Saturday, May 3, 2008

Classes of deaths!


እንዳማረበት መሞት የጀግኖች አርማ ነዉ!

ማንነታቸዉ ሲጸየፉና ያልሆኑትን ሊሆኑ የዳከሩ የዘመናችን ነጻ አዉጭዎች፤ አያቶቻቸዉ የተዉላቸዉን ታሪካዊ ጀብዱ በማንቋሸሽ አእላፍ ነብሳት የተሰዉላትን የኢትዮጵያዊነት ዓርማ መለያችን የሆነችዉ ሰነደቃላማችንን አገራቸዉ ኢትዮጵያን የመቶ ዓመት ባለ ታሪክ አገር እያሉ ከሕሊናቸዉ ተነጥለዉ የዋዠቁትን የካይዳኖች አሳፋሪ ምላስ ወደ ጎን ትተን፡ ወላጆቻችንና አያቶቻችን በአገራቸዉ ላይ ደባ የሰሩትን የዉስጥና የዉጭ ጠላቶችን እያሳደዱ ሲቀጡ የኖሩበትን አኩሪ ታሪካችን ዛሬ መላልስን መዘከርና ለጠላት እጅ ያልሰጡበትን መንፈሰ ጠንካራነታቸዉን ከተጣለበት አንስተን ወገባችን ላይ መታጠቅ ገድላቸዉን የሚያድስ ለህልዉናችን ዋስትና ነዉ። ያለፉት መራራ ገድሎች ካለወቅን የዛሬ ካይዳኖች አሳሳችና ተለዋዋጭ ባህሪይም ሆነ ያገሪቱ መጪ ህልዉና በቅጡ ማወቅ ሊያስቸግረን ነዉ።

ለዛሬ የመረጥኩላችሁ ከታሪክ ማህደር፤ አቶ ሀዲስ አለማዮሁን ነዉ።ዛሬ በሕይወት የሌሉ ደራሲ አቶ ሀዲስ አለማዮሁ፤ ከትዉልድ መንደራቸዉ ጎጃም ዉስጥ በመምህርነት ሥራ ተሰማርተዉ ቆይተዉ የጣሊያን ወራሪ ሃይል በመምጣቱ ወደ ትግራይ ጦር ግመበር ተቀላቅለዉ ከተዋጉ በሁዋላ ወደ ተቀሩት የጦር ግመባሮች በመዝለቅ ባርበኝነት ትግሉን እየቀጠሉ እንዳሉ በድንገት “ባንዳዎች” ባጠመዱት ተንኮል ከራስ እምሩ ሃይለስላሴ ጋር ተይዘዉ ጣልያን አገር ተግዘዉ አስከ 1936 ዓ/ም ለ7 ዓመታት በእስር ቆይተዉ፤ የቃል ኪዳን አገሮች ጦር ነፃ አዉጪ ሠራዊት ኢጣልያን ነፃ ካወጣ በሁዋላ ከእስር ተለቀዉ ወደ አገራቸዉ አንደገቡ፡ በየት በየት ግምባር ፤ከነማን አንደዋሉ በስደትና በእስራት ያሳለፏቸዉን የሕይወት ዘመናቸዉን ያሰፈሩበት “ትዝታ” ከተባለዉ መጽሃፋቸዉ ዉስጥ የምንመለከተዉ ቁም ነገር ፡ በጉልበት ሥልጣን ላይ የወጣ አምባገነን እንዴት አንደሚወርድ ፤ከወረደ በሗላም በአማጺዉ ላይ የሚነበብ ገጽታ፤ ከዚህ አልፎ ነፃነት የቀማ ጠላት በአሸናፊነቱ ኮርቶ በንቀት ቁልቁል እያየ “ምህረት አድርጌላችሗለሁ! ” ከሚል፦ ድል ተመትቶ ተምበርክኮ ሽቅብ እያየ “የቀማሁትን ነፃነት መልሻለሁ!” ሲል ማየት እነዴት ደስ አንደሚል እና ከዛሬዉ ከእኛዉ ክህደትና ጽናት ባህርይ ጋር ተመሳሳይነት ስለማይታጣበት አሁን ያለነዉ አሳፋሪ ትዉልዶች ካለፉት ታሪኮቻችን ማማርያ ይሆነን ዘንድ አንኳር መልእክቱን ከማቅረቤ በፊት “በገና ደርዳሪዎች” የደረደሯትን ግጥም ጀባ ልበላችሁና በዛዉ እንሸጋገር።

ቀን ሲከፋ ቀን ሲከዳ
ዘመድ ይሆናል ባዳ
ቀን ሲከፋ ሲቸግር
አገር የሰዉ አገር።

<< ኢትዮጵያ በፋሽስት ኢጣሊያ ከተያዘች በሁዋላ አንደገና ነፃ መሆንዋን እኛም በኢትዮጵያ ነፃነት ምክንያት፤ከኛ በፊት ጠላቶቻችን ምህረት እያደረጉላቸዉ አገራቸዉ እንደገቡት ጉዋደኞቻችን ሳይሆን እነሱ (ጠላቶቻችን) ድል ተመትተዉ በሙሉ ነፃነት ወደ አገራችን ለመግባት በመሰናዳት ላይ መሆናችን አንደ ታምር ሆኖ ነበር የታየን! መቸም ታምር ማለት ያስተሳሰብን ስነ ስራት ተከትሎ ይሆናል የተባለዉ ሳይሆን ሲቀር፤ <አይሆንም> የተባለዉ ሆኖ ሲገኝ ነዉ። የኢትጵያና የኛ ነፃ መሆንም አስተሳሰብን ስነ ስራት ተከትሎ ለተመለከተዉ <<ሊሆን ይችላል>> የማይባል ነበር።

በጦር ግንባሩ ተሰልፎ የነበረዉ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ድል ተመትቶ ጠፍቶ፤ አንደ ቀደሙት ነገስታት የክፍላተ ሀገሩን ህዝብ አስተባብረዉ እየመሩ ጠላትን መቁዋቋም ይችሉ የነበሩት ንጉሰ ነገስቱ አገራቸዉን ትተዉ ተሰደዉ በየጫካዉ ተበታትነዉ ይገኙ ከነበሩት አርበኞች በቀር፤ በብሄራዊ ደረጃ የተደራጀ አንዳች ሀይል በልነበረበት፤ ፋሽስት ኢጣልያ ኢትዮጵያን ከያዘች በሁዋላ፤ አስዋን (ኢጣሊያ) አስወጥቶ፤ ኢትዮጵያን እንደገና ነፃ የሚያደርግ ሀይል ይገኛል ማለት ከማንም አሳብ የራቀ ነበር።

ለእኛ ለእስረኞችም ቢሆን፤የሁለተኛዉ የአለም ጦርነት ከመነሳቱ በፊትተስፋችን ከእስረኝነት ወጥተን ወዳገራችን ተመልሰን፤ቢቻል ወደ ሌላ አገር ማምለጥ፤ካልተቻለ እዚያዉ ፋሽስት ኢጣልያ የጫነችብንን የባርነት ቀንበር ከወገኖቻችን ጋር ተሸክሞ መኖር ካለሆነ በቀር፡ ነፃነት የምንመኘዉ ምኞት ፤ ወይም የምናልመዉ ህልም አንጂ፡ <<አናገኘዉ ይሆናል>> ብለን ተስፋ የምናደርገዉ አልነበረም። ነገር ግን እኛ ሳናስበዉ ሁለተኛ ያለም ጦርነት ተነስቶ ኢጣልያ በመጨረሻ ሄዳ ድል ከተመቱት መንግስታት ወገን ተሰልፋ ስለተገኘች፤ቅኝ ግዛቶችዋን እንድትለቅ በመገደድዋ፤ ኢትዮጵያ ነፃ ሆነች! አኛም ህልማችን እዉን ሆኖ ነፃ ሆነ! <<ደስታ ቀሊል>> ያባቶች ቢህል ነዉ! መልካምና ትልቅ ነገር ሁሉ ሲጠፋ የሚከብደዉን ያክል ሲገኝ ደስታዉ ብዙ ጊዜ አብሮ የማይቆይ ቀላል ይሆናል። <<ደስታ ቀሊል>!> የሚባለዉም በዚህ ምክንያት ነዉ። <<ደስታ ቀሊል! ደስታ ቀሊል!>>

እኛ በእስረኝነት እንዳለን ሌሎች ጉዋደኞቻችን በየጊዜዉ <<የጣሊያን መንግስት ምህረት አድርጎላቸዋል>> እየተባሉ ወደ ሀገራቸዉ በገቡ ቁጥር ተለይተን በመቅረታችን እናዝን ነበር። ነገር ግን፤ ሁለተኛ ያለም ጦርነት ተነስቶ፤ ያሜሪካና የእንግሊዝ መንግስታት ከተባባሪዎቻቸዉ ጋር ጦርነቱን የሚዋጉበትን አላማ <<አትላንቲክ ቻርተር>> በተባለዉ ማስታወቂያ ካስታወቁ በሁዋላ አሳበችንን ለወጥን። በዚያ ማስታቂያ የሚዋጉበት አላማ <<የአክሲስ>> መንግስታት (ጀርመን፤ጃፓን ኢጣልያ) በጦርነት
የያዝዋቸዉን አገሮች ሁሉ ነፃ አንዲወጡ ማድረግ መሆኑን ከገለጸበት ጊዜ ጀምሮ ፤ ቀደም ብየ እንዳመለከትሁት፤ እኛም ራሳችንን የነሱ (የነፃ አዉጪዎች) ባለኪዳኖች አድርገን ቆጥረን
በአካል ባይሆን በመንፈስ፤ በግብር ባይሆን በአሳብ፤ ጦሩነቱን አብረናቸዉ አንዋጋ ነበር! ስለዚህ ጠላቶቻችን ድል ተመትተዉ ከእስረኝነታችን ነፃ ስንወጣ <<እንኩዋን እስረኞች አንደሆንን ቆየን! አንኩዋንም በጠላቶቻችን ምህረት ሳይሆን እነሱ ድል ተመትተዉ በኛ አሸናፊነት ነፃ ወጣን!>> ብለን ደስታችን እጥፍ ድርብ ሆነ! እውነትስ ነፃነትን የቀማ ጠላት ወድዶ ሳይሆን ተገድዶ፤ ራርቶ ሳይሆን ፤ድል ተመትቶ፤ <<የቀማዉን ነፃነት ሲመልስ ደስታን እጥፍ ድርብ የሚያደርግ አይደለም? እዉነትስ ነፃነትን የቀማ ጠላት ባሸናፊነቱ ኮርቶ፤ በንቀት ቁልቁል እያየ፤ <ምህረት አድርጌላችሁዋለሁ!>> ከሚል ድል ተመትቶ ተምበርክኮ ሽቅብ እያየ <<የቀማሁትን ነፃነት መልሻለሁ!>> ሲል ማየት ፤
በእዉነት በበቀል መንፈስ አለመሆኑን መግለፅ እወዳለሁ።

ሁለጊዜም ቢሆን ከበደለኛ ቅጣት አንጂ ምህረት አደለም የሚፈለገዉ! የበደል መካሱ እንጂ ዳረጎት ማጉረሱ የተበደሉትን ክብር አይመልስም!ተበድለዉ ተደብድበዉ አንኩዋ፤ዳረጎት ሲያጎርስዋቸዉ ደስ ሚላቸዉ ዉሾች አንጂ ሰዎች አይደሉም! ስለዚህ ሰዎች አንደመሆናችን፤ ጠላቶቻችን ራርተዉ በችሮታ ሳይሆን ድል ተመትተዉ በግዴታ በጌትነታቸዉ ዳረጎት ከሚያጎርሱን፤ተገደዉ ነፃነታችን በመመለስ አንደ አቻዎች ሲክሱን፤ይህ ሁሉ ሲሆን ማየቱ፤ተገፍፈን የነበረዉ የሰዉነት ክብራችን ተቀምተን የነበረዉ ነፃነታችን ለመመለሱ ማረጋገጫ በመሆኑ፤ የፋስስቶች ድለ መሆንና በዚያ ምክንያት <<አለዉድ በግድ ያደርጉት የነበረዉ ሁሉ፤ ደስታችንን የደስታ ቁነጭላለት አደረገዉ!>> ያልሁ በዚህ መንፈስ አንጂ በበቀል መንፈስ አይደለም።

ከሎንጎቡኮ ተነስተን፤ባሪ እንደደረስን፤አዚያ የክፍሉ ነፃ አዉጭ ሰራዊት አዛዥና መኩዋነንታቸዉ ባንድ ትልቅ ሆቴል ድል የተመታችዋ የጣሊያን የጦር መኩዋንንት ባጠገቡ በሌላ ሆቴል እነደሚኖሩ ሰማን። የጣሊያን የጦር መኩዋንንት ቡናና ሌላ መጠጥ በሚጠጣበት አዳራሽ ለመግበት ቢፈቀድላቸዉም፤ ነፃ አዉጪዉ ሰራዊት የጦር መኩዋንንት በሚኖሩበት ሆቴል ለመኖር ያልተፈቀደላቸዉ መሆኑንም ሰማን። ለኛ ግን፤ የነፃ አዉጪ ሰራዊት በነበሩበት ሆቴል ቦታ ተሰጥቶን አዚያ አረፍን። አመሻሹ ላይ አራት ወይም አመስት የምንሆን ኢትዮያዊያን ቡና ለመጠጣት ወደ አዳራሹ ወርደን፤ ባንድ ጠረጰዛ ዙሪያ ተቀመጥን። ከኛ ትንሽ ፈቀቅ ብሎ በነበረ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠዉ ልዩ ልዩ መጠጥ እየጠጡ የሚጫወቱ ሰዎችም ነበሩ። አሳላፊዉ መጥቶ ቡና አስክናዝዝ በመጠበቅ ላይ አንዳለ፤ እኒያ ሰዎች እኛን እየተመለከቱ ሲነጋገሩ ቆዩና ከመሃከላቸዉ አንድ ትልቅ የጦር መኮንን ከተቀመጡበት ድንገት ብድግ ብለዉ፤እኛን እየተገላመጡ እያዩ አንደሚሸሽ ሰዉ ፈጠን ብለዉ ወጡ።

መኮንኑ የሸሹበትና፤እኛን እየተገላመጡ ያዩበት የነበረዉ ሁኔታ የተመልካችን አይን የሚጠራ ስለነበረ፤ ሁላችንም ወደሳቸዉ ማየት ስንጀምር <<ጀኔራል ናዚ! ጀኔራል ናዚ!>> አሉ፤ከማሀከላችን ጀኔራል ናዚን አዲስ አበባ ያዉቁዋቸዉ የነበሩት እየተቀባበሉ። ጀኔራል ናዚ የጣሊያን እንደራሴ ምክትል ወይም ዋና ባለስልጣን ሆነዉ ኢትየጵያ በሰሩበት ጊዜ፤በፖለቲካም፤ በጦርም ያመራር ችሎታቸዉ በብዙ ኢትየጵያዊያን ዘንድ፤ ከሌሎች ፋሽስቶች የተሻለ ከፍተኛ ግመት የተሰጣቸዉ ሰዉ ነበሩ። ታድያ ያንለት <<ያባረሩዋቸዉ ይመስል፤ ያን ያክል የሸሹ፤ ምናልባት እንዲያ ከፍ ብለዉ ይታዩና ይከበሩ በነበሩበት አገር ሰዎች፤ በኢትዮጵያዊያን ፊት ምረኮኛ ሆነዉ መታየቱ አሳፈሮዋቸዉ ይሆናል!>> ብለን ገመትን። ከመሃላችን አንዳንዶቹ ሲያዝኑላቸዉ ፤ሌሎች <<አንኩዋን እግዚአብሄር ይህን ለማየት አበቃን!>> እያሉ ደስታቸዉን ገለፁ። ወዲያዉ ደስታቸዉን ከገለፁት አንዱ ቀጥሎ ያለዉን ግጥም ነገሩን።

{{ላይኞቹ ሲወርዱ፤ ታችኞቹ ሲወጡ፤
የሚጫወቱበት ቦታ እየለወጡ፤
ይህ ነዉ ላስተዋለዉ፤የዚህ አለም ነገር
ቦታዉን ሳይለዉጥ፤ በላይ አንደሆነ ዘላለም የሚኖር
ከቶ ማንም የለ ከፈጣሪ ነገር}}

ባሪ በቆየነባቸዉ ጥቂት ቀናት፤ቴድሮስ ወርቅነህ፤እንግሊዝኛና ጣሊያንኛ አዋቂ በመሆኑ፤ እንግሊዞች እየረዳ ጣሊያን አገር ለመቆየት ፈቃደኛ አንደሆነ ተጠይቆ ስለፈቀደ፤ ከኛ ተለይቶ ከእንግሊዞች ጋር እንዲቆይ ተደረገ። ሁዋላ ግን፤ ከስንት ወራት በሁዋላ መሆኑን አላስታዉስም አነጂ፤ እሱም ሎንጎቡኮ የቀሩትም አንደና አገራቸዉ ገቡ።//-//

እኛም አንደዚሁ የፋሽሰቱ የወያኔ ዘረኛ ስራት ፈርሶ አገራችንን አንድናይ ያብቃን። ለከረሞ ሰዉ ካላለንም እጅ ሳይሰጡ እንዳማረበት መሞትም ያባት ነዉ። “የቆየ”፡ የጀግኖች አርማ!
አትዮጵያ በነፃነትዋ ለዘላለም ትኑር!
ጌታቸዉ ረዳ
ሳንሆዘ ካሊፎርኒያ

አሜሪካ