Wednesday, June 23, 2021

“ኢትዮጵያ ውስጥ ጄኖሳይድ አልተፈጸመም” የሚባለው እውነት ነውን? ተሻለ መንግሥቱ Ethiopian Semay

 

“ኢትዮጵያ ውስጥ ጄኖሳይድ አልተፈጸመም” የሚባለው እውነት ነውን? 

ተሻለ መንግሥቱ 

Ethiopian Semay

6/23/2021

 

“ዳንኤል በቀለ” ዛሬ የፕሮፌሰሩን ንግግር ደግፎ ሲናገር ስሰማው እውነትን እየቀበሩ ሀሰትን የሚያነግሡ ሰዎች እየበዙ መምጣታቸው አሳሰበኝ፡፡” 

በቅርቡ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ፍጂት (ጄኖሳይድ) እንዳልተካሄደ ሲናገሩ ተደምጠው ያንን ንግግራቸውን ሚዲያዎችና ግለሰቦች በክፉም በደግም ማለትም በመቃወምም በመደገፍም ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ እኔ እውነቱን ለመናገር በሤራም ሆነ በፖለቲካ ትንታኔ በቂ ዕውቀት ባይኖረኝም በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአማሮች ላይ የዘር ፍጂት ወይም ጄኖሳይድ አልተካሄደም ብዬ ለማመን የማንንም ባርኮትና ይሁንታ አልጠብቅም፤ እንደዚያ ባደርግ በሰው ደምና አጥንት የተራቀቅሁና የተዘባነንኩ ያህል ይሰማኛል፡፡ አሟሟታቸውን በካድኩት ወገኖቼ ደምና አጥንትም እንደቀለድኩ ነው የምቆጥረው፡፡ መዋሸት ለምን ያስፈልጋል? ማንን ከኃላፊነት ለማዳን? ምንስ ትርፍ ሊገኝበት? ጄኖሳይዱን የሚያካሂደው ወገን አምኖበት ግዳዩን በጠራራ ፀሐይ በይፋ እያስቆጠረ ሳለ ይህን ገሃድ እውነት መካድ የምን አትርሱኝ ነው? እኔን የሚገዛኝ እውነት እንጂ ሰዎች ተሰብስበው “ይህን ወሰኑ፤ ይህን አልወሰኑም” የሚለው አይደለም፡፡ ያ ዓይነቱ የጄኔቫና የኒውዮርክ ሞልቃቃነት አንድም አማራ ከኦነግ ሠይፍና ከሾኔ ሜንጫ አላዳነም፤ አያድንምም፡፡ እነዚህ ቅንጡ ሰዎች ሼራተንና ሂልተን ቁጭ ብለው “እነሱ ስላልወሰኑ ጄኖሳይድ ተካሄደ ማለት አንችልም” ማለታቸው ራሱ ሌላ ጄኖሳይድ እየጠሩ ነውና “ቀባጭ አማት ሲሶ ብትር አላት” እንዲሉ መጽሐፉ ፊት ባይነሳኝ ኖሮ እነሱም የቀባጭ ምሣቸውን እንዲያገኙ ልመኝላቸው በወደድኩ - ግን ይቅር ግዴለም፡፡ በምንም ምክንያት የፈጠጠ እውነትን መካድ ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀልና ኃጢኣትም ነው፡፡ ዳንኤል በቀለን ዛሬ የፕሮፌሰሩን ንግግር ደግፎ ሲናገር ስሰማው እውነትን እየቀበሩ ሀሰትን የሚያነግሡ ሰዎች እየበዙ መምጣታቸው አሳሰበኝ፡፡

 

የዘር ፍጂት በአጭሩ አንድ ነገድ ወይ ጎሣ በሌላው ጎሣ ወይም ነገድ ላይ ጥላቻንና በቀልን አሳድሮ ከምድረ ገጽ ሊያጠፋው ይፈልግና ከማሰብ ጀምሮ በማቀድ፣ ያሰበውን በመሰሎቹ መሃል በመቀስቀስና በማነሳሳት፣ ያነሳሳውን ወገኑን በጠላው ነገድ ላይ እንዲዘምት በማዘጋጀት፣ የዕልቂት ቅድመ ዝግጅቶችን በማከናወን በመጨረሻም ሃሳብና ዕቅዱን ወደተግባር ለውጦ ግዳይ ማስቆጠር ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ብዙ መራቀቅንና ፍልስፍናን የሚጠይቅ ጉዳይ አይደለም፡፡ የአውሮፓና አሜሪካ ምሁራን ተሰብስበው በጄኖሳይድ ላይ ቢወያዩና ቢከራከሩ የሚሊዮኖች አማሮችን በትግሬና ኦሮሞ አክራሪዎች መጨፍጨፍ ሊመልሱት አይችሉም፡፡ ያልተነካ ግልግል ያውቃል ነውና እነዚህ “ምሁራን” የወገናቸውን ደም በማይረባ ፍልስፍና ሲለውጡት ሳይ ይሁዳ በ30 ብር ክርስቶስን የሸጠው በገንዘብና በርኩስ መንፈስ የመታወር ትርዒት ነው ትዝ ያለኝ፡፡ ይገርማል፡፡ በሰው ቁስል እንጨት መስደድ ለካንስ ይህን ያህል ቀላል ኖሯል፡፡ መማር የኅሊና  መታወርን ብቻ ሳይሆን የልብ መደፈንንም ማስከተሉን በነዚህ ሰዎች ተገነዘብኩ፡፡ እንኳንስ መማር ቀረብኝ!! ከዘግናኙ ተሞክሮኣችንና ከዐይናችን በላይ ሲሆኑ ሌላ ምን ይባላል? “ሩዋንዳና ኮሶቮ ብቻ ነው የዘር ፍጂት እንደተካሄደ የሚታመነው” ብለው የፈረንጅ አሽከርነታቸውን በአደባባይ አሰጡት፡፡ ፈረንጅን ማምለካቸው መብታቸው ነው፤ በሕዝብ ደም መቀለድ ግን አይችሉም፡፡

 

 

አንዳንዴ መማር ያደነቁራል፡፡ ከመማር የሚመነጭ ድንቁርና ደግሞ ካለመማር ከሚመጣ ድንቁርና የከፋ ጉዳት እንደሚያደርስ ከዶክተር ዳንኤል በቀለና ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ተረድቻለሁ፡፡ መማር አንዳንዴ ብልቃጥ ውስጥ የሚቀረቅር ይመስለኛል፡፡ እጅግ ብዙ መማር በብልቃጥ ውኃ ውስጥ የሚገኙ የዓሣ ዝርያዎችን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ይጠራ ሳያስብል አይቀርም፡፡ እውነት ነው የምላችሁ መማር እንደዚህ የሚያደነቁር ከሆነ ማይምነታችን ተፈልጎ የማይገኝ ወርቅ ነው፡፡ በመተከል፣ በወለጋ፣ በበደኖ፣ በአርባ ጉጉ፣ በአሰቦት፣ በአጣዬ፣ በከሚሴ፣ በሸዋ ሮቢት፣ በቤንሻንጉል፣ በባሌ፣ በሐረር፣ … በአማራነታቸው ምክንያት የሞቱ ዜጎች ደምና ዐፅም በገዳዮች ብቻ ሳይሆን የግድያውን ዓይነት በሚክዱ ሰዎች የእንቅልፍ ሰዓት እየመጣ ዕረፍት ይንሳቸው፡፡ ሁለተኛ ግድያ እኮ ነው!!

 

የት ሆፒታል እንደሆነ አላውቅም፡፡ አንድ ታማሚ በህክምናው ዓለም የሀኪሞች ቋንቋ “ኢክስፓየር” ያደርግና ወደ ሬሣ ክፍል ይላካል፡፡ በተላከ በማግሥቱ የሬሣ ክፍል ሠራተኛው ያን በድን ከፍኖ ቤተሰብ ወዳመጣው ሣጥን ሊከተው ሲል ሟቹ ድንገት ከሞት ይነቃል፡፡ እንደነቃም በድንጋጤ “ምንድን ነው? ምን እያደረግኸኝ ነው?” በማለት ከፋኙን ይጠይቀዋል፡፡ ከፋኙም ሥራውን ሳያቋርጥ “ሞተህ ነዋ! እየገነዝኩህ እኮ ነው” ይለዋል፡፡ ከሞት የነቃው ሰውዬም “አሃ! አሁንማ ከሞት ተመለስኩ አይደል? ተወኝ እንጂ!” በማለት ይከራከረዋል፡፡ ሬሣ ገናዡም “ወይ ሞኞ! አሁን አንተ ከዶክተሩ ልትበልጥ ነው? በል ሞተሃል ተብለሃል አርፈህ ተገነዝ?” አለው ይባላል፡፡

 

እነዚህ “ምሁራንም” (ብርሃኑና ዳንኤል) ስንትና ስንት አማሮች ወደውና ፈቅደው ባልተፈጠሩበት ማንነታቸው ምክንያት አንገታቸው ተቆራርጦ፣ ጭንቅላታቸው ተፈልጦ፣ ወገባቸው ተጎማምዶ የዐውሬ ሲሣይ ሆነው መቅረታቸውን፣ እንደየእምነታቸው የጸሎት ፍትሃት በክብር እንኳን እንዳይቀበሩ እንደአልባሌ ቆሻሻ በግሬደር በአንድ ጉድጓድ ውስጥ መቀበራቸውን ልቦናቸው እያወቀ ለተቀማጭ ሰማይ ቅርብ ነውና እነሱና የነሱ የሆነ ስላልሞተ ብቻ ይህን መሳይ ወራዳ መልስ ሲሰጡ ይስተዋላሉ፡፡ የኛ የብዙዎቻችን ችግር የሌሎችን ችግር መረዳት አለመቻላችን ነው፡፡ አማሮች የተገደሉት በአማራነታቸው እንጂ በሰውነታቸው አይደለም፡፡ ይህንን እውነታ መካድ መማር ሳይሆን መደደብ ከዚያም ባለፈ ለጥቅም ወይም ለዓላማ አንድነት ሲባል የሚዘፈቁበት ኅሊናን በመሸጥ አሻሮ ይዞ ወዳለው የመጠጋት ፍላጎት የሚፈጥረው ቅሌት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ፍጅት በአማራ ላይ መታወጁንና ብዙ አማራ ማለቁን ለመረዳት የብርሃኑ ወይም የዳንኤል ወይም እነሱ የሚያመልኩት የጄኔቭ ጉባኤን ቡራኬ አይጠይቅም፤ ምን አገባቸውና? የዘር ፍጅትን ካላወቁ ከኛ ይማሩ፡፡ ምንም ምርምር አይሻም - “ነፍጠኛን (አማራን) አጥፍተን በኦሮሙማ የገዳ ሥርዓት የሚመራ ታላቁን አባት ሀገር ኦሮምያን እንገነባለን!” ብሎ በመነሳት በየቦታው የሚገኝን አማራ የሚያርድና የሚያሳርድ አክራሪ ኦሮሞ መኖሩ ለጄኖሳይድ መኖር ዋናው መገለጫ ነው፤ ከተፈለገም የወደቀውን ፀረ-አማራ የሕወሓት ማኒፌስቶ መጨመርም ይቻላል፡፡ ከዚህ በተረፈ በሰው ደም የሚቀልድ ከዚህ የጎመዘዘ ቀልድ ቢወጣ ይሻለዋል፡፡ ችግራችን የፍልስፍና ሳይሆን የኅልውና ነው፡፡ አጓጉል ለመሰልጠኑ የቄሱ ሚስት ትበቃናለች፡፡ የርሷ መሰልጠንስ በመጽሐፍ ማጠብ ብቻ ነውና ቀላል ነው፡፡ የነዚህ ግን በላኪዎቻቸው አስገዳጅነት ዓላማቸው በሰው ደምና አጥንት መቆመር በመሆኑ ከሁሉም ወንጀሎች ይከፋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1968 ጀምሮ በዐዋጅ የፀና የዘር ፍጂት አለ - ሊያውም በ40 እና 50 ሚሊዮን በሚገመት ሕዝብ ላይ፡፡ ስለዚህ ምሁሮቻችን ሆይ እባካችሁን ወደኅሊናችሁ ተመለሱ፤ ደግሞም ስለምንም ምንነት ይበልጥ ለማወቅ አንብቡ፡፡ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ትሉ የለም?….

No comments: