Friday, August 31, 2018

ተደብቆ የነበረው የኢሳያስ አፈወርቂ “ትግራይ ትግርኚ” ዓላማ ይፋ ሆነ! ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)


ተደብቆ የነበረው የኢሳያስ አፈወርቂ “ትግራይ ትግርኚ” ዓላማ ይፋ ሆነ!
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

በዚህ ርዕስ ውስጥ ሁለት ጉዳዮችን እንመለከታለን። ሰሞኑን የትግራይ ‘ወጣት‘ ምሁራን ስለ ትግራይ ትግርኚ ምስረታ እንደ አማራጭ ፍላጎታቸው ያንጸባረቁበት 20 ወጣት ምሁራን ባካሄዱት ስብሰባ ላይ የተንጸባረቀው ፍላጎት እንመለከታለን።  ሁለተኛው ክፍል ውይይታችን ደግሞ፤ ኢሳያስ በትግራይ ትግርኚ የነበረው አቋም እንመለከታለን። ባጭሩ የተለያዩ ሁለት ማስረጃዎች ግን አንድ ግብ ያላቸው ሰነዶችን አቀርባለሁ። 
Photo-Abraha Desta participating on Ethnic Federalism and secession convention (secession as option
(Abraha Desta participating on Ethnic Federalism and secession convention (secession as option)
ሁለተኛው ምስል (ፎቶ) ስለ ትግራይ መጪው ዕድል እንደ አማራጭ ያቀረባቸው አማራች ገለጻ የሚያደርገው አቶ ጉዑሽ በርሄ ጣቱ ላይ ቀስሮ እያመለከተበት ያለው ኣንቀጽ 39ን ሲያብራራ ነው (A39 በሚል ስም በመስጠት ቻርቱ ላይ ሲያብራራ ነው)

የብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ለበርካታ አመታት በኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው ሻዕቢያ የተባለው በፋሺስት ርዕዮት የተመሰረተው እጅግ ዘረኛ እና ነብሰገዳይ ድርጅት ብዙ ሰዎች ሻዕቢያ ስለ የትግራይ ትግርኚ ምስረታ ዓላማ ይቃወም ነበር እያሉ ሲከላከሉለት እንደበር እናስታውሳለን። ድርጅቱም እራሱ የትግራይ ትግርኚ ዓላማ ይቃወመው እንደነበር ሲያሰራጫቸው ከነበረው የማታለያ ተመጻዳቂ በራሪ ሰነዶች እና በራዲዮኑ ሲያስተላልፈው እንደነበር ማስረጃየ  ብሎ የሚጠቀምበት መከራከሪያ እንደነበርም ይታወቃል። ያ ሁሉ “ቡትለካ” (መናፍሕ) ማታለያ እንደነበር ዛሬ ከድርጀቱ ከፍተኛ አባል ምስጢሩ የተቃራኒ እንደነበር ገሃድ ሆኗል። እዚህ ላይ ወያነ ትግራይ ከትግራይ ትግርኚ ዓላማው ትቶት ነበር ማለት እንዳልሆነ ይሰመርበት።

ወደ ማስረጃው ከመግበታችን በፊት፤ ታስታውሱ እንደሆን ኢሳያስ መቸም ቢሆን ትግራይ ትግርኚ የሚለው ዕቅድ እንደማይቃወመው እኔም ሆንኩኝ በይበልጥም ታላቁ ኤርትራዊው የሕግ ምሁር እና በጀርምን አገር ብረይመን ዩኒቨርሲቲ የሕግ ፕሮፌሰር ዶ/ር ተስፋጽዮን መድኅኔ በተለያዩ ሰነዶቹ ገልጾት እንደነበር ይታወሳል።  ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድኅኔ  ኢሳያስ በረሃም እያለ በፈረንሳዊው ዲፕሎማት፤ተመራማሪ እና ጋዜጠኛ ‘ፕሮፌሰር ረኔ ሊፎርት’ ኢሳያስ አፈወርቂ የጥንቱ የአክሱማዊ ስርወ መንግሥት እንደገና ለማደስ ዓላማ እንደነበረው ኢሳያስ ከተናገረው ንግግር የተመዘገበው ሰነድ ወዳጄ ፕሮፌሰር መድኅኔ መጽሐፍ ውስጥ (Eritrea Dynamics of a Nation Question – by Tesfatsion Mehanie) ገልጾት እንደነበር ላስታውሳችሁ እፈልጋለሁ።

ከላይ የተጠቀሰው የፕሮፌሰር መድሃኒየ መጽሐፍ በ1986 በፈረንጅ ዘመን አቆጣጠር በጻፈው እጅግ ጠቃሚ መጽሐፍ በገጽ 115 እንዲህ ሲል ዘግቦት ነበር።

“…The TPLF now focused on the principle of self-determination in the name of this principle, it claimed to seek the equality and freedom of the Tigrean people and other nationalities within a united Ethiopia. It stressed however that this could be realize only under a “democratic” government in Ethiopia and not under the “fascist” PMAC. It emphasized that “if the existing national oppression continues or is aggravated”- so long as the PMAC or another revolutionary democratic regime is in power in Ethiopia-self determination “means the birth of an independent Tigray” (51)

Clearly the TPLF aimed to overthrow the revolutionary government in Addis Ababa. The idea of severing Tigrai from Ethiopia was a threat designed to serve this goal.

The EPLF and the TPLF renewed their intimacy. They became twin organizations and again charted a common plan of work.

Some TPLF leaders gave clear indications of their wish to unite Eritrea and Tigrai, portraying it as an alliance against the “Showan regime,” the PMAC in Addis Ababa. French writer Rene Lefort has recorded a revealing incident which he witnessed while touring the EPLF held territory in Eritrea. He recalled listening to “a long very long soliloquy” by an EPLF leader on the reason for the struggle of the Eritreans (52) He added that EPLF leader concluded the talk by saying, “We are the inheritors of the kingdom of Axum. We will have nothing to do with this Showan regime.” (53)
The perceptive Lefort commented that, in those words of the EPLF leader, “there was…more than a mere verbal sally.” (54)- (Eritrea Dynamics of a Nation Question – by Tesfatsion Mehanie May 1986-p.115)

*51- (Rene Lefort, Ethiopia: An Heretical Revolution? (London: Zed Press, 1983), P.268    *52-Ibid  -- *53-Ibid

እንግዲህ ከላይ እንደተመለከትነው ኢሳያስ የትግራይ ትግርኚ ዓላማ የጀመረበት ወቅት በግልጽ ባይታወቅም፤ የአክሱም ስርወ መንግሥት ተረካቢዎች መሆናቸውን እና ለዚህ ተረካቢነት ዝግጁነትም በትግራይ ትግርኚ ዓለማ መተግበር እንዳለበት ኢሳያስም ሆነ ባልደረቦቹ ለተስበሳቢ ጉባኤተኛ እና ለውጭ አገር ተጋባዥ እንግዶች በግልጽ እንደተናገረ ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድኅኔ (1986) እና ረኔ ሊፎረት (1983) ነግረውናል።

የሁሉም ድርጅቶች ድብቅ ‘ዓላማ’ የተሰናከለበት ወቅት ሁለቱም ማለትም ወያኔ እና ሻዕቢያ ወደ ጦርነት ከገቡ በኋላ እንደሆነ የምናየው ማስረጃ ከዚህ ቀጥሎ አዲስ ዜና እንመለከታለን። ሁለቱም ድርጅቶች ከመጣላታቸው በፊት ግን ድብቅ ዓላማቸው ላለማሳወቅ ሲሉ ከዚያ በፊት ሁለቱም ‘ወፈፍ’ ሲያደርጋቸው (ኢሳያስ ወያኔን ‘በየ 10 አመቱ አንዴ ወፈፍ ያደርጋታል’ ይል እንደነበረው ሁሉ) ያንን ፍላጎታቸው በድብቅ ይዘውት፤ለማስመሰል ብቻ በሻዕቢያ በኩልም ሆነ በወያኔ በኩል የትግራይ ሩፑብሊክ ምስረታ “አንደግፍም” የሚል በራሪ ሰነድ ሲበትኑ እንደነበር ይታወሳል። ሆኖም ሻዕቢያ የተቃወመው (በኔ ግምገማ) የትግራይን ከኤርትራ በመወሃድ “ትግራይ ትግርኚን መመስረት” ሳይሆን የተቃወመው ፤ ትግራይ በራስዋ አገር ለመሆን “የትግራይ ሪፑብሊክ” አገራዊ ምስረታ ነው ሲቃወም የነበረው (ካሁን በፊት ባንድ ትችቴ ገልጬዋለሁ)።

ለዚህ አባባሌ በቂ ድጋፍ እንደ ማስረጃ የሚሆነኝም ሰሞኑን ‘ኤስ ቢ ኤስ - ራዲዮ’ (SBS radio) በመባል የሚታወቀው የአውስትራሊያ የትግርኛ ራድዮ ክ/ጊዜ ካሁን በፊት በሱዳን የሻዕቢያ አምባሳደር የነበረው አምባሳደር ኣብደላ ኣደም ኢሳያስ ስለ ትግራይ ትግርኚ ምስረታ ግብ ፍላጎት እንደነበረው ሰሞኑን በሰጠው የትግርኛ ቃለ መጠይቅ ሰምተነው የማናውቀው ተደብቆ የነበረ ትኩስ ዜና አስደምጦናል። ኢሳያስም ነ ወያኔዎች፤ የትግራይ ትግርኚ ዓላማ ምስረታ ፍላጎት እንደነበራቸው የሚያሳይ ማስረጃ ባለፉት 20 ምናምን አመታት ተቃዋሚዎቻቸው በየአገራቸው ቢያስታጥቁዋቸውም፤ አንዱ አንዱን እንዳይጎዳ ሲያሳዩት የነበረው ለዘብ ያለ “ያለመጎዳዳት” ባሕሪቸው ጥርጣሬ ውስጥ የሚከትት አመላካች እንደበር ፕሮፌሰር ዶክተር ተስሃጽዮን (በተለያዩ ሰነዶች በሰፊው በትግርኛ እና በአማርኛ ደጋግሞ በኢንትርኔት ሚዲያዎች በማሰራጨት ገልጾታል። አንዳንዶቹ ሰነዶቹም በአዲሱ መጽሐፌ ታሪክ እንዲመዘግበው ለማስረጃ አትሜኣቸዋለሁ። ያንን መመልከት ጠቃሚ ነው) እንዲሁም ሌላው ምሁር ፕሮፌሰር ረኔ ሊፎርትም ጭምር ሲገልጹት የነበረው የኢሳያስ ድብቅ ዓላማ ይኼው ዛሬ ከስንት አመት በኋላ እውነታው ጋሃድ ሆኗል።

ከዚህ ቀጥሎ የአምባሳደር ዓብደላ ኣደም የትግርኛውን ቃለ መጠይቅ ወደ አማርኛ ትርጉም ይቀርባል። ከዚየም ትግርኛ ለምታደምጡ አንባቢዎች የትግርኛው አውድዮው/የድምፅ ቅጂው/ አቀርባለሁ።

እንዲህ ይላል፦

“ከኤርትራ ነፃነት በኋላ ማለትም አምባሳደርነቴን ትቼ ጥገኝነት ጠይቄ ተቃዋሚ ከሆንኩኝ  በኋላ 2003 ወደ አዲስ አበባ ሄጄ ነበር። በወቅቱ ነብሱ ይማረው መለስ ዜናዊ በህይወት በነበረበት ጊዜ ለሁለት ሰዓት ያክል አነጋግሬው ነበር። መለስ ያለኝ፤ ‘እንደ እነ ናይዝጊ ክፍሉ የመሳሰሉ ከፍተኛ ባልሥልጣኖች ወደ ትግራይ እየተላኩ ስለ ትግራይ ትግርኚ አገራዊ ምስረታ እንድንቀበል ይጠይቁን ነበር' በማለት መለስ ዜናዊ በግል ለኔ አጫውቶኛል። መለስ ዜናዊ እንዲህ ብሎ ሲነግረኝ የነበሩ የወያኔ ባለስልጣኖች ለምሳሌ ስዩም መስፍንም ሌሎችም አብሮውን ነበር።” በማለት ዓብደላ ኣደም
ይህ ለጆሮኣችን አዲስ የሆነ ትኩስ ዜና አድርሶናል።

የ ‘ኤስ ቢ ኤስ - ራዲዮ’ (SBS radio) ጋዜጠኛ እንደዘገበው ‘ዓብደላ ኣደም በ977 (ፈረንጅ ዘመን) ጀምሮ የሻዕቢያ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበረ ነው። ከነፃነታቸው በኋላም የሰንሒት አውራጃ ከዚያም የደቡባዊ ቀይ ባሕር አስተተዳዳሪ፤ ከዚያም የጂቡቲ ና የሱዳን አምዳሳደር ነበር። ሱዳን ውስጥ ሁለት አመት አምባሳደር ሆኖ ከቆየ በኋላ ዓብደላ ኣደም ከ15ቱ የኢሳያስ ተቃዋሚዎች (ሪፎርሚስቶች) መካካል አባሪ ስለነበር፤ ባስቾኳይ ወደ ኤርትራ እንዲመለስ ትዕዛዝ ከተላለፈለት በኋላ ሁኔታው ስላላማረው፤ ወዲያውኔ መጣሁ ብሎ ወደ እንግሊዝ አገር በመሄድ እንግሊዝ አገር ጥገኝነት በመጠየቅ በስደት ይኖራል። በማለት ስለ አምባሳደሩ የሥራ ልምድ ገልጾታል። ሙሉውን የትግርኛ ቃለ መጠይቅ ለማድመጥ ይህንን የድምጽ ሰንድ ያድምጡ።   

ሌላው ዜና  ሰሞኑን ከትግራይ የተለቀቀው  ቪዲዮ እነ
አብርሃ ደስታ እና 20 የሚሆኑ ወጣት ምሁራን ስለ ተሳተፉበት
 ሰሚናር በሚመለከት።

የስበሰባው መሪ “ጉዑሽ በርሀ” ይባላል። ሰውየው ብዙም አይታወቅም። የትምህርት መስኩም ምን እንደሆነ አይገልጽም። በቪዲየው መግቢያ እራሱን ሲገልጽ ከውጭ አገር እንደመጣ ይገልጻል። ሰውየው ከውጭ አገር ወደ ትግራይ ሲመጣ ‘ግጭት/ኮንፍሊክት/” ሲከሰት እንደሆነ ይገልጻል። ካሁን በፊት አንዴ መጥቶ እንደነበር፡ ለዚሁም በቋንቋ የተነሳ ችግር ተከስቶ በነበረበት ወቅት ይህንን ገለጻ ለማድረግ እንደመጣ በገለጻው ውስጥ ይናገራል።

ተስበሳቢዎቹ ከ20 አይበልጡም። ሁሉም ወጣቶች ናቸው። አንዳንዶቹም ከአብርሃ ደስታ በዕድሜ ያነሱ ይመስላሉ። የስብሰባው ተካፋዮች ከተለያዩ የአውራጃ ቋንቋ ተናጋሪዎች መሆናቸው ከልሳናቸው ማወቅ ይቻላል። 99% ምናልባትም 100% ማለት በሚባል የትግራይ ትግርኚ (ስለ ግንጠላ) ፍላጎትም ሆነ፡ ከእንግዲህ ወዲህ ትግራይን እና የትግራይን ሕዝብ ዕጣ ፈንታ ‘ማዕከል’ (ትኩረታቸው) ባደረገ ፍላጎት ብቻ ማትኮር እንዳለባቸው በአጽንኦት ይስማማሉ። 

የስብሰባው ገለጻ አድራጊ ጉዑሽ በርሀ ትግርኛ ሲናገር ከእንግሊዝኛ ቃላት ጋር እየደባለቀ ስለሚናገር በቅንፍ እያደረግኩ ለማብራራት ሞክሬአለሁ። በተቻለ መጠን ለአንባቢዎቼ በይበልጥ የሰውየው ንግግር ግልጽ ለማድረግም በቅንፍ ያስቀመጥኳቸው የራሴ አገላለጾች አሉ።

 እንዲህ ይላል፤-

“ሲስተሙ (ስርዓቱ) በኤትኒክ (በጎሳ) ፌደራሊዝም የማይሰራ (የማይቀበል) ከሆነ የራሳችን ኦፕሺን (አማራጭ) መውሰድ ይቻላል። እኛ እንደ ትግሬዎች ሦስት ኦፕሺን (አማራጮች) አሉን። ያ “ኦፈር” የምናደርገው ፌደራሊዝም (ያ የሰጠናቸው ፌደራሊዝም) ተቀባይነት ካላገኘ አማራጮቹ የሚከተሉት ናቸው፡ እንደ ኢትዮጵያ አካል ሆኖ መኖር፡ ከኤርትራ ጋር “ጆይን” (ውህደት) የማድረግ ፖሲቢሊቲ (የሚቻልበት ዐድል) አለ።ሌለው ኮንፌረሺን ነው። በመጨረሻ እገልጸዋለሁ።  ምክንያቱም እኛ እና ኤርትራኖች የጋራ የሆነ የማንነት አንድነት ስላለን በቀላሉ መዋሀድ እንችላለን።

ለምሳሌ ወደ ሌላ አቅጣጫ ወሰድከን አትበሉኝ እንጂ ይላል አቶ ጉዑሽ በርሀ፦ ‘የተስፋጽየን አጋዚያን ጽንሰ ሓሳብ አለ’ (ተናጋሪው ተስፋጽየን ብሎ በስም ጠቀሰው ሰውየ በየቱዩቡ ተጥዶ ቀንም ሌሊትም ስለ አማራ ጥላቻ የሚሰብክ፤ቀለም ያልቃኘው፤ በሌብነት ተከስሶ የተፈረደበት አንድ አጭበርባሪ ኤርትራዊውን ነው “አጋዚ መሪ ብሎ እየጠራው ያለው” ተስፋጽየን የብዕር ስም እንጂ ሓቀኛ ስሙ “ዕዮብ” ይባላል።)  … ይቀጥልና- አሁን ባለው ክስተት(እኛ ትግሬዎች ያለንበት ሁኔታ) ‘በሥልጡንነታችን ጽንሰ-ሃሳብ መመዘኛ ስንመዝነው (ከሌሎቹ ቀደም ብለን ሥልጡኖች እንደመሆናችን መጠን) እኛ በሌሎች እየተጎተትን እንጂ እኛ ሌሎችን እየጎተትናቸው አይደለንም ያለነው’ (በተገላቢጦሽ ላይ ነን)። ምክንያቱም እኛ የትግራይ ምሁራኖቻችን ወደ መሃል (ኢትዮጵያ) አሰራጭተን ኢንቬስት ያደረግነው፤የረባነው ነገር እስካሁን ድረስ ምንም የለም። ወደኋሊት ነው እየተመለስን ያለነው (ሌሊችን እንጂ ሕዝባችንን አልጠቀምንም)።

ግልጽ ለማድረግ፤በኤርትራ እና በትግራይ ውስጥ ጠንካራ መሪዎች ከተገኙ እርስ በርስ እየተረዳዱ በየአለንበት ሆነን የጋርዮሽ ተጠቃሚዎች ልንሆን የምንችልበት መንገድ መቀየስ ይቻላል። ሦስተኛው አማራጭ ኮንፌደረሺን ነው። አጋአዚያን መንግሥት (ትግራይ ትግርኚ) መስርተህ የራስህ መንግሥት መስርተህ ከሌሎቹ ጋር በፀጥታ፤ ቴክኖሎጂ ወይንም በፋይናንስ የመሳሰሉ የተወሰኑ ጥቃቅን ነገሮች ተስማምተህ መኖር ነው። እኛ ትግሬዎች የተደራጀ ሕዝብ ስላለን ሌሎችን ቀድመን መመንጠቅ እንችላለን።በተለይ ኤርትራ እና ትግራይ ለማዋሃድ እንዲመች እንደ ቅድመ ኩነት (ዝግጅት) መደረግ ያለባቸው ነገሮች ‘የሁለቱም ሕዝቦች ምሁራን በመገናኘት በሁለቱም ሕዝቦች ያሉት ችግሮች ነጥረው በማውጣት ተወያይተው ዕንቅፋቶቹ እንዲወገዱ ከተደረገ በቀላሉ መዋሃድ እና የተፈለገው ንድፍ ማጠናቀቅ ይቻላል።

ወያኔ አማረዎችን እና አሮሞቹን እንዲሁም ሌሎቹ እንዲተባበሩ ሲረዳ ፤ለራሱ ሕዝብ (ለትግራይ) እንዲተባበር አላደረገም። እርስ በርስ ልንደማመጥ አልቻልንም። ወያኔ ማለት--- 'እንቆቅልሽ ምን አውቅልሽ?' ተብሎ ቢጠየቅ “እራሱን ሳያስተባብር ሌሎችን አንድ እንዲሆኑ የረዳ ንገረኝ?” ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ “የእራሱን ሕዝብ ሳያስተባብር ሌላውን ያስተባበረ “ወያኔ”  ነው የሚል መልስ እናገኛለን። (በዚህ የእንቆቅልሽ መሳሌ ተሰብሳቢው ሁሉ በአዎንታ መስማማታቸውን በቪዲዮው ድምፅ ውስጥ ይደመጣል)። ስለሆነም ለዘመናት እየተደፈርን እና እየተሰቃየን ያለንበት ምክንያት “ስላልተባበርን ነው”።

አቶ ጉዑሽ ንግግሩ ይቀጥል እና  “.. ስንነጣጠልም “ስሙዝ ላንዲንግ” (smooth landing) (ያለ ምንም ደም መፋሰስ እና ግጭት) መጠናቀቅ አለበት። አንቀጽ 39 በጣም ጠቃሚ ነው። ያንን ለመጠቀም ግን የመነጠል መብት እንዲተገበር 51% የሚለው ድምፅ ሕገ መነግሥቱ ተሻሽሎ ቢያንስ 3/4% መሆን አለበት። ድምጽ ሰጪው ዕድሜ ወደ 18 ዝቅ ማድረግ እና ብዙ የመገንጠል ድምጽ ሰጪ ማግኘት ይቻላል። ምክንያቱም 49% ሕዝብ አልገነጠልም ካለ እና በ51% ልገንጠል ብሎ ግንጠላው ተግባራዊ ቢሆንም፤ ብንገነጠልም እነዚያ 49% አልገነጠልም ያሉት የጊዜ ጉዳይ እንጂ የኋላ-ኋላ በውስጣችን ከፍተኛ ችግር እና ግጭት ሊያስነሱ ይችላሉ። በተቻለ መጠን ሁሉንም በግንጠላው እንዲስማማ ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ መረጋጋት ይቻላል። ለስሙዝ ላንዲንግ” (smooth landing) ሂደትም ይረዳል። ከሌሎቹ ጋር በተቻለ ቅራኔ ውስጥ ሳይገባ ግንጠላው እንዲከናወን ያላሰለሰ ጥበብ ያስፈልጋል።

እኛ ስንገነጠል፤ በውስጣችን ያሉ ብሔሮች እነደ እነ ኩናማ፤ ሳሆ….የመሳሰሉ መብታቸው ማክበር አለብን። ሌላው ነጥብ ዛሬም ሆነ ለወደፊቱ የዘር ሄጂመኒ (ሌለው ጎሳ በሌላው ጎሳ መዋጥ እንዳያጋጥመን) የምንመሰርታቸው ኢንዱስትሪዎች የሕዝብ ቁጥር ‘ብዛት’ ባለው የጎረቤት አካባቢ ኗሪዎች ጠረፍ አጠገብ መመስረት የለባቸውም። ምክንያቱም እኛ ጥቂት ሆነን ኢንደስትሪዎቻችን (አንድም ይሁን ሁለትም ይሁን) በኛ መሃል (በጥቂቶቹ) እና ብዛት ባለው ጎረቤት ሕዝብ ጫፍ (ድምበር) ላይ ከተመሰረቱ ስራ ፍላጋ ‘በቀላሉ ወደ ቦታው በሞግፍ’ ኢንዱስትሪው ወዳለበት ማዕከል በብዛት በመምጣት ቀስ በቀስ እየኖሩ እየተዋለዱ ብዙሃኑ ጥቂት የሆኑትን ነባሮቹን (ኢንዲጂነሱን) ሊውጡት ስለሚችሉ ከጊዜ ብዛት -ማለትም አንድ ወይንም ሁለት ወይንም ሦሰት ትውለድ ካለፈ በኋላ ይህ የኛ መሬት ነው ብለው “ዞር በል” ብለው ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ።ዞር ብል ሲሉህ ብዙሃን ስለሆኑ ‘ምን ማድረግ ትችላለህ?’። ስለዚህ ኢንዱስትሪዎች ሲመሰረቱ በተቻለ መጠን የት ቦታ መመስረት እንዳለባቸው ጥንቃቄ እና ጥናት ማድረግ አስፈላጊ ነው።’ በመለት ገላጸ ሲያደርግ

አቶ ጉዑሽ በርሀ ገለጻ ካደረገ በኋላ፤ የወያኔዎች ተከታይ የሆነው ‘ጌታቸው አረጋ’ዊ' የተባለው የ ‘ውራይና’ ጋዜጣ አዘጋጅ ወጣት ጋዜጠኛ (ታስታውሱ እንደሆነ ‘አባይ ፀሐየን ያናደደው ወጣት’ እያሉ ያልገባቸው አንዳንድ ‘ደደቦች’ በዩቱብ የለጠፉለት አክራሪ ብሔረተኛ የወያኔ አሽከር ነው ጌታቸው አረጋዊ ማለት)፡ ከጉዑሽ ጋር በመስማማት እንዲህ ይላል፡-

“አንተ የምትለው ልክ ነው። በተግባር የሆነውን አንድ ምሳሌ ልስጥህ። “አብደራፊ” የሚባል የትግራይ መሬት አለ። ይህች መሬት በአማራዎች ክልል የተጠጋች ድምበር (በአስፋልት የተለየች?) ነች። መጀመሪያ ወደ እዛቺው መሬት የሰፈሩ ትግሬዎች ናቸው። ከዚያም እነ ገዱ አንዳርጋቸው ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ በብዛት ቀስ በቀስ አማራዎች ወደ እዛቺው ቦታ በማጉረፍ አሁን ቁጥራቸው አማራው እና ትግሬው እኩል እንዲሆን አደረጉ። ፍጥጫ ሲነሳ አሁን እነሱ ቁጥራቸውም እኩል ከእኛዎቹ ጋር ስለሆነ ችግር አለ ማለት ነው። ስለዚህ ኢንዱስትሪ ሲተከል ከጎረቤት አገር /አካባቢ/ ያሉት ሕዝቦች ብዛት አንጻር እየተገመገመ (አካባቢውን እያጠኑ) ካልሆነ በሌሎች የመዋጥ ዕድል ሰፊ ነው።” በማለት ድጋፉን ሰጥቷል።

ባጭሩ እንዲህ ያለ ንግግር ምን እንደሚያመለክት የሚገባችሁ ይመስለኛል። ፋሺዝም የሚያደርገው የመጀመሪያው ጥንቃቄ ሌላ ዘር፤ሌለ ደም፤ሌላ ጎሳ፤ባዕድ ወደ "እንደ የጥዋት ውሃ የጠራው ዘር” ወደ ‘ወርቁ’ ጎሳ እንዳይዳቀልና ማንነቱ እንዳይዋጥ ማድረግ የመጀመሪያው የዘር ጥራት (racial Hygiene) ጥንቃቄ ማሳያ ነው (eugenic)። ያም ሆነ ይህ በዚህ ስብሰባ የተነገረው እጅግ አስፈሪ እና አሳፋሪ አስተያየቶች ስላሉ እሱን ሌላ ጊዜ ሲያስፈልግ በሌሎች ትችቶች ምን አንደተነገረ እጠቅሳቸዋለሁ። የስብሰባው ቪዲዮ በትግርኛ ለመመልከት/ለማድመጥ ይህንን ተመልከቱ
አመሰግናለሁ!
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)   

ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ሓቀኛን ሓደገኛን ብጉዑሽ በርሀ 1 ክፋል

2 ክፋል ብሄር ተኮር ፌደራሊዝም ሓቀኛን ሓደገኛን
     


Monday, August 27, 2018

ወያኔው ደብረጽዮን የትግራይ ሕዝብ በማንነቱ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲታይ ነበር ሲል ትግሬዎች ከደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ጋር አመሳስሎአቸዋል ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)


ወያኔው ደብረጽዮን የትግራይ ሕዝብ በማንነቱ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲታይ ነበር ሲል ትግሬዎች ከደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ጋር አመሳስሎአቸዋል
ጌታቸው ረዳ (Ethiopian Semay)

ወደ ርዕሳችን ከመግባታችን በፊት በቅርቡ ስለ አስገረመኝ ዜና ጥቂት ልበል። አብይ የሚባለው ደማሪ ስለ ምሕረት ሲናገር፤ የቀድሞ የደርግ መሪው መንግሥቱ ሃይለማርያም ጋር ሲደርስ ሕገመንግሥቱ ስማይፈቅድ ምሕረት አያገኙም ይላል። ለምን? ቢባል ሕገ መንግሥቱ በቀይ ሽብር የተካፈሉትን ምሕረት አይሰጥም ይላል። ሕገ መንግሥቱ ያረቀቁት ደግሞ እነማን ናቸው? ብለን ብንጠይቅ ከቀይ ሽብር እኩል ያልተናነሰ ግድያ እና ሽብር ክሕደት የፈጸሙ በነጭ ሽብር የተካፈሉት “መንሸቪኾች እና ቦልሸቪኮች” ወያኔዎች፤ ሻዕቢያዎች ፤ ኢሕአፓ ነባሮች፤ ኦነጎች የመሳሰሉ ሽብርተኞች የረቀቀ ሕገመንግሥት ነው።ታዲያ አብይ የተባለው ደማሪ ነጭ እና ቀይ ሽብር በሚል ለያይቶ ያንን ነጻ ያንን ወንጀለኛ የሚያደርግ ማስረጃ በምኑ ችሎት ፈትሾት ነው ሕገ መንግሥት እያለ ያለው ሊያምነው የቻለበት ድምዳሜ?

 እንዲህ ያለ ድምዳሜ ሊደርስ የቻለው በቀይ እና በነጭ ሽብር ብቻ የተካፈሉት ተገዳዳዮች ናቸው ወይንስ ስም ያልተሰጣቸው ወንጀለኞች እና ሽብርተኞችም ጭምር ታግደዋል? ሕገ መንግሥት ተብየው ከአዋጅ በላይ ከሆነ፤ በአዋጅ የመዘገባቸው ኦነግን ያክል በዘር ማጥፋት የተካፈሉ  ከወንጀል ነፃ አድርጎ ምሕረት ሲሰጣቸው ‘ሕገመንግሥቱን የሚጻረር’ ወንጀል የፈጸሙ የድርጅት ሃላፊዎች አዲስ አበባ ገብተው ባንዴራቸውን ሲያውለበልቡ አብይ በየትኛው የሞራል መመዘኛ ነው እነዚህን ሊያስገባቸው የቻለው? እሱ እራሱ ያዋቀረው የስለላ ድርጅት ለዚህ ሁሉ ግፍ እንዲፈጽም በምን መመዘኛ ነው ሕገ መንግሥቱ የፈቀደለት? ሕገ መንግሥት ያልፈቀደው ወንጀል ፈጽመናል እያለ እራሱ በሕዝብ ፊት ‘ይቅርታ እየጠየቀ” ሌላው ግን ሕገ መንገሥቱ ምህረትና ይቀርታ  አይፈቅድለትም ብሎ የማለት ሞራሉ ማን ነው የሰጠው? በሌላ ርዕስ እመለሳለሁ፡ አሁን ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባ።

  ለዓሸንዳ በዓል ተሳታፊዎች እና እንግዶች መቀሌ ከተማ ተገኝቶ የወያኔው ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በትግርኛ ቋንቋ እንዲህ ሲል ተናግሯል። (ሕዝቢ ትግራይ ብቋንቁኡን ብመንነቱን ሓፊሩን ተዋሪዱን ከም አሉታዊ ዜጋ ተቖጺሩን ክነብር ዝተገደደሉ ናይ ታሪኽ አጋጣሚ ነይሩ እዩ”)  “የትግራይ ሕዝብ በቋንቋው እና በማንነቱ ኣፍሮ እና  ተዋርዶ በገዛ አገሩ እንዲኖር እንደ አሉታዊ ዜጋ የተቆጠረበት የታሪክ አጋጣሚ ነበር” ይላል። ወደ ትንታኔአችን ከመግበታቸን በፊት “አሉታ” ማለት “ውሸት” ማለት ነው። አሉታ ደግሞ በሕክምና ‘ትርፍ አንጀት’ እንደማለት ነው። የማይፈለግ ክፍል ማለት ነው።  በሌላ መልኩ ደግሞ ‘አፍራሽ’ ማለት ነው። አጠቃላይ በፖለቲካ አጠቃቀሙ ሲተረጎም ‘አሉታዊ’ ማለት የማይፈለግ ‘ተቀናሽ’ ማለት ነው። በፎቶግራፊክ ሕግ ስንሄድ ደግሞ ነጋቲቭ ፊልም ማለት ከተፈጥሮአዊው (ኦሪጂናሌው/የጥንቱ የጥዋቱ/) የያዘው ቅርጽ ሕብሩ እና ብርሃኑ እንዳለ ሳይሆን በተገላቢጦሽ የሚታይ ቅርጽ ማለት ነው። እንግዲህ ምስል እንጂ ዋናው አይደለም ማለት ነው። አስቀድሜ እንደገለጽኩት በፖለቲካው ስንኝ አሉታዊ ማለት ”የማይፈለግ” “ተቀናሽ ማለት ነው። በግልጽ አማርኛ እና እንግሊዚዝኛው ትርጉም negative means “Reject, refuse to accept” ማለት ነው። ለምሳሌ“The Bill was negative by 130 votes to 90” የቀረበው ሰነድ 130 ለ90 ውድቅ ሆኗል ሲል 130 ድምጽ ሰጪዎች ሰነዱን አንቀበለውም ብለው ጥለውታል ማለት ነው። በዚህ መልክ ድምፅ ሰጪዎች የሰነዱ አሉታዊ ገጽታ /ጤናማ ስላልሆነ/ ስላለውደዱት ከሌሎች ሰነዶች ነጥለው አንቀበልም ብለዋል ማለት ነው። በዚህ ትርጉም የተነፈገ ማለት ነው።

ጥልቅ ትርጉም ልሰጣችሁ የፈለግኩበት ምከንያትም የደብረጽዮን አፈቀላጤዎች ለሚሰጡት የሽፋን ምክንያት በር ለመዝጋት በሚል ነው። እንቀጥል። በሂሳብም ነጋቲቭ/አሉታ/ የሚለው የሚነግረን ትርጉም “ካንድ ጥቅል የተቀነሰ ክፍል/አካል ማለት ነው”። ታዲያ ደብረጽዮን የትግራይ ሕዝብ ከመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ በማንነቱ አሉታዊ ማሕበረሰብ ተብሎ የተነጠለበት/ሁለተኛ ዜጋ ሀኖ ሲታይ የነበረበት የታሪክ ወቅት ነበር ሲል ቀጥተኛ ትርጉሙ ትግሬዎች በማንነታቸው “ትግሬዎች” ስለሆኑ ብቻ “አይፈለጉም’ ነበር” “ይገለሉ” ነበር ስለሆነም በሰብእናቸው እንዲያፍሩ ተደርጛል ይላል። እንዴት? ለምንስ ነው? ማን ነውስ በማንነታቸው ተነጥለው እንዲታዩ ያደረጋቸው?

ባዓሉን ለማክበር በተገኘበት ‘አሸንዳ’ የተባለው በዓልም እንደሆነ በታሪክ በፍጹም በማንኛውም አገዛዝ ዘመን ታግዶም ተከልክሎም አይታወቅም። ምንስ ለማት ፈልጎ ነው በዚህ በዓል እንዲህ ያለ ቀፋፊ ውሸት ሊዋሽ የገፋፋው? የሚል ጥያቄ ለመመለስ ደብረጽዮን ማን መሆኑን ከማሕደሩ ብንመለከት የውሸት እና የቅጥፈት ባሕሪው በግልጽ በሚከተለው ማሕደሩ ብንመለከት የመዋሸት ምንጭ መቸ እንደጀመረ ሊረዳን ይችላል።

ኮለኔል ፍስሃ ሃይለማርያም ይባላል;-ትውልድ ገጠሩ ተምቤን ትግራይ ነው። የወያኔ ታጋይ ነበር። በወያኔ የስለላ ክፍል አባል ነበር። ለስለላ ስምሪት ስራ የሰለጠነው ሱዳን ውስጥ ተልኮ ነው። ዛሬ በህይወት የለም። በሻዕቢያ ተገድሏል።ወያኔን ለመጣል ኤርትራ በረሃ ድረስ ለትግል ሄዶ በሰጠው በኤርትራ መርአየ ኩነት (ቴ/ቢዥን) ቃለ መጠይቅ እንዲህ ብሎ ነበር።

"እኔ በዓይኔ ያየሁት አንድ ነገር ነበር! ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን፣ አንድ ጊዜ በዚህ ደብረብርሃን እስረኞችን ለማስፈታት በተደረገው ኦፔረሽን ተሳትፈዋል ብሎ አስወንጅሎ ከባድ ፍርድ እንዲፈረድባቸው በማሰብ፣ ባገር ውስጥ ሚኒሰትር ምክትል ሚኒስተር የነበረ ደብረጽየን ገብረሚካኤል የሚባል የሰራውን ሥራ እኔ በዓይኔ ያየሁት ነበር። ፕሪፌሰር በዚህ ዓይነት ሕገ ወጥ ሥራ ተሰማርተዋል ብሎ በታይፕ አርጎ ጽፎ፣ ፊርማቸውን የፕሮፌሰር በሌላ ወረቀት የፈረሙት ፊርማ ኮፒ አደርጎ አስመስሎ በመፈረም እሳቸው ወደ እስርቤት ከገቡ በኋላ፣ ጽ/ቤታቸው የመአሕድ ጽ/ት እንዳለ ዘግቶ ማኅተም አምጥቶ አትሞ በቀጥታ እንደማስረጃ ብሎ ለፍርድ ቤት አቀረበው። ያ ወረቀት እንደ ዶክዩመንት ተቆጥሮ፣ ፍርድ ቤት ይሄ ጽሑፍ   *የሄ ፊርማ*፣ ይሄ ማኅተም የርስዎ ነው ብሎ….ምንም ባልፈጸሙት ወንጀል በእስር ቤት ተሰቃይተው ለሞት ተዳረጉ። እንዲህ ዓይነት አሰቃቂ ግፍ እየተፈጸመ ይህ የታገልክበት ዓላማ በግልባጩ ሲተገበር እያየህ…እኔ በግሌ ለሕሊናየ በጣም ቁስል ነው የፈጠረብኝ። በታሪክም ተጠያቂ የሚያደርግ ስለሆነ የነበረኝም ሁኔታ ከግምት ሳላስገባ የታገልኩለትን ዓላማ የትግራይ ሕዝብ በመሆኔ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የታገለበትን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የተሰው ታጋዮች ወንድሞቻችንና ጓዶቻችን አደራ ያሉንን ዓላማ ከግብ እንዲደርስ ዳግም መታገሉን መረጥኩ።“ (ኮለኔል ፍስሃ ሃይለማርያም- ኤርትራ ቲ/ቪ- የጽሑፍ ምንጭ የወያኔ ገበና ማህደር- ደራሲ ጌታቸው ረዳ)

እንግዲህ የደብረጽዮን የመዋሸት ልምድ መቸ እንደጀመረ በቀላሉ ማየት እንደትችሉ ማስረጃ አይተናል። ደብረጽዮን ሙልጭ ካሉ ድሃ ቤተሰቦች እንደመጣ ይነገራል። ከድሃ ቤተሰብ መወለድ ግን ሁለተኛ ዜጋ ነበርኩ፤ትግራይ  ተገልሎ ነበር የሚያሰኝ ውሸት እስኪዋሽ አያደርስም። ይህ ውሸት ተራ ውሸት ሳይሆን ፖለቲካዊ ወንጀል ነው። ደብረጽዮን ይህንን ታሪክ የሚበክል፤ የትግራይ ወጣት ትውልድ “አገራችን ነች ከሚሉዋት ኢትዮጵያ” ጋር  የሚኖራቸው ቁርኝት የማናጋት ባሕሪው መነሻው እሱ እና መሰል የወያኔ መሪዎች ለኢትዮጵያ ካላቸው ጥላቻ የተነሳ ነጸብራቅ መሆኑን በግሌ የወያኔዎች ንግግር እና ጽሑፍ እንዲሁም ከሚሰጥዋቸው ቃለ መጠይቅ እና ከላይ የተመለከትነው ማስረጃ ሰነድ ያታዘብኩዋቸው አቋማቸው እንደሆነ አውቃለሁ።

 ወያኔዎች ለፖለቲካቸው እንዲረዳቸው ሲሉ የሚነዙት “ተገልለን ነበር፤ በአሉታ እንታይ ነበርን” የሚለው እውነታው ሲመረመር መሰረተ ቢስ ነው። ትግሬዎች ከሌሎቹ ጎሳዎች በኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ሁለተኛ ዜጋ እየታዩ “በማንነታቸው” አፍረው እና ተዋርደው” እንዲኖሩ የተደረገበት ጊዜ መቸ ነው?  ትግራይ ውስጥ ጨቁኖናል ብለው ከሚወነጅሉት የአማራ ክ/ግዛቶች ውስጥ  በትምሕርት እና በጤና ይበልጥ ትግሬዎች ተጠቃሚዎች ነበሩ።

ጎንደርም ሸዋም ወሎም ጎጃምም ጅማም አዲስ አበባም ሓረርም……. ወዘተ  ሲኖሩ የነበሩ ትግሬዎች መቸ ነው በማንነታቸው ተንቀው ተገልለው ተጮቁነው ሲኖሩ የነበሩበት ወቅት?

ወደ ሌላ ሳልገባ ይህችን የወያኔዎች “ተጨቁነን ነበር..ጭቆና ፤ጭቆና…” የምትለው የሁልጊዜ የትግሬዎች መንቻካ ውሸት ላስምርባት እና አጭር ማስረጃ በመጽሐፌ ውስጥ ከሰፈርኩት ማስረጃ ልግለጽ እና ወደ ደብረጽዮን እንሻገራለን።

የወያኔ ገበና ማህደር በሚለው መጽሐፌ ውስጥ ፋብሪካ በሚመለከት እነሱ የሚሉት ትግራይ ውስጥ አንዲትም አፍብሪካ ይሁን አነስተኛ የግለሰቦች ምርት ሰጪም አልነበረችም ይላሉ።ሃቁ ሌላ ነው ለምሳሌ

ትግራይ (7) ከሰባት ባለይ እኔ የማውቃቸው

-  ጎንደር (4) - ወሎ (4) ፋብሪካዎች ነበሩ”። አማራ የሚባለው ክፍል (ጨቆነን ሲሉት የነበረው) በግማሽ ያህል አልነበረውም።

ከመቀሌ ቄራ ድርጀት (ኢንኰዶ በመባል በልምድ የሚጠራው እስራኤሎች ያቋቋሙት የሥጋ ፋብሪካ)፤

የዱቄት ፋብሪካ ፤ በኤርትራዊው አቶ ኤርምያስ (ሥራ አስኪያጁ ልጃቸው የዕብዮ ነበር) የተመሠረተ።

 አነስተኛ የእንጨት መሰንጠቂያ ፋብሪካዎችና ውጤቶች (የግል) ብዛት 3 (መቀሌ ብቻ) ማላዊ የባህል ልብስ ፋብሪካ (ወደ መላው ሀገሪቱና ወደ ውጭ አገር የባህል ልብሶችን  ኮት፤ ሱሪ፤ ሸሚዝ፤  የሴቶች ልብስና ቦርሳዎች፤ በድርጀቱ የተቀየሱ ልዩ ልዩ ቀለም ያላቸው የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች፣ በማከፋፈል ብዙ  ሠራተኞች ቀጥሮ ሲያስተዳድር የነበረ) ፤  

ታይድል በመባል የሚጠራው የዕጣን ፋብሪካ መቀሌ፣ ሽሬ ፣ አክሱም እና ተምቤን በአራቱ ከተማዎች አበጣሪዎችና ጥራት ተቆጣጣሪዎች በመቅጠር (አብዛኛዎቹ ሴቶች እህቶቻችን እና እናቶቻችን) ብዙ ሠራተኞችን የቀጠረ።

የዳቦ መጋገሪያና አከፋፋይ (መቀሌ)

የዘይትና የኑግ መጭመቂያ (ሽሬ አውራጃ)፤

 በሌሎቹ ከተሞች የሌለ የመኪና መንዳት ትምህርትና ፈተና የምስክር ወረቀት ዕደላ የሚያከናውን በኤርትራዊው አቶ መስመር ስራስኪያጅነትና ፈታኝነት በጠቅላይ ገዢው በልዑል እራስ መንገሻ ሥዩም የተፈቀደ ለማጅ (DMV) ተብሎ ሲጠራ የነበረ የቤት መለስተኛ አውቶሞቢሎችና የጭነት መኪና ነጂዎች የምስክር ወረቀት በመስጠት በሥራ ላይ እንዲሰማሩ የረዱ የሥራና የትምሕርት  ከፋች ተቋሞች ነበሩ።
ትግራይ ውስጥ

ከ8 አውራጃዎች ውስጥ ማለትም ከ7ኛ እስከ 8ኛ ክፍል
5 ት/ቤቶች ነበሩ ። 
አማራ በሚባሉ ክፍለሀገሮች
ጐጃም 3  ወሎ 2 ጐንደር 5 (ምንጭ የወያኔ ገበና ማሕደር)

9-12 ክፍል
ትግራይ 4  (አክሱም ዓድዋ ዓዲግራት መቀሌ ) ጐጃም 2 (ደብረማርቆስ እና ባሕር ዳር) ጐንደር 3 (ደባርቅ ፣ ደብረ ታቦር ጐንደር)  ወሎ 2 (ስሂን እና ወልድያ)  (ምንጭ ከእየክፍለሃገሩ ተወላጆች ጠይቄ ያገኘሑት መረጃ- የወያኔ ገበና ማሕደር- ደራሲ ጌታቸው ረዳ)

የጤና ተቋማትን በሚመለከት፦
ሰለኽለኻ (ሽሬ) ውስጥ- ሠፊ ሕክምና የሚካሔድበት ዘመናዊ ክሊኒክ:- እንዳስላሴ (ሽሬ) (አንድ ክሊኒክ 
አክሱም ውስጥ- (አንድ ዘመናዊ ሆስፒታልና ክሊኒክ)
ዓድዋ (ዓዲ አቡን) አንድ ዘመናዊ ሆስፒታልና አንድ ክሊኒክ (ዓድዋ)
ዓዲግራት (አንድ ሆስፒታል)
መቀሌ (አንድ ሆስፒታልና ክልኒክ)
ተምቤን (ክሊኒክ)
ማይጨው- በጤና መኮንን እና በነርሶች የሚካሄድ አንድ ከፍተኛ ክሊኒክ።

እያንዳንዱ የትግራይ ክሊኒክ ቢያንስ በጤና መኮንን፤ ነርስ እና የከተሞች ምግብ ቤቶች፤ ሉካንዳና መጠጥ ቤቶች ሳኒቴሪያን (የጤነ ተቆጣጣሪ) በመባል በሚጠሩ የጤና ጽዳት አያያዝ የሚቆጣጠሩ የሕክምና ባለሟሎች የተደራጀ ነው። በዚህ መልክ ትግራይ 8 አውራጃዎች ሲኖሯት በወቅቱ እያንዳንዱ ከላይ የተመለከቱት ተቋማት የያዘ ነበር። (አሁን ቡና ቤቱ (ብርጭቆዎች) በየጠላ ቤቱ እየዞረ መጠጫ ምኒሊኮቹ በሳሙና እና በውሃ በጽዳት መታጠባቸው የሚቆጣጠር ሳኒቴርያን /ክፍል መኖሩ እጠራጠራለሁ። (ምንጭ የወያኔ ገበና ማሕደር- ደራሲ ጌታቸው ረዳ)

ይህ ነው “ትግሬዎች” ተገልለን ተነጥለን አሉታዊ ኑሮ እንኖር ነበርን ወዘተ..እያሉ አማራውን በሓሰት ሲወነጅሉና አሁንም እየዋሹ የምናደምጣቸው። በማንነታችን ተጨቆንን የሚሉት አስገራሚ የሚሆነው ደግሞ ‘ባንድ ዘር ያነጣጠረ ጥቃት ሲፈጽሙ’ መኖራቸው እንደማናውቅ አድረጎ ደብረጽዮን ያለማፈር በሕዝብ ፊት ስለ ማንነት እና ስለጭቆና እና ውርደት ሲናገር ማድመጥ የሚገርም ነው።

በታሪካችን እኛ ትግሬዎች እርስ በርስ ስንነታረክ ባለፉት ወቅቶችም ሲገዳደል እና ሲናናቅ መሳፍንቶቹ ርስ በርሱ በትውልድ እና በአውራጃ አንዲነጣጠል ሲያደርጉ፤ ለጣሊያን ሲያድሩ፤ ተጠያቂ የሚያደርጉት አሁንም ምኒሊክን/ አማራውን/ ኢትዮጵያን/ ሰንደቃላማን ነው። ለውርደታቸው ሁሉ ተጠያቂው ሌላ ክፍል ነው። በቋንቋችን መጻፍ ተከልክለናል ሲሉ ውጭ አገር ሲኖሩ የነበሩ ትግሬዎቸ እንኳ ቋንቋቸውን ማሳደግ ሲችሉ እና በቋንቋቸው መጻፍ የሚችሉበት ሌላ ዓለም እየኖሩም ቢሆን ያበረከቱት ኢሚንት ነው። የነሱን ደካማ ገመና ሳይፈትሹ ሌላውን መጀመሪያ ተወቃሽ ያደርጋሉ።

ሌላ ቀርቶ የሃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሆነው ልክ ፖለቲካውን በድብቅ ጽፈው በሌሊት በየመንገዱ፤ በየት/ቤቱ ሲረጩት እንደነበረው ሁሉ የትግሉን ዕድል ተጠቅመው በቋንቋችን እንዳንጽፍ ተከልከን ነበር የሚሉትን ትግርኛ ቋንቋን እንኳ በድብቅ ሌላ ዓለምም ሆነው አገር ውስጥም ሆነው የትግርኛ ስነ ጽሑፍ እየጻፉ የተመኙትን መጻፍ ለማስተዋወቅ ሳይችሉ ሲቀሩ ለውሸት እንዲመቻቸው ንግገራቸው ሁሉ ቋንቋችን “ሃይለስላሴ ፤ ምኒሊክ፤ ደርግ…. አግዶናል’ ነው የማምለጫ ምክንያታቸው። በሕግ የታገደው የማኦ ኮሚኒሰት ማኒፌስቶ ግን እንደ አሸን እየበተኑ፡ ኪሳቸው ውስጥ ሸሽገው በየሻይ ቤቱና ጠላ ቤቱ እንያዛለን ብለው ሳይሰጉ ሲቦተልኩበት እና ሲጨቃጨቁበት፡ ‘የራሳቸውን ስነጽሑፍ’  ጽሑፍ ማሰራጨትና ማሳደግ ችል ብለው ሰንፍናቸውን ለመሸፈን  በሌላ ሰው ያላክካሉ።

 አውነት ነኝ የምላችሁ፡ ራሳቸውን ተጠየቂ ማድረግ አይፈልጉም። በዛው በነገሥታቱ ዘመን ምን የሚሉት ዲሞክራሲ ይጠብቁ እንደነበር ሳስበው ለኔ ይገርመኛል። የትግራይ ምሁራን ከታገድን ውንጀላ ሌላ ራሳቸውን መወቅስ አይፈልጉም።  ነገድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝም በትግርኛ ሲጽፉ አላየሁም። ሁሉም ነገር ያለ ትግል በብር ማንኪያ እና በብር ሳሕን እንዲያቀርብላቸው ሃይለስላሴን ፤ ምንሊክን ይወነጅላሉ። በዘመኑ የነበሩ የትግራይ ምሁራን አጼ ዮሃንስ ሲነግሱ በነበሩበት ዘምንም ትግርኛ መጻፍ ሲቻል ያንን ሳይደረጉ አሁንም ውንጀላቸው ያው ወደ ፈረደበት አማራ እና አማርኛ ቋንቋ ነው። ኦረሞዎቹም ትሬዎቹም የሚወነጅሉት ዘፈናችን አድማጭ አላገኝም ምክንያቱም የአማርኛ ዘፈን “ዶሚናንት ሆኖ” ገበያው እየነጠቀን ነው፡ እያሉ ኦሮሞቹም ትግሬዎቹም የተፈጥሮ  ጣዕም የተለገሰውን አማርኛ ዘፈን እና እስክስታ ማራኪነቱን እንዲለውጥ ይወተውታሉ። ውንጀላቸው ሁሉ መጠን የለውም። ተፈጥሮ የለገሰውን ሁሉ በጨቋኝነት /በዶሚናንትነት/ ይከሱታል። ተፈጥሮ የበደለውንም መሬት ለመሃንነቱ ምክንያት ሲሰጡ “እገሌ የሚባል ስርዓት ስለ ጨቆነን ነው” ይላሉ። ስልጣን ሲይዙ ደግሞ የለፈፉለት የሰው መብት ጥበቃ እና እል የሃብት ክፍፍል ልፈፋ  ንደለፈፉት ሳይሆን ‘ግድያ ፤ ጭፍጨፋ ፤ ማሰቃየት” እያስፋፉ ሃብት እየዘረፉ ‘ሁሉም ነገር ወደ ትግራይ ማቋቋም’ ዘመቻቸው እየተመሩ በአሳፋሪ ድምዳሜ ስርዓታቸው ተደመደመ።

አጼ ዮሐንስ እና አሉላ የጉራዕን እና የዶጋሊን ድል ተጠቅመው ምጽዋን መያዝ ሲችሉ ያንን ድል ሳይጠቀሙበት ወደ ላ ሲመለሱ እና ጣሊያን መሰረቱን ሲጥል አሁንም ተጠያቂ የሚያደርጉት ያው ምኒሊክን/ሸዌዎችን/ ነው። ምንሊክ ዓድዋ ላይ የተገኘው ድል ተጠቅመው ወደ ኤርትራ ሄደው ጣሊያን ባለማስወጣታቸው ኤርትራ ሄደች ብለው ምንሊክን ሲከስሱ፡---- አጼ ዮሐንስ እና አሉላ ግን የጉራዕን እና የዶጋሊን ድል ተጠቅመው በማግሰቱ ምጽዋን መያዝ ሲችሉ ያንን ድል ሳይጠቀሙበት በመቅረታቸው ጣሊያን ወደ መሃል እንዲቆጣጠር ዕድል አገኘ ሲባሉ፤ መልሳቸው ዛሬም “ንጉሡ  ዱርቡሽ ለመውጋት ወደ ጎንደር ስለሄዱ ነው መልሳቸው” (ሌላውን አጋጣሚ ዕድሎች ሳናናሳ በዚህ መልሳቸው እንኳ ስንመለከት ምንም እንኳ ጊዜው የዱርቡሽ ወሬ ሳይሰማ የሁለት ወር ልዩነት እና በቂ ጊዜ ቢኖርም)። የሚገርመው ደግሞ ከዶጋሊ እስከ ምፅዋ ያለው ርቀት 10 ማይል ወይንም 16.7 ኪ/ሜ ነው። በመኪና የ 18 ደቂቃ ጉዞ ሲሆን በተዋጊ እግረኛ በጥንቃቄ ቢኬድ የሁለት/ሦስት ሰዓት ጉዞ አይሆንም። (ከዓድዋ ወደ ምፅዋ ያለው ርቀት እና፤ ከዶጋሊ ወደ ምፅዋ ያለው ርቀት ጠላትን ለመምታት ያለው ልዩነት እና አስቸጋሪ እና አመቺነቱን እራሳችሁ ፍረዱት። ያውም ጣሊያን በመላዋ ኤርትራ ተንሰራፍቶ በነበረበት ወቅት ለምኒሊክ ተዋጊዎች ሊገጥም የነበረው ኤርትራ በናንዳ እና ጣሊያን ሠራዊት ያለው ስፋት እና አስቸጋሪነቱን ፍረዱ ) በሁለቱ የቦታ ርቀት እና የቦታ የተዋጊ ምሽጎች ብዛት እና ሽፋን ያለው ልዩነት ይታያችሁ።

አጼ ምኒሊክ ከጣሊያን ጋር በደብዳቤ ሲሞዳሞዱ ነበር እያሉ ሲወነጅሏቸው፤ በሌላ ወገን ድግሞ አጼ ዮሐንስ ከጣሊያን ጋር ለምንስ የደብዳቤ እና የሞዳሞዱን ባሕሪ መረጡ ተብለው የመልስ ምት ሲጠየቁ ‘መልስ የላቸውም። ወያኔዎች እና የትግሬ ምሁራን ውዥምብራም ውሸት በዚህ ብቻ  አላቆሙም፤ ምንሊክ በትግሬዎቹ ለዕርዳታ ጥያቄ ተጠይቀው ትግሬዎችን ነፃ ለማውጣት ከሸዋ ገስግሰው ጣሊያንን ዓድዋ ላይ ድል መትተው ትግሬዎች ከጣሊያን ቀንበር ነፃ ካወጥዋቸው በላም “ምኒሊክ” ወደ ትግሬ የመጣው ትግራይ በወቅቱ በመላ አገሪቱ በላይ ብር ስለነበረ የትግሬን ኗሪ ብር ለመዝረፍ ነው የመጣው” ይላሉ። አለፍ ብሎም “ምኒሊክ የመጣው ትግሬዎችን ለመከፋፋል እና ማንነታችን ለመደቆስ ነው” እያሉ ወንጅለዋቸዋል።

የትግሬዎች ውሸት በዚህ አላበቃም።

አጼ ዮሐንስ የአጎታቸው ልጅ የሆኑት የራስ አርአያ ድምጹ ልጅ (የዮሓንስ እናት (ወ/ሮ ስላስ) እና የደበብ አባት ‘ራስ አርአያ ድምጹ’ እህት እና ወንድም ናቸው) ስለ ደጃች ደበብ አርአያ ለጣሊያን ንጉሥ የጻፉት ደብዳቤ ስንመለከት እንዲህ ይላል፦ “ደጃጅ ደበብ ጣልያኖች ወዳጆቼ ናቸው እና ውደዱልኝ ብየ ብላቸው እምቢ ብለው ከአንገት በር አድፍጠው ተሰልፈው ቆይቶው ተዋጉኝ ፡ እግዚአብሔር ቸርነት በእመጽዮን አማላጅ  እና በእርስዎ ጸሎት ድል አደረግቸው እሳቸውም ሞቱ።” (ይድረስ ለጎጠኛው መምህር -ደራሲ ጌታቸው ረዳ ገጽ 230 (Archivio Storic? (Ethiopia) XV 1895 -Roma) ሲሉ ለሮማ ንጉሥ ኢምቤርቶ ደብዳቤ ሲጽፉ ግን ዮሐንስ ትግሬ ስለሆኑ ባንዳ አይባሉም። ምኒልክ ለጣሊያን ፍቅር የሚገልጽ ተመሳሳይ ደብዳቤ ሲጽፉ ግን ምኒልክ ‘ባንዳ” እና የጣሊያን ወዳጅ ነበሩ ይሏቸዋል።(ይድረስ ለጎጠኛው መምህር ገጽ 226- ደራሲ ጌታቸው ረዳ 2002 ዓ.ም)

ራስ መንገሻ የወላጅ አባታቸው የዮሐንስ “የፈረስ ኮርቻ” ለጣሊያን ሲሽልሙም ሆነ፤ በራሱ እና በጣሊያኖች መካካል የተፈረመው ውል “ራስ (መንገሻና ዤኔራል ጋንዶልፊ) “የኢጣሊያን መንግሥት የሚጠላ ለራስ መንገሻ ጠላት ነው። የኢጣሊያን መንግሥት የሚወደው ወዳጅ ነው። ራስ መንገሻ የኢጣሊያ መንግሥት ይወደዋልና ያከብረዋል። ህዳር 29 ቀን 1884 ዓ.ም” (Historica Diplomatica…Rosetti PP.108-111” (ይድረስ ለጎጠኛው መምህር ገጽ 226- ደራሲ ጌታቸው ረዳ 2002 ዓ.ም) የሚል “የአገር ክሕደት” የሚያሳይ ውል በትግሬዎች ሲፈረምም ያው የትግሬ ምሁራን ውንጀላቸው በሌላው ክፍል ብቻ ነው።

ውረደት ጭቆና፤ ማንነት… የሚሉዋቸው መገለጫዎች ሁሉ በራሳቸው ገዢዎች ሲፈጸሙ ምንም አይደለም። በሌሎች አድራጊነት በትግሬዎች ላይ ሲፈጸም ግን “አድልዎ፤ አሉታ ፤ መገለል፤ ሁለተኛ ዜጋ ….” የሚል ሓረግ ቅጥያ ይሰጠዋል።  ብታምኑም ባታምኑም በእነዚህ የታሪክ አተላዎች ምክንያት እኔ እንደ ትግሬነቴ እንደዛሬ ትግሬነቴን ያስጠላኝ የታሪክ ዘመን የለም። ምን ቢደረግ ነው እንዲህ ያለ ወገንተኛ እና የውሸት ጎርፍ ማሰቆም የሚቻለው? ውሸታቸውን ከማጋለጥና ለእውነት ስል እራሴን በውሸታሞች ምላስ  ለስድብ እና ለመገለል ከማጋለጥ ባሻገር ምን ማድረግ እችላለሁ? ምንም!!

ደብረጽዮን ዛሬም የሚከስሰው ያው ኢትዮጵያን እና አማራውን ነው። ትግሬውን እንዲህ አደረገው፤ ምኒሊክ ከጣሊያን ጋር ሲሞዳሞድ ነበር…ነው… ክሳቸው። እኛ ከሌለን በሚኒሊኮች ትጠፋለህ ወዘተ…እያሉ የውሸት ጋጋተው ሕዝቡን ይመግቡታል። እነ ደብረጽዮንም ሆኑ ከነሱ በፊት የነበሩ የትግራይ ገዢዎች በራሳቸው ጎሳም ሆነ በሌሎቹ ጎሳዎች ተመሳሳይ ድርጊት እንደፈጸሙ ማስረጃ ሲቀርብ ግን እንደማምለጫ የሚጠቀሙት መሳርያ “በውሸት ሕዝብን ማደናገር” ነው።

“ወያኔዎች ሰውን ከነ ነብሱ ጉድጓድ ውስጥ ከትተው፤ሰውነቱ ተልቶ ትሎች በጆሮው እና ባፍንጫው በአፉ እየተርመሰመሱ በቁሞናው በትል እየተበላ ቀዳው እና አጥንቱ ፈርሶ የሲኦል ሞት  እንዲሞት ያደርጉ ነበር” የሚል ክስ ሲቀርብባቸው (አሞራ የሚለው መጽሐፍ በግደይ ባሕሪሹም ይመልከቱ) ወይንም አረጋውያንን እሳት አንድደው ገላቸው እየለበለቡ ሲያሰቃዩዋቸው ነበር ለሚለው ክስ  መልስ የላቸውም። የወያኔ ገበና ማሕደር መጽሐፍ ልጥቀስ እንዲህ ይነበባል

“እኔን ለማቃጠል። ቀጭን እንጨት እና የሚቀጣጠል ሳር ዙርያየ ደርድረውበታል።ሊያቃጥለኝ የቆመው መርማሪየ ሰውየ እጁን ዘርግቶ በመለካትአንድ ክንድከለካ ኃላ እኔን ከዛፉ ጋር የፍጢኝ አስሮ ማገዶውን በዙርያየ ከምሮ የፍጥኝ እንደታሰርኩ ከዛፉ ዙርያኩምትር” ብየ እንድቀመጥ አዘዘኝ። በአንድ ክንድ ርቀት በዙርያየ የተከመረው ሳር እና ቀጫጭን እንጨት በሳር አቀጣጥሎ እሳት ለኰሰበት። እንጨቱ መጀመሪያ ጭስ ማውጣት ጀመረ፤ ሳሩም መቀጣጠል ጀመረ ጭሱ አፈነኝ። ጭሱ ሲያፍነኝ መተንፈስ አልቻልኩም ጨነቀኝ። ጥልቅ ባሕር ውሃ ውስጥ ጠልቀህ ተውጠህ መውጫ እናዳጣ ሰው ነው ትንፋሽ አጥሮኝ የተሰማኝ። ጭሱ በዙርያየ እንደ ጉም እየተልመለመለ ሲነሳ መርማሪየ  አሳቱ ይበልጥ እንዲቀጣጠል ቆሞ ይቆጣጠራል፤እኔኑም ያየኛል። ጭሱ ወደ እኔ እየገፋ እየበረታብኝአፈነኝ ሲያፍነኝ መሳል፤መተንፈስ አልቻልኩም። በጣሙን ጨነቀኝ። ነፋሱ በርትቶ ጭሱን ካስወገደው ላ፡-እንጨቱ እየተቀጣጠለ ወደ አሳት ተቀይሮ መንደድ ጀመረ። ነፋሱ ነበልባሉን በሁሉም አቅጣጫ ወደ እኔ ዙርያየ ይገፋው ስለነበር ገላየን መለበለብ ጀመረው።……..”  

(የቃለ መጠይቁ ምንጭ የወያኔ ገመና ማሕደር”- ደራሲ ጌታቸው ረዳ እና የደጀን ራዲዮ አዘጋጅ ዶ/ር ሃይለማርያም አበበ)።

በማለት ከላይ ያነበባችሁትን የሰው ልጅ እንደ በቆሎ እሳት ውስጥ ሲጠበስ፤ ያውም አረጋውያን ሽማግሌዎች በአሰቃቂ የግፍ ድርጊት ሲካሄድባቸው ወያኔዎች ሁሉንም የማድረግ መብት አለን ይላሉ። ከላይ ያነው ግፍ የተካሄደባቸው ፊታውራሪ ገዛኢ ረዳ ሲሆኑ፡ የተፈጸመውም ትግራይ በረሃ ውስጥ በወያኔዎች የጫካ ምርመራ ክፍል ነው። ወያኔዎች ስላለፉት ስርዓቶች በትግሬዎች ስለደረሰው ስለ የማንነት መብት ግፍ እና ጭቆና ሲያወሩ፤ እነሱ ለፈጸሙት አሰቃቂ ግፍ ለምን እንደተፈጸሙት ሲጠየቁ ግን መልሳቸው “ትግሉ የጠየቀው አሰራር ስለነበር በወቅቱ መፈጸም ነበረበት ካልሆነ እዚህ ባልደረስን” የሚል የሌባ ዓይነ ደረቅ መልሶ ልብ ያደርቅ ዓይነት የሚል መልስ ይሰጣሉ። ለወንጀላቸውም ይቅርታ አይጠቁም፤ ምከንያቱም “ትግሉ ዳር ለማድረስ የተደረገ ግዳጅ ነበር ነውና” የሚል መልስ ይሰጣሉ።

ይሕ አሰቃቂ ምርመራ እንዲካሄድ ያደረገው መርማሪ ደግሞ የወያኔው አየርፎርሱ ጀኔራል አበበ ተክለሃይማኖት (ጆቤ) ነው። አበበ ዛሬ የፖለቲካ ተንታኝ እና  የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ነው። በጆቤ መርማሪነት የተካሄደው ጭካኔ እንደተፈጸመ በራዲዮ የሰጡት ቃለ መጠይቅ በግል ሳወያያቸውም ብዙ ጊዜ ይህንን ግፍ እና ከሳቸው ጋር አብረው ታስረው እና በእሳት ተለብልበው የሞቱ በራሴ ቤተሰቦች ላይ የተፈጸመ ወንጅልም ጭምር ነግረውኛል። ታዲያ እነ ደብረጽዮን ሰለማንነት እና የመብት ረገጣ ሲያወሩ ሓፍረት የሚባል የላቸውም።

በማንነታችን አፍረን ነበር…የኢትዮጵያ ታሪክ ጨቁኖን ነበር… የሚለው ደብረጽዮን መነሻው ምንድ ነው? ለሚለው ከወያኔነቱ ሌላ ‘ደብረጽዮን ከትግራይ እና ከኤርትራዊያን ቤተሰቦች የተወለደ’ ከመሆኑ ጋርም ለኢትዮጵያ ያለው ጥላቻ ግፊት ሰጥቶታል። በዚህ ትችት ርዕስ የተመለከተው የትግራይ ሕዝብ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ሲታይ ነበር የሚለው ውሸት ያስተጋባው ባለፈው ሰሞን ነሓሴ 2010 ዓ.ም መቀሌ ከተማ በተካሄደው ‘አሸንዳ’ በተባለው በዓል ለአሸንዳ ተሳታፊዎች እና ተከመልካቾች ባደረገው ንግግሩ ነው።

ደብረጽዮን ያለ ምንም የታሪክ ይሉኝታ ያስደመጠን በትግርኛ ያስተላለፈው ይህንን ውሸቱን ሳደምጥ የተሰማኝ ስሜት ከመገረም አልፌ ፤ የወያኔዎች የውሸት ባሕሪ ድግምግሞሽ ስለገረመኝ “ሰው ስንት ጊዜ ይዋሻል?” የሚል ጥያቄ ጫረብኝ። በመጽሐፍ ቅዱስ በ10ቱ ቃላት ውስጥ የቁጥሩን ቅደም ተከል ባላስታውሰውም “በሃሰት አትምስክር” የሚል አለ። ወያኔዎች በኮሚኒስቶች መመሪያ ሕግ የሚያምኑ እና የመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች እንዳልሆኑ ባውቅም፤ ውሸት መልክ አለው ይባላል። መጠን ሲባል ከባድ እና ቀላል ለማለት ይመስለኛል። እንደ ሰው ሁላችንም ብንዋሽም ብንሳሳትም ‘ስንዋሽ እንዲህ ያለ ለመቀበል የሚከብድ ውሸት ግን ለመቀበል ዝግጁ የሆነ ሕዝብ ከሌለ ዋሾች እንዲሁ ከመሬት ተነስተው ሊዋሹ አይችሉም የሚል እምነት አለኝ።

 በትግራይ ሕዝብ ፊት ቆሞ “አንተ ሁለተኛ ዜጋ ነበርክ” “ወያኔ የትግራይ ሕዝብ መብት አስጠባቂ ነው ወያኔ አልገረፈህምአላሰቃየህምአልገደለህም..” የጨቆኑህ ያሰቃዩህ አማራዎች ኢትዮጵያ እና ሰንደቃላማቸው ናቸው፡’ ብሎ ሲናገር ከደብረጽዮን ይልቅ የተገረምኩት በትግራይ ሕዝብ እና ምሁር ላይ ነው። ሁለተኛ ዜጋ ነበርክ ተብሎ ሲነገረው ‘ያለ ምንም ተቃውሞ (ያለምንም ሪኣክሽን) አድምጦ ዝም ሲል ሕዝቡም ሁለተኛ ዜጋ ነበርኩ የሚል እምነት እና ወያኔ አልበደለኝም የሚል ስሜት አለው ማለት ነው። ያ ባይሆን ኖሮ ይኸኔ ብዙ ተቃውሞ መደመጥ ነበረበት።ግን አልሰማሁም። ለዚህ ነው ጊዜ ልስጥ እና እስኪ ከትግራይ ሰዎች ተቃውሞ ካለ ላድምጥ ብየ ወዲያውኑ መልስ ላለመስጠት የዘገየሁት።

ደብረጽዮን ትግሬዎች በማንነታችን እንድናፍር  የተደረገበት በቋንቋችን እንድንሸማቀቅ የተደረገበት የታሪክ አጋጣሚ ነበር ሲል ኢትዮጵያን ይከስሳል። ለመሆኑ ይህ የሚከተለው ግጥም የገጠሙት አማራዎች ናቸው ወይስ ኢትዮጵያ የምትባል በትግሬዎች ታሪክ እየተወነጀለችው ያለቺው አገር ነች የገጠመቺው? እስኪ እንመልከተው ይህንን ግጥም፤-

“ዓድዋ አኽሱም ሽረ ጹሩያት ተጋሩ
ራያ እንደርታ ተምቤን ጎረቤት አምሓሩ”

      ትርጉም  

“ዓድዋ አክሱም እና ሽሬ የጠሩ ትግሬዎች
ራያ እንደርታና ተምቤን ያማራ ጎረቤት

በማለት በትግራይ ውስጥ የትውልድ አዉራጃና አካባቢ፤በጎጥ እና የወንዜ ልጅ፤ የደም ያጥንት የዘር ጥራትና ቆሻሻነት የበላይነትን በሚያንጸባርቅ የናዚዎች እና የፋሺስቶች ቅስቀሳ እና ትምክሕት የሚገልጽ ግጥም ገጣሚው እራሳችን ትግሬዎች ነን! አይደለም እንዴ? ታዲያ በራሳችን ማንነት የዘመትን ሰዎች በምን ሞራል ነው ሌላውን በማንነታችን ተጮቁነናል ተሰድበላል አፍረናል፤ተገልለናል፤ በአሉታ ታይተናል .. እየተባለ በሕዝብ ፊት ሌላውን ለመወንጀል የሚዋሸው? በዚያ ምክንያት ይሆን ሦስቱ አውራጃዎች የጠሩ ትግሬዎች ስለሆኑ እንደርታዎች እና እነዚህ የተጠቀሱ የአማራ ጎረቤቶች ተብለው የተገጠመላቸው አካባቢዎች የራሳቸውን የትግርኛ ልሳን ጥለው በአክሱም ሽሬ ዓድዋ እና ኤርትራ ትግርኛ መናገር የጀመሩት?

በየፓልቶኩ እና በትግራይ የሚሰራጩት ራዲዮኖች፤ቲ/ቪ፤ መጽሔቶች ሙዚቀኞቻቸውንገጣሚዎችን….ብትመለከቱና ብታደምጡ ፡ በጣም ትገረማላችሁ!!! ተምቤኖች ማይጨዎች አጋሜዎች እንደርታዎች መሆናቸውን የምታውቁዋቸው “እነዚያን” ለመሆን ሲከጅላቸው ከምላሳቸው ጋር የሚያደርጉት ትግል ባያስታውቅባቸው እንደርታዎች መሆናቸውን ለማወቅ ያዳግታል። እኮ ለምን እንዲህ ሆነ? መሸማቀቅ ፥ በራስ ልሳን ማፈር መስሎ መሄድ……ማንነትን የመሸሽ ክስተት ምን አመጣው? ያውም በዛሬው በትግሬዎች ንግሥና ዘመን!

የነዚህን አውራጃ ባሕላዊ ልሳን ማን ነው እየተጫነባቸው ያለው? አማራው ወይስ ከ “አሽዓ” የመጡ የወያኔ ትግሬ መሪዎች? ትግርኛ ትግረኛ ነው፤ የሚለው የማታለያ (*ሽዋዳ) ክርክር ካሁን በፊት በስፋት ስለጻፍኩበት እዚህ አልደግመውም። የአማራ ጎረቤቶች ላለመባል ለመሸሽ  ከሆነ የማንም ይሁን የማንም  ቋንቋ ልሳን  ተናጋሪ ከቅጥያ የማንኳሰስ ልጠፋ ነፃ ስለማይሆን ራስን እና አካባቢውን መስሎ መኖር የማንነት ምልክት ስለሆነ ራስን ከመፈተሽ እና ሌላውን ከመወንጀል መቆጠብ ነው። ኦነጎች ‘ጋላ’ የሚለው መጠሪያ ‘ስድብ’ ነው ብለው ‘ኦሮሞ’ በሉን ሲሉ “ኦሮሞዎች” ኦሮሞ ስለተባሉ ከንቀት እና ከስድብ ነፃ ይሆናሉ ብሎ መመኘት የሰው ልጆች ባሕሪ ያለማወቅ ነው። ባጠቃላይ አጭበርባሪዎች ሰራንልህ ብለው በሕዝቡ ሕሊና እየተጫወቱ ለመጻደቅ የሚጠቀሙበት ማጭበርበርያ ስልታቸው ነው። ይህ ሁሉ ውሸት ለምን ነገሰ? ስንት ጊዜስ መዋሸት ይቻላል?
 
ሰው ስንት ጊዜ ይዋሻል? ለሚለው ጥያቄ መልስ ስፈልግ አንድ የስነ ልቦና ጥናት ምሁር ባደረገው ጥናት እንደሚለው ከሆነ ሰው በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ 1.65 ጊዜ ወይንም ከዚያ በላይ ይዋሻል ይላል። ይህ ጥናት “አቨረጅ” ከሚባሉት ማለትም “ተራ ዜጋ” እንጂ የፖለቲከኞችን አይጨምርም። እነሱ ጋር ሲሆን አጅግ ከፍ ያለ እንደሆነ እገምታለሁ።

የኛዎቹ ዋሾች ለየት የሚያደርጋቸው ምላሳቸው ብቻ ሳይሆን እጆቻቸውም በሰው ደም የተቀቡ ስለሆነ ሲዋሹ የተመዘገቡት የውሸት ሚዛኖች ያልፉዋቸዋል። የዓለም ዘፋኞች ለውሸት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ይሁን አይሁን ባላውቅም ውሸት ተቀባይነት እያገኘ ሄዷል። “አወሻሸትህን ወደድኩት” የሚሉ ዘፋኞች አሉ፡ (I love the way you lie) የሚሉ ዘፈኖች ተቀርጸው ለገበያ ሲቀርቡ ከፍተኛ ገበያ አላቸው። የኛ ዘፋኞችም እንዲያ ያለ ዘፈን እንዳላቸው አሁን ስሙን ባላስታውሰውም አድምጫለሁ።

የትግራይ ሕዝብ እንዲህ ያለ ውሸት በላዩ ላይ ሲዋሽበት እንዴት ሊቀበለው ቻለ የሚለው የስነ ሉቦና እና የኣእምሮ ሊቃውንት የመልሱት። ይህ ሁሉ የተማረ ትግሬ ፤ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ የመጣ የትግራይ ትወላጅ፡ ከጥላሁን ግዛው ከብርሃነ መስቀል እስከ እነ በረከት ሃብተስላሴ እስከ ሰንቱ የትግራይ እና የኤርትራ ተወላጅ ዲታ/ታጁር / የናጠጠ ነጋዴ አስመጪ እና ላኪ ባለ ዜታው የጭነት መኪና ስንቱን ሻምበል ሰንቱን ጀኔራል ስንቱን ኮለኔልስንቱን ዶክተር ስንቱ ደራሲ ስንቱን ዳኛ እና ጋዜጠኛ ስንቱ ተዋናይ እና ታዋቂ ሙዘቀኛ ፥ ስንቱ የትግራይ ተወላጅ ሹመኛ እና ሓብታም ስም ዝርዝር ጠቅሰን ያልቃል? ትግሬዎች በምን መልኩ ነው “እንደ ደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች” በማንነታቸው ተዋርደው እና አፍረው በሁለተኛ ዜጋ ይታዩ እን አሉታዎ ዜጋ  ሲታዩ የነበረው? በየትኛው የታሪክ ዘመን? ለመሆኑ ወላጆቻችን መስርተዋታል የሚሏትን ኢትዮጵያን ያውቁዋታል? አያውቁዋትም። እንዲያ ባይሆን ኖሮ ስብሓት እንዲህ ባላለ ነበር፡_

“ያቋቋምነውን ኮንስቲትዩሽን የሚቀማን ፤ የሚያደናቅፈን ሃይል ከመጣ እንገነጣጠላለን። እኛ ይኼ ኮንስትትዩሽን ከተቀማን… እንደገና እደግመዋለሁ! እኛ ይኼ ኮንስትትዩሽን ከተቀማን ወይንም ለቀማን እንደገና ጦርነት እናዉጃለን! ወደ ውግያ እንሄዳለን ! ወይንም ደግሞ ተገነጣጥለን የየራሳችንን መንደር እንይዛለን።፡ይህ ኮንስትትሽን የማንነታችን መለኪያ ስለሆነ ማንነታችንን የሚቀማን ከመጣ “እንደነት” የሚባል ነገር አይኖርም!”
በማለት አለቃቸው ስብሓት ነጋ ነግሮናል። (“ዲሞክራቲክ ፎረም ፎር ዲሞክራሲ ኤንድ ሲቪሊቲ” በታባለ የወያኔ አሽቃባጭ ፓልቶክ ቀርቦ ከተናገረው ቃለ መጠይቅ የተገኘ - አውድዮ (የድምፅ ማስረጃ ወደ ጽሑፍ የተረጎመው ‘ይድረስ ለጎጠኛው መምህር- ደራሲ ጌታቸው ረዳ - ገጽ 142)

አሁን ናዚያዊ ሕገመንግሥታቸው የሕዝብ ቅዋሜ ደርሶት በመቀማት ላይ ነው። ስብሓት ያኔ ከ8 አመት በፊት የተናገረውን ትንቢት እውን ለማድረግ ይሆን ደብረጽዮን ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለትግራይ ሕዝብ አስሬ በመዋሸት ዘመቻ ተጠምዶ ሲዋሽ ያደመጥነው?

የሕዝቡን በተለይ የወጣቱን ሕሊና ለመጥለፍ ይህ ሀሉ ተደጋጋሚ ውሸት እየተዋሸ ሲደመጥ የሚያሳየን እውነታ “የትግሬ ሕዝብ ያዋጣናል ብሎ እስካሁን ድረስ ወያኔዎችን አቅፎ ደግፎ እንደተከላከለላቸው ሁሉ ዛሬም ያንኑ ቀጥለውበታል የሚያስብል ነው”። ሕዝቡ “አይዞኹም ናይና!!! (የኛዎቹ - አይዟችሁ) እያለም እየዘፈነላቸው ነው። እንዲህ የሚሉም ጥቂት ካድሬዎች ናቸው የሚለው ማጃጃያ በኔ በኩል አልቀበለውም። ምክንያቱም በዛው ልክ ተቃውሞ ሲስደምጠን አልሰማንም አላየንም። አይዟችሁ የኛዎቹ የሚለው የኳስ ጨዋታ ቡድንተኛ መፈክር በተወጣተረ ፖለቲካ ውስጥም ጠቀሜታ አለው ተብሎ ለዕልቂት ማበረታቻ የሚያገለግል መፈክር ከሆነም ጠቀሜታው አብረን እናየዋለን።

ምንም ቢዋሹ ፤ ምንም ቢገድሉ፤ በግፍ የታፈሰ መንገደኛ ታሳሪን ቤተሰብ ተጥረቶ ውክልና ሳያረጋግጥ ሆስፒታል ተወስዶ ባስገዳጅ ሁለት እግሩ እንዲቆረጥ አድርጎ እንደገና ቁስል ሳይድን ዝቅዝቅ ሰቅሎ በመደብደብ የተካፈሉ ትግሬዎች  ምንም ቢዘርፉ፤ የእስረኛ ብልት ቢያኮላሹም ፤ ምንም የፈለገው ወንጀል ይስሩየኛ ናቸው” እና አሳልፈን አንሰጣቸውም ሲሉ እንደ እነ አብርሃ ደስታ የመሳሰሉ የትግራይ ወጣት ምሁራኖችም እየተከላከሉላቸው ነው።

በእነ ደብረጽዮን ውሸት እንደ የበጋይት የከብት አይዞህ የኛ  “የመንጋዎች” መፈክር” በሚደወልለት ቃጭል እየተመራ በመክነፍ ላይ ያለው ያልተገራ ጉዞ ለትግራይ ሕዝብ የሚጠቅም መፈክር ከሆነ መሰንበት ደግ ነው፡ እንሰንብትና ውጤቱ እናየዋለን። በወንጀለኞች ውሸት እየተነቃቃ “የትግራይ ሕዝብ ዜጋነቱ በአሉታዊ ሲታይ ነበር እየተባለ ትግሬዎች ከደቡብ አፍሪካ ጥቁሮች ጋር የሚያመሳስለው የደብረጽዮን ውሸቶች እና እንበታተናለን የሚሉ የወንጀለኞቹ መፈክሮች ትግሬዎች የወያኔዎች የውሸት ምሽግና መከታ መሆን የለባቸውም።

ጌታቸው ረዳ (Ethiopian seamy አዘጋጅ)