Sunday, July 9, 2017

መለስ ዜናዊና የአፍሪካ ሕብረት ምን አገናኛቸው? (አቻምየለህ ታምሩ) (Posted at Ethiopian Semay)መለስ ዜናዊና የአፍሪካ ሕብረት ምን አገናኛቸው?
(አቻምየለህ ታምሩ)  (Posted at Ethiopian Semay)
የአድዋው ነውረኛ መለስ ዜናዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመሰረቱት የአፍሪካ ሕብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጋር ሀውልት ሊቆምለት ነው አሉ። ይገርማል! ሰሜን ሮዴዥያና ደቡብ ሮዴዥያ አንድ ሆነው ዚምባብዌ እንድትመሰረት ያገዙ የአፍሪካ አባቶች በመሰረቱት ተቋም ፊት ለፊት፤ ታንጋኒካና ዛንዚባር ታንዛንያ እንዲሆኑ የረዱ የአፍሪካ መሪዎች ያቋቋሙት ድርጅት ቅጥር ግቢ ውስጥ የአፍሪካን ሕብረት በመሰረቱት በነ አክሊሉ ኃብተ ወልድ ተጋድሎ አንድነቷ የተረጋገጠው ኢትዮጵያ ለሁለት ተከፍላ ወያኔ የሚገዘግዛት ኢትዮጵያና ኢሳያስ አፈወርቂ የሚገዛት ኤርትራ እንዲፈጠሩ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከአለም ሁሉ አስቀድሞ ደብዳቤ የጻፈው አሳፋሪ ግለሰብ የአንድነት ምልክት ተደርጎ ሀውልት ሲቆምለት እንደማየት ምን አሳፋሪ ነገር አለ።

የመለስ ዜናዊ ስም ሲነሳ ከፊታችን ድቅን የሚለው መበታተን፣ ማጋጨት፣ ኢትዮጵያን አፍርሶ በጎሳ አጥር የሚተራመሱ የመንደር ሪፑብሊኮች የመመስረት መብት «የመገንጠል መብት» ተብሎ ሕገ መንግሥታዊ እውቅና ማግኘቱ፣ዘራፊነቱ፣ ዘረኛነቱ፣ ከትግራይ ብቻ ሳይሆን ከተወለደበት ቅዬው ከአድዋ አስፍቶ አለማሰቡ፣ ወዘተ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የመለስ ህያው መገለጫዎች ከሕብረትና አንድነት ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የለም።


መለስ ዜናዊ የሚገዘግዛት ኢትዮጵያ ሰማንያ አገሮች እድትሆን የጎሳ አጥር አበጅቶ መበታተንን ህጋዊ በማድረግ የመፍረስ አደጋ ያንዣበባት የጎሳዎች እስር ቤት እንድትሆን ያደረገው ዘራፊ ሽፍታና መገንጠልን ሲያደፋፍር የኖረው ነውረኛ ግለሰብ ነው። አንድነት በሚሰበክበት የአፍሪካ ሕብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ መለስ ዜናዊ ሐውልት ሊቆምለት ነው መባሉን ማንዴላ ባጸደ ገነት ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? የአፍሪካ ሕብረት እንዲፈጠር በተደረገው ከፍተኛ ዝግጅት ውስጥ ዋና ተዋናይ የነበሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የነበሩት ታላቁ አቶ ከተማ ይፍሩስ መለስ ዜናዊ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምልክት መባሉን ቢሰሙ ምን ይሉ ይሆን? ማንዴላ የመለስ ዜናዊዋን ኢትዮጵያን ሳይረግጥ የሞተው የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ማየት አልፈልግም ብሎ ነበር።
ለመለስ ዜናዊ በአፍሪካ ሕብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሀውልት ማቆም ማለት ኒዮርክ በሚገኘው ብሔራዊ የመስከረም 11 የመታሰቢያ እና ቤተ መዘክር ግቢ ውስጥ የቢላደንን ሀውልት እንደማቆም ማለት ነው። ስለእውነት መለስ ዜናዊና አንድነት ምን አገናኛቸው? መለስ ዜናዊኮ አይደለም የአፍሪካ መሪ ሊሆን ይቅርና ኢትዮጵያ እንኳ አንድ አድርጎ መግዛት ያልቻለ ነውረኛ ግለሰብኮ ነው። ኸረ መለስ ዜናዊ የትግራይ በሙሉም መሪ አልነበረም። መለስ ዜናዊ ምንም እንኳ በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግሥት በጣይቱ ከተማ አዲስ አበባ ቢሰየምም በአገዛዝ ዘይቤው ከትግራይ ክልል የአድዋ ወረዳ ገዢነት አልፎ አያውቅም።

እንደ መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም በተለያየ ዘመን አሳልፎ የሰጠ ከንቱ ግለሰብ የለም። ኢትዮጵያዊው አክሊሉ ኃብተወልድ ዓለምን አሸንፈው ያስመለሷትን ኤርትራን ለዘመዶቹ አሳልፎ የሰጠ መለስ ዜናዊ ነው። ፋሽስት ጥሊያን ሳይቀር ዓሰብ የኢትዮጵያ የባህር በር መሆኑን እየመሰከረ «ዓሰብ የኤርትራ ሉዓላዊ ግዛት ነው» ብሎ የኢትዮጵያን የባህር በር አሳልፎ የሰጠና ኢትዮጵያን ያለ ባህር በር ያስቀረው ጉደኛው መለስ ዜናዊ ነው።

የክዋሜ ኑክሩማህ ልጆች ሳይቀር የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሀውልት በአፍሪካ ሕብረት ቅጥር ግቢ እንዲቆም ሲታገሉ ነውረኛው መለስ ዜናዊ ግን ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በግንባር ቀደምትነት ከመሰረቱት ድርጅት ታሪካቸው እንዲፋቅ ያልቆፈረው ጉድጓድ የለም። አንድ ጊዜ ቶጎ ሎሜ ላይ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመሰረቱት የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ባደረገው ንግግር፤ በትግራይ ሕዝብ ፊት ቀርቦ «እንኳን ከእናንተ ከወርቅ ሕዝብ ተፈጠርኩ፤ እንኳን ከሌላ አልተፈጠርሁ» እያሉ መናገርን እንደ ትልቅነትና ተራማጅነት ቆጥሮት የነክዋሜ ኑክሩማህና የነጆሞ ኬንያታ ልጆች ይታዘቡኛል ሳይል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን «አድሀሪ» ወይንም Reactionary ሲል ተሳለቀ። ሌላ ጊዜ ደግሞ ለአፍሪካ ሕብረት አንድ ሰው ይጠራ ቢባል እንደ ክዋሜ ኑክሩማህ ማንም የለም አለ። ኑክሩማህ ራሱኮ ይህን ቢሰማ የአፍሪካ ሕብረት ምልክትነት ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እንደሚገባ መመስከሩ ምንም ጥርጥር የለውምኮ። ይህን ስለማድረጉ ደግሞ የሕብረቱን መመስረት ተከትሎ ስለኢትዮጵያንና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሚና ኑክሩማህ ራሱ የሰጠው ምስክርነት በቂ ማስረጃ ነው።

ለነገሩ መለስ ዜናዊም ቢሆን በጥላቻ ታውሮ የኑክሩማህ ሀውልት እንዲቆም ሽንጡን ገትሮ የተከራከረው እውነቱ ጠፍቶት ሳይሆን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይቆምላቸው ነበር። ለነገሩ እንኳን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሀውልት ይቁም ተብሎ አጽማቸው እንኳን መንግሥቱ ኃይለማርያም የሚባል ጨካኝ አውሬ በግፍ ከቀበረበት የቀበሮ ጉድጓድ ተቆፍሮ ወጥቶ እንደነገ በክብር ሊያርፍ እንደዛሬ ማታ « ከኢህአዴግ ጽህፈት ቤት የወጣ መግለጫ» በሚል ርዕስ መለስ ዜናዊ በሚቆጣጠው አንድ ለናቱ ቴሌቭዥን ባስነበበው የኃጢዓት ክስና የክፋት ፕሮፓጋንዳ በግፍ ተገድለው 17 ዓመታት ያልህ በቀበሮ ጉድጓድ ተቀሮ የኖረው የንጉሰ ነገሥቱ አጽም ላይ እስኪበቃው ድረስ ክብራቸውን ካጎደፈ በኋላ የሚያዋርድ የኃጢዓት ክስ ማውረዱ ቁስሉ መቼ ከህሊናችን መቼ ጠፋና። እነ ማንዴላ ሳይቀር ብሔራዊ ቀብር ይካሄድላቸው ዘንድ ጠይቀው በክብር እንዲያርፉ ያልፈቀደው አረመኔው መለስ ዜናዊ ብቻ ነበር። ምን ይሄ ብቻ! በወዳጅ ዘመድ ጥረት በክብር ሊያርፍ ከተቆፈረበት የቀበሮ ጉድጓድ ተቆፍሮ የወጣውን የንጉሰ ነገሥቱን አጽም አብዝቶ በማዋረድ ተቀብሮ ከነበረበት የቀበሮ ጉድጓድ ክብር ያነሰ ክብር እንዲያገኝ ያደረገው መለስ ዜናዊ ነው።

የመለስ ዜናዊ ሀውልት መቆም ካለበት ሊቆምለት የሚገባው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በመሰረቱትና አንድነትና ሕብረት በሚሰበክበት የአፍሪካ ሕብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ ሳይሆን ከመለስ ዜናዊ ጋር ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተቃውመው አገር ለመመስረት ጫካ የገቡት እነ ኦነግ፣ ኢሕአፓ፣ ሻዕብያ፣ ጀብሃ፣ መኢሶን፣ ወዘተ በወያኔ አጋፋሪነት ተሰባስበው ሕብረት ይመስርቱና ቢፈልጉ ደደቢት በረሀ፣ አሊያም አሲምባ ተራራ፣ ቢያሻቸው ሞቃዲሾ ዚያድ ባሬ ቤተ መንግሥት ወይንም ናቅፋ ተራራ ላይ በእጁ መዶሻና አካፋ፤ በትክሻው ደግሞ ቀይ ባንዲራውን አስይዘው ሐውልት ያቁሙለት። ለመለስ ዜናዊ የሚመጥነው ይህ ብቻ ነወ። ምክንያቱም የመለስ ዜናዊ ነውረኛነት የሚገጥመው ትናንሾቹ እነ ኦነግ፣ ኢሕአፓ፣ ሻዕብያ፥ ጀብሃና መኢሶን ይዘውት ከተነሱት ርዕዮት ጋር እንጅ ትላልቆቹ የአፍሪካ አሳቢዎች ከመሰረቱት አፍሪካ አንድነት ድርጅት መንፈስ ጋር አይደለምና ነው!
Ethiopian Semay