Friday, March 26, 2010

የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጩ የማንነት መግለጫዎች- ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ የሚኖራቸው ሚና

የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጩ የማንነት መግለጫዎች- ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ የሚኖራቸው ሚና ዩሱፍ ያሲን ኦስሎ ኖርዌይ የኢትዮጵያና ኤርትራ ሕዝቦች ወዳጅነት ኮንፊረንስ ሳን ሆዜ፣ ካሊፎርኒያ ማርች 12 እስክ14፣ 2010 የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጩ የማንነት መግለጫዎች- ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ የሚኖራቸው ሚና የዛሬ 19 ዓመት ገደማ ከኢትዮጵያ ሙሉ ነጻነቷን በማወጅ ኤርትራ ተብላ የዓለም የመንግሥታት ማሕበረሰብ የተቀላቀለችው የአህጉራችን አዲሲቷና የመጨረሻይቱ ሃገር በታሪክ ወስጥ በተለያዩ ስሞች ነበረ የምትታወቀው።ነገር ግን በዚሁ “ኤርትራ” በተሰኘው መጠሪያ ተጠርታ አታውቅም። ከበርካታዎቹ በታሪክ ከሚትታወቅበት ስሞች ጥቂቶቹን እንመልከት።ምድሪ ባሕሪ፤ ባሕረ ነጋሽ፤መረብ መላሽ በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ናቸው። ክፍለግዛቱ በሙሉ ሓማሴን ተብሎ የሚጣራበት ጊዜም ነበረ።ሓማሴን የተሰኘው አንድ አውራጃ ስም ለጠቅላላው አካባቢ መጠሪያና መታወቂያ የተሰጠበት ሆኔታ አልፎ አልፎ እንመለከታልን።በመሓል ኢትዮጵያም ሆነ በአጓራባቿ ትግራይ ሓማሴን ትናንትም ዛሬም ለደጋው ኤርትራ ነዋሪ በተለይም ለክርስትያኑ ማሕበረሰብ መለያ አድርገው መጠቀማቸው ከዚሁ አጠራር የመነጨ ነው።በማህል ሃገርም አልፎ አልፎ ሓማሴን የሚለውን ስያሜ ለአካባቢው ሁላ በጥቅም ላይ ሲወል ይታያል። አንድ እውነታ ግን ልያከራክረን አይገባም። በ1890 ጣልያን ይህንን አካባቢ በቁጥጥሩ ሥር አውሎ ለአዲሲቷ ቅኝ ግዛቱ ኤርትራ የተሰኘ ስያሜ ከመስጠቱ በፊት ኤርትራ የሚባል ቦታ፤አካባቢ ወይም ሃገር አልነበረም።አራት ነጥብ።ከዚያ በፊት ኤርትራ እንደ ሃገር ኤርትራውያንም እንደ ሕዝብ በዚህ አካባቢ ነበሩ ከሚሉት ጋር ጉንጭ አልፋ ክርክር ለመግጥም ዝግጁ አይደለሁም። በዚህ እውነታ ላይ ስምምነት ከተደረሰ ዛሬ ኤርትራ ወስጥ ካሉት 9ኙ በሔሮች አንዱና ዋነኛው የሆነው ትግሪኛ የተሰኘው በሔረሰብ ጣልያን ከመምጣቱ በፊት ነበረው ወይ ነው ቀጣዩ ጥያቄያችን።ካልነበረ እነዚያ በኤርትራ ደጋ አካባቢ በትክክል በሓማሴን፤ በሠራዬና በአከለጉዛይ አውራጃዎች ነዋሪ የሆኑ ወገኖቻችን በምን ስም ነበረ የሚጠሩት ወይም የሚታወቁት? ሰበረ፤ ሰብ ቀድሚ ምስባሩ፤ ስሙ እንታይ ነበረ፤ ጓያ (ሰበረ) ሰው ከመስበሩ በፊት ስሙ ምን ነበረ እንደሚሉት መሆኑ ነው።ይህ አባባል የዬተኞቹ ትግርኛ ተናጋሪዎች አባባል እንደሆነ አትጠዩቁኝ። በትክክል አላውቀውም።አሁንም ለክርክር መቅረብ የሌለብት አንድ ሌላ ጉዳይ አለ። ስማቸው ምን ይሁን ምን ጣልያን በመጣበት ጊዜም ሆነ ዛሬ ይህ ማሕበረሰብ የሚናገረው ቋንቋ ምንነት ላይ ብዥታም ሆነ ጥያቄ አይነሳም።ቋንቋቸው ልክ በአጎራባቹ ትግራይ የሚነገረው ትግርኛ ቋንቋ ነውና ።ልክ በአጎራባቹ ትግራይ ወንደሞቻቸው የሚናገሩበትን ቋንቋ ተንጋሪዎች ናቸው፤ ያለጥርጥር።ሰለዚህ እነሱም ትግሪኛ ተናጋሪዎች ናቸው።በኢትዮጵያ ትግራይ ነዋሪ የሆነው ብሔረሰብ ራሱን ተጋሩ ወይም ትግራዎት ብሎ ይጠራል። ይህ በሔረሰብ በአጎራባች በሔረሰቦች በተለያዩ መጠሪያዎች ይታወቃል።ይህም በኢትዮጵያቸን በበሔረሰቦች መካከል ያልተለመደ አይደለም።በማሓል ሃገር በአማርኛ ተናጋሪው ዘንድ ትግሬ ተብሎ ይታወቃሉ።በሔረሰቡ በራሱ ማንነትም ሆነ ሰለሚናገረው ቋንቋ የሚያሻማና የሚያነታርክ ቁም ነገር የለም።የሚያከራክርም ጉዳይም የለም።በአንፃሩ በኤርትራ ሰላሉት ተመሳሳይ የትግርኛ ተናጋሪዎች ይህንኑ ማለት አንችልም፤አያስኬድም።የሚናገሩት ቋንቋ ያው ከመረብ ወንዝ ሻገር በትግራይ የሚነገርው ራሱ ትግርኛ መሆኑን አይክዱም።የእኛው የትግርኛ አነጋገር ዘዬ የጠራና የተለየ ነዉ የሚሉትን እንደተጠበቀ ሆኖ ማለታችን ነው።የሚያከራክረን፤የሚያነታርከንና አሻሚ ሆኖ ለጽሁፋቸን መነሻ የሆነው ግን በኤርትራ ወስጥ ያሉት ትግርኛ ተናጋሪዎቹ ልዩ ማንነት መለያና የብሔረሰቡ አሰያየም ጉዳይ ብቻ ነው። ሁለቱ የትግርኛ ተናጋሪዎች እንደ ማሕበረስብ አንድ ቋንቋ እንጂ አንድ መጠሪያ ስም የላቸውም።ይህንን በአጽንኦት የሚናገሩት የኤርትራ የፖሎቲካ አድራጊዎች ማለት የፖሎቲካ ፓርቲው ፤ መንግሥትና የሕብረተስቡ መሪዎች ናቸው።ሕዝቡም ይህንን ተከተሎ የጋራ መጠሪያ ስም የለንም ባይ ነው።ሰለሁለቱ በምናወሳበት ወቅት ትግሪኛ ተናጋሪዎች ብለን ለመጥራት የተገደደነውም ለዚሁ ነው።ለምን ትግሪኛ ተናጋሪዎች እንላቸዋለን? ሌላ የወል መጠሪያ የላቸውም ወይ? ለምን የላቸውም? ከሌሎቹ ድንበር ሻገር (ዘልል) ብሔረሰቦች በምን ይለያሉ? በምንስ ይመሳላሉ? በዚሁ ረገድ ድንበር ዘለል ከሆኑት ከኩናማ፤ከአፋርና ከሳሆዎቹ በምን ይመሳሰላሉ? በምንስ ይለያያሉ? ለጹሑፋችን መንደርደሪያ መነሳት ያለበቸው ጥያቄዎች ናቸው። የሁለቱ ሃገሮች ድንበር ሻገር የሆኑት ሌሎቹ እንደ ኩናማ፤ ሳሆና አፋሮቹ ዘንድ ይህንን ዓይነቱ አንድ የመሆንና ያለመሆኑ ጉዳይ ሲያከራክር ወይም ሲያሻማ አንመለከትም።አያከራክርምም አይሻማምና።ኤርትራ እንዳንድ ነጻ ሃገር ሆና እውቅና ከተጎናጸፈች በኋላ እንኳን በሁለት ሃገሮች የምንኖረ አንድ ሕዝብ ነን ማለታቸው አልቀረም።አፋሮቹ በጀቡቲም ጭምር ቅርንጫፍ ሰላላቸው በሶስቱ ሃገሮች የምንገኝ አንድ ሕዝብ ነን ማለታቸው አልተውም። አፋር፤ሳሆና ኩናማ o አንድ ቋንቋ ያለን o አንድ ባሕል ያለን o አንድ መጥሪያ ስም ያለን o አንድ ሕዝብ ነን ሲሉ እናዳምጣለን።ትናንተም ዛሬም።አግባብነቱ አጠያያቂ አልሆነም። ለምን ታዲያ የትግርኛ ተናጋሪዎቹ አሰያየም የተለየ አቃቂር አስፈለገው መባሉ አልቀረም።ጉዳይ ከፍተኛ የፖሎቲካ እንደምታም አለው ።ዛሬ የኢትዮጵና የኤርትራ ሕዝብ ለማቀራረብ በምናደርገው ጥረቶች ጋር ተያይዞ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል የሚል እምነት አለን። ሰለዚህ ብዙ ምክኒያቶችን መደርደር ይቻላል።በኤርትራ ያለው ትግርኛ ተናጋሪ ከሃገሪቷ 9 ብሔረሰቦች አንዱ ብቻ ቢሆንም ቅሉ ፤ከኤርትራ ሕዝብ እኩሌታ ይሆናል፤ በቁጥር ደረጃ።ቋንቋቸው ትግርኛ የነፃይቷ ኤርትራ አፊሰላዊ ቋንቋ ነው። የኤርትራ ሕዝብ ቁጥርም ሆነ የሕዝቡ የብሔረሰብም ሆነ የሃይማኖት ስብጥር ስሜት ቀስቃሽ የሆነ በነፃይቷ ኤርትራ በከፍተኛ ጥንቃቄ ከሚያዙት ጉዳዮቹ ዋናው ነው።ምክኒያቱ እምብዛም አያመራምርም።ግልጽ ነውና።ትግርኛ ተናጋሪው በአማዛኙ የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ በመሆኑ በዚሁ ወገንና በሙስሊሞቹ መካካል ያለው ግንኙነት ይመለከታል።የኤርትራ ፖለቲካ ድርጀቶች ብሔራዊ አንደነት የሚሉትን ለሃገርቷ ሕልወና ሲባል በጥንቃቄ የተያዘ ጉዳዩ ነው።ለዚህም ነው የሙስሊሙና የክርስቲያኑ የቁጥር ምጥጥን አምሳ፤ አምሳ ፐርሰንት ተብሎ የሚታለፈው፤ዝንተዓለም። ልክ ሰለ ሊባኖሱ ስብጥር እንደሚነገረው መሆኑ ነው። ስብጥሩን ማወቁም ሆነ ይፋ ማድረጉ አይታሰቤና አይነገሬ ነው። ሰሜን ኢትዮጵያ በተለያዩ ያካባቢ መሳፍንቶች መካከል ሲጧጧፍ በነበረው ቁሩቁስ ባንድ ወቅት እንድ ትግራይ አካል በሌላ ጊዜ ደግሞ ራሱን በቻለ አሰላለፍ ተካፋይና ተዋናይ የነበሩ መሳፍንቶች እንደነበሯት የሚካድ አይደለም።በኢትዮጵያ ታሪክ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ በሚታወቀው የታሪክ ጊዜ ይህንን ግዛት የማስፋፋቱ፤ ማስገቡሩ፤ካንዱ መስፍን ጋር ወግኖ በሌላው ላይ መረባረቡ፤ ተለዋዋጭ የወደጅና የጠላት አፈራረጅና አሰላለፍ ወስጥ የደጋው ኤርትራ መሳፍንት ነበሩበት። በዘመነ መሳፍንቱ ማብቂያ ላይ አጼ ቴድሮዎስ ሃያልነቱን በጦር ሜዳ አስመስክሮ ሁሉን በመጠረንፍ በአክሱም ከተማ ነጉሠ ነገሥት በተባሉበት ሂደት የሃዘጋ ጸዓዘጋ መሳፍንት ነበሩበት።እነ ራስ ወልደሚካል በአብነት መጥቀሱ በቂ ይመስለናል። በኋላ ላይ አጼ ዩሃንስና አጼ ምኒልክ የዘውድ ይገባኛልና የሥልጣን የመነጣጠቁ ቁሩቁስ ወሳኝ ሚና ባይጫወቱም ከጫውታው ውጭ አልነበሩም። እነዚያ መኮንንትና መሳፍንተ ሚወዛገቡት ከላይ በተመለከትናቸው በእነዚያ በአራቱ ወይም በአምስቱ ማዕከላዊው በዚያኑ ዘመን የሃገርቷ እንብርት በነበሩት ትግራይ፤ጎንደር፤ሸዋ፤ጎጃምና ወሎ ባማከለ አካባቢ ነው።እንዚሁ ግዛቶች ናቸው እንግዲህ በተለያዩ መጠሪያዎች ቢታወቁም የታሪካዊቷና ነባሯ ኢትዮጵያ እንብርት ሆነው የሚቆጠሩት፤ በታሪክ ጸሓፊዎች ዘንድ።በሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ አበሲኒያ ፕሮፕር፤ አበሲኒያ ሃርትላንድ ትብለው የሚታወቁት 5 ቱ ኮር ግዛቶች ማለታችን ነው።ላስታና ዋግ ምንም እንኳን የወሎ አንዱ ክፍል ሆኖ ቢታወቁም ቅሉ እንዳንድ ራሱን የቻለ ግዛት ሆኖ መታየቱ አልቀረም።ከአምስቱ በተጨማሪ ማለታቸን ነው።ልክ እንደዚህ ኤርትራም ከላይ በተመለከትናቸው የተለያዩ ታሪካዊ መጠሪያዎች ታውቃ እንዳንድ ራሷን የቻለ ግዛት ሆና የታየችበት ጊዜ ነበረ ማለት ነው። ይህንኑ የዘመነ መሳፍንት እርክቻና ቁሩቁስ ወደ ማብቃቱና አዘንብሎ አጼ ምኒሊክ የነጉሥ ነገሥት ሥልጣንን ጠርንፈውና አጠቃልለው ባንድ ጠንካራ ማዕከል ባማዕከሉበት ወቅተ ላይ ነበረ የኤውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ወደ አካባቢው ብቅ ማለት የጀመሩት።በአድዋ ጦርነት ዋዜማ እኔ ካንተ አላንስም የመሳፍንቶች ፉክክር በቅኝ ገዢቹ አይዞህ ባይነትና የዘመናዊ መሳሪያዎች እርዳታ ታክሎበት ቅጥሎዋል። ያም ሆነ ይህ እስከ ዓድዋ ጦርነት ዋዜማ ድረስ፤ o የጋራ ቋንቋ (እሱም አነጋጋሪ ነው ባዮች አልታጡም) o በሓባሻነት ላይ የተመሰረቱ የጋራ የእሴቶች ሥርዓት o የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነትና ቤተክርስቲያን ቁርኝት o መረብ ሻገር ታሪካዊና ቤተሳባዊ ዝምድናዎችና መወሳሰቦች o ዓዲ፤ ርስቲ፤ የጉልቲ የጋራ ሥሪት o ልማዳዊ የእንዳ አባ ሕጎችና ትድድር ሥርዓቶች ትሥሥሮች በጥብቅ ያቆራኘው አንድ መለያ ማንነት ያለው ትግርኛ ተናጋሪ ማሕበረስብ ነበረ ማለት ያስደፈራል። ከጣልያን ቅኝ ግዛትነት በኋላ ግን ትግርኛ ተናጋሪው ከሌላው ድንበር ተሻጋሪ ማሕብረሰቦች በተጻረረ መልኩና አኳኋን በጋራ እንኳን የምንጠራበት ስም የለንም እስከ ማለት የደረሰበት ፖሎቲክዊና ባህላዊ አዲስ ማንነት አፈጣጠርና የመጎልበት ሂደት ዋና ዋና ምክኒያቶች መመለከቱ ተገቢ ነው።በተለይም ዓድዋ ጦርነት ማግሥት።በቅድሚያ ለዚህ ያበቁ ነበራዊ ሆኔታዎቹን ገረፍ ገረፍ አድረገን እንመልከት።በኋላ ላይ በፖሎቲካ ኤሌቶች ወይም ልሂቃን ሆን ተብለው የተሃነደሱና እንዲፋፋ የተደረገ ግፊቶችን ለጥቆ መመልከቱ ተገቢ ነው። ሁለቱም ማለት የጣልያን ቅኝ ግዛትነት ያስከተለው ለዉጥና በኋላ ለኤርትራ ነፃነት የታገሉ የፖሎቲካ ሃይሎች ለየቅል የሆኑ ጫና አሳደረዋል፤አስተዋፃኦ አብርክተዋል፤ያለ ጥርጥር።ለዚህ ዓለምሰገድ ዓባይ የተጣመሙ ማንነቶች (Jilted Identities-Re-imagined) በተሰኘውና በ1998 በጻፈው መጽሓፉ እየራሳቸውን ሁለት ደርጅቶች ማለት የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባርና ሕዝባዊ ሓርነት ኤርትራ የተለያዩ የማንነት መለያ አቅጣጫዎች መከተላቸውን ያትታል።በሌላ በኩል ሸቲል ቱሮንፎል የተባለ ኖርዌጂያዊ ሶሻል አንቱሮፖሎጂስት War & the Politics of Identity in Ethiopia በተሰኘው አዲስ መፅሓፉ ከደም አፋሳሹ የ1998/2000ጦርነት ወቅትና በኋላ ሁለት ወንድማማች ሕዝቦች የጋራ ትሥሥሮች ከሥር መሠረቱ የሚያናጉ እድገቶች እንደነበሩ በሰፊው ተችቶዋል።ጦርነቱ በማንነት ላይ በተለይም ትግራይ ያሉት ተጋሩ ወይም ትግርኛ ተናጋሪዎች በኤርትራውያኑ የቋን ተጋሪዎቻቸው ላይ የቋጠሩት ቂም አስመልክቶ ጦርነት በጠላትና ወዳጅ ምስል ቀረፃ ላይ የሚያሳድረው ጫና በሰፊው አብራርተዋል። እነዚህ የጋራ ቋሚ የማንነት መገለጫዎቹ የተሸረሸሩ ቅኝ ገዢዎቹ በፈጠሩት አዲስ ፖሎቲካውና ማሕባራዊ ሆኔታዎች ግፊትና አስገዳጅነት አዲስ የማንነት መፈጠር መጀመሩ አሌ የማይባል ሓቅ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ቅኝ ገዢዎቹ በፈጠሩትና በኋላ ኤርትራን ለማስገንጠል በ1962 የነጻነት ጦርነት የተያያዙት ነጻ አውጪ ድርጅቶች ለዓላማቸው መምቻ አዲስ ኤርትራዊ ማንነትና አንድ የተለየ ሃገርና የተለየ ሕዝብ ስሜት እንዲያብብ ከፍተኛ ቅስቀሳ አድርገዋል።የተወሰነ ውጤትም አስመዝግበዋል፤ያለ ጥርጥር። የሁለቱ ተግባራት ተደጋጋፊ ቢሆኑም ቅሉ ለየብቻቸው መመለከቱ ተገቢ ይመስለኛል።በተለያዩ የታሪክ መጻሕፍት ተመዝግቦ እንደምናገኘው በአሰብ ወደብ ላይ በዚያን ወቅት አንዲት ትንሽ የዓሳ አጥማጆች መንደር አንድ የጣልያን የመርከብ ካምፓኒ ወኪል ከሡልጣን ኢብራሂም ጋር አደረጉ በሚባለው ስምምነት የተወጠነው የኤርትራን ቅኝ ግዛት የማድረጉ ሂደት በ1890 በቀይ ባሕር ዳርቻ ኤርትራ ብለው ስም ያወጡላት መሬት በቀፈፉበት ጊዜ ፍጻሜ ላይ አድርሰዋል።በኋላ በ1893 በውጫሌ ስምምነት በተፈራረሙበት ወቅት ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እውቅና ታክሎበታል። በውጫሌ ውል መፍርስ ሳቢያ የአድዋ ጦርነት ተቀስቅሶ ድሉ የኢትዮጵያ ቢሆንም ቅሉ በኤርትራ ጣልያናዊ ቅኝ ግዛትነት ይዞታ ላይ ያስከተለው ለውጥ አልነበረም።አንድ እውነታ ግን መረሳት የለበትም።ከወራሪው ቅኝ ገዢዎች ጎንም በማበራቸዉና በመሰለፋቸው በንጉሡ አይቀጡ የአካል ቅጣት ደርሶባቸው ወደ ዘመዶቻቸው የተመለሱት ኤርትራውያኑ ሰለ ኢትዮጵያና ንጉሡ ያስተላለፉት ኩፉ የጠላት ምስል እንደነበረ መዘንጋት የለበትም።በአማራ ላይ በጥቅል፤ በሸዋ አማራ ላይ በተለይ ባነጣጠረ ጥላቻ የተበጃጀ ሰእል። ከሌላው ትግርኛ ተናጋሪ የተለየ ኤርትራዊ ማንነት አፈጣጠር ሂደት በዚሁ የተለየ ኤርትራዊ ማንነት፤ መታወቂያና መለያ መበጃጀቱ ሂደት ወስጥ ከዚህ የሚከተሉት ድርግቶችና እርምጃዎች ልብ ማለት ልያስፈልግ ነው፤ o ኤርትራ ዓድዋ ድል በኋላ በአስከሪዎቹ ላይ የተወሰደ የቅጣት እርምጃና በነጉሡ፤ በአትዮጵያና በሸዋ ላይ የፈጠረው ጥላቻ፤ o ኤርትራውያን ከተቀረው ሃገሬው (Indigenous ) ሕዝብ የተለዩ ማህበረስብ አድርጉ የፈረጀው በ1937 ጣልያን ቅኝገዢዎቹ ያወጡት አዋጅ፤ o በ1936 ለኢትዮጵያ ተብጅቶ ኤርትራና ትግራይ ባንድነት ኤርትራ ተብለው የተካለሉበት አዲስ የአስተዳደር ክፍፍል፤ o አስከሪ ተብለው የሚታወቁት የኤርትራ ተወላጅ የጣልያን ወታደራዊ ተመልማዮች ወደ ሊቢያና (ትሩፑሊ) ሶማሊያ መዝመት፤ o ኤርትራን ጠቅላላ ኢትዮጵያ ወረራ ማንኮባኮቢያ መሬት የማድረጉ መሰናዶ በአጧጧፉበት ወቅት በቅኝ ግዛቷ እንዱስትሪ፤የትምህርት፤የከተማና ታሕታይ መዋቅር ግንባታ ያስከተለው ለውጥ፤ o የአጋሚ አውረጃ ተወለጆች ወደ አሥመራ በብዛት መፍለስና በዝቅተኛ ሠራተኛነት መሰማራት፤ ኤርትራዊ የሚባል ማንነትና ሃገራዊ ስሜት ሥር የመሰደዱ ሂደትና የመገንጠሉ ትግል በዚሁ የተለየ ኤርትራዊ ማንነት፤ መታወቂያና መለያ ሥር የሰደደ የመምጣቱ ሂደት ወስጥ ደግሞ ክዚህ የሚከተሉት ድርግቶችና እርምጃዎች ልብ ማለት ልያስፈልግ ነው፤ o የኤርትራ ሕዝብ የተ.መ.ድ.የክፍፍሉን ሓሳብ አለመቀበሉና ዕደሉን እንደ አንድ ሕዝብና አሃድ ለመወሰን የመረጡብት ሂደት፤ o ከ1962 እስከ 1991 ለሰላሳ ዓመታት በመጀመሪያ በ ኢ.አል.አፍ በኋላ በ ኢ.ፒ.አል.አፍ መሪነት በተደረገው የነፃነት ትግል የተፈጠረው ሃገራዊ ማንነትና ስሜት፤ o እነ ኢሳያስ “ንሕናን ዓላማና” የተሰኘው ማኒፈስቶ በክርስትያኖች ላይ በ ኢ.አል.አፍ. የደረስባቸውን ግድያና ጫና ለብቻቸው ተደረጅተው መመከቱ እቅድ፤ በኋላ ላይ የኤርትራ ሕዝባዊ ሃይል(ሻዕቢያ) መፈጥር o ትግርኛ ተናጋሪው በሔረ ትግርኛ ያስኘው ፖሎቲካዊ ትምህርት ለኢ.ፒ.አል.አፍ ምልምሎች መሰጠት መጀመር፤ o ከወያኔ ሓርነት ትግራይ መስርታ ወዲህ ደግሞ የኤርትራና የትግራይ ሕዝቦች ትግል ዓላማና መደምደሚያ የመለያያቱ አስፈላጊነት ፤ o የ 1998.2000 የድንበሩ ጦርነቱና ከኢትዮጵያ ኤርትራውያን በጅምላ ማባረሩ በሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪውች መካከል የፈጠረው የጥላቻ ድባብ፤በዚሁ ሳቢያ ትግራይ ትግርኚ አስተሳሰብና መቀራረብ መኮሰሰ፤ o ዛሬ እንደገና በኤርትራ በሁለቱ ሃማኖቶች መካከል በመፈጠር ላይ ያለው ውዝግብ ክርስትያን ወጎኖቸን ማሳሰብ መጀመር፤ እንዚህና ሌሎች በርካታ እክተሮች በኤርትራ የብሔረ ትግርኛ ኤርትራዊ ብሔርተኛነት እየጎሎበት ነጥሮ እንዲወጣ አመቺ ሆኔተዎችን ፈጥሮለታል። ከነጻነት በኋላ በሔረ ትግርኛ የተሰኘው አጠራር ለትግርኛ ተናግሪው እየተዘወተረና የተለመደ መጥቶዋል። ይህ በትክክል መቼ እንደተጀመረ በውል ባይታወቅም ኢ.ፒ.አል.አፍ ድርጅት ፖሎቲካ ትምህርት ማስተማሪያ ብሎ ባዘጋጃቸው ጽሁፎች አካል እንደ ነበረ መዛግብት ያሳያሉ።በዚሁ ላይ ብቻ መቼ ቆመ። በሔረ ትግርኛ አነሱ አዲሱ ኤርትራዊነት የማንነት መንፍሰ ባለቤቶች መሆናቸው ይበልጥኑ ለማስመሰከር ይጥራሉ።በተልይም ኤርትራ ተገንጥላ ቋንቋቸው ትግርኛ የነፃይቱ ሃገር ቋንቋ ከሆነ በኋላ ትግርኛውን “ኤርትርኛ” ማሰኘት ይዳዳቸዋል።ከእነሱ ቁጥር እጥፍ ደርብ ቁጥር ያላቸው ትግርኛ ተናጋሪ ትግራዎት በኢትዮጵያ ትግራይ መኖራቸው እየታወቀ፣ ኤርትራውያን አዲሱ ሃገራዊ ማንነትና ምንነት ለማጎልበትና ከትግራዊ ማንነት በተቃራኒው ተለይቶና ነጥሮ እንዲወጣ ልዩነቶችን ሆን በለው ያገዝፋሉ።በአንፃሩ የጋራ ትሥሥሮችና እሴቶችን ያንኳሰሳሉ።አሁንም ሆን ተብሎ። በጋራ ትግላቸው ጊዜ የተፈጠረው ወዳጅነት ክደው ከጦርነቱ በኋላ አንዱ ሌላውን ጭራቅና የክፉ ከፉ አድረገው ይስላሉ።በኤርትራና በኢትዮጵያ መረብ ሻገር ያሉትን ሁለቱ ትግርኛ ተናጋሪ ስብስቦችን በመካለልና በማጠር የተለያዩ መለያ መታወቂያዎች የመፍጠሩ ሂደት በምር የተያያዙ ይመስላሉ። ሁለቱም ገዢ ፓርቲዎች በዚሁ በማካለሉና በማጎልበቱ ተግባር ቢጠመዱም በኤርትራ ያለ የትግርኛ ተናጋሪ ወገን ነው ይህንን ሥራዬ በሎ የተያየዘው። በሁለቱ ሕዝቦች መሃል የነበሩትና ያሉት ተመሳሳይነትና ትሥሥሮች የሚክዱትም እነሱ ናቸው። ለዚሁ በቂ ምክኒያቶች ማፈላለግና ማገኘት የሚሳነን አይመስልም። የተለያዩ ተፎካካሪ ማንነቶች እርስ በርስ እየተላተሙና የእተፋጩ ነጥሮ ለመውጣት ቅርጽ ለመያዝ የሚሞክሩበት ፖሮሰስ እንመለከታለን። አንዳንድ ጊዜ “ማንነት የማይዳሰስና የማይጨበጥ ምናብ ወለድ የፈጠራ ውጤት ነው” ይሉናል ማሕበረዊ ሳይንስ ተመራማርዎች።ይህ ደግም ሂደቱን ውስብስብ ያደርገዋል። በሔረ ትግርኛ ማንነት ከተለያዩ አጓራባች ማነቶች ጋር እያላተመ ነው።ጥቂቶቹን ለመጠቃቀስ፤ o ተመሣይ ትግርኛ ቋንቋ ከሚናገሩት ሙስልም ከሆነው ጀበርቲ ማንነት፤ o ትግረ ቋንቋ ተናጋሪ ባመዛኙ ሙስሊም ከሆኑት መታሕት ማንነት o ከኤርትራውያን ቆላ ሙስልሞች በጅመላ ይፎካከራል፤ o ከትግርኛ ተናጋርው ትግራዋይ ብሔርተኛነትና ማንነት ጋር ይፎካከራል፤ o ከሸዋ ኢትዮጵያዊ ማንነት ጋር ታሪካዊ ፎክክሩ አሁንም ኤርትራ ነጻ ከወጣች በኋላም እንዳለ ነው፤ o ከዓባይ ኢትዮጵያዊ ሃገር አቀፍ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛነት ጋር ሕልውናዊ ስጋት አለው፤ በዚሁ ሂደት ኤርትራዊው ትግርኛ ብሔርተኛነት ኤርትራዊ ቡሉኮ ለመደረብ ለምን እንደሚሻ ማወቁ አያስቸግርም።ኤርትራዊነት ወደ በሔረ ትግርኛነት ለመወሰና ለማውረድ ሙከራው ግልጽ ነው።ትግርኛ ቋንቋውንም ኤርትርኛ ማሰኘቱ ከዚሁ ፍላጎቱ የመነጨ ሆኖ እናገኛለን።ካላይ ከተመለክትነው በርከታና ወስብስብ ሂደቶች ለምን ኤርትራ ወስጥ ያለው የትግርኛ ተናጋሪዎች ማንነትና አሰያየም አሻሚና አነታራኪ እንደሆነ በመጠኑ እንረዳለን። በጭሩ ውስብስብ የማንነት አፈጣጠርና አጎሎባባት ሂደት ለመቃኘት ሞክረናል።እውነትኛና ጋህድ የሆኑ ወይም የምናብ የፈጠራ ዉጤት የሆኑትም ሁላ። ማንነት በምናብ የተሳለ የፈጠራ ውጤጥ ብቻ ሳይሆን ተለዋዋጭና በመቀያየር ያለ ፍርጅ ነው።ውስብስበነቱም ከዚሁ ጸባዩ የሚመነጭ ነው። ከትግራዋይ ጋር የጠመዱበት የፍቅርና የጥላቻ ፍርሪቆሹ ለመረዳቱ ሊረዱን የሚችሉ መንደርደሪያዎች አቅርበናል። አንዱ ሌላውን ዝቅ አደርጎ የመመልከት በተለያዩ አልባሌ ስሞች መሰጣጠቱ ሚስጥርም ገለጥ ይላል ብለን እንገምታለን። ማጠቃሊያ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ባንድ ሃገር ልጅነትም ሆነ በሁለት ሃገር ልጅነት ጎን ለጎን መኖር የጂዮግራፊና የታሪክ ግዴታቸው ነው።የሁለቱ ሃገር ሕዝቦች እነዚህ ሁለት አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝብ ሳይነጋገርና ሳይቀራረብ ይቀራረባሉ ብሎ ማሰቡ የዋህነት ነው። እንዴያውም በእኔ እምነት ለሁሉም መቀራረብ ጥረቶች ቅደመ ግዴታ ነው፤ የእነሱ መቀራረብ። አንድ የትግርኛ አባባል አለ ።እንቁጩን አላውቀውም እንጂ።የተጣሉ የአጎት ልጆች ወንድማማች ወላጆቻቸው ሳይነጋገሩ ልጆቻቸው ይነጋገራሉ፤ ይደራረሳሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው የሚል ።ትክክል ነው። ባንዳንድ ሃገር ወዳዶች ለኢትዮጵያ ሕልውናና አንድነት ጠንቅ ሆኖ የሚታያቸውን የሁለት ትግርኛ ተናጋሪዎች እንደገና እንዲወዳጁና እንዲቀራረቡ ማድርግ ጸረ-ኢትዮጵያ ቃል ኪዳናቸውን እንዲያድሱ መርዳት የሚመስላቸው የፖሎቲካ የወሃን አይታጡም። አሻግሮ መመለክት የተሳናቸው ናቸው። በተቃራኒው መቀራረቡና መነጋገሩ ወሳኝነት ያለው እርምጃ ነው፤ የሁለቱን ሃገሮች ሕዝቦች ለማቀራረብ።ዛሬ የዚህ የተሰበስብንበት ዋናው ዓላማ። አመሰግናለሁ!!!!

Saturday, March 20, 2010

ያላወቅነዉ ያልተነጋገርንበት የመሪዎቻችን ባሕሪ

ያላወቅነዉ ያልተነጋገርንበት የመሪዎቻችን ባሕሪ

ጌታቸዉ ረዳ

በሕዳር ወር 2000/ ማርች2010 በአሜሪካ ሃገር በሳንሆዘ ከተማ በካሊፎርኒያ ክፍለሃገር ኗሪ በሆነዉ ቅን አሳቢዉ እና አገር ወዳዱ በአቶ አበበ ገላጋይ አነሳሽነት የተጀመረዉ የኢትዬጵያዊያንን እና የኤርትራዊያን የሕዝብ ለሕዝብ ማገናኘት ሃሳብ አብረዉት ሌት ተቀን በገንዘብና በጉልበት ጊዜያቸዉን ሰዉተዉ የሱን ተነሳሺነት ቅን አሳብ በመደገፍ በአሜሪካ በሳንሆዜ ከተማ በካሊፎረኒያ ክ/ሃገር በኢትዬጵያ እና በ ኤርትራዊያን ዜጎች መሃል የሞቀ ወንድማዊ እና እህትማዊ የሃሳብ ልዉዉጥ እንዲካሄድ እንዲሳካ የረዱትን ኩሁለቱም ወገኖች የተወጣጡ ኢትዮጵያዊያን እና ኤርትራዊያን ወንድሞች ሳላመሰግን አላልፍም። አበሮ ከዚህ ጋር ጥሪያችንን አክብረዉ ከተለያዩ ያሜሪካ ከተሞች እና የዓለም አገሮች ተጉዘዉ በጉባዉ የተገኙትን ተናጋሪ ምሁራንና የጉባዉ ምንነት ለማዳመጥ በስብሰባዉ ተገኙ እንግዶች ሁሉ ምስጋና ይድረሳቸዉ እያልኩ የተዘጋጀዉ የሁለቱም ወንድማማች/እህትማማች ሕዝቦች የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ጉባኤ ለሦስት ቀናት የቆየ የምሁራን እና የሕዝብ ለሕዝብ የሃሳብ ልዉዉጥ መደረጉ (የትግርኛዉ ቪ ኦ ኤ በስተቀር- “ዉስጡ ለቄስ(?)” አብዛኛዎቹ ማለትም ባሜሪካ ድምፅ ያማርኛዉ ክፍል እና የዶቼቬለ አማርኛዉ ክፍል እንደዚሁም በሕዋዉ የዜና ሰሌዳ ማለትም በኢንቴርኔት የዘገቡትን ሁሉ አብሬ እያመሰገንኩ ስለ አዘጋጆቹ እና ለተቀደሰዉ ተግባር ትብብራቸዉን ላሳዩ ሁሉ ኮሚቴዉ ልዩ ምስጋና ለማስተላለፍ በራሱ ስም ስለሚያወጣ ያንን ለኮሚቴዉ እየተዉኩ

ከጉባኤዉ የቀሰምኩትን “ያላወቅነዉ ያልተነጋገርንበት የዘመናት ችግራችን” በሚል ርዕስ ልንነጋገርበት ያቀረብኩትን ርዕስ እነሆ።

ያላወቅነዉ ያልተነጋገርንበት የመሪዎቻችን ባሕሪ

ጌታቸዉ ረዳ www.Ethiopiansemay.blogspot.com

በኤርትራና በኢትዬጵያ ሕዝብ መሃል ለዘመናት የቀጠለ ደም ያፋሰሰ ለረዢም ጊዜ የተካሄደ አሁንም እየቀጠለ ያለዉ ጎጂ ጦርነት ሁላችንም አሰልችቶን አንድ ምዕራፍ ላይ መቆም እንዳለበት የጦርነቱና የግጭቱ ሰለባ የሆኑት ሁለቱም ዜጎች ወደ መስማማቱ ላይ እንደሉ ሁኔታዎች ያሳያሉ።ግጭቱ ዛሬም ነገም ተነገ ወዲያም ለዘላለም እንዲቀጥል በሁለቱም በኩል ያሉት በመንግሥት የተሰየሙ የሻዕቢያና የወያኔ መሪዎች ምኞትና ሴራ ቢሆንም ሰፊዉ የሁለቱ ማሕበረሰብ ዜጎች ከግጭቱ የተጠቀሙት አንዳችም አመርቂ ዉጤት ስላላዩበት፤ግጭቱ ቢቀጥል የትም እንደማያደርሳቸዉ ስለተገነዘቡ እልባት እንዲደረግበት በሰላም እና በመነገጋገር ችግራቸዉን እንዲወያዩ አዲስ ምዕራፍ ይሄዉ ጀምረዋል።

እንደሚታወቀዉ በሁለቱም ሕዝቦች መካከል ካጼ ዮሃንስ ዘመን ጀምሮ በኤርትራ በኩል የገቡ በዉጭ ተስፋፊ ሃይላት ምክንያት የተጠነሰሰዉ የሁለቱን ሕዝቦች የርስ በርስ ጦርነት እና ግጭት ሴራ ፍጻሜ ግቡን እንዲመታ በተዋረድ የጀብሃ፤የሻዕቢያ እና የወያኔ መሪዎች ሴራዉን በማስፈጸም በኩል ከፍተኛ ሚና ተጫዉተዋል።በሌላ በኩል ችግሩ እንዲባባስ እና እንዚህ ክፍሎች ለአመጽ እንዲነሳሱ ምክንያት እና አመቺ ሁኔታ የፈጠሩላቸዉ በኢትዮጵያ ዉስጥ የነበሩ (አሁንም ያለዉ) የተለያዩ ስርዓቶችም ለግጭቱ መባባስ እኩል ድርሻ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ግጭቱ ከተራ ጦርነት አልፎ ሕዝቦች በጎሳ እና በቋንቋ እንዲናናቁ ተደርጎ ለጥላቻ ፖለቲካ ተዳርገዉ የማንነታቸዉ መታወቂያ የሆነዉን “ሰብአዊነትን” ጥለዉ “የአዉሬነት” ባህሪ በመላበስ እንደጠላት በጎሪጥ እየተያየ ቂም ቋጥሮ ለዘላም የማይበርድ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ጥላቻ እንዲይዙ በመደረጉ ከዚያ አዉዳሚ ግጭት እና የጥላቻ አዙሪት እንዴት መዉጣት እንደሚቻል በጉባዉ ላይ የተጋበዙ ወደ 10 ያህሉ ኤርትራዉያንና ኢትዬጵያዊያን ምሁራን ያበረከቱት የመፍትሄ ሃሳብ ከላይ የተጠቀሱት የሚዲያ ዘገቢዎች የተነተኑዋቸዉን የተጋበዙ ምሁራን ያቀረቡዋቸዉ የመፍትሄ ሃሳቦች እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ለየት ባለ መልክ ሚዲያዎቹ ልብ ያላሉት (በስፋት ያልተነተንዋቸዉ) በጉባኤዉ ላይ የቀረቡ የሁለቱ ምሁራን ማለትም የፕሮፌሰር ተስፋጽየን መድሃኔ (የትዉልድ መንደር ሓማሴን) እንዲሁም ምሁሩና አምደኛዉ አቶ የሱፍ ያሲን (ትዉልድ መንደር ዓሰብ-ዓፋር) ለጉባዉ ያቀረቧቸዉ ሃሳቦች ለግጭቱ የመፍትሄ ሃሳብ ምን መሆን እንዳለበት ብቻ ሳይሆን ግጭቱ መፍትሄ እንዳያገኝ ደንቃራ/እንቀፋት ሆኖ ለዘመናት እንዲቀጥል ምክንያት የሆነ ያላወቅነዉ የመሪዎቻችን ባሕሪ ሕዝቡ እንዲመረምራቸዉ ጠቁመዋል። በዚህ ምዕራፍ 1 ላይ የምንመለከተዉ የፕሮፌሰር ተስፋጽየን መድሃኔ ሲሆን፤ በምዕራፍ 2 (በሚቀጥለዉ ሳምንት ይቀርባል) የምንመለከተዉ ደግሞ አቶ ያሲን የሱፍ “የትግርኛ ተናጋሪዎቹ ቋሚና ተለዋዋጩ የማንነት መግለጫዎች-ሁለቱን ሕዝቦች በማቀራረቡ ሚና” በሚል ርዕስ ለጉባዉ የላኩትን ወረቀት እንመለከታለን።

የፕሮፌሰር ዶ/ር ተስፋጽየን መድሃኔ የመፈትሄ ሃሳብ ብለዉ ያቀረቡት አምና በመጽሃፍ መልክ ታትሞ የቀረበዉን እንደተጠበቀ ሆኖ በታሪካችን ዉስጥ በተካሄዱ በዉስጥ አገርም ሆነ በዉጭ አገር በተካሔዱት ለመቁጠር በሚያስቸግሩ በርካታ ጉባኤዎች ዉስጥ ተደምጦ የማያዉቅ ትኩረት ሊደረግበት የሚገባ ያላወቅነዉ ያልተነጋገርንበት የዘመናት የመሪዎች ባሕሪ ምን እንደነበር እና ዛሬም ያ ችግር ለሁለቱም ሕዝቦች ግንኙነት ደንቃራ እንቅፋት እንደሆነ በሰፊዉ ያተቱትን ባጭሩ እንመለከታለን።

በጀርመን ሃገር ብረመን ዩኒቨርሲቲ፣ ፕሮፌሰር የሆኑት ፕሮፌሰር ዶ/ር ተስፋጽየን መድሃኔ ድክመቶችና ስህተቶች፤የኢትዮጵያና ኤርትራ የመወሃድ ሂደት ችግሮችና: ያሁኑ ሁኔታ” በሚል ያቀረቡት የመወያያ ሃሳብ ለየት ያለ ካሁን በፉት በምሁራን ዘንድ ያልተዳሰሰ አዲስ ለፖለቲካዉ በሽታችን አዲስ ምርመራ (ሪሰርች) በመዳሰስ ሰላም እንዳይሰፍን ደንቃራ እንቅፋት ሆኖ አላላዉስ ያለዉ ያለፉትንም ሆነ አሁን ሥልጣን ላይ ያሉት የመሪዎቻችን ያስተሳሰብ በሽታ ምን እንደነበር እና አሁንም ያስተሳሰብ ችግር በመሪዎች እና ባብዛኛዎቹ የሊሂቃን ሕሊና እየቀጠለ እንደሆነ አብራርተዋል።

እኔ “ያስተሳሰብ በሽታ” የምለዉ ፕሮፌሰሩ የተነተኑት የአብዛኛዎቹ የሁለቱንም ሕዝቦች ሊሂቃን እና መሪዎች ያስተሳሰብ ባሕሪ ከ“ማኒከየዝም” አስተሳሰብ የመነጨ ባሕሪ ነዉ ይሉታል። የሁለቱ ሃገር ሕዝቦች በጦርነት እንዲማገዱ በጥላቻ እንዲራራቁ ምክንያት የሆኑት በሃይል የተጫኑባቸዉ መሪዎቻቸዉ በዚህ የባሕሪ በሽታ በመለከፋቸዉ ነዉ ይላሉ። ፕሮፌሰሩ ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ ሲተነትኑ እንዲህ ይላሉ

አሁን ያለው ሁኔታም ያው ከ40ዎቹ አንስቶ ሲያደናቅፈን በኖረው አመለካከት ወይም ርዕዮተ-ዓለም የተለወሰ ነው።” ችግራችን ምንድ ነዉ? ለሚለዉ ከባዱ ጥያቄ ሲመልሱ እንዲህ ይላሉ “ አንዳንድ ታዛቢዎችና ተንታኞች የፖለቲካ ችግሮቻችን ዋና መንስዔ የማርክሰ-ሌኒንነት ውርስ የሆነው ስልጣን ለብቻ ጠቅልሎ የመያዝ ባህርይ ወይም ዝንባሌ ነው።” ይላሉ።

ፕሮፌሰር ተስፋጽየን ከላይ የጠቀሱት ካንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች የሚሉትን በምሳሌ ሲጠቅሱ

“ለምሳሌ ፕሮፈሰር ያዕቆብ ሃይለማርያም ባለፈው ታህሳስ ወር በታተመ ጽሁፍ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ባለፉት 30 ዓመታት ልዩነቶቻቸውን በመግባባት ፈትተው ሊጓዙ አልቻሉም፣ የዚህ ችግርና ውድቀት ምክንያትም የአጀማመራቸው ሂደት በማርክሰ-ሌኒንነት የተቀረጸ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም ይላሉ። ከዚህ ጋር በማያያዝም የኛን ትውልድ፡ አቶ መለስ ዜናዊ የሚመሩት ኢህአደግን ጨምሮ፡ ያሳደገ ማርክሰ-ለኒኒዝም፡ ጨዋነት እና በድርድር ስምምነት ላይ መድረስ፡ እምብዛም የማይፈቅድ አመለካከት መሆኑን ይገልጻሉ።”

በማለት ዶ/ር ያቆብ ያቀረቡትን አመለካከት ፕሮፌሰር ተስፋጽየን በመጠኑ ቢጋሩትም የችግሩ መንስኤ ያ እንዳልሆነ ሲገልጹ እንዲህ በማለት ይገልጹታል

“ችግሮቻችን ከ60ዎቹ በፊት የተነሱ በመሆናቸው፤ ያጠፉትና ስህተት የፈጸሙትም ማርክሲሰት ነን ባዮች ብቻ ሳይሆኑ፡ ማርክሲስት ያልሆኑና ጸረ-ማርክሲስት አቋም የነበራቸውም ጭምር ስለሆኑ፡ ያስተሳሰብ ችግሮቻችን መንስኤ ወይም መግለጫ ምን እንደሆነ ለመረዳት ከማርክሳዊ ርዕዮተ-ዓለም ውጪ በሆኑ ዘርፎች ማፈላለግ ይኖርብናል።” ሲሉ ለምሁራንም ሆነ ለኛ ለተራ ዜጎች ይህ አዲስ ጀሮ የሆነዉ የችግራችን ዋናዉ እምብርት ለመቃኘት እንዲመቸን ወደ ምርምሩ የህሊና አቅታጫቸዉ እንድናተኩርበት የችግራችን ምንነት እንዲህ ሲሉ ያብራሩታል፤

“ …ችግራችን "ማኒኪያዊ አመለካክት" ነዉ” ካሉ በሗላ - የመኒከይዝም ባሕሪ ሲገልጹም “

ማኒከዪዝም ፍጹማዊ የሆነ፡ ሁሉንም ነገር ከሁለት ተጻራሪ መርሆዎች ወይም ምርጫዎች አኳያ የሚያይ አስተሳሰብ ነው። ድሮ፡ ማለት በ3ኛው ክፍለ-ዘመን፡ እንደ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ቢጀምርም፡ አሁን ማኒከዪዝም ሲባል ማንኛውንም ሁኔታ ለሁለት የማይታረቁ ተጻራሪ ሃይሎች -አንዱ በጎ፤ ሌላው መጥፎ- እንደተከፈለ አድርጎ የሚመለከት እይታ ማለት ነው። ሁሉም ነገር ከሁለቱ አንዱ ተብሎ ይገለጻል። ለምሳሌ፡ ጥሩና መቅሰፍት፤ ነጭና ጥቁር፤ መጥፋት ያለበት ጠላት እና ወገን የሆነ ወዳጅ ወዘተ ወዘተ። ከሁለቱ አንዱ መሆን ብቻ ነው የሚቻለው። ሶስተኛ፡ ማለት አሻሚ ወይም መሀከለኛ ሁኔታ ሊኖር አይችልም። ይህንን ግንዛቤ ወይም ጽንሰ-ሃሳብ በምሁራዊ ደረጃ ተገልጾ ያየሁት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ዲፓርትመንት እና በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር መምህር የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በጻፉት በየካቲት 2001 በአዲስ ነገር ጋዜጣ በታተመው አንቀጽ ነው። ዶ/ር አሰፋ እንደጻፉት፡

“ከባህላዊ አመለካከት አኳያ እስከዛሬ ያልተቸነው እና ለብዙ ዘመናት ተንሰራፍቶ የቆየው (የኖረው) ‘የሴማውያን ዕይታ’ ተብሎ የሚታወቀውን የማኒኪያን አስተሳሰብ ነው። ማኒከይዝም ‘ዓለም ከጥንት ፍጥረት ጀምሮ በሁለት ተጻራሪ እና ተፋላሚ ሃይሎች መካከል ተወጥራ ትገኛለች’፡ ብሎ ስለሚያምን ሁሉንም ነገር የሚመለከተው በሁለት አጽናፎች ላይ ብቻ ተወስኖ ነው። እነዚህም ብርሃንና ጨለማ፤ በጎና ክፉ፤ አጥፊና ጠፊ ሲሆኑ፡ እነዚህ ሁለት አጽናፎች የሚጋጩበት እና በአጠቃላይ ተቃርኖ የሰፈነባት ዓለም ውስጥ እንዳለን ያቀርባል፤ በሁለቱ አጽናፎች ያለ ሶስተኛ እውነታ ሊኖር አይችልም ብሎ ያምናል። ይህ አይነቱ አመለካከት በአንድ ማህበረ-ሰብ ውስጥ የሚነሱ ባህላዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ከሁለት አጽናፎች ውጭ ለመመልከት አይችልም። ስለሆነም፡ይህ አይነቱ ግንዛቤ በባህል በስነ-ምግባር፡ እና በፖለቲካ ህይወት ዙርያ (ላይ) ተጽእኖውን ያሳርፋል።”

“ማኒከዪዝም በፖለቲካ ረገድ” ምን መልክ እንዳለው፡ ምን ውጤት እንደሚያስከትል፡ እና ምን ችግር እንደሚፈጥር ሲጠቅሱም ባጭሩ እንዲህ ይገልጹታል።

ማኒከዪዝም ማንኛዉንም ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ረገድ የሚጠቀመው እይታ ቀላል ነው። አቀራረቡም በሚከተለዉ ይገልጹታል። “ ሁሉም ነገር ነጭ ወይም ጥቁር፤ በጎ ወይም ክፉ፡ ወዳጅ ወይም ጠላት ነው። የተወሳሰበና ለመፍረድ ወይም ለመወሰን የሚያስቸግር ጥያቄ አይኖርም።

ይህ ታዲያ ችግር ለመፍታት ይረዳል ወይስ አይረዳም ለሚለዉ ጥያቄ ስመልሱ

“አይረዳም…።” …እንዲያውም ስለ ኢትዮጵያና ኤርትራ የቅርብ የፖለቲካ ታሪክ ስንመረምር ችግሮቹ እንዲባባሱ “ማኒከየዝም” ሚናዉ ከፍተኛ እንደሆነ ያምኑበታል።

በማኒከያዊ አስተሳሰብ አሻሚ ነገር ስለሌለ መደራደርና ስምምነት ላይ መድረስ አይታሰብም። አንዱ -ማለት በጎው- ወይም ሌላው -ማለት መጥፎው- ያሸንፋል። መቻቻል የሚባል ነገር ቦታ አይኖረውም።ማኒኪያዊ ፖለቲካ ልዩነትን አይቀበልም። አንዱ ወገን ራሱን እንደ ፍጹም ትክክለኛ ቆጥሮ ሌላውን ወገን ደግሞ ፍጹም የተሳሳተ ወይም መጥፎ አድርጎ ያየዋል። ስልጣን መጋራት ወይም ተደራድሮ ሁሉንም ወገን የሚያረካ መፍትሄ ማፈላለግ ለማኒኪያዊ ፖለቲካ የሚጥም አይደለም። ውድድር ቢኖር ድሉ የራሱ ብቻ እንዲሆን ይፈልጋል፤ ይጥራል፤ ቢቀናውም ያደርጋል። ለምሳሌ የብሄራዊ አንድነት መንግስት የሚባል ገንቢ ሃሳብ ማኒኪያዊ አመለካከት ላለው አካል አይስማማውም። ዶ/ር ዳኛቸው እንዳሉት፡

“የፖለቲካ ገጽታውን እንደምሳሌ ብንወስድ ማኒከዪዝም ፍጹማዊ የፖለቲካ ዕሴት (value)፡ አንድ ወጥ የፖለቲካ ትንታኔ፡ አንድ አይነት የታሪክ ዕይታ ብቻ የሚያስተናግድ አስተሳሰብ ነው። በዚህ አስተሳሰብ መሰረት በፓርቲዎች መካከል የሚነሳ ውድድር ውጤቱ ምንጊዜም ፍጹማዊ እና ብቸኛ ድል መሆን አለበት።”

ማኒኪያዊ ፖለቲካ ድሮም ነበር፡ አሁንም አለ። ‘የሴማውያን ዕይታ’ ተብሎ ቢገለጽም፡ ይህ ያስተሳሰብ ጠባብነት ከጥንታዊ ባህል ውርስ ባልተገላገሉት ታዳጊ ሃገሮች ብቻ ሳይሆን ሰለጠኑ በሚባሉት ህብረተ-ሰቦችም የሚታይ ነው።…” “…ከዚህ ጋር በተያያዘ መጠቀስ ያለበት ነጥብ አለ፡፡ አንድ ማኒኪያዊ አመለካከት ያለው መሪ ወይም ቡድን የኔ አካሄድ ብቻ ነው ትክክለኛው ብሎ በማመኑ ወይም በማሰቡ የሚከተለው ወይም የሚተገብረው ፖሊሲ (የጦርነትን ጨምሮ) ፡ ወይም በአንድ ጉዳይ የያዘው አቋም የተሳሳተና አፍራሽ መሆኑ ግልጽ በሆነበት ጊዜም ፖሊሲውን ወይም አቋሙን አይለውጥም፡፡ ለዚህ ነው አንዳንድ መሪዎች ኪሳራንና ውድቀትን ብቻ የሚያመጣ ፖሊሲ (ጦርነትን ጨምሮ) ዝም ብለው ሲቀጥሉበት የምናየው።”በአህጉራችን አፍሪቃ ያለው የፖለቲካ እውነታ እምብዛም በማኒከዪዝም የተጥለቀለቀ ነው፡፡ እንድያውም በአፍሪቃ ያለው ፖለቲካ በመሰረቱ “ባዶ ወይም ሁሉን” (zero-sum) ተብሎ የሚገለጽ ነው፣ ይህ ማለት፡ አንድ ቡድን (ወይም አንድ አምባገነን) የመንግስትን ስልጣን በሙሉ ይጠቀልላል፣ ሌላው ምንም አያገኝም፡፡ ይህ እንግዲህ እውነተኛው የዝምድና ይዘትን በተመለከተ ነው፣ ካለበለዚያ ለማስመሰል ወይም ለይስሙላ አንዳንድ የዲሞክራሲ መልክ ያላቸው ገጽታዎች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ኬንያን በተመለከተ አንድ ታዛቢ ሲተነትን፡ ያች አገር ገና በ60ዎቹና በ70ዎቹ ከነበረችበት የጐሳ ፖለቲካ አልተላቀቀችም፤ ፖለቲከኞቹ ሁኔታውን የሚመለከቱት ማኒከያዊ ከሆነው “እኛ ኪኩዩዎች እና እነዚያ ኪኩዩ ያልሆኑት” በሚለው እይታ ነው፡ ይላል፡፡

ይህ አደገኛ ነው፡፡ በአንዳንድ ከመጠን ያለፈ ሁኔታማ ማኒኪያዊ አመለካከት ያለው አምባገነናዊ ቡድን “እኛ እንገዛላን፡ ካለበለዚያ አገሪቱም ትጥፋ“ በሚል አቋም ይደርቃል፡፡.. “ በሱዳንም እንደዚሁ ሁለቱ ተፎካካሪ ቡድኖች ማኒኪያዊ ፖለቲካ እያካሄዱ ነበር፡፡ ካርቱም ያለው ብሄራዊ እስላማዊ ግንባርና ደቡቡን የሚወክል የሱዳን ህዝብ አርነት ግንባር ማኒኪያዊ የሆነ ድል ሲፈልጉ ነበር፡፡ ይህ ማለት የካርቱሙ ግንባር አረባዊት እስላማዊት ሱዳን ሲሻ፣ የደቡቡ ሃይል ደግሞ የተባበረች ዓለማዊትና ዲሞክራሲያዊት ሱዳን ሲፈልጉ ነበር፡፡ ይህ ግን፡ ሁለቱ ወገኖች ማኒኪያዊ በመሆናቸው፡ በጦርነት በማሸነፍ ብቻ ነበር ሊረጋገጥ የሚችለው፡፡ ከሁለቱ ግን ማንኛቸውም በጦርነት ሊያሸንፍ አልቻለም፡፡ የሚሊታሪ እውነታው ማኒኪያዊ መደምደሚያ እንዲቻል አላደረገም፡፡ ስለዚህ፡ ይላል አንድ ተንታኝ፡ “ሱዳንን በተመለከተ ተግባራዊ የሆነ መፍትሄ የሚገኘው ሁለት ሉአላዊ አገሮች አብረው ሊኖሩ ከሚያስችል የኮንፌዴሬሽን መዋቅር ነው፡፡ (በሌላ አነጋገር፡ ሰሜንና ደቡብ ሱዳን ይለያዩና ወዲያውኑ በኮንፌዴሬሽን ይተሳሰራሉ፡፡)” ሲሉ ድርቅ ባለ ግደለኝ ወይም ልግደልህ ባለዉ ዓይነት የተካረረ ግትርነት የ “ማኒከዩዚም” ባሕሪ መሆኑን ካብራሩ በሗላ፤-በሁለቱም አካባቢዎች (ኢትዬጵያ እና ኤርትራ ዉስጥም) እንደዚሁ ይህ ገታራ /ግትር ባሕሪም

በህብረተሰባችን እንደ ጽንሰ-ሃሳብ ተለይቶ እምብዛም የሚታወቅ ባይሆንም፡ ማኒከዪዝም እንደ ተርዕዮ በተጨባጭ የሚስተዋል መሆኑ ግልጽ ነው።…” ይላሉ።

ይህ ባሕሪም ከተወሳሰበ የህይወት ዕውነታ ጋር ሲገለጹ።

“ለምሳሌ..” በማለት “ለምሳሌ በዕውቀቱ ስዩም የተባለ ደራሲ “በራሪ ቅጠሎች” በተሰኘው መጽሃፉ “የቅጠል ቤት ታዳሚዎች” ብሎ ስለሚጠራቸው ገጸ-ባህሪዮች (characters) እንዲህ ይላል፡

“የቅጠል ቤቱ ታዳሚዎች ሁሉ ለመናገር እንጂ ለመስማት የሚመጡ አይደሉም፡ …….

“እነሱ ዘንድ መፍረድ ቀላል ነው። ሲፈርዱ ጥግ እንጂ አማካኝ መኖሩን አያውቁም። ቆላ ካልሆነ ደጋ ነው ይላሉ፤ ወይናደጋ መኖሩን አይረዱም። ብርሃን ካልሆነ ጨለማ ነው ይላሉ፤ ከጨለማ የፈካ፡ ከብርሃን የደበዘዘ ድንግዝግዝ መኖሩን አያውቁም። ንፍር ካልሆነ በራድ ነው ይላሉ፤ ለብታ መኖሩን አያስተውሉም፡፤ ጠላት ካልሆነ ወዳጅ ነው ይላሉ፤ መሃል ሰፋሪን አይቀበሉም።”

ይህ ትዝብት ማኒከዪዝም በህብረተ-ሰቦቻችን በተለያዩ ዘርፎች ያለ የባህላችን አካል ወይም ያአስተሳሰባችን ባህርይ መሆኑን ነው የሚያመለክተው። ይህ ማኒኪያዊ አስተሳሰብ የባህላችን አንድ ባህሪ በመሆኑ ባሁኑ ፖለቲካችን ላይም ትልቅ ተጽእኖ ያደርጋል፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው እንዳሉት፡ “ይህ የማኒከይዝም አመለካከት በአገራችን ለረጅም ጊዜ ስር ሰዶ የቆየ፣ ባህላዊ መሰረት ያለው ከመሆኑ አኳያ አገራችንን በሚያስተዳድረው ፓርቲ ላይ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚ ፓርቲዎችም ላይ የሚታይ ችግር ነው፡፡”

በማለት ማኒከዩዝም የተባለዉ የግትርነት ባሕሪ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሳይቀር የሚንጸባርቅ በመሆኑና ይህ ለድርድር እንቅፋት የሆነ መጥፎ ባሕሪ ካልተወገደ ዉጤቱ የከፋ እንደሚሆን ያስጠነቅቃሉ።

ፕሮፌሰሩ ሲገልጹ - ጥንትም ሆነ ዛሬ ማኒኪዩዝም በፖለቲካዉም ሆነ በዲፕሎማቲካዊ የሕዝብ ለሕዝብ ፤መንግሥት ለመንግሥት ግንኙነቶችን አስመልከቶ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሰ እና ዛሬም እያደረሰ መሆኑን ይጠቁማሉ፦

“በኢትዮጵያ ፖለቲካና በኤርትራ ፖለቲካ የዲሞክራስን፡ የብሄርተኝነትን፡ እና የብሄረ-ሰብን ያጠቃለሉ ብዙ አንገብጋቢ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የኢትዮጵያና ኤርትራ ዝምድናን በተመለከተም እንደዚሁ ከብዙዎቹ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ የታሪክ አተረጓጐምን የሚመለከት አለመግባባት አለ ማለት ይቻላል፡፡ በዚሁ አለመግባባት፡ በዚሁ ትግል ከማኒኪያዊ አመለካከት የመነጨ ድክመትና ስህተት በሁሉም በኩል ይታያል፡፡”

በማለት ማኒከዩዝም ለሁለቱም ሕዝቦች መራራቅ ለቅራኔዉ ሸካራ ግንኙነት የላቀ ሚና እንደተጫወተ እና ይህ ባሕሪ ከተራ ዜጋ እስከ የፖለቲካ መሪዎች እና የሃገር መሪዎች እንዲሁም ሊሂቃን እንዲዋጉት አጥብቀዉ ካሳሰቡ በሗላ ፕሮፌሰሩ ስለ ሁለቱም ህዝቦች ግንኙነት በሚመለከት በወቅቱ ስለነበረዉ በተባበሩት መንግሥትታት ዕዉቅና የተሰጠዉን የራስ (የዉስጥ) አስተዳደርን በተመለከተ በሰፊዉ ያተቱት ሲሆን፤ አንዳንዶቹን አንመልከት።

በማኒከዩዝም ያስተሳሰብ ባሕሪ ምክንያት ከኤርትራ ሕዝብ ተነጠቀ የሚሉትን የራስ አስተዳደር መብት እንዴት እንደተነጠቀ ፕሮፌሰሩ ያቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ ባሳተሙት በመጽሃፍቸዉ ለሕዝብ በገበያ ስለተሰራጨ ሁኔታዉን በስፋት ለማጤን ለሚፈልግ መጽሃፉን አግኝቶ ማንበቡን ጠቃሚ እንደሆነ እየጠቆምኩ፤- ባጭሩ ፕሮፌሰሩ “በፌደሬሽኑ” መፍረስ ምክንያት በሀለቱ ወገን ስለታየዉ ቅራኔና አለመረዳዳት እንደዚሁም በሕዝቦቹ ስም አስታክከዉ እንወክልሃለን በማለት ጦርነቱን የመሩ የነጻ አዉጪ ግምባሮች ግትር ባህሪ የሕዝቡን ግንኙነት ምን አህል እንደጎዱት በሰፊዉ ካተቱ በሗላ ሕዝቡ ለነጻነት እንዴት እንደበቃ ከነፃነት በሗላ የተጠበቀዉና ሲነገርለት የነበረዉ ይትግሉ ፍሬ እንዴት እንደተኰላሸ በስፋት የገለጹትንም ጭምር እዚህ አልተቅስም። ሆኖም በብዙ ሰዎች ሕሊና ሲታመንበት የነበረዉ “ኤርትራ ፌደረሽን” ነበረች የሚለዉን በተጻራሪ ሲመልሱ እንዲህ በማለት ግልጽ ያደረጉታል

“ፌዴሬሽን የተባለው የኤርትራና ኢትዮጵያ ዝምድና ሙሉ አንድነት ነበር፡፡ ኤርትራ በዚሁ አገር ባለው ስርዓት እንደነካሊፎረኒያ ወይም ኒውዮርክ ፈደረትድ ስቴት አልነበረችም፡፡ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ስር የራሷ የውስጥ አስተዳደር “ሎካል አውቶኖሚ” ብቻ ነው የነበራት፡፡ ይህ ፍፁም አንድነት ነበር፡፡ ነገር ግን ኤርትራ ‘ጠቅላይ ግዛት’ ካልተባለች ለአባ ጠቅል አንድነት አልነበረምና ፌዴሬሽኑ እንዲፈርስ ተደረገ፡፡” ካሉ በሗላ፤ ፈረሰ ሲባል ዉጤቱ ምን ነበር? ሲፈርስስ ምን ትርጉም አስከተለ? ይላሉ። “ፌዴሬሽኑ ፈርሶ ኤርትራ 14ኛዋ ጠቅላይ ግዛት ሆነች ሲባል ምን ማለት ነበር? ፌዴሬሽኑ በመፍረሱ ለኤርትራ ህዝብ ምን ነበር የጐደለው? ፌዴሬሽኑ በመፍረሱ ኤርትራውያን የራሳቸው የራስ ገዝ መንግስት እንዳይኖራቸው ሆኑ፤ ራሳቸውን የማስተዳደር መብት ተገፈፉ፤ ባንዴራቸውን ተነጠቁ፤ ኦፊሺያል ቋንቋዎቻቸውን -ትግርኛና አረብኛ- እንዳይጠቀሙ ተከልክለው፡ የአማርኛ ቋንቋ ተጫነባቸው፤ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶቻቸው - የፕረስ፡ የመናገር፡ ፖለቲካ ፓርቲ የማቋቋም፡ ለስልጣን ለመወዳደር የመሳሰሉትን አያሌ መብቶቻቸውን እኮ ነው የተነጠቁት! ባጭሩ ነጻነታቸውና መብቶቻቸው ተወሰዱባቸው፡፡ ይህ ጭቆና ነበር፡፡”

ከዛ በሗላ የታየዉ ክስተት ፌደሬሽኑ በመፍረሱ ያስከተለዉ የጥላቻ እርሾ ፕሮፌሰሩ በእንዲህ ይገልጹታል።

“ የዚህ ውጤት ምን ነበር­? ተጨቆንን፡ ተዘመትን ያሉ ቡድኖች የነጻነት ንቅናቄ አስነሱ፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት ፌዴሬሽኑ በተለይም ለእስላማዊው ወገንና ሊበራላዊ እሴት በትንሹም ቢሆን ቀማምሰው ለነበሩ ልሂቃን ዋስትና ነበር፡፡ ፌዴሬሽኑ ሲፈርስ ዋስትናው ጠፋብን ብሎ የበረገገው ይህ አካል ነበር፡፡ ቆይተውም ድሮ አንድነት ይደግፉ ከነበሩትም ሳይቀሩ ንቅናቄውን ተቀላቀሉ፡፡ ንቅናቄው አድጎ ጀብሃ ተፈጠረ፡፡ አባትና እናት ትባል የነበረችው ኢትዮጵያ ጠላት ሆነች፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን ናት! ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን፡ ወገኖቻችን ናቸው! ብለው አንድነትን የተቀበሉ ሳይቀሩ እንዴት ጠላት ይሉናል ያሉ ነበሩ፣ እስካሁንም አሉ፡፡ እንዲህ የሚሉ ኢትዮጵያውያን መብቱ የተገፈፈና የተጨቆነ ህዝብ፡ በማንኛውም ህብረተሰብ፡ ጨቋኙን፡ ወገን ይሁን ባዕድ፡ እንደ ጠላት ማየቱ የማይቀር መሆኑን ይረሳሉ፡፡ ዕውቁ ኢትዮጵያዊ ደራሲ፡ ሟቹ አቤ ጉበኛ፡ አልወለድም በሚለው መሃፉ እንዳለው፣

“ወንድም ሲሆንና፡ መልካም ሲሰራ እንጂ ከባዕድ የሚለየው፡

ነጻነትንና መብትህን ከነሳህ፡ ወገንም ጠላት ነው፡፡”

ወገን “ወገን” በመሆኑ ብቻ ጠላት ሊሆን አይችልም የሚል ግምት ስህተት ነው፡፡ በሌላው በኩል ደግሞ መብት ገፍፎ ጠላት በመሆኑ ምክንያት ወገን “ወገን” መሆኑ ይቀራል የሚል አስተሳሰብ ስህተት ነው፡፡ ሁለቱ የተሳሳቱ ግምቶች ማኒኪያዊ አመለካከትን ያንባርቃሉ ማለት ይቻላል፡፡”

ደርግ ከመጣ በሗላም ቢሆን ሁኔታዉን ወደ ነበረበት ማስተካከል ሲችል ወይንም ቢያንስ ሰብአዊ በሆነ ሕዝባዊ አያያዝ/አስተዳደር ከማስተዳደር ይልቅ በማኒኪያዊ አስተሳሰብ/ባሕሪ ሁኔታዉን እንዳባባሰዉ ሲጠቁሙ፤ደርግ በተከተለዉ ማኒኪያዊ ባሕሪ እና ጭፍጨፋ

“የኤርትራውያንን ልብ አሸፈተዉ፡፡ የነጻነት ግንባሮቹ ጠነከሩ፡፡

እንዲያዉም ይላሉ ምሁሩ ፕሮፌሰር ተስፋጽየን መደሃኔ

“ማኒኪያዊ ከሆነው ጠባብ አመለካከቱ የተነሳ የደርግ መንግስት የኤርትራ ፖለቲካዊ ችግር ምን እንደነበረ በትክክል ወይም በበቂ አልተረዳም፣ ስለዚህም ሊፈታው አልቻለም፡፡ ፖለቲካዊ ችግሩን በተግባራዊነት ሊፈታ አለመቻሉ በሁሉም በኩል ለአደጋ አጋለጠው፡ ለኤርትራ መገንጠልም አስተዋኦ ሆነ፡፡”

ሆኖም ይላሉ

“ኤርትራ የተገነጠለችው ግን የአፄውና የደርጉ መንግስታት ስህተቶች በመፈማቸው ብቻ አይደለም፡፡ የኤርትራ ቡድኖች ለዚሁ ውጤት ትልቅ አስተዋኦ በማድረጋቸውም ጭምር ነው፡፡” ሲሉ የኤርትራ ቡድኖች እንዴት ለመገንጠሉ እና ለአደገኛዉ ግጭት አስተዋጽኦ እንዳደረጉ እንደሚከተለዉ ያስቀምጡታል። “የኤርትራ ቡድኖች፡ በተለይ ህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ)፡ መገንጠልን እንደ ብቸኛ አማራጭ ከሚያደርግ ጠባብ አመለካከት ተነስተው ድርድር የማይፈቅዱ አቋሞች ወሰዱ፡ ለእርቅ እንቅፋት የሚሆኑ ድርጊቶችም ፈጸሙ፡፡”

ሲሉ ማኒከዪዝም በተግባር እንዴት ዉሎ ሌላ አማራጭ እንዳይገኝለት እንቅፋት እንደሆነ በምሳሌ ያቀርባሉ።

“አንዳንድ ምሳሌ ልጥቀስ፣

1. የኤርትራ ቡድኖች፡ በተለይ ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ፡ የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው፣ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ናት የሚል፡ ሳይንሳዊ መሰረት የሌለው አቋም ያዙ፡፡ ኤርትራ ቅኝ ግዛት ሆነች ከተባለ ለችግሩ መፍትሄ ነጻነት (መገንጠል) ብቻ ነው፡፡ ወይ ቅኝ ገዢው ይወጣል፡ ወይ ቅኝ ግዛቱ ይቀጥላል፡፡ መሃከለኛ ሁኔታ የለም፡፡

2. የኤርትራ ቡድኖች (በተለይ አቶ ኢሳያስ የሚመራው ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ) የኤርትራን ችግር ከሶሺያሊሰት ጐን ተሰልፋ የነበረችውን የደርግ ኢትዮጵያን ለማዳከም ከፈለጉት ሃያላን መንግስታት ስትራተጂ አቀላቅሎ የቀዝቃዛው ጦርነት ማኒኪያዊ ትግል አካል እንዲሆን አደረገው፡፡ በዛው ማኒኪያዊ ትግል የተፈለገው ደርግን ወይም ስርዓቱን መጣል ስለ ነበረ ለዕርቅና ድርድር የማይፈቅድ አቋም ወሰደ፡፡ ለምሳሌ ደርግ ፋሺስት ነው አለ፡፡ ከፋሺስት ጋር ዕርቅ የለም፣ ፋሺስትን እስኪወድቅ ድረስ ትታገለዋለህ እንጂ ሌላ ምርጫ የለህም፡፡

3. ቡድኖቹ፡ በተለይ ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ፡ ብዙ ጊዜ የህዝቦቻችንን ታሪካዊና ባህላዊ ዝምድና በኤርትራውያን (በተለይ በወጣቱ) እንዳይታወቅ ያደርጉ ነበር፡፡ ይህንንም ከመገንጠል በስተቀር ሌላ ምርጫ እንዳይታሰብ ለማድረግ ተገለገሉበት፡፡

4. ኤርትራ በሴራ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ቢደረግም ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ውስጥ፡ ባጠቃላይ ሲታይ፡ የተከበሩ እንደነበሩ ከመግለጽ ተቆጥበው፡ ኤርትራውያንን እንደተጨቆኑ አድርገው ብቻ አቀረቡ፡፡ ኤርትራውያን ከእጅ ወደ አፍ የሚኖሩ ብቻ ሳይሆኑ ሚኒስትሮች፡ ጀነራሎች፡ የቀናቸው ባለሞያዎች፡ የተሳካላቸው ነጋዴዎች፤ በማህበራዊ መስክም ያልተናቁና ያልተወገዱ እንደነበሩ ከመመስከር ተቆጠቡ፡፡

5. ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ የኢትዮጵያ ወታደሮች በኤርትራ የፈጸሙትን ግፍ ብቻ እየጠቀሰ ራሱ በኢትዮጵያውያን ላይ ግፍ እንዳልፈጸመ ሆኖ ቀረበ፡፡ ለፕሮፓጋንዳና ለዓለም-አቀፍ እርዳታ ብሎ አንዳንድ ምርኮኞችን ደህና አድርጎ ቢንከባከብም፡ ባጠቃላይ በምርኮኞች ላይ ጭካኔ አሳይተዋል፤ አንዳንዱን እንደ ባርያ አሰርተዋል፡፡ ታደሰ ቴለ ሳለቫኖ “አይ ምፅዋ” በተባለው መጽሃፉ እንደገለጸውም በኤርትራውያን ሬሳና በኢትዮጵያውያን ሬሳ መሀከልም አድልዎ ፈጽሟል፡፡

6. በግንቦት 1991 አስመራን እንደተቆጣጠረ ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ከኤርትራ አባረረ፡፡ አንዳንዱ ባዶ እግሩን ነበር የተባረረው፡፡

7. በረፈረንደሙ ጊዜ ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ ምርጫውን ጨርሶ ማኒኪያዊ አደረገው፡፡ ሂደቱን ምርጫው በነጻነትና በባርነት መሃከል መሆኑን በሚያሳምን ረገድ አከናወነው፡፡ ባርነትን የሚመርጥ የለም፤ ግማሽ ነጻነት፡ ግማሽ ባርነት ደግሞ የለም፡፡

ከላይ የተመለከቱት አቋሞችና ድርጊቶች ኤርትራውያን ከኢትዮጵያውያን ጋር የመቀራረብ መንፈስ እንዳያዳብሩ፡ በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን በኩል ደግሞ ጥላቻ እንዲሰፍን በማድረግ ላይ ሚና የነበራቸው ይመስላል፡፡ እንዲህ በመሳሰሉት አቋሞችና ድርጊቶች ኢ.ፒ.ኤል.ኤፍ የመገንጠል አጀንዳውን ለማሳካት ችለዋል፡፡” በማለት በ ኤርትራ ነጻ አዉጪ ግምባሮች በኩል የታየዉ ማኒኪያዊ አስተሳሰብ ለግጭቱ መባባስ እና ለኤርትራ መገንጠል ቁልፍ ቦታ እንደያዘ አስቀምጣሉ።

በኢትዬጵያ በኩልም እንደዚሁ ለመገንጠሉ ሁኔታ እኩል ጥፋት እና አስተዋጽኦ ተደርጓል።ከንጉሡ እና ከደርግ ግፍና የተሳሳተ ፖሊሲ እና የማኒኪዩዚም ባሕሪ እንዲሁም ጭፍጨፋ ሌላ ተጨማሪም አስተዋጽኦ ያደረገ ክፍል ኢሕአዴግን/ህወሓት እንደዚህ ሲሊ ይወቅሳሉ።

“….የኢህአዲግ መንግስት (ወይም ህወሃት) ደግሞ ዲሞክራስያዊ ባልሆነ፡ ሁሉንም የፖለቲካ ቡድኖች ባላሳተፈ፡ ለኢትዮጵያ ህዝብም ለውይይት እንኳን ዕድል ባልሰጠ፡ ረፈረንደም ተብዬ ኤርትራን በኢሳያስ አፈወርቅ እንድትገዛ አሳልፎ መስጠቱ የኤርትራ ህዝብን ለማመን ለሚያስቸግር ጉዳት ዳርጓል፡፡”

በማለት በኛ በኢትዬጵያ በኩል የታየዉ የቅርብ ፖለቲካ አያያዝና ግንኙነት አፍራሽ አስተዋጽኦ ከገለጹ በሗላ፤ ፌደራላዊነትን በተመለከተ ደግሞ በሁለታችን በኩል የሚደመጡ አባባሎች ወይንም እምነቶች/አቋሞችም እንዲታረሙ አበክረዉ እንዲህ ይላሉ፡

“ፌዴራላውነትን በተመለከተ በኢትዮጵያውያንም በኤርትራውያንም በኩል ችግሮች አያለሁ፡፡ ከድሮ (ማለት ከ 40ዎቹ አንስቶ) የነበረው የፖለቲካ አመለካከት ችግር አሁንም ገና ያለ ይመስለኛል፡፡ የአጼው መንግስትም ሆነ ደርግ የኤርትራ ጥያቄ ከነበሩት ጠቅላይ ግዛቶች ወይም ክፍለ-ሃገሮች ጉዳይ ወይንም ብሄረ-ሰቦች ጥያቄ የተለየ መሆኑን መቀበል አልተቻላቸውም፡፡ ይህንን ባለመቀበላቸው አላስፈላጊ እርምጃዎችን ወስደው ኪሳራ አደረሱ፡፡”

ካሉ በሗላ በሁለቱም በኩል መታረም አለባቸዉ አበይት ነገሮች በመጠቆም ሃሳባቸዉን እንዲህ ሲሉ ደምድመዋል።

“ ኢትዮጵያውያን ልሂቃንም (በተለይ ምሁራኖቹ) በበኩላቸው ኤርትራውያን ጥለውን ሄዱ እያሉ ማጉረምረም ቀንሰው የኤርትራውያኑን ስሞታ እንደሚረዱ ማሳየት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ኤርትራ በሴራ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛት እንድትሆን መደረጉ፣ ኤርትራውያን የሲቪልና የፖለቲካ መብታቸው ተገፎባቸው እንደተጨቆኑ፣ የረጅም ዘመናት ታሪካችን አንድ ቢሆንም የኤርትራ ጉዳይ ከሌሎቹ ክፍለ-ሃገራት የሚለይበት ገታ እንዳለ፣ ኤርትራውያን ኢትዮጵያ ውስጥ ተከብረው፡ ተሹመው፡ ቀንቷቸውና ተሳክቶላቸው ብቻ ሳይሆን፡ እነርሱም ለኢትዮጵያ ዕድገት በሁሉም ረገድ ብዙ እነዳበረከቱ መመስከር ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ የልሂቃን ሚና ለኢትዮጵያና ኤርትራ ወዳጅነት፡ ለወደፊቱም በሁለቱ አገሮች መሃከል ለሚከሰት ትስስር ትልቅ አስተዋኦ ያደርጋል”፡

ሲሉ ልንፈትሸዉ የሚገባን አስካሁን ድረስ ያልተፈተሸ ያስተሳሰብ ባሕሪ እንድንፈትሽ እና እንድንነጋገርበት ምሁራዊ ምርምራቸዉን ለጉባኤዉ አስሰምተዋል።

ከዚህ ቀጥሎ የምንመለከተዉ የአፋሩ ተወላጅ ምሁሩ እና በብዕር ችሎታዉ ኢትዬጵያንን እና ኤርትራዊያንን ያስመረቀነዉ አቶ የሱፍ ያሲን ተጋብዘዉ ነበር፤ ነገር ግን ባጋጣሚ እጉባኤዉ ድረስ ለመገኘት ባለመቻላቸዉ ለጉባኤዉ ያዘጋጁትን ጽሑፍ በመላክ እኔ እንዳነብበዉ የተደረገዉን ጽሑፋቸዉን በሚቀጥለዉ ሰሞን በምዕራፍ 2 እንመለከተዋለን። የሁለቱም ምሁራን ጽሑፎች በኢንተርኔት ይለቀቃሉ የሚል እምነት ስላለኝ ሙሉዉን ጽሑፎቻቸዉን/የቪድዬ ንግግራቸዉን ማንበብና ማዳመጥ ተችላለችሁ። አመሰግናሉ። ጌታቸዉ ረዳ ሳንሆዘ ካሊፎርኒያ ሕዳር 2002።www.Ethiopiansemay.blogspot.com