Sunday, June 27, 2021

ሕዝብን በማስራብ ገንዘብ የማግበስበስ የወያኔ ገመና ማሕደር ከገብረምድህን አርአያ የተላከልኝ ሰነድ ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay) 6/27/2021

 

ሕዝብን በማስራብ ገንዘብ የማግበስበስ የወያኔ ገመና ማሕደር

ከገብረምድህን አርአያ የተላከልኝ ሰነድ

ጌታቸው ረዳ

(Ethiopian Semay) 6/27/2021

ዛሬ የማቀርብላችሁ 1976 N.G.O. ለጋሽ ድርጅቶች ወደ ትግራይ መግባት እና ተከትሎ የተገኘው የውጭ አገር ዕርዳታ የወያኔ መሪዎች ለግላቸው እና ለድርጅቱ ወታደራዊ ፍጆታ እንዴት እንደተጠቀሙበት የሚያሳይ ወዳጄ የገብረመድህን አርአያ ከብዙ አመታት በፊት የላከልኝን ሰነድ ላቅርብላችሁ ነው።

 ከሰነዱ ውስጥ እንደመግቢያ ቀኝጭቤ ላስነብባችሁ፡

“…..የሰው ልጅ እየረገፈ በየመንገዱ ቀባሪ አጥቶ የጅብ ቀለብ በሆነበት ወቅት ነበር ስብሰባው ለ30 ቀናት የተካሄደው። የጉባኤውን ቆይታ ወጭ፤ የምግብና መጠጥ ወጪን ጨምሮ፤ ለትዝብት እንመልከት። በማእከላዊ ኮሚቴ የምግብ ዋና ሃላፊ ወ/ሮ ኤልሳ አስፍሃ የጻድቃን ገ/ተንሳይ ሚስት ስትሆን፤ በእሷ እዝ ስር በቅድመ ዝግጅቱ 300 ከብቶች ለእርድ ቀርበዋል። በየቀኑ ከ7-10 ከብቶችና ሁለት ፍየሎች ይታረዳሉ። ሁሉም ጉባኤተኛ የሚመገበው የነጭ ጤፍ እንጀራ ነው። በየቀኑ ጠዋት ቁርስ አምባሻና የስጋ ጥብስ ሆኖ፤ ምሳና እራት የስጋ ቀይ ወጥ፤ የስጋ አልጫ ወጥና ጥብስ ይቀርባል። በተጨማሪም የታሸጉ ፍራፍሬዎችና አትከልት እንደልብ ነበር። መጠጥ ጠጅ፤ ጉሽ ጠላ፤ የጠራ ጠላ እንደ ውሃ ተንቆርቁሯል። እንዲሁም ውስኪና ቢራ በጅምላ ነበር።

የጉባኤው ተሳታፊዎች አብዛኛዎቹ የተገኙት ከነሚስቶቻቸው በመሆኑ፤ ምርጥ ፍራሽ፤ ብርድ ልብስና አንሶላ ከሱዳን ተገዝቶ እየተንፈላሰሱ ነበር። በተለይም የማ.ሌ.ሊ.ት. ማ/ኮሚቴ አባላት። በዚህ መሰረት በቀን የሚወጣው ወጪ እንኳንስ ሽምቅ ተዋጊ ቀርቶ የአንድ ሃብታም ሃገር መንግሥትም ሲያወጣው የማይችል ነበር።………” ሙሉውን እነሆ። መልካም ንባብ (ኢትዮ ሰማይ) ።

ትግራይ ውስጥ ብዙ ቦታዎች 1975 በሚጥለው የክረምት ዝናብ አልታደለም። በመስከረም 1976 የእህል ቡቃያ አልታየም። በርካታ ቦታዎች በድርቅ ተጠቅተዋል። ለክፉ ጊዜ የሚቀመጥ የእህል ክምችትም የለውም። የህ.... አመራር ከአፉ እየነጠቁ ባዶ ቤት ይዞ የተቀመጠ ለችግር የታደለ ሕዝብ ነበር። ወደ ደርግ ገብቶ እርዳታ መጠየቅም በህ.... እንደ ትልቅ ወንጀል ሆኖ ስለሚቆጠር፤ ገብቶ የተመለሰ ተይዞ ሃለዋ ወያነ ገብቶ ይገደላል።

ድርቁ የዓለም አቀፍ እይታን ስለአገኘ የውጭ ሃገር ለጋሽ ግብረሰናይ ድርጅቶች ትግራይ ገብተው እርዳታ ለመስጠት የህ.... አመራርን ጠየቁ። የህ.... መሪዎችም እሺ ብለው የእህሉ መከፋፈል በነሱ በኩል እንዲሆን ተስማምተው ጨረሱ።

ደብዳቤ ከስብሃት ነጋ

በወቅቱ እኔ የህ.... ኢኮኖሚ ማለትም ንብረት፤ ስንቅና ገንዘብ ሃላፊ በመሆን የምሰራ ታጋይ ነበርኩ።

የታሸገ ደብዳቤ በስሜና አድራሻዬ በአሰኳይ ተላከልኝ። በውስጡ የያዘው ፍሬ ነገር፤ እርዳታ የሚሰጡን ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በአንድ አንድ አካባቢ በድርቅ ለተጠቁ እርዳታ ለመስጠት በማረት በኩል ይመጣሉ። አንተ እንደ እስላም ነጋዴ ሆነህ እህል ትሸጣለህ። ተግባርህ በነሱ ፊት እስላም ነጋዴ እንጂ ታጋይ አይደለህም የሚል ነበር።

 

ስብሃት ነጋና መለስ ዜናዊ ከአቅማራ ተምቤን ተያይዘው በመምጣት ሽራሮ ተገናኘን። እስላምነቴን ለማረጋገጥ እንዲረዳኝ ቁርአን መጽሐፍ፤ መቁጠሪያና ጥምጥም ይዘውልኝ መጡ። ይህን ያሰባሰቡት ከአብይአዲ እስላሞች ነበር።

የኔና የስብሃት ነጋ ንግግር

ሁለታችን በምስጢር የተነጋገርነው፤ እኛ እህል የለንም። እዚህ ያለው ከሻእቢያ በገንዘባቸው የሸመትንላቸው ነው። በየቦታው በብዛት ስለአለ እንጠቀምበታለን። እህሉ ለግብረ ሰናይ ለጋሾች አነስተኛ ስለሆነ በሁሉም ቦታ በብዛት የሚታይበትን ዘዴ እንፈጥራለን። ኩንታሎቹን ተከዘ አሸዋ ሞልተን ሰማይ እናደርሰዋለን። ይህ ግን ጥብቅ ምስጢር ነው አለኝ።

እህሉ የተከማቸበት ቦታ

ማይ ኩሕሊ፤ መንጠብጠብ፤ እንዳጉሬዛ፤ አዲጸጸርና ተከዘ በሚባሉ አካባቢዎች ከግማሹ በላይ በአሸዋ የተሞላ ኩንታል በየቦታው ተቆለለ። ብዛቱ 1,500 እስከ 2,500 ኩንታል የሚደርስ ነበር። የግብረ ሰናይ ተጠሪዎች መጡ። እኔ ሼክ መሃመድ የሚል ስምና የውሸት ሚስትም ተዘጋጀልኝ። ሁሉንም አሳይቼ ወደ ቤት ተመለስን። ለአንድ ኩንታል 120 ሂሳብ የአምስቱ ቦታዎች ተመን የሜሪካን ዶላር $2 ሚሊዮን ተቀበልኩ። ከነሻንጣው አስረክበውኝ ከተክለወይን አበፋ ተመልሰው ሽራሮ እንደሄደ ከግማሽ ሰዓት በኋል ቤት ማይኩህሊ ስለነበር መለስ ዜናዊ መጥቶ ገንዘቡን በሙሉ ተሸክሞ ሄደ። ቀጥሎ ደግሞ መቼ እንደሚመጡ ሥዩም መስፍን ሱዳን ሆኖ ጊዜውን እያመቻቸ ለስብሃትና ለመለስ በሬዲዮ መልእክት ስለሚያስታላልፍ ተዘጋጅቶ ለመጠበቅ አሰቸጋሪ አልነበረም።

ሌሉቹ የግብረ ሰናይ ድርጅቶች ከቦታው ለመድረስ ሰባት ቀን ስለሚፈጅባቸው፤ የታዩትን እና የተሸጡትን እህሎች በሌሊት በጭነት መኪና በማመላለስ፤ አዲ መሃመዳይ፤ ሸመልባ፤ ሱር፤ ደደቢትና ጓል ደደቢት እንዲከማቹ ተደረገ። በብዛት አሸዋ የሞላው 3,000 የማሽላ ኩንታል ተደረደረ። ብዛቱን አስቀድመው በተክለወይን አሰፋ አስተርጓሚነት ይጠይቁኛል። እኔም ባያችሁት ቦታ በየአንዳንዱ 3,000 ኩንታል ማሽላ ነው አልኳቸው። ቀጥለው ተክለወይን አሰፋን ትክክል ለመሆኑ እናንተ አረጋግጣችኋል በለው ሲጠይቁት፤ አዎን አረጋግጠናል ይላቸዋል። እኔ እንግሊዝኛ እንደማልሰማ ሆኜ ነው የቀረብኩት። እነዚህ ቦታዎችን ተዘዋውረው ካዩ በኋላ በሂሳቡ መሰረት በተጨማሪም አዲጸጸር 4,000 ኩንታል ስላሳዩአቸው በጠቃላላ ብር 20 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር አስረከቡኝ። ገንዘቡን እንደተቀበልኩ ተመልሰው ሽራሮ ሄዱ። ከግማሽ ሰዓት ገደማ በኋል ስብሃት ነጋ መጥቶ ገንዘቡን በሙሉ ተሸክሞ ሄደ።

በተመሳሳይ መንገድ ቀደም በለው የተሸጡትን የአሸዋና የህል ኩንታሎች ሽራሮ በአምስት ትላልቅ መጋዘኖች ሞልተው ከቦታ ቦታ በሌሊት እየተንቀሳቀሱ ለሌላ የግበረሰናይ ድርጅት በመሸጥ ተጨማሪ ገንዘብ ተቀበልኩ። እንደተለመደው መለስ ዜናዊ መጥቶ ጠራርጎ ወሰደው።

አዲሃገራይ፤ አዲአውአላ፤ አዲዳውሮና አዲ ነብረኢድ ቀደም ብለው የታዩትን የኩንታል ክምችቶች በመኪና ከቦታ ቦታ በማንቀሳቀስ ተደጋግመው ተሸጡ። ከአንድ አካባቢ ሽያጭ ብቻ ከግማሽ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ይዘው የመጡትንም አንድ ወይም ሁለት ክምር በማየት ገንዘቡን ቆጥረው ይሰጡኛል። አሁንም ስብሃት ነጋ ወይም መለስ ዜናዊ መጥተው ገንዘቡን ሰብስበው ይወስዱታል። ብዙ ገንዘብ የገባው አዲሃገራይና አዲአውአላ ሲሆን ከነዚ ቦታዎች ገንዘቡን የሰበሰበው መለስ ዜናዊ ነው። ከአዲደእሮና አዲነብሪኢድ የተገኘውን ገንዘብ የወሰደው ደግሞ ስብሃት ነጋ ነበር። በዚህ አይነት አሸዋ ሸጠን የውጭ ሃገር ግበረሰናይ ድርጅት ነጮችን አታለን በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር አግኝተናል።

ይህን አይነቱን የማጭበርበር ዘዴ እቅዱን ያወጡት ሁለቱ መሪዎች ነበሩ። ያወጡት የሌብነት እቅድም ግባቸውን መትተዋል። የተገኘውn ገንዘብ ሕዝብ እንረዳበታለን ብለው የሰበሰቡት ነበር። ገንዘቡ ግን በድርጅቱ ውስጥ ለሚፈለገው ተግባር ማለትም ወታደራዊ ቁሳቁሶችን መግዣና በተለያዩ ቦታ ሲውል በአይናችን ያየነው ሃቅ ነው። በድርቁ የተጠቃው ሕዝብ ምንም አልተጠቀመበትም። ለዝርፊያው ግን ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል።

1977 ድርቅ በትግራይ

1976 በበልግና በክረምት ይጠበቅ የነበረው ዝናብ እንዳለፈው ዓመት ፈጽሞ ጠፋ። ዓመቱን ሙሉ ዝናብ ባለመጣሉ ኩሬዎችና ወንዞች ሁሉ ደረቁ። በዚህ ክፉ ድርቅ የተነሳ የቤት እንሰሳት የሚበሉት ሳርና ቅጠል፤ የሚጠጡት ውሃ ጠፋ። በዚህም ምክንያት በየቦታው እየሞቱ ወድቀው ቀሩ። የድርቁ ጦስ በእንሰሳት ብቻ ተወስኖ አልቀረም። ሕጻናት፤ አረጋውያን፤ እናቶች፤ አባቶች በሙሉ ፉት የሚባል ውሃ፤ የሚቀመስ እህል አጡ። ቀባሪ ስለጠፋ፤ በየመንገዱና ጫካው እየወደቁ የአውሬ መጫወቻ ሆኑ። ሕጻናት የሞቱ እናቶቻቸውን ጡት እያጋጡ በተራቸው እስከወዲያኛው አሸለቡ። ሕዝብ እንደ ቅጠል ረገፈ። ሁኔታው ወደ ዓለም ህበረተሰብ ጆሮ ደረሰ። በመቀጠልም የእርዳታ ጥሪው ተስተጋባ። በርካታ ጋዜጦችና የለጋሽ ሃገራት ተወካዮች ሁኔታውን በአካል ተገኝተው ተመለከቱ። ይህንን አሰቃቂና ክፉ ቀን ያዩ በአፋጣኝ ለዓለም ህበተሰብ እርዳታውን እንዲቸር አልቅሰው ለመኑ፤ ተማጸኑ። የዓለም ህብረተሰብም አፋጣኝ ምላሽ ሰጠ።

በዚህ ወቅት የህ.... አመራር በድርቅ የተጎዳው የትግራይ ሕዝብ ወደ ሱዳን እንዲሰደድ በእዙ ስር ለሚገኘው የሕዝብ ግንኙነት ትእዛዝ አስተላለፈ። በትእዛዙ መሰረት የቀጠናው (ሪጅን) ሶስት ሃላፊ በነበረው አሸብር ንርአዮ የበላይ መሪነት በየወረዳውና በየጣቢያው ባሉት የሕዝብ ግንኙነት አባላት አማካኝነት ተግባራዊ ሆነ። አሸብር ከእኔ ጋር አፋር ውስጥ ወታደራዊ ትምህርት ስልጠና አድርገን ስንጨርስ ከመጀመሪያው በሕዝብ ሥራ የተመደበ ሲሆን ቀስ ብሎ የሚናገር በታጋዩም ሆነ በሕዝብ የሚወደድ ጸባይ ያለው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ አሸብርን በዚህ የስደተኛ አመላላሽነት የመደቡት በብዙ ሺህ የሚቆጠረው ስደታኛ የራያ ስደተኛ ስለነበር እሱን ስለሚያውቁት መጠቀሚያ ለማድረግ ያሰሉት ዘዴ ነበር። የህ.... አመራር ስንት ሰው በስደት መፈናቀል እንዳለበትም አስቀድመው በእቅድ ይዘውታል። ስደተኛው ገና ጉዞ ሳይጀምር ሱዳን እንደደረሱ የሚያርፉበት ቦታ ተዘጋጅቶላቸው ነበር።

1. ትዋባ 250,000 ሕዝብ

2. እንጉርጃ 500,000 ሕዝብ

3. ስፋዋ 350,000 ሕዝብ

እንዲያርፍባቸው ጣቢያዎቹን በመመደብ ድልድል አደረጉ።

ስደተኛው ከየቦታው በውዴታም አብዛኛው ደግሞ በግዴታ ወደሱዳን እንዲፈልስ ተደረገ። በጉዞው ወቅት ያቀረቡለት ዱቄት፤ ዘይት፤ ስኳር ለሕጻናት ወተት ወይም ለሰው ልጅ የሚያስፈልግ ዝግጅት አልነበረም። በጉዞው ውሃ ጥምና ረሃብ ከሚጎዳው በተጨማሪ ጉዞው በቀን በመሆኑ የተነሳ ደርግ በሚግ 21 23 እንደዚሁም በተዋጊ ሄሊኮፕተር በታገዘ የአየር ደብደባ 13,000 በላይ ሰው በተወሳሰበ ችግር በረሃ ላይ ሞተ፤ ተገደለ። በመጨረሻም የሞተው ሞቶ የቀረው 6 ሳምንት ውስጥ ሱዳን ጠቅልሎ ገባ። በየመንገዱ የሚበሉት ምግብ አልነበራቸውም። በሱዳን ፖርት ግን በየአይነቱ እህል፤ ስኳር፤ ሻይ ቅጠል፤ ለሕጻናት አልሚ ምግብ፤ ወተት፤ ወዘተ ቀደም ብሎ የተከማቸ ነበር። በየጊዜውም ያለማቋረጥም በትልልቅ መርከቦች ጭነቱ መራገፉ እንደቀጠለ ነበር።

የሚያሳዝነው ግን ትግራይ ውስጥ የቀሩት በበሽታና በረሃብ ሲሞቱ በስማቸው ከተቀበሉት እርዳታ ከመስጠት ይልቅ ጋዜጠኞችን እያስመጡ አጥንታቸው ላይ የደረቀ ቆዳቸውን፤ ከእናታቸው ጋር ተጣብቀው የሞቱትን ሬሳ እየመረጡና እርቃናቸውን የቀሩትን እየለዩ ፎቶግራፍና ቪዲዮ በማንሳት ለዓለም ህብረተሰብ እንዲጋለጡ በማድረግና በሱዳን የስደተኛ ሰፈር መጠለያ ያጎሯቸውንም በተመሳሳይ ሁኔታ የተዳከሙትን ሕጻናት፤ እናት፤ አዛውንት በሶስቱም የስደተኛ ሰፈር የውጭ ጋዜጠኞችን የወያኔ ታጋይ ፎቶግራፍ አንሽዎችን አሰማርተው በቪዲዮ እየተቀረጸ በየሃገሩ በማሰራጨት በለጋሽ ግብረሰናይ (የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች) አማካኝነት መለመኛ አድርገው ምግብ፤ መድሃኒት፤ የህክምና መሳሪያ፤ ልብስ በከፍተኛ ደረጃ ተመጸወቱባቸው።

ለስደተኛው ከፓርት ሱዳን ጥሬ በቆሎ በመኪና እየተጫነ በሶስቱ መጠለያ ጣቢያዎች በማከማቸት ክፍፍሉ ለአባወራ ከነቤተሰቡ በወር 15 ወይም 20 ኪሎ በቆሎ፤ አንድ ኪሎ ስኳር፤ ግማሽ ኪሎ ጨው በራሽን መልክ አከፋፈሉ። እንደዚሁም ለነጠላ ግለሰብ ደግሞ 10 ኪሎ ጥሬ በቆሎ፤ ግማሽ ኪሎ ስኳር፤ እሩብ ኪሎ ጨው እንዲደርሰው ተደረገ።

ህክምናን በተመለከተ .... በሶስቱም ጣብያዎች ላከማቻቸው 1.5 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እውቀትና ችሎታ የሌላቸው ሁለት ሁለት ግለሰቦች በየጣቢያው መድበው የወባ ኪኒን አስይዘው በመላክ  ስደተኛውን አላስፈላጊ የሆኑ መድሃኒት በማከፋፈል ላልተፈለገ ችግር ሲዳርጉት ከአኗኗር የተነሳ በተላላፊ በሽታ እንዲረግፍ አደረጉት። በእነዚህ ጣብያዎች የወያኔ ድርጅት ወክሎ በበላይነት የተመደበው አርከበ እቁባይ ነበር።

መጠለያን በተመለከተ፤ የማረፊያ ቦታ ይከለል እንጂ ጣቢያዎቹ ስማይና ምድር ብቻ ነው ያላቸው። በመሆኑም ስደተኛው የቻለው በየዛፉና በየግንዱ ስር ተጠለለ። በመጨረሻም የራሳቸውን መጠለያ እንዲሰሩ በየበረሃው ተሰማርተው ቅጠል ለቅመው፤ ሳር አጭደው፤ ዳስ ሰርተው እንዲኖሩ ተደረገ። ለነዚህ ስደተኞች ከዓለም ህብረተሰብ በእርዳታ ከተሰጠው ሶስት ሚሊዮን ድንኳኖች ውስጥ በየጣቢያዎቹ ለህክምና ተብለው አንዳንድ ደንኳኖች ለአብነት ተዘርግተው ይታያሉ። ቀሪው በህ.... እጅ ገባ። ከዚህም በላይ ወፍራም U.N.H.C.R. የሚል ጥቁርና ሰማያዊ ፕላስቲክ በበዛት ቢመጣም የወያኔ አመራር አንሰጥም በማለት አስቀድመው በጭነት መኪና አጓጉዘው ደጀናና በሌላ ቦታ ሰወሩት።

የመጣው እርዳታን አከፋፈል በተመለከተ

ድርቁ በመላው ኢትዮጵያ ስለነበር የሚሰጠው ደራሽ የእርዳታ ምግብ፤ ልብስ፤ መድሃኒት፤ የህክምና መሳሪያ ወዘተ የደርግ መንግሥት የህ...ትና የሻእቢያ አመራሮች በተባበሩት መንግሥታትና የግብረሰናይ ለጋሽ ድርጅቶች በጋራ በደረሱበት ስምምነት እንዲከፋፈል ተደረገ።

1. ደርግ በሚቆጣጠራቸው ከተሞችና ገጠር አካባቢዎች ሁሉ በግብረሰናይ ድርጅቶች ቁጥጥር ሆኖ እንዲያከፋፍል፤ በቀጥታም በምጽዋና በአሰብ ወደቦች እየተራገፈ የመጣውን እርዳታ ለሁሉም እንዲያደርስ፤

2. ...ትና ሻእቢያ በሚቆጣጠሯቸው ነጻ መሬት ለሚኖረው ችግረኛ ደግሞ ፓርት ሱዳን እየተራገፈ ራሳቸው ነጻ ሆነው ለሕዝብ እንዲያከፋፍሉ ሲወሰን፤ ከህ.... አመራር ወስጥ ይህንኑ በሃላፊነት የተረከቡት መለስ ዜናዊ፤ ስብሃት ነጋ፤ አባይ ፀሃየ፤ ሥዩም መስፍን፤ አርከበ እቁባይ ናቸው። የጽሕፈት ቤቱ ሥራ የሚያከናወነው በመለስ ዜናዊና ስብሃት ነጋ ፊርማ ሲሆን፤ በስምምነቱም ሁለቱ በፊርማቸው ቃል ገብተው ተረከቡ። ነገር ግን ገና ፊርማቸው ሳይደርቅ ቃላቸውን በማጠፍ ፈረንጅን ባገሩ ሸጠን በላነው በማለት በደስታና ፈንጠዝያ ወደ ትግራይ ተመለሱ። ከዚህ በኋላ ማንኛውም የእርዳታ አሰጣጥ ሙሉ በሙሉ በህ.... ቁጥጥር ውስጥ ሆነ። በዚህም ጊዜ ፖርት ሱዳን የተራገፈው የምግብ፤ መድሃኒት፤ ልብስ ወዘተ ለትራንስፖርት የሚያገለግሉ ተሽከርካሪዎች የጭነት መኪናዎችና ፈጥኖ ደራሽ ፒክአፖች መግባታቸውን ሲያረጋግጡ የትራንስፖርት ክፍል አደራጁ። ሃላፊነቱንም ለዳዊት ብርሃነ ሰጡት።

የመጣው እርዳታ

ቀደም ብሎ በፖርት ሱዳን ከተከማቸው የምግብና ሌሎች እርዳታ እቃዎች በተጨማሪ፤ ቅባት፤ ዘይት፤ ቅቤ፤ መድሃኒትና የህክምና መሳሪያዎች በየቀኑ ሁለት የጭነት መርከቦች መጉረፍ ጀመሩ። ፓርቱ እየጠበበ ስለሄደም አዳዲስ ትልልቅ ማርቼዲስ የጭነት መኪናዎች (250) ላንድ ክሩዘር ቶዮታ (89) ቤንዚን (5,000,000 ሊትር) ናፍጣ (4,000,000 በርሜል) ደረሰ።

እንደዚሁም አካፋ፤ ዶማ፤ የተለያዩ መሬት መቆፈሪያ መሳሪያዎች አብረው መጥተዋል። ካለምንም ማቋረጥ የምግብ ቅባት፤ መድሃኒት፤ የወባ መከላከያ፤ አጎበሮችና ልብስ ከመስከረም 1977 እስከ አመቱ መጨረሻ ቀጠለ። በእርዳታ የተገኘው በብዛትና መጠኑ ሲሰላ ጠቅላላ የትግራይን ክፍለ ሃገር ከተማና ገጠር ጨምሮ ለአራት ሚሊዮን ሕዝብ ካለምንም ችግር ሁለት ዓመት ሙሉ ሊቀልብ የሚችል እርዳታ ተገኝቷል።

ወያኔ ከደርግ በተለያየ ጊዜ የነጠቃቸውን 80 የጭነት መኪናዎችና ለእርዳታ የተላኩ 250 የጭነት ማርቼዲሶች ተጨምረው በጠቅላላው 330 የጭነት መኪናዎች ፖርቱን ስለአጣበቡት፤ ከሱዳን መንግሥት ቶሎ አንሱ የሚል ግፊት ስለመጣባቸው፤ መኪናዎቹ ከፖርት ሱዳን እየተጫኑ ገዳሪፍ መራገፍ ጀመሩ። ለዚህ ሥራ ደግሞ በዋና ሃላፊነት የተመደቡት ቀኝአዝማች አስገዶም የሚባሉ የአክሱም አየር ማረፊያ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩና ደርግን ከድተው ከወያኔ የተቀላቀሉ የአድዋ ሰው ነበሩ።  

በዚህ አይነት የመጣውን እርዳታ በሃላፊነት የተረከቡት የህ.... ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በስዩም መስፍን የበላይ አዛዥነት

1. አባዲ ዘሙ 3. ቴዎድሮስ ሃጎስ

2. ብርሃነ /ክርስቶስ 4. የማነ ኪዳነ

እንዲቆጣጠሩ ተደረገ። ለቀረው ሕዝብ ከሚመጣው እህል የሚሰጠው ነገር የለም። በሱዳን ስደት ላይ ያለው መጀመሪያ እንደገለጽኩት ጥሬ በቆሎ እንዲሰጠው መደረጉን ሳትረሱ፤ በትግራይ ውስጥ የህ.... መሪዎች በየቀኑ በአይናቸው የሰው ሬሳ በየመንግዱ ወድቆ፤ የሰው ልጅ በአጥንቱ ሲቀር እየተመለከቱና ሕዝቡ እንደቅጠል እየረገፈ፤ የቤት እንሰሳት ማለቁን እያታዘቡ፤ ከዚያ ሁሉ ከሚጎርፍ የእርዳታ ምግብ ሩብ ኪሎ እንኳን ለችግረኛው ሕዝብ አልሰጡም። የህ.... አመራር ጨካኝ፤ አረመኔና ጸረ-ሕዝብ መሆኑን ውስጥ ያለነው ታጋዮች በሚገባ እናውቃለን። በሕዝብ ስም ለምነው ያገኙትን ቀምተው በችግር እንዲያልቅ የፈረዱ አረመኔዎች መሆናቸውንም ተረድተናል።።

ይህ ወቅት የድርቅ ብቻ ሳይሆን የማ.... ምስረታ ጊዜም እየደረሰ ነበር። በመሆኑም፤ በመስከረም 1977 ፖርት ሱዳን የገባውን የስንዴ ዱቄት፤ ዘይት፤ ልብስ፤ መድሃኒት ወደ ገዳሪፍ ከተጓጓዘ በኋላ እንደጋና 12 የጭነት መኪናዎች በፈረቃ የማ.... ካዳድሬ ስልጠና ወደሚሰጥበት ቦታ እንዲከማች ተደረገ። የእርዳታው ንብረት ሁሉ ለዚሁ ስልጠና ወጭ መሸፈኛ ሆነ። ስልጠናውም 1ኛው እስከ 5ኛው ዙር የሁለት ወራት፤ 6ኛና 7ኛው ደግሞ በሶስት ወራት ስልጠና ተከናወነ። ከመጀመሪያው ሰልጣኞች መካከል መለስ ዜናዊ፤ አባይ ፀሃየ፤ አለምሰገድ ገብረአምላክ ሲገኙበት፤ 1 - 5 ዙር በተከታታይ 400 ካድሬዎች በጠቅላላ 2,000 ካድሬዎች ሰልጥነዋል። ስልጠናው በፈንጠዝያ፤ ማታ ማታ ጭፈራ፤ ምግብ እንደልብ የነበረበት፤ በየሁለት ሳምንቱ ጠላ እየተጠመቀ እነሱ ሲሰክሩና ለሕዝብ ተብሎ በመጣው የእርዳታ ገንዘብ ጠግበው ሲበሉና ከዚያም አልፎ ሲሰክሩ፤ በተቃራኒው ደግሞ የአካባቢው ኗሪዎች በረሃብና በጥም ሲያልቁ ... የሚያይ አይን እና የሚያስብ አእምሮ አልነበረውም።

6ኛው ዙር እኔ፤ አዲሱ ለገሰና ታምራት ላይኔን ጨምሮ 350 ታጋዮች ሰለጠንን። በስልጠናው በነበርንበት ሶስት ወር ውስጥ በየሳምንቱ ሁለት በሬ ከወልቃይት እየተገዛ ይታረድልን ነበር። ጠዋት ቁርስ፤ የፈለገ እንጀራ በወጥ ወይም አምባሻ ሻይ በወተት እየቀረበልን ተምረን ጨረስን።

7ኛው ዙር ስልጠና ሁለት ወር ትምህርታቸውን እንደተከታተሉ የማ... ምስረታ ስለደረሰ ቀሪውን ትምህርት ጉባኤው አካባቢ እንዲጨርሱ ተደረገ። ይህን ሁሉ የምገልጸው የትግራይ ሕዝብ በረሃብ እያለቀ ወያኔ ግን ለራሱ እርዳታውን እየተጠቀመበት መሆኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲረዳው በተጨማሪነት ያቀረብኩት መረጃ መሆኑን ለማሳየት ነው።

በሌላው ወገን ደግሞ ደርግ በያዛቸው ጣብያዎች እህሉ ከሞላ ጎደል በሚገባ ይከፋፈል ነበር። ወያኔ በሚቆጣጠራቸው ስፍራዎች ወሬው ስለደረሰ፤ ሕዝቡ ወደ ደርግ የዞታ መጓዝ ጀመር። የወያኔ አመራርም ይህን ስለአወቀ በሽሬ፤ በራያና አዘቦ ግራና ቀኝ ማንም ሰው ወደ ደርግ እንዳይገባ ትእዛዝ አስተላለፈ። ረሃብተኛውን ወደመጡበት እንዲመለሱ በኬላ ጠባዊ አማካኝነት ለማገድ ቢሞክሩም ሕዝቡ እምቢ በማለቱና ጠባቂዎቹም የአካባቢው ሚሊሻ በመሆናቸውና የህብረተሰቡን ችግር በሚገባ ስለተረዱ መንገዱን ክፍት በማድረግ የፈለገ ሁሉ ወደ ደርግ ገባ። እርዳታውን እንዳገኙም ብዙዎቹ ወደ ወያኔ ዳግመኛ ሳይመለሱ ቀሩ።

... ህብረተሰቡ ላይ የወረደው የድርቅ መቅሰፍት ቀላል መስሎ ሊታየው ይችል ይሆናል። ነገር ግን የታየው ሁኔታ እጅግ አስደንጋጭና መጥፎ ነበር። እናት ሁለት ሕጻን አቅፋ ለጆቹም እሷም ሞተው የታዩበት ጊዜ ነበር። ሕጻናት የሞተች እናታቸውን ጡት ሲጠቡ የታየበት ወቅት ነበር። አዛውንቶች በቁማቸው በጅብ ተበልተው የጅብ ትራፊ በየበረሃው ወድቆ የታየበት ጊዜ ነበር። አክሱም፤ ሽሬ፤ አጋሜ፤ እንደርታ፤ ራያና አዘቦ፤ አድዋ፤ ተምቤን፤ ሁለት አውላእሎ፤ እስከ ራያና ቆቦ ድረስ በተልያዩ ጊዜያትና በተደጋጋሚ የእርዳታ ለጋሾች እየተዘዋወሩ ተመልክተው የእርዳታ አስፈላጊነቱን ምስክርነት ለዓለም ሕዝብ የሰጡበትና ዓለምን ታማጽነው ያገኙትን እርዳታ ሕዝቡን ሳይጠቅም ወያኔ የፖለቲካ ትርፍና ሃብት ያካበተበት አጋጣሚ ነበር። የወያኔ ከሃዲና አረመኔያዊ አመራር የፈጸመው ተግባር እንኳን ቆሜልሃለሁ ከሚል ድርጅት ይቅርና ከሰው ፍጡር አስተሳሰብ ውጭ ከሆነ የማይጠበቅ ተግባር ነው።

ይህን ከዚህ ላይ ልግታውና ወደ ሱዳን ለገባው ስደተኛ የሚሰጠውን እርዳታ በተመለከተ ጥቂት ልበል። በድርቅ ለተጎዳው ሕዝብ የተለገሰው መጠነ ሰፊ እርዳታ አመራሩ ምን ሥራ ሰራበት? ከላይ እንደገለጽኩት ድግሞ በማ... ምስረታ ማግስት ስለነበር በቅድሚያ የማ...ትን ምስረታ ሁኔታ እንመልከት።

1977 የማ.... ጉባኤ

ወደ ጉባኤው ከመግባታችን በፊት የጉባኤው አዳራሽ እንዴት እንደነበረና በስንት ወጪ እንደተሰራ አስቀድሜ ላመላክት። የጉባኤው ቦታ ወርኢ ውስጥ ሆኖ አዳራሹን ለመስራት ወታደራዊ ጥናት ተደርጎ ከአይሮፕላን ድብደባ፤ በረጅሙ ከሚወነጨፍ ሚሳይል ጥቃት ነፃ የሆነና በሌሎች ወታደረዊ አባላት ተጠንቶ አስተማማኝ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ ነበር የጉባኤው አዘጋጅ ተመርጦ ሥራውን የጀመረው።

የጉባኤውን አዳራሽ ለመስራት ዋና መሃንዲስ የነበረው ታየ አስገዶም ሲሆን፤ የበላይ ተቆጣጣሪዎቹ ደግሞ ሙሉጌታ አለምሰገድና ሟቹ የደህንነት ሃላፊ ክንፈ /መድህን ነበሩ። ሥራውን ከሱዳን የመጡ 120 አናጢዎች ነበሩ። ለያንዳንዳቸው በወር ብር 600 እየተከፈላቸው በአራት ወራት ሰርተው አጠናቀቁ። ለምግብ አብሳዮች ደግሞ ብር 240,000 ተከፍሏል። ለአዳራሹ ሥራ በጠቅላላ ብር 4,700,000 ወጥቷል። አዳራሹ የተዘጋጀው 500 እንግዳዎችን እንዲይዝ ተደርጎ ነው። አዳራሹ ጣሪያውና ግድግዳው በቀይ ጨርቅ ተሸፍኖ የማርክስ፤ የሌኒን እና የስታሊን ምስሎች በፍሬም ወስጥ ተደርገው፤ እንዲሁም ማጭድ፤ መዶሻና ኮከብ ያለበት በቢጫ ቀለም ሆኖ ብልጭና ድርግም በሚሉ መብራቶች ያሸበረቀ ነበር። በሌሊት ሲታይ የሰለጠነች ከተማ ተመስል ነበር። አዳራሹ ኤሌትሪክ የሚያገኘው በሰዋራ ቦታ በተደበቁ ጄነሬተሮች አማካኝነት ነበር። ለአዳራሹ ማስዋቢያ ከተገዙት እቃዎች መካከል በርካታ ረጃጅም ጣውላዎች፤ ባሕርዛፎች፤ 250 የፕላስቲክ ጥቅሎች፤ 1,000 ጣቃ ጨርቅና 1,500 ቀይ ቀለም የተቀባ ጣቃ ጨርቅ ይገኙበታል።

ጉባኤው

ጉባኤው ያሰባሰበው የሰው ብዛት በጣም ከፍተኛ ነበር። ከነዚህ መካከል፤

በጉባኤው በሙሉ ድምጽ የሚሳተፉ 250

በጉባኤው ያለድምጽ የሚካፈሉ፤ እንደ ተፈራ ዋለዋ፤ ታምራት አዲሱ ለገሰ የመሳሰሉት 120

ጥበቃ የሚያካሂዱ አራት ብርጌድ 6,520

ሬዲዮ ኦፐሬተርና ሌሎችም ተጨምሮ 450

በካድሬነት ትምህርት ላይ የነበሩ ሰልጣኞች 350

ደሞዝተኛ የምግብ ሰራተኞች 200

በሃሰን ሽፋ የሚመራ ሃለዋ ወያነ ልዩ ሃይል 30

ጠቅላላው ድምር 7,970

ጉባኤው ሐምሌ 5 ቀን 1977 ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ሥራውን ጀመረ። የአዳራሹ ሁለት በሮች ተከፈቱ። በጣም አሸብራቂና ልዩ ነበር። የማናውቀው ገነት የገባን እንጂ በሰው የተሰራ አይመስልም። በጉባኤው ፊት ለፊት በአማረ መልክ የተሰራ፤ ሙሉ ለሙሉ በቀይ ጨርቅ የተሸፈነ የኮሚኒስት አርማ ይታያል። ከቀኝ ወደ ግራ ማርክስ፤ ሌኒን እና እስታሊን በትልቅ ፍሬም ሆነው ይታያሉ። የስብሰባው መሪዎች በቀይ ጨርቅ ያጌጠ ትልቅ ጠረጴዛ የህ.... ባንዲራ አለ። ፊት ለፊት አስራ አንድ ወንበሮችና አስራ አንድ

የድምጽ ማጉያዎች (ማይክራፎኖች) ተደቅነዋል። በትንሽ ፍሬም የተሰራ የነማርክስ ሶስቱ ስእሎች ከጠረጴዛው ፊት ይታያሉ።

በጉባኤው ላይ የኢ.... እና የሻእቢያ አባላት ከታጋዩ ጋር ተደባልቀው በመሳተፍ ላይ ነበሩ። በስብሰባው ድምጽ የሚሰጡና ካለድምጽ የሚሳተፉ በገመድ አጥር ተለይተዋል። በሩ ተከፍቶ ከትንሽ ደቂቃዎች በኋላ ሥዩም መስፍን ወደ መድረክ ወጥቶ እንኳን ደህና መጣችሁ የሚል በቁራጭ ወረቀት የተጻፈውን መልእክት አነበበ።

በመቀጠልም የፕሬዚዲየም አባላት አንድ በአንድ በስብሃት ነጋ እየተጠሩ ወደ መድረኩ እየወጡ በተዘጋጀላቸው ወንበር ተቀመጡ። በዚሁ መሰረት፤

1. መለስ ዜናዊ 7. አርከበ እቁባይ

2. ስብሃት ነጋ 8. ስየ አብርሃ

3. አባይ ፀሃየ 9. ግደይ ዘርአጽዮን

4. ሥዩም መስፈን 10. አረጋዊ በርሄ

5. ተወልደ /ማርያም 11. አረጋሽ አዳነ

6. ገብሩ አስራት

በየቦታቸው ተቀመጡ። በሊቀመንበርነት ጉባኤውን የመራው ሥዩም መስፍን ነበር። ጉባኤው ቀጠለ። የጉባኤው ትልቁ አጀንዳ ማርክስ ሌኒናዊ ርእዮተ ዓለምን ማእከል ያደረገ መርህ መቀበላቸውን እና የህ.... አመራር በሙሉ ማርክሳዊ ሌኒናዊ መሆኑን በማረጋገጥ በሞቀ ጭብጨባና ደስታ ቀጠለ። ሌላኛው አጀንዳ ደግሞ የድርጅቱ ፖሊሲን በተመለከተ ሲሆን፤ 1ኛው ጉባኤ የወጣውን ፖሊሲ 2ኛው ጉባኤ ያጸናል። ይዘነው የመጣነው ፖሊሲ ሳይለወጥ፤ ሳይቀነስ ይቀጥላል ተብሎ በሙሉ ድምጽ ጸደቀ። ቀጥሎ የመጣው የማእከላዊ ኮሚቴ ምርጫ ነበር። /ኮሚቴ በእለቱ ከተመረጡት 25 አባላት መካከል አረጋዊ በርሄና ግደይ ዘርአጽዮን ይገኙበታል። የፖሊት ቢሮውን ምርጫ ለቀጣዩ ቀን ተቀጥሮ የእለቱ ውሎ ተጠናቀቀ።

በሁለተኛው ቀን፤ ስብሰባው እንደተጀመረ ስብሃት ነጋ ተነስቶግደይ ዘርአጽዮን የስልጣን ስሰኛ ነው። በመሆኑም ከማ.... መርህ ጋር ሊጓዝ አይችልም፤ ረግረግ ውስጥ ገብቶ የሰጠመ ደካማ ወሬኛ ነው። በፖሊሲ ልዩነት ምንም የለንም ብቃት የለውም። ከዚሁ በመነሳት ከህ.... እና ከማ.... ተወግዷል። ወደ ፈለገው መሄድ ይችላል ገንዘብም እንሰጥዋለን። የድርጅቱን ዶኩሜንትና ንብረት አሁን እንረከባለን አለ በመቀጠል ሁለትኛውን ተባራሪ ደግሞ ሲያስተዋውቅ፤ከአረጋዊ በርሄ ጋር በፖሊሲ ልዩነት የለንም። ግን ጠቃሚ ነው ብለን እምነት ስለሌለን ከአሁን ጀምሮ ያለውን የድርጅቱን ንብረት ያስረክበናል ወደ ፈለገበት ሃገር ለመሄድ ይችላልሲል አወጀ ለአረጋዊ በርሄም ገንዘብ እንሰጥዋለን። በመቀጠል መለስና ስብሃት በእጃቸው የነበረውን የድርጅቱ ንብረት ተረከቡ። ወደ ጉባኤ አዳራሹ እንዳየገቡም ታገዱ። ከሰአታት በኋላ የማእካላዊ ኮሚቴ አባልነታቸውን ቦታ ለቀው እኛ ወደአለንበት አካባቢ ተቀላቀሉ። ሁለቱም የተባረሩት በስልጣን ሽኩቻ ብቻ ነው። ምንም ጠብና አለመግባባት አልነበራቸውም። በሁሉም በኩል የስልጣን ህረፍ ሽኩቻው በግልፅ የሚታይ መቆሳሰል ነበር። አሁንም፤ በተለይ አረጋዊ በርሄ፤ መለስ ዜናዊን ይደግፋል። የተባረሩትን ሁለት ታጋዮች አስመልክቶ በትንሹ ለመግለጽ፤ በአረጋዊ በርሄ መባረር ሁሉም ታጋይ ስሜት አልሰጠውም ነበር። በግደይ ዘርአጽዮን መባረር ግን በትንሹም ያዘኑ ጥቂት ነበሩ። እነዚህ ሁለቱ ተባራሪዎች 1980 . ሲባረሩ ለግደይ ዘራፅዮ $30000 ለአረጋዊ በርሄ $ 35000 ዶላር አሳቅፈው እስከ ገዳሪፍ ሸኝተው ሱዳን ድረስ አደረስዋቸው ወደ ስብሰባው ሂደት ስንመለስ፤ ከዚህ በኋላ የማ.... ፖሊት ቢሮ ተሿሚዎችን ዝርዝር መግለጽ ሲሆን በዚህ መሰረት ፖሊት ቢሮ፤ ስብሃት ነጋ፤ መለስ ዜናዊ፤ አባይ ፀሃየ፤ ሥዩም መስፍን፤ አውአሎም ወልዱ፤ ገብሩ አስራት፤ ስየ አብርሃ፤ ተወልደ /ማርያም፤ ጻድቃን /ተንሳይ በሙሉ አባልነት ተሾሙ። ተለዋጭ ፖሊት ቢሮ አባላት ደግሞ አርከበ እቁባይና አረጋሽ አዳነ ሆኑ። እነዚህ ሁሉ የመለስና ስብሃት ታማኞች ናቸው።

ይህ ጉባኤ የተካሄደው የትግራይ ሕዝብ በድርቅ ምክንያት እንደቅጠል እየረገፈ ባለበት ወቅት ነበር። የጉበኤው ወጪም ከዚሁ ሕዝብ የተነጠቀ ሃብት ነው። የሰው ልጅ እየረገፈ በየመንገዱ ቀባሪ አጥቶ የጅብ ቀለብ በሆነበት ወቅት ነበር ስብሰባው 30 ቀናት የተካሄደው። የጉባኤውን ቆይታ ወጭ፤ የምግብና መጠጥ ወጪን ጨምሮ፤ ለትዝብት እንመልከት። በማእከላዊ ኮሚቴ የምግብ ዋና ሃላፊ / ኤልሳ አስፍሃ የጻድቃን /ተንሳይ ሚስት ስትሆን፤ በእሷ እዝ ስር በቅድመ ዝግጅቱ 300 ከብቶች ለእርድ ቀርበዋል። በየቀኑ 7-10 ከብቶችና ሁለት ፍየሎች ይታረዳሉ። ሁሉም ጉባኤተኛ የሚመገበው የነጭ ጤፍ እንጀራ ነው። በየቀኑ ጠዋት ቁርስ አምባሻና የስጋ ጥብስ ሆኖ፤ ምሳና እራት የስጋ ቀይ ወጥ፤ የስጋ አልጫ ወጥና ጥብስ ይቀርባል። በተጨማሪም የታሸጉ ፍራፍሬዎችና አትከልት እንደልብ ነበር። መጠጥ ጠጅ፤ ጉሽ ጠላ፤ የጠራ ጠላ እንደ ውሃ ተንቆርቁሯል። እንዲሁም ውስኪና ቢራ በጅምላ ነበር።

የጉባኤው ተሳታፊዎች አብዛኛዎቹ የተገኙት ከነሚስቶቻቸው በመሆኑ፤ ምርጥ ፍራሽ፤ ብርድ ልብስና አንሶላ ከሱዳን ተገዝቶ እየተንፈላሰሱ ነበር። በተለይም የማ.... /ኮሚቴ አባላት። በዚህ መሰረት በቀን የሚወጣው ወጪ እንኳንስ ሽምቅ ተዋጊ ቀርቶ የአንድ ሃብታም ሃገር መንግሥትም ሲያወጣው የማይችል ነበር። በጣም ከፍተኛ የገንዘብ ወጭ ነበር። የተደረገውን ወጪ ቀን በጉባኤው እየዋልኩ ማታ ማታ ሂሳቡን እየሰራሁ ለረዳቴ ኃይለ-ሊባኖስ እሰጠዋለሁ። የእሱ የእጅ ጽሑፍ በጣም ጥሩ ስለሆነ በሶስት ኮፒ እያዘጋጀ ይጽፋል። በጥቅሉ የሂሳቡ ሰንጠረዥ 50 ገጽ በላይ ሲሆን ባጭሩ የየጭው ዝርዝር ለግንዛቤ ይህን ይመስላል፤

1. ለምግብና ለመጠጥ፤ ስጋን ጨምሮ ጠቅላላ ወጭ ብር 28,000,000

2. ለጉባኤው አዳራሽ ማሳሪያና ለተለያዩ እቃዎች መግዣ ብር 4,000,000

3. ለጄነሬተርና ሌሎች ቁሳቁሶች የወጣ ወጭ ብር 1,500,000

4. ለተለያዩ እቃዎች መግዣ የወጣ ወጭ ብር 2,332,000

ጠቅላላ የወጪ ድምር ብር 36,532,000

በአጠቃላይ ሰላሳ ስደት ሚሊዮን አምስት መቶ ሰላሳ ሁለት ሺህ ብር ወጭ በማድረግ የህ.... መሪዎች ተሞሽረው ወጡ። የጉባኤው ሁኔታ በዚሁ ላብቃና ወደአቋረጥኩት ቁም ነገር ልመለስ።

እነሱ በዚህ ሁኔታ ሲሙነሸነሹ በስደተኞች ጣብያ አስገድደው ያጎሩትን ሕዝብ የህ.... .... አመራር ምን አይነት የቀለብ ራሽን ያደረግላቸው እንደነበረ ቀደም ብየ እንደገለጽኩት ጥሬ በቆሎና ባቄላ ነበር። ለዚያውም የተፈቀደላቸው 10 ኪሎ ገደማ በወር ሲሆን፤ ቆልተው ብቻ እንዲበሉ በሚያስችል መቁንን ገድበውታል። በህክምና ረገድ በጣም የተጎዱ ነበሩ። በየቀኑ በበሽታ ምክንያት ሕዝብ እያለቀ ነበር። በሐምሌ 1978 አጥጋቢ ዝናብ መጣሉን የተረዱት ረሃብተኞች፤ ውስጥ ለውስጥ በመላላክ ያጠራቀሙትን በቆሎ፤ ባቄላና ጨው ይዘው የስደት ካንፑን አጥር ሰብረው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ደህና አቋም የነበረው ሌትና ቀን እየተጓዙ ወደ ትውልድ ቀበሌአቸው ደረሱ። የታመሙት ብቻ በስደት ጣቢያዎች ቀሩ። እነሱም ካገገሙ በኋላ አጥር እየገፈተሩ ወጡ። የተወሰኑት ወደ ካርቱም ሲያቀኑ ቀርዊዎቹ ደግሞ ወደ ወልቃይት ጠገዴ ተጓዙ። በሚገባ ካገገሙ በኋላ ወደየመንደራቸው ተመለሱ።

የማ.... መናኸሪያ (ቤዝ) ደጀና እንዲሆን ተወሰነ

.... እንደተመሰረተ ዋናዎቹ /ቤቶች ደጀና እንዲሆኑ ተወሰነ። በተሰጠን መመሪያ መሰረት ደጀና ገባን። በዚህ ቦታ የፕሮፓጋንዳና ህትመት ክፍል መለስ ዜናዊና አባይ ፀሃየ፤ ማህበራዊና የኢኮኖሚ /ቤት ገብሩ አስራት፤ የወታደራዊ /ቤት ስየ አብርሃ፤ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ሥዩም መስፍን የሚመሩት ቢሮ በየክፍሉ ተደራጀና ስራው ቀጠለ። ደጀና የተመረጠበት ዋና ምክንያት ከአንገርብ ተሻግሮ በቀጥታ ሱዳን ስለሚያስጋባና ከሱዳን የሚመጣውን እህልና ንብረት ካለምንም ችግር ወደ ደጀና ለማድረስ ስለማያስቸግር እንዲሁም ስልታዊ አቀማመጡ አመቺ ስለነበር ነው። ወያኔ .... .... በድርቅ ከተጎዳው ሕዝብ በተዘረፈ ንብረት ፍጹም ባለጸጋ ለመሆን በቃ።

ይህንኑ አትራፊ ተግባራቸውን በመቀጠል በረሃብና በበሽታ አጥንቱን ብቻ ተሸክሞ የሚንከላወሰውን መከራኛ የትግራይ ህብረተሰብ በየቴሌቪዥኑ ለዓለም ህብረተሰብ ጎስቋላ አካሉን እያሳዩ የሚሰጠውን እርዳታ ለተጎዳው ሕዝብ የሚደርስ የመሰላቸው ለጋሽና በስብአዊ ስሜት የተነሳሳው የዓለም ህብረተሰብ እኔ ይቅርብኝ እያለ ለግብረሰናይ ድርጅቶች ማለትም ለኦክስ ፋም፤ ሴቭ ችልድረን፤ ዩኤስ ኤይድ፤ ቀይ መስቀል፤ ኬር ኢንተርናሽናል፤ ወርልድ ቪዥን፤ ቀይ ጨረቃ፤ ዩኤን ሁማኒቴርያን ቲምና ለመሳሰሉት እርዳታቸውን እንዲያደርሱለት ሰጠ። በዓለም አቀፍ ደረጃ መሪነቱን የያዙት የመገናኛ ብዙሃን፤ ቢቢሲ፤ ሲኤንኤን፤ ሲቢኤስ ወዘተ የመሳሰሉት ሳይቀሩ የረሃቡን አስከፊ ደራጃ ወኪሎቻቸውን ቦታው ድረስ በመላክ ከፍተኛ ሽፋን ሰጡት። ዓለም የደረቀ ጉሮሮን ለማራስ፤ የታጠፈ አንጀትን ለመዘርጋት ሲረባረብ 72

ከአብራኩ ወጥተናል የሚሉት ስብሃት ነጋና መለስ ዜናዊ የሙት ተስካራቸውን ለመብላት የዘረፋ መዋቅራቸውን በከፍተኛ ደረጃ አዘጋጁ።

የወያኔ መሪዎች ለተራበው ሕዝብ ተብሎ የመጣውን እርዳታ ወደነሱ መጠቀሚያ ለወጡት። የእህል ማመላለስ እቅድ አወጡ። በዚህም መሰረት ከባድ የጭነት መኪናዎች ተመድበው ከአንገረብ ጀምሮ በየቦታው የአንድ ኪሎ ሜትር ረቀት ክፍተት በመተው በየነቁጡ ጣቢያ ከታች ድንጋይ በማንጠፍ እላዩ ላይ እንጨት እየተረበረበ 30,000 ኩንታል እህል በአንድ ቦታ እንዲከመር ተደረገ። በዚህ አይነት ከአንገረብ እስከ ተከዜ ድረስ 1,000 ክምር ተከማቸ። ይህም የስንዴ ዱቄት፤ ስኳር፤ ወተት፤ ቅባት፤ ብስኩት ሻይቅጠል ወዘተ የመሳሰሉትን ያካትታል። ከዝናብና ከፀሃይ ለመከላከል ከላይ እስከታች እየተሸፈነ በየዱሩ ትላልቅ ዛፎች ስር ተደበቀ። በሌላው ዘርፍ ደግሞ፤ አሁንም በተመሳሳይ ሁኔታ ከተከዜ እንዳባጉና ድረስ 700 ክምር ተደራጀ። በተለይ ሽራሮ፤ አዲሃገራይ፤ አዲአውአላ፤ አዲነብሪአድ ቀደም ሲል የኢ... አባላት የነበሩና ንብረታቸውን ተንጥቀው የተባረሩ ባለሃብቶች ያሰሯቸው ሰፋፊ መጋዘኖች ውስጥ አምስት ሚሊዮን ኩንታል ተጠራቀመ። ይህ ለወያኔ ትልቅ እፎይታ ሰጠው። በወያኔ አመራር እቅድ መሰረት የአምስት አመት የሰራዊት ምግብ እንዲሆን ተዘጋጀ። 05 ክፍሊ ኢኮኖሚ አከፋፋይነት ተዋጊው የሚፈልገውን የምግብ አቅርቦት ያገኝ ጀመር። በተጨማሪም የሰራዊቱ የቀን አበሉ ብር 14 እንዲሆን ተመደበለት።

ሌላው አስቃቂ ድራማ ደግሞ የተከሰተው ደጀና እንደገባን በሰር ጌልዶፍ የሚመራው ባንድ ኤይድ ተብሎ የሚጠራው የኪነት ቡድን ለስዩም መስፍን ደብዳቤ በመላክ በድርቅ ለተጎዱት የእርዳታ ገንዘብ ለመስጠት እንደሚፈልጉና በህ.... በኩል ተረክበው ለማከፋፈል እንዲቻል ግንኙነት የሚደረግበትን ሁኔታ የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰው። ሥዩም ደብዳቤውን ተረክቦ ለስብሃትና ለመለስ ነገራቸው። በመቀጠልም የት ሃገር እንደሚገናኙ ካዘጋጁ በኋላ፤ ስብሃት ነጋ አስቀድሞ ወደ ሱዳን ሄደ። በሁለተኛ ቀን ደግሞ መለስ ዜናዊ ወደ ሱዳን ተጓዘ። ሁለቱ ሱዳን ከተገናኙ በኋላ የኪነት ባንዱን ወደሚያገኙበት ሃገር ድረስ ሄዱ። ከባንድ ኤይድ $100,000,000 (አንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር) በሁለቱ ፍሪማ ተቀበሉ። ገንዘቡን ግን ለሁለት ተካፍለው በየግል የባንክ አካውንታቸው አስገቡት። የተረፈውን ለሬዲዮ መገናኛ ዘመናዊ የወታደራዊ ሬዲዮ ገዙበት። ከብዙ ቀናት በኋላ ከሱዳን እንደተመለሱ፤ ቀደም ብሎ ስብሃት ነጋ ወደ ደጀና ተመለሰ። በሶስተኛው ቀን መለስ ዜናዊ መጣ። ይህን ጉዳይ ላውቅ የቻልኩበትን ምክንያት ባጭሩ ልግለጥላችሁ። ገብሩ አስራት የኢኮኖሚ ጉዳይ ሃላፊ ስለሆነ ጉዳዩ ይመለከተዋል በሚል አባይ ፀሃየ በስህተት የደብዳቤውን ፎቶ ኮፒ አምጥቶ ሰጠው። ገብሩ አስራት ደግሞ እኔን አስጠርቶ ይኸው፤ ይህ ገንዘብ ከባንድ ኤይድ በድርቅ ለተጠቁት የትግራይ ሕዝብ ማቋቋሚያ የተሰጠ ነው። ስለሆነም ገንዘቡ ወደ ኢትዮጵያ ብር ተለውጦ ለሕዝቡ በእርዳታ እንድታከፋፍሉ አደራ እንላለን የሚል ነበር። ከአነበብኩት በኋላ አስቀመጥኩት። አባይ ተመልሶ ደብዳቤውን የሰጠው በስህተት መሆኑን አምኖ በአስቸኳይ እንዲመልስለት መልእክተኛ ለገብሩ ላከበት። ገብሩ አስራትም ከእኔ ተቀብሎ መለሰለት። ምስጢሩን ያወቅሁት በዚህ የተነሳ ነው።

የጉና የንግድ ድርጅት መቋቋም

ጉና ተብሎ የተሰየመው የንግድ ድርጅት የተቋቋመው ከዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የተገኘውን ንብረት ለመሸጥና ለማ.... ቀይ ሰራዊት ከአራት እስከ አምስት ዓመት የሚበቃ የስንቅ ክምችት ለማስቀመጥ እዲያስችል ነው። ድርጅቱ የተቋቋመው በመጋቢት 1978 ነበር። መስከረም 1978 ፖሊት ቢሮው ክሳድ ግመል በተባለ ቦታ ተሰብስቦ በድርቅ ለተጎዳው ሕዝብ የመጣውን እርዳታ በግልጽ ለመዝረፍ ውሳኔ የሰጠበት ወቅት ነበር። በውሳኔው መሰረት ከእርዳታ የሚሰበሰበውን ንብረት ሁሉ በሚከተለው ሁኔታ ሸነሸነው።

1. ለማ.... ማጠናከሪያ 55%

2. ለማ.... ቀይ ሰራዊት 45%

3. አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለሕዝብ እርዳታ 5%

 

ክፍፍል እንዲደረግ በሚል ድልድሉ ተወሰነ።

በዚህ አመዳደብ ለሕዝብ ብለው ያስቀመጡት 5% ሲሆን፤ በድልድሉ መሰረት ግን ለማንም አልተሰጠም። ቀደም ሲል እንደገለጽኩት በድርቅ የተመታው ሕዝብ ቅንጣት ታክል እንኳን አልደረሰውም። ለዚሁም የትግራይ ሕዝብ ምስክረንቱን ይሰጣል።

የህ.ወ.ሓ. ት. ታጋይ፤ ለሕዝብ እርዳታ ተብሎ፤ በሕዝብ ስም ለምነን ያገኘነውን፤ ሩብ ኪሎ እንኳን አልሰጠንም። ሕዝብ በበሽታ፤ በረሃብ እየሞተና እያለቀ በአይናችን እያየን እርዳታውን አለማድረጋችን ፍጹም ክህደት ነው።

ቀጥዬ ደግሞ የጉናን ንግድ እንቅስቃሴ ልዳስስ። ጉና ማለት የቦታ ስም ሆኖ በወልቃይት ፀገዴ የሚገኝ የሰራዊት ስንቅ በብዛት የተከማቸበት በተራሮችና በትልልቅ ዛፎች የተሸፈነ ስፍራ ነው። የጉና የንግድ ስም የተወሰደውም ከዚህ ነው።

የጉና የንግድ እንቅስቃሴ በጥቂት ፖሊት ቢሮ አባላት የሚታወቅ ሲሆን የዚህ ውስጥ ለውስጥ መሸጥ ውሳኔ ሰጭዎች ስብሃት፤ መለስ፤ ሥዩም፤ አባይና አርከበ ሆነው፤ በዚህ ሥራ የተሰማሩት 10 የጭነት መኪናዎችን በሹፌርነት የሚነዱት ግደይ ፎሮ፤ ሙሉ ወዲየኔታ፤ ጸጋይ ጠማለሁን፤ አክሊሉ አላ ብቻ ሲሆኑ፤ የየእለት ተግባሩን የሚያስተባብር ደግሞ አባዲ ዘሙ ነበር። እየተዘዋወሩ የተሸጠውን እህል፤ ልዩ ልዩ ንብረትና ገንዘብ የሚረከቡት ብርሃነ /ክርስቶስ፤ ቴዎድሮስ ሃጎስ፤ የማነ ጃማይካ፤ አዲስአለም ባለማ፤ ተወልደ አጋመ ሲሆኑ ሁሉም የህ.... /.... ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው። ከሱዳን ወደ ገዳሪፍ በማጓጓዙ የተመደቡት የጭነት መኪናዎች ቁጥራቸው 294 ማርቼዲስ ረጃጅም መኪናዎች ሲሆኑ ቀሪው 36 የጭነት መኪናዎች ደግሞ ለህ.... ሰራዊት በገዳሪፍ የተከማቸውን እየጫኑ ወደ ትግራይ ያግዛሉ። ቀደም ብለው በመለዋወጫ እጦት ቁመው የነበሩት 26 የጭነት መኪናዎች ሁሉም ተጠግነው ከፖርት ሱዳን ወደ ገዳሪፍ በመቀጠልም ወደ ትግራይ አመላላሽ ሆነው ሰርተዋል።

በጉናው የንግድ ድርጅት የተመደቡ ካድሬዎች ጸጋይ ጠማለሁ፤ ግደይ ፎሮ፤ አክሊሉ አላ፤ ሙሉ ወዲየኔታ /ሃይማኖት፤ መሃመድ ሙባረክ፤ ሮማን /ሥላሴ፤ ህረቲ ምህረተአብ፤ ፍስሃ አፈወርቂ፤ ወረደ ገሰሰ፤ ሳሙኤል /ማርያም፤ ነጋሽ ተክሉ፤ መብራት በየነ፤ ነጋሽ ኒኖ፤ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት አስራ አራት የወያኔ አባላት በሱዳን ታላላቅ ከተሞች ተሰማሩ። ለሁሉም ቶዮታ ላንድ ክሩዘር ከነሹፌሩ ተሰጣቸው። በቅድሚያ በእርዳታ የተላኩ የጭነት መኪናዎች ብዙዎቹ የተባበሩት መንግስታት “World Food Program (WEP)” የሚለው ከነአርማው የተሰጡ በመሆኑ አርማው እየጠፋ ተመሳሳይ ቀለም ተቀቡ። በመቀጠልም ሁሉም የጭነት መኪናዎች የሱዳን የሰሌዳ ቁጥር ተለጠፈባቸው። በመቀጠል ያደረጉት በሱዳን ከተሞች ከፍተኛ የመደለል ችሎታ ያላቸውን ሱዳናውያን በመቅጠር ከነጋዴዎች ጋር እያገናኙ የእርዳታውን ንብረት መሸጥ ነበር።

ከሽያጩ በተጨማሪ ወያኔ ... ት. ም ለሰራዊቱ የሚያስፈልገውን ስንቅ፤ መድሃኒት፤ የህክምና መሳሪያ እየተጫነ ገዳሪፍ ከተራገፈ በኋላ ወደ ትግራይ ያስገባሉ። ከዚህ የዘረፋ ተግባር ዋናዎቹ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ እንደሚባለው፤ በዚህ ሥራ የተሰማሩት ካድሬዎችም በበኩላቸው በድብቅ ሁለት ሶስት ጭነት መኪና ለግላቸው በመሸጥ፤ አፍ ለማዘጊያ ደግሞ አንድ ጭነት ለሹፌሩ በግልና በምስጢር ባንክ አካውንት ብዙ ገንዘብ አስቀምጠዋል። ከላይ የተጠቀሱት 14 የወያኔ ካድሬዎች በየሁለት ሳምንቱ የተገኘውን ገንዝብና ቼክ ለአባዲ ዘሙና ለብርሃነ ገብረክርስቶስ ያስረክባሉ። ቀሪዎቹ ደግሞ ለስዩም መስፍን ይሰጣሉ። በመጨረሻም ዝርዝር ሂሳቡ ተጠናቅቆ በየሶስት ወሩ ለስብሃት ነጋ ደጀና እያመጡ ያስረክባሉ። አንዳንዶቹ እየተደናበሩ ወደ እኔ እየመጡ ይሰጡኝ ነበር። በቀጥታ ለገብሩ እንዲሰጡት ስንነግራቸው፤ ገብሩ አስራት በፋንታው ይህ እኔን አይመለከተኝም፤ ለመለስ ወይም ለስብሃት ነጋ ስጡአቸው ብሎ የመልሳቸዋል። በዚህ ሂደት የጉና የንግድ ተግባር ቀጠለ። በመካከሉ 1978 ነሐሴ ወር በፖርት ሱዳን የተከማቸው ገና በበቂ ሁኔታ ባለመነሳቱ የሱዳን መንግሥት ወደቡ ጠበበ አስንሱልኝ የሚል ቅሬታ ማሰማት ጀመረ።

በዚህ ጊዜ ብርሃነ /ክርስቶስና አባዲ ዘሙ ካርቱም ውስጥ የሚኖሩ ሱዳናውያን በዓለም አቀፍ ደራጃ የድለላ እውቅና ያላቸውን አራት ደላላዎችን በማነጋገር በፖርት ሱዳን ያለውን የእህል ክምር፤ የምግብ ቅባት፤ ስኳር፤ ሻይቅጠል፤ ብስኩት፤ የህጻናት አልሚ ምግብ ወዘተ ዝርዝር ፎቶ ኮፒ በመስጠት በአረብ ሃገሮች እንዲሸጥ መርከብ ተኮናትረው በግብጽ፤ በሳውዲ አረቢያ፤ በኩየትና በዩናትድ አረብ ኤመሬትስ ከሚገኙ ካምፓኒዎች ጋር ተስማምተው በትልልቅ መርከቦች እየተጫነ ብርሃነ /ክርስቶስ፤ የማነ ኪዳነ፤ ቴዎድሮስ ሃጎስ፤ አብረው በመጓዝ አዲስአለም ባሌማ በሱዳን ፖርት ቋሚ ሆኖ በመመደብ የሶስቱን ስራ ደርቦ በመስራት በኪራይ መርከብ እየተጫነ ወደ አረብ ሃገሮች ተሸጋገረ። ቀሪው ለሱዳን ነጋዴዎች ተሸጠ። ሽያጩ በሙሉ በአሜሪካ ዶላር ሲሆን በሽያጩ በቢሊዮን የሚቆጠር ገቢ ተገኘ። ገንዘቡ ግን አውሮፓና አሜሪካ እንዲቀመጥ ተደረገ። የጉና የንግድ ዘረፋ 1979 ተጠናቀቀ። በዚህ ገንዘብ እነ ስብሃት፤ መለስ የተለያዩ ወታደራዊ መሳሪያ፤ ጥይት፤ ቦምብ፤ ሬዲዮ፤ መገናኛ ገዝተውበታል። የህ.... ሰራዊትንም በዘመናዊ መሳሪያ አስታጠቁት።

በዘረፋው የገባውን የሚያውቁት ስብሃትና መለስ ሲሆኑ፤ ገንዘቡን የተከፋፈሉት ደግሞ ስብሃት ነጋ፤ መለስ ዜናዊ፤ ሥዩም መስፍን፤ አርከበ እቁባይ፤ ብርሃነ ገብረክርስቶስ፤ አባዲ ዘሙ፤ የማነ ኪዳነ በዋናነት የሚጠሩ ሲሆኑ፤ 150 እስከ 200 ሚሊዮን ዶላር ማግኘታቸው በወቅቱ ይነገር ነበር። አነስተኛ ገንዘብ አግኝተዋል የተባለላቸው ቴዎድሮስ ሃጎስ፤ አዲስአለም baሊማና ተወልደ አጋመ እስከ አምስት ሚሊዮን ዶላር የማግኘታቸው ወሬ በስፋት ተሰራጭቶ ነበር። ቀሪዎቹ 14 ታጋዮች በየደረጃቸው 5 እስከ 10 ሺህ ዶላር ጉርሻ እንደተሰጣቸው ራሳቸው ሲነግሩን ነበር። ይህ ጉርሻ እነሱ በብኩላቸው በድብቅ እየሸጡ ከዘረፉት ገንዝብ ተጨማሪ ነው።

እንግዲህ በድርቅ ለተጠቃው፤ በረሃብና በበሽታ የተነሳ እየሞቱ ያሉትን እናቶች፤ ህፃናት ልጆች የእናታቸውን እጅ ተንተርሰው በየመንገዱ ወድቀው ሲቀሩ፤ የሰው ልጅ ሬሳ ወድቆ የአውሬ መጫወቻ ሆኖ፤ አጥንትና ቆዳው የተጣበቀ ህፃን፤ ሽማግሌ፤ እናት፤ ካሜራ አንሺ ሲመጣ ብቻ መንገድ መሪ ሆኖ ለዓለም ሕዝብና መንግስታት እያሳዩ በእነርሱ ስም የመጣውን እርዳታ መዝረፍና ማዘረፍ፤ ይህንንም በራስና በቤተሰብ ስም በተለያዩ ሃገራት በባንክ ማስቀመጥና ለግል ጥቅም ማዋል ከፍተኛ የወንጀል ወንጀል ነው።

ችግረኛውን ሕዝብ ከቦታው አፈናቅለው በሱዳን ካምፕ አስፍረው እንደ ኤክስፓ ዘርግተው ከለመኑበት በኋላ በስሙ የመጣውን እርዳታ መዝረፍ በዓለም ታሪክም ታይቶ የሚታወቅ አይመስለኝም። ይህ የሚያሳየው ነገር ቢኖር የወያኔ መሪዎች ፍጹም አረመኔ፤ ጨካኝ ሽፍቶች መሆናቸውን ያስመሰክራል። ከባንድ ኤይድ የተሰጠውን $100 ሚሊዮን ዶላር ጨምሮ በዓለም ህብረተሰብ በተባበሩት መንግሥታትና ግብረሰናይ ደጅቶች የተለገሰው እርዳታ በዋናነት መለስ ዜናዊና ስብሃት ነጋ ዘርፈው አዘርፈውታል። በሕዝቡ ላይ ጭካኔ የተሞላበት አሳፋሪ ተግባር ፈጽመዋል። በጽሑፌ ላይ ሳልጠቅስ ያለፍኩት፤ ነዳጅን በሚመለከት ወያኔ የሚበቃውን ካስቀመጠ በኋላ ቀሪውን ለሱዳን ነጋዴዎች ሽጠውታል።

ለማ.... ቀይ ሰራዊት ተብሎ የተከማቸው ምግብ በዝናብ መበላሸት

1979 አምላክ በህዝቡ ላይ ይቅርታ ያወረደበት ዘመን ነበር ማለት ይቻላል። ከግንቦት 1979 ጀምሮ ዝናብ በጣም አጥጋቢ በሆነ መልኩ ዘነበ። መሬት ጨሌ በጨሌ ሆነ፤ ዛፎች ለመለሙ፤ ሳሩ በሰው ቁመት ልክ ደረሰ፤ ከብቶች፤ ፍየሎች፤ እንሰሳት በሙሉ ጠገቡ፤ ወፈሩ። በግንቦት በጣለው ዝናብ የጓሮ አትክለት፤ ጎመን ደረሰ። አዝመራውም በአማረ መልኩ በቅሎ ገበሬውን የደረስኩልህ ተስፋ ሰጠው። እሸቱን የሚበላበት ጊዜ ደረሰ። ጥቅምትና ታህሳስ 1980 ጥሩ ምርት ተገኘ።

በተቀራኒው፤ 1979 ዝናብ ክፉኛ ያማረረው የወያኔ .... መሪዎችን ነበር። በየቦታው በፕላስቲክ ተሸፍኖ ተከምሮ የነበረው እህል በዝናቡ ሃይለኛነት የተነሳና በቀቀስ ወደ እህሉ በመግባቱ ከአንገረብ እስከ ተከዜ የተከማቸው 1,000 ክምር (30,000 ኩንታል) ያላነሰ የያዘው ክምችት ተበላሸ። ግማቱ ሰው ሊያስቀርብ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደረሰ። በዚህ ወቅት ስብሃት ነጋ፤ መለስ ዜናዊ፤ አባይ ፀሃየና አርከበ እቁባይ ተሰብስበው ክምሩን እየተዘዋወሩ ጥናት በማድረግ የተበላሸውን የሚያስወግድ ኮሚሽን አቋቁሙ። እነሱም፤

1. ህቡር /ኪዳን የቤዙ ዋና አስተዳዳሪ

2. መድህን ወታደራዊ /ቤት

3. /መድህን አርአያ የፊናንስ ሃላፊ

4. በያን ፍትዊ የስንቅና ንብረት ሃላፊ

5. ያይኔ የበያን ፍትዊ ተባባሪ የነበረ

6. ልጅአለም ሃኪም

7. መዝገብ ወታደራዊ የካርታ ጥናት ሃላፊ

ሲሆኑ፤ በሕቡር /ኪዳን መሪነት ለሁላችንም የተንቀሳቀስ ትእዛዝ ደረሰን። በዚሁ መሰረት ስራውን ከአንገረብ ጀምረን ተከዜ ለምድረስ አንድ ወር ሙሉ ወሰደብን። ባካሄድነው ምርመራም 215 ክምሮች ትል ፈጥረው በዝናብ ተጨማልቀው ተገኙ። የተበላሹት በአስቸኳይ ወንዝ ውስጥ እንዲጣሉ ተወሰነ።  

ሌሎቹ 75 ክምሮች መጠነኛ መበላሸት ደርሶባቸው ነበር። እነዚህም በአስቸኳይ ካልተለዩ በአጭር ጊዜ ከጥቅም ውጭ እንደሚሆኑ በግምገማችን ላይ ሃሳብ ቀረበ። በዚህ ስብሰባ መጀመሪያ የተናገረው መድህን ነበር። ሲናገር እያለቀሰና እንባውን በመሃረቡ እየጠረገእኛ የህ.... አባላት በድርቅ ለተጠቃው የትግራይ ህብረተሰብ የመጣውን እርዳታ ሕዝባችን በአይናችን እያየን፤ እናቶች ከሕፃናት ልጆቻቸው ተለይተው ሞተው፤ ሕፃናቱ የሟች እናቶቻቸውን ጡት ነክሰው እንሱም ሞተው፤ አዋቂዎች አጥንታቸው ወጥቶ ቆዳቸው በገላቸው ላይ ተጣብቆ የሚረዳቸው አጥተው አለቁ። ወደ ሱዳን ያጓጓዝናቸውንም 10 ኪሎ ጥሬ በቆሎና ባቄላ እያደልን የራሳችንን ሕዝብ ለሞት አሳልፈን ሰጠን። በሕዝቡ ላይ ግፍ በመፈጸም መላውን የትግራይ ዜጋ ለስቃይ ዳረግን። ይህንን ለማ.... ቀይ ሰራዊት ብለን ያከማቸነውን ክምር ቀደም ብለን ለተጠቃው ወገናችን ብነሰጠው ኖሮ ከሞት ተርፎ ምስጋናም፤ ምርቃትም እናገኝበት ነበር። እዚህ ደረጃ ያደረሰንን ሕዝብ ከዳነውብሎ ንግግሩን በለቅሶ አጠናቀቀ። ቀጥሎ የመድህንን ሃሳብ በመደገፍ መዝገቡ የበኩሉን ተናገረ። ብዙ ከተናገረ በኋላ ተጨማሪ አለኝ ብዬ እኔም የመዝገበን እና የመድህንን ሃሳብ በመደገፍ የማጠናከሪያ ሃሳቤን ሰጠሁ። መድህን እንደገና በመቀጠል የህ.... መሪዎችም የደረሰውን የሕዝብ መቅሰፍት አይተውታል። ስለዚህ እኛ ሁላችንም ሕዝብ የከዳን፤ በችግሩ ጊዜ አናውቅህም ብለን ጀርባችንን ያዞርንበት ከሃዲዎች ነን ብሎ አቆመ። የዚህን ስብሰባ ሪፖርት ህቡር /ኪዳን ለስብሃትና መለስ አቀረበላቸው። ሳይውል ሳያድር መድህን፤ መዝገበ፤ ገብረመድህን፤ በያን እና ያይኔ የኮሚሽኑ ሥራችንን እንድናቆም ተወሰነ። ለአራታችንም ህቡር በብጣሽ ወረቀት አስታወቀን። በእኛ ምትክ ሌሎች ተተኩ። ስንት እንደተበላሸ ባናውቅም በየበረሃው የተከመረው እህል ግን በብዛት የተበላሸ መሆኑን አውቀናል።

በመጀመሪያው የድርቁ ጊዜ ወደ ሱዳን አንሄድም ብለው ወደ ጎንደር፤ ወሎ፤ አዲስ አበባ፤ ባህርዳርና ወደቀሩት የሃገራችን ክፍሎች የሄዱት ወደ ግማሽ ሚሊዮን ይሆናሉ። እነዚህ በደረሱበት ቦታ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ተቀብለው አስተናግደውታል። ልብስ ለሌለው የራሱን አውልቆ ገመናውን ሸፍኖለታል፤ የተራበውን አብልቷል፤ መጠለያ ያጣውን በራሱ ቤት እንዲኖር አድርጓል። ያልቻለውን ደግሞ ከእርዳታ አስተባባሪዎች አገናኝቶታል። እርዳታውን እየተቀበለና ሙሉ ህክምና እያገኘ በሃገሩ ምድር ችግሩን እንዲወጣ አደርጎታል። ዝናብ ሲዘንብ ተመልሰው ወደ ትግራይ ቀዬአቸው ተመልሰዋል። ባረፉበት ትውልድ ቀበሌአቸው ሁሉ ኢትዮጵያዊው ወገናቸውና ደማቸው ያደረገላቸውን መጠነ ሰፊ እርዳታ በደስታና ትዝታ በሞላበት አንደበት አውግተውታል። ይህ ወሬ ሕዝቡ ዘንድ ስለደረሰ ወንጀለኛው የወያኔ አመራር ተበሳጭቶ ወሬው ደግሞ እንዳይነሳ ለሕዝብ ግንኙነት አመራር አስተላልፎ ነበር። ነገር ግን ሰሚ አላገኘም። እውነታው አሁንም ቋሚ ነው።

የደጀና ኑሮ

ቀደም ብዬ እንደ ጠቀስኩት የህ.... /.... ፖሊት ቢሮ ደጀና እንደተሰበሰቡ አይተናል። በዚህ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በየሁለት ወሩ 10,000 በላይ እያሰለጠነ የሚያወጣ ትምህርት ቤት፤ የወያኔ ትልቁ ሆስፒታል፤ የትራንስፖርት /ቤት፤ ማህበረ ኢኮኖሚ፤ ስንቅና ንብረት አከፋፋይ ከደጀና እስከ ክሳድ ግመል እንደዚሁም እስከ ጸገዴ ቆላ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ታጋይ ይገኛል። እድሜ ለድርቅ ኑሮው የተንበሸበሸ ሆነ። እየበላና እየጠገበ መኖር ጀመረ። ችግር የሚባል ነገር ተረሳ። ሴት ለሚያስፈልገው ሴት አለ። ሴቷም የመረጠችውን እንደዚሁ ታገኝ ጀመር። በየአካባቢውና በየክፍሉ ያሉ ታጋዮች በየሁለት ሳምንት ጠላ እየተጠመቀ ይጠጣል። ማታ ማታ ጭፈራና ዳንስ ሆነ።

የአመራሩ የኑሮ ለውጥ

ቀደም ሲል ደጀና ውስጥ ሆኖ ልዩ ስሙ ክሳድ ግመል የሚባለው ቦታ የድርጅቱ /ቤት ነበር። ነገር ግን አንድ ጊዜ ደርግ በአይሮፕላን ስለደበደበውና ገላጣ ስለሆነ ወደ ደጀና ልዩ ስሟ ሸቋዳ እንዲዘዋወር ተደረገ። የአሁኑ ቦታ ትልልቅ ዋሻዎች አሉት። ለአውሮፕላን ጥቃት የተጋለጠ አይደለም። አሁን /ቤቱ በሰው ሃይልም በሚገባ ተደራጀ። ፕሮፓጋንዳ ቢሮ መለስ ዜናዊ፤ ስብሃት ነጋ፤ አባይ ፀሃየና አለምሰገድ /አምላክ፤ ወታደራዊ ቢሮ፤ ስየ አብርሃና አርከበ እቁባይ ማህበራዊና ኢኮኖሚ፤ ገብሩ አስራት፤ ሕዝብ ግንኙነት ቢሮ፤ ተወልደ ሃለዋ፤ ወያኔ /ቤት ከፕሮፓጋንዳ ስር ሆኖ ክንፈ /መድህን እና ብስራት አማረ ሆነው ተመድበዋል። በተለይ ስብሃት ነጋና አርከበ እቁባይ፤ ኤልሳ አስፍሃ የምትባል ኤርትራዊት የጻድቃን /ተንሳይ ሚስት ባለችበት ተነጋግረው ፖሊት ቢሮው ልዩ እንክብካቤ እንደሚያስፈልገው ታምኖበታል። በየወሩ ብር 50,000 በገንዘብ ሃላፊው በገ/መድህን አማካኝነት እየተፈቀደ ለኤልሳ አስፍሃ እንዲሰጥ ተወሰነ። የማ/ኢኮኖሚ ሃላፊ ገብሩ አስራት ይህን አዲስ እቅድ አያውቅም ነበር። ትእዛዙ እንደደረሰኝ ጉዳዩን አለቃየ በመሆኑ አሳወቅሁት። እርሱም የሚፈልጉትን አደርግላቸው ብሎኝ በየወሩ ብር 50,000 ለኤልሳ አስፍሃ ወጭ እያደረግሁ እሰጣት ነበር።

በመካከሉ ስብሃት ነጋ በየቦታው እየዞረ ለፖሊት ቢሮ አባላት ልዩ እንክብካቤ እንዲደረግ ስለተወሰነ የሚደረግላችሁን ተቀበሉ አላቸው። ተወልደ /ማርያም፤ ስየ አብርሃና ገብሩ አስራት ግን የዚህን አይነት ልዩ ቅምጥል አያስፈልገንም አንቀበልም አሉት። ሌሎቹ በወሳኔው መሰረት ልዩ እንክብካቤውና ልዩ ኑሮ ከነሚስቶቻቸው በኤልሳ መሪነት ቀጠለ። ከዚያም የነጭ ጤፍ እንጀራ፤ ሙክት፤ ቅቤ፤ ማርና ልዩ ልዩ የአትክልትና ፍራፍሬ፤ ከሱዳን ውስኪ፤ ቢራ፤ ኮኛክ፤ ነጭ አረቄ በኮንርቶባንድ ከየቦታው እየተገዛ መቅረብ ቀጠለ። መኝታ አልጋዎች ሳይቀሩ ፍራሽ፤ ብርድ ልብስ፤ አንሶላ ሳይቀር ተደምሮ አራት ሴቶች ከሱዳን ተመርጠው ለነ መለስ ምግብ አዘጋጅ ተቀጠሩ። ብዚህ ብቻ አልተወሰነም። ሁሉም የፖሊት ቢሮ አባላት በየወሩ ብር 1,000 የኪስ ገንዘብ እንዲከፈላቸው በነስብሃት የተደነገገ፣ ሕግ ወጣ። የታዘዘውን የኪስ ገንዘብ የሚቀበሉት መለስ ዜናዊ፤ ስብሃት ነጋ፤ አባይ ፀሃየ፤ አውአሎም ወልዱ፤ አረጋሽ አዳነ፤ አርከበ እቁባይ፤ ስዩም መስፍን እና ጻድቃን /ተንሳይ ሲሆኑ ገብሩ አስራት፤ ስየ አብርሃና ተወልደ ወማርያም አንፈልግም፤ አንቀበለም ብለው ተቃወሙ። ሰሚ ግን አላገኙም።

ለማጠቃለል ያህል፤ በድርቅ ለተጠቃው ለትግርራይ ሕዝብ የመጣው እርዳታ የህ.... መሪዎች እንዴት እንደዘረፉትና ዘርፈው ለግል ጥቅማቸው እንዳዋሉት በመጠኑም ቢሆን ያየሁትን ሁሉ ምስክርነቴን አስፍሬአለሁ። የህ.... አመራር ጠቅላላ የትግራይ ህብረተሰብ በድርቅ እንደቅጠል በየቦታው እየረገፈ፤ ሕፃን፤ እናት፤ ሽማግሌ፤ አባት ወዘተ በየመንገድ ጥላ ስር ቀባሪ አጥተው በጅብ አካላታቸው ተበጣጥሶ መበላቱን በአይናቸው እየተመለከቱ፤ ለነብስ አድን የመጣውን እጅግ መጠነ ሰፊ እርዳታ ጉና የሚል ንግድ ድርጅት አቋቁመው በሱዳን አሸጋጋሪነት ለአረብ ሃገሮች እርዳታውን መሸጣቸውን እና ከባንድ ኤይድ የተገኘውን $100 ሚሊዮን ዶላርም ጨምረው በአውሮፓና በአሜሪካ ባንኮች በየራሳቸው ባንክ አካውንት ማዘዋወራቸው፤ ይህ ብቻ አይደለም በብዛትም መሳሪያ ተገዝቶበታልም ከቻይና ዘመናዊ ወታድራዊ ሬድዮ መገናኛ ከሊብያ ሶሪያ ኢራቅ ፍሊስጤም ኢራን ሱዳን ... ከባድ መሳሪያ ነብስ ወከፍ መሳሪያ ጥይት ቦንብ ፈንጅ ... በብዛት በህ... ተገዝተው በትልልቅ ካሜኖች ተጭነው ትግራይ ውስጥ ገብተዋል በተለያዩ ሃገራትም ምርጥ ቤቶች አስገዝተው ኪራይ ገቢ ቋሚ ገንዘብ መሰብሰባቸውን፤ ለቀይ ሰራዊት የአምስት ዓመት ቀለብ የቋጠሩበት መሆኑን ይህ ሁሉ ተግባራቸው የሚያረጋግጠው የህ.... /.... መሪዎች ጨካኞችና ፋሽሽስት መሆናቸውን ነው።

ከዚህ በተጨማሪ፤ የህ.... /.... መሪዎች በመለስ ዜናዊና በስብሃት ነጋ መሃንዲስነት የትግራይ ሕዝብ በረሃብና በውሃ እጦት ብሎም በተለያዩ በሽታዎች እየረገፈ፤ በሕዝብ ስም የመጣውን እርዳታ የባንድ ኤይድ $100 ሚሊዮን ዶላር ጨምሮ የተለያዩ ወታደራዊ መሳሪያዎች ከመካከለኛው ምስራቅ ገዝተውበታል። ልዩ አዲስና ዘመናዊ በርቀት የሚያገናኝ ወታደራዊ ሬዲዮ መገናኛ ተገዝቶበታል። ለሰባት ዙር የካድሬ ትምህርት ስልጠና ማስፈጸሚያ ተጠቅመውበታል። በዚሁ ብቻም አላበቁም። የማርክስ ሌኒናዊ ሊግ ትግራይ ፓርቲ ምስረታ በየትም አለም ተወዳዳሪ የማይገኝለት በከፍተኛ የገንዘብ ወጪ በወርኢ አዳራሽ አሰርተው ጉባኤ በማካሄድ እነመለስ ዜናዊ በቀይ ጨርቅ የተጠቀለለ አርማና ጉንጉን አበባ ተሸልመውበታል። ይህ ሁሉ፤ ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንደሚባለው፤ የጥፋት ድርጊት በዝርዝርና በነቂስ ሕዝብ እንዲያውቀው ካሁን ቀደም አድርጌአለሁ። አሁንም ይኸው የትግራይ ህብረተሰብ በድርቅ በአሰቃቂ ሁኔታ በየቦታው እየወደቀ፤ በህዝብ ስም የመጣውን መጠነ ሰፊ እርዳታ በነመለስ ዜናዊ እጅ ውስጥ ገብቶ ለግል ጥቅማቸው ዋለ። አራት ሚሊዮን ሕዝብ በእነዚህ ይሉኝታ ቢሶችና ሆድ አደሮች ንብረቱን ተነጥቆ ለሰቆቃ፤ ለቸነፈርና ለአስከፊ ሞት ተዳረገ።የህ... መሪዎች በህዝብ ስም የተቸረው እርዳታ ለግል ጥቅማቸው አዋሉት

የወያኔ መሪዎች 1977 እስከ 1981 የፈጸሙትን መጠነ ሰፊ ወንጀልና ክህደት በትክክል አስቀምጫለሁ። ከዚህ በተረፈ ማንም የትግራይ ተወላጅ የተፈጸመውን ግፍ አይቶና አውቆ በእውን የተወለደበት አካባቢ ግፍና ሰቆቃ ይሰማኛል፤ ይቆረቁረኛል የሚል ከሆነ፤ በአሁኑ ወቅት ከትግራይ አልፈው በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የሚፈጽሙትን ሰቆቃ ማየት ይበቃል። በተለይ ዛሬ ደግሞ እነመለስ ዜናዊ በትግራይ ላይ የፈጸሙትን ደባ ሸፍነው ለትግራይ ሕዝብ እንደቆሙ በማስመሰል በስሙ አሁንም ሲነግዱበት ይታያሉ። በመሆኑም በየውጭ ሃገር ካድሬና ደጋፊ የሆንክ ሁሉ ሁኔታውን ተገንዝበህ  ከቀረው ኢትዮጵያዊ ወገንህ ጎን እንደምትሰለፍ ጥርጥር የለኝም። አገር ቤት የሚገኘውና ታፍኖ የተያዘው የትግራይ ሕዝብ በቆራጥነት ትግሉን ከሃገሪቱ ሕዝብ ጋር እንዲያቀናጅ ጥሪዬን አቀርባለሁ።

ነባሩ ታጋይ በማ.... ግምገማ ተጠቃ

ነባሩ ታጋይ ወያኔ ከተፈጠረበት ጀምሮ አብሮ የመጣ ለህ.... በብዙ የተለያየ መንገድ አገልግሎት የሰጠ ነው። በህ.... አመራር ከመጀመሪያ ጊዜ አንስቶ የተፈጸሙትን ፋሽስታዊ ግፎች ከሀ እስከ የሚያውቅም ነው። 1977 ለሕዝብ እርዳታ የመጣውን የድርጅቱ መሪዎች ሲዘርፉት፤ የሰው ልጅ በየሄደበት በሚያልቅበት ወቅት አምርሮ ያለቀሰ ነው።

ከዚህ በመንሳት 1980 ሕዳር ወር በነባሩ ታጋይ ላይ ግምገማ እንዲደረግ ፖሊት ቢሮው ወሰነ። በዚህ መሰረት፤

1. የህ.... መእከላዊ ኮሚቴ

2. የሕዝብ ግንኙነት ሃላዊዎች

3. የየክፍሉ ሃላፊዎች

እንዲገመገሙ ተወሰነ። ግምገማው ደግሞ በስብሰባ ሳይሆን በተናጠል ነበር። የነሱ ታማኝ ካድሪዎች የሆኑት በዚህ ግምገማ አልተነኩም። የሚገመገመው የመለስና የስብሃት ነጋ ጠላቶች ናቸው ተብለው በጥቁር መዝገብ የተያዙት ብቻ ነበሩ።

ገምጋሚዎቹ፤ ስብሃት ነጋ፤ መለስ ዜንዊ፤ አባይ ፀሃየና አርከበ እቁባይ ነበሩ። ልዩ ልዩ የነብስ ወከፍ ሪፖርት አጠገባቸው ባማድረግ፣ ቢተው በላይ፤ ዘርአይ አስገዶም፤ ክንፈ ገብረመድህን፤ አረጋሽ አዳነ፤ ሙሉጌታ አለምሰገድ ወዘተ ነበሩ።

ግምገማውን የጀመሩት በህ.... የግንባሩ አባላት ሆኖ፤ ተክሉ ሃዋዝ፤ ክብሮም /ማርያም፤ ስአረ ገብረጻዲቅ፤ /ሥላሴ መስፍን ወዘተ ወደ አራቱ ፖሊት ቢሮ ገምጋሚዎች በየግል በተለያዩ ቀናት ቀርበው ተዋርደውና ተሰድበው ከሃላፊነታቸው ታገዱ። የሕዝብ ግንኙነትና የየክፍሉ አላፊዎችም በተራ በተራ እየተጠሩ ግምገማው መስከረም 1981 አለቀ። ብዙ ታጋዮች ጠፉ፤ ብዙዎቹም ወደ ሱዳን ገቡ። የተወሰኑትም ተገድለዋል። ከተገምጋሚዎቹ አንዱ እኔ /መድህን አርአያ ነበርኩ። ስድብና ውርደቴን ተቀብዬ ወደ ሱዳን ሸሸሁ። ከዛም ወደ ሃገሬ ኢትዮጵያ ገባሁ።

በውጭ ሃገር የሚኖሩ የህ.... አባላትም ተመሳሳይ ግምገማ በብርሃነ ገብረክርስቶስና በአዲስአለም ባሌማ ተካሂዶባቸው የተባረሩ ነባር ታጋዮችም አሉ። በሰራዊቱም በኩል ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ የነበሩ በጻድቃን /ተንሳይና ሳሞራ የኑስ እየተገመገሙ የታሰሩም ጠፍተው ያመለጡም ብዙ ናቸው።…….. በማለት ሰፊ ትንተና አድርጎ ያቀረበው በ1977 ዓ.ም ትግራይ ውስጥ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከውጭ አገር ዕርዳታ የተገኘውን ገንዘብ ወያኔ መሪዎች እንዴት ባለ የገንዘብ ንቅዘት ገብተው ለራሳቸው እንደተጠቀሙበት ወዳጄ ገብረመድህን አርአያ እንደፈለግከው በመጽሐፍትህ ውስጥ አስገባቸው ብሎ ከላከለኝ በርካታ ሰነዶች መሃል አንዱ ይሔው የወያኔ ገመና ማሕደር እንዲህ ይመስላል። በሚቀጥለው ሌላ ታሪክ እስካስንብባችሁ ድረስ ፤እኛ ሳናርፍ ሓላፊነታችን እየጠወጣን ነው: እናንተ ደግሞ ይህ ታሪካዊ ሰነድ “ሼር” በማድረግ ሕዝቡን አስተምሩበት።

አመሰግናለሁ

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay