Wednesday, September 23, 2020

አሁንም ጊዜያዊ ሕዝባዊ የሽግግር መንግሥት! መስከረም 13 ቀን 2013 ዓም (19-09-2020) አገሬ አዲስ (Ethiopian Semay)

 

 

አሁንም ጊዜያዊ ሕዝባዊ የሽግግር መንግሥት!

መስከረም 13 ቀን 2013 ዓም (19-09-2020)

አገሬ አዲስ

(Ethiopian Semay)

ለአለፉት 47 ዓመታት በሕዝቡ የቀረበውና ብዙም መስዋእትነት የተከፈለበት ጥያቄ የጊዜያዊ ሕዝባዊ ወይም የሽግግር መንግሥት ምስረታ  ጥያቄ ነው።ይህ የሕዝብ ጥያቄ ሥልጣኑን በጉልበት እየተቀባበሉ በያዙት አምባገነናዊ ስርዓቶች ሲደፈጠጥና መልስ ሳያገኝ እስከአሁን ድረስ እዬንተከባለለ የቆዬ አሁንም መልስ ያላገኘ ጎላ ብሎ የሚነሳ ጥያቄ ነው።የሚገርመው ነገር ጥያቄውን በመጥለፍ ሌሎቹም ህወሃትን የመሳሰሉ አገር አጥፊና የሕዝባዊ መንግሥት ጠላቶች ማንሳታቸው ነው።የነሱና የሕዝቡ ሕዝባዊ መንግሥት ግን በቅርጹም  ሆነ በግብሩ የተለያዩ ናቸው።በሥልጣን ላይ ያለውም ቡድን ይህንኑ ተከትሎ ሲያጭበረብርና ጥያቄውን የህወሃትና የመሰሎቹ አድርጎ ሲያቀርበው ይታያል።


ጥያቄው የህወሃትና መሰሎቹ አለመሆኑ የሚታወቀው  ከቀረበ ሃምሳ ዓመት ወይም ግማሽ ዘመን ሊሞላው መቃረቡ ነው።ከህወሃት በፊት ማለት ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመንግሥት ለውጥ ሲጠይቅ ሌሎች አገሮች ካልነበሩበት ደረጃ ተነስተው አገር ለመሆን በቅተዋል፤ያም ብቻ አይደለም የብዙ ዘመን ታሪክና ስርዓት መስርታ የኖረችው አገራችን የነሱ ተመጽዋች አገር ሆናለች።አንዳንድ የኢምራት አገሮችን አመሰራረትና ታሪክ ብናይ ይህንን እውነታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል።

 

በሌላም በኩል እንዲሁ በኢትዮጵያ ከለላና እርዳታ  ነጻ ለመሆን ከበቃች አስር ዓመት አልሞላት ደቡብ ሱዳን ለኢትዮጵያ ስጋትና ውጋት ለመሆን ዳር ዳር እያለችና እዬተፈታተነችም ነው።የግብጽና የሌሎቹም የኢትዮጵያ ጠላቶች ምሽግ ለመሆን እያቆበቆበች ሲሆን አልፋ ተርፋም የጋምቤላን መሬት ሸርፎ ለመውሰድ ፍላጎቷን  በተዘዋዋሪ መንገድ በመግለጽ ብቻ ሳትወሰን ሃይሏን በመገንባት ላይ ተሰማርታለች።

 

ሌላዋ የቅርብ ጠላት ሆና ለመሰለፍ የምትዳዳው ደግሞ በኢትዮጵያ ውሃና ፍራፍሬ እንዲሁም ምግብ ሕዝቧን የምትቀልበው ጅቡቲ ናት።ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ብሎም ለመላው አፍሪካ አደጋ የሚሆን የጦረኞች ምሽግ በመሆን መሬቷን እዬቸበቸበች ትገኛለች፤ይህችው ደቃቃ   ከአምስት መቶ ሽህ ሕዝብ በላይ የሌላት ወደብ ተደግፋ የቆመች አገር ጥንት የኢትዮጵያ አካል መሆኗ ሲታወቅ በ1974 ዓም በፈረንሳዮች አሻጥር ነጻ ሆና  ባንዲራ እያውለበለበች ግን  ከፈረንሳዮች መዳፍ ነጻ  ያልወጣች አገር ሆና ሳለ የመቶ ሚሊዮን ሕዝብ አገር የሆነችውን ኢትዮጵያን በወደብ ምክንያት በኤኮኖሚም በፖለቲካም ለማንበርከክ ደፍራ ከተነሳች ውሎ አድሯል።የአፋርን መሬትም ለመጠቅለል ያልሞከረችው ተንኮል የለም፤አሁንም እዬሞከረች ነው።የሱማሌና የኬንያም ቀጥተኛና የእጅ አዙር ሙከራ እንዲሁ ኢትዮጵያን አዳክሞና አፈራርሶ ፣ሕዝቧን ጨርሶ መሬቷን እንደቄራ ከብት ለመቀራመት የሚደረግ ፉክክር አካል ነው።ይህንንም በተገንጣይ ቡድኖች በህወሃት፣በኦነግና በመሰሎቻቸው በኩል ለማስፈጸም የተቀናጀ የጥፋት እርምጃ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ።ባዶ ቤት በቁንጫ ይወረራል እንዲሉ ለዚህ ሁሉ የቅርብና የሩቅ ጠላት ዓላማ መነሻና ዕድል የሆነው ያገሩን ዳርድንበር  የሚያስከብር፣ የሕዝቡን ፍላጎትና የሕግ የበላይነትን እንዲሁም የዴሞክራሲ ስርዓትን ሊያሰፍን የሚችል አገር ወዳድ መንግሥት ባለመኖሩ ነው።በስልጣን ላይ ያለው የጎሰኞች ስብስብ  ስምና ስልቱን እዬቀዬረ ለዚህ ብሔራዊ አደጋ መከሰት የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል።አሁንም እያደረገ ነው።

ይህንን ብሔራዊ አደጋ ለመቀልበስ የሚከተሉት እርምጃዎች ወሳኞች ናቸው።

በፖለቲካው መስክ አሁን ያለውን የጎሰኞች ስብስብ መንግሥት በአገር ወዳዶች በሚመሠረት ህዝባዊ ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት መተካት ሲሆን ይህ መንግሥት በሁለት መልክ ሊዋቀር ይችላል።

(ሀ)  በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ፣ለኢትዮጵያ አንድነትና ልዑላዊነት የቆሙ፣ከሃይማኖትና ከጎሳ ፖለቲካ የጸዱ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ተቋማት እንዲሁም የሙያ ድርጅቶች የሚሳተፉበት መንግሥት መመስረት

 

(ለ)  የፖለቲካ ድርጅቶች መሳተፍ በንትርክ የመንግሥቱን ሥራ ያደናቅፋሉ የሚል ስጋት ካለና እንዳይኖርም ከፖለቲካ ድርጅቶች ነጻ የሆነ በአገር ወዳድ ቴክኖክራትስ ማለትም ምሁሮች፣ባለሙያዎችና ሕዝባዊ ዘርፎች ተወካዮች ተሳትፎ የተዋቀረ መንግሥት ማቋቋም

 

የሽግግር ወይም ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥቱ ለሁለት ዓመት የሚቆይ ሲሆን ያለውን ሕገመንግሥት አግዶ ለወቅቱ የሚያገለግል አዋጅ ወይም ሰነድ(ዲክሪ) በማዘጋጀት አገሪቱን ያስተዳድራል።ቋሚ ሕገመንግሥትም እንዲረቅና እንዲጸድቅ ያደርጋል። ለቀጣዩ ቋሚ መንግሥት ምስረታ ለሚረዳው ብሔራዊ ምርጫ ዝግጅት ያደርጋል።የመንግሥት ተቋማት ሥራቸውን በሚገባ እንዲሰሩ ይቆጣጠራል፣አስፈላጊ የሆኑትን ተቋማት ሲያጠናክር የማይጠቅሙትን ደግሞ ያሶግዳል።

 

የሕዝቡን ሰላማዊ እንቅስቃሴና ኑሮ ለመጠበቅ ያለውን የፖሊስ ሃይል በአገር ደረጃ ማዋቀርና አሁን በየክልሉ ተበታትኖ ያለውን በክልል ማንነት መንፈስ የተቋቋመውን  የክልል ሃይል በማፍረስ ለአባላቱ ስልጠና እዬሰጡ በሌሎች ሃገራዊ የልማት ተቋማት ውስጥ በተለይም በፋብሪካዎችና በእርሻ መስኩ  እንዲሳተፉ ማድረግ።በሌላ አጥፊ ተግባር እንዳይሳተፉና ቤተሰቦቻቸውም ለችግር እንዳይጋለጡ ድጋፍ ማድረግ።

 

 የአገራችንን  አንድነትና ዳር ድንበር በማስከበሩ በኩል አሁን ያለው የመከላከያ ተቋም   የሽግግር ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚነሳ ሃይልና የኢትዮጵያን ህልውና አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል ማንኛውንም እንቅስቃሴ ሊያከስም የሚችል ብሔራዊ የመከላከያ ሃይል በሚሆንበት መልኩ ማዋቀርና ችግር ሲነሳ ለመከላከል ብቻ ሳይሆን ቀድሞ በማጥቃት ችግሩ ሊፈለፈል የሚችልበትን እንቁላል ለመስበር አቅምና ዓላማ ያለው፣ከመቀደም መቅደም ” በሚል ወታደራዊ መርሆና ስልት የሚመራ  ጦር  እንዲሆን ማዘጋጀት ያስፈልጋል።የማጥቃት ጦርነቱ  በጠላትነት በተሰለፉት አገሮች ድንበር ውስጥ እንጂ በኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ እንዳይሆን  የአንዳንድ አገሮችን የጦርነት ተመክሮ መቅሰም ይረዳል።

ከጎረቤትም ሆነ ከሩቅ አገር መንግሥታት ጋር የሚኖር የዲፕሎማሲ ግንኙነት ኢትዮጵያን በማይጎዳና ጥቅሟን አሳልፎ በማይሰጥ ያጎብዳጅነት ውሳኔ እንዳይሆን በራስ የመተማመኑን ስሜት መከተልና ማሳደግ ተገቢ ነው።ለፖለቲካ ድጋፍና ለውጭ ምንዛሬ ሲባል የአገር ህልውና ለድርድር አይቀርብም።ያገርም መሬት፣ ቅርስና ንብረት ለሽያጭ ገበያ አይወጣም።

አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ምርጫ ለማካሄድ ቢነሳ ለውጡ ህገወጡን የጎሰኞች ስብስብ ሕጋዊ ከማድረግና  በጎሰኞች መካከል ያለ የቦታ መቀያዬር ከማምጣት የዘለለ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም፤ያው በገሌ ነው። ስለሆነም ያለው አንዱና ብቸኛው አማራጭ የሽግግር ወይም ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግሥት ማቋቋም ነው።

ጊዜያዊ(ሕዝባዊ ) የሽግግር መንግሥት ይቋቋም!!