Friday, June 27, 2014

የአማራን ህዝብ በማጥፋት ወያኔና ተቃዋሚው በጋራ እየሰሩ ነው
ከአዘጋጁ ፦ (ጌታቸው ረዳ Editor Ethiopian semay)
መስታዎት ይገዛል ሞኝ የጨዋ ልጅ

ሁሉን የሚያሳየው መሰንበት ነው እንጂ!

ይድረስ መልዕክቴ እራሱን በዲሞክራሲ መስተዋት ለማየት ለሚጃጃለው ተቃዋሚ

ቀደም ብዬ በቃለ መጠይቄም ሆነ በተለያዩ ጽሑፎቼ “ተቃዋሚ ሚባል” እንደሌለ እና አለ የተባለለት ተቃዋሚም ‘በሰካራሞች፤ የሃይማኖት እና የፖለቲካ እውሮች እንዲሁም በአእምሮ በሽተኞች” በተጣበበው የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓልቶክ ሩም የማይሻል፤ መነሻው እና መድረሻው የማያወቅ የተሰነጠቀ እንስራ ነው ብየ ብዙ ጊዜ ተናግሬአለሁ።
አገር ውስጥም ሆነ ውጭ አገር ያለው “ተቃዋሚ እና ጋዜጠኛ” አማራውን አንደ ኢትዮጵያዊ ቀርቶ እንደሰው እንኳ ማየት ያቃተው፤ ስቃዩን በጎን አይቶ የሚያልፈው “የወያኔ ተባባሪ’ ከመሆን አልቦዘነም። ባለፈው ወር “የኦሮሞ ወጣቶች እንዲህ ሆኑ፤ ኦሮሞዎች ተገደሉ፤ ኦሮሞ ታሰረ….” እያሉ ፤ፓልቶክ ክፍሎችን፤  መድረኩን እና ራዲዮናቸውን እንዲሁም ድረገጸቻቸውን ሲያጣብቡ፤ ታዋቂ ሰዎችን እየጋበዙ ሲያስለቅሱ ያልባጁት ነገር የለም።

አስገራሚው ደግሞ፤ ያውም አማራው ልክ በወቅቱ እየተገፋ ፤እየተገደለ፤ እየተባረረ፤ ንብረቱ እየተዘረፈ በነበረበት ሰሞን ነው። “የምኒልክ ሃውልት ይፍረስ ማለት “የዲሞክራሲ” መብታቸው ነው፤ ኦኖጎች እንዲህ ሆኑ፤ አብካችሁ እዩላቸው፤ስቃያቸው እያሉ” ሲያደነቁሩን መሰንበታቸው ታዝበናል።

በተከታታይ ያለማቆም ዛሬም “በወያኔ እና ወያኔ የሾማቸው ባለስልጣን አሽከሮቹ”  እንዲሁም  “በኦሮሞዎች” (ከዚህ በታች ያለውን ቃለ መጠይቅ ኦሮሞዎች በወንጀሉ እየተባበሩ እንዳሉ ይመሰክራል) በአማራ  ገበሬ እና ኗሪ ላይ “ግድያ ፤ዝርፍያ፤ ጭፍጨፋ፤መባረር” እየገጠመው ነው። ተቃዋሚው ይህን በደምብ ያውቃል። የደላው ተቃዋሚ “የዲሞክራሲ ጥያቄ” ሲጠይቅ “ያልታደለው የአማራው ገበሬ ደግሞ “ነብስ ግቢ በነብስ ውጪ” መካካል ተወጥሮ ወላጆቹ ታግለው ያቆሟትን አገር “ገሃነም” ሆናበት፤ ግማሽ እግሩ ጉድጓድ ከትተውት ከጉድጓዱ የሚያወጣው እሪ ሲል ፤ “ተቃዋሚው”  አጠርምሞ “ሰምቶ አንዳልሰማ” ደልቶታል እና “ስለ ዲሞክራሲ፤ስለ ሕገ መንግስት፤ በየመጽሄቱ፤ በየቲቪው፤በየራዲዮናቸው እና በየፓልተኩ፤ ሲፈላሰፉ እያየናቸው “ ይገርመና  አሎ!” (ገርሞናል)።  
አንዳንዱ ስለ ጀግኖቹ እየመዘዘ እንቅልፍ አጥቶ ስለ እነሱ ሲጽፍ ያድራል።
አንዳንዶቹም ስለ አፍሪካ አንድነት እና የጋራ ገንዘብ ፍልስፍናቸውን ያስነብቡናል። ወዘተ….ወዘተ… እነዚህ በጣም የተማሩ እና በሚጽፉትም ብዙ ማሳመን የሚችሉ የአማራ ሕዝብ ጥቃት እና የወያኔን ወንጀል ለዓለም ዐቀፍ ምሁራን እና ድርጅቶች መነጋገር እና አቤት በማለት ፍሬ ማስገኘት የሚችሉ ምሁራን ናቸው። አስገራሚው ነገር ደግሞ በነገዳቸው “አማራዎች” ናቸው። በጣም ተመችተዋቸዋል። ምን እንበል!

አማራው ጸሐፊ እና ጯሂ አጥቶ የአማራ አዛውንቶች ክቡር ትከሻቸው በስድ አደግ ወረበሎች በዱላ እየተደበደቡ ከደቡብ እና ከኦሮሞ አካባቢዎች እንዲወጡ እየተደረገ ነው። ተቃዋሚ ሆይ! ዲሞክራሲህን ለነገ አቁም እና “በነብስ ውጪ ነብስ ግቢ” ተወጥሮ ያሉት አረጋዊያንን ተከላከልላቸው፤ አድናቸው። ካልቻልክም “ጭኾታቸው እንኳ አስተጋባላቸው”። እነሱም አንደ ኦሮሞቹ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።!!!!!!!! ተቃዋሚ ሆይ! ነግቶ እስኪ መሽ ስለ ዲሞክራሲ እና ሕገመንግሥት ስትፈላሰፍ “ዛሬ ስለ ዲሞክራሲ ለማሰብ የቻልክባት ቀን ነገ ስለ ዲሞክራሲ ሳይሆን ስለ ሕልውናህ ለማሰብ ትገደዳለህ”። አሁን ወደ ቃለ መጠይቁ ይዣችሁ ልግባ። ገበሬዎቹ ምን ይላሉ -  እነሆ!፦   
የአማራን ህዝብ በማጥፋት ወያኔና ተቃዋሚው በጋራ እየሰሩ ነው
 ከግለሰብ የተወረወረ ትዝብት

አቶ አዲሱ አበበ አርብ ጁን 20 2014 በአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ያስተላለፉትን ቃለ መጠይቅ ቃል በቃል በጽሁፍ ገልብጨ ከአውዲዮው ጋር እንድልክላችሁ ያነሳሳኝ ሆን ተብሎ በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈጸመው ዘር ማጥፋት፣ ድርጊቱን ቀጥታ በሚፈጽሙት አካላት ብቻ ሳይሆን የወያኔ ትግሬዎችን የጎሳ ፖለቲካ እንቃወማለን የሚሉ ሳይቀሩ ሆን ብለው የተሰሳተ መረጃ በመስጠት በአማራው ህዝብ ላይ የክህደት ስራ እየሰሩ ለመሆኑ ለመጠቆም እና አንባቢም ቃለ መጠየቁን በማንበብም ሆነ ቃለ መጠየቁን ከተለያዩ ድህረገጾች በመስማት ያራሱን ፍርድ እንዲሰጥ ነው። በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈጸመው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ዘመቻ በወያኔና የሱ ተናካሽ ውሾች በሆኑ የብሄር ድርጅቶች ብቻ ሳይሆን፤ በኢትዮጵያ ስም የተደራጁ ፓርቲዎች፣ ድርጅቶች፣ ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ ድህረገጾች ወዘተ ጭምር በጋራ የሚተባበሩበት ለመሆኑ የሚጠይቅ አይምሮ ያለው ያስተውለው።

ተፈናቃዮች አማራ ናችሁ ተብለን ከወለጋ ተፈናቀልን እያሉ፤ አቶ አዲሱ አበበ አማረኛ ተናጋሪዎች ተፈናቀሉ ይላሉ። በአማረኛ ተናጋሪነት ከሆነ ከወለጋ የተጠየቁ አፈናቃዮችኮ በአማረኛ ነው ከአቶ አዲሱ አበበ ጋር የሚነጋገሩት፤ አቶ አዲሱ አበበ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጋዜጠኛ ስለሆኑ፣ እንዲሁም የአሜሪካ መንግስት ከምንም ጊዜ ይበልጥና ከማንም በላይ የወያኔ ትግሬዎችን መንግስት በገንዘብና በሰው ሀይል ስለሚረዳ አቶ አዲስ አበበ ከቀጣሪያቸው አቋም ውጭ ሊሆኑ አይችሉም ብንል፡ ከአማራው ኪስ በሚወጣ መዋጮ የሚንቀሳቀሱ እንደ ኢሳትና ሌሎችም በየሀገሩና በየከተማው የተቋቋሙ ሬዲዮ ጣቢያዎችና ድህረገጾች፣ የአማራው ህዝብ አማራ በመሆናችን ብቻ ተነጥለን፤ ሀብትና ንብረታችን ተዘርፎ፣ ተደብድበን፣ ከፊሎችም ተገለው ከሞት አምልጠን እዚህ ደረሰን ሲሉ፣ ”ከባለቤቱ ይበልጥ ያወቀ ቡዳ ነው” እንደሚባለው፤ አማራ ስለሆኑ አይደለም፤ አማረኛ ተናጋሪ ስለሆኑ ነው ብለው በአማራው ህዝብ ላይ አማራ በመሆኑ ብቻ ወንጀል እንደላልተፈጸመበት አድርገው የተዛባ ማስተባበያ ለህዝብ ጀሮ ያቀርበዋል።  ከዚህ ተጨማሪ ስለዚህ መፈናቀል የዘገቡ ኢትዮጽያዊ የሚባሉ ድህረገጾችና ሬዲዮ ጣቢያዎች ብዙም ባይሆኑ፣ ለይስሙላ የዘገቡም ዘግበውም በነጋታው ከድህረገጻቸው ያነሱ ድህረገጾችንም ታዝቤአለሁ።

ብአዴን ማን ነው ሲሉ አቶ ገብረመድህን አርአያ ሰፋ ያለ መረጃ ሰጠውናል። ብአድኖች ከመጀመሪያው ”አማራ ህዝብ ጠላት አይደለም” ያሉትን የገደሉና ከዚያም በአማራው ህዝብ ላይ በየክፈለሀገሩ እየዞሩ የአማራውን ህዝብ ነጥለው በመሪነት ያስገደሉና ያሰደዱ ለመሆኑ መረጃዎች አሉ። አሁንም ከዚህ ቃለ መጠየቅ እንደምንረዳው የኦሮሞና የአማራው ክልል ባለስልጣኖች ይሄን ያህል አፈናቅሉ፤ ይሄን ያህል ግደሉ፤ ይሄን ያህል ደግሞ ለፖለቲካ መልሱ እየተበሉ በእቅድ የሚፈጽሙት የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል መሆኑን ቃለ መጠይቁ ይጠቁማል።

በአቶ አዲሱ አበበና በሬዲዮ ጣቢያቸው ላይ እንዲያውም ስለመፈናቀሉ በመዘገባቸው ባለውለታ እንጂ ቅሬታ የለኝም። ሌሎች በተቃዋሚነት ተሰልፈናል የሚሉ ግን አሁንም ቢሆን ለይስሙላ የሚጠይቁት ”ወደ ቀያቼው እንዲመለሱ” የሚል ነው። አንድ ሰው አማራ በመሆኑ ብቻ ሀብት ንብረቱ ተዘርፎ፤ አቅመ ደካማ የሆኑ ሚስት ልጆቹ፣ በእድሜ የገፉ እናት አባት ተገለው፤ ቤቱ ተቃጥሎ ”ወደ ቀያቸው ይመሰለሱ” የሚለው ፍርድ በአማራው ህዝብ ላይ ለሚፈጸመው የዘር ማጥፋትና ማጥዳት ወንጀል ተባባሪነት ካልሆነ በቀር ትክክለኛ ፍርድ አለመሆኑን ህሌናችሁ ፍርድ ይስጥ።

አንድ ሰው አማራ በመሆኑ ብቻ ሀብት ንብረቱን ተቀምቶ፣ የተገደለው ተገሎ የሚፈናቀል ከሆነ፤ አንድ ከአማራ ወላጆች የተወለደ ኢትዮጵያዊ መብቱ ተከብሮ ለመኖሩ የጊዜና የቦታ አለመገጣጠም ካልሆነ በቀር ዛሬ ወለጋ በሚኖሩ አማሮች ላይ የደረሰው መገደልና መፈናቀል በሱ ወይም በሷ ላይ እንደማይደርስ ምንም አይነት መተማመኛ የለም። ብሄረተኝነት የግለሰቡን ብሄር አንጂ የግለሰቡን ሰብአዊ ባህሪ አይቶ ይህ ደግ ነው ተወው፣ ያ ክፉ ነው በለው አይልም። ስለዚህ ማንም ከአማራ ወላጆች የተወለደ ሁሉ በወያኔ ትግሬዎችና የነሱም ተናካሽ ውሾች በሆኑ የብሄር ድርጅቶቹ አንዲሁም ከሀገር ውጭ መረጃ በማጣመም፣ በአማራው ህዝብ ላይ የሚፈጸመውን ወንጀል በማስተባበልና ማእቀብ በማድረግ ከወያኔ ትግሬዎች ጋር በአጋርነት የተሰለፉ ሬዲዮ ጣቢያዎችና ድህረገጾች የአማራን ህዝብ በማጥፋት ወንጀል እየተባበሩ ለመሆኑ ከኔ ጽሁፍ ይልቅ ትንሽ ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ያለው ሰሞኑን በወለጋ በአማራው ህዝብ ላይ በተፈጸመው ግድያና መፈናቀል ድህረገጾችን አይቶ፣ ሬዲዮ ጣቢያዎችን አዳምጦ ይፍረድ።

ከግለሰብ የተወረወረ ትዝብት

ቃለ መጠይቁን ለማዳመጽ ይሄንን ይጫኑ፣ በጽሁፍ ለማንበብ ከታች ያለውን ይመልከቱ

የአሜሪካ ራዲዮ ጣቢያ ከተፈናቃዮች ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ፣
ጁን 20 2014
ከወለጋ በተለይም ከግንቢና ከቄለም ከግንፍሌ ወረዳ ተባረርን ደግሞ ቤት ንብረታችን ተቃጠለ ያሉ የአማረኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት ባህር ዳር እንደሚገኙ ይናገራሉ። ቁጥራቸው እስከ 3000 ይደርሳል የሚሉ እነዚህ ተፈናቃዮች የአማራው ክልል አስተዳደር መፍትሔ እንዲፈልግላቸው በመጠባበቅ ላይ መሆኑንም ተመልክቷል። የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት በበኩሉ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ100 በታች ነው ይላል። አዲሱ አበበ ተፈናቃዮችንና ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት አነጋግሮ ተከታዩን አጠናቅሯል።

አቶ ጋሻው ፈቃደ የተባሉና ሌላ አንድ ስሜ አንዳይገለጽ ያሉ ተፈናቃይ ጨምረን አወያየን፣ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት የምእራብ ወለጋ ዞን ተፈናቃዩ ከወር በላይ ሆኖናል ብለው ይጀምራሉ።
አሁን 1 ወር ከምናምን እየሆነው ነው ምክንያቱ የድሮ ታሪክ ነው የሚያነሱት፤ ሚኒሊክ እንደዚህ አድርጎን፣ እንዲህ አድርጎን ነው የሚሉት፤ በጣም አሳደዱነ፤ የከተማው ህዝብ እንዳለ ወጥቷል እንደገና ባለስልጣኖች ደግሞ አሉበት፡ ፖሊሶች እነዚህ አድማ በታኝ የሚባሉት አብረው ነው ሲዘርፉና ሲደበድቡን የዋሉ ማለት ነው። አማራ የተባለውን።
እኮ ምክንያቱ ምንድነው አሉዋችሁ፤ በትክክል?

ምክንያቱ የድሮ ታሪክ ነው፣ እነሱ እንገነጠላለን ምናምን ነው የሚሉት፤ እራሳችን ነጻ እናወጣለን፤ አማራን አንፈልግም፣ አማራ ይውጣልነ ነው። እና ህይወታችን የተረፈው በስንት ነገር ነው። ኮርኒስ እየገባን ጫካ እየገባን በስንት ነገር ነው። ብዙ ሰው ሞቷል።
ስንት ጊዜ ሆኖት እርሶ ወለጋ ሲኖሩ?

እኔ 11 ዓመቴ ነው፣ ወደ 5 ቤተሰብ አስተዳድራለሁ፣ ሱቅም ነበረኝ፣ ጣቃ አከፋፍል ነበር፣ ጣቃውን እንዳለ ዘርፈውኛል።
ስንት ሰው ከዚያ ተሰደደ? ከወለጋ ከግንቢ በተለይ? እርሶ ካሉበት ቢያንስ ከ8000 የማያንስ ህዝብ ነው።

ባህርዳር የአማራው አስተዳደር አለ እዚያ ደግሞ ሄዳችሁ አላመለከታችሁም? ምን አሉዋችሁ?
ወደ ቤታችሁ ተመለሱ ነው የተባልነው፣

ወዴት ወደቤታችሁ?

ወደነበራችሁበት ተመለሱና እናረጋጋለን ምናምን ነው ያሉን፤ እነሱ ደግሞ አሁን እራሱ አልተውም
ሌላው አቶ ጋሻው ፈቃደ ይባላል፤ የመፈናቀላችንን ምክንያት በውል አልተረዳነውም፤ ይሉና ይቀጥላሉ።
ምክንያቱ ምን  እንደሆነ እኛ ያወቅነው ጉዳይ የለም፣ ለኛ በኳስ ነው ምናምን ነው የሚሉት
ኳስ ማለት በባህርዳር ከተማ ላይ ኳስ ጨዋታ ተካሂዶ ነበር፣ የአማራ ክልል ህዝብ ኦሮሞዎችን ጋላ! ጋላ! አሉን፣ እና የኛ ሰው ደግሞ የተደበደበ ሰው አለ። እያሉ ነው ለኛ ሲናገሩት የነበረው።

እናንተ እዚያ አልሄዳችሁም? ለምን እናንተን ውጡ አሉዋችሁ ብዬ ነው?
እኛም ግራ የገባን እኮ እሱ ነው፣ ከዚያ ወደዚያ ሰው ተይዞ መመከር እያለበት ለምን በስመ አማራ ለምን እኛ ይሄን ያክል መበደል አለብን የሚለውንኮ አቤቱታ ስናቀርብ አቤቱታችንን እዚህ ደግሞ አልቀበልም ያሉ።
ስንት ሰው ነው በጠቅላላ የተፈናቀለ ወይም እንዲወጣ የተደረገው?

ቢያንስ ከግንቢ ከተማ ብቻ አንድ 3000 ሰው ይሆናል። ያልወጣም እዚያ የቀረም ህዝብ አለ፤ በቃ ህይወታችን እስከሚያልፍ መጠበቅ ነው እንጂ ያለብን እንዴት እናደርጋለን?

ሌላ ሰው ሳናግር እንዲሁ ከ2000 ሰው በላይ ነው የሚሉኝ፤ ይሄን ያህል ሰው ሲፈናቀል እዚያ አካባቢ አስተዳደሩ፤ የፖሊስ ጣቢያው፤ የመንግስት ባለስልጣናት የሉም? ወይም እናንተ ሄዳችሁ አቤት ለማለት አልሞከራችሁም? አቶ ጋሻው።
ሄደን አቤት ብለናል፤ ግን ሊቀበሉን አልቻሉም፣ ሄደንም አመልክተናል አቤቱታችንን እያቀረብን ነው እኛ ያለነው አሁን ለነሱ

ለማን ነው አቅርበን እንቢ አሉን የሚሉኝ?

ርእሰ መስተዳደር ሄደን ነበር እኛ፣ ርእሰ መስተዳደሩ

ለማን ነው አቅርበን ነበር የሚሉኝ፣ ለባህርዳር?

አዎ ባህርዳር ከተማ ላይ፣

እና ምን ተባል…?

ከ5 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት ተቀጠርን፣ 8 ሰዓት ደግሞ ውጡ አሉን።

ሰው ምረጡ ተብሎ ሰው መርጣችሁ ከላካችሁ እንዴት እንደገና ውጡ ይላሉ ብዬ ነው። ማ ቢሮ ነበር ልትገቡ የፈለጋችሁ?
እዚያ እርሰ መስተዳደሩ ላይ፤ በቃ አስተዳደሩ፤ እሱን ፈልገን ነበር እኛ ርእሰ መስተዳደሩን
ፕሬዜዳንቱ ቢሮ ነው ወይስ ምክትላችው ወይስ ጸሀፊ ጋ ወይም

አዎ፣ ርእሰ መስተዳደሩ ቢሮ ነው እንጂ

ለመሆኑ የአካባቢው ባለስልጣናት ምን አሉ? እናንተስ አቤት ብላችሗል? ላልሁት ጥያቄ የጸጽታ ሀላፊ ናቸው፤ እርሳቸው ሁሉንም ያውቃሉ፤ በማለት የአንድ ሰው ስምና ቁጥር ሰጠውኝ ደወልሁ

አቤት፤ አቤት

እንደምን ዋሉ? አቶ አወቀ

አቤት፤ ማን ልበል?

አዲሱ እባላለሁ፤ ከዋሽንግቶን ነው የምደውለው፤ ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ
ይሄን ስልክ አላውቀውም፤ ከየት ነው?

እንዳልሁት ከአሜሪካ ነው የምደውለው፤ ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ፣ ከዋሽንግቶን፣ ከቪኦኤ
እ...!

ከዚያ አካባቢ ተፈናቀልን የሚሉ ሰዎች ኢንተርቪው አድርጌ ነበር፤ እና እርሶ የሚያውቁትን ነገር ቢነግሩኝ?

ከየት?

ከቄለም አካባቢ፤ ከግንቢም አማረኛ ተናጋሪዎች

 የት ሄድን? ወዴት ተፈናቀልን አሉ?

ተባረው ባህር ዳር ጎጃም ውስጥ ነው  ያሉት፤ ሰፈራ ጣቢያ አግኝተው?

ማን ነው ያባረረው?

እርሶ የሚያውቁትን እንዲነግሩኝ ነው አቶ አወቀ፤ አሁን የምደውለው ነዋሪዎችም ባለስልጣናት ናቸው ያባረሩን ይላሉ፤ ሁለቱንም

እነማን ናቸው እነሱ መጀመሪያ?

የሰዎቹን ስማቸውን ነው የሚፈልጉት?

አዎ

በሺዎች የሚቆጠሩ ናቸው፤ ነገረ ግን ጥያቄዬ ከቄለምና ከግንቢ አካባቢ እንዲባረሩ ሆኖዋል ወይ? እንዲወጡ ተደርጓል ወይ? የጸጽታ ክፍሉ የሚያውቀው ነገር አለ ወይ? እምሎት።

እኔ የጸጽታ ክፍል አይደለሁምና ከህዝብ ነኝ፤ እና ማን ነው ያለ? መጀመሪያ ንገረኝ፣
እርሶ ……

ከዚያ በሗላ ነው የማውቀውን የምስጥህ እንጂ የሆነም ያልሆነም ነገር ልሰጥህ አልችልም ማነው ያለህ?

አቶ አወቀ የጸጽታ ሀላፊ ናቸው ተብሎ ነው ስልኩ የተሰጠኝ ልክ አይደለም?

ውሸት ነው፤ የጸጽታ ሀላፊ አይደለሁም። እኔ ሌላ ስራ ነው ይዤ ያለሁ፤ የጸጽታ ሀላፊውን ልትጠይቅ ትችላለህ።

እርሶ በምን ውስጥ ነው ያሉት? ስለዚህ ጉዳይስ የሚያውቁት ጉዳይ የለም።

እኔ የድርጅት ጽህፈት ቤት ነኝ

የተባረሩ አማረኛ ተናጋሪዎች ስለመኖራቸው አያውቁም?

የተባረሩ የሉም። ያባረረም የለም።

የእርሶ ቢሮ ሀላፊነቱ ምንድን ነው? አቶ አወቀ፤ የድርጅት ጉዳይ ሲሉ ምንድን ነው የምትሰሩት?

የኦህዲድ የድርጅት ጉዳይ ነው

እና የኦህዲድ ጽህፈት ቤት ይሄን አያውቅም?

የተባረረ ሰው የለም እያልሁህ እኮ ነው፣ በራሳቸው ፍላጎት ሊሄዱ ይችላሉ እንጂ ያባረረ ሰው የልም፡ እያልሁህ እኮ ነው፤ ቄለብ ወለጋ ስትል ከቄለብ ወለጋ የተባረረ ሰው የለም። እንደዞኑ የምናውቀው ነገር የለንም።

ከትናት በስቲያ ማክሰኞ ወደ ኦሮሚያ የመንግስት ኮሚኒኬሽንስ ጉዳዮች ቢሮ ደወልሁና የቢሮ ሀላፊዋን ወይዘሮ ራዲያ ኢሳን አገኘሁ። ምንም የምናውቀው ነገር የለም አሉኝ። ዛሬስ ያውቁ እንደሆን ብዬ እንደገና ወደ ወይዘሮ ራዲያ ቢሮ ደወልሁ፣ በቁጥሩ ላይ ነው ያልተስማማነው እንጂ ማወቁን ያውቃሉ።

ሁለት ሺ ሶስት ሺ ተፈናቀለ የምትለው አይደለም

ከነሱ የሰማሁትን ነው

መቶ የማይሞሉ ሰዎች ናቸው

ከሁለት ቦታ ነው የሰማሁት ከግንቢና ከቄለም

አዎ ቄለም ወለጋ አሼ ቀበሌ ነች አይደለ፤

አዎ አሼ ቀበሌ ነው ያሉኝ

የሆነ ወንጀል ተፈጽሞ ነበረ

ማን ነው የፈጸመው?

እንድ ሰው ሞቶ ነበር፤ የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ የሆነ ቀጥሎ ደግሞ ሁለት ሰዎች ባልታወቁ ሰዎች ተገለዋል፤ ከፍርሀት ተነስተው ነው እነዚህ ሰዎች ክልል ሶስት የሄዱት፤ መንግስት ..
ከፍርሃት ማለት?

መንግስት፤ ፖሊስ፤ እዚያ ያለው አስተዳደር የሚባለው ስህተት ነው። አሁን እንዲያውም ወደ ቄያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ ነው ያለው ቁጥሩ አይደለም ወሳኙ፤ ነገር ግን ሰዎቹ ሁለት ሺ ሶስት ሺ ይላሉ፤ እርሶ 100 አይሞላም ይላሉ። ግን በፍርሀት ነው የወጡት የሚሉኝ ለምን ነው የፈሩት?

ነገርሁህ እኮ፤ በዚያ ቀበሌ አካባቢ ወንጀሎች ተፈጽመዋል፡ እንደነገርሁህ ወንጀሉን ይፈጽማሉ ተብሎ የሚገመተው ያው እየተፈለገ ነው።

ሁለት ሰው ወይም ሶስት ሰው ወንጀል ተፈጸመበት ሞተ ብለውኝል፤ መቶ የማይሞሉ ሰዎች ደግሞ ፈርተው ወጡና፣ እነዚህ ሁሉ የሚፈሩበት ምክንያት በመጠርጠር ስማቸው ተነስቶ ነው? ነገሩ ትንሽ የሚያያዝ አልሆነልኝም።

የተጠረጠሩ አይደለም። እኔ እስከማውቀው ድረስ ፍርሀት በቃ፤ አሁን ነገርሁህ እኮ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ አስተዳደሩም እየሰራ ነው፤ ወደ ንብረታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ነው።

እነዚህ ከመቶ የማይሞሉ እርሶ እንዳሉት ሲሰደዱ ወይም መፈናቀላቸውን መቼ ነው የእርሶ ቢሮ ያወቀው?
እንደ መንግስት ይሔን ሁለቱም የክልሉ መንግስታት ያውቁታል፤ የምናስተዳድረው ያው አንድ ሀገር ነው፤ ያው ክልሎች እራሳቸውን ያስተዳድሩ እንጂ መናበቡ ነገር አለ።

ይሄ ከሆነ መናበቡ አለ፣ ትናት ስደውል ምንም የምናውቀው የለም ብለውኛል። እና መቼ ነው ያወቁት? የእርሶ ቢሮ ያወቀው
አሁንም አሁንም አንተ የምትለው ከ2000 እስከ 3000 የምትለው አንተ ያነሳህልኝ ቁጥርና እኔ የማውቀው ቁጥር በጣም ስለሚለያይ
ቁጥሩ አይደለም ወሳኙ፤ አንድም ሰው ቢሆን ብዙ አመት ከኖረበት መፈናቀሉ ሊያሳስበን ይገባል ማለቴ ነው። ቁጥሩ አይደለም ወሳኙ፤ አሁን ደግሞ ፌደራል እዚያ ሄዶ እንዲያረጋጋ ተብሏል ተባለ፤ ነገር ግን ፌደራል አልሄደም። እንዲያውም እዚያ ያሉት ሰዎች እንዲወጡ እየተደረገ ነው የሚሉኝ ሰዎቹ።

እንግዲህ እኔ አሁን ያለኝን ትክክለኛ መረጃ ነው እየሰጠሁህ ያለሁት

እሺ

መንግስት እዚያ ያለው አስተዳደር የማረጋጋቱ ስራ ሌሎችም እንዳይፈናቀሉ ማለት የወጡትም ደግሞ እንዲመለሱ አማራ ክልል መንግስት ጋርም እየተናበቡ እየተሰራ ነው።

በጣም አመሰግናለሁ ሰላም ይዋሉ

እሺ

ለመሆኑ የአማራው ክልል ርእሰ መስተዳድር ምን እያደረገ ነው? ወደ አማራው ብሄራዊ ክልል መንግስታዊ ጽህፈት ቤት ደውዬ ፕሬዜዳንቱ የሉም ስለተባለ ወደ ሌላው ከፍተኛ ባለስልጣን ወደ አቶ ሰማ ቢሮ ተመራሁ፤ ከባለጉዳይ ጋር መሆናቸውን የገለጹልኝ ጸሀፊያቸው ወይዘሮ አዝመራ ከ 5 ደቂቃ በሗላ እንድደውል ነገሩኝ፣ ደወልሁ፤ አሁንም ከባለጉዳዩ ጋር እንዳሉ ናቸው ተባለ፤ ከ15 ደቂቃ በሗላ ደውል ተባልሁ፤ ደወልሁ፣ አስቼኳይ ስራ ገጥሟቸው አሁን ከቢሮ ወጡ ተባለ፤ በዚሁ አበቃሁ። በሌላ ጊዜ እንሞክራቸዋለን፤ የተፈናቃዮችን ሁኔታም እንከታተላለን፤ ላሁኑ በዚሁ ላብቃ፣ ሰላም። /-0-----/   Ethiopian Semay (getachre@aol.com)