Saturday, April 13, 2019

የኤርትራ ትግል ጀማሪ ስለ ተባለለት ሓምድ እድሪስ ዓዋተ ያልሰማችሁት የህይወት ታሪኩን ላካፍላችሁ ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ) ክፍል 1


ትዮ ሰማይ ዝግጅት፦
የኢትዮ ሰማይ ድረገጽ ወቅታዊ ትንታኔዎችን ለጊዜው አቁሞ እንደነበር ይታወቃል። በቅርቡ በአዲስ መንፈስ ወቅታዊ ትንታኔዎችን በተከታታይ በስፋት ማቅረብ የሚጀምር መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን። አሁን ወደ የዛሬው ትንታኔ ክፍል 1 እንለፍ።

የኤርትራ ትግል ጀማሪ ስለ ተባለለት ሓምድ እድሪስ ዓዋተ ያልሰማችሁት የህይወት ታሪኩን ላካፍላችሁ
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ) ክፍል 1

ሓምድ እድሪስ ዓዋተ (1915-1962) የሚል በኤርትራዊው ‘ሃይለስላሴ ወልዱ’ የተደረሰ በትግርኛ የተጻፈ ባለ 475 ገጽ  የኤርትራ ትግል ጀማሪ ብለው ብዙዎቹ ኤርትራኖች የሚያሞግሱት (ኩናማዎች ግን ተራ ሽፍታ እና ጸረ ኩናማ ብለው የሚዘክሩት) ጸረ ኢትዮጵያ የነበረው የጣሊያኖች ባንዳ የነበረው በአያቱ ስም የሚጠራው “ዓዋተ” የተባለው የቢንዓሚር (?) ነገድ ተወላጅ ስለ ህይወት ታሪኩ የሚተነትን “በትግርኛ የተጻፈ መጽሐፍ እያነበብኩኝ ነው። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ሰምተናቸው የማናውቃቸው ታሪኮች ተዘግበዋል። መጽሐፉ ገና በቅርብ ሰሞኑን ነው ያገኘሁት። ማነበብ ጀምሬዋለሁ። መጽሐፉን ጨርሼ እስካነብበው ድረስ ለጊዜው ለዛሬ ክፍል አንድ ያነበብኩዋቸው አጫጭር ታሪኮቹን ላስተዋቀውቃችሁ።

ኤርትራውያን እንደምታውቁት በአጉል ትምክሕት፤በዘረኝነት እና በውሸት ፖለቲካ እየተነዱ አሁን ወደ ደረሱበት አሳዛኝ ህይወት ደርሰዋል። ከ30 አመት በላይ ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ታገልን ያሉት ትግል፤ ነፃ ወጣን ባሉበት 27 አመት ያገኙት ውጤት ስንመዝነው “ስደት፤ ሞት፤ ስቃይ፤ ውርደት፤ ዘመድ ከዘመድ መለያየት፤ ርሃብ፤ ጭንቀት እና ጉስቁልና ግርፋት እና እስራት እንዲሁም የስነ ልቦና እና የአካል ውርደት ደርሶባቸዋል።

ይህ ያላሰቡት ውርደት “ናፃነት አገኘን” ያሉትን አሳዛኝ ክስተት ወደ ፊታቸው መመለክትን ሳይሆን “ሃይለስላሴ እና መንግስቱ ሃይለማርያም” በተሻለን ነበር በማለት ወደ ሊት ለማየት የተገደዱበት አጣብቂኝ ምርጫ ውስጥ ገብተዋል። ይህ ሃቅ በዱለት እየኖሩ በውጭ አገር ተጠልለው ከእውነታው አጥር ውጭ ሆነው የሚፎልሉትን በብዙዎቹ ልሂቃኖቻቸው የሚያስተጋቡት “ነጻ ነን” የሚሉትን በየአመቱ የሚያከብሩት ቅዠት የሚታመን የሳይሆን ፤ እዛው ኤርትራ ምድር ውስጥ የሲኦል ህይወት የሚኖሩ ዜጎች የሚናገሩት እውነታ ነው።

ኤርትራኖች ዛሬም ከጊዜው ጋር እራሳቸውን ማሳደስ የማይችሉ (update/ኣፕዴት/ ማድረግ የማይችሉ) በበረሃው የትግል ቅዠት ውስጥ ሲያደምጡት የነበረው “የጥይት እና የጥላቻ ጩኸት” መርቅነው በጦዘ ሕሊናቸው ዛሬም እዛው በምናባቸው የሚቃዡ ስለሆነ የሕዝባቸው መከራ ከማባባስ የተሻለ አዲስ ነገር ማፍለቅ አልቻሉም።

ልክ የኛዎቹ የወያነ ትግራይ ‘መሳፍንታዊ ፋሺስት መሪዎች’  እና አሸባሪዎቹ የአሮሞ ነፃ አውጪ ድርጅቶች እንደሚቃዡት የቅዠት ርዕየተ ዓለም ውስጥ “ኤርትራኖችም” ልክ እንደ እነዚህኞቹ ራሳቸውን “ማሳደስ” ያልቻሉ “ቆመው የቀሩ” ስለሆኑ ሰላማዊ ዜጎቻቸው በአስከፊ የህይወት ውቅያኖስ ውስጥ እንዲዋኙ እና መፈጠራቸውን እስኪጠሉ ድረስ አድረገዋቸዋል። ዛሬም ከሚያዩት ችግር ምንም ሳይማሩ ያንኑ ቅዠታቸውን ቀጥለውበታል።

ስለሆነም ነው ተራ ሽፍቶችን የነፃነት ምልክቶች እያሉ በመኳኳል ይኼው ዛሬም የባንዳው ሓምድ እድሪስ ዓዋተ (‘ዓዋተ’) የህይወት ታሪክ እንደ አፍሪአዊ አርበኛ አድርገው የኮለኒያሊስቶች የበርሜል መርዝ ተሸካሚዎች እና አገልጋዮችን እንደ አርበኞች እድርገው  እየጻፉ ይገኛሉ።
የሚገርመው እኔ እስከፈተሽኩት ድረስ (ለወደፊቱ አነብበው እንደሆን እርግጠኛ አይደለሁም) መጽሐፉ ግን ዓዋተ ያሰቃያቸው ኩናማ ማሕበረሰብ አስተያየትን ያካተተ አልመሰለኝም። መጽሐፉ የተጠናከረው ካንድ ወገን በኩል የተገኘ ቃለ መጠይቅ እና ዘገባ ይመስላል። ያም ሆነ ይህ ለወደፊቱ እምለስበታለሁ።

ወጣም ወረደ፤ ዓዋተ ኤርትራኖችን ምን ሰራቸው የሚለው ሳይሆን የዛሬ ትኩረቴ ዓዋተ ለውጭ አገር ኮሎኒያሊስቶች በመወገን ኢትዮጵያ ላይ ምን የቅጥረኛነት (የባንዳነት) አገልግሎት ፈጸመ የሚለውን ባጭሩ እንመልከት።

የዚህ ሰው ስራ በመጽሐፉ የተካተቱ ለወደፊቱ የምንመለከታቸው ዘገባዎች እና ከሌሎች ምንጮችም ያነበብኳቸው አጠቃላይ ግምገማ አስካቀርብ ድረስ ለዛሬው እነሆ፦

ሓምድ እድሪስ ዓዋተ (1915-1962) የሚል በኤርትራዊው ‘ሃይለስላሴ ወልዱ’ የተደረሰ በትግርኛ የተጻፈ ባለ 475 ገጽ የኤርትራ ትግል ጀማሪ ብለው ብዙዎቹ ኤርትራኖች የሚያሞግሱት (ኩናማዎች ግን ተራ ሽፍታ እና ኩናማዎችን የጨፈጨፈ ብለው የሚዘክሩት) ጸረ ኢትዮጵያ የነበረው የጣሊያኖች ባንዳ በአያቱ ስም የሚጠራው “ዓዋተ” ቀዳሚ ስሙ “ሓምድ እድሪስ” የትውልድ ሐረጉ ካንድ ወጥ የተገኘ ነገድ ሳይሆን አያቶቹ ከሓባብ/ናራ/ቢንዓሚር እንዲሁም ከመሳሰሉ የትግረ ቅልቅል ነገድ ተወላጆች የተገኘ እንደሆነ መጽሐፉ በግልጽ ባያስቀምጠውም ከላይ እንደገለጽኩት ነገዱ ቅልቅል ይመስላል። ከራሱ ጀምሮ እስከ አያቶቹ ድረስ ‘የደም ጸብ’ የነበራቸው  ሞገደኞች እንደነበሩ መጽሐፉ ይገልጻል። ሰውየው ሞገደኛ ስለሆነ ልጆች ስያለቅሱ “አሐምድ” መጣብህ እያሉ ልጆችን የሚያስፈራሩበት “ሞንሰተር” እንደነበረም ደራሲው በሙገሳ መልክ ያስቀምጠዋል። ልጆች እንዲህ የሚያባንን “ሞሰንሰተር” (በላኤ ነብስ/ጸላኤ ሰናያት/) ከነበረ ማሕበረሰቡ ምን ያሕል ሽበር ይሰማው እንደነበር ግልጽ ነው።

የዓዋተ ወላጅ አባት ‘እድሪስ ዓዋተ’ ጋሽ ባርካን ተከዜን አልፎ ወደ ወልቃይት ኢትዮጵያ በመሻገር ወልቃይት ውስጥ ኑሮ በመመስረት ‘ትዕበ’ የተባለች ተድሮ ወልዶ ከብዶ  እዛው ይኖር ነበር። ከዚያም ወደ ትውልድ ስፍራው እንዳልተመለሰ የነገራል። እዚህ ላይ የምንገነዘበው ከእድሪስ የተወለዱ  የዓዋተ ኢትዮጵያዊ ትውልድ ያላቸው ወንድሞችና እህቶች አገር የሆነቺውን ኢትዮጵያን ጣሊያኖችን መርቶ ወራራ እንዲፈጸም ያደረገ የመጀመሪያው ኤርትራዊ የጣሊያን ቅጥረኛ ወታደር መኖሩን በመጽሐፉ ያነበብኩትን ለንባብ አንዲያመች ከትግርኛ ወደ አማርኛ የተረዳሁትን አቀራርብ ላስነብባችሁ

በጣሊያን ጊዜ ወላጅ አባቱ እድሪስ ወደ ዳባት (ቤገምድር/ጎንደር) በመሄድ ደጃዝማች አያሌው ብሩ ዘንድ በመሄድ ተከዜን ተሻግሮ (ከተከዜ ማዶ) ‘ትክል አምባ’ እንዲኖር ፈቃድ ጠይቆ ደጃዝማች አየለ ብሩም ፈቅደውለት እሱም ደምበር ተሻግረው ለሳር ግጦሽ ብለው የሚመሩ ከብት አርቢ ዘላን “ቢን ዓሚር ነገዶች” የከብት ዝርፊያም ሆነ ቅሚያ እንዳያካሄድ ጥበቃ እያደረገ እራሱም “እርሻ” ተፈቅዶለት ለደጃዝማቹ “ግብር” እየከፈለ ከአካባቢው ከመሳፍንቶቹ ጋር ወተት እና ውሃ ሆኖ በመዋሃድ ዝምድና በማፍራት ትዳር መስርቶ ልጆች አፈርቶ ኖረ።

በዚህ ወቅት ልጁ ሓምድ (ዓዋተ) ከወላጅ አባቱ እድሪስ ጋር አልተለየውም። ጉብዝና ሲጀምረው ወዲያ ወዲህ እየተረማመደ ለጣሊያኖችን ሲጋራ እየሸጠ፤ ከጣሊያኖች ጋር መልካም ግንኙነት መሰረተ። ቋንቋቸውም ማጥናት ጀመረ። ወዳጅነት ስለመሰረተም ጣሊያኖች በ1928 ኢትዮጵያን ስለሚወርሩ፤ጎንደር መሬት ወልቃይት ውስጥ ሲኖር የነበረው ወላጅ አባቱ እድሪስ በጦርነቱ እንዳይጎዳ ‘ከተክል ኣምባ” በቶሎ ወደ ኤርትራ ምድር  እንዲያስመጣው መከሩት። እንደተባለውም አደረገ።

እራሱም በፍላጎቱ የጣሊያን ወታደር ሆኖ በመቀጠር “ዲፖዚቶ’ በተባለ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ለ6 ወር ትምህርት ወስዶ አስካሪ ሆኖ ተመረቀ። ከዚያም “ባንዳ-ካቮሎ (ፈረሰኛ) ሆኖ ተመደበ። ጥበቃውን በፈረስ ሆኖ ያከናውን ጀምር።

መረብ ተሻግሮ ጣሊኖችን በመምራት ኤርትራ አስካሪ ባንዳ ጦር እየመራ መረብን የተሻገረ የመጀመሪያው ኤርትራዊ የጣሊያን ቅጥራኛ ዓዋተ ሆነ።

1928 ዓ.ም (በፈረንጅ ጥቅምት ወር 1935) ጣሊያን የወረራ አዋጅ በማወጅ ኢትዮጵያን ሊወር መረብ ተሻገረ። መረብ ሲሻገር የባንዳው ዓዋተ ጦር  መረብን ተሻግሮ ዓድዋን ከረገጠ እና መጠነኛ የቶክስ ልውውጥ ካደረገ   ዋተ የሚመራት አንዲት የሻለቃ ተዋጊ ሃይል ወደ  ሽሬ አካባቢ በመዝለቅ “ዓዲ ነብርኢድ” በተባለ ወረዳ ልዩ ስሙ “ክሳድ ቋረ” በተባለ ጎጥ ጦርነት ገጠመች። ባልጠበቀው ከበባ ውስጥ ገባ።

ሳምንት ሙሉ በኢትዮጵያ ተዋጊ አርበኞች ተከብቦ ጭንቅ ውስጥ ገብቶ የሞት እና የሽረት ትግል አደረገ። ተከብቦ መውጫ በማጣቱ ወደ አስመራ ድረስ መልእክት ለጣሊያኖች ደርሶ፡ ረዳት እንዲላክለት በመደረጉ በጣሊያን ተዋጊዎች የቆመ አንድ የጣሊያን ዲቪዥንም ጦር (ቡድን) ወደ ስፍራው እንዲሄድ ተደርጎ በር ስለከፈተላቸው ከበባውን በመስበር አምልጦ ህይወቱን አትርፎኣል። ረዳት ባይደርስለት ኖሮ ዓዋተ የመጨረሻ ስንብቱ እዛው ይፈጸም ነበር።

ዓዋተ መረብ ተሻግሮ ወደ ዓድዋ ሲገባ የዚያው የዓድዋ ተወላጆች ሰላይ (ፎርማቶሪዎች) ተባባሪዎች ስለነበሩት ከነሱ መረጃ በማግኘት ነበር መረብን ለመሻገር የበቃው። የመጀመሪያ ጦር መርቶ የተሻገረ አስካሪ (ባንዳ) ዓዋተ ስለነበር Merito Di Guerra (ሙንጣዝ) (የአስር አለቃነት) ማዕረግ ተሰጠው።ከዚህ በታች የሚታየው የጣሊያኖች መዳሊያም አብሮ ተሰጠው።

ባንዳው ዓዋተ ሰራዊት የሚመራት የጣሊያን አስካሪ ተዋጊዎች ወራራቸውን በመቀጠል ‘ዓዲ ረመጽ” በተባለ አካባቢ አርማጭሆ ውስጥ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ብቸኛዋን የአካባቢውን የውሃ ምንጭ ከብበው ተቆጣጥረዋታል። ኢትዮጵያውያንም ምንጩን በመቆጣጠር ጣሊያኖችን ለማዳከም እና በጥም ለመማረክ የቀየሱትት የጦርነት ስልት ነበር። የአንገረብ ወንዝ ውሃም አካባቢውን ከብበው አሽገው ተቆጣጥረውታል። የጣሊያን አስካሪዎች ውሃ ለመቅዳት ወደ ምንጩ ሲወርዱ በጥይት እየተቆሉ ችግር ውስጥ ገቡ። በዚህ የተነሳ በውሃ ጥም መሰቃየት ጀመሩ።ረዳት እስኪመጣለትም ሓምድ (ዓዋተ) ሌሊት እንደምን ብሎ ጭለማ ተገን አድርጎ ተሽሎክሉኮ ውሃ በቡራሾ እየቀዳ ሰራዊቶቹን ያቀብላቸው ነበር።

ዓዲ-ረመጽ የገባቺው ዓዋተ የሚመራት የባንዳዎች ተዋጊ ሰራዊት አገር ሰላም ነው ብላ ሲትገሰግስ ነው ሳታስበው ጥልቅ ብላ በኢትዮጵያ ተዋጊ አርበኞች ከበባ ውስጥ የገባቺው። በዚህ ላይ ቀን አልፎ ሌሊት ሲተካ የውሃ ጥም ገድሎአቸው በዚያው ላይ ጥይት እየዘነበባቸው ችግር ውስጥ ገቡ። ሻለቃዋ (ቦጦሊዋ) ከበባውን ሰብራ ለማምለጥ ብትሞክርም ፈጽሞ ልታመልጥ አልቻለም። ረዳት ድረስልን ቢባል አልደረሰላትም። በርሃብ እና በውሃ ጥም ተገረፈች። ወደፊት ብትል ወደ ላ ብትል መውጫ ቀዳዳ አጣች።

ውሃም ሆነ ምግብ ከአይሮፕላን በጃንጥላ ይጣልላቸው ጀመር። ሆኖም በጃንጥላ የተጣለላቸው ምግብ ዒላማውን እየሳተ ወደ ኢትዮጵያ አርበኞች ምሽግ እየወደቀ ችግር ውስጥ ገቡ።ርሃብ አጠቃቸው።አሁን ተከብበዋል። ርሃብ ስለጠናባቸው በመሸጉበት አካባቢ የስንዴ እሸት ስለበር እየሸመጠጡ ጥሬውን (ቅጠሉን) እንዳለ ያኝኩት ገቡ። ያ አልበቃ ብሎአቸው ለመጫኛ (ለአጋሰሶች) ምግብ ተብሎ የተጫነ “የእህል ገለባ” እንደ አጋሰስ ጎሰሙት (ቃሙት)፡ ያ አልበቃ ብሎአቸው ባካባቢው ያገኙትን ቅጥል እየሸመጠጡ እያኘኩ ራሃባቸውን ለማስታገስ ሞከሩ

ከዚያ መከራ እና ስቃይ በላ “ሚኖቪረ-27” የተባለ የጣሊያን ተዋጊ ሻለቃ ከበባውን ሰብረው እንዲወጡ እገዛ አደረገላቸው። ሓምድ (ዓዋተ) በዚህ ጊዜ ረዳት ስላገኘ ባንድ መስመር ከበባውን ሰብሮ በእግረ መንገዱ የኢትዮጵያ ሰራዊቶችን ንብረት ዘርፎ ለመውጣት በመቻሉ ከሌሎች የባንዳ ጓዶቹ ጋር “ምርጥ ተዋጊዎች” (Bel Merito) የሚል የመዳሊያ ሽልማት እና “ቡሉቕባሽ” የሚል ወታደራዊ ማዕረግ ተሰጠው።

ከላይ የተመለከትነው አስቸጋሪ ከበባ ካለፈ በላ እንደገና ከጊዜ በላ ጎጃም ውስጥ “አሞራ-ገድል” በተባለ ቦታ ከራስ አያሌው ጦር ጋር ገጠመ። እዛም የባሰ ተከብብቦ የኢትዮጵያ አርበኞች የጣሊያን አስካሪዎቹን የመሸጉበትን አካባቢ እሳት ለኩሰውበት። መውጫ ቀዳዳ አጥቶ ውጥረት ውስጥ ገባ። ሦስት ቀን እሳት እና ጥይት እየተለበለቡ መከራቸውን አዩ። እዛም በእሳት እየተለበለቡ በቁም እያዩ ከመሞት ጠላት ይግደለን ብሎ ዓዋተ “እየተቃጠለ ያለው የቀርቀሃ ዛፎችን” በሰይፉ እየቀነጠሰ ወደ ጥግ በመሸመቅ ክፍት አግኝቶ ሰንጥቆ በመውጣት ከከበባውን አመለጠ። ከ178 ፈረሰኛ ተዋጊ 100ዎቹ በእሳት እና በጥይት እየተለቀሙ ሲሞቱ 78 ብቻ የዱሩን እሳት እና ጥይቱን እየተጋፈጡ ህይወታቸውን ለማዳን መብቃታቸውን ይገልጻል። በዚህ ወቅት ዓዋተ መጠነኛ የጥይት ጉዳት ስለደረሰበት ጎንደር ከተማ ሕክምና ተደርጎለት ወደ ካራቤኔሪ (የጸጥታ ፖሊስ) ተዛውሮ እንዲሰራ መደረጉን መጽሐፉ ይገልጻል።

ይህ ባንዳ ካሓዲ ባባቱ ወገን የተወለዱት ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹን የሆነቺውን አፍሪካዊት አገር ኢትዮጵያ ለመውረር የመጀመሪያ የጣሊያን ባንዳ ሆኖ መረብ የተሻገረ ሰው መሆኑን አዲስ ታሪክ ብቅ የማለቱን ክስተት እንድታዩት ብየ ነው ይህንን ላካፍላችሁ የፈለግኩት።

ክፍልት ሁለት መጽሐፉን ካቆምኩበት ገጽ በመቀጠል  ሳነብብ እመለስበታለሁ።
ጌታቸው ረዳ (ኢትዮ ሰማይ)