Wednesday, December 18, 2019

እስክንድር ነጋ በቁጭትና በተስፋ መካካል ያሉት የቅደም ተከተል ሚናዎች ኦክላንድ ካሊፎረኒያ ተገኝቶ ያብራራበት ትዝብቴ ጌታቸው ረዳ (አትዮ ሰማይ ETHIO SEMAY)


እስክንድር ነጋ በቁጭትና በተስፋ መካካል ያሉት የቅደም ተከተል ሚናዎች ኦክላንድ ካሊፎረኒያ ተገኝቶ ያብራራበት ትዝብቴ
ጌታቸው ረዳ (አትዮ ሰማይ ETHIO SEMAY)

ፎቶ ጌታቸው ረዳ በግፍ ለተጨፈጨፉት 86 ዜጎቻችን የሕሊና ጸሎት ሲደረግ ኦክላንድ ካሊፎረኒ

በመጀመሪያ የምጠይቀው ይቅርታ ‘የኢትዮ ሰማይ’ አንባቢዎቼ ሰሞኑን ያለምንም ጽሑፍ ትቼአችሁ ስለሰነበትኩ በልዩ የትምሕርት ጥናት ተጠምጄ ስለነበር ይቅርታ እጠይቃለሁ።

ይህ ካልኩ ዘንዳ፤ ወደ ሰሞኑ ክንዋኔ ልውሰዳችሁ። ኦክላንድ ካሊፎርኒያ ታሕሳስ 4 ቀን 2012 (ቅዳሜ ዲሰምበር 14/2019) የኢትዮጵያ ተስፋ የሆነው ታላቁ እስክንድር ነጋ ከሳንሆዘ፤ ከሳንፍራንሲስኮ፤ ኦክላንድ እና በበይ ኤሪያ የሚገኙ ከተለያዩ  አካባቢያዊ ከተሞችና  ከኔቫዳ ድረስ ነድተው የመጡ ኢትዮጵያውያንን ለማነጋጋር መጥቶ በነበረበት ጉብኝት ተገኝቼ በጣም ከማከብረው እስክነድር እና ለበርካታ አመታት ወያኔን ለመጣል ሲጀመር ጀምሮ አብረን ስንታገል የቆየነው ወዳጄ የጥንቱ የጥዋቱ “ሺመልስ ለገሰን” በማግኘቴ የደስታየ መጠን ወስን አልነበረውም።

(ሺመልስ ማለት ወያኔ ያዋረዳትን ሰንደቃላማችንን ከወደቀቺበት አንስቶ ዛሬ ሚሊዮኖች እንዲያውለበልብዋት ያደረገ በታሪክ ማሕደር የተመዘገበ አርአያችን የሆነ ታጋይ ነው) ፤

ወደ ሓተታየ ከመግባቴ በፊት እኔ እና እስክንድር ከሺመለስ ጋር የተነሳነው የማስታወሻ ፎቶግራፍ ያነሳችሁን በርካታ ወገኖች እባካችሁ ፎቶግራፉን በሚቀጥለው መጽሐፌ እንዳሳትመው ስለምፈልግ ከስር ባለው ኢመይል አድራሻ ብታገኙኝ እና ብትልኩልኝ ዋጋ የሚከፈል ከሆንም ለመክፈል ደስተኛ ነኝ።

አሁን ወደ ሓተታው።

ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አድካሚ የሆኑ ካገር ወደ አገር ረዢም የበረራ ሰዓቶችን በመቋቋም እስክንድርና ሺመልስ ሁለቱም ኦክላንድ ድረስ መጥተው በነበሩበት ወቅት ሕዝቡን በሚያስመሰግን መስተንግዶ ያስተናገዱ የስብሰባው አስተናጋጅ አባሎችና አዳራሹን ለመሰብሰቢያ የፈቀዱት ኦርቶዶክስ ቤተክርሰትያን ሃላፊዎች ለማመስገን እፈልጋለሁ። አንዱ ካንዱ ለይቶ ለማመስገን ባይቆጠርብኝ የዝግጅቱ አባሎች ዋና የመድረክ አስተባባሪ የነበረው “የሎሬት ጸጋየ ገብረመድህን “እናት አገር ጠኑ” የተሰኘው ትያትር መድረኩ ላይ በማቅረብ በሚገርመው የተዋናይ ችሎታው የብዙውን ተሰብሳቢ ልቦና በመሳብ እምባ እንድናቀርር ያደረገው ተዋናይ የኪነት ሰው “ተስፋየ ሲሞ” ልዩ አድናቆቴን ሳልገልጽለት አላልፍም።

እስክንድርን የማውቀው በሩቅ ነበር። ከተገናኘን በኋላ ግን በሚዲያ ላይ የምጽፋቸው ፖለቲካዊ ክርክሮቹ እየተከታተለ ሲያነበኝ እንደነበር አድናቆቱ ገልጾልኛል። እስክንድር እጅግ ሲበዛ ትሁት እና ቀና ሰው ነው። በ28 የትግል ዘምን ውስጥ ብዙዎቹ የፖለቲካ መሪዎች አግኝቼ አነጋገሬአለሁ። እስክንድር ነጋ የሚያክል ትሁት ግልጽና ምጡቅ ፖለቲከኛ ገጥሞች አያውቅም። እስክንድርን ከመተዋወቅየ በፊት የባለደረባው ትግል ብደግፍም እርሱን ካገኘሁ ወዲህ ደግሞ እስክንድርን ለመደገፍ የመረጥኩባቸውን ምክንያቶቼ ይበልጥ ትክክለኛ እንደነበርኩ አረጋግጫለሁ።

እስክንድር የመድረክ ንግግሩን ከጨረሰ በኋላ የነበረው የሕዝቡ ስሜትና አበረታችነት በተለይም የአካባቢያችን የባልዴራስ አመራሮችን/ተወካዮችን ፈቃደኞች እጃቸው እንዲያወጡ ሲጠይቅ ያላንዳች ማንገራገር ተሽቀዳድመው ፈደቃደኛነታቸው ያሳዩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች እጅግ ኮርቼባቸዋለሁ።

እዚህ ላይ በዚህ ትችቴ ላይ በብርቱ ሳልወቅሳቸው ሳልጠቅሳቸው የማላልፍቸው በርካታ የካሊፎረኒያ /የቤይ ኤሪያ/ ምሁራን የት እንደገቡ ከገረመኝ ገጠመኝ ነው። ድሮም እምየ ኢትዮጵያ በመከራዋ ጊዜ የሚደርስላት ብዙውን ጊዜ ድሃው ነው። የሚበደለውም ግፍ ቀማሹም ቁጭት እና እልክ የሚይዘውም ያው 'መንግሥቱ ሃይለማርያም' እንዳሉት “እየታነቀ ወደ ትግሉ የሚገፈተረው የድሃው ልጅ ነው”፡ በዚህ ሌላ ቀን አምለስበታላሁ። ግን ታዘብኳችሁ!
ድሃ ውለህ ግባ! አኮራኸኝ!

አሁን  በቁጭትና በተስፋ መካካል ያሉት የእስክንድር ነጋ የቅደም ተከተል ሚናዎች ኦክላንድ ካሊፎረኒያ ተገኝቶ ያብራራበት ትዝብቴ ላስነብባችሁ።

ውቅያኖስ አቋርጦ እኛን ያነጋገረበትን መብት አገር ውስጥ ሕዝብ ሰብስቦ ማነጋገር እንደማይችል ከፍተኛ ሐዘንና ጥልቅ ትካዜ በወተዋጠበት ሁኔታ እራሱን ከስሜት ለማውጣት እየታገለ በታየበት ሁኔታ ሲገልጽ የተሰማኝ ውስጣዊ ቁጭትና ሓዘን እራሴን ከውስጥ እየቆነጠጥኩ ነበር ያደመጥኩት።

እስክንድር እንዲህ ይላል።

 “ብዙ ዋጋ ከፍለን የህወሓት አምባገነን ሥርዓት ፈርሷል። ዛሬ የሱዳኑ አልበሸርን ለማስወገድ ከተከፈለው መስዋዕትነት የህወሓት ሥርዓት ለማስወገድ በብዙ ዕጥፍ በላይ ዋጋ ከፍለናል። ሱዳን ውስጥ ዛሬ ያለምንም ክልከላ ሕዝባዊ ስብሰባ ማድረግ ይቻላል። እኛ የበለጠ ዋጋ ከፍለን ግን ስብሰባ ማድረግ አንችልም። ይኼ “ናሺናል ትራጀዲ” (ብሔራዊ የልብ ስብራት) “ቪሸስ ሰርክል”) ጭራቃዊ አዙሪት ነው። ልንሰብረው በማንችል በእንደዚህ ዓይነት አዙሪት ውስጥ ሆነን ነው ስብሰባ ማድረግ ሰለተከለከልን ወደ እናንተ መጥተን የሓገራችሁን ሁኔታ ለማሳወቅ እዚህ እናንተ ጋር ምን ብናደርግ ይሻላል ለማለት ለመመካከር የመጣነው::” በማለት ልቡ በሓዘን እየተከበበ ሁላችንን በስሜት አሻግሮ ጥልቅ ትካዜ ውስጥ እየጣለ እንደገና ስሜታችንን እየተቆጣጠርን ወደ ጥንካሬአችን እንድንመለስ በሚመስጥ የነገሮችን ቅደም ተከተል በማስቀመጥ አገሪቷ የተጠናወታት “ጭራቃዊው አዙሪት” ለመስበር ምን መደረግ አለበት በሚል ሁለት ቅደም ተከተል ያስቀመጣቸው ነገሮችን እንድናተኩር እንዲህ አስቀምጦአቸዋል።

(1)  ቁጭት
(2)  ተስፋ 

   የነዚህ ቅደም ተከተል እንዲህ ያስቀምጠዋል። “በአሜሪካ ሃገር በዞርኩባቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎች ከገመትነው ሕዝብ በላይ መመጣቱ ነው። ስብሰባ በጠራንባቸው ከተሞች ለምንድነው እንዲህ ያለ ብዛት ያለው ሕዝብ በመጉረፍ ድጋፉን ያሳየን የሚል እራሴን ስጠይቅ ያገኘሁት መልስ  “እኛ የተነሳንበት መነሻ የአዲስ አበባ ጉዳይ የኛ የመላው ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነው የሚል ሲሆን ሁለተኛው ቀጥተኛ ምክንያት ደግሞ “በስፋት የተካሄደው ግድያ ጉዳይ ስላስቆጫችሁ ነው” የሚል ነው።  የተፈጸመው ግድያ ገዳዮችን በነፃ ያለምንም ሕጋዊ ተጠያቂነት እየተንቀሳቀሱ ግድያዎችን ማከናወናቸው ሕዝባችን በጣም አስቆጭቶታል። ይህ እናንተን እልክ ውስጥ አስገብቶአችኋል።….

…እንግዲህ ወደ ኋላ ወደ ሕሊና እስረኞች ጉዳይ ልመልሳችሁ ነው። ይልና እስክንድር ‘-
“እንደምታውቁት የተለያዩ ዜጎቻችን  በሽብር ተግባር ተጠርጥረው  ያለምንም ማስረጃ ባልሰሩት ወንጀል ሰብአዊ መብት የሚጥሱ ምርመራዎች ተፈጽሞባቸው ማስረጃ ስላለተገኘባቸው “በነፃ ተለቅቀዋል” የሚል ‘ምስክር ወረቀት’ ተሰጥተው ተፈትተዋል። በአንጻሩ ብዙ ዘግናኝ ግድያዎችን የፈጸሙ ነብሰገዳዮች በሕግ አልተጠየቁም። ይህ ብዙሓኑ ሕዝባችን “ድብን አድርጎታል”። ቁጭት ውስጥ ከትቶታል። እልህ ውስጥ ከትቶታል።እናንተ አገር ውስጥ ያለው የቁጭቱ ማሳያ መሰተዋቶች ናችሁ

ሕዝባችን እና እናንተን ያስቆጫችሁ ባንድ አገር ውስጥ ሁለት ወገን መኖሩን አስቆጭቶአችኋል። አንዱ ወንጀል ይፈጽማል፤እጁን በደም አጥቦ ሲያበቃ የሕግ ከለላም ይደረግለታል፤ከዚያም አልፎ ሽማግሌ ይላክበታል። አንዱ ወገን ደግሞ ሰላመዊ ዜጋና ሕግ አክባሪ፥ ወጀል ሳይፈጽም በሽብር ወንጀል እየተከሰሰ ከተሰቃየ በኋላ በነፃ ይሰናበታል። ባሕርዳር በተፈጸመ ወንጀል እዚህ አዲስ አባባ ያሉት ወንጀለኞች ተብለው ታስረዋል። ስለዚህም ሕዝባችን እናንተን ወደየ አዳራሹ ያመጣቸሁ “ቁጭት” ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ቁጭት ብቻውን ሳይሆን “ተስፋም” አለ። ተስፋ!

እንግዲህ ቁጭትና ተስፋ ሰንቃችሁ ነው ወደ እዚህ አዳራሽ የመጣችሁት። ባለንብት ሁኔታ እነዚህ ሁለት እምርታዎች እንደ ቀበቶቻችን ይዘናቸው ወደ ፊት ስንጓዝ የትኛውን ነው አጉልተን ወደ ረዢሙ ጎዳና እንዲያሸጋግረን ታጥቀነው የምንገሠግሠው? የሚለው ጥያቄ ትኩረት እንድትሰጡት እፈልጋለሁ። ቁጭቱን አጉልተን በንዴት ዙርያ ክስተቱን ልንጋፈጥ እንችል ይሆናል። የተፈጸሙትን ግፎች በዚህ ስሜት ያስገባናል1፡ አስግበቶናልም። ምክንያቱም ወንጀለኞችም አልተጠየቁምና ይኼ ቁጭት በዚህ ዙርያ አሰባስቦናል። የእንቅስቃሴ ማዕከል ይኼ ሊሆን ይችላል፡ “ቁጭቱ”! ወንጀለኞች ወንጀል ሲፈጽሙ ጠያቂ ስለሌለባቸው አስቆጭኦናል፤ ተናድደናል፤ “ድብን አድርጎናል”። ይኼ ቁጭት ሲሆን፤

በሌላው መልኩ ደግሞ “ተስፋ” የሚለው “ማዕከል” ማድርገን እንችላለን። ሁሌም በእንቅስቃሴአችን ሁለቱ ሊኖሩ ይችላሉ። ቁጭትን ብናጎላው ተስፋ ይኖራል ተስፋም ብናጎላው ቁጭቱ ይኖራል። ነገር ግን በእንቅስቃሴአችን ጉልህ ሚና እና ወሳኝ የሆነ አስተማማኝ ሚና ሊኖሮው የሚችል የትኛው ነው የሚለው ግን ወሳኙ “ተስፋ” ስናስቀድም እና ስናጎላው ነው ወሳኝ ግብ ሊያስገኝልን የሚችለው።

የምንሰባሰበው በቁጭት ብቻ ከሆነ ግባችን ረዢም አይሄድም። ጉዞኣችን “ሳስተይነብል” (አስተማማኝ) አይሆንም። የተወሰነ መንገድና የተወሰነ ጊዜ ያቆየናል። ግን ቁጭት ብቻ ይዘን ከተጓዝን ቀስ እያለ፤ እያዘገመ፤በቀስታ እየተንጠባጠበ መጨረሻ ላይ አዳራሹ ባዶውን ይቀራል። የተወሰነ ርቀት ብቻ ነው የሚያስኬደን።

ተስፋን ይዘን ከተጓዝን ግን በአገራችን አባባል “ወንዝ ያሻግራል”። ሃይለኛ ሞገዳዊው ጎርፍ እንሻገርበታለን። ለምን የምንል ከሆነ በቁጭት በኩል “አሻራ” ትትን ማለፍ አንችልም። ቁጭት ብቻ ከሆነ የሰነቅነው እና እዚህ ቁጭትን ይዘን እዚህ ካሰባሰበን- ሁልጌዜ ቅሬታን እና ብሶትን ብቻ እየተናገርን “ጭራቃዊው አዙሪት” (ቪሸስ ሰረሉን)  ሰብረነው ልንሻገረው  አያስችለንም። አርግጥ ነው “ቁጭት” ትልቅ ድርሻ አለው። ለሟቾች ቤተሰብ መድረስ ትልቅ እፎይታ አለው።  የሕሊና መጽናናትና ፈውስነት አለው። የተጎጂ ቤተሰቦች ከወገኖቻቸው ድምጽ መስማት ይፈልጋሉና የተሰበረ ሕሊናቸው ይጠግናል። ግን ከዚህ አልፈን ሊያሻግርን የሚችል “ተስፋ” ነው።
አገራችን ውስጥ ጀነሳይድ ተፈጽሟል።ስለ የዘር ማጥፋት ካነበብኳቸው መጽሓፍት ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጸመው የአገዳደል ስልት የዘር ማጥፋት ተፈጽሞባቸዋል በሚባሉ በማንኛቸውንም አገሮች ተፈጽሟል የሚል አላነበብኩም።

ሩዋንዳ ውስጥ የዘር ማጥፋት (ጀነሳይድ) ተፈጽሟል፤ ነገር ግን በኛ አገር እንደተፈጸመው ገድሎ አካላትን ቆራርጦ ለጅብ እንዲሰጥ አልተደረገም። ጀርመን ውስጥ በይሁዶች ላይ ዘግናኝ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል። ነገር ግን በሩዋንዳም ሆነ በጀርመን ናዚ የተገደሉ ሰዎች በሩዋንዳ መሬት ወይንም በጀርመን መሬት ሬሳቸው እንዳይቀበር አልከለከሉም። እኛ አገር ግን ሬሳቸው ተቆራርጦ የተገደሉት ሰዎች አንዳንድ ማሕበረሰብ አባሎች ተሰባስበው  የሙታኑ የተቆራረጠ አካላቶቻቸውን ለቃቅመው ለመቅበር ሲፈልጉ “እዚህ ኦሮሞ መሬት ስለሆነ አትቀብርዋቸውም” ተብለው ሲከለከሉ፤ ቀባሪዎቹ “ታዲያ እዚህ መቅበር ካልተቻለ ድሬዳዋ ወስደን እንቅበራቸው” ብለው ሲጠይቁም “እዛም አትችሉም” አሉዋቸው። ታዲያ የተቆራረጠው ሬሳ ምን እናድርገው ብለው ሲጠይቋቸው፤ “ለጅብ እራት እንዲሆኑ ለጅብ ስጥዋቸው እንጂ መቅበር አትችሉም”! ተብለዋል። ይህ በዚህ የሰለጠ ክፍለዘመን እንዲህ ያለ ጭራቃዊ ተግባር በዓለም የመጀመሪያ ያደርገዋል። መቆራረጥ ብቻ ሳይሆን ሰውን ከነነብሱ ዝቅዝቆ ሰቅሎ ግድያ ተፈጽሟል። ሩዋንዳ ውስጥ ብዙ የቱሲ ሴቶች ተገድለዋል። የአንድም ሴት ጡት አልተቆረጠም። ኢትዮጵያ ግን የሴት ጡት ተቆርጠዋል።  ይህ እንግዲህ በሕዝባችን ላይ በናንተ ላይ ቁጭትን አስነስቷል።  በግልጽ “ቀይ መስመር ታልፏል።


ይህ ቁጭት ወደ ተስፋ መለወጥ አለበት።ምክንያቱም እንዲህ ያለ ድርጊት የፈጸሙ ሰዎችን አባ ገዳ አይደለም የሚላከው። “ተጠያቂነት” መኖር አለበት። የፈለገው ጊዜ ይፍጅ፡ ህወሓትን ለመታገል 30 አመት ያክል ፈጅቶብናል። አሁን ይኼ ሥርዓትም ማለትም ተረኞቹ ሊገነቡት ያሱበትን ሥርዓት ሌላ 30 አመት ሊፈጅ ይችል ይሆናል፡ ግን ከ30 አመት በኋላም ቢሆን ጊዜውን ጠብቀን ዛሬ ለተፈጸመው “የጀነሳይድ ወንጀል” የሕግ ተጠያቂነቱን ተግባራዊ እንዲሆን መሰረቱ ካሁኑኑ መገንባት ይጠበቅብናል። “ተስፋ” የምላችሁ ይኸ ነው። የፈሰሰው ደም በከንቱ ፈስሶ መቅረት የለበትም። የብዙ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ይኼ ነው። ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ካልሰጠን እንደ ሃገር ፤እንደ ሕዝብ የለንም ማለት ነው።

ይህንን ተጠያቂነት እንዲኖር ለማረጋገጥ የምናደርገው እንቅስቀሴ እኔ “አሻራ” የምለው “ውጤት” እንዲኖር ትትን እንድናልፍ የሚያደርግ  እንቅስቃሴ ነው።  ይኼ ተስፋ ነው የሚያሸጋግረን ። ተስፋችን የታጠቀው ትጥቅ “የፍትሕ ጥያቄ’ ስለሆነ ነው”። ጥያቄአችን የበቀል ጥያቄ አይደልም። ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ትክክለኛ ፍትሕ መስጠት በሚችል ነፃ በሆኑ የዓለም ሆኑ አስተማማኝ ሆኖ በተመሰረተ አገር በቀል የሕግ ተቋም ፊት ቀርበው ቅጣታቸውን በሕግ እንዲያገኙ እንጂ እንደ ቀይሽብር ነፃ እርምጃ እንዲወሰድበባቸው አንፈቅም። ሁሌም ተስፋችን እና ትጥቃችን “ፍትሕን ማስፈን ነው””። እንቅስቃሴአችን ሰላማዊ እና ፍትሕ ፍለጋ ነው። ፍትሕን ለማስፈን የምናደርገው ረዢም ጉዞ  የምንሻገረው ተስፋን በመታጠቅና በማጉላት ነው። በፍትሕ ከፍታ ላይ ለመድረስ ተስፋን ታጥቀን ነው። ተስፋ የሰዎች ጥንካሬ ገምቢ ነው። እኛ ደምፅ ለሌላቸው ድምጽ እንሆናለን ብለን ተስፋ ይዘን ነው የተነሳነው።  ስለዚህ ቁጭታችንን በተስፋ እያጎላን ተስፋን ታጥቀን (ተግባርን ታጥቀን ) ድሃውን ማሕበረሰብ በግፍ የጨፈጨፉትን ገዳዮችን ወደ ፍትሕ ለማቅረብ ሕዝባችን ብሶቱን ይዞ እንዳይቀመጥ የምርጫ ካርዱን ይዞ ተግባራዊ ምላሽና ምላሽ እንደሰጥ አሻራሻችንን ማስቀመጥ እንችላለን የምላችሁ ለዚህ ነው።

ወንዝ የሚያሻግር የምለው “ቁጭትን ወደ “ተስፋ/ተግባር” ስናሸጋግርረው በተፈጸመው ግፍ ተጠያቂነትን የመፍጠር ድባብ እንፈጥራለን። በወገኖቻቸን ላይ የተፈጸመው ግፍ ያንድ ሰሞን ጫጫታ ሆኖ መታየጥ የለበትም። ‘ወንጀለኞችን ለግፍ አላቀርብም የሚል መንግሥት በሚቀጥለው ምርጫ “መንግሥት ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ አለበት ወይስ የለበትም” የሚል የማስመረጫ (ሩፈረንደም) ድምጽ መስጪያ ሆኖ መቅረብ አለበት እላለሁ። ይህም ካልሆነ ወንጀለኞችን አላቀርብም የሚለው መንግሥት በምርጫ ወቅት ሕዝባችን የምርጫ ካርዱን በመጠቀም መንግሥትን ዋጋ ሊያስከፍለው የሚችልበትን ዕደል ከተጠቀመ መጪ ሥርዓቶች ወንጀለኞችን ወደ ሕግ ያለማቅረብ ሥልጣን የሚያስነጥቅና ተጠያቂ እንደሚያደርግ እንዲያውቁ የሚያደርግ ትምህርት ይሰጣቸዋል። ስለዚህ ቁጭትና ተስፋ ሁለቱ እየተመጋገቡ የሚሄዱ ቢሆኑም ከቁጭቱ ቀጥሎ ያለው እርከን “ተስፋ (ተግባር)” ስለሆነ እሱን ማስተዋልና ማስቀጠል አለብን።

በመጨረሻ እናንተ ያላችሁን ሁሉ ድጋፍ አድርጋችኋል፤ ለኛ መስጠት ያለባችሁ  ዕድል “አንድ ዕድል ብቻ ነው” (እንደ አሜሪካ ፕረዚዳንቶች)። የኛ አማራር ብቃት እዚህ ላይ ነው የሚለካው። በሚቀጥለው ምርጫ ውጤት ለማስመዝገብ የኛ አማራር ሕዝቡን አሳምነን ገጠር ድረስ ዘልቀን “መንግሥት ወንጀለኞችን መቅጣት ሲገባው ወንጀለኞችን ባለመቅጣቱ መንግሥት ሊቀጣ ይገባል ብለን አሳምነን በካርዱ እንዲቀጣው ካላደርግን ፤እኛ ለዚያ ውድቀታችን ዋጋ መክፍል አለብን። ዋጋ የምንከፍለው ከአመራራ ቦታችን ተነስተን ሌሎች ጠንካራ አመራሮች ቦታውን ማስረከብ አለብን። ይህንን አማራር የሚተካ ከሥር እየበቀለ የመጣ ጠንካራ አማራር ተልዕኮውን እንዲቀጥልበት እናደርጋለን። በዚህ እሳቤ ውጤት ተኮር ሆነን መንቀሳቀስ አለብን።ለዚህ ነው “በቁጭት” ብቻ ከተሰባሰብን ትግሉ የረጋ ይሆናል (ስታግናንት ይሆናል)፤ ባለበት ይቆማል፡ይከሽፋል። በቁጭት ብቻ የሚያተኩር አማራርም ጭምር “ባለህበት ይረግጣል” ፤ወደ ኋላ ይጓዛል። አስፈጽመዋለሁ የሚለው አጀንዳ (ግብ) የጊዜ ገደብ ሊያስቀምጥለት ይገባዋል። በዚያ የጊዜ ገድብ ማስፈጸም ካልቻለ፤ በጊዜ ገደብ (በታይም ፍሬም) ግቦችን ማስፈጸም ለሚችሉ አማራሮች ቦታውን መልቀቅ አለበት። በሚቀጥለው ምርጫ ግባችንን በጊዜ ገደብ ማስፈጸም ካልቻልን መባረር አለብን። ምላስ ብቻ ነን ማለት ነው። ምላስ ደግሞ የትም አያደርስም። እርግጥ ምላስም አስፈላጊ ነው፤ ግን ቁጭታችን ፍትሕን ለማስፈን ወደ ተግባር መለወጥ ይኖርብናል። አመሰግናለሁ ።”

 በማለት ታላቁ እስክንድር ነጋ ንግግሩን ሲደመድም ተሰብሳቢው ከመቀመጫው በመነሳት በጋለ ጭብጨባ ድጋፍንና አድናቆቱን ከአዳራሹ ተለግሶለታል።

ያጠናከርኩላችሁን የኦክላንድ የባልዴራሱ የስብሰባ ዘገባ ስላነበባችሁልኝ አመሰግናለሁ። ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ) getachre@aol.com