Thursday, January 31, 2019

ኢትዮጵያን ያያችሁ “ና ወዲህ” በሉኝ! አሁን የት ናት? ዳግማዊ ጉዱ ካሣ - Ethio Semay


ኢትዮጵያን ያያችሁ “ና ወዲህ” በሉኝ! አሁን የት ናት?
ዳግማዊ ጉዱ ካሣ

በሁሉም ቦታ ውጥረት ነግሦኣል፡፡ ሰላም ያለችው በአንደበትና በመንግሥት ሚዲያዎች ብቻ እንጂ በተግባር የለችም፡፡ ሀገር በከፍተኛ ፍጥነት እየፈራረሰች ባለችበት በአሁኑ ሁኔታ ሕዝቡም ፀጥ ረጭ ብሎ የመርከቢቱን መስመጥ በትግስት እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡  በትብታብ የተያዝን ይመስል (ተይዘንም ሊሆን ይችላል) ሁላችንም ፈዘንና ደንግዘን እንገኛለን፡፡

ተመልከቱ - ስግብግብ ነጋዴዎች በጀሶና በሴጋቱራ እንጀራ ሆዳችንን እየቆዘሩ ላልታወቁ በሽታዎችም እየዳረጉን ሆስፒታሎችንና መቃብር ሥፍራዎችን እያጨናነቅን እንገኛለን፡፡ የግል ሀኪም ቤቶች ወላዶችን እያስፈራሩ በኦፕሬሽን እንዲወልዱ በማድረግ ልጁንም እነሱ የሰጡ ይመስል ሃያና ሠላሣ ሽህ ብር በደቂቃዎች ይዘርፋሉ፡፡ የህክምናው ዘረፋና ማምታታት ወደር አይገኝለትም፡፡ በአንዳንዶች ለካርድ የሚከፈለው ብቻ በሽዎች ነው፡፡ ለአንድ ቀን አዳር የሚያስከፍሉት ከሼራተን የአንድ ቀን መኝታ ይበልጣል፤ ግብር የሚከፍሉት ግን በሆቴል ሣይሆን በህክምና ነው፡፡ ገንዘብን የሚያመልክ ሀገርም ወገንም ማተብም አመዛዛኝ ኅሊናም  የለውም፡፡ ባጭሩ ሥሪቱ ከጅብና ከዓሣማ እንጂ እንደሰው ሰው ከተሠራበት ቀመር አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰው በቁጥር እየበዛ ሀገር የለዬላቸው የሰው ዐውሬዎች መፈንጫ እየሆነች ነው፡፡ በዚያ ላይ በየክልሉ የሚታዬው የወያኔ የዘረኝነት ፍል አድጎና ጎምርቶ መውጫ መግቢያ እያሳጣን ነው፡፡

 በበርበሬ ስም ቀይ ሸክላና ሴጋቱራ ተደባልቆ ይፈጭና ይሸጣል፡፡ በቅቤና በዘይት ስም የማይታወቁ ባዕድ ነገሮች እየተደበላለቁ ይሸጣሉ፤ በነሱም እያለቅን ነን፡፡ በሚበላና በሚጠጣ፣ በመድኃኒት ስም በሚዋጥ - በሚቀባና በሚታሽ ባዕድ ንጥረ ነገር እየተረፈረፍን ነን - በቀጣፊዎች በየሥርቻው በሚመረት “መድኃኒት”፡፡ ማን ይድረስልን? ምን ይዋጠን? ከፈጣሪም ከኅሊናም ከመሪዎቻችንም ከዓለምም ተለይተን የመከራ ዶፍ እየወረደብን እንገኛለን፡፡ (“What swallow me?” አለ አሉ አንዱ እንግሊዝኛ እንደቁምጣ ያጠረው የኔቢጤ ተማሪ - ክፍል ውስጥ እንዲናገር ታዝዞ ሲናገር፡፡ መምህሩም የዋዛ አልነበረምና “Let the Abay river swallow you!”አለው ይባላል፡፡)

የሚገርመውና የሚያሳዝነው ደግሞ በንግድ ማጭበርበርም ሆነ ባዕድ ሸቀጥና ከባህል ያፈነገጠ ሥጋ ሲሸጥ ተገኝቶ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የሚገባ ወንጀለኛ (ተጠርጣሪ ልበለው ለወጉ ያህል) ወዲያው በጉቦ ይለቀቃል፤ ወንጀለኞች “ብታሰርም ገንዘቤን ይጭነቀው!” በሚል እየተበረታቱ የፈለጉትን ከመሥራት አልተቆጠቡም፡፡ ደርግ በርበሬ ደበቃችሁ ብሎ በጥይት እንዳልቀነሸላቸው አሁን የመንግሥታችን የህግ ባለሟሎች መዝገብ እየሰወሩ ሕዝብን አውዳሚ ወንጀለኞችን በጉቦ ይለቃሉ - የጉድ ሀገር! በዚያን ሰሞን አንድ ጓደኛየ የሚያውቀው ሀብታም ነጋዴ እህል ቅጠል የማይል የቀይ አፈር በርበሬ ሲያመርት እጅ ከፍንጅ ተይዞ አሥር ሽህ ብር ለመርማሪው በመክፈል ፋይሉን አስጠፍቷል - አሁን እንደንጹሕ ሰው በነፃነት ይንቀሳቀሳል፡፡ በሀገራችን ህግ ተደፍጥጧል፤ ሞራል ጠፍቷል፤ የሀገር ፍቅር ርቆ ተቀብሯል፡፡ ሃይማኖታዊ ትውፊት በካህናቱና በጳጳሣቱ ዘንድ ሳይቀር ለይስላሙ እንጂ ድራሹ ጠፍቷል፡፡ መስቀል ረከሰ፤ ሆድ ነገሠ፡፡ ትንቢቱም ደረሰ! - እንኳንስ ደረሰ፡፡ እየጨሱ ከመኖር መገላገሉ ይሻላል፡፡

አሁን ወዴት እንሂድ? ምንስ ይዋጠን? ቆናጃጅቱ ምነው ዘገዩ? ምን እስክንሆን ይሆን ፈጣሪስ እንዲህና እስከዚህ የጨከነብን?
 እግዚዖ እንበል፡፡ ቀኑ ቀርቧል፡፡ ተያይዘን እየጠፋን ነው፡፡ የህግ ጠለላ ከሌለን፣ ባለሥልጣናቱ ዘረኛና ጎጠኛ ሆነው ለዘር ሐረጋቸው ብቻ የሚያደሉና ሌላውን የሚገፉ ከሆነ፣ ቢሮክራሲው ከአንድ ጎሣ ወደሌላ ጎሣ ሽግሽግ በማድረግ የሚመጣው የመንግሥት የሥራ ኃላፊ በአብዛኛው አገልጋይነቱ ለመላው ሕዝብ ሳይሆን እወክለዋለሁ ለሚለው ነገድ ብቻ ከሆነ ኢትዮጵያ ምን ትሁን?

“ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” እንዲሉ በዚህች ድሃ ሀገር የአዲስ አበባ ከንቲባ - ለራስ ፍላጎት እንዲያመች እንደወያኔዎቹ ህግን ለዋውጦ በተደረገ ምደባ ለተሾመ ከንቲባ ሊያውም - በወር ከ140 ሽህ ብር በላይ ለቤት ኪራይ ብቻ የሚመደብ ከሆነ ወዴት እየሄድን ነው? ለመሆኑ የአንድ ሰው ጥቅማ ጥቅም ከወር ደመወዙ ሊበልጥ ይችላል ወይም ይገባል ወይ? ለቤት ኪራይ ይህን ያህል ገንዘብ ከተመደበ የወር ደሞዙ እኮ በሚሊዮን ቤት ውስጥ መሆኑ ነው፡፡ ምን እየተሠራ ነው?  አምባሳደር ሸኝና ተቀባይ ለነበረ አንድ ቅን ታዛዥ የቀድሞ ፕሬዝደንት ከ400 ሽህ ብር በላይ በወር ለቤት ኪራይ መከፈሉስ ምን ያመለከታል? ሀገሪቱን በተራ የማሳደግ ሳይሆን በተራ የመቦጥቦጥና የማኮስመን አባዜ መፍትሔ የሚያገኘው መቼ ነው? በርግጥም እውነተኛው ሕጻን እየተቀበረ እንግዴ ልጁ እያደገ ወደ ሥልጣን እየመጣ ይሆን እንዴ? መጠርጠር ነው፡፡ አለበለዚያ ገበሬው ድሃ ሕዝብ በባዶ እግሩ እየሄደ፣ ቆሻሻ የኩሬና የወንዝ ውኃ እየጠጣ - ያም ከተገኘ - በከፈለው ገንዘብ ይህን ያህል መቀናጣት ዕብደት ወይም ትልቅ የአእምሮ በሽታ መሆን አለበት፡፡ ኅሊና ወዴት ተቀበረ?  እነጠ/ሚኒስትር አብይስ ምን እያደረጉ ነው? ለመሆኑ እየሠሩ ያሉትን ነገር ያውቃሉ ወይንስ እነሱም ጨርሰው ደነቆሩ? ስንትና ስንት ሥራ አጥ ባለባት ሀገር፣ ስንትና ስንት ሚሊዮን ዜጋ በማይምነት ጥቁር መጋረጃ ተጀቡኖ በድህነት አረንቋ ውስጥ በሚዳክርባት የድሆች ድሃ ሀገር፣ ስንትና ስንት ዜጋ በህክምና ዕጦት በቀላል በሽታዎች በሚረግፍባት ሀገር፣ ስንትና ስንት ሚሊዮን ሕዝብ በርሀብ በሚቀጠፍባት ሀገር፤ ስንትና ስንት ሚሊዮን ሕዝብ በመንገድ ዕጥረት ከከተሞች ተቆራርጦ በችግር በሚማቅቅባት ሀገር፣ ስንቶች እየተሰደዱ ከሰውነት በላቾች እንደምንም ቢያመልጡ የባህርና የዱር ዐውሬ ሲሳይ በሚሆኑባት ሀገር…. ለአንድ ከንቲባ፣ ለአንድ ጡረተኛ፣ ለአንድ ተጧሪ ባለሥልጣን ይህን ያህል ገንዘብ በወር መመደብ ምን ዓይነት የአእምሮና የኅሊና ስንኩልነት ነው? በስማም! አዙሮ ማሰብን ምን ወሰደብን? ከሰውነት ተራ ማን ይሆን ያወጣን?

የዚህች ሀገር ዕጣ ፋንታ ያገባናል የምትሉ ተሰሚነት ያላችሁ ወገኖቼ እባካችሁ ሀገራዊ የጸሎትና የምህላ ሱባኤ እንዲጠራ አድርጉ፡፡ ያለንበት ሁኔታ ካምሱሩ የተፈታ ቦምብና ፈንጂ ዓይነት ነውና እንደ ሦርያ ሳንሆን ፈጣሪን እንለምነው፡፡ ሦርያውያን መሰደጃ አገር ጠፍቶ ኢትዮጵያም የሚሰደዱባት ሀገር ሆና - እነግብጽና ሱዳንን አልፈው ወደዚህ የመጡት ለአንዳች ምሥጢራዊ መልእክት ነውና በቶሎ ወደ እግዚአብሔር እንጩህ፡፡ አለበለዚያ በሁሉም ረገድ ጠፍተናልና ወዮልን! ዳኛ የለንም፤ ጠበቃ የለንም፤ የፍትህ ዐይን ድርግም ብሎ ጠፍቷል፤ የፀጥታ ኃይል የለም፤ ጥራቱን የጠበቀ የትምህርት ሥርዓት የለም - ሀሁን የማይለዩ የተለያየ ደረጃ ተመራቂዎች ናቸው ክፍት የሥራ ቦታዎችን በአብዛኛው እየሞሉ የሚገኙት፤ ሞራልና መልካም ሥነ ምግባር የለም፡፡ ያለው ብቸኛ ነገር የገንዘብ አምልኮትና ስለገንዘብና በገንዘብ ክምችት መሟሟት ነው፡፡ የሁሉም ዐይኖች ወደ ገንዘብ አፍጥጠዋል፡፡ የፈለግኸውን ወንጀል ብትፈጽም ብዙ ብር ካለህ ነፃ ነህ፡፡ ሁሉም ላንተ አሸርጋጅና ተላላኪ ነው፡፡ ገንዘብ የእግዚአብሔርን ቦታ ተክቶ ሕዝቡን እያራኮተው ነው፡፡ በቅርቡ ምናልባት ለገንዘብ ፅላት ሳይቀረጽለት የሚቀር አይመስለኝም፡፡… ሱባሃን! እንዴት ያለ ዘመን ላይ ደረስን ሲላ?!