Saturday, October 25, 2008

ብርሃነ መስቀልን ዝለፉት ዋለልኝ ግን አትዝለፉ ብሎብርሃነ መስቀልን ዝለፉት ዋለልኝ ግን አትዝለፉ
ብሎየፈቀደላችሁ ፍርድ ቤት ብታመለክቱን!? ጌታቸዉ ረዳ ብዙ ጊዜ የታዘብኩትና ያስገረሙኝ ነገሮች ሁሉም እንኳ ባይሆኑ አንዳንድ የተማሩ፤በትግል የተፈተኑ የሚባሉት ፊዉዳሎችን ታግለናል የሚሉን ሰዎች፡ከታገሉዋቸዉ መሳፍንትና ጉልተኞች ባልተሻለ ወገንተኝነት ሲያንጸባርቁ ስመለከት እስከ ዕንጥላቸዉ የሞሉትን ዕዉቀት እየፈሰሰ ሊናገሩት የፈለጉትን ቀና ነገር እያኮላተፋቸዉም ይሁን ወይንም ቋንቁኛዉ ባልገባኝ ነገር መስተንክር እየሆኑ ሲመጡብኝ “አንታ ዝዘበን እንታይ ዘበኑ?” (አናንተየ፤ይሄ ዘመን ምን ከሚባለዉ ዘመን ደረስነዉ?) በል ያሰኘኛል።
ባለፈዉ ወር ፍካሬ የተባለዉ የኢሕአፓ መጽሄት- ዋለልኝ መኮንን- ን አስመልክቶ በእኔ የሚዘጋጅ “የኢትዮጵያን ሰማይ” የሕዋ ሰሌዳን ያለ ምክንያት ጣራዉን በከዘራዉ ወደ ላይ ቀስሮ ለመኮርኮር ቃጥቶት “በማዕለሽ አለፍኩት።ሳልፈዉ ግን፤ አንድ ነገር ልበል፡ ኢትየጵያ ሰማይ የግለሰዎች ወይንም ድርጅቶች “ቀጭን ትዛዝ” ተቀባይ ወይንም አክባሪ አንዳልሆነ ይታወቅ።
ቀጥሎ ሰሞኑ ደግሞ ዋለልኝን አትንኩ! ያትዉልድ እና ዋለልኝን ለቀቅ! የሚል ጽሁፍ ደግሞ ተለጥፏል። እኔ የገርመኝ ያ ትዉልድ የሚባለዉ ማንን ያካተተ ነበር? በያትዉልድ ጊዜ እነሱ ብቻ ተገረፉ?ቆሰሉ?ሞቱ፤ታረዙ?ተጋዙ? ሌሎቻችን ግን አልታሰርንም?አልተደበደብንም? ስለ ሕዝብ በመድረክ እና በመንግሥት ፊት ለፊት አለተጋፈጥንም?፤ አልታረዝንም?-አልተታኮስንም?-አልተጋዝንም?፤አልተሰቃየንም?፤አልተሰደብንም?-አሳረችን አላየንም-ቤተሰቦባችን አልተበተኑብንም? አልተገደሉብንም? ተማሪው እና የገበሬዉ ብሎም ሰራተኛዉ አይዞህ አላልንም?ወታደሩን በቁርጥ ቀን ከጎኑ አልቆምንም? ስለሱ ኣልጮህንም? በዛ ሁሉ ትዕይንት እንዳልነበርን ተመስሎ የሚቀርብ ትዕቢት በጣም ይደንቀኛል።
እኛም እኮ የዛ የ ያትዉልድ ዘመን ልጆች ነን። የክብር መዳልያ ሽልማት ቢኖር እኮ ሽልማቱ ለነሱ ብቻ አድርገዉ እኛኑን እከክ እንደ ፈጃት ላም ቆጥረዉ ከማዕረጉ ያስቀሩን ነበር ማለት ነዉ። ደግነቱ ሽልማት እና ዕደገት ያለመኖሩ ገላገለን። ለዚህ ለዚህ እማ ወያኔ ከዚህ የተለየ ምን አደረገ? ወያኔ እኮ አትንኵኝ በኔ ዘንድ እሸት እሸቱን እንጂ የተከልኩትን መርዘማ እሾሄን አታርሙ፤ አታንሱት፤በኔ ዘንድ ብጹዕነት እንጂ አመኬላነት አላስተማርኩም ስለሚለን ነዉ። ታድያ በዚህ መልክ ከተኬደ የፖለቲካ ምጥቀት እንዴት ሊከሰት ይችላል? ዉይይት፤በታሪክ መከራከር፡ እርማት፤ ነቀፌታ፤ በ ያትዉልድ መጥፎ ጎኑ መተቸት ለምን አያስፈልግም? ። እኔ የገርመኝ ያ ትዉልድ የሚባለዉ ማንን ያካተተ ነበር?
ዋለልኝን ስለነቀፍን የተሰጠን በጣም ያስገረመኝ ትችት ልጥቀስ፦“የለየላቸዉ አድሃሪዎች እየመሩና የቀይ ሽብር አራማጆች አጀብ ሆነዉ ዘመነ ትምክህት ናፋቂዎች ሁሉ ድነገት አዋጅና የክተት ትዛዝ የመጣባቸዉ ይመስል ለለዉጥ በታገለዉ ትዉልድ ላይ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፍተዋል።በዚህ መሰረት ሕይወቱ ለሃገሩ እና ላላማዉ ሰጥቶ ያለፈዉን ዋለልኝን በተለይ መዝለፍ አብዝተዋል።በ ዋለልኝ ሽፋን የአንድ ጊዜዉ የተማሪዎች እና ተራማጆች እንቅስቃሴ በአድሃሪዎች እየተወነጀለ እና እየተጠቃ ነዉ።” …..ይል እና ዋለልኝንም ሆነ ተራማጅ የሚባል ክፍል የነቀፈ ሁሉ “አድሃሪ፤የቀይ፡ሽብር ወንጀለኞች፤ የአፄዉ ዘመን የስልጣን ተካፋዮች፤ትግሉ ሲካሄድ በቦታዉ ያልነበሩ ወ ይንም አድሃሪ ሚና የነበራቸዉ…ወዘተ ይለናል። ወቸዉ ጉድ!
በመሰረቱ ተቺዉ እና ሌሎቹ በብርሃነ መስቀል ረዳ ሌት ተቀን ሲዘምቱ አንድም ሰዉ ከእኔ ጀምሮ ትንፍሽ አላልንም። ለምን? ምክንያቱም ብርሃነ መስቀልን የምንከላከልለት ነጥብ ታጥቶ ተዛላፊዎቹ ድንግሎች ስለሆኑብን ሆነዉ ሳይሆን ወቃሾቹ የመዉቀስ መብታቸዉ ነዉና ተለቀቁ። (ልቅ ሄዱ ልበለዉ!?)። ብርሃነ መስቀልን የሚያሞግሱት ጽሁፎች እና ስራዎች (ግንፍል በህሬነቱን የሚያጎሉለትንም በተጻራሪ “ካሪዝማቲክ-በህሪ እንደነበረዉ የመሰከሩለት ጸሃፍት)” ባህሪዉ እና መስዋእትነቱን በተጻራሪ ማቅረብ ይቻል ነበር። ሆኖም የትግል ጓዶቹ ነበሩና የመዝለፍ መብታቸዉ አስከ ዛሬ ተጠብቆ ነበር። ብርሃነ መስቀልን ሲዘልፉ (አስኪ ሰለቸን) በቃችሁ ሳይባሉ ዛሬ ደርሰዉ ዋለልኝን በታሪክ ማሕደር በአምዳችሁ ነካካችሁብን ብለዉ ዋለልኝን የተቸ ሁሉ “ነብሰ ገዳዮች፤አፄዎች፤ሃሁ ያልቆጠሩ፤በቦታዉ ያልነበሩ፤ ኢሕአፓን ሊያጠቁ የተነሱ………..ወዘተ” ሲሉን እንዴ? ወዴት ወዴት ነዉ ነገሩ!
ዋለልኝ በሕይወት የለምና፤ራሱን መከላከል በማይችልበት ጊዜ ስለሱ ስራዎች ማንሳት ነዉር ነዉ ሲሉ ተከራክረዉናል።አንዳንዱም በአካል መጥተዉ ይህንኑ ቃል ለኔ ደግመዉልኛል።እኔ ደግሞ የምለዉ- አዋጅ የመጣ የክተት ትዛዝ የተላለፈ ይመስል በብረሃነ መስቀል ላይ የዘለፉ ዘመቻ አልቦ ዕረፍት አለ አዋጅ ሲዘለፍ፤ “በሕይወት ስላለ ራሱን መከላከል የሚችል መስላቸዉ ኖሯል ልበል? ይሄ ወገንተኝነት ነዉ ወይስ ምንድነዉ? ብርሃነ መስቀልን የመዝለፍ ተገቢነቱ ዋለልኝን ግን አትንኩት ብሎ የፈቀደላችሁ ፍርድ ቤት የትኛዉ ነዉ? ብታመለክቱን!?
ዘለፋዉና ወቀሳዉ በዋለልኝ ሲደርስ ሕጋዊነት የሚያጣ በብርሃነ መስቀል ላይ ግን ሕጋዊነት ሚላበስበት መበት ማን ነዉ የሰጣችሁ? ይሄማ የትገርኛዉ ምሳሌ “ሳዕሪ አጉዶ ብማይ ዓብያስ ማይ ከይአቱ ትካለኸል” (የጎጆ ሳር በዉሃ አድጋ ዉሃ እንዳይገባ ትከላከላለች” እንደሚባለዉ ነገር ብርሃነ መስቀል ኮትኩቶ ባሳደገዉ ኢሕአፓ ሲዘለፍ፤ ሳሯም ዉሃን ጠጥታ ዉሃን አለስገባም የምትለዉ ዓይነቱ እኮ ሆነ ነገሩ። እኛ ብርሃነም ይሁን ዋለልኝን በታሪክ ማሕደራቸዉ እኩል ፍርድ ሚዛን እንጂ በወገንተኝነት ወይንም በግል ጸብ ወይንም ዝምድና፤ ትዉዉቅ፤ ደም አጥንት፤አዉራጃ፤ ጎጥ ፖለቲካ፤ ሐረግ ዉስብስብ ዉስጥ ገብተን አይደለም የሚዛን መነጽራችን የሚመዝናቸዉ። ሁሉም በሚመሰላቸዉ ታግለዋል፤፡ በታገሉበት ማሕደር ደግሞ ዘለፋም፤ስድብም፤ ዉግዘትም ምሬትም ወቀሳም እንደየስራቸዉ ይከተላቸዋል። እነሱ ሞተዋል፤ ታሪካቸዉ አልሞተም።
ስለዚህም ታሪካቸዉ አስካለ ድረስ አስካነሳነዉ እና አስካስታወስናቸዉ ድረስ በመጥፎም በደጉም ይነሳሉ።በእኛዉ ትዉልድ ካልተነሱ “ሞተዋል የምንልበት ጊዜ” ሳናነሳቸዉ ከቀሩ በሗለ ነዉ የሚሞቱት። የቀብራቸዉ ግብአተ መሬት የመጨረሻዋ ምስማር ተመታች ማለት ነዉ። ያ ሲሆን አዲስዩ ትዉልድም ማን መሆናቸዉ ሳያዉቅ ይቀርና; የ ያኔ ትዉልድ ታሪክ ታሪክም አብሮ ያኔ ያከትማል።ያ እንዳይሆን በእኛም በእናንተም የምናቀዉ እና ያነበብናቸዉ ታሪኮቻቸዉ እያነሳን አለፍ አለፍ እያልን መመራመሩ ማዉሳቱ ተገቢ ነዉ። ያ ስላልን “ሳንገድል አንበሳ ገድለናል እና ጎፈሬያችነን እዩልን አላልንም። ገዳዮች፤ታዛዦች..ሃሁ ቆጣሪዎች..ወዘተ” ሆነንም አይደለም።የስደቡ ናዳ ሳያስፈልገን በላያችን ላይ ማንዣበቡ ባልንባቸዉ ትችቶች የተሰደብነዉን ስድብ የሚያስሰድበን አይመስለኝም።
ዋለልኝ የኦነግ የወያኔ የተገንጣዮች አቀንቃኝ መምህራቸዉ ነዉ የሚለዉ አቋማችን አሁንም ያዉ ነዉ።ተሳስቶ አሳስቶናል ነዉ አቋማችን። አሁንም በሱ ብዕርና ድጋም የሚደግሙ ወያኔዎችና ተገንጣዮች መከራከራችን አልቀረም።ለመሆኑ ዋለልኝ ማን ነበር? በሚገባ ወንድማችን አቶ ዜግ ፋንታ ገልጾታልና ያንኑ አልደግምም።ይህ አቀራረብ የዋለልኝን ማንነት ትዉልድ ዕደገት ወዘተ..አይደልም። ባጠቃላይ ግን ዋለልኝ እና በዋለልኝ ዙርያ የነበሩ ፖለቲካ አማካሪዎቹን ይፈትሻል። ጀብሃ በ1958 ተመሰረተ ወይንስ በ1960 ተመሰረተ? የሚል ጥያቄዎች እንካ ስላንትያ የትምርት ጨዋታ ዉስጥ አልገባምና በ1958 ተመሰረተ በ1960 ተመሰረተ ዋለልኝ እና በዋለልኝ ዙርያ የነበሩ ሰዎች ከመገምገም ሊያግደን አይችልም።

በዋለልኝ ዙርያ የነበሩ ኤርትራዊያን ጃንደረባዎቹ አብዛኛዎቹ “ህዝባዊ ሓይልታት (ቡድን 2) ተብሎ የሚታወቀዉ የኢሳያስ ተከታዮችና ተዋጊዎች ነበሩ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ስንት ጊዜ የአይሮፕላን ጠለፋ ሙከራ እንደተደረገ እና አብዛናዎቹ በጠለፋዉ ዉስጥ የተሳታፉት እነማን እንደነበሩ ታሪኩን ሚያዉቁት ሊግልጹልን የፓልቶክ አዘጋጆች አፈላልገዉ ቢጋብዙልን እና እንድንማርበት ቢደርጉ ለመጠቆም አወዳለሁ። በተረፈ በእኔ በኩል ያዘጋጀሁላችሁን አነስተኛ ማሕደር አቀርባለሁ ከዛ ዋለልኝ ማነዉ ማን ነበር ሚለዉ የናንተ ግምገማ አስገቡና በዛ እንቀጥል።

ከዚያ በፊት ግን “ተራማጅ” የሚባል ቃል እያስቸገረኝ ስለመጣ እሱን ልነካካ። ተራማጅ ምን ማለት ነዉ? እኔ አልመልሰዉም። ተራማጆቹ ይንገሩንና እንከራከር። የአገሪቷ ሕዝቦች እንዲገነጣጠሉ ሌሊናዊ ቅስቀሳ/ኮሚኒስታዊ ቅስቀሳ ማሰራጨት ማስተማር በአዋጅ ማጽደቅ ወንጀል እንጂ አፍራሽ አንጂ ተራማጅ አይደልም እላለሁ። ያ ትዉልድ የሚባለዉ ወይንም የምንባለዉ የሰራናቸዉ ስራዎች ሁሉ ድንግል/ታቦት ሆኖ አይነካካ ማለት ተራማጅነት አይመስለኝም? ያ ትዉልድ የሚባለዉስ ስንቱ ነዉ ንጹህ ተራማጅ (የተራማጅ ትርጉሙ ከተራማጆቹ ብንጠብቅም)? መሬቱ ላይ የፈሰሰ ደም ሁሉ ደሙ ስለፈሰሰ ንጹህ ነዉ? ተራማጅ ነዉ? በዛ ያ ትዉልድ የተሰለፈ ሁሉ ንፁህ ነዉ? ተራማጅ ነዉ?
ላስፋዉ መሰለኝ። ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይ ተራማጅ ነበሩ እየተባለ ይነገራል። ተጽፏል።

አንዳንዶቻችን ንጉሡን ደግ ስራ ስናነሳ ጀኔራል መንግሥቱን የገደሉ እገሌን እንዲህ ያደረጉ ይላሉ። ማለታቸዉ መብታቸዉ ነዉ። ያልገባኝ ነገር ግን “ጀነራል መንግሥቱ ንዋይ ንጉሡን ለመገልበጥ ሲሉ በርካታ ሚኒስትሮች እና መኳንንት እና ልዑላን በአንድ ቤት በአንድ ጣራ በአንድ ወለል ዉስጥ አስገብተዉ ረሽነዋል”” ይህ ወንጀል አንጂ፤ ይህ ነብሰ መግደል እንጂ ይህ ሰብአዊ መብት መግፈፍ አንጂ ፤ይህ አምባገነንነት እና ደመ ፍሉነት አንጂ፤ የተራማጅ ባህሪ ሊሆን በፍጹም አይችልም (መራመድ በጥሩ መልኩ ብንተረጉመዉ ማለቴ ነዉ)። መራመድ -ዕድገት ነዉ፤ግስጋሴ ነዉ፤ ወደ ፊት መምጠቅ ማለት ነዉ። ታድያ 15 ስቱን ባለስልታኖች ሲረሽኑ “ተያዝ-አልያዝም” በቶክስ ልዉዉጥ ሳይሆን የገደሉዋቸዉ ትዕዛዝ አስተላልፈዉ ራሳቸዉን በግድያዉ ተሳትፊ ሆነዉ በተካፈሉበት “የጅምላ ግድያ” በምን መልኩ መገስገስን አድገትን ተራማጅነትን ያሳያል? አነዚያ ጀኔራሎች ኮሎኔሎች እንያ ተራማጅ የተባለላቸዉ መፈንቅለ መንግሥት አካሃጆቹና ተካፋዮቹ የ ያ ትዉልዶች አከላት አይደሉምን?

ኮሎኔል መንግሥቱ ሃይለማርያም 57 (?) ሚኒስትሮች፤መኳንንት እና ልዑላን ራሶች ወዘተ… በአንድ ክፍል በአንድ ወለል ግድግዳ ላይ አስጠግተዉ ፈጁዋቸዉ። የኮለኔሉ እና የጀኔራሉ ስራ ወታደራዊ ኩዴታ/የመንግስት ግልበጣ ነዉ። በሰዉ ሕይወት ላይ የጅምላ ግድያ ፈጽመዋል። ኮለኔሉ እና ጀነራሉ የሚለያቸዉ ኮሎኔሉ በዕድሜ ኖረዉ ብዙ ሕይወት እና አገር አጠፉ ፡ጀኔራሉ ግን ዕድሜ ሳያገኙ በጥቂት ደቂቃዎች ጊዜ 15 (በርካታ) ሕይወት ቀጭተዉ አሳቸዉም ዕደሜ ሳያገኙ ለሞት ስለተዳረጉ ብቻ ነዉ፡፤
ታድያ ይሄ ተራማጅነት ነዉ? ሌላዉን “የብሄር ብረሰብ መብት አስከ መገንጠል” የሚለዉ እና እራሱ “ብሄር” የሚለዉ ባገራችን የማይታወቀዉን በዛሬ ትርጉሙ አፍራሽ እና መዘዘኛ መሆኑን እንጂ ዲሞክራሲያዊነት ወይንም ተራማጅነት እንደሌለዉ በክፍል ሁለት በሌላ አርእሰት ስለማቀርበዉ እርሱን ትተን፡አሁን ወደ ተራማጁ ወደ ዋለልኝና በዙርያዉ ከነበሩ ኤርትራዊያን ጃንደረቦቹ ጋር እናምራ።ዋለልኝ በወንድማችን በአቶ ዜግ ፋንታ በሰፊዉ እንደተብራራዉ የወሎ ሰዉ መሆኑን አንብባችሗል።ዋለልኝ ተራማጅ ከሚባሉት የ ያኔዉ ተማሪዎች አንዱ ነበር። ንቁ ተማሪ ይሁን እንጂ እያጥላሉ ከሚሰድቡት ካሪዘማቲኩ ብርሃነ መስቀል ረዳ መድረክ ይዞ ለመናገር ሲሞክር እንደ ዓእዋፍ ሰማይ ወደ አሱ ሲበርሩ የነበሩ ታመሪዎችን አያክልም። ያ ተፈጥሮ የለገሰዉ ብርታቱ ተናጋሪነቱ እና የተማሪ ቤት ንቁነቱ ማንም ሊነጥቀዉ እንደማይችል፤ ዛሮም ያንኑ ተፈጥሮዉ የነጠቀዉ ተነጋሪና ንቁ የለም የሚሉ ጸሃፍት አሉ። አኔም አስማመለሁ ። ምናልባት የትግራዩ (በወያኔ እና በደርግ ካድሬዎች መሃል ተገደለ የሚባል -ለኔ ግን ዓባይ ፀሃየ እንደነገረኝ ወያኔ እርምጃዉን እንደወሰደችበት ነዉ የነገረኝ) ገዳዩ ያልታወቀ “አብርሃ ፓትሪስ” (አብርሃ በርሀ) ካልሆነ ሌላ ብርሃነ መስቀልን የሚያስከነዳ ፍጡር ያለ አይመስለኝም (መስክር ብባል ግን የንግግሩ ፍሬ ነገር ትተህ በፈጣን ተነጋሪነቱ ተምቤን እና መቀሌ ያደገዉ የዓድዋዉ ተወለጅ “አብርሃ ፓትሪስ” (“ፓትሪስ መቐለ” ወላጅ አባቱ እንደሚጠሩት)ከብርሃነ መስቀል በእጅጉ ማራኪ ድምጽና እጥፍ መስህብ እንደነበረዉ አዉቃለሁ። በነገራችን ላይ “ተሐህት”ን “የመንደር አይጥ” ብሎ የሰየማት አብርሀ ፓትሪስ ነበር። ከዚያ በሗላ ገደሉት። ዋለልኝ እንደ ብርሃነ መስቀል አንደ መለስ (በደርግ የተረሸነዉ መለስ) ከኤርትራ ተማሪዎች ዙርያ መልከስከሱን አልታጣዉም።

ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በጣም የዋሃን (በራቸዉ መዝጋት የማያዉቁ) ስለሆኑ፤ በተንኮል የተካኑ አብዛኛዎቹ የኤርትራ ተማሪዎች ይሄነን ስለሚያዉቁ የግንጠላዉ ጉንጎናቸዉ ለማካሄድ እንዲያመቻቸዉ (በወቅቱ ግቢዉ አስከ 600 ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ም ጨምሮ ያስተምር ነበር) አራት አልጋ በ አንድ ክፍል ካለ አራቱንም ክፍል በታቻለ መጠን ሁሉም ኤርትራዊያኖች በአንድ አንዲሆኑ አንዱን የዋህ ኢትዮጵያዊ እማሃላቸዉ ከነበረ፤ መኝታ ክፍሉን አንዲለዉጡት ይለምኑትና ሁሉም ተሰባስበዉ ከበረሃ የሚላከዉን ዜና “ጥሕሻ” (bully, bulldozer, trace passer-ናደዉ) በተባለዉ ቡድንና መጽሄት የግንጠላ ሴራቸዉ ያራምዱ ነበር። ልብ ልትሉት ምፈልገዉ ነገር ዩኒቨርሲቲዉ ዉስጥ ሲማሩ የነበሩ ኤርትራዊያን ተማሪዎች ግቢዉን ጥለዉ በ1965 በፈረንጆች አቆጣጠር ወደ ሜዳ /በረሃ በመሄድ የግንጠላ ዉግያ ያካሂዱ ስለነበር የበረሃ ግንኘነታቸዉ ከዛ ጊዜ ጀምሮ አንደነበር የራሳቸዉ መሕደር ይመሰክራል።
እስከ ‘ዚህ ድረስ መሰረቱ ሥር እንደነበረዉ ካወቃችሁ አሁን እነ ዋለልኝ እና መሰሎቻቸዉ “በተራማጅነት”-የአገራቸዉን ህልዉና ከግንጠላ ሃይሎች ጋር በማቆራኘት “የግንኙነቱ ዘር በመዝራት”-ለፕሮፖጋንዳቸዉ መጠቀምያ እንዳደረጉዋቸዉ አንመለከታልን።ዋለልኝ የገዛ አገሩን አምርሮ ይቃወማት ነበር።

እርሱ አማራ ሆኖ ኢትዮጵያን የአመሮች ነች! ኢትዮጵያዊ ለመሆን መታወቂያዉ ያማራ ስም መያዝ ነዉ፤ካልሆነ ዜግነትህ አይከበርም፤ አይታወቅልህም እያለ የሚነዛዉ ጸረ-ኢትዮጵያ ዉዥምብር ፕሮፖጋንዳዉና ያማራ ጥላቻዉ ከኤርትራዊያን ተጨምቆ ወደ እሱ ተላልፎ እንደ ራሱ ቅባት ሲጠቀምበት የነበረበት ጸረ አትዮጵያ አፍራሽ ነት (አሱ ፌክ-አትዮጵያ ይላታል የገዛ አገሩን) መረን የለቀቀ ነበር። ምንም አንኳ ፈረንጂኛ ችሎታዉ የደመቀ ቢሆንም በአስተሳሰቡ ግን እኛ ትግሬዎች “ተርባብ “ የምንለዉ ፈረንጁ “ዱዋርፍ/ሚጂት- ነበር። ይህ እንዲሆን ያስገደደዉ ደግሞ ከኤርትራዊያኖቹ ያላሰለሰ ምስጢራዊ ረዥም ጓደኝነት ከነዚህ የዋህ “ተራማጆች” ጋር ስለተቆራኙ እና “የአጠባዉ” ሥራ በመካሄዱ ነዉ። የእነ ሌኒን የእነ ማኦ እና ስታሊኖች የራስን በራስ አስከመገንጠል የሚባለዉ ስንኝ (ሆሆያት ልበለዉ?) የረዢሙ የህሊና ያጠባ ሥራ በመካሄዱ ነዉ። በዛ ትምርት አልታጠበ የለም ይመስለኛል፡ ነገር ግን ታጥበናል እና አጣቢቡንና አመንጪዉን አትዉቀሱ ፤አታንሱ! ማለት ስህተት ነዉ። ወያኔ ሲያሳስተን ለምን አሳሳትከን ብላችሁ አትዉቀሱት እንደማለት እኮ ነዉ።ዋለልኝና የወያኔ ስነ ሃሳብ/ቲኦሪ ለየብቻ ናቸዉ እንዳትሉን ብቻ!@
አዎን-ኤርትራኖች በወቅቱ ሁለት የሽብር ዉግያዎች በኢትዮጵያ ላይ አዉጀዉ ነበር። በምድር የቦምብ ቀበራ፤ በሰማይ ደግሞ የአይሮፕላን ጠለፋ_። በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ እኔ ባነበብኳቸዉ ታሪኮች የተመዘገቡ 3 (በገንጣዮችና ከገንጣዮች ጋር ግንኙነት የመሰረቱ ጠላፊዎች ጠለፋ ተካሂዷል) ጠለፋዎችና እና በርከት ያሉ የከተማ ቦምብ ጠመዳዎች በኤርትራ ተግንጣይ ቡድኖች ያጠቃለለ ነበር ።
የምደሩ የሽብር ጥቃት ማለት በእግር እየገቡ የቦምብ ፍንዳታዎች ለማካሄድ የተላኩ “ፈዳይን” የሚሏቸዉ የሽብር ቡድኖችን ወደ አገሪቱ እየላኩ ጥቃት ለመፈጸም የተሞከረዉን እንመለከት ።ለምሳሌ የሚከተለዉ መረጃ ያገኘሁት ከ1959 ዓም ጀምሮ ጀብሃን ያገለገለ፤ በፈዳይን ስራዎች፤በዓረብ አገሮች በዉጭ ጉዳይ ሃለፊነት አስከ 1983 ድረስ ከጀብሃ ጋር ቆይቶ በ1991 ወደ ሻዕቢያ በመቀላቀል በሚኒሰትርነት እና በ ኢሚግረሽን ጉዳዮች በሃለፊነት እየሰራ ከሻዕቢያ ጋር የሚገኝ ከፍተኛ ባለስልጣን ባሳተመዉ የመጀመሪያዉ የግሉ የገድሉ ታሪክ አምና አሥመራ በገበያ ዉሎ የተዘገበ ጠቃሚ ዶክዩመንት ዉስጥ ነዉ። ሰዉየዉ በጀብሃ የገዳሪፍ ጽ/ቤት ሃለፊ ስለነበር በስራዉ ላይ ተሳታፊነት ስለነበረዉ የገለጸዉን ነዉ።

ወቅቱ በጋ 1968 በፈረንጅ የጀብሃ አመራር አርስ በርስ የተዳከመበት ጊዜ ስለነበር ፈዳይን ወደ ኢትኦጵያ አዲስ አበባ በመለክ የ“አለሁኝ አልሞትኩም” ዮፕሮፖጋንዳ ጥቃት እና ተቀሜታ ለማግኘት ሁለት ታጋዮች መሓመድ ዑመር ሃቢብ (ወዲ ሓቢብ) እና ገብራአብ ዓንደብርሃን (ወዲ ዓንደ) የተባሉት ታጋዮች ኡዚ መሳሪያዎች ቦምቦች እና ጥይቶች በመያዝ ከገዳሪፍ ተነስተዉ በደማዚን አድርገዉ በኮሮኮን በኩል አልፈዉ ወደ አሶሳ ከተማ ሲገቡ በኢትዮ ጵያ ጸጥታ ሃይሎች ተይዘዉ እያንዳንዱ 17 ተፈርዶባቸዉ 17 ዓመት ታስረዉ መሓመድ ዑመር ሓቢብ እስራቱን ፈጽሞ ሲለቀቅ ገብራአብ ግን እስረ ቤት ዉስጥ ታስሮበት ከነበረዉ ክፍል ሞቶ ተገኘ። ይህ አንቅስቃሴ ሲካሄድ ወንድሞቻችን “ተራማጅ ኤርትራዊያን ሃይሎች” በሚሏቸዉ ተማሪዎች ዘንድ በ “ጥሒሻ” ቡድን ይታወቅ ነበር።
ይህ የተቀነባበረ ሴራ በ አገሪቷ ላይ ሲፈጸም ተራማጅ የሚባሉት የያኔዉ ትዉልድ ዲሞክራቶች እነ ዋለልኝ ስለ ኤርትራ ፍትሃዊነት በሕሊናቸዉ ሲያምጡና በስታሊን ትኩሳት ሲነድዱ ኢትዮያ ግን “የአማራዎች አገር!ፌክ ኢትዮጵያ” “የሚኒሊክ የሃይለስላሴ የፈጠራ ስራ” እያሉ እየቦተለኩ ተጨማሪ በሽታ እና ብሄራዊ ዉጋት ይሆኑ ነበር። ዓረቦቹ ያነን የነ ዋለልኝን ቡትልክና አሳምረዉ ያደምቁት ነበር። እነ ዋለልኝ አንድም ቀን ለ ዓረቦቹ ያስረዱት ጽሁፍም ሆነ ያሳዩት መከላከል የለም።
እንቀጥል!፦
አትዮጵያን ለማጥቃት ከአዲስ አበባ ዉጭ አየር መንገዶቿን ኢለማ በማስገባት በወቅቱ በፍራንክፈርት በሚላኖ እና በካራቺ እንዲከናወን እና የ ኤርትራ ትግል በመላ ዓለም ለማስተዋወቅ ከሚል መርሆ የታቀደ እንደሆነ መዛግበቱ ያስረዳሉ።እነ ዋለልኝም ይህንኑ አይጠፋቸዉም።ፓኪስታን -ካራቺ ዉስጥ የተካሄደዉ ጠለፋ እኔ ያቀረብኩት በጦቢያ መጽሄት “ኤርትራ ያመጸኞች የነዉጠኞች የእሪታ፤የሽምብረተኞች ምድር”በሚል አዲስ አበባ ታትሞ በመላ ዓለም የተሰራጨዉ ዶኩሜንታሪ ጽሁፌን ያንብቡ (የእትሙን ቅጽና ጊዜ በትክክል አላስተዉሰዉም)።ስለ የካራቺዉ የጠለፋዉ_ታሪክ፡-
በትንሹ የተከናወነዉን በጨረፍታ ላስታዉሳችሁ።በጋ 1969 በፈረንጆች አቆጣጠር ከላይ የታቀደዉ ጸረ ኢትዮጵያ ሽብር ለማካሄድ ታች አምና በሞት ከተለየዉ የያኔዉ ጀብሃ የሗላ ሗላ የሻዕቢያ የዉጭ ጉዳይ የነበረ ብዙ ሰዉ በመግደልና በመሰወር የሚከሰሰዉ የኮማነዶዉ የጸጥታዉ ክፍል ሃላፊ የነበረዉ ሲሞት ጊዜ የወያኔዉ ስብሐት ነጋ እንባዉ ያፈሰሰለትን ለቀብሩ የሃዝን ደብዳቤ መግለጫ ወደ አሥመራ በመላክ ከላይ ከምታዩዋቸዉ 4ቱ ህንዶች/ፓኪስታኖች ተመስለዉ ከሚታዩት ፎቶግራፋቸዉ፡ አንዱ በ“ዓሊ ሰይድ ዓበደላ” መሪነት ካራቺ ከተማ የኛዋን አየር መንገድ ለማቃጠል ከተላኩት ዓሊ ሰይድ ዓብደላ፤ፍስሃ አብራሃ (ካራቺ)፤ መሓመድ እድሪስ የተባሉ የጀብሃ ኮማንዶ ተዋጊዎች አይሮፕላናችን ካራቺ ከተማ እንዳረፈች ዉስጥ ገብተዉ ከጸጥታ ሃይሎቹ ጋር ተታኩሰዉ ቦምብ በመወርውር ካቃጠሉዋት በሗላ (ዓሊ ሰይድ በፀረ-ጠለፋ መንግሰታዊ ሃይላት በቡጢ ተመትቶ ወድቆ ሕሊናዉ ስቶ በነበረበት የሰከንዶች ወቅት ኢትዮጵያን ወክለዉ የተቀጠሩ ትግርኛ ተናጋሪ ሆስቴሶች “ኣጆዃ!!! ኣጆዃ!!! (በርታ አይዞህ!! አይዞህ!! በማለት የኮማንዶ ቡጢ ባደነዘዘዉ ራስ- ቅሉ ላይ ቀዝቃዛ ዉሃ በማፍሰስ ያበረታቱኝ ሆስቴሶች አልረሳዉም ብሎ ዓሊ ሰይድ በቃለ መጠይቁ አረጋግጧል) በወቅቱ በቶክስ ልዉውጡ በፓኪሰታን ፖሊስ ተይዘዉ እያንዳንደቸዉ 14 ዓመት ጽኑ እስራት ሲፈረድባቸዉ ኢትዮጵያ ወደ እኔ ይተላለፉ በማለቷ የቻይና መንግሥት ስትደግፍ ዓረቦች በሙሉ ግን አይሆንም ከማለት አልፈዉ፤ በብዙ ሺህ ዶላር ጠበቃ ከዉጭ ቀጥረዉላቸዉ በፍርድ ቤት ተካራክረዉላቸዋል። መጨረሻ ግን 11 ወር ከታሰሩ በሗላ በወቅቱ የፓኪስታን የጠቅላይ ሚኒሰቴሩ ልጅ የነበረችዉ የፓኪስታኗ ወጣሁ ወጣሁ! ባይዋ ሴትዮ “ወ/ሮ በናዚር ቡቶ” በወቅቱ የተማሪዎች ንቅናቄ አመራር ስለነበረች፤ 12 እራሷ ሆና የ72 ሰዓት የራሃብ አድማ በማድረግ ልጃችን ከምትሞትብን ይለቀቁ ተብሎ ከ14 ዓመቱ ቅጣት 11 ወራቸዉ ብቻ ታስረዉ “ሰላም አሊኩም! /“አሊበደርቺ!” ሙያቸዉ ፈጽመዉ በኛዉ ላይ አክታቸዉን “ትፍ” ብለዉብን ወደ ግድያ ጫካቸዉ በሰላም እንዲሰናበቱ ተደርጓል።
ይህ ሲደረግ፤ ተራማጆቹ እነ ዋለልኝም ሆኑ ሌሎቹ ተራማጆች አነ የ ያትዉልዶች (ፈርጦች) ይህ ታሪክ ያወቃሉ፤ያነብባሉ፡ ቢቢሲ እና ዶቾቤሌ ራዲዮን ያዳምጣሉ። ለይግረም ግን ፤ትስስሩ ከነሱ ጋር ይበልጥ እየጠነከረ፤ ወደ ዓረቡ ዓለም እነሱም ማምራት እንደጀመሩ ይታወሳል። ኢትዮጵያ “ፌክ” ነች ! የምኒሊክ “ባምቡላ”-የሃይሌ፤የሸሜዉ፡ በአማሮች ድሪቶ ተደርታ የተጠጋገነች ፤“ፌክ”-የዉሸት ስራ ዉጤት እያሉ አገራቸዉን ታሪካቸዉን ራሳቸዉ ሲያግማሙ፡ ባንጻሩ ግን እነ በናዚር ቡቶ የራሃብ አድማ አድርገዉ ተገንጣዮቹ በተራ ወንጀል መከሰስ የለባቸዉም፡ የሃይማኖት ታጋዮቻችን ናቸዉ፡አስላሞች ናቸዉ፤ “ኢትዮጵአያ ምትባል “፡ፌክ” ጨቁናቸዋለች እና ይለቀቁ ብላ የራሃብ አድማ ስታደርግ የና ተራማጆች ግን ለኢትዮጵያ የጻፉላት “ፕሬስክሪፕሽን” ዲሞክራሲ ሚባል ፈዉስ ሆኖ ምጥ ተይዞ ዲሞክራሲ ሚወለደዉም “ግንጠላ”-የሚባል በ‘ዛርቲ/በደቂ ሕድርትና’-(በኤሊያን ፎርስ) የተሰራ ፈዉስ የመሰነጣጠቂያ የተሳለ ጩቤ ነበር የሳሉላት። ያኔ የተሳለዉ ጩቤ ዛሬም አልጎተመም፡ ስራዉን በዋለልኝ ዘመቻ እየተቀላጠፈ እያየነዉ ነዉ።
ወደ ዚህኛዉ ወዳ ‘ዲስ አበባዉ ጠለፋ እናቅና፡ በወቅቱ የተመዘገቡ ይፋ የሆኑ ጠለፋዎች 3 (ሦስት) ጊዜ ተከናዉነዋል። አንዱ እኔ ከነበርኩበት ከተማ ያርፋል ተብሎ ፕሮግራም የተያዘበት በረራ ነዉ። ካልተሳሳትኩ የመጀመሪያዉ ጠለፋ ብርሃነ መስቀል እና ወንድማችን እያሱ ዓለማዮህ የነበረበት ከአዲስ አበባ ወደ ካረቱም ቤሳ-ቢሲቲን ሳይከፍሉ “በነጻ ቲኬት” የተሳፈሩበት ብሎም ወደ አልጄሪያ የተሸጋገሩበት የጠለፋዉ ትዕይንት ነዉ።

ሌላዉ ሁለተኛዉ ጠለፋ ወደ ሊቢያ እንዲጓዝ ተገዶ- በ አማኑኤል ዮሃንስ የተጠለፈዉ ነዉ። ሦስተኛዉ እና የመጨረሻዉ ህጋዊ ስሙ “አማኑኤል ዮሃንስ” የተባለዉ በተለያየ የዉሸት /መሸፈኛ ስም ሲጠቀም የነበረዉ በሜዳ/የፈረስ ስሙ “ራዲዮ” ተብሎ የሚታወቅ፤ ትምርቱን የመዲሲን /ምዲካል ተምርቱን አቋርጦ ወደ ህዝባዊ ሓይሊታት በመቀላቀል፤ የህዝባዊ ሓይሊታት ተዋጊ አባል የነበረ። ወደ ሊቢያ በተካሄደዉ ጠለፋ ተሳታፊ ኖሮ እንደገና ለሁለተኛ ጊዜ ከገረግር -ሱዳን በረሃ የአይሮፕላን ጠለፋ ለማካሄድ ታዝዞ፤ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ በመሄድ በንግድ ሥራ እየተሰማራ የሚኖር በማስመሰል ዋለልኝን በፍቅር ያኖሆለለችዉን መልከመልካምዋ “ፍያሚታ-ጊላይ” በማርታ መብራህቱን በኩል ዋለልኝን ለጠለፋዉ ስራ እንዲስማማ እና ጃንደረባዎቹም እንዲቀላቃሏቸዉ በማድረግ የተገንጣዮቹን የጠለፋ ስራ ለ ኤርትራዊያኖች ጥቅምና ተጨማሪ ሃይል እንዲሆኑ አድርጓል።ጠለፋዉ ሲካሄድ ጠላፊዎቹ እነማን እና ለምን አላማ እነደነበር ተገንጣዮቹ ባስተላለፉት የራዲዮ መልዕክት በወቅቱ ተገልጿል። አማኑኤል ዮሃንስ ለማን እየተጋለ እንደነበር ማን እንደላከዉ ከዛ በፊት በሊብያዉ የጠለፋ ተልእኮ የተሳተፈ መሆኑን በጠለፋ ስራ መሰማራቱን ዋለልኝ በሚገባ ያዉቃል።ሃሎ!!!!ኵሩሩር!!!!
እንደተባለዉ የሶሻል/የፖለቲካል ሳይንስ ተማሪ ሆኖ ያን መሳይ ጽሁፍ እየጻፈ አንዴት ይሄን ምስጢር ሊደበቀዉ ይችላል? (በሌላ ሃይል ተግፈቶ ነበር የሚጽፈዉ ሲባል- የለም-ገፊ አልነበረዉም-“ሊቅ ነዉ” የምንትስ ምንትስ 4ኛ ኣመት ተማሪ ሆኖ አንዴት ይህን ትንተና ያጣዋል ስለተባልን ነዉ ጥያቄዉን ለመጠየቅ የተገደድነዉ)።

በጠለፋዉ ወቅት የተሰማሩት 3 ኤርትራዊያኖች እና 4 ኢትዮጵአዊያን ነበሩ።ማርታ መብራህቱ፤ አማኑኤል ዮሃንስ ( “ራድዮ”) እና ዮሃንስ ፍቓዱ። በዚህ በኩል ደገሞ ዋለልኝ መኮንን፤ጌታቸዉ ሃብቴ ፤ተስፋየ ቢረጋ፤ታደለች ኪዳነ ማርያም። ነበሩ። (ከደጅም ከዉስጥም ሁኔታዉን የሚያስተካክሉ እና የሚቆጣጠሩ ለጊዜዉ ታሪክ ያላቀረባቸዉም አንደነበሩ ጥርጥር የለዉም)። በ3ቱም ዙሮች የተካፈሉ ኤርትራዊያን ስም ዝርዝር አንደሚከተለዉ ናቸዉ።አማኑኤል ዮሃንስ (በሁለተኛዉና በሦስተኛዉ ዙር ጠለፋ ከነ ዋለልኝ የተሳተፈዉ ነዉ)ደበሳይ ገብረስላሴሙሴ ተስፋሚካኤልዮሃንስ ስብሃቱሙሴ ተስፋሚካኤል (አይሮፕላናችንን ጠልፈዉ ሊቢያ የገቡ ናቸዉ)።ዮሃንስ ስብሃቱ እና ሙሴ ተስፋሚካኤል በ1973 (ፈረንጅ) በተነሳዉ የዉስጥ አመጽ/እንቅስቃሴ (መንካዕ- ተብሎ የሚታወቀዉ የኢሳያስ የአፈና አርምጃ እነደተገደሉ ይታመናል።)

የዋለልኝ የጠለፋ ጓደኛ አማኑኤል ዮሃንስን የእጅ ቦምብ እና ሽጉጥ አሥመራ ድረስ ሄደዉ በማምጣት በጠለፋዉ ዝግጅት እጅ ነበራቸዉ የሚባሉት አንዴ በአሲምባ ፓልቶክ ቀርበዉ የነበሩት ደ/ር መስፍን አርአያ እንደሚታሙ አንዳንድ ማህደሮች ያማሉ። በዚህ ጉዳይ የፓልቶክ አዘጋጆች ስለጠቅላላ ሁኔታዉ የሚያዉቁት ካለ ተጋብዛዉ ቢያስተምሩን ማለፍያ ነበር። እያለኩ “ዋለልኝን አትንኩት፤ ብርሃነ መስቀልን ግን ዝለፉት ያለችሁ ፍርድ ቤት ካለ እኛም መብታችን ያለ ተቃዉሞ ለማስከበርና ዋለልኝን ለመዉቀስ ያመቸን ዘንድ ብትጠቁሙን ምስጋናችን የላቀ ነዉ። አንባቢዎችን ለማስረዳት የምፈልገዉ_ ይህ ዉኢኢት አንጂ ጸብ አይደለም።ዉይይቱ ወንድማዊ እንጂ በእኛ እና በተማጓቾቻችን በኩል የቆሙት ወነድሞቻችን መሃል “ጸብ” እንደሌለን እና ዛሬም ትግላችን በጣምራ እንደምንቀጥል ላሳስብ እወዳለሁ። አምላክ-ኢትዮጵያን-ይጠብቅ።/--www.ethiopiansemay.blogspot.com