Thursday, October 7, 2021

የአብይ አህመድ መስቀል አደባባይ ሽር ጉድና የሂትለር የበርለን ኦሎምፒክ ስታድየም ሽልምልም ልዩነት!! (ኢትዮ ሰማይ) (Ethiopian Semay) 10/7/2021

 

የአብይ አህመድ መስቀል አደባባይ ሽር ጉድና የሂትለር የበርለን ኦሎምፒክ ስታድየም ሽልምልም ልዩነት!!


 (ኢትዮ ሰማይ)

(Ethiopian Semay)

10/7/2021

ሰሞኑን በአጋጣሚ “THE FALL OF BERLIN- (Anthony Read and David Fisher)  የሚል መጽሐፍ ገዝቼ ሳነብ ነበር። መጽሐፉ የጀመረው “So much glory, and so much shame” በሚል በምዕራፍ 1 ጀርመን ዓለም አቀፉ የኦለምፒክ ዝግጅት አስተናጋጅ ሆና የተመረጠችበት ወቅት እንደነበር እና በወቅቱ ሂትለር በ1936 ሊደረግ የተሰበው ዕቅድ ፍላጎት ባይኖሮውም ዝግጅቱ ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊት የታቀደ ስለነበር፤ ዝግጅቱ “an invention of Jews and freemason” “የአይሁዶች እና የፍሪሜሶን ፈጠራ” በሚል እየተቃወመው እንደነበር ቢታወቅም ፤ የጀርመን ኦሎምፒክ ኮሚቴዎቹ ግን ሂትለርን ለማሳመን “ለናዚው አዲስ መንግሥት አጋጣሚ የተክለሰውነት ማስተዋወቂያ ይጠቅመናል” በሚል ቢገፋፉትም “እስከዚያም ፍላጎት ባይኖሮውም፤ ከትንሽ ጊዜ ማሰላሰል በሗላ ግን ኦለምፒኩ አጋጣሚ እንደሚሆንለት በማመን በሙሉ ስሜት ተቀሳቀሶ “በ1916 ታቅዶ የነበረው ትንሹ ‘የኦሎሚክ ሜዳ’ ፈርሶ በምትኩ በጣም ሰፊ የሆነ  ዓለምን ያስደመመ ሙሉ ዝግጅት እንዲደረግ አዘዘ”። የሚገርመው ደግሞ የዱሮው ግንባታ ለማፍረስ ብቻ “አንድ አመት” ፈጀበት።

በወቅቱ ከ 4 የበርሊን ተባዕት (ወንድ) አንዱ ሥራ ፈት ሆኖ በዌልፌር (መንግሥታዊ ዕርዳ) ድጎመ ሲኖር ነበርና ሰፊ የሥራ ዕድል በርሊን ከፈተላት። ወጪው ለሰው ጉልበትም ቅባትና ሽልምልም ማሳመሪያም ጠቅላላ የወጣው 77 ሚሊዮን ማርክ ሲሆን የገንዘብ ጠበብቶቹ እና አንዳንድ አማካሪዎቹ ግን የወጪው ብዛት እጅግ ጀርመንን እዳ ውስጥ እንደሚዘፍቃት ቢቃወሙትም “ሂትለር” ግን በርሊን ድረስ ለመምጣት የተዘጋጀ “ዓለም አቀፍ ቡርዣ” ስለሚኖር የበለጠ እናተርፍ እንደሆን እንጂ አንከስርም፡ በማለት ተከራከረ።

ለክርክሩ ለውሳኔው ዋና ኢላማ ምንድነው ብትሉኝ “ጀርመን በወቅቱ የውጭ ምንዛሪ (ፎረይን ሃርድ ካረንሲ) ስላልነበራት ጎብኚዎቹ ይህንን ችግር መሸፈን እንደሚችሉ በመከራከሩ፤ እውነትም እንዳለው 77 ሚሊዮን ማርክ ያስወጣው ግንባታ እና ሽልምልም “ግማሽ ቢሊዮን” ማርክ የውጭ ምንዛሪ ገቢ አስገኘለት።

እንግዲህ እነ ሂትለር ያንን መሳይ ኦለምፒክ በሽልምልም ያጌጡበት ምስጢር አገራቸው በገንዘብ ዕጥረት ትሰቃይ ስለነበር፤ መሪውና ጥቂቶቹ ባሰሉት ሂሳብ የበርሊን እና የተቀረው የጀርመን ኗሪ የሥራ ዕድል ከፍቶ የውጭ ምንዛሪ አስገኘለት።

በአንጻሩ ኢትዮጵያ ታይቶ በማይታወቅ የርሃብ፤የመፈናቀል፤የጦርነት እና የነገድ ዘር ጭፍጫፋ እንዲሁም የምጣኔ ሃብት ንረት ስተሰቃይ በምትኖር ያለች አገር ውስጥ “ሽቅርቅሮቹ” የአብይ አሕመድ ተሿሚዎች እንደ ተዋንያን እና ሞዴሎች ሆነው አንድ አይነት ልብስ በመልበስ ተሽቀርቅረው ለሹመት ምረቃ ተሰልፈው ሲገቡ አይተን “እግዚኦ” ብለን በዛው መደነቃችን ሳያባራ፤ በጥቂት ቀናቶች ልዩነት የአጼ ሃይለስላሴን የንግሥና ድግስ እና ሽር ጉድ በሚያስንቅ መልክ በራስ ግንባታ ጭንቀት የሚሰቃየው “ንጉሥ ለመሆን ሲመኝ የነበረው 7ኛው ንጉሥ አብይ አሕመድ ሌላ ንቅዘት ውስጥ ገብቶ ለማየት በቃን።

ኮለኔል አብይ አሕመድ ያለመውን ሕልሙ አክሱም ጽዮን ድረስ ሄዶ መቀባት ባለመቻሉ “ንጉሥ በሚመስል” የንጉሰነገሥታት የቅብና የምረቃ በዓል “መስቀል አደባባይ” ከፍተኛ ወጪ በማውጣት በሥራ የተጠመዱ “ዕረፍት ያማራቸው “የውጭ እንግዶችን በመጋበዝ “ንግሥነቱን” እንዲመርቁለት አስገራሚ በዓል ያካሄደው “ኮለኔል አብይ አሕመድ” እንደ ሂትለር የውጭ ምንዛሬ ማስገቢያ ሳይሆን ከተራበው ሕዝብ ጉሮሮ በመንጠቅ የመንግሥት ካዝና ለግል መሽቀርቀሪያ እና አላስፈላጊ ድግስ ያዋለ “ብኩን” ሰው ነው።

ይህ ሰው መሪ ለመሆን እንደ ኔልሰን ማንዴላ 27 አመት እስርቤት ሳይሆን፤ ጸረ ኢትዮጵያ ሃይላትን ምስጢር ሲየቀብል የነበረ፤ ጋዜጠኖች እና ንጹሃን ፖለቲከኞችን ሲያሳስር የነበረ የወያኔ የስለላ መ/ቤት ሹም ሆኖ “ያደፈ” ታሪክ የላው ሰው ነው። ኔልሰን ማንዴላ ድግስ ሲደረግለት ለከፈለው መስዋእት ታሳቢ በማድረግ እንጂ እንደ አብይ የመሰለ ወንጀለኛ እና የሽብር ስርዓትን ሲያገለግል የነበረ ሽብርተኛ (ያውም እስካሁን ድረስ ያለ ምንም ተጠያቂነት ሽብርተኛውን ስርዓት እና ሹመኞቹን ይዞ እየገዛ ያለ) ኮለኔል በዚያ  ይነት የሕዝብ ካዝና የሚያራቁት ምርቃ ተደርጎ ማየት አገሪቷ “ከድጡ ወደ ማጡ” እዘየዘቀጠች እንደሆነ ልቦና ያለው ሰው በቀላሉ ማየት ይችላል።

እንዲህ ያሉ መሪዎች ሥልጣን ላይ ብዙ ሊቆዩ ይችላሉ። ምክንያቱ በጣም ቀላል ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ የሲቪክ/የማሕበረሰቡ/ ሱታፌ ለ30 አመት በየጊዜው እየቀነሰ ፤ በአንጻሩ “ትግሉ ርቀው በሚገኙ የባሕር ባዶ ተቃዋሚ ልሳኖች” በመወሰኑ ብቻ ውስጣዊ ልሳኖች ተውጠው (ምዩት ሆነው)፤ ጠንከር ያሉበትን ተቃዋሚዎቹ “እስርቤት በማጎር” በየወቅቱ  የሚለዋወጡ “ጋጠወጥ” መሪዎች ተንደላቅቀው በመግዛት ላይ ናቸው።

 የማሕበረሰቡ ሱታፌ “መርገብ” ምክንያት ስንፈትሽ በአምባገነን መሪዎች አመራር “ስለረካ” ሳይሆን እነዚህ በሠልጣን የባለጉ የ30 አመት ወንጀለኞችና ሌቦች/ በተቃዋሚውና በማሕበረሰቡ ህይወት ላይ በሚወስዱዋቸው “ጨካኝ እርምጃዎች” ይቋቋመዋል ተብሎ የሚገመተው አዲሱ ትውልድ “የሗሊት በመሸማቀቅ” እንደ የያይኛው ዘመን ትውልድ አምባገነነኖችን መጋጥ ስላልለመደው ተቃውሞው ረግቧል።

አጽንኦት የሚያስፈልገው ‘የፖለቲካ እና የማህበራዊ ተሳትፎ ማሽቆልቆል’ ሰበቡ በአብዛኛው የትውልዶች ልዩነት ጉዳይ ነው። የወጣቱ ትውልድ ተሳትፎ መጠን ከቀድሞው ትውልድ በጣም ያነሰ በግምት ፣ ከ 1960 ዎቹ በፊት እና በኋላ የተወለዱት ሲነጻጸር በ 1980 ዎቹ እና በ 1990 ውስጥ ያደጉ ወንዶች እና ሴቶች በቁጥር ቢበዙም ስለ “public affairs” እምብዛም አያውቁም። በዚያው ላይ በመጽሐፌ “የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ ከምን የመነጨ ነው?” በሚለው በምዕራፍ 5 በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘሩ 4ቱ የጥቃት ሂደቶች (ሳብቨርዥን/ብከላ) ያቀረብኩት ትንተና ስትመለከቱ በ30 አመት ውስጥ የተቀረጸቀው የወጣቱ ሕሊና ተለያይቶ በጎጥና በነገዱ እንዲሰራ በመደረጉ “ለገዢዎች” እጅግ አመች በመሆናቸው የተበተኑ በጎች ሆነው ለተኩላ ገዢዎች ጥቃት ተጋልጠዋል። አብይ ይህንን ለማስቀጠል ፍላጎቱ የናረ ነው። 3 አመት ለውጥ ሊያመጣ ያለቻለበትም ምከንያትም የተበታተነው “በገ መሳይ ወጣት” ለመግዛት አመች ሆኖ ስላየው፤በዛው ይቀጥልበታለ።

አዳማቂ ሆነው የቀረቡት ማሕበረሰብን ያነቃሉ የተባሉ የኪነት ሰዎች በብከላው ውስጥ ተዋናይ ሆነው የገዢዎችን ፕሮፓጋንዳ በማስተጋባት ግምባር ቀደም ተዋናይ ሆነው 27 አመትም እንዲሁ 3 አመትም አይተናቸዋል። ዛሬም በዛው የቀጠሉ አሉ። ይህ ለትግሉ እጅግ ጎጂ ሆኖ ቆይቷል።

የከተማው ወጣት ስንመለከት፤ በ30 አመት ውስጥ በከተማው ውስጥ ያደጉ ወጣቶች  እንደ ጃፓናዊያን እና እንደ እኛው 60 ዎቹ- ካስተዳደጋቸው እጅግ የተለየ ሆነው ስላደጉ ስለ አገራቸው ‘አንድነት እና ትግል፤ሰንደቃላማ እና አገራዊ ፍቅር’ ቀርቶ እናቶቻቸውን ምን ብለው እንደሚጠርዋቸው ጋዜጠኛ መሐመድ ሰልማን “ፒያሳ ማሕሙድ ጋር ጠብቂኝ” በሚለው መጽሐፉ ላይ በጥቅስ መጽሐፌ ላይ ለታሪክ ያስቀረሁትን ጥቅስ እንዲህ ይላል፡

‘ዳዲ ‘ማሚ’ እያሉ ወላጆቻቸውን የሚጠሩ ህፃናት በነዚህ ት/ቤቶች ‘እትየ፤ እቴቴ ፤ እታበባ ፤እማዬ ፤ እታብዬ’ ሚሉትን “ፋራ” ተደርገው ይታያሉ። ‘እትየ፤ እቴቴ ፤ እታበባ..እማዬ፤እታብዬ’ የሚሉትን አንጀት ሰርስረው የሚገቡ ውብ ቃላት፤ ከልጆች አፍ ለመስማት ከከተማ ወጣ ማለትን ይጠይቃል።

ህጻናት አማርኛ የሆነ መዝናኛ አይቀርብላቸውም። የኢትዮጵያ ህጻናት “እስፓይደር ማን” በእነ “ሲንደሬላ” በእነ “ሲምባ” ፊልሞች አፋቸውን ለመፍታት ይገደዳሉ። አባባ ተስፋዬ “ልጆች-የዛሬ አበቦች፤የነገ ፍሬዎች-ቁጭ በሉ፡ አትጋፉ…ጎበዝ ልጆች!” በሚሉበት ሰዓት “ሪሞት” የያዙ በዙ የአዲሲትዋ ኢትዮጵያ ሕፃናት “ዋት/what!” በማለት ያዙትን የርቀት መቆጣጠሪያ መጫን ጀምረው ነበር።” ሲል (መሐመድ ሰልማን) በሚገርም ቅኝት የ30 አመት ወጣት አስተዳደግ ምን እንደሚመስል አስቃኝቶናል።

ብዙዎቹ የዛሬ የአብይ አሕመድ “ካልቶች” በተለያዩ የየግል ምክንያታቸው አብይን በመደገፍ የምናያቸው ከድሮዎቹ ትውልዶች ቢኖሩባቸውም ብዙዎቹ ግን “በተዋበ ሰላቢ ንግግርና በማራኪ የሙዚቃ ወታደራዊ ማርሽ” ተሎ ሸብረክ ብለው ለአብይ የተንበረከኩ ክፍሎች “ከላይ ባየነው ቅኝት ያደጉ ወጣቶች ናቸው”።

ትናንትም ዛሬም አብይ አሕመድ በከፋ መልኩ የትግራይ ጦርነት ያበላሸው እንዳይበቃ ያንን ቡርቦራ በመጠቀም ሕዝብ በተራበበት ወቅት በብድር እየተለመነ የተገኘውን የሕዝብን ካዝና አራቁቶ ለግል ዝናው እና leisure ለታዳሚዎቹ “ቅንጦት” ማዋሉ በንቅዘት ወንጀል ተጠያቂ ነው። ይህ የኮለኔል አብይ አሕመድ የገንዘብ ማባከን ወንጀል “ወያኔ” በረሃ ውስጥ “ማሌሊት” ድርጅት ሲመሰርት በልመና ዕርዳታ የተረከበውን ገንዘብ ለድርጅቱ ምስረታ በዓል እና አዳዲስ የድርጀቱ መሪዎች ማስመረቂያ ያዋለው የገንዘብ ማባከን ጋር የሚነጻጸር አስገራሚ የዘመናችን ክስተት ነው።

(ሼር አድርጉና ሕዝቡ ይንቃበት!!!!! መረጃ የሕሊና ዋነኛው አዋጊ መሳሪያ ነው፡፡ ሼር!! ሼር!!)

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)