Saturday, August 20, 2011

የኢትዮጵያና የኤርትራ ዝምድናና የምሁራኑ ሚና፡፡



Note from the Editor
If you need to read the article with larger font size press the keyboard Ctrl and the + sign at the same time. If you want the page to minimize or font to minimize press Ctrl and the - sign at the same time.

የኢትዮጵያና የኤርትራ ዝምድናና የምሁራኑ
ሚና፡፡
               እንዴት ነበር? አሁንስ ምን መሆን አለበት?

 ተስፋጽዮን መድሃኔ

    ብረመን ዩኒቨርሲቲ፣ ጀርመን

               አገርህንና ታሪክህን ዕወቅ፣ ወርሀዊ መድረ

            በርሊን፡ ጁን 13፡ 2011

       መግቢያ
ይህ በፕሮፈሰር ተስፋዮን መድሃኔ የቀረበው ፅሁፍ በመጀመርያ የተደመጠው በጀርመን አገር፡ በበርሊን ከተማ፡ “አገርህንና ታሪክህን ዕወቅ” በሚለው መድረክ ላይ በጁን 13፡ 2011 ዓ. ም. ወርሀዊ ስብሰባ ነው። እዚያ ከንግግሩ ተያይዞ በተካሄደው ውይይት ላይም ኢትዮጵያውያንንና ኤርትራውያንን የሚያገናኝ ህዝብ-ለህዝብ፣ የውይይት መድረክ በአውሮጳ  ይቋቋም የሚል ውሳኔ ተደርሰዋል። ይህ መድረክ በመጀመርያ የሚቋቋመው በበርሊን ከተማ ሲሆን በሌሎች የጀርመን ከተሞችና የአውሮጳ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያንም አርአያውን እንዲከተሉ እንማጸናለን።

 ይህ ፅሁፍ፡ ወደፊት ምሁራኑ በዚህና በሌሎች የአከባቢው ጉዳዮች ላይ የሚወያዩበት፣ የተለያዩ ሀሳቦችን የሚያራምዱበት፣ እንዲሁም ትችትና ምርምር የሚያካሂዱበት አልፎ-አልፎ በሚታተም መፅሄት ላይ ከሌሎች ፅሁፎች ጋር አብሮ ይወጣል። እስከዚያ ድረስ ሃሳቡን ሰው እንዲመለከተው በማለት በተለያዩ ድህረ-ገጾች እንዲሰራጭ አድርገናል።
                        ስለ “አገርህንና ታሪክህን ዕወቅ”
                               ይልማ ይለሚካኤል፤
                                         (ሰብሳቢ)


የሚከተለው ፅሁፍና በበርሊን ከተማ በጁን 13 2011 ስብሰባ የተሰጠው ንግግር፡ በይዘቱም በቋንቋውም ሙሉ በሙሉ አንድ ነው፡፡ ነገር ግን፡ ንግግሩ ለህትመት በሚዘጋጅበት ጊዜ፡ በስብሰባው ውይይት የተነሱትን ነጥቦች ከግምት በማስገባት፡ ይዘታቸው ምንም ሳይለወጥ በበለጠ እንዲብራሩ በማለት ጥቂት ሃሳቦች ትንሽ ሰፋ ብለዋል፡፡ 

ንግግሩ በዚሁ መልክ ታትሞ እንዲወጣ ለኢትዮጵያና ለኤርትራ በጎ ምኞት ያላቸው ወዳጆቼ ተባብረውኛል፡፡ በጣም አመሰግናቸዋለሁ፡፡

ተስፋጽዮን መድሃኔ፡፡ 


የኢትዮጵያና የኤርትራ ዝምድናና የምሁራኑ ሚና፡፡   

እንዴት ነበር? አሁንስ ምን መሆን አለበት?

 ተስፋጽዮን መድሃኔ (ፕሮፈሰር) ብረመን ዩኒቨርሲቲ፣ ጀርመን

 ይህ ጥያቄ ከተነሳ በጣም ቆይተዋል፡፡ በተለይ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተገነጠለች በሁዋላ፡ በተለያየ መልኩ ሲነሳ ነበር አሁንም እየተነሳ ነው፡፡ በሁለቱ ኣገሮች መካከል የነበረው ግኑኝነት ችግር ውስጥ ሲገባና፡ በሁዋላም እየተበላሸ ሄዶ እስከመለያየት ሲደርስ ምሁራን ምን ያደርጉ ነበር? ኣሁንስ ምን እያደረጉ ነው? ለተፈጠረው ችግር ኣስተዋጽኦ ያደረጉና፡ ኣሁንም በማድረግ ላይ ያሉ ምሁራን ቢኖሩስ ድክመቶቻቸው ምን ይመስሉ ነበር? አሁንስ ምን ይመስላሉ? እነዚህንና ሌሎችንም ተመሳሳይ ጥያቄዎች በተለያዩ መድረኮች በመጠኑም ቢሆን ተወያይተንባቸዋል፡፡

 እነዚህ ጥያቄዎች የሚነሱት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው ወንድማማችነት እንዲታደስና ለሁለቱ ሀገሮች ገንቢ የሆነ ትስስር ይኖር ዘንድ ምን ማድረግ እንደሚቻል በምንመረምርበት ጊዜ ነው፡፡

 በዚሁ ንግግሬ ምሁራን ስል በተለያዩ ዓውደ ጥናቶች ሊቀ-ሊቃውንት ያሰኙ፡ ሞያቸው ሃሳብ ማፍራትና ማቀበል ወይም ማሰራጨት የሁኑ ሰዎችን ማለቴ አይደለም፡፡ እነዚህን ሊጨምር የሚችል ቢሆንም፡ ምሁራን ስል በህብረተሰቦቻችን ውስጥ ከዘመናዊው ትምህርት ጋር የተዋወቁ፡ በአገር ፖለቲካና አስተዳደር አስተያየት ያላቸው፡ አቋም መውሰድ የሚችሉ፡ ሚናዎችም የሚኖሩዋቸው ማለቴ ነው፡፡ ቃሉን በዚሁ ትርጉም ለመጠቀም ፕሮፈሰር ባሀሩ ዘውዴ በ1994 ባሳተመው አንድ ፅሁፍ የገለውን ሃሳብ መሰረት በማድረግ ነው፡፡

 ምሁራን፡ ወሳኝ ናቸው ባይባልም፡ ትልቅ ሚና አላቸው፤ በተለይ በታዳጊ አገሮች ሚናቸው ከፍ ያለ ነው፡፡ ነገር ግን ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም የሲቪል ህብረተሰብ ክፍሎች ሚናዎች ነበሩዋቸው፣ አሉዋቸውም፡፡ ይህንን ሳንረሳ ነው በምሁራን ሚና የምናተኩረው፡፡

 በኤርትራና በኢትዮጵያ ምሁራን የተለያዩ ሚና ተጫውተዋል፣ ገንቢም አፍራሽም፡፡ የኢትዮጵያውያን ምሁራን ሚና፡ በተለይ ከአፄ ኃይለሥላሤ ዘመን አንስቶን በተመለከተ ብዙ ተፅፈዋል፤ ፕሮፈሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ ኃይሥላሤ፣ ዘመናዊ ትምህርትና አብዮት በኢትዮጵያ በሚል ርእስ በእንግሊዝኛ የደረሰው መፅሀፍ ከአንጋፋዎቹ ስራዎች አንዱ ነው፡፡

 ዛሬ ከምሁራኑ ምንድነው የሚጠበቀው? ወይም ምሁራኑ ምን ማድረግ አለባቸው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ያለፈው አፍራሽ ሚናቸው ምን እንደነበረ፡ ወይም በአፍራሹ ሂደት ምን ሚና እንደነበራቸው እና አሁን ደግሞ እንዴት እንደሚታረም መወያየት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ግን ገንቢ ሚናቸውን መካድ አይደለም፤ እርማትና እድገት ስለምንፈልግ ግን ስህተቶቻችንንና ጥፋቶቻችንን በቀዳሚነት እንመረምራለን፡፡ በሌላ አነጋገር እርማትና እድገት በሚሻ መንፈስ ነው በድክመቶቻችንና በስህተቶቻችን ላይ የምናተኩረው፡፡   

 
ይህንን ዓይነት ምርምር ስናደርግ በቅድሚያ የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ምን ወይም እንዴት መሆን እንዳለበት ማየት ይኖርብናል፡፡ ያለንበት ዘመን ዘመነ-ገሎባላይዘሸን ነው፤ አገሮች ወይም ዓለም በሙሉ በተለያዩ ዘርፎች ተዛምደዋል፡ ተሳስረዋል፡፡ ማንኛውም አገር ያላትን ለሌሎች እያቀበለች፡ የሌላትን ደግሞ ከሌሎች እየተረከበች ነው የምትኖረው፡፡ ከሌሎች አገሮች በብዙ ዘርፎች ሳትተሳሰር ትርጉም ባለው ሁኔታ የምትኖር አገር የለችም፡፡

በተለይ ድሃ ወይም ታዳጊ ኣገሮች በበለጠ መተሳሰር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ ሁለት ድሃ የሆኑ ታዳጊ አገሮች ናቸው፡፡ አሁን ባለው የዓለም ሁኔታ በሁሉም ዘርፍ መዛመድ እንዳለባቸው ሁለቱን አገሮች ለሚያውቅ ሁሉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ካልተዛመዱና ካልተሳሰሩ የህዝቦቻቸውን ኑሮና መብቶች ሊያሟሉ አይችሉም፡፡ በሌላ አነጋገር፡ ተለያይተን - ማለት አንድ ዓይነት ትስስር ሳናደርግ - የዓለምን ሁኔታ ልንቋቋመው አንችልም፡፡

አሁን ባለው የዓለም ሁኔታ ኢትዮጵያና ኤርትራ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ዝምድናም ያስፈልጋቸዋል፡፡ የፖለቲካ ዝምድናውም ካሁን በፊት በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት ኮንፈደረሽን የሚባለው ነው፡፡ ኮንፈደረሽን በኢትዮጵያና ኤርትራ መሀከል ብቻ ሳይሆን ሁሉንም የአፍሪቃ ቀንድ አገሮች ያቀፈ እንዲሆን የሚፈለግ ነው፡፡ በዚሁ ጊዜ ግን ተግባራዊነት ሊኖረው የሚችል፡ ያውም አንዳንድ ቅድመሁኔታዎች ከተሟሉ በሁዋላ፡ በኢትዮጵያና በኤርትራ መሀከል ነው፡፡ የዚህ ሁለት አገሮች ትስስር ለወደፊቱ የሚቋቋመው የአፍሪቃ ቀንድ ኮንፈደረሽን መሰረት ይሆናል፡፡ 

ኮንፈደረሽን ማለት ምን እንደሆነ፤ ከፈደረሽን እንዴት እንደሚለይ ካሁን በፊት በሳን ሆዘ ስብሰባዎች ገልጬዋለሁ፡፡ በይዘቱ የሚለያይ ቢሆንም፡ ኮንፈደረሽን ሲባል፡ በጠቅላላ አነጋገር፡ አገሮች ልዓላውነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የሚያደርጉት ትስስር እና የሚያቆሙት መንግስት ነው፤ አብነት በመስጠት ነገሩን ባጭሩ ለመግለጽ፡ አሁን ያለው የአውሮፓ ህብረት ዓይነት ዝምድናና መንግሥት ማለት ነው፡፡ የፖለቲካው ትሰስር - እንዲያውም የኢኮኖሚውም ቢሆን - ለምን ያስፈልገናል? ጤናማ የሆነ መልካም - ማለት ኖርማል - ጉርብትና ብቻ ለምን ኣይበቃም? የሚል ፈታኝ ጥያቄ በአንዳንድ ስብሰባዎች ኣጋጥሞኛል፡፡ እኔን በተመለከተም፡ “ፈደረሽን፡ ኮንፈደረሽን እያለ ባያደነቁረን መልካም ነበር” የሚሉ ኤርትራውያን እንዳሉ አውቃለሁ፡፡

ይህ ፈታኝ ጥያቄም ሆነ ነቀፌታ የዓለምንና የሁለቱ አገሮቻችንን ሁኔታ በደንብ ካላጤነ አመለካከት የሚነሳ ነው፡፡እንዲያውም “ጤናማ የሆነ መልካም” (ኖርማል) ጉርብትና ሲባል በይዘቱ የተለያየ መሆኑን ያልተገነዘበ አስተሳሰብ የሚያንጸባርቅ ነው፡፡ የሁለት (ወይም በቁጥር ከዚያ በላይ የሆኑ) አገሮች ዝምድና ይዘት እንደየሁኔታቸው ይለያያል፡፡ የኢትዮጵያ ጉርብትና ከከኒያ ጋር እና ከጂቡቲ ጋር በይዘቱ አንድ ሊሆን አይችልም፤ የኤርትራ ጉርብትና ከኢትዮጵያና ከጂቡቲ ጋር ወይም ከየመን ጋር በይዘቱ አንድ ሊሆን አይችልም፡፡

ኢትዮጵያና ኤርትራ በጂዮግራፊያዊ አቀማመጣቸው፡ በታሪካዊና ባህላዊ ዝምድናዎቻቸው፡ በኢኮኖሚያዊ እርስ-በርስ ተፈላላጊነታቸው ወይም ተጠቃቃሚነታቸው (ወይም በጋራ ጥቅሞቻቸው) ምክንያት የጤናማ ጉርብትናቸው ይዘት ጥብቅ የሆነ ቅርበት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ይህ በይዘቱ ጥብቅ ቅርበት የሆነ ጉርብትና የኢኮኖሚም የፖለቲካም ገጽታዎች አሉት፡፡ የኢኮኖሚው ገጽታው መወሃሃድን የሚፈቅድና የሚያስችል መዋቅር ነው፤ የፖለቲካ ገጽታው ደግሞ፡ ኮንፈደረሽን ወይም እሱን የሚመስል ነው፡፡  

ለኔ እንደሚመስለኝ እንዲህ ዓይነት ዝምድና አለማቋቋም ወይም አለማበጀት ምክንያታዊ (ራሽናል) ወይም ብልህ ውሳኔ አይደለም፤ እንዲያውም ከዕውነታ ወይም ከገሃድ ዓለም የራቀ (ወይም  አንሪያሊስቲክ) ነው፡፡ይህን ዓይነት ዝምድናን መቃወም ዕውነታን መካድ ነው፤ ኮንፈደረሽን መሳይ ትስስር አልፈልግም ማለት ቢያንስ በሁለቱ አገሮች መካከል ሊኖር የሚገባውን ጤናማና በሰላም አብሮ የመኖርን (የመበልግን) መርሆ ወይም ዓላማ አለመቀበል ነው፡፡

አሁን ያለው የኢትዮጵያና ኤርትራ ግኑኝነት፡ ዝምድና ሊሆንስ ይቅር፡ ሰላማዊ ጉርብትና ነው ብሎ ለማለት እንኳን አያስደፍርም፡፡ የዚህ ሁኔታ አመጣጥና ታሪክ ሁላችን የምናውቀው ነውና ጊዜ ልናጠፋበት አያስፈልግም፡፡ ይልቁንስ መመርመር ያለብን ይህ አሳዛኝ ወይም የማይገባ ሁኔታ እንዲደርስ እና አሁንም እንዲቀጥል ምሁራኖቹ ምን ሚና ተጫወቱ? ምን አሰተዋጽኦ አደረጉ? ይህንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ያበቁዋቸው ድክመቶችስ ምን ናቸው? የሚሉትን ጥያቄዎች ነው፡፡ ነገሩን በግልጽ ለማስቀመጥ፡ በኤርትራ ለነጻነት ወይም ለመገንጠል ጦርነት ይካሄድ በነበረበት ጊዜ ምሁራኖቹ ምን ሚና ነበራቸው? ኤርትራ ከተገነጠለች በሁዋላስ ሁኔታው ሲባባስ ምን ሚና ነበራቸው?

ይህንን ጥያቄ ለመመለስ በመጀመርያ የትኞቹ ምሁራን ማለቴ እንደሆነ ባጭሩ መግለጽ እወዳለሁ፡፡ እነዚህ ምሁራን በ60ዎቹ፡ 70ዎቹ እና በ80ዎቹ በኢትዮጵያም በኤርትራም ትልቅ ሚና የነበራቸው፤ አሁንም እያረጁና እየተተኩ ቢሆኑም ገና መጠነኛና እያነሰ የሚሄድ ያለ ሚና ያላቸው ናቸው፡፡ ከነዚህ ምሁራን አብዛኛዎቹ “ጥላሁን ታከለ” ተብሎ ከሚታወቀው ባህሩ ዘውዴ አስቀድሜ በጠቀስኩት መጣጥፍ ሶስተኛው የአዲስ ምሁራን ትውልድ ብሎ ከሚገልጸው ክፍል ናቸው፡፡

ይህንን የምሁራን ትውልድ አውቀዋለሁ፤ የኔም ትውልድ ነውና፡፡ ብዙው ከዚህ ትውልድ፡ በተማሪነት ጊዜ፡ በጠቅላላው አነጋገር፡ ተምረው ዕውቀት የማዳበርን ዓላማ በተግባር የሚገባውን ያህል ቀደምትነት የሰጠ አይመስልም፡፡ ታሪክንና ጽንሰ-ሃሳቦችን - የፖለቲካ ጽንሰ-ሃሳቦችን ጨምሮ - በትጋት ለማንበብ፡ ለማጥናትና በጥልቀት ለማወቅ የጓጓ ነበር ቢባልም፡ አዝማሚያውንና ብቃቱን ግን በተግባር አላስመሰከረም፡፡ ይልቁንስ ለገቢራዊ ንቅናቄ እና ለአብዮት መዘጋጀት የሚለው መንፈስ ያየለበት ነበር፡፡ ይህ ግን ለብዙው ወይም ለአብዛኛው ብቻ የሚመለከት ሃቅ ነው፤ ካለበለዚያ ትምህርታቸውን በደንብ የሚከታተሉና በቂ ንባብ ያደረጉ፡ በፖለቲካ ንቅናቄም የተሰማሩ ጥቂቶች ነበሩ፡፡ በብዙ የአውሮጳና ሌሎች የምዕራቡ ዓለም አገሮችም፡ ወቅቱ - በተለይ ከ1968 አንስቶ -  ተማሪው እንደዚሁ ከመደበኛ የትምህርት ተቋማትና የህብረተሰቡ ዕሴቶች በመንፈስ እየራቀ የሄደበት ነበር፡፡      

ይህ ትውልድ  ለኢትዮጵያም ለኤርትራም ቀና ምኞትና ውብ የሆነ ራዕይ ነበረው፡፡ ለህዝቦቹ አሳቢ፡ ለሃገሩም ተቆርቋሪ ሆኖ፡ ለማስዋእትነትም ዝግጁ ነበር፡፡ ከራዕዩ ውበትና ከዓላማው ክብደት ጋር የሚጣጣምና የሚመጣጠን ዕውቀትና አሰተዋይነት ግን አልነበረውም፡፡ ይህ ትልቅ ድክመት ነበር፤ ከዚህ ድክመት የተነሳም ይህ ትውልድ፡ በኢትዮጵያም በኤርትራም፡ በህሊናው ብሄርተኛ፡ አገር-ወዳድ፡ ባለ-ጀብዱና ተራማጅ እያለ፡ አመርቂ የሆነ ስትራተጂና ስልት ቀይሶ ሁኔታውን ሊቋቋም አልቻለም፡፡ ስለዚህም ከንጉሳዊው ሥርዓት ህልፈት በሁዋላ በሁለቱም አገሮች ሥልጣን ላይ በወጡትና አሁንም ገና ሥልጣን ላይ ባሉት ቡድኖች ክፉኛ ተመታ፡፡


መሰረታዊ ከሆኑት ድክመቶች አንዳንዱን አጠር አጠር አድርጌ ልጥቀስ፡፡

- ከድክመቶቹ አንዱ አስቀድሞ ከተጠቀሰው ዕውቀትና በጥልቀት የመረዳት ችሎታ ካለመኖር ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኢትዮጵያንና ኤርትራን በተመለከተ ምሁራኖቹ በቂ ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡ የኤርትራ ምሁራን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ሆነ ፖለቲካ ዕውቀቱ አልነበራቸውም፤ ስለ ኤርትራም ቢሆን ዕውቀታቸው ጥለቀት ያለው አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያውያን ምሁራንም እንደዚሁ ስለ ኤርትራ በመጠኑ ትርጉም ያዘለ ዕውቀት አልነበራቸውም፡፡ 
ብዙው ከዚህ የምሁራን ትውልድ ታሪክንና ባህልን በተመለከተ የፍፁም ተቃውሞ (ንሂሊሰት) የሆነ መንፈስ ነበረው፤ ታሪክንም ሆነ የባህል እሴቶችን ከቁጥር ውስጥ አላስገባም፡፡ ታሪኩና ባህሉ በጎና የሚያገለግል ገፅታ እንዳለው ዘንግቶ፡ ሁሉንም ከፊውዳሉ ስርዓት ጋር በማዛመድ ችላ አለ፡፡ ታሪክንና ባህልን ችላ ማለት ስህተት ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛም ነበር፡፡ በዚህ ቸልተኝነት ምክንያት፡ በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ምሁሩ በምን ዓይነት ማህበራዊ ሁኔታ ይንቀሳቀስ እንደነበረ አላወቀም፤ በኢትዮጵያ ይሁን በኤርትራ ምን ያህል ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል፣ ለውጡን ለማሳካት ሊተባበሩ የሚችሉ የህብረተ-ሰቡ ወገኖች የትኞቹ እንደነበሩ፣ በሌላ አነጋገር፡ በዚያ ወቅት ዒላማዎቹ ወይም ጠላቶቹ እና ተባባሪዎቹ ወይም ወዳጆቹ የትኞች እንደነበሩ ብቁ ጥናት በማድረግ አልተረዳም፡፡ ስለዚህም በትግል ጉዞው ብዙ አላስፈላጊ ጠላቶች አፍርቶ ከሰረ፡፡
 ከዚህ ድክመት ጋር በተያያዘ፡ በፖለቲካው መስክ የአገሮቻችን ወይም የህብረተ-ሰቦቻችን ባህሎች የጉልበት ወይም ጭካኔ (ቫየለንስ) ባህሪም ያለባቸው መሆኑ የምሁራኑ ትውልድ በሚገባ  አላጤነም፡፡ በህብረተሰቦቻችን ሰላምና ፍቅር መሰረታዊ እሴቶች ቢሆኑም ፖለቲካዊ ታሪካችን ግን ታላቅ የጭካኔ ገፅታ ያለበት ነው፡፡ በታሪካችን ብዙውን ጊዜ ንጉስ በሌላ - ማለት፡ በአዲስ - ንጉስ ሲተካ ህጋዊና ሰላማዊ በሆነ የሽግግር ሂደት አልነበረም፤ በማንኛውም መልኩ አንዱ - ቡድን ይሁን ግለሰብ - ሌላውን በኃይል አሸንፎ እንጂ፡፡ ይህንን ነጥብ አንጋፋው ኢትዮጵያዊ ምሁር ፕሮፈሰር ንጉሴ አየለ በዚሁ ዓመት በታተመው አንድ መጣጥፍ አብራርቶታል፡፡ እንዲሁም ደራሲና የፖለቲካ ተንቀሳቃሽ  ጌታቸው ረዳ “ሓይካማ” በተሰኘው መፅሃፉ ትግራይ ውስጥ ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ የተፈጸመውን፡ በእሳት መለብለብን የጨመረ፡ አረሜናዊ የሰብአዊ መብቶች ረገጣ ዘርዝሮ በማጋለጥ ባህላችን በፖለቲካዊ ገፅታው ምን ያህል ጭካኔ እንዳለው ያስረዳል፡፡ የፖለቲካ ባህላችን ይህ ባህርይ እንዳለው በሚገባ ባለመረዳታቸው አንዳንድ  የምሁራን ቡድኖች ተመልሰው የጐዱዋቸውን የትግል ስልቶች ተጠቀሙ፡፡ በጭካኔ እምብዛም ለተካኑ፡ የጭካኔ ባህላቸው በምሁራውነት ላልለሰለሰ፡ ርህራሄ ለሌላቸው ቡድኖች ሰለባ ሆኑ፡፡

 ይህ ሲባል ግን ምሁራኖቹም በህብረተ-ሰቡ ባህል ያልተነኩና የህብረተ-ሰቡ ጠባይ ፈፅሞ የሌላቸው ነበሩ ማለት አይደለም፡፡ በህብረተ-ሰቡ ተወልደው ያደጉ በመሆናቸው እነርሱም፡ በዘመናዊው ትምህርት ሂደት ባንዳንድ ረገድ ቀየጥ ያሉ ቢሆንም፡ የህብረተ-ሰቡ ዕሴቶች ነበሩዋቸውም አሉዋቸውም፡፡ አንዳንድ የባህላችን አስከፊ ገፅታዎች - ጭካኔውን ጨምሮ - ከሌሎቹ ባነሰ መጠን ይሁን እንጂ በምሁራኖቹም ታይቷል፡፡ የሚያሳዝነው ግን ምሁራኖቹ ከህብረተ-ሰቡ ጋር መሰረታዊ ዕሴቶች እንደሚጋሩ በሚገባ መጠን አለማወቃቸው ወይም አለማመናቸው ነው፡፡ ይህ ጉደለት ከባድ ጉዳት እንዳደረሰ አንዳርጋቸው ፅጌ ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጪ በሚለው መፅሃፉ ያመለክታል፡፡   

ይህ የምሁራን ትውልድ በኤርትራም ሆነ በኢትዮጵያ የፊተኞቹ የምሁራን ትውልዶች ያህል ጨዋነት ወይም ትህትና (ሲቪሊቲ) አልነበረውም፡፡ የሃሳብ አገላለፁ ዘይቤ ብዙውን ጊዜ የተረጋጋና ክፍት ሳይሆን፡ የአክራሪነትና የጠብ ቃና ያዘለ (ፖለሚካል) ነበር፡፡ መደማመጥ፡ መግባባት፡ እና መቻቻል በሚፈለገው መጠን አልነበሩም፡፡ (ባህሩ ዘውዴ፡ ገፅ 486፤ ገላውዴዎስ አርአያ፣ ገፆች 69- 71) ፡፡ በነዚህና በሌሎች ምክንያቶች የዚህ ትውልድ ምሁራን በተፈለገው መጠን ተግባብተውና ተባብረው መስራት አልቻሉም፡፡         
አስቀድሜ ከጠቀስኳቸው ድክመቶች ጋር የተያያዘ ሌላ ጉድለትም ነበር፤ እሱም ዕውነታው ከሚፈቅደው በላይ ማቀድ ወይም ዕቅድን ለመተግበር መሞከር (አልትራዪዝም) ነው፤ ይህ ማለት ሁኔታው የሚፈቅደውና የሚያስችለው ምን እንደሆነ መርምሮ ሳይሆን፡ የተመኙት ግብ ወይም ዓላማ መደረስ አለበት ብሎ በጭፍን መንቀሳቀስ ማለት ነው፡፡ እንዲህ የመሰለ ሁኔታን ያላጠናና ያልጠበቀ አካሄድ ብዙውን ጊዜ ጠላትን ይጠቅማል፡፡ በቅርቡ ታሪካችን - በኢትዮጵያም  በኤርትራም - አይተነዋል፡፡ አሁንም ይህንን የሚመስል ጉድለት እየታየ ነው፡፡

ብዙውን ጊዜ ከዚህ ጉድለት ጋር ተያይዞ የሚከሰት ሌላ ድክመትም ነበር፡ አሁንም አለ፤ እሱም ከተባሉት ምሁራን ብዙዎቹ፡ እንደግለሰቦች ለመስዋእትነት ዝግጁ ቢሆኑና ቢሰዉም፡ የመጨረሻው ዓላማ ወይም ግብ በትውልዳቸው ጊዜ እንዲረጋገጥ መሻታቸውና መሞከራቸው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በውነቱ በሂደት እስከዚህም አያምኑም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ዕድገት ሲባል ሂደት ነውና፡ ፈጻሚ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ጀማሪ ትውልድ መሆንም ጀግንነት ነው፤ እንዲያውም ጀማሪ መሆን የበለጠ ጀግንነት ነው ማለት ይቻላል ምክንያቱም ያልተጀመረ አያልቅምና፡፡ በለውጥ ሂደት መነሳትና መጠናከር መድረክን ወይም ሁኔታን በጥንቃቄ እያገናዘቡ በመሳተፍ ፋንታ የመጨረሻውን ግብ እውን ለማድረግና ለማረጋገጥ በመሻት የተባሉት ምሁራን ትልቅ ችግር ላይ ወደቁ፡፡   

ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ምሁራን አሁን ያለው ችግር እንዲከሰት ባለፉት ዓመታት፡ በተለይ በደርግ ዘመን፡ የየራሳቸው አስተዋፅኦ አድርገዋል፤ አሁንም እያደረጉ ናቸው፡፡ አስተዋጽኦውን ያደረጉት መንግስታቱና ድርጅቶቹ ይተገብሩዋቸው ከነበሩት፡ አሁንም ገና እየተከተሉዋቸው ካሉት የተሳሳቱ ወይም ጐጂ የሆኑ ፖሊሲዎች ጋር በተያያዘ ነው፡፡ የሚከተሉት ዋና-ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ኤርትራውያን ምሁራን በተለይ የኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ. ደጋፊዎች የነበሩት፡ ትልቅ ድክመት አሳይተዋል፡፡ በመሰረቱ እነዚህ ምሁራን አውቶኖሚ - ማለት የአእምሮ ነጻነት - አልነበራቸውም፡፡ ሊኖራቸውም አይችልም ነበር፤ ያ ኢሳያስ አፈወርቅ የተቈጣጠረው ድርጅት እምብዛም ጥብቅ በሆነ ማእከላዊነት ነበር የሚተዳደረው፤ የዲሞክራሲ ጭላንጭል አልነበረውም፡፡ ምሁራኖቹ ታዲያ  ለድርጅቱ መሪ አካል ሙሉ-በሙሉ ተገዢ ነበሩ፡፡ የሚጽፏቸው አንቀጾችና የሚደርሷቸው መጻህፍት የኢ.ፒ.ኤል.ኤፍን አቋሞች የሚያንጸባርቁና፡ የ.ኢፒ.ኤል.ኤፍን ፕሮፓጋንዳ እንዳለው የሚያሰራጩ ነበሩ። በዚህ ረገድ ኢ.ኤል.ኤፍ. (ጀብሃ) የነበረው ሁኔታ የተለየ ነበር፤ ከጀብሃ ጋር ተዛምደው የነበሩት ምሁራን በመጠኑ የማይናቅ አውቶኖሚ ነበራቸው፡፡

ከአውቶኖሚ ጋር በአንዳንድ ረገድ የሚመሳሰል ሌላ ችግርም ነበር፡፡ አሁንም በመጠኑ አለ፡፡ የኢትዮ-ኤርትራ ጥያቄ በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ከርእሰ-ኃያላኑ ፉክክር ጋር ተሳስሮ ነበር፡፡ በአመሪካ የሚመራው የምዕራቡ ዓለም አፍቃሬ ሶቭየት የነበረውን የአዲስ አበባው መንግስት ይቃወሙ የነበሩትን ንቅናቄዎች፡ ኢፒ ኤል ኤፍን ጨምሮ፡ ይደግፍ ነበር፡፡ ደርግን ለማዳከም የኤርትራ ነፃነት ደጋፊዎች ሆነው የቀረቡ የምዕራቡ ስትራተጂ አራማጆችም ነበሩ፡፡ አንዳንድ የኢፒ ኤል ኤፍ አባሎችና ደጋፊዎች የሆኑ ኤርትራውያን ምሁራን ታዲያ የኤርትራን ነገር ለምዕራቡ ስትራተጂ በሚያገለግል መልኩ እያቀረቡ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ ነበር፡፡ አንዳንዱንማ እንዲህ የመሰለ ዘመቻ ማካሄድ በምዕራቡ ዓለም ኑሮ ለማበጀት የረዳው ይመስላል፡፡ እነዚህ ምሁራን በዚህ ሁኔታ ስለኤርትራ ሲፅፉና ሲንቀሳቀሱ እውነተኛ የሆነ አውቶኖሚ ሊኖራቸው ይችል እንዳልነበረ መገመት ይቻላል፡፡     

ታሪክን በተመለከተ ኤርትራውያን ምሁራን ትልቅ ስህተት ፈፅመው ጉዳት አድርሰዋል፡፡ ኤርትራ ድሮም ቢሆን ከኢትዮጵያ ጋር ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ዝምድና አልነበራትም ለማለት ታሪክን ጠምዝዘው አቀረቡ፤ እንዲያውም የውሸት ታሪክ ፈለሰፉ፡፡ እንዲህ በማድረግ ወጣቱን አደነቈሩት፤ ማንነቱን በተመለከተም ግራ አጋቡት፡፡ ይህ ተግባር የተፈመው ኤርትራ የተለየች ሉዓላዊት አገር ለመሆን መብት አላት ለማለት እንዲመች ነበር፡፡ እጅግ የሚያሳዝነው ኤርትራ ይህ መብት አላት ብሎ ለመከራከር ታሪክን መጠምዘዝ ወይም የፈጠራ ታሪክ መሸቅሸቅ አስፈላጊ አለመኖሩ ነው፡፡

 ይህንን የሚመሳሰል ምሁራኑ ያስተጋቡት ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ-ግዛት ናት የሚለው አቋም ነበር፤ ይህም መርዘኛ ውሸት ነበር፡፡ ኤርትራ የነበራት አውቶኖሚ (ራሰ ገዝነት) በሀይል ተወስዶባት ያለፍላጐትዋ እንደ ጠቅላይ ግዛት ተቀላቀለች፤ ይህ ግፍም ጭቆናም ነበር፤ የቅኝ ግዛት ሁኔታ ግን አልነበረም፡፡ ይህ ውሸትም የተፈለገው ለነፃነት ወይም ለመገንጠል ጥያቄ ደገፍ እንዲሆን በማለት ነበር፡፡ ዳሩ ግን ይህ ውሸትም ኤርትራ ለነፃነት ወይም ለመገንጠል መብት አላት ለማለት አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ህዝቡን፡ በተለይ ወጣቱን ግራ ለማጋባት ብቻ አገለገለ፡፡   

 አንዳንድ ኤርትራውያን ምሁራን ኢትዮጵያውያንንና ባህላቸውን - የትግራይ ህዝብን ጨምሮ - ያሳነሰና ያቋሸሸን ፕሮፓጋንዳ በማራመድ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ይህ ሚና አሁንም በተለይ የትግራይ ህዝብን በሚመለከት እየቀጠለ ነው፡፡

 ኢትዮጵያውያንንና ሌሎችን የቀጠናው ህዝቦች ያሳነሰ መንፈስ ስለ ኤርትራ ዓቅምና ብቃት የተጋነነ እምነት ማሰማቱ የማይቀር ነበር፡፡ በተግባር የኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ. ድምፅ-ማጉሊያ ናቸው ተብለው ይተቹ የነበሩ ምሁራን ኤርትራ ንቁና ታታሪ የሆነ ህዝብ ያላት፡ ራሷን በደንብ የምትችል የተአምር አገር ናት፤ ለወደፊቱም በፍጥነት እነዳደጉትና እንደበለጉት አንዳንድ የእስያ ሃገሮች ልትሆን ነው የሚለውን ጉራ በማራመድ ተሳትፈዋል፡፡ ይህ ብዙ ኤርትራውያንን ግራ አጋብቶ ከኢትዮጵያውያን ጋር የሚያደርጉት ግኑኝነት ተቀባይነትና ተግባራዊነት ባለው ሥርዓት እንዲሆን አልረዳም፡፡ ስለዚህም በሁለቱ ህዝቦች መካከል የነበረውን የወንድማማችነት ዝምድና ትክክለኛውን ገፅታ እንዳያሳይ አስፈላጊ ያልሆኑ ችግሮችን ሳያስከትል አልቀረም፡፡    

በዚሁ ጊዜም ኤርትራውያን ምሁራን ህዝባቸውን የማሰተማር ሃላፊነታቸውን እየተወጡ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ አሁንም ገና በኤርትራው መንግስት ፕሮፓጋንዳ ተደጋግሞ የሚለፈፈው በአፄ ኃይለሥላሤ ዘመን ይሁን በደርግ ጊዜ በህዝቡ ላይ የተፈመው ግፍ ነው፡፡ በትግሉ ጊዜ ኢፒ ኤል ኤፍ በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሰው ግፍ እንደነበረም ምሁራኖቹ አይገልፁትም ያሉት፤ ምናልባት ለራሳቸውም አያውቁትም ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ኮሎኔል አምሳሉ ገብረዝጊ በደረሱት የኤርትራ መዘዝ በሚል መፅሃፍ ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ. በኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ የወሰዳቸው አንዳንድ ኢሰብአዊ እርምጃዎች ተገልዋል፤ ኤርትራውያን ይህንን ማወቅ አለባቸው፤ ማሳወቅ ያለባቸው ደግሞ ምሁራኑ ናቸው፤ እያደረጉት ግን አይደለም፡፡

ኤርትራውያን ምሁራን በኢትዮጵያ መንግስታትና ህዝብ መሃከል አስፈላጊ በሆነ መጠን ልዩነት አላደረጉም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ኤርትራውያንን በወንድምነት እንደተቀበላቸውና፡ በሁሉም ዘርፍ ከኤርትራውያን ጋር ለመዛመድ እንዳላመነታ ምሁራኖቹ ባለፈው ጊዜያት በሚገባ አልመሰከሩም፡፡ አሁን ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመሰገን መሆኑ የሚመሰክሩ ኤርትራውያን ምሁራን በቁጥር እያደጉ ናቸው፡ ይህም ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ 

የአሁኑን የኢትዮጵያ ሁኔታ በተመለከተ ኤርትራውያን ምሁራን ሁለት ዓይነት ሆነዋል፡፡ እነርሱም በአስመራው መንግስት ጐን የተሰለፉት እና በተቃዋሚው ጐራ የሚገኙ ናቸው፡፡ የአስመራው መንግሥት ደጋፊዎች አሁንም እንደበፊቱ የመንግስታቸውን አቋም በማራመድ ኢህአዲግን የሚያስከፋ ሂስ ያዘለ መልእክት ያስተላልፋሉ፤ ይህንን  የሚያደርጉት ያሉትም መንግሥታቸው ከኢህአዲግ መንግስት ጋር፡ የዕውነት ይሁን የማስመሰል፡ ቅራኔ ስላለው ነው፡፡ ለዚህ ዓላማ እንግዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አንዳንድ ችግርና ግፍ ይገልፃሉ፡፡ እነዚህ ምሁራን ሁለቱ መንግሥታት በታረቁ ወይም ታርቀናል ለማለት በወሰኑ ጊዜ አሁን በኢህአዲግ መንግስት ላይ የሚያሰሙት ያሉት ሂስና ወቀሳ እንደማያሰሙት እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል፡፡   

በተቃዋሚው ጐራ ካሉት ምሁራን ደግሞ ብዙዎቹ የኢትዮጵያን ሁኔታ የሚፈርዱት የኢህአዲግ መንግሥት በኤርትራ ነፃነትና ሉዓላውነት ጉዳይ ላይ ባለው ፖሊሲ መሰረት  ነው፡፡ ኢህአዲግ የኤርትራ ነፃነትንና ሉዓላዊነትን በይፋ ስለሚደግፍ፡ ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎቹ ደግሞ ስለማይደግፉ ብቻ በአቶ መለስ ዜናዊ የሚመራው መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚፈፅመው ግፍ ትኩረት አይሰጡትም፡፡ ዲሞክራሲን፡ የሀገሪቱ ሉዓላዊነትንና አንድነትን፡ ሰብዓዊ መብቶችን፡ ኢኮኖሚን፡ ሙስናን ወዘተ… በተመለከተ በውጭ አገር ታዛቢዎች ሳይቀር በተደጋጋሚ የተዘገበውን ሁሉ ጨርሰው ችላ ይላሉ፤ የኢህአዲግ መንግሥት በተለያዩ ዘርፎች በደል ሲፈፅም እየታየ እኚህ ኤርትራውያን የደግፉታል፡፡ ይህ ትልቅ ድክመት ብቻ ሳይሆን ለሁለቱ ህዝቦች መቀራረብና መተባበር ዕንቅፋት የሚሆን ነው፡፡     

ኤርትራውያን ምሁራን የኤርትራን መገንጠል አስመልክቶ ኢትዮጵያውያን ለምን የኢህአዲግ መንግስትን እንደሚወቅሱ አልተረዱም ወይም ለመረዳት አልመረጡም፡፡ ለምሳሌ በ1993 የተካሄደውን ረፈረንደም እንውሰድ፡፡ ረፈረንደሙ ትክክለኛ ሂደት አልነበረም ብቻ ሳይሆን የዕብሪት መልክም ነበረው፡፡ ሂደቱ ቢያንስ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን በሃሳብና በውይይት ደረጃ ማሳተፍ ነበረበት፡ ወሳኙን ድምጽ የሚሰጥ የኤርትራ ህዝብ ቢሆንም፡፡ ሂደቱ እንኳንስ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን፡ የተለያዩ አቋሞች የነበሯቸውን ኤርትራውያን ተቃዋሚዎችንም አላሳተፈም፡፡ ስለዚህ የረፈረንደሙን ሂደት በተመለከተ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ኤርትራውያንም የኢህአዲግን መንግስት ይወቅሳሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኤርትራውያን ምሁራን ይህንን ነጥብ በደንብ ማጤን ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ነጥብ አለመረዳታቸው በዙ አለመግባባት እንዳስከተለ መገመት አያዳግትም፡፡      

ብዙዎች ኢትዮጵያውያን ምሁራን ድሮም ሆነ አሁን፡ ኤርትራና ኢትዮጵያ አንድ አገር መሆን አለባቸው ለማለት በታሪክ ላይ ያተኩራሉ፡፡ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ነበረች፡ ስለዚህም በፈደረሽን ይሁን በሌላ መልክ ከኢትዮጵያ ጋር መቀላቀል አለባት ይላሉ፡፡ የሚያነሱት የታሪካዊ ዝምድና ነጥብ በአብዛኛው ትክክል ነው፡፡ አንዳንድ ኤርትራውያን ምሁራን ሳይቀሩ ከአክሱም ሥልጣኔ ዘመን አንስቶ ሰፊ አሁን ኤርትራ ከሚባለው ቦታ የኢትዮጵያ አካል እንደነበረ ይቀበላሉ፡፡ 
በኢትዮጵያውያን ምሁራን አቋም ያለው ችግር ከዚህ ታሪካዊ ሀቅ ብቻ ተነስቶ ኤርትራ ለመገንጠል መብት የላትም ለማለት አዳጋች መሆኑ ነው፡፡ ታሪክ የተፈመውን ድርጊት ሁሉ ያቀፈ መዝገብ ነው፤ የተለያዩ ዓላማዎች ወይም አቋሞች ለማራመድ ወይም ለመደገፍ የምንገለገልባቸው፡ ውጤት ያስከተሉና ተፅዕኖ ያዘሉ ድርጊቶች አሉት፡፡ አንዳንዱ ድርጊቶች የረዱንና እና በኩራት የምናስታውሳቸው ሲሆኑ፡ አንዳንዱ ደግሞ የማንወዳቸው፡ በሃዘንና በህፍረት የምናስባቸው ናቸው፡፡
ኢትዮጵያንና ኤርትራን በተመለከተ ይህ ችግር አለ፡፡ እርግጥ ነው፡ በረጅሙ ታሪካቸው ኢትዮጵያና ሰፊ የኤርትራ ክፍል አንድ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ባንወደውና ባንኰራበትም፡ ኤርትራ ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን መጨረሻ አንስቶ ለ50 ዐመታት ያህል የኢጣልያ ቅኝ ግዛት እንደነበረችም ታሪክ ነው፡፡ የጣልያን ዘመን ካበቃ በሁዋላ ፈደራሲዮን የተባለው አውታር መቋቋምና መፍረስም ለራሱ ታሪክ ነበር፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ታዲያ የየራሳቸው ሚና ኖሮዋቸው፡ መፈታት ያለባቸው ጥያቄዎችና ችግሮች አስከተለው ፈትነዉናል፤ ገናም እየፈተኑን ነው፡፡
የታሪክ ጥያቄ እንግዲህ ቀላል እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ አስቀድሞ እንደተጠቀሰው ኤርትራውያን የሁለቱን አገሮች ታሪካዊ ዝምድና ማወቅና ማመን ሲገባቸው፡ ኢትዮጵያውያኑ ደግሞ ይህ የታሪክ ዝምድና ሁሉን ጥያቄዎች የሚገዛ፡ የሁለቱን አገሮች አንድነት የሚያስገድድ አድርገው ከማቅረብ መቆጠብ አለባቸው፡፡ አንዳንድ በታሪካዊ ጉዞአችን የደረሱትን ድርጊቶች፡ የማንወዳቸውና የማንኮራባቸው ቢሆኑም፡ ችላ ልንላቸው ትክክል አይደለም፡፡ ችላ በማለትም ችግሮችን አንፈታም፡፡ በተጨማሪም ኤርትራ የተለያዩ ብሄረሰቦች ያቀፈች አገር ሆና፡ ትግርኛ ከሚናገረው በስተቀር የተቀሩት - በተለይ ምዕራባዊው ወገን - ከታሪካዊት ኢትዮጵያ ጋራ የነበራቸው ዝምድና ላላ ያለና የተቆራረጠ (ኢንተርሚተንት) እንደነበረ ማስታወስ ይገባል፡፡  
አንዳንድ ምሁራን አሁንም የችግሩ መፍትሄ የኢትዮጵያና ኤርትራ ፈደራላዊ ውህደት ነው ይላሉ፡፡ በዚህ አቋማቸው ከታወቁት አንዱ የሆነው ፕሮፈሰር ዳኒኤል ክንዴ፡ ከ2009 ዓ. ም.  አንስቶ በሳን ሆዘ ዓመታዊ ስብሰባዎች ባቀረባቸው ፅሁፎችና በ2005 ዓ.ም. ባሳተመው መፅሀፍ ይህንን ሃሳብ በሰፊው አብራርቶታል፡፡ የነዚህ ምሁራን አባባል ቅን በሆነ መንፈስ የቀረበ ቢሆንም የኤርትራ ችግር አመጣጥን የዘነጋ ይመስላል፡፡ ምሁራኖቹ የችግሩ መንስዔዎች በአጼ ኃይለሥላሤ  ጊዜ የተወሰዱት፡ በኤርትራ ላይ የህዝቡንና የአገሪቱን ክብር የደፈረ ሁኔታ የጫኑ፣ በመጨረሻም ፈደራሲዮኑን ያፈረሱ ኢዲሞክራስያዊ እርምጃዎች መሆናቸውን መርሳት የለባቸውም፡፡ ይህንን ለመረዳት “የኤርትራ ጉዳይ” የተሰኘውን የአምባሳደር ዘውዴ ረታ አንጋፋ ስራ መመልከት እጅግ ይጠቅማል፡፡ አሁን ታዲያ ምሁራኖቹ የሁለቱን አገሮች ዝምድና አስመልክቶ በሚያቀርቡት ሃሳብ ዲሞክራስያዊ የሆነ መንፈስና ዘይቤ መጠቀም አለባቸው፡፡ አንድ ሉዓላዊነትን የሚሰርዝ ዕቅድ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ነው ብለው ድርቅ ማለት የለባቸውም፤ እንዲህ የመሰለ አቀራረብ አስፈሪ ነው፤ ለመተማመንና ለትብብር አይረዳም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ተግባራዊነት ሊኖረው የሚችል ዝምድና በአንድ ኮንፈረንስ ክፍት ኮንፈደረሽን ብዬ የገለጽኩት ነው፡፡ ይህ ማለት ሁለቱ ሉዓላዊ አገሮች በኮንፈደረሽን ይዛመዱና፡ ከዚያ በሁዋላ ህዝቦቻቸው በሙሉ ፍላጎትና በሙሉ ነጻነት ዝምድናቸውን በተመለከተ የፈለጉትን ለውጥ ሊያደርጉ ይችላሉ ማለት ነው፡፡ ኮንፈደረሽኑ በጥንቃቄና ለሁለቱ ህዝቦች በሚጠቅም አኳሃን በተግባር ሲውል ደግሞ ህዝቡን በበለጠ ሊያቀራርብ ብቻ ነው የሚችለው፡፡
ኮንፈደረሽኑ ክፍት የሚባልበት ሌላ ትርጉምም አለ፡፡ ኮንፈደረሽኑ በኤርትራና በኢትዮጵያ ብቻ ተቋቁሞ የሚቀር አይደለም፡፡ ለሌሎች የአፍሪቃ ቀንድ አገሮችም በሩ ክፍት ይሆናል፡፡ ሁኔታው በፈቀደ ጊዜ ጂቡቲ፡ ሱዳን፡ ሶማሊያ ወዘተ… የዲሞክራሲ መርሆዎችን በተከተለ ሂደት ኮንፈደረሽኑን ሊቀላቀሉ ይችላሉ፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ኮንፈደረሽን ለአፍሪቃ ቀንድ ኮንፈደረሽን መነሾ ብቻ ይሆናል፡፡    
አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የኢህአዲግን መንግስት ከመጥላትና ለማስወገዱ ካላቸው ጉጉት የተነሳ፡ ኤርትራንና የኢሳያስን መንግስት በሚመለከት የዋህ ወይም ገራገር የሆነ አቋም ይወስዳሉ፡፡ ለምሳሌ የአስመራው መንግስት የመለስን መንግስት ለመጣል የሚረዳቸው ይመስላቸዋል፤ ከዚያም አልፎ የአስመራው መንግስት በኢትዮጵያ አንድነት የሚቈረቈር - እንዲያውም አንዳንዴስ የሁለቱን አገሮች ፌደራላዊ አንድነትን የሚፈልግ -  ሆኖ ሲቀርብ ይታለሉለታል፡፡ ከመሀከላቸው ኢሳያስ አፈወርቅን በይፋ የሚመርቁም በአንድ ወቅት ብቅ ብለው ነበር፡፡ እነዚህ ምሁራን የነዚያ የኢህአዲግን መንግስት የሚወድሱ ኤርትራውያን ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያዊ ቅጂ ናቸው፡፡ የኤርትራውያኖቹ ውዳሴ-ኢህአዲግ ለሁለቱ አገሮች ትብብር እንደማያገለግል ሁሉ፡ የኢትዮጵያውያኑ ሻዕቢያን ማሞገስም አይረዳም፤ እንዲያውም ዕንቅፋት ይሆናል፡፡
አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ኢህአዲግን - በተለይ ህ.ወ.ሓ.ትን - የኤርትራ መሳርያ ወይም ለኤርትራ ጥቅም የቆመ አድርገው ያቀርቡታል፡፡ ይህ አባባል ሃቅነት የለውም፡፡ እርግጥ ነው በአቶ መለስ የሚመራው ህወሐት (ኢህአዲግ) ኤርትራ እንድትገነጠል ሙሉ በሙሉ ተባበረ፣ እንዲያውም መገንጠሉን በማራመድ ላይ ተሳተፈ፡፡ ይህንን ያደረገው ግን ለራሱ ጥቅም ብሎ ነው እንጂ ለኤርትራ ህዝብ አስቦ አይደለም፡፡ የኤርትራ መገንጠል ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄር ፖለቲካ ለማሰተጋባትና ለማጠናከር፣ እንዲሁም ላንዳንድ የሩቅ ዓላማዎቹን መንገድ ለመጥረግ ለህወሓት አስፈላጊ ነበር፡፡ ይህንን ጉዳይ ለመረዳት አቶ አብርሃም ያየህ “የኤርትራ ረፈረንደምና ነፃነት አፈፃም ሲገመገም“ በሚል አርእስት በህዳር 1994 ወይም ዲሰምበር 2001 የፃፈው አንቀፅ ያግዛል፡፡ ኤርትራ ውስጥ ከዚሁ የተጠቀመና ገናም የሚጠቀም አካል ቢኖር አገሪቱን በኃይል ጨቁኖ እየገዛ ያለ በኢሳያስ አፈወርቅ የሚመራው ቡድን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ የኤርትራን ህዝብ ከኢህአዲግ ተጠቃሚ አድርጎ ማቅረብ ስህተት ብቻ ሳይሆን ጐጂም ነው፤ ሁለቱን ህዝቦች ለማቀራረብ ለሚደረገው ጥረት ዕንቅፋት ይፈጥራል፡፡  

አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በደርግ ዘመን እንደነበረው ሁሉ በተግባር የኤርትራን አንድነት የሚፈታተን አቋም ያሰማሉ፡፡ የደርግ መንግስት በ1987 ባወጣው ፖሊሲ ኤርትራን ወደ ሁለት ራስገዞች ከፋፍሎ አንድነቷን ለማፍረስ ቃጣ፡፡ ይህ በፖለቲካ እንቅስቃሴ ተሰማርቶ የነበረውን ኤርትራዊ አሳዘነ፤ ተቃውሞዉንም አጠነከረ፡፡ በአሁኑ ጊዜ አንዳንዴ የምንሰማው ዓሰብና አከባቢዋ ለኢትዮጵያ ይሰጥ የሚል ክርክር የኤርትራን አንድነት የሚፈታተን ነው፡፡ በፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ኤርትራውያን በኤርትራ አንድነት ቀናኢ ናቸው፤ በዚህ ከኢትዮጵያውያን አይለዩም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ነገር ማስታወስ እወዳለሁ፡፡ በአንድ ወቅት በ40ዎቹ ኤርትራን ወደ ሁለት የመክፈል ዕቅድ ነበር፤ በዚያን ጊዜ የተለያዩና፡ ተፃራሪ አቋሞች የነበሯቸው የኤርትራ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ዕቅዱን ተቃወሙት፡፡ እንዲያውም ፈደረሽን የሚለውን ነገር እንደ መሃከለኛ መፍትሄ ፓርቲዎቹ በሙሉ የተቀበሉት ኤርትራ እንዳትበታተን በማለት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት በኤርትራውያን መከበር እንዳለበት ሁሉ፡ የኤርትራ አንድነትም በኢትዮጵያውያን መከበር አለበት፡፡
የኮንፈደረሽን ሃሳብ ቀርቦ እያለ ዓሰብ ለኢትዮጵያ ይሰጥ ብሎ መጠየቅ የማያስፈልግ ብቻ ሳይሆን ከኤርትራ ጋር ዝምድና አለመፈለግን የሚያመለክት ይመስላል፡፡ የሁለቱ አገሮች ኮንፈደረሽን ኢትዮጵያም ኤርትራም ምፅዋን፡ ዓሰብን እና ሌሎች በቀይ ባህር ዳርቻ ያሉትን ወደቦች በሙሉ በእኩልነት ሊጠቀሙባቸው ያስችላል፡፡ ይህ ሲታወስ እንግዲህ ዓሰብና አከባቢው ለኢትዮጵያ ይሰጥ ማለት ለብዙ ኤርትራውያን፡ ከኤርትራ ጋር ምንም ዝምድና አንፈልግም፤ ዓሰብ ብቻ እጃችን ትግባ እንጂ የተቀረችው ኤርትራ ገደል ብትገባም ግድ የለንም የሚል መልእክት የሚያስተላልፍ መስሎ ይታያል፡፡ እውነቱን ለመናገር ይህ አባባል በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ምሁራኖቹ ራሳቸው አጥብቀው የሚከራከሩለት ታሪካዊ ዝምድናን ሳይቀር የሚክድ ይመስላል!! ይህ ከባድ ዕንቅፋት መሆኑ ኢትዮጵያውያን ምሁራን እነዲገነዘቡት ያስፈልጋል፡፡       
ብዙ ኢትዮጵያውያን፡ ምሁራንን ጨምሮ፡ ኤርትራን እንደ ሉዓላዊት ሃገር የሚያውቁ መሆናቸውን ለመግለፅ ወይም ለማመልከት የቸገራሉ፤ ፈቃደኞች ያለመሆናቸው በተለያየ መልክ ይመሰከራል፡፡ የዚሁ ችግራቸው መሰረት የረፈረንደሙ ሂደት ትክክል አለመኖሩ ነው፡፡ አስቀድሞ እንደተጠቀሰው፡ ረፈረንደሙ በትክክል እንዳልተካሄደ ሀቅ ነው፡፡ እኔም ሂደቱ ልክ እንዳልነበረ በወቅቱ በተለያዩ ፀሁፎች ገልጫለሁ፡፡ ረፈረንደሙ ትክክል አይሁን እንጂ፡ አሁን የኤርትራ ከኢትዮጵያ መለየትና ሉዓላዊት ሃገር መሆን ዕውነታ ሆኗል፡፡ ይህንን ዕውነታ አለመቀበል ተግባራዊነት የሌለው ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ጦርነት ሊቀሰቅስ የሚችል አደገኛ አቋም ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ምሁራን፡ ምንም እንኳን ስለ ረፈረንደሙ ያላቸው ሂስና ቅሬታ ትከክል ቢሆን፡ ይህንን ዕውነታ መቀበል አለባቸው፤ ከዚህ ዕውነታ ሲነሱ ነው ከኤርትራውያን ጋር መግባባትና መተሳሰር እያበጁ ለሁለቱ አገሮች ዝምድና ገንቢ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ የሚችሉ፡፡ 
ይህ የረፈረንደም ጉዳይ አንድ መሰረታዊ የሆነ አስተሳሰባችንን የሚመለከት ነጥብ ያስታውሰኛል፡፡ በአንድ ስብሰባ ላይ ያጋጠመኝን ልንገራችሁ፡፡ ስለ አገሮቻችን ዝምድና፡ ስለ ኮንፈደረሽን አስፈላጊነት ጨምሮ፡ ንግግር ካደረግሁ በሁዋላ አንድ ኢትዮጵያዊ ወንድሜ ተነስተው ኮንፈደረሽን የሚባለው ነገር አይጥመኝም፣ ምክንያቱም ኮንፈደረሽን ከኤርትራ ጋር መቀበል ማለት የተካሄደውን ረፈረንደም ትከክል ነበር ብሎ ማፅደቅ ነውና ብለው ተቃወሙኝ፡፡ ረፈረንደሙ ትክክል ባይኖርም የኤርትራ ሉዓላዊ ህላዌ ዕውነታ ሆኗል፡ ከሚል ተነስቼ አስቀድሜ ከጠቀስኳት ነጥብ ጋር የምትመሳሰል መልስ ሰጠሁ፡፡ 
ኮንፈደረሽን ከተቀበልን በ1993 ዓ. ም - ማለት ከ18 ዓመታት በፊት - ያለአግባብ የተካሄደው ረፈረንደም ትክክል ነበር እያልን ነው ብሎ ኮንፈደረሽንን መቃወም ቱክረቱ ወደ ፊት ሳይሆን ወደ ሁዋላ የሆነ አመለካከትን ያንባርቃል፡፡ የኮንፈደረሽን ሃሳብ ወደ ፊት ከሚያይ መንፈስ መመዘንና መስተናገድ አለበት፡፡ በሌላ አነጋገር፡ ሁለቱ አገሮች ለወደፊቱ እንዲጠነክሩና እንዲያድጉ፡ ህብረተሰቦቻቸውም እንዲበለፅጉ በማለት ነው ኮንፈደረሽንን የምንደግፈው፡፡ ረፈረንደሙ ትክክል አለመኖሩን እያመንን ቱክረቱ ወደ ፊት በሆነ መንፈስ ኮንፈደረሽንን እንቀበላለን፡፡ ብዙ ጊዜ ያለፈውን ማወቅ አስፈላጊ የሚሆነው እኮ ችግሩንና የችግሩን አመጣጥ ለመረዳት፡ ከተደረገው ጥፋት ለመማር እና የተፈጸመው አለአግባብነት እንዳይደገም ለማረጋገጥ ነው እንጂ ስለ አንድ የአሁኑ ወይም የወደፊት ጉዳይ አቋም ለመወሰን አይደለም፡፡    


ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን ምሁራን ባለፉት ዓመታት አሉታዊ አስተዋጽኦ ለማድረግ ያስገደዱዋቸው ድክመቶች - ሞራላዊና ኣእምሮአዊ - ማጤን ይገባቸዋል፡፡ድክመቶቻቸውን ሲያጤኑ ባሁኑ ወቅት አጋጥመዉን ስላሉት ጥያቄዎች በእውነተኛነት፡ በቅንነትና በትህትና ተመራምረው ችግሮቹን ለመፍታት በሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦዋቸውን ሊያሳድጉ ይችላሉ፡፡ በሁለቱ አገሮቻችን መሀከል የአሁኑ የዓለም ሁኔታ አስፈላጊ የሚያደርገው፡ እንዲያውም የሚያስገድደው፡ ዝምድና እንዲዋቀር ዘዴዉን በማፈላለግ ሃላፊነታቸውን በብቃት ሊወጡ ይችላሉ፡፡

ይህንን ለማድረግ እጅግ ሊያግዙ ከሚችሉት ነገሮች አንዱ የኢትዮጵያና ኤርትራ የውይይት መድረኮች መቋቋም ነው፡፡ በዚህ መድረኮች ሃሳብ ለሃሳብ ኤየተለዋወጡ ከርስ በርስ መማር ይቻላል፤ እንዲሁም በየጊዜው እየተገናኙ በበለጠ ሲተዋወቁ መተማመኑ ያድጋል፤ ይህ መተማመንም ለሁለቱ ህዝቦች መቀራረብ እጅግ ይረዳል፡፡       

 ይህንን ንግግር ወይም ሀተታ ከመደምደሜ በፊት አንድ ነጥብ ልጥቀስ፡፡ የኢትዮጵያና ኤርትራ የውይይት መድረኮች ዓላማን በተመለከተ ይዘቱ ፖለቲካ የሌለው ይሁን የሚሉ አንዳንድ ተንቀሳቃሶች - ምሁራን ጨምሮ - አጋጥመውኛል፡፡ አንዳንዱማ ፈደረሽን፡ ኮንፈደረሽን የሚለው ክርክር አይኑር፤ ግኑኝነቱ ባህላዊና ማህበራዊ ብቻ ይሁን ይላል፡፡ ይህ በመሰረቱ የተሳሳተ አመለካከት ይመስለኛል፡፡ የችግሮቻችን ዋና መሰረት እኮ ፖለቲካ ነው፡፡ ይህንን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ችግራችን ወይም የችግራችን መንስዔ ፖለቲካ በመሆኑ ሁለቱ አገሮች እንዴት ይቀራረቡ? እንዴት ይዛመዱ? የሚለው ጥያቄ መሰረታዊ አስፈላጊነት አለው፡፡ ለምሳሌ እኔ በበኩሌ፡ ብዙዎቻችሁ እንደምታውቁት፡ አስቀድሜም እንደጠቀስኩት፡ በአሁኑ ታሪካዊ ወቅት ለሁለቱ አገሮች ተገቢ (ኖርማል) የሆነ የሰላም ጉርብትና በፖለቲካዊ ይዘቱ በሁለቱ አገሮች አንዳንድ አስተዳደርን የሚመለከቱ ለውጦች ከተደረጉ በሁዋላ የሚዋቀር ኮንፈደረሽን ነው የሚል አቋም አለኝ፡፡ ዝምድናው ይህ ወይስ ሌላ ይሁን? ኮንፈደረሽንስ እንዴት ይምጣ? ለዚሁ መሟላት ያለባቸው ቅድመ-ሁኔታዎችስ ምንና ምን ናቸው? በሚሉትና በሌሎች ጥያቄዎች ልንለያይ እንችላለን፡፡ ፖለቲካ የሌለው የኤርትራና ኢትዮጵያ የወዳጅነት ወይም የውይይት መድረክ የሚለው ሃሳብ ግን አጉል ነው፤ ቅንነት ያለውም አይመስለኝም፡፡

ለህዝቦቻችን ጥቅም የማያስቡ፡ የህዝቦቻችን ትስስር የማይፈልጉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች አሉ፤ እነዚህ ኃይሎች ባለፉት ዓመታት በሁሉም ደረጃ ተባብረዋል፤ አሁንም እየተባበሩ ናቸው፡፡ ኃይልና ገንዘብ ስላላቸው ለህዝቦቹ ሃቀኛ ትብብር ለሚጥሩት ምሁራን ዕንቅፋት ሊፈጥሩባቸው ይችላሉ፤ በዚህ ረገድ የማይናቅ አቅም በሚያንባርቅ የድርሰትና የቅስቀሳ ስራ የሚተባበሩዋቸው ምሁራንም አላጡም፡፡ ስለዚህም የሁለቱን ህዝቦች ትስስር ለማጠናከር የሚሹ አትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ምሁራን መተባበር አለባቸው፡፡ ይህንን ለማድረግም በተለያየ መስክ መዛመድ፡ በተለያዩ መድረኮች መገናኘትና መወያየት አለባቸው፡፡ ሃሳብ መለዋወጥ፡ ዕውቀት ለማዳበር መተጋገዝ እና ገንቢ በሆነ ሂስ እየተራረሙ በአእምሮም በህሊናም አብረው እንዲጐለብቱና እንዲያድጉ ያስፈልጋል፡፡      

አንዳንዱ ምሁር፡ ኢትዮጵያዊም ኤርትራዊም፡ በሞራል ሲቀዘቅዝ፡ አንዳንዱም ሲወድቅ አስተውያለሁ፡፡ ለኔ እንደሚመስለኝ የሞራል ውድቀት የሚመጣው ብዙውን ጊዜ ችግሮቹን - ታሪካቸውን ጭምር - ካለመረዳትና ስለመፍትሄው በጥናት ላይ የተመሰረተ ራዕይ ካለመኖር ነው፡፡ ስለዚህ አስቀድመው የተጠቀሱትንና ሌሎችን ድክመቶች አርመውና  አስወግደው፡ ከላይ የተነሱትን ጥያቄዎችና ጉዳዮች በሚገባ አጥንተው፡ መፍትሄን በተመለከተ ብሩህ ራዕይ ገንብተው፡ ያንን ራዕይ ለመተግበር ደግሞ ሰትራተጂና ስልት በንቃትና በጥንቃቄ ሲቀይሱ መተማመኑ - ኦፕቲሚዝም - ያጋግማል፤ እያደረም ይጠነክራል፣ ያድጋል፡፡ ብዙዎቻችን ታሪካችን በብዙ ጐኖቹ ትብብራችንን ይፈቅዳል፣ የዓለም ሁኔታ ይህንኑ ያስገድዳል፣ ህዝቦቻችን ደግሞ ወንድማማችነታቸውን በተግባር አስመስክረዋል ብለን እናምናለን፡፡ እንዲህ ከሆነ ታዲያ የሁለቱ ሃገሮች ሁለ-ገብ ዝምድና ተግባራዊነት ያለው ራዕይ መሆኑ ልንጠራጠር ይገባል?

 የኢትዮጵያና የኤርትራ ምሁራን፡ ይህ ራዕይ እውን ይሆን ዘንድ፡ መተባበር እንዲጀምሩ ወቅቱ ሃላፊነት እያሸከማቸው መሆኑ መገንዘብ አለባቸው፡፡       

ዋቢ ጽሁፎች
ጌታቸው ረዳ፤ ሓይካማ (ሳን-ሆዘ፡ ካሊፎርኒያ፤ ሃምሌ 2002 ዓ.ም በኢት. አቈጣጠር)

ዘውዴ ረታ፣ የኤርትራ ጉዳይ 1941 - 1963 (አዲሰ አበባ፡ 1998)

አምሳሉ ገብረዝጊ ገብሩ፤ የኤርትራ መዘዝ (አዲስ አበባ፤ ጥር 2002 በ ኢት. አቈ.)
አንዳርጋቸው ጽጌ፤ ነጻነትን የማያውቅ “ነጻ አውጭ”  (አዲስ አበባ፤ ጥር 1997)
አብርሃም ያየህ፤ “የኤርትራ ረፈረንደምና ነፃነት አፈፃም ሲገመገም“ ፤ (ህዳር 1994) ዲሰምበር 2001)
ዳኒኤል ክንዴ፣ የኢትዮጵያና ኤርትራ ፌደረሽን አስፈላጊነት (ሳን ሆዘ 2009) 
 Bahru Zewde, “The Intellectual and the State in Twentieth Century Ethiopia”, in Harold G. Marcus (ed.), New Trends in Ethiopian Studies (Papers of the 12th International Conference of Ethiopian Studies) (Lawrenceville, NJ: The Red Sea Press, 1994).
Daniel Kendie, The Five Dimensions of the Eritrean Conflict 1941-2004: Deciphering the Geo-Political Puzzle (Gaithersburg, MD: Signature Book Printing, Inc. 2005).
Ghelawdewos Araia, Ethiopia: The Political Economy of Transition, (Lanham, Maryland:  University Press of America, 1995)
Negussay Ayele, “Legitimacy, culture of political violence and violence of culture in Ethiopia”, in Jean E. Rosenfeld (ed.), Terrorism, Identity and Legitimacy: The Four Waves theory and political violence, (New York: Routledge, 2011)
Paulos Milkias, Haile Selassie, Western Education and Political Revolution in Ethiopia, (Youngstown, New York: Cambria Press, 2006)
        *** ይህ ፅሁፍ ለማንኛውም ውይይትና ተችት ክፍት ነው:: posted on www.ethiopiansemay.blogspot.com





   _____________________________________________________________



No comments: