Sunday, February 28, 2016

“ውሸት አገር ያፈርሳል፤ አንድ ቅማል ሱሬ ያስፈታል” ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay blog አዘጋጅ) ክፍል (1) February, 2016“ውሸት አገር ያፈርሳል፤ አንድ ቅማል ሱሬ ያስፈታል”
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay blog አዘጋጅ)

ክፍል (1) February, 2016
በመጀመርያ እንደምንሰነበታችሁ። ሰሞኑን ትንሽ ራቅ ብዬ ነበር።ስለሆነም ትችቶቼን በሳምንቱ ለማንበብ አልቻላችሁምና ይቅርታ። እንዲያም ሆኖ፤ ደስ ያለኝ ነገር አንባቢዎቼ በደብዳቤ እንደገለጻችሁት፤ መጀመሪያ የኦሮሞ ተማሪዎች፤ተከትሎም በቋንቋ ግርጃ በተከለሉ የኦሮሞ አካባቢ ሕዝብ የታጀበው የ “ኦሮሚያ ኬኛ!” (ኦሮሚያ የኛ!) መፈክራዊ እንቅስቃሴ አማራ በተጨፈጨፈበት ሐረርጌ በደኖ ውስጥ ኦሮሞዎች የኦነግ ባንዴራ የማውለብለባቸው ክስተት፤ በመጨረሻም አክራሪ ክፍሎች በአርሲ ውስጥ 3 ቤተክርስትያናት የማቃጠላቸው ተከትሎ አረመኔዊው የሶማሌዎቹ ባሕሪ ወደ ኦሮሞዎቹ ማሕበረሰብ ተጋብቶ “የኢትዮጵያዊ ሙት ሬሳ ሲጎትቱ ሰንብቷል”። ይህ ሁሉ የአረመኔ ባሕሪ “ለኦሮሞ ተገንጣይ ቡድን ልሂቃን እና ፋሺስት ምሁራኖቻቸው ያልጠበቁት የደራ ፕሮፓጋንዳ ገበያ አስገኝቶላቸዋል”።

ሲወተውቱን የነበሩ ኦሮሞ ያልሆኑ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን አለቅላቂ ምሁራን ክፍሎች፤ ኢትዮጵያዊነት የተላበሰ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ሲሉት የነበረውን “ክስተት” ሳስጠነቅቃቸው የነበረውን “የረጋ በሉ” (ቺል ኣውት) ማስጠንቀቂያዬ  ሳይውል ሳያድር የእንቅስቃሴው ምንነት “እፊታቸው ላይ ውሃ እንደ ያዘ እንስራ ፍርክሽክሹ ወጥቶ፤ሬሳ ወደ መጎተት ተዛውሮ እንዲያዩት ሆነ”። ይህ ክስተት አስመለክቶ አንዳንድ አንባቢዎቼ “ድሮም አስጠንቅቀህ ነበር” ብላችሁ ለጻፋችሁልኝ ወንድሞችና እህቶች አመሰግናለሁ። Oromo First” ሲሉ ቆይተው ወደMuslim First” የተሸጋገሩ “የሰው አራዊቶች” ቀስ በቀስ ጥረታቸው እየጎመራ ነው።

ዘ-ሐበሻ የመሳሰሉ ድረገፆች ፤አክራሪ እስላሞች 3 ቤተክርስትያን ሲያቃጥሉ፤ እንደተለመደው “ወያኔ ነው ያቃጠለው” የሚለው የተቃዋሚዎች አዘጋገብ “የሽብርተኞች ገጽታ ደባቂነት ባሕሪ” ዛሬም ቆጥሎበታል። ዘ-ሓበሻ የተባለው ‘ኦነጋዊ ሚዲያ’ እንዲህ ይላል።

 በአካባቢው የሚገኙ 3 ቤተክርስቲያኖች ወድመዋል:  በምእራብ አርሲ የወደሙት ቤተክርስቲያኖች የሎቄ ቅዱስ አማኑኤል /; የብሊቶ ቅዱስ ገብርኤል / እና የአለም ጤና ቅዱስ ሚካኤል / ናቸው እንደ አይን እማኞች ገለጻ በተቃውሞው የተደናገጡት የመንግስት ካድሬዎች የሕዝቡን ተቃውሞ ከሃይማኖት ጋር ለማያያዝ እና ለመከፋፈል ካድሬዎቹ እነዚህን አብያተ ቤተክርስቲያናት አውድመውታል

አዲስ አበባን እንደ ባግዳድ” የሚለው ኢሳያስ እና ኦነጎች (ኤርትራ ውስጥ የሚኖረው በኮ/ል ገመቹ/ ቅጽል ስሙ ‘ታደሰ’ የተቀነባበረው) የቦምቡ ቀበራም ቢሆን “የወያኔ ድራማ” ነው ሲሉን የነበረው አንዳንድ የተቃዋሚ ሚዲያ ዘጋቢዎችና የፖለቲካ መሪዎች (ወያኔ ከኤርትራ የስለላ መረጃዎቹ አስቀድመው አስጠንቅቀውት ስለነበር፤ድምበር ሲሻገሩ የተያዙት በወቅቱ 9ኙ አሸባሪዎች (ለስልጣናው ከጅቡቱ፤ከኬኒያ ወዘተ የተሰባሰቡት 25 ነበሩ) በሚመለከት ‘ኤርትራዊው የስለላ ኣባል’ የነበረ ስለ ሁኔታው ባስገራሚ ሁኔታ ያብራራውን የትግርኛ ቃለ መጠይቅ አቅርቤላችሁ ነበር)። አንዳንድ የተቃዋሚ ሚዲያዎች ዛሬም ካለፈው ሳይማሩ፤ “ሁሉም ሽብር ለወያኔ ብቻ በመለጠፍ፤ አሸባሪ የለም የሚለው አሳፋሪ ድምዳሜአቸው” ዛሬም፤ የቤተክርስትያኑ ቃጠሎ ያቀነባበሩት የመንግሥት ካድሬዎች ናቸው የሚለው ከጋዜጠኛነት መርህ ውጭ የሚጋልበው የብዙሃኑ ተቃዋሚ ጭፍን ወገናዊ አዘጋገብ፤ ዛሬም የ ዘ-ሓበሻ ድረገጽ አዘጋገብ፤ ከድረገጹ ማሕደርና አዘጋግብ ለማን ሽፋን እየሰጠ እንደሆነ የሚያከራክር አይመስለኝም።

ድረገጹ ለዘገባው ምስክርነት ማጠናከሪያ ሲነግረን ‘አንድ የፖለቲካ ተንታኝ አንደገለጹት’ ይላል። ይህ “ስም የለሽ” የመረጃ አጠቃቀም ደግሞ በቀ/ሃ ዘመን ጅመሮ እስከ ዛሬ ድረስ ጋዜጠኞች ሲጠቀሙበት የነበረ “አንድ የፖለቲካ ተንታኝ እንደገለጹት” የሚለው የድብብቆሽ አዘጋገብ ከድሮ ዘጋቢዎች ተወርሶ ዛሬም ተባብሶበታል። እኝህ ስም ኣይጠሬ የፖለቲካ ተንታኝ ማን ይሆኑ? የኦነግ ባንዴራ ሲውለበለብ ግን “ወያኔ ነው የሰቀለው” ያለማለታቸው ለምን ፍጆታ ታስቦ ይሆን የሚለው ጥያቄ ያስጭራል?

በዚህ ሁሉ የፖለቲካ ውዥምብር፤ አክራሪ ሃይላት ከነ ፋሺስቶቻቸው፤ ለአንድነት ቆመናል በሚሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ምሁራን እና ‘ነፃ’ ሚዲያ ተብለው የተሰየሙ የውሸት ክፍሎች ተደግፈው ‘ገበያቸው ደርቶ፤ በተለያዩ መንገዶች እያራገቡ እየሸጡላቸው ይገኛሉ”። ያ መሰረት በማድረግ፤ ከፋሺስቶቹ የተሰነዘሩ የተለያዩ አስተያየቶች መሰረት አድርጌ በለኰስኩት የመጀመሪያ የብዕር እሳት አነሳሽነት ምክንያት ተናሳስተው፤ አንቀላፍተው የነበሩ ብዙ የኢትዮጵያ “ምሁራን” ወደ ትችት መድረኩ ብቅ ብለው እየተወያዩ በማየታችሁ ደስታችሁን የገለጻችሁልኝ ወንድሞቼ አመሰግናለሁ።

ከደረሱኝ በእንግሊዝኛ የተጻፈ መልእት አንዱን ባጭሩ ልጥቀስ። “ውይቱ ተከትሎ የታዘብኩት” ብላ አንዲት እህት በላከችልኝ መልእክት እንዲህ ይላል።

“የአንድነት ሃይሎች ናቸው ተብለው በብዙዎቻችን ታምኖባቸው የነበሩ አንዳንድ ሊቃውንት፤አንተ ‘ፋሺስቶች’ የምትላቸው የኦሮሞ ተገንጣዮች፤ ከወያኔ ጋር ሆነው ያጸደቁት “ቋንቋን መሰረት ያደረገውን ነገዳዊ አስተዳዳር” ለወደፊትም ቢሆን ከመቀበል ሌላ ምርጫ የለንም ብለው ሲከራከሩ በማየቴ፤ ‘ማን - ምን’ መሆኑን ያሳየን ክስተት እንደሆነ ስታዘብ፤ ባንድ በኩል ብያሳዝንም፤ ባንድ በኩል ማን ላንድነታችን እንደቆመ ለማየት አብቅቶኛል። በበኩሌ አንተን የመሳሰሉ ወገኖች መኖር ለመንፈሳችን ጥንካሬ ነው። ቀጥልበት።” ይላል።

በዚህ ቀውስ ውስጥ እንዴት ልንገኝ ቻልን? ብዙዎቻችሁ የምትሰጡት መልስ “ዲሞክራሲ” በመታጣቱ ነው እንደምትሉ በእርግጠኛነት መናገር እችላለሁ። እንዲህ ያለ ድምዳሜ ልትይዙ የቻላችሁበት ምክንያት “የፖለቲካ መሪዎችና ተቃዋሚ ሚዲያዎች” በዚህ እምነት ብዙ ጊዜ ደጋግመው ሲያስተምሩና ሲሞግቱ በመስማታችሁ፤ ያንን እንደ እውነታ ተይዞ “የዲሞክራሲ” እጦት ለዚህ ዳርጎናል፤ ወደ እሚለው ድምዳሜ ልትድርሱ አስችሏችሗል።  ለመሰደዳችን እና ለመበጣበጣችን ዓይነተኛ ምክንያት ዲሞክራሲ በመታጣቱ ሳይሆን፤የምንከተላቸው መሪዎችና ድርጅቶች/ወይንም መንግስት እና ሚዲያ፤ “ስለሚዋሹን” ነው። ያለ ዲሞክራሲ ለዘመናት የኖሮው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ ባለ እንደ ዛርው በዚህ 40 አመት ውስጥ የታየ አስከፊ ዘመን ‘ሲሰደድ፤ሲዋረድ፤ሲንገላታ’ ታይቶም ተሰምቶም አያውቅምና በአገራችን ውስጥ ዲሞክራሲ ስለሌለ መሰረታዊ የስደታችን እና የውርደታችን ምክንያት ሊሆን አይችልም

ከዚህ ዘልቀን መሰረታዊ መነሾውን መመርምር ያስፈልጋል። ውሸት ለዚህ ሁሉ ችግራችን መሪ ምክንያት ነው። የሚጎመዝዙ ዋሾ መሪዎች በገፍ ተፈልፍለዋል። መሪዎቹ በዋሹ ቁጥር፤ ሕብረተሱም አብሮ ይዋሻል፤ወይንም ሲዋሹ ይታገሳቸዋል፤ወይንም ያምናቸዋል። ውሸት ሕብረተሰብን የሚገድል እና የሚያጋድል፤የሚያሳስት መሰረታዊ የሆነ ማሕበራዊ ነቀርሳ እንደመሆኑ መጠን ፤ ‘ዋሾ’ መሪዎች በዋሹ  ቁጥር ሕብረተሰቡም አብሮ እየዋሸ ወይንም ‘እየታገሳቸው’ በሄደ ቁጥር የሚፈለገው ሰላማዊ የሆነ ፍትሕ የነገሰበትና ‘ተጠያቂነትን’ የሚያከብር ስርዓት እንዳይመጣ እንቅፋት ይሆናሉ ማለት ነው።

አስገራሚ የሚያደርገው ደግሞ፤ በጥንቃቄ እንድትገነዘቡት የምፈልገው፤ “ውሸትና ዋሾ መሪዎች” የመቀበል ባሕል እያጎለበትን በመምጣታችን ለቀውሳችን ተጠያቂዎች መሪዎቹ ሳይሆኑ እኛ የመሆናችን ጉዳይ አስገራሚ ያደርገዋል። ተጠያቂነት ያለው ስርዓት እንዳይሰፍን ዋሾ ‘መሪዎች’ ልቅ እየለቀቅን፤ እነሱ ሲያብዱ ባልታሰበ ድንገተኛ እምርታ እኛም እነሱ ጋር እየዋሸን እና እያበድን ቀስ በቀስ “ዕብድ ሕብረተሰብ” ወደ መሆን እየተሸጋገርን ነን ። (አሁን ባለንበት ዘመን፤ የሃይማኖትም የፖለቲካ መሪዎችም ባመጡት ሰበብ የቀወሰ ሕብረተሰብ በብዛት እየተበራከተ መምጣቱ እያየነው ያለው ገሃድ የዚህ እውነታ ነው)። ኤርትራም፤ሶማሌም እኛም እራሳችን ማንንታችንን ያጣን ማሕበረሰብ ወደ መሆን የተከሰተበት ምክንያትም ይኼው ነው።በነገድም በሃይማኖትም ገብተው ሕብረተሰቡ ሲዋሹት ሕብረሰተቡም እሱም አብሮ በመዝለሉ የቀውሰ ተዋናይ እና ሰለባ ሆኗል።

ውለን አድረን ሰለጠንን ባልንበት ዘመን ወደ አራዊት ባሕሪ ጠን የኢትዮጵያዊ ሬሳ ወደ መጎተት ገብተናል። ስብእናችን አሽቀንጥረን ጥለናል። ወደ አረመኔ ባሕሪ ገብተናል። የነገድ ፖለቲካ መጨረሻው ስብእናን ነጥቆ የራሱ ያልሆነውን ነገድ እንደ አራዊት በማየት፤ ሬሳውን መሬት ለመሬት እየጎተተ፤ እየረገጠ፤ በሞተ ሬሳ ላይ ጥላቻውን እንዲገልጽ የሚያስገድድ አደገኛ በሽታ እንደሆነ ደጋግመን ስናስጠነቅቅ የነበረው “የወያኔ እና የኦነግ” አጀንዳ መጨረሻው ኢትዮጵያዊ ባሕሪይ እና መንፈሳዊ ሞራል ነጥቆ ማሕበረሰብ ወደ ‘አራዊት ዓለም” መለወጥ መሆኑን ደጋግመን ያስጠነቀቅነውን ማስጠነቂያ ሳንሞት በዓይናችን ለማየት በቅተናል።

“አክራሪ ነገድና ሃይማኖት፤ በተቃዋሚውና በወያኔ ውስጥ ተሰግስገው፤ ሽፋንና መድረክ እየተሰጣቸው፤ በጥበብ በሽፋን እየተጓዙ ፖለቲካው እና ሃይማኖቱ ወደ እንሰሳ ባሕሪ አስገብተውታል። ወደ ውሸት ጣሻ ቀስ በቀስ ገብተናል የምለውም ለዚህ ነው። ውሸትና ወገንተኛነት ፖለቲካውንም ሃይማኖቱንም የዜና አውታሮችን ሳይቀር ተቆጣጥሮአቸዋል። በውሸት የሰከሩ ዜጎች የሚሰሩት ስራ በገሃድ እያየንና እያደመጥን ነው።ውሸት አየር ነገር አይደለችም። በማሕበረሰቡ ሕሊና ውስጥ የምትኖር፤ ጠበቃዎችና ተከላካዮች ያሏት የሰዎች ባሕሪ ነች።

ሕብረተሰቡ ከሚዋሹ መሪዎች አብሮ የማበዱ ምክንያት እራሱ ሕብረሰተሰቡ ብቻ ሳይሆን፤ ውሸትን በመድረክ አደባባይ እንዳንተቻት የሚገድቡን “የሚዲያ” ክፍሎችን ፍተኛው የአጥፊነት ድርሻውን ይዘዋል። እደግመዋለሁ፦- ዩሃይማኖትና የፖለቲካ መሪዎች ሲዋሹን “እንዳንተቻቸው” የሚገድቡን፤ ‘የዜና እና የሃሳብ አሰራጭ ሚዲያዎች” ቀዳሚውን የመከላከያ እና አጥቂ መስመሩን ይዘውታል። ሚዲያዎች፤ የድርጅቶችን ጸያፍ ድርጊታዊ ምስጢሮችን ፤ ለፖለቲካ እና ጊዜያዊ ተወዳጅነት ለማግኘት ሲሉ ፤የሽብር ስራዎች ወደ እሚቃወሙት መንግስት ብቻ እያዞሩ ሽብርተኞች የሚፈጽሙዋቸው ሽብሮች፤ በመደበቅ የተባባሪነት ሙያ እያካሄዱ ናቸው።

እነኚህ የሚዲያ ክፍሎች ሕብረተሰቡ ካልነቃባቸው አደገኛ የሕብረተሰብ ጠንቆች ሊሆኑ እንደሚችሉ ደጋግሜ ገልጫለሁ። እነኚህ ክፍሎች፤ በሕዝብ ምርጫና ፍላጎት የተከሰቱ ስላልሆኑ፤ በድምፅ ብልጫ የሚመረጡ ወይንም የሚወርዱ አይደሉም። እነኚህ ሚዲያዎች በተለያየ ስም እየተጠሩ፤ ለትርጉም የማይመቹ፤ “እራሳቸው በራሳቸው የመረጡ”፤ከማሕበረሰቡ ጫንቃ መውረድ የማይችሉ  “ነገሥታት” ናቸው። በይፋ ካልተጋፈጥናቸው፤ አደገኛ ድርጅቶችና ግለሰቦችን ወደ ሕዝቡ እያስተዋወቁ፤ የሕዝብ ሕሊና በመጥለፍ፤ ወደ ስልጣን ጎትተው ሊያመጡብን የሚያስችላቸው እድል እያመቻቹ ነው። በሌላ አነጋጋር አስፈሪ “ሞንስተሮችን” (ዘንዶአዊ-ድራጎኖችን) በነዚህ የሚዲያ ሰዎች ብዕር ውስጥ ተወልደው ያድጋሉ ማለት ነው።

ሚዲያዎች ጎጂም ጠቃሚም ሊሆኑ ይችላሉ። አደገኛ ባህሪ ሲከተሉ ግን  ማሕበረሰቡ ከሚቆጣጠረው ዓለም ውጭ የሚኖሩ Dual character ድርብ ጸባይ የያዙ ክፍሎች የመሆን ባሕሪ አላቸው። እነኚህ ክፍሎች አገርን ማበጣበጥ፤ጨቋኝ መሪና ግለሰብን ማንገስ የሚያስችል ሰላቢ የብዕር ችሎታ ስላላቸው፤ ማሕበረሰብን ማፋለስ ወይንም የማረጋጋት ችሎታ አላቸው። ውሸት በነዚህ ክፍሎች ትጎለብታለች ወይንም ትታገዳለች። ስለሆነም፤ ለቀውሳችን ምክንያት “ዲሞክራሲ” ስላጣን ሳይሆን፤ወደ ዲሞክራሲ የሚወስደን መንገድ ዘጊ ሃይል ሆነው እያስቸገሩን ያሉት ‘ሚዲያዎች እና መሪዎች” በውሸት ነቀርሳ ሲበከሉ፤ የሚፈለገው ስርዓት ልናይ አንችልም። ያለ ምንም ማመንታት ወደ ቀውስ ገብተናል። ውሸትን እና ውሸታም የድርጅትም ሆኑ የመንግሥት መሪዎች፤እንድንተቻቸው እስካልተፈቀደልን ድረስ ‘ ቀውሱና ፍልሰቱ  አያባራም። 

አገራችን በተቃዋሚውም ሆነ በስርዓቱ ሰዎች ባሕሪ በብዙ ፋሺስት ባሕሪ ያላቸው ሰዎች ተወጥራለች። የገዛ ልጆቿ ደመኛዋ ሆነዋል፤ ስንል እውነት ነው። መነኮሳትን የሚያርዱ፤ ቤተ ክርስትያኖችና መስጊዶችን የሚያቃጥሉ፤ሬሳ የሚጎትቱ፤ የቀወሱ ዜጎች በብዛት ተፈጥረዋል። ኦሮሚያ ነን፤ሶማሌ ነን፤ ኤርትራ ነን…..የሚሉ ራሳቸውን ያጡ ክፍሎች ተከስተው፤ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን ለስደት ዳርገው የቀውሳቸው ሰለባ ሆነው አሁንም በቀጣይነት ለቀውሳቸው መነሾ የሆኑ ዋሾ ግለሰቦችን እያመለኩ በነሱ ሥር ያደሩ ዜጎች ተፈጥረዋል። የቀወሱ/ያበዱ የሃይሞኖት/የፖለቲካና የመንግሥት መሪዎች ውሸታቸውን አብሮ እንዲያጅብ በማስገደድም ሆነ በማታለል፤ ሕብረተሰቡ ውዥምብር ውስጥ ጨምረውታል። ይህ ለምን ተከሰተ ብለን ስንጠይቅ በዚህ ጥናት ያደረጉ ባለሞያዎች እንዲያስተምሩን እንሻለን።

መሪዎች ሲክዱ፤ሲዋሹ፤ነገሮችን ሲጠማዝዙ፤ሲያጭበረብሩ፤ ሕዝቡ የነዚህ ሰዎች ባሕሪ እየተከተለ ዋሾ እየሆነ እራሱን እያጣ፤ የዓረብ፤የቱርክ፤ የሱዳን፤የአውሮጳ፤ካናዳ፤አሜሪካ፤የአውስትራሊያ….አገሮች ዜጋ እንዲሆን እየለመነ፤እንደዋዛ  ቀስ በቀስ እራሱንም አገሩን የማጣቱ ጉዳይ “ጥቂት” ካልሆነ በቀር፤ አብዛኛው ሕዝብ የትም ተበትኖ ሲኖር የቁጭት ስሜት የሚያሳይ አይመስልም።የሌላ ዘር ዜጋ ነህ ተብሎ በገንዘብ የተሸጠ ወዶ ገብ ‘ባርያ’ ሆኖ፤ ዘሩን ክዶ፤ ኣናቱ ማሃል ላይ ‘ቆብ’ እየተጠለቀለት በገንዘብ የተሸጠ ባርያ መሆኑን አሜን ብሎ በፍላጎቱ ‘ዳንኪራ’ እየመታ ደስ ብሎት የሚኖር፤ ዓለምን በቀውስ ማዕበል እያንገላታት የሚገኘው የማፍያዎች ሴራ ሰለባ የሆኑ በርካታዎች ናቸው።

ውሸት እየተቀበሉ ማንነታቸው የካዱ ብዙ ስለሆኑ ማሕበራዊ ጠንቅ አስከትሎብናል። በየዓለማቱ እንድንሰደድ ያደረገን አንዱ ምክንያት የመሪዎቻችን “ሞገደኛ-ውሸት” ከመሃል መስምር ወደ ውጭ ተገፍትረን እንድንጣል ስለገፉን ቢሆንም፤ የሴራቸው ተካፋዮች እስከሆንን ድረስ ተወቃሾቹ እኛ እንጂ እነሱ ብቻ ሊሆኑ አይችሉም። ሳናስበው እራሰችንን አጥተን የሰው አገር ዜጋ የመሆናችን ክስተት እጅግ አሳዛኝ ነው! አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ- ለስደታችን መንስኤ የሆኑ አስቀድመው ሲዋሹን የነበሩ የድርጅት መሪዎች አገር እየጣሉ ከኛው ጋር ሲቀላቀሉም፤ እንደገና እነሱንም በማጀብ፤ ዛሬም የነዚህ ክፍሎች ሰለባ የመሆናችን ክስተት እየቀጠለ መሆኑን ስንመለከት ሕብረተሰቡ በክፉኛ የተቃወሰ ሕሊና መጠቃቱን አመላካች ምልክት ነው።ለዚህ ደግሞ የፓልቶክ መድረኮች ጠቋሚ እስኬል/ሚዛን ሆነው እናገኛቸዋለን። በነዚህ መድረኮች የሚሰነዘሩ ስብከቶች ስናደምጥ የሕብረሰተሰቡ ትክክለኛ የሕሊና ግራፊክ/ስዕል/ በቀላሉ መምዘን ያስችላችለናል። እንዲህ ያለ የተደናበረ ማሕበረሰብ የስነልቦና እና የስነ አእምሮ ሊቃውንት፤እውነተኛ ፓለቲከኞች ጋር ሆነው ተሎ ካልደረሱለት፤ ‘ጨርቁን ጥሎ’ ያበደ ማሕበረሰብ ተብሎ ባይጠራም፤ ‘ሕሊና ያጣ” ማሕበረሰብ የመሆኑ ሃቅ የማይቀር ነው።

ለዚህ ሁሉ ጠንቅ፤ ዛሬም ውሸትን የሙጥኝ ብለው እየዋሹን የሚገኙ የድርጅት/የመንግሥት መሪዎች፤እንድንተቻቸው/እንድንወቅሳቸው እስካልተፈቀደልን ድረስ ‘ቀውሱና ፍልሰቱ እንዲሁም ግጭቱ’ አያባራም። “ሕብረተሰቡ በራሱ ግቢ/ካምፕ ውስጥ የሚገቡና የሚወጡ እንዲሁም የሚተራመሱ የኢትዮጵያ ወዳጆችና ጠላቶችን” የመለየት ችግር ዛሬም እየታየበት ነው። በስሜት እየተመራ፤ ወደ ተደናበረና ወደ ውሸት የመራመዱ ባሕሪ አሁንም አላባራለትም። “መሪዎች ሲዋሹ፤ ሕዝቡ ያላንዳች ጥርጣሬ ያምናቸዋል”። በርካታ የድርጅት መሪዎች ‘በውሸት” በሽታ ተበላሽተዋል። አገር ውስጥ ያሉ መንግስታዊም ሆነ ተቃዋሚ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ፤ ለወደፊቱ እንገዛሃለን ብለው በጠመንጃ ሃይልም ሆነ በፖለቲካ ትግል ለመግባት እየተወራጩ የሚገኙ፤ ተገንጣዮችም ሆኑ ‘ኢትዮጵያዊያን ነን’ የሚሉ ክፍሎች “ሲዋሹ” እስካላጋለጥናቸው ድረስ፤ ሰላም ይገኛል ማለት ሕልም ነው። እዚህ ላይ እርማችሁን አውጡ!

ትንታኔዬን ጥቂት ምስሌዎች እየሰጠሁ ገፋ ላርገው።

መሪዎች የሚዋሹትን የአመታት ውሸት ትቼ በቅርቡ የታዘብኩትን ላወያያችሁ። እንደተለመደው የግንቦት7 መሪ የሆነው “ብርሃኑ ነጋ” በዚህ ወር ውስጥ ከኤርትራ እየበረረ መጥቶ እራሱን ለውርደት ሲያጋልጥ አድምጫለሁ። ሳዲቅ አሕመድ ከተባለ ዲሲ አሜሪካን አገር ውስጥ የሚገኘው የ “ቢ ቢ ኤን/BBN” የእስላሞች ማሕበረሰብ ራዲዮ ጣቢያ፤ ቃለ መጠይቅ ባደረገበት ወቅት፤ አዘጋጁ “ድንገት ያልጠበቀው ጥያቄ” አቅርቦለት፤ብርሃኑ ነጋ፤ ተደናግጦ ያለሆነ መልስ ሲሰጥ፤ “ኢትዮፒያኒዝም ቲቪ” የተባለ በፕሮፌሰር ሙሴ የሚዘጋጅ የኢንተርኔት ቲቪ፤ስለ ሁኔታው በትችት አቅርቦት አድምጬው፤ ብርሃኑ ነጋ ዛሬም ምንም መማር ያልቻለ፤ ለወደፊቱም መማር የማይችል መሆኑን ስገነዘብ፤ ሰው ለምን ካለፈው እንደማይማር ይገርመኛል።

ያስገረመኝ ነገር፤እንዲህ ያለ የመሸፋፋን ባሕሪ የያዙ እንደ ብርሃኑና መሰሎቹ ወደ ስልጣን ቢወጡ ‘የአገራችን ሁኔታ’ ምን እንደሚሆን በጣም ነው ያሳሰበኝ። Professor Berhanu Nega With Sadik Ahmed | BBN    https://youtu.be/fUv28Nl35ec  ስታደምጡ፤ የዚህ ሰውየ ከእውነት ለመሸሽ ያደረገው ሽሽት ስትታዘቡ፤ ራሱን ለመደበቅ ያደረገው ጥረት ብቻ ሳይሆን፤ በሕዝብ ፊት መዋሸት ሃጢያት የሌለው መሆኑን እንደሚያምን ቢያሳይም፤ ግለሰቡ እራሱን ለመደበቅ ያለ ምንም መደናገጥ ቀጥተኛ መልስ ላለመስጠት ፤እራሱን ለመደበቅ የጣረበት ምክንያት የሚጠቁመን ነገር ቢኖር፤ ግለሰቡ እየደጋጋመ ሲዋሽ ይበልጥ ሙገሳ እየተቸረው እዚህ ድረስ መጓዙ ከማወቁ ሌላ፤ ማሕበረሱ ውሸትን የመቀበል ባሕሉ የደበለ መሆኑን ከድፍረቱ ለማወቅ ያስቻለን ጠቓሚ አጋጣሚ ነው። እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን፤ “አትዋሽ” የሚለው ሃይማኖታዊ ግብረገብ፤ የፖለቲካ መሪዎች በግልጽ ሲጥሱት ማየት፤ ስልጣን ሲይዙ የሚመሩት ስርዓት “ምን ዓይነት” እንደሚሆን መተንበይ ‘ነቢይ መሆን አይጠበቅብንም።

አንድ የድርጅት መሪ፤ በብዙ ሰው “ምሁር” ተብሎ ተቀባይነት ያገኘ ምሁር፤ ሲዋሽ እና ነገሮችን እየጠመዘዘ ስለራሱ የተጠየቀውን ጥያቄ ላለመመለስ ከጥያቄው ተያያዥነት የሌለው መልስ መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ “ለምን አደረግከው” ተብሎ የተጠየቀውን የራሱን ጉዳይ ወደ “ወያኔ” አዙሮ መልስ መስጠት፤ ተከታዮቹ ካላበዱ በቀር፤ ደጋፊዎቹ  በየአዳራሹ ማጨብጨብም ሆነ፤ ድጋፋቸውን መንፈግ የሚገባቸው አሁን ይመስለኛል። እንዲህ ያሉ ሰዎች ሥልጣን ላይ ሲወጡ ላገሪቱ ጠንቅ ናቸው። ከሕዝብ የሚደብቁት ብዙ ምስጢሮች ይኖራል ማለት ነው። ስለዚህም ሕብረተሰቡ ከነዚህ ዓይነቶቹ የፖለቲካ ሰዎች ሕዝቡ እራሱን ማራቅ እንዴት እንዳቃተው የማሕበራዊ ልቦና እና የስነ ኣእምሮ ተመራማሪ ኢትዮጵያዊያን ኣዋቂዎች ጣልቃ ገብተው ቢያስተምሩን መልካም ነው።

መሪዎች እንደሚዋሹ እናውቃለን። ሲዋሹ ለአገር ጠቀሜታ ብለው የሚዋሹዋቸው አንዳንድ ውሸቶች ተቀባይነት አላቸው።ሆኖም ለግል ዝናም ሆነ ጠቀሜታ ወይንም እራስን ላለማጋለጥ ከዋሹ ደግሞ ጉዳቱ እጅግ አደገኛ ነው። ውሸት ማለት የተደረገና፤የተነገረ ነገር መካድ ማለት ነው። እውነት ደግሞ ‘ሃቅ’ ማለት ነው።ሃቅ ማለት ደግሞ ነገሮች ሳያጠማዝዙ፤ሳይደብቁ፤ሳይሸሽጉ የተደረገው፤የሆነው፤የተነገረውን ነገር ሁሉ መናገር ማለት ነው።ውሸት ብዙ ክፍሎች አሉት;
መዋሸት ማታለልመጠምዘዝ እና መደበቅ። ፈረንጆቹ deceiving lying, spinning, concealing የሚሏቸው ማለት ነው። በነዚህ ስር ደግሞ ብዙ ዘርፎች አሉዋቸው። ምሳሌ እየሰጠሁ ልደምድም።

በአገራችን ብዙ የፖለቲካ ድርጅት፤የመንግስት፤የሃይማኖት መሪዎች ሲዋሹን አድምጠናል። በባድሜ ጦርነት የኢሳያስና የመለስ ዜናዊ ውሸቶች፤ማታለሎች፤ለሕዝብ ይፋ ያልሆኑ በሁለቱ መሪዎች ብቻ ሲለዋወጡዋቸው የነበሩ ድብቅ ደብዳቤዎች በርካታ መሆናቸው ታስታውሳላችሁ። እነዚህን አስመልክቶ ሲጠየቁ ሲዋሹን የነበረውን፤ሲጠማዝዙት የነበረውን መልሳቸው እና ሕዝብን ለማታለል ሲሰነዝሯቸው የነበሩ ንግግሮች ሁሉ ወደ ሗላ ተመልሳችሁ ንግግራቸውና ተጠይቀው ሲሰጡት የነበረውን መልስ ብታጤኑ ከላይ የተጠቀሱት ሁሉም የውሸት ክፍሎች ታገኛቸዋላችሁ።

ሥዩም መስፍን

ሥዩም መስፍን የተባለው የወያኔ ቁንጮ ‘ባድሜ’ ለእኛ ተበይኖብናል፤ በጦር ሜዳ ያገኘነውን ድል በፍርድም ደገምነው” ሲል በሚዲያ የወጭ ጋዜጠኞችና የአገር ጋዜጠኞችን ሰብስቦ የዋሸውን ውሸት እና ሕዝቡም አንዲጨፍር ጥሪ አድርጎ ‘አደባባይ ወጥቶ’ ከበሮ እየመታ ያስጨፈረው ውሸት ታስታውሳላችሁ። እውነታው ግን በሳምንቱ ተገልጦ ‘ባድሜ’ ሥዩም መስፍን እንደዋሸው ሳይሆን ‘ባድሜ’ ለኤርትራ/ለሻዕቢያ መሰጠቱን አወቅን። ለምን ዋሸህ ተብሎ ሲጠየቅ “spinning /ስፒኒንግ” ዓለም ውስጥ ገብቶ ያሳሳተው ፍርድቤቱ በነገረው መሰረት እንደሆነ deceiving/ በማታለል ዓለም ውስጥ ገብቶ ሕዝብን ለማጭበርበር መሞከሩ ታስታውሳላችሁ። ፍርድ ሲሰጥ በጽሑፍ እንጂ በቃል ተነግሮናል ተብሎ ለሕዝብ መዋሸት እጅግ አስገራሚ የወያኔ የውሸት ባሕሪ ምን ርቀት እንደሚሄድ ታዝበናል።


ኢሳያስ አፈወርቂ

‘ጆሽዋ’ የተባለ ጋዜጠኛ አስረኸዋል፤ የት አደረስከው?” ተብሎ በጋዜጠኞች ሲጠየቅ፤ “የምትለው ስምም ሆነ ጋዜጠኛ ሰምቼ አላውቅም፤ ማን እንደሆነ ኣላውቀውም” ሲል በግልጽ ሲዋሽ ታደምጣለችሁ። ስደተኞች እየበረከቱ ነው ወደ ሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ከዚያም ወደ የመን እና ግብፅ በረሃ በሽፍቶች እየተያዙ ጉበታቸውና ኩላሊታቸው እየተሸጠ ነው፤ ስደተኛን ለማቆም ያደረግከው ጥረት ምን አለ? ተብሎ ሲጠየቅ፤“ከኤርትራ እየሸሸ ወደ ተጠቀሱት አገሮች የፈለሰ ስደተኛ የለንም”፤ ሲል ሽምጥጥ አድርጎ ዓለም የሚያውቀውን ሃቅ ሲዋሽ አድምጠናል።

የግንቦት 7 መሪ ብርሃኑ ነጋ

ከላይ በተጠቀሰው የእስላሞች ቲቪ ጣቢያ ቀርቦ ስለ አንዲት የእርሱ ተማሪት የነበረች እስላም፤ ሕጃቧ እንድታወልቅ ስለሰነዘረው ጉዳይ መልስ አንዲሰጥ ሲጠየቅ፤ መልሱን ከወያኔ ጋር በማያያዝ አድማጩን ለማታለል የመሞከሩ ውሸት ቪዲዮውን ስታደምጡ “ዲሲቪንግ እና ላይንግ/መዋሸትና ማታለል’ ምን ማለት እንደሆነ በዚህ ሰውዬ ባሕሪ ትረዳላችሁ።

መንግስቱ ሃይለማርያም፤

ወያኔዎች አዲስ አበባ ለመያዝ እየተጣደፉ ባሉበት ሁኔታ፤ “የትግራይ ገበሬ እንደ አንበሳ ተባብሮ ወንበዴዎችን እየተገተገው ነው” ሲል አዳራሽ ውስጥ ለተሰብሳቢ መናገሩ፤ መሪዎች ምን ያህል እንደሚዋሹ ትገነዘባላችሁ።


ፕረዚዳንት ቡሽ

ቡሽ እና ለመዋሸት ያስሰማራቸው ጀኔራል ፓወል የተባለ ጥቁር ጀኔራል እና ኮንደሊዛ ራይስ ጋር ሆነው፤ “ሳዳም ሁሴን የ911 ሽብር ተካፋይ ሆኗል፤ ዓለምን የሚያጠፋ “ኒኩሌር እና ኬሚካልም” (ዌፐን ኦፍ ማስ ዲስትራክሽን) መሳሪያዎች ሰርቷል፤ አሁኑኑ ካለቆምነው በቅርቡ ዓለምን ያጠፋታል” በማለት ሕዝባቸውን በውሸት አሳምነው ኢራቅ ሕዝብ ላይ የፈጸሙት ፋሺስታዊና ናዚያዊ ወንጀል ዓለም ያውቀዋል።


ኦነግና ወያኔ

የተባሉ ሁለት ፋሺስት ድርጅቶች በዐማራ ማሕበረሰብ ላይ የፈጸሙት የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ለመደበቅ እርስ በርሳቸው እየተወነጃጀሉ ሕዝብን ለማታለል እያደረጉት ያለውን ውሸትና ማታለል ስትመለከቱ በቀላሉ መሪዎች በውሸት ሕዝብን እንዴት ለማታለል እንደሚጥሩና የሚጠማዝዙት የመልስ አሰጣጥ ዘዴአቸው ስታጤኑ በግልጽ ትረዱታላችሁ።

ኦነግ የተባለው ድርጅት በሽግግሩ ወቅት “የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት ወታደሮች” ፈርሶ ሜዳ ላይ ፈስሶ መኮንኖችና በለማዕርጎች በረንዳ ላይ ቆመው መሎዮአቸውና መዳሊያቸውን አፈር ላይ አስቀምጠው ሳንቲም እንዲለምኑ ያደረጉት ከወያኔዎችና ኦነጎች መሆናቸው እየታወቀ፤ ሌንጮ ለታ የተባለ አደገኛ ጸረ ኢትዮጵያ ግለሰብ “እኛ መፍረስ የለበትም ስንል ወያኔ ይፍረስ ብሎ አፍርሶታል” እያለ ኢሳት ላይና ሌሎች ሚዲያዎች ሲዋሽ አድምጠናል። ይህንን ውሸትና ማታለል በሚመለከት አብሮ አዳራሹ ላይ የነበሩ አንድ ወዳጄ ምስክርነታቸው እንዲሰጡኝ ጠይቄአቸው ሌንጮን/ኦነግን በሚመለከት በሰፊው ጽፈው እንደሚልኩልኝ ሰሞኑን ቃል ገብተውልኛል። አብረን እንመለከተዋለን።

የግንቦት 7/ኢሳት ፋሲል የኔዓለም

ፋሲል የተባለ የግንቦት 7 አባል እና የኢሳት ጋዜጠኛ ‘ወያኔ’ አማራ ማሕበረሰብ ላይ የፈጸመውን ወንጀል ሊነግሩን እንግዳ አድርጎ የጠራቸው አባ ኒቀዲሞስ የተባሉ አባት ሲተነትኑ፤ አባም አያይዘው ‘ኦነግ’ በአማራ ላይ ያደረሰውን ወንጀል የሚያውቁትን ለመግለጽ ሲሞክሩ ደጋግሞ ‘ጣልቃ እየገባ’ ወደ ወያኔ ወንጀል ብቻ እንዲያቶኩሩ ሲያደርገው የነበረው የመደበቅ/ concealing እና የመጠምዘዝ ባሕሪ ታዝበናል።

ይህ ጋዜጠኛ አማራ ላይ ያለው ጥላቻ ስንመለከት፤ ‘የጎንደር ኦሮሞ ይሁን ቅማንት ወይንም አማራ ወይንም ኤርትራ?” ይሁን በይፋ የነገረን ነገር ባይኖርም፤ የአማራ ድርጅት የሚወክሉ ግለሰቦች ወይንም መግለጫዎች ወይንም ቃለመጠይቅ ሲያደርግላቸው፤ ጥላቻ እንዳለው በግልጽ ያሳየበት በርካታ ጊዜዎች አሉ። ለምሳሌ የሞረሽ ሊቀመንበር የሆኑትን አቶ ተክሌ የሻው ደ/ር ላጲሶ የተባሉት የታሪክ ምሁር ስለ ኢትዮጵያ እና አማራ ማሕበረሰብና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ክ ታሪክና የሰለሞን ሥርወ-መንግሥት ታሪኮችን አስመልክተው  የዘባረቁትን አስመልከተው አቶ ተክሌ ቅሬታቸውን ለማስሰማት  ምሁሩ (/ዶ/ር ላጲሶ) በዘባረቁበት ኢሳት ሚዲያ ላይ ቀርበው በሳቸው በኩል ያለውን ታሪክ ለማቅረብ ኢሳትን/ፋሲል የኔአለምን ጠይቀው፤ በፈቀደላቸው መሰረት ቃለ ምልልስ ሲያደርግላቸው “ፋሲል” በአቶ ተክሌ የሻው ያንጸባረቀው እግጅ አሳፋሪ እና ብልግና የቃለ ምልልስ ባሕሪ ብዙዎችን ከማስቆጣት አልፎ (ፕሮፌሰር ጌታቸው ሃይሌም ጭምር ትችት ጽፈውበታል) “የገዛ ባለቤቱ” ሳትቀር በሁኔታው እጅግ መቆጣቷ ሳይሸሽግ እራሱም ይፋ አድረጓል።

የዚህ ግለሰብ ነውራማ ጋዜጠኛነት የከፋ የሚያደርገው ደግሞ፤ በስድ ጋዜጠኛ ባሕሪው ያሳየው ሁኔታ ቀጥተኛ ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ፤ ዙርያ ጥምጥም የሄደበትን ጽሑፉ በ ዘ-ሐበሻ ድረገጽ ስናነብብ፤ቀና ግለሰብ ያለመሆኑ የ spinning  እና   deceiving ባሕሪው በይፋ መገንዘብ ትችላላችሁ። ጋዜጠኞች በዚህ ባሕሪ ሲጓዙ ለአገር ጠንቅ ናቸው የምለውም ለዚህ ነው።

ፋሲል እና መሳይ

ሁለቱ የኢሳት ጋዜጠኞች ኤርትራ ድረስ ተጉዘው ያደረጉት አሳፋሪ ዘገባ ብዙ የማታለል፤የመደበቅና የመዋሸት ባሕሪ ታዝባችሗል። ሲሳይ አገና የተባለው የኢሳት ጋዜጠኛ፤ የድምህት መሪ የነበረው ሞላ አስገዶም ጦሩን ከኤርትራ ይዞ ወደ ወያኔ ሲገባ፤ ሲሳይ አገና ‘ሲተች የነበረው የሞላ አስገዶምን ጦር’ በሃያዎቹ ውስጥ እንደሆኑና መረጃውም ሱዳን ውስጥ የተነሱት ፈቶግራፎች አስደግፎ ለሰሚው እጅግ አስገራሚና አዲስ ክስተት የሆነውን ያ ትኩስ ዜና “እርባና ቢስ” ሆኖ እንዲታይ መረጃውን ለማጠናከር የሰነዘረው ደረጃው እጅግ የወረደ የጋዜጠኛነት ትንተና ማድመጣችን ሳይበቃው፤ የድምህት መሪው የሞላ አስገዶም መክዳት፤ ኤርትራ ውስጥ ተቆርጦ ለቀረው ተዋጊም ሆነ ለትግሉ ኢምንት እንደሆነ የተቻለውን ያህል ለማሳመን “የማታለል/deceiving/ስብክት ሲሰብክ አድምጠናል።በዚህ ጉዞ የተጓዘበት ምክንያት ጋዜጠኛው የግንቦት 7 እምባ አቅራሪ ጋዜጠኛና (እንደሚባለውም ደሞዝተኛ) በመሆኑ ነው።

በዛው ሳይወሰን እሱ እና መሰል ባልደረቦቹ፤  ‘ሻለቃ ዳዊት’ የተባለውን ሻዕቢያ ለማስገደልና ከዚያም ከተቻለ አንዳርጋቸውን ለመግደል የተላከ የወያኔ አሳሲን/ነብሰ ገዳይ/ አስምልክተው የሰጡትን ዘገባ ልብ ይለዋል። ሰውየው ግንቦት 7 ተዋጊ ለመሆን ከተቀላቀላቸው በላ በገዛ እራሱ ተጸጽቶ ምስጢሩ ለታጋዮቹ ተናግሮ ከደሙ ነፃ እንደሆነ በቅን ልቦና የተጋለጠውን ምስኪን ሰውዬ፤ በግንቦት 7 የስለላና የመረጃ ክፍል ጥናት ተደርሶበት እንደተያዘ እያስመሰለቀው “ግንቦት7” እና “የግንቦት 7 ቱልቱላ የሆነው ኢሳት” ባዘጋጁት “የውሸት ድራማ” ተደግፎ ለድራማው ድምቀት ለመስጠት ፡ፈዳያኑ/ነብሰገዳዩ/ ወድዶ በፈቃዱ ከወያኔዎች ጋር  በራዲዮ ሲያደርገው የነበረውን  የራዲዮ ምስጢራዊ የመልዕክት ልውውጥ እየተነተኑ የዘገቡትን ለድርጅታቸው ወገንተኛነት በሚያሳይ መልኩ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ተብሎ አጭበርባሪ/ዲሲቪንግ ጋዜጣዊ ትንተና የተነተነውን ልብ ይለዋል። 
መሳይ የተባለው ደግሞ ሻለቃ ዳዊት የተባለ ሻዕቢያ ውጭ አገር በሚገኙ አንዳንድ ተቃዋሚ ግለሰቦች ሻለቃውን “ሽብርተኛ፤ጸረ ኢትዮጵያ፤ ብዙ ኢትዮጵያዊያን ታጋዮች ያሰቃዬ” እያሉ ስሙን ሲያጠፉት እራሴ ወደ ኤርትራ ሄጄ በነበርኩበት ወቅት ሻለቃው ውሃ ሙቅ አዘጋጅቶ  የደከመውን እግሬን ለማጠብ ጎምበስ ብሎ ወደ መሬት ሊያጥበኝ የሞከረ ሰውዬ በታቃዊሞች ያለ ስሙ መሰጠቱ ልክ ሆኖ አላገኘሁትም ፤ሲል  “እየሱሳዊ እንግዳ አክባሪ” ወደ ማለት ለመሸጋጋር ጥቂት ነበር የቀረው። ጋዜጠኞች ለጊዜያዊ ጥቅም ሲሉ በዚህ ባሕሪ ሲጓዙ የሚያስከትሉብን ችግር መገመት አያዳግትም።
ሱዳኖችና መለስ ዜናዊ፤-

ኢትዮጵያዊያን ድምበራቸው ሆነው ሲያርሱ፤ ሱዳኖች አፍነው ወደ ሱዳን ወስደው 28 ገበሬ ታሳሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ቅጣት ተበይኖባቸው ፤ወደ ቪ ኦ ኤ ተደውሎ ምስጢሩ ይፋ ሆኖ እያለም ቢሆን፤ የወያኔ መሪ የነበረው ዋሾው መለስ ዜናዊ ስለ ሁኔታው እንዲያብራራ ሲጠየቅ፤ ፓርላማ ውስጥ፤ በሕዝብ ፊት ‘የታሰረ ኢትዮጵያዊ ዜጋ የለንም’ ሲል ምስጢሩን ደብቆታል / “concealing”። የተደበቀው ምስጢር ቆይቶ መደበቅ በማይቻልበት ሁኔታ ከደረሰ በላ ደግሞ የታሰሩት ሰዎች “ገበሬዎች ሳይሆኑ ኢንቬስተሮች ናቸው” ሲል  ነገሩን ከውሸት ለመሸሸ ሲል ሁኔተውን ጠምዝዞ (spinning) ለመሸሽ ሲል እንዴት እንደተጋለጠ liar liar Pants on fire እያሉ የአሜረካን ታዳጊ ህጻናት ልጃገረዶች በገመድ እየዘለሉ የሚጫወቱትን ውሸታምን የማጋለጥ አባባል በወቅቱ እኛም በመለስ ዜናዊ ላይ የጮኽነውን liar liar Pants on fire ጩኸት እናስታውሳለን (‘ኡፉፍ ፈዬ ዲበላ’ እያሉ የመቀሌ ልጃገረዶች አሸንዳ ጨዋታ የሚዘፍኑት አይነት ማለት ነው (የሰውነቱ ጠረን ከሩቅ የሚሸት የፍየል ምኩት ማለት ነው)። 

ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው በቅጽል ስሙ ዶ/ር “0” (ዶክተር ዜሮ)፤-
የፖለቲካ አቃጣሪዎች የሚባሉት ወይንም በወላጆቻችን አጠራር ‘ባንዳዎች’ ሲዋሹ እንመልከት። ደ/ር ጌታቸው በጋሻው በቅጽል ስሙ ዶ/ር “0” (ዶክተር ዜሮ) ብለን የምንጠራው የግንቦት 7 እና የኦነግ አለቅላቂ ባሕሪ እዚህ ልጥቀስ። “ኦነግ የመገንጠል ጥያቄ አቅርቦ አያውቅም” ሲል በሕዝብ መድረክ ወጥቶ ሲዋሽ አደምጣችል። በወቅቱ የኦነግ ፕሮግራም/መርሃ ግብር አውጥቼ እየዋሸ መሆኑን የኦነግ የመገንጠል ሰነድ የሚተነትነውን ለንባብ አቅርቤአለሁ። በርካታ ወገኖችም በንግግሩ ተገርመው “አውግዘውታል”። ተጋለጥ ሲለው፤ ከዋነኛው ኦነግ ተነጥለን ‘አዲስ አስተሳሰብ የያዘ ‘ኦነግ’ መስርተናል ብለው እንደገና ከጥቂት ቆይታ በላ ‘ኦሮሞ ዲሞክራሰቲክ ግምባር’
ወደ እሚል ተሰይመናል ብለው አንደገና ራሳቸውን ለሁለተኛ ጊዜና ሦስተኛ ጊዜ፤ በሌላ ስም እንደ አሜባ እየተራቡና እየተከፋፈሉ ኦነግን አዲስ ስም “እየሸፈኑ” የመጡት እነ ጃንዳይ እና የሕግ ክፍሉ ተጠሪ እነ ዶ/ር ኑሩ ደደፎ እነ ሌንጮ ለታ እና ሌንጮ ባቲ የተባሉ ‘ኦነጎች” የጌታቸው በጋሻው ጥብቅና አድምጠው፤ “ዋሾ’ ካገኘን እኛም አብረን እንዋሽ” ብለው አብረው በየአዳራሹ  እየሄዱ “ኦነግ የመገንጠል ጥያቄ ጠይቆ አያውቅም” ሲሉ “እኛም የድረገጻቸውን አድራሻ ለሕዝቡ በማሰራጨት “የመገንጠል ጥያቄአቸውን” ቁልጭ ብሎ የሚያሳይ የፕሮግራም ዝርዝር ድረገጻቸው ላይ የሚነበበው “ቅጂውን” ለሕዝብ በማሰራጨት በማጋለጣችን፤ በሳልስቱ “አለማፈራቸው” አዎ ኦነግ የመገንጠል ጥያቄውን ትቶ አብሮነትን በመከተል /ራስን በራስ የመወሰን መብት/ በሚል አጀንዳ ለውጠነዋል፡ በማለት እራሳቸውን እና ጌታቸው በጋሻውን አስገምተው የመገንጠል ጥያቄ ሲያራምዱ እንደነበር አምነዋል። ኦነግ ያንን ሲያምን፤ ጌታቸው በጋሻው ባንድ ሚዲያ ስለ ጉዳዩ ተጠይቆ ገለጻ እንዲሰጥ ሲጠየቅ፤ “ይህ ለኔም አሳክኮኛል” ሲል መዋሸቱን በድንጋጤ አምኗል። እንዲህ ያሉ ሕዝብን የሚንቁ ‘ዋሾች’ በጣም በርካታዎች ናቸው። 

ኢሳያስ አፈወርቂ መቀሌ ዓይደር ህፃናት ት/ቤት

በናፓል ቦምብ ህጻናት እንዲጨፈጨፉ  ሲያደርግ እሱ እና አሽከሮቹ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው ሲመልሱ “እኛ ህጻናት ት/ቤት አልደበደብንም ፤ ያጠቃነው ወታደራዊ ማሰልጠኛ እና ወታደራዊ አይሮፕላን ተዋጊ ጣቢያ መከማቻ ቤዝ ነው ሲል መዋሸታቸው እንዳይበቃ “አልአሚን” የተባለ ወኪሉ በሚዲያ ቀርቦ ካሁን ወዲህ ወያኔ “አንዲት አይሮፕላን የቀረቺው ይመስለኛል፤ መቀሌ ውስጥ የተከማቹ ተዋጊ አይሮፕላኖቹ ሁሉም አጋይተናቸዋል” በማለት “ሊበራል ላይ” በመባል የሚታወቀው የውሸት ባሕሪ ሲዋሽ አድምጠናል። ቆየት ብለው ደግሞ የሰጡት መልስ አላዋጣ ሲላቸው ‘አብራሪው አዲስ አብራሪ በመሆኑ በስህተት ት/ቤቱን በመደብደብ ወታደራዊ ማሰልጠኛ መስሎት ደብድቧል” ሲሉ ከወንጀል ተጠያቂነት ለመሸሽ ሲሉ ቀጥተኛ መልስ ላለመስጠት ብዙ ከተጠማዘዙ በኋላ አድማጭን ለማጭበርበር /ስፒኒንግ/ ቀለበት ውስጥ የተጓዙት ጉዞ እናስታውሳለን።
መለስ ዜናዊና ቅንጅት፡

 በቅንጅት ምርጫ ጊዜ የትግራይ ሕዝብ አስደንግጦ ወደ ወያኔ ድጋፍ ለማስሰለፍ የጣረው “የኢንተርሃሙዬ ፕሮፓጋንዳ” አንድ መሪ ስልጣኑን ለማስቀጠል “አስደንባሪ ውሸት” (ፊር ሞንገር) ተብሎ የሚታወቀው የውሸት ዓይነት እስከመዋሸት የሚደርስበትን ባሕሪ እንመልከት። “ንብረት ወደ ቀበሌ፤ ትግሬ ወደ መቀሌ” በሚል “አስደንባሪ ውሸት/ፊር ሞንገር/ በሕቡእ በማሰራጨት የተወሰነውን ሕዝብ አስደንግጦ ወደ እራሱ ወገን ተደናግጦ እንዲሰለፍ የተደረገው “የውሸት ዓይነትም” ታስታውሳላችሁ።

በዚህ ሳይወሰኑ፤ በዛሬው ድርቅ የተከሰተው የወያኔዎች ፕሮፓጋንዳ ባለስልጣኖችና ሚዲያዎቻቸው እውነቱን ለመደበቅ ሲሉ ስለ ድርቁ ተጠይቀው መልስ ሲሰጡ ወይንም ሲተነትኑ ያልጠማዘዙት ወልጋዳ መልስ አሰጣጥ አልነበረም። ‘ድርቅ’ እንጂ ‘ርሃብ’ የለም፤ ‘ርሃብ’ አንጂ ‘ሞት’ የለም፤ ‘ከብቶች እንጂ ሰው አልሞተም’፤ ዜናው “ኤክስትሪሞች እንደሚያጋንኑትና እንደሚዋሹት አይደለም” ፤ “የሚታዩት ፎቶግራፎች በደርግ ዘመን የተነሳው የርሃብተኛ ፎቶግራፍ እንጂ የዛሬ አይደለም፡….ወዘተ ወዘተ….. እያሉ ሲያታልሉ ሲጠማዝዙ ታዝበናቸዋል።

እርዳታ የሚለው ቃል ወያኔን ስርዓት የሚያሳፍር እንደሆነ ስለሚያውቁ፤ ያንን ለመሸፈን ሲሉ ቃላት በመምረጥ፤ “መተጋገዝ እንደሚያስፈልግ በአጋሮቻችንም በመንግሥትም በኩል ተገልጿል” ይላሉ።  “እርዳታ ሰጪዎች” ላለማለት “አጋሮች” የሚለው ቃል በብዛት ይጠቀማሉ።


ጌታቸው ረዳ የተባለው የወያኔ ‘አፈኛ

እንዲህ ሲል ድርቁን ለመደበቅ ሲል “እዚህ ግባ በሚባል ደረጃ ከመንግስት ራስ አቅም በላይ ሆኖ የመጣበት ነገር የለም”፤ ሲል (በመጽዋቾቹ ጥናት ከ8 ሚሊዮን በላይ ርሃብተኛ) አቃልሎ ያቀረበውን ችግር በሳምነቱ ደግሞ ያንን በመርሳት ከባድ ፈተና መሆኑን አምኖ ከፓርትነሮቻችን ጋር በመነጋጋር ሁኔታውን ለመቆጣጠር እየሰራን ነው” ይላል። የርሃብተኛ ብዛት ወያኔ ግልጽ ስታትስቲክ ስለሌለው፤ ከመጽዋች አገሮች ጋር በቁጥር ሲጋጭ የወያኔው ሚስቴር አፈኛ ጌታቸው ረዳ ደግሞ እንዲህ ይላል 

“ቁጥር ጋር በተያያዘ በመታደልም እንዳለመታደልም ሆኖ ከኛ ጋር ያሉ ፓርትነሮች ገዘፍ ያለ ቁጥር ካልጠሩ ለዚህ ሥራ ሲባል የሚሰበስቡት የገንዘብ መጠን አደጋ ላይ ይወድቃል ብለው የሚያምኑ አሉ።” 
ሲል የርሃብተኛ ብዛት ቁጥሩ ከፍ ካለ ወያኔ ሕዝቡን መመገብ አቅቶታል ተብሎ እንዳይጋለጥ በመስጋት ለሥልጣኑ ክብር ሲል የርሃብተኛ ቁጥር ብዛት ከፍ ብሎ እንዲገለጽ አይወድም። ይህ እጅግ አደገኛ የሆነ ርሃብተኛን እየደበቁ ሥልጣንና ክብርን ለመጠበቅ የሚደረግ አደገኛ የውሸት ባሕሪ መቸ እንደሚቆም ሳስበው ይገርመኛል።

“ፉገራ ኒውስ የተባለው በጣም የምወደው ተቺ/ተንታኝ ሚዲያ፤ ይህንን በስፋት ሲተነትነው “ፓርትነሮቻችን” የሚላቸው ዕድሜ ልካችንን ሲረዱን/ሲመጸውቱን የነበሩትን ሃብታምና ሃያላን መንግሥታትን ነው እንደ የሥራ ባልደረባዎቻቸው ቆጥረው “ፓርትነር” እያሉ ‘የሚጠሯቸው’ ሲል የወያኔ ፋሺስታዊ ትዕቢተኛ ባሕሪ ምን ያህል እንደሚዋሽና እንደሚጎማለል ታዝበናል። ይህ የሚያመለክተን ባላስፈላጊ የቃላቶች ስንጠቃ በመግባት እውነቱን ለመደበቅ /ኮንሲል-ለማድረግ/ ከእውነታው ለመሸሽ እየጣሩት ያለውን ውሸት የሕዝብ ሕይወት ምን ያህል እንደሚጎዳ ቢያውቁትም፤ የሚያሳስባቸው አይሆንም።

እንቀጥል፤-

አምና አንድ የተቃዋሚ ታዋቂ ሚዲያ ‘ቦኮ ሓራም’ የተባለ የናይጀሪያ እስላማዊ ሽብርተኛ ተዋጊ ክፍል ወያኔ ጋር ንክኪ እንዳለው፤ ያውም ማሰልጠኛ እና መሳሪያ እንደሚሰጥ ያለምንም ማመንታት ዘግቧል። እንዲህ ያለ ውሸት ለማሰራጨት የሚገደዱት ክፍሎች ከጭብጥ ውጭ ሲሆኑ “ጠላትን” በሕዝብ ዓይን ለማሳጣት ሲሉ እራሳቸው በሚያስገምት ውሸት ውስጥ በመክተት “የሚዲያ ውሸት” በመባል በሚታወቅ “ቂምን ተንተርሶ” የውሸት ዓይነት ሲዋሹ አንብበናል።

በኢሳያስ አፈወርቂ እና በመለስ ዜናዊ የታቀደ “መንግሥታዊ ውሸት”

በመባል የሚታወቀው የውሸት አይነት ስንመለከት “አማራን” ለማስጠላት ሲሉ ‘አማራ ነን’ የሚሉ አሳፋሪ ግለሰቦችን መልምሎ ወደ ኤርትራ በመላክ “የኤርትራ ሕዝብን በተለይም ወደ ከረን/ተሰነይ…..በመጓዝ አማራ ያደረሰው ጭፍጨፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ የአማራ ሕዝብ እንደላካቸው በአማራ ስም ይቅርታ እንዲጠይቁ ተደርጓል። ይህ ‘በስትራተጂ’ የተጠና የጋራ/የቡድን/የመንግሥት ውሸት ይባላል።

‘ነጋሶ ጊዳዳ”

የነገድ ፖለቲካ የሚያራምዱ የምናውቃቸው ግለሰቦች የሚያራምዱት የፖለቲካ መስምር ወይንም የጠሉትን መሪ ለማስጠላት ሲሉ ‘ለዘመኑ የማይመጥን የማይሰራ ፖለቲካ ጥያቄ” ሆኖ እየተበላሸባቸው መሄዱን ሲያውቁ “ለፖለቲካ መነሻቸው የሚሰጡት “ሽፋን” እጅግ “በጣም መናኛ የሆነ፤ አነስተኛ የሆነ ‘ኢፍትሃዊ የስርዐት ባሕሪ” አጋንኖ በማቅረብ እነሱ ሥልጣን ላይ በወጡበት ወቅት የሰሩትን ዘግናኝ ሃገራዊ ወንጀላቸውን በመደበቅ ፖለቲካቸውን ለማሳመር ይጥራሉ።

 ምሳሌ ልስጥ፡-

በቅርቡ ከአንድ ጸሐፊ የቀረበ ጽሑፍ ልዋስ እና እንደ ማስረጃ ላቅርብ። “ነጋሶ ጊዳዳን” ታውቁታላችሁ። የጎሳ ፖለቲካ በአገራችን ተግባራዊ እንዲሆን ወያኔን አቅፎ ደግፎ በሽግግሩ ወቅት ከፍተኛ አሳፋሪ ስራ ሲሰራ የነበረ ግለሰብ ነው። በላም ከነ ‘ስዬ አብርሃ’ ጋር ወግኖ መለስ ዜናዊን በመክዳት ፡የኢትዮ-ሚዲያ አዘጋጅ እንደ እነ አብርሃ በላይ በመሳሰሉ በትግራይ ብሔረተኞች ታቅፎና ተደግፎ እየተሞገሰ የዘለቀው የወያኔ ፕረዚዳንት የነበረው ‘ነጋሶ ጊዳዳ” ሎሚ ከተባለ ጋዜጣ ባደረገው ቃለ ምልልስ ‘ትናንሽ የሆኑ የስርአት በደሎች በማጋነን “አጼ ምኒሊክ በአያቶቹ ላይ አደረሱት ያለቸውን በደል’ እንመልከት፤-


የአፄ ምኒልክ ወታደሮች መጥተው አያቴን 6 ሠዓት ያህል ረጅም መንገድ እህል አሸክመው ወስደዋቸዋል። እና ይህንን ለመርሳት አልችልም።” 

በማለት አነስተኛ በደሎችን ትላልቅ ስዕል እንዲኖራቸው የኔ የሚሏቸው የነገዶቻቸው ማሕበረሰብ ምሬትና ቁጭት እንዲያድርበት ‘ፖለቲካ’ ለመስራት የሚደረግ “ብሎውን አውት” “ተጋንኖ” የሚቀርብ ጥቃቅን በደሎችን እያገዘፉ የሚሰራጭ ‘የቃለ አጋኖ’ ባሕሪ ልብ ይለዋል።

ይህ እና ይህ የመሳሰሉ የውሸት ባሕሪዎች እየታገዙ ‘መሪዎችና ጋዜጠኞች…’ ሲዋሹ ሕዝቡ አብሮ እየዋሸና ውሸታቸውን በጭብጨባ እያሞገሰ ሲጓዝ መጨረሻ ላይ ማሕበረሰቡ ቀውስ ውስጥ ገብቶ ከጠበቀው በላይ ችግር ውስጥ ገብቶ ማሰሪያውና መፍቺያው ጠፍቶት “ለትርምስ፤ለጭፍጨፋ፤ ለስደት” ተዳርጎ ሬሳ እስከመጎተት፤የፈጠራ ባንዴራ እያውለበለበ፤ የሌለን የሕልም አገር እየፈጠረ፤ ሕዝብ አንዲጨፈጨፍ፤ እንዲባረር፤ቤተ-ጸሎት እያቃጠለ ወደ አረሜናዊ ዓለም እየተሸጋገረ የወንጀል ባሕሪ ለማየት የምንበቃበት ምክንያት፤ ሚዲያዎች፤ምሁራን እና የፓለቲካና የሃይማኖት መሪዎችሞራላዊ ውድቀት ደርሶባቸው በውሸት ዓለም ሲያብዱ፤ ማሕበረሰቡም አብሮ እያበደ መጨረሻ እራሱን አፍርሶ ወደ የማይጨበጠው አደገኛ የማንነት ፍላጋ ቀውስ ውስጥ ይገባል። እየሆነ ያለውም ይኼው ነው።

የአል ማርያም “ቺታ” ወጣት ወዴት እየተጓዘ እንደሆነ ባናውቅም፤ ጉዞ ድምብሩ ተደናግሮበት የሚሰራው የማያውቅ ‘እርስ በርስ’ በነገድ ተቧድኖ፤ ድንጋይ ውርወራ፤ በጩቤና በዱላ በየ ዩኒቨርሲቲው ሲራኮትና ሲሰዳደብ እየታዘብን ነው። ቤተክርስትያናት ተቃጥለዋል፤ ኦሮምያ ኬኛ ተጠናክሯል፤ ሬሳ መጉተት ተጅምሯል፤ የኦነግ ባንዴራ በይፋ በሕዝብ/ሕፃናት ጭምር ተደግፎ ሲውለበለብ አይተናል፤ … የሚቀረው ትዕይንት ምን እንደሚሆን “ኢትዮጵያ ባስተማማኝ ብሩህ ጎዳና እየተጓዘች ነች” ሲሉ በ ዘ- ሐበሻ ድረገጽ የሚጽፉ እነ “ይልማ በቀለ”፤ እና የመሳሰሉ “አክቲቪስቶች፤ ፈላስፋዎች፤ ጸሓፍትና ጋዜጠኞች” እንዲነግሩን እንጠብቃለን።

ኦሮሚያ ኬኛ ድራማዊ ግንጣላ ወዴት እየተጓዘ እንዳለ በጥሞና እየተከታተልን ነው። የሰው ሕይወት እየቀጠፈ፤ቤተክርስትያናት እየተቃጠሉ፤ሬሳዎች እየተጎተቱ፤የኦሮሚያ ኬኛ “ራዮት” በዛው ትራጀዲ እየታጀበ፤ እነ ተስፋዬ ገብረአብ የመሳሰሉ የኢሳያስ አፈወርቂ “እንሰሳ ዘቤት” እና የመሳሰሉ ፋሺስት ተገንጣዮች እየተጠራሩ በሕልም ምርቃና ውስጥ ገብተው የአማራ ማሕበረሰብ እልቂትና የኢትዮጵያዊ የሞተ ሰው ሬሳ ሲጎተት፤ የኦነግ ባንዴራ ሲውለበለብ፤ የቁንድፍቱ ገደል በዓይናቸው እየቃኙ ትውስታቸው ተነስቶባቸው በደስታ ዓለም ሲፈርጡ፤ሲቃዡ እያየን ነው።
የአልማርያም ‘ችታዎች’(አውራሪሶች) አገር አፍራሹና፤ የሽብርተኛው የኦነግ ባንዴራ በዶኖ ላይ እያውለበለቡ ላይ ያሉት ዱላ የታጠቁትን ህፃናትም ይጨምር ይሆን? ነገዳዊ ፋሺዝም ከመቸውም ጊዜ እየጎለበተ መጥቷል። ምሁራን እና ሚዲያዎች ይወቁት አይወቁት ፋሺስታዊ ድርጅቶች እንቅስቃሴ በማጎልበቱ ሂደት ላይ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው። ፋሺስት ድርጅቶች የፕሮፓጋንዳ ስራዎቻቸው የኢትዮጵያዊያን ሚዲያዎችን በሚገባ እየተጠቀሙባቸው ነው። በዚህ ወር ኢትኦ-ሚዲያዘ-ሐበሻ፤ ሕብር ራዲዮኢካዴፍ…የሚባሉት ድረገፆች “የጸረ ኢትዮጵያ የተገንጣይ ፋሺስት ድርጅት ሃይል ‘ቆሻሻ ፕሮፓጋንዳ’ መጣያ በርሜል ሆነዋል።” እነዚህ ሚዲያዎች ያልገባቸው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት “ፋሺስት ድርጅቶች” ገንነው የወጡ እንዳሉ፤ እነሱም “ወያኔ” እና ተገንጣዩ “ኦነግ” መሆናቸው የገባቸው አይመስሉም። ስለሆነም ሚዲያዎቹ ያለምንም “ሳንሱር/ሬስትሪክሽን” የኦነግ ፋሺስታዊ ፕሮፓጋንዳ በሰፊው “እያናፈሱለት” ይታያሉ።ሚዲያዎቹ “ኦነጎች” እስኪመስል ድረስ ኦነግ ፕሮፓጋንዳና ጸሐፍት ተጥለቅልቋል። ፋሺሰቶችን የሚያጋልጡ አነድነት ሃይላት ግን ከጥቂቱ በቀር አብዛኛዎቻችን በሕዝባችን አንዳይነበብ ገድበውናል። ተቃዋሚ ሚዲያዎች በመጪው አዲስ ስርዓት (ከመጣ) ወደ ሥልጣን እንዳይመጡ ትግላችን በነሱም ላይ ይቀጥላል። ምክንያቱም የከፉ ፋሺስታዊ ሚዲያዎች እንደሚሆኑ ከወዲሁ ምልክቱ ጎልቶ እየታየ ነው።

ፋሺስቶች ያለ ጦርነት እና ያለ ሚዲያ (ኮንትሮል ኦፍ ዘ ማስ ሚድያ) ትኩረት አጀንዳቸው ሊያስፈጽሙ አይቻላቸውም። የፋሺስቶች ፕሮፓጋንዳ በኢትዮጵያዊያን ሚዲያዎች ተፈቅዶ “ያለምንም ሳንሱር/ክትትል” ሲዘረጋ ያላወቁት ነገር (አርግጥ አንዳንዶቹ ሆን ብለው የሚሰሩት ትብብር ነው) ሂትለር/ Hitler ስለ ፕሮፓጋንዳ ጥቅምና  ሕብረተሰብን የማሞኘት ሃያልነቱ በእንዲህ ይገልጸዋል።

“All propaganda must be so popular on which an intellectual level, even the most stupid of those towards whom directed will understand it. Through clever and constant application of propaganda, people can be made to see paradises as hell and also the other way around to consider the most wretches sort of life as paradise.” (Hitler)

በመጨረሻ ትችቴን ለማጠቃለል ያህል፤ እየተቹ ያሉ የአንድነት ሃይሎች በርካታ ቢሆኑም ጥቂቶቹን ለመግለጽ ትችቴን ከማጠቃለሌ በፊት በዚህ አጋጣሚ ዶ/ር አበራ ወርቁ ከካናዳ እያስተማረን ያለውን ስለ የነገድ እና የፉደራል አስተዳዳር ልዩነት እጅግ ጠቃሚና የሚመሰገን ስራ ስለሆነ በርታ እንለዋለን።ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ የዘረኛች ሳትሆን የሸዋ /ሐገር ዋና ከተማ ናት!! February 23, 2016 (ከተስፋዬ ኮንን)

Respond to Prof Messay Kebede’s Article February 17, 2016 (By Kaleab Tessema)

እና  እንዲሁም  To Members of European Parliament – From : Moresh Wegenie Amhara Organization (MWAO) February 21, 2016

 ከአውሮጳ ማሕበር የቀረበው አማራን የመወንጀል አባዜ ለማስቆም የቀረበ የተቃውሞ ደብዳቤ።  ይህ በቅርቡ የተሰነዘረው የውሸት ውንጀላ የመጀመሪያ ሳይሆን ‘ሆን ተብሎ’ ከዚህ ቀደም አምና ፤ ምንጩ ማን አንደሆነ የማናውቀው  “ግንቦት 7 የአማራ ድርጅት ነው” በማለት አማራውን ከግንቦት 7 በማያያዝ የተሰራጨውን ሰንድ ሲዘረጋ ተቃውመነው እንደነበር ታስታውሳላችሁ።

ያ አልበቃ ብሎ፤ ዛሬ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ፤ አውሮፓ ማሕብር የሚባለው ‘ጉደኛ ማሕበር’ መረጃው ከየት እንደሚቀበለው ባናውቅም፤ በግምት በግንቦት 7ም፤ ሆነ ኦነግ ወይንም በወያኔዎች ወይንም ኤርትራኖች…ወይንም….. ባልታወቀ የድርጅት/የሰራተኛ/የጋዜጠኛ ወይንም የፈረንጅ ሴረኛ ግለሰብ መረጃውን እየተቀበለ ‘ማሕበሩ’ ያለ ምንም ማጣራት ‘አማራን’ የመወንጀል አባዜው ስለቀጠለበት፤ ከዚህ ደብዳቤ አያይዞ ፤“ዜጎች የተቃውሞ ሰልፍ” በጽ/ቤቱ ፊት ቢያደርጉ መልካም ነው እላለሁ። ምንጩም መጠየቅና እንዲታወቅ ማድረግ አስፈላጊ ነው።ውሸት አውሮጳ ማሕበርም፤ በተባበሩት መነግሥታትም፤ ሳይቀር ቦታ ተሰጥቷት ዓለም እያናጋች ነው።  “ውሸት አገር ያፈርሳል፤ አንድ ቅማል ሱሬ ያስፈታል” ያልኩበት ምክንያትም ለዚህ ነው።

አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ (Editor Ethiopian Semay- getachre@aol.com