Monday, October 12, 2015

ማርክሳዊ ርዕዮት አልለቅ ያላቸው የአሲምባ ፈላስፋዎች! መልስ ለአሲምባ ድረገጽ አዘጋጆች ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ)ማርክሳዊ ርዕዮት አልለቅ ያላቸው የአሲምባ ፈላስፋዎች!
መልስ ለአሲምባ ድረገጽ አዘጋጆች
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮጵያን ሰማይ ድረገጽ አዘጋጅ)
ውይይቴ ከመጀመሬ በፊት በቅርቡ ሁለት ታዋቂ አንጋፋ ኢትዮጵያዊያን ማለትም ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ (የሗላ ሗላ በመጨረሻ ዘመናቸው እዚሁ ውጭ አገር ሆነው ሲያራምዱት የነበረው አቋማቸው ባልስማማም፤ ከዚያ በፊት ላገራቸው ያደረጉት አስተዋጽ ሚዛኑ ከባድ ስለሆነ ሃዘኔን ልገልጽላቸው ተገቢ ነው) የሙሉጌታ ሉሌን ሕልፈት ተከትሎ “የኤርትራ ጉዳይ” ደራሲና ጋዜጠኛ አምባሳደር  ዘውዴ ረታ ሁለቱም በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ነብስ ይማር ለማለት እፈልጋለሁ።”
አሁን ወደ ኢሕአፓና የ ያኔ ትውልድ ጉዳያችን ይዤአችሁ ልግባ። ለብዙ ጊዜ ኢሕአፓን ስከላከል የነበረበትን ዞር ብዬ ስመለከት አሁን አሁን እራሴ እያስገረመኝ ነው። ማርክሳዊ ጥማታቸው ዛሬም እየተንከባከቡት መሆናቸው ስመለከት ባለማወቄ የሰጠሁዋቸውን ድጋፌ በዚህ ትችት ልሳበው።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት “የአዲስ አበባ ቀ.ሃ.ስ.ዩ” የተማሪዎች አንጋፋ መሪ እና “ኢሕአፓ ነበር” ተብሎ በመስራቾቹ የተነገረን ዋለልኝ መኮንን ላይ ባቀረብኩት ትቶልን በሄደው አመለካካቱ ላይ፤
 “በአሁኑ ወቅት የዚያን ትውልድ የትግል ታሪካ የማንቋሸሽና የመከለሱ ዘመቻ ለምን አስፈለገ?” በሚል ርዕስ ለኔ መልስ ተብሎ በአሲምባ አዘጋጆች በድረገጻቸው የተለጠፈው አንቤዋለሁ። “ያ ትውልድ” ብለው ለሰየሙት ያ ትውልዳቸው የተከተለው ማርክሳዊ/ፋሺስታዊ ርዕዮት፤ ዛሬም አልለቅ ብሎአቸው ስለ ማርክሳዊ ርዕዮታቸው ጥብቅና ቆመው፤ እንደ እነ ዋለልኝ የመሳሰሉት በዘመኑ የነበሩት ማርክሳዊያን ያስተማሩትን መስመር እስከዛሬ ድረስ አፍራሽ ሆኖ ኢትዮጵያን እያተራመሰ ያለው ማርክሳዊ/ሌኒናዊ/ማኦዊና ስታሊናዊ ርዕዮት አትንኩብን፤ከቶውንም ማርክሲዝምን አታንቋሽሹብን  ሲሉ መከራከራቸውን አስገርሞኛል።
ያ አልበቃ ብሎ፤ ኤርትራዊቷ ማርታ ለኤርትራ ትግል ስለመቆሟና ዋለልኝም ምናልባት ከእርሷ ጋር ከነበረው ቀረቤታ አንጻር ሲታይ በእርሷ ፍቅር ተነድፎ የኤርትራን ጥያቄ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ሕሊና ተቀባይነት እንዲኖሮው የመጣሩንና ፤ከዚያም አልፎ ዓለም ድጋፉን እንዲሰጣቸው ለማድረግ ለአይሮፕላን ጠለፋው ያደረገችው ግፊት ከጥቂት አመታት በፊት እንደሚኖር ከአስመራ ከተማ የተላኩልኝ የታተሙ የኤርትራ ፋይሎችና፤ ኢትዮጵያዊያን ታሪክ ጻሐፊዎች ከፍርድ ቤት ያገኙት የማርታ የክስ ማሕደር በማገናዘብ ባቀናበርኩት መሰረት ተነስቼ የገመገምኩትን የግል አስተያየቴን በመቃወም የአሲምባ ድረገጽ አዘጋጆች “በርዕሰ አንቀጻቸው” እኔን “ሊቅ” እያሉ በመሸርደድ ተችተውኛል።
ሊቅ የሚለው ቃል ለኔ የማይገባ መስሏቸዋል። አንዳንድ በሊቃውንትነት ማዕረግ ያሉት ሊያልፉት ያልቻሉ አስቸጋሪ ረዢም የትግል ጉዞ፤ ሁሉም አገሩን ለመግባት ሲያሰፈስፍ፤ አልገባም ብዬ የወላጆቼ ቀብርና ሕመም በቅርብ ተገኝቼ ሳላስታምም እና ሳልቀብር ለአገሬ የቆምኩኝ ታጋይ መሆኔን ያሳለፍኩት ህይወት፤ ማንነነቴንና የአገሬን መከራ ለመጪው ትውልድ ለመግለጽ 5 መጽሐፍቶች (ትግርኛ አማርኛ) በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ የቀረበ ብቸኛ ጥናት፤ (ጥናቴም አንድ ፒ ኤች ዲ አንድ ማሰተርስ ዲግሪ ለምረቃ ስራቸው እንደሚረዳቸው አስፋፍተው እንዲያቀርቡት ፈቃድ ለጠየቁኝ ኢትዮጵያዊያን ያደረስኩ) ሁሉም ስለ ወያኔ ገበና የሚያጋልጡ መጽሕፍቶቼና በሺዎች ቁጥር የሚገመቱ የጋዜጣ፤የመጽሔትና የድረገጽ ጽሑፎቼ ሲነጻጻር ብቸኛ የትግራይ ሰው ስሆን፤ እኔ እራሴ “ሊቅ” ነኝ ባልልም፤ አሲምባዎች የኔን ጥልቅ አስተዋጽኦ ማንቋሸሻቸው ከኔ ይልቅ እኔን ዶ/ር ጌታቸው ረዳ / አንድ ለናቱ/  ኢትዮጵያዊው ገዴዎን (እስራኤላዊው ጋዜጠኛና ታጋይ ገዴዎን ለቪንን በማነጻጸር) rare bird ፤ አርበኛና አገር ወዳድ ወዘተ…ወዘተ… የሚሉ በርካታ ስሞች መጠራቴን አሲምባዎች አያውቁትም አልልም።

ጥቅስ እንዲህ ይላል፤
1-   ሰሞኑን የዋለልኝ መኮንንን ታሪክ የማጥቂር ዘመቻው ተጧጡፏል። የአማራ ሕዝብ ጠላትም እየተደረገ እየቀረበ ነው። የማርታ መብራቱም የትግል ታሪክ በኤርትራዊነቷ የነሻቢያ መሣሪያ በመሆን እነዋለልኝን እንዳነሆለለች ተደርጎ የኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴም የዘረኞች መጠቀሚያ ሆኖ እንደነበር የሚሰብኩን ሊቃውንት በየመድረኩ ብቅ ብለዋል። ዕውነትና ንጋት እያደር ይጠራል ነውና የዚያን ትውልድ ትግል ለመሆኑ የዛሬውን የዘረኝነት መነጽር ተላብሶ ለመመልከት መሞከር ስህተት አይሆንም ወይ? “    

እስኪ አንዴ ባጭሩ ልድገመው!?
“የማርታ መብራቱም የትግል ታሪክ በኤርትራዊነቷ የነሻቢያ መሣሪያ በመሆን እነ ዋለልኝን እንዳነሆለለች ተደርጎ የኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴም የዘረኞች መጠቀሚያ ሆኖ እንደነበር የሚሰብኩን ሊቃውንት በየመድረኩ ብቅ ብለዋል።”
አዎ ያ ትውልድ የዘረኞች ፍልስፍና፤የጸረ ኢትዮጵያ ክፍሎች መፍለቅያ፤ የኤርትርያኖች ትግል መጠቀሚያ ነበር።  እንዲያውም ካለችሁ እማ፤ ያ ትውልድ የሚባሉ እነማን ነበሩበት? ኤርትራኖች፤ ወያኔዎች/ኦነጎች/ኢሕአፓዎች!!!! እነኚህ እራሳቸው ዘረኞች ሆነው የተመለመሉ ጸረ አማራዎች መሆናቸው ከጻፉት የጽሑፍ ስርጭት ማረጋገጥ ይቻላል። አማራውን በነፍጠኛነት ሰይመው በጨቋኝ ብሔር ወንጅለውታል (ኢሕአፓም ሳይቀር!!!!)። ያውም እንነጋገር ካላችሁ እማ፤ አማራን በደመኛ ጠላት የፈረጁት ዘረኞቹ ኤርትራዊያን ‘ማርታ መብራቱን’ መላክ አላስፈለጋቸውም። ምክንያቱም ወይንም በማርታ አማካይኝነት ወይንም በ እነሱ ስብከት ወይንም ….ባንዳች ነገር የተነሳ፤ የኤርትራ ተገንጣይ ቡድኖች መሳሪያ የመሆኑ ጉዳይ ዋለልኝ የማርታን ጉትጎታ ያስፈለገውም አይመሰልም። እንዲህ ይላል በግልጽ፦
To applaud the ELF is a sin. If anything favorable is written out, it is automatically refuted by both USUAA and NUEUS. But the Gojjam affair was different. Support for it was practically a show of identity to the so-called revolutionaries.

On The Question of Nationalities In Ethiopia By Walleligne Mekonnen – Arts IV, HSIU  Nov. 17, 1969

ዋለልኝ በግልጽ የኤርትራ የግንጠላ አቀንቃኝ እና መሳሪያ መሆኑን ነው በግልጽ ከላይ እየነገረን ያለው። ጀብሃን ማሞገስ ማለት በሁለቱም የተማሪዎች ማሕበር ማለትም USUAA እና NUEUS እንደ ሓጢያት ሆኖ ይፈረጃል። ይላል በግልጽ።  ሃሎ! ሃሎ! ሃሎ!  አሲምባዎች!

እንዲህ ይላል፤-
“…I do not oppose these movements just because they are secessionists. There is nothing wrong with secessionism as such. For that matter secession is much better than nationally oppressive government.

As long as secession is led by the peasants and workers and believes in its internationalist obligation, it is not only to be supported but also militarily assisted.”

ዋለልኝ ምንድ ነው እያለን ያለው? ከብሔራዊ ጨቋኝ መንግስት ስር ከመኖር አገርን ማፈራረስ ይሻላል። ይላል።  የጀብሃን ግንጠላ እንቅስቃሴ ተቃወዋሚ የምሆን ከሆንኩኝ፤ ተገንጣዮች ተገንጣዮች ስለሆኑ ብየ ሳይሆን፤ ግንጣለው የሚመራው ክፍል ሰራተኛውና ገበሬው የእንቅስቃሴው አካል እስካልሆነ ድረስ ነው። በሁለቱም መደቦች ተሳታፊነት የሚመራ ግንጣላ ከሆነ እና ግንጠላው አለማቀፋዊ ላብአደራዊነት ሕግጋት እስከተከተለ ጊዜ ግን ግንጠለው መደግፍ ብቻ ሳይሆን በወታደራዊ እገዛም መታገዝ አለባቸው። ነው እያለን ያለው።

ማርታ ከጎኑ ሆና ካላበረታታችው፤ ለዚህም አነሳሽነት ከራሱ ከሆነ ደግሞ እራሱ የገንጣዮች አቀንቃኝ  መሳሪያ የመሆኑ ደግሞ የባሰውኑ “በአገር ግንጠላ አበራታችነት፤ በ የተጠያቂነት ቀለበት መነጽር ክብ ውስጥ ያስገባዋል”። እንዴት ነው ነገሩ!
ስለ ያ ትውልድ/ ስለ ዋለልኝ አስተምሕሮ ባሁኑ ጊዜ መነጋጋር እጅግ ወቅታዊ መሆኑን የአሲምባ ፈላስፋዎች አልገባቸውም። ብሔር  ብሔረሰብ፤ሕዝቦች እየተባለ በማርክሳዊ ርዕዮት የታጠረ ትምሕርት የተከተለው ዋለልኝ እንዲሁም ኢሕአፓና ወያኔ ያስተማሩት ትምሕርት (አሁም ስራ ላይ ውሎ አሁንም ያስከተለው መዘዝ ገና አልበረደም፤ በቂ ብሔራዊ ውይይትም አልተደረገበትም። አገሪቷም በዚህ እየተናጠች ናት፤ ማርክሳዊ ርዕዮት ካልተገታ ገደብ ካልተደረገለት፤ ገና ትናጣለች። ስለዚህም ትችቱ አስፈላጊና ወቅታዊ ነው።)  የአሲምባ ማርክሰዊ ርዕዮት ጠበቃዎች “ዋለልኝ” አትንኩብን የሚሉትም ፡ለማርክሳዊ ርዕዮት ያላቸው ፍቅር፤ ገና እንዳልበረደላቸው  ከላይ የጠቀሱትን ፤ ርዕስ ማስረጃ ነው።

ዋለልኝ አማራን አስመልክቶ ስለተቸው፤ መልስ ሰጥቻለሁ። ባለፈው ትችቴ ዋለልኝ መኮንን “ኦርቶዶክስ ሃይማኖትና አማራ” ሁለቱም ላደረሱት የፖለቲካ፤የባሕል፤ የአስተዳዳር ተጠያቂነት ከሚገባው በላይ እያጎላ ወንጅሎአቸዋል። ለዚህም መልስ ሰጥቻለሁ። መላው ኢትዮጵያ ስራ ፈላጊ ሕዝብ የአማራ ስም ካልያዘ ሥራ አንደማይሰጠው ዋሽቷል (ግለሰቦችን እንደምሳሌ እያጣቀሱ ማቅረብ ለሰፊ ውንጀላ በቂ መረጃ ሊሆን አይችልም። የአማራ ስም የያዘ አማራ እራሱ ስራ አልነበረውም። ለዚህም በመረጃ አሳይቻለሁ። ዋለልኝ ስያሰኘው በሁለት ብዕር (በሁሉም ጽሑፎቹ እንሚያደርገው ) እያምታታ የሚጽፈውን ስንመለከት ‘አማራው የተበደለ መሆኑንም’ አልካደም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሔራዊ ስሜት የሕዝቡ ስሜት ሳይሆን “የነፍጠኞች” (የአማራዎች) ብሔራዊ አገራዊ ስሜት ብቻ እንደሆነ ዋሽቷል። ትግሬዎች የአማራ ስም የያዙት ታሪክ ሃ ብሎ ሲቆጠር “ምኒሊክ፤ሃይሌ፤………ወዘተ ባልተወለዱበት ዘመን ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ ተያይዞ የመጣ መሆኑን ረስቶ፤ በግድ የአማራ ስም እንሰተሰጣቸው አድርጎ አማራዎችን ይወነጅላል)፤ አማራው የኢትዮጵያን ታሪክና መንግስት ለብቻው እንደመራው ዋሽቷል። ሰለ ባሕል ረጋጭነት፤ ምግብ፤ ሻማ/አለባበስ፤ሙዚቃ፤ ስለ ነፍጠኛነት ሕዝብን በግድ ረግጦ እንዲከተለው ማድረግ፤ አማራውን በማይገባ ወንጀሏል። አማራና የአማራ ስም የያዘ አማርኛ የሚናገረው የጎጃምም ሆነ፤ አማራ የበዛበት የወሎ ሕዝብ በመጥፎ አስተዳዳርና በርሃብ መጠቃቱ የዋለልኝን ማርክሳዊ ውሸት ቁልጭ አድርጎ የሚያረጋግጥ  እንደሆነ ገልጫለሁ።

2-  ዕውነትና ንጋት እያደር ይጠራል ነውና የዚያን ትውልድ ትግል ለመሆኑ የዛሬውን የዘረኝነት መነጽር ተላብሶ ለመመልከት መሞከር ስህተት አይሆንም ወይ?     ብላችሁ ጠይቃችሗል።
እውነት እነዚህ ወንድሞች የሚናገሩትን ያውቃሉ? የዚያ ትውልድ ትግል ምንድን ነበር? የተከተለው ርዕዮት ምን ነበር? እኔው ልመለስስላችሁ!
“ማርክሳዊ ሌሊናዊ” አይዲኦሎጂ/አስተዳዳር ነበር ለኢትዮጵያ ያስተማረውና የተከተለው። በማርክሲዝም ጠባዩ ተነሳስቶ በቡድን ተቧድኖ፤ በጥይት የተደባደበበትም ርዕዮት ይህንን ርዕዮት ለማስፈን ነበር። የዚያ ትውልድ ርዕዮት ማርክሲዝም ማለት “ፋሺዝም” ማለት ነው። ሁለቱም ማርክሲዝም እና ፋሺዝም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። አይደለም የምትሉ የአሲምባ ሊቀውንት በግልጽ እንከራከር። 

አዎ እውነት እና ንጋት እያደረ ሲጠራ ነው ብላችሗል። ብዙ ሰዎች ይህንን እውነታ ሊገነዘቡ ሲችሉ፤ ምሳሌውን ብቻ ተገልጾላችሗል። አሳዛኙ ግን እውነታው እንደ ንጋት በርቶ እያለም፤ አሁንም ይህንን ትምህርትና ሃቅ ማገናዘብ አቅቷችሁ “ማርክሲዝም፤ያስተማሩ አስተማሪዎቻችሁና ያስከተሉብን መዘዝ ፤መነጋጋር ፤መተቸት፤መወቀስ፤የለበትም፤ትላላችሁ።” ብዙ ሰዎች የእነ ዋለልኝ ቅስቀሳ “አፍራሽ፤ አናካሽ” መሆኑን ማየት ሲችሉ፤ ለናንተ ብቻ ሊበራላችሁ አልቻለም። ንጋቱ ወለል ብሎ በርቶም ዓይናችሁ አሁንም ማርከሳዊውን ርዕዮት ብቻ አቶኩሮ ተቸክሎ ስላለ “አውነታው ጠጥሮ” ሊታያችሁ አልቻለም። ለዚህ ነው የ ያን ትውልድ ሃዋርያት ያስተማሩት “ትምሕርተ ክርሰቶስ” ነው እና ታቦቱን አትንኩብን የምትሉት።
ያኔ የት ነበራችሁ ዛሬ ወቃሾች የምትሆኑ የሚሉ ሊቃውንቶቻችሁ፤ ለኔ ያስቁኛል። ያኔ ይህንን የ “ኒሂሊሰቶች” አፍራሽ የሆነ ባዕዳዊ ርዕዮት ባሕላችን፤ታሪካችን፤አንድነታችን፤ሰላማችን ኩፍኛ ሊያደፈርስብን ነው ብለው ለተከራከሩ ሁሉ፤ ዋለልኝ ምን ብሎ ነው የመለሰላቸው “ፊውዳሎች!” ፤ “ሪአክሺነሪ!”። ያኔ የተቃወሙት እንዲህ ያለ ስም ነበር የተሰጣቸው። ያኔ አንዲያ የተቃወሙትን፤ እንዲያ ያለ ስም ሲለጥፍባቸው ፤ ዛሬ ደግሞ የትምሕርቱን መርዛማነት ስለተቸን እኔን “ሊቃውንት/ሊቅ” እያለችሁ “ማሾፋችሁ” አሁንም ከዋለልኝ አስተምሕሮ ዝንፍ አላላችሁም።
“የያኔ ትውልድ ትግል ለመሆኑ የዘረኝነት መነጽር ተላብሶ ለመመልከት መሞከር ስህተት አይሆንም ወይ?’ ብላችሗል።

ማነው ዘረኝነትን አፍራሽነትን አንባገነንነትን፤ መደባዊ መገዳደልን፤ መደባዊ አምባገነናዊነትንና ግንጠላን፤ ማአከላዊ አምባገነናዊነትን ያስተማረ? ያ ትውልድ!!!!!!!! እንዴት ብላችሁ ጠይቁኝ። መልሱ ፤ያ ትውልድ ያስተማረውና የተከተለው ርዕዮት ፡ማርክሲዝም ነው። ማርክሲዝም ምንን ያስተምራል? በቡድን መቧደንን፤ወገንተኛነትን፤መደብን፤ገበሬን ፤ወዛደርን/ላብ አደርን ተለያይቶ አንዱ ቡድን አንዱን እንዲያዘው፤ የግል ንብረትና መሬት በላብ አደር ጨቛኝነት በሚመራ በመንግስት ተይዞ/ተወርሶ፤ንብረት አልባ በመሆን፤ማንነቱ ተነጥቆ ግለሰብ/ሲቲዝን የመንግስት ጥገኛ/ጢሰኛ፤ተከራይ/ዲፐንዳንት እንዲሆንና “ኗሪ/ቡድን/ግለሰብ አሜን ብሎ ለላብ አደር ዓለም ዓቀፋዊነት መርሆ እንዲገዛ” ፤  ‘አንዱ ቡድን መሪ አንዱ ቡድን ተመሪ ሆነው፤ በስሩ፤ በማአከላዊት ትዕዛዝ እየተመሩ “ሌላወን ክፍል” እንዲጨቁኑት ነበር ያስተማረውና የታገለው። የታገለው ለማን ነበር? ለሥልጣን!? የማን ሥልጣን? “የላብ አደሩ” የበላይነት ሥልጣን! አይደለም እንዴ!? 

ለያይቶ አንዴ በጋራ ተቧድኖ አንዱን ክፍል መጨቆን፤ አንዴ ደግሞ ‘ላብ አደሩ አምባገነን ሆኖ ሁሉም በስሩ ለይ ሰጥ ብሎ አንዲገዛ መጨቆን፤ አንዴ ደግሞ ገበሬውና ላብ አደሩ ተቧድኖ በሃብታሙና በከተሜው አንዲዘምት ፤ የላብ አደሩ ፓርቲ የበላይነት አንዲኖረው፤ መሪ አንዲሆን ፤ዜጎች “ተጨቋኞች ሆነው” አንዲገዙ የሚሰብክና የታገለ መርሆ ነበር። ይህ የማርክሲዝም ትምህርት ነው። አሲምባዎች ትንሽ ሳያፍሩ “የአይጥ ምስክሩ ድምቢጡ” እንዲሉ ሆነና ገብሩ አስራትን ለእማኝነት ምስክራቸው ሲያመጡ እንዲህ ይላሉ፡

ከገብሩ በፊት ግን አሲምባዎች አንዲህ ይሉናል፤
“ከሁሉም በላይ ግን በኢትዮጵያዊነት ላይ ከማንም ሰይጣን ጋር አልተደራደረም።” አሲምባዎች ቀልደኞች ናችሁ ጃል!!!!!!
 አልተደራደረም? ድርጅታችሁስ ስለ በኢትዮጵያዊነቱ ስለ መደራደሩ ይቅርታ አልጠየቀም? ወይስ ስለምንድነው ይቅርታ ጠየቀ አስተካከለ የሚባለው?  ከኤርትራዊያን ጋር ወግኖ ዛላምበሳ ላይ በሃይል ተገድዶ የዘመተን ምስኪን ምሊሺያ ገበሬ ላይ ተኩሳችሁ አልፈጃችሁም? መሪያችሁ ክፍሉ ታደሰ እኮ ነው የነገረን! ወያኔ ምጽዋ ላይ ያደረገው የቅጥረኛነት ተሳትፎ-ታሪክ ኢሕአፓ ዛላምበሳ ላይ አልፈጸመም? የኤርትራን ነፃነት ከመደገፍ አልፋችሁ አልታገላችሁም? 

ፕሮግራማችሁ እንዲህ ይላል “ከማወቅ ባሻገር የኤርትራ ሕዝብ ለነፃነት የሚያደርገውን ትግል መደገፍ ነው” ይላል። ከነሱ ጋር ወግናችሁ ነበር ወደ ኢትዮጵያ ሚሊሺያ ምስኪን ገበሬ ያነጣጠራችሁት። ለምን እኔን መጎነታተል መረጣችሁ? ለመወያት ከሆነ፤ ሃቁ ይሄው ነው።

ደግሞ ትንሽ አታፍሩም “የአይጥ ምስክሩ ድምቢጡ” እንዲሉ እንዲህ ትላላችሁ 
 “ከሁሉም በላይ ግን በኢትዮጵያዊነት ላይ ከማንም ሰይጣን ጋር አልተደራደረም። ለምሳሌ የወያኔ አንዱ መሪ የነበረው ገብሩ አሥራት በቅርቡ በጻፈው መጽሐፍ ገጽ 54 ላይ እንዲህ ይላልለ-“   ትላላችሁ፦
ኢሕአፓ በፕሮግራሙ ውስጥ የኢርትራ ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ከመግለጹም በላይ በዴሞክራሲያ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ከሰላማዊ ድርድር ውጭ ሌላ መፍትሔ ማፈላለግ ዕልቂት እንጂ ሌላ ውጤት እንደማይኖረውም በተደጋጋሚ ይገልጽ ነበር። ይህ የኢሕአፓ አቋም የኤርትራን ድርጅቶች የሚያረካ አልነበረም። የኤርትራ ድርጅቶች ኢሕአፓ በሁለት ጉዳዮች ላይ ጠንካራ አቋም እንዲኖረው ይፈልጉ ነበር። አንደኛው አቋም የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት መሆኑና ቅኝ ገዥዋም ኢትዮጵያ እንደሆነች መቀበል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጥያቄው በኤርትራ ነጻነት መፈታት እንዳለበት መቀበል ነበር። እነዚህን ሁለት አቋሞች ከኢሕአፖ ሊያገኙ ባለመቻላቸውም የኤርትራ ድርጅቶች በኢሕአፓ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬና ጥላቻ ነበራቸው….” ወረድ ብሎ በዚሁ መጽሐፍ ገጽ 135 ላይ ለምሳሌ ከኢሕአሠ ተገንጥሎ ወደ ወያኔ የተቀላቀለው ጦር (እነ ታምራት ለይኔ፣ ሕላዊ ዮሴፍ፣ ታደሰ ካሣ፣ ያሬድ ጥበቡ (ጀቤሳ) ኃይሌ ጥላሁን፣ በረክት ስምዖንና አዲሱ ለገሠ ኢሕዴን ብለው በሰየሙት ድርጅት አማካይነት የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ነው ብለው ተቀብለዋል ብሎ ያቀርባል። የአሲምባ ድሕረ-ገጽ ዝግጅት ክፍል” ይላል ለምስክርነት የመረጣችሁት ገብሩ አስራት፦

እኛ ትግሬዎች “ሁለት ጉድጓድ የማሰች አይጥ መውጪያዋን አታጣም” እንላልን። ገበሩም እናንተም ሁለት ጉድጓድ በመማስ ለማመምለጫ እንዲመቻችሁ ሁለታችሁ ታሾፋላችሁ። ለምን ነበር የማሻሻ ለውጥ አድርገናል ያላችሁት? ገብሩ ይህን ማሻሻያ ነው እየዋዠቀ ያለው ወይስ ፕሮግራማችሁ እውን አላነበበም ነበር? 

ግንጠላን በማስተማር!፤- ኢሕአፓ/ዋለልኝ “ግንጠላን” የችግር መፍቺያና የመውጪያ ጉድጓድ ምንጭ አድርገው አስተምረዋል። ማርክስዝም የተከተለው ርዕዮት ግንጠላ ለጭቆና እንደ መፍትሔ አድርጎ አስተምሯል። ወያኔ የማርክሲዝን ትምህርት ተከትሎ በ1968 የፋሺዝም/ማርክሲዝን መግለጫ ሲያወጣ፤ ኢሕአፓ ደግሞ በ1976 ከ8 አመት ቆይታ በሗላ ማለት ነው፤ የኢትዮጵያ ሉአላዊነትን በሚጻረር መልኩ ፤ መገንጠልን በፖለቲካ ፕሮግራሙ አካትተ ብቅ አለ። ወያኔ “ጨቋኛ ብሔር” እያለ (1968) ሲያስተምር ኢሕአፓ ደግሞ “ጨቋኙ ብሔር” ሲል ያንን የወያኔ/ትሓህት ፕሮግራም በመደገፍ በ1976 ኣ/ም በፕሮግራሙ ነድፎ አሰራጭቷል። “እንዴ? !!!!!!! በሉ መሪጌታ ሃይሉ” ይላሉ ትግሬዎች። “እንዴ? !!!!!!! አሉ መሪጌታ ሃይሉ”


  
የአሲምባ ፈላስፋዎች ፕሮግራማችሁ ሳልቀንስ ፤ሳልጨምር እንዳለ እንድታነብቡት ልጥቀስ፤
“የጭቁን ብሔሮችን የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት/እስከ  መገንጠልና የራሳቸው የሆነ ነፃ መንግስት እስከ ማቋቋም ድረስ  መከበር እንዳለበት ማስተማርና መታገል አንዳለብን ሁሉ ጭቁን ብሔሮች በፈቃደኛነትና በእኩልነት “ከጫቋኝ ብሔር” ሰፊው ሕዝብ ጋር መዋሃድ እንዳለባቸውም ማስተማርና  መታገል አለብን።” ሲል የወያኔን የ1968 ንቱን የፖለቲካ ፕሮግራም ኢሕአፓ በ1976 ከ8 አመት ቆይታ በሗላ ፎቶ ኮፒ ትክክለኛ ግልባጭ በፕሮግራሙ አስፍሮታል።  ገጽ 23 እና 24 ….ይመልከቱ።
ታዲያ ጌታቸው ረዳ ፤አንድነታችን እንዲጠነክር ተቻችለን ለመኖር ስንል ባሞግሳችሁ እራሴ ላይ ወጥታችሁ ዋለልኝ ለምን ተነካ ብከላችሁ እኔን በማሾፍ ‘ሊቅ” እያላችሁ መጎነታታል ምን አመጣው? እንዴ! ትንሽ አታፍሩም? ይህንን ግንጣላ እንዳስተማራችሁ እያወቃችሁ “ያ ትውልድ” ለምን ተነካ፤ ትላለችሁ እንዴ?
አዎ! ያ ትውልድ “ጨቋኝ ብሔር” ሲል አማራ ማለቱ ነው፡ ሌላ ሊሆን አይችልም። እንዳለ ከዋለልኝ በበሳ መልኩ በፕሮግራሙ ቁልጭ አድርጎ መግለጹ ብቻ ሳይሆን ፤

ኢሕአፓ ኤርትራንም በፕሮግራሙ መርሆ ተደግፎ እንደዚህ ይገልጻታል፡
“የኤርትራ ሕዝብ የራሱን መብት በራሱ የመወስን እስከ መገንጠል ከማወቅ ባሻገር የኤርትራ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ድረስ  ያለውን መብት ከማወቅ ባሻገር የኤርትራ ሕዝብ ለነፃነት የሚያደርገውን ትግል መደገፍ ከ1969 ዓ.ም ጀምሮ የድርጅቱ አቋም ሆኗል። ……የኤርትራ ሕዝብ ነፃነቱን አረጋግጦ የራሱን መንግስት  ለመመስረት  የነበረው  ፍላጎትና  ለነፃነት ትግሉ ይሰጥ የነበረው  ድጋፍ ከፍተኛ ነበር።…” ይላል።
 ሆኖም የሗላ ሗላ፤ አውነትና ንጋት እያደረ ሲጠራለት  ኤርትራን ችግር በመገንጠል ሳይሆን “በፌደራል ሩፓብሊክ” መፈታት አለበት ይላል። ፌደራል ሪፓብሊክ ምን ማለት እንደሆነ ባያብራራውም። ይህ ይበል እንጂ የሐገሪቱ ሉዓላዊ የወደብና የመሬት፤ እንዲሁም የሕዝብ ቁርኝት በሚመለከት እርማት አድርጌአለሁ ባለው እርማት ላይ የተጠቀሱት ሉዓላዊ ጉዳዮችን በሚመለከት የመጠየቅ መብታችን በግልጽ  አላብራራም።  
ታዲያ ያ ትውልድ ጫቋኝ ብሔር በሌለበት “ጨቋኝ ብሔር” ነበር እያለ የወያኔ ትክከለኛ ቅጂ ቀድቶ “የተቀሩት ብሔር ብሔረሰቦች” ብሎ ኢሕአፓ የሚጠራቸው “በጫቋኙ ብሔር”  ላይ “ትግል አንዲያካሂዱ” ካልሆነላቸው ደግሞ “እንዲገነጠሉ” የሰበከን ያ ትውልድ በተመለከተው መነጽር መመልከቱ እንዴት ስሕተት ሊሆን ይችላል? ይህ ፍልስፍና ያመጣው ሰበብ አሁንም አገሪቷን እያመሳት ስለሆነ፤ እኔ ይህንን አንስቼ መነጋገሪያ ማድረጊዬ በምንም መልኩ አሲምባዎች ሽርደዳ ውስጥ መግባት አልነበራችሁም።     
አዎ ያ ትውልድ ትምህርት ዘረኛነትን ሳይሆን ጭቆናን ፤አምባገነንነትን አስተምሯል። ዘረኝነት በሌላ መለክያው የወያኔን አይነት እስከ መገንጠልን ሰብኳል። አንድ ሎችን ክፍሎች የጨቆነ “ጨቋኝ ብሔር” አለ ብለህ ስታስተምር “ ጨቋኝ በተባለው ብሔር ተወላጅ ላይ ጥላቻ አንዲነሳ መቀስቀስ ነው። ይህ ነው ኢሕአፓ ወያኔ ኦነግ የቀሰቀሱት ትምህርት “ነፍጠኛ/አማራ” (በዋለለልኝ አመርኛ) የሚባል “አንድ ጨቋኝ ብሔር” አለ ብላችሗል።  ስለሆነም ጨቋኝ ብሔር ብላችሁ ባስተማራችሁት ቅስቀሳ ውጤቱ “የአማራን በነፍጠኘነት” ስም መለያ መስጠትና ዛሬ እንዲባረር፤አንዲጨፈጨፍ ሰበብ ሆኗል።  አንድ ዜጋ፤ወይንም ግለሰብ በቡድን አንዲረገጥ ያ ትውልድ  እስተምሯል። ለዚህ ነው አሁንም ቡድኖች እነሱን በማይመስል (ላብ አደር፤አርሶ አደር፤ ብሔር፤ብሔረሰብ፤ሕዝብ……) ልዩ ክፍል ካለ ለጥቃት፤ለመረገጥ ምክንያት ሆነ እየተባረረ፤እየተገደለ ንብረቱ፤ንግዱ እየተቀማ ያለው።
የአሲምባ ፈላስፎች በጽሑፌ ከተስማሙ “ጥሩ” አበቃሁ በዚህ እደመድመዋለሁ ማለት ነው።  ካልሆነ ግን በሚቀጥለው ጽሑፌ ማርክሲዝም ማለት ፋሺዝም መሆኑንና ስለ ዋለልኝ በጻፍኩት ላይ ሁለት የኢሕአፓ ምሁራን ከጥቂት አመታት በፊት የጻፉትን ለኔ በዋለልኝ የሰጠሁትን  መልስ ተብሎ  ባለፈው ወቅት አሲምባ ድረገጽ ላይ የተለጠፈው በዝርዝር አብራራለሁ። ለሁለም ኳሷ ለነሱ ሰጥቻለሁ። እንቀጥል አንቀጥል፤ የናንተ ጉዳይ ነው። እውነት የመጻፍ ነጻነት ትርጉሙ ቢገባችሁ ኖሮ፤ የናንተ እና የመሪዎቻችሁ ጽሑፍ ስትለጥፉ አብሮ የኔንም መልስ እና ትችት በድረገጻችሁ መለጠፍ ነበረባችሁ፤ አለመታደል ሆኖ፤ ያንን ለማድረግ አልፈቀዳችሁም። ወደዳችሁ ጠላችሁ የኔን መልስ ከድረገጻችሁ ለመሸሸግ ብትጥሩም፤ ከቁጥጥራችሁ ውጭ በሆኑ ድረገጾች ከኢትዮጵያዊያን አንባቢዎች (ከወዳጅም ከጠላትም) ዓይን ልተጋርዱት ከቶ አይቻላችሁም። ደግነቱ እንኳን መንግሥት አልሆናችሁ። መንግስት ብትሆኑ የኔን ጽሁፍ እንዲህ ከሕዝብ እይታ የሸሸጋችሁት ፤ በላብ አደር ፓርቲ እየተመራችሁ እመንግስት ሥልጣን ላይ ወጥታችሁ ብትኖሩ ኖሮ፤ በአካል ምን ታደርጉኝ ኖሯል? ትግሬዎች እንዲህ ይላሉ “ንዘረባ አስተውዒልካ፤ ንእኽሊ ኣኾምሲዕካ” ይባላል (ስትናገር አስተውለህ ስትበላም አኝከህ” ይላሉ።  አበቃሁ!
አመሰግናለሁ፤
ጌታቸው ረዳ (Editor Ethiopian Semay) October 12, 2015