የገዳዮችና እና የሙታኖች ዝምታቸው
እንቆቁልሽ በኢትዮጵያ ምድር
ጌታቸው ረዳ
( Ethio Semay)
በኢትዮጵያ ምድር ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ እስካሁን ድረስ በመንግሥትም ይሁን “ትምህርት በቃኙ” በማሕበራዊ የፖለተካ እና በሃይማኖታዊ ለበስ ፖለቲካ መሪዎች ምክንያት በትክክል በአሃዝ ቁጥሮቹን ለማስቀመጥ በሚቸግር ሁኔታ ዜጎች በሜንጫ፤በሳንጃ በጥይት፤በቦምብ እና በቀስት ተገድለዋል፤ አካለ ጎደሎ ሆናዋል፤ ተሰድደዋል፤ ንብረታቸው ተዘርፈዋል፤ ከስራቸው ተባርረዋል፤ ሃይማኖታቸው እንዲቀይሩ ተደርገዋል፤ ቤተጸሎት ተቃጥለዋል፤ መነኮሳትና ቀሳውስት እና ሼኮች ታርደዋል፤ ባለትዳር ሴቶች እና ወጣት እህቶቻችን በጋጠወጥ ታጣቂ ወረበላ ነፃ አውጪ ተዋጊዎች እና ደጋፊወች ተደፍረዋል፤ ሳት ብሎም ከባህላችን አንጻር ላገር ክብር ሲባል (ይመስለኛል) ሊዘገብ ያልተፈለገ ነገር ግን የተከሰተ ሰውን ሰው እንዲበላ የተደረገበት ክስተት (አማራዎች በጉሙዝ ሰዎች መበላታቸውን ልብ ይለዋል) ልክ እንደ “ላይቤሪያ” በኢትዮጵያ ምድር ተከስቷል።
በዜጎቻችን ህይወት የደረሰው ይህ ጥቃት ያለፈ ታሪክ ሳይሆን እስካሁንዋ ደቂቃ ድረስ እየተካሄደ ያለ ተጠያቂ
የሌለው አስደንጋጭ እና እንቆቁልሹ መቋጫ የታጣለት ሽብር ነው። አሁን ያለው ጥገናዊ ለውጥ አራምዳለሁ ብሎ ሙሁራን አጃጅሎ ወደ ጎኑ በማስሰለፍ “ኢትዮጵያዊ” ነኝ የሚለው “የኦሮሞዎች ቡድንተኛ መንግሥትም” ሥልጣን በጮሌነት በጨበጠ በአንድ አመት ውስጥ አገሪቷ በወረበሎች መዳፍ ሥር
እየተናጠች በአራቱ የአገሪቷ መአዝኖች ‘የሚደፈሩ ሴቶች፤ ረሃብተኞች፤ተፈናቃዮች እና የሟች’ ቁጥር በሚሊዮኖች አድጎ ሕዝቡ በፍርሃት ቆፈን ተሰግጦ ተይዟል።
ይህ የጥገና አራማጅ ነኝ የሚለን “የአናርኮ ፋሺስት ቡድን” ለ28 አመት የተፈጸመው አገራዊ እና ሰብአዊ ወንጀል ተጠያቂ እንዲኖር ሲጠየቅ “የማሾፉ ብዛት” እራሱ የጠቆማቸው ግለሰቦች ያውም በወንጀል ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባቸው “ወንጀኞችን” በኮሚቴነት/ኮሚሽን (?) አዋቅሮ “የሰላምና የድምበር…” ምናምን ኮሚሽን የሚል ስም ሰይሞ “ፍትሕ” አመጣላችኋለሁ ብሎ በማሾፍ ላይ ነው።
ይህ ደግሞ ድክመቱ ከስርዓቱ የመነጨ ሳይሆን ከሕግ አዋቂ ምሁራኖቻችን የመነጨ ስንፍና ነው። ምክንያቱም ዜጎች ገዳዮቻቸውን መለየት አልቻሉም።በሚገርም ሁኔታ ገዳዮቻችን ሲሞቱ እናለቅስላቸዋለን፤ ልባችን አብሮ ይሰበራል፤ እናዝንላቸዋለን፤ ሲታመሙ ለሕክምና ገንዘብ እናዋጣላቸዋለን..ወዘተ..ወዘተ..
ከባንዳው መለስ ዜናዊና ከአባ ጳውሎስ ሞት በኋላ ተከታትለው የሞቱት የፋሺዝም ስርዓት አገልጋዮች የነበሩት ዳዊት ዮሃንሰ ፤ የመ/ቶ አለቃ ግርማ እና በቅርቡ የሞተው ነጋሶ ጊዳዳ በዜና ማሰራጫዎች እና በምሁራን ተብየዎች ሲነገር የነበረው ስለ እነዚህ ሰዎች በጎ ፕሮፓጋንዳዎች የሚገርም ነው። ለሰው ልጅ መሞት ለቤተሰብ የሃዘን ስሜት ማሳየት ምንም ችግር የለውም። ነገር ግን ቅጥ ያጣ የልባችን የመሰበር እንቆቁልሻዊ አፈጣራችን እና ስለ እነሱ በጎ ፕሮፓጋንዳ ማውራትና መጻፍ ለኔ ግራ ገብቶኛል።
ሰሞኑ ከዚህ ዓለም በፈጣሪ ትዕዛዝ ወደ ላይኛው ጌታ ለፍርድ የተጠራው “የወያኔዎች ይጥላቻ ሕገ መንግሥት አዋቃሪ” የነበረው እና አንቀጽ 39 ካላከበራችሁ ከናንተም ( አንድነት ፓርቲ) ሆነ ከማንም ጋር ውህደትም ትግልም ግምባርም አልፈጥርም ብሎ ከአንድነት ፓርቲ ራሱን አግልሎ በመጨረሻ የወንጀለኛው ኦዴፓ/ኦፒዲኦ/ ‘አማካሪ’ ሆኖ ስለ “የመገንጠል መብት ተከራካሪ” የነበረው “ነጋሶ ጊዳዳ” ሞተ ተብሎ በዜና ሲሰማ፤ “እማባቸው አፍስሰው ልባቸው የተሰበሩ የዜና አውታሮች እና ምሁራኖችን ያስተላለፉትና የሚጽፉትን ትንታኔ” ሳደምጥ እውነትም ወንጀለኞች የሚወደሱባት እና ሃዘኔታ የሚለገስላቸው አገር በምድር ፈልጉ ቢባል ብቸኛዋ አገር “ኢትዮጵያ” ነች።
መለስ ዜናዊ ሲሞት ያለቀሰው እና በሃዘን ልቡን የቧጠጠው ሃዘንተኛ ተገድዶ ነበር ያለቀሰው የሚሉ ሃያሲያን እና ፖለቲከኞች አንብቤአለሁ። እውነታ ቢኖሮውም ብዙዎቹ ግን ያው የምናውቀው ‘በቡቡ’ አንጀቱ ነበር የለቀሰው። ሕዝባችን ተገዳይን እንጂ “ገዳዩን” ለይቶ አያውቅም። ምክንያቱም ለይቶ የማሳየት ሓላፊነት ያለው የህግ ምሁርና ፖለቲከኛው አላነቃውም። የሚገርመው ምሁሩ አብሮ ለወንጀለኛው ሲያነባ ልቡ ሲሰበር፤ ዜና አንባቢውም ለማንበብ ሲሞክር እንባ ሲተናነቀው የሚታዘብ ተራ ዜጋ የሚያየውንና የሚያደምጠውን ከመከተል ሌላ ምን አማራጭ አለው?
መገንጠልን አልደግፍም እያለ ‘በጎን’ ግን “በአዋቀረው ፋሺስታዊ አንቀጽ” “ኢትዮጵያ ፍረሺ፤ፍረሺ” ለሚሉ የግንጣላ አቀንቃኞች ግን በሪፈረንደም እስከጠየቁ ድረስ መብታቸውን አከብራለሁ እያለ ሲከራከር የነበረው ነጋሶ የምድር ኮንትራቱ ጨርሶ ተሰናብቷል። ብዙዎቹ የዜና ማሰራጫዎች እና ሃያሲያን፤ለኔ ግራ በሚገባኝ ምክንያት ዛሬም የነጋሶን ሬሳን ለማክብር በመላ አውሮጳ እየጎረፉ ሬሳው ወደ አረፈበት ወደ ጀርመን የመንጋጋታቸው ትዕይንት በዜና መልክ ነግረውናል። ህይወቱ ከተሰናበተቺው ከጀርመን ወደ “ኢትዮጵያ” ሬሳው ተግዞ ለነጋሶ ጊዳዳ የሚደረገው የቀብር ስነስርዓት “እንደ ቴዎድሮስ እንደ ክርስቶስ “ዓርብ
ዓርብ ይሸበራል እየሩሳለም” የሚባልለት የስቅለት ቀን አድርገው ሚሰብኩን በርካታ የተቃዋሚም ሆኑ የአናርኮ ፋሺስቱ የዜና መዋቅሮቹ የተቻላቸውን ወራዳ ስብከታቸው እያሰራጩ ነው።
የዜና ማሰራጫዎች እና ሃያሲያን በሚያስተዛዝብ ሁኔታ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሲኖሩበት የነበረው ቤት ‘ጣራው ውሃ እያፈሰሰ’ ተቸግረው በሚኒ ባስ በታክሲ ከሕዝቡ ጋር እየተጋፉ ሲሄዱ ማየት ልብ ይሰብራል እያሉ ሲያላዝኑ መስማት የሚገርም ነው። እንደው ለመሆኑ ዶከተር ነጋሶም እኮ ሲለን የነበረው “ከወያኔ ጋር ሳለሁ ኢትዮጵያን ስለበደልኳት ይቅርታ ታድርግሊኝ» ብሎ ሲያበቃ እንደገና የበደላት አገር «የሚገባኝን ጥቅምና ክብር
አልሰጠችኝም» ሲል ምሬቱን ለዜና መዋቅሮች ሲገልጽ ያንኑ ዛሬ በሚገርመን ሁኔታ “ነጋሶ ጊዳዳ ሲኖሩበት የነበረው ቤት ጣራው ውሃ እያፈሰሰ ተቸግረው ‘በሚኒ ባስ በታክሲ’ ከሕዝቡ ጋር እየተጋፉ ሲሄዱ ማየት ልብ ይሰብር ነበር’ እያሉ ሲቆዝሙለት መስማት የሚገርም ነው። ምን ለሱ ብቻ ለወያኔዋ ‘አረጋሽ አዳነም ፤ ገብሩ አስራትም’ እንዲሁ ለተመሳሳይ ችግር ተጋርጠው ነበር’ እያሉ ለገደሉን ለደበደቡን የባሕር ወደቦቻችንን ላስነጠቁን ሁሉ ‘ልባችን እንዲደማላቸው’ ዛሬም እየሰበኩን ይገኛሉ።
እውነት የዜና ሰዎች እና ምሁራን የዜጋ ተቆርቋሪዎች ብትሆኑ ኖሮ የልጅ እያሱ የልጅ ልጆች፤ የሃይለማርያም ማሞ፤ የአጼ ቴዎድሮሰ የልጅ ልጆች፤ የበላይ ዘለቀ የልጅ ልጆች….ሌለ ቀርቶ የአፄ ሚኒልክ ዛሬም ‘በህይወት ያሉ’ (ሁለት ነበሩ አሁን አንድ ብቻ ያሉ ይመስለኛል)“ብርቅየ” አገልጋዮቻቸው ተቸግረው ተቆራምደው በችጋር ሲኖሩ ‘ምነዋ እንደ ነጋሶ ጊዳዳ አላዘናችሁላቸውም?” መልሱ ግልጽ ነው፦ “እምየ
ኢትዮጵያ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ!!!!” ስለሆነ ነው።
በ1991 ዓ.ም ደ/ር ነጋሶ ጊዳዳ “የጥንት የጥዋቱ ኢትዮጵያዊ ወታደር” ይበተን ብለው ካፈረሱት እና ለውርደት እና ለልመና ከዳረጉዋቸው የወያኔ ሹሞች አንዱ ነጋሶ ነበር።ነጋሶ ጊዳዳና ጓዶቹ ያሸማቀቀው ኢትዮጵያዊ ወታደር የትም ተጥሎ ማን ነበር የጠየቀው? (በውጭ አገር ታማኝ በየነ ፤የሐረር ወርቅ ጋሻው ፤ኮማንደር አሰፋ…….እና የማላውቃቸው የተከበሩ ጥቂት ሰዎች እንዲሁም -እኔም በአቅሜ በገንዘብም፤ በመጽሐፌም ገድላቸውን ጽፊ ሰፊ ምዕራፍ ሰጥቼ እንዲዘከሩ እና እንድናዝንላቸው አድርጌአለሁ)። ስለዚህም ሐዘናችሁና ፕሮፓጋንዳችሁ ቅጥ አጥቷል! አገር አፍራሾችን ወደ አርበኛ እየለወጣችሁ ተቸግረናል!
ግራም ቀኝም ነፈሰ ሰውየው የጸረ ኢትዮጵያ ስርዓት አዋቃሪ ሆኖ በሰራው ስራ ይቅርታ ቢጠይቅም (ካንገት በላይ) ፤ ያው ዞሮ፤ዞሮ ያዋቀረውም ሆነ ህይወቱን ሙሉ የተከተለው መገለባበጥና እና አፍራሽ ፖለቲካ አንዲት ዘለላ መስመርም ሳይጥል ነበር ሲከተል እስከ መጨራሻ የታገለው።
ወዳጄ አቻምየለህ ስለ ነጋሶ እንዲህ ሲል ይነግረናል፦
“ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የወያኔ ሕገ መንግሥት አርቃቂ ጉባኤ በነበሩበት ወቅት በሕገ መንግሥቱ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይወያይበት እንደተወያየበት አድርገው ሕገ መንግሥቱ ሲጸድቅ በመናገራቸው መጸጸታቸውን ገልጸው «ከወያኔ ጋር ሳለሁ ላጠፋሁት ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይቅርታ ያድርግልኝ» ብለው ጠይቀው ነበር። "ዶክተር ነጋሶ ይህንን አንድነት ለፍትሕና ለዲሞክራሲ ፓርቲን ሲቀላቀሉ ይቅርታ የጠየቁበትን ንግግር ወደኋላ ብለው NED የሚባለው የአሜሪካኖች ተቋም እ.ኤ.አ. በ2015ዓ.ም. ባዘጋጀላቸው ፕሮግራም ላይ ወረቀታቸውን ሲያቀርቡ ግን በሕገ መንግሥቱ እንደሚኮሩና በረቂቁ ዝግጅት ላይም ሁሉም [ቡድኖች] እንደተሳተፉ ተናገሩና አንድነትን ሲቀላቀሉ የጠየቁትን ይቅርታ አፈረሱ።" (አቻም)
ይኼ ነው እንግዲህ ሰለ ነጋሶ ጊዳዳ “ላጠፉት ጥፋት ይቅርታ ጠይቀው ተጸጽተው…” እያሉ የውሸት ፕሮፓጋንዳ እየረጩ የምንሰማቸው የዜና ማሰራጫዎች በብዛት አሉ። ከነዚህ አንዱ “ኢሳት” ነው። ሌሎቹ በየ ድረገጹ እና በየ ዩቱቡ ..የተከበሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚወዳቸው….እያሉ የሚሉ የ ዩ ቱብ ቪዲዮ “የዜና ቸርቻሪዎች” ደናቁርትም ተጨምረውበት የፕሮፓጋንዳ ዳንኪራውን እያሳመሩ ይገኛሉ።
ሦስት ነግሮችን አቀርባለሁ፡
አንደኛው- ነጋሶ ጊዳዳ ከግርማ ካሳ ጋር የተጻጻፈበት የደብዳቤው ይዘት
ሁለተኛው- ነጋሶ አዲስ አባባን በሚመለከት አዲስ አድማስ ጋር ያደረገው ቃለ መጠጥቅ ለዚያው ቃለ መጠይቅ ‘አቻምየለህ ታምሩ’ የሰጠው መልስ እያጣቀስኩኝ ማስረጃዎችን አቀርባለሁ።
ግርማ ካሳ ከተባለው እዚሁ አውጭ አገር ኗሪ የሆነ መገንጠልን እና ክልልን የሚቃወም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ዶክተር ነጋሶ ‘ከአንድነት ፓርቲ/UDJ’ የመውጣቱ ምክንያት ክርክር ለገጠመው “ለግርማ ካሳ” ሲያስረዳ “ነጋሶ ጊዳዳ” በደብዳቤ መልክ መልስ የጻፈለትን እንዲህ ይላል።
Dear Ato Girma Kassa, Mar 20, 2014 (By Negaso Gidada)
(posted at Zehabesha website)
“"I now left
UDJ because article 3.1.5 has now been changed which means that UDJ has made it
clear that it does not support the right of self determination of peoples
through referendum in case the question secession comes up." …” To
work in such an organization is for me to violate the right to self
determination, a naturally given human right. Yes it is right that I left the
party.”
ነገሶ አንድነት ፓርቲ መነጠሉን የሰጠው ምክንያት በግርድፍ ሲተረጎም ‘አንቀጽ 3.1.5 የተባለው በድርጅቱ መርሃ ግብር መተግበሪያ የተጠቀሰው አንቀጽ በመሰረዙ ምክንያት ለቅቄአለሁ።’ ይላል። ግልጽ ለማድረግ:- ይህ አንቀጽ የሚያወራው ማንም ነገድ (ጎጥ/ ከተማ/ አውራጃ፤ ክፍለሃገር/ ግለሰብ/ ቡድን) እገነጠላለሁ ካለ በደምጽ ብልጫ ተወስኖለት መገንጠል ይችላል የሚለው ድርጅቱ ስለሰረዘው ‘ይህ ደግሞ ተፈጥሮ የለገሰቺው የመገንጠል መብት ከሚጻረር ድርጅት ጋር መቀጠል ለኔ ሰብኣዊ ጥሰት ስለሆነ አዎ ከድርጅቱ ወጥቻለሁ።’ በማለት ነው እንግዲህ ከአንድነት ፓርቲ የተሰናበተበት ምክንያት ለግርማ ካሳ ያብራራለት።
“አገር እና የተዋለዱ ማሕበረሰቦች እና ጋብቻዎች በግንጠላ ሰበብ ተለያይተው ደቃቃ መንድሮች (አገሮች) ተፈጥረው እንዲበጣበጡ” አገርን የማፍረስን ስልት “የተፈጥሮ መብት
ነው እያለ ከጥንት ጀምሮ ከኦነግ ጋር ሆኖ ሲሰራበት የነበረው አገር አፍራሽ እምነቱን የገለጸ የኦሮሞዎች ምሁር ነበር ነጋሶ ማለት። ይህ ደግሞ በመጽሐፉም በቃለ መጠይቁም ውስጥ “ለተሳሳተው ፖለቲካው ይቅርታ ጠይቋል” ተብሎ ከተነገርን በኋላ የተከተለው እምነቱ ነው።
ዶክተር ነጋሶ ‘የመገንጠል መብት ከማያከበር ጋር በምንም መልኩ መስራት እንደማይፈልግ’ ግልጽ አድረጎልን ነው የሞተው። በሚገርም ብልጠት ደግሞ “መግንጠልን አልደግፍም ግን
የሚገነጠሉትን እደግፋለሁ” ሲል ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የሆነው መስመሩ በርካታ “የዋህ ምሁራኖች” እንዲያምኑት አድርጓል። እንዲህ ያለ የተገንጣዮች የብልጥነት ስልት ሁሌም ይገርመኛል።
“I oppose
secession, but support the right to secession.” (ነጋሶ ጊዳዳ)
አንድ ትግርኛ ምሳሌ አለ፤ “ወጮ እንተገልበጥካዮ ወጮ” ይባላል። ትርጉሙም “ወጮ ብትገልብጠውም ያው ወጮ” (ወጮ ሸካራ ነው ብትገለብጠውም በሁለቱም ገጽታው ያው ሸካራ/ኬሻ ነው) የሚሉት ዓይነት ነው የነጋሶ የመቃወም እና የማክበር ፖለቲካ ክርክር። እንዴት ጤነኛ ሰው ሆነህ ‘ለምትቃወመው የፖለቲካዊ ሴራ ድጋፍ ትሰጣለህ? ይህ የፖለቲካ ድንቁርና ደግሞ ኦሮሞዎችና ትግሬዎችን ብቻ አይደለም ያጠቃው፡ የአንድነት ወገኖች በሚባሉት ኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞች፤ ምሁራን እና ጋዜጠኞችም “በመብት ስም” ልክ እንደነጋሶ “መገንጠልን እንቃወማለን ፤ ግን እንገነጠላለን ካሉም "ድምጽ
ተጠቅመው" አገር እናፈርሳለን ካሉም ያፍርሱ’ ይላሉ።
እንደ ሂትለር “ዲሞክራሲያዊ ድምጽ ተጠቅመን “እስላሙንም ክረስትያኑንም ወይንም አማራውን…እንጨፈጭፋለን ካሉም በሪፈረንደም እስከተጓዙ ድረስ “ተፈጥሮ የለገሰቻቸው “ዲሞክራሲያው” መብት ነውና” መገንጠልም ማፍረስም ይችላሉ፡ ብቻ የሕዝብ ድምፅ ይጠቀሙ! የሚለው ያበዱበትን መርዝ ሳይሸማቀቁ የሚያብዱበት ዕብደት ከሕሊናቸው ዛሬም አልተወገደም።
በድምጽ እስከተከናወነ ድረስ “ውጣ እያሉ” መንደርን ማቃጣል መጨፍጨፍ፤….ማስተዳዳር በነዚህ ግርምቢጥ ሙሀራኖች ትርጉም የተፈጥሮ መብት ነው። ይህ አፍራሽ መብት እንደመብት የሚቆጥሩት ምሁራን እና ፖለቲከኞች ብያንስ (90%) ዘጠና ከሞቶ ይሆናሉ። ዲሞክራሲ ከአገር ማፈረስ ጋር እያያዙ ዲሞክራሲ የሚባል ‘እጀታ”
ያልተበጀለት ይህ አደገኛ የሕሊና መፈላሰፊያ ‘ምሁራኖቻችንን’ ጭንቅላት የዘቀጠ መሆኑን ያየንበት መስፈርት ነው።
የኛ ምሁራን ሰለጡኑ እንዲባሉ “ዘልለው” “እስከ መገንጠል” የሚል አሳፋሪ ድንቁርና ሲቀበሉና ሲሰብኩ 50 አመት ተቃርቦአቸዋል። የዲሞክራሲ አገር የምትባል “አሜሪካ” መገንጠልን አታከብርም። ይህንን ያውቃሉ። የኛዎቹ ግን አሜሪካን ለመብለጥ ሲሉ “የተፈጥሮ መብት” የሚባል ከየት አንደቀዱት አይታወቅም (ለኮሎኒ አገሮች ነፃ ሲወጡ የተደነገገው ሕግን አጣምመው) ምሁራኖቻችን ያንን ሐረግ እየመዘዙ ‘ዓድዋ ላይ ያሸነፍናቸው ፈረንጆች ጊዜ ጠብቀው ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቂሎች ምሁራኖቻችንን እየፈለጉ ‘በጥበብ ያስጋቱዋቸው ‘መርዝ’ አሳብዶአቸው እስከመገንጠል እያሉ ዕብደት ውስጥ ገብተዋል። በዚህ ዕብደት ተበክለው ከነበሩት ውስጥ አንዱ ነጋሶ ጊዳዳ ነበር።
ነጋሶ በተጠቀሰው ደብዳቤው ስለ ላቲን ቋንቋ አጠቃቀም እና ስለ ቄሮ እንዲህ ይላል።
“When
I recently hear that some people in the Diaspora attacking the “Qube
Generation” it makes me sick. To demand from people to learn Oromo language and
that they must know the language if they want to work in Oromia State"
As for Oromo
language, I personally prefer Latin, not because I do not like Geez, but
because it does not fit for the Oromo language.”
“ውጭ አገር
የሞኖሩ ኢትዮጵያውያን “የቁቤ ትውልድ”
(ቁቤ ጀኔረሺን) ስለ ተባለው
የኦሮሞን አዲሱን
ትውልድ ሲተናኮሉት ስመለከት ያመኛል!” በማለት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከ5 አመት በፊት በህይወት እያለ ለግርማ ካሳ በጻፈው ደብዳቤ ያብራራል።
ቄሮ የተባለው አሁን በዓይናችን እያየነው ያለው በኢትዮጵያውያን ነገሥታት እና እና በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንዲኖሮው ተቀርጾ ያደገ እጅግ በጣም አደገኛ የሆነ “የታሊባን” አይነት አክራሪ የሆነ የሽብር
አቀንቃኝ በዛሬው ዘመን በምን ዓይነት የወንጀል ተግባር ላይ እንደተሰማራ የቪዲዮ ፤ የፎቶግራፍ የድምጽ የጽሑፍ ማስረጃዎች በብዛት ተሰንደዋል።በጥላቻ ተቀርጾ ላደገው ወጣት ነው ነጋሶ አትተቹብኝ ስለ ቄሮ ሲነሳ “ያመኛል” ሲለን የነበረው።
አንድ የሚያሳዝን ነገር ልንገራችሁ። አገር ውስጥ የኦሮሞ እረቻ በዓል ሲከበር ብዙ ሰው በመጨፍጨፉ ምክንያት የተነሳ “ዳውን ዳውን ወያኔ!!” ሲል የነበረው የኦሮሞ ወጣት ተማሪ ወደ ውጭ አገር በስደት ሲመጣ መጀሪያ የተበረከተለት ስጦታ በደም የተነከረ የሚመስል እንኳን በእጅ ለመያዝ ለማየት እጅግ የሚዘገንን የተቆረጠ ጡት በሰው መዳፍ ተይዞ የሚያሳይ የድንጋይ ቅርጽ እንደ ዋንጫ ሽልማት ነበር የጥላቻ መምህራን ያበረከቱለት። ይህ ወጣት ምስሉን በፎቶ ተነስቶ ስመለከት የኦሮሞ ምሁራን የላይቤሪያ ዓይነት በጭካኔ የሰከረ ትውልድ ለማፍራት የተጓዙበት ርቀት ስመረምረው እጅግ ከፍተኛ ወንጀል የመፈጸማቸው ስፋትና ጥልቀት ተጠያቂነት ያለመኖሩ ሁሌም የሚከነክነኝ አሳዛኝ ሁኔታ ነው።
ነጋሶ እነዚህን ቄሮዎችን እና እነ ጃዋር መሓመድን ነው ሰው ሲተችባቸው ያመኛል ሲለን የነበረው ነጋሶ ጊዳዳ።
ነጋሶ በዚያ ሳይወሰን፤ የግዕዝ ፊደልን (የኢትዮጵያውያን ምጠቀተ ዐውቀት ላለመቀበል) ጥላቻውን ለማሳወቅ ሲል “ላቲን” የተባለ የቅኝ ገዢዎች ፊደል ለኦሮሞ ኢትዮጵያውያን የመረጠበት ምክንያት ሲናገር ግዕዝን ጠልቼው ሳይሆን ለኦሮሞ ቋንቋ አይመችም” ሲል ማስረጃ የሌለው ውሸቱን አስተጋብቷል። ለምሳሌ Qube የሚለው አራት የላቲን ፊደል “ቁቤ” የሚል በሁለት የግዕዝ ፊደል መጠቀም እየተቻለ “Qube” እና ቄሮ” ሁለቱም ቃላቶች በ “ቄ” ፊደል መጠቀም እየተቻለ “ቄ” የሚለው Q እየተጠቀሙ የማይመቸውን የላቲን ድምጽ ያለው አጠቃቀም በመጠቀም እንዴት መሳቂያ እንደሆኑ ሊገባቸው አልቻለም። ኦሮሞ ምሁራን ላቲን ከቋንቋ ልሳናቸው ጋር እንማይገጥም ያውቃሉ፤ ግን ያው በጥላቻ የታወረ ሕሊና ስለሚነዳቸው ግብዝነታቸውን ቢያርሙ ሓፍርት ስለሚመስላቸው ትውልዱ በድንቁርና አንዲሸበብ እያደረጉ ነው። ጥላቻ የሚቆመው “ሰዎች ወደ መቃብር” ሲገቡ ብቻ ነው አብሮ የሚቀበረው።
(2) ሁለተኛው_ ነጋሶ ጊዳዳ አዲስ አባባን በሚመለከት አዲስ አድማስ ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቁን። እንመልከት
ትንታጉ ተመራማሪ ወጣቱ ምሁር አቻምየለህ ታምሩ ስለ ነጋሶ ጊዳዳ እንዲህ ይላል።
“የ ያ ትውልድ>
ግብታዊ
የፖለቲካ
ንቅሳቄ
በርካታ
አቋም
የሌላቸውን ምሁራንና የፖለቲካ ተዋናዮች ፈጥሯል። ከነዚህ አቋምና integrity የሌላቸው የ ያ ትውልድ የፖለቲካ ንቅናቄ ካፈራቸው ሰዎች መካከል ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ቀዳሚው ናቸው። ዶክተር ነጋሶ
ጊዳዳ በተለያየ ጊዜ የሚጣረሱ አቋሞችን የሚሰጡና የሚጋጩ ምስክርነቶችን የሚናገሩ ሰው
ናቸው።” ይላል አቻም። (ሰረዝ የተጨመረ)
ስለ ሰንደቃላማ ጉዳይ ነጋሶ ሲሞካሽ ሰምተናል ሃቁ ግን ከነጋሶ ሁለት ምላስ እናድምጥ፡
አቻም ገርሞት እንዲህ ይላል፡-
ዶክተር
ነጋሶ
በዛሬ
እለት
አዲስ
አበባ
ላይ ለንባብ ከበቃው «ግዮን» ከሚባለው መጽሔት መጽሔት ጋር በሰንደቅ አላማ ዙሪያ ባደረጉት ቃለ ምልልስ «የባሕር ዳሩ ሰልፍ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ይጻረራል» ሲሉ ተናግረዋል።
ሕገ-መንግስቱ ሳይሻሻል ‘እኛ የምንፈልገው የድሮውን ፣ የነገስታቱን ፣ የእነ አፄ ኃይለ ሥላሴን ባንዲራ፣ የእነ ምንሊክን ባንዲራ ነው የምንፈልገው ‘
የሚሉ
ሰዎች
ሀሳባቸውን በዲሞክራሲ መንገድ አቅርበው ሕገ-መንግስቱ የሚሻሻልበትመንገድ አለ”
~ ” በባህርዳር ስታዲየም ላይ የተገኘው ህዝብ መቶ ሚሊዮን የሚሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ቀርቶ የአማራውን ህዝብ አይወክልም” (በጋሶ ጊዳዳ)
‘ በጣም የሚገርመው ነገር ይህ የዶክተር ነጋሶ የሰንደቅ አላማ አስተያየት ራሳቸው ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ባለፈው አመት በጥቅምት ወር ሁለተኛው ቅዳሜ [Saturday, 14 October 2017] አዲስ አድማስ ከሚባለው አገር ቤት የሚታተም ጋዜጣ ጋር «ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፡- በሰንደቅ ዓላማና በህገ መንግስቱ ዙሪያ» በሚል ካሳተመው ቃለ ምልልሳቸው ጋር ፊት ለፊት የሚጋጭ መሆኑ ነው።
‘ዶክተር ነጋሶ በዚህ የአዲስ አድማስ ቃለ ምልልሳቸው፤
«የሰንደቅ ዓላማ ጉዳይ ለሕዝብ ውይይት አልቀረበም» ሲሉ ተናግረዋል።
“ጤና ይስጥልኝ ዶክተር ነጋሶ! ወያኔ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ሶስት ላይ ስለ ሰንደቅ አላማ ያሰፈረው ድንጋጌ ለሕዝብ ውይይት አልቀረበም ካሉን እንዴት ብሎ ነው ይህ ለሕዝብ ውይይት ያልቀረበ የፖለቲካ ድንጋጌ የሕገ መንግሥት አንቀጽ ሆኖ «የባሕር ዳሩ ሰልፍ ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ይጻረራል» ሊሉ የቻሉት? ዶክተር ነጋሶ ስለየትኛው ሕገ መንግሥት መጣስ ነው የሚያወሩት? «ያለ ሕዝብ የተረቀቀ ነው» ብለው ስለመሰከሩለትና ስለነበራቸውም ተሳትፎ «አጥፍቻለሁ፤ አገር በድያለሁ!» ብለው ይቅርታ እንዲደረግላቸው በአደባባይ ሕዝብ ስለጠየቁበት የወያኔ ሕገ መንግሥት ነው? አንድ ራስ አራት ምላስ ሊሆን ሕሊና የሚባል ነገር የለም?” ሲል አቻም ጠይቆአቸዋል። (ሰረዝ የተጨመረ)
ኢትዮጵያን ግዛት በሚመለከት ነጋሶ ጊዳዳ፦
“ከ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት ኢትዮጵያ እስከ ደብረብርሃን ነበረች፤ ከደብረብርሃን በስተደቡብ የነበረው በነገስታቱ ስር አልነበረም።” (ነጋሶ ጊዳዳ)
በማንም የታሪክም ምሁርም ይሁን በማንም የመጻህፍት አንባቢ ሊመሰክረው የሚችለው አክሱማዉያኑ አብርሃ እና አጽብሃ እስከ መቃዲሾ ድረስ እስከ ፑንት ድረስ ሄደው እስከዛሬ ድረስም ከደብረብርሃን በስተደቡብ ባሉ ምድሮች ሁሉ የሰሩዋቸው የዋሻ ቤተ/ክርስትያን ገዳማት ዛሬም የሚታዩ ማስረጃዎች ናቸው። ከዚያም አምደፅዮን በ14ኛው ክፍለ ዘመን የነበረ የኢትዮጵያ ነጉሥና ወሰነ ግዛቱም ሐረር ድረስ እንደነበር የተመዘገበ ነው። ለዚህም በጥሩ ሁኔታ ያስቀመጡት፡ “የአምደ ፅዮኗ ኢትዮጵያ እና የዶር ነጋሶ ጊዳዳ ኢትዮጵያ (GM Melaku
an Veronica Melaku) July 22, 2017” በሚል ርዕስ በጻፉት ላይ ነጋሶን እንዲህ ሲሉ ሞግተዋቸው ነበር፦
“ ዶ/ር ነጋሶ የአማራ ነገስታቱ ኢትዮጵያ ከ19ኛው ክፍለዘመን በፊት ከደብረ ብርሃን ተሻግራ አታውቅም የሚለው ትርክት፤ “አማራ ከደብረ ብርሃን ማዶ አያገባውም” የሚል ይዘት ያለው ነው። በተለይ ይህ የሆነው የአዲስ አበባ የባለቤትነት ካርድ በተመዘዘበት ማግስት መሆኑ ደግሞ አንዳች ርካሽ የፖለቲካ ንግድ እንዲገኝበት ታስቦ የተደረገ እንጅ አንዳችም ታሪክን በታሪክነቱ የማስተማር ዓላማ የለውም። ለመሆኑ ከደብረ ብርሃን በስተደቡብ የተሰሩት አያሌ እድሜ ጠገብ ገዳማት ማን እንደሰራቸው ለዶ/ሩ ጠይቁልኝ እስኪ? “ ሲሉ ተገቢ ጥያቄ አቅርበው ነበር።
ለዚህ ነው ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በታሪክ ማሕደር በመጥፎ ገጽታ መመዝገብ አለባቸው የምለው። ለዚህ ነው ወንጀለኞች እንደ መላእክትና አርበኞች አገር ወዳዶች እየተደረጉ እየተቀረጹ ወንጀላቸው ለታሪክ እና ለሕግ እንዳይቀርብ ብዙ ተከላካይ ብዕርተኛ መበራከቱን የሚያሳዝነኝ። እናንተ ብዕርተኞች ወንጀለኞችን በብዕራችሁ ባታስደነግጡዋቸውም፤ በፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና በመንግሥት ሥርዓት የወንጀል ተሳታፊዎች የተቀጠፉ ሙታኖች በገዳዮቻቸው ሕልም እየመጡ በተኙበት ውድቅት ሌሊት ከፊታቸው እየተደቀኑ እንደሚያስጨንቁዋቸው የሚነግሩን።ማስረጃወም ለቅርብና ልደምድም።
በዚህ ጽሑፌን ላጠቃልል፡
The Mask of Anarchy (by Stephen Ellis) The destruction of Liberia
and Religious Dimension of Africa Civil War (New York University Press) የሚል ወደ 340 ገጽ ያለው ስለ አፍሪካዊቷ ላይቤሪያ ስርኣተ አልባ እና በፖለቲካ ሽፋን የተፈጸመው ዘግናኝ የመተላለቅና የግድያ ወንጀል የሚተነትን ጥልቅ መጽሐፍ በገጽ 266 እንዲህ ይላል፡
The Sychology of Transformation በሚል ንኡስ ምዕራፍ ላይ፤
“Not surprisingly, many former fighters who have
carried out such atrocious actions admit to having troubling dreams. Some
display obsessive behavior……በማለት (ስለ አንዲት ሴት ተዋጊ (ጎሪላ ፋይተር) አንድ ሴት ከታቀፈቺው ህጻን ልጅዋ ስለረሸነቻት የተሰማትን ቁጭት ምክንያት ራስዋን ላጭታ እንዴት እንዳበደች እና አንድ የራሱን አባት የረሸነ ታዳጊ ወጣት ያለ ምንም ምክንያት ያገኛቸውን ጫጩት ዶሮዎችን እያሳደደ እንዴት ይገድል እንደነበር ከዘረዘረ በኋላ) በመቀጠልም እንዲህ ይላል፡-
“In one rehabilitation center a former fighter
with the AFL said in 1992: “I dreamed about all the people I killed. The ones I
saw face to face just before I killed them. I dreamed, I saw them all in a
room, sitting around a table. There are 43 of them. I am there too. But nobody
is talking. Nothing happens, and nobody talks.’ በማለት
ይህ አስገራሚ እና አስጫናቂ ኑዛዜ ከገዳዮች እና ሕዝብን በጨፈጨፉ በወንጀል የተካፈሉ ወንጀለኞች የሚናገሩትን ስንሰማ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት መንግሥታዊ እና የነፃ አውጪ ድርጅት መሪዎች እና የወንጀል ተሳታፊዎች ዛሬም ድርጊታቸው በመቀጠል ላይ ስለሆኑ፤ ወንጀላቸውን የሚጠይቅ እና የሚያስቆማቸው መሪ እና ስርዓት ስለሌለ ልክ እንደ ላይቤሪያ ወንጀለኞች የሚቃዡበት አስፈሪው የቅዠት ስቃያቸው የሚናዘዙበት ጊዜ እንዲመጣ እየጠበቅን ነው። እስከዚያው ድረስ ግን የገዳዮችና እና የሙታኖች ዝምታቸው እንቆቁልሽ በኢትዮጵያ ምድር የሚቀጥል ይመስላል። ገዳዮችም ዝም ፤ተገዳዮችም ዝም ስርዓቱም ዝም “ተገዳዮችና ገዳዮቻቸው አብረው በአዝጋሚ ዝምታ እየታረመዱ ይገኛሉ!”
አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ (Ethio Semay)