Wednesday, December 3, 2008

ከእሳት ዘሪዎች እሸት አይጠበቅም

ከእሳት ዘሪዎች እሸት አይጠበቅም ጌታቸዉ ረዳ ስለ ጋህዲ ደራሲ ትንሽ ልበል።የጋህዲ ደራሲ አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ “ጋህዲ” የሚል መጽሐፍ በመጻፋቸዉ ሊመሰገኑ ይገባል። እኔ መጽሐፉን አላነበብኩትም።የምኖርበት ከተማ እና ከባቢዉ ያሉት የኢትዮጵያዉያን ሱቆች እንጀራ እና የሻዕብያ ሙዚቃ የሲዲ መሸጫ እንጂ አገራችንን የሚመለከት መጻሕፍት ወይንም ጋዜጦች ለአመሉም ቢሆን አንዴም እንኳ አስመጥተዉ ሊያስነብቡን አልታደልንም።በዚህ አልታልደንም እና መጽሐፉን ለማንበብ ዕድል አላገኘሁም። መጽሐፉ አንበብኩ ኣላነበብኩ ለኔ አዲስ መሰረታዊ መረጃ የሚሰጠኝ ኣይመስለኝም። ምክንያቱም ወያኔ የሻዕቢያ ሎሌ መኖሩ እና ዛሬም በግልጽ እነ ስብሐት የሚፎክሩበት እና የሚኮሩበት ስለሆነ ፤አዲስ ኣይሆንም። ቢሆንም፤ መጽሐፉን የት ማግኘት እንደሚቻል ወኪሎቹ ለሕዝብ ብያስታዉቁ ለማንበብ ዕዱልን ባገኘን።ጻሓፊዉን ማናናቅ ተደርጎ ባይወሰድብኝ አስገደ ስለ ወያኔ ሻዕብያ ሎሌነት መግለጹ ቢያስመሰግነዉም፤ በወያኔ መሰረታዊ ወታደራዊ እና በስላላ እንዲሁም በወያኔ የጉድጓድ እስርቤቶች(06) በመሳሰሉት ሰብኣዊ ጥሰት ማለትም ድርጅቱ የወሰዳቸዉ የአፈና፤ የማሰቃያ እና የርሸና ወንጀሎች የመሳሰሉት አገር አቀፍ እና አህጉራዊ የክህደት ዉል ምስጢራዊ ሰነዶችን ይፋ የሚያደርግ የህወሓት “ታጋይ-ነበር” “በጥልቀት እና በስፋት” አስካሁን ስጠብቅ ይፋ ያደረገ ሰዉ ስለሌለ በዚህ በጣም ቅር ተሰኝቻለሁ። የምጓጓዉ በዛ ረገድ ነበር ለማለት ነዉ።ቢሆንም አቶ አስገደን የማመሰግነዉ እና ከበሬታ የምሰጠዉ በድፍረት ጅቦቹ በሚኖሩበት ከተማ እየኖረ ጉዳቸዉን ማጋለጡ እጅግ አከብረዋለሁ።ትግል ዉስጥ ነበርን ከሚሉን ምንም ካለስተማሩን አብዛኛዎቹ የህወሓት ታጋዮች የሚያዉቁትን ለማስተማር የጣሩት እኔ የማመስግናቸዉ ሌላዉ ደራሲ “ታጋይ ገሠሠ እንግዳ” የተባሉ “ታሪክ አጉዳፊዉ የ አልባኒያዉ ደብተራ” የሚል መጽሐፍ በመድረስ ወያኔን ያጋለጡ እና ሌላዉ አድናቆቴ ሁሌም የምቸራቸዉ “የታላቁ ሴራ” ደራሲያን እነ አቶ ገብረመድህን አርአያ ፤ካሕሳይ በርሄ፤ ተስፋይ አጽብሃ እና ምንም እንኳ የሗላ ሗላ መጥፎ አወዳደቅ በመዉደቅ ታሪካቸዉን ራሳቸዉ ያጎደፉትም ቢሆን አቶ አብርሃ ያየህንም በዛዉ በክፉ ቀን የወያኔ ጉድ ማጋለጣቸዉን ሳላመሰግናቸዉ አላልፍም። ሌላዉ “ከዚህ ድረስ ያደረሰ መንገድ” የተባለዉ ሰነድ የጻፉትን አቶ ብስራት አማረንም ሳለመሰግን አላልፍም። በተቀረ ከወያኔ ነበር አባላት የተማርነዉ ብዙም ሰነድ የለም። ለምን? ብየ ይህ የዘወትር ጥያቄየን አቅርቤ ልለፍ። የዛሬ አመጣጤ አቶ አስገደ ገ/ስላሴ እና ቃለ መጠይቁ ያዘጋጁት አቶ አበበ በለዉንም ጭምር ለመተቸት ነዉ። ለመተቸት ስነሳ፤ ብዙ የትግራይ ወንድሞቼ እንደልማዳቸዉ በእኔ ላይ ያላቸዉ ዉዥምብራም አመለካከት ሲበራታባቸዉም ዘረኝነታቸዉን በእኔዉ ላይ ከማዝነብ ጋር ትችቴን እንደሚያነብቡት የምጠብቀዉ ነዉ። የወያኔ መሪዎች እና የትግራይ ተወላጆች አትኩሮታቸዉ በአካባቢያቸዉ ብቻ በማድረግ ትግራይን የትምርት፤የጤና፤የመገናኛ፤የእርሻ፤የኩባንያዎች እና ኢንዱስትሪዎች መዋዕለ ንዋይ ከሌላዉ አካባቢ በበለጠ እንዲፈስበት የተቻላቸዉን ሁሉ በማድረግ ለአካባቢአቸዉ ብቻ በመቆርቆር ወገንተንኝነታቸዉ እንዳሳዩ አሌ አይባልም። ለዚህም የትግራይ ሕዝብ ከአስመራ እና ከባሕር ዳር ከደብረብርሃን ...ለወራት እና ዓመታት እየጠበቀ ሲገበያቸዉ የነበሩትን የዕቃዎችና ልዩ ልዩ ምርቶች፤- ካለ ምንም የዓመት አና የወራት፤የሳምንታት እና የቀናት ጉዞ ሳያደርጉ ወይንም ጠብቅ ሳይባል ከደጃፉ በራቸዉ ካለዉ ሱቅ እና ኩባኒያ ላይ ወይንም ከቅርብ መንገዶች ርቀት እና የሰዓታት ጉዞ በማድረግ በቀላሉ በመሸመት ዕደሉ ስላገኘ፤ ከሌሎቹ ይልቅ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል። ይሄ አቶ አስገደ ገ/ብረስላሴም አቶ ገብሩም ባጠቃላይ ሁሉም ልበል እና የትግራይ ሕዝብ ምንም የተደረገለት ነገር የለም። ብለዋል። ቢህ ብዙ ጊዜ ስለሄድንበት ብዙም የምለዉ ስለሌለ፡ ወደ ዋናዉ ትችቴ ልግባ። አስገደን ስተች “ኢሕአፓዉ ጌታቸዉ ረዳ” ኢሕአፓ ስለሆነ አስገደን መተች ጀመረ ፡ በማለት እንደ ዕንቁራሪት አንዴ በሻዕቢያነት አንዴ በኢሕአፓነት ወዘተ.. ሁሌም ከሚከሱኝ ዕንቁራሪቶች የምጠብቀዉ ስለሆነ። ሁሉንም ወገን በፈትሕ ዓይን ስለምመለከት የበደለ በድሏ የካደ ከድቷል መልካም ስራ የሰራዉ መልካም ስራ ሰርቷል በማለት ለዓመታት ግራ ቀኙን ስሰደብ አስካ ሁን መቆቴ ለአገሬ ያለኝን ፍቅር ለምቾት ኑሮ ሳልደለል ታግያለሁ። ተችት አቅርቤ አለሁ። በዚህ ልዩ ኩራት ይሰማኛል። ታሪክ አንድ ቀን ሁላችንን ይመዝነናል። ስለተሰደብኩ ወይንም ዛቻ ስለተወረወረብኝ ከመተቸት አልገታኝም። አሁንም ስለ ፍትሕ ትችቴ ይቀጥላል።
እነሆ፦ ሰሞኑን አቶ አስገደ ገ/ሥላሴ አዲስ ድምጽ ከተባለዉ ራዲዮ ጋር ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር። አስገደ ወደ ህወሓት ሲቀላቀል ከመስራቾቹ አንዱ ነበር። ለትግሉ መነሻ ምክንያት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት እንደነበር ገልጿል። አሁን ግን ነገሩ ተበላሽቶ የአንድ ፓረቲ/ድርጅት የበላይነት መንገሱ “ከመነሻዉ” “ፈር” ለቋል ሲል ህወሐት አምባገነን ፓረቲ መሆኑን ገና ህወሓት የመንግስት ስልጣን ሲይዝ የወያኔ ምንነት የተገለጸለት እና ሜዳ ላይ 17 አመታት የሕዝቡን ልሳን፤ የታጋዮቹን ሕይወትና መብት በብረት ቡጢ በተ-ተበተበ ፋሽታዊ እና ማርክሳዊ የስለላ አወቃቀር ይዞ የተራመደበትን ጎዳና ኢዲሞክረሳያዊ ብቻ ሳይሆን “ፋሺስታዊ” በሕሪ እንደነበረዉ እያወቀ መስመሩ መሳት የጀመረዉ ስልጣን ላይ ሲመጣ ስልጣኑን ለሕዝብ እናስረክብ ስንለዉ “አሻፈረኝ” ስላለ ከድርጅቱ ተሰናብቼ አለሁ ብሏል። የህወሓት አነሳሱ እና አስከ ዚህ ድረስ የተጓዘበት በሕሪዉ ከልቡ እያወቀዉ፡ የወያኔን አምባገነንነት ማወቅ የጀመረዉ በ1983 እንደሆነ አስመስሎ መናገሩ ግራ ገብቶኛል? ሁሌም ግራ የሚገባኝ ነገር፤ አብዛኛዎቼ ወያኔ ዉስጥ የነበሩ ታጋዮች ሊነግሩን የሚንደረደሩት “የወያኔ” አምባገነንነት ወይንም “ካዳተኛ” ባሕሪዉ የጀመረዉ ገና በ1983 መሆኑ እና የትችታቸዉ መነሻ በአብዛኛዉ ከዚህ ከ1983 እንደሆነ ነዉ የምናነባቸዉ። ወይንም ከባድሜ ጦርነት ወዲህ። ለምን? አስገደ በቃለ መጠይቁ እንደሚለን “ወደ የቻይና ዓይነት ፈላጭ ቆራጭነት ባሕሪ እየተጓዘ ነዉ” ሲለን በእዉነቱ አስገደ የወያኔ ድርጅት አሰራር እና ባሕሪ ወደ ማኦዊ ወይንም አልባንያዊ ኮሚኒስታዊ ባሕሪ የተሸጋገረዉ /የጀመረዉ ገና ወደ መንግሥትነት ሲዞር ነዉ? አቶ አስገደ “ራሱ ከጽንሱ ጀምሮ የነበረ ያሳደገዉ የገነባዉ የታገለለት የደማለት ድርጅት ትውዉቁ በ1983 ነዉ? አስገደ ከመሰረተዉ ድርጅት የተለየበት ምክንያት ሲገልጽ “ደርግ በወታደራዊ ጉልበት ደምስሰነዋል፡ ስለዚህ ስልጣኑን ለሕዝቡ እናስረክብ ብለን ሓሳብ ስላቀረብን በዚህ ብዙ ሰዉ እንግልት ስለደረሰበት እኔም ከድርጅቱ ወጥቻለሁ ብሎናል። መልካም አቋም!ነገር ግን “ጉና ካብ ዕርዲ መንጥል! ናብ ዕርዲ መትከል” በሚል ሐምሌ 1989 “ወይን” የትግርኛ የወያኔ ልሳን ጋዜጣ ባወጣዉ የትግል ዓምዱ ላይ “ሳሞራ የኑስ” አንዳስቀቀመጠዉ “ታጋዩ ብቻ ሳይሆን ቁጥሩ አነስተኛ የማይባል በርካታ የትግራይ ሕዝብ ትግላችን ፈጽመናል፤ ይበቃናል ከዚህ ወዲያ አንሄድም፤የተቀረዉ ህዝብ የየራሱን አምባ ነጻ ያዉጣ በማለት የተከራከሩ እና ብረታቸዉን እየጣሉ ወደ ከተማ የተመለሱ እና ወደ 20ሺሕ የሚጠጋ ታጋይ “እምቢኝ” አንሄድም “ትግራይ ነጻ ወጥታለች፤የቤት ስራችን ሰርተናል ከዚህ ወዲያ የተቀረ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ ታግሎ ራሱን ነጻ ያዉጣ በማለት ለወራት የቆየ ክርክር እንደተደረገ እና ያዉም ለአንድ ወር ሙሉ ጉና ላይ በደርግ እየተደበደበ ወደ ፊት መገስገስና መላወስ ካቃተዉ ዋናዉ ምክንያት ታጋዩ ምሽጉን እየጣለ ከዚህ ወዲሕ የትግራይ ቦታ አይደለም በማለት ጥለዉት ወደ’የ ቄያቸዉ በመፍለሳቸዉ እንደ ነበር ሰነዱ እና የሳሞራ የኑስ ቃለ-መጠይቅ ያስረዳል።አቶ አስገደ ይሄንኑ ያቃል። ታዲያ የወያኔ እና የታጋዮቹ ዲሞክረሲ ፍለጋ እና አገር ዋዳድ ኢትዮጵያዊነት ፍለጋዉ ሲመረመር በጥያቄ እናስቀመጠዋለን። የእምቢታዉ ክርክር ሁኔታ ለ6 ወር ያህል እንደተካሄደም አንዳነድ ሰነዶች አንብበናል። የክልልተኝነቱ በሽታ በመሪዎቹ ብቻ ሳይሆን የተንጸባረቀዉ ከታጋዩ እና ቁጥሩ አነስተኛ ከማይባል የትግራይ ሕዝብ ጭምር “ከዚህ ወዲያ አንሄድም” እንዳለ ሳሞራ ያስረዳበትና ብዙ የትግራይ ሕዘብም ሆነ ታጋዩም የተሳሳተ ኢትዮጵያዊ አመለካከት እንደነበረዉ እያወቀ ታጋዩ ጠባብ አልነበረም፤ዲሞክራሲ ፍለጋ የታገለ ነበር፤ በማለት ለሕዝቡ እና ለታጋዮቹ የተሰጠዉ ጎሰኛ እና በትግራይ ጂኦግራፊያዊ ክልል/ማፕ ብቻ እንዲመለከት የተሰጠዉ ጠባብ የትምርት “ጠባሳ” ከፍተኛ ጉዳት አንደነበረዉ እየታወቀ ከአስገደ ገ/ስላሴ ቃለ መጠይቅ አንደበት እተደመጠዉ ግን ታጋዩ ክልልተኛ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ስሜት ኖሮት ስልጣን ለሕዝብ ይተላለፍ ብሎ የደመቀ አቋም አንደነበረዉ ነዉ።ነገሩ ግን አስካሁን ታጋዮቹ በስፋት ሊገልጹልን ያልፈለጉት “መጻጉእ” ግን ተሸፋፍኖ እየታለፈ ነዉ። ለምን? በመሪዎቹ ብቻ ሳይሆን በታጋዩ እና በህዝቡ ላይ የነበረ የተሳሳተ ሀገራዊ አመለካከት በሚመለከት ቢገልጽልን በጣም አመሰግነዉ ነበር። ሕዝቡ እና ታጋዩ በተለይም በ አማራዉ ላይ የነበረዉ አመለካከት እና የተሰጠዉ ቅስቀሳን በሚመለከት የሚናቅ አጀንዳ አልነበረም። ሆኖም ጠያቂዉ ለእንደዚህ ዓይነት ጥያቄ የተዘጋጀ አልነበረም እና አልጠየቀዉም። አስኪ አቶ አበበ በለዉ ከተናገረዉ የቃለ መጠይቁ መግቢያ ልጀምር እና ከዚያ አቶ አስገደ ስለ ኢህአፓ ያለዉን እንመለከታለን። “ሕወሐት ቀደም ብሎ ለ ኢትዮጵያ የነበረዉ አስተሳሰብ አሁን እንዴት እንደተቀየረ ብዙዎች የህወሓት ኣባላት እንዴት ጥለዉት እንደወጡ ተንትኖ የሚያሳይ ታሪካዊ መጽሐፍ በዚህ ዙሪያ ላይ ረዘም ላለ ሰዓት ይዧቸዉ እቆያለሁ…እንድትከታተሉ እጋብዛሉ።” (አበበ በለዉ- አዲስ ድምጽ)። “ህወሓት ቀደም ብሎ ለኢትዮጵያ ከነበረዉ (ቀ ና) አስተሳሰብ (ወጥቶ) አሁን እንዴት እንደተቀየረ” ለመጠየቅ ይህ የአቶ አበበ በለዉ አረፍተነገር እዉን የጋህዲ መጽሐፍ ደራሲ አቶ አስገደ ከመጽሐፉ ዉስጥ በመጽሐፉ የዘገበ አባበል ከሆነ ሊያከራክረን ነዉ። ላብራራ። ወያነ ትግራይ ስለ ኢትዮጰያ በጎ ነገር አስተሳሰቡ ድሮም ሆነ አሁን የለወጠዉ ነገር ደግ ነገር አልነበረዉም። በ አስተሳሰብ የምንለያየዉ ነጥብ እዚህ ላይ ነዉ። በትገራይ ሜዳዎች፤ተራሮች እና አምባዎች ብቸኛ የሚያገሳ አምበሳ ሆኖ ስለ ኢትዮጵያ “ቀና “ አስተሳሰብ የነበራቸዉን የኢትዮጵያ ስም የያዙ እነ ኢሕአፓ እና ኢድሕ የመሳሰሉት ኢትዮጵያዊ ድረጅቶች “ዓባይ ኢትዮጵያ” በማለት ቅጽል ስም በመስጠት ከትግራይ መሬት ጠራርጎ እንዲወጡ የጀመረዉን ኢትዮጵያዊነት የጥላቻዉ አስተሳሰብ ከዚህ የጀመረ መሆኑን አንድ በሉ። አነሱን በማባረር እና ቅጽል ስም በመስጠት ኢትዮ ያዊነቱን መፋቅ የጀመረዉን ያስተሳሰብ በሽታዉ፦ “ትግራይ የ ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነች” ስለዚህም “ከሽዋዉያን አምሓሩ” ነጻ በማዉጣት “የትግራይ ሪፑብሊክን” አንመሰርታለን፡ በማለት ማኒፌስቶ አስጽፎ፤ ጭራሽኑ አስተሳሰቡ ጸረ -ዲሞክራሲ ብቻ ሳይሆን ጸረ-ኢትዮጵያዊነቱ አስተሳሰቡ ይፋ አደረገበት ምዕራፍ “ሁለት በሉልኝ!”። ማኒፌስቶዉን ጽፈዉታል የተባሉት ከ5 ቱ 3ቱ በስልጣን ላይ ሆነዉ ኢትዮጵያን እየገዙ ናቸዉ። “ስልጣኑን የሚቀማን ሃይል ከመጣ- “ወደ እየ መንደራችን እንበታተናለን”” በማለት ስብሓት ነጋ ያስጠነቀቀንን ልብ በሉ። ይህ አስተሳሰብ አዲስ አበባ የተፈጠረ አስተሳሰብ (የተለወጠ አስተሳስብ) ሳይሆን አስተሳሰቡ ደደቢት ሜዳ ትግራይ ዉስጥ እንደነበረ ሁላችንም ማመን ይኖርብናል። “ወያኔ ለኢትዮጵያ የነበረዉ አስተሳሰብ” የተለወጠ ነገር ወይም አዲስ ነገር እንደሌለዉ አጠር አድርጌ አቶ አስገደን እና ሌሎቹን ላስታዉሳቸዉ እፈልጋለሁ። የትግራይ ሕዝብ እና ነገስታት መኳንንት እና ቀሳዉስት አርበኞች እና የትግራይ ገበሬዎች የሞቱላትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓለማ የባሕሉ የመንፈሳዊ ቅርሱ፤ መመክያዉ ተስፋዉ እና የማንነቱ መታወቂያዉ የነበረችዉን ብሔራዊ ባንዴራችን በማዉረድ ሻዕቢያ ሰፍቶ የሰጠዉን ባለ ሁለት ቀለም ቀይ ቢጫ የኮሚኒስት ሞዳ ጨርቅ ባንዴራ አስሰፍቶ በእየ ስብሰባዉ እና በጠመንጃዉ አፈሙዝ ሸምበቆዉ፤ በሙዚቃ መሳሪያዎች እና በከበሮ ሽፋን በየሰርጉ በቀብር ስነ ስርዓት እና በህዝባዊ ባዓላት የራሱን ድርጅቱን ባንዴራ ወደ ብሄራዊ ሰንደቅ ዓለማነት በማሳደግ፤ “ሰገናት” በማለት የሚጠራቹ ታዳጊ ወጣቶች ህጻናትን አንገታቸዉ ላይ መሃረሙን አስረዉ “የክብር መዝሙር በመዘመር” በማዉረድ እና በመስቀል እንዲተዋወቁዋት አደርጎ “ያገሪቱን ሰነደቅ ዓላማ ጭራሽኑ እንዳያዉቋት በማድረግ ሰንደቅ ዓላማችን ባካባቢዉ ለ17 ዓመት ተሰዉራ እንደነበር ይታወቃል። ካላመናችሁኝ (የትግል ሜዳ ሰነዶች እና ስበሰባዎች ጭፈራዎች የሚየሳዩ ፊልሞችን ተመልክቱ)። ሌለ ቀርቶ “ክብሪት” ተብለዉ በከተማዎች ዙርያ በሚገኙ ገጠሮች እና በዋና አዉራ ጎዳናዎች አካባቢ የተመደቡ የተሓሕት “ፈዳይን” ተብለዉ የሚጠሩ ለነብሰ ግዳያ እና ተፈላጊዎች/ተቃዋሚዎች ከከተማ እያፈኑ የሚያወጡ ቡድኖችን “እከተማ ዉስጥ ድረስ በመግባት በአውረጃ እና በወረዳ መዘጋጃ ቤት መንግሥት ጸ/ቤቶች፤ በትምርት ቤቶች ሰርገዉ ተሸሽገዉ በመግባት እና በማስፈራራት በክብር የተሰቀሉትን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓለማዎች የፋሸስት እና የጠላት የቅን ገዢ ባንዴራ አድረገዉ በመቁጠር ሰንደቅ ዓላማይቱን በማዉረድ “የህወሓት” ባንዴራን ሰቅለዉ ይሄዱ እንደ ነበር ይታወቃል።በህዝቡ እና በሰንደቅ ዓላማዉ ላይ የነበራቸዉ ንቀት እና ኢትዮጵያዊ “አስተሳሰብ” ሃቁ ይሄ ነበር። በቃለ መጠይቁ ያዳመጥነዉ “ህወሓት ቀደም ብሎ ለኢትዮጵያ የነበረዉ በጎ አስተሳሰብ ስለተቀየረ” አቶ አስገደም ሆነ ሌሎቹ ድርጅቱን እየጣሉት እንደሄዱ፡ ሲገልጽ ‘ህወሓት መቸ ነበር ለኢትዮጵያ በጎ አስተሳሰብ የነበረዉ? ከማለት አልፈን ‘የነበረዉ አስተሳሰብ እየተለወጠ ሄደ” የሚሉንን አስተሳሰብ “መጥፎዉን ለመተዉ እየቃጣዉ ስለሄደ ያንኑ መጥፎዉን እንዲቀጥልበት ነበር ፍላጎታችን ማለታቸዉ አንዳልሆነ ተስፋ አደርጋለሁ። ለመቀበልም ስለሚያዳግት። ወያነ ጥሩ አስተሳሰብ ኖሮት የተለወጠበት መንገድ እና ጊዜ አባካችሁ በማስረጃ እየተደገፈ ይቅረብልን። አሁን ወደ ኢሕአፓ እንግባ። አቶ አስገደ በቃለ መጠይቁ ዉስጥ በጣም ከገረሙኝ አበባሎቹ አነሆ።-“ኢሕአፓ የብሄረሰብ መብት አያስፈልግም ብሏል”_ ሲል- ኢሕአፓን ካለ ስሙ ስም ሰጥቶት ሲቀባዉ አድምጣችሁት ይሆናል። ኢህአፓ ስለ ብሔር ብሔረሰብ መብት በፕሮገራሙም የሚነበበዉ አስገደ ገ/ስላሴ ከሚለዉ እጅግ ተጻራሪ ነዉ። ያዉም እኮ አስከ መገንጠል ድረስ አክብሯል ተብሎ የሚወቀስ ድርጅት! ይህ በዉሸት እና በጥላቻ የተመሰረተ ዉንጀላ የሚያሳየን ነገር ቢኖር ሰዎቹ ከወያኔ ድርጅት በ አካል ቢወጡም በህሊናዊ አስተሳሰብ ድሮ ህወሓት ያስተማራቻቸዉን ጸረ ኢሕአፓ ትምርት ዛሬም በያንዳንዱ ወያነ “ነበር” አባሎች አለ። መከራከሪያቸዉ “ዉሃ የማይቋጥር” ነዉ። አስገደ ኢሕፓን በዛ ብቻ ሳይሆን የከሰሰዉ “በትምክህተኝነትም” ጭምር ነዉ። አስገደ ወያኔን ሲተች “በጠባብነት” ሲከስስ አድምጬዋለሁ። የራሱን ቡድን መዉቀሱ ትክክለኛ ሲሆን ኢህአፓን “በትምክህት” መክሰሱ ግን መለስ ዜናዊ ስብሓት ወይንም የመሳሰሉት የህወሓት የፓለቲካ “ሀሁ” ጽፈዉ ስለ ኢሕአፓ ጥላቻ ሲያስተምሩዋቸዉ የተጠናወታቸዉ ዉዥምብራም ትምሕርት ዛሬም እየደገመዉ መስማቴ ይገርማል። ኢሕአፓን የመሰረቱት እና በግምባር የመሩት ያዉ የ እኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች ናቸዉ። እንዴት ሲኮን? በምን ታምር ኢሕአፓ ትምክሕተኛ ሊሆን ይችላል? እንዴትስ የትግራይ ሕዝብ መብት አይከበር ብሏል (የብሔር ብሔረሰብ መብት አያስፈልግም ብሏል) ተብለዉ በእነ አስገደ ባልሆነ ዉንጀላ አገር ቤት በሚደመጥ ራዲዮን ይከሰሳል? ኢሕአፓ የትግራይ ገበሬዎች በ “ክልተ አዉላዕሎ” የሚገኙ ገበሬዎች እና አካባቢዉ አደራጅተዉ ስለ እርሻ አሰራር እና ጥናት ማህበራዊ ኑሮ እና አደረጃጀት ለማስተማር ሲጥሩ የወያኔዎቹ እነ ብረሃነ ገ/ክርስቶስ ሄደዉ ከትግራይ ዉጭ እንጂ የትግራይን ሕዝብ ለህወሓት መተዉ እንዳለበት ነግረዉ በጠመንጃ ሃይል እንዲፈረስ አላደረጉም ወይ? ታድያ ትምክህተኝነት የተሸከመዉ ማን ነዉ? ተስፋይ ደበሳይም ሆኑ ሌሎቹ ብዙ የትግራይ ተወላጆች መሪዎች እና አባሎቹ እንዴት ጸረ ትግራይ እና የትምክሕት ሃይል ሊሆኑ ይችላሉ? የራዲዮኑ አዘጋጅ መልሶ አስገደን መልሶ አምጥቶ በዚህ ጉዳይ እንዲአብራራ መጠየቅ አለበት። ተስፋይ ደበሳይ እና ሌሎቹ የሚመሩት ድርጀት (ያዉም ህይወታቸዉ ከፎቅ ወርዉረዉ ለሞት የሰጡ ሰዎች) እንዴት የአካቢያቸዉ ንጉሶች ለመሆን ፈልገዉ ነበር ብሎ አስገደ በማይሆን ዉዥምብር ዉስጥ ራሱን ከትቶ ይከሳቸዋል? ነዉር አይደለም ወይ!? ወያኔዎች እና ወያኔ ነበር “አጓጉሎች” በዚህ አስገደን በመተቸቴ “ጌታቸዉ ኢሕአፓ ነዉ ለዚህ ነዉ የሚተቸዉ” በማለት እኔን በመዉቀስ ‘ራሳቸዉን እንደሚያታልሉ አርግጠኛ ነን.. ሓቁ ግን አንድ ተቺ የማይሆን ነገር ሲሰማ የመተቸት መብቱ ስለ ፈትሕ እና እዉነትነቱ መተቸት ተገቢ ነዉ። በዚህ ተቀበሉኝ። አይሆንም ኢሕአፓ ነህ ካለችሁኝ “እሰየዉ ፤ከእዛ በፊት ግን ኢህአፓ የብሔር መብት መከበር አያስፈልግም ብሏል የምትሉትን ማስረጃችሁ አምጡ እና አሳምኑን። በመጨረሻ የአበበ በለዉን አስገራሚ እሮሮ አድምጣችሁታል? ለምን የትግራይ ሰዎች ወይም የኦሮሞ… ሰዎች በስብሰባ በሰላማዊ ሰልፍ አይወጡም ፤አይታዩም? የሚሉ ሰዎች ተገቢ አይደለም እና ስሞታቸዉን ማቆም አለባቸዉ። አርስዎ ምን ይመስለዎታል? ሲል አስገደን ይጠይቃል። ብርቱኳን ስትለዉ የነበረዉን አበበ በጠበቃነት ደግፏት ሲከራከርላት ነበረዉን “ለምን የትግራይ ሰዎች በስብሰባየ አላየሁም?” ያለችዉን እና ስንት ንትርክ ያስከተለዉን አባባሉንና አባባሏን ረስቶት መከረኛ “ተቃዋሚን” ትግራይ፤ የኦሮሞ…ለምን ወደ ስበሰባ እና ሰላማዊ ሰልፍ ለ17 ዓመት ሙሉ አልመጡም? ለምን ከኛዉ ጋር አይመክሩም ወይንም አልተሰበሰቡም? እያላችሁ ሰዉን አትለያዩ ይለናል። “የፈረደብን!” አቶ አበበ ረሳዉ እንጂ፤ ስሞታዉ እና ጥያቄዉ ሕጋዊ ተገቢ እና በምክንያት ተደገፈ አንጂ የተወሰኑ ቋንቋ ተናጋሪ ወገኖችን ለማስቀየም ወይንም አታካራ አምሮን ለመለያየት ተብሎ የተባለ አልነበረም። ስሞታችን ሕጋዊ እና ምክንያታዊ ነዉ። ለምን እንዲህ ትላላችሁ ብሎ እኛን አቶ አበበ በለዉ ተመልሶ እኛኑን ለመክሰስ ከቃጣዉ ዉጭ አገር ከመጣ በቅርብ ጊዜ ከሆነዉ ታሪክ ማጥናቱ የሱ አንጂ የኛ ፈንታ አይሆንም። ምስኪኖቹ ከ ወዳጅም ከጠላትም እየተወነጀልን እየተነተርን ነዉና እባካችሁ ዛሬስ አረፍ እንበልበት። ከእሳት ዘሪዎች እሸት አንጠብቅምና ይብቃን። //-//www.ethiopiansemay.blogspot.com