Tuesday, September 10, 2024

የተረሳው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ አርበኛ፣ እና የዓመቱ ምስጉን ኢትዮጵያዊያኖች ጌታቸው ረዳ መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ ዓመት

 

የተረሳው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ አርበኛ፣ እና የዓመቱ ምስጉን ኢትዮጵያዊያኖች

ጌታቸው ረዳ

መስከረም 1 ቀን 2017 ዓ.ም አዲስ መት

    ዛሬ በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ቀን፣ በዕለተ ቅዱስ ዮሐንስ በበጎ ተግባራቸው “መላው የኢትዮጵያ አገር ወዳድ ሕዝብ ሊያመሰግናቸው ይገባል” ስላልኳቸው ሰዎች፣ እንዲሁም አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በዝና እና በአኩሪ ተግባሩ የሚያውቀው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን፣ በኢትዮጵያውያን ሕሊና ትውስታ ስለተነፈገውና ስለ ተረሳ፣ ትግራይ ያፈራችው አንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ አርበኛ ሃሳቤን ላካፍላቹህ ወደድኩ።

  ሰውዬው በ1981 ዓ.ም አካባቢ ከወያኔ የበረሃ ትግል ወጥቶ፣ እጁን ለወቅቱ መንግሥት በመስጠት፣ የተደበቀውን የወያኔ ጸረ ኢትዮጵያነት ሴራ እና ተልዕኮ፣ አሰቃቂ የጭፍጨፋ ወንጀል፣ እንዲሁም ለድርቅ ዕርዳታ እንዲውል ከዓለም በጎ አድራጊዎች ለወያኔ የተሰጠው በሚሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የገንዘብ ዕርዳታ፤ እንዴት ለድርጅቱ ማጠናከሪያ እና ለመሪዎቹ መጠቀሚያ እንደዋለ ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢትዮጵያና ለዓለም ሕዝብ ያጋለጠ ታላቅ ጀግና ነው።በዚህም የተነሳ የሕይወት ጉዞው በብዙ ውጣ-ውረድ የተሞላ እና አስቸጋሪ ነበር።

   ትግራይ/አድዋ ላይ የተወለደው ውድና ክቡር ወዳጄ፣ አርበኛው አቶ ገብረመድህን አርአያ፣ የሚኖረው በምዕራብ አውስትራሊያ (ፐርዝ ከተማ) ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደረሰበት ድንገተኛ የአካል ጡንቻዎች አለመታዘዝ ምክንያት፣ የጤና ዕክል ገጥሞታል።

    ሆኖም በዚህ ክፉ ጊዜም ሆነ ቀደም ሲል፣ ብቸኝነት እንዳያጠቃው፣ የወያኔዎች እጅ አዙር ጥቃት እንዳይደርስበትና ተንከባካቢ እንዳያጣ፣ ለረጅም ዓመታት ከጎኑ ተለይተው የማያውቁት ምርጥ ኢትዮጵያዊያን እና ኢትዮጵያዊት፤ ማለትም ወ/ሮ የምስራች አስፋውበአቶ ፈለቀ ተገኝ እና በአቶ ዓለሙ መንገሻ እርዳታና ድጋፍ፣ በአረጋውያን መጠለያ ውስጥ ማረፊያ ተዘጋጅቶለት፣ እዚያው ምግብ መኝታና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እየተደረገለት በእንክብካቤ እየኖረ ይገኛል።

በነገራችን ላይ ወ/ሮ የምስራች አስፋው የዚሁ መጠለያ ዋና ስራ አስኪያጅ ስትሆን፣ ከመደበኛ ስራዋ ውጭ የአቶ ገብረመድህን አርአያን የዕለት ተዕለት ውሎ፣ ያለበት ድረስ እየሄደች በቅርበት የምትከታተል ታላቅ ኢትዮጵያዊት መሆኗን ተረድቻለሁ።   

  እንዲሁም ለብዙ ዓመታት በማማከርና በአይዞህ ባይነት፣ በመጽሐፉ፣ በጽሑፎቹና ዶክመንቶቹን በአርታኢነት በመርዳት ያልተለየው፣ ሌላው የቅርብ ወዳጁ ጋዜጠኛ ቅዱስ ሃብት በላቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የገዳማት የበላይ ኃላፊ፣ የምሥራቅ አውስትራሊያና ኒውዚላንድ አሕጉረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ እርሱ ወደሚኖርበት አድላይድ ከተማ /ደቡብ አውስትራሊያ በመጡበት ወቅት፣ አቶ ገብረመድህን  ያጋጠመውን የጤና እክል አጫውቷቸው በጣም አዝነው ያለበት አገር ድረስ ሄደው ሊጠይቁት ቃል ገብተውለት ነበር።

ብፁዕ አባታችን አቡነ ሉቃስ ምንም እንኳን አቶ ገብረመድህን የሚኖርበት ምዕራብ አውስትራሊያ፣ በርሳቸው አገረ-ስብከት ስር ባይሆንምና በሌላ ሊቀ ጳጳስ ስር የሚተዳደር ቢሆንም፣ ቃላቸውን አክብረው አቶ ገብረመድህን ያለበት አገርና መጠለያ ድረስ በመሄድና በአካል በመጎብኘት ቡራኬያቸውን በመስጠት፣ ታላቅና እውነተኛ የሃይማኖት አባትነታቸውን ዳግም አስመስክረዋል።

 በብጹዕ አባታችን አቡነ ሉቃስ እግር ሥር ወድቄ እሳለማለሁ! ቀደም ሲልም በስቃይ ላይ ላለው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆርቁረው በድፍረት አብይ አሕመድን በማውገዞት፣ ስምዎንና ክብርዎን ሊያጎድፉ ተነስተው ለነበሩት ሰዎች በጽሑፍ መልስ ሰጥቻለሁ፤ ዛሬም ብፁዕነትዎን በድጋሚ አመሰግናለሁ።

 እንዲሁም  በተለያየ ጊዜ ከገብረመድህን ጎን ለቆማችሁ፣ ስማችሁን ስላላወቅኩ ግን ያልጠቀስኩዋችሁ በጎ አድራጊዎችን፣ በአምላክ እና ገብረመድህን ስም ሳላመሰግናችሁ ማለፍ አልሻም።

ገብረመድህን የዛሬን አያድርገውና መላው የተቃዋሚ ሚዲያዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ “የእንግሊዝኛው ቢ ቢ ሲ” እና “የ ቪ ኦ ኤ አማርኛ ክፍል” ሳይቀር ለበርካታ ዓመታት እየተንጋጉ፣ ስልኩን በወረፋ እየጠበቁ ነበር ቃለ መጠይቅ ያደርጉለት የነበረው። ታዲያ ያኔ ለሚዲያቸው ፍጆታ የበቃቸውን ያህል እንዳልቃረሙ ሁሉ፤ ዛሬ ድንገት የጤና እክል አጋጥሞት ራሱን መንከባከብና የተወሰነ የሰውነቱን ክፍል እንደልብ ማዘዝ፣ ባልቻለበት ጊዜ “የት ወደቀ? የት ሄደ? ምን አጋጠመው?” ብለው አልጠየቁትም። ካሁን ቀደም ከሃዲ ሕዝብና ምስጋና-ቢስ ሕዝብ! ስል ሁሌም ያነበባችሁኝ ይመስለኛል።ታላቁ እስክንድር ነጋን እንደካዱት ማለት ነው!

   በብቸኝነት ላመሰግነው የምፈልገው የመገናኛ ብዙሃን ተቋም ቢኖር በቅርቡ ገብረመድህን አርአያን ያለበትን ሁናቴ ለሕዝብ ይፋ ያደረገውን ኢትዮ 360 ሚድያን ነው። በዚህ አጋጣሚ ለመላው የዝግጅት ክፍሉ ባልደረቦች፣ ከቀድሞ ጀምሮ ያለኝን አድናቆት፣ ለስራቸው ያለኝን ክብርና ከፍተኛ ምስጋና ሳልገልጽ ማለፍ አልሻም።

    ወደ እኔው ልመለስና ለበርካታ ዓመታት የገብረመድህን አርአያ የቤት ስልክ ሁሌ እየደወልኩ አብረን እንጫወት ነበር።ታዲያ እንደወትሮዬ ደጋግሜ ስደውል ስልኩ ተቋርጦ አልሰራ ብሎኝ የምጠይቀው ሰው አጥቼ ሲጨንቀኝ በራሴ ሚዲያ “አቶ ገብረመድህን አርአያ ያለበት  ቦታና ሁኔታ የሚያውቅ ሰው እባካችሁ ንገሩኝ ?” ብየ ጥያቄዬን አቀረብኩኝ።ይህንን ያነበበው ወዳጁ ቅዱስ ሃብት በላቸውም ስለ ሁኔታው ምላሽ ሰጥቶ አሳወቀኝ።

    ከዚያም አልፎ በቅርቡ ከገብረመድህን ጋር በክብርት ወ/ሮ የምሰራች አስፋው አማካኝነት ዳግም በስልክ እንድገናኝ አድርጎኛል። ገብረመድህን የሚኖርበት ፐርዝ ከተማ ቅዱስ ሃብት ከሚኖርበት አድላይድ በአይሮፕላን ከ3 ሰዓት በላይ ርቀት ያለው ሲሆን፣ ገብረመድህንን ለመጠየቅ ወደዚያው አምርቶ የሚፈልገውን እንክብካቤ አድርጎለት፣ ስልክ ገዝቶለት፣ ወንድማዊ እንክብካቤ በማድረጉ ደጋግሜ ምስጋናዬ አሁንም ይድረሰው።

   ባጠቃላይ እነዚህ ሩህሩሃን አገር ወዳድ ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ፣ ዛሬ ገብረመድህን “ቤትና ተንከባካቢ አልባ አስፋልትና በረንዳ አዳሪ ሆኖ ልናገኘው ሁሉ እንችል ነበር”። በዚህ አጋጣሚ ይህ ምንጊዜም በታሪክ የሚወሳ ታላቅ ተግባር የፈፀመ ኢትዮጵያዊ ጀግና፣ ባስቸጋሪ ወቅት ህይወቱ ለወያኔ ጨካኝ ነብሰገዳዮችና ሴረኞች ለአደጋና ለግድያ ተጋልጦ፣ በዚያ ሳይበገር የሚያውቀውን የወያኔ ወንጀልና ድብቅ አጀንዳ ይፋ በማድረግ ውለታ የዋለለት የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በሕይወት ሳለ ተገቢውን የላቀ አክብሮት፣ ምስጋና እና ሽልማት እንዲያቀርብለት ጥሪዬን ማስተላለፍ እሻለሁ።

   በተጨማሪም ኢትዮጵያውያን በጎ አድራጊዎችን የሚሸልሙ እዚህ አሜሪካ የተመሰረቱ ድርጅቶች እንዳሉ ሰምቻለሁ። እነኚህ ድርጅቶች፤ ለእውነትና ለወገን ከቆሙና “ፓርቲዛን ካልሆኑ” ገብረመድህን እስከዛሬ በክብር እንዲኖር የረዱትን ከላይ የጠቀስኳቸው ለሌሎች አርአያ መሆን የሚችሉትን ታላላቅ ኢትዮጵያዊያን፣ ወደ አውስትራሊያ  ደውለው በማነጋገር ተገቢውን ክብር እንዲያገኙ ማድረግ አግባብና አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁና ከድርጅቶቹ ጋር ግንኙነት ያላችሁ ሰዎች ጥቆማዬን እንድታደርሱልኝ እጠይቃለሁ።

    በመጨረሻም በሚኖርበት ከተማ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን አድናቂዎቹ “ዳግማዊ አሉላ የሚል ታላቅ የክብር ስም ከሽልማት ጋር ለሰጡት ለታላቁ ወዳጄ ለአርበኛው ለገብረመድህን አርአያ፣ ለበጎ አድራጊዎቹ ወዳጆቹና አጋሮቹ ከነቤተሰቦቻቸው፣ በተለያየ ጊዜ ከገብረመድህን ጎን ለቆማችሁ፣ ነገር ግን ስማችሁን ስላላወቅኩ በጽሁፌ ላይ ያልጠቀስኩዋችሁ በጎ አድራጊዎች፣ እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ መልካም የ2017 ዓ.ም አዲስ ዓመትና መልካም የቅዱስ ዮሐንስ በዓል ይሆንላችሁ ዘንድ እመኛለሁ።

    ጌታቸው ረዳ 

Ethiopian Semay ዋና አዘጋጅ