Saturday, October 26, 2019

የመደመር መጽሐፍ ምረቃ - የዘገምተኞችና አድር ባዮች ጭብጨባ በሚሌኒየም አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ) Ethio Semay


የመደመር መጽሐፍ ምረቃ - የዘገምተኞችና አድር ባዮች ጭብጨባ በሚሌኒየም
አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ) Ethio Semay
በዛሬዋ ዕለት - ጥቅምት 8 ቀን 2012ዓ.ም - የዶ/ር ዐቢይ መጽሐፍ ተመርቋል፡፡ እኔም ከዚያ በተያያዘ ራሴን ታምሜ ዋልኩ - አሁን ድረስ፡፡ የነበረኝ የEmotional Quotient አንጻራዊ የተሻለ ደረጃ ወርዶብኝ ራሴው ስቸገርና ሰዎችንም ሳስቸግር አመሸሁ፡፡ የሚገነዘብህ ሰው ሲጠፋ ራስህን ያምሃል፤ ሲያምህ ሁሉም ነገር ያስጠላሃል፡፡

“እውነት እንደፀሐይ ናት፤ ፊት ለፊት በባዶ ዐይኖች አትታይም” ይላል ናማያራ የተባለ ህንዳዊ ደራሲ በአንዲት አጭር ልቦለድ ትረካው፡፡ በጣም እውነት ነው፡፡ የኔ ነው የምትለውን እውነት ይዘህ ግትር ከላክና የሚቃወምህ እንጂ የሚደግፍህ ካጣህ በርግጥም በቃላት ልትገልጸው የሚቸግርህ ህመም ጭንቅላትህን ሰንጎ ይይዝህና ትሰቃያለህ፡፡

ባመሸሁበት ሥፍራ ከማንም ሳልስማማ ተጣልቼ ወጣሁ - በሰው ቁስል እንጨት የሚሰደው ጭፍን ዜጋ እየበዛ ነው፡፡ አያቶላ ጃዋር እየቀጠቀጠ የሚገዛትን አገር ከቤተ መንግሥት ውጪ ተሰሚነት የሌለው ወይም በማወቅም ይሁን በሆነ ነገር ተገዶ አክራሪ ኦሮሞዎች እንዳሻቸው እንዲምነሸነሹበት ወዶና ፈቅዶ ሥልጣኑን ያስረከበው ዐቢይ እንደሚያስዳድራት የሚያምነው ነሆለል ዜጋ ብዙ ነው - በሰውዬው የቅፈላ ንግግር የሚማረከው የጣፋጭ ቃላት ምርኮኛ የትዬለሌ ሆነና ከአሳባጁ ሸርና ተንኮል ይልቅ የጣዖት አምላኪው ጅልነት ይበልጥ እያሳረረን ተቸግረናል፡፡ የታምራት ገለታንና የእሥራኤል ዳንሳን ተሞክሮና የአብዶ አጋንንታዊ ጥበብ ለዓመታት ቀስሞ የመጣው ዶ/ር ዐቢይ ለጊዜው አልተቻለም - በለስ ቀንቶት በምትሃታዊ ቱማታው ታላላቆችን ሳይቀር በእግሩ ሥር አውሏል -   ለነገሩ ትንቢትም ይደግፈዋል፡፡ ለማንኛውም የኔ መጣላት ትንሽ መጮህና ዝም ማለት ነው፡፡ ዝም ስል ጓደኞቼ መናደዴን ያውቃሉ - በሚነሱ ነገሮች አለመስማማቴን ጭምር፡፡ የአሁኒቷን ኢትዮጵያ እርግፍ አድርገው ካልተው አደጋ አለው!

በሚሊየኒየም አዳራሽ ዐቢይ “እኔ ዴሞክራት መሪ ስለሆንኩ ብቻየን የምወስነው ነገር የለም” ሲልና ጭብጨባው ሲቀልጥ የተሰብሳቢዎቹ ማንነት ገባኝ፡፡ በዚህ ንግግሩም ከንቱነቱን ከመግለጥ በስተቀር ሰውዬው እውነትን እንዳልተናገረ እረዳለሁና ፖለቲካ ምን ያህል ውሸታምና ከሃዲ እንደሚያደርግ ታወሰኝ፡፡ የሚገርመው ግን የርሱ ሀሰተኝነት ሳይሆን እዚያ የተኮለኮለው አጨብጫቢ የአእምሮ ዘገምተኛና አድር ባይ ነው፡፡ ዶ/ር ምሕረት ደበበን የመሰለ በጣም የማደንቀው ሰው ሳይቀር በዚያ የጨረባ ተዝካር፣ በዚያ የስብዕና ግንባታ የአምልኮት ሥነ ሥርዓት ላይ እንደሌሎች ዘገምተኞች የዚያ በተግባር የሚቀንስ በቲዎሪ ግን የሚደምር አርቲ ቡርቲ መጽሐፍ ዋና አድናቂ ሆኖ ሲገኝ በሰዎች ተፈጥሮ ተገረምኩ፡፡ በሀገራችን በተጨባጭ ምን እየተከናወነ እንዳለ የሚገባው ሰው በዚያ የቁጭ በሉ የሚሌኒየም ትርዒት ተገኝቶ ለነገ ሀፍረትና የኅሊና ትዝብት አይዳረግም - ኅሊና ላለው፡፡ እዚያ ለተገኙ ዜጎች በነሱ ምትክ እኔ አፈርኩ፡፡ አንዳች እርኩስ መንፈስ ቢያስገድዳቸው እንጂ በውዴታቸው እንደዚያ እጃቸው እስኪግል እንደማያጨበጭቡም ገመትኩ፡፡ ልብን ከሚሰብር ሀዘን ባለፈ ዶ/ር ዐቢይ በተለይ በዚህን ወቅት ምን የሚያስጨበጭብ ነገር አለውና! “ዐይን አይቶ ልብ ይፈርዳል” ይባላል፡፡ በፈርንጆች የሤራ ፖለቲካ የተገኘ ባዶ የኖቤል ሽልማትም ኃጢኣተኛ ሰው ንስሃውን ሳያወርድ በጉልበቱ ወስዶት ሣለ ነገር ግን በረሃ ላይ እያጣጣረ ለወደቀና የክርስቶስን ሥጋና ደም መቀበል እንዳይችል ከቤተ መቅደስ ለራቀ ሰው ከማይገባው በሥውር ተነጥቆ ለሚገባው እንደሚደርሰው ሥጋ ወደሙ የሚመሰል ነው፡፡ ስንቶች እየተገባቸው ሳያገኙ ዐረቦችን በተለይም ግብጽን ለማስደሰት ሲባል በኛ ይጫወታሉ፡፡

አፄ ኃይለ ሥላሤም ሆኑ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም የዚህን ሰውዬ ያህል አላጭበረበሩም፤ አጭበርብረውም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህን ያህል አልተመለኩም፡፡ ሚሌኒየም አዳራሽ ውስጥ የተገኙና ሰውዬውን ሰማየ ሰማያት በመስቀል የሚለው ነገር ገና ሳይገባቸው ዐረፍተ ነገሩን በቅጡ ሳይጨርስ በቃላትና በሐረጋት ሳይቀር ያጨበጨቡ ኢትዮጵያውያን የሀገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ የማያውቁ ደናቁርት ከመሆናቸውም በተጨማሪ የአእምሮ ችግር እንዳለባቸው ለመገንዘብ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ ይህን እውነት በገሃድ የምመሰክረው የዛሬ ታሪካችን ተመዝገቦ የሚቀመጥ እንደመሆኑ በነፃነታችን ማግሥት - አንድዬ ለዚያ ካበቃኝ - አሁን እየሆኑ ያሉትን ፍጹም ተቃራኒ ኹነቶች በማነጻጸር ይሆናል፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አምልኮ ካልወጣን ደግሞ መቼም ሰው አንሆንም፡፡

በርግጥ ሰውዬውም ጭብጨባ ይወዳል፡፡ እውነትም እንደሚባለው የናርሲዝም ተጠቂ ሳይሆን አይቀርም - ራስን ከልክ በላይ የማፍቀርና በሌሎች የመመለክ መጥፎ ልክፍት፡፡ ይህ ዓይነቱ በሽታ በነሂትለርና ሙሶሊኒም ታይቷል፡፡ ዐቢይ አያምንበትም እንጂ ቢያምንበት ኖሮ ወደ ዘብር ገብርኤል ሄዶ አንድ ሦስት ያህል ሰባቶችን ቢጠመቅ ከዚህ ሰይጣናዊ የእዩኝ እዩኝ የፎቶና ቪዲዮ ካሜራ ፍቅር ይፈወስ ነበር፡፡ ባናውቀው እንጂ መጥፎ በሽታ ነው፡፡

ምንም ቁም ነገር እንዳልተናገርኩ ይገባኛል፡፡ ቢሆንም ለምን ከዚህ በላይ ያልኩትን እንዳልኩ ሁሉንም በዝርዝር  ስለምታውቁት ማብራራት አይጠበቅብኝም፡፡ የሰውን አድርባይነትና አጨብጫቢነት እንዲሁም ለዚህ ያበቃውን የአእምሮ ዘገምተኝነት ከገለጥኩ በቂ ነው፡፡የኢትዮጵያን የወቅቱን ሁኔታ የሚረዳ በዚያ ልጭና ጎፈሬ ወይም ቂጥ  ከፍቶ ክንንብ ዓይነት ከእውነት የሚጣረስ ዝግጅት መናደዱ አይቀርም፡፡

ቢሆንም…. ቢሆንም… በጃዋርና በበቀለ ገርባ፣ በዶ/ር ገመቹና በሕዝቅኤል ጋቢሣ የሚመለመልና በኦህዲድ ሠልጥኖ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት አንድ ሐሙስ የቀረው አክራሪ ኦሮሞ በገነነባትና ከላይ እስከታች ሀገሪቱን በወረረበት ወቅት፤ አየር መንገድን፣ ባንክን፣ ትምህርት ሚኒስቴርን፣ ሌሎች የሚኒስቴርና የኮሚሽን መ/ቤቶችን፤ ማዘጋጃን፣ ክፍለ ከተማን፣ ወረዳን፣ ቀበሌን፣ ንግዱን፣ ፖለቲካውን፣ ሃይማኖቱን፣ መሬቱን፣ ኮንዶምንየሙን፣ኮንዶሙን፣… ሁሉንም ኦሮሞና የኦሮሞ የማድረጉ ኦነጋዊ ተግባር በተገባደደበት ወቅት ይህን መሰል የተጨፈኑ ላሞኛችሁ የመደመር ፖለቲካ የሰም ለበስ ቅኔ ሲመረቅ ማየት ደግ ነው - የሚገርመው ወያኔዎች በፈራ ተባ 27 ዓመታት የፈጀባቸውን ሁሉንም ወይም ቸርነትን በተላበሰ አገላለጽ አብዛኛውን ሥልጣንና የጥቅም ምንጭ በገዢው ጎሣና በሆድ አደር ተላላኪዎች የመጠቅለል አባዜ እነዚህኞቹ ንክሮች ገና ሁለት ዓመትም ሳይሞላቸው አጠናቀቁት - የኖቤል ሽልማቱ በዚህ ርዕስ ቢሆን ይልቁንስ አሣማኝ በሆነ - ይህን ዓይነት ርዕስ ካላቸው ሸላሚዎቹ፡፡ “ራሴን መትተው እግሬን ቢያኩኝ” አይገባኝም አለ ትግሬ - ዘርን መሠረት ባደረገ መልክ ምሥኪን ዜጎች ላይ የሚሠራው ግፍና በደል ሌላ - የሚመረቀው መጽሐፍ ሌላ፤ በሀፍረተቢስነትና ይሉኝታቢስነት ወያኔን የሚበልጥ እንደማይኖር ቀደም ሲል የወሰድኩት አቋም ፈተና የገጠመው ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ነው፡፡ “ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ” አሉ? አንዱ ፈላስፋ “ተማሪ ከአስተማሪው ካልበለጠ ምኑን አስተማረ?” ይል ነበር፡፡ የሕወሓት ተማሪዎች ኦህዲድና ኦነግ ፈጣሪያቸውንና መምህራቸውን በልበ-ሥውርነት አስከንድተውት ዐረፉ፡፡ “ወያኔ ማረኝ!” እንዳንል እፈራለሁ፡፡ አሸናፊው ጎልቶ እስኪወጣ ሀገራዊ የነጻነት ትግሉ በሦስት ቃላት ሊገለጽ በሚችል መልኩ የሚቀጥል ይመስለኛል፡- ብልጥነት፣ ሞኝነትና ብልኅነት፡፡

ላጨብጫቢዎቹም ለአስጨብጫቢዎቹም መልካም የጣዖት አምልኮት ዘመን ያድርግላቸው - ሲፈልጉ ከቢዮንሴ ቀጥለው 46ኛ ጽላት ያስቀርጹለትና ለሁለትም ለሦስትም ጌቶች የሚገዙ ዲያቆናትና ቀሣውስት ከሣሎናቸው ስለማያጡ ሠርክ ተስቀድሱለት፡፡ አንድዬ ይህን ሁሉ አፍዝ አደንግዝ እያዬ ግና ዝም አይልምና ሁሉም በቅርብ ዋጋውን እንደሚያገኝ አንጠራጠር፡፡ ቀልድ በዚህኛው እንጂ በዚያኛው የለም፡፡ ችግሩ ሞት ሲዘገይ የቀረ መምሰሉ፡፡ እንጂ ሌላውን ሁሉ ትተነው ምሥራቅ አፍሪቃን በፍርሀት ያምጰረጰረው መንጌ ዛሬ እርጅና ቤቱን ሠርቶበት የዝምብ መጫወቻ ሆኖ የለ? …. Ethio semay

No comments: