Saturday, October 24, 2009

"ሰው በራሱ ሳንባ እንዳይተነፍስ እየተገደደ ነው"

"ሰው በራሱ ሳንባ እንዳይተነፍስ እየተገደደ ነው"

የህወሓት መስራችና አባል የነበረዉ አቶ አስደገ ገብረስላሴ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ያደረገዉ ቆይታ ጠቃሚ ሆኖ ስላገኘሁት እንድታነብቡት በዚህ ዓምድ ሲዘገብ፣ የህወሓት ምስጢር/ገበና ያዉቃሉ ከምንላቸዉ ሰዎች መካከል እስካሁን ድረስ በድፍረት እየወጡ የድርጅታቸዉን ገበና በማጋለጥ ሃላፊነታቸዉን ለመወጣት የሚጥሩትን አቶ ገብረመድህን አርአያ እና አቶ አስገደ ገብረስላሴን ከልቤ ሳላመሰግን አልቀርም፤፤ የድርጅቱን ወንጀል ላለማጋለጥ ዉጠዉት ዝም አሉ ሁሉ ከመጠየቅ ወደ ሗላ እንደማይሉ ላረጋግጥላችሁ እፈልጋለሁ፣፣ በተለይም በወቅቱ በተቃዋሚዎች ፖለቲካ ዉስጥ ገብተዉ የድርጅታቸዉን ገበና ሆን ብለዉ ላለማጋለጥ “ሸፍነዉት” በደፈናዉ “ኩት ኩት” የሚሉትን እነ ገብሩ አስራትን፤ስየ አብርሃን አረጋዊ በርሄን እና የመሳሰሉት ዛሬም እነሱን ከመታገል ወደ ሗላ እንደማንል ይወቁት።የሚያለቅሱላቸዉ ደናቁርት ደጋፊዎቻቸዉም ጭብጨባቸዉን እንዲያቆሙ ምክር እንለግሳለን። በነገራችን ላይ የአስገደ ገብረስላሴ መጻህፍት ከትግራይ ተልኮልኝ ለማንበብ እየተዘጋጀሁ ነኝ። ካነበብኳቸዉ በሗላ አስተያየቴን እሰጣለሁ። እስካዘዉ ድረስ ግን ካሁን በፊት እንደሂየስኩት ሁሉ በጎ እርምጃ ሲወስድም ማበረታታቱ የግድ ነዉ። ለወደፊቱ በሌሎች ሰዎች በመጥፎ ማህደር እስካልተከሰሰ ድረስ ለዛሬ ግን አቶ አስገደን ለድፈረቱ እና ላሳየዉ ትረት ከልቤ ሳላመሰግነዉ አላልፍም። ለሪፐርተር ጋዜጣ በኢትዬጵያን ሰማይ አንባቢ አመስግናለሁ። ጌታቸዉ ረዳ http://www.ethiopiansemay.blogspot.com/ Wednesday, 21 October 2009 "ሰው በራሱ ሳንባ እንዳይተነፍስ እየተገደደ ነው"አቶ አስገደ ገ/ስላሴ፣ የህወሓት መስራችና አባል የነበሩ አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ከ11 የህወሓት መስራቾች አንዱ ናቸው፡፡ ወደ ኤርትራ ወታደር መርተው ለእርዳታ ከሄዱት የሕወሓት አመራሮች አንዱ ናቸው፡፡ አቶ አስገደ በ1993 ዓ.ም. ድርጅቱን ለቀው የወጡ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በተቃዋሚነት እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ "ጋህዲ" በሚል ርዕስ ሁለት መፅሐፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ መፅሐፍቱ በህወሓት ነበረ ያሉትን ኢዲሞክራሲያዊ አሰራርና ድርጅቱ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ ፈፅሟል ያሉትን ስህተት በዝርዝር ያስቀምጣሉ፡፡ በዚህና በወቅታዊው ፖለቲካና ረሃብ ዙሪያ የማነ ናግሽ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የትግራይ ሕዝብ ያካሄደው ፀረ-ደርግ ትግል መስራችና እስከ መጨረሻ የተታገሉ ሰው ነዎት፡፡ ዓላማየ ተሳክቷል ብለው ያምናሉ? ከህወሓት እንዲወጡ ያስገዳድዎት ምንድን ነው? አቶ አስገደ፡- ትግሉ ዋነኛው ግቡን መቷል፡፡ በርካታ ደካማ ጐኖች ቢኖሩም ዓላማችን የነበረውን የደርግ ስርዓት መደምሰስ ስለነበር ግቡን መቷል ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ በፖለቲካ በኩልም ቢሆን በ1983 የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲቋቋሙ፣ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲኖር የሚፈቅድ ህገ መንግሥቱ መፅደቁ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሆኖም ግን ህወሐት/ኢህአዴግ ይህንን ያድርግ እንጂ መጀመሪያ ይዞት የነበረው መስመር እየሳተ በአገር ደረጃ ለስልጣን ብቃትና ችሎታ ያላቸው አለማሳተፍ እየታየ መጥቷል፡፡ አልፎ ተርፎ ስልጣን በዘመድ አዝማድ፣ ህብረተሰቡን ታማኝና የማይታመን፣ "ወገኔ እና ባዕዳ" አድርጓታል፡፡ ለ17 ዓመታት የታገሉ ታጋዮችም ያነሱዋቸው ዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ማፈን ጀመረ፡፡ ለምሳሌ እንደ ኤርትራ ሪፈረንደምና አካሄድ አገባብ አይደለም፣ ድርጅቱ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ አሰራር እየጠበበ ነው፣ ህውሐት/ኢሕአዴግ በጠዋቱ "ሳይጎረምስ ያረጀ ድርጅት" እየሆነ ነው፣ ድርጅቱ ከታች እስከ ላይ እየበሰበሰ ነው፣ ውስጣችን እንፈትሽ የሚሉ ጥያቄዎች ከሚያነሱ መካከል አንዱ ነበርኩኝ፡፡ ስለዚህ 84ና 85 ዓ.ም. እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች በስፋት ሲነሱ ከቆዩ በኋላ ድርጅቱ ምንም ችግር የለብኝም ታጋዮቼ ግን በሽቅጧል ብሎ ከ32 ሺህ ታጋዮች በላይ ከአንድ ዓመት ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ተኩል አስሯል፣ አባሯል፡፡
ስለዚህ እንዲህ የድርጅቱ ዴሞክራሲ እየተሰነጠቀ ሲመጣ የእኔም ልብ እየተሰነጠቀ፣ እየሸሸ መጥቷል፡፡ ከዚያ በኋላ በጤና ምክንያት አድርጌ ከመከላከያ ልሰናበት ቻልኩኝ፡፡ ከዚያም አባል ሆኜ ትንሽ ብቆይም አሁንም አልተስተካከለም፡፡ በ1993 ዓ.ም. ጨርሼ ተውኩት፡፡ ሪፖርተር፡- በቅርቡ ጋህዲ በሚል ሁለት ተከታታይ መፃህፍት ለንባብ አብቅተዋል፡፡ በትግል ወቅት ህወሓት በተለይ የውስጥ የዴሞክራሲ ጥያቄ፣ የኤርትራ ጉዳይ በተያያዘና በአንዳንድ ጉዳዮች ወቅሰዋል፡፡ ያ ሁሉ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አሰራሮች ፓርቲው ውስጥ ሲሰራ፣ እናንተም ነበራችሁበት፡፡ አሁን ከመውቀስ በወቅቱ መጠየቅና ድርጅቱን መተቸት አልነበረባችሁም? አቶ አስገደ፡- በርካታ የዴሞክራሲ ጥያቄ ያነሱ "ሓንፈሽቲ" (በጥባጮች"፣ ኢህአፓ፣ ኢድዩ፣ ተወላዋይ ሃይሎች እየተባሉ ታስረው ሞራላቸው የወደቀ ነበር፡፡ ጥያቄዎች ሁሌም ይነሱ ነበር፡፡ ኤርትራን በተመለከተ ምን እያደረግን ነው? የባህር ወደብ ጥያቄ እንዴት ሊሆን ነው? ኢኮኖሚያዊ ግንኙነታችንስ እንዴት ሊሆን ነው? የመሳሰሉ በርካታ ቁልፍ ጥያቄዎች እየተነሱ ነበር፡፡ ሻዕቢያን ለማዳን የሚደረገው ጉዞም ለምን ሰራዊት ወደ ኤርትራ እንልካለን፣ ወታደራዊ ስትራቴጂ ልዩነት አለን እያልን ለምን በአንድ ግንባር እንሰለፋለን? ይሄ ድርጅት በተለይ ለትግራይ ሕዝብና ለህወሓት ጥፋታቸው እንጂ ልማታቸው የማይመኝ ነው ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች በየስብሰባውና ኮንፈረንሶች ሲነሱ ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጥያቄዎች በግንባር ቀደም ያነሱ የነበሩት ታስረው፣ ተፈተዋል፡፡ ስለዚህ ትልቅ ተቃውሞ ነበር፡፡ በእርግጥ፣ በጋህዲ ለአብነት የጠቀስኩዋቸው ጥቂቶች ይሁኑ እንጂ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ታጋይ ተቃውሞ እንደነበረው ይታወቃል፡፡ በድርጅቱ የሚሰጥ መልስ ግን የለም፡፡ ከማሰርና ከማፈን ውጪ፡፡ትቃወሙ ነበር ወይ? ላልከኝ አዎ እንቃወም ነበር፡፡ ግን እስከ መጨረሻ ጠንክረን የምንሄድበት አልነበረም፡፡ እስቲ መጀመሪያ ደርግ ይውደቅ እንላለን፡፡ ድርጅቱ አንድ ሁለት እያለ ሲያስርና ሲፈታ በሌሎቻችን ላይ የመደናገጥና የመፍራት መልክም ነበር፡፡ ስለዚህ የአመራሩ ጡንቻ እንዲያብጥና ("ንኽግብል" እንደ ዘንዶ ሆኖ) እንደፈለገ እንዲያደርግ፣ የእኛም አስተዋፅኦ ነበረው ማለት ነው፡፡ የፈለገ ጥያቄ ብናነሳም እስከ መጨረሻ የሄድንበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ ስለዚህ በጋህዲ የፃፍኩት የነበረ ሐቅ ነው፡፡ በድርጅቱ አሁንም ቢሆን ለመሰነጣጠቅ ያደረሰው የቆየ ችግር ነው፡፡ ችግሩ በውስጡ ብቻ አይደለም፡፡ ከሌሎች ድርጅቶች ለምሳሌ ከኢድዩ ጋር የተደረገው ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ሊፈታ ይችል የነበረ ነው፡፡ የህወሓት ትልቁ ችግር የነበረው የአካባቢው ንጉስ መሆን ይፈልግ ሰለነበረ ነው፡፡ በሌላ በኩል ከኤርትራ ጋር በተያያዘ፣ ሻዕቢያ ለእኛ ምንም አስተዋፅኦ የሌለው በተደጋጋሚ እየበደለን ነው የሚል ታጋዩ ጥያቄ ሲያነሳ ዝም በል እየተባለ ሲታፈን ነበር፡፡ አሁን ያለው አካሄድም ከዚያ ጀምሮ የመጣ ባህል ነው፡፡ ስልጣን ከተያዘ በኋላ ግን እነዚያ የተለያየ ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩት እንዲወገዱ፣ እንዲባረሩ ተደርጓል፡፡ ሌላ ቀርቶ መሪዎች አምተሃል እየተባለ የታሰረ ብዙ ነው፡፡ ይሄ እኔ ተደብቄ የምናገረው ጉዳይ አይደለም፡፡ አሁንም መከላከያ ውስጥ ያለው ታጋይ ሁሉ የሚያውቀው ነው፡፡ ያልተነቀፈ፣ ያልተወቀሰ የለም፡፡ ይሄ ታሪክ ነው፣ ሕዝብም ማወቅ አለበት ብዬ ነው የፃፍኩት እንጂ ታጋይ ሁሉ የሚያውቀው ነው፡፡ ሪፖርተር፡- መጽሐፍዎ ላይ አንዳንድ ትችቶችም እየተሰነዘሩ ነው፡፡ ህውሓት በተለይ ወደ ኤርትራ የላካቸው የታጋዮች ቁጥር አስገደ አጋኖቷል፣ ህውሐት ያኔ 60 ሺህ ያህል የሰራዊት ቁጥር አልነበረውም፣ እንዲሁም ድርጅቱ ውስጥ የነበረው የአወራጃዊነት ችግር (ሕንፍሽፍሽ) እንደነበር፣ በመጨረሻ አንደኛው ወገን እያሸነፈ መጥቶ እስከ አሁን ተደራጅቶ የመንግሥትም ሆነ የፓርቲ ቁልፍ ቦታ ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ አስመስለው ያሳዩ" ነገር አለ፣ አቶ አስገደ፡- ወደ ኤርትራ የተላከው ታጋይ ቁጥር ተጋኗል የሚባለው የተጋነነ አይደለም፡፡ በእያንዳንዱ ወቅት የያዝኩት ማስታወሻ አለኝ፡፡ ያኔ ያ ቁጥር የሚያክል ሠራዊት አልነበረንም የተባለውም እውነት ነው፡፡ በመጽሐፉ ያስቀመጥኩት ኤርትራ በተለያዩ ጊዜያት የገባ ሠራዊት ነው፡፡ ለአብነት ሁለት ነገር ልንገርህ፡፡ ወደ ሻዕቢያ (ስልጠና እንዲወሰዱ ተብለው) የሄዱት እና ምሽግ የገቡት መጀመሪያ 3700፣ ቀጥሎ 3800 ቀጥሎም 2400፣ 4300". ነበሩ፡፡ ይሄ ማለት ከመጀመሪያ እስከ ሦስተኛ በአንድ ምዕራፍ ነበሩ፡፡ አራተኛው ሲገባ ግን እነሱ ወጥተዋል፡፡ 4300 ብቻ ቀሩ ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የተመለሱት በቀይ ኮከብ ዘመቻ ተቀላቅለው ገብተዋል፡፡ አንድ ታጋይ ሦስት ጊዜ የሄደበት ሁኔታም አለ ማለት ነው፡፡ ሌላ ጀብሃ ለማጥፋት በተደረገው ውጊያ ቀዳማይ ዙር ከቀይ ባህር እስከ መንደፈራ 6000 የህወሓት ታጋይ ተሳትፏል፡፡ ከመንደፈራ ቆይታ ደግሞ ከመንደፈራ እስከ ሱዳን 7000 ታጋይ ተሳትፏል፡፡ በመጀመሪያ ምዕራፍ የተሳተፉት በሁለተኛ ዙርም ተካፍለዋል፡፡ ስለዚህ በተለያየ ጊዜያት ወደ ኤርትራ እየመላለሰ የዘመተ ሠራዊት እንጂ በአንድ ጊዜ 65 ሺህ ሠራዊት ዘምቷል ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ ቀይ ኮከብ ዘመቻ የዘመቱ ብርጌዶች ተመልሰው ነበር፣ ነገር ግን በ"ሰላሕታ ወራር" ደግመው ተመልሰው ዘምተዋል፡፡ ስለዚህ ሁለትና ሦስት ጊዜ ተመልሶ የዘመተና የተዋጋም ጭምር ተደምሮ ነው እንደዚህ የሚመጣው፡፡ እንደውም፣ በትግራይ ኤርትራ ድንበር አካባቢ የተደረጉ ጦርነቶችን አላካተትኩም፡፡ አድያቦና ገርሁስርናይ፣ አካባቢ የተደረጉ ውጊያዎች አላካተትኩም፡፡ መስዋእትም ቢሆን እዚያ ኤርትራ መሬት ውስጥ ገብቶ የተሰው ብቻ ነው ያስቀመጥኩት፡፡ በአንድ ምዕራፍ ግን በሳሕል ተራሮች ምሽግ የሚጠብቅ ሰራዊት የህውሓት 13 ሺህ የእነሱ 7 ሺ (2ለ1) በኋላም (3ለ1) የሆንበት ጊዜ ነበር፡፡ ይገባል፣ ይወጣል፣ ይገባል፣ ይወጣል". (ካልተሰዋ"፡፡ ብዙ ደግሞ መስዋእት ከፍሏል፡፡ ሪፖርተር፡- እርስዎ አንዳንድ የድርጅቱን አመራሮች የሻዕቢያ ሎሌ የሚል ቅፅል ሰጥተዋቸዋል፤ አቶ አስገደ፡- አሁን ህወሓት የሻዕቢያ ሎሌ አይደለም ነው የሚሉት? ለትምክህት ኃይሎች አሳልፈህ ሰጠኸን ያሉኝም አሉ፡፡ እኔ የትግራይ ሕዝብን ወይም ታጋዩን አይደለም ሎሌ "ጊላ" ያልኩት፡፡ አንዳንድ አመራሮች ግን የሕዝቡንና የታጋዩን ጥያቄ እያፈኑ፣ ድርጅቱ በደርግ ላይ በሚፈፅመው ጠንካራ ወታደራዊ ጀብድ ተጠቅመው ከዕውቅና ውጪ ማንም ሳይፈለግ ውስጥ ለውስጥ ከሻዕቢያ ጋር ይሰሩ ስለነበር ነው "ጌታና ሎሌ" ያለኩዋቸው፡፡ በወቅቱ ዋነኛ ተዋናይ የነበሩ ደግሞ አባል ፖሊት ቢሮ የነበሩ ናቸው፡፡ ድርጅቱ እየሰፋ ሲመጣም እነ አቶ ስዬ አብርሃ፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳኤ". ተመርጠው ገብተዋል፡፡ እነዚህ ግን ወደ ኤርትራ ሠራዊት እንላክ ማለትን ሲቃወመው ነበር፡፡ ግን አልገፏበትም፡፡ አንድ ነገር ያደረጉት አለ፡፡ ጀነራል ሐየሎም፣ ጀነራል ፃድቃን እና ስዬ አብርሃ ሂዱ ጦርነት ምሩ ተብለው (በ1973 ዓ.ም". ወደ ኤርትራ ሲላኩ በማናምንበት የጦርነት ስትራቴጂ አንገባም ብለው እምቢ ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ ግን በነበረ ሻጥር ጠንክረው አልገፉበትም፡፡ ፖሊት ቢሮ የኤርትራ ተልዕኮ ነበር የሚፈፅመው፣ ማእከላይ ኮሚቴና ወኪል አመራር የነበሩ ደግሞ ውሳኔው ተቃውመው ማቆም የቻሉ አልነበሩም፡፡ ሕዝብና ታጋዩ እየተቃወመ ጥያቄ ሲያነሳ ከአመራሩ ግን የገፉበት አልነበረም፡፡ ስለዚህ አመራሩ በአጠቃላይ የሻዕቢያ ሎሌ ነበር ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ ከኤርትራ ጋር በተያያዘ በማእከላይ ኮሚቴ የነበሩ ልዩነቶች አይወጡም ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ነበር ያወቅነው፡፡ ከኤርትራ ጋር የሚደረግ ነገር ወንጀል ነው፡፡ ትክክል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ልአላዊነት የሚጥስ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆነን እናስብ ይሉ የነበሩ የተወሰኑ በመፅሐፌ ውስጥ ባስቀምጥም ሁሉም ማለት ይቻላል ሕዝብና ሠራዊት ይቃወመው የነበረ ጥያቄ ነው፡፡ የእነሱ የኤርትራ አቋም ይዘው በሠራዊቱም ሆነ በሕዝቡ ይቀሰቅሱና ይወተውቱ የነበሩ ደግሞ ነበሩ፡፡ ሁሉም ማንሳት አልቻልኩም እንጂ ለምሳሌ ብርሃነ ሞርተር፣ አለማየሁ ገዘሃይ የመሳሰሉ በርካታ ሰዎች በኮንፈረንስ የኤርትራ ጥያቄ አነሱ (ተቃወሙ) ተብለው እስር ቤት ገብተዋል፡፡ በህይወት ያሉት እነሱም አሁን የሚመሰክሩት ነው፡፡ የታሰሩበት ምክንያት በኤርትራ ላይ በነበራቸው የፀና አቋም (ጥያቄ) ነው፡፡ በተለይ ስለ ኤርትራ በተመለከተ ቅሬታ የነበራቸው በጣም ብዙ ናቸው፡፡ "ተራ" ገበሬዎችም ጭምር ጥያቄ እያነሱ ነበር፡፡ ኤርትራ ስትሉ ከየት ወዴት ነው? የባህር ወደብ ባለቤት የሆነው ኢትዮጵያስ ምን ልትሆን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች ሲያነሱ ነበር፡፡ ማሳሳቻ መልሳቸው ዕድገታችን በባህር ላይ የተወሰነ አይደለም ነው፣ አሁንም እንደሚሉት፡፡ ብዙ የአየር ማረፊያ ከሰራን ባህር ምን ይሰራል? የሚል አሰልች መልስ ነበር የሚሰጠው፡፡ "ሕንፍሽፍሽ" እየተባለ የሚጠራውም መጥፎ ስም ተሰጠው እንጂ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ የተነሳበት ነበር፡፡ አመራር በምልመላ መሆኑ ይቅር፣ ወኪል መሪነት የሚባል ነገር ይቅር፣ በዴሞክራሲያዊ አገባብ መሪዎቻችን እንምረጥ፣ ብቃት ያላቸው መሪዎች እንምረጥ፣ በጓደኝነትና በወዳጅነት (በቲፎዞ) አመራርን ማቋቋም ፍትሃዊነት አይደለም የሚሉ ጥያቄዎች የተነሱበት አጋጣሚ ነው፡፡ ሕንፍሽፍሽ አንድ ቀን ብቻ የተፈጠረ አጋጣሚ አይደለም፡፡ በመድረኩ ታጋዩ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ባነሳ ቁጥር ሕንፍሽፍሽ ፈጠረ እየተባለ እየተመታ ነው የመጣው፡፡ በኋላ (1993 ዓ.ም". የተፈጠረው መሰነጣጠቅም ቢሆን ያኔ የተፈጠረ ነው፡፡ ሕዝቡ በማእከላዊ ኮሚቴ የተፈጠረው መከፋፈል ነው ተጋኖ የሚታየው ከዚያ በፊት የነበረው መከፋፈልና ፀረ ዴሞክራሲያዊ አፈና (ለምሳሌ የ1985 ዓ.ም". ሕዝቡ ቦታ አይሰጠውም፡፡ 32 ሺ ታጋዮች "ሲረፈቱ"ና ሲባረሩ በየጎዳናው ሲወድቁ አይተናል፡፡ የህውሓት ዋነኛው መዋቅር የፈረሰው ያኔ ነው፡፡አሁን ስልጣን ላይ ያለው የአመራር ቡድን ተቀናቃኝ የመሰለው ሁሉ ቀስ በቀስ እያስወገደ ነው የመጣው፡፡ ይሄ ቡድኑ የራሱ "ሎሌ" እያጀበ ነው የመጣው፡፡ ሪፖርተር፡- በተለይ ጋህዲ 2 ላይ እያንዳንዱ ታጋይ (አመራር) አካባቢው የጠቀሱበት ሁኔታ አለ፡፡ ጎጠኝነት/አውራጃዊነት የሚያስፋፋ ነው የሚሉ ትችቶች አሉ፣ ለምን አስፈለገ? አቶ አስገደ፡- እንዲህ ዓይነት ወቀሳ የሚያበዙ ታሪክ ይሸፈን የሚሉ ናቸው፡፡ ታሪክ የሰራ ሰው የተወለደበት አካባቢ መገለፅ አለበት የሚል አቋም ነው ያለኝ፡፡ ይህንን መግለፅ አውራጃዊነት አያስብልም፣ ጀግና ከሆነ ታሪክ ነው፣ ቅርስ ነው፡፡ ይህንን እየተቃወሙ ያሉት ግን ታሪኩ አጠቃላይ (የጋራ) ብቻ እንዲሆንና ያለታሪካቸው በጀግንነት መታቀፍ ስለሚፈልጉ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው አመራር ታሪክ የሰራ አይደለም፡፡ በእርግጥ በመከላከያ ብዙ ታሪክ የሰሩ ጀግኖች አሉ፡፡ በሌላ ቦታ ግን ታሪክ የሰራ አይደለም፡፡ ስለዚህ ማን ምን ጀብድ ፈፀመ ተብሎ ከተፃፈ አሁን ስልጣን ላይ ያለው አካል ወደ ፊት ስለማያመጣ በሽፍጥ ተዳፍኖ እንዲያልፍ ነው የሚፈልጉት፡፡ እያንዳንዱ የነበረው አቋም የሰራው ታሪክ የተወለደበት አካባቢ መግለፅ እንደ ስህተት አላየውም፡፡ አስገደ የሰራው ታሪክ እንዲፃፍለት ነው የሚፈልገው፡፡ በሰው ታሪክ መኩራራት አልፈልግም፡፡ ራስ አሉላ ጀግና ነበሩ፡፡ የተወለዱበት አካባቢ ተምቤን ነው ቢባል ምን ክፋት አለው፡፡ ሓየሎም አድያቦ ዓዲነብሪኢድ ነው ቢባል ምንድን ነው ችግሩ? ይመስለኛል፣ እስከ አሁን ማንም ሰው በህይወት ተመስግኖ አያውቅም በዚህ ድርጅት፡፡ በመቃብሩ ነው የሚመሰገነው፡፡ እሱም ላይ አድልዎ አለበት አሁንም ጭምር፡፡ አሁን የድርጅቱን ታሪክ የሚመለከት መፃሕፍት እየተፃፈ ነው፡፡ እኔ ጋህዲ ጽፌያለሁ፡፡ እስካሁን ማንም ዓይነት የሚዲያ ሽፋን ሆነ ስፖንሰር የለንም፡፡ ስፖንሰር እንዲደረግ ሲጠየቅ መጀመሪያ ድርጅቱ መጽሐፉን ይየው ነው የተባልኩት፡፡ ፅንአት ግን ዘጠና በመቶ ውሸት ላይ የተመሠረተ መወድስ በአቶ ስዩም መስፍን ላይ ስለተፃፈ የትእምት (ኤፈርት) ብቻ 12 ተቋማት፣ የመንግሥት ተቋማትም 12 ስፖንሰር አድርገውት ዱባይ ታትሟል፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ መጥቶ በሂልተን በነፃ ተመርቋል፣ በድጋሚም በመቀሌ ዩኒቨርሲቲም ተመርቋል፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥን ጋዜጦች የሚያወሩት ሁሉ ስለ እሱ ነው፡፡ ጋህዲ ግን ስፖንሰር የሌለው፣ ዜና አይሠራለት፣ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ጭራሽ እንዳይሸጥ እየታገደ ነው፡፡ ለምሳሌ ፍፁም በርሄ የሚባል ሽሬ ከተማ የሚኖረው ለምን ጋህዲ መጽሐፍ ትሸጣለህ ተብሎ በሕዝብ ፊት ተገመገመ፣ እንዳይሸጥም ተከልክሏል፡፡ ሌሎች መጽሐፍትቤትም እንደዚሁ ገበያ ላይ እንዳያውሉ ተደርገዋል፡፡ ፀረ ሕዝብ መጽሐፍ ሸጣችሁ ተብሎ በሻጮቹ ላይ ብዙ እንግልትና መከራ ደርሶባቸዋል፡፡ ስለዚህ በተመሳሳይ ታሪክ የተፃፉ መጽሐፍት ቢሆንም የአንዱ ወገንና የሌላ ወገን ተደርጎ ለሁለት ተከፍሏል፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ፣ የግለሰብ ስም ለምን ተፃፈ፣ አገሩ ለምን ተገለፀ የሚለው የራሱ የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ ለምሳሌ ሕንሽፍሽፍን እንደርታ፣ ተምቤን መቀለ" ፈጠሩት ነበር የሚባለው፡፡ ነገር ግን የዓድዋና የሽሬ ልጆች ድርጅቱ ውስጥ ዴሞክራሲ የለም ብለው የተቀጡና የታሰሩ አሉ፡፡ ስለዚህ ስልጣናቸውን ለማጠናከር ያመጡት ነገር ነው፡፡ ዝም በል አትናገር ብለው ለማፈን ያመጡት መሣሪያ ነው እንጂ ጥያቄው አውራጃዊነት አልነበረውም፡፡ አብዛኛዎቹ ባለስልጣናት ጋህዲ ውስጥ ለውስጥ እንዳነበቡት አውቃለሁኝ፡፡ ውስጥ ለውስጥ ከማጥላላት ስህተት ነው የሚሉት በግልፅ መተቸት መልስ መስጠት ይችላሉ፡፡ አሁን ያለው መድረክም ለማማት የሚፈቅድ አይደለም፡፡ አዲሱ ትውልድ ሐሜትና አሉባልታ የሚሸከም አይደለም፡፡ እኔ ግን በሕይወቴ ሦስት መንግሥታታ አሳልፌያለሁ፣ በዕድሜዬ ትልቅ ነኝ፣ አስተሳሰቤ ግን የ21ኛው ክፍለ ዘመን ወጣት ነው፡፡ ሪፖርተር፡- ጋህዲ ከፃፉ በኋላ ከመንግሥት አካላት የደረሰብዎት ነገር አለ? አቶ አስገደ፡- ጋህዲን ያነበበ ሁሉ አድናቆትን ነው የሚገልፅልኝ፡፡ ይሁንና ከመንግሥትም ቢሆን የደረሰብኝ ነገር የለም፡፡ ሆኖም መጽሐፉን ማጥላላት፣ ገበያ ላይ እንዳይውል/እንዳይሸጥ የተለያየ ፕሮፖጋንዳ እየነዙ፣ የመጽሐፉ አዘጋጅ አስገደ ሊታሰር ነው፣ እናንተ ለምን ሸጣችሁ ተብላችሁ ልትታሰሩ ትችላላችሁ እየተባለ እያስፈራሩዋቸው ነው፡፡ ሌላ በምርቃት ጊዜ እነሱን የሚያወድሱ እንደ ፅንዓት ያሉ መጽሐፍት ሲመረቁ ባለስልጣናቱ እየተገኙ ያለቅሳሉ እኔ በበኩሌ ምን እንደሚያስለቅሳቸው አላውቅም፡፡ እኔ ግን አንዳንዶቹን ጠርቻቸው እንኳን በስፍራው ሊገኙ ቀርቶ መጽሐፉን ተደብቀው ነው የሚያነቡት፡፡ ከሁሉ በላይ ግን አንድ ነገር እንደ ባህል ተለምዷል፡፡ ትግራይ የተሰራ ይሁን ጋምቤላ ሌላም አካባቢ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡ እነሱ ግን የሚያወሩት በተለይ ጋህዲ (ቁ.1) ወደ አማርኛ ከተተረጎመ በኋላ አስገደ ጠላት ነው፣ ታሪካችን አሳልፎ ለትምክህተኞች ሰጠ የሚባል ነገር አለ፡፡ ሪፖርተር፡- አሁን በተቃዋሚነት እየተንቀሳቀሱ ነዎት? አቶ አስገደ፡- 97 ምርጫ በመቀሌ ተወዳድሬ ብዙ የሕዝብ ድምፅ አግኝቻለሁ፡፡ አሁን ደግሞ እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡ ህውሓት በአስተሳሰብም በዕድሜም አርጅቷል እንዲቀየር እፈልጋለሁ፡፡ ለሕዝብ የሚጠቅም ድርጅት አይደለም፡፡ ስለዚህ እየተንቀሳቀስኩ ነው፡፡ በተናጠልም በተደራጀም እንቀሳቀሳለሁ፡፡ ሪፖርተር፡- ራስዎ መስርተው ያሳደጉት ድርጅት ሲቃወምዎት ምን ይሰማዎታል? አቶ አስገደ፡- አሁን ተስፋ ያለው የተደራጀ እንቅስቃሴ (መድረክ) አለ፡፡ ተስፋ ያለው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ሳይና ስንቀሳቀስ ድሮ ህወሓት ላይ የነበረኝ ቁርጠኛ ዓላማ እየታደሰ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ ህወሓት አሁን እየበሰበሰ መጥቷል እዚያ ውስጥ ሆነህ የሚስተካከልም አይደለም፡፡ አብረህ ልትበሰብስ ካልሆነ፡፡ ስለዚህ ይህንን የዛገ ያረጀ አስተሳሰብና ድርጅት መቃወም ዳግም የትግል ትንሳኤ አድርጌ ነው የምመለከተው፡፡ አሁን ደግሞ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር አብረን ነው የምንታገለው፡፡ በእርግጥ እነሱ፣ አንድ ሰው ሲቃወም የተለያየ ስም ነው የሚሰጡህ ትምክህተኛ፣ ቅንጅት የመሳሰሉ ስሞች ይሰጡናል፡፡ አሁን በርሀ ላይ ትተናቸው በመጣን ሰማዕታት ስም እየተጠራ አፈና ነው እያካሄደብን ያለው፡፡ ካሃዲዎች እኛ ሳንሆን እነሱ ናቸው፡፡ ሕዝብ እየተራበ ሌሊት ሙሉ መጠጥ እየተጎነጩ የሚያድሩ፣ ሕዝብን በጉቦ ያሸማቀቁ፣ ወገናዊነት የሚፈፅሙ እነሱ ናቸው፡፡ ልማት የሚባል ሳይኖር ልማት አለ፣ ፍትህ አለ፣ ዴሞክራሲ አለ እያሉ ሕዝብን የሚያደነቁሩ እነሱ ናቸው፡፡ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ተንቀሳቀሱ ብለው የሚያጥላሉን ትግራይ የብቻቸው የተከለከለ መጋጫ እንድትሆን ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ትግራዋይ ተርቧል፣ ተጠምቷል፣ የውሸት ዴሞክራሲ፣ የውሸት ልማት፣ ዝናብ ጠባቂ ሆኗል፡፡ በእርግጥ ይህ ሁሉ የኢትዮጵያ አካባቢ የሚታየው ችግር ነው፡፡ ሪፖርተር፡- በህውሓት ላይ ቅሬታ አለዎት፡፡ መሠረታዊ የሆነ የአቋም ልዩነት ወይም የማይቀበሉት ርእዮተ ዓለም አለዎት ወይስ? አቶ አስገደ፡- እኔ ከድርጅቱ ጋር ያለኝ ልዩነት ተራ ቂም በቀል አይደለም፡፡ መሠረታዊ ልዩነት አለኝ፡፡ አሁን ድርጅት የሚከተለው አብዬታዊ ዴሞክራሲ የሚባል ስርዓት አላምንበትም፡፡ ሊበራል ዴሞክራሲ ስርዓት ነው የምቀበለው፤ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አጠባበቅ፣ ፕሬስ ህግ፣ ምርጫ፣ የህግ የበላይነት በመሰረቱ የለም፡፡ የኢኮኖሚ ፖሊሲውም፡፡ ግብርና መርና የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ተከትለን ወደ ኢንዱስትሪ እወጣለሁ ይላል፡፡ ይህ የትም አያደርስም፡፡ እስከ አሁን ሕዝቡ በዚህ ፖሊሲ ከረሃብ ሊያወጣው አልቻለም፡፡ ዓፈና ነው፡፡ ከዚህ ዓፈና መውጣት አለብን፡፡ አሁን በቴሌቪዥን፣ ሬዲዮ፣ ጋዜጣ ሌት ተቀን የሚለፈልፉት ምንም ተአማኒነት የለውም፡፡ ሰው በራሱ ሳንባ እንዳይተነፍስ እየተገደደ ነው ያለው፡፡ ሪፖርተር፡- ሕዝቡ "በራሱ ሳንባ እንዳይተነፍስ" እየተደረገ ነው ማለት ምን ማለት ነው? አቶ አስገደ፡- የፓርቲ አባልነት በአሁኑ ወቅት በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ገብቷል፡፡ በመምህራን ውስጥም ገብቷል፡፡ መምህር ከሆነ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማስተማር አለበት፡፡ አባል መሆን አለበት፡፡ ልጆችም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ታንፀው እያደጉ ነው፡፡ ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉት ተቋማት በአባልነት እየተጨናነቁ ነው፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ጨርሰህም አባል ካልሆንክ ሥራ የለም፡፡ አንድ አራት ነጥብ ያለው የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እያለ አባል የሆነ ባለ ሁለት ነጥብ ቅድሚያ ይቀጠራል፡፡ ለትምህርት የሚላኩት በነጥባቸው አይደለም፡፡ ቅድሚያ ለአባላት ነው የሚሰጠው፡፡ ለትምህርት ስልጠና የሚወስዱም፣ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው የሚሰለጥኑት፡፡ በኋላም አባል እንዲሆኑ ይጠየቃሉ፡፡ ምን አማራጭ አላቸው፡፡ በአጠቃላይ ህወሓት የብዙኃን ፓርቲዎች መኖር አይቀበልም፡፡ የሕዝብ ማህበራት እንውሰድ፡፡ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ ማህበራት ሁሉ ሊቀመንበሮች የድርጅቱ ማዕከላይ ኮሚቴ ናቸው፡፡ በየዞኑ ያሉት የማህበራቱ ኃላፊዎችም ካድሬዎች ናቸው፡፡ በየወረዳውም የህወሓት ታጋዮች ናቸው፡፡ የገበሬዎች ማህበርም እንደዚህ ነው፡፡ የአነስተኛና ጥቃቅን ማህበራትም እንደዚሁ፡፡ አሁን ደግሞ ካፌዎችም፣ ጠላቤቶችም በማህበር ተደራጅተዋል፡፡ እነዚህ ማህበራት በሙሉ አባላት ናቸው፡፡ ግዴታ ነው፡፡ ገጠርም ብትሄድ ሴፍትኔት የሚባል ፓኬጅ አለ በዕርዳታ የሚሰጥ፣ ቅድሚያ ለአባል ነው፡፡ ህወሓት የሚተች፣ የሚነቅፍ ከሆነ አይሰጠውም፡፡ ሌላም የደደቢት ብድር ያለው ብዙ ነው፡፡ አምጣ እንዳይሉት አባል ሆኖ ነው የሚኖረው፡፡ ሕዝቡ በተለያየ መንገድ ነው የታሰረው፡፡ እንዲህ ዓይነት አሰራር በደርግ ጊዜም አልነበረም፡፡ የህውሓት ሰንሰለት ሕዝቡ ሊያንቀሳቅሰው አልቻለም፡፡ ለምሳሌ ዓረና ትግራይ የሚባል ፓርቲ ከተመሰረተ በኋላ ከተሞች ውስጥ እያነቃነቀ ነው ያለው፡፡ ወደ ገጠር ግን እንዳይገባ ገትረው ይዘዋል፡፡ በሩ ዝግ ነው፡፡ የዓረና አባል የሆነው በአንዳንድ አካባቢ ትግረኛ ተናጋሪ ቅንጅት እያሉ ያጥላሉታል፡፡ ለቤተሰቡም አስጊ ሆኗል፡፡ ከአንድ የዓረና አባል ጋር ሻይ ጠጣ ተብሎ ይሸማቀቃል፡፡ ሪፖርተር፡- እንዲህ ከሆነ እንደ ተቃዋሚ በክልሉ ለምርጫ 2002 እንዴት መንቀሳቀስ ይቻላል? አቶ አስገደ፡- ሕዝቡ ለውጥ ፈላጊ ነው፡፡ ችግሩ ግን አሁን በአካባቢው ከፍተኛ የረሃብ አደጋ አለ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ዓፈና አለ፡፡ ይሄ አንድ ችግር ነው፡፡ ነገር ግን አልጋ በአልጋ ትግል ደግሞ የለም፡፡ ጥሰህ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ላረጋግጥልህ የምፈልገው አንድ ነገር አለ፡፡ ሕዝቡ መቶ በመቶ ለውጥ ፈልጓል፡፡ ሕዝቡ ብቻ አይደለም የራሱ ታጋይ፣ ካድሬም ጭምር ተቃዋሚ ነው የሚደግፈው፡፡ ነፃ ታዛቢዎች፣ ነፃ ምርጫ ኮሚሽን፣ ነፃ ጋዜጠኞች ግን መግባት አለባቸው፣ የዓፈና መሳሪያም መቆም አለባቸው፡፡ የደህንነት፣ የጦር ሠራዊትና የፖሊስ ዓፈናዎች መቆም አለበት፡፡ እነዚህ እያሉ ግን አሁንም እንቅስቃሴ አላቆምንም፡፡ ምንም ሆነ ምንም ግን ከመወዳደር ወደ ኋላ አንልም፡፡ ሕዝቡ ራሱ ዓፈናው ሊያውቀውና ሊያስቆመው ይችላል፡፡ ሪፖርተር፡- በተለይ ዓረና ትግራይ፣ በትግራይ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ አለ ብሎ በተደጋጋሚ ስጋቱን እየገለፀ ነው፡፡ ፓርቲው በፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ እያዋለው ይሆን? በእውነት ምን ይመስላል? አቶ አስገደ፡- በግሌ የ77 ዓ.ም. ድርቅ ዳግም ተመልሶ እንዲመጣ አልፈልግም፡፡ ራያ ሦስተኛ ዓመቱ ነው፡፡ አምና የትግራይ ልማት ማኅበር ድርቆሽ አቅርባ ነበር፡፡ ነገር ግን ከ20 ሺ በላይ ከብቶች ሞተዋል፡፡ ዋጅራት፣ አፅብደራ፣ ዓዲ ኢሮብ፣ ምሥራቃዊ ዕዳጋ ሐሙስ፣ ሳዕሲዕ ባለፈው ዓመት ሙሉ ለሙሉ ድርቅ ነበር፡፡ ሌላ ቦታ ደህና ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ከወልዲያ እስከ ቆቦ አላማጣ ማሽላ በቅሎ ነበር፤ ሊደርስ ሲል አሯል፡፡ ከአላማጣ እንደርታ፣ 2ተ እውላዕሎ"ውቅሮ"፣ ዓጋመ እንዳለ ምንም እህል የለም፡፡ ቡቃያው ተቃጥሏል፡፡ ምክንያቱ ትግራይ ውስጥ ዝናብ የጀመረው ከ5 እስከ 8 ሐምሌ አካባቢ ነው፡፡ ነሐሴ 20 ነው ያቆመው፡፡ አልፎ አልፎም ቢሆን ትግራይ ውስጥ ዝናብ የነበረው ለ42 ቀናት ብቻ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ የአንድ ብር አምስት ይሸጥ የነበረው በለስ ዘንድሮ የአንድ ብር ሦስት ሆኗል፣ በጅምላ አምስት፡፡ እምባአላጅ፣ ዓዲሹሁ፣ ኮረም ደጋዎች እህል በቅሏል፡፡ ግን አሁን ዝናብ ያስፈልጋል፡፡ በምዕራብ እንደርታ ስሐርቲ ሳሞረ፣ አበርገለ፣ ቆላ ቴምቴን፣ ዓድዋ፣ ፅድያ ድርቅ ነው፡፡ ሰሜን ትግራይ ከዛላምበሳ ጀምረህ ብዘት፣ እገላ፣ ዓዲአርባዕተ፣ ስዕሲዕ፣ እስከ ባድመ እህል የለም፡፡ ሰቆጣ፣ ፀለምቲም እህል የለንም፡፡ በእንዲህ እያለ ግን የትግራይ ፕሬዚዳንት አቶ ፀጋይ በርሀ አምና 16 ሚሊዮን ኩንታል እህል አስገብተናል አሁን እጥፍ እናደርገዋለን ብለዋል፡፡ ህልም ነው፡፡ ዘንድሮ የትግራይ ወንዞች ምንም ውሀ የላቸውም፡፡ ደርቋል አክሱምና ሽሬ ውሃ የሚባል የለም፡፡ በየትኛው ግድብና መስኖ ነው አሁን እናስገባለን የሚሉት? ጋዜጠኞችም ሂዳችሁ እዩት ዘግቡት፡፡ በእርግጥ እግረ መንገዴን ልንቀፋችሁ እንጂ ጋዜጠኞች የትግራይ ችግርም አጀንዳችሁ አይደለም፡፡ በቅርቡ ብቻ ሪፖርተር መቀሌ ስላለው የውሃ እጥረት የዘገበው ነው ያየሁት፡፡ ሕዝቡም ደስ ብሎታል፡፡ ውሃ የሚባል የለም ሀቅ ነው የፃፋችሁት፡፡ ሪፖርተር፡- የዚሁ ሁሉ ረሃብ ምንጭ ምንድን ነው ይላሉ፣ መፍትሄውስ?
አቶ አስገደ፡- ረሃብ ከአፄ ኃ/ሥላሴ ጀምሮ ነበር፡፡ በደርግም በኢሕአዴግም አለ፡፡ መንስኤው የአየር ፀባይ ለውጥ ነው፡፡ መንግሥት ግን ለሕዝብ የሚያስብ ከሆነ ባጀት ልማት ላይ መዋል አለበት የሚል እምነት ካለው አስቀድሞ መፍትሄ ማምጣት ነበረበት፡፡ ትግራይ ብንወስድ ትልቁ ተከዜ ትተህ ራሱ መጋቢ ወንዞች እንደ ገረብ ግባ፣ ወርዒ፣ ፅለረ፣ ዛሞራ፣ ሃይቅ መስሐል፣ ፆረና፣ ሩባ ሱር፣ መረብ በቀላሉ ሊወጣ የሚችል ትልልቅ ግድቦች መሥራት ይችላል፡፡ የኤሌክትሪክ ሃይል ምንጭ ሆኖ ለመስኖም ሊያገለግል የሚችል ግድብ መሥራት ይቻላል፡፡ ተከዜም ዳይቨርት ማድረግ ይቻላል፡፡ በመላ ኢትዮጵያ ያሉት ትላልቅ ወንዞች ብዙ ሕዝብ ሊሸከሙ የሚችሉ አሉ፡፡ በእነዚህ ላይ በመረባረብ ፈንታ ስልጣን ወንበር ላይ ቁጢጥ ብለህ፣ ወንበር እያሞቅክ እዚያ የምትኖርበት መንገድ ብቻ መፈለግ ተገቢ አይደለም፡፡ አሁን ባለው የተበጣጠሰ መሬት ዝናብ ላይ ጥገኛ ከሆኑ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እየተሞከረ ነው፡፡ ይሄው በኢሕአዴግም ዘመን 18 ዓመት ሙሉ ከረሃብና ከልመና አልተላቀቅንም፡፡ ስለዚህ የረሃብ ዋና ምንጭ የስርዓቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ችግር ነው፡፡