Monday, October 15, 2018

የታጠቁ እና ያልታጠቁ ቆሻሻ ፖለቲከኞች የፋሺስቶችን ሥርዓት በመንከባከብ ላይ ናቸው! ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)


የታጠቁ  እና ያልታጠቁ ቆሻሻ ፖለቲከኞች የፋሺስቶችን ሥርዓት በመንከባከብ ላይ ናቸው!

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

ኢትዮጵያ አሁን ወደአለችበት ሁኔታ እንዴት ገባች ብላችሁ ጠይቃችሁ መልስ ላጣችሁ አንባቢዎቼ ስለምትኖሩ ወደ ውይይታችን ከመግባቴ በፊት “መሓሪ ታደለ ማሩ” በተባሉ ኢትዮጵያዊ ጸሐፊ አልጀዚራ በተባለው ዓለም አቀፍ የዓረቦች የዜና ማሰራጪያ ጣቢያ Why the US is engineering political change in East Africa “The competition between great powers has triggered a string of major political developments in East Africa.” Mehari Taddele Matu (October 9, 2018) “አሜሪካ በምስራቅ አፍሪቃ ቀጠና ውስጥ ፖለቲካዊ የለውጥ ቅየሳ እያደረገችው ያለችበት ምክንያት ምንድነው?” “በሃያላን መንግሥታት መካካል የተከሰተው ውድድር በምስራቅ አፍሪቃ ቀጠና ውስጥ ስንክሳራዊ የሆነ የፖለቲካ ክር በመመዘዝ ላይ ነው” በሚል የጻፉትን ጥናት ጊዜ ስታገኙ እንድታነቡ እጋብዛለሁ።

ጽሑፉ አንባብችሁ ለመረዳት ለሚያዳግታችሁ አንባቢዎቼ ብትኖሩ ባጭሩ የጽሕፉ መልእክት የሚለው “ካሁን በፊት የአሜሪካኖች ትልቁ ስጋት “ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነት ነበር” ስለሆነም ሽብር ለመዋጋት ኢትዮጵያን አጋር አድርጋ ኢትዮጵያ ያሻትን ዕርዳታ ከአሜሪካኖች ይደረግላት ነበር፡ ሆኖም ዛሬ የአሜሪካ ስጋት ከሽብር ይልቅ፤ ሩሲያ እና ቻይና በጉልበት እየፈረጠሙ ስለሄዱ ስጋት ላይ ጥለዋታል። ስለሆነም መመሪያዋ በመለወጥ ‘ትኩረትዋ ከሽብር ይልቅ ኢኮኖሚ እና ወታደራዊ ጉለበትዋ በመፈታተን ላይ ወደአሉት ወደ ሩስያ እና ቻይና በማድረግ የፖሊሲ ለውጥ አድርጋለች።

በዚህ መሰረት፤በምስራቅ አፍሪቃ በተለይም ኤርትራ ኢትዮጵያ ጂቡቲ እና ሱዳን በነፋስ ጠረጋ ፍጥነት የተከሰተው ‘የፖለቲካ ለውጥ’ አሜሪካኖች እና ጓደኞቻ ከላ ሆነው ዓረቦችን በመላክ እነዚህ አገሮች በተለይም ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ከቻይናዎች ኢኮኖሚያዊ እና ስትራቴጂያዊ ጎበጣ (ሄጂመኒ) እጅ በማስወጣት በአሜሪካኖች ቁጥጥር እጅ አስገብቶ የምስራቅ አፍሪካ “የምጣኔ ሓብት፤የባሕል፤ የሞራል እና ያካባቢው ቀጠናዎች ጸጥታ” ጎበጣው/ነጠቃው/ (ሄጂመኒው) በምዕራባውያን እጅ እንዲገባ ያመቻቸው ዘንድ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ “ሁለቱ አገሮች” የሰላም ዕርቅ እንዲያደርጉ እና በዚህ ቀጠና ውስጥ በቻይናውያን እና በሩሲያውያን ቅልጥም እየተደፈረች ያለቺው አሜሪካ ሃይሏን ለማጠናከር እንዲመቻት የወሰደቺው ዕቅድ መሆኑን ነው ጽሑፉ የሚዘረዝረው።

ከላይ የጠቀስኩት መነሻ ከጽሑፉ ጥቅስ እንዲህ ይላል፡

Since the end of the Cold War, the "war on terror" has been at the centre of all US alliances in the world, including in the Horn of Africa. However, in recent years, the US has gradually come to perceive the rise of China and Russia, and not terrorism, as biggest threat it is facing in Africa and elsewhere.

This policy shift has been outlined in the 2018 National Defence Strategy and articulated by a number of US officials, including US Secretary of Defense, James Mattis, who in a January speech said:

"Great power competition, not terrorism, is now the primary focus of US national security. We face growing threats from revisionist powers as different as China and Russia are from each other... To those who threaten America's experiment in democracy, they must know if you challenge us, it will be your longest and worst day."

It is in this context that Washington has sought to forge alliances with African forces to support its antagonistic competition with these two great powers.” ይላል።

እንግዲህ እንደመግቢያ ይሆናችሁ ዘንድ እነ አብይ እና ኢሳያስ በዚህ ፍጥነት በሚገርም መተቃቀፍ ‘ለተመልካች እና ለሁለቱ ዜጎች’ የትዕይንቱ ክስተት ምስጢሩን ለመፍታት በሚያስችግር እንቆቁልሻዊ ሕልም “ግን ተጨባጭ እውነታ” እንዴት ሊከሰት እንደቻለ ግልጽ እንዲሆንላችሁ ተስፋ አለኝ። ታዲያ እነ አብይ እንዴት መጡ የሚለው ጠያቂ ትንሽ ልበል።

አብይ የመጣው አሜሪካኖች ወይንም አረቦች አይደሉም ያመጡት የሚሉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ክርክራቸው እንደምገምተው ደግሞ ‘የሕዝባዊ አመጽ አልገዛም ባይነት ስለበረተታባቸው ወያኔዎች ለውጥ ማድረግ ነበረባቸው እና ስለዚህም ተገድደው ጥገናዊ ለውጥ አደረጉ” የሚሉ ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ። ክርክሩ ልክ ቢሆንም፤ አሜሪካኖቹ ሊገቡብን የቻሉበት ምክንያት ሁሌም መርሳት የለባችሁም (የ1991 የለንደኑ ስምምነት እንዴት እንደገቡብን አትርሱ)። ዛሬ ደግሞ በ2017/2018 እንዴት እንደገቡ ልብ እንበል።

ሃያላን መንግሥታት በቅጽበታዊ መንገድ ‘ዘው’ ብለው ወደ አንድ አገር አይገቡም። ጣልቃ ገብነታቸው የሚጀምረው በዝግምታ ነው። የቅኝ ሃይሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለሚያደርጉት ጣልቃ ገብነት ወይንም “ጎበጣ/ሄጂመኒ” አከናዋኝ ወኪሎች መያዝ አለባቸው። ይህ ካደረጉ በላ በወኪሎቻቸው በኩል የሚነድፉት ዕቅድ መንገዱን ስታጤኑት ለማወቅ ቀላል ነው። ይኼውም ‘አድፍጠው ቆይተው አመች ሁኔታ ሲመቻችላቸው ያኔ ዘልለው በመግባት የሚታወቁበት ስልታቸው ነው።   ኢትዮጵያ በለውጥ ማዕበል ስትናጥ አንድ ስርዓት ወደ መነቃነቁ ሲቃረብ ሌላ ሃይል ወደ ስልጣን ስያነፈንፍ ሲያዩ ያኔ (“policy shift has been outlined in the 2018 National Defence….የሚለው ስተመለከቱ) “ለመቆጣጠር እያቀዱት ለነበረው የ2018 የምስራቅ አፍሪቃ እና የቀይ ባሕር ወሽመጥ “ስትራቴጂአዊ የቀጠና ፖሊሲ” ለውጥ ለማድረግ አመች አጋጣሚ ስለመጣላቸው፤ በሕዝብ ተቃውሞ እና አመጽ “ለመወደቅ እየተነቃነቁ” ለነበሩት ሁለቱም ስርዓቶች “አማራጭ ስልት” በመንደፍ ህይወት ዘርተውላቸው እንዲድኑ በማድረግ እግረመንገዳቸው ፖሊሲያቸውን አሳክተዋል።

ስልቱም አሁን አብይ እና ኢሳያስ የአሜሪካኖች እና የዓረቦች “መወጣጫ መሰላል” ሆነው በመገኘታቸው በሁለቱ ስርዓቶች አነጣጥሮ የነበረው “መጎደኛ አመጽ” ባስገራሚ ረቂቀ ስልት እንዲኮላሽ ሆነ።
 
ሴራ አንድ!

በምርጫ 97 አሜሪካኖች እና እንግሊዞች አምባሳደሮች እና የመረጃ ወኪሎቻቸውን በስፋት እጃቸውን በማስገባት ግልጽ የሆነ ጣልቃ ገብነት በመተወን “ለምስራቅ አፍሪቃ የጸረ-ሽብር ጦርነት እንዲረዳቸው ሲጠቀሙበት ለነበረው የወያኔ ስርዓት ድጋፍ በመስጠት በግልጽ ጣልቃ በመግባት ሲፈጸም የነበረው ሰብአዊ ጥሰትና ጭፍጫፋ አይተው እንዳላዩ በመሆን ስርዓቱ ሥልጣን ላይ እንዲቆይ አድርገዋል። ዛሬም በድጋሚ አመጹ ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ስለተምቦገቦገ ”አሜሪካኖቹ የሕዝቡ መነሳሳት በውስጥም በውጭም እጅግ የጋለ መሆኑን እና ወሳኝ ምዕራፍ መድረሱን ስለተረዱ፡ ወኪላቸው ተዋርዶ ከሥልጣን ከመሰናበቱ በፊት “አገልጋያቸውን” ማዳን ስለነበረባቸው አዲስ ስልት ቀየሱ።

አዲሱ ስልት ሊቀይሱት የተነሱበት ዋነኛው የራሳቸው ንድፍ እንዳለ ሆኖ በአንዳንድ ቦታዎች የስርዓቱ ታጣቂዎች እና አስተዳደራዊ መዋቅሮች ፈርሰው “በአመጹት የአካባቢ ኗሪዎችና ወጣቶች ቁጥጥር ስር እና መተዳደር ሲጀምር፡ አሜሪካኖቹ በአስገራሚ ስልት ‘የዲፕሎማሲ’ ወኪላቸውን “አምባሳደር ያማሜቶን” ወደ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ ልከው የነበረው ተቃውሞ አከሸፉት። አብይ የተባለ በብዙ ዜጎች ዘንድ የማይታወቅ በትምህርቱ ዘለግ ያለ “አፍዛዥ ሰባኪ” የሆነ የስርዓቱ ኮለኔል እና ባለሥልጣን ወደ መድረኩ ብቅ እንዲል በማድረግ ‘ከውስጥ ተጫዋች ቡድኖችን  በማደራጀት’ “አዲስ ሰው እና አዲስ መንፈስ የተላበሰ መሪ” ወደ መሪነት መድረክ እንዲወጣ ተደረገ።

ፓራያ (የተገለለ) መንግሥት ተብሎ በዓለም እና ባብዛኛ ኤርትራኖች ተወግዞ የሞቱ ምጽአት መቃረብ ሲጠባበቁ እና ሲመኙለት የነበረው የሻዕቢያው መሪ ኢሳያስ አፈወርቂን ከአብይ ጋር እንዲወዳጁ በማድረግ አዲስ እንቆቁልሻዊ ግን አውነታዊ ክሰተት ኤርትራ ውስጥም እንዲከሰት በማድረግ ‘ዲያብሎሳዊው ኢሳያስ’ ወደ መልአካዊነት በመለወጥ ስቀሉት ስቀሉት እየተባለ ሲወገዝ የነበረው የብዙ ሺሕ ሕዝብ ደም በእጁ የሚጮኸው “ኢሱ፤ ኢሱ” ተብሎ በሕዝብ እየተሳመ እና እየታቀፈ ‘የሰላም ተምሳሌት አስመስለው በመሳል ወደ ኢሱነት/ እና ወደ እየሱስነት” አስለውጠው ‘ሲቃወሙት የነበሩት ኤርትራኖች (ብያንስ ኤርትራ ውስጥ ያለ ሕዝብ) እንዲወድዱት-ተደረገ።ነፋስ ወደ ነፈሰበት የመንፈስ ባህሪ ያለው ጅላጅሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋም ከመቃብር ተቆፍሮ የወጣው ኢሳያስን እየዘለለ መሳም እና መስገድ ጀመረ።

 ሴራ ሁለት!-  ከዚያም ‘ኮለኔል ዶክተር አብይ አሕመድ’ የተባለ ሕዝብ የማያውቀው መሪ “መደመር” በሚባል ደብተራዎች ያልተማሩት አዲስ “አፍዝ ወ አደንዝዝ” ፍለስፍና በማስታጠቅ የተማረውን እና ያልተማረውን ኢትዮጵያዊ ወደ ዕብድነት በመለወጥ ሕሊናቸውን ሰልቦ እግር ጫማው ሥር ወድቀው እስኪሳለሙት ድረስ በመስበክ ባስገራሚ ሰበካ እግሩ ስር ተነጠፉለት

ሴራ ሦሰት!፦ ይህኛው የዋና ዋና ሴራዎቸቻቸው ዋነኛው ግብ ነው። የተነሳውን ሕዝባዊ አመጽ ማኮላሸት!

እንዴት ተኮላሸ? ከኔ ጀምሮ ማንም ሃቀኛ ኢትዮጵያዊ ዜጋ “ሲነገሩ በጆሮው ሊሰማቸው” የሚፈልጋቸው እና “በአፉ-እንደ ድግምት ጸሎት ሊደግማቸው” የሚፈልጋቸውን “ኢትዮጵያ እና እግዚአብሔር” የሚባሉ ቃላቶች ለ27 አመት በኦሮሞዎች እና በትግሬ ፖለቲከኞች “መራራ ጥቃት” ተሰንዝሮባቸው ስለነበር፤ ሰልጥኖ እና በስልት ወደ ሥልጣን የመጣው አብይ አሕመድ እነዚህ ቃላቶች ወደ ነበሩበት ‘ክብረ ልዕልና’ እንዲጎናጸፉ መስሕብ አድርጎ በመጠቀሙ የሁላችን ድጋፍ አገኘ። ሲናወጥ የነበረው የሕዝብ ተቃውሞ ረገብ እንዲል ’መንገዱን እኔ ላሳያችሁ’ በማለት ወያኔ ላደረገው ወንጀል ይቅርታ በመጠየቅ እስረኞችን መፍታት ጀመረ።

ከዚያ በታላቁ ሴራ በረቂቁ ቀስ እያለ መጓዝ ጀመረ። ወደ መቀሌ ሄዶ መለስ ዜናዊን ጀግና ማለት ሲጀምር፤ ከኤርትራ ወንበዴዎች ጋር ሆነው ኤርትራ ምድር እና ምጽዋ ወደብ ድረስ ሄደው የኢትዮጵያን ልጆች በጥይት ቆልተው የባሕር ወደቦቻችንን ያስዘጉብንን በአገር ክሕደት ወንጀል መጠየቅ የሚገባቸው የትግራይ ታጋዮችን “የዲሞክራሲ ታጋዮች”   እና ‘ወርቆች፤ ጀግኖች’ ማለት ጀመረ።ከመቀሌ ወደ ባሕር ዳር በሄደበት የመጀመሪያ ከአማራው ሕዝብ ጋር ባደረገው ትውውቁ የአማራዎቹ አቤቱታ ማሳነስ ጀመረ። በላያችን ላይ ሽንት እየተሸናብን “ሽንታም አማራ” እየተባልን ፤ በዜግነታችን ከተወልደንበት ምድር እንድንባረር እና ወደ ገደል ከነ ነብሳችን እንድንገፈተር ተደርጛል፤ በሚሊዮኖች አማራዎች ከምድረ ገጽ ተሰውረዋል፤ በአማራ ነገድነታችን በጥቃት ኢላማ ገብተናል! ይህ ተሎ ይቁም! ብለው ባሕር ዳር ውስጥ መጥቶ ሲጎበኛቸው “አቤት” ላሉ አማራ ማሕበረሰብ ምሁራን እና ቀሳውስት “የተጨቆናችሁ እናንተ ብቻ አይደላችሁም” አማራ ብቻ ተለይቶ አልተጨቆነም! ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ስትሉ ቆይታችሁ እንደገና ተመልሳችሁ “አማራ አማራ” ወደ እሚለው ትሄዱ እና ታበላሹታላችሁ…” በማለት የአማራዎች አቤቱታ ሲያናንቅ አድምጠን እኔም ሆንኩ ሌሎች  ባጭር ጊዜ ውስጥ የሰውየው “ የአማራ ጥቃት የሚያይበት መነጽሩ የተበላሸ መሆኑን” በመንቃታችን (የመጀመሪ ተቺው እኔ ነበርኩ) የነበረው መጠነኛ ድጋፋችንን ከነጭራሹኑ አቆምን።

ጥቂቶቻችን ስጋታችን ማስተጋባት ቀጠልን። የተቀረው መሃል ሰፍሮ የነበረው ወደ አብይ ድጋፍ በመግባት ተጠራርጎ ደጋፊ ሆነ።ከዚያም ቀስ እያለ ሕዝቡን በሚያደነዝዙ ቃላቶች ተጠቅሞ የተማሩትን ማጃጃል ያዘ። የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪዎች እና ታቃወቂ ምሁራን ሁሉም ጥርግርግ ብለው የአብይ ጠበቆች ሆኑ። የታጠቁት እና ያልታጠቁት የፖለቲካ ቆሻሻዎች ከነ ጋዜጠኞቻቸው ጥርግርግ ብለው የአብይ መናፍህ ሆኑ።

የትጥቅ ትግል “ዘመኑ ያለፈበት ነው” ብሎ ሲሰብካቸው የነገራቸውን አምነው ተቀበሉት። ቆሻሻ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞቻቸውም ‘ሰላማዊ ሰልፍ’ ማድረግ እና ማስነሳት ከነጭራሹ “ረሱት እና ሰለማዊ ሰልፍ ባደረጉ የተጨቆኑ ወጣት ወታደሮች ላይ ውግዘት እና ውርጅብኝ ማውረድ ጀመሩ”።

ብከላው በዚህ መልክ በመቀጠል፦ በውጭ ሃይላት የተሳለው “አገር ወዳድ” መሪ ተብየው “ማንም ሰው የፈለገው ባንዴራ (የካሊፌት/ሸሪዓ/ ወይንም አልሸባብ..ወይንም የግንጠላ/አገር አፍራሽ/ ባንዴራ ወይንም የግብረሰዶም ባንዴራ…የፈለገው ባንዴራ ማውብለብ እና መስበክ ይችላል በሚል የስርዐተ አልባ ስብከት በመስበኩ ምክንያት ሁሉም የፈለገውን ባንዴራ በማውለብለብ ጸረ ኢትዮጵያ ሰንደቃላማ እና ኢትዮጵያዊ ሰንደቃላማ በሚያውለበልቡ መካካል ‘ትንቅንቅ” ተጀመረ። ተቃዋሚ እና ምሁር ተብየ “ተደማሪ” የፈለገው ሰው ማንም ባንዴራ ማውለብለብ መብቱ ነው በማለት ‘ለዘመናት የተውለበለበ አርማችንን በጠላትነት ከሚፈርጁዋት ቡድኖች ጋር ሆነው ‘አገራዊ ሰንደቃላማን” ከዲሞክራሲ ጋር እያቆራኙ ሰንደቃላማን መለወጥ እና መጻረር ‘መብቱ ነው’ በማለት “በብከላው ዘመቻ አጠናካሪዎች እና ደጋፊዎች ሆኑ (በሌላ መልኩ የባንዳዎቹ የመለስ ዜናዊ እና የነ ሌንጮ ፖለቲካ አስተጋቢዎች እና ተምበርካኪዎች ሆኑ)። ”የነፈዘው የዩቱብ ጋዜጠኛ ተብየውም ትግሉን በማቀዝቀዝ  “ከፍቅር ለፍቅር” ምናምን የሚል ፖለቲካ ዩ ቱብ ቴ/ቪዥን ጣቢያው ላይ በማስተጋባት የሕዝቡን የፍትሕ ጥያቄ እንዲኮላሽ ‘ራሱን የቻለ አፍዝ ወ አደንዝዝ’ ሚናውን መጫወት ያዘ።
 
በየከተማው ግድያው እና ጥላቸው እንዲሁም መፈናቀሉ በሚገርም ሁኔታ ተጧጧፈ። ሰውን በጠራራ ጸሐይ አደባባይ ላይ ገድሎ መስቀል ተጀመረ። በዓለም ውስጥ በሕዝብ መፈናቀል አንደኛ ኢትዮጵያ ነች ተባለ። ያ ሁሉ ሲሆን ታጣቂዎቹም የኮንትሮባንድ መሳሪያዎች በየከተማው በማስገባት እንደ ባንዴራ አውለብላቢዎች እነሱም ልቅ ስለተለቀቁ ውድመቱ የት እና የት የሌለ ሆነ። መንግሥት ነኝ የሚለው የስርዓተ አልባው የፋሺስቶች ጥምረት አገሪቱ ከድጡ ወደማጡ እየመራት መጣ።

ለ27 አመት በሕዝብ ህይወት እሳት በመለኮስ ዜጎች በሲኦላዊ ህይወት እንዲያልፉ ሚና የነበራቸው የወያኔ ወንጀለኛ ባለሠልጣኖች እና ተባባሪ አገልጋዮቻቸው አሁንም ከሹመት ወደ ሹመት እያደጉ እና “አገር ወዳድ እየተባሉ” እየተሞገሱ “ተከብረው” እያየናቸው ሲሆን ፤በጡረታ ኑሩ የተባሉትም ከመዘበሩት ሃብታቸው በምቾት ተንደላቅቀው እየኖሩ ናቸው። “የመደመር ታላቁ ሴራ” በስልት እየተጓዘ በርካታ ሃይሎች “መንግሥትህ እኔ እና እገሌ ነን” የሚል ንግግር ለሕዝቡ በማስደመጥ ሕዝቡ ለማን እንደሚታዘዝ ግራ ገብቶት “መሪያችንን በውል አስታውቁን” ወደ ማለት ጥያቄ ገብቷል።
 
አሁን ኢትዮጵያ ስንት መንግሥት እንዳላት በበኩሌ አላውቅም። አንዳንዶቹ እኔ እና እገሌ ነን ሲሉ ሌሎቹም ከሁለት በላይ ሦስት ከዚያም አራት ናቸው የሚሉ አሉ። ማንነታቸው ያልታወቁ ኦሮሞ ነን የሚሉ ታጣቂዎችም በሚቆጣጠሩዋቸው ቦታዎች የራሳቸው አስተዳዳሪዎች እና ፖሊሶች መሾም እንደ ጀመሩ ተነግሯል። በየክልሉ ያሉትን ቁጫጭ መንግሥታትም እንዲሁ የየክልላቸው ሹሞኞች ያለ ሕዝባዊ ድምጽ እና ሌላ ነገድ የማይጨምር ሹመት በመሾም የነበረው ዘረኛ እና ነገዳዊ ስርዓት እንዲቀጥል አዲስ ትንፋሽ እየሰጡት ነው። ቀስ እያልን ከመገረም ወደ መርመም ተሸጋግረናል።
 
ግራም ነፈሰ ቀኝ የታጠቁት እና ያልታጠቁ ተቃዋሚዎች በሚከፈልላቸው ሆቴሎች ተኝተው በነፃ እየተመገቡ ተልእኮአቸውን ረስተውት በሰላም እየኖሩ መሆናቸው በሚደርሰን ዜና ተገርመን ሳንጨርስ “ሕዝብ እናደራጃለን ብለው በሄዱበት አገር ውስጥ” ከሁለት እስከ አምስት የሚሆኑ “ቦዲ ጋርዶች” (ነብስ ጠባቂ) ተመድቦላቸው በሚገርም ትዕይንት እየታጀቡ እየተንቀሳቀሱ ናቸው የሚል ዜና ስንሰማ ቆሻሻዎቹ ፖለቲከኞች የሕዝቡን መሰረታዊ አብየቱታ በማኮላሸት ሂደት ላይ እየተጫወቱት ያለውን ሚና በቀላል መታየት የለበትም። ማይክል ፓረንቲ የተባለ የፋሺዝም ተመራማሪ አሜሪካዊ ምሁር “ደርቲ ትሩዝ” (ቆሻሻው እውነታ) የሚለው አይነት ቆሻሻው እውነታ “ክስተት” በአገራችን ኢትዮጵያ እያየን ነው።
 
የምሁራኖቹ ቆሻሻ እውነታ ደግሞ ስንመለከት “We are free today than ever before” ዛሬ ከማንኛወም ጊዜ የበለጠ ነጻ ሕዝብ ነን” በማለት እየታየ ካለው ቆሻሻው እውነታ እራሳቸውን በማዋሃድ የተወረወለላቸውን ትንሽዋን ቁራሽ በማመስገን ብዙሃኑ ወደ ትልቁ ግብ አሻግረው እንዳይጠይቁ ሞራላቸው/መንፈሳቸው/ ያደቁታል። በገዢዎቻችን እየተጠና በሚካሄድ “ሰለክቲቭ ሪፕረሽን” (በረቀቀ ጥብብ እየተጠኑ የሚካሄዱ ሕዝባዊ አፈናዎች) ተጠቂዎች ስለማይሆኑ ምሁራኖቹ “ዛሬ ከማንኛወም ጊዜ በበለጠ ነጻ ሕብ ነን” በማለት አፋኙ ስርዓት ዕድሜው እንዲራዘም ተጨማሪ አገልጋዮች በመሆን ስብከታቸው ሕዝብን በማደንዘዝ ሚና እየጠጫወተ ነው።
 
በሚገርም ግለታዊ መንፈስ ሲራመድ የነበረው ወጣት “ዶርማንት ስታተስ” (የፈዘዘ፤የተጃጃለ)  ወጣት እንዲሆን ግፊት አድርገዋል። እነዚህ “ዛሬ ከማንኛወም ጊዜ የበለጠ ነጻ ሕዝብ ነን” የሙሉ ክፍሎች ያላቸው የኑሮ ደረጃ ከሌሎቹ ይለያል። በሚሊዮን እየተፈናቀሉ እና በሺዎቹ ታፍሰው ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ፖሊስ በሚያጉራቸው ታሳሪዎች (ለምሳሌ አዲስ አበባ፤ የራያ፤የወልቃይት ወጣቶች…) እና በመቶዎቹ በሚገደሉ ዜጎች ያላቸው “ክላስ” መደብ (ኑሮ) የተለየ ኑሮ ስለሚኖሩ “ዛሬ ከማንኛም ጊዜ የበለጠ ነጻ ሕዝብ ነን” በሚል ተርጉሞው በነሱ የግል ነጻነት ብቻ እየተረጎሙ በሚታፈኑ በሚፈናቀሉ እና በሚገደሉ ዜጎች ጫማ እግራቸውን ማስገባት አልቻሉም።

ስለሆነም የነሱ ነጻ እንቅስቃሴ እና ምቾት “የሚሞቱት እና የሚፈናቀሉት ዙጎች” እሮሮ እንዳይደመጥ ስለሚሸፍነው “በስርዓቱ ላይ ተቃውሞ ላልቷል”።በተጻራሪው ተቃውሞ እና ግለቱ ተጋግሎ የምናየው ወጣት “ኢትዮጵያ” በሚለው ወጣት ወይንም ምሁሩ ክፍል ሳይሆን “በተገንጣይ ፖለቲከኞች መዳፍ ገብቶ” ኦሮሚያ ለሚባለው የፋሺስቶች የሕልም ሪፑብሊክ እና ኦሮሚያ ለምትባለው ሪፑብሊክ ምስረታ የተዘጋጀላት ባንዴራ የሚያውለበልቡ ተገንጣይ ወጣት ኦሮሞዎች/ቄሮዎች/ በኩል እየታየ ያለው እንቅስቃሴ  ፈሩን አልለቀቀም። ይህ ክፍል የሚያንቀሳቅሱ ግለሰቦች በሚዲያ የተደራጁ እና በብረት በታጠቁ ግለሰቦች (ድርጅቶች) በኩል የሚካሄድ ግልጽ ጸረ ኢትዮጵያ ሰራ ነው።
 
እነዚህ መሪዎች “መደመር በሚባለው ታላቁ ሴራ” የሰጣቸው ነፃነት እና ‘ይሁንታ’ ተጠቅመው “አዲስ አበባም” የኦሮሞዎች እንጂ የሌላ ነገዶች ስላልሆነች የኢትዮጵያ ዜጎች እንደ ‘ኗሪዎችና ሰፋሪዎች’ እንጂ አገራቸው ስላልሆነ ኦሮሞዎች በሚፈቅዱላቸው የመኖርያ መብት ብቻ ሊኖሩ እና ወይንም ሊባረሩ እንደሚችሉ አውጀዋል ስርዓተ አልባው “ታላቁ የመደመር ሴራ” የፈቀደው የመናገር መብት “ማንም ሰው ‘ ማንም ድርጅት እና ቡድን’ እስከዚህ ድረስ የሚደርስ “አደገኛ” አዋጅ በብዙሃን መገናኛ ማወጅ እንደሚቻል ስንታዘብ፤ ታላቁ ሴራ የሚሰጠው መብት “ውጣ ከዚህ፤ ይህ የኔ ነው” እስከ ለማለት ማወጅ “ዲሞክራሲያዊ መብት ነው” ወደ እሚለው በጠራራ ጸሓይ ሳናንቀላፋ በውናችን እንድናደምጥ አድርጎናል

ይህ ሁሉ ስርዓተ አልባ እና “ልቅ አዋጅ” እየታወጀ በሌላ በኩል ለኢትዮጵያዊነት እና ለሰንደቃላማችን እስከመጨረሻ ድረስ ቆመናል እያሉ ሲዋሹን የነበሩት ቆሻሻዎቹ ፖለቲከኞች “በሰለማዊ ሰልፍ ተቃውሞ መውጣም ሆነ በትጥቅ ትግል ኢትዮጵያን ከፋሺስቶች ነፃ ማስወጣት ማለት ‘ጊዜው ያለፈበት’ ባህል ነው ስለ ተባሉ” ፋሺስቶች የሚፈሩት “የትጥቅ ትግልም ሆነ የከተማ እና የገጠር የስራ አድማ ማቆም አመጽ” በማውገዙ ዘመቻ አክባሪዎች ሆነው ትግሉን “በማቀዝቀዝ “የታላቁ ሴራ” ተዋናዮች ሆነው “አፍዝ ወ አደንዝዝ ፖለቲካው ማምለክ ጀምረዋል። እሳቱ ከመፋም ወደ መክሰሙ እየተራመደ ነው። 

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) getcahre@aol.com