Sunday, May 30, 2021

ከፍል 2 የትግራይ ተዋጊ ሃይሎች የእርስ በርስ የመታኮስ አይቀሬ እጣ ፈንታ ትንበያ ጌታቸው ረዳ ኢትዮ ሰማይ (Ethio Semay) 5/30/2021

 

ከፍል 2

የትግራይ ተዋጊ ሃይሎች የእርስ በርስ የመታኮስ አይቀሬ እጣ ፈንታ ትንበያ

ጌታቸው ረዳ

ኢትዮ ሰማይ (Ethio Semay)

5/30/2021



ይህ ሓተታ ባለፈው ጽሑፌ ማለትም በ5/29/21 ከጻፍኩት ክፍል 1 የቀጠለ ክፍል 2 ነው። እንደሚታወቀው የዛሬው “ህ.ወ.ሓ.ት” ተዋጊ ድርጅት ድሮ በየካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም ደደቢት ተብሎ በሚታወቀው በምዕራባዊ ትግራይ ውስጥ የሚገኘው በረሃማ ሥፍራ “ተ.ሓ.ህ.ት.” (ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ) በሚል ሥያሜ ተሰይሞ ወደ በረሃ መውጣቱን በታሪክ የተዘገበ ነው። ለማታውቁ ወጣቶች መስራቾቹን ለማሳወቅ ያክል ባጭሩ ልጥቀስ። በየካቲት 11 ቀን ወደ ጫካ የወጡት ሰዎች ስም ዝርዝር፤

በቅንፍ የተዘገበው ስም የበረሃ መጠሪያ ስማቸው ነው።

(1)-ኣረጋዊ በርሀ (በሪሁ በርሀ)

(2-ገሰሰው አየለ ድሮ በቀዳማዊ ሃይረለስላሴ ዘመን የፓርላማ አባል የነበሩ- የበረሃ ስም (ስሑል ኣየለ)

(3) ሙሉጌታ ሓጎስ (ኣስፈሃ ሓጎስ)

(4) አረፋይነ ካሕሳይ (ፀሓየ ካሕሳይ)

 (5)-ፋንታሁን ዘርኣፅዮን (ግደይ ዘርኣፅዮን)

 (6)-ንጉስ ታየ (ቀለበት ታየ)

 (7)-ኣምባየ መስፍን (ስዩም መስፍን)

(8)-ዘርኡ ገሰሰ (ኣጋአዚ ገሰሰ)

 ከነዚህ ሌሎች ተማሪዎች ያልሆኑ መንገድና ስንቅ ለማገዝ ይረዳሉ ተብለው የታሰቡ አብረው የተሰለፉት የሚከተሉት አንድ ትግሬ እና ሁለት አማራ ገበሬዎች/ነጋዴዎች አብረው ወደ ጫካው በመሄድ የመሰረቱ ። እነሱም

(9)-ወ/ሚካል ገ/ስላሴ (አስገደ ገብረስላሴ ትግሬ ትውልድ ቦታ ሽሬ- ሥራ እስራል የሰለጠ ወታደራዊ ኮማንዶ ጦርሰራዊት)

(10)-ኣምባየ ወ/ጊዮርጊስ (ዘውግ “አማራ”

(11)- ኣብተው ታከለ (ዘውግ -ዛሬማ በሚባል አካባቢ የተወለደ “አማራ”)

 

እነዚህ 11 ሰዎች ናቸው።

 

እነዚህ 11 ሰዎች ወደ ጫካ ደደቢት ሲሄዱ ታጥቀዋቸው የሄዱት መሳሪያዎችና ባለቤቶቹ፡

የግደይ ዘርኣጽዮን ወላጅ አባት ጠመንጃ የነበረ “ጓንዴ” ጠመንጃ። የገሰሰው አየለ “ካርባይን; ቶምሰን እና ፍሎቨር ሽጉጥ”። የአስገደ ገብረስላሴ “አልቤን ጠመንጃ እና “ብጻይ (ጓድ) “ደሳለኝ” ተብሎ በወያኔዎች የተሰየመ ወደል “ስናር አህያ”። እነኚህ መሳሪያዎች ታጥቀው ትግሉን ጀምረው በትግራዋይነት አክራሪ ብሔረተኛነት ስሜት ወጠቱንና ገበሬዎን በማነሳሳት በሺዎቹ ታጋዮችን በማስሰለፍ መድፎች፤ዘመናዊ መሳሪያዎች፤አየር መቃወሚያ “ዙ” በመታጠቅ የመንግሥት ሥልጣንነትን መቆጣጠር ችለው ነበር።

 

ለ27 አመት ኢትዮጵያን ሲቆጣጠሩ “የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘር አንድ ያልሆነ፤ እርስ በርስ የማይተዋወቅ የነበረውን ሕዝብ እንዲተዋወቅ አደረግነው” በማለት የውሸት ትርክት በማናፈስ፤አገራችንን በቋንቋ በሃይማኖትና በወገንተኝነት ሸርሽረው “ትግሬዎች ሥልጣኑን በበላይነት እንዲመሩት አዋቅረው” የትግሬ የበላይነት በማንገሥ፤ የትግሬዎች መንግሥት መስርተው ነበር።

 

የወያኔ ባለሥልጣናት በነደፉት “ዘረኛ - ፖሊሲ” ዕልቂትና ጥላቻን አስፍነው ኢትዮጵያ ውስጥ “በደም የተነከረ አስተዳዳር” ከመሰረቱ በሗላ፤ ቀናቸው ደርሶ ከሥልጣን ተባርረው ዛሬ ከ29 አመት በሗላ እንደገና “ወደ ነበሩበት” የትግራይ ጫካ በመሸሽ ደቡባዊ እና መካካለኛ ትግራይ አካባቢ ብቻ ተደብቀው ከመንግሥት ጦር ጋር በመዋጋት ላይ ናቸው።

 

ተዋጊ ሰራዊታቸው በነዚህ አካባቢ ሊንቀሳቀስ የወሰኑበት ምክንያት ፡ ሽሬ እና አክሱም ገጠር አካባቢዎች ለኤርትራ ድምበር ቅርብ ስለሆነ በሁለቱም በኩል (በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ተዋጊ ወታደሮች) እንዳይከበቡ ስጋት ስላለባቸው እዛው ራያ እና እንደርታ አካባቢ ተደብቀው መንቀሳቀሱን መርጠዋል (ለጊዜው)። በተልይ የእንደርታ እና ራያ ሕዝብና ወጣት ከትጥቁ ዘመን ጀምሮ በተለይም መንግሥት ከሆኑ ወዲህ በነዚህ ሁለት አውራጃዎች (በከፊል ተምቤን) ውስጥ ከፍተኛ የብሔረተኛ ትምህርት እንዲሰርጽ በማድረግ፤ መንግሥታዊ መቀመጫውም “መቀሌ” በማድረግ በስልት  ፤ በዘፈን እና በትምህርት ቤት እና በገበሬ ማሕበራት፤ በህጻናት ሕሊና ውስጥ ሳይቀር “የትግሬ ሃያልነት” እና “የትግራይ ጥንታዊ አገርነት የውሸት ትርክት” በመቀስቀስ የኢትዮጵያዊነት ጥላቻ በሰፊው እንዲካሄድ በማድረጋቸው እነኚህ አካባቢዎች የሚናገሩዋቸው የትግርኛ ልሳኖች ሳይቀር ወደ “ኤርትርኛ እና ዓድዋ አክሱምኛ ልሳን” በመናገር በሚገርም ሁኔታ ከሌሎቹ አውራጃዎች የበለጠ ብሔተረተኛ እና ጠባብ እንዲሆን ስላደረጉት ለዚህ አዲስ ትግላቸው መከታ እንደሚሆናቸው ስላወቁ ወታደራዊ እና ምጣኔ ሃብታዊም ሆነ የስለላ እንቅስቃሴአቸው በነዚህ አካባቢ አውራጃዎች በማድረግ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ።

 

ወደ ትንታኔአችን ከመግባታችን በፊት ግን ለጊዜው እያደረጉት ያለው አንቅስቃሴ እንመልከት። (“ክርቢት”) (ፈዳያን) ሲባሉ የነበሩ እንደ ዱሮው ዓይነት “በቅርቡ የኮማንዶ ሥልጠና የወሰዱ አልሞ ተኳሽ ወጣት ወታደሮችን” ተወርዋሪ ነብሰገዳይ እና አፋኝ ቡድን እንዲሆን በማዘጋጀት ፤ ከአጋሜ (ዓዲግራት) በጥንት ዘመን አጠራር “ትግራይ” ሲባል ወደ ነበረው “አክሱም ዓድዋ እና ሽሬ” የሚያገናኘው አውራ መንገድ ላይ በሚጓዙ መኪኖች ላይ አደጋ በመጣል የትራንስፖርት/የመጓጓዣ/ ችግር እንዲኖር እና ህዝቡ በመንግሥት እንዲያምጽ ሙከራ እያደረጉ ነው። የኔ ዘመዶች ለስራ ወደ መቀሌ ተጉዘው፤ተመልሰው ወደ አክሱም ሊሄዱ ፈልገው መንገዱ ከተዘጋባቸው እጅግ ቆይቷል።  

 

የትግራይ ተዋጊ ሃይል ተብሎ በማቆላመጥ የሚጠራው የወያኔ “ሽብርተኛው” እና “አገር አፍራሽ ቡድን” ዋና ዓላማ የትግራይ ህይት “ክሪፕል” አድርጎ  የውጭ አገር ጣልቃ ገቦች እንዲገቡ ለማድረግ ነው። በሚገርም ሁኔታ፤ ምግብና መድሃኒት  ስለሌላቸው ፤ የገጠሬው ሕዝብ ኑሮ በችግር ላይ ስላለ፤ ለችግረኞች የሚጓጓዝ  የዕርዳታ እህል “በመዝረፍ” ለተዋጊ አባሎቻቸው” ቀለብ” እንዲያገኙ በማድረግ ላይም ናቸው።  

አብሮ ከዚህ ጋር እያካሄዱት ያለው ወታደራዊ እንቅስቃሴ፤ በተጨማሪ አዳዲሶቹ የከተማ ከንቲባዎች እና ወረዳ አስተዳዳሪዎች፤ እንዲሁም ወያኔን የሚቃወሙ ግለሰቦች በከተማ ውስጥ በድብቅ ከሚገናኙዋቸው የሰለጠኑ “ገዳዮች” እና ከበረሃ በሚላኩ “ፈዳያን” (ነብሰገዳዮች) ወደ ከተማ እና ገጠር አስገብተው ተፈላጊዎቻቸውን በመግደል ህዝቡ ሳይወድ በፈርሃት አዲሱን አስተዳዳር እንዳይደግፍ በማድረግ ድሮ ወያኔ ሲጠቀምበት የነበረው የግድያ ባሕሪው በስፋት በማካሄድ ላይ ይገኛል። በዚህም ብዙ ሰዎች ከሥልጣናቸው በፍርሃት እየተውት ይገኛሉ።

 

ወያኔዎች ለምን እንደገና ወደ ጫካ ወጡ?

 

መልሱ ከስብሓት ነጋ እናገኘዋለን። “ሥልጣናችንን ከተቀማን፤ የኢትዮጵያ አንድነት የሚባል አይኖርም፤ ሁላችንም ወደ እየመንደራችን እንበታተናለን ወይንም ወደ ሁለተኛ ዙር ጦርነት እንገባለን” (ስብሓት ነጋ ፡ - አባ መላ ከተባለ ውጭ አገር የሚኖር ድሮ የወያኔ አለቅላቂ የነበረ “ኢትዮ-ሲቪሊቲ ሩም” (ፓልቶክ ሩም) ያደረገለት ቃለመጠይቅ የተናገረውን ማስታወስ አስፈላጊ ነው። በዚህ መርህ ነበር ወያኔዎች ወደ ጫካ ሊወጡ የቻሉት እና ስብሓት ነጋም ቃሉን ባለማጠፍ ወደ ጫካ በመውረድ ተማርኮ ዛሬ ቃሊቲ ውስጥ ይገኛል።

 

የወያኔ ተዋጊዎች አሁን የሚገኙበት ቁመና

የወያኔ መሪዎች ወደ ጫካ ሊመለሱ የወሰኑበት ምክንያት ከላይ የተገለጸው ምክንያት ግልጽ ከሆነ፤ ወደ ሥልጣን ሲወጡ፤ ኢትዮጵያን እንደ አገራቸው ሳይሆን የተመለከትዋት “የምትታለብ ጥገት ላም” በማድረግ ትግራይን በልማት አሳድገው ድንገት ሥልጣናቸው ቢነጠቁ “የትግራይ አገርነት” ለመመስረት አቅደው እንደገቡም ልብ ማለት አስፈላጊ ነው። ይህንን እውን ለማድረግ የ27 አመት ሥልጣናቸውን ሽፋን አድርገው ትግራይ “ራስዋን የቻለች አገር በማስመሰል” ከውጭ  አገሮች፤ አምባሳደሮችና የሳይንስ፤ የጥበብ፤ እርሻ፤ የንግድ ኩባኒያ ባለቤቶችና ጠበብቶች ጋር በመገናኘት ልዩ ጠቀሜታዎችን በማስገኘት ትግራይ “የአፍሪካ የኢንዳስትሪያል ቀጠና” በማድረግ “አንድ አገር” ያገር የሚያሰኘውን “”ልዕለ ቅርጽ እና ታህታይ ቅርጽ” (ሱፕራ እና ኢንፍራ ስትራክቸር) በመገንባት ዝግጅት አድርገው ነበር።

 

ይህንን እውን ለማድረግ በተጨማሪ ትግራይ ስትገነጠል በተማረ እና በገንዘብ ሃይል ትግራይን ለመግንባት እንዲያመች በሺዎች ምናልባትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትግሬዎች ወደ መላው  ዓለም በሚገኙ የበለጸጉ አገሮች “በማሸጋጋር” በስደተኛ  ስም “ቪዛ” ተጠቅመው በቁጥጥራቸው ሥር በነበሩት ኤምባሲዎቻቸው በኩል እንዲወጡ በማድረግ የዲሎማሲ እና በገንዘብ ገልበት ትግራይንም ሆነ አሁን ያሉት ተዋጊዎችን እንዲያግዙ አቅደው ስለነበር፤ በዕቅዳቸው መሰረት ‘ይኼው ዛሬ’ ትግሬዎቹ ‘ውጭ አገር ሆነው’ ለግንጠላው እና ለተዋጊው ሃይል በዲፕለማሲ፤በአማራ ሕዝብ እና ንግድ ቤቶች እንዲሁም በኢትየጵያ ባህል እና ታሪክ ላይ ጥላሸት እና ጥላቻ ከማሰራጨት፤ አልፈው በገንዘብ፤ በልብስ፤በቀለብ፤በመድሃኒትና ለሴት ተዋጊዎቻቸው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በመላክ በታቀደው ዓላማ ተሰማርተው “ለመጻኢት ትግራይ” በማገዝ ላይ ይገኛሉ።

የተዋጊው ዓይነት

አሁን የሚገኙበት ቁመና ከመጀመሪ የፊት ለፊት ውግያ ኩፉኛ ስለተጠቁ፤ ከዚያ ፍጥጫ አፈግፍገው ወደ ሽምጥ ተዋጊ ስልት ገብተው እራሳቸውን ለማዳንም ሆነ አልፎ አልፎም በመንግሥት የተሾሙትን ግለሰቦች በመግደል ተሰማርተው ይገኛሉ። በአካልም ሆነ በሕሊና ያልጎለመሱ አዳዲስ “ተዋጊ ህጻናት” (ልብ በሉ ህጻናት ነው እያልክ ያለሁት) በስሜትም ይሁን አስገድደው ወደ ጫካ እንዲገቡ በማድረግ ክረምቱን ለክፉ ህይወት እየዳረግዋቸው ይገኛል።

 

በሚሰራጩ ቪዲዮዎች የሚታዩት ብዙዎቹ ተዋጊዎች የድሮ ተዋጊዎች፤ የኪነት ሰዎች፤ መምህራን፤ ተማሪዎች፤ የመንግሥት ሰራተኞች እና የወያኔ መንግሥት ወታደሮች/ፖሊሶች/ልዩ ሃይሎች ሲሆኑ፤ እንደ ድሮ የገበሬ ተዋጊ ሃይል እስካሁን ድረስ አልተቀላቀልዋቸውም።  ከከተማ ተጫምተዋቸው የሄዱበትን “ሰንደል” ነጠላ ጫማ፤ አፈር ያልነካቸው “ጂንስ ሱሪዎች” እና የጸዱ የከተማ ጃኬቶች ለብሰው “በስሜት ማነሳሻ” ሙዚቃ እየተቀሰቀሱ ባንዳንድ ክፍት በሆኑ በረሃዎችና ገጠሮች ውስጥ “ዳንኪራ” ሲጨፍሩ ይታያሉ። የታጠቁም ያልታጠቁ ሰዎችም ሲጓዙም ሲጨፍሩም አብረው ይታያሉ።

 

 ቀለባቸው ምን ይሆን? ለምትሉ ጠያቂዎች እነሆ “ነፃ ትግራይ” ከሚባለው ፓርቲ መሪ የሆነው “መሓሪ ዮሓንስ” ከተባለው እኔ “መሓሪ ዱቼ” በሚል ቅጽል ስም የምጠራው የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ መምህር የነበረ፤ ዛሬ በተዋጊው ስምሪት ውስጥ “ክፍሊ ህዝቢ” (ፓብሊክ ሪሌሽን- የሕዝብ ግንኙነት) በመባል የሚጠራው ክፍል ተመድቦ በመንቀሳቀስ ላይ ያለ ይህ ወጣት ባለፈው ሰሞን “አክሱማዊት ሚዲያ” ከተባለ የዩቱብ ሚዲያ ባደረገው ቃለ መጠይቅ “ተዋጊዎቹ ምን  ዓይነት ምግብ እና ማን እንደ ሚቀርብላቸው ተጠይቆ ሲመልስ፡ እንዲህ ይላል።

“አንዳንድ ልብሶች በግል ከቤተሰቦቻችን ይላኩልናል። ይህ ወደ ድርጅቱ ቢላክ ጥሩ ነበር፡ እኔ በግሌ አልደግፈውም። ሆኖም በቤተሰብ በኩል የሚላኩልን ምግቦችም ሆነ ልብሶች፤ጫማዎች አለፍ አለፍ ብለው ይኖራል። የምንመገበው ከተገኘች ያው ገበሬው ቁራሽ እንጀራ ከራሱ ቆርሶ ይሰጠናል፤ እርስዋን መመገብ ነው።ያቺን ካልተገኘች ደግሞ “ቆሎ” ቆልተን መብላት ነው። ከሚሰጠን የየግል የዴቄት ራሽን ተጠቅምን ብዙ ጊዜ “ቂጣ” በመጋገር እንመገባለን። እንደ ተዋጊነታችን መሰረት በየተራ ምግብ በማብሰል “ተረኛ መጋቢ” ሆነን ተራ ሲደርሰን በተመደብንበት ተዋጊ ጋንት/ ሃይል/ ያንን ሓላፊነት ወስደን ሰራዊቱን እንመግባለን።

 

ጠያቂው እንዲህ ሲል መሓሪን ኩፍኛ በማሾፍ “ያስሳቀው” ጥያቄ ይጠይቀዋል፡ እንዲህ ሲል

 “የሚጠጣ ውሃ ስትጠጡ ውሃውን አፍልታችሁ ነው? ወይስ እንዴት ነው የምትጠጡት?’

መሓሪ በጥያቄው ተገርሞ ጥልቅ የማሾፍ ሳቅ ይስቅበትና እንዲህ ሲል ይመልሳል፦

 

 “አፍልተን አንጠጣም ያገኘነውን ውሃ ነን የምንጠጣው። መጀመሪያ ወደ ጫካ ስወጣ በውሃ አለመስማማት የተነሳ እጅግ ከፍተኛ የጤና መታወክ ገጥሞች ከሞት ነው የተረፍኩት። አሁን ግን “ጃርዲያው፤አሜባው፤ የሆድ ህዋሳት ትሎች ሁሉም ለምደናቸዋል፤ እነሱም ለምደውናል። አይጎዱንም። ለምጀዋለሁ።

 

 “የምትትኙትስ የት ነው?”

አሁንም መሓሪ በጥያቄው ተገርሞ ይስቃል፡

“አይሮፕላን ስለምንፈራ ብዙውን ጊዜ ሌሊት ነው የምንቀሳቀሰው፤ ቀን በጣም ውሱን እንቅስቃሴ ነው። ረዢም ጉዞ የምንጓዘው ሌት ነው። በጋ ሲሆን በጣም ከምንወደው ሞቃታ በሆነው በገበሬዎች ጓሮ ውስጥ ባለው “ገለባ -ሳር” ነው የምንተኛው። ዛሬ ግን ክርምት ስለሆነ ዝናብ ሲዘንብ ደጅ መተኛት ስለማይቻል በየገበሬው ጎጆ ተጠልለን ነው የምንተኛው።

 

 “ሓራ መሬት *ነፃ መሬት አላችሁ)?

 

“ እስካሁን ድረስ ናጻ መሬት አልያዝንም። ተንቀሳቃሽ ሃይሎች ነን። አንዳንድ ጊዜ እናንተ የምታስተላልፍዋቸው ዜናዎች ጥንቃቄ (አከሮሲ) የጎደላቸው ሆነው ስለምታዛባቸው፤ እውነታው ጋር በሚሄድ ማስተላለፍ ይኖርባችሗል ብየ ወንድማዊ ትችት ለማስተላለፍ እፈልጋለሁ (ቅር ካላላችሁ) ። በማለት በውጭ አገር ባሉት የወያኔ ሚዲያዎች በሚነዙት መረን የለቀቀ ፕሮፓጋንዳ/ዜና/ ያልተደሰተበት እንደሆነ ስለ ሁኔታው ወጋ በማድረግ አሳስቦአቸዋል።   

 

አራቱ የፖለቲካ ድርጅቶች በረሃ ውስጥ ባንድነት የመታጨቁ የሗላ ሰበብ

 

የትግራይ ሕዝብ በተዋጊዎች ላይ ያለው ስሜት፤

የትግራይ እጣ ፈንታ፤

የታጋዮቹ ዕጣ ፈንታ፤    (አሁን በረሃ ላይ የወጡት 4ቱ ፓርቲዎች “ኦለድ ጋርድስ” ከሚባሉት  “ትግራይ ትግንጠል ብለው የሚያቀነቅኑት የውጭ ተላላኪ ባንዳዎች ናቸው” (ስብሓት ነጋ ከአንድ አመት በፊት ‘ከአውራ አምባ’ ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ) ከሚሉት ጋር የወደፊት ግጭት መነሻ እንደሚሆን በዝርዝር እንመከታለን።

የኤርትራ ዕጣ ፍንታ’    በዝርዝር እንመለከታለን።

 

 ባጭሩ ስለ ኤርትራ በሰፊው የምንመለከተው ቢሆንም ለጊዜው ይህን የመነጋገሪያ ጥቅስ የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነትም ሆነ የወያኔ ተዋጊዎች የትግራይ ትግርኚ ዓለማ ከ ኢሳያስ መወገድ/ሞት/ በሗላ ተዋጊዎቹ ‘ከኤርትራ’ ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት እንድትወያዩበት ይህንን መነጋገሪያ ሰብሓት ነጋ ከ6 አመት በፊት የተናገረውን ንግግሩን ልስጣችሁና በሚቀጥለው ክፍል 3 እንገናኝ።

“ስብሃት ነጋ እንዲህ ብሎ ነበር፦

 

 “የኤርትራ ሕዝብ ጤናማ ከሆነ ምስራቅ አፍሪካን ይለውጣል፤ይህ ሕዝብ ወደ ቀውስ ከገባ ግን እንደ ሶማሌ እና ደቡብ ሱዳን አካባቢ ሕዝብ አይደለም፡ አካባቢውን ያናውጣል። ድንገት ኢሳያስ ከሄደ በቀጥታ ኤርትራ ወደ ቀውስ ትገባለች። የኤርትራ መንግሥት ይወድቃል፡ በአገሪቱ ቀውስ ይፈጠራል። በርካታ የውጭ ሃይሎች እጃቸውን የሚያስገቡበት አደገኛ ቀውስ ስለሚኖር፤ ኢትዮጵያ ይህንን በጥናት በማረጋገጥ በኢሳያስ ወቅት እና ድሕረ ኢሳያስ ወቅት አደገኛ ችግር እንዳይፈጠር………” (ስብሓት ነጋ ሰኔ 3/2007 ለፓረቲው ካደረገው ንግግር ካገኘሁት ሰነድ)   

ክፍል 3 ይቀጥላል። (ተቀባበሉት- ሼር አድርጉት ፤ ሌላውን አስተምሩበት) አመሰግናለሁ ጌታቸው ረዳ - ኢትዮ ሰማይ (Ethio Semay)