Saturday, February 18, 2012

Haileselassie the lion of Africa who refuses to die

ትኩስ ዜና

ወደ ሳምናተዊ ሐታታችን ከመግባታችሁ በፊት ይህንን ዜና አንብቡ።
በኤርትራው ሻዕቢያ ኢሳያስ አፈወርቂ ቁጥጥሩና ትዕዛዝ የሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ሃይሎች በሙሉ በኢሳያስ አፈወቂ ትዕዛዝ ጀኔራል ጠዓመ ወይንም በቅጽል ስሙ “መቀሌ” እየተባለ የሚጠራው ኰለኔል ታደሰ ሙሉነህን ከምደረ ገጽ ያጠፋቸው፡የኢሳያስ የውጭ ስለላ ሃላፊ (ካሁን በፊት መንግሥቱን ለመግደል ዝምባብዌ ድረስ ሄዶ ሲተኩስ እጅ ከፍንጅ ከተያዙት አንዱ ነው) አስመራ ከተማ ውስጥ ቦታው ባልተገለጸ ምስጢራዊ ሰብሰባ በማድረግ ያላቸውን አቅም በሙሉ በማሰባሰብ በወያኔ ላይ ሊካሄድ በታቀደው ውግያ ለመሳተፍ እንዲያመቻቸው አስፈላጊ ዝግጅት አጠናቅቀው  
 ካሁኑ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ-ትዕዛዝ እንዳስተላለፈላቸው ታማኝ ምንጮች ገልጸዋል።በሰባው ላይ የተገኙ መሪዎች ተብየዎች እነ ማን እንደተገኙ ዝርዝሩ እንደሚላክልን እንድንጠብቅ ተስፋ በተሰጠን መሰረት እየጠበቅን ነው።ዜናው የጠቆመን ምንጭ እንዳነጋገርነው  በተለይም ስብሰባው ሲካሄድ  ከመሪዎቹ ውስጥ የታየው ገጽታ ምን ይመስል እንደነበረ ሲደርሰን በዝርዝር እንደሚልክልን ቃል በገባልን መሰረት ሁኔታውን እናቀርባለን:
ኢትዮጵያን ሰማይ።ሞቶ የማይሞተው የአፍረካው አምበሳ
ጌታቸው ረዳ www.ethiopiansemay.blogspot.com
ኢትዮጵያ በወያነ ትግራይ ባንዳዎች ቁጥጥር ከገባች ጀምሮ የደረሰባት የሰንደቃላማ እና የሉአላዊነት ክብር መገሰሰ ፤የባሕር ወደብ መነጠቅና ድምበሮች ፤ ለም መሬቶች በባዕዳን እጅ መውደቅ፤የብሔራዊ ሰንደቃላማ ክብር መዋረድ እና  የጎሳ ባንዴራዎች መፈጠር፤ በሃይማኖት መጨፋጨፍ እና አብያተ ጸሎቶች በእሳት መቃጠል፤በጎሳ መፋጀት እና ጥላቻን የማስፋፈቱን በመረጃ የተያዙ፤በመጽሐፍት የተዘገቡ ፤የዓለም የዜና አውታሮች የዘገቧቸው የወያኔ መንግሥት ገበናዎች ናቸው።

ያ አልበቃ ብሎ፤ ዛሬ ደግሞ የሃገሪቱን ክብር በዓለም መድረክ እንዲታወቅ እና እንዲከበር ቦታ ያስሰጧት ንጉሡ እና የንጉሡ ጠ/ሚኒሰቴር ከአጋር ረዳቶቻቸው ጋር ሆነው ለአፍሪካ አንድነት ያደረጉት ትግል በማሳነስ ታሪክ አርካሹ ጎሰኛው የወያኔው መሪ መለስ ዜናዊ ንጉሡ በመሠረቱት የአፍሪካ ህንጻ የክብር ሃውልት ለጋናዊው ከዋሜ ንኩርማ እንጂ ለንጉሡ አይገባም ብሎ በመከራከር የለመደውን ፀረ ሸዋ የአማራ ነገሥታት ጥላቸው ስላልበረደለት ፤የምንደኛ ሥራውን በተግባር በመፈጸም የንጉሡን ክብር እና አስተዋጽኦ አንሶ እንዲታይ አድርጛል። ይህ መሸፈን የማይቻል የንጉሡ አውነተኛ እና ቅዱስ ገድል እንዲሞት ተንኮል መጎንጎን እጅግ ያሳዝናል። ለዚህም ታሪክ ይፋረደዋል። እኛም የንጉሡን ጥረት ህያው ሆኖ ለሕዝብ እና ለታሪክ እንዲነበብ እኛም አልሞትንም እና ታሪካችንም አናስገድልም ። የንጉሡ ዝና እና ሽልማት  ማለት የኢትዮጵያ ሽልማት መሆኑን ወያኔዎች ስለሚያወቁ ኢትዮጵያ በታሪኳ፤በመሪዎቿ በታታሪነቷ በሰላም ወዳድነቷ ያሳየቺው ጥረት እንዳትሸለም እና እንዳትደሰት የሃውልቱ ሽልማት ለሌላ አገር ሕዝቦች መሸለም አገር መካድ ነው። 
                                               አምበሳ እንኳን  ሳይቀር በአክብሮት የሰገዱለት የሸጋዎቹ አገር የኢትዮጵያዎቹ ንጉሥ; ዛሬ ወየኔ በንጉሡ ላይ የቆየ የቋጠረው ቂሙ የንጉሡን ጥረት ለማንኳሰስ በዓለም መድረክ እየተጠቀመበት ነው።

  ወያኔ ሊያፍነው የሞከረውን የንጉሡን የ ኢትዮጵያውያኖች ጥረት እነሆ አቀርብላችለሁ።

 ልክ ነው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ክብር ምንም ቢሆን ወያኔ በአማራ ጠሊታ በሕሪው በወያኔዎች  ዓይን የንጉሡ ክብር የተከበረ ቦታ ይሰጣቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ አይሆንም።ምክንያቱም አክሱማውያን ሳይሆኑ አክሱማውያን ሊሆኑ በመሞከር ወደ አክሱም እየመጡ ዘውድ በመጫን “ሞአ አንበሳ” እያሉ ይሾማሉ; የአክሱም ታሪክ ለተምቤን፤ለእንደርታ እና ለአጋሜ ምኑ ነው? ከሚሉ ወያኔዎች; በዓለም ፊት ስለ ንጉሡ እና ስለ ሕዝቧ በጎ ስራ ማስረዳት  ይችላሉ ብለን ከወየኔው መሪ (coiled snake) አንጠብቅም ። ወያኔዎች ብቻ እኮ አይደሉም ምሁራን ተብየዎቹም ጭምር እኮ ናቸው በዚህ አሳፋሪ ጨዋታ የተቀላቀሉት። አንድ ማስረጃ ልስጣችሁ፦ አንድ እዚሁ ውጭ የሚኖሩ ምሁር ከ7 አመት ስለ ንጉሡ  በእንግሊዝኛ ሲጽፉ፤ እንዲህ ብለው ነበር፤- ” The Arabs continued to undermine the integrity of Ethiopia by financing liberation organizations, and their belligerency is still with us to this day. The effort to hold the OAU conference in Ethiopia and  to establish the Headquarters of the OAU was all done with an eye to glorify the Emperor and satidfy his almost childish appetite for recognition as a world leader.” የተባበሩት የአፍሪካ አንድነት ጽ/ቤት ሲመሰረት ንጉሡ ዋና ጽ/ቤቱ አዲስ አባባ ሊሆን የፈለጉት ለራሳቸው ዝና እና እንደ ህጻን ሁሉንም ዝና እና ስልጣን ከአልጠግብ ባይነት ባህሪያቸው የተነሳ ነው” ብለው ነበር፡ ስማቸው ብጠቅስ ምን ያደርጋል፡ሁሌም ስማቸውን እያነሳሁ ስለምወቅሳቸው በደፈናው ልለፈው። እና እስከዚህ ነው የኛ ምሁራን ስለ ታሪካችን የሚያስተምሩን።ወየኔዎችም እንደዚሁ።
በኔ እይታ ሃውልቱ ሲሆን፤ሲሆን ለሁለቱም ካልሆነ ደግሞ ለንጉሡ ነበር ሃውልቱ መቆም  የነበረበት። ምክንየቶቼም ይሄው።

ከጠቅላይ ሚኒስትራቸው ከአክሊሉ ሃብተወልድ ጥረት ልጀምር።አክሊሉ ሃብተወልድ በደርግ ከመረሸናቸው በፊት የመጨረሻ ኑዛዜአቸው እስር ቤት ውስጥ ሆነው የጻፉት “ስንክሳር ዘኢትዮጵያ” የሚለው የዘገቡት እነሆ።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት

ይህን ድርጅት ለማቋቋም የተካሄደው ዝርዝር ትግል ብዙ ስለሆነ ባጭሩ ብቻ እጠቅሰዋለሁ።

                        ሀ/ አፍሪካ በሦስት ቡድን ተከፋፍሎ ነበር

       1/የካዛ ብላንካ ቡድን

2/የሞንሮቪያ

3/የአረብ ሊግ

ለ/ የመጀመሪያው ስብሰባ በሌጎስ በ1961 እንዲሆን አደረግን በዚህም የኢትዮጵያ ሮል ብዙ ነው።

ሐ/ በስብሰባው ጊዜም እኛ ብቻ ነበርን በቋንቋችን የተናገርነው። ሌሎቹ በእንግሊዝኛ፤በፈረንሳይኛ እና በአረብ ነበር።

ቻርተሩ ለመስራትና ለመፈራረም አዲስ አበባ እንዲሆን ብዙ ደክመን ስለነበረ በዛው ተስማሙ።

የአዲስ አባባ ስብሰባ በ1962

-ተስብሰባው በፊትም የቻርተሩ ድራፍት/ሃሳብ/ እኔ ቢሮ አሰናዳን/ ተአሜሪካ ላቲን አንድ አዋቂ ቀጥረን ነበር/።

- ለውጭ ጉዳዮች ሚኒስትሮቹ ሲሰበሰቡ ድራፍቱን አቀረብን

- የነሱ ሃሳብ መሪዎቹ ተስምንት ቀን በላ ሲሰበሰቡ አይተውት እንዲያጤኑትና ሃሳብ እንዲሰጡበት ለሚመጣው ዓመት ለማስተላለፍ ነበር፡

- ዋኖኞቹ/የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር/ዶክተር ፋውዝ የኔ የድሮ ወዳጅ ስለነበር/በየተራ ጋብዤ አሁኑኑ መፈረም አለብን እያልኩ አግባባቸው።

- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በድራፍቱ ተስማምተውበት የመሪዎች ጉባ ተከፈተ።

 -  መሪዎቹ ዲስኩራቸውን በሚያደርጉበት ጊዜያት የውጭ ጉዳይዎቹ በኮሚሲዎን ተስይመው ድራፈቱን እንዲአዘጋጁ አደረግን። /አምሰት ቀን ብቻ ስላለ/ጃንሆይም ይህን ሳንፈርም መሄድ የለብንም ብለው እንዲናገሩ ተደረገ። ሌላውም ተከተለ።

     -  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ራፖር ቀረበ፤ ክርክር ተደረገ።

- አሁን መፈረም አይቻልም ያሉትን አግባባናቸው።

          - ሌሊት በ11 ሰዓት ተፈረመ።

- የመጀመሪያው የድርጅት ስብሰባ ካይሮ በ1963 እንዲሆንተወሰነ።

_ ሄድ ኳርተሩ አዲስ አበባ እንዲሆን እዚያ ድረስ በልዩ ልዩ መንገድ ሠርተን ነበር።

-     ስብሰባው እንደተከፈተና በዲቤቱ/ክርክርሩ ጊዜያት የድርጅቱ ሥፍራ አዲስ አበባ እንዲሆን ሓሳብ አቅርቦ በጭብጨባ ተቀበሉት።

-     በዚህም ጊዜ ያገሮቹን ወሰን ሁሉ በተለቀቁ ጊዜያት ባለው እንዲረጋ ተወሰነ።

በማለት ባጭሩ ሲገልጹ። አክሊሉ ሃብተወልድ ድርጅቱ አዲስ አባባ ውስጥ እንዲቋቃም ድርጅቱ ለኢትዮጵያ የሰጠው ጥቅም እና አፍሪካውያን እርስበርሳቸው ሲጣሉና ሲነታረኩ ንጉሡ እና ጠ/ሚኒስትሩ ያደረጓቸው ከፍተኛ ጥረቶች በሰፊው ዘርዝረዋል።

አሁን ወደ ንጉሠ ነገሥቱ ጥረት እንግባ።

ኢትዮጵያ ቀደም በአለም ዘመን ታላላቅ መንግሥታት ነበሩ ከሚባሉት እኩል የሆነ ታላቅነት እንደነበራት ታውቃላችሁ።  ከአረቦች/ከእስልምና መነሣት በኢትዮጵያ/አክሱም ዙርያዋን በጠላት ስለተከበበች ከዓለም ጋር የምትገናኝበት የባሕር በሯን ስለተነጠቀች ከዓለም ጋር ግንኙነት ሳታደርግ ለዘመናት ስለቆየች የነበራት ሥልጣኔ እና ሀብት ሁሉ ሳይዳብር እና ሳትጠቀምበት ቀረ። ገናነነቷም እንደዚሁ አብሮ አንቀላፋ። ዘመን ሄዶ በሌላ ዘመን ሲተካ የንጉሡ አያቶች ተራርቀን የነበርነውን፤ተጋርዶ የነበረውን ካብ አፍርሰው አርስ በርሳችን በማገናኘት ያሁኗን ኢትዮጵያን መስርተው፤ ለንጉሡ አስረከቧቸው። ንጉሡም በፈንታቸው በታላቅ ጥበብ እና ተጋድሎ የተነጠቅናቸው ወደቦቻችን አስመለሱዋቸው። በዚህ ታላቅ ክብር ይገባቸዋል። ወያኔ የባንዳ ስራው ሰርቶ የሠሩትን ሥራ አፈርሶ ለአረብ ቅጥረኞች አስረከበው።

የሰሰይጣን መልእክተኞቹ ያኔዎች ዛሬ ክራባት አስረው ሱፍ ለብሰው በደም የተጨማለቀው እጃቸውን ድምጽ ማጉያ ጨብጠውበት በአለም ፊት ፊታቸውን የሚያሳዩበት የተባበሩት መንግሥታት አባልነት መታወቂያ እና ጽ/ቤት እንዲኖራቸው ያስቻሉዋቸው ንጉሡ በ1914 ዓ.ም ማሕበርተኛ በመሆን ከመስራቾቹ አንዱ በመሆናቸው ምክንያት ነው።

ኢትዮጵያ ብቸኛ የዓለም መንግሥታት ማህበር መስራች አፍሪካዊት አገር ስትሆን  በአፍሪካ አገሮች ውስጥ  ከላይቤሪያ በቀር በቅኝ ግዛት ተይዘው ነበር። ንጉሡ በ1955 ዓ.ም 32 የአፍሪካ አገሮች መሪዎችን አሰባስበው የአህጉሩ ጽ/ቤት እንዲኖር እና አዲስ አበባ እንዲሆን ያስደረጉ ጋናዊው ኮዋሚ ንኩርማ ሳይሆኑ  የኢትዮጵያው መሪ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ናቸው።

 በ1914 ዓ.ም አፍሪካን እና በዓለም መሬት የትም የተበተኑት ጥቁሮች ወክለው መድረክ ላይ ቆመው ብቸኛ መሪ የነበሩት ንጉሡ እና ጠ/ሚኒስትራቸው አክሊሉ  ነበሩ። ረዢሙን ኪሎሜትር ርቀት የተጓዘው የ“ፓን አፍሪካን” ጉዞ የጀመረው አርምጃ መነሻው በ1914 መሆኑን አንባቢዎች ልብ ማለት አለባችሁ። ከዚየ ጊዜ ጀምሮ ሰከራከሩት የነበረውን አቋማቸው እና ንግግራቸውን ለአፍሪካ አንድነት ምስረታ ያደረገው አስተዋጽኦ መመርመር ያስፈልጋል።   

ንጉሡ አሁን እየተነጋገርንበት ያለውን ይህን የጋራ  ጽ/ቤቱ አዲስ አበባ እንዲሆን ሲጥሩ አፍሪካውያኖች ከቅኝ ተገዢነት ወጥተው ራሳቸውን ለመቻል እውቀታቸውንና ነፃነታቸውን የሚለዋወጡበት አና የሚንከባከቡበት ተቋም እንዲሆን በማሰብ እንደሆነ ብዙ ሊቃውንት ጽፈውበታል።

አፍሪካኖቹ የሚሰበሰቡበት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ጉዳይ እና አህጉራዊ ውሳኔዎች መነጋገሪያ ጽ/ት ማሰሪያ መሬት እና ገንዘብ ወጪው የሸፈነቺው ኢትዮጵያ ናት (በንጉሡ ትዕዛዝ)። ሲመረቅ ንጉሡ ያደረጉት ልብ የሚሠርቅ አስተማሪ ትምህርት ከዚህ ቀጥሎ ያለውን አንብባችሁ፤ከንግግራቸው፤ከጥረታቸው፤ካሳዩት የመሪነት፤ የአድባርነት/የአባትነት ክብር በመላ መሪዎች የመወደድ ፋና እና አለኝታ በመላ ዓለም አፍሪካን የመወከል መጎስ እና  ክብር  ከጥነታዊነታችን ተዳምሮ ኢትዮጵያ እና ንጉሧ’ አብሮ ከጠቅላይ ሚኒስተራቸው አክሊሉ ሃብወልድ ፤ያሳዩት አድካሚ ጥረት መካድ በጣም አስነዋሪነት ነው። እንደ እኔ ቢሆን ሦስቱም ማለት  ንጉሡ፤አክሊሉ እና ንኩርማ ሃውልት ይገባቸዋል የሚል አስተያየት አለኝ። ይህንን የንጉሡን ንግግር አንባብችሁ ፍረዱ።ንጉሡ ለመሪዎቹ እንዲህ ሲሉ በጣም ከባድ በሆነው ጥያቄ የተናገሩትን በጥቅስ ልጀምርላችሁ ።
“የምናስበው የአፍሪካ አንድነት የፌዴራል አንድነት ነው ወይስ ፍጹም አንድነት? የያንዳንዶቹ አገሮች መብት ይቀንሳል? ምን ያህል? በምንስ ረገድ? በልዩ ልዩ የአገር ክፍሎች እንጀምራለን? ወይስ በአንድነት ነው? ወይስ ፍጹም አንድነት? የያንዳንዶቹን አገሮች እንጀምራለን? ወይስ በአንድ ጊዜ ለመላው ከአፍሪካ የሚሆን የፖለቲካ ሲስተም እናቋቁማለን? አንድ አርምጃ ሳንወስድ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ የምንጠብቅ የሆነ እንደሆነ የሚመጣው የአፍሪካ ትውልድ ሁኔታው ምንም ሳይሻሻል ክርክሩ እንደቀጠለ ይደርስበታል።”

ይሄ ለዚህ ትውልድ ለእኛም መልስ የሚሻው ከባድ ጥያቄ ነው። ንግግራቸው እንዲህ ሲሉ ይቀጥላሉ።
‘ጸ/ቤቱ ሲከፈት ግንቦት14/1955 ያደረጉት ንግግር

በዚህ በዛሬው ቀን በዚች በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ተካፋይ ለመሆን የመጣችሁትን የነፃ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ወንድሞቻችንን በራሳችንና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ስንቀበል በጣም ደስ ይለናል። ይህ ዛሬ እኛ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች የምናደርገው ጉባኤ  በዓለም ላይ እስከሁን ድረስ ተወዳዳሪ የለውም። የዚህ ታላቅ  ጉባኤ መደረግና የመላው የአፍሪካ አገሮች መሪዎች ተካፋይ መሆን ለዚህች ክፍለ ዓለማችንና በውስጧም ለሚገኙ ሕዝቦቻችን ላለን ጥልቅ አሳቢነት ዓይነተኛ ምስክር ነው። ባጭሩ ይህ ቀን ለአፍሪካውያን በመላ ታሪካዊና ታላቅ ቀን ነው።

የዓለምን ዓይን
በዚህ ታላቅ ጉባኤ ከ250 ሚሊዮን የማያንሱት ሕዝቦቻችን ከእኛ የሚጠብቁትን ተግባር ለመፈጸምና ክፍለ ዓለማችንም በኢንተርናሲዮናል ጉባኤ ሊኖራት የሚገባውን ትክክለኛ ሥራ እንድትይዝ ለማድረግ ተሰብስበናል።

በዛሬው ቀን መላው ዓለም አተኩሮ ይመለከተናል። አካባቢያአችን በክሪቲክ በተጠራጣሪዎችና ተስፋ በሚያስቆርጡ የተሞላ ነው፡አፈሪካውያን እርስ በርሳቸው በመጣላት የተለያዩ እና የተከፋፈሉ ናቸው የሚሉ አሉ። እውነትም አንዳንድ አለ።ቢሆንም ይህ መጥፎ አስተያየ ት ያላቸውን ሁሉ ከንቱ መሆኑን በሥራችን እናሳያቸው። ሌሎች ደግሞ አፍሪካውያን ባለፉት ዘመናት የደረሰባቸውን ጭቆና በማሰብ የሕዝቦቻቸው የወደፊት ዕድል የተቃና እንዲሆን ተጣጥረው ለመሥራት ቆርጠው ተነስተዋል የሚሉ አሉ። እነዚህ ለኛ ለአፍሪካውያን ቦጎነት  የሚያስቡ ደገሞ  ያልተሳሳቱ መሆናቸውንና በኛም ላይ የጣሉት እምነት የሚገባ መሆኑን በተግባራችን እናስሰመስክር።
የነገይቱ አፍሪካ

አፍሪካ ዛሬ ከትናንትናው አፍሪካ ወደ ነገው አፍሪካ በመሸጋገር ላይ ትገኛለ ች። የዛሬው ሁኔታ እየተሻለ ካለፈው ጊዜ እየራቅን እያደረ ወደ ነገው ዓለም በመጠጋት ላይ እንገኛለን። ክፍለ ዓለማችንን በተሻለ ሁኔታ እናቀርባለን ብለን የተነሳንበት ሥራ ሊቆይ አይቻልም።ብንፈልግም እንኳን ልናዘገየው አንችልም። ማድረግ የሚገባን ይልቅ ጊዜው ሳያልፍ የኛን ፈንታ መፈጸም ነው።

ወዴት እንደምናመራ ማወቅ ይኖርብናል። ከየትስ እንደመጣን ማወቅ አለብን። ወደፊት ለምናደርገው ሁሉ ያለፈው ታሪካችንን ማወቅ ይገባናል። በአፍሪካውያንነታችን ያለን ኩራት  ማወቅ ይገባናል። በአፍሪካዊነታችን ያለን ኩራት የሚገጥሙንን ችግሮች ሁሉ ለማስወገድ ትልቁ መሳሪያችን ነው።

ይህች ዓለም በየጊዜው አይደለም የተሰራቺው።አፍሪካም የተፈጠረቺው ሌሎች በዚች ዓለም ያሉት ክፍለ አለሞች በተፈጠሩበት ጊዜ ነው። አፍሪካውያኖችም ሌሎች ክፍሎች ያላቸው ስጦታና ችሎታ እንደዚሁ ጉድለቶች አሏቸው። ከብዙ ሺህ ዘመናት በፊት በአፍሪካ ውስጥ በሌላው ክፍለ ዓለም ካለው ያላነሰ ስልጣኔ ተዘርግቶ እንደነበር ታሪክ ይመሰክራል። በዛው ጊዜ አፍሪካውያን ራሳቸው የቻሉ ነፃና በኢኮኖሚው ረግድም ራሰቻውን የቻሉ ሕዝቦች ነበሩ። ኑሮአቸውና ባህላቸው የተውሶ ያልሆነ የራሳቸው ነበር።ከዚያ በላ አፍሪካ እንደገና እስክትታወቅ ድረስ የተረሳች ክፍለ ዓለም ሆነች። ሆኖም አፍካውያን በመሰላቸው አኳን ኑሮአቸውን ሲከታተሉ ቆዩ። በሌሎች ክፍለ ዓለም የሚኖሩትም ሕዝቦች ዓለም የምትጀምረውም የምታልቀውም በእነሱ ክፍል ብቻ እንደሆነ ቆጥረው ቆዩ።

በአለፉት መቶ ዓመታት በአፍሪካ ላይ የደረሰው ሁኔታ በዝርዝር የታወቀ ስለሆነ መዘርዘር አያስፈልግም። ንቁና ኩሩ የነበሩት የአፍሪካ ሕዝቦች በባርነት ተሸጡ። አገሮቻቸው እንደ ልብ ተከፋፈሉ። ተቆራረጡ። ብዙዎች በቅኝ አገዛዝ ሥር ወደቁ። ጥቂቶቹም በትልቅ መስዋዕትንት ትግል ከቀኝ አገዛዝ ለመዳን ቻሉ። አንዳንድ መሪዎች ከሕዝቦቻቸው በጎነት ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም በማሰብ ብቻ አገራቸው አሳልፈው ሰጡ።

የአፍሪካ ዕድል የቅኝ ገዢዎች ሀብት ማዳበሪያ ሆኖ ሕዝቦቿም የቅኝ ገዢዎች የቀን ሞያተኛ ሆኑ። አፍሪካ የአውሮፓ ሸቀጥ መጣያና የአውሮፓ እንዱስትሪዎች ጥሬ አቅራቢ ሆነች። ገንዘቧን መልሳ በመቶ እጥፍ መግዛት ግድ የሆነባት ዋናው ምክንያት አንድነትና ነፃነት በማጣቷ ነው። በመሸጥ ጊዜ የፈሰሰው ደምና የተሠራው ግፍ ከሳሽ ሆኖ በእግዚአብሔር ፊት ዳኝነት አግኝቶ ለአፍሪካ ነፃነት ብርሃን ለማስገኘት ቻለ።
አፍሪካ ከጨለማ ዘመን ወጥታለች

በዛሬው ጊዜ አፍሪካ ከነዚህ ጨለማ ከሆነ ዘመን ወጥታለች። ክፉ ጊዜ አልፏል። አፍሪካ ከሞላ ጎደል ነፃ ሆናለች። አፍሪካውያኖችም ነፃ ነን እንደገና ተወልደናል። በያንዳንዳችን ትግልና ድካም አፍሪካ ነፃ ለመሆን ትችላለች፡¨አሳባቸውን ሳያወላውሉ በአንድ መንፈስ በመመራት የቅኝ ጭቆና እና ግፍ ለደረሰባቸው ሕዝቦቻቸው ከኮሎኒያሊዝም ሁሉ በዛሬው ቀን ከልብ የሆነ ምስጋናችንን ልናቀርብላችሁ ይገባል። ታሪክም በረዢሙ ይመሰክራል።

እንደዚህ ላለው ከፍ ያለ የሚያኰራ ተግባር ሕይወታቸውን ሙሉ የታገሉ የአፍሪካ ዘር ያለባቸው የአፍሪካን መሬት ረግጠው ያማየውቁ ሰዎች እንዳሉ ይታወሳል፡ ሌሎች ደግሞ አፍሪካ ተወልደው እዚሁ ሕይወታቸውን አሳልፈዋል። አፍሪካውያን ያልሆኑ ሌሎች የሰው ልጆች በጎ ተመኚዎች ሁሉ ፤ሕይወት ያለ ነፃነት ምንም ዋጋ እንደሌለው በሥራቸው አርአያ የሆኑት ሰዎች የፈጸሙት ተግባር ራሱ ስለሚናገርላቸው ብዙ የምንጨምረው ነገር የለም። በኛ ስም እና ለኛ ሲሉ ሕይወታቸውን የሠውት ሁሉ አፍሪካውን በተሰበሰቡት ሥፍራ ሁሉ ስማቸው ሕያው ሆኖ ይኖራል። ልንቆምላቸውም ይገባል።

ሙሉ ዕድልና ድል

በክፈለ ዓለማችን ላይ ሙሉ ድል እና ዕድል ወደ ማግኘት ላይ ደርሰናል።የመጀመሪያ ተግባራችን አድርገን የምንቆጥረው ገና የነፃነት መብት  ተነፍጎአቸው የቅኝ አገዛዝ ጥላ የሚያንዣብብባቸው ወንድሞቻችን ነፃ ወጥተው ከመካካላችን እንዲገኙ ማድረግ ነው። የተቀደሰ ግብ ለመድረስና ሙሉ ድልን ለመጨበጥ ተቃርበናልና ሳናመነታ ወደ ላይ አውለን ትግላችነን ማጠናከር ጊዜው አሁን ነው። ለአፍሪካ ነፃነት የረዱትንም ሁሉ ልንረሳቸው አይገባም።

በአፍረካ ውስጥ አንድ አገር እንኳ ነፃ ሳይወጣ ቢቀር የኛም ነፃነት የተሟላ ሲሆን አይችልም። በሮዴሺ ፤አንጐላ፤በደቡብ አፍሪካ፤በሞዛምቢክና በሌሎችም ቅኝ አገሮች የሚኖሩት ወንድሞቻችን ሙሉ እርዳረታችንን እንድንሰጣቸው በመጮህ ላይ ይገኟሉ። ይህ ልመናቸው ሊታለፍ ከቶ አይገባም።ባፋችን እንርዳ እያልን በሥራ ባንገኝላቸው እንደ ክህደትና የሰው ደም እንደ ጎርፍ ሲፈስ ዝም ብሎ በቃል መደለል ሆኖ አይቆጠርብንም? በርቱ ተስፋ አትቁረጡ ፤መላው አፍሪካ ድጋፋችሁ ነው፤ ነፃነታችሁ ተቃርቧል ማለት ይገባል።ደም ሳይፈስ  እንዲፈጸም ጠበቃ ሆነን  እንድንነጋገርላቸው። በመስማማት፤ባይሆን የነሱን ደም ከደማችን እንዲቀላቀል ካላደረግን በምክር እያጣላን ዝም ብንል አሳፋሪ ሽሽት ይሆንብናል።
ቂም መያዝ አይገባም


አፍሪካ በሙሉ ነፃ እንድትሆን የገባነውን ቃል ኪዳን እንደገና ስናድስ ባለፈው ጊዜ በደረሰብን በደል ቂም መያዝ አይገባንም። የቅኝ ገዥዎች በጭቆና ያስተዳደሩ በነበረበት ጊዜ የሠሩት ሥራ ሁሉ ለራሳቸው መጠቀሚያ ቢሆንም አሁን ለአፍሪካውያን አገልግሎት ስለዋለ ያለፈውን ወደ ጎን ትተን ለወደፊቱ እንድከም። ባሉፈት ዘመናት ከበደሉን ጋር በሰላምና በመግባባት በሰላም  ለመኖር እንሞክር። ጥላቻን እና ቂምን እንተው፤ቂም በቀልን መሣሪያ እናድርግ፤ ሥራችንና ቃላችን ከኛ ከአፍሪካውያን የተያየዛ ይሁን። ጥረታችንን ሁሉ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር በመተባበርና መረዳዳት ለመፍጠር ይሁን። ራሳችንም ይህን እላይ የተናገርናቸውን አድርገን ክብርና ጥቅም አግኝተንበታል ይመስለናል።

ስለ ወደፊቱ እናስባለን

በዛሬው ቀን ተረጋግተን በሙሉ እምነትና ድፍረት ስለ ወደፊት እናስባለን። ዛሬ የምናስበው ለነፃይቱ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ስለ አፍሪካ አንድነት ነው። ስለዚህም በምናስብበትና በምንሠራበት ጊዜ ያለፈው ታሪክ ትምህርት ሊሆነን ይችላል።በጐሳ ፤በሃይማኖትና በባህል ልዩነት አንድንትን ለመፍጠር እንቅፋት ሊሆን እንደማይችል ብዙዎች ምሳሌዎች አሉ።

አንድነት ሃይል እንደሆነ እናውቃለን መለያየት ግን ደካማነትን የሰው መሣሪያነትን እንደሚያስከትል እናውቃለን። በመካከላችን ሊኖር የሚችሉትን ጥቃቅን ልዩነት ወደ ጎን ትትን ሁላችንም ለሚያስተባብረን ለአፍሪካ እንድነት መድከም አለብን። እርስ በርሳችን መነታረክ ትርፉ የሌላ ሲሳይ መሆን ነው።

ስለ አፍሪካ አንድነት ብዙ ተሠርቷል

በአፍሪካውያን መካከል አለመግባባት ስላለ የአፍሪካን አንድነት ከግብ ለማድረስ አይቻልም የሚሉ ብዙዎች አሉ። ነገር ግን የአፍሪካን አንድንት ከግቡ ለማድረስ ብዙ ነገር ተሠርቷል፤ተጀምሯል። ባለፉት ጥቂት አመታት በልዩ ልዩ ሥፍራዎች ልዩ ልዩ ከፍ ያሉ ጉባዎች ተደረገዋል።ልዩ ልዩ ወስኔዎችም ተወስደዋል።በዚህ በበተደረጉ ጉባዎች ላይ የተወሰዱ ውሳኔዎች ጥቂት የተለዩ ቢሆንም በመሠረቱ ሁሉም የአፍሪካን አንድነት  አላማ ይደግፋሉ። ልዩነት ቢኖር ስለ ግቡ ሳይሆን እግቡ ለመውሰድ የሚወስደው አርምጃና ዘዴ ነው። ስለ ዘዴው ልዩነትም ስለመኖሩ የታወቀ ነው። ይህ ልዩነት ቢኖርም የህን ያህል ትልቅ የሆነና ከመስማማት የሚያግድ ከባድ ልዩነት አይደለም። የአሳብ ልዩነት ቢኖርም የነፃይቱ አፍሪካ የወደፊት ዕድል እንዳለፈው የአውሮፓ ዕድል እንዳይሆን ሁላችንም የተስማማንበት ነገር ነው። አፍሪካ የበለጠ አንድነታችንም የተስማማንበት ነገር ነው።እኛ አፍሪካውያን አንድነታችንን  የበለጠ ማጠናከር አለብን።
በጐሣ መለያየት የአገርን አንድነት ያፈርሳል

የያንዳንዱም አፍሪካ ታማኝነት ለጐሣው ለመንግሥቱ ሳይሆን ለአንዲቱ አፍሪካ እንዲሆን ይገባል። በጐሣ መለያየት ያገርን አንድንነት የሚያፈርስ ነው። እኛው እርስ በርሳችን በጎሣ የምንጯጯህ ስንሆን የበለጠ ሁከት ተፈጥሮ እስከ ደም መፋሰስ ስንደርስ በራሳችን ላይ ጉዳትን አድርስን አገራችንና ዓለማችንን ለገላጋዮች ሲሳይ ማድረግ ይሆናል። ይህም ባለንበት ጊዜ በኮንጎ ደርሶ የታየ ነው። ኮንጎ አሁን ከዚህ ችግር መዳኗን ሳይሆን በዚህ ጠንቅ የቱን ያህል ጉዳት እንደደረሰባትና የኢኮኖሚዋም ዕድገት ብዙ  አመታት ወደ ኋላ መጐተቱን መገንዘብ አለብን። ይህን አለማድረግና ከአፍሪካ ይልቅ ለጐሣ ታማኝነትን ማጠናከር የአፍሪካን አንድነት ዓላማ ማሰናከል ይሆናል። ይህን አሠራራ ደግፍን መራራ ውሃ ከመጠጣት እንዳን።

ስለ አፍሪካ አንድነት በምንሠራበት ጊዜ በአንድ ጊዜ የፖለቲካ አንድነት መፍጠር የማይቻል መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል። በአሁኑ ጊዜ የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተለያየ የፖለቲካ አስተዳደር፤ኢኮኖሚና የሶሻል ሥርዓት ስላላቸው እንዚህን በአንድ ጊዜ ለማስተካከልና የንግድና የፊናንስ ድርጅታችንን ለማዋሐድ አዳጋች መሆኑ የታወቀ ነው። በአሁኑ ጊዜ በዱሮዎቹ አዋቂዎች የተያዙትን ሥራዎች በሙሉ በአፍሪካውያን ለመተካት ያዳግታል፡ባሠራርም ታይቷል።ከብዙ ጊዜ ሲያዝ የመጠውና ከሌሎች አገሮች ጋር ያለውን የንግድና የኢኮኖሚክ ግንኙነት ባንድ ጊዜ ማቋረጥ ትልቅ ችግር ይፈጥራል። በአሁኑ ጊዜ አፍሪካውያን የአገራቸውን ሃብት ለማዳበር ከአገር ውስጥ በቂ ካፒታል ለማግኘት አይቻልም። በአገር ውስጥ የሚገኘውን ካፒታል በሥራ ላይ በሚገባ ለማዋል ስምምነና መረዳዳት ያስፈልጋል። የዚህም መንግዱ ተከፍቷል እና አግባቡን እንወቅበት፡
የመሸጋገሪያ ጊዜ ያስፈልጋል
 
ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላ በምንሸጋገርበት ጊዜ የምንወስደው እርምጃ የተረጋገጠ እና ወደፊት መሆኑ ቀርቶ  ወደ ላ እንዳይሆን ማወቅ አለብን። የመሸጋገሪያ ጊዜ እንደሚያስፈልግ የታወቀ ነው። ከቀድሞ የነበረውን ባንድ ጊዜ ለመተው ያዳግታል። እንዳልተወውም ይታያል፡ አሁን ካለንበት ደረጃ ወደ አፍሪካ ፍጹም እስክንሸጋገር ድረስ በአፍሪካ ያሉ ልዩ ልዩ አገሮች እንደመረማመጃ የሚያገለግል ሪጂናል የሆነ የሕብርት ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆናል። እንደዚህ ያለው ሕብረት ለመጨረሻው ግባችን ለአፍሪካ አንድነት መሣሪያ መሆን አለበት እንጂ ራሱ የመጨረሻ ግብ መሆን የለበትም።

ባሁኑ ጊዜ አፍሪካውያን የሚስማሙበት ብዙ ጉዳዮች ኡሉ። የሚጐድለን አፍሪካውያን በአንድ ድምፅ የሚናገሩበትና ውሳኔያቸው መፈጸሙን የሚከታተል ድርጅት ነው። በአሁኑ ሰዓት ወሬ የሚያትቱ ሁሉ ስለሞንሮቢያ ቡድን ስለ ካዛ ብላንካ ቡድን ስለ ብራዛቢል ቡድን እያሉ ሲያወሩ ይታያሉ። የመጀመሪያው ተግባራችን ይህን ልዩነት ማስወገድ ነው።

አሁን የሚያስፈልገን የአፍሪካ ድምፅ በሕብረት የሚሰማበት የአፍሪካ ግር የሚጠናበትና የሚወገድበት በአፍሪካውን መካከል የሚፈጠር አለመግባባትና በሰላም የሚወገድበት የጋራ መከላከያ እርምጃ የሚወሰድበት በኢኮኖሚክና በካልቸር የመተባበር እርምጃ የሚወሰድበት ድርጅት ማቋቋም ነው።

ዛሬ እዚህ የተሰበሰብነው የአፍሪካን አንድነት መሠረት ለማስገኘት ነው። ይህ አህጉራችን አንድነቱን አግኝቶ በሰላምና በመግባባት እየደረጀና እየበለጸገ እንዲሄድ ለማድረግ የሚያስችለውን አንድ መሠረታዊ ነገር ለማግኘት አሁኑኑ በዚህ ስብሰባችን ላይ ልንስማማበት ይገባናል። ይህ ስብሰባችን በአህጉራችን የሚፈለገውን እውነተኛ ውጤት እንዲያስገኝ የሁላችንም አሳብና ግዴታ መሆኑን ስለምናምን ዛሬ ልንፈጽመው የሚገባንን ተግባር በማዘግየት ወይም ለሌላ ጊዜ በማስተላለፍ ጊዜያችንን ሳናጠፋ አንድ ቀዋሚና ዘላቂ የሆነ ድርጅት መፍጠር አለብን። ስብሰባችን የአፍሪካ አንድነት የሚመሠረትበትን ቻርተር ለማጽደቅ ሳይስማማበት ሊበተን አይገባውም። ከፍ ብለን የዘረዘርናቸውን ተግባሮች የሚፈጽም አንድ የአፍሪካ ድርጅት እንዲቋቋም ሳናደርግ ልንለያይ አንችልም። ይህን ሳናደርግ ብንቀር ለአፍሪካ ያለብንን አላፊነትና እምነታቸውን ለጣሉብን ሕዝቦቻችን ያለብንን አደራና ተግባር እንዳልፈጸምን የሚያስቆጥረን ይሆናል። በዚህ ጉባኤ ተሰብስበን መገኘታችን ተገቢ የሚሆነውና ተግባራችንንም በትክክል እንደፈረምን የሞቆጣጠረው የአፍሪካ አንድነት የሚመሠረትበት ድርጅት አቋቁመን የተገኘን እንደሆነ ብቻ ነው።

እንሥራው እያልን የምንመኘው ሁሉ በልዩ ልዩ ክፍል ዓለማት ተሞክራል ተሠርቷልም። ለምሳሌ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካን እና የሶቪየት ሕብርትን መጥቀስ ይበቃል። እኛም ያዛልቃል የምንለውን ዓለማችንን በፕሮግራም አድርገን ፕላናችንን ፍጻሜ ለማድረስ ቆርጠን እንነሳ።ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ስንት ዘመን እንደፈጀ እናስተውስ። መሠረት ከተጣለና መልካም ገንቢ ካለ ጥሩ ቤት ይሰራል።

የአፍሪካ የወደፊት ዕድል በአንድ ዓይነት የፖለቲካ አንድነት ላይ መመሥረት እንደሚገባው የተጋለጠ ነው። ነገር ግን ይህ አንድነት ምን መልክ  ምን መልክ እንደሚኖረው የተጣራ አስተያየት ገና አልቀረበም። የምናስበው የአፍሪካ አንድነት የፌዴራል አንድነት ነው። ወይስ ፍጹም አንድነት? የያንዳንዶቹ አገሮች መብት ይቀንሳል? ምን ያህል? በምንስ ረገድ? በልዩ ልዩ የአገር ክፍሎች እንጀምራለን? ወይስ በአንድነት ነው? ወይስ ፍጹም አንድነት? የያንዳንዶቹን አገሮች እንጀምራለን? ወይስ በአንድ ጊዜ ለመላው ከአፍሪካ የሚሆን የፖለቲካ ሲስተም እናቋቁማለን? አንድ አርምጃ ሳንወስድ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ የምንጠብቅ የሆነ እንደሆነ የሚመጣው የአፍሪካ ትውልድ ሁኔታው ምንም ሳይሻሻል ክርክሩ እንደቀጠለ ይደርስበታል።

በኢትዮጵያ በኩል ምንም እንኳን የሚወሰደው እርምጃ የተፈለገውን ያህል ፈጣን ባይሆንና የተወሰነም ቢሆን እርምጃ እንዲወስድ በሙሉ ትደግፋለች። እያንዳንዱ እርምጃ ወደ ግባችን ከማቅረቡም በላይ ቀጥሎ የሚወስደውን እርምጃ የቀለለ ያደርገል።ቅኝ ገዢዎች በአፍሪካውያኖች በልዩ ልዩ ወገን ተከፋፍለው በጥቃቅን ነገር እየተነታረኩ ለአፍሪካ አንድነት አንዳችም እርምጃ ባለመውሰዳቸው እጅግ እንደሚደሰቱ ማወቅ ቀለብን።

በዴሞክራቲክ አሠራር እናምናለን

የየአገሮቻችን የውስጥ አስተዳደር የተለያየ ቢሆንም ሁላችንም በዲሞክራቲክ አሠራር ልናቋቋም በምንፈልገው ማህበራችን እንዲሠራ እናድርገው። በዚህ ውስጥ በፖለቲካ በመከላከያ በኢኮኖሚክና እንዲሁም እርምጃ ልንወስድ እንችላለን። ይህም ማሕበር በሚገባ ሊሠራ የሚችልበት ክፍል የሕዝቦቻችንን መላ ሕይወት የሚመለከት ነው። በተሰማማንባቸውና እርምጃ ሊወሰድባቸው በሚችሉ ጉዳዮች ላይ መሥራት ከተቻለ ለአፍሪካ አንድነት ያለን ጽኑ ፍላጐት ከጊዜ በላ በሌሎችም ጉዳዮች አሁን ስምምነት ባልተገኘባቸው ላይ ወደፊት እንድንሰስማማባቸው ያስገድደናል።

የዛሬን ጸሎት መስዋዕት እናድርግ

የምናቋቁመው ድርጅት በደንብ የተጠናቀቀ ቀዋሚ የሆነ ጽሕፍት ቤት እንዲኖረው ያስፈልጋል። በማህበራችን ውስጥ ልዩ ልዩ ሥራዎችን የሚመለከቱም ክፍሎች እንዲቋቋሙ ያስፈልጋል። በኢኮኖሚክ በኩል ለምሳሌ ሊወሰዱ የሚችሉ ብዙ እርምጃዎች አሉ። አፍሪካውያኖች ከብዙ ትግልና መስዋዕትነት በላ ያገኙትን ፖለቲካ ነፃነት በስም ብቻ ይዞ መቀመጥ አይቻልም። ይህ በእጃችን የጨበጥነው የፖለቲካ ነፃነት በኢኪኖሚክና በሶሺያል ዕድገት ካልተደገፈ በስተቀር ክፍ ያለ አደጋ ላይ ሊጥለን ይችላል። የሕዝቦቻችነን የኑሮ ደረጃ ለማሳደግና የፖለቲካም ነፃነታችንን በኢኮኖሚክ ብልጽግና   ለመደገፍ በምንጥርበት ጊዜ የውጭ ዕርዳታ እንደሚያስፈልገን የታወቀ ነው። እነርሱም እርስ በርሳቸው ተረዳድተዋል። ነገር ግን ዋናውን ተግባር መፈጸም ያለብንን እኛው አድርገን የሚቀጥሉት ትውልዶች በሰው ትክሻ ላይ ከመኖር እንዲድኑ ከዛሬ ጀምሮ ማድረግ አለብን።

ኢኮኖሚ የሚመለከት

አንድ የመላውን አፍሪካ የኤኪኖሚክ ሁኔታ የሚመለከት ድርጅት ማቋቋም ከሚፈጽማቸው ሌሎች ተግባሮች በስተቀር በተጨማሪ በአፍሪካ አገሮች መካከል ረገድ በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ መለዋወጥ ለማሳደግ አሁንኑ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። አፍሪካ ያለው ማዕድን ሀብት እጅግ ከፍ ያለ ስለሆነ በሙሉ ልንጠቀምበት እንድንችል ማድረግ አለብን፡ እያንዳንዱ የአፍሪካ አገር የተፈጥሮ ሁኔታው የሚፈቅድለትን የልማት ሥራ በማሰብ አንድ ጠቅላላ የሆነ የአፍሪካ የልማት ፕሮግራም ማሰናዳት በጣም ጠቃሚ ነው። አፍሪካውያን እስካሁን በየክፍለ አገራቸው አሰናድተዋል ብለን እናስባለን። እኛም ካስናዳነው ጋር በአንድነት ተሰብስበን እርስ በርሳችን እየተመካከርን እንጠቀምበት።
የመገናኛ ዘዴ

ሌላው ዓይነት እርምጃ በአፍሪካ አገሮች መካካል ያለውን መገናኛ ማሻሻል ነው ንግድ ሊስፋፋ የሚችለው መገናኛ ሊኖር ነው። በዛሬው ጊዜ በአንድ የአፍሪካ ክፍል ወደ ሌላው በፍጥነት ለመሄድ ሲፈለግ አዳጋች ነው።በአፍሪካ አገሮች መካከል ያለው የቴሌፎንና የቴሌግራም ግንኙነት ሁሉ በዙሪያ መንገድ ነው። በአፍሪካ አገሮች መካካል የመንገድ ግንኙነት ብዙም የለ።ቢኖርም እጅግ ግንኙነት እጅግ አነስተኛ መሆኑ አያስገርምም። ይህን አሳዛኝ ሁኔታ የፈጠረው የቀድሞው አስተዳደር ውርስ ነው።
የአፍሪካ የጋራ የመከላከያ ድርጅት

አፍሪካ የራስዋ የጋራ መከላከያ ድርጅት እንዲኖራት አንድ እርምጃ ሊወስድ ይገባል። በዚህ ረገድ  ተባብረን መሥራት ይኖርብናል። አፍሪካን ደግሞ በመከላከያ ረገድ ራሷን እንድትችል ከተፈለገ አንድ ዓይነት የመከላከያ ድርጅት እንዲኖር ያስፈልጋል። ማናቸውም የአፍሪካ አገር የጦር ወረራ ሃይል የሚያሠጋው ቢሆን ዕርዳታ ለማግኘት የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር ይገባል። ነፃነታችንን እየጠበቅን ከምዕራባውያን ከምሥራቅም ተስማምተን መኖር ግዴታችን ነው።

አፍሪካ ነፃነቷን ያገኘቺው ከፍ ባለ ትግልና ብዙም ችግር አልፋ ነው። ከችግሮቹም ዋናው በቂ የተማሩ ሰዎች አለመኖር እርስ አለመተዋወቅ ነው። ከአፍሪካ ውጭ የሚገኝ ትምህርት በአፍሪካ ውስጥ ሊሰጥ ስለሚገባው ትምህርት ለጊዜው መተኪያ ሊሆን አይችልም፡ ድንቁርናን ከአፍሪካ ለማስወገድና ለልማት ሥራችንም ከፍ ያለ ችሎታ ያላቸው ሰዎች በብዛት ለማድረስ ብቻ ሳይሆን እርስ በርሳችንም ለመተዋወቅ እንዲረዳ አንድ ሰፋ ያለ የትምህርት ፕሮግራም እንዲኖረን ያስፈልጋል። በዚሁ መሠረታዊ ዓላማ በመመራት ኢትዮጵያ ከጥቂት ዓመታት በፊት ለመላው የአፍሪካ አገሮች ወጣቶች የሚያገለግል እስኮላርሽፕ ሰጥታለች።ይህም እስኮላርሽፕ ለተጠቀሙበት ብቻ ሳይሆን እኛምንም ኢትዮጵያኖችን የቀሩትን የቀሩትን የአፍሪካ ወንድሞቻችንን የበለጠ ለማሳወቅ ስለረዳን የቀሩትም የአፍሪካ አገሮች በየችሎታቸው መጠን የእስኮላርሽፕ ፕሮግራም እንዲሠረቱና እንድንለዋወጥ አደራ እንላለን።"
                                      
ንጉሡ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ፤ የአፍሪካውያንና የኢሲያውያን ድምፅ፤ የቅኝ አገዛዝ መሠረቱ የተሳሰተ እና ምንጩ ምን እንደሆነ እና እንዴት መከላከል እንደሚቻል፤ መሠረታዊ የአህጉሪቷ አምነትና ዓላማን በሚመለከት፤ እንዲሁም የዘር ልዩነት አንዴት ማቆም እና በጋራ መቃወም እንደሚቻል፤ በሃያላን አገሮች የተከማቸው የኒኩልየር መሳሪያዎችና ቅመሞች በአፍሪካ ሰማይ ላይ እያንዣበበ የወደፊት ጠንቅ እንዳይሆን እንዴት መከላከል እንደሚቻል፤ ወደ አፍሪካ የሚጐርፉ የጦር መሣሪያዎች አላስፈላጊ ሥራ ላይ እንዳይውሉ እንዴት መቆጣር አንደሚቻል በዝርዝር ገልጸው ወደ ድርጅቱ  ምስረታ አዲስ አበባ የመጡ 3ሺህ እንግዶች ከግንቦት 14 ቀን እስከ ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም የቆየው ጉባኤ  መሪዎቹ በፊርማቸው መሥሪያ ቤቱ አዲስ አበባ እንዲሆን ተስማምተው ፈርመው የድርጅቱ መተዳደሪያ ቻርተር/ደምብ በማጽደቅ በአፍሪካ ሰላምና ወንድማማችነት እንዲፈጠር የጋራ ራዕይ እንዲኖር


የኢትዮጵያ ንጉሠነገሥት ቀዳማዊ ይለስላሴ ከማንኛቸውም አፍሪካዊ መሪ የጐላ አስተዋጽኦ በማድረጋቸው ከመላው ዓለም አገሮች 101 የተለያዩ የኒሻን/መዳሊያ ሽልማቶች ባንገታቸው የሚጠለቅ እና በደረታቸው የሚለጠፍ የምስጋና መአረግ ተሰጧቸዋል። ይህ የአገሪቱ ክብር እና ጥረት ዓለም ሲያውቀው፤ወያኔ በለመደው ቆሻሻ ባህሪው አጣጥሎታል። ስለሆነም በኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ ምርጫ ሃውልቱ ለንጉሡ እና ለጠቅላይ ሚኒስትራቸው ለአክሊሉ ሃብተወልድ እና ለጋናው ፕረዚዳንት ኮዋሚ ንኩርማ ሦሰት የክብር መታሰቢያ ሃወልት እንዲቆምላቸው ይጠይቃል።
ወያኔ በብልሹ ታሪኩ ይጓዛል፤ እኛም ብልሹ ታሪኩን እየዘገብንለት ነው። ታሪክም እኛም እየተቀበለ እየዘገበን ለመጪው ትውልድ ቃላችን እያሰተላለፈ ነው።

ጊዜአችሁን መስዋእት አድርጋችሁ ሳትደክሙ ይህ ጽሑፍ ላነበባችሁ ዜጎች ሁሉ አመሰግናለሁ።Haileselassie the lion of Africa who refuses to die ጌታቸው ረዳ www.ethiopiansemay.blogspot.com