Wednesday, October 13, 2021

የትግሬዎች ሰቆቃ በባሕረዳር እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የገበና ማሕደር እና የወንድሜን መፈታት ጉዳይ አስመልክቶ ላበስራችሁ! ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ) Ethiopian Semay 10/13/2021

 

የትግሬዎች ሰቆቃ በባሕረዳር እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የገበና ማሕደር እና የወንድሜን መፈታት ጉዳይ አስመልክቶ ላበስራችሁ!

ጌታቸው ረዳ

(ኢትዮ ሰማይ) Ethiopian Semay  10/13/2021

ፎቶ Daniel Bekele Human rights commissioner (Image source Reuters)

ገበና ብዙ ትርጉም አለው። ወንጀልም፤ በደልም፤ አስከፊም፤ቸልተኛነትም… ተብሎ የሚተረጎም ብዙ ትርጉም አለው። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ገባና ብየ ስገልጽ “ከወንጀል” ጋር የተያያዘ ትርጉም ሳይሆን ከዝምታው የምገልጸው አስከፊው ዝምታው ጋር የተያያዘው ገበናውን ነው።

በታላቁ የሞራል ግጭት ጊዜ ገለልተኛ ሆነው የምናያቸው ግለሰዎችም ሆኑ ድርጅቶች ገበና ፈጻሚዎች ናቸው። ጥቁሩ አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር ኪንግ ለእንደዚህ ያሉ በክፉ ቀን አድፍጠው ዝምታን ለሚመርጡ ሰዎች “መሬት ውሰጥ ያለው የስሓራ ሲኦል” የተዘጋቸው ለነሱ ነው ይላል። ምክንያቱም በክፉ ቀን ዜጎች አቤት ሲሉ ‘ዝምታን’ መምረጥ ክህደት ነው።ለዚህ ነው ማርቲን ሉተር “በመጨረሻ የጠላቶቻችንን ቃል ሳይሆን የጓደኞቻችንን ዝምታ እናስታውሳለን።” ሲል የተናገረው። ወንደሜ ተፈቷል፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዝምታ ግን እስከመቼም እናስታውሳለን።

ይህ ድርጅት የሚመራው ዶ/ር ዳኒኤል በቀለ ይባላል። ካሁን በፊት በፋሺስቱ ወያኔ ታስሮ የተሰቃየ እንደነበር ገልጬላችሁ ። መታሰር ምን እንደሆነ በተግባር ያውቀዋልና የእስረኞች አቤቱታ ተሎ ሰምቶ አግባብ የሆነ ሙግት ያደርግላቸዋል በሚል ተስፋ ከ4 ወር በፊት ትግሬ ሆኖ በመወለዱ ብቻ በነገዱ ምክንያት ከምሽቱ 2 ሰዓት ማታ ፖሊሶች ወደ ቤቱ መጥተው ወደ እስር ያስገቡት የታናሽ ወንድሜን ጉዳይ ለጽ/ቤቱ ከፍተኛ አመራር በኢመይል አቤቱታየ አመልክቼ እንደነበርና በጉዳዩ ተከታታይ ጽሑፍ መጻፌን አስነብቤአችሁ እንደነበር የኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ ተከታታዮች የምታስታውሱት ነው።

የምታውቁኝም የማታውቁኝም ተከታታዮቼም በግልም በቡድንም ምን እናግዝህ ብላችሁ የጠየቃችሁኝ ወዳጆቼ በዚህ አጋጣሚ ላመስግን እና ወደ ጉዳዩ ልግባ።

ባሕርዳር ውስጥ ታፍነው ከጠፉ በከተማው ውስጥ እና አካባቢው የሚኖሩ ያልተጠቀሱ ትግሬዎች ሳይጨምር 40 እስረኞች አሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ወንደሜ ነው። ለ4 ወር “እንደ የጀርመን ናዚ ማጎርያ” ለብቻ ተለይተው ለቤተስብ ጉብኝት ተከልክለው፤ ከቤት ምግብ እንዳይመጣላቸው ተከልክለው፡ 17 ጊዜ በድብቅ ፍርድ ሲቀርቡ፤ በችሎቱ ውስጥ ቤተሰብ እንዳይገቡ ተደርገዋል። ያ አላንስ ብሎ ሕገመንግሥት ተብየው በሚጥስ መልኩ የግል ወይንም የመንግሥት ጠበቃ አንዲቆምላቸው አልተደረገም።

ይህንን አስመልከቼ፤ አዲስ አበባ ለሚገኘው ሰብአዊ መብት ተሟጋች አመራሮች ጉዳዩ አሳሳቢ እንደሆነ እና እስር ሲፈጸም “ዘርን/ነገድን/ ያነጣጠረ እስር መሆኑን” እና ከሌሎች እስረኞች  ተለይተው በማጎርያ (ኮንሰንትረሽን ካምፕ) ውስጥ ታፍነው መታሰራቸው ከሕግ ውጭ መሆኑን አነጋግሬአቸው፡ ከስንት ውትወታ እና የኔ የቁጣ ጽሑፍ ከአንድ የኮሚሽኑ አመራር አባል “አንድ ጊዜ ብቻ” በቅርቡ መልስ አገኘሁ።

በጣም ከሚገርመው በደብዳቤ ውስጥ ወንድሜን አስመልክቶ ሳይሆን በሌላ ቡድን የሚገኙ ማንነታቸው የማይታወቅ ትግሬዎች በታሰሩበት ውስጥ ተደብድበው በርካታ የድብደባ ጩኸት ታደምጥ የነበረቺው ለ6 ቀን ታስራ የተፈታች የወያኔ መስራች የነበሩት የአቶ ገሰሰው አየለ (ሱሑል) ልጅ አፈላልጋችሁ ጉዳዩን አጣሩ ብየ ሳመለክት “ከጉዳይም አልቆጠሩትም”።

ይህ “አላርሚንግ” (አስደንጋጭ አንቂ ደወል) ሳያሳስባቸው ሲቀር በተደጋጋሚ የታዘብኩት ነገር፤ ለሰብአዊ ጉዳይ ጥብቅና እቆማለሁ የሚለን ጽ/ቤት “ለይስሙላ” እንደሆነ  ታዝቤአለሁ። በአብይ አሕመድ የሚመራው “ኢሕአዴግ/ኦሮሙማ ብልጽግና/ በእስረኞች ላይ “ቶርች” ‘ድብደባ’ እንደሚፈጽም አምና በ2020 (በፈረንጅ ዘመን) እራሱ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳኒኤል በቀለ እስክንድር ነጋ ከጽ/ቤቱ ሲወስዱት እና ተወስዶ ከታሰረ በኋለም እስርቤቱ ውስጥም እንደተደበደበ የመሰከረበትን ማስታወስ መዘንጋት የለብንም።

ትውስታችሁን ለማደስ እንድትችሉ ይህንን ማስረጃ እነሆ ፤

በፈረንጅ ሓምሌ ወር 2020 የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ዳኒኤልን ጠይቆ ያገኘው መልስ  በወቅቱ እራሱ ዳኒኤል ወደ እስርቤት ሄዶ ጃዋር መሓመድ፤በቀለ ገርባ ሽመሰዲን ጣሃ ( የ ኦ ኤም “አርታኢ”) እንዳነጋገራቸውና የተቀሩት የምግብ ችግርና የዘመድ ጉብኝት ጉዳይ  እንዳለባቸው ሲሆን  ሁለቱ “ሽምሰዲን እና እስክንድር ነጋ” ግን በፖሊሶች እና አሳሪዎቻቸው “ድብደባ” እንደደረሰባቸው  በቃላቸው እንደነገሩት አረጋግጠውልኛል ያለውን ምስክርነቱን ልጥቀስ።  

“እስክንደር ነጋ የነበረኝ ‘ቢሮየ ድረስ መጥተው ነው ያሰሩኝ፤ ሲያስሩኝ በመጡበት ወቅት ድብደባ ፈጽመውብኛል፤እንዲሁም ፖሊስ ጣቢያ ከደረስኩኝ በኋላም እንደዚሁ ድብደባ ደርሶብኛል ብሎ ነግሮኛል”። “አቶ ሽመሰዲን በሚመለከት ግን ድብደባው እስርቤት ከታሰሩ በኋላ እንደተፈጸመባቸው ነው የነገሩኝ”። ሲል

የአብይ አሕመድ “ኦሮሙማው መንግሥት” እስረኞች ላይ ድብደባ እንደሚፈጽም እየታወቀ ሆኖ ሳለ; ባሕርዳር ውስጥ “በትግሬ ነገድ” ታሳሪዎች ላይ “ቶርቸር” እየተፈጸመ እንደነበርና እየተደበደቡ ሲጮኹ በርካታ ጊዜያት ሰምቻለሁ ብላ ጥቆማ የሰጠች ሴት ስም እና ማንነት ብገልጽላቸውም “ጀሮ ዳባ” ነበር ያሉት። ድብደባ ሲፈጸም ጩኸት ሰምቻለሁ ያለቺው እስር ቤት ወንድሜ ከታሰረበት ቦታ ሳይሆን ሌላ ስሙ ባልታወቀ ፖሊስ ጣቢያ እስር ቤት የታሰሩ ትግሬዎች ላይ መሆኑን ጠቁማለች።

መጨረሻ ላይ ወንድሜ ከ4 ወር “ኮስንትረሽን ካምፕ” (ግለላ እስርቤት) መታሰር በኋላ ወደ ተቀሩት መደበኛ እስር ቤቶች ለአንድ ሳማንት  እንዲቀላቀሉ ተፈቅዶ ከቆየ በኋላ “ፍረድቤቱ” “ማስረጃ አላገኘሁባቸውም” ስለዚህ በዋስ ይፈቱ ብሎ ፍርድቤቱ ወስኖ የ20 ሺ ብር ዋስትና በማስያዝ “ከ40 ታሳሪዎቹ 16” ብቻ ከእስር አንዲፈቱ በመወሰኑ ዛሬ ቀን  ወንድሜ መፈታቱን አብራችሁ ለተጨነቃችሁ ለወዳጆቼ ለመግለጽ እወዳለሁ።

ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ተብየው ግን ጉዳት ከደረሰባቸው በሗላ በቅርቡ ወደ ወንድሜ ቤተሰብ ደውሎ “ፈርድ ቤት” ስለቀረበ “ፍርድቤት” የመቅረብ መበት የተጠበቀላቸው እስረኞች ጣልቃ መግባት አንችልም ስትል ወንደሜ ቤት አንዲት የኮሚሽኑ ሰራተኛ ደውላ እንደነገረቸቻቸው ነግረውኛል። “ጅብ ከሄደ ውሻ ይጮሃል”። ጉዳት ደርሶ፤ ከተፈቱ በኋላ ያለ ምንም ሰብአዊ መብት ጣልቃ ገብነትና ተቆርቋሪነት “ተፈቱ፡ ማለት ነው።

ለዚች ለደወለቺው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሴትዩ የምለው ነገር አለኝ፡

4 ወር ሙሉ 40 የሚያክሉ የትግራይ ነገድ ታሳሪዎች ምን እንደደረሰባቸው አላወቅኩም እንዳይል ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አሳውቄአቸዋለሁ፤

2) ድብደባ እየተፈጸመ መሆኑን አንዲት ሴትዩ ከነ ማንነትዋ ለነሱም ይሁን ለአብይ አሕመድ አዲሱ “ሎሌ” ለዶ/ር አረጋዊ ብርሀ” (ወያኔ መስራች እና የዛሬ የግድብ ሥራ ክንውን “አጋፋሪ”) አሳውቄአቸዋለሁ። አረጋዊን በሚመለከት እራሱ የቻለ ትችቴን ስለማቀረብ እዚህ አላቀርበውም።

3) ወንድሜ ያለ ሃጢያቱ በሃሳብም በገንዘብም ትረዳላችሁ በሚል ጥርጣሬ 4 ወር ከታሰሩት ጋር ታስሮ ያለ ምንም ሃጢያት ያለ ጠበቃ እና ቤተሰብ ጠያቂ መብቱ ተገፏል አስቸዃይ ጣልቃ ገብታችሁ መብቱ ተጠብቆለት ሥራው አንዳያጣ ተሎ ድረሱለት ብየ ሳመለክት ኮሚሽኑ አልደረሰለትም።

4) አሁን ወንድሜ ቤተሰቡን ሲያስተዳድርበት የነበረውን ሥራ በሌላ ሰው ተተክቶ ያለ ስራ ከቤተሰብ ጋር ችግር ውስጥ መግባቱ ነው። መንግሥት ሆን ብሎ በነገዳችን ምክንያት “ሥራ ፈት” እና “ድሆች” እንድንሆን እያደረገ ነው ብለው ቢያማርሩ “ተሳስታችኋል” ማለት አንችልም ።  ኮሚሽኑ ይህ “ቀጥተኛ ጥቃት” ምንም አላሳሰበውም። በወቅቱ ስናመለክት “ኮሚሽኑ” ባለመድረሱ ሥራው አጥቷል፤ ጉዳት ደርሶበታል። በማጎርያ ተለይተው የታሰሩ በርካታ ታሳሪዎች 4 ወር እና ከዚያም በላይ የታሰሩ ትግሬዎች ይኖራሉ፤ ኮሚሽኑ ምንም ሳያሳስበው ቁጭ ብሎ ከርሞ ጉዳት ደርሶባቸው ከሥራቸው ተፈናቅለው ይኼው ያለ ሃጥያታቸው ትግሬ በመሆናቸው ብቻ ተይዘው ለመከራ ተዳርገው መጨረሻ ተፈትተዋል።

5) ሰብአዊ ኮሚሽን ተብየው ባሕርዳር ውስጥ የተፈጸመወ የዘር ጥቃት ለምን አላሳሰበውም? ለምንስ ነው ታሳሪዎቹ ፍርድቤት “እስከሄዱ” ድረስ “ጣልቃ አንገባም ብሎ “በመፈታታቸው ሰዓት” ስልክ “መደወል” የቻለው?” 4 ወር ምን ይደርስባቸው እንደነበር ስንገልጽ “ጆሮ ዳባ ብሎ ቆይቶ” አሁን ሲፈቱ ደውሎ “ፍርድቤት ለቀረበ እስረኛ “ጣልቃ አንገባም” ሲል ብምን ሕግ እና ደምብ ነበር? የሰደረሳባቸው ዕንግልት ጠይቆ መዝግቦ ለሚመለከተው መንግሥትና ፍርድቤት ማቅረብ ለምን አልፈለገም? ፍርድቤት እንዲቀርቡ የተደረጉ እስረኞች ላይ ሌላ ግፍ አይፈጸምባቸውም ብሎ የነገራቸው ማን ነው? እስከ ዶክትርነት የደረሱበት እነ ዳኒኤል የሰለጠኑበትስ ሙያ ይህንን ያስተምራል?

6) የወንድሜ ልጅ እና ባለቤቱ ለመጠየቅ ይፈቀድላቸው የሆን ብለው በቀጠሮው ቀን ወደ ፍርድቤት ሲሄዱ የከፍተኛ ፍርድቤት ጠባቂ የክልል ልዩ ሃይል ባለቤቱንም ደብደወበው፤ ከዚያም ታዳጊ የሆነው ወጣት ልጁን የጁንታ ልጅ በማለት “ፕለስቲክ በተለበጠ የብረት ብትር” አይኑን መትተው ቆዳው ተተርትሮ አጥንቱ ተሰብሮ ደም በደም ሆኖ ናላው  ዞሮበት ፤“ወድቆ” ሆስፒታል ወስደውት ተሰፍቶ እስካሁን ስቃይ ላይ ነው። የማየት ችግር ገጥሞታል። ለዚህ ሁሉ በደል ሰብአዊ መብት ተብየውም ይሁን የክልሉ ሃላፊ ለምን አላሳሰባቸውም። ይህንንም በደብዳቤ ገልጨላቸዋለሁ። ልዩ ሃይል የሚባለው የተማሩትን ኮማንዶ ትምህርት “ሴቶች እና ህጻናት” ለመደብደብ ነው ወይስ አማራን በመጨፍቸፍ ላይ ያለውን ኦነግንና ወያኔን ተብሎ ነበር ስልጠና የተሰጣቸው?

ለማንኛውም ኢትዮጵያ በክፉ እጅ ውስጥ ገብታለች እና በራስዋ የምትድንበት መንገድ ካለ እንጂ በነዚህ ድርጅቶች ተከላካይነት እንደማትድን ከቤተሰቦቼ ችግር ለማየት ችያለሁ። ዘረኝነት ክፉ በሽታ ነው እና በዚህ በሽታ ላለመለከፍ ሁላችንም እንበርታ።

ከ40 ታሳሪዎች 16 ተፈትተዋል። ከ16 አንዱ በናንተው ብርታት ወንድሜ በ20 ሺሕ ብር በዋስ ተፈትቷል። ገንዘብ ማስያዝ የመይችል የኔ ቢጤ ድሃ ግን ካቴና ውስጥ ገብቶ ይቆያል። ሰብኣዊ መብት ተሟጋች ነኝ የሚለን አዲስ አባባ የተኮፈሰው ድርጅት ግን “ፍርድ ቤት” ስለቀረቡ “እንደማያገባው” ነግሮናል። የሚያስቅ ባይሆንም፤ ሳይስቁ ማለፍ አይቻልም።

ማሳሰቢያ

ድርጅቱ የሰው ሃይል እና የገንዘብ እጥረት ሊኖሮው ይችል ይሆናል ብለን እንውሰድለትና ፤ የኮሚሽኑ ተወካይ ነኝ ባይዋ ሴትዮ ወደ ወንድሜ ቤት ስልክ ስትደውል፤ መደወልዋ ላልቀረ፤ በልጁ እና በባለቤቱም ይሁን በታሳሪው ወንድሜ ላይ የደረሰበትን ሕግ ያልተከተለ እስር እና መንገላታት መመዝገብ ለምን አልፈለገቺም?

ከዚህ በማያያዝ ያለ ምንም ወንጀል ላሥራቸው እና ሥራቸው በሌላ ሰው ቅጥር ተይዞ ለቆያቸው እስረኞች መንግሥት ተብየው በምን መልክ ሊረዳቸው ነው የሚል ይያቄ አቀርባለሁ (ሼር ብታደርጉት)? አላግባብ ለደረሰባቸው እንግልትስ “ካሳ” ይከፍላል? ሰብአዊ ተቆርቋሪ ነኝ የሚለን የዶ/ር ዳኒኤል በቀለ ጽ/ቤትስ ለዚህ ምን አስተያየት አለው? ተመልሰው እንዳይያዙስ ምን ዋስትና አለ? 16 ቱንም ሆኑ 34ቱ ላይ የሰብአዊ መብት ጽ/ቤት ቃለ መጠየቅ ለማድረግ አለመፈለጉና ለሕዝብ ዘገባ አለማቅረቡ ይገርማል።

አመሰግለሁ

ጌታቸው ረዳ