Monday, November 8, 2021

ያመነም ያላመነም! ጌታቸው ረዳ ኢትዮ ሰማይ (Ethio Semay) 11/8/2021 ዕለተ ሰኞ በፈረንጅ

 

 

ያመነም ያላመነም!

ጌታቸው ረዳ

ኢትዮ ሰማይ

(Ethio Semay)

11/8/2021

ዕለተ ሰኞ በፈረንጅ

ሰሙኑን እየተካሄደ ያለው በንጹሃን የትግርኛ ተናጋሪ የትግራይ ተወላጆች ላይ እየተካሄደ ያለው በየመንገዱ ማፈስና በየመንደሩ ምንጠራ በማካሄድ እየታሰሩ ያሉት ንጹሃንን ያካተተ እስር ቁጥራቸው ለማወቅ አስቸጋሪ ሆኗል።

ቁጥሩን ለማወቅ የሚያስቸግረው ምክንያት ብዙ ሰዎች ከሰዎች ጋር የማይተዋወቁ፤ ቤተሰብ የሌላቸው ከመሆናቸው ሌላ “አሜሪካ በሁለተኛው አለም ጦርነት በ‘ጃፓን አሜሪካዊያን’ ዜጎች ላይ እንደፈጸመቺው የአፈሳ ዘመቻ፤ በአገራችንም በትግራይ ነገዶች ላይ ሴቶች እና ወንዶች ያካተተ እስር ስለሆነ የታሳሪና ማንም ዘረኛም በሚወስደው ነጻ እርምጃ የግድያና የዘረፋ ብዛት መለየት አልተቻለም።

በንጹሃን የትግራይ ተወላጆች ላይ ጥላቻ ያደረባቸው ሰዎች ተደጋጋሚ የመጨፍጨፍ ፍላጎት የሳዩ ከነበሩት አንዱ ለበርካታ አመታት ዘረኛነቱን ስንቃወመው የነበረውን የኢሳት ቴ/ቪ ጋዜጠኛ የሆነው መሳይ መኮንን (ካቡጋ) ለመንግሥት ያቀረበው ጥሪ እና አቤቱታ የጅምላ እስር ጥሪውን ተከትሎ ብዙዎቻችን አስቆጥቶናል።

ይህ “ያመነም ያላመነም በአንድ ሰይፍ የመጨፍጨፍ” ባሕሪ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን በደርግ ጊዘ የተጀመረ ነው። ዛሬ እየከናወነ ያለው ይህ በትግሬዎች ላይ የጅምላ እሰር በደርግ ጊዜ “ያመነመ ያላመነም” የሚባል  መጽሐፍ ስታነቡ ታሪክ እራሱን እንዴት እንደሚደግም የዚያኛው ቅጅ መሆኑን ታያላችሁ።

የትግራይ ብሔረተኞች በአማራ ላይ ያላቸው ጥላቻ በሚለው መጽሐፌ ውስጥ “በደርግ የቤርሙዳው የትግሬዎች ስቃይ” በሚል የተፈጸመ የጅምላ ግድያ እና አሰቃቂ እስር ገልጫለሁ።

ዛሬ ያመነም ያላመነም በትግሬዎች ላይ የታወጀው የጅምላ አፈሳ በእነ “መሳይ መኮንን” ጥሪ አቅራቢነት አገሪቱን እየመራ ባለው በፋሺሰቱ አብይ አሕመድ መሪነት በደርግ ጊዜም ተመሳሳይ ድርጊት በመፈጸሙ  “ደርግ” የማነቂያ ገመዱ ለወያኔዎች በማቀበል ሞቱን እንዴት እንዳቀላጠፈው ለዛሬው ተመሳሳይ ክስተት ከታች እንመልከት።

  ደራሲ ግርማይ አብርሃ በሐምሌ 2004 በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ባሳተመው “ያመነም ያላመነም …” በተባለው መጽሐፍ ሁኔታው እንዴት እንደነበር በሰፊው ያሳየናል። በነገራችን ላይ ግርማይ እራሱ የወቅቱ ታሳሪ ሆኖ ያየው ምስክርነት ነው የጻፈው።

መጽሐፉ ረዢም ስለሆነ አንዳንዶቹ ለአንባቢ እንዲመቹ እያሳጠርኩ አቅርቤአቸዋለሁ።

እንዲህ ይላል፤፡

“ደርግ ሰርጎ ገብን ለመንቀል ሲል ወደ ጅምላ እስራት ማዕበል መግባቱ  በሚገርም ሁኔታ ፖለቲካዊ ክስረት ከመከናነቡ ባሻገር እራሱ በድንገተኛ ሞት እንዲሞት ምክንያት ሆኗል።

በጅምላ የማሰር እና የመግደል እርምጃ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት ተከታዮች እና ተከታዮች ያለሆኑት ላይ እርምጃ የመውሰድ  አጠቃላይ የደርግ መንግሥት ተፈጥሮአዊ ባህሪ ቢሆንም፤ ይህ በዓይነቱ ለየት ያደረገው ነገር ቢኖር ‘በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የታቀፉት ደርግን የተቀበሉ

‘ት ሓ ህ ት’ ን በጠመንጃ የተፋለሙ፤ በቀይ ሽብር ወቅት በካድሬነታቸው ብዙ የትግራይ ተወላጆችን ሲደበድቡ እና ሲያስረሽኑ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን በአንደኛ ደረጃ ተጠርጣሪ በማድረግ በዓይነቱ መጠነ ሰፊ የተለየ ክስተት ነበር። በጣም አድርጎ እጅግ የሚገርም ክስተት!

 ይህ በ1976 ዓ.ም ትግራይ ተወላጅ በሆነው ሁሉ የተከናወነው የጅምላ እስራት ሲከናወን “የህወሓት” አባላትን ከመንግሥትና ኢሠፓአኮ መዋቅር “መመንጠር በሚል” ስም በትግራይ፤ አዲስ አባባ እና በመላ አገሪቱ በግል እና በመንግሥት ሥራ ተመድበው ይሰሩ የነበሩት ምሁራንም ያልተማሩትንም ሁሉ “ዒላማ” በማድረግ ፖለቲካ ውስጥ ይገባሉ ተብሎ በፍጹም የማይታሰቡና የማይጠረጠሩ ንጹሃን ሁሉ አስከፊ በሆነ የጅምላ እስራት ድብደባ እና በገመድ እያነቁ መግደል ተጀመረ።

በ1974 ዓ.ም ማብቂያ ላይ በኲሓ እና በመቀሌ የነበረው የህወሓት መዋቅር በደህንነት መስርያ ቤቱ ደርሶበት ከአባላቱ ውስጥ ሁለቱ ሲያመልጡ ሌሎቹ ግን በሙሉ ተይዘው ታስረዋል። በታሥሩት ላይ በተደረገው ምርመራ አማካይነትም እስከ 1976 ዓ.ም ድረስ የህወሓት አባላት የነበሩ ሰዎች ተጋልጠው ከየቦታው ተይዘዋል። ይሁን እንጂ የዚህ ምርምራ ውጤት በትክክልለኛው የድርጅት አባላት ብቻ መገደብ የነበረበት ሲሆን የምርመራ ድርጅቱ ሆን ብሎ በፈጠረው ግፍት ምክንያት በርካታ ንፁሃን ዜጎችን እንዲታሰሩ አድርጓል (አበሪ 4 ይመልከቱ)፤” ይላል፡

በመቀጠልም ግርማይ እንዲህ ይላል፡

ይህ ቀስ እያለ በትግራይ ክ/ሀገር የጀመረው የጅምላ አፈሳ “የአብዮቱ ጋሬጣዎች ለማስወገድ” በሚል ሽፋን ወደ መላው አገሪቱ በነበሩ የትግራይ ተወላጆች ማፈስ ተጀመረ።’’

በማለት ይተነትናል።

አሁን በዘመነ ብልጽግና (በዘመነ ኦሮሙማ) እየተፈጸመ ያለው የጅምላ እስራት በሚገርም ሁኔታ  በደርግ ዘመን የተፈጸመው የጅምላ እስራት ተመሳሳይነት አንድ ነው።

የያመነም ያለማነም መጽሐፍ ደራሲ እንዲህ ይላል፤

‘ደርግ በጅምላ እንዲያስር ያስገደደው አንዱ ምከንያት ሲገልጽ ሰላማዊ ዜጎች በመምሰል በመንግሥት መዋቅሮች ተሰግስገው ሠራዊቱን በማስመታት እና መረጃ በማቀበል አንዳንድ ጉዳቶች እንዲደርሱ በማውረዳቸው “የአብዮቱ ጋሬጣዎች ማስወገድ” አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።’ ይላል ደርግ ለጅምላው እስራት ምክንያት ሲሰጥ።

በተመሳሳይም የጀናሳይድ ቅስቀሳ ወትዋቹ እና ጥሪ አቅራቢው መሳይ መኮንን (ካቡጋ) ለመንግሥት ባስተላለፈው ጥሪ ተቀባይነት አግኝቶ እውን እየሆነ ያለው እርምጃ ምክንያቱን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡

“የህወሀት ደጋፊዎች፣ በየከተማው የሚገኙ፣ መረጃ ከማቀበል አንስቶ በተደራጀ ሁኔታ ታጥቀው አስቀድመው የስነልቦናና ሌሎች ጥቃቶችን በህዝቡ ላይ የሚፈጽሙና በቀጣይም በስፋት ሽብር በመፍጠር ለህወሀት ታጣቂዎች ጥርጊያ መንገድ የሚያመቻቹት ላይም …..ከህወሀት ጋር ግንኙነት የሌላቸውንም ሆነ ያላቸው የትግራይ ተወላጆችን በጊዜያዊ ማቆያ ጣቢያዎች እንዲሰባሰቡ ለኢትዮጵያና ህዝቧ የህልውና ጉዳይ ነው። ምርጫ የለንም። ይህም እርምጃ በከፍተኛ ትኩረት፣ ቁርጠኝነትና ፍጥነት ተግባራዊ መደረግ አለበት። እነሱን በጉያ ይዞ ጦርነቱን ማሸነፍ በፍጹም የሚቻል አለመሆኑን በማሳሰብ ለእነሱም ደህንነት ጭምር ሲባል እርምጃው በአስቸኳይ ሊወሰድ ይገባል። በዚህን ወቅት እያንዳንዷ ሰዓት ወሳኝ ናት። ጊዜ ከእኛ ጋር እንዲሆን ማድረግ አለብን።” (ኢሳት ጋዜጠኛ  መሳይ መኮንን)።

ይህ በዘር ጽዳት የታጀበ ጸረ ሕዝብ አዋጅ ለደርግ ምን አስገኘለት ለሽምቅ ተዋጊዎችስ አንዴት ጠቀማቸው? የሚለው ለማየት ወደ “ያመነም ያላመነም መጽሐፍ ልውሰዳችሁ፡

ደጋፊዎቹን በስመ ትግሬ ሲጨፈጭፋቸው ደርግ በገዛ እራሱ ሞቱን አስተናገደ። የተጀመረው ማዕበላዊ የጅምላ እስራት ለወያኔዎች ስለተነገራቸው፤ በቁጭትና በፍጥነት ተነሳስተው “ሕዝቡ እንዲተባበራቸው በማድረግ…የሕዝባዊ መራጃ (ፒ 1) ወኪሎቹን በየከተማው ማእከላት፤ በጠላት ሠራዊት፤ በቀበሌዎች፤ በሚሊሺያ/ነጭ ለባሽ/ በአገዛዙ በነበሩ ሲቪክ ማሕበራት፤ አስፈላጊ በሚባሉ የመንግሥት መዋቅሮች “ሠርገው” እንዲገቡ በማድረግ ባጭር ጊዜ በደርግ ላይ የበላይነት ተቀዳጁ።

ደርግ እራሱ በጀመረው ሕዝብን የማስጨነቅና የማበሳበስ ዘመቻ በትግራይ ከተሞች ሽንፈቱን ሙሉ በሙሉ እንዲቀበል ተገደደ ። ይህ ሁሉ የሆነው በ1976 ዓ.ም አገልጋዮቹ የነበሩት የትግራይ ተወላጆች የሆኑ አስተዳዳሪዎች፤ካድሬዎችና ፤ምሁራን እንዲሁም ነጭ ለባሾችን ሰብሰቦ አፍሶ እሰር ቤት እንዲገቡ በማድረጉ ያልጠበቀው ሞቱ ተጎነጨ”።

በማለት ደራሲው ግርማይ አብርሃ ይነግረናል።

የአብይ መንግሥት እና አብይን የሚደግፉም ሆኑ የማይደግፉ የትግራይ ንጹሃን መንገላታት የሚደግፉ የኢንተርሃሙዌው ቡድን ካሁኑ ካለቆመ የራሱን መዋቅራዊ ሞት ማበሰር ብቻ ሳይሆን “የኢትዮጵያን አንድነት” መፍረስ አደጋን ይጋብዛል።

በሚቀጥለው ክፍል 2 ልብ የሚሰብር አሳዛኙ የንጹሃን የትግራይ ተወላጆች “ትግሬዎች በመሆናቸው ብቻ”  አገራቸውን በወታደርነት አገልግለው ከፍተኛ ማዕረግ የነበራቸው የሰራዊት አዛዦች እና ጡረተኞች እንዲሁም ስመ ጥር ዶክተሮች በጅምላ ታስረው በግርፋት እና በገመድ ከበዓሉ ግርማ ጋር ቤርሙዳ ተወስደው በኮማንዶ ወታደሮች በ 4 አቅጣጫ በመጎተት“በገመድ እየታነቁ” እንዴት እንደተገደሉ እንመለከታለን። ይህ የጅምላ እስራት የደርግ ዕድሜ ሲያሳጥረው ፤አሁን እየተወሰደ ያለው የጅምላ አፈሳም ያ ዕጣ የናፈቀው ይመስላል። ከላይ በፎቶ የታዩት የትግራይ ተዋለጆች ከፍተኛ ምሁራን አገዳደል በሚቀጥለው ይቀርባል፡

ጌታቸው ረዳ

ኢትዮ  ሰማይ