Friday, July 1, 2011

ለወጣት አስራት አብርሃም የተሰጠ መልስ

                     

ለወጣት አስራት አብርሃም የተሰጠ መልስ
ጌታቸው ረዳ

አንባቢዎች ሆይ ወደ ቁም ነገሩ ከመግባታችሁ በፊት ይህን ላስነብባችሁ።
         
         ለኢትዮ ሚዲያ አዘጋጅ፤
ከጌታቸው ረዳ ኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ፤
ደብዳቤው ለሕዝብ እንዲለጠፍ እጠየቃለሁ፡
ደብዳቤው አጪርና ግልጽ ጥያቄ ነው፡
አዘጋጁ ደብዳቤየን ካላገዱት  የማሳወቅ ግዴታቸው እየተወጡ ነው ማለት ነው።
የደብዳቤው ይዘት:- “ለአቶ አስራት አብርሃም  የዓረና ትግራይ የሕዝብ ግንኙነት ሐሊፊ ከፍትሕ ጋዜጣ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ በሚመለከት በሰጠው መልስ ላይ” የማልስማማቸው ነገሮችን ለመግለጽ ነው።

ድብዳቤው ሲላክ ከላይ የተመለከታችሁት ነበር የሚለው። የተጠቀሰው ድረገጽ ሲቋቋም ዕርዳታ ስለጠየቀን እኔና ጓዶቼ አስተባብረን የተቻለነን የገንዘብ መዋጮ ያደረግኩ ብሆንም፤ የድረገጹ ባለቤት አገልግሎቱ ሁሌም የሚታወቅበት ቡድናዊ አገልግሎቱ ነውና አላተመውም።

             ሌላው ልትገነዘቡልኝ የምፈልገው ጉዳይ፦ትችቴን ለወጣት መምህር አስራት አብርሃም ስሰነዝር፤ከልቤ እያዘንኩ ነው። ምክንያቱም አስራት ካሁን በፊት በሌላ ጣቢያ በተከታተልኩት ቃለ መጠይቁ ከሆነ በጣም ደፋር፤ተስፋ ያለው፤ግሩም ኢትዮጵያዊ የትግራይ ሰው ነው። ጠባብነት የለውም፤ስለ ኢትዮጵያ ይቆረቆራል፤አገራችን በወያኔ ማፍያዎች እጅ መውደቋን በጣም አሳስቦታል። እራሱን ከዓረና ፓርቲ አግልሎ ወጣቶቹን ይዞ ሌላ ድርጅት ቢመሰርት በጣም ተስፋ ያለው ወጣት ነው የሚል እምነት አለኝ።
ዛሬ መምህር አስራት አብርሃምን ለመተቸት ካበቃኝ አንዱ ነገር ብዙ በጣም ለብዙ ደምና መፈናቀል ግድያና ወንጀል ግርፋትና በሥልጣን መባለግ የትግራይም የተቀረው ኢትዮጵያዊም ኗሪ በነዚህ ሰዎች ለደረሰበት ግፍ ለወደፊቱ በወንጀል ከሚከሳቸው ውስጥ ተጠያቂዎች እነ ገብሩ እነ ዓውዓሎምና መሰሎቻቸው ስላሉበት ወጣቱ አማራጭ ብሎ የያዘው ከነዚህ ሰዎች ጋር ሆኖ ፍትሕ አመጣለሁ ብሎ ራሱን ማጎዳኘቱ ለትችቴ መነሻ አድርጎታል።ከነዚህ ሰዎች (አንጃዎቹ) ላደረሱት በደል ይፋ ዝርዝር ይቅርታ ሳይጠይቁ አብሮ መተሻሸት ለግፉአን (ቪክቲም) ክብር መንሳት ነው። እኛ በማናወቃቸው እነ ገብሩ እነ አውዓሎም በሚያወቁዋቸው ብዙ ነብስ በከተቱት ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ የሚጮህ ነብስ አለ! ይቅርታ ቢጠይቁ እኔ የመጀመርያ ይቅር ባይ እንደምሆን አትጠራጠሩ።ግን አላደረጉትም።
ለምን? ያደረጉት ሰብአዊ ግፍና የስልጣን መባለግ አልነበረም? እሱን ለተመራማሪዎች/ሪሰርቸሮች ልተውና ወደ ዋናው ርዕስ ልሻገር፡፤
ኢትዮ-ሚዲያ ውስጥ ከፍትህ ጋዜጣ አደረገው የተባለው ቃለ ምልልስ ለእኔ የተስማማኝን የወጣት አስራት አብርሃም አንዱን ሐረግ ልጥቀስ “ከእያንዳንዱ የህወሓት አመራር ጀርባ ወንጀል አለ” አስራት አብርሃም ከሰጠው ቃለ መጠይቅ የተገኘ።በግሩም አገላለጽ አስቀምጦታል።
 አሁን ወደ ጥያቄዬ ለመግባት ከሰጠው ቃለ መጠይቅ ልጀምር።
ጥያቄ፤-   ፍትህ፡- በአንዳንድ ሰዎች አስተሳሰብ የትግራይ ህዝብ እና ህወሀት የማይነጣጠሉ ተደርጎ የሚቀርቡበት አጋጣሚ አለ፡፡ አንተስ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ምን ያህል ተጠቅሟል ትላለህ ?
አቶ አስራት እንግዲህ የትግራይ ህዝብ ወደ 5 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ በህወሀት የሚጠቀመው ስንቱ ይሆናል? የሚለው ነው መታሰብ ያለበት፡፡ የተቀረው የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ያተረፈው ጦርነት ነው፡፡ በደርግ ጊዜም፣ እንደገና ከኤርትራ ጋር በተደረገው ጦርነት፡፡ ሌላው ቀርቶ እዚህ መሀል አገር ያለውን የፈለገውን ፓርቲ የመደገፍ መብት እንኳን አላገኘም፡፡ እናም በአንዳንድ አክራሪዎች እና በህወሀት ሳይቀር የተለየ ጥቅም እንዳገኘ ተደርጎ የሚነገረው ስህተት ነው::
 ፍትህ፡- በግልፅ መልስልኝ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት አልተጠቀመም?
አቶ አስራት፡ አዎ፡፡ ምንም አላገኘም የተወሰኑ ፋብሪካዎች እዚያ አሉ ተብሎ ይወራል፡፡ ቁም ነገሩ ግንእነዚህ ፋብሪካዎች የማን ናቸው? “ የሚለው ነው፡፡ ልንገርህ እነዚህ ፋብሪካዎች የህወሓት ናቸው፡፡ ህወሓት እነዚህን ፋብሪካዎች ኦዲት አስደርጎ አያውቁም፡፡ በእነዚህ ፋብሪካዎች ገቢ በትግራይ ውስጥ የተሰራ ትምህርት ቤትም ሆነ ጤና ጣብያ የለም፡፡ ልክ የውጭ አገር ሰው እዚህ መጥፎ ፋብሪካ ቢተከል ፋብሪካ የህዝብ ነው እንደማይባለው ሁሉ እነዚህ ፋብሪካዎች የሚያገለግሉት ለህወሀት እንጂ ለትግራይ ህዝብ አይደለም፡፡ እንዲያውም በአንፃሩ የትግራይ ህዝብ በፊት ወደ ኤርትራ ወደ ሱዳንም እየተመላለሰ ሰርቶ ይበላ ነበር፡፡ አሁን የለም፡፡ ታጥሮ ነው ያለው፡፡ የትግራይ ህዝብ በፊት በቀላሉ በምፅዋ በኩል የውጭ ዕቃ ማስመጣት ይችል ነበር፡፡ አሁን በበርበራ፣ በጅቡቱ፣ በአዲስ አበባ፣ በጎንደር ዞሮ ነው የሚደርሰው፡፡ እናም በአጭሩ የትግራይ ህዝብ በዚህ ስርዓት መጠቀሚያ ነው የሆነው እንጂ ተጠቃሚ አልሆነም፡፡
አንዱ ችግር ምን መሰለክ? የትግራይ ህዝብ ተጠቀመ የሚሉ የተወሰኑ ሰዎች ምንም አይነት መረጃ የሌላቸው ወይም ሄደው ያላዩ ናቸው፡፡ በሆነ አጋጣሚ ትግራይ የሄዱ ሰዎች ግን ተገርመው ነው የሚመለሱት፡፡ አንዱ ችግራችን እኛ ኢትዮጵያውያኖች ተዛዙረን አገራችንን አለማየታችን ነው፡፡ ነገር ግን በአመት አንድ ክልል የማየት እቅድ ቢኖረን 12 ዓመት ሁሉንም ክልሎች እናይ ነበር፡፡ እንደ ባህል ግን የተወለድንበት አካባቢ እንሄዳለን እንጂ ሌላው አካባቢ ሄደንህብረተሰቡ እንዴት ነው የሚኖረው? የሚለው አናይም፡፡ እናም ይሄ የመረጃ እጥረት ይፈጠራል፡፡ አዲስ አበባ ወይም ውጭ አገር ከህወሀት ተጠግተው የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ብቻ በማየት የትግራይ ህዝብ እንዲህ ነው የሚኖረው ማለት አንችልም፡፡
የዓረናው የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ሓላፊ ወጣት አስራት ትግራይ በህወሓት አድልዎ ተጠቅሟል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ሲመልስ ነው ከላይ ያነበብነው። አንድ ማወቅ ያለብን ሰለ ጦርነቱ ሲነሳ ትግራይ ብቻ ሳይሆን የተጐዳው መላው ኢትዮጵያ ከጫፍ እስከ ጫፍ ጭምር ስለሆነ በመቶ ሺዎቹ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ልጆችም በየትግራይ ተራራ እና በየሰሃል ተራራ በምፅዋ ባሕር ቀርተው ቤተሰባቸው ተበትነው የዳኑትም ለልመና ተዳርገው የአካልና የሕይወት እንዲሁም ለጦርነቱ ሲባል በሁለቱም ዓይነት ጦርነቶች የንብረት ድጋፍና መስዋእት ከፍለዋል። ያ ማወዳደርያ እና መከራከሪያ ሊሆን አይችልም፤እሳቱ የሁሉንም ቤት አቃጥሏልና።  
ወያኔዎች ለትግራይ ሕዝብ አዳልተው ንግድ፤ልማት፤የስራ ቅጥር አቀጣጠር፤ፍትሕ ለትግራይ ዜጎች ከሌሎች ይልቅ የተለየ አትኩሮት አድርገዋል ወይንም አላደረጉም የሚለው ክርክሩ ለአመታት በሠፊው የተቸንበት ስለሆነ አሁን አዳዲስ ወጣቶች በመጡ ቁጥር እየተመለስን ማብራራት ሊሆንብን ነው።እንዘግብ ብንልም መረጃዎቹ በጣም ሰፊ ናቸውና እዚህ ማቅረብ ላይመቹ ይችላሉ።
ይህን በተመለከተ መምህር አስራት የትግራይ ሕዝብ በጎሳ መርህ ለሚሰሩ በወያኔዎች በኩል ከሌላው ይልቅ በተወሰነ ደረጃ ትኩረት ተደርጎለታል፡ ብለን ለተከራከርን ወገኖች “አክራሪዎች” ብሎ ከሚጠራን ከእኔ እና መሰል ወንድሞች ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ጋዜጦች በኩል መረጃዎቻችን የታተመ ነውና፡ ላሁኑ ግን የምወዳት ታናሽዋ እህቴ “ብኹዱኑ” (ተከድኖ ይብሰል) የምትለው አባባልዋ ልጠቀም እና “ብኹዱኑ” ብየ ልለፈው ካስፈለገም መረጃዎቹን መቆፈርና ማወዳደር ነው። የትግራይ ሕዝብ በተለየ ትኩረት ተደርጎለታል ስንል ግን የትግራይ ሕዝብ ተጠያቂ ነው ማለት አይደለም። በዚህ ደግመን ደጋግመን ተናግረናል። ምክንያቱም ተጠያቂዎቹ/ጐሰኞቹ መሪዎቹ ናቸውና፤ላለመረታት ስትሉ የትግራይ ሕዝብ ተጠያቂ ነው እያለ ነው እንዳትሉ ብየ ነው።  
ባጭሩ የመምህር አስራት አብርሃም እንግዲህ የትግራይ ሕዝብ ወደ 5 ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ በህወሓት የሚጠቀመው ስንቱ ይሆናል? የሚለው ነው መታሰብ ያለበት ለሚለው የወጣቱ ጥያቄ ለመመለስ ያክል፡ ትግራይ ውስጥ የተተከሉት ፋብሪካዎች ለምሳሌ አልመዳ፤መሰቦ ስሚንቴ፤ሱር የሕንጻ ምርቶች አከፋፋይ፤ ጨርቃ ጨርቅ፤አዲስ ኢንጂኔሪንግ፤ ስታር የመድሃኒት ውጤቶች ፋብሪካ፤ኢንሹራንስ፤ትራንስ ኢትዮጵያ፤መስከረም ኢንቨስትመንት፤ ሰገል ኮንስተራክሽን፤ ሜጋ ኔት ኮርፖሬሽን፤ ኤክስፐርየንስ አትዮ ትራቭል፤ደደቢት የቁጠባና የብድር፤ ከሚካል አክስዮን፤ አዲስ ኮንሳልታንሲ፤ ህይወት ወዘተ ወዘተ…... የሚባሉ ተቋማት እንቁጠር ቢባል ቦታ ይፈጃል። በተጨማሪ ሦስት ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች፤ ሆስፒታሎች፤ማሰልጠኛ ተቋማት በርካታ በኮምፕዩተር የተደገፉ ትምህርት ቤቶችና ክሊኒኮች… የመሳሰሉ ማሕበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከሌሎቹ በብዛትም በጥራትም ትግራይ ውስጥ ተተክለዋል። እነዚህ ተጠቃሚው ሕዝቡ እንጂ “ለመለስ ዜናዊ እና ለአዜብ ለአባዲ ዘሞና ለስብሓት ነጋ፤ለጐበዛይ ወ/አረጋይ፤ለአርከበ ዑቑባይ፤ለጸጋይ በርሄ ቤተሰብ እና ተከታዮች ብቻ የሚውሉ መገልገያዎች የሚል ማስታወቂያ አልተለጠፈባቸውም። ተቋማቶች በሙሉ ለትግራይ ሕዝብ ከነልጆቻቸው ጭምር ነው የሚያገለግለው።
አስራት አብርሃም እራሱ 9ነኛ ክፍል የተማረበት ተምቤን ሁለተኛ ኛደረጃ ትምህርት ቤት ህወሓት የቋቋመው ትምህርት ቤት ነው። ለመለስ ቡድን ብቻ ፤ለህወሓት ተከታዮች እና ልጆቻቸው ልጅ ልጆቻቸው ብቻ አልተገነባም። የተንጣለሉ አስፋልቶች እና የሚያማምሩ ህንጻዎች ተሽከርካሪና እግረኛ የሚጓዝበት ለትግራይ ክልል መንግሥት ፓርላማ አባላትና ልጆቻቸው፤ ለብርሃነ ገ/ክርስቶስ፤ ለዓባይ ወልዱ መመላለሻ ጎዳናዎችና ህንጻዎች የሚል የለበትም። ባጃጅ ብሎ የሚጠራቸው “ኩሩሩ’’ ብየ የምጠራቸው/ደንክየ ሸራ የለበሱ የሞተር ሳይክል ታክሲዎች”፤መኪናውም አምቡላንሱም እግረኛውም የሚጓዘው እና የሚያመላልሰው የመለስ ዜናዊ ባለቤትና የትግራይ ፓርላማ ምክርቤት አባሎችን ብቻ አይደለም፤ በጠቅላላ ሕዘቡ ነው። እነዚህ ፋብሪካዎችና ተቋማት ኗሪዎችና በቀጣይነት አድገው ለትግራይ መገልገያ የሚቀሩ እንጂ ወያኔዎች ስልጣን ሲለቁ እንደ ዱንኳን አፍርሰዋቸው የሚሄዱ ነገሮች አይደሉም።እዛው ቋሚ ናቸው።ተጠቃሚ የሚያደርገውም ዓይነተኛ ነገርም ለትውልድ የሚተላለፉ ቋሚ መሆናቸውን ነው። 
ሌላው ልጥቀስ:-
  አንዱ ችግራችን እኛ ኢትዮጵያውያኖች ተዟዙረን አገራችንን አለማየታችን ነው፡፡ ነገር ግን በአመት አንድ ክልል የማየት እቅድ ቢኖረን 12 ዓመት ሁሉንም ክልሎች እናይ ነበር፡፡ እንደ ባህል ግን የተወለድንበት አካባቢ እንሄዳለን እንጂ ሌላው አካባቢ ሄደንህብረተሰቡ እንዴት ነው የሚኖረው? የሚለው አናይም፡፡ እናም ይሄ የመረጃ እጥረት ይፈጠራል፡፡ አዲስ አበባ ወይም ውጭ አገር ከህወሀት ተጠግተው የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ብቻ በማየት የትግራይ ህዝብ እንዲህ ነው የሚኖረው ማለት አንችልም፡፡” 
ጥሩ አባባል ነው። ግን ተዟዙረው የተመለሱ ሰዎች ከሚሰጡት መረጃ እና ጋዜጠኞች ከሚሰጡት መረጃ ተመርኩዘን የምንመለከተው ዘገባ ጋምቤላ እና ወሎ ሌሎችም ሲመዛዘኑ (አሁን እያወራሁ ያለሁት መለስ ዜናዊ በመጀመርያው ምርጫ አዲስ አበባ ውስጥ እንኳ ለምሳሌ በተቃዋሚዎች ደምጽ ብልጫ ተዘርሮ አፍንጫው ሲደማ “በድንጋጤ” ተሃድሶ ብሎ ወደ ሌሎቹ ወደ ነፈጋቸው ክፍሎች የልማት ትኩረት ለማድረግ ከመጀመሩ በ አይደለም እየተናገርኩ ያለሁት) በእነ ገብሩ አስራት ጊዜ የታተመው ወያኔዎች ያሳተሙት “ግሪን ቡክ” ተብሎ በሚያማምሩ የልማት ዘርፎች ባሸበረቀ የፎቶግራፍ ቀለም ተደግፎ የታተመው የልማት ዘገባ መጽሐፍ ሲቀርብ የነበረው ዘገባ በጣም አስደንጋጭና አሳሳቢ የነበረውን የብዙ ዜጎች ቀልብ በብስጭት ያጠመደ አድልዎ ቁልጭ ብሎ የሚያሳይ ዘገባ ነው አሁን እያስታወስኩ ያለሁት።አንተ ተማሪ በነበርክበት ጊዜ ማለት ነው።
ለምሳሌ በወቅቱ ዜጎች ሲጠይቁትና ሲጽፉት የነበሯቸውን እሮሮዎች ብንመለከት የትግራይ ልማት በግሪን ቡክ ተዘግቦ በፎቶ ተደግፎ ሲያሸበርቅ የሌሎቹ ግሪን ቡክ ዘገባ የት አለ? ለምን ወደ ላ ቀሩ? ተመጣጣኝ ዕድገት አልታየም! አብረን እያደግን አይደለም! የተቀሩት የሻይ ቤት ንግድ ሲያጧጡፉ የትግራይ ከልል የጭነት ተሽከርካሪ መኪና ትልቅ ተጎታች/ ቦቴ እየገጣጠመ ለገበያ እና ለባድሜ ጦርነት ስንቅ ማመላለሻ በማድረግ አዲስ ክስተት እንዴት በቅጽበት ተወነጨፈ ተብለው ሲጠየቁ፤ “ሌሎቹ እንደ ትግራይ ሕዝብ ታተሪዎች ስላልሆኑ፤ እንደ ትግራይ ተወላጆች የተማረ የሰው ሃይል ባካባቢያቸው ስለሌላቸው…” ነበር ያሉት። ይሄ ደግሞ ዋሽቼ የምለው አይደለም። የመምህር አስራት አብርሃም የዛሬዎቹ የዓረና የትግል ጓዶቹ የሚያወቁት ታሪክ በግልጽ የተዘገበ ህዋሕቶች ሲመልሱት የነበረ መልስ ነው። እውነት ወያኔዎች 2ቱ የተጠቀሱት ነጠቦች አንስተው እንደመለሱት ነው ወይስ አድልዎ ስለተደረገ? ለነገሩ ተዟዙሮ መመለክት ጠቃሚ ቢሆንም፤ የዓለም ሕዝቦች ታሪክ ለማወቅ ኑሮ ባሕል ህይወት ጦርነት አመልና ዕድገት ለማወቅ የግድ በነዛው አገሮች መሬት መኖር ያስፈልጋል? ዞሮ መመለክት አለበት ማለት የግድ አይልም። ስለ ዮሐንስ ጀግንንት አገር ወዳድነት  ስለ ምኒሊክ እያነሳ የሚተነትነው የትግራይ ምሁር እና “እኔ እና አስራት አብርሃም ጭምር” በዮሐንስ እና በምኒሊክ ጊዜ ስለኖርን አይደለም። ዶግአሊንና መተማን አናወቀውም። ስለገድሉ እና ስለተደረጉ መጥፎ አድለዎ እና ድርጊቶች ወይንም ፍትሃዊ ውሳኔዎች ልማቶች ድረቆች፤ረሃቦች በወቅቱ ዘጋቢዎች፤ተመራማሪዎች (ሪሰርቸሮች) ተዘግበዋልና ዛሬ ለክርክራችን እየተጠቀምንባቸው ናቸው። ስለሆነም አሜሪካ ስለኖርን እገሌ መቀሌ ደርሶ ስለመጣ ባሌ ስላልሄደ ነው ዕድገቱን ማወቅ ያልቻለው ማለት አንችልም። እንደ ዓይን እና ልሳናችን ሆነው የሚያገለግሉን ነፃ ዘጋቢ ጋዜጠኞች በወቅቱ እንድናነጻጽራቸው ዘግበውልናል። እርግጥ አሁን ይኼ ነው ለማለት ያስቸግረኛል፤ ምክንያቱም እንደ ዱሮው ነፃ ዘጋቢ የለም። አውራ አውራ ጸሐፍት የተባሉት እንዲሰደዱ አድሮጓቸዋል። አሁን ያሉት ትንሽ ልፈራገጥ ቢሉም “እዚህ ግቡ የማይባሉ ጯጩቶች” ብቻ ናቸው።ዘገባቸው ጯጭት ጭራ የምታገኘው ነው።የተመናመኑ ናቸው። መሕበሩ የተዳከመ ነው። መሪ የላቸውም።
እንደገና ልጥቀስ
“አዲስ አበባ ወይም ውጭ አገር ከህወሀት ተጠግተው የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ብቻ በማየት የትግራይዝብ እንዲህ ነው የሚኖረው ማለት አንችልም፡፡” ስትል ወንድሜ መምህር አስራት መልሰሃል።
እንዴ?! ባንተም አንደበት ቆየት ብያ ከወደ እንደምገልጸው የገለጽከው በወቅቱ በስፋት አድልዎ ሲደረግ ልጅ እግር በመኖርህ እንጂ መረጃዎች አየተዘገቡ በንጽጽር የቀረቡ ናቸው። በምጽሐፍም በጋዜጣም በድምጽ የተቀረጹ መረጃዎች ናቸው። በጣም የሚገርመው ደግሞ “እነዚህ ፋብሪካዎች የሚያገለግሉት ለህወሀት እንጂ ለትግራይ ህዝብ አይደለም፡፡” ብለሃል። አስገራሚ ነገር ነው! ምን ማለት ነው?  ህወሓት እንጂ የትግራይ ሕዝብ ባለቤትነት የለውም የሚባለው አባባል በጣም ሁሌም ይገርመኛል። ወያኔዎች ማፊያዎች መሆናቸውን በምሳሌ አስቀምጠኸዋል።ትክክል ነው። ማፍያዎች ንብረት ለሕዝብ አያካፍሉም። የሚከተሉት ነፃ ገበያ ነው። ሕጋዊ ዝርፍያ ነው። ንብረቱ ሁሉ ለሕዝቡ ከሰጡትም ወደ “ሶሺያሊዝም/ኮሚኒዝም” ወያኔ በማኒፌስቶ ትግራይ “ዴሳዊት ትግራይ/ስርዓት” (ኮሚኒስታዊት ትግራይ) ሲለው ወደ ነበረው ስርዓት ተመሠረተ ማለት ነው። ይኼ ካደረገ ደግሞ ሌላ  ጥያቄ ሊያስከትል ነው። ምክንያቱም በነፃ ገበያ እይታ ግለሰቦችና ቡድኖች/አክስዩን/ኮርፔረሺን ንብረትና ሃብት ያከማቻሉ በዋናነት ይይዛሉ እንጂ  ሕዝብ ፋብሪካዎችና ሆስፒታሎች ማመላለሻ አውታሮች ከያዘ ስርዓቱ ከነፃ ገበያ ይወጣል ማለት ነው። የኼ ለሊቃውንት ልተው። ነገር ግን አንደ እነ ገብሩ አባባል መሰረት የትግራይ ሕዝብ ንብረት ናቸው፤መሆንም አለባቸው ከተባለም፤ እንዲህ ያክል ካፒታል/ገንዘብና ሃብት የትግራይ ሕዝብ ከየት አመጣው የሚል ጥያቄ ሊያስከትል ነው። ከጦርነቱ ጊዜ ጀምሮ ብዙ የተዘረፉ ባንኮች ንብረቶች እንደነበሩ አብሮ መዘንጋት የሌለበት ቁም ነገር ሊያስከትል ነው (መንግሥት ከሆኑ በላ ያደረጉት ጉድ ሳይጨምር ማለቴ ነው)። በወቅቱ ከነሱ ያገኙት ዘገባ ከቪዲዩ የተቀዳው ወደ አማርኛ የመለስኩት የፋብሪካዎቹ አነሳስ ወያኔዎች ከጫካ አገር ሲገቡ ከወዳደቁ ቆርቆሮ “ፈርኔሎ” መሳይ ነገሮች በመገጣጠም እና ከምሰማር ምናምንቴ በመልቀም በመገጣጠም  እዚህ ግባ በማይባል ካፒታል ነበር የተነሳነው ብለው ከፋብሪካዎቹ ስራስኪያጅ አንደበት የተነገረው ቃለ መጠይቅ በወቅቱ ሃዋርያ ጋዜጣ ላይ (ካናዳ) አቅርቤው ነበር።
እንግዲህ ሃብቱ ከመቸው አደገ? በምን ሂሳብና ፍጥነት? በምን ታምር? ከነማን ጋር ገበያ ውስጥ ተወዳድሮ እንዲህ ዓይነቶቹ ብዛት ያላቸው ከባድ ከባድ ተቋማት ሊገነቡ በቁ? የሚለው ያስከትላል። የትግራይ ተወላጆች ምንም ያክል የብር የገንዘብ መዋጮ ለልማት አዋጥተዋል ቢባልም ምንም ከቶ ያን ያክል የሚያከማች ግዙፍ ካፒታልና ንብርት አዋጥተወ ገንብተዋል ማለት አይቻላቸውም። ሌላ ቀርቶ በ “ተማላጠጥ” (የጫካ ጐማ ጫማ) ተጫምቶ ከጫካ የገባው ሟቹ የኪነት ሰው ወያኔው ትንሹ አላሙዲ በመባል የታወቀው እያሱ በርሄና መሰሎቹ ከመቼው ሚሊዮነር ሊሆኑ ቻሉ? ተቋማቱም ምንጮቻቸው ከየትኛው የኩሬ ውሃ እንደተገኘ እንዲነግሩን እንፈልጋለን እንጂ ከወዳደቁ ቆርቆሮ “ፈርኔሎዎች” ተቀጥቅጦ ቦቴ መኪና ማውጣት ቻልን የሚባለው ዘገባ እግዚሃር እንዳያየው “ተክድኖ መብሰል አለበት”።
ተቋማቱ የሚያገለግሉ ለህ.ወ.ሓ.ት ነው ስትል አንተ የምታስተምርበት ትምህርት ቤት እና በዋና አስተዳዳሪነት ስትመራው የነበረው ተቋም የሚመሩት ተማሪዎች የትግራይ ሕዘብ ልጆች አይደሉምን? በነሱ (በህወሓቶቹ) አስታባበሪነትና ኣብዛኛዎቹ በነሱ ሂሳብ /ቡክ/ ቁጥጥር ካፒታል አይደለም ወይ የታነጸው? የሚያገለግሉት ለህወሓት ነው ስትል ተማሪዎቹም ህወሃት ናቸው? ስሚንቶ ጨርቃጨርቅ ጎማ ጫማ፤ወዘተ ወዘተ ምርቶች የሚገለገሉትና የሚቀርበላቸው ህወሃት ናቸው? እናቶቻችን እና እህቶቻችን ከገጠር እየተመላለሱ ከተማ የሚገኙት ነገሮች የሚገዙት ህ.ወ.ሓ.ት ናቸው? ለነገሩ አስመራ ሲመረቱ የነበሩ ምርቶች በሙሉ ትግራይ ውስጥ በመመረታቸው አይደለም አንዴ ሻዕቢያ የመቀሌን ህጻናት በክላስተር ያጋያቸው? “ኢሳያስ አፈወርቂ “አደገኛ ቦምቦች” በሕልሙ ያቃዡት እኮ የልማቱ ሩጫ ከተመለከተ በኋላ ነው። ካስመራ ጎማ ጫማ፤ሹፈን፤መንከሽከሽ፤ጣቓ…ማስመጣት እንደሚቆም ታውቆት ስለነበር ነው። ወዲ አፎም በህልሙ ቦምብ ሆነውበት የተመለከታቸው ፈብሪካዎች እኮ የተተከሉት ጋምቤላ ወይንም ደሴ /ጐንደር/ጋሞጐፋ አልነበረም፡ትግራይ ውስጥ ነበር የተተከሉት። አስገራሚው ደግሞ፡ ህወሓት እንጂ የትግራይ ሕዝብ ባለቤትነት የለውም የሚባለው አባባል በጣም ሁሌም ይገርመኛል። ወያኔዎች ማፊያዎች መሆናቸውን በምሳሌ አስቀምጠኸዋል።ትከክል ነው። ማፍያዎች ለሕዘብ ንብረት አያካፍሉም። የሚከተሉት ነፃ ገበያ ነው። ሕጋዊ ዝርፍያ ነው። ንብረቱ ሁሉ ለሕዝቡ ከሰጡትም ወደ “ሶሺያሊዝም/ኮሚኒዝም” ወያኔ በማኒፌስቶ ትግራይ “ዴሳዊት ትግራይ/ስርዓት” (ኮሚኒስታዊት ትግራይ) መሠረተ ማለት ነው። ይኼ ካደረገ ደግሞ ሌላ ጥያቄ ሊያስከትል ነው።ምክንያቱም በነፃ ገበያ እይታ ግለሰቦችና ቡድኖች/አክስዩን/ኮርፔረሺን ንብረትና ሃብት ያከማቻሉ በዋናነት ይይዛሉ እንጂ  ሕዝብ ፋብሪካዎችና ሆስፒታሎች ማመላለሻ አውታሮች ከያዘ ስርዓቱ ከነፃ ገበያ ይወጣል ማለት ነው።
ይኼኛው ለሊቃውንት ልተው። ነገር ግን እንዲህ ያክል ካፒታል/ገንዘብና ሃብት የትግራይ ሕዝብ ከየት አመጣው የሚል ጥያቄ ሊያስከትል ነው። ከጦርነቱ ጊዜ ጀምሮ ብዙ የተዘረፉ ባንኮች ንብረቶች እንደነበሩ አብሮ መዘንጋት የሌለበት የቁም ነገር ጥያቄ ሊያስከትል ነው። በወቅቱ ከነሱ ያገኙት ዘገባ ከቪዲዩ የተቀዳው ወደ አማርኛ የመለስኩት የፋብሪካዎቹ አነሳስ ወያኔዎች ከጫካ አገር ሲገቡ ከወዳደቁ ቆርቆሮ መሳይ ነገሮች በመገጣጠም እና ከምሰማር ምናምንቴ በመልቀም በመገጣጠም  እዚህ ግባ በማይባል ካፒታል ነበር ተነሳን ብለው ከፋብሪካዎቹ ስራስኪያጅ አንደበት የተነገረው። እንግዲህ ሃብቱ ከመቸው አደገ? በምን ሂሳብና ፍጥነት? በምን ታምር? ከነማን ጋር ገበያ ውስጥ ተወዳድሮ እንዲህ ዓይነቶቹ ብዛት ያላቸው ከባድ ከባድ ተቋማት ሊገነቡ በቁ? የሚለው ያስከትላል። የትግራይ ሕዘብ ንብረት ነው፤ ለሕዝቡ መሰጠት አለበት ፤ኦዲት መደረግ አለበት ወዘተ የሚባለው ነገር ሕዘቡ በነዚህ ማፍያዎች ንብረት እጁ ባያስገባ ጥሩ ነው። ይመለስ ከተባለ ወያኔዎች ከጫካ ይዘውት የመጡ ካፒታል ነው ከተባለም ላገሪቱ ብሔራዊ ባንክ መግባት ነበረበት፤መደረግም ያለበት እንደዚያ ነው።
ጠቅሼም አልዘልቀው ነገር ግን እስኪ ሁለት ጥቅሶች ጠቅሼ ላጠቃልል።
ፍትህ፡- በዚህ አይነት አስተያየት የሚሰጠው በአገሪቱ ቁልፍ የስልጣን ቦታዎች መከላከያ እና ደህንነትን ጨምሮ የትግራይ ተወላጆች በሀላፊነት በመኖራቸው መሰለኝ?

አቶ አስራት - ….”…በስልጣን ላይ የተወሰኑ ጄነራሎች እና ኮለኔሎች አሉ፡፡ እርግጠኛ ነኝ ከሃምሳ አይበልጡም። እነዚህም ቢሆኑም ለአቶ መለስ በጣም ታማኝ የሆኑ ናቸው፡፡ እንድያውም ከትግራይ አልፈው የአንድ አካባቢ ተወላጆች በመሆናቸው ነው። ሌላው ቀርቶ እራሳቸው አቶ መለስ የትግራይ ህዝብን ይወክላሉ ብዬ አላስብም፡፡ ልክ እንደ አቶ አባዱላ ማለት ነው፡፡ አቶ አባዱላ የኦሮሞን ህዝብ ይወክላሉ እንዴ? እናም ሀምሳ ሰዎች እዛ ውስጥ ስላሉ 5 ሚልዮን ሰዎች ይወክላሉ ማለት አይደለም፡፡ በደርግ ውስጥም እኮ የትግራይ ተወላጆች ነበሩ፡፡ እነ ፍስሃ ደስታን የመሳሰሉ፡፡ ሌላው መታሰብ ያለበት በሰራዊቱና እና አሉ ያልናቸው ሀላፊዎች የተሾሙት በትግራይ ተወላጆችነታቸው ሳይሆን ስልጣን ላይ ላሉት ሰዎች በተለያዩ መንገድ በጋብቻውም በደምም በመሳሰሉት የተዛመዱ ስለሆኑ ነው፡፡”
ይህ ለሰፊው አንባቢ እንዲተችበት ልተው። ለመሆኑ አምስት ሚሊዮን ሕዘብ ስልጣን ላይ መውጣት ይችላል እንዴ? ይኼማ ዲሞክራሲ በሚባለው ስርዓት መራጮቹ መርጦ የሚያስቀምጣቸው ተወካዩቹ ነው። አድልዎ እና አንድ አካባቢ ሹማምንቶች በወገኔ ወገኔ እየተደጋገፉ ስልጣኑን ተቆጣጠሩት “የሚባለው እውነታ” እኮ በምርጫ ስላልያዙት ነው።የትግራይ ሕዝብ “አማራ ገዢ/አማራ” በድሎናል አድልዎ አድረጓል “የሸዋ አማራዎች” “ደርግ ትግሬን ይጠላ ነበር/የአማራ ብሔር ወኪል ነው/የነፍጠኞች ወኪል ደጋፊ ነበር… ፤ትግራይን በአድልዎ በድለውታል” ሲሉ እነ ገብሩ አማራውን ሲከሱት የነበረው እኮ፤ ያውም በቅጽል ስማቸው “የሸዋ አማራዎች/አማራዎች/ደርጎች” የሚባሉት እኮ “በዲሞክራሲ የተመረጡ ስላልነበሩ” ነው፤አድለዎ ሲያደርጉብን ነበር ብሎ ወያኔ በየወቅቱ እስካሁን ድረስ ያማራ ስም የያዙ በንጉሡ ጊዜ እና በደርግ ጊዜ የነበሩ ባለስልጣኖች በዝርዝር በየጋዜጣው እና ድረ ገጾች የሚለጠፉት እኮ ያንን አድልዎ ለማሳየት ነበር (የአማራ ብሔር/አማራ የሚለው)። በዲሞክራሲ ያልተመረጠ ክፍል ስራውና ባሕርይው ያ ነው። አድልዎ! እንግዲህ ትግሬ ስልጣን አልተቆጣጠረም ዓድዋዎች ናቸው የሚባል ከሆነ እና እኔ ከላይ በተነተንኩት ሁኔታ ካልተስማማን “የሸዋ አማራ/ደቂቀ ምኒሊክ/የአንኰበር አማራ” የሚለው ክስ ክሳቸውን ማቆም አለባቸው ማለት ነው። ለነገሩ በወታደሩ ውስጥ የተንሰራፉት የትግራይ ተወላጆች የዓድዋ ብቻ አይደሉም። ሌላ ቀርቶ ጀኔራሎቹ እና ኮሎኔሎቹ ከአክሱም ከእንደርታ፤ከተምቤን፤ከራያ፤ከሁለት አውላዕሎ ከዓጋሜ …የተወለዱ ናቸው። ውትድርናው የተቆጣጠረው የትግራይ ታጋይ ነው። መረጃውና የመንግሥት መ/ቶች በሙሉ የሚታዘዘው በወያኔዎች ነው። በትግሬዎች ማለት ነው። ትግሬ አይደሉም ካላልን በተቀር።  
ስልጣን ድረስ የደረሰው በትግራይ ሕዝብ ተወክሎ እና ተደገፎ ሕዝቡም በወያኔ ተወክሎ ይታገል እንደነበር ከአምናው ቃለ መጠይቅ ካደረግኸው ከደጀን ራዲዮ መረዳት ይቻላል። ስልጣን ላይ ሲወጣም በሚገባ በሕዘቡ ሙሉ ፈቃድ ነበር ተንደላቆ የገባው።ወያኔ በ1983 ግንቦት 20 አዲስ አበባ ሲቆጣጠር የዘር ጉድ ጐንጉኖ ኢትዮጵያን መልኳን ለወጧታል። ከዚያ በላ ትግራይ ሕዝብ ስልጣኑን ለሌሎች አስረክቡ፤ እስከዚህ አድርሰናችል ብሎ ሲል የጻፈው ደብዳቤ ወይንም ሰላማዊ ሰልፍ አላውቅም አላነበብኩም።
ሁሌም የፖለቲካው መዘውር የሚባለው ልሂቁ ክፍልም ቢሆን የትግራይ ምሁራን ባብዛኛው ቁጥር ወያኔን ደግፎ እሽሩሩ በማለት ሲንከባከበው የነበረ ነው። ሽማግሌዎቹ ሳይቀሩ “መከፋፈላችሁ አስደንግጦናል” ብለው ወደ ባህላዊ ሽምግልና የተገባባት ንግግር እንደነበር እናውቃለን። ስለ ተሰዉ ጓዶቻችን እባካችሁ ታረቁ ሲሉ የነበሩ ውጭና ውስጥ የሚገኙ አብዛናዎቹ የትግራይ ተወላጆች ነበሩ። ለትግሬ ብቻ ነበር በየአዳራሹ ስብሰባ ሲካሁድ የነበረው። ዓለምሰገድ ገብረ አምላክ እማ ከነጭራሹ በየ እስቴቱ ሲዞር ዋሺንግተን ዲሲ ትገሬውን ሰብስቦ ሲያንግር “በመከፋፈላችን የነፍጠኛ ሪዘረክሺን አበሳሪ ነው” ነበር ያለው። አማራ ወይንም ኦሮሞ ስልጣን ይዞ እንደወያኔ ተሰንጥቆ ቢሆን ኖሮ የትግራይ ተወላጅ ምን ብሎ ነው የሚሰበስበው? ወያኔ ማለት የትግሬዎች ድርጅት ስለሆነ ነው። ኦሮሞውንም አማራውንም ቢሆን ቢሰነጠቅ በተራው የራሱን ነበር የሚጠራው። በጎሳ መደራጀት ትርፉና ምልክቱ የኼ ነው። ይህንን ምን ያሳየናል። የትግራይ ተወላጅ ከተቃዋሚ ጋር ለብዙ አመት ከተቃዋሚው ክፍል እራሱን አግልሎ እንደቆየ አንተም በዛው ራዲዮን ተናግረሃል (ወያኔ እስኪሰነጠቅ ድረስ ተገልሎ ነበር ለ10 ከባዱና ረዢሙ ዓመት ማለት ነው)። ይህ የሆነው ወታደራዊውም መንግሥታዊ ስልጣኑም ትግሬዎች በመቆጣጠራቸው ምክንያት ነው።
እነ ገብሩ እስኪሰነጠቁ ድረስ እኛ የምናውቀው ባብዛኛው የወያኔ ደጋፊ የነበረ ነው። እነ ገብሩ አስራት ሲባረሩም “ጅገኖቻችን ናቸው” ሲሏቸው የነበሩት የትግራይ ተወላጆች አንጂ ከሌሎች አካባቢዎች የተገኙ ኢትዩጵያውያን ዜጎች እንዲያ ያለ ቃል ሰመቼም አንብቤም አላውቅም። ያውም እባካችሁ ለጠላቶቻችን አታጋልጡን ፤ልታስበሉን ነው ወይ፤ ወደ ስራቸው መልሷቸው” ሲሉ የነበሩት ያው የትግራይ ተወላጆች ናቸው። በመሰንጠቃቸው የተደሰተ በጣም ጥቂት የትግራይ ተወላጅ ነበር። እኔ ከተደሰቱት አንዱ ነኝ። አንተም አስራት አብርሃም እንደዚሁ። ልዩነታችን ግን አስራት ያስደሰተው እነ ገብሩ ለትግራይ ሕዝብ “አማራጭ” ናቸው ብሎ ነው። እኔ ደግሞ ህወሓት ማፍያ እና የአገር ጠላት ስለሆነ ተሰነጣጥቆ አፈር ድቤ ቢበላ ሰላምና ዲሞክራሲ የነፈገው አጥር ፈርሶ  አንቀጽ 39 የተባለው ጉደኛ የስታሊን መርሖ ይጠፋል ነበር ደስታየ። በነዚህ ወንጀለኞችም ፍርድ ይሰፍን ይሆናል ነበር። የወጣት አሰራት ግን “አማራጭ” ብሎ ያስደሰተው ዓረና አንቀጽ 39 ይዞ ብቅ ሲል “እሺ ብሎ” ተቀብሎ የመገንጠል አማራጭ እንደ አማራጭ ይዞ መቀጠሉ ነው ልዩነታችኝ።
በጣም የከነከነኝ ስድብ ግን ይኼኛው የሚከተለው ለተጠየቀው መለስ ሲመልስ የሰደበን ስድብ ነበር፦
 “ ከእያንዳንዱ የህወሓት አመራር ጀርባ ወንጀል አለ” አስራት አብርሃም። እርግጥ አስራት ልክ ነው።ትክክል ብሏል። እኛኑን ህወሓት በጐሰኛ ባሕርይ አነሳሱና ፖሊሲው የተነሳ የባጀት አደላደል አድልዎ ሲያደርግ ቆይቷል ስንል የነበርነውን ክፍሎች እናም በአንዳንድ አክራሪዎች እና በህወሀት ሳይቀር የተለየ ጥቅም እንዳገኘ ተደርጎ የሚነገረው ስህተት ነው፡፡” ስትል መከራከሪያ ሰነዶችን ከማምጣት ይልቅ  እኛኑን “አክራሪዎች”  ስትል ሽልማቱን ሰጠኸን ። የኔ ጥያቄ ላንተ ደግሞ፡ ከእያንዳንዱ የህወሓት አመራር ጀርባ ወንጀል ያለ መሆኑን ከነገርከን እና ካወቅክ፤ ዓረና ትግራይ ከመሰረቱት የህወሓት አማራር አባላት የነበሩት ውስጥ ከጀርባቸው ወንጀል መኖሩን እያወቅክ ለምን ከወንጀለኞች ጋር ኢትዮጵያን/ትግራይን (አንቀጽ 39ኝን መመሪያ በመያዝ) የትግራይን ሕዝብ የማይወክሉት ከምትላቸው የመለስ ቡድኖች ነፃ ለማድረግ መታገል መረጥክ?
ለመሆኑ አክራሪ እና ወንጀለኛ ልዩነቱ ልትነግረን ትችላለህ? መቸም አርዕስቱ  በተለየ ምልክት በቀይ ቀለም ተሰምሮበት እንድንማርበት ተብሎ ስለሆነ የኢትዮ ሚዲያ አዘጋጅ የአቶ አብረሃም ቃለ መጠይቅ የለጠፈው፤ የአንባቢዎች እይታም እኩል ሕዝቡ እንዲያነበው ቢያደርጉ በጣም ይመሰገን ነበር። አለመታደል ሆኖ ኢትዮሚዲያ ባለቤት አቶ አብርሃ በላይ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ማወቁ በቻ አንጂ የሚዲያ ትርጉም አገልግሎት አላወቀውምና ይህ ጽሑፍ ከመነበብ አግዶታል።ከመነበብ ማገድ ግን ከቶ አይቻለውምና ይኼው በሌሎቹ ሚዲያዎች ለሕዝብ ቀርቧል። ሌላ ቀርቶ ለሌሎች በማስታወቂያ ሲሸጥ የወጣት አስራት አብርሃም “ከአገር በስተጀርባ” መጽሐፍ እንኳ የመግዛት ዕድል አቶ አብርሃ በላይ ሁለት ጊዜ እንዲልከልኝ ጠይቄው “ነፍጐኛል”። የወጣት አስራት ምሁርነት ለማስተዋወቅ  ለአንድ ምሁር ጓደኞየ መጽሐፉን በነፃ ልላክልህ ተመልከተው ሲል ኢመይል ሲጽፍለት፤ለኔ በገንዘቤ ልግዛህ ላክልኝ ብየው ነፍጐኛል።የአብርሃ በላይ ያላደገው ጭንቅላት የሚያስበው ያን ያክል ነው። ለነገሩ አሁንም መጽሐፉ አላነበብኩትም።አሁን በዚህ አባባሉና ስድቡ ብወቅሰውም ወጣቱ ቆራጥ ኢትዮጵያዊ የትግራይ ተወላጅ መሆኑን አልተጠራጠርኩትም።ለወደፊቱ እየተግባባን እንደምንሄድ ተስፋ አለኝ።
ወደ ርዕሱ ልመለስ። ወጣት አብርሃም የተወለደው በ1970 ዓ.ም ነው። እስከ12ኛ ክፍል ብሎም እስከ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ የተማረው እዛው አዲስ አበባ ውስጥ ነበር (ከደጀን ራዲዩ ካገኘሁት መረጃ ከራሱ ቃለ መጠይቅ የተረዳነው ለአንድ ዓመት 9ኛ ክፍል ብቻ ነበር ተምቤን ውስጥ ተመልሶ የተማረው 10ኛ ክፍል አዲስ አበባ ተመልሶ ሄዶ ቀጠለ)። ወያኔ ሲገባ በ1983 ዓ.ም የ13 አመት ልጅ እግር ነበር። ወያኔ ከጫካ በገባ ቢያንስ 5 አመት እስከ 10 አመት ያህል  ወጣቱ አስራት አብርሃም ትግራይ ውስጥ እና በሌሎቹ ክፍለሃገሮች (በወያኔ አጠራር ክልል መንግሥታት) ሲደረግ የነበረው የባጀት እና የማምረቻ ዕድገት እንቅስቃሴና ርብርብ ከሌሎቹ ክፍለሃገራት ይልቅ ለትግራይ አትኩሮት ሲደረግ በነበረበት ወቅት የተቃዋሚ (ነፃ ጋዜጦች) ጋዜጦች ሲዘግቡት የነበረውን የተለያዩ የጐሳ አድልዎ እሮሮ በመረጃ እየተነፃፀረ ሲዘገብ ወጣቱ አስራት አብርሃም በወላጆቻችን የአነጋገር ዘይቤ “ወጠጤ ነበር” ትንሽ ወጣት ነበር። በተለይ አምስ አመት ውስጥ ከሻዕቢያ ጋር ሆነው ሲዝቁትና ሲያሻግሩት የነበረውን ድርጊት እና አድልዎ የዛሬው የ32 አመት ጐልማሳው ወጣት መምህር አስራት አብርሃም ድርግቱ ሲፈጸም በወቅቱ ከአስራ ሰባት አመት እድሜ አይዘልቅም ነበር። ያውም ደጀን ራዲዬ በተባለው የትግርኛ ራዲዬ ጣቢያ ልክ የዛሬ አንድ አመት (ጁን ) በሰጠው ቃለ ምልልስ ስናስታውስ በራሱ አንደበት ወያኔ ለሁለት ሲሰነጠቅ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ተማሪ እያለ “ጨቅላ ህፃናት ስለነበርን ብዙም ፖለቲካው ጠለቅ ብለን እንደዛሬው የተረዳነው አልነበረም።” ይላል።
በወቅቱ የንበረት/(የእድገት የአስተዳደር የፍትሕ እና የጋለ የጎሳ አድልዎ በታየበትና ሲከናወን በነበረበት ወቅት “ልጆች ስለነበርን” በማለት እራሱ በገመገመበት የልጅነት ሕሊና ስናመዛዝን የዛሬው የዓረና ትግራይ ድርጅት የሕዝብ ግንኙት ክፍል ሐላፊ መምህር አስራት አብርሃም ከሌሎቹ ይልቅ በውቅቱ ለትግራይ አካባቢ እና ለትግራይ እና ለኤርትራውያን ተወላጆች ፍትሕን ያልተመረኰዘ አድልዎ ሲደረግ በነበረበት ወቅት ወጣቱ የሚያወቀው ጉዳይ አልነበረም። ስለዚህ “አክራሪዎች” በማለት የሰጠንን የማዕረግ ስም ከይቅርታ ጋር ማንሳት ይኖርበታል።
እኛ አክራሪዎች አይደለንም፤ በመረጃ ነበር አስደግፈን ክርክራችን በወቅቱ ያቀረብነው። አድልዎው ሲደረግ ትግራይ እነ ገብሩ አስራት እነ አረጋሽ ትግራይ ሲያስተዳድሩ ነበር።ለኑዛዜ አልታደሉም እንጂ ብዙ ድርጊት ያውቃሉ የሚል ግምት አለኝ።
አንድ የአድልዎ ታሪክ ላቅርብና ልሰናበት። የሚከተለው መረጃ በዚህ ወር በሚቀጥለው ወር ለሕትምት በተዘጋጀው በአዲሱ መጽሐፌ ውስጥ የተገኘውን ለምሳሌ ልጥቀስ፡
ሌላው በጣም ልብ ብሎ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊገነዘበው የምፈልገው ነገር ለየት ያለ የአገሪቱን ከኢኮኖሚ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የዘረፋ ድርጊት ልግለጽ። አንድ ባገሪቱ ውስጥ በግምባር ቀደም የሚጠቀስ ድረጅት አለ እና በጥሞና እንድታዳምጡኝ እጠይቃለሁ። የድርጅቱ ስም "የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን" የሚባል። መረጃው እንደሰማሁት ምናልባትም ካገሪቱ በጀት ግማሹን ለዚህ ድርጅት ተመድቧል። በዚህ መ/ቤት ውስጥ የሚደረግ ምዝበራ አስመልክቶ አንድ ማስረጃ ላቅርብ። ይህ ድርጅት በወረዳ 021 ቀበሌ 24 ልዩ ቦታው መክሲኮ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው የሚገኘው። ትልቅ ሕንጻ ነው። መስሪያ ቤቱ በማዕከልነት ለመምራት የተቋቋመ መስሪያ ቤት ነው። ሌሎች የክልሎች ባለሥልጣኖች አሉ። ይሄ የጠቅላላ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ነው። ግዙፍ ነው። ሥራው መንገድ መስራት ነው። ሁለት የመንገዶች የሥራ ዘርፎች አሉት። አንዱ በመንግሥት የሚከናወን ሌላው የግል ኮንትራክት ተጫራቾች የሚያከናውኑት አሠራር ነው። ኮንትራክተሮቹ ከዚህ ድርጅት ጋር ተፈራርመው የሚሰሩ ተዋዋየች ናቸው።
እኔ እስከ ማውቀው ድረስ በ1989 ዓ.ም. አካቢ ጀምሮ በዚህ መስሪያ ቤት ውስጥ በተከታታይ ዘረፋዎች ሲካሄድ እኔ የማውቀው በተጫባጭ የደረስኩበት ምርመራ ነው። ዘረፋው ሚካሄደው ምንድ ነው? የመስሪያቤቱ ንብረት ይሰረቃል፤ በወረዳ 21 እና ቤሎችም ንበረቶች የሚቀመጥበት ግምጃ ቤት አለ። ሌሎችም በወረዳ 18 እና ሌሎች ግምጃቤቶች አሉት። ግን እኔ መግለጽ የምፈልገው በእኔ ወረዳ በነበረው ጉዳይ ነው። ምረመራዎች በሂደት እየተደረጉም እያሉ፤ አሁንም በተደጋጋሚ ያለማቋረጥ ሌላ ስርቆት ይካሄዳል። ዕቃዎች ይጠፋሉ ይዘረፋሉ። ዘራፊው አይታወቅም። መቸ ተዘረፈ? በማን ተዘረፈ? የሚል አይታወቅም። የመስሪያ ቤቱ ኀላፊዎች ለይስሙላ ብቻ መሰረቁን ደብዳቤዎች ይጽፉ ነበር። የሚጽፉት ለማን ነው ለማዕከላዊ ፖሊስ ምርመራ ማስተባበሪያ ለእነ "ታደሰ መሠረት"፤ ታደሰ መሠረት የፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ማስተባበሪያ ኀላፊ ነው። ለነሱ ይጻፋል። ቀጥሎ የሚጽፉት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ነው። "ተስፋይ አብረሃ" ሳይቀር ያውቀዋል። ኮሞሽነር በነበረበት ጊዜ በተከታታይ ደብዳቤ ተጽፎለታል።
ይሄ መስሪያ  ቤት በእኛ ወረዳ በወረዳ 21ፖሊስ ጽ/ቤት ክልል በመሆኑ ለተጠቀሱት መ/ቤቶች ሲጻፍ ለእኛ በግልባጭ ያመለክቱን ነበር። እኔ ጋር ይመጣል፥ቢሮ ውስጥ ተመዝግቦ ይቀመጣል። ሁኔታውን አያለሁ። ከስድስት ወር በፊት የተጻፈው ደብዳቤ መልስ የለውም፤ ዘረፋው አሁንም ቀጥሏል፣ አሁንም አዲስ የዘረፋው አመላካች ደብዳቤ በተከታታይ ይጎርፋል። በክልሉ የምርመራ ሐለፊ የነበሩ መቶ አለቃ አስፋ አየለ የሚባሉ ይሄን ነገር ጠየቅካቸው። እንዴ! ይሄ መስሪያ ቤት ተከታታይ ደብዳቤዎች ለናንተ ይጽፋል፡ ለኛም በግልባጭ ያስታውቀናል፤ የተካሄደ ምርመራም የለም ብሔራዊ ወንጀል/ናሺናል ክራይም ነው እና እንዴት ነው መቶ አለቃ አሰፋ የምታውቀው ነገር አስቲ አካፍለኝ፣ ይሄ ጉዳይ አሳሳቢ ነው፣ አገሪቱን ይጎዳል ብየ አወያየሁት። መቶ አለቃ አሰፋ አየለ ጥሩ አዋቂ የፖሊስ መኮንን ነው። አይ! "አበረ" ይሄን ነገር ባታነሳብኝ ጥሩ ነው አለኝ። የተወሰኑ ሦስት የመስሪያ ቤቱ ዘበኞች ምርመራውን ለማጣራት አስሮ እንደነበር ነገረኝ። በሁለተኛው ቀን ልቀቁዋቸው ተብሎ ተለቀቁ። እንዴት? ለምን? ሲባል በስርቆቱ ጉዳይ ብዙ የተለያዩ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች እጅ ስላለበት እነኚህ ዘበኞች ለትንሽ ጊዜ በእስር ቢቆዩ ምስጢሩን ስለሚያወጡ እና ባለሥልጣኖቹ እና ንክኪያቸው አብረው ስለሚጋለጡ በዚህ ስለሰጉ እንዲለቀቁ ተደረገ።
ነገሩ የአገሪቱ የመንገድ ሥራ ባለሥልጣን መ/ቤት ባለሥልጣኖች በተራ ዝርፍያ እና ንብረቶችን ማለትም ቡልደዘሮች፤ ትራክተሮች፤ ትላልቅ እና ትናንሽ የመንገድ እና የሕንጻ አጋዥ መኪናዎች የመሳሰሉት በእነ መለስ ዜናዊ ትእዛዝ በእነ አቶ ተስፋየ ናሁ ሰናይ (የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ሹም) ተባባሪነት ዕቃዎቹ ከውጭ አገር በግዢ ወይንም በመሳሰሉት እርዳታ የተገኙ ንበረቶች በመርከብ ተጭነው ከጅቡቲ ወደብ ላይ ተመዝግበው እንዳረፉ፤ ከጅቡቲ ግምጃ ቤት በቀጥታ ወደ ትግራይ አንዲተላለፉ ትራክተሮች፤ ቡለዶዘሮች የመሳሰሉ ከባድን ብረቶች ከመነሻው ለግዢ ወይንም በእርዳታ መጠይቅ ሲመዘገቡ በሌሎች ክልሎች ስም የግዢ ቅጽ ይሞላና፤ ከተገዙ በላ ግን በቀጥታ ወደ ትግራይ ተመዝግበው እንዲተላለፉ ይደረግ እንደነበር እነዚህ ሰዎች ያገሪቱ መንግሥታዊ መስሪያቤቶች እና የሕግ ክፍሎች ለግልና አድሎአዊ መጠቀሚያ ያደርጉት የበነበረውን የማጭበርበሪያ ስልቶቻቸው አጣርተን የደረስንባቸው ጭብጥ የምርመራ ሰነዶች ሁሉ ነበሩን።”{ ምንጭ- በቅርቡ ወደ ህትመት የሚገባ “አቅጣጫውን የሳተ ነፃ አውጪ” ከሚለው አዲስ መጽሐፍ፤ ደራሲ ጌታቸው ረዳ”} ኢትዮጵያንና አምላክዋን አጥብቀን እንሳለም። ደህና እንሰንብት። www.ethiopiansemay.blogspot.com  getachre@aol.com