Thursday, April 4, 2019

የአገርቤት ቆይታዬ ትዝብት ከአገሬ አዲስ Ethio Semay


Note rom the Editor:-
A must read astonishing important document.

የአገርቤት ቆይታዬ
ትዝብት
አገሬ አዲስ
መጋቢት ቀን 2011 ዓም(28-03-2019)

ከአስራአንድ ዓመት በዃላ ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት ችዬ ለሦስት ወር ባደረኩት ቆይታ የየሁትን፣የሰማሁትን፣የታዘብኩትን ለሌላው ለማካፈል የዜግነት ግዴታዬ አድርጌ እቆጥረዋለሁ።ከዚህም ቀደም ለብዙ  ዓመታት ይህንኑ ከማድረግ አልቦዘንኩም።በአገር ቤቱ ቆይታዬ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን፣ የሲቪክ ማህበራትን፣የመንግሥት ተቋም የሆነውን የምርጫ ቦርድን ተከታታይ ስብሰባዎች ተሳትፌለሁ፤ሃሳቦችን አዳምጫለሁ።ብዙ ክንውኖችን  ተከታትያለሁ።የምሁራንን የጥናት ትንታኔ አዳምጫለሁ፤ተያይዞም ከውጭ የገቡ ምሁራኖች ቦታ ለማግኘት ያደርጉ የነበረውን ሽር ጉድ ታዝቤአለሁ።አንዳንዶቹም ተሳክቶላቸው እንደ ነጮቹ በዶላር እየተከፈላቸው በመንግሥት አማካሪነት የተሰለፉ እንዳለ የውስጥ አዋቂ ሹክ ብሎኛል።

በትዝብት ዓምድ ስር መጻፍ ካቆምኩኝ እረጅም ጊዜ ሆኖታል።ይህ ማለት ግን ብዕሬን ሳላነሳ ዝምታን መርጬ ቆይቻለሁ ማለት አይደለም።በተለያዩ ዕርእሶች በርከት ያሉ ጽሁፎችን ለንባብ አቅርቤአለሁ።በተለይም ከሁለት ዓመት ጀምሮ ለውጥ መጣ እስከተባለበት ጊዜ ድረስ በአገራችን የተከሰተውን የፖለቲካ ምስቅልቅል ሁኔታና አደገኛ አቅጣጫ፣መጣ የተባለው ለውጥ አነሳስ፣ይዞት የሚራመደው ተልእኮ ምንና በነማንስ እንደሆነ በዝርዝርና በድፍረት ለማሳዬት ሞክሬአለሁ።ያቀረብኩትን አስተያዬት ጥቂቶቹ የሚጋሩት መሆናቸውን የተረዳሁትን ያህል ብዙሃኑ የለውጡ ተቃዋሚ አድርገው እንደቆጠሩት  ከማደርጋቸው ውይይቶችና  ክርክሮች ለመረዳት ችያለሁ።አንዳንዶቹም በዶር አብይ ላይ የግል ጥላቻ እንዳለኝ የቆጠሩም አይጠፉም።እውነቱ ግን ካለኝ የፖለቲካ ንቃትና የጎሰኞችን አካሄድ ብሎም የነዶክተር አብይ ድርጅት የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራቲክ ድርጅት(OPDO)ከፍተኛ አመራር አባላት በ2017 እ.አ.አ በምኖርበት አገር በኔዘርላንድ ውስጥ ለስልጠና መጥተው በነበረበት ጊዜ ከአሰልጣኙ መንግሥት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት  ባለሥልጣኖች ጋር ባደረኩት ውይይት የአንድ ጎሳ ድርጅት ነጥለው በማምጣት ማሰልጠናቸውን ተቃውሞ ማቅረቤን በወቅቱ ሁኔታውን የገለጽኩላቸው ያውቁታል።ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ህወሃት ቦታውን ለኦህዴድ እንደሚሰጥና ለውጡ የጎሳ መተካካት እንደሆነ በመረዳት ሌላውም እንዲረዳ የተለያዩ ጽሁፎችን(የዱላ ቅብብሎሽ፣ተቀምጠው የሰቀሉት ቆመው ለማውረድ ያዳግታል፣ከጭፍን ድጋፍ ገንቢ ትችትና ነቀፋ ይሻላል፣መልከጥፉ በስም ይደግፉ፣……ወዘተ)የሚሉ ጽሁፎችን በተከታታይ  በድረገጽና በግለሰብ አድራሻዎች መላኬን ያነበቡ ሁሉ ምስክሮች ናቸው።

ብዙም አልቆዬም የኦህዴዱ ዶር አብይ አህመድ የሃይለማርያም ደሳለኝን ቦታ ተረከቡና ሕዝብ ለ27 ዓመት ከመሪዎቹ አንደበት በኩል ሰምቶ የማያውቀውን ኢትዮጵያዊነት ሲያቀነቅኑ ሙሉ ተስፋና እምነቱን ጥሎ ፣ከሰውነት ደረጃ አውጥቶ ከአማልክት ደረጃ አሰለፋቸው።ተራው ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ተምረዋል የተባሉትም አብዩ ነብዩ፣የኢትዮጵያ ሙሴ፣አምላክ የላከው የለውጥ ሃዋርያ….ወዘተ እያሉ ከሚችሉት በላይ ውዳሴ ዳረጓቸው፤ዶር አብይ ግን የኢሕአዴግ መሪና ተመራጭ፣የኦሕአዴድ አባልና ፕሬዚደንት፣ህገመንግሥቱን አክብረው ለማስከበር የተሰየሙና አደራ የተጣለባቸው መሆናቸውን በመደጋገም ተናገሩ።

ዶር አብይ የሚወክሉት ላለፉት 28 ዓመታት በጎሳ ፖለቲካ አገር የሚያምሰውን የኢሕአዴግን ስርዓት ነው።የዚያ ስርዓት ዋና ምሰሶ የሆነው ሕገመንግሥት መመሪያቸው ነው።በዚያው ስርዓት የተቋቋመው ሕግ አውጭው ፓርላማም የሳቸው መሳሪያ ነው።ዶር አብይ የነበረውን የቢሮክራሲና የአስተዳድር መዋቅር እንዳለ የተረከቡ፣ የደህንነቱና ሕግ አስፈጻሚውም አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ሲገለገሉበት የኖረው እንጂ የተቀዬረ አይደለም።ተቀዬረ ቢባል ስርዓቱ ሳይሆን የስርዓቱ ቁንጮ የሆኑት ግለሰቦች በሰሩት ወንጀል ሳይጠዬቁ የቦታ መቀያዬር ማድረጋቸው፣አንዳንዶቹ በጡረታ፣አንዳንዶቹ በሹመትና ሽልማት አንቱ ተብለው ለከፍተኛ ስልጣን መታጨታቸው፣ ብሎም በአማካሪነት ቦታ መሰየማቸው ነው።ሌላው በስፋት የሚታዬው  በየመስሪያ ቤቱ የጎሳ መተካካት ወይም ሹም ሽር ነው።ይህ  እንደለውጥ ከተቆጠረ ለውጡ ለተሾመውና ለተሻረው እንጂ ለሕዝቡ ያመጣው መሰረታዊ ለውጥ የለም።አሁንም ሕዝቡ በሙስና ይዘረፋል፣መብቱ የሚፈቅድለትን አያገኝም። ቢያጣም ቢያገኝም በባለስልጣኑ ፍላጎት ላይ ያረፈ እንጂ ሕጉን የተመረኮዘ ውሳኔ አይደለም። አሁንም በባሰ ደረጃ በኑሮ ውድነት፣በሥራ አጥነት፣በበሽታ፣በጎሳ ማንነቱ  መፈናቀሉ፣መገደሉ፣መዘረፉ አልቆመም።ለውጡ ያው በገሌ ነው።እርግጥ ለጊዜው ለመናገርና ለፖለቲካ ድርጅቶች መሰባሰብ ለቀቅ ያለ ሁኔታ መፍጠሩ አይካድም።እንደዚያ ያለ ሂደት በታሪክ ተደጋግሞ የታዬ ነው።አዲስ መጡ የሕብረተሰቡን ድጋፍ ለማግኘት ከነበረው የተጠላ ቡድን ለዘብተኛና ሕዝባዊ ሆኖ መቅረብ ይኖርበታል፤ያ ግን ውሎ አያድርም።።ከጊዜ በዃላ እየተቆናጠጠ ሲሄድ በከፋ መልኩ ወደ ማንነቱ ይሸጋገራል።ህወሃት ደርግን ጥሎ ሲመጣ መጀመሪያው ላይ ሕዝብን የሚያማልል አቋም ነበረው።ያሁኑም ከዚያ የተለዬ አይሆንም፤ምክንያቱም ከተለዬ የፖለቲካ ርዕዩተዓለም አልተነሳም እና ነው።ህወሃትም ጎሰኛውን ኢሕአዴግን የመራ ቡድን ነው።ኦሕዴድም እንዲሁ ኢሕአዴግን በመምራት ላይ ነው። ዶሮን ሲያታልሏት እንዲሉ የኢሕአዴግ ድርጅቶች ስማቸውን በዴሞክራቲክ ፓርቲ ታፔላ(ሰሌዳ)ቀይረው ብቅ ብለዋል።ወደፊትም የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ነን ብለው ለምርጫ መቅረባቸው አይቀርም።ውስጠ ህዋሳቸው ግን ያው የጎሳ ፣የኦሮሞ፣የአማራ፣የትግሬ፣የደቡብ ማንነታቸው ነው።
የዶር አብይ መንግሥት ከጎሳ ፖለቲካ አለመራቁና ሊርቅም እንደማይችል ዋናው ማስረጃ በከባቢያቸው ያሉት አማካሪዎቻቸውና በመከናወንም ላይ  ያለው የጎሳ ተኮር እርምጃ ነው።በአጠገባቸው የተኮለኮሉት አማካሪዎች አሁን ላለው የሽብርና የስጋት ኑሮ፣የመፈናቀልና የአዲስ አበባ ከተማ ሕዝብ መብትን የመካድና  የመንጠቅ ዕቅድ ቀደም ሲል በአደባባይ አቋማቸው አድርገው ለዘመናት የቆዩ የኦሮሞ ልሂቃን ናቸው።እነዚህ ልሂቃን አሁንም ቢሆን አርባ ዓመት የታገልንለት የኦሮሞ ሕዝብ መብት አልተረጋገጠም እያሉ በየሚዲያው ይለፍፋሉ።ያልተረጋገጠው ነገር ኢትዮጵያ በነሱ መዳፍ ሥር  ሆና  የአዲስ አበባ ብቸኛ  ባለቤትነት ነው።ለማረጋገጥም ሕዝቡን ማፈናቀልና የከተማዋን የሕዝብ  ስብጥርነት(ዴሞግራፊ)ለመለወጥ በትጋት በመሥራት ላይ ናቸው።ይህንን ሲያደርጉ ከመንግሥት እውቅና ውጭ አይደለም።በየክልሉና በአዲስ አበባ ክፍለከተማ አስተዳደር ውስጥ የበላይነቱን በያዙት የኦሕዴድ መሪዎችና አባላት ትብብርና ፈቃድ ነው። በአጭሩ መንግሥታዊ ደባ ነው ማለቱ ይቀላል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት የታገለበትና ብዙ መስዋዕት የከፈለበት የስርዓት ለውጥ አሁን ባለው አነስተኛ የጥገና ለውጥ(ለውጥ ከተባለ)እንዲቆም የፖለቲካ ጥያቄው ሙሉ ለሙሉ ተመልሷል፣አሁን በኤኮኖሚው ላይ መረባረብ ነው የሚሉ የኦሕዴድን በስልጣን ላይ መምጣት እንደለውጥ የሚቆጥሩ የኦሮሞና የሌላው ጎሳ  ቡድኖችም መኖራቸው ተስተውሏል።

አገራችንን ለመበታተን ጭፍን የጎሰኝነት ፖለቲካ የሚነዛውም ቡድን ዓላማውን ከግቡ ለማድረስ ቆንጨራ እዬሳለ፣ጠመንጃ እዬወለወለ ይገኛል፤በዚያ ላይ መንግሥት ነኝየሚለው አካል ከቃላት ባለፈ እርምጃ ከመውሰድ በመቆጠቡ ለሽብር ተዋንያኑ የልብ ልብ የሰጣቸው  ይመስላል።እነዚህ የጥፋት ሃይሎች የዶር አብይን የመለሳለስ አቋም አይወዱትም፤እንደውም የድክመት ምልክት አድርገው ሳይወስዱት አይቀሩም።እነዚሁ ቡድኖች ለሌላው የአገሪቱ ዜጋ  ብቻ ሳይሆን ለለዘብተኛ ኦሮሞውም ቢሆን ምናልባትም በዶር አብይና የቅርብ ተከታዮቻቸው ላይ  አደጋ ከመጣል አይመለሱም።

በፖለቲካ ዓለም በአንድ ካምፕ ውስጥ ለዘብተኛና አክራሪ ቡድን መፈጠሩ የተለመደ ነው።የአክራሪውን አቋም በመፍራት ለዘብተኛው ተቀባይነትና ድጋፍ በማግኘት አክራሪውና ለዘብተኛው ለሚፈልጉት የጋራ ዓላማ መድረሻ ስልት ሆኖ እንደሚያገለግል መታሰብ አለበት።በሌላም በኩል ከሚፈልጉት በላይ በመጠየቅ በድርድር የሚፈልጉትን ማግኘት እንደሚቻል የትግል ተመክሮ ያረጋግጣል።በዚህ ዕይታ የተለያዩ የሚመስሉት የኦነግና የኦሕዴድ ቡድኖች የማታ ማታ የሁለቱም የጋራ ዓላማ የሆነውን  የኦሮሞን የበላይነት ማረጋገጥ ስለሆነ ሌላውን አጃጅለው በድል አድራጊነት ለመውጣት የሚያበቃ ስልት እንደሚከተሉ መታወቅ አለበት።

በተቃዋሚው ጎራ አለን ከሚሉትም መካከል አንዳንዶቹ ካለው ስርዓት ጋር ተለጥፈው፣አማራጭና ተቃዋሚ ከመሆንና ሕዝቡን ለለውጥ ከማዘጋጀትና ከመምራት ይልቅ የስርዓቱ አጃቢ በመሆን ፤በተቃዋሚ ስም በጓዳ በር የስልጣን ተቋዳሽ እንሆናለን በሚል ተስፋ ሽር ጉድ ሲሉ ይታያሉ።እራሳቸውን  ብቸኛ ተቃዋሚ አድርገው በመቁጠር በትዕቢት ተወጥረው የጎሳ ፖለቲካን ከመቃወም፣ከማውገዝና  ከመታገል ይልቅ ከጎሰኞች ጋር በመፈራረም አጋርነት ሲፈጥሩ ማዬት የተለመደ ትእይንት ሆኗል። ዓላማ ሳይሆን ውድድሩ ቁጥርህን አብዛ ሆኗል።በዚያ አካሄድ የተፈረመ ውልና ስምምነት ግን ውሎ ሳያድር እንደሚፈራርስ በተደጋጋሚ ታይቷል። ከታሪክና ከራስ ስህተት አለመማር ነው።ጎሰኛና አገር ወዳድ ድርጅት ከሚስማማበት ይልቅ የሚለያይበት ነጥብ ይበዛል።

   ዶር አብይ የሚመሩት መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ የሰፈነውን ግጭትና አለመግባባት ለማሶገድ የእርቅና መግባባት እንዲሁም የድንበርና ወሰን ኮሚሽኖችን ማቋቋማቸውን ይፋ አድርገዋል። በእርምጃው ላይ ተቃውሞ ባይኖርም በኮሚሽኑ ውስጥ የተካተቱት ግለሰቦች ማንነት ሲመረመር ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል።ምክንያቱም ለሕዝቡ ሰላም መናጋትና ለአገሪቱ አንድነት ስጋት ምክንያት የሆነ የጎሳ ፖለቲካ ሲረጩ የነበሩትና አሁንም በጎሳ ፖለቲካ ውስጥ የተዘፈቁ ሰዎች የተካተቱበት ኮሚሽን በመሆናቸው ነው።ሰላማዊ ሕዝብን ያፈናቀለ፣ወጣቱን አሸባሪ ብሎ የወነጀለ፣ ያሰረ፣የገደለ፣ያሳደደ፣ ኢሕአዴግ የተባለውን ወንጀለኛ ቡድንና  ስርዓት የመራና የወከለ እንደ ሃይለማርያም ደሳለኝ ያለ ግለሰብ የሚመራው የሰላም እርቅና  መግባባት ኮሚሽን የት ይደርሳል?ለወንጀሉ ተጠያቂ የሆነው ሰብሳቢ ከሆነበት ኮሚሽን ምን ይጠበቃል?የራያና አዘቦን፣የወልቃይትን መሬት የትግራይ ነው ብለው ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ እንደ ዶር አረጋዊ በርሔ ያሉ የህወሃት መስራቾች ለእውነተኛ የክፍላተሃገር ወሰን ይቆማሉ ተብሎስ እንዴት  ይጠበቃል?የሚጠብቅ ካለ የሰዎቹን ማንነትና ያላቸውን አቋም  የማያውቅ ብቻ ነው።የጠቡና ቀውሱ መነሻ የጎሳ ፖለቲካ ያመጣው እንጂ ለዘመናት አብሮ በሰላም የኖረው ሕዝብ የፈጠረውና የፈለገው ችግር አይደለም።ችግሩ የሚወገደው በኮሚሽን ሳይሆን ፍጹም ኢትዮጵያዊ በሆነ፣ከጎሳና ከሃይማኖት የጸዳ የሥርዓት ለውጥ ሲመጣ ብቻ ነው።ሽማግሌና ኮሚሽንም ይቋቋም ቢባል ወገንተኝነት የሌላቸው፣ የችግሩ ፈጣሪዎች ሳይሆኑ ከሕዝቡ የተውጣጡ ያገር ሽማግሌዎች፣የታሪክ አዋቂዎችና ስለውስጣዊ ያገር አስተዳደርና አወቃቀር የሚያውቁ ምሁራን የጆግራፊ፣የኤኮኖሚ፣የሶሾሎጂ ሊቃውንት  ሊሆኑ ይገባል እንጂ  የጎሳ ድርጅት መሪዎችና አባላት ሊሆኑ አይገባም።

ስለ አዲስ አበባ

የአዲስ አበባ የይገባኛል ጥያቄ  የቅርብ ጊዜ ጥያቄ ሳይሆን ከአርባ ዓመት በፊት ኦነግ ሲነሳ አልሞ የተነሳበት ጉዳይ ነው።እንደ ኦነጎች እምነት ኢትዮጵያ የምትባል አገር ሳትፈጠር አዲስ አበባ (ፊንፊኔ) ኦሮሚያ የሚል አገር ከተማ ነበረች ባዮች ናቸው።በዚህም አያቆሙም፤በአዲስ አበባ የሚኖረው ኦሮሞ ያልሆነው ሕዝብ ለኦሮሚያ መንግሥት የሚጠቅመው መኖሪያ ፈቃዱን እያሳደሰ መኖር ሲችል የማይጠቅመው ደግሞ ከአዲስ አበባ ተጠርዞ  ወደ መጣበት ይሄዳል የሚል አቋም ነበራቸው።አሁን ለመተግበር የሚሞክሩት ይህንኑ አቋማቸውን ነው።የዚህ አቋም አቀንቃኝ የሆኑትም የኦነጉ መስራች ዶር ዲማ ነገዎ፣በአሁን ላይ  የጠቅላይ ሚኒስትር ዶር አብይ አህመድ የበስከጀርባ (Shadow advisor)አማካሪና የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ግንባር(ኦዴግ) ሊቀመንበር ናቸው።ይህንን አቋማቸውን ከ28 ዓመት በፊት ወያኔና ግብረአበሮቹ ስልጣኑን ከመያዛቸው በፊት ከስድስት ወር ቀደም ሲል በጀርመን አገር ኢሕአፓ፣ኦነግ፣ህወሃት፣የደርግ አምባሳደር በተካፈሉበት፣እንደኔ ያሉ ኢትዮጵያንም ለመታዘብ የተገኘንበት ስብሰባ ላይ በግልጽ የተናገሩትና አንድ  ጀርመናዊ ምናልባት ተሳክቶላችሁ  ስልጣን ብትይዙና ኦሮሚያ የተባለ አገር ብትመሰርቱ፣ብዙ ሕዝብ የሚኖርባትን የአዲስ አበባን ከተማ ብትቆጣጠሩ ከያቅጫጫው የመጣውን ኦሮሞ ያልሆነውን ሕዝብ ምን ታደርጉታላችሁ?ብሎ  ላቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ ነው።ይህንን አባባላቸውን ግን ከስድስት ወራት በዃላ የኢሕአዴግ የማስታወቂያ ሚኒስትር ሆነው አገር አገር ሲዞሩ በሆላንድ በተደረገ ስብሰባ ላይ  ሲጠየቁ ሽምጥጥ አድርገው ክደዋል።አሁንም ድረስ ይቅርታ ያልጠየቁበትና ያልተጠየቁበት ስህተት ነው።አሁን የሚካሄደውን ዘመቻ ከወትሮው አቋማቸው ጋር ሳገናዝበው ጭራሽ ተግባራዊ ለማድረግ የሚመኙ መሆናቸውን አልጠራጠርም።በቦታው ላይ እንደነበሩት እንደ ሌሎቹ በጆሮዬ የሰማሁትን ሲክዱ እያዬሁ በሰውዬው ላይ እምነት የለኝም።

በእኔ አቋም አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ንብረት፣ የታሪክና የባህል ፣የኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገር መዲና ፣የሸዋ ክፍለሃገር ዋና ከተማ ከመሆኗም በላይ ለአፍሪካና ለዓለም አቀፍ ተቋማት ማእከል ነች።አዲስ አበባ አሁን ከደረሰችበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ላቡን፤ገንዘቡን እውቀቱን ከዚያም በላይ ህይወቱን ገብሮላታል። አዲስ አበባ ማንም ነጠላ ጎሳ የኔ ብቻ ናት ብሎ ጥያቄ ሊያነሳባት የሚችል የመንደር ይዞታ አይደለችም።አዲስ አበባ ለኢትዮጵያ እምብርት፣የፖለቲካ፣የኤኮኖሚ፣የሁሉም መንግሥታዊና ሕዝባዊ ተቋማት ማእከል ነች።አዲስ አበባን ማስከበር ኢትዮጵያን ማስከበር ነው።የ6 ሚሊዮን ኑዋሪዎች ድምጽና  መብት በጥቂቶች ኑዋሪዎች ፍላጎት መዳፍ ሥር መውደቅ የለበትም።በጋራ ለመጠቀም መተባበሩ እንጂ በግለኝነት መፎካከሩ የያዙትን ያሳጣል።ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም። ስለሆነም የአዲስ አበባን ጉዳይ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች መተው ትልቅ ብልህነት ነው።ነባር ነዋሪውን እያፈናቀሉ ከሌላ ቦታ ኦሮሞውን እያመጡ በማስፈር የሚቃለል ጉዳይ አይደለም።

በአዲስ አበባ ውስጥ የመኖር መብት የሁሉም ኢትዮጵያዊ መብት ነው።ሌላው ቀርቶ ሕግና ደንቡን ያሟላና  ያከበረ የውጭ አገር ዜጋም ቢሆን  የመኖር መብቱ ሊከበርለት ይገባል።ከወራት በፊት ከኦጋዴ በጎሰኞች የተፈናቀሉት የተለያዬ ጎሳ ተወላጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን  መሆናቸው ሲታወቅ የአንድ ጎሳ ተወላጆችን  ማለትም የኦሮሞውን ብቻ እዬመረጡ በአዲስ አበባ ከተማ ማስፈር ለታለመው ከይሲ ዓላማ እንደሆነ ይታወቃል።ተፈናቃዬችን ሳይሆን አፈናቃዮችንና በዚህ ሰበብ ያለሙትን ዓላማ ለማስፈጸም የተሰማሩትን ማውገዝና መቃወም ተገቢ ነው።እውነት ለተፈናቃዮቹ ቢታሰብ ኖሮ በኖሩበት ቦታ ተመልሰው እንዲቋቋሙ የሕግ ጥበቃና ድጋፍ ቢደረግላቸው የተሻለ ነበር።  
          
በሶስቱ ወራት ቆይታዬ ምንም እንኳን ከአዲስ አበባና አካባቢዋ እርቄ ባልሄድም ከየክፍላተሃገሩ ከመጡት ሰዎች ጋር ባደረኳቸው ውይይቶች፣በአዲስ አበባ ውስጥ በታዘብኳቸው ሁኔታዎችና በዜና ማሰራጫዎች በኩል  ያለውን ሁኔታ ከሞላ ጎደል ለመገንዘብ ችያለሁ ብዬ አምናለሁ።

የአዲስ አበባ ሕዝብ ብዛት ከሚገመተው በላይ ነው፤በገጠሩ የሥራ ዕድል ባለመፈጠሩና ችግር በመስፈኑ ሁሉም ለተሻለ ኑሮ ወደ ከተማዎች መፍለሱ አይቀሬ ነው።ለትዝብት መገናኛ ከሚባለው ቦታ ላይ የሚርመሰመሰውን የሕዝብ ብዛት ሲያዩት ለዚያ ሕዝብ የሚያስፈልገውን የቤት፣ ፣የምግብ፣የልብስ፣የጤና፣የትምህርት፣የሥራ…ወዘተ ፍላጎት ለማሟላት እንኳንስ በጎሳ ጭቅጭቅ ላይ ሆኖ በአገራዊ ፍቅርና ህብረት በቀላሉ የሚመለስ ጥያቄ እንዳልሆነና ብዙ ሥራ መሰራት እንዳለበት ለማስተዋል ከባድ አይሆንም።

የአዲስ አበባ ከተማ ተለጥጧል፤ዱሮ የማላውቃቸው የቦታ ስሞች አሁን እንደ አሸን የፈሉ መኖሪያ መንደሮች፣ የከተማው አካል ሆነዋል፤ሁሉም ግን ቀድሞ በማይታወቁበት  የኦሮሞ ስያሜዎች የሚጠሩ መንደሮች ናቸው።በዛፍና በጫካ ተሸፍኖ የነበረው ኮረብታ ሳይቀር የሆቴልና መኖሪያ ሕንጻዎች ተከምረውበታል።የመኪናው ና የትራፊኩ ትርምስምስ በሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት ላይ በ10 ኪሎሜትር ስፋት( ራዲዬስ) አምስቱን ኪሎሜትር ለመጓዝ ካለማጋነን ከአንድ ሰዓት ተኩል በላይ ይፈጃል።ታክሲና አውቶብስ በብዛት ቢኖርም የሕዝቡን ፍላጎት ሊያሟላ አልቻለም።ከተሽከርካሪው የሚወጣው ጭስ ለከተማዋ የአየር ብክለት ዋናው ምክንያት ነው። አዲስ አበባ በውጭ አገር ካላዬሁት ዘመናዊና ውድ መኪና  ቸርኬው ተጣሞ በሩ በገመድ እስከታሰረ አሮጌ ታክሲና የቤት መኪና የሚሽከረከሩባት ከተማ ነች።ሁለቱም መኪና ተብለው ይሽከረከራሉ።ብዙሃኑ የከተማው ኑዋሪ ታክሲ፣አውቶብስና የባቡር ቦታ ለመያዝ ይራኮታል።በተለይም አውቶብስና ባቡር ክፍያው ዝቅተኛ ስለሆነ የተሳፋሪ ገደብና ልክ የለውም።አዲስ አበባ !ለጥቂቶች ገነት ለብዙሃኑ ሲኦል፣የዋይታና የአስረሽ ምችው ከተማ!

 የብዙዎቹ ሕንጻዎቹ አሰራር ጥራት ዕድሜ ተሻጋሪ መሆናቸው አጠራጣሪ ቢሆንም ፎቅ አለኝ የማለቱ ውድድር ሌላውን የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ አዳክሞታል።በገጠር የቅባት እህል አምራቹ ገበሬ ሳይቀር ያጠራቀመውን ትርፍ በአካባቢው የሥራ መስክ  ላይ ሳይሆን የሚያውለው በአዲስ አበባ የሕንጻ ስራ ላይ ነው ።ያም አከራይቶ ብዙ ገንዘብ ከማግበስበሱ ፍላጎት የተነሳ ነው።በአዲስ አበባ የቦታውና የቤቱ ኪራይ ውድነት አይጣል ነው።በሕዝቡ ገቢ ጋር ሲነጻጸር የሰማይና የመሬት ያህል ነው። ለደሳሳ ጎጆ የሚጠዬቀው ኪራይ በሽዎች የሚቆጠር ነው። ገንዘቡ ከዬት እንደሚመጣ ባይታወቅም ግን ፎቁ  ይገነባል።በአንድ ሕንጻ ስር ከሁለት ያላነሱ የባንክ ቅርንጫፎች ተከፍተው ሲታዩ የገንዘቡ ሽክርክሪት (cerculation)ከመብዛቱ የተነሳ ሊመስል ይችል ይሆናል ግን ለህንጻው ግንባታ ላበደሩት ገንዘብ በኪራይ ስም የሚታሰብ ክፍያ እንደሆነ ይነገራል።ሚሊዬን ብር የትንሽ  የንግድ ማንቀሳቀሻ ወረት  ወይም በካዛንችስ አካባቢ  የ15 ካሬሜትር ባዶ ቦታ ተመን ሆኗል፣የዕቃ ዋጋም በየእለቱ ይጨምራል፤ሸማቹ ግን ያሉትን አጉርምርሞ ከመግዛት በቀር ምርጫ የለውም።በሌላው አገር በቅርቧ ሱዳን ስኳር ጠፋ ወይም ዋጋ ጨመረ ብሎ ሕዝብ ተነስቶ መንግሥት ሲያናጋ የእኛ ሕዝብ ግን ብሶቱን ለፈጣሪው እየነገረ አንገቱን ደፍቶ፣የባሰ አታምጣ ብሎ  ይቀበላል። የፖለቲካ መሪዎች ነን የሚሉት ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች  ይህንን የሕዝብ ብሶት ማሶገድ ቀርቶ ደፍረው ለተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ  አልውጡም።በጣም የሚያሳዝነው ለስብሰባ ሲጠሩ የቀን አበል መጠየቃቸው ነው።መንግስትም ስብሰባ ሲጠራ መርከሳቸውን ስለሚያውቅ ከሁለት ኩባያ ሻይ የማያልፍ መቶ ብር ይጥልላቸዋል።የፖለቲካ ድርጅት ለቆመለት የሕዝብ መብትና ዓላማ ህይወቱን ለመዳረግ የቆረጠ እንጂ ኪሱን ለብር የሚከፍት መሆን አልነበረበትም።ግን በአገራችን የተኮለኮሉት ከመቶ በላይ የሆኑ የክልልና የጎሳ ፖለቲካ ድርጅቶች ይህንን በመሰለ ተግባር ላይ መዋላቸው ነገ ሥልጣን ላይ ቢወጡ ለሚዘርፉበት ሙስና አሠራር ቅድመ ስልጠና ሳይሆናቸው አይቀርም።በዚህ ጉዳይ ላይ ከአንዳንድ የፖለቲካ ድርጅት አባሎች ጋር ስነጋገር ሕዝብ ተፈናቅሎ ለችግር በተጋለጠበት ሰዓት የሚሰጣቸውን የቀን አበል ለተፈናቀለው ሕዝብ ይሁን ቢሉ የተሻለና ለእነሱም ኩራት እንደነበር ገልጨላቸው አንዳንዶቹም ከመጀመሪያው አምቢ አንወስድም ብለው ማለታቸውን ገልጸውልኛል።

የአዲስ አበባ አዬር ዱሮ ከማውቀው ፍጹም የተለዬ ሆኗል።ሙቀቱ የበረሃ ስሜት ይዟል።ለዚህ ምክንያቱ የዓለም አዬር ለውጥ መሆኑ ቢታወቅም ከላይ የተገለጸው የተሽከርካሪ ብዛት ከሚያደርሰው በተጨማሪ፣ ለመኖሪያ ቤትና ለንግድ ፎቅ መስሪያ የጫካ መመንጠርና በሕዝቡ በኩል የሚከናወነው የንጽህና ጉድለትና የከባቢ ውድመት ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል። አሁንም በጎዳና መሽናትና መጸዳዳት አልቀረም። ይህንን ለመቀልበስ ከሚደረጉት ሙከራዎች፣ከደረቅ ቁሻሻ ሃይል የማመንጨቱ ፣የጽዳት ሰራተኞች ተሰማርተው የመንገድና የሰፈር ቁሻሻ ማንሳትና ማጽዳት የሚታዩ ሙከራዎች ናቸው።በይበልጥ ግን ህብረተሰቡ ስለንጽሕና ይበልጥ ግንዛቤ እንዲኖረው ያላሰለሰ ቅስቀሳና ትምህርት ያስፈልገዋል።የቁሻሻ ማጠራቀሚያ እያለ ከማጠራቀሚያው ጎን ቁሻሻ መጣሉ የተለመደ ሆኗል።አብዛኛው በሽታ ከጽዳት ጉድለት መሆኑ እየታወቀ ትኩረት የሚሰጠው በጣም ጥቂቱ ነው።  

ከተማዋ ከዳር እስከዳር በተመሳሳይ ሸቀጥ በተጠቀጠቁ መደብሮች ተጨናንቃለች።ከአረብ አገር፣ከቻይናና ከህንድ በውጭ ከረንሲ በተገዙ ቁሳቁስ የሚካሄደው የገበያ ልውውጥ የህብረተሰቡን ፍላጎት በውጭ ምርት ላይ እንዲያተኩርና ጥገኛ እንዲሆን አድርጎታል።በአገር ውስጥ የሚመረተው በአቅርቦትም ሆነ በጥራቱ ብሎም በዋጋ ደረጃ ሊፎካከር ባለመቻሉ የፈላጊው ቁጥር አነስተኛ ነው።በዚህ ሂደት የአገር ኤኮኖሚ ለማሳደግ የሚኖረው ፈተና ቀላል አይደለም።ሕዝብ ለአገሩ ምርት ክብርና ቅድሚያ እንዲሰጥ የሚያደርግ መንግሥታዊና ማህበረሰባዊ ዘመቻ መካሄድ ይኖርበታል።ይህ የአገር ወዳድነት የመጀመሪያው ተልእኮ ነው።      
          
ብዙ ፕሮጀክቶች ተዘርግተው  ይታያሉ።አንዳንዶቹ ያልተሟሉና ያላለቁ፣ገንዘቡ የተዘረፈባቸው ናቸው፣ከተሰራው ሥራ ጥራትና ዘላቂነት ጋር የወጣው ወጪ ሲታይ እርይ ያሰኛል። የኮንደሚኒዬም(የጋርዮሽ ቤት) አሰራርማ አይነሳ።ምንም እንኳን ጽንሰ ሃሳቡ ቀናና ተገቢ ቢመስልም የወጣበት ገንዘብና የቤቱ አሰራር ሲታይ ታዛቢ ያለው አገር አይመስልም።አንዳንዱ ቤት አስር ዓመት ሳይሞላው ብሎኬቱ እየረገፈ ነው።የውሃና የመብራት ችግር በዚያ ላይ ሲጨመርበት ኮነደሚኔም ለምኔ ያሰኛል።የብዙ ወጣት ላብና ያገር ሃብት  የፈሰሰበት የኮብልስቶን የመንገድ ፕሮጀክትም በአልተደቀደቀ አፈር ላይ የተቀመጠ በመሆኑ እንዲሁ በዝናብ ጠብታ እዬወላለቀ  የሰፈሩ መንገድ ወደ ነበረበት አሮንቃ  በመመለስ ላይ ነው።  በእኔ በኩል ያደነኩት ቢኖር  ሙሉ በሙሉ የሕዝቡን ፍላጎት ያሟላ ባይሆንም በቅርብ የጊዜ ገደብ ተጠናቆ አገልግሎት የሰጠው የባቡር መስመሩ ነው፤ይህም ሊሆን የቻለው በቻይናዎች ስለተሰራ ነው የሚል ተችት ሰምቻለሁ። ትላልቅ የባንክ ሕንጻዎችም በቻይናዎች በመገንባት ላይ ናቸው።ብዙ መሃንዲስና ባለሙያ ባለበት አገር የሌላ አገር ባለሙያዎች ጥገኛ መሆን ለአገር ወዳዱ የሚያቃጥል ስሜት ያሳድራል። ሥራው ሲሰጠው እምነትን ማጉደል፣አገርን መዝረፍ ከተወላጁ በኩል ሲሆን ይበልጥ ያማል።ለዚህ አንዱ ምሳሌ የህዳሴ ግድቡ ነው።ከ7ዓመት በፊት በ80 ቢሊዮን የኢትዮጵያ (5.5 ዶላር)ብር ይጠናቀቃል የተባለው ግድብ ገና ሳይጠናቀቅ 60%ብቻ ላይ 97.8ቢሊዮን የኢትዮ .ብር መፍጀቱ ይነገራል።መቼ እንደሚያልቅና ስንትስ ወጭ እንደሚጠይቅ የተገለጸ ነገር የለም፤ አሁንም ሕዝብ እንዲያዋጣ ጥሪና ቅስቀሳ ይደረጋል።የግንባታው ሥራ ለውጭ ኩባንያዎች እንደተሰጠ ሹክሹክታ ይሰማል፤ከዚያም በላይ ሱዳን፣ግብጽና ሌላ አገር በሽርክና (ባለቤትነት ድርሻ)እንዳላቸው ይወራል።በግንባታው ዙሪያ  የተካሄደው የሙስናና ዘረፋ ወንጀል ሁሉንም ባለሥልጣን ስለሚነካካ ውሾን ያነሳ ውሾ ይሁን ተብሎ የተተወ ይመስላል።

በአንድ መስሪያ ቤት ያዬሁትን ልጨምርና ወደሌላው ነጥብ ልሻገር
የግንባታ ፈቃድና ጥራት የሚቆጣጠር የክፍለ ከተማ መስሪያ ቤት ነው።አዲስ ባለስምንት ፎቅ ትልቅ ሕንጻ አሰርቷል።ሥራም ጀምሮ ብዙ ባለጉዳይና ሠራተኛ ይርመሰመሳል።በዬጠረጴዛው ላይ የተቀመጠው የባለሥልጣኑ ስም ሰሌዳ  ወደ አንድ ጎሳ ያደላ ይመስላል ፤መጨረሻው ፊደል ሳ የሆነው ስም ይበዛል። ።ወደ ሕንጻው ልመለስና ከሊፍቱ ጎን የደረጃ መወጣጫም አለው።ከደረጃው ዳር ላይ ለደህንነት በብረት የተሰራ ገረገራ(ድጋፍ) አለው።ያ ገረገራ በብዙ ወጭ ተገዝቶ የተገጠመ የሚያብረቀርቅ አሉሚኒዬም ነው።ተገጥሞ ካለቀ በዃላ ወር  ሳይሞላው ያ ብዙ ብር የወጣበት አሉሚኒዬም ጥንካሬ የለውም ተባለና በብረት መጋዝ እዬተቆረጠ በሌላ ብዙ ወጭ በሚጠይቅ የብረት ገረገራ እንዲተካ ተወሰነ።ታሪኩን ጠይቄ ስለተረዳሁ በሁኔታው እያዘንኩ፣የተቆረጠውንና ሊተካ የቀረበውን በከፊል እያዬሁ የሄድኩበት ጉዳይ ሳይፈጸምልኝ መስሪያ ቤቱን ጥዬ ወጣሁ። ይህ እንግዲህ እኔ በአካል ያዬሁት አንዷ የግዴለሽነትና የሙስና ምልክት ነች።የጥራት ተቆጣጣሪ ነኝ ብሎ ሕዝብን የሚያስጨንቀው መስሪያ ቤት እራሱ ባሰራውና በሚቆጣጠረው የጥራት ጉድለት ያገር ሃብት ሲያባክን  ማን ይጠይቀው ይሆን? ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ ይሏል ይህ ነው። ባለቤት የሌለው አገር!   

በመኖሪያና በንግድ ቤቶች ኪራይና ግብር ላይ ከፍተኛ ተመን ተጥሏል። የተጣለው ጭማሪ ነግዶ አዳሪውን ብቻ ሳይሆን የተጠቃሚውንም አቅም ያላገናዘበ ነው።በነጋዴው ማህበረሰብ ላይ ኪራይና ግብር ሲጣልበት ጭማሪውን ለመክፈል ሲል በሚሰጠው አገልግሎትና በሚሸጠው ሸቀጥ ላይ የዋጋ ጭማሪ  ያደርጋል፤ያንን እንዲሸከም የሚገደደው ተጠቃሚው ህብረተሰብ ነው።ብዙ ብሶት ቢሰነዘርም ሰሚ አላገኘም።ችሎ ችሎ ትከሻው መሸከም ሲያቅተው ማህበረሰብአዊ ቀውስ መፍጠሩ አይቀርም።ቀውሱ እንደ ቱኒዝያ የስርዓት ለውጥ ቢያመጣ መልካም ነበር፤በጥንቃቄ ካልመራና በግብታዊ መንገድ  ትግሉ ከሄደ ባገራችን ሁኔታ  ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ይሄድና የአገር ሰላምና ህልውና እስከመደፍረሱ  ደረጃ ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት አለኝ።

ሕዝብ እንደመሪው ነው የሚባለውን አባባል በገሃድ ተከስቶ ለማዬት ችያለሁ። በሥልጣን ላይ የነበሩትና አሁንም ያሉት  መሪዎች፣የመስሪያ ቤት አላፊዎች አብዛኛዎቹ  እራስ ወዳድ፣ጨካኝና በሙስና የተጨማለቁ፣የአገርና የወገን ፍቅርና አክብሮት የሌላቸው፣ለገንዘብ የሚሞቱና የሚገሉ በመሆናቸው ለሕዝቡ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ ያወረሱት  ስነምግባር ይህንኑ ነው።አዛውንትና አሮጊት የማይከበርበት፣ሕጻንና እርጉዝ ሴት ቅድሚያ የማይሰጥበት የጥሎ ማለፍ ወይም ጨፍልቆ ማለፍ ባህል የሰፈነበት መሆኑን በቀላሉ በታክሲ መሳፈሪያ ቦታ የሚታዬው ትዕይንት  ያረጋግጣል። ግንኙነት በጥቅምና በገንዘብ የሚተመንበት ጊዜ ላይ እንደደረስን በዘመድ መካከል ሳይቀር ሊኖር የሚገባው መተሳሰብ መጥፋቱን በጉልህ ተረድቻለሁ።ይህ ባህል ጊዜያዊነት ያለውና ከአሁኑ  የተሻለ ስርዓት ሲሰፍን ሊለወጥ እንደሚችል እርግጠኛ ነኝ።”የራባት ድመት ልጇን ትበላለች” እንደሚባለው ችግርና ተስፋ መቁረጥ የሰውን ልጅ ጸባይ ወደ አውሬነቱ እንደሚለውጠው በታሪክ ታይቷል፤ በአገራችንም እያዬነው ነው።ለዛም ነው ያገራችን ሰው ክፉ ቀን አታምጣ! የሚለው።ይህንን ክፉ ቀንና  ባህል ለመለወጥ ምክንያትና ምንጭ የሆነውን ሰው ጠሌ ጎሰኝነትንና እራስ ወዳድነትን  ካጠፋን፣ክልል የተባለን እስርቤት ካሶገድን ፣ በህብረት ድህነትንና ዃላቀርነትን እናጠፋለን፤ወደ ነበርንበት ሰብአዊነትና ኢትዮጵያዊነት ለመመለስ ከቆረጥን የሚያግደን የለም።ያንን ለመቀዳጀት ጥቂቶች የሚያደርጉት ትግል ግቡን እንዲመታ መተባበር ይኖርብናል።አገር የጥቂቶች ብቻ አይደለችም፤እያንዳንዱን ዜጋ ይመለከተዋል። ይህንንም ዓላማ በማድረግ ወደ አገር ቤት ይዤ ሄድኩትን የኢትዮጵያ ክፍላተ ሀገር ህብረትን  ተልእኮ በተግባር ለመግለጽ ሞክሬአለሁ።

አገራችንን ከመበታተን ስጋትና አደጋ  ላይ የጣላትን የጎሳ ፖለቲካና በዚያው እምነት ቋንቋና ጎሳን መሰረት ያደረገው የክልል አወቃቀር ተወግዶ፤ዴሞክራሲያዊና ዘመናዊ በሆነ የክፍላተሃገር አስተዳደርና ፌዴራላዊ አወቃቀር እንዲተካ ከሕዝቡና ከአገር አቀፍ(በጎሳ ካልተደራጁት )የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለመመካከር ችያለሁ። ስኬታማ ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።ከዚያም በተረፈ የፖለቲካ ድርጅት ከሲቪክ ድርጅት፣የሲቪክ ድርጅትም ከፖለቲካ ድርጅት ተነጥሎ መሄድ እንደማይችል በመገንዘብ በተለይም አገር የማዳኑ ትግል ቅድሚያ መሆን ስለሚገባውና የሁሉንም ተሳትፎ ስለሚጠይቅ በጋራ አገራዊ የትግግዝ መድረክ(National Solidarity Forum)ለማቋቋም ተችሏል። 

የተበታተነው የአንድነት ሃይል የተባለውን ጎራ በማሰባሰቡ ተግባር ላይ ተሰማርቼ ከ22 የአገር አቀፍ ፓርቲዎች መካከል 18 ተሳትፈው የአንድነት የቃል ኪዳን ሰነድ ባቋቋሙት ኮሚቴ በኩል ተፈራርመዋል።የቀሩትም እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።ከትልልቅ የሙያና የህብረተሰብ የሲቪክ ተቋማት ጋር በመነጋገር የመድረኩ አካል ለመሆን ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን ሌሎቹም የመድረኩ አባል እንዲሆኑ ውይይቱ ቀጥሏል።ትግሉ አገራዊ መንፈስ የተላበሰ እንዲሆን የሚደረገው ጥረት በብዙዎቹ በኩል ድጋፍና ተቀባይነት እያገኘ መጥቷል።በአንጻሩ የአንድነት ሃይሉን መሰባሰብ የማይወዱትና የሚፈሩት  ሃይሎች የመበታተኛ መርዛቸውን ከመርጨት እንደማይቆጠቡ ስለታመነበት መከላከያ ዘዴም አብሮ ታስቧል።  

የብሔራዊው የትግግዝ(የትብብር) መድረክ (National Solidarity Forum)መመሪያና ዓላማ
1 ከሁሉም በፊት አደጋ ውስጥ የምትገኘዋን ኢትዮጵያ አገራችንን ተባብረን ህልውናዋንና አንድነቷን ለማስከበር፣

2 የጋራና ሕገመንግሥታዊ ስርዓት እንዲመሰረት አብሮ ለመታገል፣
3 በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን ሕዝቡ በእኩልነት ተጠቃሚ የሚሆንበትን መርሃግብር ወይም ፍኖተካርታ ለመንደፍ፣

4 የጋራ ዕቅድ በማውጣት በኢትዮጵያዊነት ካስማ ላይ የቆመ ስርዓት ለመመስረት፣በተናጠል የሚደረገውን ትግል ለማቀናጀትና ለማስተሳሰር፣የሕግ የበላይነትና የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲሰፍን፣የሰብአዊነትና የዜግነት መብት እንዲከበር ከሚታገሉ ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ከአገር አቀፍ የፖለቲካ ድርጅቶችና የሲቪክ ማህበራት የተውጣጣ አንድ የጋራ ብሔራዊ የትግግዝ መድረክ(National Solidarity Forum)ለመፍጠር፣

5 የአንድነቱን  ጎራ የሚያጠናክርና የሚያስተባብር የጋራ ዓላማ በመንደፍ የጎሳ ፖለቲከኞች ጎራ ብቸኛ ሃይል ሆኖ እንዳይወጣ እስከመጨረሻው ለመታገል፣
6 ቋንቋንና ጎሳን መሰረት ያደረገው የክልል አወቃቀርና አስተዳደር ሕዝብን ከፋፍሎ የሚያጫርስና የሚያፈናቅል፣የአገርን አንድነት የሚያናጋ ስለሆነ በተሻሻለና ዴሞክራሲያዊ ይዘት ባለው የክፍላተ ሃገር አወቃቀር ቢተካ ለሰላሙ፣ለአብሮነቱና ለአገራዊ ዕድገቱ ዋስትና እንደሚሰጥ በማመን ተግባራዊ ለማድረግ፣

7 በየክልሉ በግልጽና በሚስጥር፣በቡድንና መንግሥታዊ አካል በስፋት የሚካሄደውን የሰው ልጅ በጎሳ ማንነቱ እየተፈረጀ መበደሉንና መፈናቀሉን፣ሰብአዊ መብቱን መገፈፉን በመቃወም ይህ ሁኔታ ካልተቀየረ በአፍሪካ ቀንድና በአካባቢው ሊፈጥር የሚችለውን ቀውስና አለመረጋጋት ለዓለም ህብረተሰብ ለማሳወቅና ለማጋለጥ፣ለተበደሉትም ድጋፍ ለማሰባሰብ፣ድርጊቱን የፈጸሙት ለሕግ እንዲቀርቡ ለማድረግ፣

8 ሕዝቡ እምነትና ተስፋ ጥሎበት የነበረው የለውጥ ጅማሮ መዋቅራዊ ባለመሆኑና በነበረው ስርዓት ቢሮክራሲ(ማሽነሪ)የሚንቀሳቀስ በመሆኑ አቅጣጫውን የመሳት አዝማሚያ ይታይበታል።ለመጨናገፍም ያለው ዕድል ከፍተኛ ነው።ያንን አደጋ ተከላክሎ ከጥገና ለውጥና ከጎሳ መተካካት አውጥቶ ወደ መሰረታዊ ለውጥ የሚሸጋገርበትን መንገድ ቀይሶ ሕዝቡ እንዲነቃና እንዲደራጅ የሚረዱ ሥራዎችን ለመሥራት፣

9 በአገራችን ላይ የሚታዬውን የፖለቲካ፣የኤኮኖሚና የማህበረሰብ ችግሮች ለመፍታት በሚያስችለው ተግባር ላይ ለመሳተፍ፣
10 የሕዝቡን ስጋትና ጭንቀት፣የኑሮ ውድነት ለማቃለል ከሚጥሩ ሃይሎች ጋር ለመተባበር
  
ከመሰናበቴ በፊት የመቃብር ቦታ ትዝብቴን ላካፍላችሁ።
ባለፉት ዓመታት ብዙ የቤተሰብ አባላትን በሞት አጥቻለሁ፤በእርቀት መርዶ ከመስማቴ በላይ በቅርበት ታመው ለመጠዬቅና ሲሞቱም አፈር ለማልበስ አልታደልኩም።ታዲያ በአሁኑ ጉዞዬ ቢያንስ የተቀበሩበትን ቦታ ማዬትና እርሜን ማውጣት ስለነበረብኝ ወደመቃብር ቦታው ሄድኩ።የአገራችን የመቃብር ቦታ ምንም አይነት መለያ ቁጥርም ሆነ ምልክት የለውም።የዘመዶቼን መቃብር ለማግኘት ብዙ ተንከራተትኩ፣ያለኝ መንገድ ስም እያነበቡ መፈለግ ነው።በዚያ ሂደት የተገነዘብኩት ቢኖር በዚያ የመቃብር ቦታ ላይ  ሃጎስ፣ረጋሳ፣ከበደ፣ሌሊሾ፣ኦባንግ፣ወልዴ፣ዓለሚቱ፣አሰለፈች፣ጌጤ፣አብረኸት … ወዘተ በሚሉ የተለያዩ  ስሞችን በተሸከሙ ሰሌዳዎች ስር  የተለያዩ ጎሳ ተወላጆች ጎን ለጎን ተቀብረው መሬትና አፈር ሆነው ማዬቴ ነው።።ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ”በህይወት ስንኖር ኢትዮጵያውያን ስንሞት ኢትዮጵያን እንሆናለን“ያሉት አባባል ትዝ አለኝና ተገረምኩ።እነዚያ የተለያዬ ጎሳ ተወላጆች በጎሳ ሳይለያዩ፣ በሞት ሰልፍ ተደርድረው፣አንዱ ሌላውን ከጎንህ አልቀበርም ብሎ  መቃብር ሳይገለብጥ ሁሉም  ያገራቸውን አፈር ተቀላቅለዋል።ካለምንም የሙታን ጭቅጭቅ በጸጥተኛው ዘለዓለማዊ  ሰፈር አርፈው ሲታዩ ከሙታን  እሻላለሁ የሚለው በላያቸው ላይ የሚኖረው የአንድ አገር ዜጋ በጎሳ ማንነት እርስ በርሱ ሲባላ፣ሲጋደል፣አንዱ ሌላውን በመጥላት በማፈናቀል ተግባር ላይ መሰለፉን ሳስብ ምን ያህል ከሞቱት በታች የቁም ሞት መሆኑን የተረዳሁበት መልካም አጋጣሚ ነበር።አገር(መሬት) ሁላችንንም አስተናግዳ ጥለናት የምንሄድና መልሰንም አፈሯን መሆናችን የማይቀር የጋራ የተፈጥሮ መዳረሻችን መሆኑን ከሙታኑ የመጨረሻው ምንነት ልንማር እንችላለን።እነዚህ ሙታን  በጎረቤትና በዘመድ አዝማድ በኖሩባት አገር መሬት ለመቀበር ችለዋል።ሌላው ቀርቶ ቀባሪና የመቃብር ቦታም ለማግኘት አገርና ሕዝብ መኖር እንዳለበት መረዳት አለብን።
   
ኢትዮጵያን ለማዳን ሁላችንም እንተባበር!
ጎሰኝነት የዃላቀርነት መግለጫ፣ ለወራሪዎችም የመግቢያ ቀዳዳ ነው!!
ኢትዮጵያ  በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!! 
አገሬ አዲስ