Tuesday, January 28, 2020

ይቺ ልጅ ግን ጤነኛ ናት? ዳግማዊ ጉዱ ካሣ Ethiopian Semay


ይቺ ልጅ ግን ጤነኛ ናት?

ዳግማዊ ጉዱ ካሣ
Ethiopian Semay

ሆ! “ወደው አይስቁት” አሉ? ኤል ቲቪ የማን ነው ግን? ከጊዜ ዕጥረት የተነሣ ሁሉንም ቲቪዎች ማየት ለማንም ከባድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ አንድ ሰው አንድ ነው፡፡ አንዳንዴ በአንዴ ዘጠኝ ሰው መሆን እንደሚችል ይናገር እንደነበረው የቲቤቱ ባለሦስት ዐይን ቲዩስደይ ሎብሳንግ ራምፓ መሆን ያምረኛል፡፡ የሚዲያ መብዛት አማራጭን እንደማብዛቱ ጥሩ ሆኖ ሳለ ችግሩ አንድ ሰው በአንድ ጊዜ ብዙ መሆን አለመቻሉ ነው፡፡ በሾርኒ የብዙዎቻችንን አንገብጋቢ ችግር መጥቀሴ ነው፡፡


ወደተነሳሁበት ጉዳይ ከመግባቴ በፊት የዛሬ ደስታየን ልግለጽ፡፡ በአማራው አካባቢ የነበረው የዛሬው ሰላማዊ ሠልፍ ልዩ ነበር፤ ተስፋን ያለመልማል፡፡ እውነትም አማራው ላይመለስ አምርሮ ተነስቷል፡፡ ዱሮም አበያ በሬ ሲነሳ አይጣል ነው፡፡ መመለሻ የለውም፡፡ ልግመኛም ሰው ሲነሳበት እንደዚሁ ነው፡፡ እንግዲህ እነእንቶኔም ይወቁት፡፡ ምርጫቸውን ያስተካክሉ፡፡ ከረፈደ በኋላ ማቄን ጨርቄን አይሠራም፡፡ የዛሬው ምልክት ነው፡፡ ምኑ ታየና! በነገራችን ላይ በጎንደርና በደሴ እንዲሁም በአንዳንድ የአማራው አካባቢዎች ሰልፍ የተካሄደ አልመሰለኝም፡፡ለምን እንደሆነ ቢታወቅ ደስ ባለኝ፡፡ መለያየት ለጠላት በር ይከፍታልና አማሮች ሳትነጋገሩ እንኳን መግባባት አለባችሁ፡፡ ብዙ ስለተገፋችሁና ስለተበደላችሁ መጪው ጊዜ የእናንተም ነው፤መጪው ጊዜ ችላ ለተባሉ የሌሎች ዘውጎችም ጭምር ነው፡፡ እናም ተናበቡ፤ መለያየትና ቸልተኝነት ብዙ ዋጋ አስከፍሏችኋልና ከአሁን በኋላ ተጠንቀቁ፡፡ ትልቁ ትንሹን፣ ምሁሩ ማይሙን፣ ሀብታሙ ድሃውን፣ የደጋው የቆላውን፣ ታችኛው ላይኛውን …ያቅርበው፣ ያፍቅረው፣ አይናቀው፣ ያወያየው፣ ልባዊና ሥሙር ግንኙነት ይመሥርትና ሁሉም ለጋራ ነፃነት በጋራ ይታገል - ከሌሎቹ ተማሩ -ከእስራኤላውያን ተማሩ - ከተጋሩ ተማሩ፤ ንፋስ አይገባባቸውም፡፡ የግል ብልጽግናና ምንም ዓይነት ትምክህት ከስደትና ከውርደት አላዳናችሁም፤ የግል ኩራታችሁና ትዕቢታችሁ እትብታችሁ የተቀበረባትን አገራችሁን እንደናፈቃችሁ ልጆቻችሁም የሁለት አገር ሰዎች እንደሆኑ ከመኖር አላተረፋችሁም፤ አሁን እንኳን ተማሩ፡፡ ትልቅ ሆናችሁ ሳለ ለምን ለዚህ መሰል ሕይወት እንደተጋለጣችሁ ታውቃላችሁና ካሁን በኋላ አስተዋይነትንና የቀደመ የአያት የቅድመ አያት ጥበባችሁን መልሱ፡፡ መናናቅና በተናጠል መጓዝ ለበለጠ ጭቆናና ዕልቂት ይጋብዛልና ሁሉም በሞረሽ እየተጠራራ ጎጃም ሳይል፣ ወሎ ሳይል፣. ሸዋ ሳይል፣ ጎንደር ሳይል፣ ባሌ ሳይል… የጠነከረ የትግል ትስስር ይፍጠር፡፡ ድል ሳይገኝ የድል ባለቤትነት ክፍፍል ውስጥ መግባት፣ በጋራ እየተጨቆኑ ሳለ በሌለ የማንነት ልዩነት መኩራራትና እርስ በርስ መነቃቀፍ ለጠላት በርን በርግዶ መክፈት ነውና እንጠንቀቅ፡፡ የሚመከር አይደለም እንጂ መናናቅ ራሱ እንኳን የሚያምረው ሀገር ሲኖርና የናቂ ተናቂ ድርብ ናቂ በሌለበት ሁኔታ ነው፡፡ የምለው ይግባችሁ፡፡ “ቂጥ ከፍቶ ክንንብ ይቅርባችሁ” እያልኳችሁ ነው፡፡ በብኣዴንም ሆነ በአብን በኩል ጠላት ሠርጎ ሊገባ ስለሚችል ጠንቀቅ ማለት ተገቢ ነው፡፡ አማራ የቋንቋም ሆነ የሥነ ልቦና አጥር የሌለው በመሆኑ ለዚህ ዓይነቱ ጥቃት የተመቻቸ ነው፡፡ በነበረከትና በነጥንቅሹ ይብቃ፡፡ አማርኛ የተናገረና በዘዬህ ወግ የሚጠርቅ ሁሉ ወገንህ እየመሰለህ የሆድህን ስታዋየው ጠላት ሆኖና ለጠላት ወግኖ ሲያስበላህ ኖሯል - ሰውን ማመን በድርበቡ ነው፡፡ ባህልህን ባህሉ አድርጎ፣ ወግ ልማድህን ተላብሶ፣ በአምቻ ጋብቻ ተጣልፎ፣ በአበ ልጅነት ተጋምዶ፣ በዕቁቡና በፅዋ ማኅበሩ ተሳስሮ … እንደመዥገር ጉያህ ውስጥ ከተሰነቀረ በኋላ ጉድ ሲሰራህ የቆየውን አሰለጥ ሁላ አሁን ንቃበት፡፡

በሌላም በኩል ወያኔዎች የዘሩት እሾህና አሜከላ በደምብ ማፍራቱን ዛሬ ተረዳን፡፡ ከካናዳና ከስዊድን ስንዴና ሳልቫጅ እየተላከ ነጩ ጥቁሩን ከርሀብና ከርዛት እንዳላዳነ የከበደ ልጅ በጉርሜሣ ልጅ ታግታ የስንሻው ባለቤት ወ/ሮ ብርጣሉ ፊቷን ስትነጭና የአለምነሽ ጓዴ ባል አቶ አገሩ አበረ አለወጉ ሙሾ ሲያወርድ የባጫ ወርዶፋ ሚስት ሻሽቱ ጫልጪሣ ከነቤተሰቧ ማዘኗን በሰልፍ አለመግለጹዋ፣ የሸዋርካብሽና የሞላልኝ ልጅ ለአብረኸትና ለሐጎስ ባዕድ ሆና እነማንጠግቦሽና ጓንጉል “ልጆቻችንን አምጡ!” ብለው ሲጮሁ ለድጋፍ አለመውጣታቸው… ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን አያቀባብርም፡፡ በሰውነታችን ብቻ መተዛዘን ነበረብን፡፡ ኢትዮያዊነቱ ቀርቶ የአንድ አምላክ ልጆች መሆናችን ብቻውን ለመተዛዘን በቂያችን ነበር፡፡ ትልቅ መረግምት በኢትዮጵያ ላይ መውረዱን ዛሬ ከምንጊዜውም በላይ ተረድቻለሁ፡፡ ደግነቱ ይህም ሁሉ ያልፋል፡፡ ወያኔን ለጊዜውም ቢሆን ደስ ይበላት! የርሷ የቤት ሥራ በደምብ ሠርቷል፡፡ ይህን ነቀርሣ ከሥሩ ነቅሎ ለመጣል ብዘዙ መስዋዕትነት ይጠብቀናል፡፡ አይዞን! ለአንድዬ ቀላል ነው፡፡

“ንግባኢኬ ሃበ ጥንተ ነገር” ይላል ቅዳሤ ማርያም - እኔም ወደ ቀደመው ነገሬ ተመለስኩ፡፡ አልፎ አልፎ ግሩም ዝግጅቶች እንዳሉት ባልክድም ከኦ ኤም ኤን ቀጥሎ ከሚያስጨንቁኝ ጣቢያዎች አንዱ ኤል ቲቪ ነው፡፡ የአንዲት ጦጣ ትሁን ዝንጀሮ ሴት ልጅ ዝግጅት ግን እጅግ ያሳስበኛል፡፡ ጦጣ ያልኳት ወልጄ ስለጨረስኩ ነውና ይቅርታችሁን፡፡ ወልዶ የጨረሰ ሰው እውነትን ነው መናገር ያለበት፡፡ እርግጥ ነው እርሷ ስለውበቷ የምትለው ከኔና ከብዙዎች ዕይታ በተቃራኒ ነው፡፡ “የልብን ተናግሮ የምን ጨዋታ” እንዳትሉኝ እንጂ እንዲህ የምለው እንኳን ለጨዋታ ያህል ነው፡፡ ነገሩ ያለው ከውጫዊው የሰውነት ውበት አይደለም፡፡ እርሱ እንዲያውም ምንም ማለት አይደለም፡፡ የሚበልጠው ውስጣዊው ውበት ነው፡፡ እንጂ የዚያች ልጅ ፀጉር ምን ሆነ ምን፣ የዚያች ልጅ ፊት የፈረስ መሰለ የቀጭኔ ታጥቦ አይጠጣምና ስለርሱ ማውራት እኔን ጨምሮ ጊዜን በከንቱ ማባከንና ንዴትን ባልተገባ መንገድ ለማስተንፈስ መሞከር ነው፡፡ አዎ፣ ለወደፊት ከመልክና ከሰውነት ሳይሆን ከሃሳብና ከአስተሳሰብ መንገድ ጋር ብቻ እንጋፈጥ፡፡ በሃሳብ ማሸነፍ ሲያቅተን ከመነሻችን ጋር ከማይያያዙ ነገሮች ጋር በመታገል ኃይላችንንና ጊዜያችንን ገንዘባችንንም በከንቱ አንጨርስ፡፡ እኔን ጨምሮ፡፡ ምክር ከየትም ይምጣ ጥቅሙ ለሁሉም ነውና፡፡

ያቺ ልጅ ሁለት ዝግጅቶች አሏት፡፡ አንዱ የምትሽቆጠቆለት የአክራሪ ኦሮሞዎች ዝግጅት ነው - የቆመችለት ዓላማ ይመስላል፡፡ ሁለተኛው ከርሷ ብሶ በዐይኗ መቀመጫ (በዐይኗ ቂጥ ለማለት አፍሬ ነው) አዎ፣ በዐይኗ ቂጥ የጎሪጥ እያየች የምትጠይቃቸው የአማራ እንግዶችን ወይም አፍቃሬ አማራዎችን የምታቀርብበት ዝግጅት ነው፡፡ ይህች ልጅ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርም ሆነ ዕውቀት፣ ልምድም ሆነ ችሎታ የላትም፡፡ መጠየቅ የቻለ ሁሉ፣ አንዳች ደካማ ጎን ያገኘ ሲመስለው ተጠያቂን ማፋጠጥ የቻለ ሁሉ ጋዜጠኛ ነው ማለት እንዳልሆነ መረዳት ተገቢ ነው፡፡

ጋዜጠኝነት ሙያ እንጂ ማንም እየገባ እንደዚያች ልጅ የሚጨመላለቅበት የስዶች መድረክ አይደለም፡፡ እርግጥ ነው - አንድ ሰው ኮሌጅ ወይም ዩኒቨርስቲ ሳይገባ በግሉ በማንበብና ሰውን በመጠየቅ፣ ሚዲያዎችን በመከታተልና ለሙያው ልዩ ትኩረት በመስጠት የጋዜጠኝነትን ሙያና ክሂሎት ከመደበኛ ትምህርት ቤት ውጪ በኢ-መደበኛ ትምህርት ሊያገኝና አንቱ የተባለ ጋዜጠኛ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁሉ ነገር በግድ በትምህርት ቤት ይገኝ ማለት ስህተትና የመደበኛ ትምህርትን አባትና እናት መካድ ነው፤ ዲግሪ ሳይጀመር እኮ ማኅበረሰብ ነበር፡፡ ዋናው ጉዳይ መስሎ ሳይሆን ሆኖ መገኘት ነው፡፡ እንዲህም ሲሆን የሙያውን ሥነ ምግባርም በዋናነት ማስታወስ ይገባል፡፡ ምሣሌ ልሰጥህ እችላለሁ - በሥነ ጽሑፍ ሙያ ስንትና ስንት ዲግሪ ይዘው አንድም አጭር ልቦለድ ያልጻፉ ምሁራን የመኖራቸውን ያህል አንድም የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ቤት ደጃፍ ሳይረግጡ በግል ጥረታቸውና ተፈጥሯዊ ተሰጥዖዋቸው ብቻ እጅግ የሚመስጥና ሁሉንም የሥነ ጽሑፍ መሥፈርት የሚያሟላ ዘመን ተሻጋሪ ረጂም ልቦለድ የሚጽፉ የሌላ ሙያ ባለቤቶች አሉ - ለአብነት ዶክተር ምሕረት ደበበ፤ ጓደኛየና አብሮ አደጌ ጎበና ዳንኤል፡፡ ካልጻፉት ደግሞ እኔ ራሴ፡፡ እ… ጓደኞቼ እነ እንትና - ስማቸውን ምን አስጠራኝ፡፡
ጋዜጠኝነት እንደማንኛውም የዕውቀትና የሙያ ዘርፍ ሁሉ ክብር አለው፡፡ ማንም በልጣጣና የዘረኝነት ልምሻ ያሽመደመደው ወልጋዳ ሁላ ዘው ብሎ እየገባ የሚያንቧችርበት የከተማ አውቶቡስ አይደለም፡፡ ከልካይ የሌለባቸው ሙያዎች በጣም ያሳዝኑኛል፡፡ ተቆጣጣሪ የሌለባቸው ሙያዎች አንጀቴን ይበሉታል፡፡ በህክምናው ቢሆን ይህን ያህል ልቅ ባልሆነ - የአሁኑን እንጃ እንጂ ቀደም ሲል ጥብቅ ቁጥጥር ነበር፡፡ ጋዜጠኝነት እንደልመናና ሴተኛ አዳሪነት ሁሉ እንደዚያች ልጅ ያለ በሁሉም ረገድ አስቀያሚ ሰው እየገባ አንዱን በመሽቆጥቆጥና በመለማመጥ ሌላውን ግን በመሳደብና በማላገጥ ሲቀርብበት ማየት የቲቪውን ባለቤት አልባነትና የሙያ ሥነ ምግባርን መውደቅ በግልጽ ያመለክታል፡፡ ቲቪው እርግጥ ነው የማን እንደሆነና ለነማን እንደሚያሸረግድ አውቃለሁ፡፡ ይህ ቲቪ የዝምባብዌውን ሚሌ-ኮሊንስ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በኢትዮጵያ ተክቶ እንደሚንቀሳቀሰው የጃዋሩ ኦኤምኤን የሚቆጠር በተለይ በአማራና በኦሮሞ መካከል እንክርዳድ እየዘራ የሚገኝ አደገኛ ቲቪ ነው፡፡ መንግሥት ቢኖር ኖሮ መከልከል ካለባቸው ቲቪዎች ሁለቱ እነዚህ ናቸው - የጃዋር ኦኤምኤንና የዚያችን የመርገምት ፍሬ ቀጫጫ ሴት ልጅ መርዝ የሚረጭ ቲቪ፡፡

በአንድ በኩል ችግሩ ያለው ከነእስክንድርም ነው፡፡ ምን ሊያተርፉ ወደዚያ ጣቢያ ሄደው ለውርደትና ለትዝብት እንደሚዳረጉ አይገባኝም፡፡ ባለጌን ባለጌ ብሎ ጅባት ብሎ እንደመተው አጉል ዴሞክራሲያዊነት ዋጋ እንደሚያስከፍል እየተረዳን ነው፡፡ እንዴ! አማራ ነኝ እንዲላት የማታደርገው ጥረት እኮ የላትም፡፡ የአማራን ብሔርተኝነት አምኖ እንዲቀበላት ያልወጣችበት ቆጥ አልነበረም፡፡ አንዴ በፀጉሩ፣ አንዴ በብሔሩ... በዚያ ሾጣጣ ነገረኛ አገጯ እያሸሞረች ስትጎነትለው ሳይ እኔ ራሴም ተናደድኩ፡፡ በነገራችን ላይ ጥሎብኝ ከሰውነት ቅርጽ ተነስቼ ሰውን ማንበብ እችላለሁ - የፈለግኸውን በለኝ፡፡ ግዴለኝም፡፡ እናም ስለዚያች ልጅ ጠባይ ልንገርህ - ስማ፤ ልጂቱ እጅግ ሲበዛ ነገረኛ ናት፡፡ ነገርን ማዞርና በተንኮል መረዳት ዋና ሥራዋ ነው፡፡ ከንፈረ ስስና አገጨ-ሾጣጣን ሰው ተጠንቀቁ! የፊት ቅርጹዋ በአጠቃላይ የሚናገረው ክፉ ሰው መሆኗን ነው - በርሷ ሰበብ ሌሎችም እንደሚነኩ ይገባኛል፤ ግን እውነትን መናገር ኃጢኣትም ሆነ ወንጀል አይደለምና በተቻለ መጠን ይህን የተፈጥሮ ዝማሜ በጥበብና በአስተውሎት ለማረቅ ከመሞከር ውጪ መካድ አያዋጣም፡፡ ማሻሻል ይቻላል፤ የኮከብን ጥመት፣ የክፍልን ጽላሎት በዕውቀትና በጥበብ ለማስተካከል መሞከር ብዙ ከባድ አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ችግርን በቶሎና ሰውን ሳይጎዱ መረዳት ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ቀልድ የሚመስላቸው ብዙዎች ናቸው - ግን ወሳኝ ናቸው፡፡ ስንትና ስንት ጓደኝነቶች፣ ትዳሮች፣ መልካም ግንኙነቶች፣የሃይማኖትና የፖለቲካ አመራሮች፣ ወዘተ. አምረው ተጀምረው ሲያበቁ ብዙም ሳይጓዙ የሚጨነግፉት በነዚህ ምክንያቶች ጭምርም ነው፡፡ “ያንን ሰው ሳየው ይቀፈኛል!” “ይቸን ሴት ሳያት ውስጤን አንዳች ነገር ይወረኛል!” ብለህ አታውቅም? አዎ፣ ነገሩ እንደዚያ ነው፡፡ የአንድ ሰው ስድስተኛ ስሜት እያጎነቆለ ሲመጣ ብዙ የማንጠብቃቸው ክስተቶች ብቅ ብቅ ማለት ይጀምራሉ፡፡

ያች ዐውሬ ልጅ ሰውን በማናደድ የምትደሰት፣ ጭራ በማስበቀል እንደጌታዋ እንደጃዋር ሃሤትን የምታደርግ ደምበኛ የሴት ጋንኤል ናት፡፡ ስለዚህ እባካችሁ የወዲህኛዎቹ ወገኖች ወደዚያ ቤት መሄድን ለጊዜው ተውት፤ መሣቂያና መሣለቂያ አትሁኑ፡፡ “ያልወለድኩት ልጅ ቢለኝ አባባ አለኝ አፌን ዳባ ዳባ” ሲባል አልሰማችሁም? እናሳ! ዘመድ የማይሆንህን ሰው ብትለማመጠው ልቡ አንዴውኑ ሸፍቷልና ላትመልሰው ምን አለፋህ?

ተናድጄ ስለጻፍኩ ውድ የዘወትር አንበቢዎቼን ይቅርታ መጠየቅ አለብኝና ይቅርታ፡፡ በብሂላችን “ስትናደድ ልጅህን አትቅጣ፤ አንደበትህንም ቆልፋት” ይባል ነበር ዱሮ - ያቺ ድውይ ዘረኛ ተሳስታ አሳሳተችኝ፡፡ ግን ግን ማን ትሆን እንዲህ የወረድኩባት? ስሟን ረሳሁት፡፡ “ባለጌና ዋንጫ ከወዳፉ ይሰፋል” የሚባለው እውነት እኮ ነው እናንተዬ፡፡ በነገራችን ላይ ባለጌና ዋልጌ ሰዎች በዚህ መልክ የሰው መነጋገሪያ ሲሆኑ ከመናደድ ይልቅ ደስ እንደሚላቸው ታውቃላችሁ? ለምን መሰላችሁ - በመልካም ነገር ሊታወቁ እንደማይችሉ ውስጣቸው ይነግራቸዋል፤ ተፈጥሯቸው ከX እና Y ጋር የተያያዘ Chromosomatic የDNA ጥመት እንዳለበት እኛም እነሱም አሣምረን እናውቃለን፡፡ የሚገርማችሁ የተፈጥሮ ችግር ያለባቸው ጎደሎ ሰዎች የላይኞቹን ወንበሮች እየያዙ ነው ክፉኛ የተቸገርነው፤ እንደነዚህ ያለ ብልሹ ሰው ሥልጣን ላይ ሲወጣ ደግሞ ደህነኞቹ ይፈሩና ይደበቃሉ፡፡ ያኔ እነሱ ሁሉን ዐዋቂ፣ ሁሉን አድራጊ ይሆኑና በምሥኪኑ ሕዝብ ላይ እንደልባቸው ይዘባነናሉ (አትክልተኛ ሞልቶ አትክልተኛ የሚሆኑት፣ ፓይለት ሞልቶ ፓይለት የሚሆኑት፣ ሹፌር ሳይጠፋ ዘዋሪ የሚሆኑት፣ ሀኪም እያለ ሀኪም የሚሆኑት … ይሄው ሁሉን የመሆን አባዜያቸው ስለሚያንቀዠቅዣቸው እንጂ አርአያ ሆነው ሰውን ለማነቃቃት ባላቸው ስሜት እንዳይመስላችሁ - ይሄ አቢይ የሚሉት ከውካዋ ልጅ ግን እንዴት ይቀየመኝ!)፡፡ ስለዚህ ለነጃዋርና እህቱ ቀጮ ዋናው ነገር በሰዎች መታወቁና የቡና ማጣጫ መሆኑ እንጂ የሚነሱበት ጉዳይ ክፉ ሆነ ደግ አያሳስባቸውም፡፡ ኧረ እንዲያውም በክፉ ሥራቸው ይኮሩበታል! አንዳንድ ጥያቄ ሲጠየቅ የተገረመ ወይም ቀድሞ የሚያውቀው ተራ ነገር እንደሆነ ለማስመሰል የትከሻና የፊት እንቅስቃሴው ሥልት እያጣበት  እንዴት እንደሚፍነከነክ ጃዋርን ታዩት የለም እንዴ? - መፍነክነክ ራሱ እስኪከዳው ድረስ ማለት ነው፤ በሉ ቻው፡፡ ዛሬስ ብዙ ጨቀጨቅኋችሁ መሰለኝ፡፡ ይቅርታ፡፡