የወንጀለኞች ጥምረት የወንጀል መሸፈኛ ስልት ነው
ጌታቸው ረዳ
Ethiopian Semay 9/28/26
በጸረ አማራ ሕዝብ እና በጸረ ኢትዮጵያ ተጣምረው የተከሰቱ 7 በወንጀል የተሳተፉ ፖለቲካዊ
(?) ድርጅቶች እንዲሁም 8ኛው ቡድን “አገሪቱን በአገርኛ-ቅኝ ገዢነት ከተሰየመው ቡድን” ጋር እየተፋጩት ያለው ጦርነትና ፍትግያ
ምክንያት “ሁሉም የወንጀል ተሳታፊዎች ሰለሆኑ” ከተጠያቂነት ለማምለጥ እያደረጉት ያለው ፍትግያ ነው። በፍትጊያው መሃል ላይ እንደ
ደሮ የሚያታልሉት እና የሚሞትላቸው ሕዝብ አለ።
ጥምረቱ በጥቂቶች በኛ ዘንድ ሳይታለም የተፈታ የወንጀለኞች ጥምረት ነው። ይህ የወንጀለኞች
ጥምረት እጅግ ስልታዊ በሆነ በነፃ አውጪነት ሥም የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ በዚህ ውስጥ የተለያዩ አካላት በሥራቸው በማሠለፍ እነዚህ
የወንጀል ቡድኖች (ታጣቂዎች) የፕሮፓጋንዳ መረቦችን በመዘርጋት የነፃ
አውጪነትን እየተሰበከላቸው «የጋራ ሕልውና» በሚል ትብብር
ፋኖ የተባለው “ቅጥረኛ” (በተለይ “የዘመነ ፋኖ” እያልኩ የምጠራው የጎጃም ታጣቂ) በርካታ
ታዳጊ ለጃገረዶች እንዳውም መስማት የማትችል “የጀሮ ሕምመተኛ” የሆነች የ14 አመት ታዳጊ ልጃገርድ ሳይቀር “ሰላይ ነች” በሚል
“የረሸነ” በርካታ ነብሳትን በማን አለብኝነት እንዲረሸኑ ያደረገ ፤ ምርኮኞችን በዱላ የቀጠቀጠ
“በጋሚዶ” እና እንዲሁም በኢትዮጰያ ሉአላዊነት እና በአማራ ሕዝብ ላይ የዘር ማጥፋትና ብሔራዊ
ወንጀል ከፈጸመው ድሮ በመለስ ዜናዊ ፤ አሁን በደብረጽዮን ቡድን ከሚመራው ህ. ወ. ሓ.ት ጋር ፤
እንዲሁም የአማራን ሕዝብ የዘር
ማጥፋት “ፈር ቀዳጅ” ከሆነው ሰው በላው ከጂሃዳዊው “ኦነግ” እና ከመሳሰሉ አደገኛ አገር አፍራሽ ታጣቂዎች ጋር ጥምረት ፈጥሮ
ሲንቀሳቀስ እያየን ነው።
ጥምረቱ የተመሰረተው በወንጀለኞች መካከል ነው። እነዚህ ድርጀቶች በዘር ማጥፋት ወንጀል የተሳተፉ
ናቸው። ይህ በወንጀል ዓላማዎች ላይ የተመሰረቱ አጋርነቶች በብዙ ሕዝብ ላይ ጥልቅ ጥርጣሬ እና ከባድ ማህበራዊ መከፋፈልን እየፈጠረ ነው።
ሌላ ቀርቶ ለጥምረቱ “እያሽቃበጠ” ያለው የድሮው የ360 ባልደረባ የነበረው “ሃብታሙ አያሌው” እንኳ ገና ከጅምሩ ኦ.ነ.ግ በማኒፍስቶው ላይ ያሳተመው የEmpire ትርጉም ሃብታሙ አያሌው በማይሆን መንገድ ቀባበቶ ሲያሽሞነሙናልቸው እና የተናገሩትን ትርጉም ሲያለሳልስላቸው ሰምተነዋል።
ሃብታሙ ያ ብቻ ሳይሆን የተደረገ ጉዳት ካለ አሁን እንተወው እና በሽግግሩ ወቅት እንተሳሰባለን፤
የሚል ድንቁርናም ለአድማጮቹ ሲሰብክ ሰምተነዋል።
ይህ አባባሉ ካሁን በፊት ዘመነ እና አስረሰ ማረ የተባሉ “በጋሚዶዎች” በነብስ
ማጥፋት እና በምሳሰሉ የወንጀል ድርጊቶች መሳተፋቸውን እያወቀ ያለፈውን አታንሱ “አሁን ተባበሩ ፤ ኋላ እንደርሰበታለን” እያለ
የሰው ደም ያፈሰሱት ወንጀልኞችን በሕዝቡ ሕሊና ልክ እንደ “የነፃነት ታግዮች እና የሰው ልጅ ሕይወት ጠበቃዎች” አስመሰሎአቸው
እየሰበከ እነሆ አሁን “ድርጀቱን በመዳፋቸው ሥር አድርገው” “እስክንድር ነጋን እንዲታሰር” እሰከመጠየቅ ደርሰዋል። የክሕደት እና
የወንጀል ጥግ ማሳያው እስክንድርን እሰከማሰር መጠየቅ!!! መሃረነ ክርስቶስ!
ይህ ጥምረት ማለትም በእነዚህ
7 ድርጅቶች ውስጥ የተሰገሰጉ ወንጀለኞች በጦርነት ቢያሸንፉ «በሽግግሩ ወቅት የሚያዋቅሩት ሕግ እራሳቸውን የሚቀጣ ሕግ አይቀርጹም»
ይህ ባሕሪ ከ13 አመት በፊት በሰፊው ጽፌአለሁ።እየተደጋገመ እየመጣ ያለው ያው አዲሶቹ እና ነባር ወንጀለኞች የወንጅለኞቹ “ሪሳይክል” (ድግምግሞሽ) መርሃግብርና ስልታዊ ስሪት ነው። ሳንሸሽግ እንነጋገር፡
በሽግግሩ ሂደት የሚድነው ሕዝቡ ሳይሆን
የሚድነው የሚድኑትና
ነጻ የሚወጡት እነዚህ ድረጅቶች እየመሩ ያሉ መሪዎች ናቸው።
“ዶሮን ሲያታልልዋት
በመጫኛ ጣልዋት”
“ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣሏት” የሚለው የታወቀ የኢትዮጵያ ምሳሌያዊ አነጋገር እዚህ ላይ
እያየን ነው።
ትርጉሙም አንድን ሰው (ቡድን) በቀላል ማታለልና ማባበል ፍፁም ቁጥጥር ስር ማዋልን ወይም
ማጥመድን ያመለክታል። ዶሮ እህል ወይም አምሳያ ነገር እየተወረወረላት ስትሸወድ፣ በመጨረሻ ጭነት ለማሰር በሚያገለግል ሰፊ ገመድ
(መጫኛ) ውስጥ ተተብትባ (ገብታ) ተሰናክላ በቀላሉ እንደምትወድቅ ሁሉ፣ አንዳንድ የዋህ ወይም ስግብግብ ሰዎችም በትንሽ ጥቅማጥቅም
ወይንም “አታላይ ፖለቲካ” ተደልለው ትልቅ አደጋ ውስጥ እንደሚገቡ ለማስተማር የተነገረ ምሳሌያዊ አነጋገር ነው። አሁን እየሆነ
ያለው ያ ነው።
ለሕልውና ስንል ጥምረት
ፈጥረናል ሲሉን «የወንጀለኞችን ዘላቂ ሕልውና ለማስጠበቅ ነው»። ሕዝብ የሚለው የማሞኛ ስልት ከላይ በጠቀስኩት በ “ዶሮ” ቀይሩት።ከፖለቲካ
ወንጀለኞች ጋር አንድነትን የምንቃወምበት ክርክር አገራችን እንዳንገባ፤ ከገባንም እንደሚገድሉን እና እዛው አገር ውስጥ ያሉትንም
ከዚህ ክልል ወጣ እያሉ ዜጎችን የሚጨፈጭፉ ጨፍጫፊዎች እና ዘረኞች ሰለሆኑ ነው።
የወንጀለኞቹ ትብብር ታዋቂ ጥሩምባኞችን አሰማርተዋል።ከነዚህ አንዱ ሃብታሙ አያሌው ነው።ሃብታሙ
አያሌው ከነጠባሳችሁ ዝምበሉ እያለን ነው። ዘረኞች ሆይ! እርሱ ይቅርታ
ሊያድርግላቸው ይችላል፤ እኔ እንደ ትግራዋይነቴ በወላጆቼ ቀብር እንዳልገኝ፤ ዘመዶቼ እንዳልጠይቅ እንዲሁም 93 አመት በኖረበት
በራሱ ምድር ውስጥ በወላጅ አባቴ ላይ የፈጸሙት ድርጊት የማልረሳው ጠባሳ ስላለኝ በሽግግሩ ወቅት ፍትሕ ታገኛለህ እያለኝ ያለው
ሃብታሙ አያሌውም ሆነ የጥምረቱ አሽቃባጮች በቁስላችን ላይ ጨው እየነሰነሳችህ ነው ለማለት እወዳለሁ።
በነዚህ የድረጅት መሪዎች ላይ «የተቆጣ ሕዝብ» አለ።እውነተኛ ስምምነት አድርገናል ስትሉ የሕዝብ
ቁጣ ዋና መንስኤዎችን መፍታትን ይጠይቃል።ያንን አላደረጋችሁም። “እውነተኛ ስምምነት የሚደረገው አሁን ነው”። የራበውን ሰው ይኸው
እንካ ትለዋለህ እንጂ እየራበህ ቆይ እና በማይታወቀው የሽግግር ወቅት አበላሃለሁ አትለውም። የፍትሕ ሰዎች እና የአንድነት ሰዎች
ስለ Empire የሚቃዥ የድንቁርና ልሳን አያስደምጡም። ግራ የሚያጋባ እና አምታች ቃላቶችና ንግግር አይጠቀሙም፤
በመጨረሻም ይህንን ልበልና ልደምድም።
ኢትዮጵያዊያን እንዲህ እያንገላታን ያለው፤ የሃይለሥላሴ እና የሚኒስትሮቻቸው ደም እርግማን
ይመስልኛል “የፍትህ መጓደል ባህል እና የኮሚኒስቶች ፖለቲካ እንደ አዋጪ ባሕል አድረገን እየተንገላታን ተሸንክረንበታል”።
የፖለቲካ ወንጀሎች በአንድነት ስም ችላ ሲባሉ፣ የወደፊት መሪዎች በኋላ ላይ በብሔራዊ እርቅ
ሽፋን «ያለመከሰስ ድርድር» ማድረግ እንደሚችሉ ስለሚያውቁ “የወንጀለኞች አጋርነት” አዋጭ ስልታቸው ነው። ለዚህ ነው የወንጀለኞች
ጥምረት የወንጀል መሸፈኛ ስልት ነው የምለው ለዚህ ነው።
ጌታቸው
ረዳ Ethiopian Semay
