Wednesday, September 19, 2018

መልስ ለፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay ድረገጽ አዘጋጅ) ታርሞ እንደገና የተለጠፈ ትችት


መልስ ለፕሮፌሰር ጌታቸው ይሌ
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay ድረገጽ አዘጋጅ)

ታርሞ እንደገና የተለጠፈ ትችት

የተከበሩ ፕሮፌሰር ሆይ!
ለእርስዎ ያለኝ አክብሮት ዛሬም የተቀነሰ ስላልሆነ አክብሮቴ እንዳለ ሆኖ ቅር የተሰኘሁበዎትን ትችትዎትን ለመተቸት እፈልጋለሁ። በቅርቡ የሰሞኑ ሁኔታ” በሚል የተቹበትን ሁኔታ አንብቤ እጅግ ካዘንኩበዎት አንዱ ይኼኛው የከፋው ነው።አለፍ እያልኩ ካልሆነ እንደው ልጥቀስ ካልኩኝ አንጀቴ ስለሚቃጠል ጥቂቶቹን እምነትዎን ብቻ ልጥቀስ። “ዶክተር ዐቢይ አሕመድ” በሚል ንዑስ ርዕስ ውስጥ እንዲህ ያሉትን ሃሳብዎ ልጥቀስ፡-

“ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በቅርብ ጊዜ በባንዲራው ምክንያት ስለተነሣው ብጥብጥ የተናገረው ብዙዎችን አስቈጥቷል። ይኸ ብቻ አይደለም፤ የኢሕአዴጉ መሪ የኢሕአዴግን ባንዲራ ሲያውለበልብ ሲያዩም የሚገረሙ አሉ።እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያ ባንዲራ በመንግሥት ደረጃ 1964 . . ጀምሮ ሁለት ጊዜ እንደተለወጠ ልብ አላሉትም።” ብለዋል።

የወያኔው ፋሺስት እና አሁን ያለው ‘የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ያልቻለ የራስዎ ጠ/ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ቡድን ፤ እያውለበልቡት እና እያከበሩት የሚታየው ሰንደቃላማ ሕጋዊ ነው ብለን አልተቀበልነውም። ትክክለኛ የመገለጫ ቃል “ኢሕጋዊ” ነው። ትናንትም ዛሬም ለወደፊቱም ሕጋዊነቱን አንቀበለውም (በግልጽ አነጋጋር ኢሕጋዊ ነው)። ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑ ቡድኖች የቀረጹት ሰንደቃላማ “የአገሪቱን እሴቶች ለማፍረስ የታገሉ እና በተግባርም ጣሊያን ያቀዳቸው ፖሊሲዎችን የተገበሩ ስለሆኑ ሰንደቃላማን በሚመለከት የወስደዋቸው እርምጃዎች “በሙሉ“ ጸረ ኢትዮጵያ ስለሆነ ሕጋዊነቱን እርስዎ እና የሚጋሩዎትን ቡድኖች ካልሆነ በስተቀር በኔ በኩል ሕጋዊ አይደለም።

ሰንደቃላማ ለዋጩ ባንዳው መለስ ዜናዊ ‘ለሰንደቃላማው መለወጥ ምክንያት ሲገልጽ’ ከሰንደቃላማው በስተጀርባ በመቃወም ነው’ ብሎ ነግሮናል። በስተጀርባ ያለው ማን ነው? የሚለው እራሱ ሲነግርን “አማራ፤ኢትዮጵያ እና ኦርቶዶክስ”። የፓርላማው አጽዳቂዎችም እነዚህ በስተጀርባ የተባሉትን ክፍሎች እየጠቀሱ የተናገሩዋቸውን ንግግሮች በሙሉ በ ‘ዩ ቱቡ’ በተንቀሳቃሽ ምስል እና በድምጽ ተቀርጾ እየታየ ነው። ፋሺስቶቹ የነዚህ ሦስት ክፍሎች መብት እና ሕግ በመጣስ የተሰራ ሰንደቀላማ ስለሆነ ሕጋዊ አይደለም።

ሥርዓቱ ፋሺሰት ነው። ስለሆነም ሕግ አልባ ቡድኖች የተሰባሰቡበት ፋሺሰቶች ከጫካ ትግላቸው ይዘውልን የመጡዋቸውን በርካታ “ባንዴራዎቻቸውም ሆኑ” አርስዎ ሕጋዊ ነው እና “ቅር አትሰኙ” እያሉን ያሉትን የሰይጣን አምላኪዎች ምልክት የተጨመረበት ባለ ሰማያዊ ኮከብ ባንዴራ የኛ ስላልሆነ “ጸረ ሕግ” ነው። እርስዎ እንደሚሉት በትክክል ከተረዳሁዎት ‘ካሁን በፊት ሁለቴ ተለውጧል እና የወያኔ ፋሺሰት ባንዴራም ሆነ (አገር ለመገንጠል የተነሱትን የተለያየ ስም ያላቸው የኦሮሞ ቡድኖች እና ኦጋዴኖችም ሌሎችም ባንዴራዎች ቢውለበለቡ አይክፋችሁ የሚሉም ይመስላሉ) በአፓርታይድ ምስል የተዋቀሩ የክልል ባንዴራዎችም ሆነ ዋናው ሰንደቃላማ ሕጋዊ ነው የሚሉትን አስተያየትዎንም ከታች ስሕተትዎን በዝርዝር አቀርባለሁ።

የአገሪቱ ሰንደቃላማ እርስዎ እንደሚሉት ከ64 ዓ.ም ጀምሮ ሁለቴ መለወጡ ልብ ያላልንበት ምክንያት እርስዎ በነበሩበት ከተማ/አካባቢ ምን እንደተውለበለበ አላውቅም እንጂ በየክፍለሃገራቱ አደባባይ እና መንግሥታዊ መ/ቤቶች ሲውልበለብ የነበረው “ሌጣው” ሰንደቃላማችን ነበር። እኔ የማውቀው ጦር በሙሉ ከምስራቅ ወደ ሰሜን ጦር ግምባር ሲመጣ ሲያውለበልበው የነበረው ያንኑ ሌጣ እንደነበር የአይን ምስክር ነኝ። አልጌና ናቅፋ ምፅዋ፤ከረን አስመራመቀሌተምቤን ሸራሮማይጨው…..ወዘተ..ወዘተ.. ሠራዊቱ በመሸገባቸው ሥፍራዎች ሁሉ (እርስዎ የት እንደነበሩ አላውቅም እንጂ) ስትውለበለብ የነበረቺው ይህቺው ከላይ የለጠፍኩዋት በግልጽ የምትታየው መትረየስ አፈሙዝ ላይ ተሰቅላ ወደ ጠላት ያነጣጠረቺው ውቢቱ “ሰንደቃላማችን” ነች። ይህች ጦሩ ጠላትን ድል በነሳበት ወቅት ሁሉ አስቀድሞ የሚተክላት ሰንደቅ ይህቺው ሰንደቅ አላማ ነች። ሌላ አይቼ አላውቅም።ያለ እርስዋ ሌላ ጨርቅ ስመለከት ሰውነቴ ሁሉ በቁጣ ተወርሮ  በመከፋት “ኪፍ” ይላል። የኦነጎች እና የሻዕቢያዎች ምንጣፍ አንጣፊው ‘ተቃዋሚ ተብየው” ከሰንደቃላማችን ጋር የነሱን ባንዴራ ደባልቆ አዳራሽ ሲቀመጥም ሆነ ስብሰባ እና ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርግ ስመለከታቸውም ሆነ ባንዴራዎቻቸውን ከታቀፉ “ባንዳዎች’ ጋር ተቃቅፈው ፎቶ ሲነሱም ሆነ ፊታቸው በእነሱ ባንዴራ ቀለም አቅልመው ስመለክት ሰውነቴ ሁሉ በቁጣ እና በሓዘን ይነዝረኛል። እስከዚህ ድረስ ያጎለበትዋቸው የኛ የምንላቸው ምንጣፍ አንጣፊዎቻቸው ናቸው እና ክፉኛ እቃወማቸዋለሁ።

 ዛሬ እርስዎም በማልጠብቀው ሁኔታ ከነሱ ጋር ተደምረዋል። ለነገሩ ስለ መደመር ሲወሳ የርስዎ ነገር አዲስ አይደለም። ግንቦት 7 አስመራ ሲንሸራሸር “ደግፍዋቸው ወይንም አፋችሁ ዘግታችሁ እቤታችሁ ተቀመጡ” ብለውናል። ግንቦት 7 ሰው ሲያስረሽን፤ ሲያስገርፍ፤ ሲያስር፤ ተጎጂዎች/ሰለባዎቹ/ “እርይ እያሉ ሲያለቅሱ ስለ እኛ ተናገሩልን ሲሉን” አርስዎ እና ኢሳት የተባለው የግንቦት 7 አፈቀላጤ እና ጋዜጠኛ ካድሬዎቹ ጭምር “ዝም ብላችሁ እረፉ” ስትሉን ነበር። እነ ኤፍሬም ማዴቦ ኦክላንድ ከታማ እዚሁ አሜሪካ ሰንደቃላመናችንን እና አማረውን ነፍጠኛ እያለ ከሻዕቢያ ፌሰቲቫል ተገኝቶ አገራችን እና ሕዝባችንን ሲያዋርድ “ስለ ግንቦት 7 መሪዎች አትተንፍሱ፤ እቤታችሁ ተቀምጣችሁ አፋችሁን ዝጉ” እያሉን ነበር፡ (እርስዎ!!) ዛሬ ግንቦት 7 ውስጥ ተሰልፈው የነበሩት አባሎች ከኤርትራ ተሰናብተው አብይ ኑ ካላቸው በላ ‘ምን  ዓይነት ፍዳ እና ተንኮል’ ይሰራባቸው እንደነበረ ይፋ አድርገውልናል። ለሁሉም ጊዜ አለው!


ሰንደቃላማውም ቢሆን ከ1964 ዓ.ም ጀምሮ ሁለት ጊዜ እንደተለወጠ ልብ ባንለውም ቢሆን እርስዎ ባስተማሩበት ዩኒቨርሲቲ ተቁዋም ሲውለበል የነበረው ሰንደቅ ያዩት ምን እንደነበር ባለውቅም፤ ምንአልባትም የራስዎ የግል ጽ/ቤት ጠረጴዛዎ ላይ ሰንደቃላማ ከኖረም ያንኑ ሌጣ ሰንደቃላማ እንደነበር እገምታለሁ። ከተሳሳትኩኝ ይንገሩኝ፡ (በ1983 ዓ.ም እርስዎ አገር ውስጥ ባይኖሩም የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የዓለም ዋና ጸሐፊ የነበረው ግብጻዊው “ቡጥሮስ ቡጥሮስ” ጋሊ አዲስ አባባ መጥቶ በነበረበት ወቅት ኤርትራን እና የባሕር ወደባችንን በሚመለከት ለመቃወም ሰልፍ ሲወጡ፡ ይዘውት የወጡት ሰንደቃላማ ያንኑ ሕጋዊ እና ሌጣ ሰንደቃላማ እንጂ ሁለቴ ተለውጦ ነበር የሚሉት የተለየ ሰንደቅ የዘው አልወጡም (አሌፍ መጽሄት ያወጣውን የሰልፈኛው ሽፋን ይመልከቱ) በፎቶግራፍ የምትታየው ወጣት እና ሰንደቃላማ የተጻፈውን ሐተታ ያንብቡ ። 
እርስዎ ሁለቴ የሰንደቃላማ ለውጥ ተደርጓል እያሉ ያሉት የውስጥ አስተዳደር መሪዎች (ንጉሳዊ ዙፋን) ላይ ወይንም የቡዱኖቹ (የደርግ/የቡዱኑ/) የሰርዓት መርሆ ምልከቶች ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል፡ እንዲያም ሆኖ አስቀድሜ እንደገለጽኩት አደባባይ ላይ በሕዝብም ሆነ በመከላከያ ሃይላችን ሕሊና የተቀረጸው እና በየቀብሩ ስርዓትም ሆነ በየጦርነቱ ኮረብታዎች ሲውለበለብ የነበረው ያው የተከበረው ሌጣው ሰንደቃላማችን ነው።

በመቀጠል እንዲህ ይላሉ፦

“አደባባዩ ሌጣውን ባንዲራ እነሱ ስላውለበለቡት የሀገሩ ሕጋዊ ባንዲራ መስሏቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ከባለ ኮከቡ በቀር ማንኛውም ባንዲራ (ሌጣው ባንዲራ ሳይቀር) የኢትዮጵያ መንግሥት ሕጋዊ ባንዲራ አይደለም።” ብለዋል።

ባደባባይ የምናውለበልበው ሰንደቃላማችን ለእርስዎም ሆኑ ለኢሕአዴጎች/ወያኔዎች/ “ሕጋዊ ሰንደቃላማ አይደለም። ይህን እናውቃለን። ልዩነታችን እርስዎ “የኢትዮጵያ መንግሥት” እያሉ እየጠሩት ያለው የትግሬዎች ፋሺሰት ቡድን በመንግሥትነት መጥራት ከፈለጉ “የትግሬዎች መንግሥት ወይንም የፋሺስቶች መንግሥት” ብለው መጥራት እንጂ “የኢትዮጵያ መንግሥት አይደለም”። እርስዎም ካሁን በፊት አሁን ያለው መንግሥት ማለትም ወያኔዎችን በምን ባሕሪ ይገልጽዋቸው እንደነበር ከረሱት ላስታውሰዎት።

አንዷን ሐረግ ልጥቀስ።

“አዲሱን መንግሥት ያቋቋሙት ትግሬዎች ይባላሉ” (ኢትኦጵ መስከረም 4 ቀን 1998 ዓ.ም) ሲሉ አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት እያሉ በመጥራት እየተለማመዱበት ያለውን ቃል “የትግሬዎች መንግሥት እንጂ እርስዎ እየገለጹት ባለው ቃል “የኢትዮጵያ መንግሥት” አይደለም። ሌላ ቀርቶ እንኳን የወያኔ መንግሥት የመንግሥቱ ሰርዓትም የኢትዮጵያ መንግሥት አልተባለም። ሕዝቡ ሲጠራው የነበረው “የደርግ መንግሥት” በማለት ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያን ለመበተን በጎሳ/በቋንቋ ፖሊሲ ለማስተዳደር የመጣ ቡድን የኢትዮጵያ መንግሥት አይደለም።

ጠ/ሚኒስትር የተከበሩ አክሊሉ ሃብተወልድ (በንጉሡ ዘመን የነበሩ ደርግ የረሸናቸው) ለሕአፓው ጸጋየ ገብረመድህን /ደብተራው/ እንዲህ ብለው መክረውት እንደነበር “የትግራይ ሕዝብና የጥምክሕተኞች ሴራ ከትናንተ እስከ ዛሬ” ደራሲ የትግራይ ዘረኛው መምህር ገብረኪዳን ደስታ (1998) በጻፈው መጽሐፍ ገጽ 198 ውስጥ እንዲህ ይላል፡-

 “አደገኞች ናቸው ተብለን ከዩኒቨርሲቲው ከተባረሩት 45 ተማሪዎች አንዱ እኔ ነበርኩ። በዚህ ወቅት ጠ/ሚኒሰትሩ አክሊሉ ሃብተወልድ ተማሪ ጸጋዬ ገብረመድህንን /ደብተራው/ አስጠርተው “ትግሬዎች የአክሱምን መንግሥት እንደገና ለመመስረት እየታገሉ ነው ያሉት። እናንተ ደግሞ በማታውቁት ዓለማ እየነሱ ጀሌዎች ሆናችሁ አገራችሁን ለመናድ ተሰልፋችኋል” ብለው እንደመከሩት ለብርሃነ እያሱ በወቅቱ ነግሮታል።” ይላል።

 (ጸጋየ ማለት ጎጃሜው የኢሕአፓ መሪ የነበረው ነው። ኢሕአፓው ‘ብርሃነ እያሱ’ ማለትም መጀመሪያ ከማሕበር ገስገስቲ ትግራይ ሲነጋገር ነበር እየተባለ የሚታማ ኋላ ወደ ኢሕፓ የገባ አማራር ነው። (እሱም እንዲሁ የአጋሜ አውራጃ ‘ትግሬ’ ነው) ። ጠ/ሚኒሰትሩ ትግሬዎች እያሉ ያሉት ‘ኤርትራኖችን እና ትግሬዎቹ እነ ገብረኪዳን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲፈጥሩት የነበረው ጎሰኛ እንቅስቃሴ ለዛሬ ጥፋታችን ‘መነሻ’ የሆነው ‘የብሔር ማነሳሳትን’ ሲቀሰቅሱት የነበሩበትን  ዓላማ ወዴት እንደሚያመራ ሲያስጠነቅቁት ነው’። ዛሬ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ማስጠንቀቂያ እንደተነበዩት ሆኖ ‘ትግራይ ትግርኚውንም/በአይሁዳውያን እስራኤሎች እየተደገፈ ያለው “የአጋአዚያን እንቅስቃሴ ዓላማ እና አርማ/ በዝግታ እየተጓዘ እያየነው ነው (ትግራይ ኦንላይን ድረገጽ የሚጻፉትንም ሆነ መቀሌ ውስጥ በሚደረጉ ስብሰባዎች የሚሰነዘሩትን ቃላቶችንም ልብ በሉ)። እርስዎ ኢትዮጵያ መንግሥት እያሉ ያሉት አክሊሉ ሃብቴም ሆኑ እርስዎ ካሁን በፊት የትግሬዎች መንግሥት ሲሉት የነበረውን ስለሆነ ዛሬም “የትግሬዎች መንግሥት እንጂ ‘የኢትዮጵያ መንግሥት’ አይደለም። በሰንደቃላማችን ላይ የቀረጸልን የሰይጣን አምላኪዎች ኮከብ ምልክትም ሕጋዊነቱን አንቀበለውም! ያ ባንዴራ ትግሬዎች ሕጋዊ ነው ቢሉ ያምርባቸዋል። እነሱ ያመጡት እና የሚያመልኩት ስለሆነ። በእርስዎ ግን አያምርም። 
  
በመቀጠልም እንዲህ ብለዋል፡-

 “ራሱ ዶክተር ዐቢይና ባንዲራው ከሕገ መንግሥቱ ጋራ የኢሕአዴግ ወገኖች ናቸው።” ብለዋል።

ልክ ነው፡ በዚህ እስማማለሁ። ኢሕዴግን የመሰረቱት ደግሞ ትግሬዎች ናቸው። ስለሆነም የትግሬዎች መንግሥት ነው። አሁንም ትግሬዎች ከሥርዓቱ ውስጥ አሉ። ከፈለጉ (ጊዜ እየጠበቁ ነው እንጂ -የወያኔዎች ባሕሪ እንደዚያ ስለሆነ) የገነቡትን ኢሕአዴግ የማፍረስ ጉልበት አላቸው (ያፈርሱታልም)። መንግሥት የመሆን ዕድል ግን የላቸውም።

ይቀጥሉ እና፤-

የኢሕአዴግን ሕገ መንግሥት መጣስና የኢሕአዴግን ባንዲራ አለመቀበል ዶክተር ዐቢይን አለመቀበል ነው።”

 የሚለው እያነበብኩት ሳነብብ እውን ከእርስዎ የተጻፈ ነው? ብያለሁ። እንዴት ረሱት? የታገልነው እኮ የፋሺስቶችን አፓርታይዱን ሕገመንግሥቱን እና አርማዎቹን ከነስንደቃላማዎቹ ጭምር እንድንጥስ እኮ ነው ለ27 አመት የታገልነው? እርስዎ ማንን ሲታገሉ እንደቆዩ እናውቃለን። እንደተቀረነው ወያኔ ነበር ሲቃወሙ የነበረው። እኔም ሆነኩኝ እርስዎም ሆነ ሚሊዮኖች ዜጎች የታገልነው፤ መጽሐፍት የጻፍነው ‘ሕገመንግሥቱ አፓርታይድ” ስለሆነ መጣስ ብቻ ሳይሆን መነቀል እንዳለበት ነው የታገልነው። አብይ የፋሺስቶች ሕገመንግሥት አስፈጻሚና ፈጻሚ ኮለኔል ነበር። እንዲሁም ወያኔዎች በጫካ የስለላ አሰራራቸው ሲገለገሉበት የነበረው የስለላው አሰራር ዘመናዊ በሆነው የስለላው መረብ እንዲጠቀሙ መሃንዲስ ሆኖ የቀየሰው እራሱ አብይ እንደሆነ በሚዲያ ይፋ ሆኗል። ስለዚህ የፋሺስቶችን ባንዴራ አለመቀበል እና የፋሺስቶችን ሕገመንግሥት አንቀበልም ለሚሉ ሁሉ አብይን መቃወም ነው ሲሉ አብይ “የፋሺስቶችን ሕገመንግሥትን እና ባንዴራውን” አስከባሪ እና አስፈጻሚ ከሆነ አብይ ፋሺስት ስለሆነ ሕዝቡ መደገፍ ሳይሆን መቃወም ነው ያለበት።

የቡራዩ ዕልቂት ከተከሰተ ወዲህ ማለትም ከሁለት ቀን በፊት ንግግሩ ሁሉ ‘ኦሮሚያዊ’ የሆነ ትምክሕት ሲናገር አድምጠናል። የዓድዋን ጦርነት ድል አድራጊዎች እና አሸናፊዎቹ ኦሮሞዎቸች እንደነበሩ ለወገኖቹ ሰጥቶአቸዋል (እባካችሁ ፈግግ እንዳትሉ)፤ የአማራ ራስ በገጀራ እየቀነጠሰ ለሚያስረክበው ሰው ገንዘብ ሲሸልም የነበረው ጸረ አማራ እና የታወቀው “ባርያ ሸያጭ እና ለዋጩ” አብይ ተወለዶበታል የተባለው ክ/ሃገር ገዢ (ንጉሥ) የነበረው የጅማው “አባጅፋርን” እንደ ሰብአዊነት እና ታላቅ አገር ወዳድ እንደነበር አድርጎ ሲሰብከን አድምጠናል። “አሮሞ ሁሌም አሸናፊ” (ኦምኒፖተንስ) እንጂ ተሸናፊ እናዳልሆነ ሲቀባጥር አድምጠናል። (ኢትዮጵያ ውስጥ 3/4ኘኛውን አፓርታይድ መሬት ስላልበቃቸው የኦሮሞዎችን ሄጂመኒ በአፍሪካ አገሮች ላይም እንዲስፋፋ የቃጣውም ይመስላል)። በትምክሕት ያደጉ ሕሊናዎች ታጥበው አይጠሩም የምለውም ለዚህ ነው። ለ27 አመት በጎሳ ፖለቲካ የታጠቡ ሕሊናዎች የትምክሕት ገደቡ የት ድረስ እንደተዘረጋ እርከኑን አያውቁትም። ትምክሕታቸውን ማቆምን አያውቁም። አሸናፊዎች ውግያ ሰሪዎች አገር መስራቾች ኦሮሞ አሸናፊ እንጂ ገዳይ አይደለም እያለ ፤ ኦሮሞ ሌላውን ሕዝብ ያልጨፈጨ ከወንጀል ከግድያ ነጻ የሆንን እኛ ኦሮሞዎች ነን ይላል። ያለ እኛ /ኦሮሞዎች/ ሰው እና አገር እራሱን ቆሞ መኖር እንደማይችል እና አገር ሆኖ እንደማያውቅ ፤ግን አገር የመሰረቱት ኦሮሞዎች ናቸው …. እያለ …. ሁሉንም በእኛ እኛ እኛ የሚታጀቡ የታወቁበት ንግግሮቻቸው እሱም ያንኑ ባሕሪ ደግሞታል!! ፋሺስቶች እና ጎሰኞች ሲመኩ መነሻቸው “እኛ አሸናፊዎች፤ የሁሉም ነገር መስራቾች” የሚለው ነው። የነጸጋየ አራርሳ እና የነ ዳውድ የነ ሌንጮ የነ ጃዋር … ፍልስፍና ከዚህ ከአብይ አሕመድ “እኛ እኛ” ትምክሕት የሚለይ አይደለም።

ስለዚህኛው በልዩ ርዕስ እመለስበታለሁ። አብይን የምንቃወምበት ምክንያት ብዙ ነው። ኦነግ ኦነግ የሚሸተው ጎሰኛ ትምክሕታዊ ንግግሩ አማራን በሚመለከት ጥያቄና አማራን በሚመለከት ሲያደምጥ የሚሰጠው መልስ እና ጥያቄ ሲቀርብለት የሚሸሽበት መንገድ ከዚሁ የተነሳ ባሕሪው ነው። ብታምኑም ባታምኑም ‘ዓብይ” ገና የወያኔ ተማሪነቱን ሙሉ በሙሉ አልተላቀቀም። ለማ እንኻ እራሱ የቡራዩን ዕልቂት በ አንድ 16 አመት ሕጻን ልጅ ምክንያት በተነሳው ጠብ/ንትርክ የተከሰተ ሁከት ነው ሲል ተናግሯል። የጎሳ ፖለቲካ የቀመሰ ታጥቦ አይጠራም። አርስዎ አብይ የሚያስተዳድረው ስርዓት ‘ሕአዴግ’ የሚል ስም ነው ቢሉም በእዛው ስም ‘ቢቀባም’ ዞሮ ዞሮ “የትግሬዎች መንግሥት” ነው። አሁንም መዘውሩ ትግሬዎች በወሳኝ ቦታ ላይ ስላሉ አብይ አሕመድ “ታላቁ መሪ እያለ በጀግንነት የሚጠራው መለስ ዜናዊን ለምን እንደሆነ ግልጽ ነው!! እነ ‘ሞንጀሪኖ’ እነ ‘ደብረጽዮን’…እነ…… አሁንም ስርዓቱ ላይ ናቸው እርስዎ እንዳሉት ራሱ ዶክተር ዐቢይና ባንዲራው ከሕገ መንግሥቱ ጋራ የኢሕአዴግ ወገኖች ናቸው።” ትክክል!

መንግሥት እለውጣለሁ ግን የናዚን ሕገመንግሥት እና የናዚ ምልክቶችን መቀበል አለባችሁ፤ ካላከበራችሁ ግን ጸረ “አዲሱ ለውጥ” ናችሁ ብሎ ነገር ለኔ አይገባኝም። ሕገ መንግሥት ተብየው እኮ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦች የሚባሉ ቡድኖችን ነው ኢትዮጵያን ባለቤት ያደረገው እንጂ ዜጎች እንደ ዜግነታችን እኮ “ባለቤትነት/ዜግነት/የላችሁም” ብሎ ዜግነታችን እና ባለቤትነታችንን ሰርዞናል። ዜግነት የለኝም ከብዙ ጎሳ የተወለድኩ ነኝ እና “ምረጥ ብላችሁ አታስገድዱኝ” ፤ ምርጫ ከሆነ ግን ብሔሬ ‘ኢትዮጵያዊ’ ነኝ ለሚሉ ዜጎች ሁሉ የደረሰው ፍዳ እናውቃዋለን። ብሔርዬ ኢትዮጵያዊ ነኝ ለሚሉ ዜጎች የድሮው የወያኔ አሽከር የዛሬው ‘የግንቦት 7 ቱ መሪ ‘አንዳርጋቸው ጽጌ’ ከወያኔዎች ጋር እየተሞዳሞደ ‘መጽሐፍ ጽፎ’ ሙልጭ አድርጎ ስብዕናቸው እየገፈፈ ሲያሸማቅቃቸው እንደነበር ይታወቃል(ምሳሌ-ለመስጠት)።እንዴት ታድያ ዛሬ ከነዚህ ብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦች ከሚባሉ ቡድኖች ውጭ የሆናችሁ ሁሉ ባለቤትነታችሁ/ኢትዮጵያዊነታችሁን/ አናወቅም ብሎ በሕግ ያጸደቀ የፋሺስቶች እና የጎሳ ባለቤትነት የሚቀበል ሕገ መንግሥትን አለመቀበል አብይን መቃወም ነው ብለው ሊሉ ቻሉ? 

አለፍ ብለውም እንዲህ ብለዋል፤-

“የዶክተር ዐቢይን አመራር ተቀብሎ፥ የኢሕአዴግን ሥርዓት አለመቀበል፥ከመረቁ አውጡልኝ ከሥጋው ጦመኛ ነኝማለት ይሆናል።” ይላሉ፡-

 ትግሬዎች እንዲህ ያለ ግራ የገባ አነጋጋር ሲገጥመን “ናበይ ናብይ እዩ ነገሩ?” እንላለን። ወዴት ወዴት ነው ነገሩ? አብይም ሆነ ለማ ለመለወጥ የፈለጉት ለኔ ለጌታቸው ረዳ ብለው ሳይሆን ለራሳቸው እና ለልጆቻቸውም ደህንነት እና የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው ሲሉ ነው። የእርስዎ ጠ.ሚኒሰትር አብይ ፓርላማው ውስጥ የተናገረውን እንዴት ረሱት? እንደ እርስዎ “ሕገ መንግሥት ተጣሰ! ሕገ መንግሥት ይከበር! ሕገ መንግሥቱን አልተቀበሉመ! ሽብርተኞች ናቸው መፈታት የለባቸውም ወዘተ.. ስትል የነበረቺው በፓርላማው ውስጥ የወያኔዋን ደንቆሮ ላቀረበችለት ጥያቄ ሲመልስ “ሕዝቡን አገሪቱን በድለናል ሁላችንን ሰብስቦ እስር ቤት ቢያስገባንስ ምን እንጠቀማለን?” ሲል ነበር የመለሰላት፡ አይደለም እንዴ? አብይ ሁኔታው ወዴት ያመራ እንደነበር አውቋል። ስለዚህ ለራሱም ጭምር እንጂ ለኔ ሲል አይደለም መለወጥ የፈለገው። ካልተለወጠ አንድ ቀን ሕግ ፊት መቅረቡ አይቀርም።ምናልባትም ባለቤቱ እና ልጆቹን ወደ አሜሪካ እንዲጠለሉ ያደረገበትም ምክንያት ያ ስጋት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ዛሬም በሕግ የሚያስጠይቀው ክሶች አሉት። እሱን ከእርስዎ ጋር አልከራከርም።

“የዶክተር ዐቢይን አመራር ተቀብሎ ፥ የኢሕአዴግን ሥርዓት አለመቀበል፥ከመረቁ አውጡልኝ ከሥጋው ጦመኛ ነኝማለት ይሆናል።” የሚሉት አነጋገር ሕገ መንግሥቱም ሆነ ስርዓቱ እና የሥርዓቱ የዜና ማሰራጫዎቹ የመለስ ዜናዊ የሙት ቀን የሚያከብር “ታላቁ ባንዳን” ጀግና እና ወርቅ መሪ እያለ የሚያወድስ የፓርላማ አባል ፥ የዜና ማሰራጫ እና ሕገመንግሥት(ስርዓት) ወይንም መሪ ለኔ መረቁንም ሥጋውንም ቢደፋ ደንታ አይሰጠኝም። መለስ ዜናዊን እኮ ነው ወርቅ እና ጀግና ብሎ ያሞካሸ መሪ ነው! ኤርትራን ለማስገንጠል ናቅፋ እና ምጽዋ ድረስ ሄደው የኢትዖጵያን ሠራዊት በጥይት የቆሉ የትግሬ ተዋጊዎችን እኮ ነው ‘በጀግንነት” ሲጠራቸው የነበረው። በአገር ክሕደት መከሰስ ያለባቸውን የባንዳ ቡድን ተዋጊዎችን እኮ ነው እንዲህ ያቆላመጣቸው! (ለነገሩ ወንደሞቼም፤ዘመዶቼም እኮ ከነሱ ሥር ተሰልፈው በዚህ ባንዳዊ ስራ ተካፍለዋል፤ቆስለዋል።) እንዴት ነው ነገሩ?

ከሦስት ቀን በፊት አሸዋ ሜዳቡራዩ ከፋ እና አስኮ…. እንዲሁም ጅጅጋ፥ጉምዝ፥አርሲ፥ወለጋ፥ጂማ..ባሌ….በየክልሉ የተቃጠሉ ቤተክርስትያኖችንም ሆኑ የጠፉ የተደበደቡ፥የታረዱ ነብሳት ሁሉ “መረቁንም ሥጋውንም መቅመስ አይፈልጉም”። ለነሱ መረቁም ሥጋውም መርዝ ሆኖ ከዚህ ዓለም አጥፍቶአቸዋል። እነዚህ ተቋማት እና ነብሳት መከላከል ያልቻለ መሪ እና የቡደኑ አባሎች “መረቁንም ሆነ ሥጋቸው” ይዘው እስር ቤት ቢገቡ እርስዎ እንጂ ‘ሙታኖቹ’ አይቃወሙትም። በጠራራ ጸሐይ ሴቶች ሲደፈሩ? አዛውንቶች እና ህጻናት ሲደፈሩ? ምን የሚሉት መሪ እና “ሕገ መንግሥቱ አይጣስ” ብለው ነው እየመከሩን የሚገኙት? ለነገሩ እንጂ “አቻምየለህ ታምሩ” በትክክል እንዳስቀመጠው እኮ ሕገ መንግሥቱ “እየተገበረ” ስለሆነ እኮ ነው ይህ ሁሉ እልቂት እያየን ያለነው። ትክክል ብሎታል። ሕግ መንግሥቱ የዕልቂት ምንጭ ነው! እንዲህ ከሆነ መረቁም ሥጋውም ለራስዎ ቢያደርጉት ቅር አይለኝም። ለኔ ግን ከነሥጋው እና ከነመቀረቁ  (ወያኔንም ጨምሮ) እስር ቤት የሚያስገባልኝ ሃይል በግዚሃአብሔር ቢመጣልን ደስታውን አልችለውም።ይህ ጸሎት የኔ ብቻ ሳይሆን የሙታን ነብሳትን ሁሉ ነው። ክቡር መምህሬ ፕሮፌሰር በሙታኖች ዓይን እና በጋጠወጥ ጎሰኞች የተደፈሩ እመቤቶች እና ወጣት ልጃገረዶች ቤተሰቦች ዓይን መነጽር እየተመለከቱ እስኪ ይፍረዱት? እርስዎ ከነዚህ ተጠቂዎች መሃል ቢሆኑ ወይንም ቤተሰብ ቢኖረዎት ‘መረቁም ስጋወም ስለ ባንዴራውም ሕገመንግሥቱን’ መስማትና ማየት ይፈልጉ ነበር?   

አከታትለውም፤-

“ሌጣውን ባንዲራ ማውለብለብ ያሳስር ነበረ። ዶክተር ዐቢይአንድ ኢትዮጵያዊ የፈለገውን ባንዲራ ቢያውለበልብ፥ ያልፈለገውን ቢያቃጥል ሐሳብን በነፃ ከመናገር የተለየ አይደለምብሏል። በዲሞክራሲ የሚምል ሰው ይኸንን  አነጋገር  መቀበል  እንዴት ያቅተዋል?” ሲሉ  ሌለው አስገራሚው ትችትዎ የሚገርም ነው።

ሌጣው ባንዴራ እያውለበለበ ነው እኮ ወያኔ የባድሜ ጦርነት ያስኬደው። ባለ የሰይጣኑ ኮከብ ባንዴራ እኮ ከባድሜ በፊት በሽግግሩ ወቅት ነው የጸደቀው። ባድሜ ላይ ግን ከ100 አመት የትግሬዎች እና ኦሮሞዎች ፖቲካ ውሸት ወጥተው ኢትዮጵያ ታሪክ ወደ 3000 አመት እንደሆነ እነ መለስ እና እነ ስዩም ሲወሻክቱም ሆነ ለምን የቺን ሰንደቃላማ እንደተጠቀመ ያውቃል። ሕዝቡ ያችን ሰንደቅ ሲያይ ወደ እሳት ግባ ቢባል እንደሚገባ ፋሺስቶቹ ያውቁ ነበር። ስለሆነም ተጠቀመበት። (ዛሬም አብይም ያንን ስለሚያውቅ አውለብልቡ ብሎ ፈቀደላቸው። በዚህ እሱም “አገር ወዳድ ተብሎ” አውለብላቢዎችም የልባቸው አግኝተው ‘እኩል’ ተጠቀሙ።) በዘው ወቅትም ቢሆን ‘ሌጣውን ባንዴራ’ ማውለብለብ እርስዎ እንዳሉት ሳይሆን ማለትም ‘ሙሉ በሙሉ’ የሚያሳስር አልነበረም። ፓርላማ ውስጥ እና ሻለቃ አድማሴ እና ሌሎች አገር ወዳድ አርበኞች ሰንደቃላማውን የለወጠው መለስ ዜናዊን ሲቃወሙት በመቃወማቸው ለእሰር አልተዳረጉም። በሟቹ በክቡር ሃይሉ ሻውል ሲመራ የነበረው መኢአድ ስለ ሰንደቃላማው ጉዳይ ለማስከበር ፍርድ ቤት ሁሉ ክስ መስርተዋል። ክስ መመስረት ብቻ ሳይሆን መላዋን ኢትዮጵያ የሚያሳይ መልክኣ ምድር (ካርታ) እና ሌጣው ሰንደቃላማ በአደባባይ እናውለበልባለን ብለው በድፍርት ያውለበለቡ የገጠር ሰልፈኞች አልታሰሩም፦ ይህንን ሰላማዊ ሰልፍ/ ፎቶ/ ይመልከቱ፡
-ይህ ፎቶግራፍ ከ97 በኋላ  ነው የተነሳው። እስላመዊው ቡድን (ድመጻችን ይሰማ) ተሰላፊም ሲሰለፍ የግራኝ መሓመድ ቀለሞች የያዙ ቀለማት ነበር ይዞ ማውለብለብ የጀመረው። አውጭ አገር “ድምጻችን ይሰማ አባልትም ቢጫ ጨርቅ ነበር ሲያውለበልቤ የነበሩት”። ዛሬ ግን በሚያስመሰግን ሁኔታ ዋሺንግቶን ውስጥ እስላም ሴቶች ሕጃባቸው በሰንደቃላማችን ያጌጠ ልብስ ተሸፋፍነው አጊጠው፤አምሮባቸው ነበር ያየሁዋቸው። (በጣም ነው ያመሰገንኳቸውም ያደነቅኳቸውም። ያውም ሲያምርባቸው!!!!)።

 ሰማያዊ ፓርቲ የተባለው ከጸረ አማራዎቹ ከግንቦት 7 ከነ ኤፍሬም ማዴቦ ጋር ግንባር የፈጠረው “ሰማያዊ” የተባለው “ግልብ” ፓርቲም ሲያውለበልበው የነበረው ጨርቅ ሰማያዊ እና እመሃል ላይ ምስጢሩ የማይታወቅ ምልክት ያለበት ሰማያዊ ጨርቅ ሲያውለበልብ፤ ለሰንደቃላማቸው በድፍረት የቆሙት የመኢአድ አባሎች ግን ይህንን መሳይ ትግል እና መጋተር/ረዚዝስታንስ/ሲያሳዩ አልታሰሩም። መታሰርና ጥብቅ ክትትል የጀመረው ዲያስፖራ የሚኖሩ የወያኔ ትግሬዎች፤በድረገጾቻቸው እና በመግለጫ ለአለቆቻቻው የተቃውሞ “እሪታ” ሲያስሰሙ “ወያኔ መሪዎች” የነሱን እሪታ ሰምተው በሥርዓቱ ያሉት ትግሬዎችና ተባባሪ ጠባብ ኦሮሞ ባለሥልጣኖች በመቀናጀት ይህንን ሌጣ ሰንደቅ የሚያውለብልብን ሰው/ቡድን መከታተል ጀመሩ። ጥብቅ የሆነበት የመጨረሻው ወቅት ግን እልክ ውስጥ ገብተው ማሰር የጀመሩት በአብይ ጊዜ እነ እስክንድር እና እነ ሙላልም አንዳርጌ ወዘተ..ሲፈቱ ነው። መኖሪያ ቤታችሁ ግቢ ውስጥ ልሙጡን ሰንደቃላማ ለጥፋችኋል በሚል ተከስሰው ከየቤታቸው ድረስ ሄደው እየጎተቱ አሰርዋቸው። ጩኸቱ ሲበረታ አብይ አማራጭ አልነበረውም እና ቸል አለው።

አናርኪስቱ ዐቢይአንድ ኢትዮጵያዊ የፈለገውን ባንዲራ ቢያውለበልብ፥ ያልፈለገውን ቢያቃጥል ሐሳብን በነፃ ከመናገር የተለየ አይደለምሲል አርስዎ ለዚህ አናርኪስት አነጋገሩ በዚህ ረገድ ከሠለጠኑት አገሮች እኩል አደረገን እኮ” ብለው ያሞካሹታል። የግንጣላ ባንዴራዎች የኦጋዴኖች እና የኦነግ ባንዴራዎች በማንኛውም አገሪቱ ሥርዓት በፋሺስት ወያኔ ሥርዓት ዘመን ካልሆነ ሕጋዊነት የላቸውም። ምክንያቱም የግንጣላ እና ሕዝብ ማፈናቀያ እና መተራመሻ ምልክቶች ስለሆኑ ነው። በኢትዮጵያ ጽንፈኛ እስላማዊ የፓልቶክ ክፍሎች “የሸሪዓ መንግሥት ይመጣል” እያሉ በገሃድ ሲናገሩ የነበሩት ይህንን ቢሉ ይረዳኛል። ይህንን የሚያራምዱ ደግሞ ታዋቂ እስላሞች በጆሮአችን ያደመጥናቸው ሰዎች (በስም መጥቀስ ይቻላል) ቢሉ አሁንም ይገባኛል። ላሁኑ አንገታቸው ያቀረቀሩ ድብቅ የአልሸባብ እስላማዊ ቡድኖችም (ሸሪዓ መንግሥት እና የክርስትያን ጸሎት ቤት አቃጥሉ! ከመሓመድ ከዓሊ፥ ካቡበከር፥ከማዕሩፍ ፥ እና ከጀማል፤ዘህራ፤ጀሚላ…ከሚል እስላማዊ ስም ካላቸው ወንድም እህቶች እንጂ  ‘ገብረማርያም፥ ከጌታቸው፥ ሰላማዊት፥ ምስራቅ ፥ ገብሩ ፥ ሓጎስ …የሚል ስም ካላቸው በምንም የማንገናኝ “ኩፍሪዎች” (ሃይማኖተ ቢሶች/ክርስትያኖች) ጋር ጓደኝነት አትግጠሙ የሚሉትን) ይፋ ሆነው ፥ ተደራጅተው ነገ ባንዴራቸው በኢትዮጵያ ምድር ያለማውለብለባቸው ዋስትና የለንም። የእርስዎም ይሆነ የአብይ ዲሞክራሲ የሚሰጠን ቢኖር የሸሪዓ መንግሥት ታጋዮች ፥ ናዚዎች እና አልሸባቦችን ከጽንፈኛ ባንዴራቸው ጭምር በዲሞክራሲ ስም ወደ ገሃዱ ዓልም እንዲከሰቱ የሚጋብዝ አሰራር (አቬኑ) ነው።

የኢትዮጵያን ሰንደቃላማ ማቃጠል ዲሞክራሲ ብለው የሚያምኑበት መብት እና ስብከትዎ ተሞርኩዘው ‘ሰንደቃላማየን ከፊቴ ቆመው ቢያቃጥሉልኝ ባየዎት እንዴት እንደምቃጠል እና ምን እንደሚሰማኝ አላውቅም” የጽላተ ሙሴን ታቦት ፖሊስ ጣቢያ መጋዘን አፈር ላይ ተጥሎ እንዲታሸግ ያደረገቺው ኦሮሞዋ ከንቲባ (የ ኢሕአዴግዋ የኦሮሚያዋ ዮዲት ጉዲት) በቅርቡ በስራዋ ተጸጽታ ይቅርታ ጠይቃለች የተባለቺው፤- እርሰዎ ሕገመንግሥትን እና አብይን አክብሩ በሚሉን ሕገ መንግሥት ተብየው ተሞርኩዛ ይህንን ጉድ ሰርታለች።
 ምክንያቱም እንደ እርስዎ እና አብይ የመሳሰሉት ባንዴራን ማቃጠል የዲሞክራሲ መብት ነው  (ከፈረንጅ ጋር እኩል አደረገን እኮ) እያላችሁ ከውጭ አገር ጋጠወጦች ጋር በማነጻጸር ባንዴራ በማቃጣል የሚገኝ ዲሞክራሲ አለ እያላችህ ስትሰብኩ (አንዳንዱ ተባባሪም ኢትዮጵያ ሴት መነኮሳት “ለዝቢያን” ነበሩ እያሉ ለውጭ አገር መሰሪዎች በግዕዝ የተጻፈ ‘የመነኮሳትን ሕልም’ እያጣመሙ እንደሚተረጉሙላቸው ሁሉ) ቀስ እያለ ታቦት ማቃጠል እና ታቦት ፖሊስ ጣቢያ መጋዘን ውስጥ ማሸግም እንዲሁ ተለምዷል። ይህ ሁሉ የሚደረገው በዲሞክራሲ ወይንም በሕገመንግሥት ስም ነው።

ዶክተር ዐቢይ አንድ ኢትዮጵያዊ የፈለገውን ባንዲራ ቢያውለበልብ፥ ያልፈለገውን ቢያቃጥል ሐሳብን በነፃ ከመናገር የተለየ አይደለም የሚለው አናርኪስቱ አብይ “ሳክረድ/sacred/holy” ቅዱስ የሚባሉት አገራዊ ምልክቶችን ማቃጠል ወይንም የፈለገው “የአልሸባብ” ባንዴራም ቢያውለብልብ አንቃወመውም ይላል።  (የፈለገው ባንዴራ ሲል አብይ የካሊፋ ባንዴራም ቢሆን ማለቱ ነው)። በቅርቡ ጅግጅጋ ውስጥ እንደተውለበለበው “ባለ አምስቱ የሶማሊ ኮከብ ባንዴራ” እና የኦሮሞ የግንጣለ ባንዴራቸው ማውለብለብ ዲሞክራሲ ከሆነ እርስዎም በዚህ በዲሞክራሲ የሚምል ሰው ይህንን አነጋገር  መቀበል  እንዴት ያቅተዋል? የሚለውን አባባልዎ ‘የፈለገው አልሻባብ እና የግንጠላ ባንዴራ ማውለብለብም ሆነ ቅዱሰት ሰንደቃላማችንን የሚያቃጥል የጣሊያን አስካሪ፤ ወይንም አልሸባብ እና “የሸሪዓ መንግሥት አንጋሽ ፓርቲ’ የመሳሰሉት በኢትዮጵያዊ  ምድር በቅለው ስንመለከት እንቀወማለን።

“መቃወም” ብቻ ሳይሆን ብዙ ሰበብ የሚያስነሳ ስለሆነ “ሰንደቃላማችን ሃይማኖታችንና ልብሳችንማዕረጋችን ስንቀበር ስንዳር እና ስናሸንፍ የምናውለበልባት በተጠንቀቅ ዘብ የምንቆምላት “ቅዱስ ንብረታችን ስለሆነች” ”በዲሞክራሲ ስም እንድትቃጠል “ባይሰብኩን” ወይንም እንዲቃጥለዋት ለሚሰብክ ቡድን እና መሪ “ጥብቅና ባይቆሙ” ይመረጣል።

የሚገርመው ደግሞ፦ እንዲህ ያሉትን አባባልዎ የሚገርም ነው።

አንድ ሆነናል “የጥንቱ ባንዲራችን እንዲመለስልን እንታገላለን። እስከዚያ ግን ሕጋዊው የኢትዮጵያ ባንዲራ የምንጠላው ባለኮከቡ ነው። ሌጣውን ባንዲራና የኦነግን ባንዲራ ስናውለበልብ ላለመታሰራችን ዶክተር ዐቢይን እናመስግን። በሕግ ፊት አሁን ሁለቱም እኩል ሌላ ባንዲራዎች ናቸው። ዶክተሩ፥በዘዴ የማመጣው ለውጥ ካላስደሰታችሁ ያውላችሁ አገሪቷን ሌላ ሰው ይምራትብሎ ሥራውን ቢለቅ እናጨበጭባለን ወይስ ሌላ ሰው ሲተካ፥ጉልቻ መለወጥ ወጡን አያጣፍጥምእንላለን? እሱ ቢለቅ የሚተካ አይጠፋም። ግን ማነው የሚተካው? ሰዶ ማሳደድ እንዳይሆንብን እፈራለሁ። ሆኖም፥ ሕገ ወጦችን በስብከት ብቻ ማስተዳደር አይቻልም።

እንደውም አብይ ካለመምጣቱ በተመረጠ። ምክንያቱም አሁን እሱ በመምጣቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታችን ምን እንደሆነ ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው። በብዙ መልኩ ሽብር ውስጥ ከትቶናል። ወያኔዎች ስልጣን ላይ ቆመው ቢኖሩ ኖሮ በግዳቸው መውረዳቸው አይቀሬ ነበር። ተተፍተው ስለነበር። ተበትነን ነበር (አብይ ባይመጣ እንበተን ነበር) የሚለው የብዙዎቹ እምነት ብናነሳ “አሁንም ያለመበተንዋ ማስተማመኛ የለም” (በታኞች ያለምንም ገድብ ከነትጥቃቸው አስገብቶአቸዋል እና ስጋታችን ከመቸውም የበረታ ነው)። ያ እንዝህልላነት ክፍት አድርጎ ስለሰጣቸው ‘በጣም አደገኛ” አድርጎታል። ገንጣዮች እና በጭፍጨፋ የተካፈሉ ወንጀለኞች ሁሉ “ጥይት ሳይቶኩሱ” ማንምን ሰያሸንፉ “ሰራዊታቸውን ወደ መሃል አገር ገብተው ያለ ምንም ስጋት እና መስዋእት ሳይከፍሉ” ስላደረገ ፤ የወደፊቱ ፖለቲካቸው እና ምኞታቸው ክልልቻውን እንዲቆጣጠሩት በር ከፍቶላቸዋል። ያ እንዝህላልነት ስርዐረተ አልባነት ነው።ዓብይን በወንጀል ያስቀጣዋል። ተደርጎ የማያውቅ እንዝህላልነት እና ሞኝነት እንዲህ ያለ አሰራር ሰምቼ አላውቅም። አንዴ ወደ ውስጥ ያስገባኸው ጠላት ላስወጣ ብትል አደጋው በጣም ከባድ ነው። በቀላሉ በሚፈለጉት ቦታቸው ላይ ገብተው አሁን በአዳዲስ ተቀልባሾች እና በነባር ደጋፊዎቻቸው ምሽግ ገብተዋል/ምሽግ ሠርተዋል!! አሁን ብጥብጥ ቢነሳ አስቸጋሪ የሚሆኑት እነዚህ ከአስመራ እና ከየትም የተግበሰቡ አደገኛ ቡድኖች ናቸው አደጋውን የሚያባብሱት።ለዚህ ነው ከ26 አመት በላይ ኤርትራ በረሃ ውስጥ መሽጎ የነበረው “የአርበኞች ግምባር” የተባለው ከ20 የማይበልጡ ተዋጊዎች የነበሩትን “ግንቦት 7ን” በጦር ያደራጀው ይህ ሃይል ዛሬ ወደ አገር ሲገባ “ግንቦት 7ን” ትቶ ወደ አማራነቱ የገባበት ምክንያት ኦነግ እና ወያኔዎች ለወደፊቱ ምን ክስተት እንደሚያመጡ ስለታያቸው ነው። በዚህ ምርጫቸው መመስገን አለባቸው! አብይ አደገኛ መንገድ እየተከተለ እንዳለ አውቀውታል።

እንዲሁም እረስዎ

 “ሌጣውን ሰንደቅ ስናውለበልብ ባለመታሰራችን እናመስግን”
 ይላሉ።

አባባልዎ ትንሽ ፈገግ ቢያሰኘኝም አስገራሚ ነው። ሰንደቃላማ ሳያውለበልቡ እቤታቸው እና ቤተጸሎት እና ንግድ ቤታቸው የተቀመጡ ዜጎች ናቸው እኮ  ከገዛ አገራቸው እየታረዱ ፥ ህጻናት ወጣት ሴቶች አዛውንት እናቶች እየተደፈሩ ያሉት። ቡራዩ ላይ ቤንሻንጉል ላይ፤ጉራጌ ውስጥም ሰንደቃላማ ስላውለበለቡ አይደለም እኮ የታረዱት። ሳያውለበልቡም ተጨፍጭፈዋል/ተገድለዋል/። ሆኖም አብይ የፈለጋችሁ የአልሸባብም/ኦነግም/ ባንዴራ ማውለብለብ መብታችሁ እና ዲሞክራሲ ነው ስላለ፤ ይህን ስለፈቀደ ይበልጥ ጭፍጨፋው እንዲስፋፋ እንዲባባስ አድርጓል!

ጨፍጫፊዎቹ እኮ ኢትዮጵያን ሰነደቃላማ ይዘው አይደለም ወንጀል የፈጸሙት። የራሳቸውን ምልክት ይዘው ነው ሲጨፈጭፉ የነበሩት? እንዴት ነው ነገሩ? (ቱትሲ እና ሁቱ  ዓይነት እኮ ነው የታየው) የገዳዮቹ ያውለበለቡዋቸው ምልክቶቹ እኮ መልዕክት አላቸው! አይደለም እንዴ? የኦነግ ባንዴራ መልእክቱ እና ዓላማው ምንድ ነው? ሊነግሩኝ ይችላሉ? ኦሮሚያ ሪፑብሊክ የተባለ የወደፊት አገር መስራቾች ቢያንስ ሦስት ወይንም አራት ባንዴራዎች አሉዋቸው።ከግብጾች ጋር የጠበቀ ግንኙነት እና ሴራ እየጎነጎኑ እንደነበረ በቪዲዮ የተደገፈ ማስረጃ ከካይሮ ተሰራጭቶ አይታናል። ምልከታቸው እየነገረን ያለው ከተቀረው ሕዝብ በአበሻዎቹ (ማራዎች እና ትግሬዎች) በባዕድ “አቢሲኒያዎች’ ስለተገዛን የጥንት አገራችንን ስለምንመስርት እናንተ መጤ ናችሁ እና ከዚህ ኦሮሚያ አካባቢ ውጡ! እያለ ነው እኮ ግልጽ ቅስቀሳ እያደረገ ያለው (ለ45 አመት ሙሉ)!

አዲስ አበባ ኦሮሞ ነች፤ስምዋም ፍንፍኔ ነው፤ የተቀረው “መጤ ነው”  የሚል ከንቲባ የሚመራት ርዕሰ ከተማ ነው እኮ እየተነጋገርን ያለነው። አዲስ አበባ መሃል ኦሮሞዎች ከ70ሺሕ የሚገመት ኦሮሞ በተሰበሰበበት አደባባይ “ፍንፍኔ የማናት?”፡ “ኦረሚያስ” እያሉ ሕዝቡን ለፍጅት እና ለጸብ ሲቀሰቅሱ ሰምተናል።  ጭፍጨፋውም ከቀናት በፊት የተፈጸመው ዕልቂት እኮ በዚቺው ከተማዋ ዙርያ ነው። ጃዋር እንዳለው “እንደቀለበት ከብበን አዲስ አበባን በቁጥጥራችን ማስገባት እንችላለን፡ አሁንም የሚያግደን ሃይል የለም” እኮ ነው እያለው ያለው። የተደረገው ከበባ እና እልቂት ስንመለከት ከዚያ ስትራተጂ ጋር ይመሳሰላል። አሁን በምድራችን ሁለት ምንግሥታቶች አሉ። አንዱ ቄሮ አንዱ ኢሕአዴግ ነው። ጃዋር በግልጽ ነግሮናል።

ቄሮ የተባለው ደግሞ በግድያም በዘረፋምሴቶችን በመድፈርም በማስፈራራትም አገር በመገንጠል ሴራ እና እንቅስቃሴም….ሆነ አዲስ አበባን ከብቦ በቀለበት መልክ “ለማስገባት” ለጥፋት የተዘጋጀና በድርጊቱም የታየ አደገኛ የኦሮሞ የወጣቶች ቡድን ነው። እኛ ቄሮዎች የተለየን ነን የሚል ቡድን አለ። እኛ ነን ቄሮዎች የሚልም አለ። ዳውድ ኢብሳም፤ ጃዋርም ሌላውም በየበኩላቸው ይህንን ቡድን እንመራዋለን ይላሉ። የቱን እንመን!? ቄሮ የሚባለው ጤነኛውም በሸተኛውንም ያካተተ አናርኪ ስብስብ ከሆነ ‘የማጥራት ስራው’ የኛ ሳይሆን የኦሮሞዎች ነው።  ኮሚቴውም ሓለፊውና መሪው ማን እንደሆነ አይታወቅም። ክቡር ፕሮፌሰር ማንን እና የትኛውን መንግሥት እንታዘዝ? ቄሮውን መንግሠት ወይንስ የኢሕአዴግን መንግሥት?

ጃዋር የፈለገው ቃል እንዲናገር አብይ ፈቅዶለታል። የቄሮ መንግሥትነቴን እና እኔ ጃዋርም መንግሥት መሆኔን (እነሱም ያውቁታል ብሎአቸዋል) “እነሱም” ሲል ፡እነ አብይ እና እነ ለማ” ማለቱ ነው። መንግሥት ነኝ ማለትም “ዲሞክራሲ ነዋ!” አይደለም እንዴ? ባንድ አገር ሁለት መንግሥት!!!! ለየትኛው እንታዘዝ?

እንዲህ ያለ ነገር ያዩ “ባሻይ ደበስ” የተባሉ የመቀሌ ከተማ ታዋቂ ቀልደኛ (እኔም በቀርብ ወዳጄ የነበሩ ዕድሜ ትልቅ ቢሆኑም) ሴት ልጃቸው ወደ ቀበሌ እየሄደች አምሽታ እየመጣች ስታስቸግራቸው “የት ነበርሽ ሲልዋት “ቀበሌ ስብሰባ” ትላቸዋለች፡ እሳቸውም ስላልጣማቸው፤ “ቀበሌ መናብርት ሕዝብ በተሰበሰበበት ፊት ቆመው “ልጆቻችን ማታ እያመሹ ሲመጡ “ይኼ ማምሸት አልተመቸንም እንዴት ነው ነገሩ” ብለን ሴት ልጆቻችንን ስንጠይቃቸው የሚመልሱልን መልስ “ቀበሌ” ይሉናል። ከቀበሌ ማስቆም አቅም የለንም፤ አንድ ነገር ግን እንድታደርጉልን የምንጠይቀው በዚህ መልክ ድንገት ቢያረግዙ “ናኽራይና” (አማቾቻችንን) ማን እንደሆኑ አሳውቁን።” ሲሉ ሕዝቡን በሳቅ ገደሉት። ያንን እንዲደግሙልኝ እኔ እና ዘመዴ የሆነ አቶ ታፈረ ገሠሠ ሆነን ስንጠይቃቸው ያንን ደግመውሉን “አነጋገራቸውም በጣም አሳቂ ስለሆኑ ለረዢም ጊዜ መሳቄን አላቀምኩም ነበር”። አሁንም በዚህ እሳቤ ክቡር ፕሮፌሰርም ሆነ አብይን የምንጠይቀው “መንግሥታችን” የቄረው መንግሥት ነው ወይንስ የኢሓዴግ መንግሥት? አንዱን ብታስመርጡን እቅጩን እናውቅ ነበር፡ ካልሆነ ሁለት መንግሥት ባለበት ስርዓተ አልባ ስርዓት “መንግሥት የሚባለው ይኽኛው ነው” ብለን ለመቀበል አስቸግሮናል።

ኦነጎችም ሆኑ “ቄሮአዊው ጃዋር” ከእኛው ኢትዮጵያውያኖች ጋር አንድ ለመሆን ነው የመጡት እየተባለ ኢትዮጵያዉያኖች ሲሰበክለትም ሰምተናል። ቂሎቹ አማራዎችም “ጃዊ” አልብሰውታል። ስለ እኛ ጨሆልናለህ ብለው (ኢትዮጵያውያኖች ከኦሮሚያ አገራችን ውጡ!) ብሎ እንዲባረሩ የቀሰቀሰባቸው ጃዋር አማራዎቹ ባሕር ዳር ውስጥ ጋብዘው በአሳፋሪ ‘ንቃተ ሕሊናቸው’ “ለ27 አመት ስለ እኛ በመቆምህ እናመሰግናለን ብለው አወድሰውታል” (ባሕርዳር ውስጥ)፡ ኦሮሞ ሱሉጣኖች (አክቲቪስቶች) በጣም ብልጥ አጭበርባሪዎች ናቸው።ሲናገሩ እውነት ያስመስላሉ። የምስጦች ዓይነት ችሎታ ነው የሚከተሉት። ከላይ ላይ ሌላ ይሰብካሉ ከውስጥ አላማቸውን ለማሳካት መቦርቦራቸውን ግን አያቆሙም።

ኦሮሞዎቹ በተለያዩ ድርጀቶች ታቅፈው ኢትዮጵያን “ኮሎኒ-ኢመፓየር ነች” ብለዋታል። ይህንን ካሉን ኢትዮጵያ ከኦሮሞዎች ጋር ያለው ግንኙነት ‘ኮሎናይዝ ካደረገው አገር’ በቅኝ ግዛት ከገዛት አገር ጋር ተመልሶ አንድ የሆነ አገር መመስረት በታሪክ ታውቆ አይታወቅም። እንዴት እንመናቸው? ኢጣሊያ ቅኝ አድርጎ በገዛቸው ሶማሌዎች እና ሊቢያ እንዲሁም ለአጭር ጊዜም ቢሆን ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር ከነዚህ ጋር አብሮ አንድ ሕዝብ/አንድ አገር/ መመሰረት ይቻለዋል? አይቻለውም። ኦሮሞዎችም የያዙት ምልክት ጸረ ኢትየጵያ የሆነ የግንጣላ ምልክት ስለሆነ “የቅኝ ግዛት አገር የተባለቺውን ኢትዮጵያን ኦሮሚያ ከተባለ አገር ለማስወጣት ነው መሰረታዊ ምልክቱ (ሰንደቃላማው ያንን ነው የሚያመለክተው)። ስለዚህ ምልክታቸው መታገድ አለበት!

ብዙዎቹ በግንጠላ የተሰማሩት ኦሮሞዎች በውሸት በክሕደት የታወቁ ናቸው። በዋሾነታቸው ባሕሪይ ከወያኔዎችና ከግንቦት 7ቶቹ ኢሕአፓዎች እና ከሻዕያ መሪዎች ጋር መንትያዎች ቢሆኑም ‘ኦኖጎቹ’ ዓይን አውጣ ውሸታሞች እና ተቀያያሪ እስስት ባሕሪያቸው ከሌሎቹ በብልሃት ሳይሆን በድፍረት እና በመዋዥቅ “መገንጠልንም ሆነ በግድያ” ተሳትፈንም ጠይቀንም አናውቅም ብለው “አሉ” የሚሉ ሊታመኑ የማይችሉ ናቸው። ብዙዎቹ ደግሞ በዘር ማጥፋት የተካፈሉ ወንጀሎች ናቸው። ግንጠላን አቀንቅነን አናውቅም እያሉ ሲክዱ ይደመጣሉ፤ ፕሮግራማቸውን ስታሳያቸው ግን መልስ የላቸውም። የሚያናድዱኝ ግን “ምንጣፍ አንጣፊዎቻቸው” የሆኑት ኢትዮጵያውያኖቹ ናቸው (አኮሞዴት እና ኮምፕሮማይዝ የሚያደርጉ)።

ውሸታቸው እንደለ ሆኖ ይህ  የግንጠላ ባንዴራ አብይም ሆነ እርስዎ እና ተቃዋሚ ተብየ (አኮሚዲተር) “ተለሳሰላሽ እና መጋረጃ ዘጊ እና ምንጣፍ አንጣፊ” ሁሉ ኦነጎች የግንጣላ ባንዴራዎች በማውለብለባቸው አብይ መመስገን አለበት ሲሉን ኦነጎች ሕገ ወጥ ብቻ ሳይሆኑ እስር ቤት መግባት ያለባቸው ወንጀለኞችን ናቸው።

አብይ እና ኢሳያስ ተመሳጥረው እነዚህን ነብሰገዳዮች ወደ አገር አስገብቶ ለውጥረት እና ግድያ በር ከፍቶ ሕዝባችንን ለፍርሃት የዳረገ ስለሆነ አናርኪ ስላነገሰልን መመስገን ሳይሆን መወገዝ አለበት። ኦነጎች ምን እንደፈጸሙ ይህንን ለእርስዎ መንገር ‘ለቃባሪ ማርዳት’ ነው። የሶማሊ ኦጋዴንም ይኼውለዎት ከነባንዴራው ገብቶ የመገንጠል ጥያቄው ሳያነሳ “ኢትዮጵያን” ለማፍረስ ይፋ መግለጫ እየበተነ ነው” (ከሦስት ቀን በፊት!!) ። አገር ማፍረስ የዲሞክራሲ አንደኛው ገጽታ ነው እና ያም መብት ስለሆነ ዲሞክራሲ የሚባለው የአብይ ሽቶ መቀባት አለባችሁ ሲሉን “እኛ ደግሞ አንቀባም”!!! ብለናል።

 ኦነግም ያስተላለፈው አንዲት አቁዋሙን አልለወጠም! ሁለቱ ኦሮሞዎች ለማ እና ወርቅነህ ገበዮህ አስመራ ሄደው ምን እንደተፈራረሙ ያወቅነው ነገር ሳይኖር “ጎትቶ በመቀሌ በኩል አስገባቸው”። ጃዋርን ከአሜሪካ ፍሬው(ዳውድን) ከአስመራ “ጸረ አማራው ምስጡ እና ጃርቱ” በቀለ ገርባን ከእስር ቤት ጎትቶ አስመጣልን። ከዚያ ምን እንደተፈጠረ የምናውቀው የሰሞኑ ዜና እና የታየው አዲስ አባባ የታየው የሰላማዊ ተቃውሞ ገላጭ አመላካች ነው። ኦሮሞዎቹም ሆኑ ኦጋዴኖች ዓላማቸውንና የግንጠላ ባንዴራቸው እስካልጣሉ ድረስ ሰው መግደል፤ማባረር፤ ማጋጨት የማይቀር የለመዱበት እና ዘወትር ዓላማቸው ስለሆነ፡ ሰንደቃላማችን እያቃጠሉ (ከተሰቀለበት እየነቀሉ) እየተነኮሱ ‘ሕዝቡን ግጭት” ውስጥ ከትተውታል (ለወደፊቱም ይቀጥላሉ)። በዲሞክራሲ ስም ለትንኮሳ እና የብጥብጥ ምንጭ የሚረዱ 44 ባንዴራዎችን እንዲውለበለቡ በመፍቀድ በዲሞክራሲ እየተመካኘ ለኢትዮጵያ የተሰራላት የመርዝ ብልቃጥ መርጨት እንቃወማለን! እስኪቆም ድረስ ተቃውሞው ይቀጥላል። ያለ አንድ ብሔራዊ ሰንደቅ በስተቀር የተቀሩት በሙሉ (የክልል የገዳ የቅብጥርጥሮሽ በሙሉ የጠብ ምንጭ ስለሆኑ በሙሉ መታገድ አለባቸው እላለሁ!

በመቀጠልም እንዲህ ይላሉ፦

የፖለቲካ ለውጥ፤ በአሁኑ ሰዓት ሁለት ዓይነት የፖለቲካ ለውጦች ይታዩኛል፤ ግን ሁለትነታቸውን መለየት አቅቶን እያምታታናቸው ተቸግረናል። አንዱ ለውጥ ኢሕአዴግ የራሱን ሕገ መንግሥት ጥሶ ሕዝብ ማጥቃቱን እንዲያቆም ማድረግ ነው። ኢሕአዴግ ያለ ሕግ ያስር፥ ይገርፍ፥ ያኰላሽ፥ በሰው አፍ ውስጥ ይሸና፥ ይዘርፍ ነበር። ዶክተር ዐቢይ ሊያመጣ የሚችለው ለውጥ ይኸንን -ሕገ-ኢሕአዴጋዊ ወንጀል ማቈም ነው። አቁሞልናል ነፃነት ተሰምቶናል። ሳንፈራ እንናገራለን፥ እንጽፋለን፤ ሕዝብ (ከወያኔ በቀር) ከዳር እስከ ዳር እልል ብሏል።”

የራሱን ሕገ መንግሥት ከጣሰ እኛ ሕገመንግሥቱን የማንጥስበት ምን ምክንያት አለ ብለው ያምናሉ? ለእርስዎ ነጻነት አምጥቶለዎት ይሆናል። የራሱን ሕገ መንግሥት ጥሶ ያቆመው የቱ ነው? አዲስ አባበ ውስጥ ከሦስት ቀን በፊት 5 ሰላማዊ ተሰላፊዎች (አንዳንዶቹ ሰልፍ ውስጥ የሌሉበት መንገደኞች ይሏቸዋል) በጥይት ረሽኖአቸዋል።ባሕር ዳር ውስጥም እንደዚሁ ፈጽሟል። ቤንሻንጉል ውስጥም አማሮች እየተባረሩ ነው (ሰሞኑን) ጉራጌ አካባቢም እንዲሁ….የአየር መንገድ ትራፊክ ተቀጣጣሪዎች ሰላማዊ ጥያቄ ስላቀረቡ ያለ ሕግ ታፍሰው “ሽብር” በመፍጠር ተከስሰዋል ይባላል (እውነት ነው አይደለም እኔ አላውቅም። ያነበብነው ዜና ግን ያንን ነው)። ኢሕአዴጋዊ ወንጀል አቁሞታል የሚሉት ዛሬም እስረኞች እስር ውስጥ እየማቀቁ የሚገኙ አሉ (እስር ቤት ውስጥ አብይ ውሸታም” ሲሉ መፈክር አሰምተዋል)። ሰለ የመጻፍ ነፃነትም እርስዎ ሳይፈሩ ጽፈው ይሆናል፤ ቡራዩ እና ቤንሻንጉል ባሕርዳር እና አዲስ አበባ ግን የቤተሰቦቹን የቤቱን እና ንብረቱን ደህንነት ስጋት ላይ ወድቆ ሰርዓቱን ማመን አቅቶአቸዋል። አዲስ አበቤዎች ስያስተጋቡት የነበረው ‘መፍክር’ ‘አብይ እንወድሃለን ግን ስራህን ስራ ወይንም ቦታውን ልቀቅ!” ነበር የሚሉት። አሸባሪዎችንና የጥላቻ ሰባኪዎችን በስርኣተ አልበኛነት መንገድ (እርስዎ ዲሞክራሲ የሚሉት) ያለ ገደብ እና ቁጥጥር ያለምንም ውል እና ጥርጣሬ ወደ አገር አስገብተህ አስጨረስከን አስሰደብከን አስደፈርከን ስጋት ላይ ጣልከን…ነበር ብለው እየከሰሱት የነበረው! (አዲስ አበቤዎች!!)

በመጨረሻም ስለሰንደቃላማ ሕጋዊነት ነጋሶ ጊዳዳ የነገርንን በዚህ ልደምድም፤

የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ በሰንደቅ ዓላማ ዙሪያ አሁን ለነገሰው አለመግባባት መንስኤው ምን እንደሆነና መፍትሄውን እንዲሁም ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮችን አንስቶ አነጋግሯቸዋል፡፡ ይላል ከዶ/ ነጋሶ ገዳዳ ጋር በጥቅምት 2010 የተደረገውን ቃለ ምልልስ ሲያብራራ
“እኔ እስከማስታውሰው ድረስ፣ ይሄ ሁሉ የረቂቅ ሂደት ሲከናወን የሰንደቅ አላማ ጉዳይ አልተነሳም ነበር፡፡በረቂቅ ህገ መንግስቱ ላይም ሆነ በፀደቀው ህገ መንግስት ላይ ህዝቡ የራሱ ፍላጎት ስለመካተቱ የሚያንፀባርቅበት ህዝበ ውሣኔ አልተካሄደም፡፡ እንዳለ ወደ ህዝቡ ነው ፀድቆ የወረደው፡፡ የሠንደቅ ዓላማው ሆነ ሌሎች ችግሮች የሚመነጩት፣ አንደኛው ከዚህ አንፃር ነው፡፡  ትልቁ ጥያቄ የነበረው ሀገሪቱ ፌደራሊዝም ያስፈልጋታል አያስፈልጋትም የሚለው ነበር እንጂ የሰንደቅ አላማ ጉዳይ እንደ ሌሎቹ አንቀፆች የድጋፍና የተቃውሞ ድምፅ ከህዝብ አልተሰበሰበበትም፤ ለህዝብ ውይይትም አልቀረበም ነበር፡፡ ኮሚሽኑ የሰንደቅ አላማን ጉዳይ ለህዝብ ውይይት አላቀረበም። ለምሳሌ አጨቃጫቂው የህገ መንግስቱ አንቀፅ 39 ማለትም፣ የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከ መገንጠልን የሚፈቅደው በመጠይቅ ዝርዝሩ ተካትቶ ነበር፡፡ በዝርዝር ጉዳዮች ላይ ደግሞ በተመረጡ 23 ሺህ ቀበሌዎች ላይ ነው የህዝብ ውይይት የተደረገው፡፡ እኔ ለምሳሌ ደምቢዶሎ ላይ አወያይቻለሁ፡፡ ደምቢዶሎ ትልቅ ከተማ ነው። ህዝቡ 50 ሺህ አያንስም ግን እኔ ያወያየኋቸው 200 አይበልጡም፡፡ በዚህ አይነት ነው ውይይቶች የተካሄዱት፡፡ (ሕገ መንግሥቱን ካዋቀሩት ወንዱ- ነጋሶ ጊዳዳ)

እንግዲህ እርስዎ አብይ ካከበራችሁ ሕገመንግሥቱንም አክብሩ እያሉ የሚወተውቱን ሕገመንግሥት ተብየው በዚህ መልክ ነበር የተተገበረው። ነባር ሰንደቃላማ ዓለም ያወቀው ሰንደቃላማችንበጦር ሜዳ በሠርግበሓዘን እና በየድል ቀን በዓላት ሲውልበለብ የነበረው ሰንደቃላማችን ለሕዝብ ድምጽ መቅረብ የለበትም። አክራሪ እስላሞች እንደሚዋሹት ሰንደቃላማችን ከሃይማኖት ጋር የተያያዘም አይደለም። የተያያዘው ከተፈጥሮ የተቀዳ ነው። ቀስተዳመና ነው። ሁሉም  ዓይናችን ማየት የሚችላቸው የዓለም ‘ቀለሞች’ የተቀዱት ምንጩ ሦስቱ መሰረታዊ የቀለሞች ውስጥ “የቀለሞች ሁሉ ቤዝ/ምንጮች” የሆኑት አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ቀለም የሚባሉት ናቸው። ስለሆነም የሁሉም ምንጭ የሆነ የአንደነት ምልክት ነው እና ለደምጽ አይቀርብም። ማንም የማይፍቀው የወንዝየሰማይ እና የባሕር ታምረኛው ቀስተ ደመና ሃይማኖታዊ ተብሎ የሚተረጎመው ምክንያት ይቁም! 


እስኪ እንደው ልጠይቀዎት “ይህንን የፈጣሪ ቀስተደመና” የያዘን ሰንደቅ ማቃጠል ዲሞክራሲ ነው? ምን እሚሉት ሕሊና ነው አንዲህ ያለውን ሕብር በማቃጠል የሚረካ ዲሞክራቲክ የሚባል ፍጡር? ምናልባት ክርስትያኖችን የሚያርዱ አልሸባቦች’/አይሲሶች? ኦነግ? የሸሪዓ መንግሥት ይመጣል የሚሉ “የከሊፋ” እንቅስቃሴ ኢትዮጵያውያን እስላማዊ አቀንቃኞች? ሻዕቢያዎች? አዎ እነዚህ ከሆኑ እስማማለሁ። ከእነዚህ ውጭ ግን ጤነኛ ቡድን ይህንን ቀለም በመበት እና ዲሞክራሲ ተነሳስቶ ሊያቃጥል የሚያስችል አንጀት አለው ለማት ያዳግተኛል። ይህች ሰነደቅና ቤተክርስትያኖቻቸው ትቃጠል የሚሉ አሉ ። ይህንን የሚሉት እነማን እንደሆኑ አርስዎ በሚኖሩበት ከተማ የሚሰራጨው ኦሮሞ አክራሪ አስላሞች እንደሆኑ ይህንን ቪዲዮ በትዕግስት ይመልከቱ። እነዚህ የነጃዋርና የነ ኦነግ ተማሪዎች ናቸው።

የክርስትያን ባንዲራውና ባህሉን ይዞ ከኦሮሚያ የሚባለዉ ክልል ይውጣልን!
 ሰንደቃላማችን እንዲቃጠል ፍለጎት ያላቸው “ሸሪዓ” (ከሊፋ) እንዲመጣ የሚነግሱ ቡድኖች ካልሆነ በቀር “አገር እና ሰንደቃላማ፤ሃይማኖት እና ነባር ቅርሶች ይለወጡ ይፍረሱ” በሚል የዲሞክራሲ ሽፋን ለድምጽ አይቀርቡም። ሰንደቃላማችን “ነባር ቅርስ” ነው። ባለፉት ወቅቶች ሃይማኖታዊ ወይንም ‘አምበሳዊ’ ምስሎች ተካትተውበት ነበር። ይህ ሃቅ ነው ፤ ሆኖም ያንን ለማስታረቅ “ሌጣ ሆኗል”። ችግር የሚመጣው አላስፈላጊ ምልክት ሲጨመርበት ነው። ነባር አገሮች እና ሰንደቃላማ ሲመሰረቱ (እናንተ ዲሞክራሲ የምትሉት) አልነበረም። በዚያም አይገነባም፤አይፍርስም! እናንተ ሰንደቅ ማቃጠል ‘ዲሞክራሲ/መብት/ነው እንደመትሉት ሳይሆን፤ እንደ “ታቦት” እንደ “ቤተ መስጊድ” ለቃጠሎ እና ለአደጋ የማይጋለጥ ቅዱስ እና ክቡር እሴት ነው።
አመሰግናለሁ ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) getachre@aol.com