Sunday, July 18, 2010

በአቶ አማረ አፈለ ብሻው የተጻፉ ድንቅ መጻሕፍቶች

ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ አዘጋጅ) http://www.ethiopiansemay.blogspot.com/ getachre@aol.com (408) 561 4836

እኔም ሆነ ሌሎቻችሁ ብዙ ጊዜ የምንለው አንድ ነገር አለ፡ “አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ምሁር ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ በአገሩ ልጆች የተጻፉ መጻሕፍቶችን የማንበብ ልምድ የለውም፡ ቢያነ’ብም በአመስት/አስር ዓመት አንድ መጽሐፍ ያነ’ብ ይሆናል። አንዳንዴም የገዛዉን መጽሐፍ አንብቦ የመጨረስ ልምድ የለዉም፤በደፈናዉ “ግብዝ” ነዉ።” የሚል ድምዳሜ ደርሰናል። መጻሕፍ የማንበብ ጉጉት ያደረባቸዉ አንባቢዎችም ቢሆን የመጻሕፍት መሸጫ መደብሮች አከፋፋዮች/አሰራጮች ስለሌሉን የታተሙ መጽሐፍት በበቂ ማግኘት አልቻሉም። ለዚህ ብዙ ምክንያቶች አሉ። የኢትዮጵያ ሱቅ/መደብሮች/ግሮሰሪዎች/ምግብ ቤቶች… እንደ የሙዚቃ ሸክላ/ክሮች( ይግረም ብለዉ የሻዕቢያ ፖስተሮች/ጌጦች/ሰንደቃላማዎች/የሙዚቃ ሸክላዎች/የሻዕቢያ ሰንደቃላማ ያለባቸዉ ልብሶች ሳይቀሩ በጉግት በጅምላ እየገዙ ለደምበኞቻቸዉ እንደሚያሰራጩት) ጉጉትና ቅድሚያ ሲሰጡ- መጽሐፍቶች፤መጽሄቶች እና ጋዜጦች የመሳሰሉትን ግን በንግድ ዓይን ስለሚመለከቷቸዉ ከአገር ጉዳይ የተያያዙት እንኚህ የአገሪቱ እና የራሳቸዉ ህይወትን የሚጠቁሙ ቋሚ ማሕደሮች/ሰነዶች በቁም ነገር ስለማያይዋቸዉ፤ ደራሲያኑ በኪሳራ ያሳተሟቸዉን መጻሕፍቶች፤መጽሄቶች እና ጋዜጦች ለዜጎች በበቂ እንዲዳረሱ ለማድረግ ከፍተኛ ችግር እየተጋረጠባቸዉ እንደሆነ ለብዙ አመታት የተነጋገርንበት ጉዳይ ይመስለኛል (ብዙዎቹ ባለ መጽሄቶችና ጋዜጦች አገልግሎታቸዉን ለምን እንዳቆሙ እሮሮአቸዉን በስፋት አንብባችሁ ወይንም አድምጣችሁ ይሆናል)።በዚህ ጉዳይ ባለ ሱቆች/ምግብ ቤቶች ለዚህ ዕንቅፋት እንደሆኑ የምታዉቁት ይመሰለኛል። ስለሆነም ደራሲዎች፤የታሪክ እና የዜና ዘጋቢዎች ሕዝቡን ለማስተማር እና ፈር ለማስያዝ ያለባቸዉ ችግር አሁንም እንዳለ ነዉ። እናሰራጫለን የሚሉ ባለ ሱቆችም ቢሆኑ ደራሲያኑ እንዲሸጡላቸዉ ወይንም የመጽሄት እና የጋዜጣ ባለቤቶች የላኩላቸዉን መጽሐፍት እና መጽሄቶች ከሸጣሰቸዉ በሗላ ገንዘቡን በወቅቱ አይሉኩላቸዉም አንዳንዴም ውጠዉት ይቀራሉ። ባለፈዉ ወር በእኔ የተጻፉ ሁለት መጻሕፍቶች ማለትም “ይድረስ ለጎጠኛው መምህር” (አማርኛ) እና “ሓይካማ” (ትግረኛ) ለሕትምት በቅተው ወደ ጥቂት አንባቢዎች መዳረሳቸው ይታወሳል። የአማርኛዉ መጽሐፍ ተሎ በማለቁ አንባቢዎች በብዛት እንዲላኩላቸዉ ስለጠየቁኝ በቅርቡ ተጨማሪ ቅጅ ስላስፈለገ ቅጁ እንደተባዛ ይዳረሳል። ወዳጄ ደራሲና የጉግሳ መጽሄት አዘጋጅ አቶ አማረ አፈለ ብሻው ትውውቃችን ብዙ ዐመት ነዉ። ወንድሜ አማረ ሲኖርበት ከነበረዉ ሎስ አንጀለስ ከተማ ለቅቆ መኖርያው ሌላ ቦታ ካደረገ ወዲህ የስልክ ቁጥር አድራሻ ለዉጥ በማድረጉ መገናኘት አልቻልንም ነበርና ስለኬን በመጽፌ ማስታወቂያ አማካንነት አግኝቶ መጽሃፌን እንድልክለት ደዉሎ ሲያነጋግረኝ ደስ ብሎኝ ስንወያይ ሰባት መጻሕፍት እንደጻፈና በቅርቡ “ከጋምቤላ እስከ ሁመራ”የተባለዉ አዲስ መጽሐፍ እንደጻፈ እና ሌሎቹም በስም ዝርዝራቸዉ ሲነግረኝ እኔ ራሴ “ክዉ” ብየ ነበር የቀረሁት። ምነዉ ይህ ሁሉ መጽሐፍ ስትጽፍ እኔ ላይ ሲደርሱ ተደበቁብኝ? ብየ ስጠይቀዉ ከላይ የጠቀስኩትን እኔ የሚሰማኝን የስርጭት ችግር እና እሱም በአንደኛዉ መጽሐፉ መግቢያ ዉስጥ እንደጠቀሰዉ ሁሉ በዝርዝር የመጽሐፍቱ በበቂ ያልተሰራጨበት ምክንያት እና ህብረተሰቡ ገዝቶ ያነብባል ብሎ ቅጂዎች በብዛት ማሳተም ትርፉ ዕዳ እና ኪሳራ እንደሆነ ተነጋግረን፤ መጽሐፍቶቹ በመታተማቸው ደስ ብሎኝ መጽሐፍቶቹ እንዲልክልኝ ጠይቄዉ ልኮልኝ በማንበብ ላይ ነኝ። እናንተም እነኚህ በሰነድ የተደገፉ መጽሐፍቶቹ ገዝታችሁ እንድታነቧቸዉ አደራ እላለሁ። አሁን ወደ ደራሲዉ አማረ “ከጋምቤላ እስከ ሁመራ”መጽሐፉ መግቢያ ውስጥ ደራሲያን ስለ ስርጭት የሚሰማቸዉን ጉዳይ በራሱ አንደበት ያስተላለፈዉን እነሆ። ደራሲዉ አቶ አማረ አፈለ ከጋምቤላ እስከ ሁመራ መጽሐፉ ለመጻፍ ምን እንዳነሳሳዉ ባጭሩ ካብራራ በሗላ እንዲህ ይላል “ የኢትዮጵያ ጉዳይ ከአደር አደር እየባሰ እንጂ እየተሻለ ባለመምጣቱ የነበራትን ገናና ታሪክ ሳነብ አለቅሳለሁ። በተለይ ነባሩን ታሪኳን ስመለከት ሰላም ይነሳኛል።…አንባቢያን ለማስገንዘብ የምፈልገዉ ነገር ቢኖር እኔ የምጽፈዉ አንዱን ቡድን ለማስደሰት ሌላዉን ቡድን ለማስከፋት አይደለም። መጽሐፉን ብትገዙት ባትገዙት እኔ ግድ የለኝም። እኔ ደስ የሚለኝ ነገር መጽሐፉ ከማተሚያ ቤት ወጥቶ ከተወሰኑ አንባቢዎች እጅ ከገባ በሗላ ትልቅ ደስታ ይሰማኛል።…የኔ ትርፍ የተሰማኝን መግለጽ የሀገሬን ጉዳይ መግለጽ ነዉ።” ሲል “ከጋምቤላ እስከ ሁመራ” የተባለዉ በሰነድ አስደግፎ በጻፈዉ እጅግ ወቅታዊ ታሪካዊ እና ጠቃሚ መጽሐፍ እንድናነበዉ ሰጥቶናል። ይህ እና ሌሎች ስድስቱ መጻሕፍቶቹን ለማግኘት በሚከተለዉ አድራሻ ብትጠይቁ ማግኘት ትችላላችሁ።ቢሆንም ኢትዮጵያዊያን ለሙዚቃ ድግስ እስከ $400ዶላር (ለጸጉር ማስርያ፤ አዲስ ልብስ፤ሽቱ/ሽቶ፤ጫማ፤ለመግቢያ ቲኬት…) ለአንድ ምሽት ፈንጠዚያ ያን ያህል ከፍለዉ መዝናናት እንጂ በስሟ የሚጠሩባት ዜግነታቸዉ “ኢትዮጵያዊያን”ነን የሚሉባት አገራቸዉ ምን እየተባለላት፤ምንስ እየደረሰባት እንደሆነ ጉዳያቸዉ ያልሆነ ዜጎች (በተለይም ምሁር የሚባለዉ ክፍል) የ$15 እና የ$20 ዶላር መጽሐፍ ገዝተዉ ለማንበብ ልምዱም ፍላጎቱም እንደሌላቸዉ ሁሌም የሚሰማኝን የኔን እሮሮ ወዳጄ ደራሲዉ አማረ አፈለ ከላይ የገለጸዉን ስሜቱን እንደገና ደራሲያንን ሲያጽናና እንዲህ ይላል“አባ ቀዉስጦስ የሰሜን ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ‘ይግባኝ ለክርስቶስ’ በተባለዉ መጽሐፋቸዉ ገጽ 58 “ምን አልባት ላይሰሙን ምን አደከመን እንል ይሆናል። ነገር ኢግን እነሱ ሰሙም አልሰሙም እኛ መናገር አለብን። ፀሐይ የሚሞቀኝ የለም ብላ ከመዉጣት፤ወንዝም የሚጠጣኝ የለም ብሎ ከመፍሰስ እንደማያቋርጥ ሁሉ መምሕራንም የሚሰማን የለም ብለን ዝም ማለት የለብንም” ሲሉ ጽፈዋል። ሲል ደራሲ አቶ አማረ አፈለ ብሻው ደራሲያን/አስተማሪዎች/የሕዝብ ልሳን አስተጋቢዎች….አንባቢ የለም ብለዉ ከመጻፍ/ከማስተማር/ሃሳባቸዉን ከማሰራጨት/የዘገቡትን ለትዉልድ ከማስተላለፍ እንዳይቆጠቡ አደራዉን አስተላልፏል። እመኑኝ ኢትዮጵያዊያን (ያለንበት ትዉልድ)መጽሐፍ ከማንበብ ይልቅ በሙዚቃ ድግስ እና በየሬስቶራንቱ እየዞሩ መዝናናት የሚደርሳቸዉ በዚህ ዓለም ያለ አይመስለኝም። እንዲሁ በደፈናዉ “ያላለለት ትዉልድ”ብየ ልሰናበታችሁ። የታላቁ ደራሲ አማረ አፈለ ብሻው መጽሐፍቶች ገዝቶ ለማንበብ ፍላጎት ያላችሁ ሁሉ በሚከተለዉ አድራሻ ማግኘት ትችላላችሁ።የማናዉቀዉ፤የረሳነውና የተነጠቅነዉ ማንነታችን ማፍረስ በማይቻል መረጃ አስደግፎ ያስታውሰናል። የመጻሕፍቱ ስም ዘርዝርም እነሆ ከዚህ በታች ያሉት ናቸው።አመሰግናለሁ። ጌታቸዉ ረዳ Editor www.ethiopiansemay.blogspot.com getachre@aol.com የመጻሕፍቶቹ ስም ዝርዝር 1-ከጋምቤላ እስከ ሁመራ! 2-በአባ ጳዉሎስ በጳጳሳት ምክንያት በቤተክርስትያን ላይ የተነሣዉ እሳት! 3-አሰብ የኢትዮጵያ አካል ነች 4-የሁለት ሺህ ዓመታት ውጣ ውረድ በኢትዮጵያ 5-ኢትዮጵያ! የሰው ዘር የተገኘባት የእምነትና የሥልጣኔ ምንጭ ናት! 6-ገድሉስ ገደል ነው! Amare Afele Bishaw P.O.Box 492 Seatle WA 98111 U.S.A

Newer Posts Older Posts Home