Thursday, June 22, 2023

ለትውስታችሁ አማራውን ለማግለል አብይ የሄደበት ግልጽ ስበሰባ ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) 6/22/2023


ለትውስታችሁ አማራውን ለማግለል አብይ የሄደበት ግልጽ ስበሰባ 

ጌታቸው ረዳ

(Ethiopian Semay)

6/22/2023

ሰነዱ የተገኘው ከታሪክ ተመራማሪና የምጣኔ ሃብት ምሁር አቻምየለህ ታምሩ ነው።

ይህ ሰነድ እንድታስታውሱት በሚል ነው፤ በማሕደራችሁ ለታሪክ ማስታወሻ አስቀምጡት።

አፓርታይዱ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትክለኛ ገጽታ!

(አቻምየለህ ታምሩ)

የአገሪቱ ከፍተኛው ባለሥልጣን ጠቅላይ ሚንስትሩ የተገኘበት ይህ መድረክ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ከሚወሰንባቸው መድረኮች አንዱ ነው። በዚህ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ከሚወሰንባቸው መድረኮች አንዱ በሆነው «የለውጥ» ጉባኤ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰባ ከመቶ በላይ የሚሆነውን ከሚሸፍኑት ሁለት ነገዶች አንዱ የሆነው አማራ ግን አልተወከለም ወይንም ባለጊዜዎቹ እንዲወከል አልፈለጉም ። ይህ በአጋጣሚ የተደረገ አይደለም! ይህ አማራን ማግለል የኢትዮጵያ ፖለቲካ ትክክለኛ ገጽታ ነው። ላለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት የኖርነው ልክ በፎቶው ላይ እንደሚታየው በኢትዮጵያ እጣ ፈንታ እንዳንሳተፍ ተቀሟዊ በሆነ መልኩ ተገለንና መንግሥታዊ እግድ ተጥሎብን ነው። የኢትዮጵያ ፖለቲካ የአፓርታይድ ፖለቲካ ስለመሆኑ ከዚህ በላይ ማሳያ ሊቀርብ አይችልም!

«ለውጡን እናግዝ» የሚሉን ሰዎች እናግዝ እያሉን ያለው ይህንን አማራ መቶ በመቶ ከጨዋታ ውጭ የተደረገበትን ሴራ ነው። ተጀመረ የሚሉን የለውጥ ሂደት እንዳይደናቀፍ አግዙ እየተባልን ያለነው አማራን እንዲህ እያገለሉና እንዲገለል እያደረጉ ከአማራ የጸዳ አካባቢ ለመመስረት እንደተንቀሳቀሱ ሁሉ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከአማራ ለማጽዳት እያደረጉት ያለውን የአፓርታይድ ተግባር ነው።

ከአማራው መካከል የወጡ የሌሎች ጉዳይ ፈጻሚዎችም በውጭም በውስጥም ሆነው ለአማራ አንዳች ነገር ጠብ ያለለት ይመስል «ለውጡን እናግዝ» በማለት ከአማራ አንጻር የቆሙ የአፓርታይድ አራማጆችን እያገለገሉ ያሉት አማራው ተጠናክሮ እንዳይደራጅ ማደንዘዝንና በላዩ ላይ የተጫነውም የአፓራይድ አገዛዝ አማራው መቶ በመቶ እ እንዲህ እያገለለ የሚያካሂደውን ፋሽዝም እንደለውጥ ቆጥረውት ነው።

እስቲ የተጀመረው የለውጥ ሂደት እንዳይደናቀድ አግዙ ስትሉ የምትውሉ ለአማራው የትኛውን ነው ለውጡ? ከታች የምታዩዋቸው ስድስቱ ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከዛሬ ሀያ ሰባት ዓመታት በፊት በሐምሌ 1983 ዓ.ም. በወያኔ፣ በሻዕብያና ኦነግ አጋፋሪነት አማራን አግልለው በኢትዮጵያ ምድር ሰላምንም ዲሞክራሲንም ለመቅበር በአፍሪካ አዳራሽ በተካሄደው «የሰላምና ዲሞክራሲ» ኮንፍረንስ በአንድም በሌላው መንገድ ተሳታፊዎች ነበሩ አልያም ወኪሎቻቸው ተሳትፈዋል። ከሀያ ሰባት ዓመታት በፊት ዋና ተዋናይ የነበረው ሻዕብያ በዚህ መድረክ ባይገኝም በኢትዮጵያ ጉዳይ ወሳኝ ሁኖ «ጠረጴዋው» ላይ ግን ዛሬም አለ። ዶክተር ብርሃኑም ቢሆን ከሀያ ሰባት ዓመታት በፊት የሽግግር መንግሥት ተብዮው ኮንፍረንስ ተሳታፊና ታዛቢ የነበረው የጉራጌ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ግንባር አባል ነበር።

ዛሬ የጎደለው መለስ ዜናዊ በአካል አለመኖሩና ከ27 ዓመታት በፊት በአምስት ድርጅቶች የተወከለው ኦሮሞ ዛሬ በሶስት ድርጅቶች መወከሉ ብቻ ነው። ሰዎቹ ኢትዮጵያን ቢወክሎ ጥያቄ ባልተነሳባቸው ነበር። ሆኖም ሰዎቹ የወከሉት ኢትዮጵያን ሳይሆን ነገዳቸውን ብቻ ነውና የተቀረው ነገድ በነሱ ውስጥ ራሱን ባያይ አይፈረድበትም።

ዛሬም፣ ከሀያ ሰባት ዓመታት በፊትም ሁለት ተመሳሳይ ነገሮች ይታያሉ። አንዱ መለስ በአካል ባይኖርም የራዕዩን ተሸካሚዎች መድረኩ ከጫፍ እስከጫፍ መሙላታቸው ነው። ሁለተኛው ደግሞ ዛሬም ከሀያ ሰባት ዓመታት በፊትም አማራው በመድረኩ አለመኖሩ ነው። ከሀያ ሰባት ዓመታት በፊት በአማራ ጥላቻ የናወዙት እነዚህ ስድስቱ ግለሰቦች ወይንም ወኪሎቻቸው አማራ እንዳይገኝ አድርገው ከፕሮግራማቸው በማውጣጣት ሕገ መንግሥት ያሉትን የቅሚያና የግድያ ደንብ አዘጋጅተው ነበር። እነሆ ዛሬ ከ27 ዓመታት በኋላ ስድስቱም የ27 ዓመታት የሥራ ውጤታቸውን ለመመረቅ በመድረክ ተገናኝተው ሽር ብትን እያሉ ናቸው።

እነዚህ ስድስቱ ዛሬ ከሀያ ሰባት ዓመታት በኋላ ለውጥ፣ ለውጥ እያሉ ቢሰብኩም የተለየ ውጤት እናመጣለብ ብለው እያታከቱን ያለው ግን አንዳች የመዋቅርና የሕግ ለውጥ ሳያካሂዱ በተመሳሳ መንገድ [በአብዮታዊ ዲሞክራሲ፣ በጎሳ ፌድራሊዝም፣ ሕጋዊነት በሌለው ሕገ መንግሥት፣ ወዘተ] በመሄድ የመንፈስ አባታቸውን የመለስ ዜናዊን ራዕይ እያስቀጠሉ ነው። ዛሬም ችግሩን በፈጠረው አስተሳሰብ እየተመሩ፣ አገዛዙ የተዋቀረበት ርዕዮተ ዓለም ሳይቀይቱና የመዋቅርና የአደረጃጀት ለውጥ ሳያደርጉ የተለየ ውጤት ሊያመጡና አገራዊ ተቋማትን ሊፈጥሩ ያስባሉ!

ደግነቱ ዛሬ ትናንት አይደለም! «ለውጡን እናግዝ» ብለው የተኮለኮሉት የኛዎቹ አደንዛኞችም ሆኑ ባለጉዳዮቻቸው እነ ዐቢይ ባይፈልጉትም የአፓርያድ አገዛዝ የወለደው አማራው ግን በሚገርም ፍጥነት ራሱን ለመታደግ በአንድ ላይ ተነስቷል፡፡ ካሁን በኋላ እንደ ሰማንያ ሶስቱ የፋሲካ ዶሮ ለመሆን ለዳግም እርድ የሚዘጋጅ አማራ የለም! የአገሩና የመንግሥት ባለቤት እስኪሆን ድረስ የጀመረውን የኅልውና ተጋድሎ ያለርሕራሔ ይቀጥላል::

Posted Ethiopian Semay – Source File –Achamyeleh Tamiru