Tuesday, July 31, 2018

አክራሪ ብሄረተኛነት በሰዎች ላይ የሚያስከትለው ስነልቦናዊ ለውጥና የሚፈጥረው ተፅዕኖ - በፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ጽሁፍ አማካይነት የአክራሪ ብሄረተኛነትን ተፅዕኖ አሳያለሁኝ። በዶክተር አሰፋ ነጋሽ --› አምስተርዳም (ሆላንድ) – ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ. ም.

አክራሪ ብሄረተኛነት በሰዎች ላይ የሚያስከትለው ስነልቦናዊ ለውጥና የሚፈጥረው ተፅዕኖ


ልዩ ማሳሰቢያ
ክቡራን የኢትዮጵያን ሰማይ አንባቢዎች፦ በእዚህ ድረግጽ ላይ እያያችሁት ያለው የዶ/ አሰፋ ነጋሽ ሳይንሳዊ ጥናት በአገራችን ልዩ የሆነ ምርምር ስለሆነ በዚህ ድረገጽ ለረዢም ጊዜ እንዲቆይ ወስኛለሁ። እንዲህ ያሉ ከባድ ምርምር ድካም እና ጊዜ የሚፈጁየአዋቂ ጭንቅላትንየሚጠይቁ ጥናቶች ወደ ድረገጾች ሲላኩ ለዝሕብ የሚታዩት ካንድ ሁለት ቀን የማያልፍ ዕደሜ ተሰጥቶአቸው በማግስቱ በሌሎች ዜናዎች/ጽሑፎች ስለሚተኩ በስፋት ለሕዝቡ እንዲነበቡ በሚል ምክንያት በዚህ ድረገጽ የዶክተሩ ጽሑፍ ተለጥፎ ለጊዜው ይቆያል። የኔን ወቅታዊ ጽሑፎች/ትችቶች/ ለማንበብ ለጊዜው አይቀርቡም። የኔን ትችት ለማንበብ ስትፈልጉ ሰሞኑን የኢትዮጵያን ሰማይ (Ethiopian seamy) ፌስ-ቡክእንደገና እንዲቀጥል ስላደረግኩ አድራሻው እዚህ ጫን አድርጉት ወደ ፌስቡኬ ይወስዳችኋል


ወይንምፌስቡክጉጉል ገብታችሁ ልታነብቡኝ ትችላለችሁ። ወደ ፌስቡኩን ለመግባት ችግር ከገጠማችሁ አስታውቁኝ። የዶ/ አሰፋ ክፍል 1 2 3 ከስር ታገኙታላችሁ።
አመሰግናለሁ።

            ጌታቸው ረዳ  
(Ethiopian Semay)

አክራሪ ብሄረተኛነት በሰዎች ላይ የሚያስከትለው ስነልቦናዊ ለውጥና የሚፈጥረው ተፅዕኖ - በፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ጽሁፍ አማካይነት የአክራሪ ብሄረተኛነትን ተፅዕኖ አሳያለሁኝ።

በዶክተር አሰፋ ነጋሽ --› አምስተርዳም (ሆላንድ) – ሰኞ ሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ. ም.
የኢሜይል አድራሻ ---› Debesso@gmail.com
ክፍል አራት
አክራሪ ብሄረተኛነት በሰው አስተሳሰብ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ  ምንድነው? -

ከዚህ በታች የፕሮፌሰር ገብሩ ጽሁፍ እንደ ማሳያ ምሳሌ ሆኖ ይቀርባል።

ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በ1932 ዓ. ም. አክሱም ውስጥ የተወለዱ ሲሆን በንጉሱ ዘመን ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኑቨርሲቲ በሚባለው ዩኑቨርሲቲ ትምህርታቸውን ተምረው በ1956 ዓ. ም. (በኢትዮጵያ አቆጣጠር) ከጨረሱ በኋላ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኑቨርሲቲ ቅርንጫፍ በነበረው የጎንደር የጤና ጥበቃ ኮሌጅና እንደዚሁም አዲስ አበባ በሚገኘውም የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ዩኑቨርሲቲ በታሪክ መምህርነት ያገለገሉ የ78 ዓመት እድሜ ባለጸጋ ናቸው። እኚህ ሰው ከአብዩቱ በፊት ለከፍተኛ ትምህርት ወደ አሜሪካ ከተላኩ በኋላ በዐጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት በባሌ፤ በትግራይና በጎጃም የተደረጉት የገበሬዎች ዐመጾች[1] ታሪክ ላይ ለዶክትሬት ዲግሪ ያበቃቸውን ጥናት በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1969 ዓ. ም ጽፈው ጨርሰው ያበረከቱ ሰው ናቸው። እኔ ከእኚህ ሰውዬ የጽሁፍ ስራዎች ጋር ለመጀመሪያ የተዋወቅሁት ከዛሬ ሰላሳ አምስት በፊት ይህንን የመመረቂያ ጽሁፉቸውን እዚህ በምኖርበት ሆላንድ ሀገር ውስጥ በሚገኘው የLeiden University የአፍሪካ ጥናት ማእከል መጽሃፍት ቤት ውስጥ አግኝቼ ባነበብኩበት ወቅት ነው። እኚህ ሰው አሜሪካን ሀገር ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በዚያው ሀገር ከሰላሳ ዓመታት ያላነስ በታሪክ መመህርነት አገልግለዋል። እኒህ ሰው ለወያኔ መንግስት ያላቸውን ፍቅር የገለጹት ገና ከጠዋቱ የወያኔ ትግሬዎች መንግስት እንደተመሰረተ ነው። ለዚህም እንደ ምሳሌ የምጠቅሰው ይህንን በአንድ ጥናታዊ ውይይት በሚደረግበት ስብሰባ ላይ ያደረጉትን ንግግር ነው። ፕሮፌሰሩ በዚህ ስበስባ ላይ የሚከተለውን ተናገሩ።

“የአርሶ አደሮችን የዐመጽ እንቅስቃሴ መርቶና አቀናጅቶ በሥልጣን ላይ የተቀመጠ መንግስት የአሁኑ መንግስት ብቻ ነው፤ ህዝባዊ ወገናዊነቱን ያንጸባርቃል። ስለዚህ በዶክተር ላፒሶ አነጋገር ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብ የሥልጣን ምንጭ ሆኗል[2] 

በማለት የሰብዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶች ህገ መንግስታዊ ዋስትናን በተመለከተ ታህሳስ 19 ቀን 1986 ዓ. ም. በህገ መንግስት ኮሚሽን አዳራሽ በተካሄደው የአንድ ቀን ጥናታዊ ውይይት ማብቂያ ላይ ባደረጉት ንግግር ገልጠው ነበር። የዐይጥ ምስክር ድንቢጥ እንደሚባለው ፕሮፌሰር ገብሩ በምስክርነት የጠሩት ዶ/ር ላጲሶን[3] ነው። ዶ/ር ላጲሶ ደግሞ የሚታወቁት የፓለቲካ ቀለማቸውን እቀያየሩ (እንግሊዞች ይህን የመሰለን ተለዋዋጭ አቋም ያለው ሰው a man of all seasons) በየጊዜው ሥልጣን ላይ የሚወጣን መንግስት በመደገፍ ነው። ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ዶ/ር ላጲሶን በመታከክ የወያኔን መንግስት ህዝባዊነት ለማሳየት የሄዱበት ርቀት በእኔ እይታ የሚያስገምታቸው ድርጊት ነው። ይህ ድርጊት ወያኔዎች ከየነገዱ ደካሞችን እየመረጡ እከሌ ይህንን ነገድ ይወክላል እያሉ በመሳሪያነት ከሚጠቀሙበት ሁኔታ ተለይቶ የሚታይ አይደለም። ዶ/ር ላጲሶ በደርግ ዘመን በኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን ላይ እየቀረቡ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ዋና ሰባኪ የሆኑ ግለሰብ እንዳልነበሩ ሁሉ ዛሬ ደግሞ ቀኝ ኋላ ዙር ብለው ኢትዮጵያን በነገድና በቋንቋ መስፈርት ከፋፍሎ የአፓርታይድ ሥርዓት የመሰረተን መንግስት “ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብ የሥልጣን ምንጭ ሆኗል” ብለው ለማለት አልገደዳቸውም። ዐጼ ሱስንዮስም ሆኑ ዐጼ ቴዎድሮስ ወይም ዐጼ ዮሃንስ ወዘተ የመሳሰሉ የቀድሞ የኢትዮጵያ መሪዎች አርሶ አደሮችን አሰልፈውና ታግለው እንጂ ብቻቸውን ሆነው አልነበርም ሥልጣን ላይ የወጡት። ታዲያ የወያኔዎች ሥልጣን ላይ መውጣት ከሌሎች አርሶ አደሮችን በስራቸው አሰልፈው ሥልጣን ላይ ከወጡት የኢትዮጵያ የቀድሞ መሪዎች በተለየ ህዝባዊ የሚያሰኘው መስፈርት ምንድነው? 

ወያኔዎች በህዝብ ድምጽ በዲሞክራሲያዊ መንገድ  ተመርጠው ይሆን ሥልጣን ላይ የወጡት? እንዴትስ የወያኔዎች ሥልጣን ላይ መውጣት ፕሮፈሰር ገብሩ እንደሚነግሩን “ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብ የሥልጣን ምንጭ ሆኗል” ያሰኛል? ይህ እንግዲህ የመጀመሪያው የፕሮፌሰር ገብሩን ሚዛናዊነትና እውነተኛነት እንድጠይቅ ያደረገኝ አጋጣሚ ነበር። ይህንንም የፕሮፌሰር ገብሩን አቋም ጥያቄ ውስጥ ማስገባት የጀመርኩት በወያኔ ወደ ሥልጣን በመውጣቱ “ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብ የሥልጣን ምንጭ ሆኗል” ካሉበት ከዛሬ 24 ዓመት ጀምሮ ነው።

ፕሮፌሰር ገብሩ የወያኔ መንግስት ሥልጣን ላይ ከወጣ በሁላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው የኢትዮጵያ የጥናት ኢንስትቲዩት ዳይሬክተር ሆኖው ተሹመው አገልግዋል። እኚህ ሰው በሥልጣን ላይ ላለው መንግስት ባለቸው በጎ አመለካከትና በትግሬነታቸው ባገኙት ሰፊ እድል የመከላከያ ሚኒስቴር መረጃዎችን በስፋት ለመመርመር እድል ተሰጥቶአቸው ነበር። በዚህም እድል ተጠቅመው ኢትዮጵያ ከሶማሌያ ጋር ስላደረገቸውና በሰሜን ኢትዮጵያ ስለተደረጉት ጦርነቶች 437 ገጾች ያሉት ዳጎስ ያለ መጽሃፍ[4] ከዛሬ ዘጠኝ ዓመታት በፊት ጽፈው በአሜሪካን ሀገር አሳትመዋል። እኚህ የታሪክ ምሁር በዚያ በጻፉት መጽሃፍ ውስጥ በእኔ እይታ አስገራሚ የምላቸውንና የእሳቸውን የታሪክ አዋቂነት እንደዚሁም እንደ አንድ ታሪክ ጸሃፊ ለእውነት ሊያሳዩና ሊሰጡ የሚገባቸውን ዋጋና ክብር ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ጽሁፎቻቸውን ከዚህ በታች እየጠቀስኩኝ ለአንባቢ አስተዋውቃለሁኝ። መጽሃፉ በእንግሊዘኛ የተጻፈ ስለሆነ ከመጽሃፋቸው ውስጥ የጠቀስኳቸውን የእንግሊዘኛውን ጽሁፎች እኔው እራሴ ወደ አማርኛ ተርጉሜዋለሁኝ። ጽሁፋቸውን ከእንግሊዘኛ ወደ አማርኛ ስተረጉም አዛብቼ ተርጉሜውም ከሆነ አንባቢን እንዳላሳስት ብዬ የእንግሊዘኛውንም ጽሁፍ በአባሪነት አካትቼያለሁኝ።

፩ - ፕሮፌሰር ገብሩ በመጽሃፋቸው ውስጥ አሁን በወያኔ ዘመን ባለው ጦር ውስጥ ስላለው የወታደራዊ መኮንኖች የነገድ (ethnic composition of military officer corps) ስብጥር ምን አሉ?

እኚህ ሰው አሁን በኢትዮጵያ በወያኔ መንግስት አገዛዝ ዘመን በሀገራችን ስላለው የብሄራዊ ጦር ዲሞክራሲያዊ ስብጥር “The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa” በሚለውና እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2009 ዓ. ም. ባሳተሙት መጽሃፋቸው ውስጥ የሚከተለውን ጽፈዋል።

የአዲሱ ጦር መሪዎች ስብጥር የህብረተሰቡን ብዝሃነት እንዲያንጸባርቅ ተደርጎ ተዋቅሯል። ምንም እንኳን አዲሱ ጦር ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተዋቀረ ቢሆንም ቅሉ በይበልጥ ወገንተኛና ከፋፋይ ለሆነ የፓለቲካ ታማኝነት የተጋለጠ ነው “The make-up of the officer corps of the new army has been diversified to reflect society. Although the new army is more democratically constituted, it may be more susceptible to sectarian and divisive politics and allegiances[5]”.
ፕሮፌሰሩ የአዲሱ ጦር መሪዎች ስብጥር የህብረተሰቡን ብዝሃነት እንዲያንጸባርቅ ተደርጎ ተዋቅሯል ካሉን በኋላ ዘወር ብለው ደግሞበይበልጥ ወገንተኛና ከፋፋይ ለሆነ የፓለቲካ ታማኝነት የተጋለጠ ነውይሉናል። ይህ መቼም እርስ በእርሱ የሚቃረን ሃሳብ ነው። ምክንያቱም በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተዋቀረና ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ጦር ለወገንተኛነትም ሆነ ለከፋፋይ ፓለቲካ የሚጋለጥበት አንዳችም ምክንያት አይኖርም። እንኳን በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ይቅርና በዲሞክራሲያዊነታቸው በማይታወቁት የንጉሱና የደርግ መንግስታት ዘመን የኢትዮጵያ ጦር ለወገንተኛነትም ሆነ ለከፋፋይ ፓለቲካ አልተጋለጠም ነበር። ፕሮፌሰሩ ምሁራዊ ቅንነት ቢኖራቸው ኖሮ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተዋቅሮአል የሚሉት ጦር ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ መልክ ለወገንተኛነትም ሆነ ከፋፋይ ለሆነ ፓለቲካ የሚጋለጥበትን ምክንያት ምንድነው ብለው ይጠይቁ ነበር። ነገር ግን ራሳቸውን ይህን ጥያቄ ቢጠይቁ ኖሮ የሚያገኙት መልስ የሚያስደስታቸው አይሆንም። ይህ እሳቸው የህብረሰብን ብዝሃነት በሚያንጸባርቅ መልክ ተዋቀረ የሚሉት ጦር የትግሬዎች የነገድ ፓለቲካ በወለደው የአድሎ ሥርዓት ስለተበተበ አመራሩ በአብዛኛው ከአናሳው የትግሬ ነገድ የወጣ ነው። ስለሆነም የአሁኑ የጦሩ አደረጃጀት የሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶችን ተወላጆች ከከፍተኛ የሥልጣንና የኃላፊነት ቦታዎች የሚያገል ነው። በዚህም ምክንያት ነው ጦሩ ለወገንተኛነት ስሜትና ከፋፋይ ለሆነ የፓለቲካ ታማኝነት የተጋለጠው።

ከላይ የጠቀስኩት የፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ጽሁፍ አንድ ሰው በአክራሪ ብሄረተኛነት ስሜት አይምሮው የተበከለ አዋቂ ሰው የሰባት ዓመት ህጻን ልጅ እንኳን ሊያይ የሚችለውን እውነታ እንደሚክድ ያሳየናል። ፕሮፌሰሩ በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተዋቀረ በሚሉን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጦር ውስጥ በከፍተኛ እርከን ላይ ያሉት ከዘጠና በመቶ በላይ (>90%) አዛዦች ትግራይ ከሚባልና በቁጥር ስድስት በመቶ (6%) ብቻ የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚወክል አናሳ ነገድ የወጣ ነው። በእኔ ትውልድ አድሃሪ ተብሎ በተወገዘው የንጉሰ ነገስታዊ መንግስት ስር ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በወያኔ አገዛዝ ውስጥ የታየው ዓይነት ወደ አንድ ነገድ ያጋደለ የወታደራዊ መኮንኖች ስብጥር አልነበረም። በእውቀት-አልባነቱና ስሜታዊነት እንጂ በጥልቀት እውቀትን ፈልፍሎ፤ መረጃን ተንተርሶ መከራከር በማያውቀው ትውልድበሚባለው የግራ ትውልድ (የእኔ ትውልድ) ካለ እውቀትና በስህተትፋሽስትተብሎ የተፈረጀው የደርግ ወታደራዊ አምባገነን መንግስት ዘመን የአንድ ነገድ ተወላጆች የሆኑ መኮንኖች 90% በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያን ጦር አመራር የያዙበት ሁኔታ አልነበረም። ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ ግን ይህን ሁሉ ሀገር የሚያውቀውን፤ ጸሃይ የሞቀውን እውነታ ክደው የወያኔ ትግሬዎችን የዘረኛነት ፓሊሲ በብእራቸው አፋልሰዋል፤ በአደባባይም ዋሽተዋል።

- ፕሮፌሰር ገብሩ ሀገሮችን ስላፈረሰው በነገድ ማንነት ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ሥርዓት ምን አሉ? 

የታሪክ ፕሮፌሰሩ በዓለም ውስጥ በሀገር አፍራሽነቱ የታወቀውን በነገድ ማንነት ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ሥርዓት (ethnic-based federalism) ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሆን ግን የተለየ ውጤት እንደሚኖረውና ሀገር ሊያፈርስ እንደማይችል ሳያፍሩና ህሊናቸውን ሳይሰቀጥጣቸው በሚከተለው መንገድ ሊያስረዱን ሞክረዋል።
የኢትዮጵያ በነገድ ላይ የተመሰረተ የፌዴራል ሥርዓት አዲስና ማራኪ የሆነ የፓለቲካ ሙከራ ሲሆን በውስጡ አደጋና ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችንም የያዘ ነው። ነገር ግን ይህ (በነገድ ላይ የተመሰረተ) ፌዴራሊዝም ችግር ባለመፍጠር በታሪክ የተለየ ሊሆን ይችላል   
“The Ethiopian ethnic-based federalist system is a novel and fascinating political experiment laden with potential problems, but one that may prove to be the historical exception[6]”.
ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ከትግራይ በታች ባሉት የኢትዮጵያ ክልሎች የተከሰቱት ደም-አፋሳሽ ግጭቶች፤ የብዙ ሚሊዮን ህዝብ መፈናቀል፤ በራሱ ሀገር ውስጥ ስደተኛ መሆን ወዘተ ለፕሮፌሰር ገብሩ አልታዩአቸውም። ሌላው ቀርቶ ይህ የአንተ ክልል ስላልሆነ ክልሌን ለቀህ ውጣ በሚል አስተሳሰብ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኦሮሞዎችና ኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች ከቀድሞው የሀረርጌ ክፍለ ሀገር የተፈናቀሉበትን፤ አንድ ሚሊዮን ያህል የጌዴኦና የጉጂ ኦሮሞዎች ከቀድሞው የሲዳሞ ክፍለ ሀገር የተፈናቀሉበትን፤ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አማራዎች በወልቃይት፤ ጸገዴ፤ መተከል፤ ቤኒሻንጉል ወዘተ የተፈጁበትን፤ በጥቂት ቀናት ውስጥ 78,000 የአማራ ተወላጆች ከጉራ ፈርዳና ደቡብ ኢትዮጵያ ቤት ንብረታቸው እየተዘረፈና እየተቃጠለ የተባረሩበት -ሰብዓዊ ድርጊት ለእኚህ የትግራይ ምሁር የጥፋት ሥራ ሆኖ አልታያቸውም። ፕሮፌሰር ገብሩ ቋንቋና ባህልን መሰረት አድርጎ ህዝብን እያፋጀ ያለውን፤ ልዩነትና ጥላቻን የሚያራግበውን፤ በኢትዮጵያ ነገዶች መካከል በጥርጣሬ አይን መተያየትን ወዘተ ያስፋፋውንና ከትግራይ በታች ላሉ ለብዙ ሚሊዮን ትግርኛ ተናጋሪ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን መፈናቀልና ሞት ምክንያት የሆነውን መርዘኛ ሥርዓት በበጎነት መታየት አለበት ብለው በሚከተለው አይነት ተከራክረዋል።

- የፌዴራል ህገመንግስት ፋይዳ፤ ዲሞክራሲያዊ ማዕቀፍን ስለመፍጠር፤ የራስን ጉዳይ ስለመምራት።

1987 . . የፌዴራል ህገ መንግስት የኢትዮጵያን አስቸጋሪ ብሄራዊ ክፍፍሎች ችግር በዘላቂነት ለመፍታት፤ የሚያስችል ዲሞክራሲያዊ ማዕቀፍን ለመፍጠር የተደረገውን ቁርጠኛ ጥረት ይወክላል። ኢህአዴግ በመጨረሻ ላይ የሀገሪቱ የተለያዩ ነገዶች የየራሳቸውን ጉዳዮች በራሳቸው ለመምራት ቋንቋቸውን፤ ባህላቸውን እና ልማዶቻቸውን ለማዳበር የሚያስችላቸውን አዲስ አሰራር (ዘዴ) በመተግበሩ ሊመሰገን ይገባል ከዚህ ቀደም የተጨቆኑና የተገለሉ ህዝቦች በመቶ ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የራሳቸው እጣ-ፈንታ ወሳኞች/ዳኞች ሆነዋል

“The federal constitution of 1995 represented the most determined effort to create a democratic framework in which Ethiopia’s intractable national cleavages find a permanent solution. It is to the credit of the EPRDF that if finally implemented an innovative structure that allows the country’s ethnic components sufficient power to manage their own affairs and to develop their languages, cultures and individual customs. Formerly oppressed and marginalized peoples have, for the first time in a hundred years, become arbiters of their own destiny[7]”.
በእርግጥ ነው ፕሮፌሰር ገብሩ ከላይ እንደ ገለጹት የተለያዩ ነገዶች በቋንቋቸው መዳኘት፤ መማር ችለዋል። የብሄር-ብሄረሰቦች ቀን በሚባለው ወያኔዎች በሚያዘጋጇቸው በዓላት ላይ የየክልላቸውን ባንዲራ እያውለበለቡ በባዶ ሆዳቸው መጨፈር ችለዋል። ይህ በጎ ነገር ነው። ነገር ግን የተለያዩ ነገዶች ቋንቋቸውንና ባህላቸውን ከሌሎች ጋር ድልድይ መስሪያ ሳይሆን የልዩነት መገንቢያም አድረገውታል። ይህ ሁሉ ሆኖ ግን እነዚህ የተለያዩ ነገዶች የሀገራቸው ባለቤት አልሆኑም። እነዚህ ነገዶች በዋናነት የእነዚህን ፓለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ህይታቸውን በሚወስኑት ጉዳዮች ላይ ድምጽ የላቸውም። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ እንደ ቅኝ ገዢዎች የሞግዚት አስተዳደር ሾሞ ከላይ ሆኖ በህይወታቸው ላይ የሚወስነው ህወሃት እንጂ የእያንዳንዱ ነገድ እውነተኛ ተወካዮች አይደሉም።

እስቲ ይህንን በምሳሌ ላስረዳ። የአማራ ክልል በሚባለው ሰፊ የኢትዮጵያ ክፍል ውስጥ ብአዴን የሚባል የህወሃት ተወካይ በአማራ ህዝብ ሥም ይህንን ክልል ያስተዳድራል፤ ስለ ህወሃት ሆኖ የአማራን ህዝብ ያሰቃያል፤ ይገድላል፤ ያሰድዳል። በብአዴን ውስጥ ከላይ እስከ ታች በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሰየመው ደመቀ መኮንን ጀምሮ እታች ባለው የብአዴን እርከኖች ላይ የተሰገሰጉት የህወሃት ተላላኪዎች ናቸው እንጂ የአማራውን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብሩ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አስመስክረዋል። እነዚህ የህወሃት ተላላኪዎች፤ እንደዚሁም በዚህ የአማራ ድርጅት ውስጥ የተሰገሰጉት አማራ-ጠል የሆኑ የትግራይ፤ የኤርትራ ተወላጆች እንደዚሁም በችሎታቸውና ለአማራ ህዝብ ጥቅም ቀናኢነት ሳይሆን በአድርባይነታቸውና በሆዳምነታቸው የተመረጡት የአማራ ተወላጆች ናቸው። የወልቃይትን፤ የግጨውን፤ የጸለምትን፤ የራያን ወዘተ መሬቶች እየፈረሙ የሰጡት የብአዴን ካድሬዎች የአማራን መብት የሚያስከብሩና የአማራ ህዝብ ጥቅሜን ያስጠብቁልኛል ብሎ የወከላቸው ሰዎች አይደሉም። እነዚህ የብአዴን ካድሬዎች የአማራ ክልል ተብሎ ለተሰየመው የኢትዮጵያ ክፍል የተመደበው ዓመታዊ በጀት ሥራ ላይ እንዳይውል እያደረጉ በጀቱ በተደጋጋሚ ወቅት ወደ ትግራይ ክልል እንዲዛወርና እዚያ በከፍተኛ ፍጥነት እየተካሄደ ላለው የትግራይ ክልል ልማት እንዲውል አድርገዋል። ህወሃት እያንዳንዱ ክልል የተመደበለትን በጀት በወቅቱ ሥራ ላይ ሳይውል የሚቀር ከሆነ ያ በሥራ ላይ ያልዋለው በጀት በጀቱን በተመደበለት የበጀት ዓመት ውስጥ ሥራ ላይ አውሎ ለሚጨርስ ክልል ይተላለፍ የሚል አስገራሚ መመሪያመሰረት[8] በፓርላማ በኩል አስጸድቋል። በዚህ ዓይነት የአማራ ክልል የተባለው በወያኔ ተላላኪዎች የሚመራ ክልል በጀቱን በተመደበለት የጊዜ ገደብ መጠቀም አልቻለም እየተባለ በተደጋጋሚ ለአማራ ክልል የተመደበው በጀት ወደ ቀልጣፋውና በጀቱን በተመደበለት ጊዜ ሥራ ላይ ወደሚያውለው የትግራይ ክልል ተላልፏል። በዚህ ዓይነት የአፋር፤ የኢትዮጵያ ሶማሌ፤ የጋምቤላ፤ የቤኒሻንጉል ወዘተ ክልሎች በጀት እየታጠፈ ለትግራይ ክልል መገንቢያ ፈሰስ ሲደረግ ቆይቷል። ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በዚህ ዓይነት መንገድ የትግራይ ክልል እድገት[9] በሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ኪሳራ ሲካሄድ ቆይቷል። ይህ ነው እንግዲህ ዶ/ር ገብሩ ታረቀ “ኢህአዴግ በመጨረሻ ላይ የሀገሪቱ የተለያዩ ነገዶች የየራሳቸውን ጉዳዮች በራሳቸው ለመምራት ቋንቋቸውን፤ ባህላቸውን እና ልማዶቻቸውን ለማዳበር የሚያስችላቸውን አዲስ አሰራር (ዘዴ) በመተግበሩ ሊመሰገን ይገባል” የሚለን።

በቅርቡ የአማራ አክቲቪስቶች የሚባሉ ወጣቶች በአማራ ክልል ውስጥ ያለውን እጅግ ኋላቀርነት የሚያሳዩ ምስሎችን (የአማራ ልጆች በፈራረሱና ከከብት ጋጣ በባሰ ደረጃ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩበትን ሁኔታ በፌስ ቡክ ገጾች አሳይተውናል። ህጻናት ዛፍ ጥላ ሥር የሚማሩባቸው ትምህርት ቤቶች፤ የፈራረሱና አንዳችም ዓይነት የጤና ተቋማት መሆናቸውን የሚያሳይ ቁመና የሌላቸው የህክምና መስጫ ክሊኒኮች ወዘተ ናቸው በሃያ ሰባት ዓመታት ውስጥ ፕሮፌሰር ገብሩ እያንዳንዱ ነገድ የራሱን ጉዳዮች በራሱ ይመራል በሚሉትና ራሱን በሚያስተዳድረው የአማራው ክልል ውስጥ የሚታዩት። ይህን መሰል በተዘዋዋሪ መንገድ በወያኔ ትግሬዎች የሚዘወር፤ የአማራውን ህዝብ ሆን ብሎ የሚያደኸይ፤ በተጠና መንገድ ለአማራው ህዝብ የተመደበው በጀት ሥራ ላይ እንዳይውል ሊያደናቅፉ የሚችሉር አስተዳደራዊና ቢሮክራሲያዊ መዋቅሮችን ፈጥሮ ለአማራው ክልል የተመደበውን በጀት በጊዜ ሥራ ላይ አልዋለም እያለ ተመላሽ በማድረግ የተመደበለትን በጀት በቅልጥፍና ሥራ ላይ ወደሚያውለው የወርቁ የትግራይ ህዝብ ክልል እንዲዛወር የሚያደርግና በህወሃት የሚዘወር የሞግዚት አስተዳደር እንዴት ነገዶች የየራሳቸውን ጉዳዮች በራሳቸው ለመምራት የሚያስችላቸውን አዲስ አሰራር ተግብረዋል ሊያሰኝ ይችላል። ህወሃት ከአማራው መሃል የተማረ ሰው የጠፋ ይመስል ገነት ገብረ እግዚአብሄርን የመሰሉ አማራ-ጠል የትግራይ ተወላጅ የሆነች የህወሃት ካድሬ የአማራ ክልል የከተሞች ልማትና የእንዱስትሪ ልማት ዋና ኃላፊ አድርጎ የአማራው ክልል በልማት የኋሊት እንዲሄድ አድርጓል። ከጣና በለስ ላይ ያለው የመብራት ኃይል በብዙ መቶ ኪሎሜትሮች መስመር ዘርግቶ የትግራይን ከተሞች ሲያበራ፤ ለትግራይ እንዱስትሪዎች የኃይል ምንጭ ሲሆን ጣና በለስ የሚገኝበት የአማራ ክልል ግን ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት አንዳችም የኃይል አቅርቦት ሳይደረግለት ኢንቨስተር የተባሉት ሰዎች በአካባቢው የልማት ሥራ ለመስራት ዝር እንዳይሉ ተደርጓል። ይህ በሥልትና በጥናት ሆን ተብሎ የተደረገ የወያኔ ትግሬዎች የክፋት ሥራ ነው። ይሄ በአማራና በትግራይ ህዝብ መካከል ጥላቻን እንጂ ፍቅርን የሚገነባ አይደለም።

ፋሽስቶች የሆኑት የወያኔ ትግሬዎች ዋነኛ ጠላታችን ነው የሚሉትን የአማራ ህዝብ ለመጉዳት ምን ያላደረጉት ነገር አለ? ለመሆኑ በረከት ስምዖንን፤ ህላዌ ዮሴፍን፤ ከበደ ጫኔን፤ ገነት ገ/እግዚአብሄርን፤ ካሣ ተክለብርሃንን የመሳሰሉ ትግርኛ ተናጋሪዎች ሁሉም የራሱን ክልል ያስተዳድራል በሚባልበትና በነገድ ማንነት ላይ በተመሰረተ የፌዴራል ሥርዓት ባለበት ሀገር ውስጥ የራሳቸው ክልል ባልሆነው የአማራ ክልል ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ ተደርገው የተሾሙት በምን ቀመር ወይም በምን ሂሳብ ነው? የትኛው አማራ፤ ጉራጌ፤ ኦሮሞ ወይም ኢትዮጵያዊ ሶማሌ ወዘተ ነው በትግራይ ክልል ውስጥ በኃላፊነት ቦታ ላይ ተመድቦ የሚሰራው? የወያኔ ትግሬዎች፤ ኤርትራውያን (በረከት ስምዖን የመሳሰሉ) ወዘተ ታሪካዊ ጠላታችን ብለው በሚቆጥሩት ህዝብ ላይ በሚፈነጩባት በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዴት የተለያዩ ነገዶች የየራሳቸውን ጉዳዮች በራሳቸው ለመምራት የሚያስችል አዲስ አሰራር አለ ብለው ፕሮፌሰረ ገብሩ ለመጻፍ በቁ?። ፕሮፌሰሩም ይህንን ሁሉ ከላይ የጠቀስኩትን ሀቅ ያጡታል፤ ወይም አያውቁትም ብዬ አልልም። ነገር ግን ህሊናቸው በአክራሪ የትግራይ ብሄረተኛነት ስሜት ስለታወረ የትግራይ ክልል ተወላጆች በአማራና በሌሎች የኢትዮጵያ ነገዶች ኪሳራ የሚጠቀሙበትን ይህ የአፓርታይድ ሥርዓት ለእሳቸውና እሳቸው ለወጡበት የትግራይ ክልል ህዝብ ተስማሚ ነው። ስለሆነም ይህንን የአፓርታይድ ሥርዓት መደገፋቸው አስገራሚ አይደለም።

እስቲ የወያኔ ትግሬዎች የአፓርታይድ ሥርዓት በአዲስ አበባ የከተማ ቦታዎች ሽንሸና ላይ ምን ዓይነት ተፅዕኖ እንዳለው የሚከተለውን የአቶ ዮሃንስ ታደሰ አካን ጥናት ውጤት በማየት ለመረዳት እንሞክር።

“የአዲስ አበባ ከተማ የሪል ስቴት ልማትን የሚመለከት ዝርዝር ጥናት በአስቸኳይ ተዘጋጅቶ ይቅረብ የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ከጠቅላይ ሚንስትር ፅህፈት ቤት ሲወርድ ሲዋረድ መጥቶ እኔ ዘንድ ደረሰ። አቶ መኩርያ በቀጥታ እኔ ቡድን አዋቅሬ በአስቸኳይ እንዳቀርብ አዘዘኝ። በጥናቱ ወቅት ከታዘዝኩት ይልቅ ያልታዘዝኩት ቀልቤን ገዛኝ። የሪል እስቴቶቹ ባለቤቶች! በአዲስ አበባ ከ130 በላይ ሪል እስቴቶች ይገኛሉ።  ከ5.000.000.00 ካሬሜትር በላይ ቦታ በሪል እስቴት ልማት ለመኖሪያ ቤት ግንባታ ብቻ የተላለፉ ናቸው። ከዚህ ቦታ ውስጥ አንድ ሶስተኛው በተራው ትግሬ የተያዘ ሲሆን ሌላኛው አንድ ሶስተኛ በአያት ሪል ስቴት የተያዘ ነው። አያት ሪል እስቴት እንደ ዛሬው ጌዜ ሳይከዳው በፊት ጀርባው በምርጥ የጡት አባቶች የተደገፈ ነበርና በግልፅ ይህን ያህል ተብሎ መግለፅ ቢያቅትም በተዘዋዋሪ ምርጦቹን ባለ መሬት እንዳደረገ ይገመታል። ቀሪው አንድ ሶስተኛ በዳያስፖራ ማህበራት እና ሌሎች ባለ ሀብቶች የተያዙ ናቸው። ከነዚህ የዲያስፖራ ማህበራት አብዛኛው የትግራይ ተወላጆች ዳያስፖራዎች ናቸው። በእርግጥ አንዳንድ ነቄ ዳያስፖራዎች ከትግሬዎቹ ማህበር በመጠጋት መሬት የደረሳቸው አሉ። በአጠቃላይ እስታቲክሱን ስናየው በትንሹ ሰባ በመቶ የአዲስ አበባ ሪል እስቴት የተያዘው በትግራይ ተወላጆች እና በአያት አክሲዮን ማህበር ነው[10]”። 

እንግዲህ ከዚህ ከላይ ከጠቀስኩት የአቶ ዮሃንስ ጥናት መረዳት እንደምንችለው ለቤቶች ልማት ከሚውለው የአዲስ አበባ ከተማ ቦታ ውስጥ ሁለት ሶስተኛውን የተቀራመቱት የትግራይ ተወላጆች ናቸው። የትግራይ የበላይነት የሚለው ሃሳብ ትክክል አይደለም ለሚሉት ሰዎች ከሀገሪቱ ስድስት በመቶ 6% ድርሻ ካለው የህዝብ ክፍል የወጡ ሰዎች የኢትዮጵያ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ ለከተማ ልማት ከተመደበው ቦታ ውስጥ 66% የሚሆነውን መሬት የሚያገኙበት ሁኔታ የአንድ አናሳ ነገድ ተወላጆች በፓለቲካው፤ በኢኮኖሚው መስክ ያላቸውን ጉልህ የሆነ የበላይነት የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። 

ከላይ የአማራ ክልል ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የሚገኝበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አስመልክቼ ፕሮፌሰር ገብሩ ህወሃት-ሰራሽ ስለሆነው የነገድ ፌዴራሊዝም በጎነት የደረሱበትን ድምዳሜ ህፀፅ ነቅሼ ካወጣሁ በኋላ አሁን ደግሞ የጋምቤላን ክልል እንደ ምሳሌ በመውሰድ የእሳቸው ድምዳሜ ቅንነት የጎደለውና ሀሰተኛ መሆኑን አሳያለሁኝ።

ክፍል - አክራሪ ብሄረተኛነት ምንድነው? ተከታዮቹ በሆኑት የአንድ ነገድ ተወላጆችስ ላይ የሚያስከትለው ስነልቦናዊ ለውጥ ምን ይመስላል?--› (የዚህን ጽሁፍ ክፍል በዚህ ማስፈንጠሪያ አማካይነት ማንበብ ትችላላችሁ)https://welkait.com/?p=15736
ክፍል - አክራሪ ብሄረተኛነትና የሚፈጥረው ከማንኛውም ነገር በላይ ለራስ ነገድ ጭፍን ታማኝነትን የማሳየት ዝንባሌ --› የዚህን ጽሁፍ ክፍል ይህንን ማስፈንጠሪያ በመጫን ማንበብ ትችላላችሁ።  -› https://welkait.com/?p=15802
ክፍል - አክራሪ ብሄረተኛነትና የሚፈጥረው የራስን-ነገድ ብቻ እጅግ አብልጦ የመውደድ ስነልቦና ምን ይመስላል? - --› (የዚህን ጽሁፍ ክፍል በዚህ ማስፈንጠሪያ አማካይነት ማንበብ ትችላላችሁ) https://welkait.com/?p=15998

ክፍል - አክራሪ ብሄረተኛነት በሰዎች ላይ የሚያስከትለው ስነልቦናዊ ለውጥና የሚፈጥረው ተፅዕኖ ምን ይመስላል -› የፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀን ጽሁፎች በምሳሌነት በመጠቀም ይህን አሳያለሁኝ።
ክፍል - አክራሪ ብሄረተኛነት በሰዎች ላይ የሚያስከትለው ስነልቦናዊ ለውጥና የሚፈጥረው ተፅዕኖ ምን ይመስላል -› የፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀን ጽሁፎች በምሳሌነት በመጠቀም ይህን አሳያለሁኝ።


[1] - Gebru Tareke, “Rural Protest in Ethiopia, 1941-1970: A Study of Three Rebellions” PhD dissertation, Syracuse University, 1977
[2] - አዲስ ዘመን ጋዜጣ - ጥር 19 ቀን 1986 . . (ለዝርዝሩ በዚህ በጠቀስኩት ዕለት የወጣውን የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ይመልከቱ)
[3] - የሌሎች ነገድ ተወላጆችን በመታከክ ሆነ ከፊት በማስቀደም የልብን መናገር በትግራይ ልሂቃን በኩል የተለመደ ነገር ነው። ለዚህ አንድ ምሳሌ ልጥቀስ። በቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኑቨርሲቲ መለስ ተክሌ የሚባል አክራሪ የትግራይ ብሄረተኛ ነበር። ይህ ሰው በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ተራማጅና የግራ-ቀመስ ፓለቲካ አራማጅ መስሎ ራሱን ቢያቀርብም ቅሉ እንደ አንዳንድ የትግራይ ልሂቃን በአማራ ህዝብ ላይ ያለውን ጥላቻ መደበቅ የሚችል ሰው አልነበረም። ታዲያ 1966 .. አዲስ አበባ ዩኑቨርሲቲ ውስጥ በተካሄደ የተማሪዎች ስብሰባ ላይ መለስ ተክሌና መሰሎቹ የሆኑ የትግራይ ተወላጆች ሰለሞን ዋዳ የሚባል አንድ የወላይታ ተማሪ ከፊት በማሰለፍ የወላይታው ተማሪ አማራን የሚያወግዝ ንግግርና መፈክር እንዲያሰማ ያደርጉታል። ሰለሞን ዋዳ ደግሞ የአማራን ህዝብ ስም እየጠራ አማራን ሲያወግዝ እነ መለስ ተክሌ ከኋላ ሆነው በሳቅ ይንፈቀፈቁ እንደነበረ ከዛሬ ሃያ አምስት ዓመት በፊት እዚህ ሆላንድ መጥቶ ያገኘሁት የቀደሞ የአዲስ አበባ ዩኑቨርሲቲ ተማሪ አጫውቶኛል። አስገራሚው ነገር የአማራው ህዝብ በዚያ ቦታ ላይ በአድሃሪነትና በጨቁኝነት በጅምላ ሲሰደብ የአማራ ተራማጆች ደግሞ ተሽኮርምመው ያዩ እንደ ነበረ ይህ ሰው ገልጾልኛል። ይህንን ታሪክ የነገረኝም ሰው እራሱ አማራም ቢሆን ዝም ብሎ ይመለከት እንደነበረ ራሱ ያደረገውን ቸልተኝነት በመታዘብ ገልጾልኛል። እንዲያውም ይህ ሁሉ ሲደረግ ምንም አላልንም፤ አንዳንዶቹም አማራው በጨቋኝነትና በትምክህተኛነት ሲወገዝ አብረው ከነሰለሞን ዋዳ ጎን ቆመው ነበር ብሎ በቁጭት ነግሮኛል። በተለይ በአማራ ህዝብ ላይ ጥላቻ ያላችውን የውሁድ ማህበረሰቦች (minority communities) ተወላጆችን እየፈለጉ የአማራን ህዝብ ሥም ለማጠልሸት መሞከር የትግራይ ልሂቃን በተደጋጋሚ የሚያደርጉት ነገር ነው። ለአማራ ህዝብ ከፍተኛ ጥላቻ የነበረው ሰለሞን ዋዳ 1967 . . ገበሬዎችን የከተማ ነዋሪዎችንና ሥራ-ፈቶችን ወዘተ በማስተባበር ወላይታ ሶዶ ከተማ ውስጥ ገብተው የነገድ ማነንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እንዲፈጽሙ በማስደረግ በርካታ የአማራ ተወላጆችና ሌሎች መጤ በሚባሉ ነገዶች ተወላጆች ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርጓል፤  ንብረታቸው ተዘርፏል። ይህንን ያስተባበረውና የመራው በፀረ-አማራነቱ የሚታወቀው ሰለሞን ዋዳ ሲሆን ይህ ሰው በደርግ መንግስት ተይዞ ኋላ ላይ ተገድሏል። ዲሞክራሲያ የተባለው የኢህአፓ ልሳን በወቅቱ እጅግ ዘግናኝ በሆነ መንገድ ሰለሞን ዋዳ ባስተባበራቸው የወላይታ ተወላጆች በአሰቃቂ ሁኔታ በገጀራና በጦር ተጨፍጭፈው ስለሞቱት አቶ ጥሩነህ የሚባሉ የአማራ ተወላጅም ሆነ ሌሎች ተጎጂዎች አንዳች ነገር ሳይል የእኚህንና የሌሎችን መጤ ተብለው የተፈረጁ ነገዶች ህይወት በማስጠፋት ጭፍጨፋውን ስለመራው ሰለሞን ዋዳ መታሰርና መገደል በቁጭት ሲጽፍ ነበር። የኢትዮጵያ አብዮት በሚባለው እንቅስቃሴ ውስጥ የተደረጉ ግጭቶች፤ ግድያዎች ወዘተ መደባዊ መሰረት ያላቸው ነው ቢባልም በወላይታ ሶዶ ውስጥ ያሉ ጠላ ሽጠው የሚተዳደሩ የአማራ፤ የጉራጌ ወዘተ ተወላጆች ላይ በሰለሞን ዋዳ መሪነት የተደረገው ጭፍጨፋ ግን መሰረቱ የመደብ ግጭት ሳይሆን የነገድ ጥላቻ ነበር። ሰለሞን ዋዳ በተለይ አማራ ለሚባለው ህዝብ እጅግ ከፍተኛ ጥላቻ የነበረው (he has visceral hatred for the Amara people) ሰው ነበር። በዚህም ጥላቻው ምክንያት መለስ ተክሌን የመሰሉ ፀረ-አማራ የሆኑና የተራማጅነት ካባ ደርበው የተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ እንደልባቸው ሲጨፍሩ የነበሩ ግለሰቦች ሰለሞን ዋዳን የመሰለ ጸረ-አማራ ጃስ እያሉና ከፊት እያስቀደሙ አማራውን ያወግዙ ነበር። ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት በአማራው ላይ የተቃጣው የወያኔዎች የዘር ማጥፋት ዘመቻ እነዚህን በመሰሉና ባለፉት ስድሳ ዓመታት በተለይ የግራውን የፓለቲካ ኃይል በሽፋንነት በመጠቀም የአማራውን ህዝብ ማንነት ጥላሸት ሲቀቡ በነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በተደረገ ዘመቻ መደላድል ላይ የተመሰረተ መሆኑን ይህ የዛሬው ትውልድ ልብ ሊል ይገባል። ክፍሉ ታደሰ የተባለው የቀድሞ የኢህአፓ መሪ ካድሬ “The Generation” ብሎ በጻፈው የኢህአፓ ታሪክ ውስጥ የሰለሞን ዋዳን ሰብዕና አሽሞንሙኖ ሲያቀርብ፤ በተቃራኒው አቶ ጥሩነህን የመሳሰሉ በሆቴል ሥራ  ላይ የተሰማሩ የአማራ ተወላጆች መጤ ተብለው ወላይታ ሶዶ ውስጥ በማንነታቸው ምክንያት የደረሰባቸውን አሰቃቂ ግድያ ከቁም ነገር ሳይጽፈው እንዲያውም ለውጡን አንቀበልም አሻፈረኝ በማለት ባደረጉት እንቅስቃሴ እንደተገደሉ አድርጎ አቅርቧል። መለስ ተክሌ አክራሪ የትግራይ ብሄረተኛ ከመሆኑም በላይ ለአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ካለው የመረረ ጥላቻ የተነሳ በቀዳማዊ /ስላሴ ዩኑቨርሲቲ መድረክ ላይ ግርማቸው ዓለሙ የሚባል የተማሪዎች ማህበር የአማርኛ ቋንቋ መጽሄት አዘጋጅ የነበረን ሰው በተማሪዎች ስብሰባ ላይ በአማርኛ ቋንቋ በመናገሩ (የጨቋኝ ህዝብ ቋንቋ ተብሎ) መድረክ ላይ ወጥቶ ከግርማቸው ማይክራፎን ነጥቆ ግርማቸውን ከመድረኩ ላይ እንዲወርድ ማድረጉን አንድ በጊዜው የዩኑቨርሲቲ ተማሪ የሆነ ሰው ነግሮኛል። ይህ ሁሉ ሲሆን ይህንን እብሪተኛ የሆነ የትግራይ ዘረኛ ፊት ለፊት ወጥቶ የተናገረው ሰው አልነበረም። የዛሬው ትውልድ ከእንግዲህ ወዲህ መለስ ተክሌን የመሳሰሉ የትግራይ ብሄረተኞችን እሽሩሩ የማለት ዝንባሌ ያለፈ ታሪክ ማድረግ አለበት።
[4] - Gebru Tareke, “The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa, published in 2009 by Yale University Press.
[5] - Gebru Tareke, “The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa”, 2009 (see on Pp. 328)
[6] - Gebru Tareke, “The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa”, 2009, page 327
[7] - Gebru Tareke, “The Ethiopian Revolution: War in the Horn of Africa”, 2009, page 329
[8] - አዲስ ዘመን ጋዜጣ የካቲት 2 ቀን 1989 . .  እትም መለስ ዜናዊ ለፓርላማ ያደረገውን ንግግርና የያዘ ሲሆን መለስ በዚህ ንግግሩ ውስጥ 1988 . . ጀምሮ የተመደበላቸውን የዓመት በጀት በጊዜው ተጠቅመው የማይጨርሱ ክልሎች ላይ በጀታቸው ተወስዶ ለሌሎች የተመደበላቸውን በጀት በጊዜው ለሚጨርሱ ክልሎች እንደሚሰጥ ተናግሯል። ይህም ፓሊሲ 1988 . . ጀምሮ በተግባር ላይ ውሏል። በዚህ ዓይነት ነው በተደጋጋሚ አማራ ክልል የሚባለው ክልል በጀቱን በጊዜ መጠቀም አልቻለም እየተባለ በጀቱ እየተወሰደበት በቅልጥፍናና በፍጥነት የተመደበለትን በጀት ለሚጨርሰው የትግራይ ክልል እየተላለፈ የተሰጠበት ምክንያት። ይህንን ደግሞ ለማስፈጸም እንዲቻል ነው የአማራውን ክልል ልማትና እድገት ሆን ብለው የሚያደናቅፉ የኤርትራና የትግራይ፤ የሲዳማ እንደዚሁም ለሆዳቸው ያደሩ የአማራ፤ የአገው ካድሬዎች ተመልምለው ይህንን ክልል በማናቸውም የልማት መስፈርት ኋላ-ቀር እንዲሆን ያደረጉት። ገነት ገብረእግዚአብሄርን የመሰሉ የትግራይ ተወላጆች የአማራ ክልል የእንዱስትሪና የከተሞች ልማት ኃላፊ ሆነው የአማራውን ክልል በእፉቅቅ እንዲሄድ ያደረጉት በዚህ ዓይነት ነው። ይህን የወያኔ ትግሬዎች የክፋት ሥራ ይህ ትውልድ ልብ ሊልና ፈጽሞ ሊዘነጋው የማይገባና ታግሎ ማስቆምም ያለበት ጉዳይ ነው።
[9] - የትግራይ ክልል እድገት በሁለት መንገዶች እንዲፋጠን ተደርጓል። አንደኛ በፌዴራሉ መንግስት የሚቀረጹ ፓሊሲዎች የዚህን ክልል ህዝብ በበጀት ድልድልም ሆነ በፕሮጄክት ድልድል ከማንም ክልል በተሻለ ተጠቃሚ አድርጓል። በሁለተኛ ደረጃ በመላው ሀገሪቱ ውስጥ ተሰራጭተው የሚገኙት የክልሉ ተወላጆች የሆኑና በያዙት መንግስታዊ ሥልጣን፤ በሚያገኙት መንግስታዊ ድጋፍ (ብድር፤ ካለ ታክስ እቃ ወደ ሀገር የማስገባት፤ ወዘተ ጥቅሞች) የሀገሪቱን ሃብት የአንበሳ ድርሻ (በንግድ፤ በእርሻ፤ በእንዱስትሪ፤ በፋይናንስ ወዘተ) የተቆጣጠሩ ግለሰቦች በርካታ ካፒታል ወደ ትውልድ መንደሮቻቸው እየወሰዱ በትግራይ ክልል ውስጥ ጉልህ እድገትና መሻሻል እንዲመጣ አድርገዋል። 
[10] - ዮሃንስ ታደሰ አካ፤ “የተስፋው ነፀብራቅ” ሚያዝያ 2013 ዓ. ም. እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በጀርመን ሀገር የታተመ መጽሃፍ