Wednesday, June 23, 2021

የብርሃኑ ነጋ አድናቂና ተከታይ “አንዱአለም አራጌ” ከመምህሩ “ከብርሃኑ ነጋ “ ጋር ለምን በሕዝብ ድምጽ ተዘረረ? ጌታቸው ረዳ Ethiopian Semay

 

የብርሃኑ ነጋ አድናቂና ተከታይ “አንዱአለም አራጌ” ከመምህሩ “ከብርሃኑ ነጋ “ ጋር ለምን በሕዝብ ድምጽ ተዘረረ?

ጌታቸው ረዳ

Ethiopian Semay



ሁለት ርዕሶች አሉኝ፡

ቅደም ተከተል ይነበባሉ።

የዘር ጭፍጨፋ አልተደረገም፤ - የሆነ ከሆነም ኢሕአዴግ ሳይሆን “እንደሚመስለኝ የችግሩ መንስኤ ያገኘነውን ነፃነት በግባቡ ያለመጠቀም ነው፡፡” (የዘር ጭፍጨፋ “ፍግር” በሚል ቃል የተካው “አንዱአለም አራጌ” የኢትዮጵያ ዜጐች ማህበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ምክትል መሪ)

ጋዜጠኛዋም ቢሆን የዘር ጭፍጨፋን “በግጭት” እየተረጎመች ሁለቱም ጠያቂና ተጠያቂ ነገሩን እንዴት አንደሚያዩት እንመለከታለን። ካሁን በፊት ከአንዲት ጋዜጠኛ ጋር ባደረገው ቃለመጠይቅ በኔው ድረገጽ የለጠፍኩት የአሻንጉሊቱ እምነት ምን እንደነበር ላስታውሳችሁ እና ዛሬ ኢዜማ የተባለ የአብይ አሕመድ አሻንጉሊት ከአማራ ማሕበረሰብ ሕዝብ ልብ የተገፈተረበት ምክንያት በጥቂቱ ምክንያቶቹን እነሆ ላስታውሳችሁ።

ለዚህ የተያያዘ አስታዋሽ ቀዳሚው ርዕስ ባጭሩ ላስነብባችሁ፡

ይህም የተማሩ አማራዎች መመርምር ያለበት የስነልቦና  ችግር በሚመለከት ነው።

ጎንደር ውስጥ ተመረጠ የተባለ የወያኔና የዛረ ኦሮሙማ አገልጋይ የሆነ ተመስገን የተባለ ሰው እንደተመረጠ ሰማሁ። ሕዝቡ በተማሩ ሰዎች ሰባኪነት እንደተወናበደ ጥርጥር የለኝም።፡በነገራችን ላይ የተማሩ አማራዎች ችግር አለባቸው የምለውም ለዚህ ነው። ካሁን በፊት ብዙ ማስረጃዎች አይተናል። ጸረ አማራ የሆኑት አንዳርጋቸው ጽጌ እና ብርሃኑ ነጋን የመውደድ በሽታቸው ከምን እንደተነሳ እኔ አላውቅም።

 

ለምሳሌ የዛሬዋ ብርቱ ታጋይ እየሆነች የመጣቺው መስከረም አበራ (ዛሬ ዛሬ እኔም እያመሰገንኳት ነው) ካሁን በፊት መምህርት መስከረም አበራ “የኦባገዳዎች ልብስ” እየለበሰች “ህልም የመሰለኝ እምዬ አንዳርጋቸው ፅጌ” እያለች ስትጽፍ ነበር። በስዋ የአማርኛ  ጠንካራ የአጻጻፍ ችሎታ እነዚህ ጸረ አማራ ፖለቲከኞችን ባደነቀችበት ብዕረዋ ብዙ የዋህ የተማረና ያልተነማረው አማራ እንደሰበከች ጥርጥር የለውም። የአማራ ምሁራን ችግር አለባቸው። ምን እንደሆነ ግን አላውቅም።

 

መሰረት አበራ አዲሱን መጽሐፍዋን ባላገኘውም ፤ አንዳንድ ወዳጆቼ እንደነገሩኝ “ኦሮሙማ” የሚለው ቃል የተሳሳተ ትርጉም እንደሰጠቺው እና ኦሮሙማ የሚለው ‘ፖለቲካ ቃል’ መሆኑን የነገራት ያለ አልመሰለኝም። ትግራዋይነት፤ … የሚለው ቃል “ሌላውን ለመፎካከር በአክራሪ ነገዳዊ “የኔነት ፍቅር” ቃል የታጨቀ አክራሪ የፖለቲካ ቃል ነው። ለወደፊቱ  በዚህ ሰፋ ያለ ትንታኔ አደርጋለሁ። “አማራ ነኝ! አማራዋ! ጎንደሬዋ! ትግራዋይነት!” የሚሉ የጽሑፍ መፈክሮች ሲለጠፉ አያለሁ። እነዚህ ሁሉ በጠባብ አክራሪ ነገዳዊ ስሜት የገፈተራቸው በልዩ ዘርነት /ነገዳዊነት/ የታጨቁ ስሜታዊ ምልክቶች ናቸው።

ለምሳሌ “ኦሮሙማ” የሚለው ቃል “ኦሮሞነት’ ማለት ነው የሚሉ ብዙ የተጃጃሉ ሰዎች ይጋሩታል (ከነዚህ የዋሃን አንዱ “ሳቅና ወግ” የሚባል ዝግጅት የሚያቀርብ “አበበ ቶላ” የሚባለው “እዚህም እዛም የሚረግጥ አቋመ ቢስ ሰው “ኦሮሞነት ማለት ነው ሲል አድምጬዋለሁ”። ኦሮሙማው ትርጉሙ የነገረን ብዙዎቻችን የምናውቀው ኦነጋዊው “አሰፋ ጃለታ” ማን መሆኑን በፖለቲካው ዓለም የቆየን ሰዎች እናውቀዋለን። አሰፋ ጃለታ የኦሮሙማ ቃል ትርጉም በእንግሊዝኛ የጻፈው ሁላችሁም የምታውቁት “ወጣት አቻምየለህ ታምሩ” ተርጉሞት እንዲህ ያቀርበዋል፡ “እዚህ ላይ ቀንጭቤ ነው ያቀረብኩት” ።

ትርጉም

 ኦሮሙማ ኦሮሞ ያልሆኑ ነገዶችን ኦሮሞ ማድረጊያ፣ የኢትዮጵያ ነገዶችን ጨፍልቆ በኦሮሞ ባሕልና ቋንቋ መሰልቀጥና መዋጥ፣ የኦሮሞ የተባለውን ሃይማኖት ብቻ እንዲቀበሉ ማስገደድና ባጠቃላይ ሰማዩንም ምድሩንም ኦሮሞ የማድረጊያ ፕሮጀክት እንጂ ኦሮሞነት ወይም የኦሮሞ ማንነት ማለት አይደለም። ይህንን የኦሮሙማ ትርጉም የሚነግረን የርዕዮተ ዓለሙ ፈጣሪ የኦሮሞ ብሔርተኛው ፕሮፈሰር አሰፋ ጃለታ ነው። በሌላ አነጋገር ኦሮሙማ ከኦሮሞ ማንነት ጋር አንድ አይደለም። እንዴውም ኦሮሙማ ለአብዛኛው የኦሮሞ ሕዝብ ጸረ ኦሮሞ የሆነ ፕሮጀክት ነው። በኦሮሙማ ፕሮጀክት እሳቤ መሰረት የክርስትና የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነ ኦሮሞ እንደ ኦሮሞ አይቆጠርም። የኦሮሙማ ፕሮጀክት አይዲዮሎጉ ፕሮፈሰር አሰፋ ጃለታ አንድ ኦሮሞ የክርስትናና የእስልምና እምነትን ከዋቄ ፈታ እምነት የሚመርጥ ከሆነ በፍቃዱ ኦሮሞነቱን እንደተወ ይቆጠራል ይላል።…. ለዚህም ማስረጃ

The concept of Oromummaa and Identity formation in contemporary Oromo society (Asafa Jalata- The University of Tennessee Knoxville) የሚለው የአክራሪው አሰፋ ጃለታ ጽሑፍ አንብቡ።

 

አሁን ወደ አንዳርጋቸው፡

 

ጥያቄ፡

በአንተ እምነት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ፖርቲዎችን የመሰረተው ኢህአዴግ አለ ብለህ ታምናለህ? 

 

አንዱአለም አራጌ መልስ፡

 

“እኔ አላምንም” ። ነገር ግን ክርክሬ ምን ያህል እንደሚወስደኝ አላውቅም አንዳንዴ ግራ ይገባኛል። እንደሚመስለኝ የቀድሞው ኢህአዴግ የለም፡፡ ምክንያቱም ኢህአዴግን ኢህአዴግ የሚያሰኘው ገዳይነቱ አፋኝነነቱናና ጨቋኝነቱ ነው፡፡” (በማለት አንዱአለም አራጌ ዛሬ ኦሮሙማው ፕሮጀክት ወደ ሥልጣን የመጣው  በንጉሥ አብይ አሕመድ ዘመን “ገዳይነት ፣ አፋኝነትና ጨቋኝነት” የለም ይለናል፡)

ጥያቄ፡

በርካቶች አሁን በየቦታው ያለውን ግጭት፣ግድያ እና መፈናቀል ከለውጡ ድክመት ጋር ያይዙታል፡፡ አንተ በዚህ ላይ ምን ትላለህ? ይህ ሁሉ የሚከሰተው ስር ነቀል ለውጥ ባለመምጣቱ ነው?

 

አንዱአለም አራጌ መልስ፡

ሞት እና መፈናቀሉን ያመጣው ኢህአዴግ ነው ወይ? እኔ እጠራጠራለሁ፡፡አሁን ኢህአዴግ ከስሩ ባለመነቀሉ እንግልቱ መፈናቀሉ እና ግድያው በዶ/ር አብይ መሰሪነት ነው ብሎ የሚያምን ካለ እኔ በበኩሌ አይመስለኝም፡፡ ይሄ ነገር እየተከሰተ ያለው በተለያየ አካባቢ ነው፡፡ አንደኛ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ታፍኖ እና ተጨቁኖ ነው የኖረው፡፡ ስለዚህ እንደሚመስለኝ የችግሩ መንስኤ ያገኘነውን ነፃነት በግባቡ ያለመጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ አንቺ አንድ አካባቢ ሄደሽ በቀናት ውስጥ የሆነ ነገር ተናግረሽ 40 እና 50 ሺህ ሰው ማሳለፍ የምትችይበት ሁኔታ ተፈጥሯል ፣ ነፃነት አለ መሰለፍ ይቻላል መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ያንን ነፃነት ለበጐ ነገር ሰዎች እየተጠቀሙበት አይደለም፡፡ ይሄ ነፃነትን በግባቡ ማስተዳደር አለመቻል ነው፡፡ ኢህአዴግ ከስሩ ቢነቀል ምን ትርፍ እናገኝ ነበር እኔ አላውቅም፡፡ ድሮም ቢሆን እኔ ኢህአዴግ እንዲነቀል ሳይሆን በምርጫ እንድናሸንፈው ነበር ፍላጐቴ ማንኛውም ቡድን በሀሳብ እንዲሸነፍ ነው የምፈለገው፡፡ ይሄ ባህል እንደቀጥል እንጂ የተለየ ሀሳብ ያለው ይነቀል አይደለም፡፡ ስለዚህ ለውጡ ስርነቀል ስላልሆነ ይሄ ሁሉ መፈናቀልና ግጭት ደረሰ ማለት ይከብደል ስርነቀል ለውጥ ብዙ ግጭት ደም መፋሰስና ንብረት መውደም ያመጣል፡፡  ደርግም ተነቅሎ ኢህአዴግ ሲመጣ ወደ ተረጋጋ ነገር አላመጣንም ሥርነቀል ለውጥ በራሺያም በሌላውም አገር እንዳየነው በመፍትሄ የተሞላ ነው ማለት አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ አሁን ላይ ያለው ግጭትና መፈናቀል መንስኤው ነፃነትን በአግባቡ ያለመያዝና ያለመረዳት ችግር ይመስለኛል፡፡

ከለውጡ በኃላ አንዱ የውጥረት መነሻ የአዲስ አበባ ጉደይ ነው ብዙዎች ብዙ ብለዋል አቋማቸውን ገልፀዋል ኢዜማ በአዲስ አባ ጉዳይ ላይ አዲስ እንደመሆኑ አቋሙ ምን ይሆናል?

አሁን እኔና አንቺ ስንነጋገር ከተቋቋምን ገና ሁለተኛ ቀናችን ነው ገና ከድካሙም አልወጣንም፡፡ ስለዚህ ገና በአጀንዳዎች ላይ መወያየት አልጀመርንም ተወያይተን ብንነጋገር ይሻላል፡፡ ዞሮ ዞሮ እኛ እንደምናምነው ኢትዮጵያ የኢትዮጵያዊያን ነች፡፡ አዲስ አበባም የኢትዮጵያ ክፍል ናት፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን በየትኛውም ቦታ መኖር ይችላሉ የኢትዮጵያ የሆነው ሁሉ የኢትዮጵያዊያን ነው፡፡ ስለዚህ የሆነ ቦታ ተከልሎ ለእከሌ ይሁን የሚባል ነገር የለም ለምሳሌ መቀሌም በይው ጐንደር ፣ ሐዋሳም ይሁን አዲስ አበባ የአንድ የተለየ ብሔረሰብ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያን ከተሞች ናቸው ብለን ነው የምናምነው፡፡ ከዚህ የተለየ ሀሳብ ካለን ወደ ፊት እናየዋለን፡፡”

በማለት አንዱአለም አራጌ የተፈጸመ ያለው የዘር ጭፍጨፋ የችግሩ መንስኤ ያገኘነውን ነፃነት በግባቡ ያለመጠቀም ነው፡፡ ይላል። እዚህ ላይ ጉልህ ጭፍጨፋ እየተፈጸመነት ያለው የራሱ ወገን አማራ ሕዝብ (እራሱ አማራ ነገድ ከሆነ) ለጭፍጨፋው (የዘአር ጥቃት መኖሩንም አያምንም- ምክንያቱም ኢሕአዴግ የሚባል ጨፍጫፊ ጨቋኝ አሁን የለም ሲል ይከራከራል) ዋናው ተጠያቂና የችግሩ (ችግር ብሎ ነው ጭፍጨፋውን የሚተረጉመው) መንስኤው “ሕዝቡ/አማራው/ያገኘነውን ነፃነት በግባቡ ያለመጠቀም ነው፡፡ ሲል ሕዝቡን ተጠያቂ ያደርጋል። ስለዚህ ለምን በሕዝብ ደምጽ 0 (ባዶ) ተሰጠው ለሚለው መነሻው ፤ ይህ አሻንጉሊትነቱና ግብዝነቱ መንስኤ ከዚህ ውጭ ሌላ ነገር የለም። ምናልባትም የስነ ልቦና ሕክምና ያስፈልገዋል እላለሁ። ጤነኛውን ሰው እንዴት እንዲህ ትላለህ የምትሉ ስለምትኖሩ ጤነኛ ከሆነም አነጋገሩ ለክፋ ትችትና ለአሳፋሪ ውጤት ዳርጎታል። ለወደፊቱ ሌሎቹ እንዲህ እንዳይደግማቸው ሕዝቡ እንዲያው “ሼር” አድርጉት።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ

“ኢትዮጵያ ውስጥ ጄኖሳይድ አልተፈጸመም” የሚባለው እውነት ነውን? ተሻለ መንግሥቱ Ethiopian Semay

 

“ኢትዮጵያ ውስጥ ጄኖሳይድ አልተፈጸመም” የሚባለው እውነት ነውን? 

ተሻለ መንግሥቱ 

Ethiopian Semay

6/23/2021

 

“ዳንኤል በቀለ” ዛሬ የፕሮፌሰሩን ንግግር ደግፎ ሲናገር ስሰማው እውነትን እየቀበሩ ሀሰትን የሚያነግሡ ሰዎች እየበዙ መምጣታቸው አሳሰበኝ፡፡” 

በቅርቡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ፍጂት (ጄኖሳይድ) እንዳልተካሄደ ሲናገሩ ተደምጠው ያንን ንግግራቸውን ሚዲያዎችና ግለሰቦች በክፉም በደግም ማለትም በመቃወምም በመደገፍም ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ እኔ እውነቱን ለመናገር በሤራም ሆነ በፖለቲካ ትንታኔ በቂ ዕውቀት ባይኖረኝም በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአማሮች ላይ የዘር ፍጂት ወይም ጄኖሳይድ አልተካሄደም ብዬ ለማመን የማንንም ባርኮትና ይሁንታ አልጠብቅም፤ እንደዚያ ባደርግ በሰው ደምና አጥንት የተራቀቅሁና የተዘባነንኩ ያህል ይሰማኛል፡፡ አሟሟታቸውን በካድኩት ወገኖቼ ደምና አጥንትም እንደቀለድኩ ነው የምቆጥረው፡፡ መዋሸት ለምን ያስፈልጋል? ማንን ከኃላፊነት ለማዳን? ምንስ ትርፍ ሊገኝበት? ጄኖሳይዱን የሚያካሂደው ወገን አምኖበት ግዳዩን በጠራራ ፀሐይ በይፋ እያስቆጠረ ሳለ ይህን ገሃድ እውነት መካድ የምን አትርሱኝ ነው? እኔን የሚገዛኝ እውነት እንጂ ሰዎች ተሰብስበው “ይህን ወሰኑ፤ ይህን አልወሰኑም” የሚለው አይደለም፡፡ ያ ዓይነቱ የጄኔቫና የኒውዮርክ ሞልቃቃነት አንድም አማራ ከኦነግ ሠይፍና ከሾኔ ሜንጫ አላዳነም፤ አያድንምም፡፡ እነዚህ ቅንጡ ሰዎች ሼራተንና ሂልተን ቁጭ ብለው “እነሱ ስላልወሰኑ ጄኖሳይድ ተካሄደ ማለት አንችልም” ማለታቸው ራሱ ሌላ ጄኖሳይድ እየጠሩ ነውና “ቀባጭ አማት ሲሶ ብትር አላት” እንዲሉ መጽሐፉ ፊት ባይነሳኝ ኖሮ እነሱም የቀባጭ ምሣቸውን እንዲያገኙ ልመኝላቸው በወደድኩ - ግን ይቅር ግዴለም፡፡ በምንም ምክንያት የፈጠጠ እውነትን መካድ ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀልና ኃጢኣትም ነው፡፡ ዳንኤል በቀለን ዛሬ የፕሮፌሰሩን ንግግር ደግፎ ሲናገር ስሰማው እውነትን እየቀበሩ ሀሰትን የሚያነግሡ ሰዎች እየበዙ መምጣታቸው አሳሰበኝ፡፡

 

የዘር ፍጂት በአጭሩ አንድ ነገድ ወይ ጎሣ በሌላው ጎሣ ወይም ነገድ ላይ ጥላቻንና በቀልን አሳድሮ ከምድረ ገጽ ሊያጠፋው ይፈልግና ከማሰብ ጀምሮ በማቀድ፣ ያሰበውን በመሰሎቹ መሃል በመቀስቀስና በማነሳሳት፣ ያነሳሳውን ወገኑን በጠላው ነገድ ላይ እንዲዘምት በማዘጋጀት፣ የዕልቂት ቅድመ ዝግጅቶችን በማከናወን በመጨረሻም ሃሳብና ዕቅዱን ወደተግባር ለውጦ ግዳይ ማስቆጠር ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ መራቀቅንና ፍልስፍናን የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ የአውሮፓና አሜሪካ ምሁራን ተሰብስበው በጄኖሳይድ ላይ ቢወያዩና ቢከራከሩ የሚሊዮኖች አማሮችን በትግሬና ኦሮሞ አክራሪዎች መጨፍጨፍ ሊመልሱት አይችሉም፡፡ ያልተነካ ግልግል ያውቃል ነውና እነዚህ “ምሁራን” የወገናቸውን ደም በማይረባ ፍልስፍና ሲለውጡት ሳይ ይሁዳ በ30 ብር ክርስቶስን የሸጠው በገንዘብና በርኩስ መንፈስ የመታወር ትርዒት ነው ትዝ ያለኝ፡፡ ይገርማል፡፡ በሰው ቁስል እንጨት መስደድ ለካንስ ይህን ያህል ቀላል ኖሯል፡፡ መማር የኅሊና  መታወርን ብቻ ሳይሆን የልብ መደፈንንም ማስከተሉን በነዚህ ሰዎች ተገነዘብኩ፡፡ እንኳንስ መማር ቀረብኝ!! ከዘግናኙ ተሞክሮኣችንና ከዐይናችን በላይ ሲሆኑ ሌላ ምን ይባላል? “ሩዋንዳና ኮሶቮ ብቻ ነው የዘር ፍጂት እንደተካሄደ የሚታመነው” ብለው የፈረንጅ አሽከርነታቸውን በአደባባይ አሰጡት፡፡ ፈረንጅን ማምለካቸው መብታቸው ነው፤ በሕዝብ ደም መቀለድ ግን አይችሉም፡፡

 

 

አንዳንዴ መማር ያደነቁራል፡፡ ከመማር የሚመነጭ ድንቁርና ደግሞ ካለመማር ከሚመጣ ድንቁርና የከፋ ጉዳት እንደሚያደርስ ከዶክተር ዳንኤል በቀለና ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ተረድቻለሁ፡፡ መማር አንዳንዴ ብልቃጥ ውስጥ የሚቀረቅር ይመስለኛል፡፡ እጅግ ብዙ መማር በብልቃጥ ውኃ ውስጥ የሚገኙ የዓሣ ዝርያዎችን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ይጠራ ሳያስብል አይቀርም፡፡ እውነት ነው የምላችሁ መማር እንደዚህ የሚያደነቁር ከሆነ ማይምነታችን ተፈልጎ የማይገኝ ወርቅ ነው፡፡ በመተከል፣ በወለጋ፣ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በአሰቦት፣ በአጣዬ፣ በከሚሴ፣ በሸዋ ሮቢት፣ በቤንሻንጉል፣ በባሌ፣ በሐረር፣ … በአማራነታቸው ምክንያት የሞቱ ዜጎች ደምና ዐፅም በገዳዮች ብቻ ሳይሆን የግድያውን ዓይነት በሚክዱ ሰዎች የእንቅልፍ ሰዓት እየመጣ ዕረፍት ይንሳቸው፡፡ ሁለተኛ ግድያ እኮ ነው!!

 

የት ሆፒታል እንደሆነ አላውቅም፡፡ አንድ ታማሚ በህክምናው ዓለም የሀኪሞች ቋንቋ “ኢክስፓየር” ያደርግና ወደ ሬሣ ክፍል ይላካል፡፡ በተላከ በማግሥቱ የሬሣ ክፍል ሠራተኛው ያን በድን ከፍኖ ቤተሰብ ወዳመጣው ሣጥን ሊከተው ሲል ሟቹ ድንገት ከሞት ይነቃል፡፡ እንደነቃም በድንጋጤ “ምንድን ነው? ምን እያደረግኸኝ ነው?” በማለት ከፋኙን ይጠይቀዋል፡፡ ከፋኙም ሥራውን ሳያቋርጥ “ሞተህ ነዋ! እየገነዝኩህ እኮ ነው” ይለዋል፡፡ ከሞት የነቃው ሰውዬም “አሃ! አሁንማ ከሞት ተመለስኩ አይደል? ተወኝ እንጂ!” በማለት ይከራከረዋል፡፡ ሬሣ ገናዡም “ወይ ሞኞ! አሁን አንተ ከዶክተሩ ልትበልጥ ነው? በል ሞተሃል ተብለሃል አርፈህ ተገነዝ?” አለው ይባላል፡፡

 

እነዚህ “ምሁራንም” (ብርሃኑና ዳንኤል) ስንትና ስንት አማሮች ወደውና ፈቅደው ባልተፈጠሩበት ማንነታቸው ምክንያት አንገታቸው ተቆራርጦ፣ ጭንቅላታቸው ተፈልጦ፣ ወገባቸው ተጎማምዶ የዐውሬ ሲሣይ ሆነው መቅረታቸውን፣ እንደየእምነታቸው የጸሎት ፍትሃት በክብር እንኳን እንዳይቀበሩ እንደአልባሌ ቆሻሻ በግሬደር በአንድ ጉድጓድ ውስጥ መቀበራቸውን ልቦናቸው እያወቀ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነውና እነሱና የነሱ የሆነ ስላልሞተ ብቻ ይህን መሳይ ወራዳ መልስ ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ የኛ የብዙዎቻችን ችግር የሌሎችን ችግር መረዳት አለመቻላችን ነው፡፡ አማሮች የተገደሉት በአማራነታቸው እንጂ በሰውነታቸው አይደለም፡፡ ይህንን እውነታ መካድ መማር ሳይሆን መደደብ ከዚያም ባለፈ ለጥቅም ወይም ለዓላማ አንድነት ሲባል የሚዘፈቁበት ኅሊናን በመሸጥ አሻሮ ይዞ ወዳለው የመጠጋት ፍላጎት የሚፈጥረው ቅሌት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ፍጅት በአማራ ላይ መታወጁንና ብዙ አማራ ማለቁን ለመረዳት የብርሃኑ ወይም የዳንኤል ወይም እነሱ የሚያመልኩት የጄኔቭ ጉባኤን ቡራኬ አይጠይቅም፤ ምን አገባቸውና? የዘር ፍጅትን ካላወቁ ከኛ ይማሩ፡፡ ምንም ምርምር አይሻም - “ነፍጠኛን (አማራን) አጥፍተን በኦሮሙማ የገዳ ሥርዓት የሚመራ ታላቁን አባት ሀገር ኦሮምያን እንገነባለን!” ብሎ በመነሳት በየቦታው የሚገኝን አማራ የሚያርድና የሚያሳርድ አክራሪ ኦሮሞ መኖሩ ለጄኖሳይድ መኖር ዋናው መገለጫ ነው፤ ከተፈለገም የወደቀውን ፀረ-አማራ የሕወሓት ማኒፌስቶ መጨመርም ይቻላል፡፡ ከዚህ በተረፈ በሰው ደም የሚቀልድ ከዚህ የጎመዘዘ ቀልድ ቢወጣ ይሻለዋል፡፡ ችግራችን የፍልስፍና ሳይሆን የኅልውና ነው፡፡ አጓጉል ለመሰልጠኑ የቄሱ ሚስት ትበቃናለች፡፡ የርሷ መሰልጠንስ በመጽሐፍ ማጠብ ብቻ ነውና ቀላል ነው፡፡ የነዚህ ግን በላኪዎቻቸው አስገዳጅነት ዓላማቸው በሰው ደምና አጥንት መቆመር በመሆኑ ከሁሉም ወንጀሎች ይከፋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1968 ጀምሮ በዐዋጅ የፀና የዘር ፍጂት አለ - ሊያውም በ40 እና 50 ሚሊዮን በሚገመት ሕዝብ ላይ፡፡ ስለዚህ ምሁሮቻችን ሆይ እባካችሁን ወደኅሊናችሁ ተመለሱ፤ ደግሞም ስለምንም ምንነት ይበልጥ ለማወቅ አንብቡ፡፡ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ትሉ የለም?….