Saturday, June 17, 2017

የግንቦት 7ቱ መስቀሉ አየለ “በወልቃይት ተርጓሚዎች” ያሳበበው ውሸት ሲጋለጥ ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ-ሰማይ አዘጋጅ) Ethiopian Semay



የግንቦት 7ቱ መስቀሉ አየለ “በወልቃይት ተርጓሚዎች” ያሳበበው ውሸት ሲጋለጥ
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ-ሰማይ አዘጋጅ) Ethiopian Semay

የሳምንቱን ትዝብቴን በሌላ ርዕስ ለመዘጋጀት ስዘጋጅ የግንቦት 7 ደጋፊ ሃይላት  በሆኑት በብዙዎቹ የዲያስፖራ ተቃዋሚ ድረገፆች ላይ የግንቦት 7ን መናፍሕ በመልቀቅ ያጣበበው ከግንቦት 7ቶቹ ጉመቱ ሰዎች አንዱ የሆነው የግንቦት 7ቱ መናፍሕ “መስቀሉ አየለ” በሚል የብዕር ሥም ብዙ ውሸቶችን የሚለቀልቀው ሰውዬ፤“ድውያን አክሊሉን በደፉ ግዜበሚል ርዕስ የጻፈው ያነበበ ወዳጄ፤ እኝህ መኖኩሲት ምን እያሉ ነው፤ መስቀሉ አየለ የተባለ ጸሐፊ ተርጉሞታል እና እስቲ ንገረኝ? ሲል እንድተረጉመለት ጠይቆኝ ፤ጉዳዩ ሳነብበው እና ቪዲዮውንም ለማድመጥ ስመለከት፤ የመስቀሉ አየለ የፈጠራ ውሸት አልገጥም ስላለኝ፤ የሰውየው ውሸት በብዙ ጹፎቹ ስለታዘብኩለት፤ ወደጃንም ምን ብዬ እንደማስረዳው ግራ ስለገባኝ፤ አግራሞቴን በይፋ ባደርገው የተቀረው አንባቢም ይጨምር ይሆናል   በሚል ቀልቤን ስለሳበው፤ ሳምንታዊውን ዝግጅቴን በይደር አቆይቼ ይህን አጭር ትዝብት ለመጻፍ ተነሳሳሁ።

እጅግ የሚያስገርመው ብዙዎቹ የተቃዋሚ ዲያስፖራ ድረገፆች፤ በኔ ጽሑፎች ላይ እገዳ ከማድረግ ሌላ የእነ መስቀሉ አየለ የመሳሰሉት የግንቦት 7 መናፍሓን ቢልኩላቸው ፤ ውሸት ወይንም እውነት ብለው “ማጣራት/ኤዲት/ማድረግ የማይታሰብ ነው። እጅግ ይገርሙኛል። ይህ ጽሑፍም ቢያወጡት ልኬላቸዋለሁ። ባያወጡትም የለመድኳቸው ወገንተኞች ስለሆኑ ለኔ ‘አዲስ አይደሉም”። እንዳውም የሚቀጥለው ሰሞነኛ ጸሑፌ በነሱ ላይ ያነጣጠረ ስለሆነ ተከታተሉኝ።ከነዚህ ጋር መጪው ጊዜ ነፃ ውይት የሚባል ይፈቅዳሉ/ያስፋፋሉ ተብሎ የሚታሰብ አይደለም። የበረሃዎቹ ግልባጮች ናቸው።

መስቀሉ አየለ፤ የአማራ ተቆርቋሪ ለመምሰል ዛሬ ደግሞ  በምንም መስረጃ ማረጋገጥ በማይቻል የፈጠራ ሥራ ይዞ ወልቅያቴዎችን ለማስወቀስ ሆን ብሎ ከአመራ ጋር የማያገናኝ የወያኔ ዘፈን ተተርጉሞ ተላከልኝ ብሎ ሚዲያዎቹ ለጥፈውለታል። የተለቀቀው ስዕለ ድምፅ እንደ መስቀሉ አየለ ትዝብት ‘መነኩሴ’ ሳትሆን መነኩሴ ተመስላ የተወነች (“ወ” ን ጠበቅ) የወያኔ ሙዚቃ የኪነት አባል ነች። መስቀሉ አየለ እያለን ያለው፤ ‘አንዲት የትግሬ መነኩሴ አማራን ለመግደል ስላላት ፍላጎትና ጥላቻ ስትገልጽ የያዝኩዋት መቆሚያዬ እና ቆቤ ጠመንጃ ቢሆኑልኝ ኖሮ “ግፈኛውን አማራን” እገድለው ነበር እያለች በመዝፈን በአማራ ላይ ያላትን ጥላቻ ገልጻለች በማለት የፈጠራ ውሸቱን በመለቅለቅ ተረጐሙልኝ የሚላቸው ተርጓሚዎች “የወልቃይት ወንድሞች” ናቸው፤ ይላል።

 እንደገባኝ ወልቃይቶችን ዋሾች ለማድረግ ያደረገው ጥረት ከመሆኑ በቀር በመስቀል ስም የሚነግደው “መስቀሉ አየለ” ተደመጠ ብሎ በግንቦት 7 ድረገጽ በ ‘ኢካዴፍ’ እና በመሳሰሉት የለጠፈውን የወያኔ ቪዲዮ፤ ወልቃይቴዎች ተርጉመው ላኩልን የሚለን መስቀሉ “አንዲት ሐረግ እንኳ ስለ አማራ የተጠቀሰ ነገር ካለ መጠቆም እንደማይችል” እርግጠኛ ነኝ።

የተጠቀሰው ‘ቪዲዮ/ሙዚቃ/’ 1977 ዓ.ም አባዲት ደስታ በምትባል የወያኔ የኪነት አባል የተዘፈነ እና ዛሬ በዘመናዊ አቀራረጽ እንደገና ታድሶ የቀረበ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ፍሬ መሆኑን ስገልጽ፤ ክርክሬ የወያኔ ፕሮፓጋንዳ ውጤት ለመከላከል ሳይሆን፤ ያውም፤ እንደሚታወቀው ሕዝቡን ለመሳብ እንደማንኛውም ብሔረተኛ ድርጅት ወያንም ሕዝቡን ለመሳብ የማሕበረሰን ልቦና ለመሳብ፤ ልብስ ባሕል፤አጨፋፋር፤ ባሕሪ እየተከተሉ ‘መናፍሓቸውን” የሚዘረጉበት ዓይነተኛ መሳሪያቸው “ሙዚቃ” እንደነበረ ከዚያው ሰፈር በመውጣቴ አውቀዋለሁ። ነገር ግን እንደ እነ መስቀሉ አየለ የመሳሰሉ ግለሰቦች ግን፤ ወያኔን የሚከሱበት የጥላቻ ሥራዎችን ያጡ ይመስል፤ በጸሐፊነት ስም የግንቦት 7 ሰዎች የሚነዙትን የፈጠራ ውሸት ሌላም ውሸት እንደማይዋሹን ምን መተማመኛ አለን? በዚህ ጦርነት ተካሄደ፤ እንዲህ ያለው ወታደር ማረክን…..የሚሉ ዜናዎች እናደምጣለን፤ እንዲህ ያሉ የፈጠራ ውሸቶች ሲነገረን የሚነገሩን ዜናዎች እና ጽሑፎች እውነታነታቸው ምን ያህል እናምነዋለን? ከሚል ነው።

 ወደ ቪዲዮው ከመግባታችን በፊት ተረጎሙልን የሚላቸው የወልቃይት ወንድሞች እነማን ናቸው? ወልቃይቶች መሆናቸው ማለትም  “የፈጠራ” ያለመሆኑ በምን እናረጋግጣለን? የግንቦት አጋር የሆኑ ኤርትራ ውስጥ ያሉት ታጣቂ ትግሬዎች ተረጎሙልን ቢለን  “የአይጥ ምሰክር ድምቢጥ” ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም ወልቃይት ወንድሞች የሚባሉት እነማን መሆናቸው ቢገለጽልንና በምን ታምር እንደተረጎሙት መልስ እንጠብቃለን።    

የመስቀሉ አየለ ጽሑፍ እና ርዕስ እንዲህ ይላል። “ድውያን አክሊሉን በደፉ ግዜ (መስቀሉ አየለ)”
(Posted by: ecadforum June 16, 2017)

“ ይህን ቪዲዮ ተርጉመው የላኩልኝ የወልቃይት ወንድሞቸ ናቸው። ወያኔ ለክፋት የጫነባቸውን የትግርኛ ቁዋንቁዋ እነሱ ለበጎ እያዋሉት ነው።ቢያንስ እንዲህ ያለውን ነውር እያወጡ ያሳዩናል። ቋንቋ መግባቢያ እንጅ ዘር እንዳልሆነ ወልቃይቴዎቹ እያሳዩት ነው። ትርጉሙ ሲጠቃለል እንዲህ የሚል ይዘት አለው አሉ። በትግርኛእዛ ምርኩሰይ ጠመንጃ ተትኸውን ነዚ ግፍዐኛ አምሓራይ ምቀተልኩላ አነውንይሄ በቀጥታ ሲተረጎም ይሄ የያዝኩት ምርኩዝ ጠበንጃ ቢሆን ኖሮ ግፈኛውን አማራ በገደልኩበት ነበረ የሚል ትርጉም ይሰጠናል።ስላጠለቁት ኮፍያም ልክ እንደዛው እየዘፈኑ ነው ሲጀምሩ በኮፍያቸው ነው የሚጀምሩት።ኮፍያዬ ቦንብ ቢሆን ኖሮ አማራን በገደልኩበት ነበር። ምርኩዜ ጠመንጃ ቢሆን ኖሮ አማራ በገደልኩበት ነበር። ረሽነው እምበር ተጋዳላይ

ከላይ እንደገለጽኩት መስቀሉ አየለ መነኩሴ መስሎት “በአንቱታ” እየጠራት ያለው ሙዚቀኛዋ ‘አባዲት ደስታ’ ወያኔ እንጂ ‘አንቱ’ የምትባል መኖክሴ አይደለችም። በተደመጠው ደምፀ-ስዕሉ/ሙዚቃው/ ውስጥ የትግርኛ ቋንቋ አዋቂ እና የማድመጥ ችሎታ ያለውም ሆነ የማድመጥ ችሎታም ባይኖሮው “አማራ” “አምሓራይ” የሚል ደምፅ ወይንም ቃል፤ ማድመጥ ይችላል። በዚያ ቪዲዮ ውስጥ ግን ‘አማራ” ወይንም “አምሓራይ” የሚል በምንም ተአምር አያገኝም። ዘፋኝዋ የምትለው፤ ይህች መቆሚያየ እና ቆቤ ጠምንጃ ብትሆን ኖሮ እኔም  “ግፈኛን” እገድልበት ነበር” ነው የምትለው። እንዳውም ተርጉሞው ላኩልኝ የሚለው ትርጉም የሌለ የፈጠራ ቃላት ከመጨመር ባሻገር፤ “እዛ ምርኩሰይ ጠመንጃ ተትኸውን ነዚ ግፍዐኛ አምሓራይ ምቀተልኩላ አነውን” የሚለው “ ንግፍዐኛ” (“ለ”ግፈኛ) እንጂ “ነዚ ግፍዐኛ” (ለዚህ ግፈኛ) የሚል በዘፋኝዋ አንደበት አልተደመጠም። ይህ የቃላት ስህተት ሳይሆን ሆን ተብሎ “አማራ” የሚለውን ቃል ለመጨመር “ነዚ ግፍዐኛ” “ለዚህ”/ ግፍኛ አማራ/ የሚል የፈጠራ ቃላት እና ሐርግ ተጨምሯል። “ረሽነው- እምበር ተጋዳላይ” (ከየት እንዳገኙት አልገባኝም) ማንን “ረሽነው”ተብሎ ቢጠየቅ? አማራውን! የሚል ፈጠራ ታገኛለህ ተርጓሚዎቹ ከየት እንዳመጡት ይገርመኛል። የተማሩ ጸሐፊዎች ወደ ተራው የፓልቶክ መንደርና የፈጠራ ስራ ከገቡ ያልተማረው ማን ያስተምረው?

በመስቀሉ አየለ ሰብከት “የወልቃይት ወንድሞች የተጫነባቸው የትግርኛ ቋንቋ ለበጎ አውለውታል” ሲል ይደሰኩራል። መጀመሪያ ነገር ወልቃይቶች ትግርኛ መናገር የቻሉት ወያኔ ሲገባ ሳይሆን ወያኔ ሳይጫንባቸው ድሮ ከጥንት ጀምረው ነው ቋንቋውን የሚችሉት፤ እነሱም እንደሚሉት ትግርኛ ብቻ ሳይሆን ኩናማ እና ሱዳንኛ/ዓረብኛ/እንደሚችሉ ተናግረዋል። መስቀሉ ግን ፖለቲካውን አሳመርኩ ሲል እነሱን ወደ ዋሾነት ከተታቸው። ሆን ተብሎ ይሆን? አላውቅም! ሲዋሽ ግን በልኩ ይሁን። ውሸት ሲለቀለቅ አውነቱም ጭምር ውሸት እያሉ ጠላቶች እንደሚጠቀሙበት የዲያስፖራ ሊቃውንት ሊገባቸው አልቻለም። ሚዲያዎች በወገንተኛነት እያመኑ ኤዲት ሳያደርጉ የሚላክላቸውን የመለጠፉን በሽታቸው ለመጠንቀቅ ከዚህ ይማሩ።

ይልቁንስ አቶ መስቀሉ እንድትነግረን የምንፈልገው የራስህ ኢሳት ቴ/ቪ በ5 ሚሊዮን ትግሬዎች እና በ90 ሚሊዮን ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል መደረግ ያለበት የፍጅት ግብግብ የገለጸልንን ያንተው ይፕሮፓጋንዳው ክፍል ኢሳት “የተበላሸን ባሕርና ዓሳን ማስወገዱ አንዱ ነው፡’ የባሕር ውሃ ማስወገድ(“የገማ ዓሳ ከነውሃው ካልተደፋ አይበጅም) ብሎ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያስተላለፈውን የዘር ፍጅት ትርጉም፤ ምን ማለት እንደሆነ ብትነግረን መስቀሉም አይወቅስህም። ብዙዎቹ የዲያስፖራ ተቃዋሚዎች ይህንን ጥያቄ ስንጠይቅ፤ እንዳንጠይቅ አግደውታል። ይህ የሚያመለክተን ስለ እኛ የትግራይ ሰዎች ህይወት ምናቸው እንዳለሆን እና እንደማያሳስባቸው ማመላከቻ መብራት ነው። ይህ ደግሞ በቀላሉ ታፍኖ የሚቀር አይደለም። ሚዲያዎች ይህንን ወገንተኛ እና የምንተቸውን “አፈናችሁን” የትም እንደማይደርስ ልገልጽላችሁ እወዳለሁ። ከወያኔ የአፈና ባሕሪና የሚያስከትለው ውጤት መማር ለምን እንደማይችሉ ግን ሁሌም “ፍንቁርናቸው” ይገርመኛል። ማፈን፤የባሰውን ትግላችንና እልሃችን እንዲቀጥል ያበረታታናል እንጂ አያለሳልሰንም። አባሪም ተባባሪም በታሪክ እንፋረዳለን!

አመሰግናለሁ
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ አዘጋጅ Ethiopian Semay) getachre@aol.com