Saturday, August 10, 2019

አባ ባሕርይ ወይንስ አባ ኦሮሞ? አቻምየለህ ታምሩ (posted at Ethio Semay) 8/11/2019 (5/12/2011)


አባ ባሕርይ ወይንስ አባ ኦሮሞ?
አቻምየለህ ታምሩ (posted at Ethio Semay)
8/11/2019 (5/12/2011)
Photo-Achamyeleh Tamiru, exceptional intellectual Ethiopian  
የአባ ባሕሬይን መጽሐፍ አንብቦ ለጨረሰና የአጻጻፉን ጥራትና የስነ መዋቅሩን ልቀት ላስተዋለ ፊልም የማየት ያህል ቢሰማው አይፈረድበትም። መጽሐፉ በትዝታ አምስት መቶ ዓመትን ወደ ኋላ መልሶ ታሪኩ የተነገረበትን ዘመን የኖሩ ያህል ስሜት ይፈጥራል። ብዙዎቹ ኦነጋውያን ግን ይህን የመሰለ የኦሮሞ ታሪን የጻፉትን አባ ባሕርይንና መጽሐፉን ከግዕዝ ወደ አማርኛ በስተ እርጅና ዘመናቸው እረፍት ሳያምራቸው የተረጎሙልንን ፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌን ሲያብጠለጥሏቸው ይውላሉ። ይህ የውለታ ቢሶቹ ኦነጋውያንና ተከታዮቻቸው አስጸያፊ ተግባር የግብዞችን የእውቀት ጾመኛነትና ወደር የማይገኝለት ድንቁርናቸውን እንዲሁም የበሉበትን ወጪት ሰባሪና የጎረሱበትን እጅ ነካሽ መሆናቸውን ብቻ ነው የሚያሳየው።

ኦነጋውያን ሕሊና አልባ ነውረኞች ስለሆኑ እንጂ የአስራ ስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መነኩሴ አባ ባሕርይ ፍጹም ሞያዊነትንና ስነ ምግባርን በተላበ መልኩ ባይናቸው ያዩትን የኦሮሞ እውነተኛ ታሪክ በመመዝገባቸው መታሰቢያ ሊያቆሙላቸው በተግባና የሚመጥናቸውን የታላቅ ሰውነት ክብር ሊያጎናጽፏቸው በተገባ ነበር።

ዛሬ ታሪክ እንጽፋለች የሚሉን ኦነጋውያን የታሪክ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች ሁሉ የአባ ባሕርይን ሩብ ያህል ሞያዊና ሚዛናዊ የታሪክ አመዘጋገብ የላቸውም። የአባ ባሕርይን ጠንቃቃ ጸሐፊነትና ሞያዊ ስብዕና ለመገንዘብ ሩቅ ሳንሔድ ራሳቸው አባ ባሕርይ ያስቀመጡልንን ታሪክ ብቻ በማንበብ መጽሐፋቸውን ሲቋጩ ያሰፈሩትን መደምደሚያ ማየቱ ይበቃል። አባ ባሕርይ በመጽሐፋቸው በሙሉ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ከደቡብ ኢትዮጵያ ተነስተው ወደ ሰሜን በሚፈልሱበት ወቅት የተቀዳጇቸውን ድሎች እንደወረዱ ሲዘግቡ በተለምዶ በራስ ወገን ወይንም በሌላ አቅጣጫ የተፈጸመን ተግባር እንደ ጀብዱ ማንሳት ባልተለመደበት ዘመን ሆነው ያንን ታሪክ መጻፋቸው የርሳቸውን የተለየ የአጻጻፍ ዘዴና ሚዛናዊ አቀራረብ አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

አባ ባሕርይ በዘመናቸው ወደር የማይገኝላቸው ምሁርና የማያዳሉ ሀቀኛ ጸሐፊ መሆናቸውን በማያወላውል መልኩ ለመገንዘብ በድርሳናቸው ክፍል 18 በቀረበው ታሪክ ላይ ለሚዛናዊነታቸው በሰጡት ምክንያት ውስጥ የዘረዘሩትን አመክንዮ መመልከት ይቻላል። ፕሮፌሰር ጌታቸው ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙት ይህ ታሪክ የሚከተለውን ይመስላል፤ 

የቦረን ሙልአታ የዳሞትን ክርስቲያን አዳከማቸው፣ በታተናቸው፣ አገራቸውን አጠፋው። በሱ ዘመን ሸዋና ዳሞት ምድረ በዳ ሆኑ።
አንድ ጊዜ የጋላን ድል፥ አንድ ጊዜ የክርስቲያን ድል ብጽፍ፥ ዛሬ ላንተ ነገ ለሌላህ የሚለው የመጽሓፍ ልማድ ነው። ድሉም አንድ ጊዜ ለዚህኛው ሌላ ጊዜ ለዚያኛው ነው። ሁል ጊዜ የሚያሸንፍ አንድ እግዚአብሔር (ብቻ)ነው። ሀገሪቱም በጋላ እጅ ገባች፤ የተረፈ የለም።
ይህ መጽሐፍ በተጻፈበት ጊዜ የቢፎሌ ልጅ የሙልአታ ሹመት ሰባት ዓመት ሆኖታል። በዘመናቸው የሚሆነውን ውጊያና እልቂት በሕይወት ካለሁ እጽፈዋለሁ። ከሞትኩም ታሪኬንና የሚመጣውን ሉባ ታሪክ ሌሎች ይጽፉታል። ግን የሞተ ብፁዕ ነው፤ አርፏልና።
[ምንጭ፡ ጌታቸው ኃይሌ (1995) የአባ ባሕርይ ድርሰቶች፤ ኦሮሞዎችን ከሚመለከቱ ሌሎች ሰነዶች ጋር፥ ገጽ 89]

ይህ አባ ባሕርይ አሳዝኝ በሆነ መልኩ የጻፉት ታሪክ በዘመኑ ሲሆን ያዩትን የዐይን ምስክርነት ነው። ይህ እንግዲህ በወቅቱ ስለ ነገሥታት ገድል ቀባብተውና አሰማምረ ይጽፋሉ በሚል «ደብተራ» እየተባሉ ከሚሰደቡት መካከል የሆኑት የኢትዮጵያዊው የጋሞው መነኩሴ የአባ ባሕርይ የአጻጻፍ ዘይቤ ነው። ስለ እውነት ለመናገር ይህ የአባ ባሕርይ ሞያዊና ሚዛናዊ የአጻጻፍ ዘዴ ዛሬ ካሉትን ሁሉም ብሔርተኛ የታሪክ ደራቾችና ጸሐፍት ጋርም የሚወዳደር አይደደም።

አለም በሙሉ በጨለማ ይኖር በነበረበት 16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አንድ አባ ባሕርይ የሚባሉ ኢትዮጵያዊ የብርብር ማርያም መነኩሴ ቄስ ከፍ ሲል በተጠቀሰው የሕሊና ሚዛን እየመዘኑ በነበሩብት ወቅት ሲፈጸም ያዩትን ታሪክ በመክተብ በጨለማው ዘመን ላይ ብርሃን ፈንጥቀው ታሪካችንን አሳምረው ስለጻፉ የምስጋና ሐውልት ሊቆምላቸው ሲገባ ተማርን በሚሉት ኦነጋውያን ግን የኖሩበትን ዘመንና በዐይናቸውን ያዩትን ታሪክ ስለጻፉ ብቻ ሲያብጠለጥሏቸውና ሲያወግዟቸው ይውላሉ።

የኦሮሞ ብሔርተኞች ውለታ ቢስ ሆነው ነው እንጂ ኅሊና እንዳለው ሰው ቢያስቡ ኖሮ አባ ባሕርይ የመዘገቧቸውን የኦሮሞ የዘመኑ መገልገያዎችና ልዩልዩ ስያሜዎች በሙዚየምነት የያዘውና አዲስ አበባ የተገነባው «የኦሮሞ ባሕል ማዕከል» የኦሮሞን ባሕል፣ አደረጃጀትና አኗኗር በተሟላ መልኩ ስዕላዊ ይዘት ሰጥተው በጻፉት በአባ ባሕርይ ስም የባሕል ማዕከሉን በሰየሙት ነበር። ይህንን ማድረግ ባይቻል እንኳ ልክ እንደ ኤሮፓዊው ኢራስመስ መንደስ በቀለሙ ሰው በአባ ባሕርይ ስምም «አባ ባሕርይ ነጻ የትምህርት እድል» ወይንም Abba Bahrey Scholarship Program ባቋቋሙና ሕዳግ ሰጥተው የአማርኛውን ትርጉም ሙሉዕ በማድረግ ከፍ ወዳለ ደረጃ ላደረሱት ለፕሮፈሰር ጌታቸው ኃይሌ መጦሪያ እንዲሆናቸው «ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት» የሚባለው የገንዘብ ሽልማት፤ ከፕሮፌሰር ጌታቸው በፊት የአባ ባሕርይን ጽሑፍ ወደ አማርኛ በተሳካ መልኩ ለመለሱት ለብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ደግሞ የክብር ዶክትሬት ሊያበረክቱላቸው በተገባ ነበር። 
በነገራችን ላይ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የአባ ባሕርይን መጽሐፍ ወደ አማርኛ የተረጎሙት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት የተሰጠው ኤርትራዊው አስመሮም ለገሰ ስለ ገዳ ምርምር ማድረግ ሳያስብ ነው። ጥላቻ ካልሆነ በስተቀር የአባ ባሕርይን መጽሐፍ ተጠቅሞ የዶክትሬት ማሟያ የጻፈውን አስመሮምን የክብር ዶክትሬት ሸልሞ ፕሮፌሰር ጌታቸውንና ብላታ መርስዓ ኀዘን ወልደ ቂርቆስን ለኦሮሞ ጥናት ባደረጉት አስተዋጽኦ የሚገባቸው ክብር የማይሰጡበት አንዳች ምክንያት የለም።

ኦነጋውያን አገር ለመመስረት ሲነሱ ስለ ኦሮሞ ባሕል ያስተጋቡትን እድሜን መሰረት ያደረገውን የቦረናና የባሬንቱ የገዳ አደረጃጀት ከስራ ስምሪት ጋር አዋደው ለታሪክ ያበረከቱት አባ ባሕሪ እንጂ አስመሮም ለገሰ አልነበረም። የገዳ ስርዓትን ለሁሉም የቦረናና ባሬንቱ ትውልድ ብቻ እድሜን መሠረት አድርጎ ኦሮሞ በሚስፋፋበት ወቅት እያንዳንዱ ቦረናና ባሬንቱ የያንንዳንዱን ቦረናና ባሬንቱ ዕጣ ፈንታ የሚወስንና ዕድል የሚሰጥ መሆኑን የመዘገቡት ብቸኛው ሰው የጋሞው አባ ባሕርይ እንጂ ሻዕብያው አስመሮም ለገሰ አልነበረም። ኦነጋውያን ባባሕርይ የተጻፈውንና በየ ስምንት አመቱ የሚካሄደውን የቦረናና ባሬንቱ ስልጣን ልውውጥ ታሪክ በማውሳት ፑልቶ ዲሞክራሲን ከኦሮሞ ወስዷል የሚሉትን ትርክታቸው ለማያሳየት በማጣቀሻነት የሚያቀርቡት ብቸኛው ምንጭ የአባ ባሕርይን ዜናሁ ለጋላ እንጂ የአስመሮምን የዲግሪ ማሟያ ወረቀት አይደለም። ሆኖም አስመሮም ለገሰ የአባ ባሕሪን የታሪክ ጥናት በእንግሊዝኛ ጽፎ የዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ ወረቀት ስላቀረበ አክብረው አባገዳነትና የክብር ዶክትሬት ሲሰጡ ዋናውን ጸሐፊ አባ ባሕሬን ግን ደብተራ እያሉ ማውገዝ እንጂ ስማቸውን እንኳ በክብር ማውሳት አይሹም።

ደብተራ እየተባሉ በኦነጋውያን ዘንድ የሚንቋሸሹት አባ ባሕሪ ግን ከኦነጋውያን ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች የተሻለ የሞያና የሕሊና ታማኒነት የነበራቸው ወደር የለሽ ምሁር ነበሩ። የትኛውም የኦነግ ዶክተርና ፕሮፌሰር ሲራቀቅ ቢውል እስከዛሬ ከአባ ባሕርይ ዜናሁ ለጋላ የተሻለ ጽሑፍ ስለ ኦሮሞ ታሪክ ሊያቀርብና ሊያገኝ አልቻለም። እንዴውም አንዳንዶቹ ለምሳሌ እንደ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን ያሉ የኦሮሞ ብሔርተኞች የአባ ባሕርይን መጽሐፍ እየኮነኑ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ የተረጎሙትን የአባ ባሕርይን መጽሐፍ ግን የቻሉትን ያህል ዝቀው በመተርጎም መጽሐፍ አሳትመው ቸብችበዋል። ለነገሩ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን ይህንን የሚያደርጉት አስተማሪዎቻቸው ፈረንጆቹ የኦሮሞን ታሪክ በሚመለከት ሲጽፉ የሚተነትኑት የተዋጣለቱን የአባ ባሕርይን መጽሐፍ ስለሆነ ብቻ ነው። ባጭሩ ኦነጋውያን ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች «ታሪካችን» የሚሉትን አጣመውና ፈጥረው ሲጽፉም እንኳ ደብተራ እያሉ ከሚጠሏቸው ከአባ ባሕርይ የተሻለ የታሪክ ምንጭ ግን የላቸውም፤ አያቀርቡምም።

እንደ እውነቱ ከሆነ አባ ባሕርይ እንኳን በሌጣዎች ኦነጋውያን አንደበት ግዕዝ ጠንቅቀው በሚያውቁ በኢትዮጵያ ልሒቃን ዘንድ እንኳ ለማጣጣል የማይመቹ ምሁር ናቸው። «ኦሮሚያ» የሚባለው ክልል መስተዳደር የኦሮሞ ታሪክና ባሕል ጉዳይ የሚያሳስበው ቢሆን ኖሮ የኦነግንና የተስፋየ ገብረአብን ፈጠራ የኦሮሞ ታሪክ አድርጎ በሌለ ታሪክ የጥላቻ ሐውልት ከሚያቆም በየቦታው የተቀበሩ የአብያተ ክርስቲያን ድርሳናትንና መዛግብቶችን ለማፈላለግና ለመፈተሽ ባጀት ቢመድብ ጥሩ ስራ በሰራ ነበር። በተስፋዬ ገብረ አብ ልብ ወለድ ላይ ተመስርቶ ኦሮምያ ክልል የሚባለው አካል ወጪውን ሸፍኖ በወያኔ ኮንትራክተሮች የተገነባበው የአኖሌ ሐውልት ላይ የባከነው ገንዘብ በየ አብያተ ክርስቲያናት ተቀብረው የሚገኙትን ድርሳናትና መዛግብቶች ለመፈተሽ ጥቅም ላይ ቢውል ኖሮ ስለ ኦሮሞ የተጻፈውን ታሪክ ይበልጥ የተሟላና የነጠረ እውቀት እንዲኖር ባገዘ ነበር።

ኦነጋውያን የሚያወግዙት ስለ ገዳና ኦሮሞ ታሪክ የሰማይ ያህል ርቀት ከፍ ብለው እንዲናገሩ ያስቻሏቸውን አባ ባሕርይን ብቻ ሳይሆን አባ ባሕርይን ያፈራችውን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጭምር ነው። ኦነጋውያኑ ግብዝ ባይሆኑ ኖሮ ዶክተርና ፕሮፌሰር የሚሆኑበትን የአባ ባሕርይ ታሪክ ጥናት ጠብቃ ለብርሃን ያበቃችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን ያውቁ ነበር። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አሁንም ልክ እንደ አባ ባሕርይ አይነት ገና ያልተመረመሩ ድርሳናትና መዛግብቶች አሏት። ከአባ ባሕርህይ ዜናሁ ለጋላና በኦሮሞ ታሪክ ዙሪያ ካበረከተቻቸው አስተዋጽኦዎች የምንማራቸው ቁምነገሮች ዋናው ከፍ ሲል ለመግለጽ የሞከርሁትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ማክበርን ነው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያፈራቻቸው አባ ባሕርይ የኦሮሞ ወታደራዊ ጭፍራ ጥንካሬ ተንትነው ሲያበቁ ባንጻሩ ደግሞ የኢትዮጵያን መንግሥት ድክመት ሲነቅፉ፣ እንደ እርሳቸው ካህን የሆኑ ሰዎችና ካህን ያልነበሩ ሰዎች ከውጊያ ለመሸሸ ሲሉ ካህንነትን መምረጣቸውን በመተቸት እውነታውን ሲያስቀምጡ፤ ኦሮሞን ጠላት ብለው አሳንሰው፣ የኢትዮጵያን መንግሥትና ወገኖቹን ወዳጅ ብለው አግዝፈው አልጻፉም። በእውነቱ እንደዚህ አይነቱ የኦሮሞ ታሪክ ፀሐፊ አባ ባሕርይ ሳይሆን አባ ኦሮሞ መባል በተገባቸው ነበር።