Wednesday, November 30, 2011

ሰንደቃላማችን በስያትል ባንዳዎች ለድርድር ቀረበ!


To see the page/font with a wider range, please press the key Ctrl and + sign. To view the page/font with a narrow range, please press the key CTRL and _ sign.

የሚታየው የወያኔ ገበና ማህደር አዲሱ መጽሐፍ ለመግዛት $30.00 ዶላር ሲሆን ይድረስ ለጎጠኛው መምህር መጽሐፍ ደግሞ $25.00 ወይንም ሓይካማ የሚለው የትግርኛ መጽሐፌ ደግሞ $15.00 ዶላር ብትልኩ መጽሐፎቹን ማግኘት ትችላላችሁ።Getachew Reda P. O.Box 2219 San Jose, CA 95109 getachre@aol.com Phone (408) 561 4836

ከሃዲ ባንዳዎችን ራስ ሙሉጌታ እንዲህ ነው የሚያደርጓቸው።”
ከማቀርብላችሁ ታሪክ የተቀነጨበ።


ከላይ የሚታዩት ሁለት ፎቶ ግራፎች አክሱም ውስጥ ይገኛሉ። አንዱ አጼ ዮሐንስ የተናገሩት የአገር እና የሰንደቃላማ ትርጉም ሲሆን። ከዳገት ላይ የሚታየው ገዳም ከአክሱም ከተማ ሁለት/ሦስት ኪሎሜትር ራቅ ብሎ የሚገኝ ካሁን በፊት የደብሩ አስተዳዳሪ የነበሩት የኔ አጎት  ከነፎቶግራፋቸው በዚህ ድረገጽ ለጥፌው የነበረው የአባ መንጠሌዎን ደብር ነው። በገዳሙ የተቀበሩት እና የመቃብራቸው ሃውልቱት አሁንም በግልጽ ቆሞ የሚታየው ከተስአቱ ቅዱሳን አንዱ አባ መንጠሌዎን የመሰረቱት ገዳም ነው።

እንደ ምታዩት ገዳሙ የተመሰረተው በጣም ረዢም በሆነ ጫፍ ተራራ ላይ ስለሆነ፤ ልጅ ሆኜ ባዓሉን ለማክበር ከወላጆቼ ጋር ሄጄ፤ ብርዱ አይጣል ስለነበር፤ የአባታችን የእህት ልጅ (በወቅቱ ዲያቆን ገብረክረስቶስ) ከነበረው ጋር ሌሊቱ ያኔ ወደ መቅደስ አልሄድም ብየ በአባታችን መኖርያ ውስጥ ተኝቼ አድሬ (ሲቀደስ ብቻየን ቅዱሳን መጻሕፈቱ በተከማቹበት ቤት ብቻህን አትቅር ተብየ እምቢ ስላለሁ ተኝቼ በማደሬ ወደ ሦስት ሰዓት “ከንጋቱ/ሌሊት” ፀጥ ባለው አስፈሪ የገዳም ሌሊታዊ ፀጥታ ተኝቼ እያለሁ በገዳሙ  አድባር “ዓንደረቢ” ይሉታል ጉሮሮየ ታፍኜ አፌ ተዘግቶ በወቅቱ፤ የለፈለፍኩት የህጻንነት ፍርሃት ምን እንደገጠመኝ ሳስታውሰው አሁን አሁን ያስቀኛል/ይገርመኛልም።)  ጥዋት ሲነጋጋ ሰንደቃላማ እንድሰቅል ቀስቅሶኝ፤ በታዘዝኩት መሰረት ወደ ላይ ወጥቼ ስነደቃላማው ለመስቀል ገደሉ አፋፍ ላይ ስሞክር ድንጋይ አዳልጦኝ ወደ “አነስተኛው” ገደል  በመወደቅ ትረፍ ብሎኝ ባንድ ቋጥኝ ተቀርቅሬ በመትረፌ በሰዎች ተጎትቼ ስድን ሰንደቃላማዋ አንገቴ ላይ ከጠመጠምኩት ነጠላ ከነ እንጨቷ ተጠምጥማ ስለነበር እጄ ሳልይዛት እሷም አብራኝ ከገደሉ አደጋ መዳንዋ ሳስታውሰው አሁን የዛሬዎች ባንዳዎች ሰንደቃላማዋን አሳንሰው ሲመዝኗት ማየቴ አንጀቴ ይቃጠላል። ታሪክ በማሕደሩ እየዘገበን ይጓዛል፤እኛም አየተመዘገብን አብረነው አንጓዛለን።

ሰንደቃላማችን በስያትል ባንዳዎች ለድርድር ቀረበ!
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ ድረ ገጽ)
አርዕስቱ ሰንደቃላማችን በስያትል ባንዳዎች ለድርድር ቀረበ! ወይንም በእንግሊዝኛው “ The Seattle Conspiracy” ብትሉት ቅር አይለኝም።
 ሌላ መነጋገርያ ርዕስ ትቼ ለዛሬ ይህን ሳቀርብ ይህ ፋታ ያልሰጠኝ ሁሉም አገር ወዳድ እና ለኢትዮጵያ ሰንደቃላማ የክብር ቦታ የሚሰጥ ዜጋ ሁሉ አበክሮ መከታተል ያለበት ጉዳይ ለማስገንዘብ ነው። በፈረንጅ አቆጣጠር Saturday November 12, 2011 በስያትል ከተማ ውስጥ በተሰባሰቡ ጠባብ ብሔረተኛ ግለሰቦች (ከትግራይ፤ ከኦሮሞ፤….ከመሳሰሉት ግለሰቦች) የተዘጋጀው ስብሰባ “የኢትዮጵያን ሰንደቃላማ ለኦነግ ባንዳዎች ለድርድር ቀርቧል”።
ስብሰባውም ካሁን በፊት ከተደረገው ስብሰባዎች ሁሉ በጣም “ልዩ” ያደረገው አንድ  የስብሰባው አጀንዳ አድናቂ የሆነ ግለሰብ የሚከተለውን በድረገጸች ያስተላለፈውን አረፍተ ነገር ይመለከቱ። እንዲህ ይላል።
 By Kirubeal Bekele-  Seattle had its first Forum meeting last Saturday November 12, 2011. This meeting was highly anticipated mainly due to its unique nature of trying something new that has never been tried before.” እንግዲህ ልዩ ያደረገው ስበሰባው ባሕሪ የኢትዮጵያ አገራዊ ሰንደቃላማ  ለሽብርተኛው “ለኦነግ ባንዴራ” ለድርድር በመቅረቡ፤ ስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ሁለቱም እንዳይውለበለቡ የተደረገበትን ባሕሪ ነው “ልዩ የሆነበት ምክንያት”።
በወቅቱ በተዘጋጀው ስብሰባ ተናጋሪ እንግዶች ተብለው የተጠሩ የክብር እንግዶች የግንቦት 7ቱ መሪ ብርሃኑ ነጋ እና የኦሮሞ ነጻ አውጪ ደርጅት ፀሐፊ አሚን ጃንዳይ ማለትም ሁለቱም ድርጅቶች በኢትዮጵያ/ትግራይ ሕዝብ ላይ ለፈጸመው ወንጀል ተፈላጊ በሆነው በኤርትራው “ሽብርተኛ” “ኢሳያስ አፈወርቂ” የሚደገፉ እና ሕብረት በተባለ ኢትዮጵያዊ ድርጅት ውስጥ የተካተተው የታንዱ ሊቀ መንብር አረጋዊ በርሐ ናቸው።
ሦስቱም እንግዶች ሲጋበዙ አዘጋጆቹ የተስማሙት አንድ አጀንዳ ነበር። አጀንዳውም “አዳራሹ ውስጥ የኦነግ ባንዴራ ካልተሰቀለ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰንደቃላማም መሰቀል የለበትም በሚል ተስማምተው፤ በአያቶቻችን ደም ተከብሮ ወደ ጥንት ስፍራዋ በመመለስ በተባበሩት የዓለም መንግሥታት/አገሮች የክብር ስፍራ ተሰጥቷት በያገሩ አምባሲዎች እና ስብሰባዎች በክብር እንድትውለበለብ የተደረገቺውን የእናት አገር ኢትዮጵያ አርማ እንደ ማፈሪያ ጨርቅ እና እንደ ድርጅታዊ አርማ ተወስዳ እንዳትውለበለብ በመስማማት ሰንደቃላማችን በስያትል ባንዳዎች ለኦነግ ባንዴራ ሲሉ ለድለርድር አቅርበዋታል።
ከላይ የተጠቀሰው የባንዳዎች ሴራ በMeleket Ethiopian Radio: (ካናዳ ውስጥ የሚተላለፍ) በሚባለው ራዲዮን የተደመጠውን በኢትዮጵያዉያን ሃይሎች እና ለሻዕቢያ እና ለኦነግ ጥብቅና የቆሙ አዲስ በቀል የቅርብ አመት መጤ ባንዳዎች የተደረገው ውይይት ነበር ሴራውን ልናደምጥ የቻልነው።  (http://ecadforum.com/blog1/2011/11/28/meleket-ethiopian-radio-interesting-radio-discussion/)
ከላይ የተመለከተው የራዲዮ ውይይት የምታዳምጡት በሁለት ተጻራሪ ጎራ የተሰለፉ ወገኖች ስታደምጡ በተለይ በሻዕቢያ እና በኦነግ ፋሺስታዊ ፖለቲካ የተማረከ “ለሰይጣን ጥብቅና መቆም ባልተለመደው ዓለም ለዲያብሎስ ጥብቅና የቆምኩኝ/ዘዴቪልስ አድቮኬት ነኝ” “ኢትዮጵያ ሰንደቃላማ በሕዝባዊ የስብሰባ ላይ ቢሰቀል ባይሰቀል ጉዳዬ አይደለም” “ ሻዕቢያዎችን አጭበርባሪዎች አትበሏቸው! አጭበርባሪዎች አይደሉም!” “ሻዕቢያዎች በጉልበት አሸንፈውናል!”  ‘እገሌ ሲ አይ ኤ ነው … ምናምን የምትሉት ያፈጀ ያረጀ የድሮ ተረት ተረታችሁን አታውሩ…..” በማለት በኩራት እና በትዕቢት ያለ ምንም ማሰላሰል እና ማመንታት ሲደነፋ የምታደምጡት የ97ቱ ዓ.ም. ያዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሊቀ መንበር ነበርኩ የሚል “ሌሎቹ ሲጋፈጡ እሱ ግን ነብሱን ለማዳን  የተደበቀ ጮሌ”፤የግንቦት 7 እምባ አፍሳሽ እና ecadforum.com የተባለ ድረገጽ እና ፓል ቶክ አዘጋጅ የሆነው “ተክሌ” የተባለው ካናዳ አገር የቫንኩቨር ኗሪ ወጣት ከላይ የተመለከተው ማሕደር በመግባት በጥንቃቄ እንድታደምጡት እጋብዛለሁ።
ልጁ ጅላጅል ብቻ ሳይሆን ወላጆቹን፤ አገሩን፤ ሃይማኖቱን፤ሰንደቃላማውን ክብር ሲያጣጥል እና የሰንደቃላማ ክብር እና ከባድ ዙፋን አንደ ኳስ ጫዋታ የሸሚዝ ልውውጥ  ያክል በመመልከት ሲዘልፍ ነውር መሆኑን ብቻ ሳይሆን ጅላጅልነቱ፤ በጣም አደገኛ እና ባሕልንና ያገሪቱ ሰንደቃላማ ክብርን በማይገባ “አልትራ አናርኪዝም” (አክራሪ አጣጣይ) የፋሺሰቶቹ “ቀይሕ ዕማባባ” የወላጅ እና የአዛውንቶች ውጤት
የሚረግጥ ባሕሪ የተጠናወተው አደገኛ ኩታራ መሆኑን ትገነዘባላችሁ። የዚህ ልጅ አነጋገር እና የመለስ ዜናዊ ለሰንደቃላማ እና ያገር ክብር ያለው የዘቀጠ ንግግር ስታስተያዩት ልዩነት አታዩም። ለሚወዳት ፍቅረኛውም፤ ለአገርም፤ለሰንደቃላማም ምንም ክብር የማይሰጥ ተደራዳሪ እና አልትራ መሆኑን ትገነዘባላችሁ። መለስ ዜናዊ ኣእላፍ ሕዝብ አሰልፎ ለሞት የዳረገበትን የባድሜ መሬት “ከርስድ ላንድ” ብሎ ነበር የሰየመው። ቢሄድም ቢመጠም ጉዳየ አይደለም/ኢን ፕሪንሲፕል መሬቱ ለወራሪው ለሻዕቢያ እንዲሰጥ ተስማምተናል። ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ‘አንወያይ” ነበር ያለው ያ ሁሉ ሰው ለሞት ዳርጐ። ተክሌ እና የሲያትል ባንዳዎችም የኦነግ ባንዴራ ካልተሰቀለ የኢትኦጵያ ሰንደቃላማም እንዳይሰቀል/እንዳይውለበለብ ከጠየቁት ጋር ተስማምተው ለድረድር ቀረቡ። ያውም “ጥይት ሳይጮህባቸው”!
የዚህ ኩታራ ድፍረት መጠን ከማለፉ የተነሳ “ካረንት አፈይርስ/ኢካዴፍ” በሚባለው ጸረ ትግራይ ዘመቻ በሚካሄድበት የፓል ቶክ/ራዲዮን የሚኩራራ ወጣት መሆኑን አትዘንጉ።ይህ ድፍረት እንዴት እና በእነማን አመካይነት እየተከናወነ እንደሆነ ታሪክ እየዘገበው ነው። ታሪኩ ደግሞ በድምጽ መቅጃ እየተዘገበ ይገኛል። ወጠቶቹ የባንዳ ቃላቸው እና አቋማቸው በየሄዱበት አንደ እነ መለስ ዜናዊ እና ኢሳያስ አፈወርቂ እንዲሁም እንደ እነ ሌንጮ ለዘላለሙ በሕዝብ ጀሮ እየተደመጠ ይኖራል። ሲያረጁም ያፍሩበታል። የጥቁር ሕዝቦች አርማ በመሆን ወድቃ የተነሳቺውን ሰንደቃላማችን ዳግም በዓለም አደባባዮች እና አዳራሾች አንድትውለበለብ  ወላጆቻችን ከጣሊያን ወራሪዎች እና ባንዳዎች ጋር ያደረጉት ግብግብ ዳግም እንዲመለከቱት በዚህ ድረገጽ ዛሬም በድጋሚ ልብ እንድትሉት እጋብዛችለሁ።
የሲያትል ባንዳዎች እና የግንቦት እና የኦነግ ባንዳ ጭፍራዎች ወላጆቻችን ያሳለፉት መራራ ሕይት እና ግብግብ፤ የተባበሩት መንግሥታት የማያውቀውን “የፈሺስቶች የኦነግ የድርጅት ባንዴራ” ዓለም ካወቀው እና አፍሪካኖች እና ጃማይካኖች በሚኰሩበት ብሐራዊ ሰንደቃላማችን ለድርድር ማቅረብ ታሪክ የማይረሳው አስቀያሚ የፖለቲካ ንግድ በመሆኑ በዚህ አሳፈሪ ሴራ የተሳተፉ እያንዳንዱ ባንዳ ከታሪክ እንዲማር ከዚህ ቀጥሎ ያለውን የባንዳዎች ቅጣት እና የወላጆቻችን ቆራጥ አቋም እነሆ። ባንኩቨር ወይንም ሲያትል እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ አንኖርም እና የሃገር አርማ መድፈር እንችላለን የምትሉ ወይንም ከኢትዮጵያ ሰንደቃላማ ጋር የተፈራረምነው ውል የለም የምትሉ ባንዳዎች ሁሉ እናንተ ካልፈረማችሁበት ወላጆቻችን በድረድር ሳይሆን በደማቸው ፈርመው የዓለም ሕዝቦች ፤መስጊዶች፤ቤተ መቅደሶች፤ገዳማት፤መካነ መቃብሮች፤ አደባባዮች፤ ሰማዩ፤ኮዋክብቱ፤ እእዋፋት እና አራዊቱ ሁሉ እንዲያከብራት አድርገዋል። አናከብርም ብሎ ከጠላት የተሰለፈ ወይንም የሰንደቃላማን ክብር ዝቅ ያደረገ፤ የዘለፈ፤ያንቋሸሸ፤ለድርድር ያስተናገደ፤ “ባንዳ” ምን ቅጣት ይደረስበት እንደነበረ የሚከተለው የታሪክ ቅጣት እንድናስታውሳችሁ ተገደናል። የነዚህ ሰዎች አገር የማፈራረስ ስልት የሚከሽፈው ዛሬም እንደ ትናንቱ ባንዳዎች ፊት ለፊት ካልተጋፈጥናቸው እንደ እነ ሻዕቢያዎች እና ወያኔዎች የመቶ አመት ታሪኩ ግብግብ ብቻ ሳይሆን እየደረሰን ያለው “ሰንደቃላማችንም ጭምር ለድርድር ቀርቦ እንዳይውለበለብ የማድረግ ዘመቻው ወዴት እያመራ እንደሆነ መገንዘብ አያዳግታችሁም የሚል እምነት አለኝ።
የሚከተለው ታሪክ የተገኘው ዶ/ር ተስፋዬ መኮንን ባይለየኝ የተተረጎመ “ቀይ አምበሳ” ከተባለ ለኢትዬጵያን ሰንደቃላማ እና የነፃነት ክብር ብሎ ሲጀመር እስኪጨረስ ከ1928 .ም በጣሊያን ወረራ የተደረገው የመከላከል ውጊያ ተካፍሎ ለኢትዮጵያን ክብር የቆመ ኩባዊው ኮሎኔል አሊሃንድሮ  ዴል ባዬ በዓይኑ የተመለከተውና በጦርነቱ የተሳተፈበት ትዝታ በጻፈበት መጽሐፍ የተቀነጨበ ታሪክ ነው። ታሪኩ ረዘም ቢልም ታግሳችሁ አንብቡት። ሶፋ ላይ ተመቻችቶ ረዢሙን ታሪካቸው ለማንበብ ከሰለቸን ሕይታቸው አከላታቸው አጥተው “ኢትዮጵያዊ” ዜጋ የሚለው የምንኮራበት መታወቂያ ደብተራችንን እንድንይዝ ያደረጉትን የበጐ አድራጊ ወላጆቻችንን ገድል መናቅ እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ። 
“ ………..በዚህ መንገድ ህይወት
አንድ ቀን ምሽት ወደ አርባ የሚጠጉ ጥቁር የቆቦ ጐሳዎች ወደ እኛ ሰፈር ተሳስተው ገቡ። ሀሳባቸው ከጣሊያን ጦር ጋር ለመደባለቅ ነበር። የእኛን ሰራዊት “የዱቼ” ሰራዊት ከሆኑት ከኤርትራ ተወላጆች ጋር በማመሳሰል በስህተት ነው የተደባለቁት። ስህተታቸውን ሲያውቁት እጅግ በጣም ዘግይተው በመሆኑ ወደ ወደ ላ ሊመልሱት አልቻሉም።
ራስ ሙሉጌታም ወደ አሉበት ቦታ እንዲመጡ አስጠሯቸው። በጥሩ አቀባበልና በተለሳለሰ መንገድ ያነጋግሯቸው ጀመር።
“ለምንድነው ከጣሊያኖች ለማበር የምትሄዱት?”
እነዚህ አሳዛኝ የሆኑ የቆቦ ተወላጆች በፍጹም እውነተኝነት እንዲህ ሲሉ መለሱ።
“ጌቶች! ምክንያቱ ለእያንዳንዳችን ጠመንጃ በየወሩ 20 ታለር የእነሱን ገንዘብ ስለሚሰጡን ነው።”
“20 ታለር ጥሩ… እኔ ደግሞ 20 ጅራፍ እሰጣችለሁ። እኔ ግን በየቀኑ ነው።”
ያሉትን ፈጸሙት። ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ብዙ ከፍተኛ ሥነ ሥርዓት እየተደረገ እስረኞቹ እየተሰበሰቡ በዚያች የአለንጋ ግርፍ ይተለተሉ ነበር። ለብዙ ቀናት ቁስላቸው እስኪገጥምና እስኪጠግ ድረስ ይተዋአቸውና እንደገና ሌላው ዙር የአለንጋ ግርፍ ይቀጥላል። እንዲህ እያለ ጨዋታው ሲቀጥል ሌላው አይነት የቅጣት አይነት ተፈፀመባቸው። አፍንጫቸውን፤ እጃቸውን፤ጆሯቸውን፤ምላሳቸውን፤ከንፈራቸውን ቀስ እያሉ ተራ በተራ ቆረጧቸው። አንዱን የሰውነት ክፍል ከቆረጡ በ እንዳይሞቱ ያክሟቸዋል። ሲጠግግ ሌላውን ይቆርጣሉ። የመጨረሻው የተደረገው በመጨረሻው ቀን በአንድ በጋለ ብረት ፊታቸው ላይ ምልክት ጠባሳ ማድረግ ነበር። ይህ ደግሞ ከሃዲ ለመሆናቸው መለያ እንዲሆን ነው። እናም ብዙዎቹን ዲዳ፤ ዓይነስውሮች፤ እጅ አልባ፤አፍንጫ ቆራጣ አስቀያሚ ገፅታ ይዘው አንድ መልዕክት የያዘ ፅ ሑ ፍ አሲዘዋቸው ወደ ጣሊያኖቹ መስመር መሄጃ መንገድ ላይ እንዲቀመጡ አደረጓቸው። የፅሑፉም መልዕክት እንዲህ ይል ነበር።
“ከሃዲ ባንዳዎችን ራስ ሙሉጌታ እንዲህ ነው የሚያደርጓቸው።”
ደራሲው ኮሎኔል አሊሃንድሮ ስለ ቅጣቱ አስመልክቶ እንዲህ ይላል፡-
“ በበከሌ እንዲህ ያለው ነገር እንዳይፈፀም ተቃዉሜአለሁ። ምክንያቱም እጅግ ዘግናኝ አሰቃቂ ቅጣት ብቻ መሆኑ ሳይሆን እንዲህ ላለው ነገር ማረጋገጫ የጣልያን መንግሥት ካገኘ በኢንተርናሽናል ሊግ ኢጣልያዎቹ አጋጣሚና ተሰሚነትን ሊረዳት ስለሚችል ነው።ራስ ሙሉጌታ ግን አፍጥጠው፤
ለእኔ ኢንተርናሲዮናልና አንድ የሞተ ጅብ አንድ ናቸው። ሁሉም አገሮች አቢሲኒያን በመቃወም ሊሰለፉ ይችላሉ። እኔ ግን ሁሉንም ላሸንፋቸው እችላለሁ። ከፈለጉ ሁሉም ፈረንጆች ይምጡ ልንሸነፍ አንችልም! ልንሸነፍ አንችልም፤ ገባህ!?”
ራስ ሙሉጌታ ማታ ማታ ስለ ጦርነት ድርጊታቸውና ውሎአቸው በጐራዴያቸው ነጮችን እንዴት እንደቆራረጡና እንደገደሏቸው ሲተርኩ ያመሻሉ።
በእነዚህ ቀናት በአንዱ ከራስ ካሳ አንድ መልዕክት ደረሰን። የጥቁር ሸሚዝ ለባሾች ከፍተኛ የጦር ቡድንን ከብበው እንደሚገኙና ለማጥፋትና ለማሸነፍ ወሳኝ በሆነ መልኩ ለመግጠም ተጨማሪ ሀይል እንደሚያስፈልጋቸው ነበር የጠየቁን። በተለይ እንድንሰጣቸው የጠየቁን በዚህ በጦርነቱ ላይ የሁሉን ኢትዮጵያዊ ቀልብ የሚስበውንና ሁሉም እንዲኖረው የሚፈልገውን ፀረ አውሮፕላን መትረየስ በመድፍ ሆነ በዘመናዊ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ለሚደረግብን ጥቃት ለመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ ወቅት ከፍተኛ ጠቀሜታ ስለሚሰጥ በጣም ተፈላጊ ስለነበር ነው። ራስ ሙሉጌታ ጓድ “ዶኒ ኦዳዩን” እና  እኔን ወታደሮቻቸውንንና ለውጊያ የሚያስፈልጉንን ቁሳቁሶች ሁሉ ይዘን እርዳታውን እንድናደርግ አዘዙን። ዝግጅታችንን ጨርሰን ጉዟችንን ልንጀምር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩን ልጃቸውን ታደሰን ጠርተው ከእኛ አገር እንዲደባለቅ አዘዙት።
“እነኝህ ውሾች ፈረንጆች መያዝ አለባቸው። አንድም በህይወቱ ወይም ጤነኛ ሆኖ መቅረት የለበትም።” አሉን።
ሊመሻሽ ሲል ጉዟችንን ጀመርን። ድቅድቅ ያለ ጨለማ ሙሉ በሙሉ ፀጥ ባለው ሰፈር ሲሰፍንና ሌሊቱ እየጠለቀ ሲሄድ ከወታደሮቻችን ጋር ወደ ሞት ወይም ወደ ድል አቅጣጫ ወደ ጠላት ሰፈር መሬት ለመሬት መሳብ ጀመርን። ሊነጋጋ ሲል ራስ ካሳ በያዙት ስፍራ ደረስን።
ቀዳሚ ጦራቸው ወደ ብልህ አለቃቸው ድንኳን ድረስ ይዘውን ሄዱ። ራስ ካሳም ጠላትን ከብበው በሚገኙበት ከፍተኛ ተራራዎች ላይ ከሚገኙት የተፈጥሮ ዋሻዎች ሆነው የ “ዱቼ” አገልጋይ ወታደሮች የያዙትን ቦታ ያሳዩን ጀመር።
…….. ይህ በእንዲህ እንዳለ በቡድን እየተከፈለን በተራሮቹ መሀል በተለያየ አቅጣጫ ቁልቁል መውረድ ጀመርን። እነኛ የኢትዮጵያ ልጆች ቁልቁል ሲወርዱ ጐራዴያቸውን መዝዘው አየሩን እየቀዘፉ በመንገዳቸው ላይ ሲጓዙ በጣም ያስፈሩ ነበር። ክፉኛ የተደናገጡ ጣልያኖች እውነተኛውን የሽንፈት ፊት ለማሳየት ሁለት እጆቻቸውን ወደላይ እያነሱ ያለምንም ጥርጣሬ የራስ ካሳ ወታደሮች ቃል በገቡላቸው መሰረት የጠየቁትን እንደሚያደርጉላቸው ባለመጠራጠር በሙሉ ተማምነው ነበር። ሆኖም ግን ቀዳሚዎቹ የጣልያን ጥቁር ሸሚዝ ለባሾች የመጀመሪያው መስመር ላይ እንደደረሱ ያ ዘግናኝ ጐራዴ እላያቸው ላይ ጭንቅላታቸውን በመፍለጥ እጆቻቸውን በመቁረጥ አንጀታቸውን በማውጣት ጀመሩ። በዚህ ዘግናኝ ጥቃት የተደናገጡት ጣልያኖች ለዚህ መጠነ ሰፊ ለሆነው ምላሽ ለመስጠትም ቢፈልጉ በፍፁም አይችሉም። ጊዜ አልነበረምና። ይህ ድንገተኛ የሆነ ጭፍጨፋ ለሁለት ሰዓት ያህል ቀጠለ። በመጨረሻም የ8000 ነጮች ሬሳ አንዱ በአንዱ ላይ ተነባብሮ  ምድር ደም ለብሶ፤ የነበረው እንዳልነበረ ሆኖ ቀረ። ውጊያው ፊት ለፊት ጨበጣ ለጨበጣ ነበር። 40,000 ኢትዮጵያውያን ጦረኞች ተሰልፈዋል። ያንን የሚጠሉትን ወራሪ ፊት ለፊት በጨበጣ ውጊያ ስጋ ለስጋ በመግጠም ፈጅተውታል።
አንድ የጣልያን ሻምበል ብቻ ከነ ህይወቱ ይዘዋል። እሱም ቢሆን በታደሰ ሙሉጌታ (የራስ ሙሉጌታ ልጅ ነው) ነው። ታደሰም ከነ ህይወቱ  ወደ ራስ ካሳ ዘንድ እንዲያቀርቡት አዘዛቸው። ጦሮኞቹ ከጦሩ ፊት ልብሱን አስወለቁት። የሰሜን ተራሮችን እየቧጠጠ እስከ አለቃቸው ድንኳን ድረስ እንዲጓዝ አደረጉት። ከጫካው በቆረጣቸው ልምጮች እየገረፉ በዚህ ባልታደለ ነጭ ሰው ቆዳ ላይ ቀይ ሰንበር እያወጡ ነዱት። የጥቁር ሸሚዝ ሻምበል መስዋዕትነት አስፈሪ ሆነ። አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዳልነበረ ሆነ። አንገቱ ተቀላ። የንጉሱ ወታደሮች ለልዩና ለተከበሩ እስረኞች የሚጠቀሙበት የመግደያ ዘዴ አንገትን ሙሉ በሙሉ ሳይቆረጥ መተው የጣልያኑ ሻምበል እድል ሆኗል። ሻምበሉ ቆዳው ላይ በግርፍ በተፈጠሩት ከመቶ በላይ በሚደሙ ቦታዎች ብዙ ደም ስለፈሰሰው ከአንገቱ የፈሰሰው ትንሽ ነበር። ምንም ሳይናገር፤ምንም ብሶቱን ሳያሰማ ከራስ ካሳ ፊት ወደቀ። ዓይኖቹ ነጥተው እርቃነ ስጋውን እንደተጠቀለለ ስጋ ተጠቅልሎ ደም ተፍቶ ወድቆ ቀረ። ለእሱ በጣም ከፍተኛ የሆነ ሀዘን ተሰማኝ። ምንም እንኳን መጀመሪያ የሰራው ስራ የሚያዋርድ መስሎ ቢታየኝም በላ በጣም አዘንኩለት። ያንን ዳገት ሽቅብ ሲወጣ በሚያሳዝን ድምፅ እየጮኸ ይለምን ነበር። በንጉሱ ሰራዊት ውስጥ እያለፈ ሲሄድ በሚያሰማው ፍርሃትና ሃፍረት በጣም ተሸማቋል።
“እባካችሁ አትግደሉኝ አትግደሉኝ። ተገድጄ ነው ለመዋጋት የመጣሁት፡ እኔ ለአቢሲኒያን እዋጋለሁ። ወደ ጣልያን መስመሮች ላልመለስ ቃል እገባለሁ። ከእናንተ ጋር አብሬ እዋጋለሁ። ጣልያን እወጋለሁ፤ እትግደሉኝ።” የመጨረሻዎቹ ቃላተች ነበሩ።
ከጭፍጨፋው በላ ባለ 101 እና ባለ 105 ሚ.ሜ መድፎች፤ 200 የነፍስ ወከፍ መትረየሶች አንድ ሺህ ጠመንጃዎች፤ ብዛት ያላቸው ቦምቦች፤ፈንጂዎች፤ብዛት ያለው ምግብ፤5ሺህ የውጭ አገር የንግድ ምልክት ያለው ከጦርነት ለኔ ስጦታ የሆኑ ሲጋራዎች አግኝተናል፤ወርሰናል።
…. ቀኑ በፍጥነት መሸ። ጨለማውም ምድሩን ነከሰ። ዘማቾቹ ድላቸውን ማክበር ጀመሩ። ያገኙትን ድል ሰንደቃላማቸውን እያነሱ በሽለላቸው፤በፉከራቸው፤ በጭፈራቸው፤ያደምቁት ጀመር። በዚያ ሸለቆ ውስጥ  የተጋደመው ሬሳ ከምድር ላይ ለብርሃን ማረፊያ እንኳን አትገኝም።ሁሉም በኢትዮጵያ ጦረኞች እነኛን ሙታን ሙሉ በሙሉ በእነዚያ በልዩ የቀዶ ጥገና ማሳሪያቸው (እዚህ ላይ የደራሲው አገላለጽ ጐራዴያቸው ማለቱ ነው) አገለባበጧቸው፤ የጦርነት ድል መግለጫቸውን፤የወንድነታቸውን ምልክት ያንን ትኩስ የሰውነት አካል ሸልተው ጦራቸው ላይ ሰክተው ይዘውታል፤፡
ራስ ካሳን በሚገኙበት ቦታ በጦር ሰፈራቸው ጐበኘናቸው።
“ለምን አስከሬኖቹ እንዲቃጠሉ አያዙም? ሁሉንም ሰብሰቦ አንድ ቦታ ማቃጠሉን ይመረጣል። ሽታው ይወገዳል። ከአስከሬኖቹ ሊነሳ የሚችል ተላላፊ በሽታ ማስወገድ ይቻላል።” ብለን ጠየቅናቸው።
ራስ ካሳም በመገረምና ትካዜ በሞላው ፊት ትኩር ብለው ያዩኝ ጀመር።
“የጦረኞች ገላ አይበሰብስም፡ የሚቃጠለው ገላ ከእግዚአብሔር ጋር የተቆራኘው ብቻ ነው። እንዴት እነኝህ እርኩስ መጤዎች አቃጥላለሁ?”
….በሬሳ ሽታ በዚያ ቦታ ለመተንፈስ እንኳን አስቸጋሪ ሁኔታ ስለተፈጠረ የግድ መልቀቅና ወደ ተራረው መውጣት ተገደድን። ጅብና ጥንብ አንሳ አሞራው ያንን የሙታን ገላ ይቀራመቱት ጀመር።…….የ8000 ጥቁር ሸሚዝ ሰራዊቱ የገጠማቸው እድል “የዱቼን” ጦር እንደ ውስጥ እግር እሳት ስላንገበገበው የመልሶ
ማጥቃት ዘመቻው ከሦስት አቅጣጫ በተመሳሳይ ሰዓት በከፋ መልኩ ጀመሩ። …….ከሦስት ቀን አስከፊ የአንገት መቅላትና የጨበጣ ውጊያ በላ የራስ ካሳ በሰፈረበት ጦር ከሰፈረበት ብዙም ያልተከለለ ቦታ እረፍት በማድረግ ላይ እንዳለን ልክ ከሌሊቱ 9 ሰዓት ሊነጋጋ ሲል መደበኛው የጣሊያን ጦር በተለያዩ የኤርትራ ተወላጆች ከተገነቡ የጦር ክፍሎች ጋር በመሆን የማጥቃት ዘመቻ በድንገት ሰነዘረብን። ውጊያውም ቀጠለ…….”
በማለት የኢትጵያ ሰንደቃላማ እንዳትውለበለብ ለማድረግ የጣረው ወራሪው የዱቼ ጦር እና  ያገሪቱ ዜጋ ሆነው ለሰንደቃላማይቱ ክብር የሌላቸው ተባባሪ ባንዳዎቹ፤ ከኢትዮጵያ አርበኞች ጋር የተደረገው ግብ ግብ ይህን በሚመስል አሰቃቂ ገድል በተሞላበት የመከላከል ጦርነት ተደርጐ ሰንደቃላማችን እንድትውለበለብ ያደረጉትን የወላጆቻችን የገድላቸው አርማ እና መመኪያ በማራከስ ፤ ዛሬ በምናያቸው የዘመናችን አመኬላዎች ሰንደቃላማችን  ለኦነግ ክብር ሲሉ በሕዝብ ስብሰባ እንዳትውለበለብ በማውረድ አሳፋሪ የባንዳዎች ስራ የፈጸሙ  የሲያትል ባንዳዎች እና ካናዳ ቫንኩቨር የሕግ ተማሪ ነኝ የሚለው “ተክሌ” እያለ ራሱን የሚጠራ የግንቦት 7 እና የሻዕቢያ አወዳሽ በካሃዲነታቸው ታሪክ ያስታውሳቸዋል። ለዚህ አሳፋሪ ድርጊታቸው ለኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር እና አገር ወዳድ ሽማግሌ ማሕበሮች ይቅርታ ካልጠየቁ፤ ድርጊታቸው መወገዝ አለበት።
ቃላችን አሁንም ትናንትም ወላጆቻችን በደማቸው ፈርመው ያስረከቡን ሰንደቃላማችን ለኦነግ፤ ለኦጋዴን ሶማሊ ተገንጣይ ቡድን ወይንም ለማንኛውም የፖለቲከካ ቅጥረኛ የድርጅት አርማ ለማስደሰት ብለን ብንሞትም ለድርድር አናቀርብም! ሰንደቃላማችን ከወደቀበት አንስተው የትም ቦታ እንድናውለበልባት ያስረከቡን የወላጆቻችን የአደራ ቃል እንጠብቃለን!!! ወያኔ በሰንደቃላማችን ላይ “ሰማያዊ ቀለም” ለጠፈባት ብለን ስናማርር የባሰውኑ “ከነጭራሹ ደብቋት” የሚሉ ደግሞ መጡብን። ወይ ኢትዮጵያ አገሬ አትሰሚው የለ! የራስ ሙሉጌታና የራስ ካሳ ፤የአርበኞቻቸው አጥንት ይውጋችሁ! መለስን ባንዳ እያሉ ሲሰድቡት ከርመው ተመልሰው እራሳቸው ሰንደቃላማችንን አውርዷት የሚሉ የባሱ ባንዳዎች ሆነው ቁጭ አሉብን እኰ!።ወይ ጉድ! ወይ አገሬ በውርጋጦች እንዲህ ተዋረድሽ?  አመሰግናለሁ። ጌታቸው ረዳ (www.ethiopiansemay.blogspot.com     getachre@aol.com   ( 408) 561 4838