>ለጎጠኛው መምህር (አማርኛ) $25.00 እና ሓይካማ (this is diffrent book/story that is defferent than the Amharic indicated) (ትግርኛ) $15.00 መጽሐፌን ለመግዛት ዕድሉን ያላገኛችሁ ካላችሁ በሚከተለው አድራሻ ደውላችሁማግኘት ትችላላችሁ Telephone (408) 561 4836 (Getachew Reda P.O.Box 2219 San Jose, CA 95109) getachre@aol.com www.ethiopiansemay.blogspot.com
ቀን ሲደርስ አምባ ሲፈርስ
ከዲዳክ
ተክለ ጻድቅ መኩርያ በጻፉት ዐፄ ቴዎድሮስ እና የኢትዮጵያ አንድነት በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ዐፄ ቴዎድሮስ አንቱ የተባሉ ጉምቱ ጉምቱ መሳፍንትን እየረቱ ከቋራ ጎንደር የደረሱበትን ምክንያት ሲገልጡት «መኳንንቱ እና መሳፍንቱ የተጠናወታቸው መጠን ያለፈ ንቀት ነው» ይላሉ፡፡ እነርሱ የሚያውቁት ይህ ነው የተባለ የሚጠቀስ የነጋሢ ዘር የሌለው፣ «የኮሶ ሻጭ ልጅ»፣ ካሣ የተባለ ሽፍታ፣ አንድ አሥር ጀሌ አስከትሎ የት ይደርሳል? የሚል ንቀት ነበራቸው፡፡ ካሣ እቴጌ መነንን ድል ነሥተው እንኳን መሳፍንቱን ሊያስደነግጣቸው አልቻለም፡፡ ለውጡን ከጎንደር፣ ከመቀሌ እና ከጎጃም አብያተ መንግሥታት ነበር የሚጠብቁት፡፡ እነ ደጃች ውቤ፣ እነ ራስ ዐሊ፣ እነ ደጃች ጎሹ፣ እነ ደጃች ክንፉ፣ እነ ደጃች ወንድ ይራድ፣ አንዳቸው ሌላቸውን እንጂ ካሣን ለአልጋው አይጠረጥሩም ነበር፡፡
ሁሉም ምክንያታቸውን በአንድ ቃል ነበር የሚገልጡት «ይህ የኮሶ ሻጭ ልጅ የት ይደርሳል?» እያሉ፡፡ ከጎንደሯ ንግሥት ከእቴጌ መነን መኳንንት አንዱ የነበረው ደጃች ወንድይራድ «ይህን የኮሶ ሻጭ ልጅ አንገቱን እንደ ሙጭልጭላ አንቄ አመጣልሻለሁ» ብሎ ፎክሮ ነበር ጭልጋ ጫቆ ወረደ፡፡ ነገር ግን ያሰበው ከሽፎ በጦር ተወግቶ በካሣ እጅ ተማረከ፡፡ ካሣም «እናቴ ከገበያ ኮሶ ሳይሸጥላት የቀረ አለ፤ እህል ጠፍቷልና ይህንን ተመገብ» ብለው ደጃች ወንድይራድን የኮሶ ሻጭ ልጅ ብለው በተሳደበበት አፉ ኮሶ አጠጡት ይባላል፡፡
እቴጌ መነንም በሰኔ 1840 ዓም ካሣን ለመውጋት ሰባት ነጋሪት አገር አስከትተው ወደ ቋራ ሲጓዙ ከንቀታቸው ብዛት «ይህ ቆለኛ ወዴት አባቱ ሊገባ ነው ይሆን?» እያሉ የትዕቢት ቃል ተናገሩ ይባላል፡፡
ይህንን ክፉ ቃል የተናገሩትን እቴጌ መነንን ለመበቀል ካሣ ከማረኳቸው በኋላ በዋሻ ውስጥ አስገብተው ባቄላ አስፈጯቸው ይባላል፡፡
ይህ ሁሉ ሆኖ መሳፍንቱ እና መኳንንቱ ስለ ራሳቸው ኑሮ እና ሥልጣን ይጨነቁ ነበር እንጂ እየመጣ ያለው ነገር ሊታያቸው አልቻለም፡፡ አንድ ካሣ የሚባል ሰው ከቋራ ተነሥቶ ታሪክ እየሠራ መሆኑን ለማየት የሚችል ዓይነ ልቡና አልነበራቸውም፡፡
እንዲያውም ደጃች ጎሹ ዲ አባዲ ለሚባል ፈረንሳዊ በጻፉት ደብዳቤ «ተካሣ ጋር የተዋጋን እንደሆነ ጎንደር እገባለሁ፤ እንገናኛለን፡፡ ወደ ቆላ የሸሸ እንደሆነ ሰው ባገኝ እሰድልሃለሁ ፈረሱን» ብለው ጽፈው ነበር፡፡ ደጃች ጎሹ ካሣ እንደሚሸነፉ እንዲያውም ወደ ጫካ እንደሚሸሹ ነበር የሚያስቡት፡፡
ራስ ዐሊም ከደጃች ካሣ ጋር ታርቀው እናታቸውን እቴጌ መነንን ካስመለሱ በኋላ ካሣን ንቀው ተዋቸው፡፡ ካሣ ጎንደር ቤተ መንግሥት ደጅ ጥናት መርሯቸው ሀገራቸው ቋራ ሲሸፍቱ ቀድሞ የተሾሙበትን ርስት ደንቢያን ለደጃች ጎሹ ሰጧቸው፡፡
ሁሉም መሳፍንት እና መኳንንት የካሣን ጀግንነት እና ታሪክ ሠሪነት ለማየት የቻሉት ሊመለስ በማይችል አጋጣሚ ውስጥ ሆነው ነበር፡፡ ደጃች ጎሹ ጉር አምባ ላይ በኅዳር 19 ቀን 1845 ዓም በካሣ ሠራዊት ድል ከመሆናቸው ከቀናት በፊት
አያችሁት ብያ ይህንን ዕብድ
አምስት ጋሞች ይዞ ጉር አምባ ሲወርድ
ያንጓብባል እንጂ መች ይዋጋል ካሣ
ወርደህ ጥመድበት በሽንብራው ማሳ
እያሉ ያዘፍኑ እንደ ነበር የቴዎድሮስን ታሪክ የጻፉት አለቃ ወልደ ማርያም ይነግሩናል፡፡ ጎሹ እንደ ፎከሩት የሽንብራ ማሳ አልነበረም የገጠማቸው፤ እንደ አንበሳ የሚደቁስ የካሣ ክንድ እንጂ፡፡ በጦርነቱ ቆስለው ወዲያው ነበር ጎሹ የሞቱት፡፡
ይህንን የሰሙት ራስ ዐሊ አሁንም ንቀት አልለቀቃቸውም፡፡ ካሣ የሚባል ጀግና ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡ ከእውኑ ዓለም ይልቅ የሕልሙን ዓለም መርጠው «እኔ ለካሣ ጦር አልጭንም» ብለው በሦስት መኳንንት የተመራ ጦር ጎርጎራ ሰደዱ፡፡ ሚያዝያ 5 ቀን 1853 እኤአ ይህ ጦር በካሣ ሠራዊት ድባቅ ተመታ፡፡ ራስ ዐሊም ጭንቅ ውስጥ ገቡ፡፡ «ጦር አልጭንም» ማለት ትተው ካሣን አይቀጡ ቅጣት ሊቀጡ ሰኔ 23 ቀን 1845 ዓም አንድ መቶ ሺ ጦር ይዘው ጎርጎራ ወረዱ፡፡ የካሣን ጦር በመነጥራቸው አዩና «ሠርገኛ እንዳንለው በዛ፣ ጦረኛ እንዳንለው አነሰ» ብለው ዘበቱ፡፡
አይሻል ላይ የተደረገው ውጊያ እሳት እና ጭድ ሆኖ መቶ ሺው የዐሊ ሠራዊት በካሣ እጅ ተደቆሰ፡፡ ዐሊ ያልጠረጠሩት ሆነ፣ ያልገመቱት ደረሰ፤ ሊቀበሉት ያልፈለጉትን መራራ እውነት መዋጥ ጀመሩ፡፡ በመጨረሻዋ ሰዓት «ይህ በትር የእግዚአብሔር ነው እንጂ የሰው አይደለም» ብለው ራስ ዐሊ በየጁ አልፈው ራያ ወሰን ገብተው በዚያው ሞቱ፡፡
በመጨረሻ የቀሩት ደጃዝማች ውቤ «ቀን ደርሷል አምባ ፈርሷል» ይግቡ የሚል መልእክት ከካሣ መጣላቸው፡፡ ለአንድ የኮሶ ሻጭ ልጅ መግባት መደፈር ነው፡፡ ደጃች ውቤ «ምንኛ የጠገበ ነው አያ» ብለው ጦር አስከተቱ፡፡ ካሣን ገድለው ወይንም ማርከው ደረስጌ ላይ ሲነግሡ እየታያቸው ውቤ ገሠገሡ፡፡
የካቲት 3 ቀን 1847 ዓም ደረስጌ አጠገብ በተደረገው ውጊያ ውቤ ቆስለው ተማረኩ፡፡ በቴዎድሮስ እጅም ገቡ፡፡ መሳፍንቱ ሳይጠረጥሩ ዘመነ መሳፍንት አለቀ፡፡ መሳፍንቱ ሁሉ ዘመነ መሳፍንት ማለቁን የተረዱት ሁሉም ሲቆስሉ እና ሲማረኩ ነበር፡፡
«ቀን ሲደርስ አምባ ሲፈርስ መመለሻ የለውም» እንዲሉ በናቋቸው ካሣ ሁሉም ተረትተው ታሪክ ሆነው ቀሩ፡፡
ሆስኒ ሙባረክ የዛሬ ሃያ ቀን አካባቢ ግብፃውያን ወደ ጣሂር አደባባይ ሲወጡ ከጩኸት ያለፈ ነገር ይመጣል ብለው አልጠበቁም ነበር፡፡ ብርዱ ሲለበልበው፣ ሆዱ ሲሞረሙረው ወደ ቤቱ ይገባል ብለው ሕዝቡን ንቀውት ነበር፡፡ ቀን መድረሱን አምባ መፍረሱን መጠርጠር አልቻሉም፡፡
ውኃ በመርጨት፣ አንዳንዶቹን በማሠር፣ ትዊተር እና ፌስ ቡክ በመዝጋት፣ የሳተላይት ቴሌቭዥኖችን በማስተጓጎል፣ ጋዜጠኞችን በማንገላታት፣ ደጋፊዎቻቸውን በኃይል በማሠማራት ችግሩን በቀላሉ እፈታዋለሁ ብለው ገመቱ፡፡ እልፍ ሲልም የጉልቻ መለዋወጥ የመሰለ የሥልጣን ለውጥ አምጥተው ያላችሁትን ፈጽሜያለሁ ለማለት ሞከሩ፡፡ ሕዝቡ እርሳቸውን እየተቃወመ «የካቢኔ አባላቱ ስለ በደሉት እንጂ እኔንማ ሕዝቡ ይወደኛል» ይሉ ነበር፡፡
ያ ጣሂር አደባባይ የወጣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ለእርሳቸው መወድስ ሊያቀርብ፣ ለዋሉለት ውለታም ሊያመሰግን፣ ለአመራራቸው ያለውንም አክብሮት ሊገልጥ የወጣ መሰላቸው፡፡ ሕዝቡ ማምረሩን፣ አንጀቱ መቃጠሉን፣ ቋቅ ብሎት አንገሽግሾት መውጣቱን መገመት አልቻሉም፡፡
ሕዝቡ «ይውረዱ» ሲላቸው እርሳቸው ስለ ልጃቸው ያወራሉ፡፡ ሕዝቡ «ይውረዱ» ሲላቸው እርሳቸው ስለ መስከረም ምርጫ ይደሰኩራሉ፤ ሕዝቡ «ይውረዱ» ሲላቸው እርሳቸው በቴሌቭዥን ቀርበው ምዕራባውያንን ይሳደባሉ፤ ጋዜጠኞችን ይኮንናሉ፡፡ ሕዝቡ «ይውረዱ» እያላቸው እርሳቸው «እኔ ከወረድኩማ ግብፅ አበቃላት» ይላሉ፡፡ ቀን መድረሱን አምባ መፍረሱን ማየት አልቻሉም፡፡
እርሳቸው በጦር ኃይል ነው የመጡት፤ ራሳቸውም ወታደር ናቸው፡፡ አገዛዛቸውም ወታደራዊ ነው፡፡ ጦር የሌለው ሕዝብ አደባባይ ቢውል ቢያድር፣ ቢራብ ቢበላ፣ ቢጮኽ ቢያቅራራ፣ ዳስ ቢጥል መፈክር ቢሰቅል፤ ቢሰለፍ ቢለፈልፍ ምን ያመጣል? ደግሞ ከመቼ ወዲህ በጩኸት መንግሥት ተቀይሮ ያውቃል? ሙባረክ ያነበቡት መጽሐፍ እንዲህ አይልም፡፡
እንዲያውም በመጨረሻ «እኔኮ እወድዳችኋለሁ» ብለው የዓመቱን ታላቅ ቀልድ ቀለዱ፡፡ ምክትላቸውም ብቅ ብለው «የሳተላይት ቴሌቭዥን አትዩ፤ እነርሱ ናቸው የሚያታልሏችሁ» ብለው በአሥር ዓመታት ውስጥ ተገኝቶ የማያውቅ ምክር ሕዝቡን መከሩ፡፡
«አልወርድም» አሉ ሙባረክ፡፡ ስዕለት ያለባቸው ይመስል ከመስከረም ወዲህ ወይ ፍንክች አሉ፡፡ ሕዝቡ ደግሞ ከጣሂር አደባባይ ወይ ፍንክች አለ፡፡ የሚያዩት ነገር እውነት ሳይመስላቸው፤ የናቁት ሕዝብ እየገነገነ መምጣቱ ሳይገለጥላቸው፤ ሰባት ወር የቀረውን መስከረም ሕዝቡ አሳጠረውና ሙባረክ ወረዱ፡፡
እኔ እንጃ፤ አሁን ራሱ ሲያስቡት «በሕልሜ ነው፣ ወይስ በውኔ፣ ወይስ በቴሌቭዥን» እያሉ ሳይቃዡ አይቀሩም፡፡ ከሳምንት በፊት እንኳን፣ አሁን የሆነው ነገር ሊሆን ይችላል ብለው ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ አልነበራቸውም፡፡ ጦር ጭነው ያገኙትን መንበር ጦር ያልጫነ ያስለቅቀኛል ብለው እንኳን በታሪክ በተረት አስበውት አያውቁም፡፡ ግንመናቅን የመሰለ የመሪዎች ክፉ በሽታ የለም፡፡ ቀን ከደረሰ፣ አምባ ከፈረሰ የተናቀው ተነሥቶ መሳፍንቱን ሁሉ ነድቶ ጎንደር ቤተ መንግሥት ይገባል፡፡ ቀን ከደረሰ፣ አምባ ከፈረሰ፣ የበጎች እረኛ ሙሴ እሥራኤልን እየመራ የኤርትራን ባሕር ያሻግራል፡፡ ቀን ከደረሰ፣ አምባ ከፈረሰ አገር ያንቀጠቀጠ ፈርዖን ባሕር ውስጥ ይወድቃል፡፡ ቀን ከደረሰ፣ አምባ ከፈረሰ ትንኝ ዝሆንን፣ ቁንጫም አንበሳን ትረታለች፡፡
ቀን ሲደርስ፣ አምባ ሲፈርስ በፈቃድ ያልሆነ በግዳጅ ይሆናል፤ እንደ ደጃች ወንድይራድ ኮሶ ያስጠጣል፤ እንደ እቴጌ መነን ባቄላ ያስፈጫል፤ እንደ ሙባረክ የሠላሳ ዓመት ቤት ጥሎ ያስኬዳል፡፡
ምናለ የአፍሪካ እና የዓረቡ ዓለም መሪዎች ዛሬ እንኳን ቢነቁ፡፡ ቀን እየደረሰ አምባ እየፈረሰ እኮ ነው፡፡