በቅደም ተከተል ከላይ ወደታች የቀረቡት ፎቶግራፎች አፄ ቴዎድሮስ፤ብርጋዴር ጀኔራል ተሾመ ተሰማ፤ ሻምበል ሸዋንታዮ ዓለሙ እና ከሥር የሚታየዉ የመጨረሻዉ ፎቶግራፍ በምፅዋ ጦርነት ወቅት ከመጀመሪያ አስከ መጨረሻ ድረስ በጀግንነት ተዋግተዉና አስተባብረዉ የጀግኖችን አደራ እና ቃል ዘግበዉ ለኛ ያስተላለፉልንን የ“አይ ምፅዋ!” ደራሲ ባለዉለታችን ናቸዉ።
ከተረሱት ጀግኖቻችን ማህደር
-አይ ምፅዋ!
ሞት የተፈረደባቸዉ 17ሺህ የኢትዮጵያ ሠራዊት
ደራሲ (ታደሰ ቴሌ ሰልቫኖ) (የብዕር ሥም)
ጌታቸዉ ረዳ
(www.Ethiopiansemay.blogspot.com)
“ሰዓቱ ለካቲት 9 አጥቢያ ከንጋቱ 11፡30 ሰዓት ነበር።… በሁሉም አቅጣጫዎች የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት በከባድ ጀግንነት ከሻዕቢያ ጋር በጥይት፤በእጅ ቦምብና ላዉንቸር ተጨፋጨፈ። መሬቱ እየነጋ ሲሄድ የምፅዋ ከተማ በአስከሬን ክምር፤በሰዉ ሥጋ ብጥስጣሽና በደም ጎርፍ ጨቅይታለች፡ ድመትና ዉሻ የመረጡትን አስከሬን ይጎትታሉ።አንዳንድ ቦታ ደግሞ የሰዉ እስከሬንና የዉሻ ሬሳ ጎን ለጎን ተኝቷል። በጣም የሚዘገንን ዕልቂት ነበር። የከባድ መሣሪያ ጥይት የቆራረጠዉ ሰዉ አካል በየቦታዉ ዕጣ ያልወጣለት የቅርጫት ሥጋ መደብ መስሏል…”
ለዛሬ “ከረሳናቸዉ ጀግኖቻችን ማህደር” ይህነን የመሰለ የሉአላዊነት የሞት የሽረት ኢትዮጵያዊ የጀግንነት ገድል በምቾት እየተንደላቀቀ አእምሮዉ ለላሸቀበት ባልታገለበት ባዶ ሜዳ ላይ እቅፍ አበባ የሚታቀፈዉ አስሰዳቢዉ የዘመናችን “ሀፍረተ-ቢስ ምሁር”- “አይ ምፅዋ” ከሚል በየካቲት 1982 ዓ.ም ታትሞ ለሕዝብ ይፋ የሆነ እጅግ ታሪካዊ መጽሓፍ ጀግንነትና ኢትዮጵአዊነት ምን ማለት እንደሆነ ቢገባዉ ከሚል እሳቢ የቀረበ ዝግጅት እነሆ።
ግብዞቹ “የደርግ ወታደር” እያሉ የሚጠሩት “ኢትዮጵያዊ ሠራዊት” በግብዞቹና በእርሱ መሃል ያላቸዉና የነበራቸዉ የኢትዮጵያዊነት ትርጉም ልዩነታቸዉ በግበር እንመለከታለን።የታሪክ ከሃዲዎች ናቸዉና ይህ ገድል ዛሬም ቢያንኳስሱት አይገርመንም።ዛሬ የምሁራን ዓይን ታዉሮ የተደረጉት ዕልክ አስጨራሽ የሉአላዊነት የደም ገድል ማየት ቢያቅተዉም ፤መጪዉ ትዉልድ የምጸፅዋ ዳግማዊ ቴዎድሮሶቻችነን መስዋእትና ታሪክ በቁርጥ ቀን ልጆቻቸዉ መታደሱ ምንም አልጠራጠርም።
በታሪኩ ዉስጥ የምናየዉ የእነ ራስ አሉላ እና የንጉሥ ዮሐንስ ገድለ ታሪክ በማንኳሰስ ለዓረቦችና ለሻዕብያ በባንዳነት አድሮ ምፅዋ ላይ ታሪካዊ ወደባችንን ላለማስነጠቅ ዘብ ቆሞ በነበረዉ በ17 ሺህ ሰራዊታችን ላይ ጥቃት ያደረሰዉ “ባንዳዉ -ህዝባዊ ሐርነት ትግራይ” እና የዓረቦቹ “ቀንደኛዉ ዉሻቸዉ ሻዕብያ” ከተባለዉ ቡድን ፤ማንነታቸዉን አምታትተዉ “ዉዥምብር ፍለጋ” ገብተዉ ሁለቱም አሳፋሪ የጫካ መንጋዎች በጋራ ያደረጉት ብሔራዊ ወንጀል የፈጸሙት ክህደትና ጭካኔ፤ እንዲሁም ለምፅዋ ሽንፈት ምክንያት ቀዳሚ ምክንያት የነበረዉ በመንግሥቱ ሃይለማርያም ደካማ እና አረሜናዊ አመራር የተከናወኑትን ሁሉ ጦርነቱ ተጀምሮ አስክያልቅ በጦርነቱ ተካፍሎ ቆስሎ ተማርኮ በወታደራዊ ሞያዉ የተሻገረባቸዉ ደራሲዉ ከዘገባቸዉ የጦርነቱ ድርጊቶች በከሃዲዎቹ እና በጀግኖቻችን መሃል የተደረጉት የሞት ሽረት “የመጨረሻ ትግል” መጽሀፉን ለማንበብ ዕድሉን ላላገኛችሁ ኢትዮጵያዊያን ወገኖች ከመጽሐፉ ምስክርነት ፤ አንጀት የሚበላዉን በምፅዋ ወደብ እና ከተማ “የመጨረሻዋ የግብግብ ሰዓት” እንዴት እንደተደመደመ ከዛ የሞት በር በርግዶ ሞትን ካሸነፉት ከጀግኖቻችን አንዱ ከሆነዉ በደራሲዉ አማካኝነት የምፅዋ ጀግኖቻችን ከመሰዋታቸዉ በፊት እንድንሰማቸዉ ያስተላለፉልነን የተናገሯቸዉ ንግግሮች በደራሲዉ እንደበት አደራቸዉን እና የጦርነቱ ሁኔታ አነሆ።
“በየካቲት ወር 1982 ዓ.ም በአብዮታዊ ሠራዊት እና በሻዕቢያ መካከል በቀይ ባሕር አዉራጃ በምፅዋ ግንባር ከባድ እና አሰቃቂ ዉጊያ ተካሂደዋል። ለአስር ቀናት ቀንና ሌሊት ለ240 ሰዓታት በእያንዳንዷ ሰኮንድና ደቂቃ እንደ ቅጠል የረገፉት የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ጎን ተሰልፌ ተፋልሜአለሁ። የሠራዊቱን ተጋድሎ እና የመጨረሻ ዕጣ ፈንታ መስክሬአለሁ። በምፅዋ ግንባር የተደረገዉ ፍልሚያ ለ ኢትዮጵያ ሕዝብ ለሠራዊቱና ቤተሰቡ ይህን የታሪክ መጽሐፍ ለማዘጋጀት ችያለሁ።….
“…እኔ የዚህ መጽሓፍ ደራሲ በምፅዋ ግንባር ከመጀመሪያ አስከ መጨረሻ የዉጊያ ሰዓት ድረስ ተሳትፌ የኢትዮጵያን ሠራዊት ሽንፈት ተጋርቼአለሁ። በዉጊያዉም ቆስየ በሻዕቢያ ተማርኬ ከምፅዋ ወደ ናቅፋ ሳሕል አዉራጃ አንደርበብ በተባለ ቦታ የሻዕቢያ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ተወስጄ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ምርመራ ተደርጎብኛል። ጭልጥ ባለ የበጋ በረሃ የሳሕል ሀሩር በጉድጓድ እስር ቤት ታስሬ ፍዳየን አይቻለሁ። እንደዚህ ዓይነቱ መከራ ዉስጥ አልፌ ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት መብቃቴ ራሱ ከሙታን ዓለም ተመልሼ የመታየት ያህል መስሎ ታይቶኛል።”
-ለታሪክ ፀሐፊዎች-
(ገጽ 187 አስከ 198)
የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ምፅዋ ከተማ ለተከማቸዉ አብዮታዊ ሠራዊትና አመራሩ ክፉ ቀን ነበረች። ሻዕቢያ ደግሞ እንደ ልደት ቀን ይቆጥረዋል። ምክንያቱም ለመጀመሪያ ጊዜ ምፅዋ ከተማን የረገጠዉ በዚች ዕለት ነዉና።
ሻዕቢያ በ1970 ዓ.ም ከጀብሃ ተዋጊዎች ጋር በመሆን አብዛኛዉን የኤርትራ ግዛት ተቆጣጥሮ ነበር። አሥመራ፤ባሬንቱ፤ምፅዋና ዓዲቀይህ ከተማ የነበሩትን የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት ደምስሶ እነዚህን ከተሞች መቆጣጠር ግን አልቻለም። በመሆኑም የሃያ ስምነት ዓመታት ምኞቱን ሻዕቢያ በምፅዋ እዉን ያደረገበት ቀን የካቲት 9 ቀን 1982 ናት።
የ6ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ጀኔራል ተሾመ ተሰማ ካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡30 ሰዓት ላይ በምፅዋ ከተማ ርዕሲ ምድሪ በተባለ አካባቢ በከባድ መሣሪያ በፈራረሱ ቤቶች ጥግ ሆነዉ የተወሰኑ የጦር መኮንኖችን እና ባለሌላ ማዕረግተኞችን ሰብስበዉ ንግግር አደረጉ።
“ሻዕቢያ ያለ የሌለ ሃይሉን ተጠቅሞ በእጅ ቦምብና በክላሽን በአሁኑ ሰዓት የከተማ ዉስጥ ዉጊያ በማድረግ ላይ ነዉ። ሻዕቢያ ከባድ መሣሪያ ድብደባ አቁሞ በእግረኛ ብቻ ለመዋጋት አዲስ ተዋጊ ሃይሉን በመኪና እያመላለሰ ዕዳጋ ከተማ ላይ እያከማቸ ነዉ። በአዲስ ጉልበት ተዋግቶ ምጸፅዋን ለመያዝ ቆርጦ ስለመነሣቱ ጥርጥር የለዉም።…
“እኔ የሚፈለግብኝን አደራ ተወጥቻለሁ። ከጥር 30ቀን 1982 እስከ ዛር የካቲት 9 ቀን 1982 ሞት ሽረት ትግል አድረጌአለሁ።የሻዕቢያን የጥፋት ዓለማ ለመግታት ያላደረግኩት ጥረት የለም። ከዚህ በሗላ ግን የራሴን ሕይወት በክብር ከማጥፋትና ለኢትዮጵያ ጀግኖችና ታሪክ ፀሐፊዎች ታላቅ ተምሳሌት ከመሆን ሌላ አማራጭ የለኝም። ጀግንነት ማለት በሁሉም መልክ ለጠላት አመች ሆኖ አለመገኘት ማለት ነዉ።…
“በዚች የኢትዮጵያ ህዝብ የባሕር በርና ዓለም አቀፍ ወደብ በሆነችዉ በምፅዋ ከተማና በቀይ ባሕር ጠረፍ ላይ ቆሜ ሽጉጤን ለመጠጣት ዝግጁ ሆኜአለሁ። በ እዉነት እኔ ዛሬ በሞት ብሸነፍም በታሪክና በመጭዉ የኢትዖጵያ ትዉልድ ፊት አልሸነፍም። የ አፄ ትዎድሮስን ዕድል በማግኘቴም በጣም እኮራለሁ። እኔ አሁን የተዘጋጀሁለት ሞት ዘለዓለማዊ ክብርና ሕይወት ይሰጠናል። በሻዕቢያ እንደ እነ ጀኔራል ጥላሁን እና ጀኔራል ዓሊ ሓጂ ተማርኬ የሻዕቢያን መሪዎች ዓይን ማየት ግን የሞት ሞት ነዉ።
አፄ ቴዎድሮስ በእንግሊዞች እጅ ወድቀዉ ከመዋረድ ሞትን መርጠዉ የራሳቸዉን ሕይወት መቀቅደላ ላይ አጠፉ። እኔ ደግሞ በተራየ ከኢትየጵያ ሕዝብ መንግሥት የተሰጠኝን የጄኔራልነት ማዕረግ ሳላስደፍር ለመንግሥትና ለሕዝብ በገባሁት ቃል ኪዳን መሰረት አስቀድሜ የፈቀደዉን ያህል ተዋግቼና አዋግቼ ሻዕቢያን አራግፌአለሁ። እንደ ጦር መሪም እንደ ተራ ተዋጊም ሁኜ ክላሽንኮቭ ጠመንጃ ይዤ ተፋልሜአለሁ። አሁን ግን ለመጨረሻዋ መስዋዕትነት ህይወቴን ለማጥፋት የቀሩኝ ጥቂት ደቂቃዎች ናቸዉ።…
“ጎበዝ ስሙኝ! ይህ አደራ መልዕክቴ ነገ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይደርስ ይሆናል። ምናልባት አምለክ ካለ ከእናነተ አንዱ መልዕክቴን ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግሥት አደርስ ይሆናል። ዛሬ ሻዕቢያ ምፅዋን ተቆጣጥሬአለሁ በማለት የዓለምን መገናኛ ብዙሃን እንደሚያጨናንቅ ጥርጥር የለዉም። ይህ ደግሞ ለ ኢትዮጵያ ሀግርና ሕዝቧ ትልቅ አደጋ ነዉ። በቀይ ባሕር በራችን በኩል ብዙዉን ጊዜ ወረራ ፈጽመዉብን በተደጋጋሚ የሳፈርናቸዉና ፊት ለፊት ያልቻሉን ምዕራባዉያን ሀገሮችና ዓረቦች ዛሬ የሻዕቢያን ጊዜያዊ ድል ሰምተዉ ይፈነጥዛሉ። ምናልባትም የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ድንበር የሆነዉንና ለዘመናት በአባቶቻችን የደም ዋጋ ፀንቶ የቆየን የባሕር በራችንን በመዝጋት እንዲሁም ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ባሕር አይደለም በማለት በምድር ተወስነን እንድንቀር ይደረግ ይሆናል። ይህ ደግሞ የሞት ሞት ነዉ።
“ ይሁን! ምንም ማድረግ አልችልንም። ሁሉም ነገር ከቁጥጥሬ ዉጭ ሆኗል። ከሙታን ዓለም መጥቼ ማረጋገጥ ባልችልም የፈለገ ጊዜ ይጠይቅ እንጂ ጀግናዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ የባሕር በር አልባ ሆኖ ፤
በኢምፔርያሊስቶችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸዉ ተሸንፎና እጁን አጣጥፎ አይቀመጥም። ይህ ከሆነማ የአፄ ዮሐንስ የቀይ በሕር ተጋድሎ እና የጀግናዉ ራስ አሉላ አባነጋ አጥንት እንዲሁም የእኔን ጨምሮ የ እበዮታዊ ሠራዊት አባላት አጥንትና ደም የኢትዮ ያን ትዉልድ ሁሉ እሰከዘላለሙ የፋረዳል። ኢትዮጵያ ሀገሬ የጀግኖች መፍለቅያና ገናና ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በመሆኑም ጀግናዉ ሕዝቧ ሕዝባዊ የባሕር በሩ በሻዕቢያ ተይዞና የጠላቶቹ መፈንጫ ሆኖ አይኖርም። የፈለገ ጊዜ ይቆይ እንጂ ሻዕቢያ ምፅዋን እንደያዛት ለዘላለሙ አይኖርም”። ጊዜዉ ጠብቆ የኢትዮጵያ ጀግና ጠላትን ደምስሶ ምፅዋን ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንደሚያስረክብ እምነቴ የፀና ነዉ።” አሉና ትንፋሽ ዋጡ: የትንሽ ፋታ ወሰዱ።
የጀኔራል ተሾመ ዓይን የቆሰለ የነብር ዓይን መስሏል፡ ከንፈራቸዉ በዉሃ ጥም ደርቆ ቅርፊት ይዟል። ፊታቸዉ በደረቅ ላብ ዥንጉርጉር ሆኗል። ሆዳቸዉ ከወገባቸዉ ተጣብቋል።
በተሰበሰበዉ አባል ዉስጥ በሰፈነዉ ጸጥታና ዝምታ መሃል “እናንተ አብየታዊ መኮንኖች ባለሌላ ማዕረጎች! ስሙኝ አንድ ምሳሌ ልንገራችሁ።” አሉ ጀኔራል ተሾመ ቆጣ ብለዉ።“አንድ ሰዉ ቤት ሲሰራ የሚሠራዉ ቤት በርና መስኮቶች አሉት። አንድ ሰዉ ደግሞ ሞተ እንበል። መቃብር በርና መስኮት የለዉም። በርና መስኮት የሕይወት ምልክቶች ናቸዉ። በመሆኑም ያለሀገር ነፃነትና ያለባሕር በር ብልጽግና ስለሌለ የኢትኦጵያ ሕዝብ የባሕር በር ተነጥቆ የሚኖር ሕዝብ አይደለም። ከሻዕቢያ ጀርባ ሆነዉ ቀይ በሕር የኢትዮጵያ አይደለም የሚሉ ሀገሮችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸዉ ሁሉ በቀጥታም ሆኑ በተዘዋዋሪ ፍላጎታቸዉ የ ኢትዮጵያ ሞት ነዉ።
“ይህ ምሳሌ ከገባችሁ የባሕር በር የሌላት ሀገር ሞቶ ከተቀበረ ግለሰብ የምትለየዉ በትንሹ ነዉ። ምክንያቱም የባሕር ሀብት ከማጣቷ በላይ ምርቷን ወደ ዉጭ ለመላክ የግዴታ ወደብ ስለምትከራይ ለወደብ ክፍያ የምትከፍለዉ የገንዘብ ዉጭ ዜጎቿን ያደኸያል። በአኳያዉ ጠላቶቿን ባለወደቦቹን ያበለጽጋል። ይህ ዕድል
ለኢትዮጵያ እንዳይደርሳት ቀይ ባሕር የኢትየጵያ ትዉልድ ይፋረድ።፡ቀይ ባሕር ለእኔ ዘላለማዊ ቤቴ እንዲሆን ወስኛለሁ። ደስተኛ እና ዕድለኛ ጀኔራል ነኝ። እኔ ብሞት ታሪኬ አይሞትም። የእኔ ታሪክ
በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሕሊና ዉስጥ እንደሚኖር አምናለሁ። ቻዉ! ቻዉ!ቻዉ!” አሉና ጀኔራል ተሾመ ፤መኮንኖቹን ከሰበሰቡበት ቦታ ተፈናጥረዉ ወደ ቀይ ባሕር ጠረፍ አመሩ። የባሕሩ፡ጠረፍ ከስብሰባዉ ቦታ በግምት ከስልሳ ሜትር አይበልጥም። በፍጥነት ወደዚህ በሕር ጠረፍ ገሰገሱ። ክላሺንኮቭ ጠመንጃዉን አቀባብለዉና አዉቶማቲክ ላይ አድርገዉ በቀኝ እጃቸዉ ጨብጠዋል፡
ከምፅዋ ወደብ በስተቀኝ ከሚገኘዉ ወታደራዊ ወደብና መደብር ላይ ሲደርሱም ለቀይ ባሕር ዉሃ መገደቢያ በተሰራ ግንብ ጠርዝ ላይ ጀርባቸዉን ወደ ቀይ ባሕር ፊታቸዉን ወደ ምፅዋ ከተማ አድርገዉ ቆሙ። ቀጥሎ በእጃቸዉ የነበረዉን ክላሺንኮቭ ጠመንጃ ወደ ቀይ ባሕር ወረወሩት። ከዚያም በወገባቸዉ ታጥቀዉት የነበረዉን ኮልት ሽጉጥ አወጡና የሽጉጡን አፈሙዝ በአፋቸዉ ጎርሰዉ የካቲት 9 ቀን 1982 ዓ.ም ከጥወቱ 2፡10 ሰዓት ሲሆን ቃታዉን ሳቡት። የሽጉጥ ቶክስ ድምፅ እንደተሰማ ወደ ጀርባቸዉ በቀይባሕር ዉሃ ላይ ወድቀዉ ሰጠሙ። ከጭንቅላታቸዉ የሚፈስ ደም በቀይ ባሕር ዉሃ ላይ ቀልቶ ይታይ ነበር።
ወዲያዉም ይህን የጀኔራል ተሾመ ሞት በምስክርነት ቆመዉ ከአዩት መካከል ከ150
የማያንሱ የጦር መኮንኖች ባለሌላ ማዕርጎች በሽጉጥ፤ በእጅ ቦምብና በክላሽ ጠመንጃ ሕይወታቸዉን አጠፉ። ከ እነዚህም መካከል ሻለቃ ሮሪሣ ዳዲ በእጅ ቦምብ፤ሻምበል ሸዋንታዮ ዓለሙ በማካሮቭ ሽጉጥ፤ሻምበል አዲሱ በማካሮቭ ሽጉጥ፤ሻምበል ባሻ አማረ ናጂ በክላሽ፤ሻምበል ወንድወሰን በሽጉጥ የሃምሳ አለቃ ፈቃዱ ቦጋለ በክላሽ፤ወታደር ሽንገረፋ በክላሽ ሕይወታቸዉን አጠፉና በስም የሚታወሱ ናቸዉ። ሌሎችም በብዛት ራሳቸዉን ገድለዋል። በአጭር ደቂቃ ዉስጥ አካባቢዉ ሬሳ በሬሳ ሆነ።
ሌሎች ደግሞ ሻዕቢያን ገድየ መሞት አለብኝ እያሉ ወደ ጠላት ወረዳ በመገስገስ ገድለዉ የሞቱትም ነበሩ። ወደ ጠላት እየሮጡ በእጅም በቦምብም ታንክ ተሽከርካሪዎችን እያቃጠሉ ራሳቸዉን የገደሉ በሻዕቢያም የተገደሉ ጥቂት አልነበሩም።
ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ የ3ኛ ሜካናይዝድ ክፍለጦር ምክትል አዛዥ ከጀኔራል ተሾመ፤ከሌሎች መኮንኖችና ባለሌላ ማዕረጎች ሞት በሗላ የተረፉትን አሰባስበዉ የሻዕቢያን ከበባ ሰብሮ ለመዉጣት ሞከሩ። የአምሳ አለቃ ታደሰን (ደራሲዉ) እና ከ300 ያላነሱ የአብዮታዊ ሠራዊት በቀጥታ በመምራት ከምፅዋ ከተማ ዋናዉን የመኪና መንገድ ይዘዉ አዋጉ። ዉጊያዉ ከባድ ዕልቂት አስከትሎ ነበር። ሸዕቢያን እያባረሩ እየገደሉ
፤ሻዕቢያም የአብኦታዊ ወራዊት አባላትን እያባረረ እየገደለ
የእጅ በእጅ ዉጊያ ጭምር ተደረገ። የኮሎኔል በላይ ሠራዊት በዚህ መራራ ፍልሚያዉ ከምፅዋ ዓለም አቀፍ ወደብ በግመት በሁለት ኪሎ ሜትር ርቃ ወደ ምትገኘዉ በረዶ ፋብሪካ ወይም ጠዋለት ወደተባለችዉ የምፅዋ ክፍለ ከተማ የ70 ደቂቃ ዉጊያ በማድረግ ሻዕቢያን ሰብሮ ለማለፍ ቀይ በሕር ሆቴል ደረሰ። ግማሹ ሃይልም ቀይ ባሕር ሆተል ያዘ።
ይሁን እንጂ በዚህ አካባቢ የተከማቸዉ የሻዕቢያ ሃይል በጣም ብዙ ስለነበር የሠራዊቱ ሙከራ ተገታ። ሻዕቢያን ሰብሮ ወደ ዕዳጋ ከተማ ለመሻገር አልቻለም። በዚህም ሁለተኛ ትራጀዲ ተከሰተ።
ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ
የኢትዮጵያን ሰንደቃላማ ለብሰዉ ከቀይ ባሕር ሆቴል በረንዳ ላይ በአንዲት ጥልፍልፍ የቃጫ ወንብረ ላይ ተቀምጠዉ አጠገባቸዉ ለነበሩት ጥቂት አባላት መልዕክት ያስተላልፋሉ። “ጀግና ቢሞት በእልፍ እአላፍ ጀግና ይተካል።የእኔ ታሪክ ለትዉልድ ይቀራል። ታሪክ ይናገራል እንጂ እኔ አልናገርም።” የምትል መልዕክት ነች። መልዕክታቸዉም አንደጨረሱ ፊታቸዉን ወደ ምፅዋ ቅድስት ማሪያም ቤተክርስትያን አዙረዉ አማተቡና የክላሽንኮቭ ጠመንጃቸዉን አፈሙዝ ጎርሰዉ ቃታዉን ሳቡት። ለጥቂት ሰኮንዶች አዉቶማቲክ ክላሽንኮቭ ድመፅ አስተጋባና ፀጥታ ሆነ።
ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ ክላሽንኮቭ ጠመንጃቸዉ እንደያዙ ወንበር ተደግፈዉ ተዝለፍልፈዋል። የለበሱት የ ኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ባንዴራ በላያቸዉ ላይ ደምቆ ይታያል።
ይህነን ትዕይንት ሻዕቢያ በፎቶግራፍ አንስቶታል። በቪዲዮ ካሜራም ቀርጾታል፡ የወታደዊ ሸሚዝና ሱሪያቸዉን ኪስ ሻዕቢያ ሲበረብርም ከንጽህና ወረቀት በስተቀር ምንም አላገኘም። አንድ የሻዕብያ ተዋጊ ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ ለብሰዉ የተሰዉትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ባንዴራ ካላያቸዉ ላይ ገፈፈና ክብሪት ጭሮ አቃጠለዉ። የኮሎኔሉ አስከሬን ከወንበሩ ላይ ገፍትሮ በመጣልም በደም የተጨማለቀዉን ወንበር በአንድ እጁ ወደ ላይ አነሳዉ። ይህ ድርጊት ጋብ ያለዉን ተኩስ በመጠኑ ቀሰቀሰዉ። ከአንድ አቅጣጫ የተተኮሰች ጥይት ያን የሻዕቢያ አባል ከወንበሩ ጣለችዉ።ከዚያ በሗላም የሻዕቢያ ተዋጊዎች ተደናግጠዉ አካባቢዉን ማሰስ ጀመሩ።ፎቅ ላይ እየወጡና ምድር ቤቱን አሰሱ ቁስለኛም ይሁን ጤነኛ በየቤቶቹ ፍርስራሽ ሥር ተደብቆ ያገኙትን የአብዮታዊ ሠራዊት አባል ጭምር በየቦታዉ መረሸን ጀመሩ። የአብዮታዊ ሠራዊት አባላትም ሻዕቢያን ገድሎና የራሳቸዉን ጥይት እየጠጡ ሞቱ። “ኢትዮጵያ ወይም ሞት! ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ዘላለማዊ ባሕር ነዉ!”። እያሉ መፈክር በማሰማት የክላሽ ጥይት እየጠጡ የተሰዉም ብዙ ናቸዉ።
ከጥዋለት ወደ ባፅዕ ከተማ ወይም ወደ ምፅዋ ወደብ የሸሹም
የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት ብዙ ናቸዉ። የሃምሳ አለቃ ታደሰም ከሸሹትና ካመለጡት አንዱ ነበር።
በዚህ ግርግር ዉስጥ ብዙ አስደናቂ የግለሰብ ጀግንነቶች ታይተዋል። ለአብነት የሚከተሉትን እንመልከት።
አንድ የ6ኛ ክፍለጦር መረጃ መምሪያ ባልደረባ የሆነ ዕድሜዉ በግምት 42 የሚሆን፤ መልኩ ጠየም ያለ እና ቀጭን ሰዉነት ያለዉ የሃምሳ አለቃነት ማዕረግ ያለዉ ኤም 14 ጠመንጃ ታጥቆ በምፅዋ ወደብ አካባቢ ቦታ ይዟል። ሻዕቢያዎች ሊማርኩት እንደተጠጉ ባረጋገጠ ጊዜ “ዘራፍ! አልሆንም ምርኮኛ! ጀኔራል ተሾመ ዛሬ ጠዋት “የጀግናዉ የአፄ ቴዎድሮስን ዕድል በማግኘቴ ዕድለኛ ነኝ” በማለት ሽጉጥ ጠጥተዉ በጀግንነት በቀይ ባሕር ዉሃ ላይ ወድቀዉ መቃብራቸዉን ቀይ ባሕር ሲያደርጉ መስክሬአለሁ። ዛሬም ነገም ለዘላለም ይህ የጀኔራል ተሾመ ጀግንነት በትዉልድ ፊት በወርቅ ቀለም ተጽፎ የሚቆይ በመሆኑ እኔም በሻዕቢያ ተማርኬ የመኪና መንገድ ለሻዕቢያ ጠራጊ ሆኜ ከምሠራ ሞቴን በጀግነንነት እንደ ተሾመ መርጫለሁ።“ዘራፍ! ዘራፍ! የጎንደር ልጅ! የጎንደር ልጅ ሞት አይፈራም! ዘራፍ!ዘራፍ! የአማራ፤የኦሮሞ፤የትግሬ የአገዉ፤የጉራጌ፤ወላይታ፤የሶማሌ፤ባጠቃላይ ኢትዮጵያ ልጅ ሁሉ ለሀገሩ አንድነት ክብርና ነፃነት በግምባር ቀደምትነት ይሞታል! ኢትዮጵያዊ ማለት ጀግንነት ማለት ነዉ። ኢትዮጵያ ወይም ሞት!! ሞት ለሻዕቢያ!! ዘራፍ!ዘራፍ!የቴዎድሮስ፤የአሉላ የዬሓንስ የአብዲሳ የተሾመ ወኔ በእኔ ልብ ዉስጥ በቅሏል!” አለና ቦታዉን በመልቀቅና ወደ ሻዕቢያ ተዋጊዎች በመሮጥ እያከታተለ የ እጅ ቦምብ ወርዉሮ አራት የሻዕቢያ አባላትን ገደለ። በመቀጠልም ብቻዉን በሻዕቢያ መካከል ገብቶ ካላሽን ጥይት እሩምታ አወረደባቸዉ። ሃምሳ አለቃዉ አጥፍቶ ለመጥፋት በልበ ሙሉነት ከጠላት ጋር ተቀላቅሎ የልቡን አደረሰ። በሻዕቢያ ጥይት ቆስሎ ከወደቀበት ቦታ ሆኖም ቦምብ በራሱ ላይ አፈነዳና ሰዉነቱን በታተነዉ። ሕይወቱ አለፈች።
የሃምሳ አለቃዉን ጀግንነት ያየ ብዙ የጦር መኮንኖችና ወታደሮች ሽጉጥና ጠመንጃ ሕይወታቸዉን አጠፉ። ቢያንስ ቢያንስ ከዘጠና ያላነሱ ራሳቸዉን በዚህ መንገድ አጥፍተዋል። በዚሁ ዕለት በዚህ ጊዜ ከነሙሉ ትጥቃቸዉ እየዘለሉ ቀይ ባሕር ዉሃ ገብተዉ በመስጠም ያለቁት ደግሞ ከ150 በላይ ናቸዉ።
የቀይ ባሕር ዉሃ የአብዮታዊ ሠራዊት አባላትን አስከሬን እያንሳፈፈ እያንገላታና ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ እየገፈተረ የዋለባት እንዲት ቀን በታሪክ ብትኖር ይህቺ ናት። የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት እዉነተኛ የሀጋር ፍቅር ምን ያህል እንደሆነም የቀይ ባሕር ዉሃ የተገነዘበ ይመስላል። ምክንያቱም አስከሬናቸዉ እየገፋ ከየባሕሩ ጠረፍ ወደ መሃል መበዉሰድ በአጠቃላይ ሻዕቢያ ሊማርከኝ ቀርቶ ሬሳየን በዓይኑ ማየት የለበትም የሚል የዉስጥ ኑዛዜያቸዉ ተግባራዊ ያደረገ ይመስላል።
የቀይ ባሕር ዉሃ የጨዉ ዉሃ ስለሆነ ዉስጡ ወለል ብሎ ይታያል። የአብየታዊ ሠራዊት አባላት ዘለዉ ሲገቡ አስከተወሰነ ርቀት ይታያሉ። እንደገቡም እጃቸዉ የያዘዉን ጠመንጃ ይለቃል። ከዚያም ከአንድ ከ አስር ደቂቃ በሗላ ሆዳቸዉ ተነፍቶ ከባሕሩ ዉስጥ ወደ ላይ ይወጡና በባሕር ላይ ይንሳፈፋሉ። ባሕሩ በማዕበሉ እየገፋ ወደ መሃል ይወስዳቸዋል።
የካቲት 9 ቀን 1982 በምፅዋ ከተማ አዉራ ጎደናዎችም ልዩ ትርኢትታይቷል። የቆየ እና ትኩስ የአብዮታዊ ሠራዊት እና የሻዕቢያ ሬሳ በየጎደናዎቹና በየቤቱ ሥር ተከምሮ ነበር። ይሁንና የሻዕቢያ ታንክና መኪና እየተነዳበት ተጨፈላለቀ። መጥፎ በሽታና ጠረን አካባቢዉን ተበክሎ ሰዉ መሆንን ያስጠላል።
በየቤተክርስትያኑም እንዲሁ ልዩ ትርኢት ታይቷል። ለምሳሌ ጠዋለት በተባለ ቦታ የቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን አለች።የቤተክርስትያኗ መስኮቶች፤በሮች ግድግዳዎችና ጣርያ በሻዕቢያ ከባድ መሣሪያ ድብደባ ወድሟል። የቤተክርስትያኗ ዉስጣዊ አካል በእሳት ተለብልቦ ከአገልግሎት ዉጭ ሆኗል። አብዛኛዉ አካሉ ማለት ከመቶዉ እጅ ሰማኒያዉ ፈርሷል። በቤተክርስትአኗ ዙሪያ በየፍራሹ ጥግ የኢትዮጵያን ባንዴራ በአንገታቸዉ በእጃቸዉ፤በራሳቸዉ፤በወገባቸዉና በጠመንጃቸዉ ላይ አስረዉ ራሳቸዉን የረሸኑ ብዙ የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት የዘለዓለም እንቅልፍ አሸልበዋል። መሣሪአዎቻቸዉ ለአስከሬኖቻቸዉ የክብር አጀብ ሆነዋል።
በምፅዋ ከተማ በሕይወት በየምሽጉ የሚገኙት የአብዮታዊ ሠራዊት አባላትም ቢሆኑ ጀኔራል ተሾመ ተሰማ እና ኮሎኔል በላይ አስጨናቂ ራሳቸዉን በመግደላቸዉ መሪና አስተባባሪ መዳከሙን እነደተገነዘቡ ሻዕቢያ ከአንድ ሺህ የማያንሱ ተዋጊዎች በተጨማሪ ከዕዳጋ ከተማ ወደ ምፅዋ ከተማ አሰማርቶ ስለ አስከበባቸዉ መፈናፈኛ አጥተዋል። ዉጊያዉ ሙሉ ለሙሉ ቆመ።
ከዚህ በሗላ ምፅዋ ከዉጊያ ቀጠናነት ወደ ሙርኮ ጣቢያነት ተቀየረች። በወጣት ሃይል የተገነቡት የሻዕቢያ ተዋጊዎች በኮማንዶ የሰለጠኑ ናቸዉ። በምፅዋ ከተማ ተበታትነዉ የነበሩት የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት እያሰሱ ከአለምንም ቶክስ መማረክ ጀመሩ። የመጀመሪያ ሥራቸዉ ትጥቅ ማስፈታት ነበር። ቀጥሎ ፍተሻ ይከናወናል። በፍተሻዉ የእጅ ሰዓት የጣት ቀለበት፤የአንገት ሐብል ወርቅ፤የጋብቻ ቀለበት የመሳሰሉት ሻዕቢያዎች እየተስገበገቡ የሚቀራመቷቸዉ ናቸዉ። ጥሬ ገንዘብ ቀበቶ የእግር ጫማ፤ ካልሲ የዓይን መነጽር፤የግል ማስታወሻ፤መንጃ ፈቃድ፤መታወቂያ ፊልድ ጃኬት፤የጦር መለዮ፤ስክሪፕቶ እና ወረቀት ሳይቀር ከምርኮኞቹ ኪስ ወስደዋል። ከተሰዋ የሠራዊቱ አባል ላይ እንኳን ፊለድ ጃኬት ጫማ ሳይቀር አስከሬንን እየጎተቱ ያወልቁ ነበር።
ማንኛዉም ምርኮኛ የሚሄደዉ ባዶ እግር ነዉ። ለብዙ ጊዜ ጫማ የለመደ እግር ያለጫማ መሄድ ባለመቻሉ አብዛኛዎቹ የ አብዮታዊ ሠራዊት አባላት ያነክሳሉ። አንዳንዶቹ በአሸዋ በጠጠር፤በእሾህ፤በጠርሙስ ስባሪ ብረታ ብረት በእንጨት ስንጥር እየተወጉ የእግራቸዉ መዳፍ በደም ተጨማልቆ ይታይ ነበር።
በመጨረሻም ሻዕቢያ በዚህ መልክ ከምፅዋ ከተማ በየቦታዉ የተቆጣጠራቸዉንና የማረካቸዉን የአብዮታዊ ሠራዊት አባላት አጠቃልሎ ወደ ምፅዋ ወደብ ወታደራዊ መደብር አሰባሰባቸዉ። የተማረኩት የአብዮታዊ ሠራዊት የፖሊስ የባሕር ሃይል የሕዝባዊ ሠራዊት አባላት ናቸዉ። ከእንግዲህ ወዲያ ምፅዋ የምርኮኞችን ሥቃይና የሻዕቢያን ፈንጠዝያ የምታስተናግድ ከተማ ሆነች።” }
በማለት ደራሲዉ በዛ እሳት ፤ሰማይና ምድር በተደበላለቀበት ዉጊያና ፈታኝ ሕይወት በማስታወሻቸዉ ዘግበዉት የነበረዉን ሰነድ ዘርዝረዉ እንዴት እንደነበረ በአደራነት የተረከቡት የጀግኖቻችን ቃል ለኢትዮጵ ሕዝብ ማስተላለፋቸዉ በእኔና በአንባቢያን ስም ከፍ ያለ አድናቆትና ምስጋና አቀርባለሁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማስተላለፍ የምፈልገዉ በዛ ጦር ግምባር በአዛዥነትና በዉሳኔዉ ዉስጥ የተሳተፉት የህዝባዊ ወያነ ሓርነት አመራር አባላት ለፍረድ እንዲቀርቡ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ጠንክሮ መግፋት አለበት። ይህ አደራ የገዛ ዓይኑ ጠብሶ ለበላዉ አሰፋሪዉ ምሁር ሳይሆን አደራዉና ምከሬ ለኔ ብጤዉ ኢትዮጵያዊ ነዉና ወያኔን በጠላትነት ፈርጃችሁ አስከ መጨረሻዉ ፍልሚያ በቻላችሁት መንገድ ሁሉ ብሔራዊ ወንጀሉን አጋልጡት! ታገሉት! የባሕር በራችን የጊዜ ጉዳይ እንጂ ይመለሳል! ቴዎድሮሶች ትናንት ኖሯል ለወደፊቱም ይኖራሉ!
ኢትዮጵያዊነት የኢትዮጵያዊያን አንጂ የባንዳዎች መፈንጫ እንድትሆን መፍቀድ ተባባሪነት ነዉ። ወየነ የኢትዮጵያ ክፉ ጠላት ነዉ። መጽሐፉን ብታነብቡ ጀነራሎቹን ምጽዋ ላይ ሲማርክ የነበረ ወታደሮችን በጨካን አንጀቱ በዉሃ በተከበበ መሬት በከባድ መሳሪያና በእጅ በቦምብ ሲፈጅ የነበረዉ አብዛኛዉ የወያኔ እጅ እንደነበር የተለያዩ የተዘገቡት ሰነዶች መስክረዋል። በመሆኑም ኩፉ ጠላትነቱን አስመስክሯልና ለጠላት የሚገባዉ ትግል አትንፈጉት። እናዉቅልሃለን የሚሏችሁ ሙሁራን ነን ባዮቹ “ከባሕሩ ዉሃ የተቀላቀለዉ የጀግኖች ደም “እርሱት” ቢሏችሁ እንኳ “አንረሳም!” በሏቸዉ። ድሮም ሰንፈዉ ያስሰነፉን እነሱ ዛሬም ሰንፈዉ እያስሰነፉን የሚገኙት ያዉ እነሱ ናቸዉና ወደር የሌለዉ የጀግኖችን ገድል የመንፈሳችሁ መመሪያ አድርጉ። የጀግኖች ደም በኢትዮጵያ ሰማይ ሕያዉ ሆኖ በክብር ለዘላም ይኖራል! www.Ethiopiansemay.blogspot.com
/-////-/