Sunday, October 6, 2019

ቀላሉን ድክመት ማሶገድ ያልቻለ ከባዱን ችግር አያሶግድም፤ ቀጠሮ ይከበር! By Agere Addis መስከረም 26 ቀን 2012 ዓም (03-10-2019) Posted Ethio Semay


ቀላሉን ድክመት ማሶገድ ያልቻለ ከባዱን ችግር አያሶግድም፤
ቀጠሮ ይከበር!
By Agere Addis
መስከረም 26 ቀን 2012 ዓም (03-10-2019)
Posted Ethio Semay
የሰው ልጅ አቅምና ችሎታ የሚለካው ትንሽዋን ችግር ወይም ድክመት ማሶገድ ሲችል ነው።ያንን በተግባር ያላሳዬ ለትልቁ ችግር ብቃት አለው ብሎ ለመገመት ያዳግታል።በመቶ ሜትር እሩጫ ላይ ያለከለከ እሩዋጭ ማራቶንን ይዘልቃል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።በትንሽዋ ተፈትኖ ወድቋልና!
በተመሳሳይ እኛ ኢትዮጵያውያን ብዙ ከባድ አገራዊ ችግሮችን ለማሶገድ ብዙ ጥረትና ድካም እናደርጋለን፤ከስኬቱ ውድቀቱ እያመዘነብን ሄደ እንጂ ችግሩን እዬቀረፍነው አልመጣንም። ምክንያቶቹ ብዙ ቢሆኑም ዋናው ግን በራስ አለመተማመን፣ ቁርጠኝነት፣ ቃልኪዳንና ቀጠሮ አለማክበር ዋናዎቹ ናቸው።እነዚህ ደግሞ በራስ ውሳኔ የሚሻሻሉና የሚወገዱ ድክመቶች ናቸው።ከፍተኛ ትምህርት ወይም ዕድሜን የሚጠይቁ እውቀቶች አይደሉም።የግል ግንዛቤን እንጂ!
በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ላነሳና እንዲወገድ የምሻው ነገር የቀጠሮ ሰዓትን ባለማክበር ዙሪያ የሚታይብንን ድክመት ነው።ጊዜ ውድ ነው፣ጊዜ ወሳኝ ነው።ጊዜ የዕድሜ መለኪያ አሃዝ ነው።በጊዜ ሊያገኙት ወይም ሊያጡት የሚችሉት ነገር ብዙ ነው።መፈጠርና መወለድ መኖርና መሞት የጊዜ ድርሻ ነው።ሁሉም በጊዜው የሚከናወን ሂደት ነው።የእለታዊ ኑሮዋችን በጊዜ ክፍፍል ካልተጠናቀቀ ዕለቱ ትርጉመቢስ ይሆናል።አንድ ቀን የእንቅልፍ፣ የስራ፣የእረፍት፣የምግብ፣የቀጠሮ ሰዓቶች የሚከናወኑበት ዕለት ነው።ቀኑ በነዚህ ክንውኖች ይጠናቀቃል።ሁሉም እለታዊ ክንውን ተራውን ጠብቆ ይጠናቀቃል፣ መጠናቀቅም አለበት።ፈረንጆች የጊዜን ዋጋና ትርጉም ሲገልጹ ጊዜ ወርቅ ነው(Time is Gold)ወይም ጊዜ ገንዘብ ነው  (Time is Money)ይሉታል።እኔ ግን ከዚያም በላይ ነው ብዬ አስባለሁ፤ጊዜ ህይወት ነው።

ኢትዮጵያውያን እንደ አለመታደል ሆኖ የቀጠሮ ነገር አይሆንልንም።ሰዓት አናከብርም።ሆኖም  በውድ ገንዘብ የገዛነው  ሰዓት በጃችን ላይ አስረናል ግን ትርጉምና ጥቅሙን የተረዳነው አይመስለኝም።ወይም ለቀጠሮ የማይሰራ ለጌጥ ያሰርነው አድርገን ቆጥረነዋል ማለት ነው። ሚዜው ብቻ ሳይሆን ሙሽራው የሰርጉን ቀን ፕሮግራም አክብሮ በቦታው አይገኝም፣የተጋባዡ ነገርማ አይነሳ!በሽተኛው የሓኪም ቀጠሮውን አክብሮ በሰዓቱ አይደርስም፤የአገር ጉዳይ ለመወያዬትማ ከሆነ ስብሰባ ከተጠራበት ሰዓት ሁለት ሰዓት ዘግይቶ መድረስ መለመዱ ብቻ ሳይሆን የሚኮሩበት ባህል እዬሆነ መጥቱዋል። የስብሰባው ተሳታፊ ሳይሆን የስብሰባው አዘጋጅና ተናጋሪ እንግዳ ከተሰብሳቢው ዃላ ዘግይቶ እንጂ ቀድሞ አይደርስም።ታዲያ ዘግይቶ በተጀመረ ስብሰባ በቂ ውይይት ሳይደረግ የአዳራሹ ቦታ ሳይዘጋ” በሚል ሩጫ ለብ ለብ የሆነ ፈረሰኛ ውይይት ይደረግና እልባት ሳይኖረው መበተን የተለመደ ነው።

“የአበሻ ቀጠሮ” በሚለው ደካማ ምክንያትና ስያሜ እራሳችንን ከአበሻነት  ነጥለን አውጥተን የሌሎች አድርገን የማዬት ይዘነው የመጣነው ልክፍት  መታረም አለበት።በተለይ እውጭ አገር የምንኖረው ብዙዎቻችን ለምንኖርበት አገር ሕዝብ የቀጠሮ ባህል ባዳና እንግዳ ነን። ስብሰባ ሲጠራ ” አበሻ በሰዓቱ አይመጣም፣ለምን ባዶ አዳራሽ ውስጥ እጎለታለሁ” በሚል ሰበብ ዘግይተን እንደርሳለን።ስብሰባ ትልቅ አገራዊ ወይም ማህበረሰብአዊ ጉዳይን የሚመለከት፣ችግርን ለማሶገድ የሚደረግ  ሲሆን በቦታውና በጊዜው የመገኘት ግዴታ ይጠይቃል።ሆኖም ግን በተደጋጋሚ በዬቦታው  ሰዓት ያለማክበር ድክመት ይታያል።ለትልቁ ችግር ስናስብ  ትንሹዋን የሰዓት አለማክበር በሽታ ግን ለማሶገድ አልቻልንም። ሳናርመው አብሮን የሚኖር ክሮኒክስ በሽታ ሆኑዋል።በራሳችን ተሸክመን የምንኖረውን ትንሹን ችግርና ድክመት ሳናሶግድ ትልቁን አገራዊ ችግር እናቃልላለን ማለት ዘበት ነው።በጊዜ መከናወን ያለበት ጉዳይ ከዘገዬ ጉዳቱ እጥፍ ድርብ ነው።በአንድ ዘመቻ ላይ በተወሰነው ሰዓትና ቦታ ካልደረሱ ግዳጁ(ሚሽኑ) ይሰናከላል።ለአደጋም ያጋልጣል።የበጋ፣የክረምት፣የጸደይና መኸር ወቅትም ጊዜን ያከብራል፤ጨለማና ብርሃንም እንዲሁ።ሰዓት ማክበር ያቃተን፣የጊዜ ትርጉም ያልገባን እኛ ሰዎች በተለይም ኢትዮጵያውያን ነን።እዚህ ላይ ሁሉንም በጅምላ ማውገዝ አይገባም፤ቀጠሮና ቃላቸውን የሚያከብሩ አሉ።ለነሱ ክብርና አድናቆት አለኝ።ሌሎቻችን የነሱን ፈለግ መከተል ይኖርብናል።

እባካችሁ ቀጠሮ እናክብር!የሰዓት፣የቀን፣የሳምንት፣የወርና የዓመት  ትርጉሙ ይግባን።ዕድሜያችን የሰከንድ፣የደቂቃና የሰዓት ጥርቅም ወይም ድምር መሆኑን እንረዳ።ጊዜ የሚንቁት የአቡዋራ ክምር አይደለም።የመኖርና ያለመኖር እጣ ፈንታ የሚወሰነው በጊዜ ገደብ ነው።አፈጣጠራችን ሳይቀር በሰከንድ ውስጥ በሚከናወን አካላዊ እንቅስቃሴ ወይም ቅንብር ነው።ስለዚህ ጊዜ ትልቅ ትርጉምና ዋጋ አለው።ቃላችንንና ቀጠሮ ስናከብር ኩሩና ሙሉ ሰዎች እንሆናለን።ዘግይተን ስንደርስና ቃላባይ ስንሆን በይሉኝታ  ውስጣችንን እንደሚነዝረንና  እንደምንሰቀቅ አንካድ።ከዚህ ሁሉ በራሳችን ላይ ሂስ አቅርበን እንታረም።ሰዓት የማክበሩን ባህል ወርሰን እናውርስ። በጊዜው መድረስ የማይቻልበት ብዙ አጋጣሚ ይኖራል፤ ድንገተኛ አደጋ፣የትራፊክ ጫና፣የመጓጓዣ መስተጓጉል፣ የመሳሰሉት ያልተጠበቁ ደንቃራዎች ይኖራሉ።ያም ቢሆን ሁኔታውን በመንገድ ላይ እያሉ እድሜ ለዘመኑ ሞባይል ስልክ መግለጽ ይቻላል።

የቀጠሮ ሰዓት በማያከብረው ላይ ማህበራዊ ቅጣት ይጣልበት፣ ዘግይቶ ሲመጣ ለመሰብሰቢያ አዳራሹ ኪራይ የወጣውን ወጭ ለማካካስ የሚረዳ የገንዘብ ቅጣት፣  ወይም  ዘግይቶ የመጣ  የሚቀመጥበት ቦታ ተለይቶ ቢዘጋጅ እራሱን በራሱ እንዲታዘበው ይረዳል።
ቃላቸውንና ቀጠሮ ለሚያከብሩት ሁሉ ክብርና ምስጋና አይለያቸው!
ቀጠሮ ያለማክበር የጋራ ድክመታችንን በጋራ እናሶግድ!ዘግይቶ ሳይሆን ቀድሞ ለመድረስ እንዘጋጅ!
አገሬ አዲስ

No comments: