Saturday, March 10, 2018

አገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል- ወልደማርያም ዘገዬ (Ethiopian Semay)



አገር ሲያረጅ ጃርት ያፈራል
ወልደማርያም ዘገዬ (Ethiopian Semay)

እንዳጀማመራቸው የማያልቁ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ የአንዳንዶቹ አስተላለቅ ግን ከሌሎቹ በበለጠ የሚያስጠላና መፈጠርን እስከሚያስረግሙ ድረስ የሚዘገንን ነው፡፡ ለዚህም ነው ባላገር በርዕሴ የገለጽኩትን ተረትና ምሣሌ የቀመረውና የነገሮች ግምኛ አስተላለቅ ሲገጥመው የሚጠቀምበት፡፡

 በጀመርነው የነገር ዐውድ ዙሪያ ሊጠቀሱ ከሚችሉ መጥፎ አስተላለቆች አንዱና ዋናው የኢትዮጵያ እንደሀገርና የኢትዮጵያውያን እንደሕዝብ መቀጠልን ክፉኛ እየተፈታተነ ያለው የሀገራችን የመጨረሻ ዕጣ ፋንታ ነው - እንዳሁኑና እንደእስካሁኑ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ከሆነ፡፡ ሲያስቡት ራሱ ሁለመናን በቁጭት ቋያ ያነዳል፡፡ ከቅርብ አሠርት ዓመታት ወዲህ እውነተኛው ሽል እየተቀበረ እንግዴ ልጅ የሚያድግበት ሁኔታ የተፈጠረ ይመስላል፡፡ አእምሮ እየጨነገፈ ሆድ የነገሠበት ማኅበረሰብኣዊ ድባብ ሲከሰትና እንደባህል ሲወሰድ ማየት ከማስገረም አልፎ የማኅበረሰብ አባልነትን በገዛ ፈቃድ እስከማሠረዝ ይደርሳል፡፡ ያለንበት ዘመን አሣፋሪነቱ ወደር አይገኝለትም - በተለይ በኢትዮጵያ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የምታስቡ ወገኖች ካላችሁ ጤነኛ ሰው እስኪፈጠር ባላችሁበት ጥቂት ቆዩ፡፡ ትልቅ ሰው የለም፤ ከሞላ ጎደል ሁላችንም ተበለሻሽተናል፡፡ ወያኔ አቅልሎናል፤ ሆዳችን አቅልሎናል፤ በገንዘብ ፍቅር ናላችን ዞሮ የምናደርገውን የማናውቅ ሞልተናል፤ ሚስት በባሉዋ፣ ባልም በሚስቱ፣ ወንድም በወንድሙ እህትም በእህቷ ይጨካከናሉ - ለገንዘብ ሲሉ፡፡ ሃይማኖት ጠፍቷል፡፡ ባህልና ወግ ልማድ ተጥሷል፡፡ ባዶው የወያኔ የትምህርት ሥርዓት ከሚዛን በታች ዘርሮናል፤ በየዐውደ ምሕረቱ የሚጮኸው ባዶ ስብከት ከደመና ቀርቶ ከዛፍና ከቤት ጣርያ በላይም ሊጓዝ አልቻለም፤  ጠባያችን ከውኃም ቀጥኗል፤ ባሕርያችን ክፉኛ ተወለጋግዷል፡፡ መቻቻል ብሎ ነገር የለም፡፡ በትንሹም በትልቁም ቱግ ነው፡፡ እንደ እንስሳት ወደታች ወርደን በቋንቋና በዘር መስመሮች ተቧድነን እንጠቃቀማለን ወይም እንጎዳዳለን፡፡ ያ ትልቅ ኢትዮጵያዊ ማንነት ዛሬ ተዋርዶ አይሆኑ ሆኖ ማየት ኅሊናን ያቆስላል፤ ዙሪያ ገባውን የሚታየው ነገር ሁሉ እጅግ ያማል፡፡ ከአእምሮ በላይም ነው፡፡  በ “ምነው ባልተፈጠርኩ” ራስህን ስትራገምና ፈጣሪህን ስትወቅስ ትውላለህ፤ ታድራለህም፡፡ እንቅልፍ ደግሞ የለም፤ አለም ከተባለ የውሸትና የቅዠት ነው፡፡ በ”ህልም እልም” የምኞት ጸሎት የማይጠፋ ቅዠት!

ሀገራችንን ወደዚህ የዘቀጠ ደረጃ ያንደረደሩዋትን በስም ሦስት በግብር ግን አንድ የሆኑ ነገሮች በአጭሩ ልጥቀስ፡፡

1.   ማይምነት ወይም ድንቁርና - መንፈሣዊም ሥጋዊም ትምህርቶች ተዛንፈዋል ወይም ጥራታቸው ተጓድሏል ብቻ ሣይሆን ከናካቴው እየጠፉ ለመሆናቸው ከየተቋማቱ የሚመረቁ ባለዲግሪዎችንና መለኮታዊ የማሰርና የመፍታት ሥልጣን ይዘው ወደየአብያተ ክርስቲያን የሚሠማሩ ካህናትና ጳጳሣትን መታዘብ ብቻ በቂ ነው፡፡ ቤተ ክህነቱ ከግርጌ እስከራስጌ በማይማን የተሞላ ነው - በአብዛኛውና በኃላፊነት ደረጃ ከሰሜን በመጡ ደናቁርት የወያኔ ካድሬዎች፡፡ ማይምነት ደግሞ ድፍረትንና ዋልጌነትን “ያጎናጽፋል”፡፡ አለማወቅን የመሰለ፣ ደደብነትን ያህል እንደልብ አስደራጊ የለም፡፡ የተወሰነ ትምህርታዊ ዕውቀት ቢኖርም እንኳን ድንቁርናው ጎልቶ የሚታይበት ሰው የሚያደርገውን አያውቅምና ጉዳቱ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ክርስቶስን እያዳፉ ለስቅላት ያበቁት ሰዎች እኮ እንደነ አቶ “ፓትርያርክ” ማትያስ ተማሩ የተባሉ ነበሩ፡፡ ለመማር ለመማርማ ሰይጣንም እኮ ብዙ ዕውቀትና ትምህርት ነበረው፤ አለውም፡፡ ነገር ግን የሚጠቀምበት ልክ እንደደቀ መዝሙሩ እንደመለስ ዜናዊ ሁሉ ለጥፋትና ለተንኮል ብቻ  ነው፡፡
 
በወሮበላው የወያኔ መንግሥት ውስጥ በኃላፊነትም ሆነ በተራ ሠራተኝነት የሚሰገሰጉ ዜጎች ዐይናቸውን በጨው ያጠቡ ፍጹም ማይማን ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ አብዛኞቹ በተጭበረበረ ዲግሪ (ከዲፕሎማ እስከ ፒኤችዲ) ሥራ የያዙ ናቸው፡፡ ከነዚህም ብዙዎቹ በዘረኝነት መለኪያ ተመዝነው አንድም የትምህርት ማስረጃ ሳያስፈልጋቸው ወይም እንደነገሩ ለፋይል ብቻ የሆነ ነገር ተቀምጦላቸው ሀገርን የሚያበክቱ ሕዝብን በሰላ የኢ-ፍትህና የሙስና ቢላዎ የሚሸረክቱ ናቸው፡፡ 

  በቅርብ ጊዜ ከታወጀው የገቢ ግብር ግመታ ጥቂት ምሣሌዎችን እንመልከት፡፡ የገቢ ግብር (income tax) በመሠረቱ ሀገር ላለውና ጥሩ አስተዳደርን ለታደለ ሕዝብ ጠቃሚ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ነገር ግን ግምቱም ሆነ አጠቃላይ አሠራሩ ፍትሃዊና በባለሙያ የተጠና መሆን አለበት እንጂ አንዱን የማኅበረሰብ አባል ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ ሌላውንና የራሴ ነው ብለው በሸውራራ የፍርድ ሚዛን የሚያዳሉለትን ማኅበረሰብ ደግሞ ለመጥቀም ታስቦና ታቅዶ መሆን የለበትም፡፡ ከዚህ አኳያ ባለፈው የተጣለው ግብር ከፍጹማን ደናቁርት ብቻ የሚጠበቅ እንጂ ከጤናማ አሠራር የሚጠበቅ አልነበረም፡፡ በአንዲት አሥር ሺህ እንኳን አባወራ በሌላት አነስኛ ከተማ እንዲህ ሆነ፡፡ አንዲት ሴት ጥሩ ጠጅ ትጥላለች፡፡ ስሟ ገናና ነው፡፡ ለፍታ ደክማ በምታገኘው ገንዘብ መጠነኛ ዕድገት ማሳየቷ የሚጠበቅ ነው፡፡ ሰው ከሠራ ያልፍለታል፤ እንዲያልፍለትም ነውና የሚለፋ የሚደክም፡፡ የዚያ አካባቢ ውርጋጥ የወያኔ ባለሥልጣናት ግን በድንቁርናና በምቀኝነት አባዜ የታወሩ በመሆናቸው አንድም ጥናት ሳያካሂዱ በዚህች ትንሽ ጠጅ ቤት ላይ በዓመት የ200 ሺህ ብር ግብር ጣሉባት፡፡ ወደ ወር ለውጡት - 16415. 86867305062 ብር፡፡ ወደ ቀንም ለውጡት - 547.1956224350205 ብር፡፡ ይህች ጠጅ ጣይ ሴት ይህን ገንዘብ ከየት አምጥታ ልትከፍል እንደምትችል እነዚህ የወያኔ ጭፍሮች አላወቁትም - ማይምነቱና ምቀኝነቱ ሸብቦ ስለያዛቸው ሁለመናቸው ታውሯልና፡፡ በመሠረቱ ሥሪታቸው ከጥቅጥቁ የወያኔ ዲያብሎሣዊ ዋሻ እንደመሆኑ የዕኩይ ተግባራቸውን የዞረ ድምር ሊያውቁም አይጠበቅባቸውም፡፡ የነሱ ሥራ ሕዝብን ማማረርና ከንግድም ከኑሮም ከትዳርም ከሀገርም እያፈናቀሉ ቢቻል ራሳቸውን እንዲያጠፉ ማድረግ ያ ካልሆነም እንዲያብዱና ከሀገር እንዲሰደዱ ወደ ዐረቡም ዓለም እየሄዱ በፎቅ እንዲወረወሩ ዜጎችን “ማበረታታት” ነው፡፡ ያች ምሥኪን ሴት ያልገባችበት ቢሮ የለም፡፡ የምትሄድባቸው ቢሮዎች የሥራ ኃላፊዎች “ብትከፍይ ምናለበት! ብዙ ታገኚ የለም እንዴ?” እያሉ በቁስሏ ላይ ጨው ከመነስነስ ባለፈ የፈየዱላት ነገር የለም፡፡ ምክንያቱም ወያኔ ጋር የተሠለፈ ኃይል አንዴውኑ በሰይጣን ቆርቧልና ከሆዱ በስተቀር ሌላ ዘመድም ሆነ ወገን የለውም፡፡ ለማንም የሚራራ አንጀትም የለውም፡፡ ገንዘብ ሲያይ ግን መላ ሰውነቱ ይፈካል፤ ዐይኑ ለማየት የሚከፈተው፣ እጁ ለመጻፍ የሚፍታታው ረብጣ ብር ሲቀበል ነው፡፡ መብት በገንዘብ ይገዛል፤ ዜግነት በገንዘብ ይሸቀጣል፡፡ ትሞት ትንፈራፈራለህ እንጂ በእግርህ ሄደህ የምታስፈጽመው ጉዳይ የትም የለም፡፡

የሚገርመው ነገር ደግሞ ገማቾቹ ሊገመቱ ወደዚያች ጠጅ ቤት የሄዱት በገበያ ቀን ነው፡፡ በሣምንት አንድ ቀን የገጠሩም የከተማውም ሰው አንድ ብርሌ በስድስት ብር በሚሸጥ አነስተኛ ጠጅ ቤት ውር ውር ስላለ ያ ቤት በሚሊዮን የሚገመት ገቢ እንዳለው ተቆጥሮ ያን ያህል ግብር መጣሉ የኃላፊዎቹን የአስተሳሰብ ድህነትና የድንቁርና ደረጃ በግልጽ ያሳያል፡፡ እነዚያ ማይማን ልጆች በስማ በለው ያን የመሰለ ለመጻፍ እንኳን የሚከብዳቸውን የገንዘብ መጠን ከመጣል በፊት ቢያንስ ለሦስት ወራት በየቀኑ በዚያች ጠጅ ቤት እየተቀመጡ ገቢንና ወጪን ቢያጠኑ ትክክለኛው ግምት ላይ ይደርሱና ቤትንም ከመፍረስ ያድኑ ነበር - ይህን መሰል አሠራር በመከተል ግምት ቢጥሉ ኖሮ ማንም ዜጋ አይንገላታም ነበር፡፡ የዚህ ዓይነት ዘመናዊና አስተዋይነት ያለው አሠራር ደግሞ ለወያኔ እርሙ ነው፡፡ በሌላ በኩል ግን የዘረኛው ወያኔ የነገድ አባላት - ኅሊናቸውን በዘረኝነት ለውጠው ልክ እንደቃየልና እንደኤሣው የወንድሞቻቸው ጠላት የሆኑ እፉኝቶችን ማለቴ ነው-  የቀን ገቢያቸው ሚሊዮንም ቢሆን በነሱ ላይ የግምት ግብር የሚጥል አንድም ደፋር የለም - ጫናው የሚበረታውና ከእንቅስቃሴ ውጪ እንዲሆን የሚፈለገው በተለይም አማራው ነው፤ በገዛ ሀገሩ እንደመፃተኛ የሚቆጠረው አማራ በየፈርጁ የሚያየው አበሳ ተነግሮ አያልቅም - ይህ የሚሆነው ደግሞ ወያኔ አሰልጥኖ ጃዝ በሚላቸው የራሱ ደናቁርት ልጆችም ጭምር ነው፡፡ የወያኔው ምርጥ ዜጎች ለስሙ ጥቃቅን ሳንቲሞችን በግብርና በቤት ኪራይ ስም ይከፍሉ እንደሆነ እንጂ እነሱ ከዚህ ዓይነት ከባድ ሸክም ውጪ ናቸው፡፡ ለማንኛውም ያቺ ሴት ሥራውን ትታ ቦዘኔ ሆናለች፡፡ የወያኔ ቡችሎች ተልእኮም ይሄው ነው፡፡ ነገ ግን ይከፍሏታል፡፡ እኛም መዝግበን ይዘናቸዋል፡፡ የፍርድ ቀን ሲመጣ የት ሄደው እንደሚኖሩ እነሱው ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ ያስለቀሰ ማልቀሱን የሚረዱበት ቀን እየመጣ ነው፡፡ ያላስቀመጥከውን ከባንክ አታወጣም፤ ካስቀመጥክ ደግሞ አንተ ባትችል ዘር ማንዘርህ ከነወለዱ አውጥቶ “እየመነዘረ ይጠቀምበታል”፡፡ የነበረና ያለን ተፈጥሯዊ ህግ ለማስታወስ መሞከር ብልኅን እንደማስጠንቀቅ እንጂ ጀብደኛን እንደማስፈራራት ሊቆጠር አይገባም፡፡ የእግዚአብሔር ፍርድ ከሰማይ ሲወርድ ማቄን ጨርቄን ማለት የለም፡፡ መዘጋጀትና መስተካከል ጊዜ ሳለን አሁንና አሁን ብቻ ነው፡፡

2..   ስና - በአሁኑ ወቅት ሙስና የእስትንፋስ ያህል ነው፡፡ የማይሞስን ለማግኘት ምናልባት ወደ መቃብር ሥፍራዎች መሄድ ወይንም ወደ ጋንዲና መሰል ማዋለጃዎች ጎራ ማለት ሳይኖርብን አይቀርም፡፡ የሞቱና አዲስ የሚወለዱ ሕጻናትን ብቻ ነው “ከሙስና የፀዱ ናቸው” ማለት የምንችለው፡፡ ሌላው በክቷል፡፡ ደሞዙ 1500 የማይሞላ ፖሊስ የ2000 ቤት ተከራይቶ ሲኖር የምታየው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ባይገርምህ ደሞዙም አይረባም፤ ሰውም አይረባም፤ መንግሥትም የለም፤ ተያይዘን ልናልቅ ነው፡፡ ገድለህ እንዳልገደልክ፣ ሰርቅህ እንዳልሰረቅህ፣ ሕዝብን በጀሶ እንጀራና በሸክላ በርበሬ እየጨረስክ ምንም ነውር እንዳላደረግህ በበሰበሰ ርጋጭ የቤት ሥሪት ዘይትና በሞራ ቅቤ ሕዝብን እየረፈረፍክ ብትያዝ ገንዘብ እስካለህና ለየቢሮው ኃላፊ እስከረጨህ ድረስ ምንም ወንጀል እንዳልፈጸምክ የምትቆጠርባት ሀገር ኢትዮጵያ ብቻ ናት፡፡ ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ብልሹ ድርጊት የፈጸመ - ለምሣሌ የሁለት ዓመት ሕጻን የደፈረና በላዩ ላይ ያችኑ ሕጻን በጩቤ የገደለ ሰው አለ እንበልና - ያን መሳይ “ሰው” በጉቦ ፍርድ ቤት ነፃ ሲያወጣው ስታይ የኢትዮጵያ ማኅጸን እንዴቱን ያህል እንደመከነ ትረዳለህ፡፡ ገንዘብ አፍ አውጥቶ እየተናገረ ነው፤ እግርም አውጥቶ እንደልቡ እየተንጎራደደ ነው - አላንዳች ሀፍረት፡፡ “ካለህ አለህ፤ ከሌለህ የለህም” ማለት አሁን ነው፡፡ በየሥርቻው የሚከናወነው ከሃይማኖትና ከባህል የወጣ ሰይጣናዊ ሥራማ አታንሳው፤ ፈጣሪ ፊትና ጀርባውን አይደለም ቤተ መንግሥቱንም ቢያዞርብን ሊፈረድበት አይገባም፡፡ በቆሻሻ ቱቦ ከሚያልፍ ውኃ ማን ይጠጣል? በገማ ቤት ውስጥ ገብቶ ማን በሰላም ተኝቶ ያድራል? እኛን ታዲያ እግዜሩ እንዴት ይቅርበን? ፍርድ ለራስም ነው፡፡ “ቤታቸውን ክፍት ትተው ሰው ሌባ ይላሉ” ይባላልና እኛም እንስተካከል፡፡
 
         በሀገር ውስጥ የሚሠራውን የሙስና ወንጀልና የህግ አካላት ተብዬዎች ለወንጀለኞች የሚያደርጉትን “ቀና ትብብር” ስታይና ስትሰማ ኢትዮጵያዊነትህን ትጠየፋለህ፡፡ መድረሻም ታጣና መፈጠርህን ትራገማለህ፡፡ በግምቱ ረገድ የሚሰማው ጉድማ ለጆሮ የሚቀፍ ነው፡፡ በቀን 100 ብር የማያገኙ አነስተኛ የመንደር ውስጥ ጋራጆች ወይ ግሮሠሪዎች በዓመት 200 እና 300 ሺህ ብር ግብር እንዲከፍሉ ሲገደዱ ታያለህ - የዚህ ጭፍን ብያኔ ለከት የለሽነት ጎልቶ የሚወጣው ደግሞ አቤቱታ የምታቀርበው ግምቱን ከፍለህ መሆኑን ስትገነዘብ ነው፡፡ በቀን 200 ብር የማያገኝ ፀጉር ቆራጭ በዓመት 50 ሺህ ብር ግብር ይጣልበታል፡፡ ስንቱ ንግዱን ዘጋ? ስንቱ ራሱን አጠፋ? ስንቱ ከሀገር ተሰደደ? ስንቱ አበደ? ስንቱ ራሱንና ቤተሰቡን ለበረንዳ ሕይወት ዳረገ? እነሱና የነሱዎቹ ግን እየሳቁ የድሎት ኑሮ ይኖራሉ -  እነዚህ ራሳቸው ቀለው ሰውን የሚያቀሉ ወያኔዎች የማይነጋ መስሏቸው ቋታቸውን ባልተለመደና ባልተጠበቀ ሁኔታ አጨመላለቁት፡፡ ይብላኝ ለነሱ፤ እኛስ ለምደነዋል፡፡ ከሞትም እንነሳለን ብለን እናምናለን ፡፡ ወያኔዎች በዚህች ግብር ሰበብ ምድረ ሀበሻን አገኙዋት! ሠሩላትም፡፡ በነዚህ ደንቆሮ የወያኔ ሠራተኞች እየተፈጸመ ያለው ግፍና በደል በራሱ በጽርሃ አርያም ደጆች ይጮሃል፡፡ ጽዋው ሲሞላም የሚገባቸውን ያገኛሉ፡፡ ያም የዋይታ ቀን እየመጣ ነው፡፡

3. ዘረኝነት - ይሄ “የትግሬ የበላይነት የለም/አለ” የሚሉት ጉንጭ አልፋ ክርክር ያስቀኛል፡፡ አሁን አሁንማ አቤ ቶኪቻው ሳይቀር ወደዚህ ከንቱ ነገር ገብቶ ሲንቦራጨቅ ሳየው አግራሞቴ እየጨመረ ነው፡፡ ግዴላችሁም - አቤ ቶኪቻው ወደ አዲስ አበባ - ወደ ሸገር - ሊገባ እያኮበኮበ ሣይሆን አይቀርም፡፡ “ትግሬ አልተጠቀመም” የሚል አቋም ወደማራመዱ ገብቷል አሉ - ይህ ብርቅዬ ኢትዮጵያዊ፡፡ ለነገሩ ከሀገር ከወጣ “አንድ 40 እና 50 ዓመታትን” ያስቆጠረ በመሆኑ የአሁኑን ሀገራዊ ምስል በቅጡ ላይረዳው ይችላል፤ እንጂ ጤናማ ሰው ሲጀመር ወደዚህን መሰሉ የሞኞች ክርክር አይገባም፡፡ ወያኔዎች ራሳቸው ጥርሳቸውን ተነቅሰው ነው የሚስቁብን - “በወያኔው ሥርዓት ትግሬ አልተጠቀመም” ስንል፡፡ አድርባይነትና ይሉኝታ ድንበር ካልተበጀላቸው ያጃጅላሉ፤  ቀላል ለማይባል ትዝብትም ይዳርጋሉ፡፡ አበበ ቶላ ምንም ትርፍ ለማያገኝበት ነገር በሁለት ወገን ከሚሳቅበት ይልቅ አዲስ አበባ ዘመድ ካለው ይጠይቅና እውነቱን ይረዳ፡፡ ወያኔ ያመጣብን ዘረኝነት እስካሁን በታሪክ አልታየም፤ አሁንም ከኢትዮጵያ ውጪ በየትም የለም፤ ወደፊትም ከዚህ ከወያኔዎች እንደውሻ አጥንትና ደምን የማነፍነፍ አስነዋሪ የዘረኝነት ድርጊት  አይደለም የሚስተካከል፣ የሚጠጋጋ እንኳን በዓለም ታሪክ ሊከሰት አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ የተያዘችው በወያኔ ትግሬዎች መሆኑን የማያውቅ ወይም ለማወቅ የማይፈልግ ካለ እርሱ ጨረቃ ላይ የሚገኝ ለዚህችኛዋ የመሬታውያን ዓለም ባይተዋር መሆን አለበት፡፡ የሰውን ስሜት ለመጠበቅ እንሞክር ጎበዝ! በሰላማዊ ቦታ ተቀምጦ በኛ ቁስል መጫወት ለከፋ ጉዳት የሚዳርግ ዋጋ እንኳን ባያስከፍል ኋላ ላይ በትንሹ ለኅሊና ጸጸት ሊዳርግ ይችላል፡፡ ዛሬ ማን ነው የሀገርን ሀብትና ንብረት እየተጫወተበት ያለው? እስኪ ሕንጻውና መኪናው ሁሉ ይፈተሽ፡፡ የማን ነው? የመንግሥት መ/ቤቶች እስኪ ይፈተሸ - በነማን ቁጥጥር ሥር ነው ያሉት? በረንዳ አዳሪው እስኪ ይፈተሸ፡፡ እነማን ናቸው? ቀልድ ይቅር እንጂ፡፡ ከተቀለደም በቅጡ ይሁን፡፡ አንድ መቶ የማይሞሉ ንጹሕ ኢትዮጵያውያን ትግሬዎች እዚህና እዚያ አሉና እነሱን ላለማስቀየም ሲባል አዳሜ እየተነሣ “ትግሬ አልተጠቀመም!” እያለ ቢወሻክት እውነት እንዳይመስላችሁ፡፡ ኑና እዚህ እዩ፡፡ ለምንም ዓላማ እንጠቀምበት ውሸት በተለይ የተጋነነ ውሸት ወንጀል ነው፡፡ ሊያውም ትልቅ ወንጀል፡፡  ሀገራችንን ከገደሏት ሌሎች ምክንያቶች ሁለቱ እንዲያውም በወያኔዎች መንደር የማይታወቁት ይሉኝታና እውነትን ያለመናገር ናቸው፡፡ አንድን ሰው ለማስደሰት ስትል አንድ ሚሊዮን ሰው ማስከፋት የለብህም፤ እንዲያ ካደረግህ የሒሣብ ስሌት ችሎታህ ዜሮ ሆኗል ማለት ነውና በእግረ መንገድ  ጤንነትህን ተመርመር፡፡ ይሰማል አቤ? ታዲያ እነማን ተጠቀሙ? እነጓንጉልና እነአበጋዝማ በየእሥር ቤቱ ታጉረው ኤሎሄ እያሉ ነው፡፡ እነደቻሣና እነ ፈይሣማ በአጋዚዎች አናት አናታቸው እየተበረቆሰ ነው፡፡ የምን ማሽቃበጥ ነው ጃል!  

       በነገራችን ላይ እነአላምረውና እነቶሎሣ በመካከላችሁ የጋራ ጠላቶቻችሁ የጣሉባችሁን አንደርብ ካላፈረሳችሁ መጨረሻችሁ አያምርም፡፡ አሁን እንደሚስተዋለው ትግላችሁ የተፈናጅራ እንደሆነና የግጥማችሁ ቤት ”እንካስላንትያ በብጣሽ” ሲባል “ምን አለ በድሪቶ?” ዓይነት ሆኖ ከቀጠለ መዳረሻችሁን የምታገኙት ሶማሊያና ሦርያ ውስጥ ነው፡፡ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር የሚቆረጠው ግፋ ቢል ሁለቴ መሆን ሲገባ የዘላለም ጅልነት በተፈጥሯዊ ብልህነት ቦታ ከተተካና መቀራረብ ቀርቶ መራራቅ ከሠፈነ ወዮ ለልጆቻችሁ!! ለልጆቹ የማያስብ ትውልድ ባለፈ ታሪክ እየተንጠራወዘ የአሁን ወርቃማ ዕድሉን በከንቱ ያበላሻልና ከዚህ ዓይነቱ የመሠሪ ጠላቶቻችን ዕኩይ ሤራ እንጠንቀቅ፡፡

        የሆኖ ሆኖ እነዚህ ሦስት ነገሮች ሀገርን እያፈራረሷት ነውና አንድዬ በአፋጣኝ ደርሶልን ከለዬለት ዕልቂትና ውድመት እንዲታደገን በተለይ በውጪ ያላችሁ ፈጣሪ ለኪሰማችሁ የሚችል ደጋግ ሰዎች ጸልዩልን፡፡ እኛ እንኳን በኃጢኣት ስለበሸቀጥን የሚሰማን አምላክ ያለ አይመስለኝም፤ ዘረኛ ፓትርያርክ ዙፋን ላይ ተቀምጦ የአጋዚዎች ግድያ እንዲሳካ የሚጸልይ “አባት” ባለበት ሀገር እግዜር ሥራ ፈትቶ ጸሎትን ሲሰማ ይታያችሁ፡፡ በቃኝ እባክህን፡፡ የምታሳብድ ሀገር ውስጥ ተቀምጦ ማንንም አለማስኮረፍ ያዳግታልና በዚህ ጽሑፌ የተከፋችሁብኝን ሁሉ በጅምላ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ሀገረይ በእግዚሃር ስትጎበኝ ለመካስ ያብቃኝ፡፡ የአሁኑ ግን ተከድኖ ይብሰል፡፡ ሆ! “ትግሬ አልተጠቀመም?” “አቸፍቻፊ!” ያለው ማን ነበር? ልጅ ይውጣለት፡፡