Wednesday, April 24, 2019

ኢሳትዋ ርዕዮት አለሙ ኢሳት ውስጥ ባሉ የአብይ አሕመድ አሽቃባጮች ዝግጅትዋ እየታፈነ ነው! ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)


የኢሳትዋ ርዕዮት አለሙ ኢሳት ውስጥ ባሉ የአብይ አሕመድ አሽቃባጮች ዝግጅትዋ እየታፈነ ነው!
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)

በፈረንጆች አቆጣጠር ረቡዕ 24/2019 የአንድ ለናቱ (እናቱ ኢትዮጵያ) ቴድሮስ ጸጋየ የሚያዘጋጀው “ርዕዮት” የተሰኘው የዜና ማእከል ሳደምጥ ካሁን በፊት ኢትዮጵያ እያለች በወያኔ አፋኝ ስርዓት መከራዋን ያየች የዛሬዋ የኢሳት ጋዜጠኛ ‘ርዕዮት ዓለሙ’ በሚዲያው አዘጋጅ በቴዲ ስልክ ተደውሎላት ባለፈው ሰሞን እርስዋ በምታዘጋጀው የእንግዶች ቃለ መጠይቅ ክፍለጊዜ ውስጥ ባገራችን ውስጥ ስለ እሚታየው ሁኔታ ለፕሮግራምዋ ተከታታዮች እንዲያስረዳ ቴዲን ጋብዛው ነበር። እርሱም ግብዣዋን አክብሮ ‘ቃለመጠይቁን አካሄደ’። ቃለ መጠይቁ እንደተካሄደ ለአየር እንዲበቃ ስትዘጋጅ ስሙ ባልተጠቀሰ በኢሳት አርታኢ/ኤዲተር ዋና ሹም ትዕዛዝ ምክንያት ቃለ መጠይቁ “እንደማይተላለፍ መታገዱ ከታወቀ በላ”፤ (በስንት ውጣ ውረድ ተቆራርጦ እንዲተላለፍ መፍቀዱን እና እርስዋም ሙሉ ካልሆነ ቆርጬ አላቀርብም በማለትዋ) ቴድሮስ ጸጋየም በመገረም፤ “ሁኔታውን ከእርስዋ ለማድመጥ” ሲል  ርዕዮትን  ደወለላት።

እርስዋም የስልክ ጥሪውን ተቀብላ እንድታብራራለት ለጠየቃት ጥያቄ “በኢሳት የተወሰደው አፋኝ እርምጃ ያለመደሰትዋና እጅግ በግና ተበሳጭታ ቅሬታዋን በሃዘኔታ ገለጸቺለት። እኔም ይህንን ቃለ መጠይቅዋን ከማድመጤ በፊት ማለትም ማክሰኞ ዕለት “ኒው ኢሳት” አቋቁመን ስሙን ለውጠናል ብለው ያንን ፖለቲካዊ ትንተናቸውን ለማድመጥ ወደ ‘ዩ ቱብ’ ሄጄ ኢሳት እየጠነከሩ ነው ብየ “ማክሰኞ ዕለት” ኢሳትን “ሳብስክራይብ” ያደረግኩትን “ሮብዕ” የርዕዮት ሚዲያ ሳደምጥ እና ርዕዮተ አለሙ “ሃዘን የተቀላቀለው ንዴት” ስሰማ ወዲያውኑ ወደ ዩ ቱብ ሄጄ ኢሳትን “ኣን ሳብስክራይብ” በማድረግ ሰርዤአቸዋለሁ።

የርዕዮት አለሙ ብስጭት እና ቅሬታ አንጀቴ ነው ያቃጠለኝ እና ሃዘን የተሰማኝ። አንባቢዎቼ “ኢሳት” የወሰደው “አምባገነናዊ/አፋኝ” ውሳኔ ጋዜጠኛ “ርዕዮት-አለሙ” የተሰማትን ቅሬታ ለማድመጥ ይህንን ብታደምጡ እንደእኔው አንጀታችሁ ይበግናል።

Ethiopia: ርዕዮት || በኢሳት የአፋኙ ቡድን ጫና በርትቷል... ርዕዮት አለሙ የተፈጠረውን ታብራራለች...|| Reyot 4/24/2019

ዱሮውኑም ኢሳት የተባለው የሻዕቢያና የብርሃኑ ነጋ አለቅላቂ ቱልቱላ ቁም ነገር ይወጣዋል ብለን አልጠበቅንም ነበር። ሆኖም በቅርቡ ለውጥ በማድረግ ባንድ አጋጣሚ እዛው ውስጥ በሚሰሩ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች አብይ አሕመድና ስርዓቱ የሚሰራው አሳፋሪ እርምጃ ፊት ለፊት ተጋፍጠው በማስረጃ እያስደገፉ ስርዓቱ መስመሩን እንዲያስተካክል ሲጠሩ በመስማቴ ልዩ ክብር በመስጠት አሞግሼአቸው እንደነበር ይታወሳል።

ሆኖም በአሳዛኝ ክስተት ያንን ክብር እንደተጎናጸፉ እና ብዙ ሰው በተደሰተባቸው ቅጽበታዊ ፍጥነት ለሻዕቢያ እና ለሥልጣን ጥመኛው ለሞላጫው ‘ብርሃኑ ነጋ’ ሲያለቀልቁ እንደነበረ ሁሉ፤ ዛሬም በተመሳሳይ የማሽቃበጥ ባሕሪያቸው ለብዙ ሰው መጥፋት ተጠያቂ የሆነው “አፋኙ የፋሺስቶቹ ቁንጮ አምባገነናዊው አብይ አሕመድ” ስላላቸው ልዩ ፍቅር እና አርጋጅ ባሕሪ ለመግለጽ ሲሉ በርዕዮት አለሙ እና በቴድሮስ ጸጋየ የመናገር መብት አፈና ማድረጋቸው እጅግ የሚገርም ክስተት ነው።

ወ/ት ርዕዮት አለሙ የዜጎችን ሃሳብ በነፃነት ለሕዝብ እንዲወያይባቸው የምታዘጋጀውን ክፍለጊዜ በእነዚህ አለቅላቂ ግለሰቦች መታፈን የሚያሳየን ክስተት ኢሳት ውስጥ ያሉ የምናውቃቸው አለቅላቂዎች “አናርኮ ፋሺቱን ስርዐት” ለማሽሞንሞን ሲሉ እንዲህ ያለ ታሪክ ሊመዘግበው የሚገባ የፖለቲካ አሽቃባጭ ነት ባሕሪ ዛሬም እንደ ርዕዮት አለሙ እና እንደ ቴድሮስ ጸጋየ የመሳሰሉ በዚህ ፈታኝ እና አስተዛዛቢ ወቅት “ነጥረው” የወጡ ጋዜጠኞችን ማፈን “የኢሳት ቅሌት” በቃላት ለመግለጽ ያስቸግራል።

በታማኝ በየነ፤ በሲሳይ አገና፤ በአበበ በለው ፤ በመሳይ መኮንን….የመሳሰሉ የሚሞገሰው አብይ የሚመራው “የኦፒዲኦ” (የኦዴፓ) መንግሥት እኮ “እስክንድር ነጋን” መፈንቅለ መንግሥት እያደረገልኝ ነው’ ብሎ በውሸት በመወንጀል “ግልጽ ጦርነት አፋፍምብሃለሁ” ብሎ የዛተ “አናርኮ ፋሺሰት” መሪ እኮ ነው አብይ ማለት። ቃል በቃሉ ምን እንዳለ የረሳችሁት ካላችሁ ላስታውሳችሁ። እንዲህ ነበር ያለው፡

“አብርሃ ደስታ በድምጽ ብታሸንፍ ሥልጣኔን አስረክብሃለሁ። ግን ሳታሸንፍ ‘አሁን አደራ ባለ አደራ እንደሚባለው ጨዋታ እምትጫወት ከሆነ ግን “ግልፅ ወደ ሆነ ጦርነት አንገባለን ማለት ነው (እዛ አዳራሽ ውስጥ የተሰበሰቡት የአሽቃባጮች በእስክንድር እና አዲስ አበቤዎች ህይት ላይ ጦርነት ለማፋፋም(ወደ ቀይ ሽብር ለመግባት?) ሲዝትባቸው የድጋፍ ጭብጫባ ሲያቀልጡ የሰማል)። ይኼ መታወቅ ይኖርበታል።….በአዲስ አባባ በሚመለከት ጉዳይ ላይ እውነቱን ለመናገር እኔ ያልተመቸኝ “መፈንቅለ መንግሥት የሚመስል ጉዳይ ስለሆነ ነው”። (አብይ አሕመድ)።” በማለት በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እስክንድርን ዝቶበታል! ይኼ ዛቻ በጣም አስፈሪ ነው!
ይህንን መሳይ የአናርኮ ፋሺሰት ምላስ የሚሰነዝር አስፈሪ አምባገነንን እና የሕዝብን እሮሮ እና ልቅሶ የሚያስተጋባ ሕዝባዊ አብየቱታን “ጨዋታ” እያለ በጨዋታነት የሚያናንቅን “ፌዘኛ” መሪያቸውን ነው ከላይ የተጠቀሱ የኢሳት ግለሰቦች ምን ይዘን እንጠጋው ብለው ለመሪያቸው በማሽቃበጥ “ርዕዮት አለሙ” በነጻነት እና በተመቻት የዝግጅት ቅንብር ፖለቲካም ይሁን ፤የወታደራዊ ፍልስፍና እና የማሕበራዊ ተንታኝ ግለሰቦችን ጋብዛ የምታቀርበውን ዝግጅት በማፈን ላይ የሚገኙት።

አሁን እኔ ለማሳሰብ የምፈልገው ጥሪ ኢሳትን በመደግፍ ገንዘብ የምታዋጡ ግለሰቦች (እኔም ለመስጠት አስቤ ነበር) እባካችሁ ርእዮት አለሙ እና ቴድሮስ ጸጋየን በመደገፍ አዲስ የቴ/ቪዥን ጣቢያ በማቋቋም እንርዳቸው። እነዚህ አፋኞች ተሻላቸው ሲባል ወደ ጭቃ እየገቡ ስለሆነ “በቃችሁ” እንበላቸው። በዚህ አጋጣሚ ርዕዮትን ለቅን እና ስተዋይ አስተሳሰብዋ አመሰግንዋት። ካሁን በፊት እኔም ግንቦት 7ን በሚመለከት ወቅሼሽ ነበር፤ ሆኖም እሱ አልፏል ዛሬ የመሰለሽን ለዜጎች እያስተማርሽ “ነፃነት” እስኪመጣ ቀጥይ ፤በርቺ! አይዞሽ!
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)