Monday, October 11, 2010

ሀቁን መፈለግ ወይስ ሀቁን መናገር-….(By Dr.Fekadu Bekele)

ይድረስ ለጎጠኛው መምህር (አማርኛ) $25.00 እና ሓይካማ (ትግርኛ) $15.00 መጽሐፌን ለመግዛት ዕድሉን ያላገኛሁ ካላችሁ በሚከተለው አድራሻ ደውላችሁ ማግኘት ትችላላችሁ Telephone (408) 561 4836 (Getachew Reda P.O.Box 2219 San Jose, CA 95109) getachre@aol.com http://www.ethiopiansemay.blogspot.com/ ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ ሀቁን መፈለግ ወይስ ሀቁን መናገር… በሚል ርዕስ ክፍል አንድ እና ክፍል ሁለት ሰፋ ያለ በተለይም 29 ገጽ ያካተተ ክፍል ሀለት ላይ በምሁሩ ላይ ያላቸው ብሶት/ትችት እና መፍትሄው በመጠቆም ያሰፈሩትን ሙሁራዊ ትንተና በተለያዩ ድረገፆች ተለጥፈዋል። በዚህ ብሎግ የሚቀርበው መላው ጽሑፋቸው ሳይሆን በኔ እይታ “ለሁሉም ዓይነት አንባቢ” በቀላሉ መረዳት የሚችሉ ዋና ዋና ብየ ያሰመርኩባቸው ገጾች ብቻ አንድለጥፋቸው ከዶክተር ፈቃዱ በቀለ ፈቃድ ጠይቄ ስላስፈቀድኩ እነሆ ልናስተውላቸው የሚገቡ ሃተታዎቻቸው በሃጽሮት አቅርቤአለሁ። እነሆ። በዶክተር ፈቃዱ በቀለ የቀረበ አገራችንንና የምሁራኑ ሚና ያቀረቡት ሰፊ ትንተና ምላሽ ያገኘ አይመስልም። ምሁራኑ ያልተሳተፉበት ምክንያት ምንይሆን? በሳቸው አንደበት እነሆ “ፕሮፌሰር ሀይለማርያም ሀቁን መናገር ብሎ በተከታታይ አምስት ጽሁፎች ካወጣ በኋላ እኔም እንደ አቅሚቲ ለዚህ የሚሆን መልስ ስጽፍ ውይይታችንና ክርክራችን በዚያው ተከታታይነት ባለው መልክ ይቀጥላል ብዬ ገምቼ ነበር። ፕሮፌሰር ሀይለማርያምና እኔ ብቻ ሳንሆን፣ ሌሎችም በመሳተፍ የውይይታችንና የክርክራችንን አድማስ ያሰፉታል የሚል ዕምነት ነበረኝ። ይሁንና ግን እንደገመትኩት ሁላችንም በውይይቱ ልንገፋበት አልቃጣንም። በኛ ኢትዮጵያውን ምሁራን ዘንድ አንድ እንደ ፈሊጥ የተያዘ የአሰራር ስልት አለ። ይኸውም አንድን አርዕስት እስከመጨረሻው ሳይገፋበትና መቋጠሪያ ሳያገኝ ወደ ሌላ አርዕስት በመሸጋገር የመጀመሪያው እንዲረሳ ማድረግ ነው። ሁለተኛ፣ እንደዚህ ዐይነት ህብረተሰብን የሚጠቅምና ለህብረተሰብ መገንቢያ የሚያገለግል አርዕስት ሲጻፍ፣ ሁለት ወይንም ሶስት ሰዎች ብቻ እንዲከራከሩበት መንገዱን ለእነሱ ብቻ በመልቀቅ ምሁራዊ ኃይል ሰፋ እንዳይልና አስተሳሰባችንም ጥልቀትና መሰረት እንዳይዝ በር መዝጋት እንደባህል ተወስዷል። በእዚህ ጸሀፊ ዕምነት፣ ከሚደርሱኝ ደብዳቤዎች እንደምረዳው ከሆነ ብዙ አዋቂዎች እንዳሉ ነው። እነዚህም ሆኑ ሌሎች ምሁራን ምንም የሚያስፈራቸው ነገር የለም። ብዕራቸውን በማንሳትና ሃሳባቸውን በመሰንዘር ሌሎችም ሆኑ እኔ የምንጽፈውን መፈተሸና ለፈተና ማቅረብ መቻል አለባቸው። አንድ አስተሳሰብ ተቀባይነት ከማግኘቱ በፊት መፈተን፣ መፈተሸና መመርመር አለበት። ይህ ፕላቶናዊ የአሰራረር ስልት ነው።” አዎ እሳቸው እንዳሉት አንድን አርዕስት እስከመጨረሻው ሳይገፋበትና መቋጠሪያ ሳያገኝ ወደ ሌላ አርዕስት በመሸጋገር የመጀመሪያው እንዲረሳ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካውን የሚመሩት ሰዎችም እንደዚሁ የያዙትን አጀንዳ እግቡ ሳያደርሱ ካንዱ ዋዳንዱ እየዘለሉ አንዱን ድርጅት አፍርሰው አንዱን በመገንባት የገነቡትን በማፈረስ ሌላ እንዳዲስ በመፍጠር ጥልቀት ያለው ጥናት ሳያደርጉ የጦጣ የዛፍ ዝለላ ጨዋታ ልምዳቸውም በሚቀርቡ ሕብረተሰባዊ/ፖለቲካዊ ክርክሮችም ዶክተሩ እንዳሉት አንዱን ክርክር መቛጫ ሳይደረግበት በእንጥልጥል መተው እንደ ባህል ተይዘዋል። ምሁሩን “ጥናቱን ይስጠው!መጥኔ ይስጠው! ከማለት ምን እንበል? ሀቁን መፈለግ ወይስ ሀቁን መናገር-….( ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ fekadubekele@gmx.de) ከዚህ በታች የቀረበው ሓተታ ከገጽ 20 እስከ 29 ብቻ ያለውን ነው። ጽሑፍ የቀረበው በፒ ዲ ኤፍ ፎርማት ስለነበር “በማይክሮሶፍት ወርድስ” ካልታቀፈ “ብሎግ” ላይ ሲለጠፍ ባንድነት የታቀፈው ጽሑፍ የመበታተን ስርዓት ሰለሚያሳይ ስለ ጥራቱ ይቅርታ እጠይቃለሁ። “የብሄረ-ሰብ ጭቆናና ኢትዮጵያ የብሄረ-ሰቦች እስር ቤት ነች የሚለው ጎልቶ በመውጣትብዙዎችን ሊያሳስት በቅቷል። በተጨማሪም ማርክሲዝምን እጅግ በጠባብ ጎኑ መመልከትና፣ በአውሮፓ ምድር ውስጥ ከማርክሲዝም አኳያ በተለያዩ መልኮች የተተነተኑትን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ አለማስገባት የትግሉን አቅጣጫ ሊወስን ችሏል። ሰፋ ላለ ምሁራዊ እንቅስቃሴ እንዳያመች በሩ የተዘጋ ነበር። ይህ ማለት ግን ምሁሮች አልነበሩም ማለት አይደለም። የኋላ ኋላ ደግሞ ጠቅላላው ትግል ሌላ አስተሳሰብ ያላቸውን በውይይትና በክርክር ማሳመን ቀርቶ በወዳጅና በጠላት መሀከል ከልሎ ለተለያዩ አስተሳሰቦች ክፍት አለማድረግ፣ ለማዳመጥና ለመደማመጥ አለመቻል፣ ትንሽ ዕውቀት የነበረውን መናቅና ማግለል፣ እነዚህ ሁኔታዎች ከነበሩን ከህብረተሰባችን ከቀሰምናቸውና ካደግንባቸው ባህል ጋር ተደምሮ የትግሉን አቅጣጫ ሊወስን ችሏል። በተጨማሪም፣ የሚነሱ ጥያቄዎችንም ሆነ አፍጠው አግጠው የሚታዩትን ችግሮች በክርክርና በውይይት ከመፍታት ይልቅ በአመጽ ለመፍታት መሞከር የህብረተሰብአችንን ችግር የባሰ ውስብስብ አደረገው። ችግርን በውይይትና በክርክር ለመፍታት የመቻል ባህል አለመኖር ደግሞ ከውስጥ ሆነው የራሳቸውን ህልም ለሚያልሙና፣ ብሄራዊ ባህርይና የመንፈስ አንድነትን አዳብሮ ለአንድ ዓላማ መታገልን ለማይፈልጉ ኃይሎች በሩን ከፈተላቸው። እጅግ በጠባብ አስተሳሰብ ጭንቅላቱ የተናወጠው የኤርትራ ነጻ አውጭ የሚባለው እንቅስቃሴ፣ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት ነኝ የሚለው እምብዛም የምሁር መሰረት የሌለው እንቅስቃሴና፣ የትግሬ ነጻ አውጭ ነኝ ብሎ እዚህና እዚያ ይፘፘጥ የነበረውና ዛሬ በምሁራዊ ዕወቀት አልባነቱን ያጋለጠው፣ ይህንን ዐይነቱን ቀዳዳና የተወሳሰበ ሁኔታ በመመልከት፣ ጠቅላላውን ትግል ወደ ጦር ትግል እንዲያመራ አደረጉ። ነጻነትን ከዕውነተኛ ዕውቀት፣ ከመንፈስና ከባህላዊ ተሃድሶ ነጥሎ በመመልከት የወጣቱንም አስተሳሰብ በአመጽ ዙሪያ እንዲሸከረከር በማድረግ ችግሩ እንዲባባስ ሆነ። ዕውነተኛ ስልጣኔ በሃሳብ ኃይል ብቻ ይገኛል የሚለው የተቀደስ አስተሳሰብ ቀርቶ፣ ድል በጦርነት፣ በመጨፋጨፍና ወንድምን ገድሎ ጀግና ተብሎ በመጠራት ይገኛል ወደሚለው በመቀየሩ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠር ወጣትና ህዝብ በከንቱ ደሙን አፈሰሰ። የኑሮ ትርጉምን፣ የህበረተሰብ ምንነትና፣ የቤተሰብ መመስረትን አስፈላጊነት በሚገባ ያልተገነዘበውና የነጻነትን ትርጉም ያጣመመው የብሄረ-ሰብ እንቅስቃሴ ሁሉ ራሱን ከሌላው በመለየትና፣ የሌላው ጥያቄና ችግር እኔን አያገባኝም በማለት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን አሳሳተ። ኑሮአቸውን አጨለመ። ይህም የሆሜሩን የግሪክ ዘመን ታሪክ ያስታውሰናል።በተማሪው እንቅስቃሴ ላይ የሚደረገውን ከታሪክ፣ ከህብረተሰብ መዘበራረቅተነጥሎ የሚወሰደውንና የሚሰነዘረውን ታሪከ-ቢሰ ትንተናና፣ ማን ነው ተጠያቂው?የሚለውን የማያስፈልገውን ውንጀላ ወደ ጎን ትተን-ለሳይንስና ለስልጣኔ የሚበጅ የትግል የትንተና ስላልሆነ- ወደድንም ጠላንም ሁለቱ የሚታወቁት እንቅስቃሴዎች ብሄራዊ ባህርይ እንደነበራቸው ነው። ይሁንና ግን፣ የመጨረሻ ውጤቱ የተቃራኒው ሆነ። ሶክራተስም እንደሚለው አንድ ሰው የሚሳሳተው ወይም የሚያጠፋው ሆን ብሎ አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ለስህተት መፈጸም ዋናው ምክንያት አንድም አለማወቅ፣ ወይም ዕውቀት ቢኖር እንኳ ለማሰብ ፋታ ሊገኝ የማይችልበት ሁኔታ በሚፈጠርበት ወቅት ነው። እንደሚታወቀው ማንኛውም ሰው መቶ በመቶ አርቆ-አሳቢ(Rational) ሊሆን አይችልም።ወይም ደግሞ በአንዳች ምክንያት ከቁጥጥር ውጭ የሚወጣበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ታላቁ ፑሽኪን በጣም አርቆ-አሳቢ ብቻ ሳይሆን በሊትሬቸር ስራውና በግጥሙ በጣም የታወቀና ለራሺያም ዕድገት ትልቅ አስተዋጽዎ ያደረገ ሰው ነው። ይሁንና ግን የቤተ-መንግስት መሳፍንቶች በዕወቀቱ ስለሚቀኑበት ያበሸቁት ስለነበር በመጨረሻ ላይ ግን ራሱን መቆጣጣር ስላልቻለ ከአንዱ መስፍን ጋር ትግል እንጋጠም ብሎ፣ በአርባ ዐመቱ ህይወቱ ተቀጨ። እንደዚህ ዐይነት ቶሎ የሚከሰት የአጭር ጊዜ አርቆ-አላሳቢነት በሁላችንም ዘንድ ሊታይ ቢችልም፣ ይህ ዐይነቱ ባህርይ ስር የሰደደ ከሆነና ከግለሰቦች አልፎ ወደ ድርጅቶችና ወደ ታዳጊ ትውልድ ልክ እንደ ወረርሸኝ በሽታ ከተላለፈ እንደ ነቀርሳ በሽታ አንድን ህብረተሰብ በመገዝገዝ መጨረሻ ላይ ህብረተሰቡ አቅድ እንዲያጣና ተስፋ እንዲቆርጥ ይደረጋል። የሚገርመው ነገር ደግሞ ይህ ዐይነቱ የእልክ ጉዞ የሚያይለውና ዘለዓለሙን የሙጥኝ ብሎ የሚይዘው ትንሸ ፊደል ቀመስን የሚሉትን ነው። ባለፉት አርባ ዐመታት በአገራችንና በብዙ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች ኤሊት በሚባለው የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ የሚታይ መጥፎ በሽታ ነው ብሎ አፍን ሞልቶ መናገር ይቻላል።ያም ሆነ ይህ የተማሪው እንቅስቃሴ ማየል የአገራችን የህብረተሰብና ኢኮኖሚዕድገት ነጸብራቅ ነው። በዘመናዊነት የገባው የዕድገት ፈለግ አዲስ የኢኮኖሚና የባህል እንዲሁም የፖለቲካ ኃይል ብቅ ብሎ እንዲወጣና ፊዩዳላዊ አገዛዙንና የባህላዊ መሰረቱን እንዲቀናቀን የሚያስችል አልነበረም።የኢኮኖሚው ውስጠ-ኃይል ውስን በመሆኑ ከነጋዴ የህብረተሰብ ክፍልና እጅግ ከተዘበራረቀ ንዑስ ከበርቴ የህብረተሰብ ክፍል በስተቀር ዕድገትን በቴክኖሎጂ መሰረት ላይ ያደረገ የኢንዱስትሪ ከበርቴ ብቅ ሊል አልቻለም።አገዛዙ ከሚከተለው እጅግ የተወላገደ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጋር የውጭው ኃይል ግፊት ተደምሮበት ለአዲስ ብሄራዊ ከበርቴ መደብ ብቅ ማለትና መዳበር መፈናፈኛ ሊሰጥ አልቻለም። በየክፍለ ሀገሩም የተዘረጉት ኢንስቲተሸኖች በሙሉ ለዕድገት የሚያመቹ ስላልነበሩ ህብረተሰቡ በዚያው ቀጭጮ እንዲቀር የማድረግ ኃይላቸው ከፍተኛ ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው የተማሪው እንቅስቃሴ ብቅ ሊልና ጎልቶ መታየትም የጀመረው። የተማሪውም እንቅስቃሴ በሁኔታዎች በመሳሳትም ሆነ ለማውጣትና ለማውረድ ፋታ ባለማግኘት ሚናውን ከሚገባው በላይ ከፍ አድርጎ እንዲያይ አድርጎታል። ዛሬ በዚህ መልክ ሲጻፍም ሆነ ሲታይ የትግል ልምድ ያላቸውና እህቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውን ያጡ፣ ይህ ደግሞ የማያውቀውን ዝም ብሎ ነው የሚዘላብደው ሊሉ ይችሉ ይሆናል። በስልጣኔና በለውጥ የምናምን ከሆነ እያንዳንዱ ተከታይ ትውልድ ያለፈውን ታሪክ ከብዙ አቅጣጫዎች ለመገምገም መቻል አለበት። የነበሩንና ያሉንን ድክመቶችና መልካም ጎኖች አንስተን የማንወያይ ከሆነ ደግሞ በፍጹም መሻሻል አንችልም። ዕድገትም ሊኖር አይችልም። ስለዚህም እዚህ ላይ በዚህ መልክ ሲተነተን የተማሪውን እንቅስቃሴ ለመወንጀል ሳይሆን በምን ዐይነት ሁኔታ ውስጥ እንደተፈጠረና ይህንን ዐይነቱን የትግል ፈለግ ለመከተል ምን እንዳስገደደው እኔ በምረዳው መልክ ለማቅረብ ብቻ ነው። ተሳስተሀል የሚሉ ካሉ በነጻ ዓለም ውስጥ ስለምንኖር የዚህን ግለሰብ ትንተና የመተቸትና አስተያተቻውን የመሰንዘር መብት አላቸው። ለህብረ-ብሄርና ለብሄራዊ ነጻነት እንታገላለን የሚሉትን የተለያዩ ድርጅቶች አርቆ የማሰብና ያለማሰብ ጉዳይ ብንተው፣ እነዚህ ኃይሎች የኢትዮጵያን አንድነት ድርድር ውስጥ ስለማያሰገቡ- ለብሄረ-ሰቦቻቸው ነጻነት እስከመገንጠል ደረጃ እንታገላለን የሚሉትን ብንወስድ በምንም ዐይነት የሳይንስ መከራከሪያ ዘዴ ሊያምኑ አይችሉም። አይፈልጉምም። አስተሳሰባቸው ሁሉ፣ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ፣ ከጥበብና ከፍልስፍና እንዲሁም ለአንድ ህብረተሰብ አስፈላጊ ከሆኑ ዕውቀቶች ውጭ ትግላቸውን ስለሚመለከቱና ስለሚሸከረከሩ ሰፋ ላለ ስልጣኔ ብንታገል ይሻላል ብሎ በፎርሙላ መልክ እንኳ ቢቀርብላቸው በፍጹም አይቀበሉም። ይህ የሃሳብ ግትርነታቸውና ዘለዓለማዊ ጥርጣሬያቸው ለአንድ ህብረተሰብ የሚደረገውን ጠቅላላውን ህዝብ የሚመለከት የስልጣኔ ፈለግ እያጨለመው መጥቷል ማለት ይቻላል። ይህ የትግል ዘዴያቸው ደግሞ የመጨረሻ መጨረሻ ራሳቸውንም እንደሚያጠፋና እንታገልለታለን ለሚሉት ህዝብ ዘለዓለማዊ ጠንቅ እንደሚሆን ግልጽ ነው። ሳይንሰ-አልባና የፍልስፍና መሰረት የሌለው ትግል የሚያመረቃ ውጤት ለማምጣት የማይችል ስለሆነ ነው። ነገሩን ይበልጥ ለመረዳት ሁለቱ የብሄረ-ሰብ ነጻ አውጭ ነበርን በሚሉትና አሁን ወደ መንግስትነት በተለወጡትና፣ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ድርጅት ነኝ የሚለውን የትግል ዘዴዎችና አደገኛነት ጠጋ ብለን እንመልከት። የሶስቱም ድርጅቶች መሪዎች የማይሆን መፈክር አንግበው በመነሳት በወጣቱ ጭንቅላት ውስጥ ስርጎ በመግባትና የአስተሳሰብ አድማሱን በማጥበብ ካለምንም ፍርሃት ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ተቀራርቦ እንዳይወያይ መሰናክል እንደፈጠሩበት የታወቀ ጉዳይ ነው። ይህንን ችግር መፍታት ስንችልና የተለያየ ብሄረ-ሰብ አባል ነን የሚሉ ግለሰቦች ከተተበተቡበት አጉል የድንቁርና ሰንሰለት ሲላቀቁ ብቻ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚስማማ አገር መገንባት የሚቻለው። ጥርጣሬ ባለበት፣ ጥያቄ በማይጠየቅበትና የሃሳብ መንሸራሸር በማይኖርበት ሁኔታ ውስጥ ለጋራ ዓላማ መታገል በጣም አስቸጋሪ ነው። የኤርትራን ነጻ አውጭ ድርጅትና(EPLF) የኤርትራውያንን አስተሳሰብ ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ እንመልከት። በአፄ ኃይለስላሴም ሆነ በደርግ ዘመን በኤርትራ ህዝብ ላይ ስህተትና በደል እንደተፈጸመ የማይካደ ሀቅ ነው። ይሁንና ግን፣ በተለይም በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የተፈጸመው በደል ከጠቅላላው የአገሪቱ ወደ ኋላ-መቅረትና የአፄው መንግስት ከሚከተለው አጠቃላይ ፖለቲካ ተነጥሎ ሊታይ የሚችል አይደለም። በጊዜው አፄው ለኤርትራውያን ዲሞክራት፣ ለተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ ደግሞ ተቃራኒውን ሊያደርጉ አይችሉም ነበር። ፊዩዳላዊ አመለካከታቸውና ከጣሊያን መሸነፍና መባረር በኋላ ያዋቀሩት አገዛዝ በተወሰነ ክልል ብቻ ነው እንዲያስቡ ያስገደዳቸው። ኤርትራውያንም ሆኑ ሌሎች የነጻ አውጭ ነን የሚሉት ድርጅቶች ይህንን በኢትዮጵያ ውስጥ ለዕድገትና ሰፋ ላለ ስልጣኔ እንቅፋት ሆኖ የተዘረጋውን የአገዛዝ ሰንሰለት ነው ሊገነዘቡ ያልቻሉት። ይህም ሊሆን የቻለው ሺለር እንደሚያስተምረን ነገሮችን በጣጥሰው ስለሚመለከቱና ራሳችውም በፈጠሩት፣ አብዛኛውን ጊዜ ከተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር ሊጣጣም የማይችል አስተሳሰብ የትግል መመሪያቸው ስለደረጉና ዛሬም ስለሚከተሉ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ያልተጠናቀቀው የህብረ-ብሄር አገዛዝ ምስረታ ከየብሄረ-ሰቡ የወጣውን ኤሊት ነኝ ባይ ዕውነተኛ ነጻነት ፈላጊ መሆኑ ቀርቶ፣ ተበዳይነትን አጉልቶ በማሳየት እኔም ስልጣን ይገባኛል ወይም ተገንጥዬ ሄዳለሁ የሚለውን መፈክር ወደ ውጭ አውጥቶ እንዲታገል አስገድዶታል። በብዙዎቹ ዘንድ ያልነበረውና ያለው የግንዛቤ ችግር በዕውነተኛ ግለሰብአዊ ነጻነትና በብሄረ-ረሰቦች ነጻነት መሀከል ያለው ዲያሌክቲካዊ ትግል ተሳስሮ ለመታየት ያለመቻሉ ነው። ይህ ነገሮችን ገነጣጥሎና በጠባቡ መመልከት ወደ ባሰ መሰሪህነትና እልክ ወደሚያሲዝ ትግል እያመራ መጣ። ትግሉ በምንም ዐይነት፣ በየትኛውም የሳይንስ መነጽር ቢታይ ለዕወነተኛ ነጻነት የሚያመች አይደለም። የተለያዩ ብሄረ-ሰብ አባላትን በጥርጣሬ እንዲመለከቱ የሚያደርግና የኑሮን ትርጉም መሪዎቻቸው በተረጎሙላቸውና በነደፉላቸው የአስተሳሰብ ክልል ውስጥ ብቻ እንዲሽከረከር ከማድረጉ በስተቀር። ስለሆነም የኤርትራው ነጻ አውጭ ድርጅት ለሌሎችም ምሳሌ በመሆን፣ በአንድ በኩል ከውስጥ እንደ ነቀርሳ በሽታ መሰርሰር፣ ከውጭ ደግሞ ርዳታ በማግኘት የደፈጣ ውጊያ ማድረግና ጠቅላላውን ህብረሰተብ ማናጋት እንደሙያ አድርጎ ተያያዘው። የትግሉ ፈሊጥ አንድ ቤት በመሰራት ላይ እያለ ወይም ከተሰራ በኋላ እሱን አፈራርሶ በተበላሸ መልክ እንደገና እገነባዋለሁ እንደማለት የሚቆጠር ከተጣመመ አስተሳሰብ የመነጨ ነው። ይህ እልከኝነት የተሞላበት ትግል ወደ ውስጥ ወጣቱን በማዳረስና ተደላድሎ የሚኖራውን፣ በአንዳንዶች በተሰሳሳተ መልክ ሚድል ክላስ ተብሎ የሚጠራውን ኤርትራዊ ሁሉ በማዳረስ አገዛዙን ብቻ ሳይሆን ጠቅላላውን ህብረተሰብ የሚገዘግዝ ሆነ። አዲስ አበባና ሌሎች የኢትዮጵያ ክፍለ-ሀገሮች ተወልዶ፣ ከሌሎች ብሄረ-ሰቦች ጋር ጭቃ እያቦካ አድጎና ትምህርት ቤት ሄዶ በተነሰነሰው የጥላቻ መርዝ ኢትዮጵያውነቱን መካድና ለኤርትራ ብቻ ፍቅር ማሳደር ጀመረ። ለማንኛውም ሰው የተወለደበትና ያደገበት፣ እንዲሁም ጫካም ሄዶ ተራራ ላይ ወጥቶ ብዙ ነገር ያያበትን ነው እንጂ ፍቅር የሚያሳድርበት፣ ያልተወለደበትና ያላደገበት እንዴት አድርጎ ፍቅር ሊያሳድርበት ይችላል? የማይገባኝ የህሊና አወቃቀርና በምንም ሳይንስ የማይደገፍ “የብሄረተኝነት ስሜት” ነው። ያም ሆነ ይህ አብዛኛው በመሳሳት “የበላበትን ወጪት ሰባሪ” እንዲሉ፣ ቢበደሉም እንኳ እስከዚህ ድረስ የከረረ አቋም መወሰድ አይገባቸውም ነበር። ግን ደግሞ ጭንቅላት ሲታወር፣ የማመዛዘን ኃይል ተሟጦ ሲያልቅ ከአውሬነት በታች ባህርይ የሚይዝ ብዙ ሰው አለ። በወታደር መዋቅርና በስለላ ድርጅት ውስጥ አልፎ በከፊል በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉትንና በንግድ የተሰማሩትን አንዳንድ ኤርትራውያንን በማካተት፣ ኤርትራውያንን እንደህብረተሰቡ አካልና ለዕድገት የቆሙ ሳይሆኑ ለጊዜያዊ ጥቅም የተቀመጡና አንድ ቀን ኤርትራ ነጻ ስትወጣ ጓዛቸውን ጠቅለለው የሚሄዱ ነበር የሚያስመስላቸው። ይህ ችግር የመነጨውና ዛሬም በብዙዎቹ መንፈስ ተንጠልጥሎ የቀረው፣ ኤርትራ ውስጥ የተለያዩ አናሳ ብሄረሰቦች ቢኖሩም፣ በንፅፅራዊ መልክ ሲታይ ያልተቀላቀለና በህበረተሰቡ ውስጥ የሃሳብ መሽከርከር ያልዳበረበት በመሆኑ ነው። ከሌሎች ክፍለ ሀገሮች በተለይ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጭቆናና አመለካከት የኢጣሊያኑ ስድሳ ዐመት ካፒታሊዝም ባህላዊ ተሃድሶ እንዳላመጣ ነው። አንዳንዶች እንደሚሉት፣ በኢጣሊያን የቅኝ አገዛዝ ስር ስድሳ ዐመት ያህል መቆየት ስልጣኔን ያላበሰ ሳይሆን፣ በዕውነተኛ ስልጣኔ የማይለካን ጉራንና ከሌላው እንበልጣልን የሚለውን አስተሳሰብ በተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል በጭንቅላቱ ውስጥ እንዲተከል ነው ያደረገው። ቱካዳይስ የሚባለው ከሄሬዶተስ ቀጥሎ የነበረው ሰብአዊው የታሪክ ጸሀፊ እንደዚህ ዐይነቱን ጉራ ፕራውድ አሮጋንሲ(Proud Arrogancy) ብሎ ይጠራዋል። ግለሰቦች ራሳቸውን ካለወቁና የሌላውን ሰው መብት ካላረጋገጡና ሌላውንም በንቀት የሚመለከቱ ከሆነ ለራሳቸውም ነጻነት ሆነ ላሉበት ህብረተሰብ ዘለዓለማዊ ጠንቅ ሆነው ነው የሚቀሩት። አሰቸጋሪው ጉዳይ በአንድ በኩል የተለየሁ ነኝ፣ በታሪክም ሆነ በባህል የሚያገናኘን የለም፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከናንተ ጭንቅላት ላይ አንወድቅም የሚለው አስተሳሰብ ጤናማ ስርዓት ለመመስረት አያስችልም። ይህ ዐይነቱ በአንድ በኩል ነጻነቴን እወቁልኝ በሌላ ወገን ደግሞ ከናንተ ጭንቅላት ላይ አልወርድም ማለት በአጉል የፖለቲካ ስሌት ሲታይ የበላይነትን እንቀዳጅ ማለት ነው። ይህ ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ደግሞ በሃያኛው ክፍለ-ዘመን ሊሰራ በፍጹም አይችልም። ያም ሆነ ይህ ኤርትራውያን ከባርነት ይልቅ ነጻነትን እንመርጣለን ብለው የራሳቸውን መንግስት ከመሰረቱ በኋላ ገነት ሳይሆን የሲኦል አገዛዝ ነው የጠበቃቸው። መራብና መሰደድ እንዲሁም መንገላታት ነው እጣቸው የሆነው። አሁንም ቢሆን በአብዛኛዎቹ ጭንቅላት ውስጥ ተተክሎ ያለው ይህንን ምስቅልቅል ሁኔታ ያለመረዳት ነው። በጭንቅላታቸው ውስጥ የተተከለው መርዝና ሌላውን በንቀት ማየት ያሉበትን ሁኔታ በትክከል ማየት እንዳይችሉ ጋርዷቸዋል። ለምሳሌ በጦር ሜዳ ላይ በነበሩበት ጊዜ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱ በስልጣኔ የቀደሙ፣ አማራው ጭራቅ ነው፤ ሰውን ይበላል ብለው ያወሩ እንደነበር ከራሱ ኤርትራዊ፣ ኤርትራ ከሚመላለስ የነሱ ትግል አጋዥ አፍ ሰምቻለው። ይሁንና የደርግን ወታደር ከወያኔ ጋር ድል እያደረጉ ሲመጡ የአማራው ግዛት ውስጥ ይደርሳሉ። ርሃብና ጥማት ስላሰቃየቸው ወደ ቤት ጎራ እያሉ የሚቀመስ ነገር ሲጠይቁ የሚቀርብላቸው እንጀራ በወጥና በእርጎ ነበር። ይህንን ይገነዘባሉ። ኤርትራ ከገቡ በኋላ መሪዎቻቸውን ይጠይቁ የነበረው፣ አማራው ጭራቅ ነው፣ ሰው ይበላል ብላችሁ ነበር የነገራችሁን፣ ሆኖም ግን ርህሩህና ቀና ህዝብ ነው ያጋጠመን እያሉ ነበር የሚነግፘቸው። እዚህ ላይ መገንዘብ ያለብን ጥቂት ኤሊት ነን የሚሉ የራሳቸውን ስሜትና ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ አንድን ታዳጊ ትውልድ የጥላት መርዝ እንደሚነሰንሱበትና የታሪክ ወንጀል እንደሚሰሩ ነው። ይህ እንደ ዕውነት ሆኖ በጭንቅላት ውስጥ በመቀረጽ እስከ ዕለተ-ሞት ድረስ በመፈራራትና በጥላቻ ይኖራል። የስልጣኔው በር ይዘጋል። የኢትዮጵያችን አንደኛው አስቀያሚ ጎን ይህንን ነው የሚመስለው። ከተራው ህዝብ ሳይሆን ፊደል ከቆጠረውና ዪኒቨርሲቲ ገባሁ ከሚለው የሚነሰነስ የመርዝ ጥላቻ። አቶ ኢስያስ አፈወርቂ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። በጊዜው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ምሁራን ጋር ሆነን እንታገላለን ያሉ ወደ 400 የሚጠጉ ወጣት ኤርትራውያን በአቶ ኢሳያስ አፈውርቂና በግብረ-አበሮቻቸው እንደታረዱ መታወቅ አለበት። ይህ ጸሀፊ ኤርትራውያን በሙሉ ወንጀለኞች ናቸው ብሎ አጉል ጥላቻ ለመንዛት አይፈልግም። ብዙ ቀና ጓደኞችም አሉት። ያም ሆነ ይህ፣ ይህ ዐይነቱ የማያስፈልግ የትግል ዘዴ እየታወቀ እንዳንድ ዕውቀት አለን የሚሉ ኤርትራውያን ከውጭ እርማት ለማድረግ ጥረት ያለማድረጋቸው ነው። አንዳንዶቹ ይባስ ብሎ ራሳቸው የዚህ የቆሻሻ ትግል ዘዴ ሰለባ መሆናቸውና በውሸት _ዓለም ውስጥ መዋኘታቸው ነው። ለምሳሌ ፕሮፌሰር ለገስ አስማሮምን የማያወቀው የለም። ስለ ጋዳ ስርዓት በሰፊው ያጠናና መጽሀፍም የጻፈ ነው። ይህ ፕሮፌሰር ኤርትራ ነጻ ወጣች ከተባለች በኋላ የሚያስተምርበትን ዩኒቨርሲቲ በመተው ከኢሳያስ አፈወርቂ አጋዛዝ ጋር ያበረ ነው። እዚህ የምኖርበት ከተማ መጥቶ ስለ ኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የሰጠው ትንተና የሚያሳዝንና አንድ ተማርኩ ከሚል አፍ ሊወጣ የማይገባው ውሸት ነው የተናገረው። የማያስፈልገውን ጻፍክ አልባልና፣ የአንድ ምሁር አመለካከት እንደዚህ ከሆነ ካልተማረው ምን ነገር ልንጠብቅ እንችላለን? መማር ማለት መሻሻል፣ በሃሳብ መጽዳትና ለሌላው ብርሃን የሚሆን ነው ብለን ከወሰድን፣ የእነ ፕሮፌሰር ለገሰ አስማሮም ትምህርት ዕውነትን ሳይሆን ውሸትን እንዲጎናጸፉ ነው ያደረጋቸው። ይህ ዐይነቱ የጥላቻ መርዝ ደግሞ በህዝብ ጭንቅላት ውስጥ በመነስነስ የስልጣኔን ብርሃን እንዳያዩ ነው የጋረዳቸው።የሰመጥንበት ማጥ በቀላሉ የምንወጣው አይደለም። ያለፈው አልፏል ብንልእንኳ አሁንም በሌላ መልክ እየተከታተለን ነው። ለሰብአዊ መብት ተቆርቋሪዎችናለዕውነተኛ ነጻነት ታጋይ ነን ለምንል ኃይሎች ግራ የገባን ኤርትራን በሚመለከት ምን ዐይነት ፖለቲካ እንከተል የሚለው ነው። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የደረስኩበትድምደማ፣ በማንኛውም መልኩ ከኤርትራ መንግስት ጋር የሚደረገው መቀራረብ ብዙጥንቃቄን የሚጠይቅ ነው ። የኤርትራ መንግስት ድሮም በነጻነት ትግልም ዘመን ይሁንባለፉት ሃያ አመታት ውስጥ ያስመሰከረው ኢትዮጵያ እንድትበታተን ነው። የኢሳያስአፈወርቂና ግብረ-አበሮቹ ይህንን ለማንም የማይበጅና ለማንም ግልጽ የማይሆን ፖለቲካግባቸውን ተግባራዊ ለማድረግ የማይሸርቡት ተንኮል ይህ ነው አይባልም። ስለሆነምማንኛውም ፖለቲከኛ ነኝ ባይ ኢትዮጵያን ከወያኔ መንጋጋ ለማላቀቅ በሚያደርገው ትግልአስቸጋሪ ወጥመድ ወስጥ የገባ ቢሆንም፣ ከእነ ኢሳያስ አፈውርቂ ጋር ሆኜ ለኢትዮጵያህዝብ የሚበጅ ነገር እሰራለሁ ማለት ዘበት ነው። በማንኛውም የፖለቲካ ፍልስፍናየሚደገፍ አይደለም።ከኤርትራ ሆኜ፣ ከኤርትራ መንግስት ጋር ተቀራርቤ ኢትዮጵያን ነጻነት አወጣለሁ የሚለው አስተሳሰብ በፍጹም ሊሰራ የሚችል አይደለም። በታሪኩ ውስጥ ለብዙ መቶ ሺህ ህዝብ ዕልቂት ምክንያት ከሆነ፣ ዛሬም ጭቆናን አስፋፍቶና የራሱን ህዝብ ለስደት ከሚያደርግ መንግስት ጋር ቆሞና ርዳታ አግኝቶ ዕውነተኛ ነጻነት ለኢትዮጵያ ህዝብ አመጣለሁ ማለት በህዝብ ላይ እንደማላገጥ የሚቆጠር ብቻ ሳይሆን ትልቅ የፖለቲካ ወንጀልም እንደመስራት የሚቆጠር ነው። ይህ ጉዳይ በጥብቅ መታሰብ ያለበት ነው። በተረፈ ግን ከኢትዮጵያ ጋር አብረን መኖር እንፈልጋለን፣ የሰለጠነች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ዝግጁ ነን ለሚሉና፣ ከማንኛውም ተንኮል ለጸዱ ኤርትራውያን በሩ ክፍት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ቀናው ምሁር ጠቡ ከኤርትራ ህዝብና በቀና መንፈስ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ቆሞ ለመታገል ዝግጁ ከሆነው ኤሊት ጋር ሳይሆን፣ ጦርነትንና መተላለቅን ፍልስፍናውና ባህሉ ካደረገው ከኢሳያስ አፈወርቂና ከግብረ-አበሮቹ ጋር ነው። ስለሆነም፣ የኤርትራና የኢትዮጵያ ግኑኝነት ከኢሳያስ አፈወርቂ መንግስት ባሻገር መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ሊፈታም የሚችለው በፖለቲካና በረዥም ጊዜ የሰላምና የመግባባት ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው። ሁለቱም ህዝቦች ለሰላምና ለዕድገት ብለው ቢነሱ ጥሩ ታሪክን ለተከታተዩ ትውልድ ሊያስተላልፉ ይችላሉ።የወያኔንና የኦሮሞን ነጻ አውጭ ነኝ ባይን ድርጅቶች ጉዳይ ስንመለከት በተለያየ መልኩ የአንድን ህዝብ መቀራረብና ለጋራ ዓላማ መነሳትን አጥብቆ የሚቃወሙ ናቸው። የሁለቱም ድርጅቶች ችግር የራሳቸውን ታሪክ ከኢትየጵያ ህዝብ ታሪክ ነጥለው በማየትና፣ በነሱ ላይ ይደርስ የነበረውን በደል ብቻ አጉልቶ በማሳየት የታሪክን ሂደት በማጣመም አብዛኛውን ወጣት ማሳሳት ነው። የየራሳቸውን የታሪክ አመጣጥ ባለማገናዘብ፣ በውሸት ቅስቀሳ ላይ በመመርኮዝ፣ ሌላው ወራሪ እነሱ ተወራሪ አድርጎ ማቅረብ የህብረ-ብሄር አመሰራረትን እጅግ በተሳሳተ መልክ ይመለከታሉ። ለምሳሌ ዛሬ የኦሮሞ ኤሊት የኦሮሞ ግዛት ነው ብሎ በባንዲራው ላይ የሳለው ካርታ ከስንት ሚሊዮን ዓመታት ጀምሮ ነበር ኦሮሚያ የምትባል አገር የነበረችው? ኦሮሞዎች ዛሬ የእኔ የግዛት ክልል ነው ብለው በሚጠሩት ከነሱ ቀደም ብለው የዳበሩና በስራ ክፍፍል የላቁ መንግስታት አልነበሩም ወይ? በታሪክ ውስጥ በማንኛውም አገር የህዝብ እንቅስቃሴ አልነበረም ወይ? በተለያዩ ምክንያቶች አንድ ህዝብ ወይም ብሄረ-ሰብ ቀድሞ ይኖርበት ከነበረበት ቦታ ተነስቶ ሲሄድና ሌላ አካባቢ ሲኖር፣ በሰፈረበት ቦታ ከሌላው ጋር በመጋባት ልዩ ባህል አይፈጥርም ወይ? ወይም ደግሞ የኗሪውን ብሄረ-ሰብ ባህል በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በመደምሰስ የሱ ባህል በበላይነት እንዲወጣ አያደርግም ወይ? በጣም በብቸኝነት ከሚኖሩ አናሳ ህዝቦች በስተቀር፣ በማንኛውን አገር የህዝብ እንቅስቃሴዎች ነበሩ፤ ዛሬም አሉ። ስለሆነም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ራሱን ችሎ የሚኖር፣ በአንድ አገዛዝ ስር የተዋቀረ፣ የራሱ ወታደር፣ ቢሮክራሲና በልዩ ልዩ የስራ ክፍፍል የተደራጀ የህብረተሰብ ክፍል በኦሮሚያ ታሪክ ውስጥ የለም። በሌላ አነጋገር፣ ኦሮሚያ ተብሎ የሚጠራው ክፍል እንደ ህብረ-ብሄር የተዋቀረ አልነበረም። ኦሮሞዎች ግን በታሪካቸው ከብት አርቢዎች ስለነበሩ ከአንድ ቦታ ፈልሰው በመነሳት በአስራስድስተኛው ክፍለ-ዘመን አብዛኛውን የኢትዮጵያ ግዛት በማዳረስ በንጉስ ደረጃ ተራጅተው የነበሩ ነገስታትን በመደምሰስ የተስፋፉ ናቸው። የጋደም ስርዓት እነሱ እንደሚሉት ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ ሳይሆን፣ “በመደብ” ላይ የመሰረተና ሴቶችን ከማንኛውም ተግባርና ከግል ሀብትም ያገለለ የአገዛዝ መዋቅር ነው። ከሞላ ጎደል ይህ ሆኖ ሳለ፣ አፄ ምኒልክ ያደረጉት የግዛት መስፋፋት ተፈጥሮአዊ ሂደት ነው እንጂ ወረራ አይደለም። የዚያን ጊዜውን ይህን የመሰለውን የታሪክ ሂደት በግንዛቤ ውስጥ ሊገባና ሊመረመር የሚችለው በዚያን ጊዜ የነበረውን ንቃተ-ህሊና ከቁጥር ውስጥ ያስገባን እንደሆን ብቻ ነው። ይሁንና ደግሞ አፄ ምኒልክም ሆኑ እትጌ ጣይቱ በንቃተ-ህሊና፣ በአስተዋይነትና በተራማጅ አስተሳሰብ ዛሬ አለሁ ከሚለው አብዛኛው ኢትዮጵያዊም ሆነ የብሄረ-ሰብ መሪ ነኝ ከሚለው ልቀው የሄዱ ናቸው። የዓለም ታሪክና የኢትዮጵያ ህብረተ-ሰተብ አወቃቀር ስላልፈቀደ እንጂ የተገለጸላቸው ፍጹም-ንጉስ(Enlightened Absolute Monarchy) ተብለው ለመጠራት የሚችሉ ናቸው። ይህንን ግንዛቤ ውስጥ ካስገባን ከመቶና ከሁለት መቶ ዓመት በኋላ የዛሬይቱ ኢትየጵያ ምን ዐይነት መልክ እንደሚይዝ አናውቅም። ድርቅ ብሎ ይህ የኔ ክልል ነው፤ የሰው ልጅ ከተፈጠረና ታሪክ መሰራት ከተጀመረ ጀምሮ እኔው ብቻ ነበርኩ በዚህ አካባቢ የምኖረው ማለት በታሪክ ውስጥ በልዩ ልዩ አገሮች የተደረገውን የህዝብ እንቅስቃሴና፣ በመጋባትና በመወላለድ የተፈጠረውን መቀላቀል መዘንጋት ወይም ከቁጥር ውስጥ አለማስገባት ትልቅ የታሪክ ወንጀል እንደመፈጸም ይቆጠራል። ተማርን የሚሉት የኦሮሞ ኤሊቶች የሚሰጡት ትንተና ከህብረተሰብ ሳይንስ ውጭ ነው። በአውሮፓና በአሜሪካ ዪኒቨርሲቲዎች እያስተማሩ- _እንዴት እንደሚያስተምሩ አይገባኝም- የኦሮሞ ጥያቄ ሲነሳባቸው ያንገሸግሻቸዋል። ለምሳሌ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚማሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚያስተምሩ ከተለያዩ ብሄረ-ሰቦች የተውጣጡ ምሁሮችን ስለኢትዮጵያ ሁኔታ ገለጻ እንዲሰጡ ይጋብዛሉ። ከተጋበዙት ውስጥ ፕሮፌሰር አርአያ ይገኝበታል። ሁሉም በየተራቸው ንግግር ካደረጉ በኋላ በአንድ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሶስዮሎጂ የሚያስተምር ኦሮሞ ፕሮፌሰር ተራ ይደረሰዋል። ንግግሩን የጀመረው በምስጋናና በትህትና ሳይሆን በድንፋታ ነው። ያለው ሀቅ አለ፣ ትላንትና አማራ ነበር የሚገዛን፣ ዛሬ ደግሞ ትግሬ ነው በቅኝ ግዛትነት የሚገዛን ብሎ መደንፋት ጀመረ። ተመልከቱት፣ እንደዚህ ዐይነቱ አነጋገር በሶሲዮሎጂ የሚደገፍ አይደለም። የአማራም ሆነ የትግሬ ብሄረ-ሰቦች በጥቅምና በመደብ እንዲሁም በጾታና በዕድሜ የተከፋፈሉ ናቸው። እልም ያለ ገጠር ውስጥ የሚኖረው አማራና ከተማ ውስጥ ከዚህም ከዚያም አካባቢ የመጣው አማራ በንቃተ-ህሊናም ሆነ በህሊና አወቃቀር ይለያያሉ። በገቢም ሆነ በአኗኗር ስልት እንደዚሁ ይለያያሉ። ይህንን ሳይረዱ በጥቅሉ አንድን ብሄረ-ሰብ መወንጀል ስህተት ብቻ ሳይሆን በጣም አደገኛ ነው። ውድ እህቶቼና ወንድሞቼ ተመልከቱት እንግዲህ፣ ምሁር ነኝ የሚለው እንደዚህ ዐይነት ገለጻ ሲሰጥ ከአልተማረው ምን ይጠበቃል? እስካሁን በጥብቅ እንደተከታተልኩት ተማርኩ ከሚለው ፊደል ያልቆጠረው ኢትዮጵያዊ በአርቆ-አስተዋይነት በብዙ እጥፍ እንደሚበልጥ ነው። ያም ሆነ ይህ ከአውሮፓ ታሪክ የምንማረው የየህብረ-ብሄሮች አመሰራረት ውጣ ውረድ የበዛበትና፣ ከበደል ነጻ ሊሆን እንደማይችል ነው። በታሪክ ውስጥ አንድ ህዝብም ሆነ ህብረተሰብ ራሱን ለማወቅና ግንዛቤን ለማግኘት ብዙ ጊዜ እንደሚፈጅበት የተለያዩ አገር ታሪኮች ያስተምሩናል። በደልንና ጭቆናን ለመደገፍ ሳይሆን፣ በአገሮች የህብረ-ብሄር ምስረታ ውስጥ በደልና ጭቆና የታሪክ ግዴታዎች መሆናቸውን ብቻ ለማሳየት ነው። ይህንን ሳንገነዘብ የምናደርገው ትግል በሙሉ የመጨረሻ መጨረሻ ወደ መጠፋፋት ነው የሚያመራን። የምንፈልገውንና የምንመኘውን የመገንጠልም ሆነ አንድነቱን የመመስረቱን ጉዳይ ሳናይ እያረጀንና እየመነመን፣ መጨረሻ ላይ ደግሞ እጅግ ወደሚያሳፍር ቦታ ላይ ወድቀን እንገኛለን። በዚህች አጭር ዕድሜዬ የተመለከትኩት ይህንን አሳዛኝ ሁኔታ ነው። ሰዎች ተምረው፣ የዶክትሬት ዲግሪ ጨብጠው ዘለዓለሙን በጨለማ ዓለም ውስጥ መኖራቸውን ነው። የኑሮ ትርጉሙ ምንድነው? ለምንድን ነው የምኖረው? ወዴትስ ነው የማመራው? ብሎ የመጠየቅ ጉዳይ፣ በተለይም ተማርኩ በሚለው ጭንቅላት ውስጥ መብሰልሰል ያለበት ጉዳይ ነበር። ስልጣን ለመያዝና የራስን ህልም ተግባራዊ ለማድረግ ተብሎ የብዙ ሚሊዮንን ህዝብ ዕድል የማጨለምና የማውደሙ ጉዳይ የተማሩ ሰዎች ተግባር መሆን አልነበረበትም። ከዚህ ስነሳ፣ የኦሮሞ ብሄረ-ሰብ የስልጣኔ ህልሙን ዕውን የሚያደርገው የኦሮሞ ነጻ አውጭ በተለመለት የትግል ስልት አይደለም። የኦሮሞ ብሄረ- ሰብ ፍቅርንና ስልጣኔን ሊቀዳጅ የሚችለው ሳይንሳዊውን የትግል ፈለግ የተከተለ እንደሆን ብቻ ነው። የወያኔም ችግር ራሱ ከተፈጠረበት ሁኔታ የመነጨ ነው። የአገራችን ያልተስተካከለ ዕድገት ውጤት ሲሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ በትግሬ-ብሄረ-ሰብ ውስጥ የሰፈነ ባህልን ሊያድስ የማይችል የአኗኗር ስልት ከአስተሳሰቡ ጋር በመዋሃዱ ነው። የታሪክን ሂደት በጥልቀትና በሰፊው እንዲመለከት አላስቻለውም። በዚህ ላይ አንዳንዶቹ ከኢኮኖሚና ከህብረተሰብ የኑሮ ሁኔታ አንፃር ከተሻለ አካባቢ የመጡ ስለሆነ ትግላቸውን በአማራና በትግሬ ኤሊት መሀከል የሚካሄድ አድርገው እንዲተረጉሙት ተገደዋል። አፄ ኃይለስላሴ እስከወረዱ ድረስ የአማራ ኤሊት ነበር የሚገዛው። አሁን ደግሞ የኛ ተራ ነው ብለው አመቺውን ሁኔታ በመጠቀም ነው ትግላቸውን የጀመሩት። በእነሱ አተረጓጎም፣ በትግሬ ውስጥ ዕድገት ያልታየው የአፄው አገዛዝ በትግሬ ህዝብ ላይ የነበራቸው አመለካከት የቀና ስላልነበረ ነው። በሌላ አነጋገር፣ በጊዜው በሌሎች ክፍለ-ሀገሮች ሌላው ህዝብ በዕድገት ሲያሸበርቅ ትግሬ ይህ ዕድል አላጋጠመውም። ዕድገት ምን መሆኑን የማያውቁ ብቻ ናቸው እንደዚህ ብለው የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚተረጉሙት። ሌላው ቢቀር አዲስ አበባ ራሷ እንኳ ኋላ-ቀርነትና ዘመናዊነት፣ ቆሻሻና “ንጽህና” እዚያው በዚያው ጎን ለጎን የሚታዩባት ከተማ ነች። ሀቁ ይህ ከሆነ፣ ታዲያ ሌላው ክፍለ-ሀገር ሲያሸበርቅ ትግሬ ብቻ ነው የተበደለው የሚለው ያላዋቂዎች አነጋገር ከየት ነው የመጣው?ያም ሆነ ይህ፣ ወያኔ እንደምንም እየተንገዳገደ እዚህ ደርሷል። ራሱ በፈጠራቸው የተወላገዱ ፕሮግራሞችና የገባባቸው ምስቅልቅል ሁኔታዎች ራሱን እንዲጠይቅ በማድረግ ፈንታ አሁንም በእልክ እንዲገፋበት አስገድደውታል። እሱም በተለየ መልክ ልክ ብሄረ-ሰቡን ተገን በማድረግና በማስፈራራት የተዳከመውን የፖለቲካ ኃይል አሰላለፍና የህዝባችንን የፖለቲካ ሁኔታ በመጠቀም ወደ ዘራፊ መንግስትነት(Predatory State)ተለውጧል። ጸረ-ስልጣኔና ፀረ-ሳይንስ በመሆን የአገራችንን የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የፖለቲካና የባህል ሁኔታዎች እያዘበራረቀ ነው። ወዴት እንደሚያመራም በትክክል ማወቅ ባይቻልም፣ ከሃያ ዐመት በኋላ ብዙም ዘልቆ ሊሄድ እንደማይችል እያረጋገጠ ነው። የማምታት ፖለቲካው ተሟጦ አልቋል። እንዲሁም “የምሁር መሰረቱ” ተሟጦ አልቋል። እስከዛሬም በስልጣን ሊቆይ የቻለው የሚጋፈጠው ኃይል ስለጠፋ ብቻ ነው። የኛ ትግልም ከዚህ እልከኛና አልበገርም ባይ አገዛዝ፣ እንዲያም ሲል እጅግ በሚያሳፈር መልክ አገርን በሚቸበችብና፣ አገሪቱን ወደ አስረሽ- ምቺው ሁኔታ በለወጠበት ወቅት እንዴት መላቀቅ ይቻላል ነው። ትግሉ ምን ዐይነት መልክ መያዝ አለበት የሚለው ነው ጭንቅላታችንን ወጥሮ የያዘው። ሰፋ ያለ ምሁራዊ ትግል ማካሄድ ወይስ አሁንም እንደድሮው የትግሉን አድማስ በማጥበብ መደናበር። ከሁለት አንዱን መምረጡ እጅግ አስፈላጊ ይመስለኛል። በእኔ ዕምነት የትግሉን አድማስ እስካላሰፋነው ድረስና በግልጽ ውጭ ወጥተን እስካልተወያየንና እስካልተከራከርን ድረስ ህዝባችን የሚመኘውን ዕውነተኛውን ስልጣኔ ልናመጣለት እንችልም። አስቸጋሪው ጉዞአችን-ውሸት ለጊዜው ብታሸንፍም ዕውነት ግን መጨረሻ ላይ በድል አድራጊነት ትወጣለች! “Pitiful man, who, with the noblest of all tools, with science and art, desires, and obtains nothing higher than the day-labourer with the worst of tools, who, in the kingdom of complete freedom, drags, an enslaved soul around with him. Still more pitiful, however, is the young man of genius, whose natural beautiful stride is led astray by harmful theories and models upon this sad detour, who persuaded to collect ephemeral details for his future vocation, so wretchedly meticulous. His vocational science of patchwork will soon disgust him, desires will awaken in him which it cannot satisfy, his genius will revolt against his destiny. Everything he does appears to him but fragments, he sees no purpose to his work, but purposelessness he cannot bear. The tribulation, triviality in his professional business presses him to the ground, because he cannot encounter it with the joyful courage which accompanies only the enlightened understanding, only expected perfection. He feels secluded, torn away from the connectedness of things, since, he has neglected to connect the activity to the grand whole of the world. Jurisprudence disrobes the jurist as soon as the glimmer of a better culture casts its light upon its nakedness, instead of his now striving to become a new creator of law, and to improve deficiencies now discovered out of his own inner wealth. The physician is estranged from his profession as soon as grave errors demonstrate to him the unreliability of his system; the theologian loses respect for his calling as soon as his faith in the infallibility of his system begins to totter. ( Friedrich Schiller- What Is, and to What End Do We Study, Universal History? Speech delivered to students at Jena University, May, 26-27, 1789)’ ፕላቶን የሰው ልጅ ሁሉ ትልቁ ችግር የማሰብ ኃይል ችግር ነው።Man’s main problem is the problem of thought or knowledge! ይህ ዐይነቱ ችግር የሰው ልጅ ችግርቢሆንም-በዓለም አቀፍ ደረጃ በኤሊቶች አማካይነት በንጹህ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ መመልከት ያስፈልጋል-በተለያዩ አገሮችና ህዝቦች የሚደርሰው ጭቆና ይለያያል። አንዳንዶቹ የሃይማኖትን ልዩነት የግብግብ መነሻ አድርገው ይነሳሉ። ሌሎች ደግሞ ብሄረ-ሰብንና ርዕዮተ-ዓለምን ተገን አድርገው የኔ ይሻላል፣ ስበደል ነበር፣ አሁን ደግሞ የኔ ነው ተራው በሚል የማይሆን ቅራኔ እየተፈጠረ ህዝቦች ለረሃብ፣ ለስደትና ለጦርነት ይዳረጋሉ። በታሪክ ውስጥ በማንኛውም ጊዜ እንደታየው በተራ ዜጎች መሀከል ቅራኔ የለም። በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ችግርን የሚፈጥሩ ምሁራን ነን ወይም ኤሊት ነን ባዮች ናቸው። ኤሊቶች ንጹህ ከሆነው አርቆ-አሳቢነትን ከሚያሰከነው ፕላቶናዊና ሶክራታዊ ፍልስፍናና አስተሳሳብ በመላቀቅ ለራሳቸው ስልጣን መወጣጫ የሚበጃቸውን ርዕዮተ-ዓለም ይፍጥራሉ። ሃይማኖት፣ ርዕዮተ-ዓለሞችና ብሄረ-ሰብ የሚሉት ከሳይንስና ከተፈጥሮ ውጭ የሆኑ ነገሮች ተፈጥረው የሰውን ልጅ እያበጣበጡ ነው። የስልጣኔን ታሪክ ስንመረምር፣ የሰው ልጅ ከምንም ተነስቶ ብዙ ነገሮች ፈጥፘል። ከተማዎች ገንብቷል። ካቴድራሎችና መስጊዶች፣ የገበያ አዳራሾችና መናፈሻዎች፣ እንደዛሬው በሰፊው በግሎባላይዜሽን አማካይነት ዕውቀት ቅጥ ባላጣበት ዘመን ነው የተገነዘቡት። የተለያዩ ህዝቦች ከራሳቸው ክልል በመሻገር በንግድ አማካይነት ባህልን አስፋፍተዋል። በዚያውም አማካይነት የማሰብ አድማሳቸውን አዳብረዋል። አንዱ ከሌላው ተነጥሎ እንደማይኖር በታሪክ ውስጥ አስመስክረዋል። በማሰብ ኃይል ብቻ ዕውነተኛ ታሪክን እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። ከዕውነተኛ ሃሳብ፣ ከሳይንስና ከጥበብ ውጭ የሚደረጉ ትግሎች ጥፋትን እንጂ ጥቅምን እንደማያመጡ በታሪክ ውስጥ ተረጋግጧል። ታዲያ ለምንድን ነው ራሳችንን የማንጠይቀው? በተለያዩ የሶስተኛው ዓለም ተብለው በሚጠሩ አገሮች የሚኖሩ ህዝቦች ለምን ዕጣቸው ድህነትና መሰደድ ሆነ? የተማርኩ ነኝ ለሚለውና ለማንኛውም ንጹህ ሰው ይህን ዐይነቱን ጥያቄ ለመመለስ ከባድ ባልሆነም ነበር። ይሁንና ግን ሺለር እንዳለው በተሳሳተና በተበጣጠሰ አስተሳሰብ ስለምንመራ፣ ራሳችንን ለመጠየቅ አቅቶን በዚያ መሸምጠጥ እንዳለብን አምርረን ተያይዘናል። ስለሆነም በኛ ኢትዮጵያኖች ዘንድ፣1ኛ) የፖለቲካ ትግል ከዕውነተኛው ምሁራዊና ዕውቀት ውጭ ተነጥሎ በመታየት፣ ይህ ቅዱስ አስተሳሰብና የብዙ ሚሊዮኖች ዕድል የተንጠለጠለበት የማንም መጨዋቻ ሆኗል፤ ረክሷል። ለምሳሌ በአገራችን የክርስቲያን ባህል ያፈረሰ ቄስ፣ ደብተራና ሴትም ጭምር-የሴቶችን መግባትና አለመግባት የሚያጠያይቅ ቢሆንም-መቅደስ ውስጥ መግባት አይፈቀድላቸውም። መግባት የሚፈቅዳለቸው ቄሶችና ዲያቆኖች ሲሆኑ፣ ያላፈረሱ በመሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ መንፈሳቸውም ከማንኛውም ተንኮልና የእግዚአብሄርን ቃል ከሚፃረር ተግባር የፀዱና በከፍተኛ መንፈሳዊ ተልዕኮ ምዕመናኑን ከእግዚአብሄር ጋር ያገናኛሉ ተብሎ ስለሚታመንበት ነው። ለፖለቲካም እንታገላለን የሚሉ ግለሰቦች በከፍተኛ ዕውቀት የተካኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከማንኛውም ተንኮል የጸዱና ከራሳቸው ጥቅም ይልቅ ለአገርና ለህዝብ ብለው የቆሙ መሆን አለባቸው። አስተዋይ፣ አንድን ነገር ከብዙ አኳያ ማየት የሚችሉና ሚዛናዊ ፍርድ መስጠት የሚችሉ፣ እንዲሁም ደግሞ የአገሪቱ ህገ-መንግስት ከሚፈቅደው ውጭ መስራትና ውሳኔዎችን መደንገግ የማይችሉ መሆናቸውን የተረዱ መሆን አለባቸው። ቢያንስ ያለፉትን የሃያ ዓመት ትግል ስንመረምር አገዛዙም ሆነ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል በራሳቸው ስሜት እየተነሳሱ ነው ፖለቲካን የሚያካሂዱት። ይህ እንደ ባህል የተወሰደ የፖለቲካ ስልት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊታረም የሚችል አይመስለኝም። ለታዳጊውና ለመጭው ትውልድ የሚተላለፍ መልእክት ነው። 2ኛ) ለህብረተሰብአዊ የፖለቲካ ፕሮጀክት መታገል ማለት በሁሉም አቅጣጫ ሊገለጽ የሚችል ስልጣኔ መታገል ማለት ነው። ዕውነተኛና ሳይንስን የሚያቅፍ ፖለቲካ ወደ ህግ በላይነትና ሲቪል ማህበር፣ እንዲሁም በየጊዜው የሚፈራረቅ ልዩ ልዩ ስም የያዙ ፓርቲዎች የሚቀነስ ጉዳይ አይደለም። በሌላ በኩል ግን የህግ የበላይነትም ሆነ የነቃ ሲቪል ማህበረ-ሰብ በሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ የረዢም ጊዜ ክንውኖች ናቸው። በህግ የበላይነትና በፓርቲዎች መፈራረቅ ዙሪያ የሚደረገው ትግልና ከፍተኛ አትኩሮ ለዕውነተኛ ስልጣኔ የሚደረገውን ትግል ይሸፍነዋል። የመጨረሻ መጨረሻም እንዲከስም ያደርገዋል። ዋናው የስልጣኔው ፕሮጀክት ይረሳና ፓርቲዎች ብቻ የሚፈራረቁበትና የሚወነጃጀሉበት ሁኔታ ይፈጠራል። ከብዙ አገሮች ልምድ እንደምናየው፣ ከሰላሳና አርባ ዐመታት በኋላም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ለድህነት፣ ለረሃብና ወደ ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ ያተኮረ ስደት እጣቸው ይሆናል። ስለዚህ ለስልጣኔ የሚደረገውም ትግል ዕውነተኛ ዲሞክራሲንም የሚያጎናጽፍ መሆን አለበት። ጥቂቶች ብቻ የሚመጻደቁበት መሆን የለበትም። በካፒታሊስት አገሮች በቀጥታ የህዝብ ተሳትፎዎች መኖር አለበት፤ ውሳኔዎች ከጥቂት ፖለቲከኞችና ፓርላሜንታሪያን ብቻ የሚመጣ መሆኑ ቀርቶ፣ በተለይም ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የሚመለከቱ ስራዎች ህዝቡ ውሳኔ መስጠት አለበት እየተባለ ከፍተኛ ትግልና ክርክር ይደረጋል። የውክልና ዲሞክራሲ ብቻ የህዝብን ጥያቄ በትክክል ተግባራዊ አያደርግም እየተባለ ሰላማዊ ሰልፍ ይደረጋል። ወደኛም ስንመጣ ቀጥታ ህዝባዊ ተሳትፎና ክርክር የሚካሄድበት መድረክ መፈጠር አለበት። የፖለቲካው መድረክ ለጥቂት አውቅን ባዮች መለቀቅ የለበትም። 3ኛ) የፖለቲካ ትግል በሀቀኛ ክርክርና ውይይት ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት። የአውሮፓን ረዥሙን የፖለቲካ ትግል ታሪክ ስንመለከት፣ በክርክር ላይና በጥያቄና በመልስ ላይ የተመረኮዘ ነው። ዕውነተኛ የፖለቲካ ትግል የጥቂት ግለሰቦች ምርኮ በመሆን ሚሊዮን ህዝብ የሚታሽበትና አፉን እንዲዘጋ የሚደረግበት አይደለም። ስለሆነም ዕውነተኛ የፖለቲካ ክርክር ከሳይንስ ውጭ ሊሆን አይገባውም። እንደሌሎችም ይህም ጉዳይ በፖለተካ ተዋንያኖቻችን ግንዛቤ ውስጥ የገባ አይደለም። ተረበኞችን፣ ግለሰብ አምላኪዎችን፣ ባንዲራ ለብሰው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያሉ የሚጮሁትን በዕውነተኛ ሳይንሳዊ ክርክር ብቻ ነው መቆጣጠረና፣ ካስፈለገም የትግሉን መድረክ ጥለው እንዲወጡ ማድረግ የሚቻለው። ፖለቲካ በየቡና ቤቱ የሚወራና ወደ ሆያ ሆዬነት የሚቀየር አይደለም። ይህንን መሰረተ-ሃሳብ የማይረዳ ስለ ፖለቲካ ማውራት በፍጹም አይችልም:: 4ኛ) ዕውነተኛ ፖለቲካ፣ ውሸታሙ ከሀቀኛው ተልይቶ የሚታይበት የትግል እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን፣ በረዢም ሂደት የባህል ለውጥም የሚታይበት ነው። የባህል ለውጥ ማምጣት ማለት፣ አንድን ህዝብ ከታሰረበት የውሸት ሰንሰለት አላቆ ዕውነተኛውን ነጻነት እንዲቀዳጅ ማድረግ ማለት ነው። እያንዳንዱ ግለ-ሰብ በእግዚአብሄር አምሳል የተፈጠረ ነው። የፖለቲካ ሰዎች በሳይንስ የሚመዘንን የህዝብ ፍላጎት ከህዝብ ጋር ሆነው ተግባራዊ የሚያደርጉበት ፖለቲካ የራስን አስተሳሰብ መለወጥ ብቻ ሳይሆን፣ በየወቅቱ የራስንም አስተሳሰብ መፈተኛ መሳሪያ ነው። ከላይ የተዘረዘሩት መሰረተ-ሃሳቦች በጭንቅላት ውስጥ ሳይቋጠሩ ስለፖለቲካ ማውራት በፍጹም አይቻልም። 5ኛ)ያለፉትን የአገራችንን የሃያ ዓመታት ፖለቲካ ታሪክ የተከታተለ ሰው የሚገነዘበው፣ የፖለቲካው ስልት ከላይ እስከታች ሙሉ በሙሉ ፊዩዳላዊ ነው። በማንኛውም ጥንታዊም ሆነ ዘመናዊ የፖለቲካ ፍልስፍናና ቲዎሪ የተደገፈ አይደለም። ትንተና የሚጎድለው፣ ከፍልስፍናና ከቲዎሪ ይልቅ፣ ያልሰሩ ግለሰቦችን ስም አግኖ የሚያቀርብና ተጨባጩን የአገራችንንም ሆነ የዓለም አቀፉን ፖለቲካና የኢኮኖሚ አወቃቀር በሳይንስ መነጽር እንንድንመረምር የሚያደርግ አይደለም። በአጠቃላይ ሲታይ፣ የፖለቲካ አየሩ የሰውን ልጅ ምንነት በማይረዱ፣ የህብረተሰብ ህግ ሊገባቸው በማይፈልጉና ከዕውቀት ይልቅ ቁንጹል አቀራረቦችን በሚያስቀድሙ የተወጠረ ነው። ሳይንስና ልዩ ልዩ ዕውቀቶችን ያላስቀደመ ፖለቲካ መጨረሻ ላይ ወደ ጥፋት ነው የሚያመራን።ዛሬ በአገራችንም ሆነ በውጭ ያለው ችግር ወያኔን የመጣሉና ያለመጣሉ ጉዳይ አይደለም። በኛ መሀከል ያለው የሃሳብ መዘበራረቅና በጠራ መንፈስ ለመታገል ያለመሻት ነው ለትግሉ እንቅፋት የሆነው። ከዚህ እዚህና እዚያ ተቆራርጦ ከሚካሄድ ትግል እስካልተላቀቅንና የመንፈስ አንድነት እስካላገኘን ድረስ ትግሉ የመረረ ይሆናል። የምንመኘውን በፍጹም አናገኝም። እኛም እንደ ብሄረ-ሰብ ታጋዮች እየመነመንና ባለፈው ታሪካችን ብቻ እየተጽናናን እስክናልፍ ድረስ እንኖራለን። ከዚህ አዙሪት ለመላቀቅ እያንዳንዱ ጥረት ማድረግ አለበት። ግለሰብአዊ ነጻነትና ነገሮችን ከሁሉም አንጻር መመርምር ብቻና የማያቋርጥ ምርምር ነው ወደ ዕውነተኛው ነጻነት የሚያመራን። ትግሉ ምናልባት የመረረ ሊሆን ይችላል። በየጊዜው ብቅና ጥልቅ የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዝብርቅርቅ ሁኔታዎችን ይፈጥሩ ይሆናል። የህዝብን ጥያቄዎች እስካልፈቱና የአገራችንን የተወሳሰበ ችግር በሳይንሳዊ መነጽር መርምረው ፍቱን መፍትሄ ማቅረብ ካልቻሉ እነሱም በበኩላቸው የሚጋለጡበት ሁኔታ ይፈጠራል። በዚህ ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ዕውነት በአሸናፊነት ትወጣለች። ይህ ጸሀፊ እስካሁን ድረስ የተቻለውን የበኩሉን አስተዋጽዎ አድርጓል። በሌላ መልክ ካልሆነ በስተቀር ከእንግዲህ ወዲያ በዚህ ሁኔታ በጽሁፉ አይቀጥልም። እልክ ተያይዞ አንድ ጥሩ ጽሁፍ ለማውጣት የራስን ኑሮ የሚያናጋ ይሆናል። ቀዳዳ ሲገኝ ብቻ ነው መጻፍ የሚቻለው። አሁን ግን ቀዳዳው እየጠበበ መጥቷል። በፕሮፌሽናል ደረጃ የሚሰራ ስራ በዚህ መልክ ሊቀጥል አይችልም። ካለበለዚያ የሰውን አስተሳሰብ እንዲጣመም ማድረግና ትግሉን ማዘበራረቅ ይሆናል። ስለዚህም አማራጭ መንገድ እስኪገኝ ድረስ ብዕሬን እንዳሳርፍ ተገድጃለሁ። ፈረንጆች ምርታማ እረፍት የሚሉት ዐይነት ነው። እስካሁን ድረስ ለሰጣችሁኝ መልካም አስተያየትም ሆነ ትችት፣ እንዲሁም ስድብ ታላቅ ምስጋና አቀርባለሁ። መልካም ንባብ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ! ፈቃዱ በቀለ fekadubekele@gmx.de ማሳሰቢያ: የሃሳብ ፍጹማዊነት እንደሌለና ሊኖር እንደማይችል እጅግ በጣም ጥሩ በሆነ ይዘት የተዘጋጁ መጽሀፎችን መመልከቱ ለትግላችን ያግዛል ብዬ አምናለሁ። Feyerabend, Paul, (1989); The Wrong Road of Reason, USA Orrell, David, (2010); Econo Myths: Ten Ways That Economics Gets it Wrong, UK