የምንረዳ ወገኖች መጪው ዘመን ለማን ምን ይዞ በመገስገስ ላይ እንደሆነ መገመት አይከብድምና ለሌላ ሳይሆን ለራሳችሁ ተጠንቀቁ፡፡

በኢትዮ - ኦሮ እና በፊንፊኔ - አዲስ አበባ ተወጥራ ልትፈነዳ የደረሰች ሀገር ውስጥ መኖር ከጀመርን አንድ ዓመት ከመንፈቅ ሆነን፡፡ እመለስበታለሁ፡፡

በዜጎችና በሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በተመለከተ በትናንትናው ዕለት በበርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች የተደረገው ሰላማዊ ሠልፍ እጅግ ደማቅና የሀገራዊ ትንሣኤያችንን ጅማሮ አመላካች ነበር፡፡ በሕይወቴ ከተደሰትኩባቸው ቀናት አንዱ ትናንት ነበር፡፡ምንም እንኳን የመንግሥት ሚዲያዎች ተኩረት በሌላ ግንጥል ጌጥ ላይ ሆኖ ይህ ክስተት በነሱ በወጉ ባይሸፈንም ባሉን ሌሎች አማራጭ የዜና አውታሮች እንደተከታተልነው የሕዝባችን ተነሳሽነት በእጅጉ አበረታች ነው፡፡ ይህን የሕዝብና የሀገር ጩኸትና ዋይታ የራሔልን ዕንባ ከጽርሐ አርያም ሰምቶ በሕወሓት-ኦህዲዳዊ የፈርዖን አገዛዝ ሥር ለነበሩ እሥራኤላውያን ሙሤን የላከላቸው የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ይሰማል፡፡ ሰምቶም ዝም አይልም፡፡ ሁነኛ መሢሑን ይልካል፡፡ በዚህ ጥርጥር የለንም፡፡

በተመሳሳይ ወቅት በትናንትናው ዕለት አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው የኢሬቻ ሩጫ ግሩም አጀማመርና አጨራረስ ነበረው፡፡ በሰላም ተጀምሮ በሰላም መጠናቀቁ አስደሳች ነበር፡፡ የአዲስ አበባና (የፊንፊኔ ለማለት ነው) የ“ኦሮሚያ ክልል” ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ ሽመልስ አብዲሣ በኦሮምኛ የተናገሩትን ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ስሰማው ግን አስከፍቶኛል፡፡ “አበበ ቢቂላና ደራርቱ ቱሉን የመሰሉ የኦሮሞ ልጆች በጨለማው ዘመን የብሔራችንን ስም ከፍ ብሎ እንዲጠራ የድርሻቸውን ተወጥተዋል....” ዓይነት ንግግር ማድረጋቸው ነውር ነው፡፡ የጨለማ ዘመን ያሉት ለኦሮሞ ብቻ ከሆነ በተለይ ትልቅ ነውር ነው፡፡አላልኩም ካሉም ማስተባበያቸውን ይንገሩን። 

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሤ ኦሮሞ ነበሩ፤ ጄኔራል ተፈሪ በንቲ ኦሮሞ ነበሩ፤ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ኦሮሞ ነበሩ፤ ደበላ ዲንሣ፣ ጄኔራሎች ጃጋማ ኬሎ፣ ደምሤ ቡልቶ፣ ... እነዚህና ሌሎችም ኦሮሞ ነገሥታት፣ የሀገር መሪዎችና የጦር አበጋዞች ከጃዋር ሞሀመድ የበለጡ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ እርሳቸው ግን ከቋንቋው በስተቀር አንድም የኦሮሞ ደም ከሌለበት ከፊል የመናዊ ሰው አጠገብ ቀምጠውና ከዚህ ኦሮሞ ያልሆነ ሀገር ሻጭ የዐረብ ደላላ ጋር እየተቃቀፉ የኦሮሞዎችን ሀገር የአማሮች ለማስመሰል ባደረጉት ከንቱ ሙከራ አሁን ላይ ሆነን የኋሊት ስንመለከተው ለኛ ለጭቁኖች ወርቃማና ብርሃናማ የነበረውን ዘመን “የጨለማ ዘመን” አሉ፡፡ ፈጣሪ ፍርዱን ይስጣቸው፡፡ ለዚህ ጀብደኛ አነጋገር ያበቃቸው ራሱ አዴፓን ወይም ብአዴንን ተመስሎ በአማራው ሕዝብ ስም የሚንቀሳቀሰው የሠርጎ ገቦች ጥርቅሙ ድርጅት መሆኑን ሊረዱ በተገባቸው ነበር፡፡ ቀሪውን የንግግራቸውን ስህተት በጊዜ ሂደት ያወራርዱታል፡፡ አንቸኩልም፡፡

እመለስበታለሁ ወዳልኩት ተመለስኩ፡፡ አዲስ አበባን የተቆጣጠረ ኢትዮጵያንም እንደሚቆጣጠር የታመነ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአሥመራ ተለምኖ ከአንድ ሽህ ሁለት መቶ ጥገኛ ወታደሮቹ ጋር ወደ መሀል አገር የገባው ኦነግ ዕድሜ ለልጆቹ ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖለት አዲስ አበባን ብቻ ሣይሆን መላዋን ሀገራችንን በሚገባ ተቆጣጥሯል፡፡ ይህን ሃቅ መካድ የኅሊና መታወር ነው፡፡

ከሞላ ጎደል ሁሉንም የ“ፌዴራል” የሥልጣን ቦታዎች በቀጥታና በተዛዋሪ የተቆጣጠረው ኦነግ/ኦህዲድ መሆኑ እንዳለ ሆኖ ኦሮምያ የሚባለው ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ አዲስ አበባ እንደመሆኑ የፌዴራል ተብዬው መንግሥት በዚህ ክልል መንግሥት ተፅዕኖ ሥር ወድቆ አዲስ አበባ የሁለት መንግሥታት ተዕዛዛት ፈጻሚና አስፈጻሚ ሆናለች፤ ልትፈነዳ የቀራት አንድ እሬቻ ማነው አንድ ሐሙስ ቢሆን ነው፡፡ በምሣሌ ላስረዳ፡፡ አ.አ የሚል የመኪና ታርጋ አለ፡፡ ኢትዮ የሚል የመኪና ታርጋ አለ፡፡ ኦሮ የሚል የመኪና ታርጋ አለ - መኪናና ሌላው ንብረትም በጎሣ መጠራቱን ልብ በሉ በዚህ አጋጣሚ ታዲያ፡፡ ደሕ፣አማ፣ሱማ፣ትግ፣... የሚሉም አሉ፡፡ ልብ አድርጉ! በአዲስ አበባ አ.አ የሚልና ኢትዮ የሚል ታርጋ ነበሩ እንደልባቸው የሚንቀሳቀሱት፡፡ ሌሎች እንደ ደሕ. (ደቡብ ሐዝቦች) ያሉት እንደተላላፊ ወይም እንደ አድሮ ሂያጅ እንግዳ ነበር እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቀድላቸው - ከተሳሳትኩ እታረማለሁ፡፡ አሁን ባለው የመንግሥት አወቃቀር ግን አዲስ አበባ ራሷ በፊንፊኔ የዋቄ ፈታ ስም በጉልበትና በማን አለብኝነት የዘረኝነት ጥልፍልፎሽ የፌዴራልና የኦሮምያ ዋና ከተማ ሆናለችና ኦሮ. የሚል ታርጋ አዲስ አበቤ ሆኗል፡፡ 

አ.አ የሚል ታክሲም ሆነ የቤት መኪና የሚተዳደረው በአዲስ አበባ የክልል መስተዳድር ፖሊስና የመንገድ ባለሥልጣን ሲሆን ኦሮ. የሚል ማንኛውም ተሸከርካሪ የሚተዳደረው ደግሞ በዚችው ከተማ በሠፈረው  የኦሮምያ ክልል ፖሊስና የመንገድ ባለሥልጣን ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች ባመቻቸው ቢሮ እየሄዱ ይስተናገዳሉ - በተለይ ኦሮምኛ የሚችል እልል በቅምጤ እያለ ነው፡፡ ዜጎች የአዲስ አበባው ሲጠብቅባቸው ወደፊንፊኔው ያመራሉ፡፡ የፊንፊኔው ያዝ ሲያደርጋቸው ወደ አዲስ አበባ ይሄዳሉ -  በዓለማችን የመጀመሪያዋ የሁለት መንግሥታት ዋና ከተማ - አዲስ አበባና ፊንፊኔ - አንድም ሁለትም፡፡ ዕርግብም እባብም፡፡ ቫቲካን እንኳን ለራሷ ተከልላ በሊቀ ጳጳሱ ሥር ነው የምትተዳደረው - መሀል ሮም፡፡ የኛ ግን ፊስቱላ ገጥሟታል - መደበላለቅና የለዬላት ባቢሎን መሆን፡፡ 

በምሣሌ ላይ ሌላ ምሣሌ ልስጥና - ለምሣሌ አንድ ቁጥር ታክሲ በአዲስ አበባ ቀርቷል - ፈቃድ አይሰጥም፡፡ በሌላዋ አዲስ አበባ ማለትም በፊንፊኔ ግን አለ፡፡ ስለዚህ 20ሽህ ብርና ከዚያ በላይ ጉቦ እየከፈሉ በዚያኛው መንግሥት ፈቃድ በማውጣት በአንዲት ከተማ የሁለት “ሀገራት” ታክሲዎች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም - ሌላው ነገር ሁሉ ልክ እንደዚህ ነው፤ የጨረባ ተዝካር፡፡ አዲሶቹ ገዢዎች ደግሞ ጉቦ ሲጠይቁ ዐይን የላቸውም አሉ - አምስት ሽህ ብር ለምታገኝበት ጉዳይ ሃምሣ ሽህ ብር ጉቦ ሊጠይቁህ ይችላሉ - ጉቦም እኮ ዕውቀት ይጠይቃል ወንድሜ፡፡ እነሱ ግን ምን ገዷቸው! እከሳለሁ ብትል “ሰባራ ዶሮ ሳቲቃድሚህ ወደፈለካው ሄዴ ኪሰስ፤ ኢልማ ሃጥራው!” ቢሉህ እንዳይደንቅህ - ከየወረዳውና ክፍለ ከተማው የምንሰማው ጉድ ይሄንኑ ነውና በዚህ አልኮነንም፡፡ ወይ ጊዜ መስታወቱ!... (የምን ዝምታ ነው? ትንሽ ፈገግ በሉ እንጂ! እነአባ ጫላና ገመዳም የዲጂታል ኦህዲድ ጦራችሁን ምዘዙና እንደለመደባችሁ የክት ስድቦቻችሁን ዘክዝኩ፤ ወገናዊነት ለመቼ ሊሆናችሁ ትቆጥቡታላችሁ? አይዟችሁ እንጀራችሁ መሆኑን ስለምናምን ከፈገግታ በስተቀር አንከፋባችሁም፡፡ ለምኑ ብለን?)

  በዚህ መንገድ አዲስ አበባ እንደፉክክር ደጃፍ ሳትዘጋ እያደረች ለማንም ቀማኛና ወሮበላ ምቹ እንደሆነች አለች፡፡ እኛም ኤሎሄያችንን ቀጥለናል፡፡ መልስ የምናገኝበት ጊዜም በጣም ቅርብ ነው፡፡ ተስፋህ ሲጨልም ከወዲህ፣ ሌላ ተስፋህ ይፈነጥቃል - ከወዲያ፡፡ አይዞን!