Monday, September 26, 2022

በጠና ከታመሙት ትንሽ ዝቅ ብሎ ሻል ያላቸው የበሽተኞቹ ንኡስ ክፍሎች ጌታቸው ረዳ ኢትዮፕያን ሰማይ 9/27/22

 

በጠና ከታመሙት ትንሽ ዝቅ ብሎ ሻል ያላቸው የበሽተኞቹ ንኡስ ክፍሎች 

ጌታቸው ረዳ

ኢትዮፕያን ሰማይ 9/27/22

ከብዙ አመት በፊት “አምባ ገነኖችን ማራባት” እና ““የነገድ ፌደራሊዝም” ፤ የግማሽ ንክ ግለሰቦች የፖለቲካ ቅዠት” እና  “ኦሮሙማ አፓርታይዳዊው የስልቀጣ ርዕዮት” (የመጨረሻው ርዕስ ለስልቃጮች ጥብቅና የቆመው ፌስቡክ አግዶታል) የሚሉ ሦስት የተለያዩ መጣጥፎች አቅርቤ ነበር። ለዚህም መነሻየ ሁላችሁም እንደምታውቁት ኢትዮጵያ የደቡቡ ክፍል “ብሑር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች” ተብሎ በተሸነሸነው አፓርታይዳዊ ክልል እና 3/4ኘኛው የኢትዮጵያዊያኖች የጋራ መሬት የሆነው ለብቻው በባለቤትነት ለኦሮሞዎች ብቻ የሰጠው አፓርታይዳዊ  የአስተዳዳር መብት ምክንያት የአማራ ማሕበረሰብን እና ኦርቶዶክስ ክርስትያኖችን ለይቶ በተከታታይ ለ30 አመት ‘አስካሁንዋ ቀን ድረስ እየተፈናቀለ ፤ እየተገደለ፤ንብረቱ እየተዘረፈ፤ የዘር ማጥፋት እየተፈጸመበት ይገኛል። በዚህ ምክንያት ነበር ሦስቱንም ርዕሶች ለንባብ ለጠፌአቸው የነበሩት።

ይህ የዘር ማጥፋት ወንጀል ዛሬም በባንቱስታው ክልል ኦሮሙያ በሚባለው ”ወያኔአዊው የአብይ አስተዳደር’ መሪነት የዘር ማጽዳቱ ወንጀል በባሰ ቀጥሏል።

በሩዋንዳ የሁቱ መንግሥት የታወጀው የቱትሲዎች የዘር ማጥፋት አዋጅ አንዳች ልዩነት ሳይኖሮው ትከክለኛ ቅጁ በኢትዮጵያ ምድር በሕገመንግሥት የጸደቀ “ቋንቋን/ጎሳን መሰረት ያደረገ “ጸረ አማራ የነገድ ፌደራሊዝም” ሥራ ላይ ውሎ እያደረሰው ያለው ጥፋት ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው።

በዚህ ወር ባንድ ሦሰት ቦታዎች ምሁራን ተብየዎች አንዳንዱ ዶ/ር አንዳንዱ የዩኒቨርሲቲ መምህራን የሚሰጡትን አስተያትና ቃለ መጠይቅ አድምጬ ገርሞኛል። ይህ ስርዓት እንዴት ይወገድ ከማለት ይልቅ እንዴት ይሻሻል የሚሉ ምሁራን ቁጥራቸው እጅግ የበዙ ናቸው። እነኚህ ካደመጥኳቸው ሰዎች መካከል “በጠና ከታመሙት ትንሽ ዝቅ ብሎ ሻል ያላቸው የበሽተኞቹ ንኡስ ክፍሎች ናቸው”። ጠቅላላ ሕገ መንግሥቱ በአዋጅ የይታገድ ተብሎ እንደ አፓርታይድነቱ መሠረት ሕገመንግሥቱን እንዳለ ከማስወገድ ይልቅ “ሕገ መንግሥቱ አንዳንድ ጥሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችም አሉት እኮ” እያሉ “ሴት አዳሪዋ በሽታ ይኑራት እንጂ ደስ የሚል ዳሌና ወፈር ያለ ደስ የሚል መስህብ ያለው ለስላሳ “የሊት ሰውነት” አላት እኮ’’ በማለት አደገኛውን በሽታ በሴትዮዋ ቅርጽ ምክንያት እንዲታቀፉዋት የሚከራከሩ ሰዎች ናቸው። ፖለቲከኞቹም “ሕገመንግሥቱ ደስ የሚሉ ጥሩ ነገሮች አሉት እኮ” እያሉ ለለውጡ ዕንቅፋት እየሆኑ ነው።

አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ፤

የኢትዮጵያ ዜጎች ማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢ-ዜማ) አመራር አባል አንዳለም አራጌ በ21/05/2019 ሸገር ታይምስ ባልደረባ ከሆነቺው ‘መክሊት ኃብታሙ’ ያደረገውን ቃለመጠይቅ። እንዲህ ይላል፤-

“ጥያቄ” ፤_--- 

 በርካቶች አሁን በየቦታው ያለውን ግጭት፣ግድያ እና መፈናቀል ከለውጡ ድክመት ጋር ያይዙታል፡፡ አንተ በዚህ ላይ ምን ትላለህ? ይህ ሁሉ የሚከሰተው ስር ነቀል ለውጥ ባለመምጣቱ ነው ?

መልስ-

አንድአለም አራጌ፡ እንዲህ ይላል፦

“ሞት እና መፈናቀሉን ያመጣው ኢህአዴግ ነው ወይ? እኔ እጠራጠራለሁ፡፡አሁን ኢህአዴግ ከስሩ ባለመነቀሉ እንግልቱ መፈናቀሉ እና ግድያው በዶ/ር አብይ መሰሪነት ነው ብሎ የሚያምን ካለ እኔ በበኩሌ አይመስለኝም፡፡

 ይሄ ነገር እየተከሰተ ያለው በተለያየ አካባቢ ነው፡፡ አንደኛ የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ታፍኖ እና ተጨቁኖ ነው የኖረው፡፡ ስለዚህ እንደሚመስለኝ የችግሩ መንስኤ ያገኘነውን ነፃነት በግባቡ ያለመጠቀም ነው፡፡ ለምሳሌ አንቺ አንድ አካባቢ ሄደሽ በቀናት ውስጥ የሆነ ነገር ተናግረሽ 40 እና 50 ሺህ ሰው ማስሰለፍ (መመልመል) የምትችይበት ሁኔታ ተፈጥሯል ፣ ነፃነት አለ መሰለፍ ይቻላል መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን ያንን ነፃነት ለበጐ ነገር ሰዎች እየተጠቀሙበት አይደለም፡፡ ይሄ ነፃነትን በግባቡ ማስተዳደር አለመቻል ነው፡፡ ኢህአዴግ ከስሩ ቢነቀል ምን ትርፍ እናገኝ ነበር እኔ አላውቅም።”

አንዷለም ስለ ዶር ብርሀኑ ነጋና ስለ አማራ ብሄርተኛ..! እንዲህ ይላል፡-

"የአማራ ብሄርተኞች ብርሃኑ ነጋን ነጥለው የሚዘምቱበት የብሄር አጥራቸውን እንዳያፈርስባቸው ሰግተው ነው። ሌላ የተለዬ በብርሃኑ ነጋ ላይ በማስረጃ የሚያቀርቡት ወንጀል የለም" (አንዱአለም አራጌ የኢዜማ ምክትል መሪበ21/05/2019 ሸገር ታይምስ ቃለ መጠይቅ።)”

ሲል “ኢህአዴግ ከስሩ ቢነቀል ምን ትርፍ እናገኝ ነበር እኔ አላውቅም።” በማለት አፓርታይዱ ቢነቀል/የፋሺስት ሥርዓት/ ቢነቀል ምን ይውጠን ነበር እስከማለት የደረሰው አንዱአለም አራጌ ‘ሲያስረው ሲገርፈው ሲያሰቃው የነበረው ኢሕአዴግ ከፊቱ ላይ ቆሞ እያው ማየት ያቃተው ፖለቲከኛው “በጠና ከታመሙት ትንሽ ዝቅ ብሎ ሻል ያላቸው የፖለቲካ በሽተኞች” ከምላቸው እንደዚህ አይነቶቹ ታዋቂ ፖለቲከኞች የሥርዓቱ ዕደሜ እንዲጨምር እና ግድያው መፈናቀሉ ጦርነቱ እንዲቀጥል ሰበብ ናቸው።

 የኔን ሃሳብ የምትጋሩ አንባቢዎቼ ፤ የነገድ አስተዳዳር አንዴ ከተቸከለ፤ እንደ “ጎበጠ ምስማር” ለማስተካካል እጅግ የሚያስቸግር “ጠማማ” ስርዓት ነው። ኢሕአዴግ ተክቶ የመጣ በኢሕአዴግ ሕገመንግሥት የሚሰራ ቀርቶ ከሥር ቢነቀልም አስተሳሰብ ቀርጾት የሄደ ሕሊና ለማጥራት ችግር ይገጥማል። “ፌደራሊዝም” (ነገድ ይኑሮው አይኑሮው) “ከነ አካቴው” ለኢትዮጵያ የሚበጅ አይደለም። ምክንያቱም አፓርታይ ከነ ጥፍሩና እግሮቹ ተነስራፍቶ እንዲቀጥል የማድረጊያ ድልድይ ነው።

የሚበጀው የዘር መፋጀት ያልነበረው እንደ ዱሮው በሪጂናል /በክፍሃገር/ አስተዳዳር አንዲተዳዳር ካልሆነ አንዲያው ‘“ፌደራሊዘም” የሚለው ስነ ሃሳብ እራሱ “ነገድ ይኑሮው አይኑሮው” በአካባቢያዊ ሕሊና አስተዳዳር ብቻ የሚያተኩር አጥር የሚያበጅ የፈረንጅ ዕብዶች ያጋቡብን “ፋሺሰትቶች” የዘረጉት ወጥመድ ነው። ፈረንጆች እንደሚሉት “ያልተሰበረውን አትጠግን” ይላሉ። ሳይሰበር እጠግናለሁ ብለህ እየሰራ የነበረውን ከነ አካቴው ብትሰብረው ያንን መተኪያ ብለህ ያመጣኸው ያልታሰበ ብልሽት ቢያመጣ “ቁጭቱ የማይቻል ነው፤ ማለት ነው። የ60ዎቹ የወያኔ እና ኦነጋዊያን ኮሚኒሰት ተማሪዎች የክፍለሃገራዊ አስተዳደሩን ሰብረው ‘ክልል’ (ባንቱስታዊ) ብለው በነገድ ሸንሽነው ያልታሰበው የሕዝብ ዕልቀትና መፈናቀል አመጡ። ለዚህ ነው “ያልተሰበረውን አትጠግን” የሚባለው።

ወያኔም ሆነ በአብይ አሕመድ የሚካሄደው ‘የብልግና ፓርቲ’ ‘የነገድ ፌደራል አስተዳዳር’ ስለሆነ ማለቂያ የሌለው አቤቱታና ግጭትን የሚያስከትል “ጤነኛ” የነበረ ማሕበረሰብ ወደ “ዕብደት” ለውጦ “ንክ” የሆነ ማሕበረሰብን የመፍጠር በር እጅግ እየሰፋ በመሄዱ “ፌደራሊዘም” የሚል የማይጨበጥ ጣዕም ያለው የሚመስል ግን አገርን ያለ ውጊያ በቀላሉ ለማምበርከክ ቀላል ዘዴ ሆኖ ያገኙት የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ጠላቶች በጋራ በኢትዮጵያ ሕልውና የከፈቱብን ጦርነት ስለሆነ አሁን ያለው ሕገ መንግሥትም ሆነ ሕገመንግሥቱን እየመሩት ያሉት “ወያኔአዊና ኦሕዴዳዊ የነገድ መንጋ” ስብስቦች የሚሻሻሉ ሳይሆኑ ከሠልጣን ማስወገድ አማራጭ የሌለው አዲስ ትግል ሆኖ ፌደራሊዝም የሚባል የማጃጃያ “ከረሜላ” ሳንቀበል ክ/ሃገራዊ (ሪጅናል) አስተዳዳር መተካት አለበት። ያንን ባታደርጉ ቁስሉ ገና ያገረሻል።

ሌላው ነጥብ፦ ሌለው ዕንቅፋት ደግሞ “ማወላወል እና ሰከን በሉ የሚሉትን” አለመቀበል። መጀመሪያ እራስን በትልቁ ተራራ መቆም ያስፈልጋል። ካልሆነ ጠመንጃ ይዞ መሸሸግ፤ ለዕርቅ ማጎብደድ፤ ‘በሩን ከፈት በሩን መዝጋት’ “በተሰጠቺን በር ገብቶ መታገል” ወይንም “አብይ አሕመድ ሰው ሰውኛ የሚሸት ነገር አላቸው” ማለት ወይንም ልክ ታማኝ በየነ እንዳለው “ዶክተር አብይ የተሸከመውን ችግር እኛ ላንድ ቀን መሸከም አንችልም፡ ዶ/ር አብይ በገዛ ፈቃዱ ለቅቄአለሁ ቢለን ምን ሊውጠን ነው?” ወይንም “ነፃነት አለ መሰለፍ ይቻላል መናገር ይቻላል” “የችግሩ መንስኤ ያገኘነውን ነፃነት በግባቡ ያለመጠቀም ነው፡፡” “የትግራይ ሕዝብና ወያኔዎች ለየቅል ናቸው” “የኦሮሞ ሕዝብ እና ኦነግ ኢሕአዴግ ለየብቻ ናቸው” ወዘተ….ወዘተ… የሚሉ ሰዎች ተሰሚነት ያዳበሩ የብዙ አመት ፖለቲከኞች ስለሆኑ የሚናገሩት ንግግሮች በተቃውሞ ሕዝብ እንዲያውቃቸው ዕርምት እንዲያደርጉ ማሳወቅ ያስፈልጋል።

እንዳይከፋቸው፤ እንዳይቀየሙን እየተባለ ፤ ዕርምት እንዳያደርጉ ንግግራቸው ያለ ተቃውሞ ልቅ ከሆነ እንኚህ “በጠና ከታመሙት ትንሽ ዝቅ ብሎ ሻል ያላቸው የፖለቲካ በሽተኞች ንዑስ ክፍሎች የሚናገሩት ንግግር ከጦርነቱ በባሰ የሰው ሕሊና የማኖሁለልና የማኮላሸት አቅም ስላላቸው ትኩረት ያስፈልጋል።

አድርባይነት እና መሞዳሞድ አልለቅ ያለን የኢትዮጵያዊያን አደገኛ ባሕሪ ነው። በአቋም መጽናት አስፈላጊ ነው። በሺዎቹ ተቃዋሚዎች አገራቸው እየተመላለሱ ሲቦርቁ እኔ በተራራው አናት ላይ ሆኜ የሚሄዱት የሚመላላሱትን በማየት የምታዘበው የአቋም ጥራት አስፈላጊነት በመያዝ ነው።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ

Ethiopian Semay