Saturday, June 30, 2018

ወታደሮቹን ከድቶ ከሻዕቢያ ጋር የወገነው ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ዛሬም ሳያፍር ለኢሳያስ ማሽቃበጡን ብሶበታል! ጌታቸው ረዳ (የኢትዮጵያን Ethiopian Semay)


ወታደሮቹን ከድቶ ከሻዕቢያ ጋር የወገነው ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ዛሬም ሳያፍር ለኢሳያስ ማሽቃበጡን ብሶበታል!
ጌታቸው ረዳ (የኢትዮጵያን Ethiopian Semay)
 
ወደ ርዕሱ ከመግባቴ በፊት አንዳንድ የዜና ዘጋቢዎች አንባቢን ለማግኘት ሲሉ የማይሆን ወሬ እየዘገቡ አንባቢን ስያጃጅሉ እንደነበር ታዝቤአለሁ። ለምሳሌ አባይ ፀሓየ አሶሳ ውስጥ ባንድ ሆቴል ውስጥ አንዳይገባ እንዳይወጣ ታግቶ ይገኛል። አብይም በስልክ ደውሎ እንዳትንቀሳቀስ አንዳትለቁት…ብሎ ደውሎለታል..” እያሉ ሲዘግቡ ዜናውን እንደ ትኩስ ዜና በየድረገጹ ሲያስፋፉት አንብቤ ገርሞኛል። እንዲህ የሚጽፉ ደግሞ ታዋቂ ጋዜጠኞች የሚባሉ ናቸው። እውነቱ ግን ሌላ ነው። እኔ በቅርብ ስለምከታተል (ከውስጥ አዋቂ) አባይ ያለው አዲስ አበባ ውስጥ ነው። በነፃ ነው የሚንቀሳቀሰው። ወያኔዎች እንደልባቸው በነፃነት እየኖሩ ሆሆታው ግን ቀጥሏል። አብይን ማሞገስ ትክክል ነው። እኔም የምደግፈው ነው፡ ግን ‘አብይ አብይ’ ብሎ በጣም የተለጠጠ ‘ዘኒት’ የሚሉት የማሽቃበጥ ወረርሺኝ ተፈትሾ ረጋ ተብሎ “እውነተኛውን መሰረታዊ ለውጥ” እንዲካሄድ ጫና መፍጠር ካልሆነ በስተቀር “ፈገግ ላለላት ሁሉ እግርዋን እንደ እምታነሳዋ ባልቴት አይነቱን ያልለየለት ግልቢያ “የፖለቲካ እፍፍ እፍፍ ፍቅር” መጥፎ የሆነ የመንጋ ባሕላችንን በጥንቃቄ መፈተሽ ያሻዋል። “ያዋከቡት ነገር ምዕራፍ አያገኝም፤ ፍቅሬ ፍቅሬ በዛ እኔ አላማረኝም” (ጥላሁን ገሠሠ)።

አሁን ወደ ርዕሱ እንግባ፦
 

ኤርትራን ግንጣላ መቃወም የለብንም  ዓሰብ የኛ ኣይደለም የተባበሩት መንግሥታት ፈርሞ ሰጥቷቸዋል፤ ስለዚህ ኤርትራ ዓሰብ የኛ ነው ብሎ መሟገቱ ይቁም ብሎ ጌቶቹ ምዕራባውያን እና ሸሪኮቹ ሻዕቢያዎች የሰጡትን የቤት ስራ ለማከናወን በየሚዲያው ሳያፍር በድፍት ሲቦተልክላቸው መቆየቱ ጽሑፌን የተከታተላችሁ የምታስታውሱት ነው።ዛሬም ቀጥሎበታል።
 
 ዳዊትን ከኢሳያስ ባርያዎች ጋር ጦርነት ገጥመው ኤርትራ ዘምተው የነበሩት ጉዱን የሚያውቁት የድሮዎቹ የኢትዮጵያ ወታደሮች “ባንዳው ሻለቃ” ብለው ይጠሩታል። ስለ ዳዊት በጻፍኩኝ ቁጥር በስልክ ያነጋገሩኝ ወታደሮች የሚጠሩት በዚሁ ስም ነው። ባንዳው ሻለቃ በሚገርም ሁኔታ ‘በጣም አለቅላቂ አድርባይ ከወታደራዊ ማዕረጉ ጋር የማይሄድ ሓፍረተ-ቢስ እና ዋሾ’ በሚል ነው ብዙዎቹ ሳነጋግራቸው የሚገልጹት። ስለ መሆኑ ደግሞ በብዙ ጽሁፎቹ እና በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በሰነድ የተደገፈ  የሻለቃው የገዛ እጅ ጽሑፉ ይነግሩናል።
ከሻለቃው ጋር አብሮ በአገር ክሕደት የሚንቀሳቀሰው ከፍተኛ የደርግ ባልሥልጣን የነበረው ዶ/ር ካሳ ከበደም የዚህ “የግም ለግም አብሮ ያዘግም ቡድን” አባል ነው። ካሁን በፊት ስለሁለቱ ሰዎች በሰፊው አንደተቸሁት ለኤርትራኖቹ ያልበጃቸው ነብሰ ገዳዩ ኢሳያስ አፈወርቂን ለኛ በማሻሻጡ ደላላነት ተሰማርተው ስለዚህ ነብሰ በላው አረሜ ቅዱስ ስብእና ሲሰብኩን ሲባጁ እንደነበር በሰፊው ገልጫለሁ።
 
መለስ ዜናዊ የሸቀለበትን ኤርትራን የማስገንጠል ሴራ እውን አደርጋለሁ ብሎ የተነሳው አብይ አሕመድ ህጻናቶቻችን እና ወታደሮቻችንን የፈጁብንን ሰው በሊታዎችን ለሻዕቢያዎቹ ያደረገው አስገራሚ አቀባበል በማየት ዳዊት እና ከበደ ከግንቦት 7 ከኮኸን እና ከመሳሰሉት ጋር ከበስተጀርባ ሆነው ሲያሴሩት የነበረው ሴራ ዛሬ በድንገት ስለተሳካላቸው ዛሬ ዳዊት “The Moment of Truth for Eritrea and Ethiopia” በሚል ርዕስ የለመደበትን ለሻዕቢያዎቹ ዕልልታ እያቀለጠ ነው።
 
አብይም ሆነ ካሳ እና ዳዊት እስከ እዚህ ድረስ ድፍርት የሰጣቸው ከበስተጀርባ ሆኖ የሚገፋው ሃይል ማን አንደሆነ ፖለቲካውን የምንከታተል ሰዎች የምናውቀው ነው። ዛሬ ጃፓናዊው አሜሪካዊው አጭሩ ሰውዶናልድ ያማሞቶእና በብዙ ሺሕ ዶላር እየተከፈለው ለኤርትራኖችሎቢ” (ዳላላ) ሆኖ ተቀጥሮ እየሰራ ያለው ከቀዝቃዛው በረዶ ኢሳያስን አውጥተው በአሽቃባጭ ሙዚቀኞች እና በአስቃባጭ ስፖርተኞች ታጅበውገዛ ኣእዱግየአህዮች /አማራዎች/ ቤተመንግሥትእያሉ ሲሰድቡት በነበሩበት የእነ እምየ ሃይለስላሴ የነ እምየ ምኒለክ አዳራሽ ገብተው ሻዕቢያዎች እንዲጨፍሩበት ከበስተጀርባ ስራቸውን ሰርተው ድምጻቸውን አጥፍተው በተላላኪዎቻቸው ለነዳዊት አስረክበው ይኼው እነ ዳዊት ዕልልታቸውን እያስተጋቡ ነው።
ይህ አፍረተ-ቢስ ሰው ለአረመኔው ኢሳያስ የጋለ ፍቅር ስላለውኢሳያስ አፈወርቂን የኢትዮጵያ መሪ እንዲሆንእራሱ በነገረን ጽሑፍ እንደጠየቀው  እንዲህ ይላል።
 
“Why don’t you take over the whole of Ethiopia with Eritrea? Ethiopians will accept you as their leader of a united country and my colleagues and myself will immediately change our organization in support of this.”
 
በማለት ኤርትራን ወደ ገሃነመ እሳት የቀየራት የአፍሪቃ ሰሜን ኮርያ ተብላ እንድትታወቅ ያደረገ የብዙ ሚሊዮን ሕዝብ ህይወት ስቃይ ምክንያት የሆነ፤ ሰዎች ለበደዊኖች እንዲሸጡ ወታደሮቹ እና ጀኔራሎቹ በዚህ የሰው ማዟዟር ሽያጥ እና የወርቅ፤ በአልማዝ እና በጦር መሳሪያ ማዟዟር ጥቁር ገበያ ተሰማርቶ ሚሊዮኖቹን ወደ ስደት እንዲሰማሩ እና በታሸገ የብረት ሳጥን ውስጥ (ኮንተይነር) ተቆልፈው ብዙዎቹ ታፍነው በትንፋሽ እጥረት እየተሰቃዩ እንዲሞቱ፤ምላሳቸው በምላጭ እየተቆረጠ እንዲሰቃዩ እያደረገ

ያለው አረመኔው ኢሳየስ (የወያኔ ጭካኔ አንሶን) እኛን እንዲያሰቃይ ኢትዮጵያዊያኖችን ረግጠህ አንድትግዛ አኔ አግዝሃለሁ ብሎ ከላይ ያያችሁትን ልመናውን አቅርቦለት አንደነበር አይተናል

ዳዊት የረሳቸው ወታደሮች የሐረር ወርቅ ጋሻው ኤርትራ ድረስ ሄዳ እምባቸውን አብሳለች እመባቸው ሲያቀርሩ አብራ አምባዋን አፍስሳለች። ታሪከ ለባለታሪኩ!
 
እንዲህ ያለ እንደ እነ ዳዊት የመሳሰሉ የወታደር አዛዦች ወታደሮቻችን ከጠላት ጋር ሲዋጉ ከበስተጀርባ ከውስጥ እና ከላይ ሆነው ምን ሴራ ይጎነጉኑ እንደነበር ከነ ዳዊት ማሕደር ማወቅ ችለናል። ዛሬ ደግሞ ሳያፍር ወደ አስመራ ሄዶ የኢትዮጵያ ወታደሮችን በመጨፍጨፉ አማራ የተባሉት ወታደራዊ ሙርከኮኞችን በልዩ ማሕደር እየተመዘገቡ ለስቃይ እንዲዳረጉ ያዘዘው ኢሳያስ አፈውርቅን ለማመስገን ወደ አስመራ እሄዳለሁ ሲል ነግሮናል። እንዲህ ሲል፦

I am quiet sure I will go to Asmara to extend this gratitude personally to the government of Eritrea and president Isayas personally”

ለምን? ብላችሁ ስትጠይቁ፤ የሚከተለው ምክንያት እራሱ ዳዊት ይነግራችል። እንዲህ ሲል፡

“I am grateful for that and the numerous encounters I had with them to advance the struggle for freedom justice equality in Ethiopia. At every point they have been extremely cooperative

የዳዊት የንቀት ደረጃ በመለኪያ የለውም። ሻዕቢያዎች ለራሳቸው ተከታዮች ፍትሕ፤እኩልት እና ነፃነት ሳያጎናጽፉኮሎኒያሊስትብለው ለሚጠርዋት አገር እና ወታደሮቿን ያሰቃዩ አረመኔ ሰው መሳይአራዊቶችለፍትሕ እና ለነፃነታችን ተቆርቋሪ ስለሆኑ ላመሰግናቸው ወደ አስመራ እሄዳለሁ እናንትም ለነፃነትና ለፍትሕ ያደረጉትን ትግል ሻዕቢያን አመስግኑ ሲልበመራራ ስድብሰድቦናል። የዚህ ሰው ሚዛን እስከዚያ ድረስ ይርቃል።
ከጉብኝቱ የምንጠብቀው ግን ምናልባት መለስ ዜናዊ አማራ ያልሆኑትን ሰብስቦ “አስመራ እና ከረን’ ድረስ ሄደው አማራ ለኤርትራ ሕዝብ ስቃይ ተጠያቂ ስለሆነ የአማራ ሕዝብ ወክሎን ይቅርታ እንድንጠይቅ መጥተናል፡ ብለው እንዳሉት ቅጥረኞች ዛሬም ‘አብይ ወደ አስመራ’ ሲሄድ አብረውት የሚሞሸሩት እነ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ  አስመራ ሄደው ያንን ይደግሙ ይሆን? ወይንስ የቀድሞ ወታደር ይቅርታ እንድጠይቅ ልኮኛል ብሎ “ለነፃነታችን፤ ላንድነታችን፤ ለፍትሕ እና ለዲሞክራሲ ላደረጋችሁልን ትብብር ”በወታደሩ ስም ይቅርታ ሊጠይቅ መጥቻለሁ” ሊል  ይሆን ወይንስ ሌላ ያልሰማነው አሳዛኝ የቅጥረኞች ልሳን ልንሰማ ይሆን?   
 
ይህ ሰው ለኢሳያስ ያለው ፍቅር የጀመረው የደርግ ባለሥልጣን ሆኖ እያለ ነው። አለቃው ኮ/ል መንግሥቱ ስለ ዳዊት ማንነት ሲገልጹ “የጠላት ቅጥረኛ ነው” ሲሉ ይኮኑኑታል። “አብዮታችንን  ክዶ ሲያበቃ በጎን  በግል ደብዳቤ ጽፎ እኔን ቢያሞግስም ክሕደቱና የውጭ ጠላቶች አገልጋይነቱን ይቅር የሚባል አይደለም።” ሲሉ ትክክለኛ ባሕሪው ገልጸውታል።
 
ይህ ካልኩኝ ዘንድ፤ “ሻለቃ ዳዊት ማን ነው? የሚለው፤ የሻለቃ ዳዊት እውነተኛ ገጸ ባሕሪ ካሁን በፊት በሰነድ ታሪክ ደጋግሞ ካልተናገሩ እየተረሳ ስለሚሄድ ዛሬም አስታውሳችለሁ። አብይ እነ ዳዊትን ይአስመራ መሄድ ይችላል። እኛ ደግሞ የሻዕቢያ እና የውስጥ አርበኞቹን ገበና ለታሪክ ማስመዝገብ እንቀጥላለን።
 
ነብሳቸው ይማር ሟቹ በሻለቃ ጌታቸው የሮም የተጻፈ አገር እና ሠራዊት ፍረጅ ኢትዮጵያ” ስለ ዳዊት ምን ብለው ነበር? እንከታተል።
 
በደርግ ዘመን፤ ሻለቃ ዳዊት ወታደሮቹን ከከዳ በላ ተመልሶ ከሻዕቢያ እና ከውጭ ሓይላት ተመሳጥሮ በሱዳን በኩል አድርጎ፤ ከኤርትራ ቡድኖች ጋር አየተነጋገረ፤ ኤርትራ በረሃ ናቅፋ  ድረስ ምስጢር ሲለዋወጥ(ሃይልና እልክ የማይጠቀሙ መሪ እያለ ሲያሞግሳቸው የነበሩትን መሪውን ከሥልጣን ለመፈንቀል፤ ወታደሩን ለማዳከም “ዱለታና….የመሳሰሉ” ለማካሄድ) እንደነበረና፤ በጉዞውም አንዳንድ ሙርኮኛ ወታደሮች አግኝቶ ሲያነጋግር፤ ከአንደበቱ ሲወረወር የነበረው  ርሕራሄ ያልተላበሰ መልስ ሲሰጣቸው እንደነበረ የተለያዩ ሰነዶች አንብበናል። ስለ ሻለቃው በአገር ካሃዲነት ማንነቱን በመጽሐፍ መልክ ተጽፎለታል። ከነዚህ መጽሐፍቶች አንዱ  “አገርና ሠራዊት-ፍረጅ ኢትዮጵያ” የተሸኘ በሻለቃ ጌታቸው የሮም የተጻፈ እውነተኛ የሰነድ ክምችት ነው። 

የኢትዮጵያ ወታደሮች በሻለቃ ዳዊት ላይ የሰላ ሂስ ሲያሰሙ፤ ተቃዋሚ ጋዜጠኞች ስለ እነዚህ ከፍተኛ የደረግ ባለሥልጣኖች ምን እያሉ እና ምንስ እየሸጡልን እንደከረሙ ዛሬም የሚያስተናግድዋቸው የፖለቲካ አሻሻጭነታቸው ቀጥለውበታል? አብይን እያመሰገኑ ዛሬም ወንበሩን ለመጋራት የቋመጡ ብዙ ናቸው። ዳዊት አንዱ ነው። አብይ ለኤርትራ ሽማግሌ አንዱ አድርጎ ሊሾመው የችል ይሆናል።ያም ሆኖ ስለ ዳዊት የተዘገቡ እውነተኛ ታሪካዊ ሰነዶችን እንመልከት”።

ሻለቃ ጌታቸው የሮም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ በ1983 ዓ.ም ሓምሌ 26 (የቀኑ ትክለኛነት በግለጽ ሰለማይታየኝ ምናልበት 26 ተብሎ ይነበብ) “ከደርግ መንግሥት ምሰጢራዊ ጉዳዮች” በሚል ታትሞ ለሕዝብ ይፋ የወጣው ሰነድ ዋቢ በማድረግ ያሳተሙት ሰነድ፤ ሻለቃ ጌታቸው የሮም ፤ ሻለቃ ዳዊት ውለደጊዮርጊስ ደርግን ከድቻለሁ ብሎ እውጭ አገር እንደቀረ ወደ አለቃው ወደ ኮለኔል መንግሥቱ ሃይለማርያም (ወደ ኢትዮጵያ) በራሱ የእጅ ጹሑፉ የጻፈውን ምስጢራዊ የግል ደብዳቤ ከመመልከታችን በፊት፤ በመግቢያው ላይ ሻለቃ ጌታቸው የሮም ስለዚህ ደብዳቤና ስለ ሻለቃ ዳዊት ያለቸውን ግምገማ ያሉትን እንመልከት።

“አገሪቱንና ሕዝቦቿን በግለኛ አገዛዝ የማሰነው የደርግ መንግሥት የዚህ ዓይነት የአፋና ተግባር ሲያካሂድና ሲመራበት የቆየ የደህንነት ተቋም፤ አለው። ይህ የደህንነት ተቋም የአፈና ሥራውን እንዴት እንደሚካሄድ የሚታይ ቢሆንም፤ለዛሬው ግን በጓዳው ውስጥ ካጠራቀማቸው ሰነዶች፤ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ኢትዮጵዮጵያን ጥሎ፤ከኮበለለ በሗላ ለመንግሥቱ ሃይለማርያም የጻፈውን ደብዳቤ እናቀርባለን።

ሻለቃ ዳዊት የኰበለ ሰሞን፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብት ምን ያህል እንደታገለ በየጊዜው መድረክ በተከፈተለት በአሜሪካን ድምፅ ራዲዮ ጣቢያ የአማርኛ ክፍል ብዙ ተናግሯል። በሗላም ሬድ ቲርስ (Red Tears) ወይም ቀይ እንባ በተባለው መጽሐፉ መንግሥቱን አብጠልጥሎ ለመውቀስ የማይፈራ ደፋርና ቁርጠኛ የኢትዮጵያና የሕዝብ ልጅ እንደሆነ ለማሳየት ተጣጥሯል። የደርግ ምሰጢራዊ ጓዳዎችስ ምን ይላሉ? ሻለቃ ደዊት ከተሰደደ በሗላ ወኔ እንደነበረው ያመላክቱ ይሆን?
በምድረ ኢትዮጵያ እያለሁ በምንግሥቱ ፊትም ሳይቀር የልቤን ለመናገር ደፍረቱ ነበረኝ ይል እንደነበረው፤በስደት እያለስ መንግሥቱን እውነተኛ ማንነቱ ይገልጸው ይሆን? ሻለቃ ዳዊት- ለሻለቃ መንግሥቱ ወይስ ለሰፊው ሕዝብ ተቆርቋሪነት አንደነበረው ያሳዩ ይሆን? መልሱን በራሱ በሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ የእጅ ጽሑፍ ከተጻፈው የራሱ ደብዳቤ እናግኘው።” ይላሉ።

ሻለቃ ዳዊት በራሱ ጽሑፍ ይህ ከታጭ የሚታየው ቅጅ ‘ሁለተኛው የደብዳቤ መልዕክት ጽሑፋ ነው’። ተከታታይ ደብዳቤ እንደሚልክላቸውም ደብዳቤው ላይ ጠቅሰዋል። የሻለቃ ዳዊት የእጅ ጽሑፍ ሰነድ ቅጅ/ኮፒ፤(ኮፒ ስካን) ያደረግኩላችሁን ከማንበባችሁ በፊት ጹሑፉ እጅግ ሰፊ ትንተና ያያዘ ሲሆን ባጭሩ ሻለቃው ለኮለኔሉ የሚሉት ይህንን ነው፡

ከገጽ 114 ልጥቀስ “ለኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት አመራር ከእርስዎ ሌላ አማራጭ የለውም ብየ እኔ አምናለሁ።”

 “የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃላፊነቱ የሰጠው ለርስዎ ነው።” (ገጽ 115)

 ለትንሹም ለትልቁም ነገር የእርስዎ መመሪያ በሚጠበቅበት ሁኔታ፤የእርስዎ ፈገግታ፤እየርሰዎ አዎንታ ለማግኘት ብዙ ፍትግያ ይታያል። ከነዚህ ሁሉ ሃላፊነት ሥልጣን ሽሚያ ውስጥ የሌሉ እርስዎ ብቻ ነዎት። የእርስዎ መሰረት Power one-ሕዝብ ነው። አሁን አካባቢዎ ያሉ ሃላፊዎች ግን….’BASE’ በሌላ አነጋገር የሕይወታቸው፤የሕልውናቸው ወይንም የሥልጣናቸው መጀመሪያም መጨረሻም- እርሰዎ ነዎት።…የእርስዎ ልብ ለማሸነፍ ይቀጥፋሉ፤ይዋሻሉ..”(115-116)፤
ስለ ኤርትራ ጉዳይ ደግሞ እንዲህ ይላሉ፡
 
“ታዲያ ኩራታችን ይዘን ልንቀመጥ? በድህነት፤በጦርነት በዘወትር ሥጋት እንኑር ወይንስ አዲሱ ዓለም-ውስጥ ገብተን ዐለም የሚጫወተውን የፖለቲካ ጨዋታ እየተጫወትን ለማሸነፍ ለማግኘት እንሞክር? (116)
 
ከላይ አገላለጻቸው ሻለቃው ምን ለማለት እንደፈለጉ ግልጽ ነው።ዛሬም ለተገንጣይ አረብ ደላላዎች ጥብቅናቸው እንደቀጠለ ነው። ዞሮ ዞሮ፤ ኢሳያስ ተገንጥሎም የዓረቦች ፔትሮ ዶላር እየተርከፈከፈበት ጨዋታውን በሕዝብቻን ላይ እየተጫወተ አንደሆነ ለሁላችሁም ግልጽ ይመስለኛል። ወያኔ ዓለም የሚጫወተውን ጫዋታ እንጫወት ብሎ ኤርትራን አስገንጥሎ ባሕራችንን አስዘግቶ ለዓረቦች ተሰጠ። ተከብበን አንገኛለን! ዓለም የሚጫወተው የግሎባላይዘሸን ፕሮፓጋንዳ አስራጮች እነ ሻለቃ ዳዊት እና፤ እነ ካሳ ከበደ ዓለም እየተጫወተው ያለው “አዲሱ” ጫዋታ እንቀጥልበት እያሉን ነው። ሚዲያቸውም ያው ኢሳት ነው። እየተለፈፈብን ያለውም ያው እዚያው ነው።
 
 ኩራት ወይንም ውርደት! አዲሱ የዓልም ጨዋታ! የፖለቲካ ወይስ የወታደራዊ መፍትሔ የሚለው የሻለቃው ጥያቄ እውነት ያስቃል።ደርግን የጣለው በወታደራዊ መፍትሔ ስለሄደ ሳይሆን ኤርትራ ልትገነጠል የበቃችው፤ “የብዙ ምክንያቶች ክምችት ነው” (መንግሥቱ የመጀመሪያው ተጠያቂ ቢሆኑም) አብረው በዙርያ ሥልጣን እና በወታደራዊ፤በስለላ መዋቅር የነበሩ ባለሥልጣኖች በተገንጣዮች የቤት ሥራ የተ-ተበተቡ ቅጠረኞች ፤አገራዊ ፍቅር የጎደላቸው ካሃዲዎች ስለነበሩ ነው። በዚያው የአሜሪካኖች የስለላ መዋቅር ተንሰራፍቶ ደርግ  እጉያውና ማንቁርቱ ውስጥ  ገብተው ምን ይሰሩ እንደነበርና ለተገንጣዮች የስላላ እና የወታደራዊ ዕርዳታ ሳተላይት እና ራዲዮ እርዳታ ያደረግ እንደነበር አይዘነጋም። ለዚህ ማስረጃ እነ ደረጀ ደሬሳ፤ እነ ክፍሌ ወዳጆ ከአሜሪከን ገንዘብ አየተቀበሉ ፤ በአንዱት ሴት አሜሪካዊት መሪነትና አማካሪነት ሱዳን ውስጥ ምን ይሸረብ እንደነበረ ሻለቃው የሚያውቁት ምናልባትም እጃቸው የጨመሩበት “ ዓለም ሲጫወተው የነበረው አዲሱ የዓለም ጨዋታ” ምን ይመስል እንደነበር ሻለቃው ሱዳን ኤርትራ ሲመላላሱ የሚያውቁት ጉዳይ ነው። ኤርትራ በዚህ መልክ ነበር የሄደቺው፤ወያኔም በዚህ ሽራባ ነው የገባው፤ ደርግ በግራም በቀኝም በራሱም እንደ አበደ ውሻ እራሱ እየነከሰ ለውድቀት ደርሷል። ግልጽ ግልጹን!
እንቀጥል፤
 
በገጽ 118 ላይ ሃይሉ ይመኑ በተባሉ የደርግ ባለሥልጣን ላይ ሻለቃው ለመንግሥቱ ሃይለማርያም ምን ብሎ እንደጻፉላቸው ስትገነዘቡ፤ ሰው የገዛ ለጓዱና ለዜጋው ሞት እና ግርፋት እንዴት እንደሚመኝለት ታያላችሁ። ሻለቃው እራሱ በካቢኔው ውስጥም ሆነ በመሪው ፊት እና በባለሥልጣናት ስብሳባ ወቅት ለመናገር ድፍረቱ ያጣ የራሱን ሃሞት ሳይገመግም የትግል ጓዱ በነበሩት በሃይሉ ይመኑ ላይ “ድፍርት ለምን እንዳልኖራቸው ለኰለኔሉ ደብዳቤ ጽፏል”
 
በገጽ 119ም እንደ እነ ጀኔራል ሃይለጊዮርጊስ ወርቅነህን ያረጁ ያፈጁ የሚያሾፉ መኮንንኖችን ትዕግስት ማድረግና መሸከምዎ አግባብ አይደለም ሲል ለኮለኔሉ ምክር ሰጥቷል። ለእርሰዎ threat የማይሆኑ ሰዎች ከሆኑ መምረጡ ትከክል ነው…. በጀኔራልነት ማዕረግ ያሉትን ያረጁ ያፈጁ እያለ ሲወርፏቸው፤ በሻለቃው ዕድሜ ክልል ያሉ መኮንኖች ግን ሲያብራሩ ማባረርን ተገቢ እንዳልሆነ እና “መሰሪ” የሚላቸው ሰዎች እየተሾሙ ለኮለኔሉ ታማኝ የሆኑትን ሰዎች ማራቅ ተገቢ አይደለም’ ሲሉ ሻለቃው ኮለኔሉን ይመክራል። “ለእርስዎ threat የማይሆኑ ሰዎች ከሆኑ መምረጡ ትከክል ነው….” ይላል (እግዚኦ መሃረነ ክርስቶስቶስ!) (118-119)
 
በዛው በገጽ 119 ደግሞ በእልህና በሃይል የማያምኑ መሪ ነዎት፡ በማለት ኮለኔሉን ያሞግሳል። “ብዙ መሪዎች ራሳቸው ላቋቋሙት ሥርዓት መውደቂያ የሚያዘገጁት፤ የራሰቸው ዕቅድ ትክክል ነው ብለው በማመን የሕዝብን ግን ባለማመዛዘንና የሕዝብን ድምፅ ባለመመልከት በእልህና በሃይል ለማሳየት ሲሞክሩ ነው። እርስዎ እንዲህ አንዳይደሉ ይሰማኛል።”
 
ጓድ ሊቀመንበር!
 
እኔ ተንፍሻለሁኝ። በቅንነት የጻፍኩትን እርስዎን አስቆጥቼ እንደሆነ ግን በጣም ነው የማዝነው። እርስዎን የረዳሁኝ መስሎኝ ነው በቅንነት ያቀረብኩት። በዚህ ምልክ ይቀበሉኝ… ሌላ ምንም ምክንያት የለኝም። ለወደፊት በዝርዝር ስለምጽፍለዎ ይህ መግቢያ ይሆናል ብዬ አምናለሁ። (119)
አብዮቱን በቅን ያገለገሉ፤ ለአብዮቱና ለአመራሩ ፍጹም ታማኝ የሆኑ ሰዎች ከእርስዎ እየራቁ መሄዳቸው ያሳስበኛል።

ለአብዮቱና ለእርስዎ ሁልጊዜ ታዛዥ ወንድምዎ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ።
 
*- ለእርስዎ ብቻ የተላከ የግል ደብዳቤ ነው፡

*በጓድ ተስፋዬ ወ/ሥላሴ በኩል ስለተላከ እንደሚደርስዎት አርግጠኛ ነኝ።
 
ሲል በሰፊው የጻፈውን ሰፊ የግል ደብዳቤ ለማንበብ እነሆ ከዚህ በታች ያለውን ቅጅ/ፎቶ ኮፒ አንብቡ:: በተረፈ ሻለቃው ሊቀመንበር መንግስቱ “ሃይልና እልህ” የማይጠቀሙ ናቸው በማለት ባቆለባበሳቸው አመራር ሥር የተካሄደው በዜጎች ላይ የመብትና የጭካኔ እርምጃ ለማወቅ ስለ ደርግ የተጻፉት መጻሕፍቶች እና የታሪክ ሰነዶችን ያንብቡ። ከታች ያሉትን የሻለቃው የእጅ ጽሑፍ ደብዳቤ ያንብቡ እነሆ፦
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ
(የኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ) (Ethiopian Semay)