Sunday, June 12, 2016

በምስጢር የተቀዳ የኢሳያስ አፈወርቂ እስርቤቶች ቪዲዮ ላስጎበኛችሁ ጌታቸው ረዳ Getachew Reda ኢትዮ- ሰማይ አዘጋጅ (Editor- Ethio Semay)

በምስጢር የተቀዳ የኢሳያስ አፈወርቂ እስርቤቶች ቪዲዮ ላስጎበኛችሁ
ጌታቸው ረዳ
Getachew Reda ኢትዮ- ሰማይ አዘጋጅ (Editor- Ethio Semay)
ከጥቂት ቃናት በፊት ኦ! ሲሳይ አገና!ኦ! በሚል ርዕስ  በሰብአዊ መብት መጋፋት ወንጀል ከሚጠየቁት አንዱ የሆነ የኢሳያስ ሹመኛ የማነ ገብረአብ ኢሳት ጋር ከሲሳይ አገና ስላደረገለት ቃለ መጠይቅ የጻፍኩትን ትችት እንዳስነበብኩዋችሁ ይታወሳል። በወቅቱ የኤርትራን የውሸት ነፃነት ትግል የመሩ መሪዎች ማንነትና መነሻ ምክንያታቸው እዘረዝራለሁ ብየ ነበር። ሆኖም በእዛው አርዕስት እመለሳለሁ ያልኩት በዚህ አስደንጋጭ በሆነ የቪዲዮ ማስረጃ ፤ኤርትራዊያን ከ350 እስርቤቶች በላይ ታጉረው እየተገረፉና እየተሰቃዩ የሕሊና መቃወስ እንዴት እየደረሰባቸው እንዳለ በቀጥታ ከእስር ቡቶች በምስጢር የተቀዳውን ስዕለ ድምፅ/ቪዲዮ እንድታዩት አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘሁት ይህንን አቅርቤላችለሁ።

 በነገራችን ላይ ጣሊያኖች መጀመሪያ ወደ ኤርትራ ሲገቡ ‘ሌጋው ሽቦ’ እያሉ ከረኖች በአማርኛ ሲጨፍሩ እንድታደምጡ የለጠፍኩትን ቪዲዮ እንደወደዳችሁት ተስፋ አለኝ። አመርኛ፤ሃይለስላሴ አመጣብን የሚሉት ውሸት የሚንድ፤ የጥንት ቋንቋቸውም መኖሩ ማስረጃ ነው።

ወደ ጉዳያችን እንግባ። ጉንበት 7 የተባለው እጅግ አሳፋሪ የሆነ የኢሳያስ አፈወርቂ መልዕክተኛ ድርጅት፤ የኢሳያስ አፈወርቂ ዕድሜ ያርዝምልን ብላችሁ ኢትዮጵያዊያን ለኢሳያስ ለሻዕቢያ የፌርማ ድጋፍ አሰባስቡ ብሎ ኤርትራ ውስጥ ያሉ የሰው ልጆች ሁሉ ስቃይ እንዲራዘም የባንዳ መልዕክታቸው ለኢትዮጵያዊያን ዜጎች በዩ ቱብ እና በዘሐበሻ እና በመሳሰሉ የግንቦት 7 ሚዲያ ዘርፎች ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡ ይህንን የኢሳያስ ማንነትና የኤርትራ ነፃነት ያስከተለው መዘዝ እንድታዩት ለእነ ንአመን ዘለቀ እና ሲሳይ አገና ፤ ካሳ ከበደ፤ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ፤ብርሃኑ ነጋ፤….(ሁሉም የግንቦት 7 እና የኢሳያስ አዳማቂዎች) ተከታታይ መልስ ይኼውና ቪዲዮውን በጥሞና እምባችሁን እየተቆጣጠራችሁ (ደግ ይሁኑ፤ የኢትዮጵያ/የአማራ ሕዝብ ግፍና እርግማን ነው፤ እራሰቸው ያመጡት መዘዝ ነው ብላችሁ፤ ደስታ የሚሰማችሁ ካላችሁም ፤በእርጋታ ስሜታችሁን እየተቆጣጠራችሁ) በጥሞና ተመልከቱት።

ግንቦት 7 እና ኢሳት ለርካሽና ጊዜአዊ ፖለቲካ ሲሉ የምናውቃቸው ጸረ ኢትዮጵያ የሆኑ ኤርትራዊያን መሪዎች ወንጀላቸውን እየሸፈኑ በማቆነጃጀት የፕሮፓጋንዳ ተክለሰውነት እንደለመዱት ይቅረጹ፤ እኛ ደግሞ እነዚህ ወንጀለኞች በሰው ልጆች እያደረሱት ያለውን ሰቆቃ እና የሰው ልጆች የድረሱልን ጩኸትና ደምፅ አናስደምጣለን።ማን ለሰውልጅ መብትናና ፍትሕ እንደቆመ አንባቢና ተከታታይ ይፈርደናል። ተከታታይ መልሴም ይቀጥላል።

በታቸለኝ መጠን ከተርጉሙ ወደ መጨረሻ ወደ ታች የለጠፍኩትን የቪዲዮው የትግርኛ ዝግጅት ወደ አማርኛ ተርጉሜ አቅርቤላችሗለሁ (ለአማርኛ ተናጋሪዎች በመጠኑም ቢሆን ሃሳብ እንዲሰጣቸው አድርጌ ማለት ነው)። ቪዲዮው ከማቅረቤ በፊት፤ ይህ ከቪዲዮው የወሰድኩት “ኮርቴሎ” የሚባል የእስረኞች አስተኛኘት ዘዴ በፎቶ ተመልከቱት።  “ኮርቴሎ” ማለት ቦታ ስለሚጠብ፤አንዱ እራሱን ወደ ታች አንዱ ወደ ተቃራኒው የሚተኛበት ስልት ነው። ቆሞ የምታዩት እስረኛ፤ ቦታ ስለጠበበው፤ፈቃደኛ ሲገኝ እንቅልፉ ሲያበቃ ቦታው ለቆመው ይለቀቅለታል። በተራ፤በተራ ነው የሚተኙት ማለት ነው። ቪዲየው ስትመለከቱት የቀይ ሽብር እስር ቤት እና ሁኔታን ያስታውሳችል።
ፎቶው “ኮርቴሎበሚባል የእስረኞች አስተኛነኘት ዘዴ እስረኞች ተኝተው እንዳሉ የተነሳ ነው።
  
ዝግጅቱ የተላለፈው በተቃዋሚ ወገን የሆነ፤ “ራዲዮ ወጋሕታ” (ሳሊና ራዲዮ) ተብሎ የሚታወቅ፤ ድሮ ዜናው ከሱዳን ሲተላለፍ የኖረ፤ ዛሬ ግን ጣቢያው ወደ ኢትዮጵያ የተዛወረ የኤርትራ ተቃዋሚ ራዲዮ ጣቢያ ነው።

በመጨረሻም ስለ እራሴ አንድ ነገር ልበል። በታይፕ መጻፍ እጅግ አድካሚና አሰልቺ ሥራ ነው። ይህንን ሳደርግ፤ ጊዜ ኖሮኝ፤ እረፍት ጠልቼ ሳይሆን እንዲህ ያሉ ትችቶች የማቀርብላችሁ፤ ለአገሬ ቃል የገባሁላትን ትግል ዛሬም ያለመሰልቸት እረፍት እንቅልፍ ሳልል፤ በባንዳነት ተሰልፈው አገሬን ለማፍረስ የተሰለፉ አሳፋሪ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሚሰሩትን ድብቅና ይፋ ስራቸውን ለማጋለጥ በገባሁት ቃል ኪዳን እነሆ ሳይሰለቸኝ አንባቢን ማስተማሬን ቀጥየበታለሁ። መልካም ንባብ።

ቪዲዮውን ስትምለከቱት ዘገባው በትግርኛ ስለሆነ ምን እያለ እንደሆነ ግራ እንዳይገባችሁ፤ የተናጋሪው አጠቃላይ አባባል ጨምቄ ላቅርብ። ዘጋቢው እንዲህ ይላል።

በቪዲዮው ላይ የሚታዩት እስረኞች ኤርትራኖች ናቸው።350 እስር ቤቶች ውስጥ በአንደኛው እስር ቤት ውስጥ በሁለት ቅርንጫፍ እስርቤቶች ብቻ ለናሙና በምስጢር የተቀዳ ቪዲዮ ነው የምታዩት። ዓዲ አብዮቶ ይባላል። እዚህ እስር ቤት ውስጥ፤ በአንደኛው እስር ቤት ውስጥ ከ1000 እስርቤቶች በላይ ታጭቀው ይገኛሉ። 4 ሻለቃ የያዘ በታጠቀ ጠባቂ ሠራዊት ይጠበቃል። ጥብቅ እና መፈናፈኛ የሌለው “ገሃነም” ነው። የመግረፊያ ቦታው በጠብቅ ስለሚጠበቅ በምስጢራዊ ‘ቪዲዮ’ ማንሳት አልተቻለም።በዚህ እስር ቤት ውስጥ 4 ቅርንጫፎች አሉት ። ማይ ስርዋማይ ሑፃዓዲ ንፋስ እና ዓላ ይባላሉ።

እስር ቤቱ፤ካሁን በፊት በዟሪ እዝ ሥር ሲመራ የነበረ ሲሆን፤ ዛሬ ግን በቺፍ አስታፍ በጀኔራል ፍሊጶስ ወ/ዮሐንስ ነው የሚታዘዘው።በዚህ እስር ቤት ውስጥ 17 በጭካኔአቸው የታወቁ መርማሪዎች አሉ። ከመርማሪዎቹ መካከልም፤ ሜጀር ብርሃነ ከበደ (ወዲ ኸበደ)የፍሊጶስ ውሻ/አሽከር የሆነው ሚካል ይሳቅካሕሳይ ሓይለ፤ መሓሪ ወዲ ከኒሻ (የ1986 ታጋይ የነበረ)፤ ሃብተማርያም፤ ሙሴሱሌማንአምባሳጀር እና ወዘተ… ወዘተ.. ይገኙበታል።

ኢሳያስ አፈወርቂ የፍትህ ሰው በመምስል ሕዝብን ለትግል አስሰልፎ ነፃነት ከተገኘ በላ፤ኤርትራ ወደ ገሃነም ገፈተራት።ከት/ቤት እና ከሕክምና ፈንታ አሰቃቂ የሆኑ ከ350 በላይ የስቃይ አስርቤቶች በማስራት ዜጎች ከውጭ አገር እየጠለፈ፤ ከየመንገዱ፤ ከመኖርያ ቤቶች እና ከመንገድ እያነቀ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ እስርቤቶች እየገፈተረ መግረፍ ጀመረ።በቪዲዮው የምትመለከቱት እስርቤት፤ በኮንተይነር፤ ቤጉድጓዱ እና ሳሕል በረሃ… እየታጨቁ የሚሰቃዩ ዜጎችን አይጨምርም። እሱ ለብቻው ያዘለ ምስጢራዊ አሰቃቂ የእስር ሕይወት ነው። እነኚህ እስርቤቶችና ማጎርያ ቤቶች፤ የያዝቸው የዕድሜ ጣርያ ከጎልማሶች ጀምሮ እስከ ህጻናትና አረጋዊያን ሽማግሌዎች ይገኙባቸዋል።

ይህ በቪዲዮ በምስጢር ተቀድቶ በምስጢር የወጣ ዘገባ፤ በአገራዊ/ብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት በሚካሄድባቸው ማሰልጠኛ ቦታዎች ዙርያ ያሉ እስር ቤቶችን አይጨምርም። ጨቃኝና አሰቃቂ ማጎርያ እስር ቤቶች ለምሳሌ የህል ተሃድሶ፤ዒራ-ዒሮ፤አደርሰር፤ዊዓ፤ገልዓሎ፤ ዓዲ ንፋስ፤ማይ ስርዋ፤ ትራክ-ቢ፤ ወንጀል ምርመራ ወዘተ…ወዘተ የሚባሉ ከ350ዎቹ እስርበቶች ከሚጠቀሱ ናቸው። ዲክታቶር/ጨቛኙ ኢሳያስ አፈወርቂ የአገሪቱ ሞተር የሆነው ወጣት በየወታደራዊ ማሰልጠኛ በማጎርና ወደ ጦርነት በመክተት ያስፈጀው አልበቃ ብሎት፤ አሰቃቂ በሆኑ እስር ቤቶች ውስጥ በመክተት የወጣቶች ህይወት እንዲበላሽ አድርጓል።አስገራሚ የሚሆነው ደግሞ፤ በተለያዩ እስርቤት ማጎርያቤቶች በማጐር፤ ከአንድ የውጭ ባዕድ ወራሪ የሆነ ጠላት አንኳ የማትጠብቀው ጭካኔና ግፍ እያወረደበት ይገኛል።

እንግዳውስ፤ ከዚህ በታች ያለው ራዲዮ ወጋሕታ በምስጢር የቀዳቺውን  ዓዲ ዓብየቶ በሚባለው አስር ቤት ውስጥ ሾልካ በመግባት የፈጸመቺው ጋዜጣዊ  ጀብዱ እነሆ እናሳያችሁ።

እንዳ-ግፋፋት እንዳ-ኬዝ እንዳ-ጓላት በሚባሉ እስርቤት ክፍሎች እንጀምር። ይህ ዓዲ ዐብዮቶ እስር ቤት ነው። ይህች የምታይዋት እስር ቤት “ዐዲ አብየቶ” ትባላለች። ከ2002 ዓ.ም (ፈረንጅ) ጀምሮ ብዙ ኤርትራዊያን አስረኞች የሕሊና መታወክና አካል ጉዳት የደረሰባቸው በዚች እስር ቤት ውስጥ ነው።ከ350 በላይ ካሉት እስርቤቶች ውስጥ ግርፋትና ግፍ ከሚካሄድባቸው እስር ቤቶች አንዷ ነች።

ይህ የምታዩት እስረኛ በእግረሙቅ ሰንሰለት እየታሰረ ነው። ጎምበስ ብሎ ወተደራዊና ፋቲክ ለብሶ መግረፊያ የያዘው እና ሲቪል የለበሰው አሳሪዎች ናቸው። ይኼኛው እስረኛ ደግሞ እንደምታዩት እጁን በሃይለኛ ሰንሰለትና ሽቦ እየጠመዘዙ ሲያስሩት የሚያሳይ ነው።ይህ  ቅርንጫፍ “እንዳ ኬዝ” የሚባለው ክፍል ነው። ሁለት ትላልቅ እስርቤት አዳራሾች የያዘ ነው። በቀኝና በግራ የምታየዋቸው ክፍሎች በቀኝ በኩል “ካሜራ 1” በግራ ደግሞ፤ ካሜራ 2” ተብሎ የሚታወቁት ክፍሎች ናቸው ነው።

እንደምታዩት ሁለቱም በጠንካራ ብረት የተሰሩ መዝጊያዎች አሉዋቸው። በካሜራ 1 መዝጊያዎቹ አናት ላይ የተጻፈው መፈክር “አገሬ ምን ላድርግልሽ እንጂ ምን ታደረጊልኝያለሽ አትበል” የሚል መፈክር ይነበባል።ሆኖም በእነ ኢሳያስ ቤት ወርቃማ ማታለያ ቃላቶች ላእኵይ ስራቸው መጠቀሚያ እንጂ ከልባቸው የሚፈጽሙት ተግባር አይደለም።

ኢሳያስ ይህ ወርቃማ ቃላት እየተናገረና እንዲጻፍ እያስደረገ በጎን ግን በየጉድጓዱና በየኮንተይነር እያጎረ ዜጎችን የሚገድል ጨካኝ ሰው ነው።ለመሆኑ መፈክሩ እንዳለ ሆኖ፤ ወጣቱ  መፈክሩን ልከትል ቢልስ በየጉድጓድ እየታሰረ፤ የት ሆኖ ነው ለአገሩ መስራት የሚችለው?

ከበሩ መዝጊያ ስር የምታዩት ደግሞ ከውስጥ አዳራሽ ታጉረው መዝጊያ ተዘግቶባቸው ያሉት እስረኞች የምግብ ሳህን/ስልጣኒያ ሻንጣ ነው። ከካሜራ 1 ቀጥላ የምትገኘው በቴንዳ/ቡሊኬት የምታይዋት ትንሽ ቤት፤ ሕክምና ቤት ነች።ለስሙ ሕከምና ቤት ትሁን እንጂ፤ አስገራሚው ደግሞ “አስረኛው በገንዘቡ አዋጥቶ ያስራትና የሚታከምባት ክፍል ነች።

ከእስር ቤቱ ቪደዮ ጣልቃ በቪዲየው ውስጥ  ስርዓቱን ከድተው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ አንድ ኤርትራዊ ኮለኔል እንዲህ ሲናገሩ ይደመጣሉ።

“የኤርትራ ሕዝብ የማያውቀው፤ሰው የሚሰቃይባቸው ጉድጓዶችና ኮንተይነሮች ሕዝቡ እንዲያየው አይደረግም፤ አያውቀውም!~ስለዚህ አስደንጋጭ እና አስፈሪ ገሃነማዊ የኮንተይነር እስርቤት ማጎርያ ኤርትራ ሕዝብ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ምስጢሩ ተሸሽጎታል።” ይላሉ።

እነኚህ ከካሜራ 1  በር ተከፍቶላቸው ቀስ በቀስ በተራ እየወጡ የምታዩዋቸው አስረኞች ወደ ውጭ እየወጡ ነው። ከጥዋቱ 2 ሰዓት ነው (በፈረንጅ 8 ኤ-ኤም)። በአንድ ቡድን በ60 በ60 ሆነው ወደ ሽንት (እዳሪ) ለመውጣት እየተሰለፉ ናቸው። እንደምታዩዋቸው አብዛኛዎቹ ባዶ እግራቸው ሲሆኑ፤ የሱካር በሽታ ያላቸው ሕመምተኞች ግን ጫማ እንዲያደርጉ ይፈቀድላቸዋል። የምታዩዋቸው በርከክ ብለው ታጉረው የምታዩዋቸው አስረኞች ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ ወደ እዳሪ ወጥተው በተሰጠቸው ጥቂት ደቂቃ ማጠናቀቅ አለባቸው። አንዳንዴም ከተሰጠቻው ደቂቃ ባነሰ ፊሽካ ተነፍቶ ግማሽ መንገድ እንዳሉ ከተቀመጡበት ተሎ ተነስ ተብለው እንዲነሱ ይደረጋል።

ከፊት ለፊት የምትታየው ትንሽ ክፍል አስረኞች ጫማቸው የሚያስቀምጡባት ክፍል ነች። ወደ ላይ ስትመለከቱ፤ ከወደ ጎን የሚታየው  “ደብር” በአንድ ጊዜ 15 እስረኛ መደብደብ ማሰቃየት፤መመርመር የሚቻልበት ሰፊ ክፍል ይገኛል።   ወደ ደብሩ ስትወጡ የመጀመሪያው ክፍል “ምርመራ ክፍል” ይባላል።

ተመልካቾች፤ አሁን እየተመለሱ የምታዩዋቸው አስረኞች እዳሪ ወጥተው፤ የመጀመሪያዎቹ 60 አስረኞች እየተቆጠሩ   ወደ ክፍላቸው ሲመለሱ ነው።በተመሳሳይ አሁንም ወደ ቀኝ የምታዩዋቸው እስረኞች ከካሜራ 2  ወደ ውጭ ወጥተው እዳሪ እንዲወጡ ተፈቅዶላቸው እየተሰለፉ ነው።በሁለት ደቂቃ ውስጥ ቆሻሻቸውን ማጽዳት ካልቻሉ በምንም መንገድ ሌላ ደቂቃ  አይፈቀድላቸውም። አንዳንድ ጌዜም ሲያሰኛቸው ገና ሱሪህ አውልቀህ ቁጭ ስትል “ተነስ” ተብለህ የምትመለስበት አጋጣሚም አለ።

ከወደታች ከደብሩ እግርጌ የሚታዩ ክፍሎች በዜጎች ላይ ግፍ እየፈጸሙ የሚረኩት መርማሪዎች እንደ እነ መሓሪ፤ ሱሌማን፤ ሓብተማርያም፤ ሳሙኤል፤ ሳንዲያጎ፤ ሮሞዳን - ወዲ ዓኽርያ፤ ወዲ ምንሽ....ወዘተ የሚባሉ በጭካኔአቸው ያተወቁ አረሜኔዎች መኖርያ ክፍሎች ናቸው። ከላይ በዚህ ቪዲዮ የምታዩት ደብር 7 ክፍል የያዘ ነው። እንኚህ ክፍሎች ኡኡታ፤ልቅሶ፤ዋይታ…..የሚደመጥባቸው በደም የጨቀዩ  የመግረፊያ ክፍሎች ናቸው። 7ቱም “ገሃነማዊ ከፍሎች” ይባላሉ።

በነዚህ ክፍሎች ውስጥ አስረኛ የሚገረፉባቸውና የሚደበደቡባቸው ከውስጡ ቀጭን ብርት ሆኖ በጠንካራ ፕላስቲክ ጎማ  የተሰፋ ሽፋን ያለው ብትር ፤ እንዲሁም ‘ የቆላ ሰዎች የሚይዙዋቸው “ሻፎ  ብትሮች” (ጎባጣ ብትሮች) እና ዱላዎች፤ የተደረደሩበት እና በነዚህ መግረፊያዎች እየተገረፉ ትንፋሻቸው እያጠረባቸው ዘላለማዊ እንቅልፍ አሸልበው የሚሞቱ ብዙዎች ናቸው።

አሁን የምታዩዋቸው እየተመለሱ ያሉ አስረኞች ወደ ካሜራ 2 እየገቡ ናቸው። እደጅ የምታይዋቸው ጥቂት እስረኞች ደግሞ “ውሃ እንዲቀዱ የታዘዙ ሲሆኑ፤ ጥቂቶቹ ደግሞ ጀሮ ጠቢ ሆነው እስረኛ በመመስል ወሬ የሚያቀባብሉ ናቸው። በዚህ ክፍል ውስጥ የሕሊና ቀውስ ደርሶባቸው የተቀወሱና የፈዘዙ እስረኞች በብዛት አሉ።

እነኚህ የምታዩዋቸው ምግብ ሲታደሉ ነው። የሚመገቡት ምግብ በቀን ሁለት ጊዜ ሲሆን፤ ቁርስ ሳይበሉ፤ ምሳ እና  እራት ብቻ ነው የሚሰጣቸው። የምታዩት ወጥ በውሃ ያጥለቀለቀ ምሰር ወጥ ሲሆን፤ መለወጫ ወጥ ደግሞ “ሽሮ” ነው። ዳቦ ግን “ለማኘክ እጅግ የሚያስቸግር ወዲ ዓከር የሚባል የሟሽላ ዳቦ ነው።” ወዲ ዓከር ለማኘክ እጅግ ስለሚያስቸግር፤ መንጋጋን ያደክማል። የሚፈቀደው ደግሞ ሁለት ደረቅ ወዲ ዓከር ዳቦ ብቻ ነው የሚፈቀደው።

ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ “ኪሮስ” የሚባለው ወታደራዊ ሙዚቀኛ፤ ወደ ኢትዮጵያ በመሸሽ ስርዓቱን በመጋፈጥ ተደናቂነት ያተረፈ የኪነት ሰው ነው። እንዲህ ይላል።

‘አሉ የሚባሉ ጭካኔ የሚካሄድባቸው አስር ቤቶች በሙሉ ኖሬባቸዋለሁ። አውቃቸዋለሁ። ከ1999 ጀምሮ “ግፋ” (ገፈፋ) ሲካሄድ ትዝ ይለኛል፤ አስታውሳለሁ። ሰረጀቓ፤ በተበለ ቦታ ተወስደን ያገኘነው ግፍ ለማማን አስቸጋሪ ነው። እውን እኛ የዚህ አገር ዜጎች ነን? ወይስ እነዚህ እንዲህ የሚፈጽሙብን ሰዎች የዚህ አገር ዜጎች ናቸው? ምንድ ነው ነገሩ? ብለን ግራ ተጋብተን ማመን አቅቶን ነበር። እስካሁንም ይገርመኛል። ከዚያ ወደ ገለዓሎ ወሰዱን; ገላ ዓሎ ማለት ደግሞ፤ የሚያሰቅቅ ነው። ከሰረጀቓ በትላልቅ ካሚየን መኪኖች ነው የወሰዱን። ገላዐሎ ማለት ምድረበዳ ነውበቁሙ እሳት ነው። ጫማችን ነጠቁን፡ አውጡት ተባልን።

ጫማችን ነጠቁን። መሬቱ እንዴት እንርገጠው! እሳት መርገጥ ትችላለህ? እሳት እኮ ነው እንድንረግጥ ያደረጉን። ይለበልብሃል; ነብሰ ስጋህ ትወጣለች። ያቃጥላል። በዚያው ደግሞ “ቁጭ በል፤ ቁም” እየተባልን ነው ያለነው። እንዲህ እየተቃጠልን እያለን ፡፤ አረፍ በሉ ተብለን። ጸጉራችን እንድላጭ አንድ ምንላጭ  ለሁለት ሰብረን እረስ በርስ  እንድንለጫጭ ተደረገ። ሳስታውሰው ትርጉሙ አይገባኝም። ድንቁርና ነው ግፍ ነው? ምንድነው፤ ትርጉም አጣለታለሁ። ሰዎች ናቸው?  እንሰሳዎች ናቸው? እነዚህ ሰዎች ለመግለጽ መልስ የለኝም። ይላል “ኪሮስ”

ክቡራን ተመልካቾች፤ አሁን ወደ ሌላው ቅርንጫፍ “እንዳ ግፋፍ” ወደ እሚባለው ቀጥሎ ወዳለው እስር ቤት እንመለክት። ይህ አስርቤት ልክ አስቀድመን እነደተመለከትነው የ እንዳኬዝ ማሰርያ ክፍሎች ፤ይህም ሁለት ትላልቅ ካሜራዎች (እስር ቤት ክፍሎች) አሉት። እነዚህ በተራ ተሰልፈው ከማሰርያ ክፍላቸው እየወጡ የምታይዋቸው፤ እያንዳንዱ 2 ፤ ሁለት ወዲ ዓከር እየተቀበሉ ለምሳ ሲወጡ ነው። አሁን እዚህ በሰፊው የምታይዋቸው ከ1000 እስረኛ በላይ የሆኑ ናቸው። ኮብላለችል፤ መንቀሳቀሻ ሳትይዙ ተዘዋውራችል፤ … ወዘተ በሚል የታሰሩ ናቸው። ወደ ማዶ የምታዩዋቸው ከቅጥሩ ግቢ ወደ ውጭ ያሉት ቤቶች’ ሱቆች” ናቸው። እነዚህ ደግሞ የእስር ቤቶች ሃላፊዎች የሚያስተዳድሩዋቸው የራሳቸው ንግድ ቤቶች ናቸው። አስረኞች፤ ገንዘብ ካላቸው ከዚህ ሱቅ ነው እንዲገዙ የሚደረገው።ፍየሎችና በጎችም እዛው እያራቡ ይሸጥዋቸዋል። አብሮ ከፊት ከለፊቱ የምታዩት ኮንተይነር ደግሞ “እንዳ አዋልድ/ጛላት” (የሴቶች ማሰርያ”) የሚባለው ነው።

በዚህ በሴቶች አስርቤት ውስጥ መስጢራዊ ካሜራችን ሰርጎ ለመገባት አልቻለም። እንደሚነገረን ግን የአካል ጥቃት ፤ የወሲብ እና የሕሊና ቀውስ የደረሰባቸው እንዳሉ መረጃዎች አግኝተናል።

አንድ የኪነት ሰው ደግሞ በቪዲዮው ትዕይንት ጣልቃ እንዲህ ይላል።

“9 ብሔር አላት በምትባል ኤርትራ 300 የሚያክል አስር ቤቶች አሉዋት። 25 ዓመት ሙሉ 300 ሕክምና ፤300 ት/ቤቶች ሳይገነባ፤ 300 እስር ቤቶች መገንባቱ እጅግ አስገራሚ ነው።በየማሰልጠኛው፤ በየግመባሩ፤ በየፖሊስ ጣቢያው በየ ..በየ… የየራሱ መጎርያና ማሰቃያ ቤቶች አሉ።ይህ ዕብዶች የሚመሩት ሥርዐትና አገር ነው። የህ ስርዓት በሕዝብ ልሳን እና ቋንቋ እየተናገረ፤ ሕዝብ ለማጥፋት ሆን ብሎ የተመሰረተ ሥር ዓት ነው።” ይላል

አሁን ደግሞ ወደ ካሜራ 1 እንውሰዳችሁ። እነዚህ የምቷዩዋቸው እስረኞች፤ ገንዘብ በጥቁር ገበያ መንዝራችሗል፤ ለማምለጥ ስትል ተይዘሃል፤ መንግስት ነቅፈሃል፤ እየተባሉ የተያዙ ናቸው። በዚች ክፍል ወደ 500 የሚገመቱ እስረኞች አሉ።

እዚህ ክፍል የሚታሰሩ ሰዎች በጀኔራል ፍሊጶስ ትዕዛዝ አመካይነት የሚታሰሩ ናቸው።እዚህ ክፍል ዌሃ እጥረት ስላ፤ በሳምባ በሽታ፤ በ ኤች አይ ቪ ፤ በተቅማጥ፤የደም ግፊት፤ የሱካር በሽታ  ወዘተ..; የሚሰቃዩ ብዙ ናቸው።የሳምባ በሽተኞች፤  የኤች አይ ቪ በሽተኞችም ተደባልቀው እመካከላቸው ይገኛሉ።

የምታዩዋቸው እስረኞች፤ “ኮርቴሎ’ በሚባለው የአስተኛኘት ስልት ተኝተው ነው የምታዩዋቸው። ቦታ ጥበት ስላለ አንዱ እራሱ ወደ እግርጌ ሲያደርግ አንዱ ወደ ተቃራኒው አድርጐ ይተኛል። እንዲያም ሆኖው፤ ፤ ሰላማዊ እንቅልፍ አይተኙም። በር “ኳ….ኳ” ብሎ ተቆርቁሮ በተከፈተ ቁጥር በሌሊት ማን ይሆን ተረኛው ከመካከላችን ተወስዶ የሚገደል በሚል ስጋት በድንጋጤ ነው ሳይተኙ እየባነኑ ለተሊቱን የሚያሳልፉት። መዝጊያ ተንኳኩቶ ሳያድር፤ ሰላም ተኝተው ቢያድሩም፤ በቱሃን፤በቁንጫ እና በቅማል ምከንያት ነብሳቸው ዕረፍት ልታገኝ የማትችልበት-እስር-ቤት-ነች።

በግድግዳው ላይ ተለጥፈው የምታዩዋቸው መፈክሮች፤ በግድ እስረኛ እያዋጣ በገንዘቡ እየተገዛ ለፕሮፓጋንዳ መፈክር የሚለጠፍ አታላይ መፈክሮች ናቸው። ወርቃማ መፈክር እየተለጠፈ ስርዓቱ ግን አምራች የሆነው አፍላ ወጣት በእስር ቤት እየማሰነ፤ ህሊናው እንዲሟሽሽ፤ እንዲጠፋ፤ እንዲላሽቅ እያደረገ ነው።

 ባጭሩ ዓዲ አብዮቶ እስር ቤት 4 ሻለቃ የያዘ የታጠቀ ጠባቂ ሠራዊት የሚጠበቅ። ጥብቅ እና መፈናፈኛ የሌለው “ገሃነም” እስር ቤት በምስጢር የቀዳነው ጋዘጣዊ ግዳጃችንን ለመወጣት እንድታዩ አድርገናል። ይህ አስር ቤት እንዳያችሁት የመገረፊያ ክፍሎችና የሹማምነቱ ምርመራ ክፍሎች በጠብቅ ስለሚጠበቅ በምስጢራዊ ‘ቪዲዮ’ ማንሳት አልተቻለም።እንደተመለከታችሁት በዚህ እስር ቤት ውስጥ 4 ቅርንጫፎች አሉት ። ማይ ስርዋ፤ማይ ሑፃ፤ዓዲ ንፋስ እና ዓላ።

እስር ቤቱ፤በቺፍ አስታፍ በጀኔራል ፍሊጶስ ወ/ዮሐንስ የሚታዘዘው የሲኦል እስር ትና ማጎርያ ክፍሎች አሳይተናችል። እንደገለጽነው በዚህ እስር ቤት ውስጥ 17 በጭካኔአቸው የታወቁ መርማሪዎች አሉ። ከመርማሪዎቹ ውስጥ፤ ሜጀር ብርሃነ ከበደ (ወዲ ኸበደ)፤የፍሊጶስ ውሻ/አሽከር የሆነው ሚካል ይሳቅ፤ካሕሳይ ሓይለ፤ መሓሪ ወዲ ከኒሻ (የ1986 ታጋይ የነበረ)፤ ሃብተማርያም፤ ሙሴ፤ሱሌማን፤አምባሳጀር እና ወዘተ… ወዘተ.. ብዙ ግፍ ፈጻሚዎች ናቸው። በሰለባዎቻቸው የሚዘነጉ አይሆኑም።

ኢሳያስ አፈወርቂ የፍትህ ሰው በመምስል ሕዝብን ለትግል አስሰልፎ ነፃነት ከተገኘ በሗላ፤ኤርትራ ወደ ገሃነም ገፈተራት ስንል ይህነን የመሰለ ግፍ መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን ከዚህ የባሰ ግፍ ለሕዝብ ያልተገለጸ፤ይፋ ያልሆኑ ደብቅ የሆኑ ብዙ አሰቃቂ ግፎች አሉ።።ከት/ቤት እና ከሕክምና ፈንታ አሰቃቂ የሆኑ ከ350 በላይ የስቃይ አስርቤቶች በማስራት ዜጎች ከውጭ አገር እየጠለፈ፤ ከየመንገዱ፤ ከመኖርያ ቤቶች እና ከመንገድ እያነቀ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ እስርቤቶች እየገፈተረ የሚገርፈው ስርዓት  የዓለም ሕዝብ አንዲኮንነው እንጠይቃለን ። ለዘልዓለም ፍተሕ እና ሕዝብ ረግጦ በማስጨነቅ የሚኖር ስርዓት የለም። ግፈኞች ለወደፊቱ የፍትሕ ዳኝነት ይጠብቃቸዋል።”
ይላል።
ትርጉም ጌታቸው ረዳ
አመሰግናለሁ። አሁን ቪዲዮው እነሆ ተመለክቱት፤
Mistrawit camera wegahta ab bet maeserti adi abieto